Search

Sermons

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[3-3] ለፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 3፡7-13 ››

ለፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 3፡7-13 ››
‹‹በፊላደልፊያም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡፡ የዳዊት መክፈቻ ያለው የሚከፍት የሚዘጋም የሌላ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እንዲህ ይላል፡- ሥራህን አውቃለሁ፡፡ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፡፡ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፡፡ ሐይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፡፡ ስሜንም አልካድህምና፡፡ እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማህበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፡፡ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ፡፡ የትዕግስቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ፡፡ እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፡፡ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ፡፡ ድል የነሳው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፡፡ ወደፊትም ከዚያ ከቶ ከቶ አይወጣም፡፡ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 7፡- ‹‹በፊላደልፊያም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡፡ የዳዊት መክፈቻ ያለው የሚከፍት የሚዘጋም የሌላ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እንዲህ ይላል፡-››
ጌታ በመንግሥተ ሰማይ የሁሉ ንጉሥ ሆኖ ነግሶዋል፡፡ እርሱ ፍጹም ሥልጣንና ሐይል ያለው አምላክ ነው፡፡ እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም፡፡ ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሐጢያተኞችን ያዳነ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ የሰማይ ደጅ ሊከፈት የሚችለው ጌታ በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ቁልፍ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ምንም ነገር ሊከፍተው አይችልም፡፡ የዚህ መንግሥት ክፍል የሆነው እያንዳንዱ ነገር የተመረኮዘው በጌታ አምላካችን ላይ ነው፡፡
 
ቁጥር 8፡- ‹‹ሥራህን አውቃለሁ፡፡ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፡፡ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፡፡ ሐይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፡፡ ስሜንም አልካድህምና፡፡››
ጌታ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን አማካይነት የወንጌል ስርጭትን በር ከፍቷል፡፡ ስለዚህ ለጌታ ፈቃድ ማንም በሩን መዝጋት አይችልም፡፡ በመሆኑም ቅዱሳን ጌታ እስከሚመጣበት እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ የቀደመውን እምነታቸውን አጠብቀው መያዝ አለባቸው፡፡ የእግዚአብሄር አገልጋዮችና ቅዱሳን ሊኖራቸው የሚገባው የእምነት ዓይነት ይህ ነው፡፡ እምነታቸው ጅማሬው ታላቅ ቢሆንም ውሎ አድሮ በመጨረሻ ግን ሙት የሆነ እምነት መሆን የለበትም፡፡ ጌታ የሰጣቸውን የቀደመውን የማይለዋወጥ እምነት መያዝ አለባቸው፡፡
የቅዱሳን እምነት በውሃውና በበመንፈሱ ወንጌል የሚያምን እምነት የጌታችን መንግሥት ወደዚህ ምድርና ወደ አዲሱ ሰማይና ምድር የምትመጣ የመሆንዋን፤ እኛም ሁላችን በዚህች መንግሥት ውስጥ ለዘላለም የምንኖር የመሆናችንን እውነት የሚያምን እምነት መሆን አለበት፡፡ ቅዱሳን የሚመጣውን ጌታ እስከሚገናኙበት ቀን ድረስ ይህንን እምነት አጥብቀው መያዝ አለባቸው፡፡
የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን አገልጋይና ቅዱሳኖች የነበራቸው ሐይል ጥቂት ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሁሉ የሚበልጠው የእግዚአብሄርን ቃል መጠበቃቸውና ጌታን አለመካዳቸው ነበር፡፡
 
ቁጥር 9፡- ‹‹እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማህበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፡፡ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ፡፡››
እግዚአብሄር በእርግጥ የራሱ የሆነችውን የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን ምን ያህል እንደወደዳት ያውቁ ዘንድ ከሐሰተኛ ምዕመናን አንዳንዶቹን እንደሚያንበረክካቸው ተናግሮዋል፡፡
‹‹አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ከሰይጣን ማህበር›› የሚለው የሚያመለክተው በእምነታቸው ራሳቸውን የሚቆጥሩ አይሁዶችን ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ እንደዚያ አልነበሩም፡፡ በተቃራኒው የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያንና የእርሱን ቅዱሳን ያደናቅፉ ነበር፡፡
ዛሬም እንደ ቀድሞው የኢየሱሰን ስም የሚጠሩና እርሱን የሚያመልኩ ብዙዎች የዲያብሎስ መሳርያ ሆነው በማገልገል ወደ ሰይጣን አገልጋይነት ተለውጠዋል፡፡ እግዚአብሄር ለወደደውና የክብር ዕቃ አድርጎ ለተጠቀመበት የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ለየት ያለውን ፍቅሩን አሳየ፡፡
 
ቁጥር 10፡- ‹‹የትዕግስቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ፡፡››
በተለይ ጌታ እንዲጸና ያዘዘውን ትዕዛዝ በመጠበቁ የፊላደልፊያን ቤተክርስቲያን አገልጋይ አመስግኖታል፡፡ እንዲህ ዓይነት የተለየ ትዕግስት ከሌለን የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃሎች ሁሉ ፍጻሜ መጠበቅ አንችልም፡፡ እንድንጸና የሰጠውን ትዕዛዙን ለመጠበቅ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ፍጹም የሆነ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን በመጽናቷ ጌታ ልዩ ሽልማት ሰጣት፡፡ ይህ ልዩ ሽልማት የፊላደልፊያን ቤተክርስቲያን ከፈተናው ሰዓት በመጠበቅ መልክ ሆኖ መጣ፡፡ እዚህ ላይ የፈተናው ሰዓት የሚያመለክተው የጸረ ክርስቶስ እንቅፋት ነው፡፡
 
ቁጥር 11፡- ‹‹እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፡፡ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ፡፡››
የጌታ ምጽዓት ቅርብ ስለሆነ ቅዱሳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ጌታ ተስፋ በሰጠው የአዲስ ሰማይና ምድር ተስፋም ማመንና ይህንንም መጠበቅ አለባቸው፡፡ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ሽልማታቸው እንዳይወሰድባቸው ከቅዱሳን ጋር ሆነው እምነታቸውን ከሽንፈት መጠበቅ አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 12፡- ‹‹ድል የነሳው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፡፡ ወደፊትም ከዚያ ከቶ ከቶ አይወጣም፡፡ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፡፡››
ሰይጣንን ድል የነሱ ሰዎች የሰማዕታትን ዓምድ ይቀላቀላሉ፡፡ ስሞቻቸውም በቅዱስ መቅደስና በእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ ይጻፋሉ፡፡ አሁንም እንኳን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ታላላቅ ሰራተኞች ሆነው እያገለግሉ ነው፡፡ ጌታ እንዲህ ዓይነት መሳሪያዎች አድርጎ እየጠጠቀመባቸው ይቀጥላል፡፡
 
ቁጥር 13፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡››
የእግዚአብሄርን ቃል የሚሰሙበት ጆሮ ያላቸው ሰዎች የእግዚአብሄር አገልጋዮችና የእርሱ ቅዱሳን ናቸው፡፡ መንፈስ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኩል የሚላቸውን ይሰማሉ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር አገልጋዮችና የእርሱ ቅዱሳን እግዚአብሄር በፈቀደላቸው ቤክርስቲያን ውስጥ መቆየትና ይህችንም ቤተክርስቲያን መጠበቅና መንከባከብ አለባቸው፡፡