Search

Sermoni

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-6] በግርዘቱ ኪዳን ውስጥ የጸናው የእግዚአብሄር ተስፋ አሁንም ለእኛ ይሰራል፡፡ ‹‹ ዘፍጥረት 17፡1-14 ››

በግርዘቱ ኪዳን ውስጥ የጸናው የእግዚአብሄር ተስፋ አሁንም ለእኛ ይሰራል፡፡
‹‹ ዘፍጥረት 17፡1-14 ››
‹‹አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሄር ለአብራም ተገለጠለትና፡- እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ! በፊቴ ተመላለስ፡፡ ፍጹምም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፡፡ እጅግም አበዛሃለሁ አለው፡፡ አብራምም በግምባሩ ወደቀ፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- እነሆ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፡፡ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ፡፡ ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራም፡፡ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፡፡ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ፡፡ ሕዝብም አደርግሃለሁ፡፡ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ፡፡ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን አቆማለሁ፡፡ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ፡፡ በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር የከንዓን ምድር ሁሉ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፡፡ አምላክም እሆናቸዋለሁ፡፡ እግዚአብሄርም አብርሃምን አለው፡- አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፡፡ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው፡፡ በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ የቁልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በአንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፡፡ የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ፡፡ በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ፡፡ ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል፡፡ የቁልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቁላፍ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና፡፡››
 
 
በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ እግዚአብሄር ከአብርሃም ጋር የተጋባው የግርዘት ኪዳን እስራኤሎች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚያቀርቡት መስዋዕት ራስ ላይ እጆቻቸውን በመጫን ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ ወደ መስዋዕቱ የሚሻገሩበትንና የሚወገዱበትን መንፈሳዊ ግርዘት ያሳያል፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ከአብርሃም ጋር ያጸናው ቃል ኪዳን የሐጢያት መስዋዕትና የሚቃጠል መስዋዕት መግለጫ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ለአብርሃም እርሱና የዘሮቹ አምላክ እንደሚሆን የሰጠው የግርዘት ተስፋ ከመገናኛው ድንኳን ጋር ተያይዞ የአብርሃም ዘሮች ሐጢያቶቻቸውን እጆቻቸውን በመስዋዕቱ ቁርባኖች ላይ በመጫን ማሻገር እንደነበረባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደሚወስድ የሚያሳይ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ 
 
እግዚአብሄር ለአብርሃም ይህንን ተስፋ ሰጠው፡- ‹‹ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ክዋክብቶችን መቁጠር ትችል እንደሆነ ቁጠር፡፡…ዘርህም ንዲህ ይሆናል፡፡›› (ዘፍጥረት 15፡5) እግዚአብሄር እንደገና በአብርሃም ፊት ተገልጦ ተስፋ ሰጠው፡- ‹‹እጅግም አበዛሃለሁ፤ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ፡፡ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፡፡ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ፡፡›› (ዘፍጥረት 17፡6-7) 
 
እግዚአብሄር ለአብርሃምና ለዘሩ ያደረገው ቃል ኪዳን የመጣው ግርዘት አማካይነት ነው፡፡ ይህ ግርዘት እስራኤላውያን ለእግዚአብሄር መስዋዕታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ ከሚፈጽሙት የእጆች መጫን ጋር የተመሳሰለ ነው፡፡ ይህ ግርዘት በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች ሁሉ የወሰደበትን የሐጢያት ስርየት ፍጻሜም የሚተነብይ ነበር፡፡ እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ለአብርሃም የሰጠው የግርዘት ተስፋ በአዲስ ኪዳን በኢየሱስ ጥምቀት የተፈጸመውን ከሐጢያት የመንጻት መንፈሳዊ ግርዘት የሚጠቁም መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ በተጨማሪም እስራኤሎች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ መስዋዕትን በሚያቀርቡበት ጊዜ የአብርሃም እምነት እንደሚያስፈልጋቸውም ይነግረናል፡፡ 
 
እግዚአብሄር ለአብርሃም እንዲህ አለው፡- ‹‹የቁልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በአንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፡፡ የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ፡፡›› (ዘፍጥረት 17፡11-12) በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር በግርዘት አማካይነት ከአብርሃምና ከዘሮቹ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ የአብርሃምና የዘሩ አምላክ እንደሚሆን ቃል ገባ፡፡ ነገር ግን በምላሹ አብርሃምና ዘሮቹ መገረዝ ነበረባቸው፡፡ ‹‹በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ፡፡ ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል፡፡›› (ዘፍጥረት 17፡13) 
 
ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ በዓለም ላይ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የቁልፈታቸውን ሥጋ የተገረዙት እስራኤሎች ብቻ የነበሩት ለዚህ ነው፡፡ ዛሬ ከጤና ጠቀሜታዎቹ የተነሳ ግርዘት ተስፋፍቷል፡፡ በዚያን ጊዜ ግን የተገረዙት የእስራኤል ወንዶች ብቻ ነበሩ፡፡ ይህ እግዚአብሄር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ምልክት ነበር፡፡ እግዚአብሄርም እርሱንና ዘሮቹ የሆኑትን የእስራኤል ሕዝብ ከእነርሱ ጋር ያጸናውን የዚህን ቃል ምልክት በሥጋቸው እንዲሸከሙ አደረገ፡፡ 
 
ዘፍጥረት 17፡11 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የቁልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በአንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፡፡›› (ዘፍጥረት 17፡11) ጠቅለል አድርጎ ለማስቀመጥ እግዚአብሄር ተስፋውን የሰጠው እንደዚህ ነው፡- ‹‹እናንተ የእኔ ሕዝብ እንደሆናችሁ እንዴት ታውቃላችሁ? ይህንን የምታውቁት የግርዘታችሁን ጠባሳ በማየት ነው፡፡ ከአሁን ጀምሮ በመካከላችሁ የሚወለድ እያንዳንዱ ወንድ የቁልፈቱን ሥጋ መገረዝ አለበት፡፡ በዚህ መንገድ ቃል ኪዳኔ ለዘላለም ቃል ኪዳን ይሆን ዘንድ በሥጋችሁ ላይ ይሆናል፡፡ እኔም የእናንተና የዘራችሁ አምላክ ለመሆን ቃል እገባለሁ፡፡ እንደምባርካችሁ፣ እንደማበዛችሁ፣ ወደ ከንዓን ምድር እንደማስገባችሁ፣ ከዚያም ለዘላለም ትኖሩ ዘንድ እንደማደርጋችሁ፣ ከእናንተም ሕዝብንና ነገሥታትን እንደማወጣ ቃል እገባለሁ፡፡›› (ዘፍጥረት 17፡4-14) 
 
እግዚአብሄር ከአብርሃምና ከዘሮቹ ጋር ያጸናው ኪዳን በሥጋቸው ላይ እንደሚገኝ ተናግሮዋል፡፡ በሌላ አነጋገር የእግዚአብሄር ተስፋ በተገረዙት የእስራኤል ወንዶች ጠባሳዎች ላይ አትሞዋል፡፡ እግዚአብሄር በግርዘታቸው አማካይነት ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ ስለዚህ ሰዎች የአብርሃም ዘሮች መሆን አለመሆናቸው የሚታወቀው በመገረዛቸው ወይም በአለመገረዛቸው ነው፡፡ የተገረዙት የአብርሃም ዘሮች መሆናቸው ታውቆ ሲባረኩ ያልተገረዙት ግን በዚህ ሁኔታ አይታወቁም፡፡ 
 
 
አብርሃም በእርግጥም ለእስራኤል ሕዝብ በጣም አስፈላጊ ሰው ነበር፡፡
 
ለእስራኤል ሕዝብ የእምነት አባት የነበረው አብርሃም የሕግ አባት ከነበረው ከሙሴም በላይ እንኳን በጣም አስፈላጊ ሰው ነበር፡፡ ኖህን የማያስታውሱ ብዙ እስራኤላውያን ቢኖሩም አብርሃምን ማስታወስ የሚሳናቸው ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከእነርሱ ውስጥ ሴምን፣ ሴትን ወይም ማቱሳላን ማስታወስ የሚችሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ አብርሃም ግን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ የማይረሳ የእምነት አባት ሆኖ ቀርቷል፡፡ ሁሉም እርሱን የአገራቸው የእምነት አባት አድርገው ያውቁታል፤ ያምኑታል፤ ይከተሉታልም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በአብርሃም አማካይነት ከእስራኤሎች ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን አሁንም ይሰራል፡፡ 
 
የእስራኤል ሕዝብ ‹‹እኛ የአብርሃም ዘሮች ነን፡፡ ሕዝቦቻችን በሥጋቸው ላይ የግርዘትን ምልክት ይዘዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር አምላካችን ነው፡፡ እኛም የእርሱ ሕዝብ ነን›› ብለው በማመን በራሳቸው ሙሉ በሙሉ ተማምነዋል፡፡ እስራኤሎች ራሳቸውን የተመረጡ ሕዝብ አድርገው የሚቆጥሩት እግዚአብሄር በግርዘት አማካይነት ከአብርሃም ጋር ባጸናው ቃል ኪዳን አሁንም ስለሚያምኑ ነው፡፡ 
 
አብርሃም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፡፡ አንደኛዋ በኋላ ሣር ተብላ በእግዚአብሄር የተሰየመችው ሕጋዊ ሚስቱ ሦራ ስትሆን ሁለተኛይቱ ሚስቱ ደግሞ የሣራ ገረድ የነበረችው አጋር ነበረች፡፡ ሣራ ልጅ የማትወልድለት ይመስል ስለነበር አብርሃም የራሱን አስተሳሰቦች በማመን ከአጋር ልጅ ለማግኘት ፈለገ፡፡ (ዘፍጥረት 16፡1-4) እግዚአብሄር ግን ሣራ የአብርሃም ሕጋዊ ሚስት ስለሆነች ለአብርሃም እንደ ሰማይ ክዋክብት ብዙ የሆኑ ዘሮችን የሚሰጠው እርስዋ በምትወልደው ልጅ በኩል እንደሆነ ነገረው፡፡ እግዚአብሄር የራሱ ሕዝብ አድርጎ የሚቀበላቸው ከሣራ ማህጸን የወጡትን እንደሆነ ቃል ስለገባ ከሁለተኛዋ ሚስት ከአጋር የተወለደው እስማኤል በዚህ መንገድ በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ 
 
የእስራኤል ሕዝብ ባይገረዙ ኖሮ እግዚአብሄር ከእነርሱ ጋር የተጋባው ቃል ኪዳን ውጤታማ አይሆንም ነበር፡፡ እግዚአብሄር ይህ ኪዳን በሥጋቸው ላይ እንዲሆን የኪዳኑ ምልክት ይሆን ዘንድ እንዲገረዙ ነገራቸው፡፡ ስለዚህ እሰራኤላውያን ለመገረዝ እርግጠኞች ሆኑ፡፡ ምክንያቱም አለመገረዝ የእግዚአብሄርን ቃል ኪዳን ፉርሽ ያደርገዋልና፡፡ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ምናልባትም ያልተገረዘ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ያልተገረዘ ሰው ልክ እንደ አሕዛብ ስለሚቆጠር የእግዚአብሄር ቃል ኪዳን እንደማይመለከተው በሚገባ ያውቁ ነበርና፡፡
 
 

መንፈሳዊው ግርዘት፡፡

 
እግዚአብሄር ከአብርሃምና ከዘሮቹ ጋር ያጸናው ቃል ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደ ጊዜ በተፈጸመው የሐጢያቶች ስርየት አማካይነት ሙሉ በሙሉ ተከናውኖዋል፡፡ 
እግዚአብሄር ለእስራኤላውያን የመገናኛውን ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በርና የመሸፈኛውን መጋረጃ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ጠልፈው እንዲሰሩ ነገራቸው፡፡ (ዘጸዓት 26፡31፤27፡16) በዚህ ጥልቅ የመገናኛው ድንኳን ገጽታ አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስለሚመጣው ደህንነት አስተማረን፡፡ ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ በ30 ዓመቱ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በመውሰድ፣ በመስቀል ላይ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ ሁሉ እንደሰጠን በሚናገረው እውነት የሚያምኑ ሁሉ የአብርሃም ዘሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና በጥሩው በፍታ ለሚያምኑት አምላካቸው ሆንዋል፡፡ 
 
እኛ ሁላችን በኢየሱስ ጥምቀት በማመን በመንፈሳዊ ሁኔታ መገረዝ አለብን፡፡ መንፈሳዊ ግርዘት ሐጢያቶቻችን በሙሉ በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መሻገሩን በማመን በልቦቻችን ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች ማስወገድ ነው፡፡ (ሮሜ 2፡29) 
 
ስለዚህ ዛሬ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን የሐጢያት ስርየትን ያገኙ ሁሉ የእግዚአብሄር መንግሥት ነገሥታትና የራሱ ልጆች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹ነገሥታት ከአንተ ይወጣሉ›› (ዘፍጥረት 17፡6) በማለት ተስፋ እንደሰጠ ሁሉ የእርሱ ሕዝብ በእርግጥም በመላው ዓለም ላይ እየተነሱ ናቸው፡፡ 
 
እኛ የአብርሃም ዘሮች መሆን ከፈለግን ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ማመን ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ የኢየሱስን ጥምቀት ማወቅና ማመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፡፡ እርሱ ሐምራዊ መጎናጸፊያ ለብሶ የመጣ የነገሥታት ንጉሥ ነው፡፡ (ዮሐንስ 19፡5) ኢየሱስ ክርስቶስ የአጽናፈ አለማት ንጉሥና ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ ስለሆነ የአባቱን ፈቃድ በመታዘዝ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ እኛን ሊያድነንም በአንድ ጊዜ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፡፡ ሐጢያቶቻችንን ለመደምሰስም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ከልቦቻችን ውስጥ ቆርጦ በማውጣት በጥምቀቱ በራሱ ሰውነት ላይ ተሸከማቸው፡፡ በመስቀል ላይ ደሙን በማፈሰስም ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ተኮነነ፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት የሚያምኑ ሁሉ የአብርሃም ዘሮች መሆን ይችላሉ፡፡ 
 
አብርሃም፣ ቤተሰቡና ዘሮቹ ሁሉ በሥጋ ተገረዙ፡፡ ከአሕዛቦች በገንዘብ የተገዙ ባሮች እንኳን ተገርዘዋል፡፡ እነርሱ በኪዳኑ አምነው በተገረዙ ጊዜ እነዚህም ባሮች ተባረከዋል፡፡ እግዚአብሄርም ደግሞ የእነርሱ አምላክ ሆንዋል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ልጆች የምንሆነው በእምነት ነው፡፡ የምንባረከው በእምነት ነው፡፡ ሰማይ የምንገባው በእምነት ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ እንደ ነገሥታት የምንኖረውም በእምነት ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ይህ እምነት ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ መውሰዱን የሚያምኑ ሰዎች እምነት ነው፡፡ 
 
ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ይህ የኢየሱስ ጥምቀት ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያገኙት በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመናቸው እንደሆነ ያምናሉና፡፡ በመገናኛው ድንኳን ዘመን ይፈጸም በነበረው እጆችን በመስዋዕቱ ራስ ላይ መጫን ቢያምኑም በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ግን ብዙም ትኩረት አያደርጉም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ ምድር ከመምጣቱና የሙሴ ድንኳን ከመሰራቱ ከረጅም ጊዜ በፊት የአብርሃም እምነት በመጽደቁ ግልጽ በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ቃል ባያምኑም በመስቀሉ ደም ቃል በማመን ብቻ አሁንም መዳን እንደሚችሉ በግትርነት ይናገራሉ፡፡ 
 
ነገር ግን እግዚአብሄር ለአብርሃም የሦስት ዓመት ጊደር፣ የሦስት አመት እንስት ፍየል፣ የሦስት አመት አውራ በግ፣ ዋኖስና ርግብ እንዲያመጣለት -- ይህንን ሁሉ ያደረገው የከንዓንን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ ርስት አድርጎ እንደሚሰጠው አብርሃም ያውቅ ዘንድ ነበር -- እግዚአብሄር በእሳት የሚቃጠል መስዋዕት ፈለገ፡፡ ዘፍጥረት 15፡17 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጸሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፤ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ፡፡›› እግዚአብሄር የአቤልን መስዋዕትና እምነቱን ሲያፀድቅ በዚህ የሚቃጠል መስዋዕት እምነት ያልነበረውን የቃየንን እምነት አልተቀበለውም፡፡ 
 
በዛሬዎቹ ክርስቲያኖች መካከል በእምነት መንፈሳዊ ግርዘት ሳያገኙ በዕውር ድንብር በኢየሱስ በማመን ብቻ እንደዳኑ በተሳሳተ መንገድ የተረዱ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሐጢያቶቻቸው በሙሉ በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ የተሻገሩ የመሆናቸውን እምነት ሳያምኑ በኢየሱስ ስቅለት ብቻ ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በፍጹም የእግዚአብሄር የራሱ ሕዝብ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚህ መንገድ ማመን ሐጢያቶቻቸውን ከልቦቻቸው ውስጥ በፍጹም ሊደመስስላቸው አይችልምና፡፡ እግዚአብሄር የኪዳኑ ምልክት ያለው በተገረዙት ሥጋ ላይ መሆኑን ተናግሮዋል፡፡ ስለዚህ ያልተገረዙት ከዚህ የእግዚአብሄር ኪዳን ጋር አንዳች የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ 
 
ሰዎች ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ሳያምኑ ከሐጢያት መዳን ይችላሉን? እንደዚህ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄር ልጆች መሆን ይችላሉን? ሰማይ መግባት ይችላሉን? የመንግሥቱ ነገሥታቶችስ ሊሆኑ ይችላሉን? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ የማያወላዳ አይችሉም ነው! ዛሬ ያነበብነው ዋናው ምንባብ ለዚህ መልስ ግልጽ የሆነ መረጃ ይሰጣል፡፡ ዛሬ እግዚአብሄር ለአብርሃም ያደረገው ቃል ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አዳኛችን አድርገን ለተቀበልነው ለእናንተና ለእኔ የገባው ያው ቃል ኪዳን ነው፡፡ እንደዚህ የሚያምኑትን ለአብርሃም የተነገረው ያው የበረከቶች ቃል ይመለከታቸዋል፡፡
 
 

እውነተኛ የኢየሱስ አማኞች ራሳቸው የፈጠሩዋቸውን የእምነት ትምህርቶች አይከተሉም፡፡ 

 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው የእግዚአብሄር ቃል እውነተኛና ግልጽ የደህንነት እውነት ነው፡፡ አብዝተን ባነበብነውና ባሰላሰልነው ቁጥር ይበልጥ ተጨባጭና ግልጽ ይሆንልናል፡፡ በዛሬዎቹ ክርስቲያኖች መካከል በራሳቸው አስተሳሰቦች ላይ በመመርኮዝ እግዚአብሄርን በማመንና በመከተል የተሳሳተ እምነትን የያዙ ብዙዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የሚያምኑት በተጨባጭ ሐሰት መሆኑን አያውቁም፡፡ የእነዚህ ሰዎች እምነት መሰረት የተሳሳተ ነው፡፡ ኢየሱስ ሆነም ቀረም እንዳዳናቸው በዕውር ድንብር ማመን የራሳቸውን ሕሊና ለማርካት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ዕውር እምነታቸውን እንደማይቀበል መገንዘብ አለባቸው፡፡ 
 
ጌታችን እርሱን መከተል የሚፈልግ በመጀመሪያ ራሱን መካድና መስቀሉን መሸከም እንዳለበት ተናግሮዋል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል የሚያምን ሁሉ የራሱን አስተሳሰቦች ጥሎ የእግዚአብሄር ቃል በትክክል በሚናገረው ነገር ማመን አለበት፡፡ ዛሬ እናንተና እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመምጣት በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰድና በመሸከም ደሙን በመስቀል ላይ በማፍሰስና እንደገና ከሙታን በመነሳት በሰጠን የሐጢያት ስርየት ማመን አለብን፡፡ 
በዚህ ዘመን እንደዚህ የሚያምኑ ነገር ግን የራሳቸው የሆነ የእምነት መንገድ እንዳላቸው በመናገር በዕውር ድንብር የኢየሱስን ስም አጥብቀው የያዙ እጅግ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች እምነት በኢየሱስ ከተሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች በአንዳንድ ጥልቅ ተራራዎች ላይ እየጸለዩ ሳለ ኢየሱስ እንደተገለጠላቸው የሚናገሩና የዳኑትም በዚህ መንገድ እንደሆነ የሙጥኝ ብለው የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ ምሳሌ ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው በፆሙና ሌሊቱን ሁሉ በጸሎት በተጉ ጊዜ ሐጢያቶቻቸው በሙሉ እንደከሰሙ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም በንስሐ ጸሎቶቻቸው ሊያስወግዱዋቸው ባልቻሉዋቸው ሐጢያቶች ተሰቃይተው ነበርና፡፡ 
 
የዚህ ዓይነቱ እምነት በጌታችን በተሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል አማካይነት ብቻ ከሚገኘው እውነተኛ ደህንነት ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ የዚህ ዓይነት እምነት ቢኖረን ሐጢያቶቻችንን ይቅር እንደሚለን የእግዚአብሄር ቃል የሚናገረው የት ቦታ ላይ ነው? የለም! እነዚህ ሰዎች እግዚአብሄር ፍጹም እንደሆነና ኢየሱስም ሁሉን ቻይ እንደሆነ በደፈናው ስለሚያውቁ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ተበድረው ተዓማኒነት በሌለው እምነታቸው ላይ ጥራዝ ነጠቅና ያልተረጋገጠ ዕውቀታቸውን ጨምረዋል፡፡ በዚህም ሐጢያቶቻቸውን ረስተው የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ በመጥራት የእግዚአብሄርን ቁጣ ይበልጥ እያከማቹ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ልብ ወለዳዊ ኢየሱስና የራሳቸውን የደህንነት ትርጉም በመፍጠር በእነዚህ በራሳቸው የአስተሳሰብ ፍንጣቂዎች ያምናሉ፡፡ 
 
ዘፍጥረት 17፡14 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የቁልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቁላፍ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና፡፡›› እግዚአብሄር በመንፈሳዊ ግርዘት አማካይነት ከሐጢያቶቻችን እንደሚያድነን በግልጽ ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር የእርሱ ልጆች የሚሆኑት ከውሃና ከመንፈስ የተወለዱት ብቻ እንደሆኑ በማያሻማ መንገድ ቃል ገብቶልናል፡፡ ስለዚህ በጥምቀቱ ሳያምኑ በመስቀል ላይ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ብቻ የሚያምኑ ምንጊዜም ቢሆን የእግዚአብሄር ልጆች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሄርን ክደውታል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር ተስፋ በሰጠው ወንጌል አላመኑምና፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ሕዝብ መካከል ተለይተው ይጠፋሉ፡፡ በእርሱም የተረገሙ ይሆናሉ፡፡
 
ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን የሚችለው የእምነት መሰረት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል በጽናትና በሙላት ማመን የምንችለው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል መሰረታችን ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ልባቸው በመንፈሳዊ ሁኔታ ሳይገረዝ መንፈሳዊ አሕዛቦች የሆኑ የእግዚአብሄርን ቃል እንዴት በልባቸው ውስጥ ሊያኖሩ ይችላሉ? በጭራሽ ይህንን ማድረግ አይችሉም! የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በመንፈሳዊ ሁኔታ እንድንገረዝ በመፍቀድ የእግዚአብሄር ልጆች እንድንሆን ያስችለናል፡፡ ይህ እውነተኛው መሰረት ከሌለን የእግዚአብሄር ቃል ወደ እኛ የሚመጣው የአእምሮ እውቀት ብቻ ሆኖ ነው፡፡
 
ዳግመኛ የተወለዱ ባሮች የሚያስተምሩዋቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች በመሰረታዊ መልኩ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምኑ ብቻ የሚስተዋለውና ተቀባይነት የሚያገኘው ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእግዚአብሄርን ቃል ሰምተው መረዳት የሚችሉት ዳግመኛ የተወለዱት ብቻ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁ በመስቀሉ ደም በማመን ብቻ ዳግመኛ እንደተወለዱ የሚናገሩ ሰዎችን ስናገኝ ምንም እንኳን በአንድ አምላክ እንደምናምን ቢናገሩም እኛ ግን ፈጽሞ ልዩ ስለሆነ አምላክ እየተናገርን ያለን ይመስለናል፡፡ እዚህ ላይ እውነተኛው አምላክ ማነው? እውነተኛው አምላክ የተስፋውን ቃል ለአብርሃም የሰጠው አምላክ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ለአብርሃምና ለዘሩ ይህንን ተስፋ ሰጠ፡- ‹‹ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል፡፡›› (ዘፍጥረት 17፡13) ለሐጢያቶቻችን ስርየትን እንደተቀበልን የሚነግረን ምልክት ያለው የት ነው? የሚገኘው በልባችን ውስጥ ነው፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት በልባችን በማመን የእርሱ ልጆች ሆነናል፡፡ ልባችንም በእውነተኛው ወንጌል በማመን መንፈሳዊ ግርዘትን ተቀብሎዋል፡፡ ጌታ ከሐጢያቶቻችን የተነሳ እነዚህን ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመውሰድ መጠመቁን በልባችን በማመንና መንፈሳዊ ግርዘትን በማግኘት የእርሱ ልጆች ሆነናል፡፡
 
ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወደ ኢየሱስ ያሻገርነው በዚህ እውነት በማመናችን ነው፡፡ ኢየሱስም ደግሞ እነዚህን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ በመሸከም በእኛ ፋንታ ተሰቀለ፤ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉም አዳነን፡፡ በሌላ አነጋገር ሐጢያት አልባ የሆንነው በእምነት ነው፡፡ ታዲያ በውስጣችን የቀረ አንዳች ሐጢያት አለን? በእርግጥም የለም! ምንም ዓይነት ሐጢያት የለብንም! ይህ ሁሉ በእውነትም አስገራሚ በሆነው ወንጌል ተፈጽሞዋል፡፡
 
 

እናንተና እኔ የአብርሃም ዘሮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? 

 
የአብርሃም ዘሮች የሆንነው በመገናኛው ድንኳን ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ጥሩ በፍታ በተገለጡት የኢየሱስ ሥራዎች በማመን መንፈሳዊ ግርዘትን ያገኘነውና የእግዚአብሄር ልጆች የሆንነው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ስላመንን ነው፡፡ የሐጢያት ስርየትን የተቀበልነው ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እንደወሰደና ለሐጢያቶቻችንም ሁሉ በመስቀል ላይ እንደተኮነነ ስላመንን ነው፡፡ እናንተና እኔ በመንፈሳዊ መልኩ የአብርሃም ዘሮች የሆንነው በዚህ መንገድ ነው፡፡
 
ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ የተወለዱ በእርግጥ ማን እንደሆኑ ማወቅ አለባቸው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያመንን እናንተና እኔ በእምነት መንፈሳዊ ግርዘትን ያገኘን የእግዚአብሄር ልጆችና የራሱ ሕዝብ ነን፡፡
 
እኛ በመጭው የሺህ ዓመት መንግሥት ውስጥ በእግዚአብሄር ፍጥረቶች ሁሉ ላይ የምንነግስና በእርሱ ክብር የምንደሰት ነገሥታት ነን፡፡ አሁን ማዕረጋችን የተለወጠው በዚህ መንገድ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች በእርግጥ እኛ ማን እንደሆንን ያውቃሉን? አያውቁም፡፡ እኛ ግን በእግዚአብሄር ቃል በማመናችን መንፈሳዊ ማዕረጋችን የተለወጠ ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ አሁን ማንነታችንን በግልጽና ያለ ምንም አሻሚ ሁኔታ ማወቅ እንችላለን፡፡
እነዚያ በእግዚአብሄር ቃል ዳግመኛ የተወለዱ በትክክል ማን እንደሆኑ ያውቃሉ፡፡ እኛ በዓለማዊ የሐይማኖት ማህበረሰቦቻቸው ውስጥ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ከሚያዘነብሉ፣ ፈጽሞ ዕውቀት ስለሌላቸው የሐሰት ትምህርቶችን ከሚሰብኩና እውነተኛ የእግዚአብሄር ሕዝብ የሆኑትን ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች በጎሪጥ ከሚያዩት ፈጽመን የተለየን ነን፡፡ የእስራኤል ሕዝቦች ምርጥ ሕዝብ መሆናቸውን በማመን የእስማኤልን ዘሮች በተለየ መንገድ እንደተመለከቱዋቸው ሁሉ እኛም የአብርሃም መንፈሳዊ ዘሮች የሆንን ራሳችንን የእግዚአብሄር ምርጥ ሕዝብ አድርገን የመመልከት መብት አለን፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ የምናምን ሰዎች በእምነታችን አማካይነት የአብርሃም ዘሮች በመሆናችን ዕድለኞች ነን፡፡ በመገናኛው ድንኳን ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው ወንጌል ላይ ባለን እምነት መንግሥተ ሰማይ መግባት እንችላለን፡፡
 
እግዚአብሄር ለአብርሃም ዘሩን እንደ ሰማይ ክዋክብት እንደሚያበዛለት ቃል እንደገባለት ሁሉ ይህ ቃል ኪዳን በትክክል ሲፈጸም በዓኖቻችንን ማየት እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን በረከት ይህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር በልባችን መገረዝ ከዓለም ሐጢያቶች አዳነን፡፡ ይህ የእምነት ግርዘት የተከናወነውም ለመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር በሚያገለግለው ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ነው፡፡