Search

Predigten

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[20-1] ዘንዶው በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ይታሰራል፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 20፡1-15 ››

ዘንዶው በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ይታሰራል፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 20፡1-15 ››
‹‹የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡ የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አሰረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፡፡ አሕዛብንም ወደፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማህተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል፡፡ ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሄር ቃል ራሶቻቸው የተቆረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፣ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን፣ ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ፡፡ የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም፡፡ ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው፡፡ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ ዳሩ ግን የእግዚአብሄርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፡፡ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ፡፡ ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፡፡ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ ጎግንና ማጎግን እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቁጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው፡፡ ወደ ምድርም ስፋት ወጡ፤ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፡፡ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው፡፡ ያሳታቸውም ዲያብሎስ፣ አውሬው፣ ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያሉ፡፡ ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፡፡ ሥፍራም አልተገኘላቸውም፡፡ ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻህፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ፡፡ ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲዖልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ፡፡ ሞትና ሲዖልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፡፡ ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው፡፡ በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ፡፡››     
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡
ለወንጌል የለፉትን ቅዱሳን ለመሸለም ጌታ አምላካችን ለሺህ ዓመት የክርስቶስን መንግሥት ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ለማድረግ በመጀመሪያ ከመላዕክቶቹ ለአንዱ ዘንዶውን ለሺህ ዓመት በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ያስረው ዘንድ እንዲይዘው ትዕዛዝ ይሰጠዋል፡፡ እግዚአብሄር በመጀመሪያ ይህንን ሥራ መስራት አለበት፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን በሺህው ዓመት የክርስቶስ መንግሥት ውስጥ መኖር ከመቻላቸው በፊት ዘንዶው ተይዞ በጥልቁ ጉድጓድ መታሰር አለበት፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ለመልአኩ የጥልቁን ጉድጓድ መክፈቻ ቁልፍና ታላቅ ሰንሰለት በመስጠት ዘንዶውን የመያዝና በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ የማሰሩን ሥራ እንዲጀምር ትዕዛዝ ሰጠው፡፡
    
ቁጥር 2፡- የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አሰረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፡፡
አዳምንና ሔዋንን ፈትኖ የጣላቸው ይኸው እባብ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን እባብ ዘንዶና ሰይጣን ብሎ ጠርቶታል፡፡ ቅዱሳን ከክርስቶስ ጋር በሰላም በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ ይኖሩ ዘንድ እግዚአብሄር ይህንን ዘንዶ ይዞ ለሺህ ዓመት በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ያስረዋል፡፡
 
ቁጥር 3፡- አሕዛብንም ወደፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማህተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል፡፡
እግዚአብሄር በዚህ ምድር ላይ የክርስቶስን መንግሥት ይመሰርትና ቅዱሳንም ለሺህ ዓመት ከጌታ ጋር ይነግሱ ዘንድ ዘንዶውን ለሺህ ዓመት በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ያሰረውና ቅዱሳኖችን እንዳያስት ይከለክለዋል፡፡
እዚህ ላይ ምንባቡ ‹‹ከዚህ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል›› ይላል፡፡ ሺህ ዓመት ሲፈጸም እግዚአብሄር ዘንዶውን ለጥቂት ጊዜ ይፈታዋል፡፡ ዳግመኛ ቅዱሳንን ማሰቃየት ሲጀምርም እንደገና ከቶ ላይታይ ለዘላለም ወደ ሲዖል ይወረውረዋል፡፡
  
ቁጥር 4፡- ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሄር ቃል ራሶቻቸው የተቆረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፣ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን፣ ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ፡፡
ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች በክርሰቶስ መንግሥት ውስጥ የመፍረድ ሥልጣንን ይቀበላሉ፡፡ ቅዱሳን የክርስቶስ ካህናት ከሆኑ በኋላ ከጌታ ጋር በሺህ ዓመቱ መንግሥት ላይ ይነግሣሉ፡፡ በዚያ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩትም ለኢየሱስ ምስክርና እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት የሆኑት የአውሬውን ምልክት ያልተቀበሉና ለምስሉም ያልሰገዱት ናቸው፡፡
ጸረ ክርስቶስ ባመጣው የመከራዎች ዘመን ውስጥ ሰማዕት የሆኑት እነዚህ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ዳግመኛ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ያስነሳቸውና ለሚመጣው ሺህ ዓመት በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ እንዲነግሱ ያደርጋቸዋል፡፡ በእርግጥ በፊተኛው ትንሳኤ የተሳተፉትም ሁሉ ይኸው በረከት ይሰጣቸዋል፡፡
በጌታ የተሰጡ ሁለት ትንሳኤዎች አሉ፡፡ እነርሱም የመጀመሪያው ትንሳኤና ሁለተኛው ትንሳኤ ናቸው፡፡ በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ የሚኖሩት ቅዱሳን የመጀመሪያውን ትንሳኤ የሚያገኙና የሚሳተፉ ናቸው፡፡ በዚህ በመጀመሪያው ትንሳኤ ዕድል ያላቸው ሁሉ በሺህው ዓመት የክርስቶስ መንግሥት ውስጥም በክብር የመኖር ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ትንሳኤ የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን ሁሉ ለመንጠቅ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡ (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡1517) ሁለተኛው ትንሳኤ የሚሆነው ግን በሺህው ዓመት መንግሥት ፍጻሜ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ በሐጢያተኞች ላይ የዘላለም ሞት ፍርድ ይፈረድባቸው ዘንድ ለእነርሱ የተዘጋጀ ነውና፡፡
ቅዱሳን ለሺህ ዓመት ይነግሱ ዘንድ ሥልጣኑን የሰጣቸው ሁሉን የሚገዛው እግዚአብሄር ነው፡፡ የክርስቶስ መንግሥት ለእነርሱ የተሰጣቸው በጌታ የውሃና የመንፈስ ወንጌል ስላመኑና በእርሱ ያላቸውን እምነት ለመጠበቅም ሕይወታቸውን በመስጠታቸው ነው፡፡
   
ቁጥር 5፡- የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም፡፡
በዚህች ምድር ላይ ሐጢያተኞች ሆነው ከኖሩ በኋላ ከጌታ ዘንድ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ሳይቀበል ወደ እርሱ የሚቀርቡ ሰዎች ጌታ ለቅዱሳን በሚሰጠው የመጀመሪያ ትንሳኤ ውስጥ ተካፋይ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ለሺህ ዓመት በደስታ ሲኖሩ እነርሱ የመጀመሪያውን ትንሳኤ አያገኙም፡፡ በፋንታው ዕድል ፈንታቸው ሁለተኛው ትንሳኤ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያውን ትንሳኤ በረከት የተቀበሉ ቅዱሳን በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ በብልጥግናና በክብር ሺህ ዓመት የሚኖሩበትንም ሥልጣን ተቀብለዋልና፡፡
ሆኖም እግዚአብሄር ለሐጢያተኞች ‹‹ሁለተኛውን ትንሳኤ›› ይፈቅድላቸዋል፡፡ ለምን? ምክንያቱም እግዚአብሄር በሐጢያቶቻቸው ይፈርድባቸው ዘንድ በሁለተኛው ትንሳኤ ዘመን ከሙታን ያስነሳቸዋልና፡፡ ዕጣ ፋንታቸው እንደዚህ ስለሆነ ለሐጢያቶቻቸው ፍርድን ያገኙ ዘንድ ዳግመኛ ከሙታን መነሳት አለባቸው፡፡ የሐጢያተኞች ትንሳኤ በቅደም ተከተሉም ሆነ በውጤቶቹ ከቅዱሳን ትንሳኤ የሚለየው ለዚህ ነው፡፡
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመናቸው ምክንያት የመጀመሪያው ትንሳኤ ተካፋይ ከሆኑት ውጭ ጌታ ሺህው ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሌላ ማንም ሰው በሕይወት እንዲኖር አይፈቅድም፡፡ ጻድቃን ትንሳኤን የሚያገኙት የዘላለም ሕይወትንና ብጽዕነትን ለመቀበል ነው፡፡ ሐጢያተኞች ትንሳኤን የሚያገኙት ግን ለሐጢያቶቻቸው የዘላለምን ቅጣት ለመቀበል ነው፡፡
      
ቁጥር 6፡- ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው፡፡ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ ዳሩ ግን የእግዚአብሄርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፡፡ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ትንሳኤ ዕድል ባላቸው ላይ ሁለተኛው ሞት ሥልጣን እንደሌለው ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ይህም እነዚህ በመጀመሪያው ትንሳኤ ተካፋዮች የሆኑት ብጹዓን እንደሆኑ ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ ይነግሳሉና፡፡
 
ቁጥር 7-8፡- ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፡፡ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ ጎግንና ማጎግን እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቁጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው፡፡
ዘንዶው ለሺህ ዓመት በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ከታሰረ በኋላ ሲፈታ እንደገና ቅዱሳንን ለመቃወም ይሞክራል፡፡ ያን ጊዜ እግዚአብሄር ዳግመኛ ከቶ እንዳይነሳ በዲን ወደሚቃጠል እሳት ይወረውረዋል፡፡ በዚህ ፍርድ ዘንዶው ሊገኝ የሚችለው ሲዖል ውስጥ ብቻ ነው፡፡
‹‹ይህ ማለት ዳግመኛ የተወለዱት ገናም በዚህ የሺህ ዓመት መንግሥት ውስጥ ይኖራሉ ማለት ነውን?›› ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡ መልሱ ‹‹አዎ›› ነው፡፡ ዮሐንስ ራዕይ 20፡8 በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ብዙ የምድር ሰዎች እንዳሉ መዝግቦዋል፡፡ እነርሱ እግዚአብሄር በአዲስ መልክ የፈጠራቸው ሕዝብ ይሁኑ ወይም ከዚህ ቀደም በዚህች ምድር ላይ የኖሩ ሕዝቦች አናውቅም፡፡ ነገር ግን የምናውቀው ነገር ቢኖር እነርሱ እነማን እንደሆኑ እንደሚያውቅና ቅዱሳንም ይነግሱ ዘንድ እጅግ የማይቆጠሩ እንደ ባህር አሸዋ የበዙ መሆን እንደሚኖርባቸው ነው፡፡
እውነቱ ቅዱሳን በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ሲኖሩ ገናም የምድርን ሕዝብ የሚያዩ መሆናቸው ነው፡፡ እነርሱ የሚኖሩት ቅዱሳንን ለማገልገል ነው፡፡ ቁጥራቸውም እንደ ባህር አሸዋ ብዙ ይሆናል፡፡ እነርሱ ዳግመኛ ቅዱሳኖችን ከመቃወም ከዘንዶው ጋር ቢተባበሩም ሁሉም እግዚአብሄር በሚያወርደው እሳት ይጠፋሉ፡፡ የታላቁን ነጭ ዙፋን ዘላለማዊ ፍርድንም ይቀበላሉ፡፡ ለዘላለም በሚነድ እሳት ውስጥም ይጣላሉ፡፡ በዚህም የሺህው ዓመት መንግሥት ወደ ፍጻሜው ይመጣል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ቅዱሳን ለዘላለም ወደሚኖሩበት አዲስ ሰማይና ምድር ይዛወራሉ፡፡
  
ቁጥር 9፡- ‹‹ወደ ምድርም ስፋት ወጡ፤ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፡፡ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሄር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው፡፡››
ዘንዶው ያለ ማቋረጥ እግዚአብሄርንና ቅዱሳንን የተቃወመው ሰይጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን እርሱ በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩትን የምድር ሕዝቦች ቢያስትና ቅዱሳኖችንም ቢያስፈራራ እግዚአብሄር ሁሉን የሚገዛ አምላክ ስለሆነ ከሰማይ እሳትን ያወርድና ሁሉንም ይበላቸዋል፡፡ ዘንዶውንም ዳግመኛ ከቶ እርሱንና ቅዱሳኖችን እንዳይቃወም ወደ ዘላለም እሳት ይጥለዋል፡፡
  
ቁጥር 10፡- ያሳታቸውም ዲያብሎስ፣ አውሬው፣ ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሰቃያሉ፡፡
እግዚአብሄር ዘንዶውን ወደ እሳትና ዲን ባህር በመጣል ቀንና ሌሊት መሰቃየቱን ያረጋግጣል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር የጽድቅ ፍርድ ነው፡፡ ዘንዶውና ተከታዮቹም እንዲህ መሰቃያታቸው የሚገባቸው ነው፡፡
 
ቁጥር 11፡- ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፤ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፡፡ ሥፍራም አልተገኘላቸውም፡፡
እግዚአብሄር ለሺህ ዓመት የሚሆነውን የቅዱሳንን ሽልማት ካጠናቀቀ በኋላ አሁን የራሱን አዲስ ሰማይና ምድር ይፈጥርና በዚህ ስፍራ ከእነርሱ ጋር ለዘላለም ይኖራል፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ለመከወን የሰራቸውን ሥራዎች በሙሉ ወደ ድምዳሜና ወደ መጨረሻ ፍጻሜ ያመጣቸዋል፡፡ ይህ የመጨረሻ የመዝጊያ ገቢር ጌታ ዳኛ ሆኖ በነጩ ዙፋን ላይ መቀመጡና ምግባሮቻቸው በምግባራት መጽሐፍ ውስጥ በተመዘገቡት ሐጢያተኞች ሁሉ ላይ የመጨረሻ ፍርዱን መስጠቱ ነው፡፡ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉት ይህ ፍርድ አይመለከታቸውም፡፡
እግዚአብሄር በሐጢያተኞች ላይ የሚወስነው ፍርድ በዚህ ያበቃል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአዲስ ሰማይና ምድር ግዛት ይከፈታል፡፡ ጌታችን የመጀመሪያውን ሰማይና የመጀመሪያውን ምድር እንዲሸሹ በማድረግ ሁለተኛውን የአዲስ ሰማይና ምድር ዓለም ይፈጥራል፡፡ ቅዱሳንም በዚህ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ እንዲኖሩ ይፈቅዳል፡፡ እግዚአብሄር በሕይወት መጽሐፉና በፍርድ መጽሐፎቹ ውስጥ በተጻፈው መሰረት ለአንዱ የሕዝብ ቡድን አዲስ ሰማይና ምድርን ሲሰጥ ለሌላው ቡደን ደግሞ የሲዖል ቅጣትን ይሰጣል፡፡
    
ቁጥር 12፡- ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻህፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ፡፡
በዚህ ጊዜ የክርስቶስ ፍርድ የመጨረሻውን ቅጣት ይወስናል፡፡ ይህ ማለት በሐጢያተኞች ላይ የሚሰጣቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች የሲዖል ቅጣት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ እነርሱም በፍርድ መጽሐፍ ውስጥ በተመዘገበው መሰረት እንደ ሥራዎቻቸው ይፈረዳሉ፡፡ በዚህም ሐጢያተኞች ሁለት ጊዜ ይሞታሉ፡፡ ሁለተኛው ሞታቸው መጽሐፍ ቅዱስ የዘላለም ሞት በማለት የገለጠው የሲዖል ስቃይ ነው፡፡ ሐጢያተኞች ከሲዖል ቅጣት ማምለጥ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ገናም በዚህች ምድር ላይ እየኖሩ ሳሉ አሁኑኑ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመማር መሻት፣ በእርሱም ማመንና ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚጻፍበትን በረከት መቀበል አለባቸው፡፡
        
ቁጥር 13፡- ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲዖልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ፡፡
‹‹ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲዖልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፡፡›› ሐጢያተኞች በሙሉ ለሐጢያቶቻቸው የመጨረሻውን ኩነኔ መቀበል አለባቸው፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥ ሞትና ሲዖል ተብለው የተገለጡት ስፍራዎች በተለይ የሚያመለክቱት በሕይወት ሳሉ በእርሱ ታልለውና በቁጥጥሩ ሥር ሆነው እግዚአብሄርን የተቃወሙትና በእርሱ ላይ ሐጢያት የሰሩ የእርሱ አገልጋዮች የሚሰሩባቸውን ስፍራዎች ነው፡፡ ይህ ቁጥር እግዚአብሄር የሐጢያቶቻቸውን ፍርድ ለጊዜው ቢያዘገየውም አሁን የመጨረሻውን ፍርድ የሚቀበሉበት ጊዜ እንደመጣ ይነግረናል፡፡
ስለዚህ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ የማን ወገን የመሆናቸው ጉዳይ ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው መረዳት አለባቸው፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው የሰሩ ሰዎች ለቅጣት በሆነው ትንሳኤ ከሙታን የሚነሱት የመጨረሻ ፍርዳቸውን ለመቀበል ነው፡፡ ነገር ግን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ያገለገሉ ለዘላለም ሕይወትና ለብጸዕነት ትንሳኤን ያገኛሉ፡፡
ስለዚህ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ጌታ የሰውን ዘር ሐጢያቶች የደመሰሰበት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ታላቅ ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘብ አለባቸው፡፡ በዚህ ምድር ላይ የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው የሰሩ ሰዎች ቅጣታቸውን ለመቀበል ትንሳኤን ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን የጌታችንን የጽድቅ ሥራዎች ያገለገሉ የዘላለምን ሕይወትና የብጽዕናን ትንሳኤ ያገኛሉ፡፡ ሐጢያተኞች በሙሉ በሐጢያቶቻቸው ይፈረድባቸዋል፡፡ በሲዖልም የመጨረሻውን ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡ እኛ በዚህ ምድር ላይ ሳለን ጌታ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ያስቀረበትን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለምን ማመን እንደሚገባን ግልጽ የሆነው ምክንያት ይህ ነው፡፡
    
ቁጥር 14፡- ሞትና ሲዖልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፡፡ ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው፡፡
ይህም የሰው ዘር ከሰይጣን ጎን በመቆም በእግዚአብሄር ፊት ለፈጸማቸው ሐጢያቶች የሚሰጠውን ፍርድ ይነግረናል፡፡ ሰዎችን ወደ ሰይጣን ለነዱት ክፉ ሰዎች የተመደበላቸው ቅጣት ወደ እሳት ባህር መጣል ነው፡፡ እግዚአብሄር በሐጢያተኞች ላይ የሚያመጣው ሁለተኛው ሞትና የእሳት ባህር ቅጣት ይህ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ የሚናገረው ሞት እንዲያው ዝም ብሎ መጥፋት ሳይሆን በሲዖል እሳት ውስጥ ለዘላለም የመሰቃየት ቅጣት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት ደህንነት ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ደህንነት ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሳሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ወደ ዘላለማዊው መንግሥተ ሰማይ ይገቡና ለዘላለም በደስታ ይኖራሉ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ምዕመናን በሚያገኙት ሽልማትና የማያምኑ ሰዎች በሚያገኙት ቅጣት መካከል ያለው ልዩነት በሰማይና በምድር መካከል እንዳለው ልዩነት የተለቀ ነው፡፡
     
ቁጥር 15፡- በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ፡፡››
ይህ ቁጥር እዚህ ላይ ‹‹ማንኛውም›› በሚለው ቃል የሰዎች ስሞች በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፉ ወይም አለመጻፉ ሙሉ በሙሉ የሚወሰነው ጥሩ ቤተክርስቲያን አዘውታሪዎች ቢሆኑም ባይሆኑም ወይም ቤተክርስቲያኖቸቸው ኦርቶዶክሶች ወይም ሄትሮዶክስ የእምነት ድርጅቶች ቢሆኑም ባይሆኑም ሐጢያቶቻቸው በሙሉ እንደ በረዶ ነጭ እስኪሆኑ ድረስ ይቅርታን በሚያገኙበት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቃል በማመንና ባለማመናቸው ነው፡፡ ስለዚህ ስሞቻቸው በጌታ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ያልተጻፉላቸው ሰዎች በሙሉ ያለምንም ልዩነት ወደ እሳት ባህር ይጣላሉ፡፡
የዓለም ሐይማኖተኞች ከሐጢያት በመዳናቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ በሐይማኖት ስርዓቶቻቸው ላይ ይበልጥ ትኩረት የማድረግ የታወቀ አዝማሚያ አላቸው፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ፊት በሚቆምበት ጊዜ ኢየሱስ የሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በልቡ ውስጥ ያልተገኘበት የዚህ ሰው ስም በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አይጻፍም፡፡ ስለዚህ እርሱ ጥሩ ክርስቲያን ቢሆንም እንኳን ወደ እሳት ባህር ይጣላል፡፡
እንግዲያውስ ገናም በዚህ ምድር ላይ እየኖራችሁ ሳላችሁ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ያስወገደውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በጆሮዎቻችሁ መስማትና በሙሉ ልባችሁም በእርሱ ማመን አለባችሁ፡፡ ያን ጊዜ ስሞቻችሁ በሕይወት መጽሐፍ ላይ የመጻፍን ክብር ታገኛላችሁ፡፡