‹‹ ዘጸዓት 27፡1-8 ››
‹‹ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ፡፡ ርዝመቱ አምስት ክንድ ስፋቱም አምስት ክንድ ሆኖ ባለ አራት ማዕዘን ይሁን፡፡ ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማዕዘኖች ላይ ቀንድ አድርግለት፡፡ መሠዊያውንም በነሐስ ለብጠው፡፡ ዕቃዎቹን ሁሉ ይኸውም የአመድ ማስወገጃ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ጎድጓዳ ሳህኖችን፣ ሜንጦዎችንና የፍም መያዣዎችን ከነሐስ አብጃቸው፡፡ አመድ ማውረጃ የሚሆን እንደ መረብ የሆነ የነሐስ ፍርግርግ አድርግለት፡፡ በአራቱም የመረብ ማዕዘኖች ላይ የነሐስ ቀለበቶች አብጅ፡፡ እስከ መሠዊያው ወገብ እንዲደርስ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው እርከን ሥር አድርገው፡፡ የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው፡፡ በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱ ጎኖች እንዲሆኑ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ፡፡ መሠዊያውን ውስጡን ባዶ ከሆኑ ሳንቃዎች አብጀው፡፡ ልክ በተራራው ላይ ባየኸው መሰረት ይበጅ፡፡››
በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የተገለጠውን እምነት ማብራራት እወዳለሁ፡፡ እስራኤሎች በቀን ተቀን ሕይወታቸው መጠበቅ ከነበረባቸው ከ613ቱ የእግዚአብሄር ሕግ አንቀጾችና ትዕዛዛቶች አንዳቸውንም በሚጥሱበትና ሐጢያቶቻቸውን በሚገነዘቡብት ጊዜ አርሱ ባስቀመጠው የመስዋዕት ስርዓት መሰረት እንከን የሌለባቸውን መስዋዕቶቻቸውን ለእግዚአብሄር ያቀርባሉ፡፡ እነዚህን መስዋዕቶች የሚያቀርቡበት ስፍራም የሚቃጠለው መስዋዕት የሚቀርብበት መሰውያ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእስራኤል ሕዝብ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የሚቀበሉት እጆቻቸውን እንከን የለሽ በሆነው መስዋዕት እንስሳ ራስ ላይ ጭነው ጉሮሮውን በመቁረጥና ደሙን በማፍሰስ ነበር፡፡ ይህንን ደምም በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ ይቀባውና የቀረውን ደም መሬት ላይ ያፈስሰዋል፡፡ የዚህን መስዋዕት ሥጋም በመሰውያው ላይ ያቃጥለዋል፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ መንፈሳዊ ትርጉም ምንድነው?
የሚቃጠል መስዋዕት የሚቀርብበት መሰውያ ስፋቱና ወርዱ 7.5 ጫማ ሲሆን ቁመቱ ደግሞ 4.5 ጫማ ሆኖ ከግራር እንጨት የተሰራና በናስ የተለበጠ ነበር፡፡ እስራኤሎች ይህንን የሚቃጠል መስዋዕት መሰውያ በሚመለከቱበት ጊዜ ሁሉ በፍርድ የተከረቸሙትና ኩነኔያቸውን ማስወገድ የማይችሉት እነርሱ እንደሆኑ ይገነዘባሉ፡፡ ነገር ግን መሲሁ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመኮነንና ልክ ለመስዋዕት እንደቀረበው ጠቦት በሐጢያቶቻቸው ምክንያት በመሞት ሐጢያቶቻቸውን እንደሚደመስስላቸውም አምነዋል፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የአዳኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ ነበር፡፡ ነውር የሌለባቸው እንስሶች በእጆች መጫንና ደማቸውን በማፍሰስ እንደሚሰዉ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ወደ እኛ በመምጣት የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ ሁሉ ተሸከመ፡፡ በብሉይ ኪዳን ይቀርቡ የነበሩት የመስዋዕት ጠቦቶች በእጆች መጫን አማካይነት ሐጢያቶችን በሙሉ መቀበልና ደማቸውን ማፍሰስ እንደነበረባቸው ሁሉ ኢየሱስም በዮሐንስ በመጠመቅ ወደ እርሱ የተሻገሩትን ሐጢያቶች በሙሉ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ የእነዚህን ሐጢያቶች ኩነኔ ተሸከመ፡፡
በዚህ መንገድ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ኢየሱስ ክርሰቶስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰድ በመስቀል ላይ እንደሞተ፣ ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳና እንዳዳነን ያሳየናል፡፡
እስራኤሎች የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ለማግኘት የመስዋዕት ቁርባኖቻቸውን በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ ማቅረብ ነበረባቸው፡፡
የዘሌዋውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 4ን ስንመለከት የተቀቡት ካህናቶች መላው የእስራኤል ጉባኤ አለቃ ወይም ከተራው ሕዝብ ማንም ቢበድል የሐጢያት ስርየታቸውን የሚያገኙት ለእግዚአብሄር መስዋዕት በማቅረብ፣ እጆቻቸውን በራሱ ላይ በመጫን፣ በማረድ፣ ደሙን በማፍሰስ፣ ወደሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ በመውሰድና ለእግዚአብሄር በማቅረብ እንደነበር እናያለን፡፡
እስራኤሎች የሐጢያት ቁርባኖቻቸውን የሚያቀርቡት በዚህ የመስዋዕት መሰውያ ላይ ስለነበር መሰውያው ሁልጊዜም ሥራ ይበዛበት ነበር፡፡ ከሐጢያቶቻቸው መላቀቅ የሚፈልጉ እስራኤሎች ነቁጥ የሌለበት እንስሳ ያዘጋጁና መስዋዕታቸው አድርገው በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ ለእግዚአብሄር ያቀርቡታል፡፡ ሐጢያተኞች እጆቻቸውን በራሱ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ወደ መስዋዕቱ እንሰሳ ላይ ያሻግራሉ፡፡ ለእነዚህ ሐጢያቶች ፍርድ ይሆን ዘንድም ጉሮሮውን በመቁረጥ ደሙን ያፈስሱታል፡፡ ከዚያም ካህናት ይህንን የመስዋዕቱን ደም በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ በመቀባት ሥጋውንና ስቡን በመሰውያው ላይ ያቃጥሉታል፡፡ እስራኤሎች የሐጢያቶቸቸውን ስርየት የሚቀበሉት በዚህ መንገድ ነበር፡፡
የበደለው የእስራኤል ሕዝብ መሪ ሊቀ ካህን፣ ተራ ካህናት፣ ጠቅላላው ጉባኤ ወይም ተራው ሕዝብ ማንም ይሁን የሐጢያት ስርየታቸውን የሚያገኙት እንደ ኮርማ ፍየል ወይም አውራ በግ ያለ የመስዋዕት እንስሳ በማምጣትና የመስዋዕት ቁርባን አድርጎ ለእግዚአብሄር በማቅረብ ነበር፡፡
ሐጢያተኞች ወይም የእነርሱ ወኪሎች በመስዋዕቱ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጭነው ያርዱትና ከደሙ የተወሰነውን ወስደው በሚቃጠል መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ ይቀቡታል፡፡ የቀረውን ደም መሬት ላይ ያፈስሱታል፡፡ ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታ የሚያስገኝላቸውን መስዋዕት ስብም ያቃጥሉታል፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ የመስዋዕት እንስሶቻቸውን ወደሚቃጠል መስዋዕት መሰውያ ያመጡና በእንስሶቹ ራስ ላይ እጆቻቸውን በመጫን ደማቸውን ያፈስሱና ለካህናቶች ይሰጡዋቸዋል፡፡
በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ መስዋዕቶች ሲቀርቡ የሚቀርቡት እነዚህ የመስዋዕት እንስሶች ነውር የሌለባቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ ሐጢያተኞች ለእግዚአብሄር መስዋዕቶችን ሲያቀርቡ በእግዚአብሄር ፊት ነውር የሌለባቸውን እንስሶች ለማቅረባቸው እርግጠኞች መሆን ነበረባቸው፡፡ ሐጢያቶቻቸው ወደ እነርሱ የሚሻገረውም በእነዚህ ነውር በሌለባቸው የመስዋዕት እንስሶች ራስ ላይ እጆቻቸውን በመጫን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መስዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ የሚቀር አንዳች ነገር አይኖርም፡፡
ሐጢያት የሰራ ግለሰብ ባቀረበው የመስዋዕት እንሰሳ ራስ ላይ እጁን መጫን ያለበት መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ሐጢያት በሚሰራበት ጊዜ ወኪል የሆኑት ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በመስዋዕት እንስሶች ላይ ይጭናሉ፡፡ (ዘሌዋውያን 4፡15) እጆች የተጫኑበት የመስዋዕት እንስሳም ጉሮሮው ተቆርጦ ይታረድና ደሙ ይፈስሳል፡፡ በመጨረሻም በመሰውያው ላይ ይቃጠላል፡፡
ስለዚህ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ዙሪያ ያለው አካባቢ ሁልጊዜም የሚቃጠል ሥጋ፣ ስብና እንጨት ጢስ እንደታወደ ነው፡፡ የመሰውያው ቀንዶቹ ከበታቹ ያለው መሬትም ለመስዋዕት በሚቀርቡት እንሰሶች ደም እንደረሰረሰ ነው፡፡ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የእስራኤልን ሕዝብ ሐጢያቶች ለማንጻት ለእግዚአብሄር መስዋዕቶች የሚቀርቡበት የሐጢያት ማስተሰርያ ስፍራ ነበር፡፡
ጢስ ያለ ማቋረጥ የሚንቦለቦልበት ይህ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ርዝመቱና ወርዱ 7.5 ጫማ ቁመቱ ደግሞ 4.5 ጫማ የሆነ ካሬ ነበር፡፡ በመካከሉም እንደ መረብ ያለ ነገር የነበረበት የነሐስ ፍርግርግ ነበረው፡፡ በፍርግርጉ ላይ በሚነደው የእንጨት እሳት ላይ ከሚቃጠሉት መስዋዕቶችም ያለማቋረጥ የሚንቦለቦል ጢስ ይወጣ ነበር፡፡ ልክ እንደዚሁ መስዋዕቶቹ የሚቃጠሉበት ለእግዚአብሄር የሚቀርቡበት ስፍራም የሚቃጠል መስዋዕት መሰውያ ነበር፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ዕቃዎች በሙሉ የተሰሩት ከነሐስ ነበር፡፡
አመዶቹን ለማስወገድና ለማፍሰስ የሚያገለግሉት የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ዕቃዎች የተሰሩትም ከነሐስ ነበር፡፡ ራሱ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የተሰራው በነሐስ ከተለበጠ የግራር እንጨት ነበር፡፡ ስለዚህ መሰውያውና ዕቃዎቹ ሁሉ የተሰሩት ከነሐስ ነበር፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የተሰራበት ይህ ነሐስ ግልጽ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም አለው፡፡ ነሐስ በእግዚአብሄር ፊት የሐጢያትን ፍርድ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ሐጢያተኞች በሐጢያቶቻቸው በእርግጥ እንደሚፈርድባቸው በግልጽ ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄር ሰዎችን ስለ ሐጢያቶቻቸው ይኮንናቸዋል፡፡ ለመስዋዕት የቀረቡት እንስሶች በሐጢያተኞች ፋንታ በይፋ በመቃጠል የሚኮነኑበት ስፍራ ይህ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ነበር፡፡ መሰውያው ራሱና ዕቃዎቹ ሁሉ ከነሐስ የተሰሩ ነበሩ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እያንዳንዱ ሐጢያት ፍርዱን እንደሚቀበል በእርግጠኝነት ይነግሩናል፡፡
መሰውያው ሰዎች በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ለኩነኔ እንደታጩና እንደሚሞቱ ነገር ግን የመስዋዕት እንሰሳቸውን ወደሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ በማምጣትና ለእግዚአብሄር በማቅረብ ከሐጢያቶቻቸው መታጠብ፣ የሐጢያት ስርየትን መቀበልና ዳግመኛም በሕይወት መኖር እንደሚችሉ ያሳየናል፡፡ እዚህም በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የሚሰዉት እንስሶች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ያፈሰሰው ደሙ የምዕመናንን ሐጢያቶች በሙሉ ይቅር እንዳለ ይነግሩናል፡፡ ስለዚህ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ መስዋዕትን ያቀረበው ይህ እምነት በአዲስ ኪዳንም በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ደም የማመን እምነት ሆኖ ቀጥሎዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን ስናምን የሐጢያት ስርየትን በምናገኝበት የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ የሚያምነውን እምነታችንን ለእግዚአብሄር ማቅረብ አለብን፡፡ ይህ እምነት በብሉይ ኪዳን ለመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር የተፈተለውን ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ጥሩ በፍታ ተከፍቶ ከሚገባው እምነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የተሰዉት መስዋዕቶች በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ምን አደረገ? እኛ ሐጢያተኞች ነበርን፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ሐጢያት ሰርተናል፡፡ ሕጉንና ትዕዛዛቱንም ጥሰናል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለመደምሰስ በዮሐንስ ተጠመቀ፤ የዓለምን ሐጢያቶችም በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ በመስቀል ላይም ደሙን አፈሰሰ፡፡ የመስዋዕቱ እንስሳ በእጆች መጫን ወደ እርሱ የተሻገሩትን የእስራኤሎች ሐጢያቶች እንደተሸከመ፣ እንደታረደና በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ እንደተቃጠለ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም ነውር የሌለበት የመስዋዕት ጠቦት ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት ተጠመቀ፡፡ ከዚያም የመስዋዕት ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ሁለቱም እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው ደሙን በማፍሰስ ጌታችን እኛ በሐጢያቶቻችን እንዳንኮነን ስለ እኛ የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ኩነኔ ተሸከመ፡፡
የዚህ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ አካል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ ምን አደረገ? ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ፣ በመስቀል ላይ በመሰቀልና በመሞት እንደዚሁም ዳግመኛ ከሙታን በመነሳት አዳነን፡፡ ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የተረጋገጠውን ደህንነታችንን አጠናቀቀ፡፡ ከዚያም ወደ መንግሥተ ሰማይ አረገ፡፡
እኛ ሁልጊዜም ሐጢያትን እንሰራለን፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ሌላም ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም ‹‹ማረግ›› ነው፡፡ እናንተና እኔ ሁልጊዜም ሐጢያት መስራታችን የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም ለእግዚአብሄር መስዋዕቶቻችንን ማቅረብ አለብን፡፡ ከዚህ የተነሳ የሐጢያቻችን ኩነኔ ጢስ ሁልጊዜም ወደ እግዚአብሄር ያርጋል፡፡ ሐጢያት ሳትሰሩ ፍጹማን ሆናችሁ የምትኖሩበት አንዳች ቀን አለን? የእስራኤል ሕዝብ የሚያቀርቡዋቸው የመስዋዕት እንሰሶች ካህናት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው የእስራኤላውያን ሐጢያቶች ይቅርታ የሚያስገኙትን እነዚህን መስዋዕቶች ለእግዚአብሄር ማቅረብ እስኪታክታቸውና ዳግመኛ ማቅረብ እስከማይችሉ ድረስ ያለማቋረጥ ይቀርቡ ነበር፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በየቀኑ ሕጉን ስለሚጥሱና በእግዚአብሄር ላይ ሐጢያት ስለሚሰሩ በየቀኑ መስዋዕቶቻቸውን ማቅረብ ነበረባቸው፡፡
ሙሴ እስራኤልን በመወከል የእግዚአብሄርን ሕግና ትዕዛዛት 613 አንቀጾች ለእስራኤላውያን አወጀ፡፡ ‹‹አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑኛላችሁ፡፡ እናንተም የካህናት መንግሥት፣ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ፡፡ ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው፡፡›› (ዘጸዓት 19፡5-6)
ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ይህንን ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ ‹‹እግዚአብሄር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡›› (ዘፀዓት 19፡8) ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በሙሴ ፊት ተገልጦ እንደ እውነተኛ አምላካቸው በእርሱ በኩል የተናገራቸውን ይህንን አምላክ ለማወቅና ለማመን ፈለጉ፡፡ ይህ አምላክ እንዲጠብቃቸውም ፈለጉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ትዕዛዛቶች በሙሉ ለመጠበቅ ሞከሩ፡፡
እግዚአብሄር እስራኤሎች እንደሚወድቁ አስቀድሞ ያውቅ ነበርን? በእርግጥም ያውቅ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን ወደ ሲና ተራራ ወስዶ የመገናኛውን ድንኳን በራዕይ ያሳየው፣ መዋቅሩን በዝርዝር ያብራራለትና በዚያው መሰረትም እንዲሰራ የነገረው ለዚህ ነው፡፡ በዚህ የመገናኛው ድንኳን ውስጥ መስዋዕቶች የሚቀርቡበትንም የመስዋዕት ስርዓት አቋቋመ፡፡
የእስራኤል ሕዝብ ለእግዚአብሄር መሰዋዕት ለማቅረብ ሲፈልጉ ነውር የሌለበት ኮርማ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዋኖስ ወይም ርግብ ማቅረብ ነበረባቸው፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር እጆቻቸውን በራሱ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን ወደ መስዋዕቱ እንስሳ ማሻገራቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው፡፡ (ዘሌዋውያን 1፡1-4) ከዚያም ጉሮሮውን በመቁረጥ ደሙን ማፍሰስና ይህንን ደም ለካህናቶች መስጠት ነበረባቸው፡፡ ከዚያ ካህናቶቻቸው ይህንን ደም ወስደው የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ከቀቡ በኋላ የቀረውን ደም በመሬት ላይ ያፈስሱታል፡፡ ለመስዋዕት የቀረበውን እንስሳ በመቆራረጥም እነዚህን የተቆራረጡ ብልቶች በመሰውያው ላይ በማኖርና በማቃጠል ለእግዚአብሄር ያቀርቡዋቸዋል፡፡
እስራኤሎች የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ የሚያገኙት በዚህ መንገድ ነው፡፡ መስዋዕቱ ሲቃጠል ሥጋውን ብቻ አያቃጥሉትም፡፡ ስቡን ሁሉ ያቃጥሉታል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ መንገድ የእስራኤሎችን ሐጢያት በሙሉ ይቅር ይላል፡፡
ለሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ስርየት የምታገኙበት ብቸኛው መንገድ፡፡
ራሳችንን ስንመለከት ሁልጊዜም ሐጢያትን ከመስራት በሰተቀር የምናደርገው ሌላ ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን፡፡ ሕይወታችንን የምንኖረው ሁልጊዜም ሐጢያትን እየሰራን ነው፡፡ ደካሞች ስለሆንን፣ ብዙ እንከኖች ስላሉብን፣ በጣም ስስታሞች ስለሆንን ወይም ብዙ ሥልጣን ስላለን ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ሐጢያቶችን እንሰራለን፡፡ ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው በሚያምኑት መካከልም እንኳን ሐጢያት የማይሰራ ማንም የለም፡፡
በእግዚአብሄር እያመንን ሁልጊዜም ሐጢያትን የምንሰራ እኛ ከእነዚህ ሐጢያቶች በሙሉ ታጥበን መዳን የምንችልበት ብቸኛው መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ማመን ነው፡፡ እርሱ ራሱ በውሃና በመንፈስ የመጣ አምላክ ነው፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 5፡6) እርሱ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የሚቀርብ መስዋዕት ሆኖ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ ይህ ኢየሱስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ከወሰደና በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ በመሞት የሐጢያቶቻችንን ዋጋ ከከፈለ የሐጢያትን ስርየት በእምነት የማንቀበለው እንዴት ነው? በመሲሃችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደህንነት የተነሳ እናንተና እኔ በእምነት አማካይነት የሐጢያት ስርየታችንን በአንድ ጊዜ መቀበል ችለናል፡፡
እኛ ሁልጊዜም ሐጢያትን የምንሰራ መሆናችን እርግጥ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ በጥምቀቱና በደሙ ደህንነትን ስለፈጸመ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጻ መውጣት ችለናል፡፡ ጌታችን ሐጢያቶቻችንን በጥምቀቱ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ የዓለምን ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ ተሸክሞ ተሰቀለ፡፡ በዚህም ከሐጢያቶቻችን ሙሉ በሙሉ ነጻ አወጣን፡፡ እርሱ ለሐጢያቶቻችን በመጠመቅ በስቅለቱም የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ ሁሉ ተሸከመ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ በዚህ እውነት የምናምነውን ሁሉ ሙሉ በሙሉ አድኖናል፡፡ ለሐጢያቶቻችን መኮነናችንን ማስወገድ ስላልቻልን ኢየሱስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ አማካይነት በሰጠን የደህንነትና የምህረት ፍቅር ምክንያት እናንተና እኔ በእምነት ዳንን፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አድኖናል፡፡ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የሚያሳየን ይህንን ነው፡፡
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ነገር ውብ ነበር ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወደ አደባባዩ ስትገቡ ያልተጠበቀና የሚያስጠላ ትዕይንት ይገጥማችኋል፡፡ በአራት ማዕዘን የተሰራው የናሱ የሚቃጠል መስዋዕት መሰውያ በማንኛውም ጊዜ ጢስና እሳት ሊተፋ እንደሚችል ይዝታል፡፡ የነሐሱ መሰውያ የሚጠብቀው ሐጢያተኞችን ነው፡፡ መሬቱም በደም ይጨቀያል፡፡ ማንም ሰው ይህ የሐጢያት ኩነኔ ስፍራ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ይህ ስፍራ በየቀኑ መስዋዕቶች የሚቀርቡበት በመሆኑ የሚቃጠለው ሥጋና እንጨት ግማት ሊያጥወለውላችሁ ይደርሳል፡፡
ከሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ በታች ደም እንደ ወንዝ ይፈሳል፡፡ እስራኤሎች ሐጢያት በሰሩ ጊዜ ሁሉ የመስዋዕት እንስሶቻቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ይዘው በመምጣት እጆቻቸውን በመጫን ሐጢያቶቻቸውን ወደ እርሱ ያሻግራሉ፡፡ ጉሮሮውንም ይቆጥሩታል፡፡ ደሙን ያፈስሱታል፡፡ ይህንንም ደም ለካህናቶቹ ይሰጡዋቸዋል፡፡ ከዚያም ካህኑ ይህንን ደም በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ ይቀባና የቀረውን በመሬት ላይ ያፈስሰዋል፡፡
ያን ጊዜ መስዋዕቱን ይቆራርጡትና ከኩላሊቶቹና ከስቡ ጋር ሥጋውን በፍርግርጉ ላይ አስቀምጠው ያቃጥሉታል፡፡ ደም ሲፈስስ መጀመሪያ ላይ ቀይ ፈሳሽ ሆኖ ይፈሳል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ይረጋና የሚያጣብቅ ይሆናል፡፡ በትክክል ወደ መገናኛው ድንኳን ገብታችሁ ከሆነ ይህንን አስደንጋጭ ደም አይታችኋል፡፡
የእስራኤል ሕዝብ የእግዚአብሄርን ትዕዛዛት በጣሱ ጊዜ ሁሉ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ አማካይነት በመሰውያው ላይ ለመስዋዕት እንዳቀረቡዋቸው እንስሶች መሞት እንደነበረባቸው ይገነዘባሉ፡፡ ለምን? ምክንያቱም እግዚአብሄር ከእነርሱ ጋር የደም ቃል ኪዳን አድርጓልና፡፡ ‹‹ሕጌን የማትጠብቁ ከሆነ ሕዝቤና የካህናት መንግሥት ትሆናላችሁ፡፡ ነገር ግን ሕጉን የማትጠብቁ ከሆነ እነዚህ የመስዋዕት እንስሶች እንደሚሞቱ መሞት አለባችሁ፡፡›› እግዚአብሄር የደም ኪዳኑን የመሰረተው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ እስራኤላውያን ይህንን እውነት ነው ብለው በመቀበላቸው ሐጢያት ቢሰሩና ሕጉን ቢጥሱ ደማቸውን ማፍሰስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለሐጢያቶቻቸው የመስዋዕት ደም ማቅረብ ያለባቸው እስራኤሎች ብቻ ሳይሆኑ በእግዚአብሄር የሚያምኑትም ጭምር ናቸው፡፡ ይህም በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት የሚሰራ ማንኛውም ሰው ምንም ያህል ታላቅ ወይም ታናሽ ይሁን በልቡ ውስጥ ሐጢያት ስላለበት የሐጢያቱን ኩነኔ መጋፈጥ አለበት፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የሐጢያት ደመወዝ ሞት መሆኑን በሚናገረው ሕግ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር በተገለጠው ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ጥሩ በፍታ አማካይነት ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔ እንዳዳነን ይነግረናል፡፡ ሁልጊዜ ሐጢያት ለምንሰራውና በሐጢያቶቻችንም መኮነን ለሚገባን ለእኛ ክርስቶስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት በዮሐንስ ተጠምቆ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፡፡ እነዚህንም የዓለም ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ተሸክሞ ተሰቀለ፡፡ በመስቀል ላይም ደሙን አፈሰሰ፡፡ ታላቅ ስቃይና መከራንም ተቀበለ፡፡ በዚህም እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡
እናንተና እኔ በእምነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን የቻልነው ክርስቶስ ሥጋውን መስዋዕት አድርጎ በመስጠቱ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ከሞት ማምለጥ ለማይችሉት ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በጥምቀቱ በራሱ ላይ ወስዶ ለሞት ተሰቀለ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ በዚህም ከሐጢያቶቻቸውና ከኩነኔያቸው ሁሉ አዳናቸው፡፡
እግዚአብሄር የእስራኤሎችን መስዋዕት ተቀብሎ ሐጢያቶቻቸውን ከመኮነን ፋንታ ሐጢያቶቻቸውን ይቅር ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር የእስራኤል ሕዝብ እጆቻቸውን በራሱ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን በመስዋዕቱ እንስሳ ላይ እንዲያሻግሩ በማድረግና መስዋዕቱን አርደው ደሙን፣ ሥጋውንና ስቡን እንዲያቀርቡ በማድረግ የእስራኤሎችን ሐጢያት ይቅር አለ፡፡ የእግዚአብሄር ምህረትና ፍቅር ይህ ነበር፡፡
እግዚአብሄር በሕጉ ብቻ አልተገናኘንም፡፡
እግዚአብሄር እናንተንና እኔን እንዲሁም የእስራኤልን ሕዝብ በሙሉ በሕጉ መሰረት ቢኮንነን ኖሮ በዚህ ምድር ላይ ምን ያህሎቻችን እንኖር ነበር? እግዚአብሄር በሕጉ ብቻ ቢለካንና ቢፈርድብን ኖሮ ማናችንም ለአንድም ቀን እንኳን በሕይወት አንኖርም ነበር፡፡ አብዛኞቻችን ለ24 ሰዓታት እንኳን ሳንቆይ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንሞት ነበር፡፡ አንዳንዶቻቸን በአንድ ሰዓት ውስጥ ልንሞት እንችላለን፡፡ ሌሎች ደግሞ በ10 ሰዓታት ውስጥ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ልዩነቱ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በሁለቱም መንገድ ሁላችንም ለመሞት የታጨን ነን፡፡ ሰዎች አሁን እንደሚኖሩት 60, 70, 80 እና ከዚያ በላይ መኖር አይችሉም ነበር፡፡ ሁሉም ያለ ጊዜው ይኮነን ነበር፡፡
በዚህ ጠዋት ስለሆነው ነገር አስቡ፡፡ ልጃችሁ ሌሊቱን በሙሉ ሲጨፍር አድሮ ከአልጋው ለመነሳት እየታገለ ነው፡፡ ሚስታችሁ ልትቀሰቅሰው እየሞከረች ነው፡፡ የጩኸት ግጥሚያ ይከሰትና ልጅ ስለቀሰቀሰችው በሚስት ላይ ሲጮህ ሚስታችሁ ደግሞ ስለጮኸባት በልጃችሁ ላይ ትጮህበታለች፡፡ በዚህ ሁኔታ የማለዳው ጦርነት ይጀምራል፡፡ በመጨረሻም እናትና ልጅ ሁለቱም በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያትን በመስራት ያጠናቅቃሉ፡፡ ሁለቱም ይህንን ቀን አያልፉትም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ለዚህ ሐጢያት ይኮነኑ ነበር፡፡
እግዚአብሄር ግን ጻድቅ በሆነው ሕጉ ብቻ አይገናኘንም፡፡ ‹‹እንደ ሐጢአታችን አላደረገብንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም፡፡›› (መዝሙረ ዳዊት 103፡10)
እግዚአብሄር ጻድቅ በሆነው ሕጉ በእኛ ላይ ከመፍረድ በጣም ርቆ ይህንን ጻድቅ ሕግ ለመፈጸም የእኛን ስፍራ የሚወሰድውን መስዋዕት አዘጋጀ፡፡ እጆቻችንን በዚህ መስዋዕት ላይ ጭነን ሐጢያቶቻችንን እንድናሻግርና የራሳችንን ሕይወት በመስጠት ፋንታም የዚህን መስዋዕት ደም ለእርሱ እንድናቀርብ በማድረግ እግዚአብሄር በእኛ ሕይወት ምትክ የመስዋዕቱን እንስሳ ሕይወት በመቀበል የእኛንና የእስራኤሎችን ጨምሮ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ይቅር በማለት እንደገና በሕይወት እንድንኖር አደረገን፡፡ እግዚአብሄር ምዕመናንን ከሐጢያቶቻቸው በማዳን የራሱ ሕዝብ አደረጋቸው፡፡ እግዚአብሄር የእስራኤልን ሕዝብ የአምላክ የካህናት መንግሥት ያደረጋቸው በዚህ መንገድ ነው፡፡
እዚህ ላይ የተጠቀሰው የመስዋዕት እንስሳ የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ በሐጢያቶቻችን ምክንያት ኢየሱስ ክርሰቶስ የመስዋዕት እንስሳ ሆነ፡፡ የሐጢያት ኩነኔ የገጠመንን እኛን ለማዳንም በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፡፡ በመስቀል ላይም ደሙን በማፍሰስ ሞተ፡፡ የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት በጥምቀቱ የመስዋዕት እንስሳ ሆነ፡፡ ይህንን ያደረገው የአባቱን ፈቃድ በመታዘዝ ነበር፡፡ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በራሱ ላይ በመውሰድ፣ እነዚህንም የዓለም ሐጢያቶች በመስቀል ላይ በመሸከም፣ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት ኢየሱስ እናንተንና እኔን ሙሉ በሙሉ አዳነን፡፡
ኢየሱስ በእኛ ፋንታ መጠመቁን፣ መሰቀሉንና በሦስት ቀናት ውስጥም ከሙታን መነሳቱን የሚነግረንን የደህንነት ቃል ስንሰማ ልባችን በአያሌው ይነቃቃል፡፡ ምክንያቱም በእኛ ፋንታ ሐጢያት የሌለበት እርሱ ሐጢያቶቻችንን ወደ እርሱ ያሻገረውን ጥምቀት ተቀብሎዋልና፡፡ የሐጢያቶችን ዋጋ ለመክፈልም ሁሉንም ዓይነት ስደት፣ ግፍ፣ ስቃይ፣ መከራና በመጨረሻም ሞትን ተሸከመ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ከመጀመሪያውም እኛ ልንቀበላቸው የሚገቡን ነገሮች ነበሩ፡፡ ክርስቶስ በዚህ መንገድ ከሐጢያቶቻችን ስላዳነን በዚህ እውነት አለማመን ግፍ ነው፡፡
በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ አማካይነት በተፈጸመው ደህንነት ማመን አለብን፡፡
ኢየሱስ ለእኛ በተጠመቀው ጥምቀት ሐጢያቶቻችንንና የእነዚህን ሐጢያቶች ኩነኔ ስለተሸከመና በእኛ ፋንታ መስዋዕት በመሆንም እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችን ስላዳነን ሁላችንም ‹‹ጌታ ሆይ አመሰግንሃለሁ!›› የሚል ዓይነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ብዙ ሰዎች ልብ በሚነኩ የፍቅር ታሪኮች፣ የሕይወት ታሪኮች ወይም በማንኛውም ዓይነት አስደማሚ ታሪኮች በቀላሉ ቢነቃቁም ስለ እግዚአብሄር ወሰን የለሽ ፍቅር ልባቸው ወደሚያስበው ነገር ሲመጡ እንደ በረዶ የቀዘቀዙ ናቸው፡፡ የጌታችን ጸጋ ታላቅ ሆኖ ሳለ እርሱ ስለ እኛ ሲል ተጠመቀ፡፡ በመስቀል ላይም ሞተ፡፡ አሁንም ይህንን ጸጋ መረዳትና ለዚህ ሁሉ እርሱን ማመስገን የማይችሉ እንስሳ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡
የእግዚአብሄር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ለእኛ መስዋዕት ሆነ፡፡ በጥምቀቱም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በሰውነቱ ተሸክሞ በመስቀል ላይ በመሞት ራሱን መስዋዕት አደረገ፡፡ በጥፊ ተመታ፤ ተራቆተ፤ ተሰደደ፤ ተጨነቀ፤ ይህንን ሁሉ የሆነው ለእኛ ሲል ነው፡፡ ያዳነን በዚህ መንገድ ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሄር ልጆች የሆንነው ይህንን እውነት በማመን ነው፡፡ ይህ ከሁሉም የሚበልጥ ማነቃቂያ ነው፡፡ ቃላቶች ሊገልጡት የማይችሉት የእግዚአብሄር ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ ክርስቶስ ያዳነን በዚህ መንገድ ሆኖ ሰለ ብዙ ሰዎች ይህንን ከሰሙ በኋላ እንኳን አሁንም አለማመናቸውና እርሱን አለማመስገናቸው በጣም ያሳዝነኛል፡፡
እናንተና እኔ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የዳንነው ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቁና ራሱን መስዋዕት በማድረጉ ነው፡፡ ስለዚህ ኢሳይያስ 53፡5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደህንታችንም ተግሳጽ በእርሱ ላይ ነበረ፡፡ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡››
በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ሐጢያትን እንሰራለን፡፡ ጌታችን ከመኮነን በቀር ምንም ማድረግ የማንችለውን ከሐጢያቶቻችን፣ ከኩነኔ፣ ከጥፋትና ከእርግማኖች ሁሉ ለማዳን የመንግሥተ ሰማይን ዙፋን ትቶ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ በዮሐንስ ፊት ራሱን አጎንብሶ ተጠመቀ፡፡ እነዚህን ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ ተሸከመ፡፡ ክፉኛም ተሰቃየ፡፡ በልቡ ውስጥ ያለውን ደም ሁሉ በመሬት ላይ አፈሰሰ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ ለእኛም መስዋዕት ሆነ፡፡ የደህንነታችንም እውነተኛ አምላክ ሆነ፡፡
ስለዚህ እውነት አስባችሁ በልባችሁ ውስጥ ቀብራችሁታልን? ቃሉን ስትሰሙ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት እንደተጠመቀ፣ እስከ ሞት ድረስ እንደተሰቀለና ሕዝቡን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን እንደተነሳ ማመንና በልባችሁ ውስጥም በአያሌው መነቃቃት ተገቢ ነው፡፡ ሁላችንም ለሲዖል የታጨን እንደነበርን ስንገነዘብ ይህ ደህንነት ምን ያህል በአያሌው እንደሚያነቀቃና አመስጋኝ እንደሚያደርግ ከልባችን እንረዳለን፡፡ በእግዚአብሄር አምነን የእርሱ ሕዝብ ለመሆን ብንሻም እዚህ ደረጃ ላይ የምንደርስበት መንገድ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የሐጢያት ስርየትን በትክክል ስንሻ የነበርነውን እናንተንና እኔን ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቁ፣ በመስቀል ላይ በመሞቱና በሦስት ቀናት ውስጥ ከሙታን በመነሳቱ የእውነት ቃል ተገናኘን፡፡
ይህ የኢየሱስ መስዋዕትነት ባይኖር ኖሮ ደህንነትን እንዴት መቀበል እንችል ነበር? በጭራሽ መቀበል አንችልም ነበር! በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ባይሆን ኖሮ፣ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በተገለጠው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ደህንነት ባይሆን ኖሮ መዳን እንዲያው በእኩለ ሌሊት የሚመጣ የበጋ ሕልም ሆኖ ብቻ ይቀርብን ነበር፡፡ በእርሱ መስዋዕትነት ባይሆን ኖሮ ከሐጢያቶቻችን ከቶውኑም ነጻ መውጣትና ቅጣትን ማስወገድ ስለማንችል ወደ ዘላለማዊ የሲዖል እሳት ተጥለን ለዘላለም እንሰቃይ ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ልክ የብሉይ ኪዳን መስዋዕት እንደሚያደርገው ራሱን ስለ እኛ መስዋዕት በማድረግ አዳነን፡፡
በአዲስ ኪዳን የተፈጸመው የሰማያዊው፣ የሐምራዊውና የቀዩ ማግ ደህንነት፡፡
ውድ አንባቢዎቼ ለመገናኛው ድንኳን ሲያገለግሉ የነበሩትን የሰማያዊ፣ የሐምራዊ፣ የቀይ ማግና የጥሩ በፍታ እውነት ከቶውኑም መርሳት የለባችሁም፡፡ ጥሩው በፍታ የብሉይና የአዲስ ኪዳናት ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል እግዚአብሄር ከረጅም ጊዜ በፊት እርሱ ራሱ አዳኛችን ሆኖ ወደ እኛ እንደሚመጣ ተስፋ የሰጠበት ቃል ነው፡፡ በዚህ የተስፋ ቃል መሰረትም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ ሰማያዊው ማግ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመምጣት በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ እንደወሰደ ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር ከሐጢያቶቻችን እንደሚያድነንና ከኩነኔያችን ነጻ እንደሚያወጣን በሰጠን ተስፋ መሰረት ተጠመቀ፡፡ እርሱ የእኛን ሐጢያቶችና በዚህ ምድር ላይ ያለውን የእያንዳንዱን ሰው ሐጢያት በራሱ ላይ ለመውሰድ በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ በእርግጥም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ተሸከመ፡፡ ይህንን ከቶውኑም መርሳት የለብንም፡፡ ኢየሱስ መስዋዕታችን ሆኖ መምጣቱንና በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ መውሰዱን ከረሳን ደህንነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡
ብዙውን ጊዜ እዚህ ዓለም ላይ የምንኖረው ራሳችንን በጣም እየካብን ነው፡፡ የሰዎች ልብ እንደዚህ ያለ ስለሆነ አንድ ሌላ ሰው ጉራውን ሲነዛ መታገስ ባይችሉም ራሳቸው ግን ጉራቸውን መንዛት ይወዳሉ፡፡ ነገር ግን በራሴ ሳይሆን በሌላ ሰው አማካይነት ጉራዬን መንዛት የጀመርሁበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህም ኢየሱስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ስላዳነኝ አመስጋኝ የሆንሁበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር በኢየሱስ ኮራሁ፡፡ አሁን በቻልሁኝ ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ ሐጢያቶቻችንን ለመደምሰስም በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በራሱ እንደወሰደ፣ ኢየሱስ የተሰቀለው በመጠመቁ ምክንያት እንደሆነና ጌታችን ያዳነን በዚህ መንገድ እንደሆነ በመናገር እኮራለሁ፡፡ በዚህ እውነት ከመኩራት፣ ከመስበክ ለእግዚአብሄርም ክብሩን ሁሉ ከመስጠት አልቆጠብም፡፡
ነገር ግን በኢየሱስ እናምናለን እያሉ የእርሱን ጥምቀት ከስዕሉ ውጪ አድርገው ቃሉን የሚሰብኩ ወይም የእርሱን ስም በመያዛቸው ብቻ የሚኩራሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ለኑሮው በወር የሚያጠፋው $300 ብቻ እንደሆነ መናገር የሚወድ አንድ ሐሰተኛ አገልጋይ ነበር፡፡ ልክ ትልቅ ድል ይመስል በወር በ$300 ብቻ መኖር እንደሚችልና ተከታዮቹም ወጪዎቹን ሁሉ ስለሚሸፍኑለት ጉዞ በሚያደርግበት ጊዜም ምንም ገንዘብ እንደማይዝ በመኩራራት መናገር ይወድ ነበር፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ምዕመናን ገንዘብ ቢያንስ ገንዘብ አይደለምን? ይህ ገንዘብ ለአንዳች ነገር አያገለግልምን? ቁም ነገር የሚሰራው የእርሱ ገንዘብ ብቻ ነውን? ይህ ክርስቲያን መሪ አንድ ነገር በሚፈልግበት ጊዜ ሁሉ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ‹‹ጌታ ሆይ የጉዞ ወጪዎቼን ሸፍንልኝ! ጌታ ሆይ አምንሃለሁ!›› ብሎ መጸለይ ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህንን ጸሎት ከጸለየ በኋላ ከየት መጣ ሳይባል አንድ ቅዱስ ሰው መጥቶ ብዙ ገንዘብ እንዳሸከመው መስክሮዋል፡፡ የሚኩራሩበት ነገር ያላቸው ይመስል እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን የሚናገሩ ሰዎችን ስታዩ ወደ አእምሮዋችሁ የሚመጡት አሳቦች ምንድናቸው?
ማቴዎስ 3፡13-17 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፤ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፡፡ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፡፡›› ይህ ምንባብ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ምን እንደተፈጠረ ያብራራል፡፡ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠምቆ ከውሃው በወጣ ጊዜ የሰማይ በር ተከፍቶ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› የሚል የእግዚአብሄር ድምጽ ተሰማ፡፡ በዚያን ጊዜ አጥማቂው ዮሐንስ ተገረመ፡፡
አጥማቂው ዮሐንስ በዚህ በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ ሁለት ጊዜ ተደንቋል፡፡ በመጀመሪያ የተደነቀው ኢየሱስ ወደ እርሱ መጥቶ በእርሱ ሊጠመቅ መፈለጉን ባየ ጊዜ ነበር፡፡ እንደገና የተደነቀው ደግሞ ኢየሱስን ካጠመቀ በኋላ የሰማይ በር ተከፍቶ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› የሚለውን የእግዚአብሄር ድምጽ በሰማ ጊዜ ነበር፡፡
ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ የተጠመቀበት ምክንያት ምንድነው? እዚህ ላይ ማቴዎስ 3፡15 መልሱን ይሰጠናል፡፡ እንደገና ቁጥር 15 እና 16ን እናንብብ፡- ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፤ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፡፡››
ማቴዎስ 3፡15 ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ የተጠመቀበትን ምክንያት ይነግረናል፡፡ ኢየሱስ የመንግሥተ ሰማይ ሊቀካህንና የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ ቢሆንም የእርሱ ሕዝብ የሆንውን እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ እነዚህን ሐጢያቶች በራሱ ላይ በመውሰድና በእኛ ቦታ መስዋዕት በመሆን የሐጢያቶቻችንን ዋጋ የሚከፍል የመስዋዕት በግ ሆኖ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ የፈለገው ለዚህ ነበር፡፡
ነገር ግን ኢየሱስ በሌላ ሰው ሳይሆን በአጥማቀቂው ዮሐንስ የተጠመቀው ለምንድነው? ምክንያቱም አጥማቂው ዮሐንስ የሰው ዘር ወኪልና ከሴቶች ከተወለዱት ሁሉ እጅግ ታላቁ ሰው ሆኖ ስለተወለደ ነው፡፡ ማቴዎስ 11፡11 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ለመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፡፡›› አጥማቂው ዮሐንስ በብሉይ ኪዳን ዘመን በሚልክያስ መጽሐፍ ውስጥ ትንቢት የተነገረለት የእግዚአብሄር ባርያ ነበር፡፡ ‹‹እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሄር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡›› (ሚልክያስ 4፡5) አጥማቂው ዮሐንስ እግዚአብሄር እንደሚልከው ቃል የገባለት ይህ ኤልያስ ነበር፡፡
እግዚአብሄር አጥማቂውን ዮሐንስ ኤልያስ ብሎ የጠራው ለምንድነው? ኤልያስ የእስራኤሎችን ልብ ወደ እግዚአብሄር የመለሰ ነቢይ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን የእስራኤል ሕዝብ በኣልን አምላካቸው አድርገው ያመልኩ ነበር፡፡ ኤልያስ ግን እውነተኛው አምላክ በኣል ወይም የሆዋ እግዚአብሄር እንደሆነ በግልጽ አሳያቸው፡፡ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ በእምነቱና በመስዋዕቱ ቁርባን አማካይነት ሕያው የሆነው አምላክ በተጨባጭ ማን እንደሆነ በማሳየት ጣዖታትን ያመለኩ የነበሩትን ለእስራኤል ሕዝብ ወደ እውነተኛ አምላክ የመለሰ ነቢይ ነበር፡፡ እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ማብቂያ ላይ ‹‹ኤልያስን እልክላችኋለሁ›› በማለት ቃል የገባው ለዚህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠሩ ሰብዓዊ ፍጡራን በሙሉ በተሳሳተው የጣዖት አምልኮ መንገድና በአጋንንት አምልኮ የተያዙ በመሆናቸው እግዚአብሄር ወደ እርሱ የሚመልሳቸውን ባርያውን እንደሚልክላቸው ተናገረ፡፡ በዚህ ሁኔታ የመጣውም አጥማቂው ዮሐንስ ነበር፡፡
ማቴዎስ 11፡13-14 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፡፡›› የሚመጣው ይህ ኤልያስ አጥማቂው ዮሐንስ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በቁጥር 11-12 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ግን ሁሉ የሚያንስ ይበልጠዋል፡፡ ከመጥምቁ ከዮሐንስ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል፡፡››
ስለዚህ እዚህ ላይ ‹‹ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም›› ማለት እግዚአብሄር አጥማቂውን ዮሐንስን የሰው ዘር ሁሉ ወኪል አድርጎታል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር አጥማቂው ዮሐንስ ከኢየሱስ ውልደት ስድስት ወራት ቀደም ብሎ እንዲወለድ አደረገው፡፡ እግዚአብሄርም የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነቢይና ካህን አድርጎ አዘጋጀው፡፡ ስለዚህ አጥማቂው ዮሐንስ የምድር ሊቀ ካህን ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስን አጠመቀው፡፡ በዚህም የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በእርሱ ላይ አሻገረ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ የተጠመቀው በጥምቀቱ አማካይነት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ለመውሰድ ነበር፡፡
ኢየሱስ በማቴዎስ 3፡15 ላይ ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ ጽድቅ ሁሉ ሊፈጸም የሚችለው የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመቀበል ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ ሲጠመቅ በመሆኑ ኢየሱስ ይህ ተገቢ እንደሆነ ተናገረ፡፡
ጌታችን በዚህ ዘዴ ሐጢያተኞችን አዳነ፡፡
ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ይህ ጥምቀት ከብሉይ ኪዳኑ እጆችን መጫን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በብሉይ ኪዳን ዘመን የአንድ ሰው ሐጢያቶች በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ፊት ለመስዋዕት ወደቀረበው እንስሳ የሚሻገረው በእጆች መጫን ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቁ የእጆችን መጫን ተስፋ ፈጸመ፡፡ ዘወትር መስዋዕቶች በሚቀርቡበት ጊዜ ሁሉ ሐጢያተኞች እጆቻቸውን በራሱ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን ለመስዋዕት ወዳቀረቡት እንስሳ ያሻግራሉ፡፡ በሰባተኛው ወር በ10ኛው ቀን ማለትም በስርየት ቀን ዓመታዊ መስዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ሁሉ ሊቀ ካህኑ እጆቹን በራሱ ላይ በመጫን የዓመቱን የእስራኤሎች ሐጢያቶች ሁሉ ያሻግራል፡፡
ልክ በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንዳለው እጆችን መጫን ኢየሱስም በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ተቀብሎ እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ አስወገደ፡፡ እነዚህን የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ስለወሰደ በእኛ ፋንታ የእነዚህን ሐጢያቶች ኩነኔ ተሸክሞ ተሰዋ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የደህንነታችን እውነተኛ አምላክ መሆን የቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡
ስለዚህ በሐጢያቶቻችን ምክንያት ከመሞትና ከመኮነን በስተቀር የምናደርገው ነገር እንደሌለ ማመን አለብን፡፡ ይህንን ማወቅ አለብን፡፡ ስሜቱም ሊሰማን ይገባል፡፡ መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ስለ እኛ መስዋዕት በመሆን እንዳዳነን መገንዘብ አለብን፡፡ ያም ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ፣ በስቅለቱና በትንሳኤው የደህንነት ሥራዎቹ አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አንጽቶ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቻችንን አዳነን፡፡ ኢየሱስ የደህንነት ስጦታን እንደሰጠን ደህንነታችንን እንደፈጸመና ይህንን የተጠናቀቀ ደህንነት ስጦታ አድርጎ እንደሰጠንም ማመን አለብን፡፡ ኢየሱስ ጽድቅን ሁሉ ስለፈጸመ በማመንና በመቀበል ብቻ በእርግጥም መዳን ይቻላል፡፡
ይህንን እንድንገነዘብ ለማድረግ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ተፈትሎ ተሰራ፡፡ ይህንን የመገናኛውን ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር ከፍተን ስንገባ በመጀመሪያ የምናየው የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የሚቀርቡት መስዋዕቶች ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ያዳነበትን የደህንነት ዘዴ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የሚሰዉት መስዋዕቶች በእጆች መጫን አማካይነት የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በራሳቸው ላይ በመውሰድ በሐጢያተኞች ፋንታ እስከ ሞት ድረስ ደማቸውን ያፈሱ ነበር፡፡ ከዚያም የመስዋዕቶቹ ደም በመስውያው ቀንዶች ላይ ይቀባል፡፡ የቀረውም መሬት ላይ ይፈስሳል፡፡ ከዚያም የእንስሶቹን ሥጋና ስብ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ ያቀርቡታል፡፡ እነዚህ የመስዋዕት ቁርባኖች ገጽታዎች በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛ አዳኝ ከሆነበት ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር በመስዋዕቶቹ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በዚህ መንገድ እንደሚያድነን አሳይቶናል፡፡
ሐጢያተኞች ያለ ምንም መሳሳት በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ በሚቀርቡት የመስዋዕት እንስሶች ላይ እጆቻቸውን መጫን ነበረባቸው፡፡ የመገናኛው ድንኳን ስለ ውሃውና ስለ መንፈሱ ወንጌል እየነገረን ያለው ለዚህ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በራሱ ላይ ለመውሰድ ተጠመቀ፡፡ ጥምቀት ኢየሱስ በእግዚአብሄር አብ ፊት ለዓለም ሐጢያተኞች በሙሉ የመስዋዕት ቁርባን ለመሆን የተቀበለው የደህንነት አካል ነው፡፡
አሁን በዚህ በመገናኛው ድንኳን አማካይነት ግልጽ የሆነ እምነት ሊኖረን ይችላል፡፡ የመስዋዕቱ እንስሳ በስርየት ቀን በሊቀ ካህኑ እጆች መጫን አማካይነት የእስራኤልን ሕዝብ ሐጢያቶች እንደተቀበለና አሁን ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ወደ እርሱ በመሻገራቸው ምክንያት በእነርሱ ፋንታ መስዋዕት መሆን እንደነበረበት ሁሉ (ዘሌዋውያን 16) ኢየሱስ ክርስቶስም ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ለመውሰድና ለእነዚህ ሐጢያቶችም መስዋዕት ለመሆን ወደዚህ ምድር መጥቶ በእርግጥ የመስዋዕት ጠቦት ሆነ፡፡ በዚህም ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔያችን ሁሉ አዳነን፡፡ አሁን በዚህ የፍቅር ደህንነት ሙሉ በሙሉ ማመን እንችላለን፡፡ እርሱ ለሰጠን ለዚህ የፍቅር ደህንነት እርሱን ማመስገንና ለእግዚአብሄር ያለብንን ዕዳ መክፈል የምንችለው ይህንን እውነት በማመን ነው፡፡
አንድ ሰው ምንም ያህል ስለ መገናኛው ድንኳን ዕውቀት ቢኖረውም የማያምን ከሆነ ይህ ሁሉ ዕውቀት አይረቤ ነው፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ምን ያህል በተጨባጭ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብና ማመን አለብን፡፡ የመገናኛው ድንኳን ሦስት በሮች የነበሩት ሲሆን ሁሉም ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ተፈትለው የተሰሩ ነበሩ፡፡ ሰዎች ከድንቁርናቸው የተነሳ እያንዳንዱን የመገናኛውን ድንኳን የመግቢያ በር በተለያየ መንገድ ያብራሩት ይሆናል፡፡
በአፈታተል ቅደም ተከተሉ መሰረት መጀመሪያ የተፈተለው ሰማያዊው ማግ ሲሆን እርሱን ተከትለው ደግሞ ሐምራዊው፣ ቀዩ ማግና ጥሩው በፍታ ናቸው፡፡ የመገናኛው ድንኳን እውነተኛ ሆኖ በተገቢው መንገድ ሊገለጥ የሚችለው የመግቢያውን በር በዚህ መንገድ በመስራት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤሎች እንዲሰሩት በትክክል ያዘዛቸው ይህንን ነውና፡፡
የመግቢያ በሮቹ በዚህ መንገድ ለመሰራታቸው ምክንያት አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ዘር አዳኝ ለመሆን የሰው ሥጋ ለብሶና በማርያም አካል በኩል መጥቶ ቢወለድም በመጀመሪያ ደረጃ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ለመውሰድ ባይጠመቅ ኖሮ እውነተኛ አዳኛችን መሆን አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ሰማያዊው ማግ መፈተል ነበረበት፡፡ ተዛማጅ ጠቀሜታውም እንደዚሁ ወሳኝ ነበር፡፡
ማመን ያለብን በማነው?
ስለዚህ ከሐጢያቶቻችን ባዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አለብን፡፡ በትክክል ዳግመኛ መወለድ የምንችለው ይህ የእግዚአብሄር ልጅ የሆነው አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ደህንነት ስናምን ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ልጅ የደህንነታችን አምላክ አድርገን ስናምነውና ወደዚህ ምድር መጥቶ ስለ እኛ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በአንድ ጊዜ በራሱ ላይ የወሰደና ኩነኔያችንንም በመስቀል ላይ የተሸከመ በመሆኑ እውነት ስናምን ያን ጊዜ ሁላችንም እውነተኛ ደህንነታችንን መቀበል እንችላለን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ አማካይነት ካልሆነ በሌላ በማናቸውም መንገድ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ መውሰድ ስለማይችል ወደ መስቀል መሄድ፣ ደሙን ማፍሰስና በዚያ ላይ መሞት የሚችለው ሐጢያቶቻችንን በዚህ ትክክለኛ ዘዴ በመሸከም ብቻ ነው፡፡ ምንም ያህል የእግዚአብሄር ልጅ ቢሆንና ምንም ያህል አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር ቢመጣም በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ባይወስድ ኖሮ በዚህ ዓለም ላይ ደህንነት ባላገኘን ነበር፡፡
ስለዚህ ሐጢያቶቻችሁ ቀድሞውኑም የተደመሰሱ ስለመሆናቸው ሙሉ በሙሉ ለማመን የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃዎችን በዝርዝር ማረጋገጥ ያሰፈልጋችኋል፡፡
ለጥቂት ጊዜ ትልቅ ዕዳ እንዳለባችሁ እንገምት፡፡ ከዚያም አንድ ሰው ‹‹አትጨነቁ፤ ዕዳችሁን እከፍልላችኋለሁ፡፡ ይህንን ችግር እፈታዋለሁ›› ይላችኋል፡፡ ከዚህ ሰው ጋር በተገናኛችሁ ጊዜ ሁሉ ‹‹አትጨነቁ ብዬ አልነገርኋችሁምን? ዕዳችሁን እንደምከፍልላችሁ ነግሬያችኋለሁ!›› ማለቱን ይቀጥላል፡፡ ይህ ግለሰብ ለምን እንደማታምኑት በመጠየቅ በእናንተ ላይ እንደሚቆጣ እናስብ፡፡ ይህ ግለሰብ በየቀኑ ‹‹ሁሉንም እከፍላለሁ፤ እመኑኝ ብቻ!›› ቢልም ዕዳችሁን በተጨባጭ የማይከፍል ከሆነ እርሱን በማመናችሁ ብቻ ከዕዳችሁ በተጨባጭ ነጻ መውጣት ትችላላችሁን? አትችሉም!
ምንም ያህል እርግጠኛ ሆኖ ‹‹ከታመናችሁብኝ ዕዳችሁ ይከፈላል›› በማለት ቢነግራችሁም ዕዳችሁን በተጨባጭ ካልከፈለ ዕዳችሁ ባለበት ይቀራል፡፡ ይህ ግለሰብ እያታለላችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ደጋግማችሁ ‹‹ዕዳዬን ከፈልክልኝ?›› በማለት ትጠይቁታላችሁ፡፡ እርሱም ደጋግሞ ‹‹ለምን እንደዚህ ተጠራጣሪ ትሆናለህ? ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እመነኝ! ዕዳህን ሁሉ እንደምከፍል ነግሬሃለሁ፡፡ አንተ ማድረግ ያለብህ በእኔ ማመን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በጣም ተጠራጣሪ ነህ! እንደዚህ አትሁን!›› በማለት ይነግራችኋል፡፡ ነገር ግን ምንም ያህል አብዝታችሁ ብታምኑትም በእርግጥ ዕዳችሁን ካልከፈለላችሁ ቃሎቹ በሙሉ ውሸት ናቸው፡፡
የዘመኑ ክርስቲያኖች እምነት እንደዚህ ነው፡፡
የዘመኑ ክርስቲያኖች ‹‹ኢየሱስ ክቡር ደሙን በመስቀል ላይ በማፍሰስ አድኖዋችኋል፡፡ እዚያ ላይ የሐጢያትን ኩነኔ በሙሉ ተሸክሞዋል፡፡ ያዳናችሁ በዚህ መንገድ ነው›› ይላሉ፡፡ ብዙ መጋቢዎች ለጉባኤያቸው የሚሰብኩት ይህንን ነው፡፡ በጉባኤው መካከል ያለ አንድ ሰው ተነስቶ ‹‹ነገር ግን እኔ አሁንም ሐጢያተኛ ነኝ›› ቢላቸው ‹‹እንደዚያ የሆነው እምነትህ ትንሽ ስለሆነ ነው፡፡ እመን ብቻ! ሐጢያትህ ሌላ ሳይሆን አለማመንህ ነው›› ይሉታል፡፡ ‹‹ጌታዬ እኔም በተጨባጭ ማመን እፈለጋለሁ፡፡ ነገር ግን ለምን ማመን እንደማልችል አላውቅም፡፡›› ‹‹ባምንም አሁንም ድረስ ለምን ሐጢያተኛ እንደሆንሁ አላውቅም፤ በእርግጥ አምናለሁ፡፡›› ‹‹አንተ በቂ እምነት የለህም፡፡ በብዙ ማመን ያሰፈልግሃል፡፡ ወደ ተራራው ውጣና ለመጾም ሞክር፡፡ ምግብህን ረስተህ እመን፡፡›› ‹‹ምግቤን ሳልረሳ ማመን አልችልምን?›› ‹‹አትችልም፤ እየጾምህ ለማመን መሞከር አለብህ፡፡››
ብዙዎቹ የዘመኑ መጋቢዎች እንድታምኑ ይነግሩዋችኋል፡፡ ነገር ግን የሐጢያቶቻችሁን ችግር አይፈቱም፡፡ ባለማመናችሁ ይወቅሱዋችኋል፡፡ እናንተ ለማመን ትሞክራላችሁ፡፡ ነገር ግን ማመን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ወይም ከልባችሁ በዕውር ድንብር ታምናላችሁ፡፡ የሐጢያቶቻችሁ ችግር ግን አሁንም እዚያው ነው፡፡ እዚህ ላይ ችግሩ ምንድነው? ይህንን ማብራራት የሚችለው ምንድነው? ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በራሱ ላይ እንደወሰደ ስለማያውቁ እውነተኛና ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ምንም ያህል አብዝተው ቢያምኑም የሚያምኑት በመታለሎች ስለሆነ የሐጢያቶቻቸውን ችግር መፍታት አይችሉም፡፡
እምነት ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃ በልቅነት በማመን ብቻ ይመጣልን? አይመጣም! ምሉዕ እምነት በአንድ ጊዜ የሚመጣው የሐጢያት ችግር እንዴት እንደሚቃለል ስታውቁና በዚያም ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ብጠራጠርህም ቀድሞውኑ የሐጢያቶቼን ችግር እንደፈታህ ከሚገባው በላይ ግልጽ ነው፡፡ ላለማመን አብዝቼ ብሞክርም በአንተ ከማመን በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻልሁም፡፡ ምክንያቱም ይህ ደህንነት የተረጋገጠ ነውና፡፡ ችግሬን ስላቃለልህልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡›› በሌላ አነጋገር መጀመሪያ ላይ ብንጠራጠርም የመዳናችን ማስረጃ የተረጋገጠ ስለሆነ ዳግመኛ በጭራሽ አንጠራጠርም፡፡ ኢየሱስ የመዳናችን ምልክትና ማስረጃው በመሆን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ተብሎ የሚጠራውን የራሱን ደረሰኝ አሳይቶናል፡፡ ‹‹ዕዳህን በዚህ መንገድ ከፍያለሁ፡፡›› እውነተኛ እምነት ወደ እኛ ሊመጣ የሚችለው ዕዳዎቻችን በሙሉ መከፈላቸውን የሚያሳየውን ይህንን ደረሰኝ በመመልከት ብቻ ነው፡፡
እንዴት እንዳዳነንና ሐጢያቶቻችንም እንዴት እንደተደመሰሱ ማስረጃው ሳይኖረን ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን ነው፤ በአዳኙ አምናለሁ በማለት በእግዚአብሄር እናምናለን እያልን የሐጢያታችንን ደመወዝ ሙሉ በሙሉ መከፈሉን የሚያሳየውን ደረሰኝ እስካልተመለከትን ድረስ ጽኑ እምነት ሊኖረን አይችልም፡፡ ይህንን ደረሰኝ ሳያዩ በመጀመሪያ ላይ ጠንካራ የእምነት ስሜት ያላቸው ቢመስሉም እምነታቸው ግን ዕውር ነው፡፡ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እምነት ነው፡፡
ጥራዝ ነጠቅ የሆነን እምነት ጥሩ እምነት አድርጋችሁ ትመለከቱታላችሁን?
ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እምነት ያለው መጋቢ ከሌሎቹ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እምነትን ቢጠይቅ እንዴት ታዩታላችሁ? ‹‹እመን! እሳትን ተቀበል! እሳት፤ እሳት፤ እሳት! እንደ እሳት የሆንከው መንፈስ ቅዱስ በእሳት ሙላን! ጌታ ሁላችሁንም እንደሚባርካችሁ አምናለሁ! ሁላችሁንም ሐብታሞች እንደሚያደርጋችሁ አምናለሁ! እንደሚባርካችሁ አምናለሁ! እንደሚፈውሳችሁ አምናለሁ!›› ይህ መጋቢ እንደዚህ ያለ ትዕይንት በሚያሳይበት ጊዜ የአድማጮቹ ጆሮዎች መደወል ይጀምራሉ፡፡ ልባቸውም መዝለል ይጀምራል፡፡ እጅግ ከፍተኛ ጥራት ባለው የድምጽ ታንቡር በመታገዝ ‹‹እሳት፤ እሳት፤ እሳት›› እያለ መጮህ ሲጀምር የአድማጮቹ ልብም የድምጹን ግርማ ሞገስ ተከትሎ መዝለል ይጀምራል፡፡ ያን ጊዜ አንድ ጠንካራ እምነት በተጨባጭ የወረደባቸው ይመስል በስሜት ይናጡና ‹‹ጌታ ኢየሱስ ና! መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና!›› በማለት ያላዝናሉ፡፡
ልክ በዚህ ጊዜ መጋቢው ‹‹እስቲ እንጸልይ፡፡ አሁን መንፈስ ቅዱስ እየወረደና ሁላችንንም እየሞላን እንደሆነ አምናለሁ›› በማለት የጉባኤውን ስሜት ያነሳሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ የሙዚቃ ባንዱ ወዲያውኑ የሚያነቃቁ መዝሙሮችን ይጫወታል፡፡ ሰዎችም እጆቻቸውን ከፍ አድርገው በማንሳት በስሜት ግለት ቅጥ ያጣሉ፡፡ የስሜት ግለታቸውም ጫፉ ላይ ይደርሳል፡፡ ልክ ይህ ምልክት ሲታይ መጋቢው ‹‹እስቲ መባዎቻችንን እንስጥ፡፡ በተለይ በዚህ ምሽት እግዚአብሄር ከእናንተ የተለየ መባ ይፈልጋል፡፡ ሁላችንም ይህንን የተለየ መባ ለእግዚአብሄር እንስጥ›› ይላል፡፡
ያን ጊዜ ሰዎች በስሜቶቻቸው ይናጡና ኪሶቻቸውን በማራገፍ ያጠናቀቅቃሉ፡፡ ይህ ሐሳዊ መጋቢ ቀድሞውኑም የተሰበሰበው ገንዘብ በሙሉ የሚከማችበት ሰፊ ምስባክ አዘጋጅቶ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ከረጢቶችን ከፊት ለፊት አስቀምጦዋል፡፡ የሙዚቃ ቡድኑ መዝሙሮችን መጫወት ሲጀምር የሰዎች ልብ በደስታ ይናጣል፡፡ ያን ጊዜ ከረጢቶቹን በጉባኤው መካከል የሚያዞሩ አስተናጋጆችን ይልካል፡፡
እንደዚህ ያሉ ሐሰተኛ መጋቢዎች ብዙ መባ መስጠት ማለት ብዙ በረከቶችን መቀበል ማለት ነው እያሉ በመዋሸትና የሰዎችን ስሜቶች በማነሳሳት ዕንባዎቻቸውን እያፈሰሱ የገንዘብ ቦርሳዎቻቸውን እንዲከፍቱ ይቀሰቅሱዋቸዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ሕሊናቸውንና አስተውሎታቸውን በመስረቅና በስሜቶቻቸው እንዲነዱ በማድረግ ገንዘባቸውን እንዲያስረከቡ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ በእግዚአብሄር ቃል ላይም ሆነ በማንኛውም ዓይነት ስብከት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን በማጭበርበር ላይ የተመሰረተ ጥራዝ ነጠቅና ዕውር ድርጊት ነው፡፡ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እምነት ያላቸው መጋቢዎች የራሳቸውን ድብቅ ዓላማዎች ለማስፈጸም የሰዎችን ስሜቶች ያነሳሳሉ፡፡
ጌታችን በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ እንደወሰደ የምናውቅ ከሆነና ይህንን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን የምናምነው ከሆነ ያን ጊዜ ሰላም እንሆናለን እንጂ አንናወጥም፡፡ በጸጥታ የሚያነቃቃን ብቸኛው ነገር ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን መሸከሙና እስከ ሞት ድረስ መሰቀሉ ነው፡፡ ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ወስዶ የእነዚህን ሐጢያቶች ዋጋ ለመክፈል መሞቱን ስናስብ ከልክ በላይ አመስጋኞች እንሆናለን፡፡ ልባችንም በታላቅ ደስታ ይሞላል፡፡ ነገር ግን በልባችን ውስጥ ያለው ይህ የተረጋጋ መነሳሳት በዚህ ዓለም ላይ ካለ ከማንኛውም ሌላ ነገር በላይ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ማንኛውም ቀልብ የሚስብ የፍቅር ኑዛዜም ሆነ በዚህ ዓለም ላይ ያለ ማንኛውም እጅግ የከበረ የዕንቁ ስጦታ ከዚህ የበለጠ ሊያነሳሳን አይችልም፡፡
በንጽጽር በስሜት ላይ የተመሰረተ የጥራዝ ነጠቆች መነቃቃት ዕድሜ የለውም፡፡ ለጊዜው በዚህ መነቃቃት ውስጥ ቢቆዩም በየቀኑ ሐጢያት ሲሰሩና በእነዚህ ሐጢያቶች ሲያፍሩ ፊታቸውን በሐፍረት ከመሸፈን በቀር ሌላ የሚያደርጉት ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ‹‹ኢየሱስ ኩነኔያችንን ተሸክሞ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ሞቶ ሳለ አሁንም በየቀኑ ሐጢያት የምሰራው ለምንድነው?›› ስለዚህ በሐፍረት ስለሚከደኑ ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ ዳግመኛ ሊነቃቁ አይችሉም፡፡ ከዚህም በላይ ከሐፍረት የተነሳ ወደ እግዚአብሄር ሊቀርቡ እንኳን አይችሉም፡፡
እግዚአብሄር የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ ያሳየን ለዚህ ነው፡፡ በመስዋዕት ስርዓቱ መሰረት በዚህ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ የሚቀርበው መስዋዕት አዳኛችን ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ማንንም አያመለክትም፡፡ ስለዚህ የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ሁላችንንም በአንድ ጊዜ እንዳዳነን ይገልጣል፡፡ እግዚአብሄር ይህንን የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ እንድንመለከት አድርጎናል፡፡ በዚህ በማመንም እንድንድን ይፈልጋል፡፡
በዚህ ዘመን እኛ ማድረግ ያለብን ምንድነው?
እኛ ዳግመኛ የተወለድን በዚህ ዘመን ልናደርጋቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመላው ዓለም ሁሉ መስበክ ይኖርብናል፡፡ እውነቱን ይህንን የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት ለማያውቁት ማሰራጨት አለብን፡፡ በሲዖል እሳት ውስጥ ከመኮነን እንዲድኑም ልንረዳቸው ይገባናል፡፡ ለምን? ምክንያቱም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተገለጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁና ሳያምኑ ኢየሱስን እየተከተሉ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡
ይህንን እውነት ለእነርሱ ለማሰራጨት እኛ ልናደርጋቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በመላው ዓለም የሚላኩትን መጽሐፎቻችንን ማሳተም አለብን፡፡ እነዚህን መጽሐፎች ከመተርጎም፣ ከማረምና ከማስተካከል ጀምሮ ለሕትመት የሚያበቁ መዋዕለ ንዋዮችን እስከ ማግኘትና በመላው ዓለም በሚገኙ አገሮች እስከ መላክ ድረስ ብዙ መሰራት የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች እንዳሉ እርግጥ ነው፡፡
ስለዚህ አብረውን የሚሰሩ ሰራተኞቻችንንና አገልጋዮቻችንን ስንመለከት ሁሉም ባተሌዎች ሆነው እናያቸዋለን፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ቅዱሳንና ሰራተኞች በሙሉ በዚህ መንገድ ባተሌ ስለሆኑ በሥጋቸው በአንዳንድ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ያልፋሉ፡፡ የማራቶን ሯጮች እንደሚያደርጉት ወደ ግባችን ለመድረስ ረጅም ርቀት መሮጥ ማለት ነው፡፡ ለወንጌል የምናደርገው ሩጫ ጌታችን እስከሚመጣ ድረስ መቀጠል ስላለበት ሁላችንም ችግር ያጋጥመናል፡፡
ነገር ግን ጌታችን በውስጣችን ስላለ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ስላለን እምነታችን ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ እንዳዳነን ስለሚያምንና በጣም በተረጋገጠው እውነት ስለምናምን ሁላችንም አዲስ ጉልበት እንቀበላለን፡፡ እናንተና እኔ ይህንን ስጦታ የተቀበልነው ኢየሱስ የደህንነትን ስጦታ ስለሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ የሥጋ መከራዎቻችን ሊያስቸግሩን አይችሉም፡፡ በተቃራኒው ነገሩ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ ሲሄድ ጻድቃንም ይበልጥ ጉልበት ያገኛሉ፡፡ እኔ ከልቤ ጌታን አመሰግናለሁ፡፡
በመንፈሳዊ መልኩ በልባችን በአስተሳሰቦቻችንና በዙሪያችን በከበቡን ነገሮች ጌታችን የሰጠን አዲስ ጉልበት ስሜቱ ይሰማናል፡፡ እርሱ ከእኛ ጋር እንደሆነም እናውቃለን፡፡ እርሱ እየረዳን፣ እየደገፈንና ከእኛ ጋር እንደሆነ ስለሚታወቀን አብዝተን እናመሰግነዋለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ሐይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን አደርጋለሁ፡፡›› (ፊልጵስዩስ 4፡13) ስለዚህ ጌታ ሐይልን ከሰጠን ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምንችል በየቀኑ እንመሰክራለን፡፡ ኢየሱስ ለእኛ የተጠመቀ ብቻ ሳይሆን በመስቀል ላይ በመሰቀልም ስለ እኛ ተሰውቷል፡፡ ሞትንም ተጋፍጦዋል፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነስቶ እውነተኛ አዳኛችን ሆኖዋል፡፡ የሚቀጥለውን መስዋዕት መሰውያ በምንመለከትበት ጊዜ ሁሉ ይህንን እውነት ለራሳችን እናስታውሰዋለን፡፡
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ከግራር እንጨት ተሰርቶ በውስጥና በውጪ በነሐስ የተለበጠ ነበር፡፡ ቁመቱ 4.5 ጫማ ሲሆን ከነሐስ የተሰራው መረብም በመካከሉ ተቀምጦዋል፡፡ የዚህም ቁመቱ 68 ሳንቲ ሜትር አካባቢ ነበር፡፡ የሥጋው ቁርባን በዚህ መረብ ላይ ይቀመጥና ይቃጠላል፡፡
የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ በምንመለከትበት ጊዜ ሁሉ እኛነታችንን እንደ ማንነታችን መመልከት መቻል አለብን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ እንደወሰደና ደሙን በመስቀል ላይ በማፍሰስም የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ በሙሉ እንደተሸከመ ማየት መቻልም አለብን፡፡ እናንተና እኔ በእግዚአብሄር ፊት በሐጢያቶቻችን ከመሞት በስተቀር በተጨባጭ ልናደርገው የምንችለው ነገር አልነበረንም፡፡ ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔያችን የተነሳ እናንተና እኔ ከመሞትና ለዘላለም ከመረገም ማምለጥ የምንችል አልነበርንም፡፡ ነገር ግን ዘላለማዊ የስርየት መስዋዕት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁላችን በመጠመቁና ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋዕቱ በመሞቱ ዳንን፡፡
ለመስዋዕት የቀረበ እንስሳ በሕይወት ሳለ የሚያሳሳና የዋህ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን በእጆች መጫን ሐጢያቶችን ከተቀበለ በኋላ አንገቱ ታርዶ እስከ ሞት ድረስ ደሙን ሲያፈስስ ምንኛ ያስደነግጣል? በዚህ አስደንጋጭ ሁኔታ መሞት የሚገባን እኛ ከኩነኔያችን ማምለጣችን በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው፡፡ ይህ በረከት እውን የሆነው ጌታ የደህንነትን ስጦታ ስለሰጠን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው መሰረት የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም እናንተንና እኔን አዳነን፡፡ በዚህም እውነተኛውን የደህንነት ስጦታ ሰጠን፡፡ እግዚአብሄር በዚህ መንገድ የደህንነትን ስጦታ ለእናንተና ለእኔ ሰጥቶናል፡፡ ይህንን በልባችሁ ታምናላችሁን? በዚህ የኢየሱስ ፍቅር በሆነው የደህንነት ስጦታ ታምናላችሁን? ሁላችንም ይህ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡
የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ ስንመለከት ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መንገድ እንዳዳነን መገንዘብ አለብን፡፡ የደህንነትን ስጦታ ሊሰጠን እንደዚህ ሆኖ ተሰዋ፡፡ በመስዋዕቱ እንስሳ ላይ እጆች እንደሚጫኑና ይህም የመስዋዕት እንስሳ እስከ ሞት ድረስ ደሙን እንደሚያፈስስ ሁሉ ኢየሱስም ደህንነታችንን ሊሰጠን በዚህ መንገድ ተሰቃየ፡፡ ከሐጢያቶቻችን ያዳነን በዚህ መንገድ ነው፡፡ ይህንን በመገንዘብ በእግዚአብሄር ፊት በልባችን ማመንና ከሙሉ ልባችን እርሱን ማመስገን አለብን፡፡
እግዚአብሄር የሰጠንን የደህንነት ስጦታና ፍቅር በእምነት እንድንቀበል ይፈልግብናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ አማካይነት በመምጣት የፈጸመውን የጥምቀቱን ውሃና የመስቀል ላይ ደሙን በልባችን እንድናምን ይፈልግብናል፡፡ ሁላችሁም በልባችሁ የጌታችንን ፍቅር እንድታምኑና ከልባችሁ የደህንነት ስጦታውን እንድትቀበሉ ተስፋችን ነው፡፡ ይህንን በእውነት በልባችሁ ትቀበሉታላችሁን?
በዚህ መንገድ የተሰዋላችሁ ማነው?
በአንድ ወቅት ‹‹ማን ይሞትላችኋል? ዛሬስ ያጽናናችሁ ዘንድ ማን ይገናኛችኋል? ኢየሱስ ክርስቶስ ለእናንተ ተሰውቷል፡፡ ልባችሁ በዚህ አልተጽናናምን?›› የምትል የምስክርነት በራሪ ወረቀት ተመለከትሁ፡፡ ሐጢያቶቻችሁን ለመደምሰስ በእናንተ ፋንታ ተጠምቆ ሐጢያቶቻችሁን የሚሸከምና በመስቀል ላይ በተጨባጭ የሚሞት ማነው? ፍቅሩን ለእናንተ ለመስጠት ደሙን በሙሉ የሚያፈስስና የሚሞት ማነው? ፍቅሩን ለእናንተ ለመስጠት ደሙን በሙሉ የሚያፈስስና የሚሞት ማነው? ይህንን መስዋዕት ሊሰዋላችሁ ማን ፈቃደኛ ይሆናል? ዘመዶቻችሁ ናቸውን? ልጆቻችሁ ናቸውን? ወላጆቻችሁ ናችሁን?
ማናቸውም አይሆኑም! የፈጠራችሁ ራሱ እግዚአብሄር ነው፡፡ ይህ አምላክ እናንተን ከሐጢያቶቻችሁ ለማዳን የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት ሐጢያቶቻችሁን በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ የሐጢያቶቻችሁንም ኩነኔ ለመሸከም ተሰቀለ፤ ደሙንም አፈሰሰ፤ እውነተኛ አዳኛችሁም ሆነ፤ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ አሁንም በሕይወት እየኖረ ነው፡፡ ደህንነቱንና ፍቅሩንም ስጦታ አድርጎ ሰጥቶዋችኋል፡፡ ይህንን የፍቅር ደህንነት በልባችሁ ውስጥ መቀበል ትፈልጋላችሁን? በእርግጥ በልባችሁ ታምናላችሁን?
የሚያምን ሁሉ ጌታን ይቀበላል፡፡ እርሱን የሚቀበል ሁሉ ይድናል፡፡ እርሱን መቀበል ማለት ክርስቶስ የሰጠንን ደህንነትና ፍቅር መቀበል ማለት ነው፡፡ የምንድነው በዚህ ፍቅር፣ በዚህ የሐጢያቶች ስርየት፣ በዚህ ሐጢያቶችን መሸከምና በዚህ የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ በልባችን በማመን ነው፡፡ የደህንነትን ስጦታ የሚቀበለው እምነት ይህ ነው፡፡
የመገናኛው ድንኳን እያንዳንዱ ነገር ኢየሱስ ክርስቶስን ይገልጣል፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ አንዳች መስዋዕትን አልጠየቀም፡፡ ከእኛ የጠየቀን ነገር ቢኖር እርሱ በሰጠን የደህንነት ስጦታ በልባችን እንድናምን ነው፡፡ ‹‹የደህንነትን ስጦታ ልሰጣችሁ ወደዚህ ምድር መጣሁ፡፡ ልክ በብሉይ ኪዳን እንዳለው የመስዋዕት እንስሳ በእጆች መጫን አማካይነት ወደ እኔ የተሻገሩትን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰድሁ፡፡ ልክ እንደዚህ የመስዋዕት እንስሳም ስለ እናንተ አስደንጋጭ የሆነውን የሐጢያቶቻችሁን ኩነኔ ተሸከምሁ፡፡ ያዳንኋችሁ በዚህ መንገድ ነው፡፡›› እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን አማካይነት እየነገራችሁ ያለው ይህንን ነው፡፡
እግዚአብሄር እንደዚህ ቢያድነንም፣ ይህን ያህል አብዝቶ ቢወደንና በዚህ መንገድ ፍጹም የሆነውን የደህንነት ስጦታ ቢሰጠንም የማናምን ከሆነ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፡፡ በኮመዲኖው ውስጥ ያለው ጨው ወጣችሁ እንዲጣፍጥ መጀመሪያ መጨመር አለበት፡፡ ልክ እንደዚሁ እናንተና እኔ በልባችን ካላመንን የእርሱ ፍጹም ደህንነት እንኳን ሙሉ በሙሉ ከንቱ ይሆናል፡፡ ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል ከልባችን አመስጋኝ ካልሆንንና ይህንንም በልባችን ካልተቀበልን የኢየሱስ መስዋዕትነት ከንቱ ይሆናል፡፡
ደህንነት የእናንተ ሊሆን የሚችለው አዳኝ የሆነው አምላክ ኢየሱስ የሰጣችሁን መስዋዕትና ፍቅር በማወቅና በልባችሁ ተቀብላችሁት እርሱን በማመስገን ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስን ፍጹም ደህንነት በልባችሁ ሳትቀበሉ በጭንቅላታችሁ ብቻ የምታውቁት ከሆነ ይህም ፈጽሞ ዋጋ የለውም፡፡
እናንተ ማድረግ የሚኖርባችሁ እውነትን መጨበጥ ነው፡፡
የምትቀቅሉት ሾርባ በምድጃው ላይ ምን ያህል እየበሰለ መሆኑ ከቁም ነገር የሚቆጠር አይደለም፡፡ ጨው ለመጨመር አስባችሁ ያንን ማድረግ ካልቻላችሁ ሾርባችሁ ከቶውኑም ሊጣፍጥ አይችልም፡፡ ልትድኑ የምትችሉት ጌታችን በመጠመቅና ልክ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ላይ መስዋዕት እንደሆነው የመስዋዕት እንስሳ ስለ እኛ በመሰዋት ከሐጢቶቻችሁ እንዳዳናችሁ በመቀበልና በማመን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የደህንነትን ስጦታ ሲሰጣችሁ በምስጋና ተቀበሉት፡፡ ጌታችን ሙሉ በሙሉ እንዳዳነን ሲነግረን እኛ ማድረግ የሚኖርብን ትክክለኛው ነገር እንደዚያ ማመን ነው፡፡
እርሱ የሰጣችሁ የእግዚአብሄር ፍቅር ጎዶሎ ነውን? አይደለም! የጌታችን ፍቅር ፍጹም ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታችን እናንተንና እኔን ሙሉ በሙሉና ፍጹም በሆነ መንገድ አድኖናል፡፡ እርሱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ስለወሰደና በእርግጠኝነት በመስቀል ላይ ስለሞተ ስለዚህ ፍቅር አንዳች ጥርጣሬ ሊኖረን አይችልም፡፡ እርሱ ሙሉ በሙሉ አድኖናል፡፡ እርሱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ስለወሰደና በእርግጠኝነት በመስቀል ላይ ስለሞተ ስለዚህ ፍቅር አንዳች ጥርጥሬ ሊኖረን አይችልም፡፡ እርሱ ሙሉ በሙሉ አድኖናል፡፡ የደህንነትንም ስጦታ ሰጥቶናል፡፡
እጅግ ከከበሩ ሉሎች የተሰራ በጣም ውድ ዋጋ ያለው ጌጣጌጥ አለኝ ብለን እንገምት፡፡ ይህንን ስጦታ አድርጌ ብሰጣችሁ እናንተ የምታደርጉት ነገር ቢኖር በደመ ነፍስ መቀበል ብቻ ነው፡፡ እንደዚያ አይደለምን? ይህንን ጌጣጌጥ የእናንተ ለማድረግ ምን ያህል ቀላል ነው? ይህንን ጌጥ የራሳችሁ ለማድረግ ማድረግ የሚኖርባችሁ እጃችሁን ዘርግታችሁ መውሰድ ብቻ ነው፡፡ እንደዚያ ነው፡፡
ልባችሁን ብትከፍቱና በጥምቀቱ አማካይነትም ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ወደ ኢየሱስ ብታሻግሩ በቀላሉ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት በማግኘት ልባችሁን በእውነት መሙላት ትችላላችሁ፡፡ እግዚአብሄር ደህንነትን ነጻ ስጦታ አድርጎ የሚሰጠን በዚህ መንገድ እንደሆነ የነገረን ለዚህ ነው፡፡ እጃችሁን ዘርግታችሁ ብትወስዱት ደህንነት የእናንተ ሊሆን ይችላል፡፡
እኛ ደህንነታችንን የተቀበልነው አንዲት ሰባራ ሳንቲም ሳንከፍል በስጦታ ነው፡፡ ይህንን ስጦታ መቀበል ለሚፈልግ ሰው ሁሉ ለመስጠት የተደሰተው እግዚአብሄር ስለሆነ በምስጋና የተቀበሉት የተባረኩ ናቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቅር በደስታ የተቀበሉ የእርሱን ፍቅር ለብሰዋል፡፡ ይህንን ለጋስ የሚወዱትም እነርሱ ናቸው፡፡ ይህንን በመቀበል ልቡን አስደስተውታልና፡፡ ይህንን ደህንነት መቀበል ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ነው፡፡ ይህ እውነተኛ የደህንነት ስጦታ የእናንተ ሊሆን የሚችለው ይህንን ፍጹም የሆነ የደህንነት ስጦታ ስትቀበሉ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ስጦታ በልባችሁ የማትቀበሉ ከሆናችሁ ምንም ያህል ብትፍጨረጨሩ ከቶውኑም የእናንተ ሊሆን አይችልም፡፡
እኔም ብሆን ይህንን የደህንነት ስጦታ ተቀብያለሁ፡፡ ‹‹አሃ! ጌታ በዚህ መንገድ ለእኔ ተጠመቀ፡፡ እንደዚህ በመጠመቁ የሐጢያቶቼን ኩነኔ በሙሉ ተሸከመ፡፡ ስለ እኔ ሲል ፈጽሞ ተጠመቀ፡፡ አቤቱ አመሰግንሃለሁ!›› ያመንሁት ይህንን ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ሐጢያት አልባ ነኝ፡፡ ፍጹም የሆነውን የሐጢያት ስርየት ተቀብያለሁ፡፡ እናንተም ደግሞ ይህንን የሐጢያት ስርየት መቀበልና መዳን የምትወዱ ከሆናችሁ አሁኑኑ ተቀበሉት፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለዚህ የደህንነት ስጦታ ብዙውን ጊዜ አስቤያለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ስለዚሁ ነገር ደግሜ ሳስብ ጌታን ስለ መዳኔ ከማመስገን በቀር አንዳች ላደርገው የምችለው ነገር እንደሌለ እገነዘባለሁ፡፡ ይህ የደህንነት ፍቅር በልቤ ውስጥ ስላለ ከቶውኑም ልረሳው አልችልም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌልና በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውን እውነት በመቀበልና በማመን የሐጢያት ስርየቴን ስቀበል ከልክ በላይ እግዚአብሄርን አመስግኜዋለሁ፡፡ አሁንም እንኳን ብዙ ዓመታቶች ካለፉ በኋላ ይህ ዓይነቱ አመስጋኝ ልብ ስላለኝ በየቀኑ እየተደሰትሁ ነው፡፡
ኢየሱስ እኔን ለማዳን በእርግጥም ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ ሐጢያቶቼን በሙሉ በራሱ ላይ ለመውሰድ ተጠመቀ፡፡ የሐጢያቶቼን ኩነኔ ለመሸከም በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ለእኔ የተደረጉ መሆናቸውን ስገነዘብ ወዲያውኑ ተቀበልኋቸው፡፡ የራሴም አደረግኋቸው፡፡ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ያደረግሁት የተሻለው ነገርና ከድርጊቶች ሁሉ ጥበብ የተሞላበትና ብልህ የሆነው ድርጊት ይህ እንደነበር ሁልጊዜም እገነዘባለሁ፡፡ ስለዚህ ጌታ በእውነት እንደሚወደኝና እንደሚንከባከበኝ አምናለሁ፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደረገልኝ ስለወደደኝ መሆኑን አምኜም እመሰክራለሁ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ ምስጋናዬን ሁሉ ለአንተ እሰጣለሁ፡፡ አንተ እንደወደድኸኝ ሁሉ እኔም እወድሃለሁ፡፡›› እንደዚህ ብሎ መመስከር ዳግመኛ ለተወለደ ሰው ትልቅ ደስታ ነው፡፡
የጌታችን ፍቅር ለዘላለም የሚለወጥ አይደለም፡፡ እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅር ለዘላለም እንደማይለወጥ ሁሉ እኛ ለእርሱ ያለን ፍቅርም ሊለወጥ አይችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስንቸገርና መከራዎች ሲገጥሙን ልባችን ሊስት ይችላል፡፡ ይህንን ፍቅር ልንረሳና ልንከድም እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በስቃያችን ግራ ብንጋባና ሕሊናችንም ቢከዳን እንኳን የምናስበው ነገር ቢኖርም ስለ ስቃያችን ቢሆንም እንኳን ልባችን ከቶውኑም የእርሱን ፍቅር እንዳይረሳ እግዚአብሄር በታማኝነት ደግፎ ይይዘናል፡፡
እግዚአብሄር ለዘላለም ይወደናል፡፡ ጌታችን ፍጥረት ሆኖ ስለ እኛ ወደዚህ ምድር የመጣው እስከ ሞት ድረስ ስለወደደን ነው፡፡ አሁን ይህንን የእግዚአብሄር ፍቅር ራሳችሁ እንድታምኑት በአደራ እማጸናችኋለሁ፡፡ በልባችሁም ተቀበሉት፤ አሁኑኑ ታምናላችሁን?
ጌታ በዚህ ፍቅር ከሐጢያቶቻችን ፈጽሞ ስላዳነን አመሰግነዋለሁ፡፡