Search

Sermoni

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-33] ከግራር እንጨት ተሠርቶ በናስ የተለበጠው የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ፡፡ ‹‹ዘጸዓት 38፡1-7››

ከግራር እንጨት ተሠርቶ በናስ የተለበጠው የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ፡፡ 
‹‹ዘጸዓት 38፡1-7›› 
‹‹ርዝመቱ አምስት ክንድ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠውያን ከግራር እንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበረ፤ ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፡፡ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ነበሩ፡፡ በናስም ለበጠው፡፡ የመሠውያውንም ዕቃ ሁሉ ምንቸቶቹንም፣ መጫሪያዎቹንም፣ ድስቶቹንም፣ ሜንጦዎቹንም፣ ማንደጃዎቹንም አደረገ፡፡ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ፡፡ እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠውያው አደረገ፡፡ መከታውም እስከ መሰውያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠውያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው፡፡ ለናሱም መከታ ለአራቱም ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ፡፡ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አደረገ፡፡ በናስም ለበጣቸው፡፡ ይሸከሙትም ዘንድ በመሠውያ ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፡፡ ከሣንቆቹም ሠርቶ ባዶ አደረገው፡፡››
 


እያንዳንዱ ሐጢያተኛ በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ላይ መሥዋዕትን ማቅረብ ነበረበት፡፡ 


በእስራኤል ሕዝብ መካከል የሚገኝ ማንኛውም ሐጢያተኛ ከሐጢያቶቹ ለመላቀቅ ወደ መገናኛው ድንኳን የመሥዋዕት እንስሳ ማምጣት፣ እጆቹን በራሱ ላይ በመጫንም ሐጢያቶቹን ማሻገር፣ ደሙን ማፍሰስና ከዚያም ይህንን ደም ለካህኑ መስጠት ነበረበት፡፡ ከዚያም በመደበኛ ሥራው ላይ ያለው ካህን ይህንን የመስዋዕቱን እንስሳ ደም በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ ስቡንና ስጋውንም በመሠውያው ላይ ያስቀምጥና ለእግዚአብሄር አምላክ ጣፋጭ ሽታ ይሆን ዘንድ በእሳት ያቃጥለዋል፡፡ ሊቀ ካህኑም ቢሆን የሐጢያቶቹን ስርየት ለማግኘት መሥዋዕት በቀረበው እንስሳ ላይ እጆቹን በመጫን በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ፊት ወዳለው እንስሳ ሐጢያቶቹን ማቅረብ ነበረበት፡፡ ይህ ከግራር እንጨት ተሠርቶ በናስ በተለበጠው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠውያ ላይ የሚቀርብ የስርየት መስዋዕት ነበር፡፡ ይህ የሐጢያቶች ስርየት የሚያስገኘው መሥዋዕት ሊቀርብ የሚችለው በእጆች መጫንና ደምን በማፍሰስ አማካይነት ብቻ ነበር፡፡
እግዚአብሄር ዓለም ሳይፈጠር በፊት በእጆች መጫንና ደምን በማፍሰስ አማካይነት እያንዳንዱን ሰው ከሐጢያቶቹ ሁሉ ለማዳን አስቀድሞ የደህንነትን መንገድ አቀደ፡፡ እግዚአብሄር አብ ደህንነታችንን ካቀደ በኋላ ልጁን ወደዚህ ምድር መላክ፣ በአጥማቂው ዮሐንስ መጠመቅና ደሙንም በመስቀል ላይ እንዲያፈስስ ማድረግ ነበረበት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ሐጢያተኛ ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ የተቀበለው ለዚህ ነው፡፡ ይህም ከብሉይ ኪዳን እጆች መጫን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ለመውሰድና በእኛ ፋንታም በመስቀል ላይ ደሙን ለማፍሰስ የእነዚያን ሐጢያቶች ሁሉ ኩነኔ መሸከም ነበረበት፡፡
በናስ የተለበጠው የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ እግዚአብሄር ያለ ምንም መሳሳት በእያንዳንዱ ሰው የልብ ጽላት ላይ የተጻፈውን እያንዳንዱን ሐጢያት እንደሚኮንን ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሐጢያተኛ እጆቹን በራሱ ላይ በመጫን ሐጢያቶቹን ለመሥዋዕት ባቀረበው እንስሳ ላይ ማሻገር፣ አንገቱን መቁረጥና ደሙን ማፍሰስ ነበረበት፡፡ ካህኑም የእንስሳን ደም በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ቀንዶች ላይ ማኖር ነበረበት፡፡ ስለዚህ በናስ የተለበጠው የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እነደተሸከመና ለእነዚህ ሐጢያቶችም በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ እንደተኮነነ አስታውቆናል፡፡


የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ትርጉም፡፡

 
የመሥዋዕት እንስሳ ለእግዚአብሄር በሚቀርብበት ጊዜ ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ለእግዚአብሄር ጣፋጭ ሽታ ይሆን ዘንድ ስጋው መቆራረጥና በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ላይ መቅረብ ነበረበት፡፡ እግዚአብሄር አብ ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠምቆ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ በእኛ ፋንታ መሰቀሉን በማየቱ በጣም ተደስቶ ነበር፡፡ እግዚአብሄር አብ ይህ ነውር የሌለበት ኢየሱስ ለሐጢያተኞች ሁሉ የዘላለም ማስተሰርያ ሆኖ ራሱን መስዋዕት በማድረጉ ተደሰተ፡፡
በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ላይ የቀረቡት እነዚህ መሥዋዕቶች እግዚአብሄር እያንዳንዱን ሐጢያተኛ ከሐጢያቶቹ ሁሉ እንዴት እንዳዳነው ያሳያሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ሰብዓዊ ዘር ከሐጢያቶቹና ከኩነኔ የዳነበትን ደህንነት ይገልጣል፡፡ እያንዳንዱ ሐጢያተኛ በሲዖል ወዳለው የእሳትና የዲን ባህር መጣል እንዳለበት ያሳየናል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እያንዳንዱ ሐጢያተኛ እንዴት ከሐጢቶቹ መዳን እንደሚችልም ያሳየናል፡፡ ስለዚህ ሐጢያት ያለበት ማንኛውም ሰው ወደ ሲዖል እሳት መጣል ስላለበት እያንዳንዱ ሐጢያተኛ ያለ ማመንታት የእግዚአብሄርን ምህረት ማግኘት አለበት፡፡
በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ላይ የሚቀርበው እያንዳንዱ የመሥዋዕት እንስሳ የሐጢያተኛውን ሐጢያቶች መሸከምና ለእነዚህ ሐጢያቶችም መኮነን ነበረበት፡፡ በሌላ አነጋገር ለመሥዋዕት የቀረበው እንስሳ በእጆች መጫን አማካይነት የአንድን ሰው ሐጢያቶች ተቀብሎ በእርሱ ፋንታ ደሙን ማፍሰስ ነበረበት፡፡ መሥዋዕቱ ሐጢያተኛው የሚጋፈጠውን የሐጢያት ኩነኔ ተሸክሞዋል፡፡ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተሰዋው ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ተቀብሎ በእኛ ፋንታ ደሙን እንዳፈሰሰ ያስተምረናል፡፡
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ዕቃ እግዚአብሄር ለእኛ የሰጠውን የሐጢያቶች ይቅርታ እንዴት እንደፈጸመው ያሳየናል፡፡ ስለዚህ ግልጥ የሆነውን የደህንነታችሁን መስመር ለማስመር በመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች በተገለጠው እውነት ትክክለኛ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ታዲያ የእምነታችሁን መስመር ማስመር የሚኖርባችሁ እንዴት ነው? በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተደበቀው የደህንነት እውነት በማመን ግልጥ የሆነ የደህንነት መስመር ማስመር አለባችሁ፡፡ በእውነት ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ ሊቀርቡና እምነታቸውን በትከክል ሊኖሩ የሚችሉት የዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
እግዚአብሄር ሐጢያተኞች ወደ መቅደሱ መግባት ይችሉ ዘንድ ለሐጢያቶቻቸው ማስተሰርያ የሚሆን መሥዋዕት አዘጋጀ፡፡ ሊቀ ካህኑም ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ለማዳን በእነርሱ ምትክ የስርየት መስዋዕት አቀረበ፡፡ እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የደህንነት ተስፋውን ፈጸመ፡፡ ስለዚህ እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት በማመን ይህንን እምነታችንን መኖር አለብን፡፡ አሁን እምነታችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያረፈ ነውን? እናንተ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ትድኑ ዘንድ ከሙሉ ልባችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለባችሁ፡፡ እውነተኛውን የሐጢያቶች ስርየት መቀበል የሚቻለው በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተመሰከረው መሰረት በውሃውና በመንፈሱ ቃለ ወንጌል እምነት ሲኖራችሁ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ በብሉይ ኪዳኑ የመገናኛው ድንኳን በታየው ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ የተገለጠው የደህንነት እውነት ሁሉ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተገለጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ውስጥ ተካቷል፡፡ ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል ትቆማላችሁን? ወይስ በመስቀሉ ደም ላይ ብቻ የሚያተኩረውን ወንጌል ትደግፋላችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደተጠመቀና ደሙን እንዳፈሰሰ በሚያውጀው ወንጌል ታምናላችሁን?
በብሉይ ኪዳን ዘመን የመገናኛው ድንኳን የመሥወዕት ስርዓት ከዓለም ሐጢያቶች እንደሚያድነን ለእኛ ቃል የገባበት የደህንነት ኪዳን ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግልጥ የሆነውን የደህንነት ዕቅዱን ለመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር በተጠለፈው ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ጥሩ በፍታ አማካይነት ገልጦዋል፡፡ በዚህ በር ውስጥ መግባት የሚፈልግ ሰው ሁሉ በእነዚህ ቁሳ ቁሶች በተገለጠው እውነት ማመን ነበረበት፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የእስራኤል ሕዝብ እጆቻቸውን በመሥዋዕት እንስሶቻቸው ላይ ጭነው ሐጢያቶቻቸውን ወደ እርሱ በማሻገርና ደሙንም ለእግዚአብሄር በማቅረብ በመገናኛው ድንኳን በሚቀርበው መሥዋዕት አማካይነት እንዲድኑ ፈቀደ፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የሐጢያቶች ስርየት የሚገኘበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ሕዝቦች ይህንን ወንጌል በሚገባ ተረድተው ያመኑበት ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሁሉ ግን ገና ወደፊት ከእግዚአብሄር ሕዝብ እንደ አንዱ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ለመገናኛው ድንኳን አደባባይ ጥቅም ላይ በዋሉት በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠው እውነት የአዲስ ኪዳኑ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ስለሆነ ነው፡፡
ጌታችን በዮሐንስ 3 ላይ ለኒቆዲሞስ እንዲህ አለው፡- ‹‹ሰው ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› እዚህ ላይ ውሃ የሚያመለክተው ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት እንደሆነ ማወቁ ለሁላችንም አስፈላጊ ነው፡፡ በእምነት በእግዚአብሄር ዕቅፍ ውስጥ የምንገባው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስንረዳ ብቻ ነው፡፡

 
እያንዳንዱ ሰው ለሐጢያቶቹ ከመኮነን እንደማያመልጥ መገንዘብ አለበት፡፡


በማርቆስ 7፡21 ጀምሮ እንደተገለጠው ሁሉም ሰው ከልቡ የሚወጡ እነዚያው ተመሳሳይ አስራ ሁለት ሐጢያቶች አሉበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰው የሚያስባቸው ክፉ አስተሳሰቦች በእግዚአበሄር ፊት ሐጢያት ናቸው፡፡ መግደል፣ ምንዝርና፣ ስርቆት፣ መመኘት፣ ክፋት፣ ትዕቢት፣ ስንፍናም እንደዚሁ ሁሉም ሐጢያቶች ናቸው፡፡ በሰዎች ልቦች ውስጥ ያሉት ክፉ አሳቦች የእግዚአብሄርን ቅድስና የሚያሰናክሉ ተጨባጭ የሐጢያት ምንጮች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር አዳምን ዘላለማዊ ፍጥረት አድርጎ በአምሳሉ ቢፈጥረውም አዳም በእግዚአብሄር ላይ ሐጢያትን ሠራ፡፡ ከዚህ የተነሳ የአዳም ዝርያዎች የሆንን ሁሉ ከእግዚአብሄር ኩነኔ ማምለጥ የማንችል ሐጢያተኞች ሆነን ተወለድን፡፡ ሁላችንም የመጀመሪያው ሰው የአዳም ዝርያዎች በመሆናችን የውርስ ተፈጥሮዋችን ሐጢያትን በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊቶች ከመሥራትና የእግዚአብሄርን ቅድስና ከማጉደፍ በቀር አንዳች የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ሐጢያት እንሠራለን፡፡ በእርግጥም ሰብዓዊ ፍጡራን በሙሉ በተፈጥሮዋቸው አተሳሰቦቻቸው በመሠረቱ ክፉ ናቸው፡፡ ሁልጊዜም የእግዚአብሄርን ቅድስና የሚቃወሙና በቀላሉ በሰይጣን የሚታለሉ ተሰባሪ ፍጡራን ናቸው፡፡
እግዚአብሄር ከሰው ልብ ውስጥ ክፉ አሳቦች እንጂ ሌላ አንዳች ነገር እንደማይወጣ ተናግሮዋል፡፡ በእርግጥ እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር በማርቆስ 7 ላይ እንደተዘረዘረው ከመግደል ጀምሮ እስከ ምንዝርና፣ ስርቆት፣ መመኘት፣ ዝሙት፣ ስንፍናና ወ.ዘ.ተረፈ ድረስ በአስራ ሁለት ዓይነት ሐጢያቶች ተሞልቶ ጎስቋላ ሐጢያተኛ ሆኖ ተገልጦዋል፡፡ የእያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ ሰውኛ ተፈጥሮ በክፉ አስተሳሰቦች የተሞላ ነው፡፡ እጅግ ብዙ ሰዎችም በሐይማኖታዊ ቅድስናቸው የእግዚአብሄርን ቅድስና እየተቃወሙ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ያለ ምንም ማመንታት ስለ ሐጢያቶቻችን በእግዚአብሄር መኮነን ነበረብን፡፡ በመገናኛው ደንኳን ውስጥ በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ላይ በየቀኑ ያለ ማቋረጥ የመሥዋዕት እንስሶች መቃጠል የነበረባቸው ለዚህ ነው፡፡ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ በሚቃጠል ስጋና በሚነድድ የእንጨት ጢስ ሽታ የተሞላ ነበር፡፡
 


ርኩሰታችንን በናሱ የመታጠቢያ ሰን ውስጥ ባለው ውሃ ታጥበን ማስወገድ አለብን፡፡ 


የብሉይ ኪዳን ካህናት ሁልጊዜም በሚቃጠለው ስጋና በሚጤሰው ጥቁር ሽታ የተከበቡ ነበሩ፡፡ ፊቶቻቸው በጢስ ስለሚጠቁርና ሰውነታቸውም በጥላሸት ስለሚሸፈን ንጹህ መሆን ያዳግታቸዋል፡፡ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ ያለው የናሱ መታጠቢያ ሰን ያስፈለገው ራሳቸውን ለማጠብ ነበር፡፡ ካህናቱ በየቀኑ በናሱ የመታጠቢያ ሰን ውስጥ ባለው ውሃ በመታጠብ ቆሻሻቸውን ማስወገድ ነበረባቸው፡፡
ይህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያለው የናሱ የመታጠቢያ ሰን በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ማስወገድ እንደነበረበት ይጠቁማል፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህናት ሰውነታቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ባለው የመታጠቢያው ሰን ውሃ መታጠብ ያለባቸው የመሆኑ እውነታ የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ይህ ጥምቀት በመስቀል ላይ እንዳፈሰሰው ደሙ ለደህንነት ሥራው ያን ያህል አስፈላጊ ነው፡፡ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለማስወገድ ፈጽሞ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ነበር፡፡ ያለዚህ ጥምቀት ማንም ሰው መንጻት አይችልም፡፡ ካህናት ቅድስናቸውን ጠብቀው ማቆየት የቻሉት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚያገለግሉበት ጊዜ የተጠራቀመውን ቆሻሻቸውን ሁሉ ወደ ናሱ የመታጠቢያው ሰን ሄደው መታጠብ በመቻላቸው ነው፡፡
ካህናቱ በናሱ የመታጠቢያ ሰን ውስጥ በመታጠብ ቆሻሻቸውን ማስወገዳቸው ሰው ሐጢያተኛ ማንነቱን ማመንና እያንዳንዱ ሰው በሐጢያቶቹ ምክንያት በእግዚአብሄር ተኮንኖ እንደሚጠፋ መገንዘብ ያለበት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በሐጢያቶቻችሁ ምክንያት እንደምትኮነኑና ለዘላለም ለመሰቃየትም ወደ ሲዖል እሳት እንደምትጣሉ በእግዚአብሄር ፊት ስታምኑ የደህንነት መንገድ ይከፈትላችኋል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ፊት ልትቀርቡ የምትችሉበት ብቸኛው መንገዳችሁ ሐጢያቶቻችሁን ማመንና ኢየሱስ ለእናንተ በፈጸመው ትክክለኛ የደህንነት እውነት ማመን ነው፡፡ መሲሁ በተጨባጭ ወደዚህ ምድር የመጣው እናንተንና እኔን ከዓለም ሐጢያቶች ለማዳን ነው፡፡ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅም በተጨባጭ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ተሸክሞዋል፡፡ በእኛ ፋንታም በመስቀል ለይ ተኮንኖዋል፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት ይህ ነው፡፡ ይህ ልናምንበት የሚገባን ፈጽሞ አስፈላጊ የሆነ የደህንነት እውነት ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ክፉ አሳቦችን ያስባል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ሌሎችን የመጉዳት፣ የማሰቃየትና የመግደል ክፉ ምኞት ይመኛል፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን ምን ያህል ክፉና ብልሹ እንደሆኑ መገንዘብ አለባችሁ፡፡ ታዲያ ሰዎች እንደዚህ ክፉ የሆኑት ለምንድነው? ሁልጊዜም ክፉ አሳቦችን በማሰብና ሁልጊዜም ሐጢያትን በመሥራት በተፈጥሮዋቸው የክፉ አድራጊዎች ዘር ስለሆኑ ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን ሁልጊዜም እነዚህን አስራ ሁለት ዓይነት ሐጢያቶች ስለሚፈጽሙ በማንኛውም ጊዜ እንደሚፈነዳ ቦምብ ናቸው፡፡ በእርግጥም እርስ በርሳቸው በተደጋጋሚ በመዋሸት፣ እርስ በርስ በመሰራረቅ፣ በማመንዘርና በመዘሞት የእግዚአብሄርን ክብር በመስደብና ስንፍናንና ዕብደትን በመውደድ ሁልጊዜም ክፋትን ያደርጋሉ፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን በተፈጥሮዋቸው የክፉ አድራጊ ዘሮች ስለሆኑ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ክፉ አሳቦችን ያስባሉ፡፡ የእግዚአብሄርንም ጽድቅ ይቃወማሉ፡፡ 
 

እኛ በእግዚአብሄር ፊት ምን ያህል ክፉዎች ነን? 

በእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮ ውስጥ ራስ ወዳድነት አለ፡፡ ሳይንቲስቶች አንድ ሰው ከአንድ ትሪሊዮን ሴሎች በላይ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ እነዚህ የማይቆጠሩ ሴሎች እያንዳንዳቸው በጣም ራስ ወዳድ ከመሆናቸው የተነሳ ለሌላው አያስቡም፡፡ ሰው በእጅጉ ራስ ወዳድ ፍጡር የሆነው ለዚህ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው በዘረ መል እንዲህ ራስ ወዳድ ይሆን ዘንድ ስለተደረገ የሰውን ባህርይ የሚቆጣጠሩ ማህበራዊ ድንጋጌዎችና ሕጎች ባይኖሩ ኖሮ ማንም በዚህ ምድር ላይ መኖር አይችልም ነበር፡፡ ሰዎች በጣም ራስ ወዳዶች ስለሆኑ እንዲህ ዓይነት ሕጎች ባይኖሩ ኖሮ እርስ በርሳቸው ይጨራረሱ ነበር፡፡ አብሮ የመኖር ሕጎችን ያወጡት አብረው ለመኖር እንዲችሉ ነው፡፡ ማህበራዊ ድንጋጌዎችና ሕጎች የወጡት ለዚህ ነው፡፡ ማህበራዊ ድንጋጌዎች የተፈጠሩት የሰውን አጥፊ ዝንባሌ ለመቆጣጠርና ይበልጥ የጋራ ስምምነትን ለማጎልበት ነበር፡፡ በአጭሩ ሰዎች ክፉዎችና ዓመጸኞች ስለሆኑ ባህሪያቸውን የሚቆጣጠሩና ክፉ ዝንባሌዎቻቸውን የሚገቱ ማህበራዊ ድንጋጌዎችንና ሕጎችን ማቋቋም አስፈላጊ ነበር፡፡ ክፋት በዓለም ላይ ይበልጥ በገነነ መጠን ማህበራዊ ድንጋጌዎችንና ሕጎችን መመሥረቱ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡
በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛችሁ አድርጋችሁ ማመንና ወደ እግዚአብሄር አብ ፊት መቅረብ የምትፈልጉ ከሆናችሁ በመጀመሪያ ያለ ምንም ማመንታት በዋናነት በተፈጥሮዋችሁ ክፉዎች መሆናችሁን መረዳት፣ ፈጽሞ ብልሹ የሆናችሁና ለሲዖል የታጫችሁ ሐጢያተኞች መሆናችሁን መቀበልና ከዚያም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን አለባችሁ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ማመንና የሐጢያቶቻችሁን ሁሉ ስርየት መቀበል አለባችሁ፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ ቢሆንም ሰዎች ግን ፈጽሞ ክፉዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም ሐጢያት ይሠራሉ፡፡ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠሩ ቢሆኑም የእርሱን ቅድስና የሚሳደቡ ተሳዳቢዎች ናቸው፡፡ ሰዎች መዳን የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሙሉ ልባቸው በማመን ብቻ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ልትድኑ የምትችሉት የኢየሱስ ክርስቶስን ጽድቅ ስትፈልጉት፣ ስትረዱትና ስታምኑበት ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ መሻትና ‹‹አቤቱ እኔ ሁልጊዜም ሐጢያተኛ መሆኔን አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜም በጉድለቶች የተሞላሁ ነኝ፡፡ በተደጋጋሚ ሐጢያት እሠራለሁ፡፡ ስለዚህ በሲዖል ውስጥ መቀጣት ይገባኛል፡፡ አንተ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ያቀረብከው ደህንነት ለእኔ ፈጽሞ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት እንዳዳንከኝ አምናለሁ›› በማለት በጸጋው ማመን አለባችሁ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶሰ ጽድቅ ማመን የሚችሉት ድካሞቻቸውንና ሐጢያተኝነታቸውን የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡
ሶቅራጥስ የተነቃቃው ‹‹ራስህን ዕወቅ!›› በምትልና በመታጠቢያ ክፍል ግድግዳ ላይ በነበረች ጥቅስ ነበር ይባላል፡፡ ይህች ቀላል ጥቅስ በአእምሮው ውስጥ የነበረውን ነገር ስላጋለጠች በሶቅራጥስ ላይ የማይፋቅ ተጽዕኖ አሳደረች፡፡ ስለዚህ ሶቅራጥስ በሥነ ምግባር የታነጸና አዋቂ ነኝ ብሎ እያሰበ የሚያስመስል ሰው ባየ ቁጥር ይህንን ሰው ‹‹በመጀመሪያ ራስህን ዕወቅ!›› በማለት ይመክረው ነበር፡፡ ይህች ቀላል አባባል ብቻዋን ሶቅራጦስን እስከ ዘሬ ድረስ የሚታወስ ታላቅ ፈላስፋ አደረገቸው፡፡
ሐጢያተኛ ማንነታችሁን መገንዘብ፣ ለእነዚህ ሐጢያቶችም ዋጋ ይሆን ዘንድ ወደ ሲዖል እንደምትጣሉ ማወቅና ይህንን በልባችሁ ማመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚገባውን ያህል አበክሬ አልተናገርሁም፡፡ በመጀመሪያ እናንተ በእግዚአብሄር ፊት ምን ያህል ብልሹ ሐጢያተኞች እንደሆናችሁና በቀጥታ ሲዖል ከመግባት የማታመልጡ እንደሆናችሁ ካልተረዳችሁ በስተቀር የእግዚአብሄርን ጽድቅ በትክክል መገንዘብ አትችሉም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በቅድሚያ የሐጢያቶቹን ውጤቶች ማመን አለበት፡፡ የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ከግራር እንጨት የተሠራ ነበር፡፡ ውጭያዊ ክፍሉም በናስ የተለበጠ ነበር፡፡ ይህም እያንዳንዱ ሰው ለሐጢያቶቹ መኮነን እንደሚኖርበትና እያንዳንዱ ሐጢያተኛም ወደ ሲዖል ከሚያደርገው ጉዞ ለማምለጥ አቅም እንደሌለው የሚጠቁም ነው፡፡ ነገር ግን በራሳቸው ፈጽሞ አቅም እንደሌላቸው የሚያውቁ ሰዎች የኢየሱስን ጽድቅ አክብረው በፍቅሩ ማመን ይችላሉ፡፡
እዚህ ላይ ወደ ሉቃስ 18፡10-14 እንሂድ፡- ‹‹ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ፡፡ ፈሪሳዊውም ቆሞ በልቡ ይህንን ሲጸልይ እግዚአብሄር ሆይ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ ቀማኞችና ዓመጸኞች አመንዝሮችም ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሠግንሃለሁ፡፡ ከማገኘውም ሁሉ አስራት አወጣለሁ አለ፡፡ ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሳ እንኳ አልወደደም፡፡ ነገር ግን አምላክ ሆይ እኔን ሐጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር፤ እላችኋለሁ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል፡፡›› 
በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ሰውን ሁሉ በጽድቅ እንዲኖር እያስተማሩ በውጫዊ ገጽታቸው በጣም ሐይማኖተኞች ነበሩ፤ነገር ግን ስርቆት ወይም ምንዝርና ፈጽመው አያውቁምን? በእርግጥም ያውቃሉ! ፈሪሳውያን ከውጭ ሲታዩ ጥሩዎች ቢመስሉም ማንም ሳያያቸው ከማንኛውም ሰው ይልቅ በጣም የበዙና አስከፊ ሐጢያቶች ፈጽመዋል፡፡ ይህም ሆኖ ራሳቸውን ሐጢያተኞች እንዳይደሉ በማመን አደንዝዘውታል፡፡ በዙሪያቸው ላሉትም ሐይማኖተኞች እንደሆኑ ያስመስሉ ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን ቅድስና የሚቃወሙ እጅግ ብልሹ ሐጢያተኞች እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች መሆናቸው ግልጥ ነው፡፡
የቀራጩ ጸሎት ከፈሪሳዊው ጸሎት የተለየ ነበር፡፡ ቀራጩ ሐጢያተኛ እንደነበር ለማንም ግልጥ ነው፡፡ እንዲያውም በእግዚአብሄር ፊት ሲቀርብ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ እንኳን አልተመለከተም፡፡ በፈንታው ግን ደረቱን እየደቃ ‹‹አቤቱ ሐጢያተኛ ነኝና ማረኝ!›› በማለት ተናዘዘ፡፡ እግዚአብሄርም ምህረትን የለመነውን የቀራጩን ጸሎት ሰምቶ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመኑ ከሐጢያቶቹ ሁሉ አዳነው፡፡ በአንጻሩ ፈሪሳዊው በእግዚአብሄር ፊት ክፉ አድራጊ መሆኑ ተጋለጠ፡፡ እግዚአብሄር ያጸደቀው ቀራጩን እንጂ ፈሪሳዊውን አልነበረም፡፡
የሐጢያቶቻችንን ስርየት ተቀበልነው በምግባሮቻችን ላይ ተደግፈን ሳይሆን ከልባችን በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመናችን ብቻ ነው፡፡ ምግባሮቻችን ሁልጊዜም ከእግዚአብሄር ቅድስና የጎደሉ በመሆናቸው ሁልጊዜም ሐጢያት ከመሥራት በቀር የምናደርገው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ለመሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሶች የእስራኤል ሕዝብ ከሠሩዋቸው ሐጢያቶች የተነሳ ሁልጊዜም እንደሚሞቱና በሚቃጠለው መሠዋዕት መሠውያ ላይ እንደሚቃጠሉ ሁሉ ሁላችንም ስለ ሐጢያቶቻችን በእሳት መኮነን ይገባናል፡፡ ስለዚህ ምን ያህል ሐጢያተኞች እንደሆንን ለእግዚአብሄር መናዘዝና በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን አለብን፡፡
እሳትና ጢስ በናስ ከተለበጠው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠውያ ላይ ሲትጎለጎል ስናይ በእግዚአብሄር ፊት እኛ ራሳችን ስለ ሐጢያቶቻችን በሲዖል እሳት ለመኮነን የታጨን ሐጢያተኞች እንደሆንን ማየት እንችላለን፡፡ እያንዳንዳችሁ ይህንን እውነታ መገንዘብ አለባችሁ፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በመሥዋዕቱ ደም በማመን ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ኩነኔ ፈጽሞ መዳን የምትችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ የምትድኑበትን ደህንነት አቅርቦላችኋል፡፡ ነገር ግን በቅድሚያ ፈጽማችሁ ክፉዎችና ለሐጢያቶቻችሁም የምትኮነኑ መሆናችሁን እስካላመናችሁ ድረስ ይህንን ደህንነት ከልባችሁ በመጓጓት ልትሹት አትችሉም፡፡ ደህንነታችሁን ማግኘት፣ ከሐጢቶቻችሁ ሁሉና ከኩነኔያችሁ ሁሉ ነጻ መውጣትና የእግዚአብሄርን ፍቅር መቀበል የምትችሉት የደህንነትን እውነት ከሙሉ ልባችሁ ስትቀበሉ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብሎ እንደተወሳው በደህንነት እውነት ከማመናችሁ በፊት በቅድሚያ እውነተኛ ማንነታችሁን ተረድታችሁ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኛ ተፈጥሮዋችሁንና ጉድለቶቻችሁን በቅንነት ማመን አለባችሁ፡፡ የእግዚአብሄርን ቅድስናና ፍትህ ከልቡ ማመን የሚችለው ሐጢያተኛ ማንነቱን የሚያምን ሰው ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመን የሐጢያቶቻችሁን ስርየት መቀበል የምትችሉት በመጀመሪያ እግዚአብሄር ፈጽሞ ቅን፣ እውነተኛና ታማኝ ቢሆንም እናንተ በእርሱ ፊት ፈጸሞ ዓመጸኞች፣ የረከሳችሁና ክፉዎች መሆናችሁን ስታምኑ ብቻ ነው፡፡
እናንተ በእግዚአብሄር ፊት ራሱን እጅግ ጻድቅ አድርጎ እንደቆጠረው ፈሪሳዊ በራሳችሁ ጻድቃን ከሆናችሁ የቆማችሁት በሚያንሸራተት በረዶ ላይ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ፡፡ የእግዚአብሄርን ምህረት በማግኘት ፋንታ እግዚአብሄር ይተዋችኋል፡፡ በአንጻሩ እንደ ቀራጩ ከሆናችሁ ለሐጢያቶቻችሁ በሲዖል የምትኮነኑ ሐጢያተኞች መሆናችሁን ማመንና በዚህ ትሁት እምነታችሁም የእግዚአብሄርን ምህርት ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ እግዚአብሄር አብ ልክ እንደ ቀራጩ ትሁት የሆኑትን ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሐጢያቶቻቸውን ደምስሶ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመላክ አድኖዋቸዋል፡፡
በዚህ ዓለም ላይ እጅግ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ሁሉም በሁለት ለየት ያሉ መደቦች ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ እነርሱም የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበሉና ገና የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያልተቀበሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሙሉ በሙሉ ብልሹ መሆናቸውንና ለሲዖል የታጨውን ዕጣ ፈንታቸውን በማመናቸው የእግዚአብሄርን ምህረት የሚናፍቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ደህንነት በማመን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ተቀብለዋል፡፡ እግዚአብሄርን ከልባቸው ተቀብለዋል፡፡ በቅድስናው፣ በፍትሃዊነቱና በታማኝነቱ ይደገፋሉ፡፡ በአንጻሩ ሁለተኞቹ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት መቀበል እምቢ ከማለታቸውም በላይ እግዚአብሄርንም ይቃወሙታል፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛቸው እንደሆነ አያምኑም፡፡ ራሳቸውም ሐጢያተኞች እንደሆኑ አይቀበሉም፡፡ እግዚአብሄር በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እውነት ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ ሙሉ በሙሉ እንዳስወገደ ማመን አለባችሁ፡፡ በእውነት ደህንነታቸውን የሚያገኙት ይህ የማይናወጥ እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡
በናስ የተለበጠው የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ሁላችንም ስለ ሐጢያቶቻችን በእግዚአብሄር ለመኮነን የታጨን ብንሆንም በጌታችን ጥምቀትና በስቅለቱ በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንደታጠብን ያሳየናል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስን አዳኛችሁ አድርጋችሁ ከማመናችሁና እምነታችሁን ከመመስከራችሁ በፊት በቅድሚያ ለመሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሶች በናስ በተለበጠው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠውያ ላይ ይቃጠሉ እንደነበር ሁሉ እናንተም ራሳችሁ ለሠራችሁዋቸው ብዙ ሐጢያቶች መኮነን እንደሚገባችሁ ማመን አለባችሁ፡፡ ለመዳናችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን የምታስተውሉትና የምታምኑት ሐጢያተኛውን ማንነታችሁን ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ሕዝብ አንዱ መሆን የምትችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ 
 


በኢየሱስ ደም ብቻ ማመን በቂ አይደለም፡፡ 


አንዳንዶቻችሁ ‹‹ቀድሞውኑም በኢየሱስ ደም አምኜ ሳለ ሬቨረንድ ጆንግ ሐጢያተኛውን ማንነቴን ማመን እንደሚገባኝ ደጋግመው የሚናገሩት ለምንድነው? ጥቂት እንከኖች ሉብኝ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ለሐጢያቶቼ በእግዚአብሄር መኮነን የሚገባኝን ያህል ሐጢያተኛ አይደለሁም፡፡ ለመኮነን እስኪያበቃኝ ድረስ እያንዳንዱ አስተሳሰቤ፣ እያንዳንዱ ዕቅዴና እያንዳንዱ ምግባሬ በሐጢያት የተሞላ ነው ብዬ አላስብም›› ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ አሁን የምታስቡት ይህንን ከሆነ ልክ እንደዚያ ፈሪሳዊ በጣም እንደተሳሳታችሁ መገንዘብ ይኖርባችኋል፡፡ ራሳችሁን እንዲህ ለጋስ ሆናችሁ በመገምገማችሁ ግዙፍ ስህተት እየሰራችሁ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያት ደመወዝ ሞት መሆኑን በግልጥ ይናገራል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ትልቅም ይሁን ትንሽ እያንዳንዱ ሐጢያት ተመሳሳይ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት ያለበት ማንኛውም ሰው እጅግ ኢምንት የሆነች ሐጢያት ብትሆንም እንኳን ለዚህች ሐጢያት ተኮንኖ ወደ ሲዖል እሳት ይወረወራል፡፡ ሐጢያቶቻችሁ ምን ያህል ትልቅ ወይም ትንሽ መሆናቸው ከቁም ነገር የሚቆጠር አይደለም፡፡ ሐጢያት እስካለባችሁ ደረስ በቅዱሱ አምላክ ፊት እንደ ማንኛውም ሌላ ሐጢያተኛ ያው ናችሁ፡፡
ይህ ለምን እንደዚህ ሆነ? እግዚአብሄር ራሱ ቅዱስ ስለሆነ ሐጢያቶቸችሁ ምንም ያህል የከበዱ ወይም ያነሱ ቢሆኑም በጭራሽ ሐጢያትን መታገስ ስለማይችል ነው፡፡ እግዚአብሄር እያንዳንዱን ሐጢያት ያለ አድልዎ መኮነን ስላለበት ነው፡፡
ሕይወታችንን በሙሉ በእግዚአብሄር ፊት በቅንነት ብንገልጠው ማናችንም የሠራናቸው ሐጢያቶች ጥቂቶች ብቻ ናቸው ብለን መናገር አንችልም፡፡ የሠራችኋቸው ሐጢያቶች ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ የምትናገሩ ከሆነ ምናልባትም ራሳችሁን ቢያንስ በዓለም መለኪያ ጻድቅ አድርጋችሁ እየቆጠራችሁ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የምትሉት የእግዚአብሄር ፍርድና የሐጢያት ኩነኔ አስተሳሰባችሁ ፈጽሞ የተሳሳተ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሄር ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ አታውቁም፡፡ በሌላ አነጋገር ራሳችሁን የምትገመግሙት በእግዚአብሄር መለኪያ ሳይሆን በራሳችሁ መስፈርትና ዕውቀት ላይ ተመርኩዛችሁ ነው፡፡ ክፉኛ የተሳሳታችሁት ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን ‹‹በእግዚአብሄር ፊት የምቀርበው እንዴት ነው? እግዚአብሄር ሲመለከተኝ ኩነኔ የሚገባው ሰው ሆኜ አልታይምን? በየጊዜው የሠራኋቸው እጅግ ብዙ ሐጢያቶች በእርግጥ ወደ ሲዖል የሚልኩኝ አይደሉምን?›› ብላችሁ በመጠየቅ በእግዚአብሄር ፊት ራሳችሁን በትክክል ደግማችሁ መመርመር አለባችሁ፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን በእግዚአብሄር ፊት በትክክል መመርመርና እናንተም ራሳችሁ ለሐጢያቶቻችሁ ደመወዝ ይሆን ዘንድ ወደ ሲዖል እሳት ለመወርወር የታጫችሁ መሆናችሁን በግልጥ መረዳት ይገባችኋል፡፡
በእምነት ያልተደረገ ማንኛውም ነገር በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት እንደሆነ፣ (ሮሜ 14፡23) እናንተም ራሳችሁ እነዚህን ሐጢያቶች በተደጋጋሚ እንዳደረጋችሁና ለእነዚህ ሐጢያቶችም እንደምትኮነኑ መገንዘብ ያለባችሁ መሆኑ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የደህንነትን እውነት የምትገነዘቡትና ጌታ እንደ እናንተ ያለውን ብልሹ ሐጢያተኛ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ እንዳዳናችሁ የምታውቁት ከዚህ በኋላ ብቻ ነው፡፡ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት መቀበል የምትችሉትም በዚህ ቅጽበት ብቻ ነው፡፡
የመገናኛውን ድንኳን በዝርዝር የሚያብራራውን የእግዚአብሄር ቃል ስንመለከት የሚከተለውን እንመሰክራለን፡፡ ‹‹አቤቱ ሁላችንም ለሐጢያቶቻችን የታጨን ነበርን፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜም ሐጢያትን እንሠራለንና፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን እኛን ለማዳን በጥምቀትህና በማፍሰስ ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔ ሁሉ አዳንኸን፡፡ ሁላችንም ወደ ሲዖል ለመጣል የታጨን እንደነበርን እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ምስጋና ይግባህና አንተ ባቋቋምኸው የመሥዋዕት ስርዓት በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነናል፡፡ ይህ አንተ የሰጠኸን የደህንነት ስጦታ እንደሆነ እናምናለን፡፡ እንዲህ ባለ አስገራሚ ጸጋ ፊት ልናደርገው ያለን ነገር ቢኖር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና ምስጋናችንን ሁሉ ለአንተ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡›› 
ገና ወደ ክርስቶስ ጽድቅ ያልመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ አሉ፡፡ ጌታ እያንዳንዱን ሐጢያተኛ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እውነት አማካይነት ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ እንዳዳነ ሳይገነዘቡ አሁንም ድረስ የደህንነትን እውነት የማያውቁ አጅግ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ክፉዎች እንደሆኑና ምን ያህል በሐጢያቶቻቸው ለመኮነን የታጩ እንደሆኑ አያውቁም፡፡ ሁልጊዜም እጅግ ብዙ ሐጢያቶችን ቢሠሩና ለሐጢያቶቻቸው የሚኮነኑ ቢሆኑም እነርሱ ራሳቸው ብልሹ ሐጢያተኞች እንደሆኑ ስለማይገነዘቡ ራሳቸውን እያታለሉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በእግዚአብሄር ፊት በተጨባጭ ጥሩ ምግባሮችን እያደረጉ እንደሆኑ በተሳሳተ መንገድ ያስባሉ፡፡ የራሳቸውን በጎ ምግባር ለማሳየትም በጣም ይጓጓሉ፡፡ ወደ እግዚአብሄር ሲቀርቡ ከእግዚአብሄር ጽድቅ ይልቅ የራሳቸውን ጽድቅ ለማቅረብ አያመነቱም፡፡ በራስ ጽድቅ በተሞላው ዕብሪታቸው ሐጢያት ቢኖርባቸውም ወደ ሲዖል እንደማይወርዱ ያስባሉ፡፡ ሐጢያቶቻቸው ጥቂቶች ብቻ ስለሆኑ የእነዚህን ሐጢያቶች ስርየት እንደሚቀበሉ ለራሳቸው በማሰብ በጭራሽ ወደ ሲዖል እንደማይወርዱ ፈጽመው ይተማመናሉ፡፡
በመላው ዓለም በኢየሱስ ቢያምኑም አሁንም ድረስ ጥቂት ሐጢያቶች እንዳሉባቸው፣ እነዚህ ሐጢያቶችም የንስሐ ጸሎቶችን በማቅረብ ብቻ በቀላሉ ሊወገዱ እንደሚችሉ፣ ውሎ አድሮም እንደሚቀደሱና በመጨረሻም ሁሉም መንግሥተ ሰማይ እንደሚገቡ የሚያስቡ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ሐጢያተኞች ቢሆኑም በኢየሱስ ስለሚያምኑ ብቻ እግዚአብሄር እንደማይፈርድባቸው እርግጠኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ነገር የሚያምኑት ሰዎች ምንም ያህል ብዙ ቢሆኑም ሁሉም ለሚነድው የሲዖል እሳት የታጩ ናቸው፡፡ በመገናኛው ድንኳን ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና በጥሩው በፍታ ውስጥ የተገለጠውን የደህንነት ምስጢር በተጨባጭ ብታውቁም ወደ ሲዖል እንደማትገቡ የምታስቡ ከሆነ ወይም በጥምቀቱ ሳታምኑ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለላችሁ ብቻ የምታምኑ ከሆነ እምነታችሁ የተሳሳተና ሕጸጽ ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ልባችሁ ሐጢያተኛ ቢሆንም ቢያንስ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝ አድርጋችሁ ስላመናችሁ ወደ ሲዖል እንደማትወርዱ የምታስቡ ከሆነ የእግዚአብሄርን ቅድስና በተጨባጭ እየተቃወማችሁ ነው፡፡ ሲዖል የእግዚአብሄር ኩነኔ እንደሚገጥማቸው ለማያምኑ የዚህ ዓለም ዕብሪተኛ ሰዎች በትክክል የተዘጋጀ ስፍራ ነው፡፡ 
በጣም ብዙ ሐጢያተኞች ሞኞች በመሆናቸው በቀጥታ ወደ ሲዖል እየነጎዱ መሆናቸውን አለመገንዘባቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሁሉ ሐጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሄርም ክብር ጎድሎአቸዋል›› (ሮሜ 3፡23) እንደሚል ሁሉም በእርግጥ ወደ ሲዖል መጣል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሐጢያተኞች ናቸውና፡፡ የእግዚአብሄር ክብር በውሃና በመንፈስ የመጣው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ እናምናለን ቢሉም አብዛኞቹ ኢየሱስ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ እንደመጣ በትክክል ስለማይረዱ አሁንም ድረስ ሳይድኑ ቀርተዋል፡፡ በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ የመጣውን ይህንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማታውቁና የማታምኑበት ከሆነ ገና ከሐጢያቶቻችሁ አልነጻችሁም፡፡ ስለዚህ ብሩህ ወደሆነው የእግዚአብሄር ቤት መግባት አትችሉም፡፡ ወደ እግዚአብሄር ቤት መግባት የማትችሉ ከሆናችሁ ከእግዚአብሄር መንግሥት ተካፋይ ከመሆን ርቃችሁ በመጨረሻ ወደ ሲዖል ትጣላላችሁ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችሁ አድርጋችሁ የምታምኑ ክርስቲያኖች ብትሆኑም ባትሆኑም በውኑ ዳግመኛ ካልተወለዳችሁ ስለ ሐጢያቶቻችሁ ለሲዖል የታጫችሁ መሆናችሁን መቀበልና ከዚህ ጊዜ ጀምራችሁ በትክክል በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አለባችሁ፡፡ የእግዚአብሄር ሕግ የሐጢያት ደመወዝ ሞት እንደሆነ በግልጥ ይናገራል፡፡ እናንተም ይህንን መለኮታዊ ሕግ ተቀብላችሁ ያለ ምንም ተቃውሞ ልታምኑበት ይገባችኋል፡፡ እግዚአብሄር በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን የምትችሉት በቀጥታ ወደ ሲዖል እየገሰገሳችሁ መሆናችሁን ስታውቁ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄር የደህንነት ስጦታ የሐጢያቶች ስርየት ነው፡፡ ይህ ስጦታ የሚሰጠው በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሳኤው ለሚያምኑ ብቻ ነው፡፡
ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የዳንንበት ደህንነታችንና ነጻ መውጣታችን ከራሳችን የመነጨ ሳይሆን እግዚአብሄር ለእኛ የሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ማናችንም በፈቃዳችን በዚህ ምድር ላይ አልተወለድንም፡፡ ነገር ግን የእርሱ ልጆች እንሆን ዘንድ በዚህ ምድር ላይ እንድንወለድ የፈቀደው እግዚአብሄር ነው፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሳኤው በማመን ብቻ እግዚአብሄር ሁላችንንም ለደህንነት እንዳበቃን ከተረዳን ሁላችንም በዚህ እውነት ማመን አለብን፡፡
እግዚአብሄር የሐጢያት ደመወዝ ሞት መሆኑን የሚናገረውን ሕጉን ካጸና በኋላ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት ሊሰጠን አቀደ፡፡ እግዚአብሄር ከግራር እንጨት የሚቃጠል መሥዋዕት መሠውያ እንዲሠራ፣ በናስ እንዲለበጥና እሳት እንዲነድበት አዘዘ፡፡ ይህም የሐጢያት ደመወዝ ሞት እንደሆነና እያንዳንዱም ሐጢያት ለዘላለም መኮነን እንደሚገባው ይጠቁማል፡፡ ይህ እግዚአብሄር ያቋቋመው ሕግ ማናችንም ልንለውጠውና ልንሽረው የማንችለው ሕግ ነው፡፡ እኛ ራሳችን አቅመ ቢስ ሐጢያተኞች መሆናችንን አምነን በእምነት የደህንነትን እውነት ወደ ልባችን መቀበል ያለብን ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያቋቋመውንና ለእኛ የፈጸመውን እያንዳንዱን ሕግ ማወቅና ማመን ለሁላችንም ፈጽሞ አስፈላጊ ነው፡፡
የመገናኛውን ድንኳንና ትክክለኛውን እምነት በተጨባጭ በግልጥ ከተረዳችሁ እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉና ከእነዚህ ሐጢያቶች ኩነኔ ሁሉ የሚያድናችሁ ከመሆኑም በላይ በረከቶቹንም ሁሉ ይለግሳችኋል፡፡ ነገር ግን ሐጢያቶቻችሁን አንድ ጊዜ እንኳን የምር ለማጤን እምቢተኞች ከሆናችሁና ምንም ሐጢያቶች እንደሌለባችሁ በግትርነት የምታስቡ ከሆነ፣ አንዳች ለሞት የሚያበቁ ሐጢያቶች ፈጽሞ እንዳልሠራችሁ የምታስቡ ከሆነ ወይም የሠራችኋቸው ጥቂት ሐጢያቶች ከሠራችኋቸው ጥሩ ነገሮች ጋር ሲነጻጸሩ ምንም እንዳልሆኑ የምታስቡ ከሆነ ነፍሳችሁ ለእግዚአበሄር የቁጣ ሕግ የተገዛች ትሆናለች፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ነው፡፡ ክርስቶስን አዳኛችሁ አድርጋችሁ ብታምኑትና በጌታ በተፈጸመው የእግዚአብሄር ጽድቅ ብትታመኑ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ነጻ መውጣት ትችላላችሁ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን አንድ ጊዜ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ነጻ ከወጣችሁ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር እንደምትኖሩ የተረጋገጠ ነው፡፡
በመገናኛው ድንኳን የመሥዋዕት ስርዓት ውስጥ በተደበቀው የደህንነት እውነት አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉና ከሞት ስላዳነን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋናን ሁሉ አቀርባለሁ፡፡