Search

Sermones

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-1] መንፈስ ቅዱስ የሚሰራው በእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ የሐዋርያት ሥራ 1፡4-8 ››

መንፈስ ቅዱስ የሚሰራው በእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ውስጥ ነው፡፡
‹‹ የሐዋርያት ሥራ 1፡4-8 ››
‹‹ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፡፡ ነገር ግን፡- ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ፡፡ እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፡- ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለኢየሩሳሌም መንግሥትን ትመልሳልህን? ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም፡- አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ሐይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡›› 
 
 
መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው ወይስ አንድ ሰው በራሱ ጥረት ሊያገኘው የሚችል ነገር ነው?
መንፈስ ቅዱስ ለሐጢያቱ ይቅርታ ላገኘ ሰው የተሰጠ ስጦታ ሲሆን የእግዚአብሄርን ተስፋ ፍጻሜ ትርጉም ይዞዋል፡፡
 
በአንድ ወቅት ስጸልይ ሳለ ልክ መንፈስ ቅዱስን የሚመስል የአንድ ነገር ነበልባሎችን የመቀበል ልምምድ አገኘሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነበልባሎች በተጠራቀመው ሐጢያት ፊት በነው ጠፉ፡፡ ሆኖም በውስጣችን ለዘላለም ስለሚኖረው መንፈስ ቅዱስ እውነቱን ላሳያችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ይህንን የማሳያችሁ በቀላሉ በሐሰት መንፈስ የሚጠፋውን ሳይሆን በእውነተኛው ወንጌል አማካይነት የሚነደውን ነው፡፡ በዚህ መልዕክት በኩል የማስተዋውቃችሁ መንፈስ ቅዱስ በጸሎቶች አማካይነት ስለምትቀበሉት ሳይሆን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባላችሁ እምነት ብቻ የምትቀበሉትን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
በዚህ መጽሐፍ አማካይነት 1በውስጣችሁ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ እንድትቀበሉ እመራችኋለሁ፡፡ ለእናንተ የማቀርበው መልዕክት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የመጣ መሆኑንም ትገነዘባላችሁ፡፡ በዚህ ወቅት መንፈስ ቅዱስን እንቀበል ዘንድ የእግዚአብሄር ፍጹም ፍላጎት ነው፡፡ በውስጣችሁ ስለሚያድረው መንፈስ ቅዱስ መማርና በዚህ መጽሐፍ አማካይነት መቀበል ትችላላችሁ፡፡ ይህ መጽሐፍ ለእናንተ በቂ ካልሆነ ቀደም ብዬ ያሳተምኋቸውን ሁለቱን መጽሐፎቼን እንድታነቡ እመክራችኋለሁ፡፡ በእነዚህ መጽሐፎች አማካይነት በእግዚአብሄር ፊት ፍጹም እምነትን ትቀበላላችሁ፡፡
 
[1]መንፈስ ቅዱስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ባገኙ ዳግም የተወለዱ ልቦች ውስጥ ይኖራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አንድ ጊዜ በቅዱሳኑ ውስጥ ከገባ በውስጣቸው ለዘላለም ይኖራል፡፡ በወንጌል እስካመኑ ድረስም ትቶዋቸው አይሄድም፡፡ ለቅዱሳን አመኔታን ይሰጣቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሄር ፈቃድ እንዲያውቁ ይመራቸዋል፡፡ በአለም ውስጥ ያሉትን ፈተናዎችና ችግሮች እንዲያሸንፉ ያበረታቸዋል፡፡ የመንፈስ ፍሬዎችንም አብዝተው እንዲያፈሩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ እግዚአብሄር በውስጣቸው በሚያድረው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት የቅዱሱን አካል የእግዚአብሄር መቅደስ አድርጎ ያከብረዋል፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 2፡38-39፤ ዮሐንስ 14፡16፣ 16፡8-10፤1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16፣ 6፡19፤ገላትያ 5፡22-23) 
 
ብዙ ክርስቲያኖች በበዓለ ሃምሳ ቀን በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ እንደወረደው መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ይሞክራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህን ዘዴ በመጠቀም ብዙ ገንዘብ አከማችተዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሰው ጥረት የሚገኝ ነገር እንደሆነ አድርገው ያታልላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ራዕዮችን ማየት፣ ተዓምራትን ማድረግ፣ የኢየሱስን የራሱን ድምጽ መስማት፣ በልሳን መናገር፣ ሕሙማንን ማዳንና አጋንንትን ማስወጣት ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም በልባቸው ውስጥ ሐጢያት ያላባቸው ስለሆኑ በክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ስር ናቸው፡፡ (ኤፌሶን 2፡1-2) አሁንም እንኳን ብዙ ሰዎች በክፉ መናፍስት ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ሳያውቁ በመኖር ላይ ናቸው፡፡ ሰይጣን እንደ ድንቆችንና ተአምራቶች ያሉ ዘዴዎችን በመጠቀም ሰዎችን የሚያስተውና የሚያታልለው ለዚህ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ምናብ ናቸው፡፡  
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ በማለት አዘዛቸው፡- ‹‹ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፡፡ ነገር ግን፡- ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 1፡4) በሐዋርያት ሥራ ላይ ያለው መንፈስ ቅዱስ የተገኘው ‹‹በሥራ››፤ ‹‹በልምድ›› ‹‹በመሰጠት›› ወይም ‹‹በጸሎት›› ሳይሆን ‹‹የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ነው፡፡›› ከዚህ ምንባብ መማር የምንችለው ነገር ቢኖር መንፈስ ቅዱስ በሰው ልጆች በሚደረግ ተደጋጋሚ ጸሎት ሊገኝ እንደማይችል ነው፡፡ ይህ እግዚአብሄር አብና ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ዘር በሰጡት ውብ የውሃና የመንፈስ ወንጌል ሙሉ በሙሉ በማመን ብቻ የሚገኝ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ እውነተኛውን መንፈስ ቅዱስ ማግኘት የሚቻለውም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ወንጌል ላይ ባለን እምነት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር በውስጣችን የሚያድረውን መንፈስ ቅዱስን በትክክል ለማግኘት እንችል ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰጥቶናል፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 3፡3-5)  
 ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ›› የሚለው ሐረግ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ተጽፎአል፡፡ ጴጥሮስ በበዓለ ሐምሳ ቀን ስለወረደው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በመልዕክቱ ላይ እንደተናገረው (የሐዋርያት ሥራ 2፡38-39) ‹‹በውቡ የውሃና የመንፈስ ወንጌል አምነው የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ላገኙ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡››
በውስጣችን የሚያድረው መንፈስ ቅዱስ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ላገኙት የሚሰጥና የእግዚአብሄርን ተስፋ ፍጻሜ ትርጉም የያዘ ስጦታ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሄርና በሰዎች መካከል በተደረገ ስምምነት ሊሰጥ የሚችል አንዳች ነገር ሳይሆን ከእግዚአብሄር የመጣ ተስፋ የተሰጠበት ስጦታ ነበር፡፡ ስለዚህ በውስጣችሁ የሚያድረው መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደተገለጠው በጸሎት አማካይነት ሊገኝ የሚችል ስጦታ አይደለም፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 8፡19-20)      
መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው ኢየሱስ በሰጠን የውሃና የመንፈሱ ወንጌል በሚያምኑት ላይ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ እንዲኖር መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክ ቃል ገብቶላቸው ነበር፡፡ ‹‹ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 1፡5) ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል እስኪፈጸም ድረስ ጠበቁ፡፡   
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ሰዎች ያምኑዋቸው የነበሩትን እምነቶች ስንመለከት ይህን ያገኙት በእግዚአብሄር ስጦታ እንጂ በራሳቸው ጥረት አለመሆኑን ማየት እንችላለን፡፡ በሐዋርያት ሥራ ላይ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የወረደው በሰብአዊ ጥረት ወይም በመንፈሳዊ ስኬት አልነበረም፡፡ 
በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጻፈው የመንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መውረድ እውን ሆነ፡፡ ይህም ልክ ኢየሱስ ‹‹ከጥቂት ቀናት በኋላ›› ብሎ እንደተናገረው ነበር፡፡ ይህ በጥንቷ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው በረከት ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻህፍትን በመመልከት የእግዚአብሄር ተስፋ የተፈጸመው በኢየሱስ በማመን እንጂ በዖም፣ በጸሎቶች ወይም ራስን መስዋዕት በማድረግ እንዳልሆነ ማየት እንችላለን፡፡ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ምዕመናን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ አግኝነተው በዚያው ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ 
 
 

መንፈስ ቅዱስ ድንገት በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ከሰማይ ወረደባቸው!

 
‹‹በዓለ ሃምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡1) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው የገባውን ቃል እንዲፈጸም በአንድነት ተሰብስበው ነበር፡፡ በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፡፡ 
‹‹ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፡፡ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሞላው፡፡ እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፡፡ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፡፡ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡2-4) 
መንፈስ ቅዱስ ‹‹በድንገት ከሰማይ›› ወረደባቸው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ድንገት›› የሚለው ቃል ይህ በሰው ልጆች ፍላጎት የተደረገ አልነበረም ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከሰማይ›› የሚለው ሐረግ የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ ከየት እንደሚመጣ ከማብራራቱም በላይ በውስጣችን የሚያድረው መንፈስ ቅዱስ በሰው ፈቃድ ወይም ጥረት ሊገኝ ይችላል የሚለውን እሳቤ ይቃረናል፡፡ አንዳንዶች ‹‹ከሰማይ›› የሚለውን ቃል መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው በጸሎት ነው በሚል ሰዎችን ለማታለል ይጠቀሙበታል፡፡ 
በሌላ አነጋገር መንፈስ ቅዱስ በድንገት ከሰማይ መጣ ሲባል መንፈስ ቅዱስ በልሳን እንደ መናገር ወይም ራስን መስዋዕት እንደ ማድረግ ባሉ ምድራዊ ዘዴዎች ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመጀመሪያ በልሳን የተናገሩት ውቡን ወንጌል ከየአገሩ ለመጡ ሁሉ ለማሰራጨት ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አማካይነት የውጪ ቋንቋ ለሚናገሩት አይሁድ ተናጋሪዎች በራሳቸው ቋንቋ ወንጌልን ለማሰራጨት ነበር፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡት ሰዎችም ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ራሳቸው ቋንቋዎች በልሳን መናገራቸውን ሲሰሙ ነገሩ እንግዳ ነው ብለው አሰቡ፡፡ ምክንያቱም ከደቀ መዛሙርቶቹ አብዛኞቹ የገሊላ ሰዎች ነበሩና፡፡   
‹‹እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፡፡ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡3-4) እዚህ ላይ መንፈስ ቅዱስ ‹‹በያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው›› ለሚለው ሐረግ ልዩ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ አንድ ቦታ ተሰብስበው የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ይጠባበቁ የነበሩት ደቀ መዛሙርት በሙሉ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ዳግም የመወለድን ወንጌል ቀድሞውኑም ያመኑ ነበሩ፡፡  
በዚህ ዘመን ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች ይህን የመልዕክት ክፍል በትክክል አልተረዱትም፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ሆኖ የመጣው ሲጸልዩ በነበረ ጊዜ ነው ብለው አምነዋል፡፡ ሆኖም ስለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ያለው የተሳሳተ መረዳት የመጣው ከድንቁርናና ከግራ መጋባት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ ሲመጣ እንደዚህ ያለ ድምጽ ይፈጥራልን? የለም አይፈጥርም፡፡
ሰዎች በጆሮዎቻቸው የሚሰሙት ድምጽ ሰይጣን የሰዎችን ነፍሶች በሚውጥበት ጊዜ የሚፈጥረውን ድምጽ ነው፡፡ እርሱ ይህንን ድምጽ የሚፈጥረው መንፈስ ቅዱስን ተመስሎ ሰዎችን ግራ መጋባት ውስጥ ለመክተት በሚያደርጋቸው ጥረቶቹ በምናቦች፣ በአስመሳይ ድምፆችና በሐሰተኛ ተአምራቶች በሚሰራበት ጊዜ ነው፡፡ ሰዎች እነዚህን ነገሮች የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ማስረጃ እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ይሳሳታሉ፡ አንዳንድ ሰዎችም መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ እንደ ነፋስ አይነት ‹‹ሽሽሽ…›› የሚል ድምጽ እንደሚፈጥር ያስባሉ፡፡ እነዚህ በሰይጣን እየተታለሉ ነው፡፡ በሐዋርያት ስራ ውስጥ እንደተጻፈው መንፈስ ቅዱስ ሊገኝ የሚችለው በውቡ ወንጌል ላይ ባለን እምነታችን ብቻ ነው፡፡    
 
 

የጴጥሮስ እምነት (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21) መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ይፈቅድለት ዘንድ ፍጹም ነበር፡፡ 

 
በሐዋርያት ሥራ ላይ የተጻፉትን የበዓለ ሃምሳ ክስተቶች በማሰማመር እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ የወረደው አስቀድመው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመናቸው የመሆኑን እውነት ማበከር ፈለገ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ብዙውን ጊዜ ‹‹በዓለ ሃምሳን›› መንፈስ ቅዱስ ከልዕለ ተፈጥሮ ምልክቶችና ከአሸባሪ ድምጽ ጋር ከሰማይ የወረደበት ጊዜ እንደነበር ያስባሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመነቃቃት ጉባኤዎች ሰው በትጋት በመጸለይ፣ በመጾም ወይም ደግሞ በእጆች በመጫን መንፈስ ቅዱስን ማግኘት እንደሚችል የታመነው ለዚህ ነው፡፡ በአጋንንት መያዝ፣ ራስን መሳት፣ ለብዙ ቀናት ያህል ምናብ ውስጥ መቆየት ወይም ደግሞ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ መንቀጥቀጥ የመንፈስ ቅዱስ ስራዎች አይደሉም፡፡ 
መንፈስ ቅዱስ ሚዛናዊ አካል ስለሆነ የሰውን ማንነት ችላ የሚል አይደለም፡፡ በሰው ላይ በዕብሪት አይወርድም፡፡ ምክንያቱም እርሱ እውቀት፣ ስሜትና ፈቃድ ያለው ሕላዌ እግዚአብሄር ነውና፡፡ እርሱ በሰዎች ላይ ሊወርድ የሚችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሲያምኑ ብቻ ነው፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)
ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የመጣው ነቢዩ ኢዩኤል በተነበየው መልኩ መሆኑን መስክሮዋል፡፡ ይህም ሐጢያታቸው የተሰረየላቸው መንፈስ ቅዱስን ያገኛሉ የሚለውን በእግዚአብሄር የተሰጠ ተስፋ የሚፈጽም ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የሚችሉት ኢየሱስ የሰውን ልጆች ከሐጢያት ለማዳን መጠመቁንና መሰቀሉን የሚያምኑት ብቻ ናቸው፡፡ የጴጥሮስ ስብከት ከኢዩኤል ትንቢት ጋር አብሮ ኢየሱስ ለምን እንደተጠመቀና እኛም ይህን ማወቅ ለምን በዚህ ማመን እንደሚያስፈልገን ያሳየናል፡፡ ይህንን እውነት ማወቅ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ይመራቸዋል፡፡  
ጴጥሮስ በመሰከረለት ውብ ወንጌል ታምናላችሁን? ወይስ አሁንም ድረስ ከዚህ ውብ ወንጌል ጋር የማይገናኙ አይረቤና ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዙ አመኔታዎችን ይዛችኋል? ያለ እግዚአብሄር ዕቅዶች መንፈስ ቅዱስን በራሳችሁ አድራጎት ለመቀበል ትሞክራላችሁን? (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21) ሰዎች ከሐጢያቶቻቸው ለመንጻት ተስፋ በማድረግ በእግዚአብሄር ቢያምኑና የንስሐ ጸሎቶችን ቢያቀርቡም መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከማመን በስተቀር ሌላ መንገድ የለም፡፡
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ባታውቁም አሁንም በውስጣችሁ የሚያድረውን መንፈስ ቅዱስ እየተጠባበቃችሁ ነውን? መንፈስ ቅዱስ በልባችሁ ውስጥ እንዲኖር የሚያደርገውን የኢየሱስን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን እውነተኛ ትርጉም ታውቃላችሁን? መንፈስ ቅዱስ በልባችሁ ውስጥ ሊያድር የሚችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስታምኑ ብቻ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ፡፡ እውነተኛው መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው እንዲኖር የተፈቀደላቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግም የተወለዱት ብቻ ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን እንድንቀበል የሚፈቅድልንን የውሃና የመንፈስ ወንጌሉ ስለሰጠን እግዚአብሄርን እናመሰግነዋለን፡፡