Search

Sermons

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-2] የእግዚአብሄር ጽድቅ ሕግ የሚጠይቀው ቅን መጠይቅ ፍጻሜ፡፡ ‹‹ሮሜ 8፡1-4››

‹‹ሮሜ 8፡1-4››
‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከሐጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡ ከሥጋ የተነሳ ስለደከመ ለሕግ ያልተቻለውን እግዚአብሄር በሐጢያተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢያትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትዕዛዝ ይፈጸም ዘንድ ሐጢአትን በሥጋ ኮነነ፡፡››
 
 
ሮሜ 8፡1-4 ያሉት ምን አይነት እምነት እንዳላቸው ይነግረናል፡፡ የዚህ ምንባብ ምስጢር በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ ባለን እምነታችን የሕግን መጠይቆች በሙሉ መፈጸም የምንችል መሆናችን ነው፡፡
 
ታዲያ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምነው እምነት ምንድነው? ይህ እምነት ጌታችን የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደበት የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ በማመን የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበልንበት እምነት ነው፡፡ ስለዚህ አዳኛችን ሆኖ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሙሉ በፈጸመው በኢየሱስ በማመን ሐጢያትን ማሸነፍ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚከተለውና ድልን የሚያቀዳጀን እምነት ይህ ነው፡፡
 
በመጀመሪያ ሮሜ 8፡1-2 ይህንን ይነግረናል፡- ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡›› በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩ ሰዎች በእርግጥም ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ይህ እምነት የሕጉን የጽድቅ መጠይቅ በሙሉ በፈጸመው የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምን እምነት ዳግም ለተወለዱ ቅዱሳን በጣም አስፈላጊ እምነት ነው፡፡ ተራ የሆኑ ሟች ሰዎች እንዴት በሌላ መንገድ ሐጢያት አልባ መሆን ይችላሉ? በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው የእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ ባላቸው የማይናወጥ እምነት ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ተወግደዋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ በእግዚአብሄር ጽድቅ ለሚያምኑት ሰዎች ሲል በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በሥጋው ስለወሰደ ነው፡፡
 
ሮሜ 8፡3 እግዚአብሄር ‹‹የገዛ ልጁን በሐጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢአት ምክንያት አድርጎ›› እንደላከና ‹‹ሐጢአትንም በሥጋው እንደኮነነ›› ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር አብ ሐጢያትን በኢየሱስ ‹‹ሥጋ›› በመኮነን የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ አንድያ ልጁ አስተላለፈ፡፡ ይህ የእውነት ቃል በማቴዎስ 3፡13-17 ላይ ተገልጦዋል፡፡ (በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በጣም ሰፋ ያለ ውይይት ‹በውኑ ከውሃውና ከመንፈሱ ዳግመኛ ተወልዳችኋልን?› በሚለው መጽሐፌ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡) በዚህ እውነት የሚያምኑ ሰዎች ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጽድቁ ይቅር ብሎዋልና፡፡
       
 

‹‹እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!›› 

 
ከሮሜ 7፡24 እስከ 8፡6 ድረስ ያሉት ምንባቦች ሁለት በጣም ተነጻጻሪ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዘዋል፡፡ ከእነርሱ አንዱ የሐጢያትን ችግር ማለትም በሥጋ ምኞት ምክንያት በእግዚአብሄር ላይ ማመጽን የሚተነትን ሲሆን ሌላው በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን የዚህን የሐጢያት ችግር መፍትሄ የሚተነትን ነው፡፡
 
ሮሜ 7፡24-25 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን፡፡ እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሄር ሕግ በሥጋዬ ግን ለሐጢያት ሕግ እገዛለሁ፡፡›› ጳውሎስ የራሱን ሥጋ ሲመለከት ምንኛ ጎስቋላ ሰው እንደነበር በማየት ጮኸ፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በሥጋው ስለዳነ እግዚአብሄርን አመሰገነ፡፡ ጳውሎስ በአእምሮው ለእግዚአብሄር ሕግ ቢገዛም በሥጋው ለሐጢያት ሕግ እንደተገዛ መገንዘብ እንችላለን፡፡
 
ጳውሎስ ሥጋው እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት ከመኖር ይልቅ የሐጢያትን ሕግ እንደሚከተልና እግዚአብሄርን እንደማያስደስት ተናግሮዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ በአእምሮው አሁንም የእግዚአብሄርን መንፈስ ሕግ እንደሚከተል ተናግሮዋል፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ሕጎች መካከል ተጨፍልቆ ተጎሳቆለ፤ ተስፋም ቆረጠ፡፡ ሆኖም የእግዚአብሄር ጽድቅ ፍጻሜ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለው እምነት አማካይነት ከሐጢያቶቹ ስላዳነው እግዚአብሄርን በማመስገን የእምነትን ድል ያውጃል፡፡
 
ጳውሎስ ይህንን ምስጋና ማቅረብ የቻለው ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን ሐጢያቶች ሁሉ እንዲሁም የሰውን ዘር ሁሉ ሐጢያቶች በማስተሰረዩ ነው፡፡ ኢየሱስ እነዚህን የዓለም ሐጢያቶች ለመውሰድ በዮሐንስ በመጠመቅ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በሰውነቱ ተሸከመ፡፡ በመስቀል ላይም ለሐጢያት በመኮነን በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ አዳናቸው፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8፡1 ላይ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ ኩነኔ የለባቸውም ማለት በእግዚአብሄር ጽደቅ በሚያምኑ ሰዎች ውስጥ ፈጽሞ ሐጢያት የለባቸውም ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን በኢየሱስ ክርስቶስ ያሉ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ፈጽሞ ሐጢያት የለባቸውም፡፡ በሥጋቸው ደካማ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ምንም አይነት ሐጢያት የለባቸውም፡፡
 
በንጽጽር ኩነኔ ማለት የሐጢያት መኖር ማለትም የመኮነን ሁኔታ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው የተሳሳተ ነገር ሲያደርግ እኛ ብዙውን ጊዜ ያንን ሐጢያት ብለን እንጠራዋለን፡፡ ነገር ግን እርሱ ሐጢያተኛ የሚሆነው በእግዚአብሄር ጽድቅ ስለማያምን ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት ኩነኔ እንደሌለባቸው ይነግረናል፡፡
 
ሆኖም ይህ መግለጫ የዓለም ሰዎች እንደቆሙበት በሚናገሩት የመንጻት ትምህርት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ‹‹በእምነት ጻድቅ ሆኖ የመቆጠር ፍልስፍና›› እግዚአብሄር አንድን ሰው በተጨባጭ ጻድቅ ባይሆንና በልቡ ውስጥ ሐጢያት ቢኖርበትም በኢየሱስ ባለው እምነት ብቻ ጻድቅ አድርጎ ይመለከተዋል የሚል መላምታዊ አባባል ነው፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ እግዚአብሄር እንዴት ሊዋሽና ሐጢያተኛን ሐጢያት አልባ ነህ ብሎ ሊጠራው ይችላል? ይህንን አያደርገውም፡፡ በፋንታው እንዲህ ያለውን ሐጢያተኛ ‹‹በሐጢያቶችህ ምክንያት ሞትህ የተረጋገጠ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ በተገለጠው የእኔ ጽድቅ እመን!›› በማለት ይጠራዋል፡፡
 
በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች የተሳሳተውን እምነታቸውን ለማሰማመር እንዲህ ካሉ ትምህርቶች ጋር ተጣብቀው የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት ይሞክራሉ፡፡ የዚህ አይነቱ እምነት ግን በጣም የተሳሳተና አደገኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር የእውነት አምላክ ባይሆን ኖሮ ምናልባት ሐጢያተኛውን የእርሱ ተከታይ ብሎ ይጠራው ነበር፡፡ ነገር ግን እውነት የሆነው ኢየሱስ ሐጢያተኛውን ጻድቅና ሐጢያት አልባ ብሎ እንደማይጠራው መረዳት አለባችሁ፡፡ ሐጢያተኛውን ጻድቅና ሐጢያት አልባ ብሎ መጥራት በእግዚአብሄር ጽድቅ፣ ፍትህና ቅድስና ፊት የማይቻል ነው፡፡
 
ከሐጢያት መዳናችሁ የሚመጣው በኢየሱስ በማመን ብቻ ሳይሆን የራሳችሁ በሚሆነው የእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን እንደሆነ መረዳት አለባችሁ፡፡ በኢየሱስ ብታምኑም የእግዚአብሄርን ጽድቅ የማታውቁና የማታምኑበት ከሆነ እግዚአብሄር ጻድቃን ብሎ አይጠራችሁም፡፡ ዛሬ የሚታየው ግን በሒደት የመቀደስ ትምህርትና የመንጻት ትምህርት ትክክለኛ የክርስትና ትምህርቶች ሆነው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ትክክለኛ የክርስትና ትምህርት ተብዬዎች ሰው የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንዳያውቅ ወይም እንዳያገኝ በትክክል የሚያግዱ መሆናቸውን የሚያውቁ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ እየተቃወሙ እንደሆኑ ሳያውቁ በእነዚህ ትምህርቶች በማመናቸው የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል ተስኖዋቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ትምህርቶች የማሰናከያ ድንጋዮቻቸው ናቸውና፡፡
 
እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ከፈለጋችሁ በእርግጥ በክርስቶስ እንደሆናችሁ ወይም እንዳልሆናችሁ ለማየት ራሳችሁን በእግዚአብሄር ቃል መለካት አለባችሁ፡፡ ይህንን ለማድረግም የውሃውንና የመንፈሱን ቃል መስማት፣ ማየትና መረዳት አለባችሁ፡፡ ራሳችሁን ‹‹በኢየሱስ ያለኝ እምነት ትክክለኛው እምነት ነውን? በኢየሱስ አምናለሁ ስል ሃይማኖትን እየተለማመድሁ አይደለምን? በኢየሱስ ውስጥም ሆነ ከኢየሱስ ውጪ ሳልሆን መካከል ላይ ሆኜ እየተንገታገትሁ ነውን?›› በማለት ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ እናነተ በእርሱ በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የምትቀበሉበትና ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩኔ የለባቸውም›› በሚለው እውነት በማመን የምትኖሩበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
 
በኤፌሶን ውስጥ ‹‹በኢየሱስ በሆነው ቤዛነት በኩል›› የሚል ምንባብ ብዙውን ጊዜ ይገጥመናል፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ሊያድነን እግዚአብሄር አስቀድሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ወስኖናል መርጦናልም ማለት ነው፡፡ በኢየሱስ አማካይነት በእግዚአብሄር ጽድቅ ስርየትን ያገኙና በክርስቶስ ውስጥ የተጠቃለሉ ሰዎች ሐጢያቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ተደምስሶላቸዋል፡፡ በጌታችን በተሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ኩነኔ የለባቸውም፡፡ አንድ ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሲያምን በጌታ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የተቀበለና ይህንን ወንጌል የሚሰብክ ሰው ይሆናል፡፡
 
በኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑና ወደ እቅፉ የገቡ ሰዎች ሐጢያት የለባቸውም፡፡ እውነቱና ትክክለኛው መልስ ይህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን በክርስቶስ ያሉ ሰዎች ሐጢያቶች በሙሉ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ስለተወገዱ ሐጢያት ሊኖርባቸው አይችልም፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ያሉ ሰዎች በእርግጥም ሐጢያት የለባቸውም የሚለው ይህ እውነት በውሃውና በመንፈሱ ቃል ውስጥ የሚገኝ እውነት ስለሆነ የሐጢያት ችግርን በሚመለከት ምንም የተወሳሰበ ነገር ነገር አይኖርም፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት በተገለጠው የእግዚአብሄር ጽድቅ ስታምኑ እናተንም ደግሞ በእርግጥም ትጸድቃላችሁ፡፡ በውስጡ የእግዚአብሄርን የያዘውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አውቃችሁ እመኑበት፡፡ ያን ጊዜ በክርስቶስ የምትኖሩ ጻድቃን ትሆናላችሁ፡፡
በጣም አስቸጋሪ ችግር ገጠመን እንበል፡፡ ለዚህ ችግር ከልባችን መፍትሄ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ የገጠሙን ችግሮችና መከራዎች ምንም ይሁኑ መልሱን ለማግኘት ፍለጋውን መቀጠል አለብን፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን በእርሱ ውስጥ ያልተጠቃለሉ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሄርን ጽድቅ መፈለግ አለብን፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች ክርስትና ከብዙ የዓለም ሃይማኖቶች አንዱ ነው ብለው በማሰብ ቅድስና በሒደት ነው የሚሉ አይነት ትምህርቶችን በመቀበልና በማመን ለሐጢያቶቻቸው መፍትሄን ለማግኘት ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ትምህርቶችም ሆኑ የገዛ ራሳቸው ጽድቅ ሐጢያቶቻቸውን ሊያነጹላቸው እንደማይችሉ ፈጥነው ይገነዘባሉ፡፡ በፋንታው የሐጢያት ችግራቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በቀላሉ ሊፈታ እንደሚችል ይገነዘባሉ፡፡
 
እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ከፈለጋችሁ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባችሁ በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል አለባችሁ፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ግን በሒደት የመቀደስ ትምህርትና የመንጻት ትምህርት በመሳሰሉ ትምህርቶች ላይ በመደገፍ የሐጢያት ችግሮቻቸውን በሥራዎቻቸው ለመፍታት በሚያደርጉት ሙከራ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት ይሞክራሉ፡፡ የዚህ አይነቱ እምነት በንስሐ ሎቶች ላይ የሚደገፍ ነው፡፡ ይህም በስተ መጨረሻ ከተረጋገጠው ጥፋታቸው ሊያድናቸው አይችልም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ባለ ጸሎት ላይ እየተደገፉ ሐጢያቶቻቸውን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ ይበልጥ ሐጢያተኛ ይሆናልና፡፡
 
ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በሥጋቸው ደካማ ቢሆኑም በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን የሐጢያት ችግሮቻቸውን በሙሉ ፈተዋል፡፡ እንዲህ በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የተቀበሉ ሰዎች በእምሮዋቸው ውስጥ ሐጢያት ስለሌለባቸው ኩነኔ የለባቸውም፡፡
    
 
የእግዚአብሄር ጽድቅ በኢየሱስ ውስጥ ያለ በመሆኑ ምክንያት፡፡   
 
ቁጥር 2 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከሐጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡›› እግዚአብሄር ለሰው ሁለት ሕጎችን የሰጠ ሲሆን እነርሱም በኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግና የሐጢያትና የሞት ሕግ ናቸው፡፡ ጳውሎስ እንደነገረን የሕይወት መንፈስ ሕግ ከሐጢያትና ከሞት ሕግ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አርነት አውጥቶናል፡፡ አዲስ ሕይወትን ለመቀበል ጳውሎስ የተናገረውን ይህንን እውነት መገንዘብና መረዳት አለባችሁ፡፡ ይህ እውነት በዚህ ዓለም ላይ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው በእኩል ደረጃ ይመለከታል፡፡
 
እኛም በሕይወት መንፈስ ሕግ በማመን ከሐጢያትና ከሞት ሕግ አርነት ወጥተናል፡፡ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ በሐጢያትና በሞት ሕግ መጥፋታችን እርግጥ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሄር ጽድቅ ማለትም በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በልባችን በማመን የእርሱን ጽድቅ ተቀብለናል፡፡ በሕይወት መንፈስ ሕግ ውስጥም ሆነናል፡፡ ለእኛ የተዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወትም ተቀብለናል፡፡ ታዲያ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ሊያስተሰርይ የሚችለውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማግኘት የምትችሉት ከየት ነው? ይህ የሚገኘው ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና ደሙን ባፈሰሰበት መስቀል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእግዚአብሄር ጽድቅ የሚገኘው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ ነው፡፡
ታዲያ ከሐጢያትና ከሞት ሕግ አርነት ያወጣን የእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል ምንድነው? ጌታችን በዚህ አርነት ያወጣን የእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል ምንድነው? ጌታችን በዚህ ምድር ላይ እንደተወለደ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ለመውሰድም በሰላሳ ዓመቱ በዮሐንስ እንደተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ፣ እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን ከሙታን እንደተነሳ የሚናገር ወንጌል ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጽድቅ የተሰራው ወንጌል ይህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ሰው ደካማ በመሆኑ ሐጢያትን ለመስራት የታሰረ እንደሆነ ስለሚያውቅ ከሐጢያትና ከሞት ሕግ አርነት ሊያወጣቸው የሚችለውን የደህንነት ወንጌል በመስጠት ሐጢያተኞችን በሙሉ ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን አቀደ፡፡ በዮሐንስ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ውስጥ የሚገኘው ግልጽ  የስርየት ወንጌል ይህ ነው፡፡ በዚህ ወንጌል በማመን ሰዎች ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው የሞት ሕግ አርነት መውጣት ይችላሉ፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ሁሉ ያዳነ የሕይወት ሕግ ነው፡፡      
 
እግዚአብሄር የሕግን ቃል ለሰው ሰጠ፡፡ በሕጉ ከመኖር መውደቅም ሐጢያት እንደሚሆን ወሰነ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ነጻ ሊያወጣቸው የሚችል ሕግንም ደነገገ፡፡ ይህ የደህንነት ሕግ በእግዚአብሄር ጽድቅ ውስጥ በእርሱ ለሚያምኑ የዘላለምን ሕይወት በሚሰጠው የጸጋ ሕግ ውስጥ የተደበቀ እውነት ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሰው የደነገገው የስርየት ሕግ በውሃውና በመንፈሱ የማመን የእምነት ሕግ ማለትም የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ ይህ እምነትም የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚያለብሳቸው የሕይወት ሕግ ነው፡፡
 
ታዲያ ለሕይወት ሕግ ጀርባውን መስጠት የሚችል ማነው? እግዚአብሄር በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው ከዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ይድናል፡፡ በዚህ እምነትም የአግዚአብሄርን ጽድቅ ያገኛል፡፡
 
እግዚአብሄር የሕይወትን መንፈስ ሕግ የሰጣችሁ እንዴት ነው? ከድንግል የተወለደውን ልጁን ኢየሱስን ወደዚህ ምድር በመላክ፣ በዮሐንስ ጥምቀት አማካይነትም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በማሸከም፣ ለእነዚህ ሐጢያቶች ዋጋ ይሆን ዘንድም በመስቀል ላይ እንዲሞት በማድረግና ከሙታን በማስነሳት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስወግዶ ኢየሱስን የሐጢያተኞች አዳኝ በማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሄር በዚህ እውነት ለሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ይቅርታንና አዲስ ሕይወትን ሰጥቷል፡፡ እርሱ የሰጠን የሕይወት መንፈስ ሕግ ይህ ነው፡፡
 
ታዲያ የሐጢያትና የሞት ሕግ ምንድነው? እግዚአብሄር ለሰው ዘር የሰጣቸው ትዕዛዛቶች እነዚህ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር የደነገገው ሕግ ትዕዛዛቶቹን ‹‹በአድርግና በአታድርግ›› ዘርዝሮ አስቀምጦዋቸዋል፡፡ ከእነዚህ ትዕዛዛቶች የማፈንገጥ ማንኛውም ውድቀት ሐጢያት ይሆናል፡፡ የሐጢያት ደመወዝም ወደ ሲዖል በመውረድ ቅጣት መከፈል አለበት፡፡
 
ስለዚህ ሰው ሁሉ ከሞት ሕግ በታች ሆንዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ከዚህ የሞት ሕግ አድኖናል፡፡ ከኢየሱስ በስተቀር ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ማዳን የሚችል ማንም የለም፡፡ እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን የምንችልበት ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል በቀር ሌላ መንገድ የለም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እናንተን ለማዳን እንዴት ወደዚህ ምድር እንደመጣና የእግዚአብሄርም ጽድቅ ምን እንደሆነ ማወቅና ማመን አለባችሁ፡፡
 
ነገር ግን በዚህ ዘመን በኢየሱስ እናምናለን የሚሉና ስለ ሕጉ ማለትም የሐጢያትና የሞት ሕግ ከፍተኛ የሆነ ዝርዝር እውቀት ያላቸው ሆኖም ከሐጢያቶቻቸውም ሁሉ ያዳናቸውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ሙሉ በሙሉ የማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ብዙዎች አሁንም ድረስ በዚህ ድንቁርናቸው በኢየሱስ ማመናቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከዚህም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ለምን ያህል ጊዜ ተደብቆ እንደቆየ ማየት እንችላለን፡፡ ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በመስቀል ብቻ የሚያምነውን እምነት ከያዘው ወንጌል የተለየ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ትልቅ ጠቀሜታ የሚያኖሩት በመስቀል ላይ በሆነው የኢየሱስ ደም ላይ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ኢየሱስ በመስቀል ላይ የደማው በተሰቀለ ጊዜ ሳይሆን በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ እንደሆነ ይናገራል፡፡
 
ይህ የእውቀት ልዩነት ሰማይ በመሄድና ሲዖል በመውረድ መካከል ልዩነትን እንደሚያመጣ መገንዘብ አለባችሁ፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ልዩነት ይመስል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለት መረዳቶች አንዳቸው ከሌላቸው በስፋት ይለያያሉ፡፡ በመሰረታዊ ሁኔታም የተለያዩ ውጤቶችን ይይዛሉ፡፡ ኢየሱስን አዳኛችሁ አድርጋችሁ ለማመን ስትፈልጉ እምነታችሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዙሪያ ማማከል ያለባችሁ ለዚህ ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ መዳን የምትችሉት እንደዚህ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ዘመን በኢየሱስ እናምናለን የሚሉ ሰዎች ለእግዚአብሄር ጽድቅ መደንቆራቸውን ቀጥለዋል፡፡
 
እንደዚህ አይነት ሰዎች በተቻለ መጠን ጥቂት ሐጢያቶችን ለመስራትና በራሳቸው ለመቀደስ በመሞከር ምሉዓን ሆነው በእግዚአብሄር ፊት ለመቆም ይሞክራሉ፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ግን በሰው አስተሳሰቦች፣ ጥረቶች ወይም ሥራዎች ሊደረስበት አይችልም፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ መድረስ የሚችለው በውሃውና በመንፈሱ እውነት ውስጥ የተደበቀውን የስርየት እውነት በማመን ብቻ ነው፡፡ ሕግን በመከተል ራሳቸውን ለመቀደስ የሚሞክሩ ሰዎች እምነት ሞኝ እምነት ነው፡፡ የሕጉን መጠይቆች በሙሉ ማሟላት የሚችለው ሰው የለም፡፡
               
 

በኢየሱስ ሥጋ ሐጢያትን በመኮንን፡፡ 

 
ቁጥር 3 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከሥጋ የተነሳ ስለደከመ ለሕግ ያልተቻለውን እግዚአብሄር የገዛ ልጁን በሐጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፡፡ ሐጢአትን በሥጋ ኮነነ፡፡›› በዚህ ምንባብ ውስጥ ጳውሎስ ስለ ውሃውና መንፈሱ ሕግ ምን ያህል በዝርዝር እንደመሰከረ መረዳት እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ ጳውሎስ እግዚአብሄር አብ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዴት በኢየሱስ ላይ እንደጫነ ይነግረናል፡፡ ‹‹የገዛ ልጁን በሐጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጓልና፡፡ ሐጢአትን በሥጋ ኮነነ፡፡››
 
እግዚአብሄር ሐጢያትን በሥጋ ኮነነ ሲል ምን ማለቱ ነው? እግዚአብሄር አብ አንድያ ልጁን ወደዚህ ምድር በመላክ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በሥጋው ላይ እንዲሸከም በዮሐንስ እንዲጠመቅ አድርጎ የአማኞችን ሐጢያቶች በሙሉ ለዘላለም አነጻ ማለት ነው፡፡ ‹‹ለሕግ ያልተቻለውን…እግዚአብሄር አደረገው›› የተባለው ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በልጁ ላይ በመጫን አስወገዳቸው፡፡ በመስቀል ላይ እንዲሞትና ከሙታን እንዲነሳ በማድረግም የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ  ተወገዱ፡፡
እናንተን የሚያድናችሁ ወንጌል ይህ ነው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌልም ይህ ነው፡፡ ጌታችን በዮሐንስ 3፡5 ላይ ለኒቆዲሞስ ‹‹ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሄርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› በማለት የነገረው በግልጽ ይህንን ወንጌል ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚገልጠው ይህ ወንጌል ኢየሱስ በዮሐንስ ሲጠመቅ በመስቀል ላይ ሲደማና ከሙታን ሲነሳ ተገለጠ፡፡
 
ማቴዎስ 3፡15 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡›› ይህ ምንባብ የእግዚአብሄርን ጽድቅና በኢየሱስ በኩል የሆነውን መገለጡን ይመሰክራል፡፡ ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጥቶ በአጥማቂው ዮሐንስ ሊጠመቅ ሲሞክር ዮሐንስ ከመጀመሪያውም ‹‹እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?›› ብሎ በመጠየቅ ያንን ለማድረግ እምቢተኛ ሆነ፡፡ ኢየሱስ ግን በተከታዩ ምንባብ ዮሐንስን መረር ባለ ቃል አዘዘው፡፡ ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡››
 
ታዲያ ‹‹ጽድቅን ሁሉ መፈጸም›› ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶዋል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ተጠምቆ ከውሃ ሲወጣ ሰማያት ተከፈቱለት፡፡ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ወረደ፡፡ ከዚያም ‹‹ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፡፡›› እግዚአብሄር የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደበት በኢየሱስ ጥምቀት ተደሰተ፡፡ እዚህ ላይ የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ለማዳንና ይህንን ተስፋ ለመፈጸም የወሰኑትን የአምላከ ስላሴን ሦስቱን ሕላዌዎች በአንድ ላይ እናያቸዋለን፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ሰማያት ተከፍተውለት ከሰማይ የመጣ ድምጽ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ እንዳወጀ ይነግረናል፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር አብ የእርሱ ልጅ በዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ በመውሰዱ ሐቅ ተደስቷል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ስለተጠመቀና በጥምቀቱም የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በሰውነቱ ላይ ስለተጫኑ በመስቀል ላይ በመሰቀልና ዳግመኛ ከሙታን በመነሳት ጽድቅን ሁሉ ፈጸመ፡፡
 
በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በዮሐንስ የተጠመቀው የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ ለመፈጸም ነበር፡፡ ከዚያም በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ይህ ጥምቀትና ይህ ሞት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ ለመፈጸም የታቀዱ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ይህ ጥምቀትና ይህ ሞት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ ለመፈጸም የታቀዱ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ በመስቀል ላይ ደሙን ማፍሰስ የቻለው ለዚህ ነው፡፡ ከሙታን በመነሳትም የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሁሉ ፈጸመ፡፡   
 
‹‹የእግዚአብሄር ጽድቅ ሁሉ›› ማለት የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ሁሉ የማዳን ተግባር ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ይህንን የጽድቅ ተግባር ለመፈጸም በጥምቀቱ የሰዎችን ሁሉ ሐጢያቶች ወስዶ በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ሁሉ እጅግ ቀናና ተገቢ በሆነ መንገድ ተፈጸመ፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት፣ ደምና ትንሳኤ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ፈጽመዋል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅም ሐጢያት አልባ አድርጎናል፡፡ በዚህም በውስጣችን የእግዚአብሄርን ጽድቅ አንብሮዋል፡፡ አምላከ ስላሴ ይህንን እቅድ አቀደ፡፡  ኢየሱስ ፈጸመው፡፡ መንፈስ ቅዱስም እስከ አሁን ድረስ ይህንን ጽድቅ ይመሰክራል፡፡ እግዚአብሄር በላከው ቃል ማመን አለባችሁ፡፡ ‹‹የገዛ ልጁን በሐጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጓልና፡፡ ሐጢአትን በሥጋ ኮነነ፡፡››
 
ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ በቀሪው የሕይወት ዘመናችሁ የሕጉን ትዕዛዞች በሙሉ ፈጽማችሁ በተጨባጭ መጠበቅ እንደምትችሉ የምታስቡ ከሆነ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ እነርሱን ለመጠበቅ የተቻላችሁን ሁሉ እንደምታደርጉ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በሕጉ መኖር ፈጽሞ አትችሉም፡፡ ትንሽዋን የሕጉን ዝርዝር ከጣሳችሁ ሕጉን ሁሉ መጣሳችሁ ነው፡፡ (ያዕቆብ 2፡10) ሁሉም ያለ ምንም ልዩነት ከሕጉ በታች ሙሉ በሙሉ ሐጢያተኛ ሆኖ የሚያበቃው ለዚህ ነው፡
 
ሕጉን ለመከተል ያላችሁ ፍላጎት ቀና ሊሆን ይችላል፡፡ የቻላችሁትንም ታደርጋላችሁ፡፡ እርሱ ከእኛ የሚጠይቀው የእግዚአብሄር ጽድቅ ግን ሕግን በመከተል ፈጽሞ አይደረስበትም፡፡ እግዚአብሄር ሕጉን ለእኛ የሰጠበት ብቸኛው ምክንያት ሐጢያቶቻችንን እንድናውቅበት መሆኑን መረዳት አለባችሁ፡፡ እኛ በሥጋችን ደካማ ስለሆንን ማንም የእግዚአብሄርን ሕግ በሙላቱ መጠበቅ አይችልም፡፡
 
እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ጥልቀት እኛን ለማዳን ልጁን ወደዚህ ምድር የላከውና የእያንዳንዱን ሰው ሐጢያቶች እንዲወስድ በዮሐንስ እንዲጠመቅ ያደረገው ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በሥጋው እንዲጠመቅ በማድረግ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በሥጋው ላይ ተጫኑ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሄር በኢየሱስ ‹‹ሥጋ ሐጢአትን ኮነነ›› ብሎ የሚነግረን ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያት አልባ ያደረገን በዚህ መንገድ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን ያስወገደበትን መንገድ ማወቅና ማመን አለብን፡፡ እግዚአብሄር ልጁ የሰው ዘር ወኪል በሆነው በዮሐንስ እንዲጠመቅ በማድረግ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በኢየሱስ ላይ ጫነ፡፡ ከዚያም ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመስቀል ላይ እንዲሸከምና በእኛ ምትክም የእነርሱን ዋጋ እንዲከፍል፣ ደሙን እንዲያፈስስና እንዲሞት አደረገው፡፡ ከሙታን በመነሳትም በዚህ ለሚያምኑት ሁሉ የደህንነትን መንገድ ከፈተላቸው፡፡ እግዚአብሄር ከሐጢያት መዳናችንን እንደዚህ አቅዶ እንደዚህ ፈጸመው፡፡
 
ስለዚህ የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ስርየታችን እንደሆኑ በልባችን ማመን አለብን፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች በተጨባጭ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አለባቸው፡፡
 
እናንተም ደግሞ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት ለማግኘት፣ ፈጽማችሁ ለመጽደቅና ሐጢያት አልባ ለመሆን እንደዚህ ማመን አለባችሁ፡፡ እናንተም በራሳችሁ ጥረቶች በማመን ፋንታ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችሁን እንዴት እንደደመሰሰው በትክክል መረዳት፣ ፈቃዱን መከተልና በእግዚአብሄርም ፊት በዚያ ማመን አለባችሁ፡፡