Search

Sermones

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[19-2] የክርስቶስን ምጽዓት ተስፋ መጠበቅ የሚችሉት ጻድቃን ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 19፡1-21 ››

የክርስቶስን ምጽዓት ተስፋ መጠበቅ የሚችሉት ጻድቃን ብቻ ናቸው፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 19፡1-21 ››
 
ቀደም ባለው ምዕራፍ እግዚአብሄር አሰፈሪ መቅሰፍቶቹን እንዴት በዚህ ዓለም እንደሚያወርድ አይተናል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ክርስቶስና የከበረው ጭፍራው ከጸረ ክርስቶስ ጭፍሮች ጋር ተዋግቶ በማሸነፍ አውሬውንና የእርሱን አገልጋዮች በሕይወት እያሉ ወደ እሳት ባህር እንደሚወረውር፣ ቀሪዎቹን የጸረ ክርስቶስ ጭፍሮችም ከጌታ አፍ በሚወጣው ሰይፍ እንደሚገድልና በመጨረሻም ከሰይጣን ጋር የሚያደርገውን ተጋድሎውን ሁሉ እንደሚያጠናቅቅ እናያለን፡፡
 
የዚህ ምዕራፍ አንኳር አሳብ በሦስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ሊከፈል ይችላል፡- 1) የተነጠቁት ቅዱሳን እግዚአብሄር ታላላቆቹን መቅሰፍቶች በዚህ ዓለም ላይ በማምጣቱ ያመሰግኑታል፡፡ 2) የበጉ ሰርግ እራት የመምጣቱ እወጃ፡፡ 3) ጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጭፍሮች ጋር ከሰማይ መውረዱ፡፡
 
እግዚአብሄር በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ የነገረንን እያንዳንዱን ነገር በእርግጠኝነትና በቅርቡ ይፈጽማል፡፡
 
 
የእግዚአብሄር ፍርድ! 
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምነው በእምነት የእግዚአብሄር ሕዝብ የሆኑ ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ ስላዳናቸው እርሱን ያመሰግኑታል፡፡ ቁጥር 3-5ን እንመልከት፡- ‹‹ደግመውም፡- ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል፡፡ ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሄር፡- አሜን፤ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት፡፡ ድምጽም፡- ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆችም ሆይ አምላካችንን አመስግኑ ሲል ከዙፋኑ ወጣ፡፡››
 
ዕብራውያን 9፡27 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከዚያም ፍርድ እንደተመደበባቸው፡፡›› ሰው በእግዚአብሄር ፊት አንድ ጊዜ ሊፈረድበት ይገባል፡፡ ነገር ግን የዚህ ፍርድ ውሳኔ የመጨረሻና የማይቀለበስ ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር እያንዳንዱን ሰው ስለ ሐጢያቶቹ አንድ ጊዜ ፍርዱን በመስጠት ሐጢያተኞችን ለዘላለም በሚቃጠል እሳት ውስጥ በመወርወር ዘላለማዊ ፍርዱን ይፈርዳል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ጢስዋም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል›› ብሎ የሚነግረን ለዚህ ነው፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች ‹‹አንድ ጊዜ ከሞትህ ያ የመጨረሻ ነው›› ብለው ሊያስቡና ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የሰው አስተሳሰብ እንጂ የእግዚአብሄር አይደለም፡፡ ሰው ሁሉ አካልና ነፍስ ስላለው ሰዎች በእግዚአብሄር ቢያምኑም ወይም ባያምኑም ሁሉም በደመ ነፍስ እግዚአብሄር እንዳለና ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ለሐጢያቶቻቸው በእርሱ ፊት እንደሚፈረድባቸው ያውቃሉ፡፡
 
ለሰዎች የመናፍስቶች ዓለም ስላለ እግዚአብሄርን በዓይኖቻቸው ባያዩትም እንዳለ ግን ያውቃሉ፡፡ በሥጋ ዓይኖች ሊታይ የሚችለው ዓለም ለዘላለም አይቆይም፡፡ ነገር ግን የእኛ ዓይኖች የማያዩት ዘላለማዊ የእውነት ዓለም አለ፡፡ ሰው የሚኖርበት ምክንያት ገንዘብን ብቻ በማሰብና ቁሳዊ ስስትን ብቻ በመከተል በዚህ ምድር ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ እውነተኛው ዓላማው የመላው ዩኒቨርስ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ በማወቅና እርሱ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማወቅና በማመን ዘላለማዊ ወደሆነው የበረከት ዓለም መግባት ነው፡፡
 
እኛ እግዚአብሄር የነገረንን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በእርሱም ደግሞ ማመን አለብን፡፡ የራሳችንን አስተሳሰቦች በማመንና በመታመን መጨረሻችን ሲዖል መሆን የለበትም፡፡ ለሐጢያቶቻችን ለዘላለም ከመሰቃየታችን በፊት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ይቅርታን አግኝተን አሁን በዚህ ምድር ሳለን ኢየሱስ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን የዘላለም ሕይወትን ማግኘት አለብን፡፡
የዚህ ምድር ሕይወት ለሰው ሁሉ በጣም አጭር ናት፡፡ ፀሐይ በየቀኑ እንደምትወጣና እንደምትጠልቅ ሁሉ የሕይወታችን አጭሩ ጉዞም ፍሬ አልባና ትርጉም የለሽ ሆኖ በጣም በፍጥነት ያበቃል፡፡ ለመቶ ዓመት ብትኖሩም እንኳ ያን ያህል ረጅም ዕድሜ ኖሬያለሁ ብላችሁ መናገር አትችሉም፡፡
 
የቀን ተቀን ሕይወታችሁን እዚህ ግቡ የማይባሉ ዑደቶች ማለትም እንደ መተኛት፣ መብላት፣ ወደ መታጠቢያ ቤቶች መሄድና ሌሎች እንዲህ ያሉ ተደጋጋሚ ነገሮች ከመላው የሕይወት ርዝማኔያችሁ ብትቀንሱ በትክክል የሚቀራችሁ በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፡፡ ከተወለዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ አስቀድሞ ያያችሁዋቸውን ነገሮች ስታዩና ከዚህ ቀደም የምታውቁዋቸውን ሰዎች ስትገናኙ ጠጉራችሁ ሙሉ በሙሉ ይነጣል፡፡ ድንገትም መጨረሻችሁን እየተጋፈጣችሁት መሆናችሁን ትረዳላችሁ፡፡
 
የእኛ ቅዱሳን ሕይወት ትርጉም የለሽ የማይሆንበት ብቸኛው ምክንያት እኛ ወደዚህ ዓለም ከተወለድን በኋላ በውሃውና በመንፈሱ ከመጣው ጌታ ጋር ተገናኝተን በእርሱ በማመን የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስርየት መቀበላችን ነው፡፡ እኛ እንዴት ዕድለኞችና አመስጋኞች ነን! በውሃውና በመንፈሱ በኩል በመጣው ጌታ ባይሆን ኖሮ ሁላችንም ወደ ዘላለማዊው እሳት ተጥለን በተሰቃየን ነበር፡፡
 
ይህንን ባሰብሁ ቁጥር አሁንም ያስፈራኛል፡፡ ደግሜም ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡ በሰይጣን የተነሳ የተፈጠረው ሲዖል ስቃዩ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ ሰው መሞት የሚናፍቅበት ነገር ግን መሞት የማይችልበት እጅግ አስደንጋጭ ስፍራ ነው፡፡ እሳትና ዲን ለዘላለም የሚነዱበት ስፍራ ነው፡፡
 
ኢየሱስ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በትክክል ለማወቅና መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በመጀመሪያ አስቀድመው ከዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል ጋር ተገናኝተው ዳግመኛ የተወለዱ የእግዚአብሄር አገልጋዮችን ማግኘት ይገባል፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ለመኖር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ የመወለድንና መንፈስ ቅዱስን የመቀበልን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ለሁሉም ነገር መፍትሄ ማግኘት ይችላል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየትን ላገኙ ሁሉ የእግዚአብሄር መንፈስ ስጦታ እንደሚሰጣቸው ይነግረናል፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 2፡38) ትክክለኛ ኢየሱስ እምነት አላቸው የሚባሉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባላቸው እምነት የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ አግኝተው በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ ዘላለማዊ ወደሆነው የእግዚአብሄር መንግሥት መግባት የሚችሉትም ይህ እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ (ዮሐንስ 3፡5) ሰው መባረኩ ወይም መረገሙ የሚወሰነው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየት በመቀበል ወይም አለመቀበሉ ነው፡፡
 
 
ጥሩ፣ ንጹህና የሚያብረቀረቅ በፍታን መልበስ፡፡ 
 
ስለ ወደፊት ሕይወታቸው የሚያስቡና አሁን ያለባቸውን የሐጢያቶች ስርየት ችግራቸውን ለመፍታት የሚፈልጉ ብልህና የተባረኩ ናቸው፡፡ ሰው በጉድለቶቹ የተሞላ አይረቤ ሕይወት ቢኖርም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምኖ በልቡ የሐጢያት ስርየትንና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ ይህ ሰው እጅግ የተሳካለት ሕይወትን ኖሮዋል፡፡
 
ዮሐንስ ራዕይ 19፡4-5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሄር፡- አሜን፤ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት፡፡ ድምጽም፡- ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆችም ሆይ አምላካችንን አመስግኑ ሲል ከዙፋኑ ወጣ፡፡››
 
እዚህ ላይ ‹‹የምትፈሩት›› የሚለው ሐረግ የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በልብ ውስጥ ተቀብሎ በእርሱ ምሪት መሰረት መኖር ማለት ነው፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ እግዚአብሄርን ማየትና ማመስገን የሚችሉት የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያገኙ ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያላገኙ ሰዎች በሚነደው የሲዖል እሳት ውስጥ እየተሰቃዩ እግዚአብሄርን ይረግማሉ፡፡
 
ቁጥር 6-9ን እንቀጥል፡- ‹‹እንደ ብዙ ሕዝብም ድምጽ፣ እንደ ብዙ ውሃዎችም ድምጽ፣ እንደ ብርቱም ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና፤ የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል፡፡ ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና፡፡››
 
እዚህ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምጽ፣ እንደ ብዙ ውሆች ያለ ድምጽና የብርቱ ነጎድጓድ ድምጽ እንደሰማ ይናገራል፡፡ ይህ ድምጽ የሐጢያት ስርየት ያገኙ ሰዎች ተባብረው እግዚአብሄርን የሚያመሰግኑበት ድምጽ እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡ ይህ የምስጋና ድምጽ በመጀመሪያ የተዋቀረው ሁሉን በሚችለው አምላክ አገዛዝ ሥር እንዲሆኑ፣ በእርሱ እንዲገዙና ከእርሱ ጋር በክብር እንዲኖሩ የፈቀደላቸውን አምላክ በማመስገን ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቅዱሳኖችን ከመጠን በላይ ሐሴት እንዲያደርጉ፣ እንዲደሰቱና ለእግዚአብሄርም ታላቅ ክብር እንዲሰጡ አድርገዋቸዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹ደስ ይበለን ሐሴትም እናድርግ፤ ለእርሱም ክብርን እንስጥ›› ብለው በመጮህ እርሱን ያመሰግኑታል፡፡
 
ሁለተኛ ቅዱሳን ማመሰገናቸውን ይቀጥላሉ፡- ‹‹የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል፡፡ ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና፡፡›› ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ኢየሱስ ለሰው ዘር በሰጠው ተስፋ መሰረት ወደዚህ ምድር በመምጣት በእርሱ በማመንና ዳግመኛ በመወለድ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉትን አግብቶ ከእነርሱ ጋር ለዘላለም ይኖራል፤ ያድርማል ማለት ነው፡፡
 
ሰርግ የሙሽራውና የሙሽሪቷ ጥምረት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ የሚቀበላቸውና አብሮዋቸው የሚኖረው ከውሃውና ከመንፈሱ ዳግመኛ ከተወለዱት ጋር ብቻ ነው፡፡ ይህም እርሱ ከቅዱሳኑ ጋር ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖር ዘንድ የሺህ ዓመት መንግሥቱንና አዲስ ሰማይና ምድርን ይመሰርታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሙሽራ ጋር አብረው የሚኖሩት ሙሽሮች ክብር እጅግ ታላቅ በመሆኑ ቋንቋ ሊገልጠው አይችልም፡፡ ይህንን ነገር በማሰብ ብቻ ልባችን በሐሴት ይጥለቀለቃል፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግስበት ዓለም ሲመጣ የእርሱ ሙሽሮች ቋንቋ ሊገልጠው ከሚችለው በላይ ከመጠን በላይ ይደሰታሉ፡፡ በመልካሙ እረኛ አገዛዝ ሥር በሚሆኑበት ጊዜ ምን ያህል ደስተኞች ይሆናሉ? ኢየሱስ ክርስቶስ ደግ የሆነ ሙሽራ በመሆኑ ፍጹም የሆነው የመልካምነቱና የተፍጻሜት አገዛዙም እንደዚሁ ይሆናል፡፡ እርሱ በመንግሥተ ሰማይ ላይ ይነግሣል፡፡
 
 

ለሰማይ የሚያበቃችሁ አንዱና ብቸኛው ወንጌል፡፡ 

 
ሰው መንፈስ ቅዱስን ለመቀበልና ሰማይ ለመግባት በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ብቻ ማመን አለበት፡፡ ጌታችን ወደዚህ ምድር የመጣው እንዲህ ያሉትን የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ ሐጢያተኞችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን በመሆኑ በዮሐንስ መጠመቅ ነበረበት፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ከተጠመቀ በኋላ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ ለሐጢያቶቻችን በሙሉም ተኮነነ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ ለሚያምኑትም የዘላለም ደህንነትን የሚሰጥ ጌታ ሆነ፡፡
 
አሁን ይህ ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ በእምነት የእርሱ ሙሽሮች የሆኑትን ሕዝቦቹን በማቀፍ ከእነርሱ ጋር ለዘላለም ይኖራል፡፡ የእርሱ ሙሽሮች የሆኑትም አሁን ከጌታ ጋር በአዲስ ሰማይና ምድር ይኖራሉ፡፡ ይህም ለሙሽሮቹ ክቡርና ክብርን የሚያቀዳጅ በረከት ይሆናል፡፡ በዚህም የዳኑት የእግዚአብሄር ልጆች እርሱን ለዘላለም በማመስገን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርን ይሰጣሉ፡፡ እግዚአብሄር የሚነግስባቸው እነዚህ ሕዝቦች በደስታቸው ይደሰታሉ፡፡ በዚህ ደስታ የተነሳም ክብርን ሁሉ ለሙሽራው ይሰጣሉ፡፡
 
የሰው ዘር በሙሉ ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮ ይህንን ክስተት ሲጠብቅ ቆይቷል፡፡ ኢየሱስ ሲመጣ፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉትን ሲነጥቃቸውና ከእነርሱ ጋር ሲኖር ይህ ክስተት ይፈጸማል፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ዘር አዲስ ዓለም አዘጋጅቶ እኛን እየጠበቀን ነው፡፡ የምንኖረው ለዚህ ነው፡፡ ወደዚህ ዓለም የተወለድነውም ለዚሁ ነው፡፡
 
ዋናው ምንባብ፡- ‹‹ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል›› በማለት እንደነገረን እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑትን ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ አልብሶዋቸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር በዚህ ቃል የሚያምኑ ሰዎች የሐጢያት ስርየትን ተቀብለው ልባቸው እንደ በረዶ ነጭ ሆኖ ነጽቷል፡፡
 
የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽሮች ቀደም ብለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ተዘጋጅተዋል፡፡ ሰው በዚህ ምድር ላይ ሳለ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመስማትና በማመን የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ሆኖ ዳግመኛ ሊወለድ ይችላል፡፡ የክርስቶስ ሙሽራ የሚያደረጋችሁ እምነት ይህ ነው፡፡ ሰማይ እንድትገቡ የሚያበቃችሁም እውነት ይኸው ነው፡፡
 
 
እነዚያ በተስፋ የሚጠባበቁ፡፡ 
 
ዋናው ምንባብ ‹‹ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው›› ብሎ ይነግረናል፡፡ የሐጢያቶቻቸወን ስርየት ያገኙ ሰዎች ሊኖሩ የሚገባቸው በምን ዓይነት እምነት ነው? ሙሽራውን ኢየሱስ ክርስቶስን የተገናኙና በክብር እየኖሩ ያሉ ሙሽሮች ከዚህ ሙሽራ ጋር የሚጣመሩበትን ቀን አርቀው እየተመለከቱ ሕይወታቸውን በእምነትና በተስፋ መኖር አለባቸው፡፡
 
ዓለም እየጨለመ ሲሄድ ለዳኑት ሙሽሮች ግን አሁም ተስፋ አለ፡፡ ይህ ተስፋ ሌላ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሙሽሮቹ አዲስ ሰማይና ምድር ካዘጋጀ በኋላ እነርሱን ለመውሰድ የሚመጣበትን ቀን መጠበቅ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሙሽራው ሙሽሮቹን ሁሉ ከሞት አስነስቶ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፡፡ ሙሽራውና ሙሽሮቹ ለዘላለም ሊኖሩበት ያለው ዓለም ከክፋት የጸዳ፣ ሐጢያት የሌለበትና አንዳች የማይጎድለው ስፍራ ነው፡፡ ሙሽሮቹ የሚጠብቁት ይህንን ቀን ብቻ ነው፡፡ የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስርየት የተቀበልን ሰዎች እንዲህ ባለ እምነትና ተስፋ መኖር ያለብን ለዚህ ነው፡፡
 
አሁን በዚህ ዘመን እየኖሩ ያሉ ሙሽሮች በተለይ ብዙ የሥጋ ድካሞች አሉባቸው፡፡ ነገር ግን 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13 ‹‹እንዲህም ከሆነ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው›› ብሎ እንደሚነግረን ሙሽራው ሙሽሮቹን እንዲህ ስለወደዳቸው በጥምቀቱ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ አንጽቶ ፍጹም የሆኑ ሙሽሮቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል፡፡
 
ይህ ዓለም ወደ መጨረሻ ፍጻሜው እየሮጠ ስለሆነ በውስጡ የቀረው ተስፋ የለም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ወደ ጥፋት እየቀረበ ቢሆንም ሙሽሮቹ በያዙት የተለየ ተስፋቸው ሕይወታቸውን መኖር አለባቸው፡፡ ይህ ተስፋ የሚፈጸምበት ጊዜ አሁን እየቀረበልን ነው፡፡ አሁን መላው ዓለም በመሬት መናወጦች በመፈረካከስ አደጋ ላይ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚኖር እያንዳንዱ ሰው የጥንት ዘመን ዳይኖሰሮች እንደጠፉ ሁሉ የሚጠፋበት ቀን ቀርቦዋል፡፡ ይህ ዓለም በድንገት ይወድቃል፡፡
 
ሆኖም እያንዳንድዋ ሙሽሪት ተስፋ አላት፡፡ ጊዜው ሲደርስ የሙሽሮቹ አካላት ፍጹም ወደሆኑ አካሎች ይለወጣሉና፡፡ እነርሱም ሙሽራቸው ከሆነው ጌታ ጋር ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራሉ፡ ስለዚህ ሙሽሮቹ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በዚህ ዘመን ለሚኖሩ ዓለማዊ ሰዎች በታማኝነት መስበክ አለባቸው፡፡
 
 

በእውነተኛው የእግዚአብሄር ቃል እንመን! 

 
ኢየሱስ በዮሐንስ 3፡5 ላይ እንዲህ ነግሮናል፡- ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሄርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፡፡›› የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ታዲያ ምንድነው? መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ‹‹ውሃ›› በግልጽ የሚያመለክተው የኢየሱስን ጥምቀት እንደሆነና የደህንነትም ምሳሌ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)
 
ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሞላው የእስራኤልን ሕዝብ በዮርዳኖስ ወንዝ ያጠምቅ ወደነበረው ወደ ዮሐንስ ሄደ፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ የሰው ዘር ወኪልና የብሉይ ኪዳንም የመጨረሻው ሊቀ ካህን እንደነበር ኢየሱስ ይነግረናል፡፡ ኢየሱስ ከዮሐንስ ጋር ተገናኝቶ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ የፈጸመውን ጥምቀቱን ከእርሱ ተቀበለ፡፡ (ማቴዎስ 3፡15፤ 11፡11-14) ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ የተቀበለው ጥምቀት የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ራሱ ወደ ክርስቶስ የተላለፉበት የዘላለም ቁርባን ነበር፡፡
 
ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ሥጋ መልበሱ፣ ጥምቀቱ፣ ደሙና የመስቀል ላይ ሞቱ፣ ትንሳኤውና ዕርገቱ -- እነዚህ ሁሉ ነገሮች የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ሰው ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በውሃና በመንፈስ አማካይነት ሐጢያቶቹን ሁሉ በአንድ ጊዜ እንዳስወገደ ሲያምን ያን ጊዜ ከሐጢያት ነጻ ወጥቶ ጻድቅና የክርስቶስ ሙሽራ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በሰው አስተሳሰቦች የሚከናወን ነገር ሳይሆን ከራሱ ከእግዚአብሄር አስተሳሰቦች የመነጨ ነው፡፡
 
እውነቱ የሰውን ዘር ከሐጢያት ለማዳን የሚያስፈልጉት ሦስቱ መሳሪያዎች ውሃ፣ ደምና መንፈስ ቅዱስ መሆናቸው ነው፡፡ ከእነዚህ አንዳቸውም ከቶ መጉደል የለባቸውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን በ1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 5 ላይ በግልጽና በትክክል አብራርቶታል፡፡ ይህም እነዚህ የውሃው፣ የደሙና የመንፈስ ቅዱስ ሦስቱ ፍሬ ነገሮች ሁሉም አንድ እንደሆኑና ከእነዚህ አንዱ ቢጎድል ከሐጢያት መዳናችን ምሉዕና ተቀባይነት ያለው ሊሆን እንደማይችል ይነግረናል፡፡
 
ፍጹም የሆነው ደህንነት በእነዚህ በሦስቱ--ውሃ፣ ደምና መንፈስ ቅዱስ-- ማመን የመሆኑን ይህንን እውነት ስናውቅና ስናምን ያዳነንን የኢየሱስ ፍቅር መረዳትና ማመን እንችላለን፡፡ በዚህም ልባችን በእርግጥም ሙሉ በሙሉ ሐጢያት አልባ ሊሆን ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ 2፡38 ላይ ተስፋ ሰጥቶናል፡- ‹‹ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡››
 
መንፈስ ቅዱስን እንድንቀበል የሚያስችለን ይህ ቃል ታዲያ ምንድነው? ይህ ቃል ሌላ ሳይሆን የኢየሱስ ጥምቀት (ውሃው)፣ የመስቀል ላይ ሞቱ (ደሙ) እና አምላክ የመሆኑ የትንሳኤውና የዕርገቱ (መንፈስ ቅዱስ) ቃል ነው፡፡ ይህ የደህንነት ቃል በብሉይ ኪዳን የሙሴ መጽሐፎችና በሌሎች ነቢያቶች ውስጥ በተጨባጭ የተተነበየለትና በአዲስ ኪዳን በአራቱም ወንጌሎች ሁሉ ውስጥ የተፈጸመና የተመሰከረለት ቃል ነው፡፡ በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ የተብራራው ‹‹አንድ ጊዜ የተፈጸመው የዘላለም ደህንነት ስርየት›› እኛ በእምነታችን ስለተቀበልነው የእግዚአብሄር ጽድቅ በተደጋጋሚ መስክሮዋል፡፡
 
በዚህ ሐጢያተኛ ዓለም ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሄር ፊት እንከን ያለበት የሥጋ ሕይወት እየኖረ ቢሆንም እግዚአብሄር ያቀረበውን የሐጢያት ስርየት መቀበልና ተስፋውን በሰማይ ላይ በማኖር ሕይወቱን መኖር ይገባዋል፡፡ ይህ እግዚአብሄር ለሰው ዘር የሰጠው ስጦታው ነው፡፡ ሁላችንም በነጻ የተሰጠንን ይህንን ጸጋ መቀበል አለብን፡፡ ጌታችን እንደሚመጣና አዲሱን መንግሥት እንደሚመሰርት በማመን በእውነተኛው ተስፋችን እንኑር፡፡ በዚህ ተስፋ መኖር አለብን፡፡ እኔ እጅግ ከልቤ የማምነው ይህንን ነው፡፡
 
ሐጢያት በዚህ ዓለም ላይ ምን ያህል እንደተሰራጨ ታውቃላችሁን? የዚህ ዘመን ሐጢያተኞች ከኖህ የጥፋት ውሃ ጋር ሲነጻጸሩ ከመጠን በላይ ተስፋፍተዋል፡፤ እግዚአብሄር በኖህ ዘመን የሰው አሳብ ሁልጊዜም ክፉ እንደሆነ ተመልክቶ የመጀመሪያውን ዓለም በውሃ ጥፋት ለማጥፋት ወሰነ፡፡ ኖህ መርከብ እንዲሰራ ነገረው፡፡ ቃሉን በማመን ወደዚህች መርከብ የገቡትንም አዳናቸው፡፡
 
እግዚአብሄር ዓለምን በውሃ እንደሚፈርድበት በእርግጠኝነት ቢናገርም ቃሉን ያመኑት ስምንቱ የኖህ ቤተሰብ ብቻ ነበሩ፡፡ ስለዚህ በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ መርከብ ሰርተው ከውሃ ጥፋት ለማምለጥ ወደ ውስጡ ገቡ፡፡ ይህንን ካደረጉ በኋላ እግዚአብሄር በመጀመሪያው ዓለም ላይ ፍርዱን ማምጣት ጀመረ፡፡ ድንገት ሰማዩ ጨለመ፡፡ ማዕበል የቀላቀለ ዝናብም መዝነብ ጀመረ፡፡ ምናልባትም በአንድ ሰዓት ውስጥ ውሃው እስከ ሦስተኛው ሰገነት ከፍታ ደርሶ ይሆናል፡፡ ለ40 ቀናት ዘነበ፡፡ መላው ዓለምም በውሃ ሰጠመ፡፡
 
ኖህና ቤተሰቡ አዲስ ዓለም ሊመጣ መሆኑን በማመን ወደ መርከቢቱ እንደገቡ ሁሉ እናንተና እኔም በዚህ በተስፋ መኖር አለብን፡፡ እነርሱ በእግዚአብሄር ስላመኑ ለመቶ ዓመት ያህል መርከብ መስራት እንደቻሉ ሁሉ እኛም እንደዚሁ መጽናትና ወንጌልን መስበክ እንደሚገባን አምናለሁ፡፡ እግዚአብሄር ኖህን አለው፡- ‹‹መርከብን ለአንተ ሥራ፡፡›› (ዘፍጥረት 6፡14) ይህ ቃል ‹እኛም እምነታችንን ለመከላከል› በመጀመሪያ ራሳችንን ለእግዚአብሄር መስጠትና ወንጌልን መስበክ እንዳለብን ይነግረናል፡፡
 
ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ተስፋ ቢኖራቸውም በወንጌል የማያምኑ ግን ተስፋ የላቸውም፡፡ እነዚህ በወንጌል የማያምኑ ሰዎች የሚገጥማቸው ተስፋ መቁረጥ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቢያምኑም ባያምኑም ለእነርሱ መስበካችንን መቀጠል አለብን፡፡ ይህ ዘመን ሰዎች በተቻለ ፍጥነት በዚህ እውነተኛ ወንጌል ሊያምኑ የሚገባበት ዘመን ነው፡፡ እኛ በምንሰብከው ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በሐሴት ይሞላሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ የማያምኑ ሰዎች የተረገሙ ይሆናሉ፡፡ እነዚህኞቹ ማለትም በወንጌል የማያምኑት ሰዎች የእግዚአብሄርን ዘላለማዊ ቅጣት የሚቀበሉና ወደ ሲዖል የሚወረወሩ ሞኞች ናቸው፡፡
 
ተስፋችሁን አትጣሉ፡፡ ጻድቃን ተስፋቸውን ሲጥሉ የሚጠብቃቸው ሞት ብቻ ነው፡፡ ተስፋ ከሌለን የመኖር ፍላጎትም ሆነ ስሜት እንደዚሁም አንዳች ተጨማሪ ምክንያት አይኖረንም፡፡ ስለዚህ በተስፋ እንኑር፡፡
 
በዚህ ዘመን በኢየሱስ የሚያምኑና በዚህም ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች በእርግጥም ደስተኞች ናቸው፡፡ የሰው ዘር የቀረለት ተስፋ ቢኖር የሐጢያትን ስርየት መቀበል ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል በቀር ሌላ ተስፋ የለም፡፡ ሰዎች ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ሲያገኙ ተስፋ ስለሚኖራቸው ለዘላለም በደስታ ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ይቅርታ ካላገኙ የሚጠብቃቸው ጥፋት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስን አልተቀበሉምና፡፡
 
በዚህ በዛሬው ዓለም ውስጥ በተስፋ የምኖረው የሐጢያቶቼን ሁሉ ስርየት ስላገኘሁ ነው፡፡ እናንተም እንደዚሁ ሕይወታችሁን በዚህ ተስፋ ትኖሩ ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልያለሁም፡፡ ራሳችሁን ከንቱ ከሆኑት የዓለም አስተሳሰቦች ጋር እንዳታቆራኙ ነገር ግን በፋንታው አብረዋችሁ ያሉትን ወንድሞችና እህቶቻችሁን በመውደድ፣ በክርስቶስ ጸንተው እንዲቆሙ በማገዝ፣ እምነታችሁን ባለማጣት፣ ሙሸራውን በመጠበቅና በመጨረሻም ሊወስዳችሁ ሲመጣ እርሱን በመገናኘት ብልህ ሙሽሪቶች ሆናችሁ ሕይወታችሁን እንድትኖሩ እጸልያለሁ፡፡
 
በእርሱ ክብር ውስጥ እንድንኖር ስለሚያስችለን እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፡፡