Search

Predigten

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-14] መንፈስ ቅዱስን ወደ ማግኘት የሚመራን ትክክለኛው ንስሐ ምንድነው? ‹‹ የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ››

መንፈስ ቅዱስን ወደ ማግኘት የሚመራን ትክክለኛው ንስሐ ምንድነው?
‹‹ የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ››
‹‹ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡››
 
 
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የሚያስፈልገው እውነተኛው ንስሐ ምንድነው?
ወደ ውሃውና ወደ መንፈሱ ወንጌል መመለስናበኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ማመን ነው፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ የጴጥሮስ ስብከት ብዙ ሰዎች ለሐጢያታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ በጥልቀት እንደቀሰቀሳቸው ይነግረናል፡፡ ከልባቸው መነካታቸውንም ለጴጥሮስና ለተቀሩት ሐዋርያት ይናገሩ ነበር፡፡ ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው ሲጠይቁትም ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- ‹‹ንስሐ ግቡ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን አስፈላጊ እንደሆነና እውነተኛ ንስሐም ምን እንደሆነ የጴጥሮስ ስብከት በግልጽ ያሳየናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከሐጢያቶች ስርየት ጋር አብረን መቀበል የምንችለው  መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በመመልከትና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ሊኖረን የሚያስፈልገው የመጀመሪያው ነገር በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ንስሐ ማመን ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ንስሐ መጸጸት አድርገን  እንዳንተረጉመው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ እዚህ ላይ ንስሐ ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ማለት ነው፡፡ ሰዎች ጌታን በመስቀላቸው እንደተጸጸቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማየት እንችላለን፡፡ ተጸጽተው ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጴጥሮስን ጠየቁትና ጴጥሮስ ንስሐ እንዲገቡ ሳይነግራቸው በፊትም ሐጢያቶቻቸውን አመኑ፡፡ ጴጥሮስ የተናገረለት ንስሐ ለሐጢያት መጸጸት ወይም ሐጢያትን ማመን ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኙ አድርጎ በልቡ መቀበልና እርሱ በሰጠን ውብ የሆነ ወንጌል ማመን ነበር፡፡ እውነተኛው የንስሐ ባህርይ ይህ ነው፡፡
የኢየሱስ ፍቅር ወደ እኛ የመጣው በልባችን ውስጥ አንዳች የሐጢያት ጸጸት ሳይኖር በፊት ነው፡፡ ይህ ማለት ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ በሞተና ዳግመኛም ከሙታን በተነሳ ጊዜ ሐጢያቶቻችንን ወሰደ ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ከሐጢያቶቻችንና ከበደሎቻችን ሁሉ አነጻን፡፡
እውነተኛ ንስሐ ማለት በዚህ እውነት ማመን ማለት ነው፡፡ ስለ ሐጢያቶቻችን ስለተጸጸትንና ይቅርታን ስለለመንን ብቻ ሐጢያቶቻችን ለዘላለም ይጠፋሉ ብላችሁ ታስባላችሁን? ይህ እውነተኛ ንስሐ አይደለም፡፡ እውነተኛ ንስሐ ማለት ውብ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻችንን ስርየት ማግኘት ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ የምናገኘው በንስሐ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ልክ እንደዚሁ ለሐጢያቶቻችን ሙሉ የሆነ ስርየትን ለማግኘት በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ወንጌል ማመን ይኖርብናል፡፡
ጴጥሮስ በኢየሱስ ያመኑትን ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም›› አጠመቃቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ለመውሰድ ተጠመቀ፡፡ ጥምቀቱና በመስቀል ላይ መሞቱ ምዕመናን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንዲቀበሉ የሚያስችላቸው ውብ ወንጌል ፍጻሜ ነው፡፡ (ማቴዎስ 3፡15-17) የሰው ዘር በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰው ደሙ በማመን ሊቀደስ ይችላል፡፡ በአጭሩ በወንጌል በማመን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያገኙ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፡፡
 
 

ጸሎት ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ሊያመጣ ይችላልን?

 
ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ምንም ያህል አጥብቀው ቢጸልዩም የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል አይችሉም፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ  ለመቀበል በኢየሱስ ጥምቀት የተፈጸመውን ውብ ወንጌልና በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ደሙ ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ሐጢያቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ለነጹላቸው ብቻ ነው፡፡
በወንጌል ማመን ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ አዳኝ አድርጎ ማወቅ ማለት ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ 2፡38 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ንስሐ ግቡ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)  ሐዋርያው ጴጥሮስ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው በትክክለኛ ንስሐ በማመን ሐጢያቶቻቸው ይቅር ለተባሉላቸው እንደሆነ ተናገረ፡፡ የሐጢያቶች ይቅርታና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል የተሳሰሩ ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38-39)
አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችለው በአንድ ቅድመ ሁኔታ ብቻ ሲሆን እርሱም ልቡ ሲቀደስና ያለ ሐጢያት ሲሆን ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ወንጌል ማመን ይኖርብናል፡፡ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ታጥበው መንጻታቸውን በሚናገረው ድንቅ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ ከተቀበልን በኋላ መቀደስ ይኖርብናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሰው ዘር ውስጥ ያድር ዘንድ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡ ‹‹ይህም የእግዚአብሄር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፡፡›› (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡3)
እውነተኛ ይቅርታ የሚገኘው በሰዎች ጥረቶች፣ መስዋዕትነቶች ወይም ተፈጥሮአዊ በጎነት ሳይሆን ቅዱስ ስላሴ የሆነው እግዚአብሄር በአጥማቂው ዮሐንስ አማካይነት በፈጸመው ውብ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ስላሴ የሆነው እግዚአብሄር ውብ በሆነው ወንጌል በማመን ይቅርታን ላገኙት ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስን ስጦታ ይለግሳቸዋል፡፡
ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ቀን የተናገረውን የሰሙ ብዙ ሰዎች ልባቸው ተነክቶ ‹‹ምን እናድርግ?›› በማለት ጮሁ፡፡ ይህ የሚጠቁመው አሳባቸውን መቀየራቸውንና አሁን ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው ማመናቸውን ነው፡፡ ጴጥሮስ በሰበከው እውነተኛ ንስሐ በማመናቸውም ከሐጢያቶቻቸው ዳኑ፡፡ የሐጢያቶች ይቅርታ ውብ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ወንጌልና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ባላቸው እምነት መሰረት ለሰው ዘር ሁሉ ተሰጥቶዋል፡፡
የኢየሱስ ጥምቀት አላማው የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዲሸከም መፍቀድ ነበር፡፡ በዚህ ማመን ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ እግዚአብሄር ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ተመስርቶ በእውነት ወንጌል ለሚያምኑት ነው፡፡ ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፡፡ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፡፡›› (ማቴዎስ 3፡16) መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ ቀን መውረዱ ሐዋርያት ውብ በሆነው ወንጌል በኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሳኤው ላይ ካላቸው እምነት ጋር የተለየ ግንኙነት አለው፡፡
ሰዎች በኢየሱስ ስም ተጠምቀው መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ የሐዋርያት ሥራ ይናገራል፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ከእግዚአብሄር ዘንድ የተሰጠ የተለየ ስጦታ መሆኑን ማመን ይኖርብናል፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመቀበል በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ሐጢያቶቻችን በሙሉ መንጻት ይኖርባቸዋል፡፡
በሐዋርያት ሥራ መሰረት ‹‹ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡40) የሚለውን የጴጥሮስ ስብከት የሰሙ ሁሉ ምክሩን ተቀብለው ተጠመቁ፡፡ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ዘመን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ላይ ባላቸው እምነት መሰረት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል መሠረታዊው ቅድመ ሁኔታ ይህ ነው፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን የሐጢያት ይቅርታን ለማግኘት ለሚፈልግ ሰው ወሳኝ ነው፡፡
  
 

በእውነተኛው ንስሐ መንፈስ ቅዱስን ወደ ማግኘት የሚመራን እምነት 

 
የሐዋርያት 3፡19ን እንመልከት፡- ‹‹እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ ሐጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ፡፡››
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንስሐ ማለት ወደ ቤዛነት እምነት መመለስ ማለት ነው፡፡ በዚያን ዘመን ሰዎች እንደፈለጉት ይኖሩና እግዚአብሄር ለፈጠራቸው ነገሮችም ይሰግዱ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃውና በደሙ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንዳዳናቸው ከተረዱ በኋላ ተለወጡ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ንስሐ ይህ ነው፡፡ እውነተኛ ንስሐ ውብ ወደሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል መመለስ ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የሚያስፈልገው እውነተኛ ንስሐ ምንድነው? በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን ነው፡፡ ‹‹እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ፡፡›› ሰዎች ይህ አይነት እምነት ካላቸው ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን አግኝተው መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ፡፡ ኢየሱስ በዓለም ላይ ያሉትን ሐጢያተኞች በሙሉ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ ስለቀደሳቸው በዚህ ውብ ወንጌል ማመን፣ ቤዛነትን ማግኘትና መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይኖርብናል፡፡
በኢየሱስ ለማመንና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ሐጢያት በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ወደ እርሱ መሻገር አለበት፡፡ ኢየሱስ ለሐጢያቶቻችን ይኮነን ዘንድ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደና በመስቀል ላይ እንደሞተ ማመን ይገባናል፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ እንዲኖረን የሚያስችለን ትክክለኛው እምነትና እውነተኛው ንስሐ ይህ ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው የሐጢያቶች ሁሉ ይቅርታ ባላቸው ላይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ቤዛነትን ላገኙት መንፈስ ቅዱስን እንደ ስጦታ የሚሰጣቸው ለምንድነው? ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ ስለሆነ በውስጣቸው ሊኖርና የራሱ ልጆች አድርጎ ሊያትማቸው ስለሚፈልግ ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸው፡፡ ሦስት ሕላዌዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ለሚያምኑት አንድ አምላክ ናቸው፡፡ አብ እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን ዕቅድ ነበረው፡፡ ስለዚህ ወልድ የሆነው ኢየሱስ ወደዚህ አለም መጣ፡፡ የዓለምንም ሐጢያቶች  ለመውሰድ በዮሐንስ ተጠመቀ፤ በመስቀል ላይ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን እንደገና ከሙታን ተነሣ፡፡ ወደ ሰማይም አረገ፡፡ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን በመመስከር በዚህ ውብ ወንጌል እንድናምን ይመራናል፡፡
እግዚአብሄር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የዳኑትን ያትማቸዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰዱ ወንጌል ለሚያምኑት መንፈስ ቅዱስን ይለግሳል፡፡ እግዚአብሄር ልጆቹ አድርጎ ያትማቸው ዘንድ ዋስትና አድርጎ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል፡፡ ውብ በሆነው ወንጌል ለሚያምኑ መንፈስ ቅዱስ ከሐጢያት የመዳኛው የመጨረሻ ማስረጃ ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ ያላቸው የጌታ ልጆች ናቸው፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች ሁሌም ይደሰታሉ፡፡ እነርሱ በእግዚአብሄር ቃሎች፣ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ጽኑ እምነት አላቸው፡፡ በእውነትም ደስተኞች ናቸው፡፡ በትክክለኛው መንገድ ንስሐ የገቡ በልባቸው ውስጥ ሐጢያት ስለሌለ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ አላቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያቶችን ይቅርታ የሚያስገኝ ንስሐ እንዳለ ይናገራል፡፡ በዚህ አይነቱ ንስሐ ውስጥ አልፋችኋልን? ንስሐ ከገባችሁና እውነተኛ አመኔታዎችን ከያዛችሁ ደግሞ ውብ የሆነውን ወንጌል መቀበል ትችላላችሁ፡፡ ለሐጢያቶቻችሁ ንስሐ እንድትገቡና መንፈስ ቅዱስን እንድትቀበሉ እመክራችኋለሁ፡፡ ንስሐ ለመግባትና መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በሚመራችሁ ውብ ወንጌል ለማመን ዝግጁ ናችሁን?