‹‹ሮሜ 8፡26-28››
‹‹እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፡፡ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፡፡ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና፡፡ እግዚአብሄርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡››
ዛሬ ከላይ በሮሜ ምዕራፍ 8 ውስጥ ያለውን ምንባብ መመልከት እንወዳለን፡፡ እግዚአብሄር የአምላክ ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ያለነውን እኛን አስቀድሞ እንደወሰነን፣ እንደጠራንና እንዳከበረን ተነግሮዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይና ሰዎች በሒደት የመቀደስን ትምህርት እንዴት ወደ መረዳት እንዳዘነበሉም እንነጋገራለን፡፡
ሮሜ 8፡28 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሄርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡›› እነዚያ ‹‹እግዚአብሄርን የሚወዱት›› እነማን እንደሆኑ ልናስብ ይገባናል፡፡
በእርግጥ ነገር ሁሉ ለበጎ ይደረጋልን? እግዚአብሄር ሰዎችን ከመፍጠሩ በፊት ገና በመጀመሪያው በዓላማው መሰረት የራሱ ሕዝብ ሊያደርገን አቀደ፡፡ ይህንንም በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለበጎ አደረገው፡፡
በኤድን ገነት ክፉውንና በጎውን የምታስታውቅ ዛፍ እንደነበረች ማስታወስ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሄር ይህችን ዛፍ ለምን ተከላት? እግዚአብሄር ከመነሻውም ክፉውንና ደጉን የምታስታውቀውን ዛፍ ባይተክል የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ይህንን ጉዳይ ለማወቅ ይጓጓሉ፡፡
ነገር ግን እግዚአብሄር ጥልቅ ዓላማና እቅድ ነበረው፡፡ እግዚአብሄር ሰዎችን በራሱ አምሳል ፈጠረ፡፡ የሰው ዘር የእግዚአብሄርን መንግሥት እስካልተቀበለ ድረስ ከቀረው ፍጥረት የተለየ አልነበረም፡፡
እግዚአብሄር ክፉውንና ደጉን የምታስታውቀውን ዛፍ ለምን ተከለ?
እግዚአብሄር አዳምንና ሄዋንን መልካምንና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ እንዳይበሉ ያዘዘበትን ምክንያት ማወቅ አለብን፡፡ ምክንያቱ ምን ነበር? ሰዎችን ከእግዚአብሄር ሕግ በታች ለማቆየትና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እኛን በመቤዠትም የራሱ ልጆች ለማድረግ ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ በሙሉ ‹‹እግዚአብሄርን ለሚወዱት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን›› በሚለው ቃል ውስጥ ተሰውሮዋል፡፡ እግዚአብሄር ‹‹እግዚአብሄርን ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን›› (ሮሜ 8፡28) በማለቱ የጥያቄውን መልስ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ ማግኘት አለብን፡፡
ይህንን ለማድረግ በመጀመሪያ የእግዚአብሄርን ወንጌል ማወቅ አለብን፡፡ ያን ጊዜ እግዚአብሄር ያቀደውና የሚያደርገው እያንዳንዱ ነገር መልካም እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ይህንን እውነት ለመረዳት ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግም መወለድ ይገባናል፡፡ መልሱን እግዚአብሄር በሰጠን ወንጌል ውስጥ መፈለግ አለብን፡፡
እግዚአብሄር እኛን የፈጠረው በኤድን ገነት ውስጥ መልካምንና ክፉውን የምታስታውቀውን ዛፍ የተከለውና አዳምና ሄዋንም ከዚህ ዛፍ እንዲበሉ የፈቀደው እኛን ልጆቹ ለማድረግ ነው፡፡ ሁላችንንም ያዳነን ጌታ የሐጢያቶችን ይቅርታ፣ የዘላለም ሕይወትን፣ ክብርንና ሰማይን ይሰጠን ዘንድ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንዲሆኑ ፈቀደ፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ከአፈር አበጀው፡፡ ለሰው ዘር ደካማ ሆኖ እንዲወለድ ተደረገ፡፡ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ከሸክላ ዕቃዎች ጋር ያመሳስለናል፡፡ ሸክላ ሰሪው እግዚአብሄር ሰውን ከአፈር አበጀው፡፡ ሰውን ከአፈር አበጅቶ የውሃውንና የመንፈሱን ፍቅር በውስጡ እፍ አለበት፡፡ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን እውነት የሰጠን የገዛ ራሱ ልጆች ሊያደርገን ነው፡፡
ከሸክላ የተሰራ የሸክላ ዕቃ በቀላሉ ይሰበራል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ መንገድ አስቀድሞ ደካማ ይሆን ዘንድ የሰውን አካልና መንፈስ የፈጠረው የራሱ ልጅ ሊያደርገው ስለፈለገ ነው፡፡ ዓላማውም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግም እንዲወለዱ በማድረግ፣ የዘላለምን ሕይወት በመስጠት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ባነጻውና የእግዚአብሄርን ክብር ባለበሳቸው በኢየሱስ ተፈጸመ፡፡ እግዚአብሄር እኛን ገና ከመጀመሪያው እንከን የለሽ ከማድረግ ይልቅ ጉድለት ያለብንና ደካሞች አድርጎ ያበጀን ለዚህ ነበር፡፡
እግዚአብሄር በመጀመሪያ ሰውን ለምን ደካማ አድርጎ ፈጠረው?
እግዚአብሄር መልካምንና ክፉን የምታስታውቀውን ዛፍ በኤድን ገነት ከተከለ በኋላ አዳምና ሄዋን ከዛፊቱ እንዳይበሉ ለምን አዘዛቸው? ከዚህ ጀርባ ያለው ምክንያት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ መስተዋልና መታመን አለበት፡፡ እግዚአብሄር አዳምና ሄዋን በሐጢያት ከወደቁ በኋላ የሴቲቱ ዘር የሰይጣንን ራስ እንደሚቀጠቅጥና ሰይጣንም ሰኮናውን እንደሚቀጠቅጥ የተናገረው ለምንድነው? እነዚህ ነገሮች በሙሉ የተደረጉት ሰዎችን የራሱ ልጆች ለማድረግ ነው፡፡ ይህ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለእኛ ያቀደው እቅድ ነው፡፡
ታዲያ እንደ እግዚአብሄር እቅድ ‹‹የተጠሩት›› እነማን ናቸው? እነርሱ ሐጢያቶቻቸውንና በደሎቻቸውን አውቀው የእግዚአብሄርን ፍቅርና ምህረት የሚሹ ሰዎች ናቸው፡፡ በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ምርጫ አስተምህሮትና በሒደት የመቀደስ አስተምህሮት የሥነ መለኮታዊ አባባሎች የተሳሳቱ እንደሆኑ መገንዘብ አለብን፡፡ በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ምርጫ አስተምህሮት የተሳሳተ ነው፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ሌሎችን ያለ ምንም ምክንያት በማግለል አንድ ሰው ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሚመርጥ አይነት አምላክ አይደለም፡፡
በፋንታው እግዚአብሄር የሚመርጣቸውና የሚጠራቸው ሰዎች በሐጢያቶቻቸው ተስፋ ቆርጠው ወደ ሲዖል ከመውረድ በቀር ምርጫ የሌላቸው መሆኑን የሚናገሩ -- እግዚአብሄር የሚምራቸውና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚጠራቸው ሰዎች ናቸው፡፡
በዚህ ዓለም ላይ ተወልደው ወደ እግዚአብሄር ከተመለሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች መካከል ያለ አንዳች ምክንያት በእግዚአብሄር የተመረጠ ወይም የተተወ አንድም ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄር ምክንያት ሳይኖረው ካልመረጣችሁ እግዚአብሄርን ትቃወሙታላችሁ፡፡ እግዚአብሄር እናንተን ወይም ሌላውን ሰው ያለ ምንም ምክንያት የዲያብሎስ ልጅ አድርጓችኋል ማለት ስሜት አይሰጥም፡፡ እግዚአብሄር ያደረገው ይህንን አይደለም፡፡
በእግዚአብሄር ካልተመረጣችሁ ያልተመረጣችሁት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለማመናችሁ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የማታምኑ ከሆናችሁ ያን ጊዜ እግዚአብሄር ይተዋችኋል፡፡ ጌታችን እንዲህ ብሎዋልና፡- ‹‹ሐጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፡፡›› (ማቴዎስ 9፡13) አሳዛኙ ነገር የሥነ መለኮት ምሁራን ያደረጉት ነገር ቢኖር እግዚአብሄርን ጥራዝ ነጠቅና ወገንተኛ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የተጠሩት እነማን ናቸው?
በእግዚአብሄር የተጠሩት ለሲዖል ታጩ ሐጢያተኞች ናቸው፡፡ እነርሱ ወደ እግዚአብሄር ቀርበው ደካሞች ስለሆኑና እስከ ዕለተ ሞታቸውም ድረስ የእርሱን ትዕዛዛቶች ከማፍረስ በቀር ሌላ ምርጫ ስለሌላቸው ሲዖል መውረድ እንደሚገባቸው ይናዘዛሉ፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን ጠርቶ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሐጢያቶቻቸውን አንጽቷል፡፡ እርሱ ሲዖል ከመውረድ በቀር ምርጫ ያልነበራቸውን ሰዎች ጠርቶ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው፡፡
እግዚአብሄር መልካም የሆኑትንና ሕጉን የሚታዘዙትን ሰዎች ሊጠራ አልመጣም፡፡ እግዚአብሄር የጠራው እንደ ፈቃዱ ለመኖር በተጨባጭ የጣሩትን ነገር ግን እግዚአብሄርን ቢያምኑና ቢደገፉም ድካሞቻቸው ሐጢያት እንዲሰሩ ያስገደዱዋቸው መሆኑን የሚያምኑት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዓላማ ደካሞችን፣ ጎስቋሎችንና ልፍስፍሶችን በመጥራት ጻድቅና የራሱ ልጆች ማድረግ ነው፡፡ እንደ ፈቃዱ የሆነው የእግዚአብሄር ጥሪ ይህ ነው፡፡ እንደ አሳቡ ለተጠሩ ሁሉ ነገር ሁሉ ለበጎ ይደረጋል፡፡
በእግዚአብሄር ጥሪ ማመን አለብን፡፡ በኢየሱስ የምናምነው ያለ ምክንያት ነው ብለን መናገር የለብንም፡፡ እንዲህ ያለው እምነት ትክክለኛ እምነት አይደለም፡፡ ትክክለኛው እምነት እንደ ራሳችን አሳብ ሳይሆን እንደ እግዚአብሄር አሳብ ማመን ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር ድካሞቻችንን በሚገባ እንደሚያውቅ፣ ሐጢያቶቻችንንም ለአንዴና ለመጨረሻ እንደወሰደና በዚህ እንዳጸደቀን ማመን ማለት ነው፡፡ እምነታችንን በእግዚአብሄር አሳብ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ደም ላይ በማኖር የእርሱ ልጆች መሆን እንችላለን፡፡ የእርሱን አሳብ አውቀን ስንቀበል እኛን ሐጢያት አልባ ልጆቹ ማድረግ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡ እነዚህ እግዚአብሄር በሚገባ የሚወዳቸውና የሚጠራቸው ሰዎች ናቸው፡፡
እግዚአብሄር የመረጣቸው እነማን ናቸው?
እግዚአብሄር ሰዎችን በሁለት መስመሮች በማሰለፍ በስተቀኙ ያሉትን ‹‹ኑና በኢየሱስ አምናችሁ ሰማይ ግቡ››፤ ከዚያም ወደ ግራው ዞሮ ‹‹ሲዖል ውረዱ›› በማለት እያንዳንዱን ሰው አይመርጥም፡፡
የካልቪን ተከታዮች እግዚአብሄር ከመጀመሪያውም የተወሰኑ ሰዎችን ያለ ምንም ምክንያት መርጦ የቀሩትን ሊተዋቸው ወስኖዋል ይላሉ፡፡ እግዚአብሄር ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር እንደ አሳቡ ለተጠሩት ሁሉ ነገርን ለበጎ አድርጓል፡፡ እኛ ያለ ምንም ምክንያት ያለ ቅድመ ሁኔታ ተመርጠናል ብሎ ማሰብ ስሜት የማይሰጥ ነው፡፡
ታዲያ እግዚአብሄር አመጸኛ አምላክ ነውን? ፈጽሞ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በፍርድ ፊት እኩል ነው፡፡ እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ያዳነንን የደህንነት ጸጋ ከእግዚአብሄር ተቀብለናል፡፡ በዚህ እውነት የማመኑ ዕድልም ለእያንዳንዱ ሰው በእኩል ደረጃ የተሰጠ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን አሳብ እንዲቀበሉና ድክመቶቻቸውን እንዲያውቁ የፈቀደላቸው ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዲያውቁና እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል፡፡
ታዲያ እውነተኛው የመለኮት አስቀድሞ መወሰንና ምርጫ ምንድነው? እነዚህ እግዚአብሄር በሰጠን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ዓላማ መሰረት ለተጠራነው ለእኛ የተሰጡን ናቸው፡፡ እኛ ወደዚህ ዓለም ተወልደን ወንጌልን የማድመጥ ዕድል የተሰጠን እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በኢየሱስ አማካይነት ስለወሰደ ነው፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ሁሉ አስቀድሞ በኢየሱስ ክርስቶስ አቀደ፡፡ ይህ የእግዚአብሄር እቅድ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ በመጀመሪያ ያዕቆብ እንሁን ወይም ኤሳው መመርመር አለብን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ያዕቆብን እንደወደደ ኤሳውን ግን እንደጠላ ይናገራል፡፡ ስለ ቃየንና ስለ አቤልም ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር አቤልን እንደወደደ ቃየንን ግን እንደጠላ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር ኤሳውንና ቃየንን የጠላውና ያዕቆብንና አቤልን የወደደው ያለ ምክንያት ነውን? አይደለም፡፡ ይህ የሆነው ኤሳውና ቃየን በራሳቸው ጉልበት ስለተማመኑና ፈጽሞ የእግዚአብሄርን ምህረት ስላልጠየቁ ያዕቆብና አቤል ግን ድክመቶቻቸውን አውቀው የእግዚአብሄርን ምህረት ስለለመኑና በቃሉ ስለታመኑ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች እንደ ምሳሌ በመጠቀም የእግዚአብሄርን አስቀድሞ ውሳኔና ምርጫ ያብራራል፡፡ እኛ ከየትኛው ወገን ነን? ኤሳው እንዳደረገው በራሳችን ጉልበት የምንታመን ከሆንን እግዚአብሄርን መገናኘት እንችላለንን? አንችልም! እግዚአብሄርን የምንገናኝበት ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሄርን ምህረት የተሞላው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ፊት ከእነዚህ ከሁለቱ በየትኛው ወገን እንቆማለን? እኛ በእግዚአብሄር ፊት መባረክን የምንሻ ሰዎች ነን፡፡ ነገር ግን ከድክመቶቻችን የተነሳ ሁልጊዜም ይህንን ማድረግ ይሳነናል፡፡ እንደ እግዚአብሄር አሳብ ለመኖር ብንፈልግም አሁንም በእግዚአብሄር ፊት ደካሞችና ልፍስፍሶች ነን፡፡ ስለዚህ እኛ መጠየቅ የምንችለው ብቸኛው ነገር የእርሱን ምህረት ነው፡፡
በእግዚአብሄር መባረክ ከፈለግን እንደ ያዕቆብ መሆንና አቤል የነበረውን አይነት እምነት መያዝ አለብን፡፡ በእግዚአብሄር ፊትም ደካሞች፣ ልፍስፍሶችና ድንጉጦች የመሆናችንን እውነታ ማመን አለብን፡፡
መዝሙረ ዳዊት 145፡14 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እግዚአብሄር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፡፡ የወደቁትንም ያነሳቸዋል፡፡›› በእውነት ሰው ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት ይወድቃል፡፡ እኛ ድፍረት የለንም፡፡ በጣም ትንሽ ጥቅም ለማግኘት ስንል እናመቻምቻለን፡፡ ባሮች ነን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደፋሮች እንመስል ይሆናል፡፡ ይህ ግን ለተወሰነ ሰከንድ ብቻ ነው፡፡ ሕይወታችንን በጥንቃቄ ብንመለከተው ምን ያህል ባሮች እንደሆንን በቀላሉ ማወቅ እንችላለን፡፡ እውነትን እንድንደፈጥጥ ለሚያስገድደን ብርቱና ሐሰተኛ ፍጡር እንገዛለን፡፡ እግዚአብሄር ግን ባሮችን እንድንወዳቸውና በኢየሱስ ክርስቶስም ደህንነትን እንድንሰጣቸው ጠርቶዋቸዋል፤ ልጆቹም አድርጎዋቸዋል፡፡
እኛ በእግዚአብሄር እንወደድ ዘንድ ምን ያህል ደካሞችና ሐጢያተኞች እንደሆንን መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ ሕጉን ፈጽሞ በሚያረካው መልኩ በተጨባጭ ልንታዘዘው እንችል እንደሆነ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ያን ጊዜ እኛ ሕጉን የመጠበቅ ችሎታ እንደሌለንና በዚህ ምከንያትም ፍጹም የሆነ ሕይወትን መኖር እንደማንችል በሚገባ ወደ መረዳት እንደርሳለን፡፡
እኔ ፍጹም ብሆን ኖሮ በጭራሽ አዳኝ አያስፈልገኝም ነበር፡፡ እኛ ፍጹማን ብንሆን ኖሮ የእግዚአብሄር እርዳታና ባርኮቶች ለምን ያስፈልጉናል? የእርሱ ባርኮቶች የሚያስፈልጉን በእግዚአብሄር ፊት በጣም ደካሞች ስለሆንን ነው፡፡ የእርሱ ምህረት ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለው ርህራሄ በጣም ብርቱ በመሆኑ አንድያ ልጁን በመላክ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ያነጻ ዘንድ እንዲሸከም አደረገው፡፡ እግዚአብሄር እኛ ከሐጢያት እንድን ዘንድ በእኛ ፋንታ የሐጢያትን ፍርድ ወደ ኢየሱስ አስተላለፈ፡፡ እኛ ልናምነው የሚገባን ይህንን ነው፡፡
ተወዳጅ የእግዚአብሄር ልጆች መሆን የምንችለው በዚህ እምነት ብቻ ነው፡፡ የእርሱን ፍቅር የለበስነው በዚህ ምህረት የተነሳ ነው፡፡ ወደ ደህንነታችን የደረስነው በራሳችን ጥረቶች አይደለም፡፡
ብዙ ክርስቲያኖች አስቀድሞ የመወሰንንና የምርጫን ትምህርቶች ቢያስተምሩም ስለ እነዚህ ትምህርቶችም ይጨነቃሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በእግዚአብሄር ተመርጠው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ግራ ስለሚጋቡ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ትምህርቶች 90% የሚሆነውን የካልቪናውያን ትምህርቶች ይይዛሉ፡፡ ጥያቄው እነርሱ በኢየሱስ ቢያምኑም በእርግጥ ተመርጠዋል ወይስ አልተመረጡም የሚለው ነው፡፡ የሚያስጨንቃቸውም ይህ ነው፡፡ አስፈላጊው ነገር የእናንተ መመረጥ ወይም አለመመረጥ አይደለም፡፡ ለእናንተ አስፈላጊው ነገር የእግዚአብሄርን ጽድቅ በመቀበል ትድኑ ዘንድ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ነው፡፡ ይህንን የእግዚአብሄር ጽድቅ በእምነት የተቀበሉ ሰዎች ምርጦች ናቸው፡፡
በአንድ ወቅት የኮንሰርቫቲቭ ቲዎሎጂ ሊቃውንት ከሆኑት እንደ አንዱ የሚቆጠር የቲዎሎጂ ዶክተር ነበር፡፡ ይህ ሰው እንደ አስቀድሞ መወሰንና መለኮተ ምርጫ ባሉ ተምህርቶችና የካልቪናውያን አስተምህሮቶች ላይ ትልቅ ዋጋ ያኖራል፡፡
አንድ ቀን በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትምህርታዊ ትንተና ሲሰጥ አንድ ተማሪ ‹‹አንተ በእግዚአብሄር ተመርጠሃልን? እግዚአብሄር ማንን እንደመረጠ እንዴት ልታውቅ ትችላለህ?›› በማለት ይጠይቃል፡፡
ይህ የሥነ መለኮት ምሁር ‹‹ይህንን ማን ሊያውቅ ይችላል? ያንን ማወቅ የምንችለው በእግዚአብሄር ፊት ስንቆም ብቻ ነው›› በማለት መለሰ፡፡
በዚህ ጊዜ ተማሪው ‹‹ታዲያ በእግዚአብሄር ፊት ቀርበህ እርሱ አንተ እንዳልተመረጥህ ቢነግርህ ምን ታደርጋለህ?›› በማለት በድጋሚ ጠየቀው፡፡
ፕሮፌሰሩ ‹‹እግዚአብሄር በራሱ አስቀድሞ ስለወሰነው ነገር ምን ማድረግ እችላለሁ? የምታውቀው በእግዚአብሄር ፊት ስትቆም ብቻ ነው ያልሁት ለዚህ ነው›› ብሎ መለሰለት፡፡
ተማሪዎቹ ‹‹ይህ በጣም ትሁት ሰው ነው፡፡ እንደ እርሱ ያለ ትልቅ ሰው እንኳን ተመርጦ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እንደማያውቅ ተናግሮዋል፡፡ ስለዚህ ማንም የተመረጠ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ማወቅ አለመቻሉ የተለመደ ነው›› ሲሉ አሰቡ፡፡
ነገር ግን የእግዚአብሄር ጽድቅ የተደበቀበት እውነት አሁን በግልጽ ተግልጦዋል፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሰወራቸው ጥቂት ነገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ገልጦዋቸዋል፡፡ ወንጌላውያን ድነውና ተመርጠው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ሳያውቁ እንዴት ወንጌልን ሳያውቁ እንዴት ወንጌልን መስበክ ይችላሉ፡፡ በእግዚአብሄር የተጠሩ ሰዎች በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች ናቸው፡፡
ሮሜ 8፡29 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፡፡›› እግዚአብሄር አብ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ የአንድ ልጁን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ ‹‹በኩር›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በኢየሱስና እርሱ በሰጠን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ብናምን ከሐጢያቶቻችንን ሁሉ ድነን የእግዚአብሄር ልጆች እንሆናለን፡፡ ያን ጊዜ ኢየሱስ ከእኛ ጋር በምን ይዛመዳል? ታላቅ ወንድማችን ይሆናል፡፡ እርሱ የእግዚአብሄር በኩር ነው፡፡ እኛም ታናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ነን፡፡
ከረጅም ጊዜ በፊት በጸሎት በፊት ውስጥ እኖር በነበረበት ጊዜ አንድ ሸምገል ያለ ወንጌላዊ ይጎበኘኝ ነበር፡፡ እርሱ ቻይና በነበረ ጊዜ በኢየሱስ ማመን ጀምሮ ስለነበር ወደ ኮርያ መጣ፡፡ አንድ ቀን ሲጸልይ ሰማሁት፡፡ ያለው ይህንን ነበር፡፡ ‹‹ወንድም ኢየሱስና እግዚአብሄር አብ ስላዳናችሁን በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡ ወንድም ኢየሱስ እባክህ እርዳኝ፡፡››
እግዚአብሄር ስለ እኛ ሁሉን ያውቅ እንደሆነ እንጠይቅ ይሆናል፡፡ ስለ እኛ ሁሉን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር አብ ስለ እኛ ሁሉን ያውቃል፡፡ እኛን በአንድያ ልጁ አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን ያቀደው ይህ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር እቅድ ነው፡፡ ልጁ ኢየሱስ ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን ወደዚህ ዓለም መጥቶ ተጠመቀ፤ ተሰቀለም፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ያቀደው ቀድሞውኑ ነበር፡፡
ከዓለም ፍጥረት በፊት እግዚአብሄር እግዚአብሄር የሦስትዮሽ ኮንፍረንስ ተጠርቶ ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ስላሴ አምላክ -- አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ -- በእርሱ ጽድቅ የሚያምኑትን ለማዳን አቀዱ፡፡ ሰዎችን መፍጠርና ፍጹም በሆነው መንግሥቱ ውስጥ አብሮዋቸው ይኖር ዘንድ ልጆቹ ማድረግ ነው፡፡
አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በእቅዱ ተስማሙ፡፡ ከዚያም ሰውን እንዴት እንደሚፈጥርና የሰውን ዘር እንዴት ልጆቹ እንደሚያደርግ በማሰብ ሒደት ውስጥ እግዚአብሄር የልጁን መልክ መምሰል ይችሉ ዘንድ ልጁን ኢየሱስን ወደ ዓለም ለመላክ እንዲጠመቅና በመስቀል ላይ እንዲሞት ለማድረግ አቀደ፡፡
እግዚአብሄር እኛን የመፍጠሩ ዓላማ ምን ነበር? የእርሱ ልጆች እንሆን ዘንድ ነበር፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሄር በኩር ነውን? አዎ ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሄር ልጆች ስለሆንን የእርሱ ወንድሞች ነን፡፡
ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ ለ33 ዓመታት ያህል ሲኖር ሁሉንም ሰብዓዊ ድካሞችና ስንኩልናዎች ተለማምዶዋል፡፡ ስንጸልይ ‹‹ኢየሱስ እኔ በጣም ደካማ ነኝ፡፡ እንዲህ ሆኛለሁ፡፡ እባክህ እርዳኝ፤ ጠብቀኝም፡፡ ቃልህን ይቀበሉ ዘንድ የሰዎችን ልብ አለስልስ፡፡ ጠብቃቸው፤ ጸጋን ስጣቸው፤ እርዳቸውም›› የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጌታም ጸሎታችንን ሰምቶ ይመልሳል፡፡ ወደ ኢየሱስ መጸለይና ወደ እግዚአብሄር መጸለይ አንድና ተመሳሳይ ናቸው፡፡
እግዚአብሄር እኛን የፈጠረበት ዓላማው ምን ነበር? የራሱ ልጆች ያደርገን ዘንድ ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለ እኛ ሁሉን ያውቃል፡፡ ወደዚህ ዓለም እንድንወለድ አድርጎ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አድኖናል፡፡ ምክንያቱም የራሱ ወንድና ሴት ልጆች ያደርገን ዘንድ ከዓለም ፍጥረት በፊት አስቀድሞ ወስኖናልና፡፡ ስለዚህ እርሱ ሕይወታችንንና ሞታችን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችን ሁሉ ያውቃል፡፡ መቼ እንደተወለድን፣ ከማን እንደተወለድን፣ መቼ እንዳገባን፣ ልጆቻችንን መቼ እንደወለድንና በሕይወታችን ውስጥም ምን እንደገጠመን ያውቃል፡፡ ስለ ሕይወታችን ሁሉን የሚያውቀው አምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን የእግዚአብሄር ልጆች እንሆን ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰጠን፡፡
እግዚአብሄር አስቀድሞ አወቀን፡፡ አስቀድሞም ወሰነን፡፡ ሮሜ 8፡30 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡›› ይህንን ምንባብ መረዳቱና ማመኑ ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በበቂ ሁኔታ ትኩረት ላደርግበት አልቻልሁም፡፡
ብዙ ሰዎች ከላይ የተጠቀሰውን ምንባብ በሒደት የመቀደስን ትምህርት ለመደገፍ ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህ ምንባብ ላይ በመመስረት -- እግዚአብሄር አስቀድሞ እንደወሰነን፣ እንደጠራን፣ እንዳጸደቀንና እንዳከበረን -- በልባችን ውስጥ ሐጢያት ቢኖርብንም እግዚአብሄር ሐጢያት እንደሌለብን የሚቆጥረንና ቅዱስ ለመሆን ደረጃዎች ያሉ ይመስል በቅድስና ጊዜ ውስጥ ካለፍን በኋላም እንከብራለን ይላሉ፡፡
እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሊጠራቸው አስቀድሞ አልወሰነምን? እርሱ ሁላችንንም ጠርቶናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ለጥሪው ምላሽ አይሰጡም፡፡ እነርሱ ልክ እንደ ኤሳውና ቃየን ናቸው፡፡ እነርሱ ወደ ሲዖል የሚወርዱ ሰዎች ናቸው፡፡
በእግዚአብሄር ምህረት፡፡
እግዚአብሄር አብ በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሊጠራን አቀደ፡፡ ሐጢያቶቻችንንም በውሃና በደም በማንጻት የገዛ ልጆቹ አድርጎ ሊወስደን አስቀድሞ ወሰነን፡፡ እግዚአብሄር እየጠራቸው ወደ እርሱ የማይመጡ ሰዎች በሙሉ ከእግዚአብሄር ደግንነት ውጪ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከጸጋው ተገልለው ለሲዖል ታጭተዋል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ጥሪ የሚታዘዙ ሰዎችም ደግሞ አሉ፡፡ እነርሱ ‹‹አቤቱ እኔ እንዲህ ደካማ ሆኜ እኔን የመሰለ ሰው ትቀበላለህን?›› ይላሉ፡፡
እግዚአብሄርም ‹‹በእርግጥ እቀበላለሁ›› ይላል፡፡
‹‹እውነት? እኔ እንዲህ ደካማ ሆኜ ትቀበለኛለህን?››
‹‹በእርግጥ እቀበልሃለሁ፡፡››
‹‹አቤቱ ለአንተ የማቀርበው ምንም ልዩ የሆነ ነገር የለኝም፡፡ ከአሁን ጀምሮም ጥሩ እሆናለሁ ብዬም ተስፋ መስጠት አልችልም፡፡››
‹‹አሁንም እቀበልሃለሁ፡፡››
‹‹የተሻልሁ እንደምሆን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ያንን የማድረግም አቅም የለኝም፡፡››
‹‹አሁንም እቀበልሃለሁ፡፡››
‹‹ምናልባት ስለማታውቀኝ ይሆናል፡፡ በራሴ አዝናለሁ፡፡››
የሆነ ሰው በእኛ በእርግጥ እንደሚያምን እየነገረን ሳለ ማንነታችንን ስናውቅ የሆነ ቦታ መደበቅ እንደምንፈልግ ሁሉ አዘውትረን ሐፍረት አይሰማንምን? መሻሻል ስለማንችልና እስከ አሁን ድረስ ያደረግነውንም መቀጠል ስለሚያዳግተን መደበቅ እንፈልጋለን፡፡
‹‹በጣም ደካማ ብሆን እንኳን ትቀበለኛለህን? በአንተ እንዳምንስ ተፈቅዶልኛልን? እኔን የመሰለ ሰው የሐጢያቶችን ይቅርታ ማግኘት ይችላልን? ወደፊት ጥሩ ሰው መሆን ባልችልም እንኳን እኔን የመሰለ ሰው ሊጸድቅ ይችላልን?›› በማለት የምንጠይቀው ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን አምላካችን የበረሃውን ወይራ ያማረ የወይራ ዛፍ አድርጎ ሊለውጠው ይችላል፡፡
እኛ በመጀመሪያ ከፍጥረታችን የበረሃ ወይራዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በሰጠን ወንጌል ያማረ የወይራ ዛፍ ሆንን፡፡ ሐጢያት ከመስራት መቆጠብ የማንችለውን እኛን ጠራን፡፡ እርሱ የጠራን ትንሽ ደካሞች በነበርን ጊዜ ነውን? እርሱ እኛን የጠራን ፈጽሞ አቅም አልባ በነበርን ጊዜ ነው፡፡ በጣም የከበዱ ጉድለቶችና የትየለሌ የሆኑ ድክመቶች ቢኖሩብንም ጠራን፡፡ እኛን ልፍስፍሶቹን ጠራን፡፡ እርሱ ከጠራን በኋላ ምን አደረገ? ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶ የዘላለም ሕይወት ይሆንልን ዘንድ ጽድቁን ሰጠን፡፡
እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደረገው እንዴት ነው? በማቴዎስ ምዕራፍ 3 ላይ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጥቶ እግዚአብሄር ለሰው ዘር ያቆመውን ጽድቅ ሁሉ ለመፈጸም ተጠመቀ፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በመሸከምም በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ከዓለም ሐጢያቶች ሊያድናቸውም በሦስተኛው ቀን ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡ አዲስ ሕይወትንም ሰጠን፡፡ እንዲህ በማድረጉም አጸደቀን፡፡ በውሃና በደምም ሐጢያቶቻችንን አነጻ፡፡ የእግዚአብሄርንም ጽድቅ ሰጠን፡፡ ሐጢያት አልባም አደረገን፡፡ ከዚያም ያጸደቀንን እኛን አክብሮ የእግዚአብሄር ልጆች አደረገን፡፡
ኢየሱስ ሰማይ እንድንገባና የእግዚአብሄር ልጆች ሆነን ለዘላለም እንድንኖር አከበረን፡፡ ይህ ገብቶዋችኋልን? የሃይማኖት ትምህርቶች ግን ሐጢያተኞች ብትሆኑም በኢየሱስ ካመናችሁ ቀስ በቀስ ትቀደሳላችሁ፤ ስትሞቱም በእግዚአብሄር ፊት ፍጹም ሰው ሆናችሁ ትቆማላችሁ ብለው ያስተምራሉ፡፡ ይህ እውነትን የሚቃወም ነው፡፡ ይህ እውነተኛ እምነት አይደለም፡፡ የዚያ አይነቱ እምነት ለቅድስና ትምህርት እንጂ ለእውነት የቆመ እምነት አይደለም፡፡
ጌታ ከሐጢያቶቻችን አዳነን፡፡ እግዚአብሄርም አስቀድሞ ወሰነን፤ ጠራን፡፡ በአንድ ጊዜም በውሃውና በደሙ ከሐጢያቶቻችን አነጻን፡፡ ልጆቹ አደረገን፤ አጸደቀን፡፡ በክብር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንገባ ዘንድም ባረከን፡፡ እውነቱ ይህ ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ያሉትን በረከቶች በሙሉ በአንድ አረፍተ ነገር በማጠቃለል እውነትን የተናገረው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ይህ ምንባብ በሒደት ስለሚሆኑት የቅድስና ትምህርት ሰባት ደረጃዎች እየተናገረ አይደለም፡፡ ሙሉ በሙሉ የተቀደስን ለመሆን በሰባቱ ደረጃዎች ውስጥ ካለፍን በኋላ ቀስ በቀስ ፍጹማን እንሆናለን አይልም፡፡
ሮሜ 8፡30 እግዚአብሄር በኢየሱስ ካመንን በኋላ ይጠራናል ወይም እየሸመገልን ስንሄድ እንቀደሳለን አይልም፡፡ በመጨረሻ ሙሉ ወደሆነ ቅድስና ላይ እስክንደርስ ድረስ የቅድስናን መሰላል ደረጃ በደረጃ ቀስ በቀስ እንወጣለን አይልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ስናውቅና ኢየሱስ ክርስቶስም ሲጠራን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ በውሃውና በደሙ ይቅር ብሎዋል፡፡ በእቅፉ ውስጥ የምንገባው በዚህ የእውነት ወንጌል ወደ እግዚአብሄር ስንቀርብ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ከዚህ በፊት ሐጢያቶቼን አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን ስብከት ከሰማሁ በኋላ ሐጢያቶቼን ማወቅ እየጀምርሁ ነው፡፡ ከትዝታዎቼ የማስታውሳቸው አንድ ወይም ሁለት ሐጢያቶች ናቸው፡፡ ወደፊትም ሐጢያት መስራቴን እቀጥል ይሆናል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ማመን የምችል አይመስለኝም፡፡›› ያ ግን ትክክል አይደለም፡፡ በፈንታው እንደዚህ ብለን ልናስብ ይገባናል፡- ‹‹አሃ! ያ ትክክል ነው፡፡ ስሰራቸው የነበሩትን ሐጢያቶቼን አላውቃቸውም ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ሁሉም ትክክል ነው፡፡ በእርሱ ቃል ማመን አለብኝ፡፡ ነገር ግን እንደ ቃሉ መኖር አልቻልሁም፡፡ እኔ ለሲዖል የታጨሁ ክፉ ሐጢያተኛ ነኝ፡፡ ኢየሱስም የመጣው ለዚህ ነው፡፡››
በኢየሱስ በማመንና የሐጢያቶችን ይቅርታ በማግኘት ሐጢያት አልባ ሆነናል፡፡ ተቀድሰን የዕግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ስለሆንን ሰማይ መግባትና መክበር እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅና እውነት ይህ ነው፡፡
እግዚአብሄር አስቀድሞ ወሰነን፤ ጠራን፤ አጸደቀን፤ አከበረንም፡፡ ‹‹ቀስ በቀስ እለወጣለሁ፤ ሐጢያት አልባ ሰውም እሆናለሁ›› በማለት በሒደት የመቀደስ ትምህርት ትክክል እንደሆነ ታስቡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባመናችሁበት ቅጽበት በአንድ ጊዜ ጸድቃችኋል፤ ተቀድሳችኋል፡፡ ልባችሁ ደረጃ በደረጃ አይለወጥም፡፡ ልባችሁ በአንድ ጊዜ ሐጢያት አልባ ሆንዋል፡፡ በእግዚአብሄር ቃልና በቤተክርስቲያኑ ስታምኑም እምነታችሁ ቀስ በቀስ እያደገ ይሄዳል፡፡
የእግዚአብሄርን ቃል ስንመገብ እምነታችን ቀስ በቀስ እያደገ ይሄድና ውሎ አድሮ ሌሎችን ማስተማር ወደምንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ልጆች የምንሆነው ይበልጥ ፍጹማንና ይበልጥ ሐጢያት አልባ ስንሆን ነው የሚለው አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በአንድ ጊዜ ቅዱሳንና ሐጢያት አልባ ሆነናል፡፡
እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ አስቀድሞ በወሰነው መሰረት ጠርቶናልን? አዎ ጠርቶናል፡፡ እርሱ በኢየሱስ ክርሰቶስ ጠርቶን ጻድቃንና ሐጢያት አልባ አድርጎናል፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት አጸደቀንና ሐጢያት አልባ አደረገን፡፡ ልጆቹም አድርጎ ወሰደን፡፡ ወደ መንግሥቱም እንድንገባ አከበረን፡፡
የእግዚአብሄርን ጽድቅ በፈጸመው በኢየሱስ ክርስቶስ ደህንነት በማመን በአንድ ጊዜ ጸድቀናል፡፡ ደካሞች ብንሆንም የእግዚአብሄርን ጥሪ ስለታዘዝንና ኢየሱስም ሐጢያት አልባና ጻድቃን የእግዚአብሄር ልጆች የመንግሥቱ ሕዝብ ሊያደርገን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንዳነጻን ስላመንን ተባርከናል፡፡
የቅድስና ትምህርት የተሳሳተ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ስሜት አይሰጥም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡›› እምነት ቀስ በቀስ ያድጋል፡፡ ነገር ግን የሐጢያቶች ይቅርታ የእግዚአብሄር ልጆች መሆንና ሰማይ መግባት-- እነዚህ ሁሉ በአንድ ጊዜ የሚሆኑ ናቸው፡፡ በዚህ ታምናላችሁን?
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእግዚአብሄር ልጆች መሆን ችለናል፡፡ እግዚአብሄር የማይረባውን ሕይወታችንን ሁሉ አድኖታል፡፡ እኛ ለደህንነታችን ለእግዚአብሄር ያደረግንለት አንዳች ነገር አለን? ጻድቅ ለመሆን ያደረግነው አስተዋጽዖ አለን? እኛ ያቀድነው ምንም ነገር የለም፡፡ ማንም ሰው ከመወለዱም በፊት ቢሆን እንኳን በኢየሱስ ለማመን አልወሰነም፡፡ በእናቱ ማህጸን ውስጥ ሆኖ በኢየሱስ ለማመን የወሰነ ሰው አለን?
እኛ እውነቱን ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሚያምኑት ሰምተን እውነት እንደሆነ በመረዳት ለራሳችን ‹‹በዚህ ከማመን በቀር ምርጫ የለኝም፡፡ እኔን የመሰለ ሐጢያተኛ ሰው በዚህ ማመን አለበት›› ብለን አሰብን፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አመንን፡፡ የሐጢያቶቻችንን ይቅርታም ተቀበልን፡፡ የእግዚአብሄርም ልጆች ሆንን፡፡
የእግዚአብሄር ልጆች ጻድቃን ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሄርም በመንግሥተ ሰማይ ዘላለማዊ ባለጠግነቶችና ክብሮች ለዘላለም አከበረን፡፡ መክበር ማለት ይህ ነው፡፡ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለተቀበሉ ምዕመናኖች እነዚህን በረከቶች ሰጥቶዋቸዋል፡፡
ጌታ ይመስገን!