Search

Sermones

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-5] በእግዚአብሄር ጽድቅ መመላለስ፡፡ ‹‹ሮሜ 8፡12-16›› 

‹‹ሮሜ 8፡12-16›› 
‹‹እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ፡፡ በእግዚአብሄር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸውና፡፡ አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡››
 
 
ከእግዚአብሄር ዘንድ ደህንነትን የተቀበለው ሐዋርያው ጳውሎስ ዳግም የተወለዱ ምዕመናን እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር እንደሌለባቸው ተናግሮዋል፡፡ በተለይም የእግዚአብሄር ጽድቅ ያለን እኛ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብንኖር እንደምንሞት በመንፈስ ብንኖር ግን በሕይወት እንደምንኖር ጳውሎስ ተናግሮዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት ማመን አለብን፡፡ ታዲያ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች መኖር የሚገባቸው በምንድነው? መኖር የሚገባቸው እንደ እግዚአብሄር ጽድቅ ነው ወይስ እንደ ሥጋ ምኞት? ትክክል የሆነው ነገር ምን እንደሆነ አውቀው ራሳቸውን ለእግዚአብሄር የጽድቅ ሥራዎች ቀድሰው ለመስጠት ሰውነታቸውን መግራት አለባቸው፡፡
  
 

የማይመለጠው  ግዴታ፡፡

 
ጳውሎስ እንደ ሐጢያተኛ ተፈጥሮ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ የመኖር ግዴታ እንዳለብን አሳይቷል፡፡ ምክንያቱም እኛ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሄር ቁጣ ድነን ወደ ጽደቁ ተመርተናል፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ አውቀን በእርሱ ከማመናችን በፊት እንደ መንፈስ ፈቃድ መኖር አልቻልንም፡፡ አሁን ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ስላወቅንና ስላመንን ልባችንን፣ አስተሳሰቦቻችንን፣ መክሊቶቻችንን፣ አካሎቻችንንና ጊዜያችንን ለጽድቅ ሥራዎቹ ማዋል እንችላለን፡፡ ራሳችንን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የመስበክና የጽድቅ ሥራዎቹን የመስራት መሳሪያዎች አድርገን መጠቀም ይገባናል፡፡
     
 

እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር፡፡   

 
የክርስቶስ ሆናችሁ በመንፈስ ሳይሆን በሐጢያተኛ ተፈጥሮዋችሁ የምትኖሩ ከሆናችሁ የማያምኑ ሰዎች ሁሉ እንደሚጠፉት እንደምትጠፉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ምክንያቱም ዳግም የተወለዳችሁ ክርስቲያን ብትሆኑም እንደ እግዚአብሄር ጽድቅ አልኖራችሁም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ትሆኑ ዘንድ በእግዚአብሄር ጽድቅ እንጂ ዳግመኛ በሥጋ መኖር አይገባችሁም፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ስለምታምኑ ጽድቁን ለማገልገል የታጫችሁ ናችሁና፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብቻ የምትኖሩ ከሆናችሁ መንፈሳችሁ ይሞታል፡፡ ነገር ግን እንደ እግዚአብሄር ጽድቅ የምትኖሩ ከሆናችሁ ለዘላለም በሰላም ትኖራላችሁ፡፡
     
 

የእግዚአብሄር ልጆች፡፡ 

 
‹‹በእግዚአብሄር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸውና፡፡›› (ሮሜ 8፡14)
 
በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በስጦታ መልክ ተቀብለዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ይመራቸዋል፡፡ እነዚህ ‹‹እግዚአብሄር ልጆች›› ናቸው፡፡ ‹‹የእግዚአብሄር ልጆች›› በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ ይኖራል፡፡ ስለዚህ በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ የማይኖርባቸው ሰዎች የእርሱ አይደሉም፡፡ እግዚአብሄርን ለመከተል መነሻው በእርሱ ጽድቅ ማመን ነው፡፡ የሚጀምረውም የእግዚአብሄር ልጅ ለመሆን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቃል በማመን ነው፡፡ ይህ ማለት በእርሱ ጽድቅ በማመን የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባል ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሄርም እናንተን ከሐጢያቶቻችሁ ለማዳን ጽድቁን ሰጥቶዋችኋል ማለት ነው፡፡
 
የአይሁድ መሪ የነበረው ኒቆዲሞስ ኢየሱስን በጎበኘው ጊዜ ማንም ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሄር ልጅ መሆን እንደማይችል ነግሮታል፡፡ ኒቆዲሞስ በዚህ ተደንቆ እንዲህ በማለት ጠየቀ፡- ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?›› (ዮሐንስ 3፡4) ኢየሱስም እንዲህ በማለት መለሰ፡- ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፡፡ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምጹንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፡፡ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው፡፡›› (ዮሐንስ 3፡5-8)
 
ኢየሱስ ከውሃና ከመንፈስ ያልተወለደ ሰው ዳግም የመወለድን ትርጉም መረዳት እንደማይችል ተናግሮዋል፡፡ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን በእርሱ የጽድቅ ሥራ የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንዲቀበሉ እንደሚያስችላቸው ተናግሮዋል፡፡ በወንጌል ቃል የሚያምኑ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በስጦታ መልክ መቀበል ይችላሉ፡፡ ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ መድረስ ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የተቀበለ ሁሉ የእግዚአብሄር ልጅ መሆን ይችላል፡፡ የእርሱ ሕዝቦች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው፡፡
        
 
እኛ የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ይመሰክራል፡፡ 
 
‹‹አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡›› (ሮሜ 8፡15-16)
እኛ የእግዚአብሄር ልጆች የመሆናችንን እውነታ መመስከር የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች ብቻ አሉ፡፡ የመጀመሪያው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የተገለጠው የእግዚአብሄር ጽድቅ የእርሱ ልጆች ያደረገን መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ መምጣቱ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውሃና በመንፈስ ወንጌል ውስጥ ይሰራል፡፡ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ያቀደው እግዚአብሄር ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን እኛ የእግዚአብሄር ልጆች ለመሆናችን የሚነግረን የራሳችን ምስክር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በማወቅና በማመን የእግዚአብሄር ልጆች የሆኑ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር ‹‹አባ›› አባታችን ብለው የመጸለይ መብት አላቸው፡፡
 
በተገቢው መንገድ ለማሰብ እንሞክር፡፡ በልቡ ወስጥ ሐጢያት ያለበት ሰው እግዚአብሄርን እንዴት አባቱ ብሎ ሊጠራው ይችላል? እግዚአብሄር አብ በጭራሽ ሐጢያተኛን የራሱ ልጅ አድርጎ አልወሰደውም፡፡ ሐጢያተኛም እግዚአብሄርን እንደ አባት ፈጽሞ አገልግሎት አያውቅም፡፡ ወደ ውስጣችሁ ተመልክታችሁ እናንተም በማናቸውም አጋጣሚ የዚህ አይነት ስህተት ሰርታችሁ እንደሆነ ማየት አለባችሁ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሄር ልጆች ለመሆናቸው የሚመሰክሩ ሰዎች በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለ እግዚአብሄር ጽድቅ በጥልቀት ማሰብ አለብን፡፡