Search

Preken

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 1-2] በወንጌል ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሄር ጽድቅ፡፡ ‹‹ ሮሜ 1፡16-17 ››

‹‹ ሮሜ 1፡16-17 ››
‹‹በወንጌል አላፍርምና አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሄር ሐይል ለማዳን ነው፡፡ ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና፡፡››
   
 

የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል አለብን፡፡  

 
ሐዋርያው ጳወሎስ በክርስቶስ ወንጌል አላፈረም፡፡ ወንጌልን በድፍረት መሰከረ፡፡ ሆኖም ብዙ ሰዎች በኢየሱስ እያመኑ ከሚያለቅሱባቸው ምክንያቶች አንዱ ሐጢያቶቻቸው ናቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በማወቅ ረገድም አላዋቂዎች በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን የገዛ ራሳችንን ጽድቅ በመተው መዳን እንችላለን፡፡
  
ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል ያላፈረው ለምንድነው? ከሁሉ በፊት የእግዚአብሄር ጽድቅ በዚያ ውስጥ ስለተገለጠ ነው፡፡
   
ወንጌል በግሪክ ‹‹ኢዋጂሊዮን›› ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹የምስራች›› ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም በተወለደ ጊዜ የእግዚአብሄር መልአክ መንጎቻቸውን በሌሊት ይጠብቁ ለነበሩት እረኞች ተገልጦ ‹‹ክብር ለእግዚአብሄር በአርያም በምድርም ሰላም ለሰውም በጎ ፈቃድ›› በማለት ነገራቸው፡፡ (ሉቃስ 2፡14) ወንጌል የምሥራች--‹‹ሰላምና ለሰው በጎ ፈቃድ›› ነው፡፡ የጌታ ኢየሱስ ወንጌል ከሐጢያቶች ሁሉ አድኖናል፡፡ ከዓለም ሐጢያቶችም አንጽቶናል፡፡ እርሱ ራሱ ልክ እንደ ዕበት ትል በሐጢያት ውስጥ የሚዳክሩ ሰዎችን ሐጢያቶች በሙሉ አንጽቶዋል፡፡
  
ሐዋርያው ጳውሎስ አስቀድሞ የእግዚአብሄር ጽድቅ በወንጌል ውስጥ እንደተገለጠ ተናግሮዋል፡፡ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የደመሰሰው የእግዚአብሄር ጽድቅ በወንጌል ውስጥ ተገልጦዋል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ቅዱሳንና ጻድቃን እንድንሆን ፈቅዶልናል፡፡ የዘላለምን ሕይወት እንድናገኝና ሐጢያት አልባም እንድንሆን ፈቅዶልናል፡፡
  
የሰብዓዊ ፍጡራን ጽድቅ ምንድነው? እኛ ሰዎች አንዳች የምንኮራበት ነገር ሲኖረን በእግዚአብሄር ፊት ራሳችንን ማሳየት እንወዳለን፡፡ በጎ ምግባሮችን በማድረግ የራስን ኩራት ማከማቸት የሰውን ጽድቅ የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን የኢየሱስ ምግባር የእግዚአብሄር ጽድቅ በወንጌል ውስጥ እንዲገለጥ ፈቅዶዋል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡
  
በዚህ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወንጌል ሳያውቁ ወንጌልን ይሰብካሉ፡፡ ‹‹በኢየሱስ ታመን ትድናለህ፤ ባለጠጋም ትሆናለህ›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል ትምህርቶች አይደሉም፡፡ ወንጌል ከማንኛውም ነገር የበለጠ ገናና የሆነ ይመስላል፡፡ ብዙ ሰዎች ግን ወንጌልን አያውቁትም፤ አይረዱትምም፡፡ ነገሩ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ ከመሆኑ እውነታ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ሰዎች ግን አሁንም ድረስ በውስጡ የያዛቸውን ነገሮች በትክክል አልተረዱትም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እጅግ የከበረውና ጠቃሚው ነገር እግዚአብሄር የሰጠን ወንጌል ነው፡፡
  
‹‹የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና፡፡›› የእግዚአብሄር ወንጌል ልክ በበርሃ እንዳለ ምንጭ ነው፡፡ ኢየሱስ ብዙ ሐጢያቶች ወደሰሩ ሐጢያተኞች መጥቶ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ አነጻላቸው፡፡ ሆኖም ሰዎች የገዛ ራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ሲሞክሩ የዓለምን ሐጢያቶች ያነጻውን የእርሱን የጽድቅ ስጦታ ንቀውታል፡፡ የራሳቸውን ጥረቶች (አገልግሎት መስጠት፣ ቅንአት፣ ስጦታ፣ የንስሐ ጸሎት፣ ጾም፣ ጸሎት፣ የጌታን ቀን ማክበር፣ የእግዚአብሄርን ቃል በምግባር መተርጎም ወ.ዘ.ተ) የሚያስቀድሙና የእግዚአብሄርን ስጦታ እምቢ የሚሉ ሰዎች የእርሱን ጽደቅ የሚንቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል የሚችለው የገዛ ራሱን ጽድቅ ሲተው ብቻ ነው፡፡
 
 

የበለስ ቅጠል ለራሳቸው ሰፍተው ራሳቸውን አለበሱ፡፡   

   
በዘፍጥረት 3፡21 ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹እግዚአብሄር አምላክም ለአዳም ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፤ አለበሳቸውም፡፡››
  
የመጀመሪያው ሰው አዳም በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ ወድቆ እግዚአብሄርን በደለ፡፡ አዳምና ሄዋን ከበደሉ በኋላ የሰሩት ትክክለኛው ነገር የበለስ ቅጠል ሰፍተው ራሳቸውን ማልበሳቸው ነው፡፡ ከበለስ ቅጠሎች የተሰፉት ልብሶች ከቁርበት ከተሰሩት ልብሶች ጋር የደመቀ ተቃርኖ አላቸው፡፡ ጉዳዩ ‹‹በሰው ጽድቅ›› እና ‹‹በእግዚአብሄር ጽድቅ›› መካከል ያለው ልዩነት ነበር፡፡ ዘፍጥረት 3፡7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የበለስንም ቅጠል ሰፍተው ለራሳቸው ልብስ አደረጉ፡፡›› በጥሬ የሚበሉ ቅጠላ ቅጠሎችን ተመግባችሁ ታውቃላችሁን? እኛ ኮርያዎች በጥሬው የሚበሉ ቅጠሎች ለማድረቅ ከሩዝ ዘንጎች ጋር እናስራቸዋለን፡፡ በክረምትም ከእነርሱ ጋር የባቄላ ወጥ እንቀቅላለን፡፡ በጣም ጣፋጭ ነው!
  
አዳምና ሄዋን ከበደሉ በኋላ የበለስ ቅጠሎችን ሰፍተው ለበሱ፡፡ ይህ አይነቱ ምግባር-- ሰናይ ምግባሮች፣ ራስን መፈተንና ራስን መስዋት ማድረግ-- የሰው ጽድቅ ውጤት ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ሳይሆን የራስ ጽድቅ ነው፡፡ እነርሱ ከበለስ ቅጠሎች ልብሶችን የመስራታቸው እውነታ ሐጢያቶቻቸውን በእግዚአብሄር ፊት በሰናይ ምግባሮቻቸው ለመሸፈን የሞከሩበትን የኩራት ሐጢያት ያሳያል፡፡ ይህ የአንድን ሰው ጽደቅ-- መሰጠቶቹን፣ ራሱን ማቅረቡን፣ ራሱን መፈተኑንና የንስሐ ጸሎቶችን ወደ ልብስ ቀይሮ በአእምሮ ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች በዚያ በመሸፈን በእግዚአብሄር ፊት ኩራትን የማቅረብ ‹‹ጣዖት አምልኮ›› ነው፡፡
  
ከበለስ ቅጠል ልብሶችን በመስፋት በእግዚአብሄር ፊት በልቦቻችን ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች መደበቅ እንችላለን? በሰናይ ምግባሮቻችን ሐጢያቶቻችንን መደበቅ እንችላለን? በፍጹም! ቅጠሎቹ በአንድ ቀን ውስጥ መርገፍ ይጀምራሉ፡፡ በመጨረሻም ቅጠሎቹ በሙሉ ይረግፋሉ፡፡ ከቅጠል የተሰሩ ልብሶች ዘለቄታ የላቸውም፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፍተው ልብስ የሚሰሩ ማለትም በራሳቸው ምግባሮች እግዚአብሄርን በሚገባ በማገልገል ጻድቃን ለመሆን የሚሞክሩ ሰዎች መንግሥተ ሰማይ ሊገቡ አይችሉም፡፡ በገዛ ራሳችን የጽድቅ ምግባሮች የሐጢያቶች ይቅርታ ማግኘት አንችልም፡፡
  
አዳምና ሄዋን ከበለስ ቅጠል የተሰፉ ልብሶችን በመስራት ሐጢያቶቻቸውን ለመደበቅ ሲሞከሩ እግዚአብሄር አዳምን ጠርቶ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› አለው፡፡ እርሱም በገነት ዛፎች መካከል ተሸሽጎ ሳለ ‹‹ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም›› አለ፡፡ ሐጢያት ያለበት ሰው ጫካ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል፡፡ ዛፎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚያመላክቱት ሰዎችን ነው፡፡ በልቡ ውስጥ ሐጢያት ያለበት ሰው ራሱን በሰዎች መካከል ለመደበቅ ይሞክራል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥም በጣም ወደኋላ ወይም ብዙ ሰዎች ወደሚሰበሰቡበት የፊት ወንበር ላይ ሳይሆን መካከል ላይ መቀመጥ ይወዳል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ራሱን በሰዎች መካከል መደበቅ ስለፈለገ ነው፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያቶችን መደበቅ አይችልም፡፡ የራሱን ጽድቅ በመተውና በጌታ ፈቃድ በማመን ለሐጢያቶቹ ይቅርታን ማግኘት አለበት፡፡ ያልጠራ እምነት ያላቸውና በእውነት የሚያምኑ ሰዎች ራሳቸውን በተመሳሳይ ሰዎች መካከል በመደበቅ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ሐጢያቶቻቸውን በሰናይ ምግባሮቻቸው ለመደበቅ ከሚሞክሩት ጋር አብረው ሲዖል ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኞች የሆኑ መሆናቸውን መግለጥና ራሳቸውንም ለእግዚአብሄር አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
  
እግዚአብሄር ከበለስ ቅጠሎች ልብስ የሰራውን አዳምን እንዲህ ሲል ተናገረው፡፡ ‹‹ፍሬውን ለምን ወሰድህ? እንድትበላስ ማን አደረገህ?›› ‹‹አቤቱ እግዚአብሄር ከእኔ ጋር ትሆን ዘንድ አንተ የሰጠኸኝ ሴት ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ፡፡›› ‹‹ሄዋን ለምን እንደዚህ አደረግሽ?›› ‹‹እባብ አታለልኝና በላሁ፡፡›› ስለዚህ እግዚአብሄር አምላክ እባቡን እንዲህ አለው፡፡ ‹‹እንዲህ ያለ ነገር ስላደረግህ ከምድር እንስሶች ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ትሆናለህ፡፡ በሆድህም ትሄዳለህ፡፡ በዘመንህም ሁሉ አፈርን ትበላለህ፡፡›› እባቦች በሆዳቸው የሚሳቡት ለዚህ ነው፡፡ እንደገናም እግዚአብሄር አዳምንና ሄዋንን እንዲህ አላቸው፡፡ ‹‹እናንተም ደግሞ በድላችኋል፡፡ እናንተ የተታለላችሁትና አታላዮች የሆኑትም ያው ሐጢያተኞች ናችሁ፡፡›› በዚህ ዘመን ሐሰተኛ ነቢያቶችም እንደዚሁ ‹‹እሳትን ተቀበሉ!›› በማለት አስመሳይ ወንጌሎቻቸውን ይሰብካሉ፡፡ በእነርሱ የተታለሉ ሰዎች ልክ እንደ ሐሰተኛ ነቢያቶች ተመሳሳይ ቅጣት ይደርስባቸውና ወደ ሲዖል ይወርዳሉ፡፡
 
 

ጌታ ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበት ልብስ አደረገላቸው፡፡ 

 
እግዚአብሄር እንዲህ ብሎ አሰበ፡፡ ‹‹ባሉበት ሆነው በሰይጣን ተታልለው የበደሉትን አዳምንና ሄዋንን አልተዋቸውም፡፡ ዕቅዴን ይፈጽሙ ዘንድ ላድናቸው፣ ሰዎችን በራሴ አምሳል ልፈጥርና ልጆቼ ላደርጋቸው ያሰብኩት ከቀድሞው ነው፡፡›› ይህ ዕቅድ ከእግዚአብሄር ጋር ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻቸውን ወደ አንድ እንስሳ በማስተላለፍ እንስሳው ከተገደለ በኋላ ቁርበቱ ተገፎ ልብሶች ተሰሩ፡፡ አዳምና ሄዋንም እነዚያን ልብሶች ለበሱ፡፡ ይህንንም የደህነታችን ተምሳሌት አደረገው፡፡ ከበለስ ቅጠል የተሰሩት ልብሶች ለአንድ ቀን እንኳን መቆየት አልቻሉም፡፡ በተደጋጋሚ እየተሰሩ መልበስ ነበረባቸው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹እናንተ አዳምና ሄዋን ኑ አዲስ የቁርበት ልብስ ሰርቼላችኋለሁ፡፡ ቁርበቱ ለእናንተ ከሞተው እንስሳ የተወሰደ ነው›› በማለት የዘላለምን ሕይወት አለበሳቸው፡፡ እግዚአብሄር ምዕመናንን በማዳን ጽድቁን እንዳለበሳቸው ሁሉ ጌታ አምላክ ለአዳምና ለሄዋን ከቁርበት የተሰሩ ልብሶችን አበጅቶ አለበሳቸው፡፡
   
ነገር ግን ከእግዚአብሄር ደህንነት ለተለየ ሰው ደህንነት ከበለስ ቅጠል የተሰራ ልብስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የአምላክ ጽድቅ የሆነውን የቁርበት ልብስ አልብሶናል፡፡ ጌታ ሥጋውንና ደሙን በመስጠት በእግዚአብሄር ጽድቅ በሚገኘው የሐጢያቶች ስርየት አልብሶናል፡፡ በእኛ ፋንታ ኩነኔውን ሁሉ ይወስድ ዘንድም በጥምቀቱና በስቅለቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አስወግዶዋል፡፡ በኢየሱስ የጥምቀትና የደም ወንጌል አማካይነት በእግዚአብሄር ጽድቅ ስናምን እግዚአብሄር የሐጢያቶች ይቅርታ እንድናገኝ ፈቅዶዋል፡፡ ይህ ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው የሚያድን ወንጌል ነው፡፡
 
በዓለም ላይ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ንቀው የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም የሚሞክሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱ የራሳቸውን ጽድቅ መተው አለባቸው፡፡ በሮሜ 10፡1-4 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ወንድሞች ሆይ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሄር ልመናዬ እንዲድኑ ነው፡፡ በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሄር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ ለእግዚአብሄር ጽድቅ አልተገዙም፡፡ የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና፡፡››
   
እስራኤሎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ ችላ በማለት የራሳቸውን ጽድቅ ለማቆም ሲሉ ሕግ አጥባቂነትን የሙጥኝ ብለው ቀሩ፡፡ እግዚአብሄር ለሰዎች ሕግን የሰጠው ስለ ሐጢያት እንዲያውቁ ነው፡፡ ሰዎች ሐጢያትን የሚያውቁት በአስርቱ ትዕዛዛት በኩል ሲሆን የሐጢያት ይቅርታ የሚያገኙትም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚቀርበው የመስዋዕት ስርዓት አማካይነት በእርሱ የማዳን ጽድቅ በማመን ነው፡፡ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን የሚቀርበው የሐጢያት መስዋዕት ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሄር ትክክለኛ አምሳያ መሆኑን ያመላክታል፡፡
 
 
ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ?
 
ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ያነጻ ዘንድ ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀው፡፡ ኢየሱስ ከመጠመቁ ጥቂት ቀደም ብሎ አጥማቂውን ዮሐንስን እንዲህ አለው፡- ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) ኢየሱስ የተጠመቀበት ምክንያት ይህ ነው፡፡ እርሱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ያነጻ ዘንድ ተጠመቀ፡፡ በጥምቀቱም የዚህን ዓለም ሐጢያቶች ወሰደ፡፡ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› (ዮሐንስ 1፡29) እርሱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወሰደ፡፡ ሐጢያቶችንም ለማንጻት ተሰቀለ፡፡ ሆኖም እስራኤሎች ኢየሱስ ፍጹም የሆነ የሐጢያተኞች አዳኝ እንደሆነ አላመኑም፡፡
  
እስራኤሎች ራሳቸውን ለእግዚአብሄር ጽድቅ አላስገዙም፡፡ ኢየሱስ ግን የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ የሕግ ፍጻሜ ነው፡፡ የሕግ ፍጻሜ ማለት ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስወግዶዋል ማለት ነው፡፡ ምዕመናን ሁሉ ይቀደሱ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ እርግማን ሆኖ ተኮነነ፡፡ የሕግንም እርግማን ፈጸመ፡፡ ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ተቤዣቸው፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ለማንጻት ተጠመቀ፡፡ ሥጋውን ለጥምቀት ለዮሐንስ በማቅረብና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ሥጋው በማስተላለፍ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፡፡ በዚህም ሰዎችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው፡፡ በጥምቀቱና በስቅለቱ አማካይነት የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በመውሰድ የሕግ እርግማን ኩነኔን አስወገደ፡፡ እርሱ ከሕግ ኩነኔና እርግማን ፈጽሞ አድኖናል፡፡
  
ይህ የሕግ ፍጻሜና የእግዚአብሄር ማዳን ጽድቅ ጅማሬ ነበር፡፡ ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅና ወደ መስቀል በመሄድ የዓለምን ሐጢያቶች በብቃት ወሰደ፡፡ አንድ ሰው በኢየሱስ የማዳን ጽድቅ በልቡ እያመነ በልቡ ውስጥ እንዴት ሐጢያት ሊኖር ይችላል? ‹‹የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና፡፡›› የኢየሱስ ጥምቀትና ደም የእግዚአብሄር ጽድቅ ነበር፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ማመን ነው፡፡
  
የእግዚአብሄር ጽድቅ በትክክለኛው መንገድ በኢየሱስ ጥምቀት ተፈጽሞዋል፡፡ በዚህ እንድታምኑ እፈልጋለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ትድናላችሁ፡፡ ሐጢያተኞች በኢየሱስ ጥምቀት አማካይነት ሐጢያት አልባ ይሆኑ ዘንድ ጽድቅ ተሰጥቶዋቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ የእግዚአብሄር ፍርድ ጽድቅ የኢየሱስ ስቅለት ነበር፡፡ ‹‹ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነው፡፡›› ሕጉ እስካለ ድረስ የእግዚአብሄር ፍርድ ገና ባልተፈረደባቸው ሰዎች ላይ ይመጣል፡፡ የእግዚአብሄር ሕግ ሐጢያትን በመግለጥ የሐጢያት ደመወዝ ሞት፣ እርግማንና ሲዖል መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ ጥምቀትና የመስቀሉ ላይ ደሙ የሕግን እርግማን ወደ ፍጻሜ አምጥተውታል፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፡፡ ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸምም ሕግን ፈጸመ፡፡
 
 
ሰነፎቹ መብራታቸውን ያዙ ነገር ግን ዘይት አልያዙም፡፡
 
ማቴዎስ 25፡1-13ን እንመልከት፡፡ እዚህ ላይ ሙሽራቸውን፤ የጌታን መምጣት ስለሚጠብቁ አስር ቆነጃጅት የተነገረ ምሳሌ አለ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሄር ጽድቅ ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
  
‹‹በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አስር ቆነጃጅትን ትመስላለች፡፡ ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ፡፡ ሰነፎቹ መብራታታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፡፡ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮዋቸው ዘይት ያዙ፡፡ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ፡፡ እኩለ ሌሊትም ሲሆን እነሆ ሙሽራው ይመጣል ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ፡፡ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሱና መብራታቸውን አዘጋጁ፡፡ ሰነፎቹም ልባሞቹን መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን አሉዋቸው፡፡ ልባሞቹ ግን መልሰው ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉዋቸው፡፡ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፡፡ በኋላ ደግሞ የቀሩት ቆነጃጅት መጡና ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ክፈትልን አሉ፡፡ እርሱ ግን መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ አላውቃችሁም አለ፡፡ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ፡፡›› (ማቴዎስ 25፡1-13)
  
መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመገናኘት ከወጡት አስር ቆነጃጅት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነች ተጽፎዋል፡፡ መንግሥተ ሰማይ የገባው ማነው? ከአስሩ ቆነጃጅት መካከል መንግሥተ ሰማይ የገባው ነው? አንዳንዶቹ ቆነጃጅት በኢየሱስ ቢያምኑም መንግሥተ ሰማይ መግባት ያልቻሉት ለምንድነው? ጌታ ስለዚህ ጉዳይ ከላይ በተጠቀሱት ምንባቦች ውስጥ ነግሮናል፡፡ ከአስሩ ቆነጃጅት አምስቱ ሰነፎች ሌሎቹ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ፡፡ ሰነፎቹ መብራታቸውን ቢይዙም ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙም፡፡ መብራቶች ‹‹አብያተ ክርስቲያኖችን›› ያመላክታሉ፡፡ እነርሱ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አለመያዛቸው ያለ መንፈስ ቅዱስ (ዘይት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያመላክተው መንፈስ ቅዱስን ነው) በቤተክርስቲያን የሚመላለሱትን ያመላክታል፡፡
 
ሰነፎቹ ምን አደረጉ? ዳግም ያልተወለደ ሰው በኢየሱስ ቢያምንም ከልቡ ቤተክርስቲያን ያዘወትር ይሆናል፡፡ ሰው ሁሉ ‹‹የእኔ ቤተክርስቲያን በእርግጥም ትክክል ነች›› ይላል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲህ ይላል፡፡ እነርሱ በቤተክርስቲያን ድርጅቶቻቸው ውስጥ ባሉ መስራች አባቶችና አንዳንድ ሰዎች ይኩራራሉ፡፡ ሰነፎቹ መብራቶቻቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙም፡፡ ልባሞቹ ግን ከመብራቶቻቸው ጋር በማሰሮዋቸው ዘይት ያዙ፡፡
  
ሰብዓዊ ፍጡር ምንድነው? ሰብዓዊ ፍጡር በእግዚአብሄር ፊት ዕቃ ነው፡፡ እርሱ አፈር ነው፡፡ ሰው የተሰራው ከአፈር ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ዘር እግዚአብሄርን መያዝ የሚችል ዕቃ ነው፡፡ ልባሞቹ በማሰሮዋቸው ውስጥ ካለው ዘይት ጋር አብረው መብራቶቻቸውን ያዙ፡፡
 
 
ሰነፎቹ ቆነጃጅት ዘይት በሌላቸው መብራቶቻቸው ስሜቶቻቸውን ብቻ አነደዱ፡፡ 
 
በኢየሱስ በሚያምኑ ሰዎች መካከል ሰነፍ ቆነጃጅት እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ እነርሱ መብራቶቻቸውን ያዙ፡፡ ዘይት ግን አልነበረውም፡፡ ይህም ዳግም አልተወለዱም ማለት ነው፡፡ ዘይት የሌለው ጧፍ ብዙ ይቆያልን? እዚህ ላይ ዘይት የሌለው መብራት ጧፉ ምንም ያህል ጥሩ ሊሆን ቢችል በቶሎ ነዶ ያልቃል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ዳግም ያልተወለዱ ምዕመናን ከመነሻው ለጌታ የሚቃጠል የፍቅር ስሜቶች አሉዋቸው፡፡ ይህ የሚቆየው ለ4 ወይም ለ5 ዓመታቶች ብቻ ነው፡፡ በኋላ ለጌታ ያላቸው ያ የጋለ ፍቅር ይጠፋል፡፡ እነርሱ የሐጢያት ስርየት እንደሌላቸው መረዳት አለባቸው፡፡
  
ዳግም ያልተወለዱ ወይም ዘይት (መንፈስ ቅዱስ) የሌላቸው ሰዎች እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከረጅም ዘመን በፊት ጥሩ እምነት ነበረኝ፡፡ በመጀመሪያ ጥሩ ነበርሁ፡፡ አሁን ግን አይደለሁም፡፡ አንተም በቅርቡ እንደ እኔ ትሆናለህ፡፡›› እነርሱ ዳግም ሳይወለዱ የሃይማኖትን ሕይወት ሲኖሩ የቆዩ ሐሰተኛ ነቢያቶችና ሐሰተኛ ቅዱሳን ናቸው፡፡ እምነቶቻቸው በዘይት (መንፈስ ቅዱስ) ላይ የተመሰረቱ ስላይደሉ የደህንነት እምነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እምነቶቻቸው የተመሰረቱት በስሜቶቻቸው ላይ ብቻ ነው፡፡ በውሃውና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በማመን ደህንነትን ማግኘትና የእግዚአብሄርን ዘይት እንደ ስጦታ መቀበል አለባቸው፡፡ ጧፉ የሰውን ልብ ያመለክታል፡፡
  
ከላይ በተመለከትናቸው ምንባቦች ውስጥ ቆነጃጅቱ ሙሽራውን ጠበቁ፡፡ እዚህ ላይ የእስራኤሎችን ባህላዊ ታሪክ በሚገባ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ እነርሱ የሰርግ ስርዓቶቻቸውን የሚያደርጉት በምሽት ነበር፡፡ ሰርጉ የሚጀምረውም ሙሽራው ሲመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ሙሽራይቱ ሙሽራዋን መጠበቅ አለባት፡፡
  
‹‹ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ግን ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ፡፡›› ‹‹እነሆ ሙሽራው ይመጣል!›› የሚል ውካታም ሆነ፡፡ ያን ጊዜ ቆነጃጅቱ ተነስተው ፊቶቻቸውን ለመቀባባት ተጣደፉ፡፡ አስሩ ቆነጃጅት ሙሽራውን እየጠበቁ ሳሉ ሙሽራው ‹‹እነሆ ሙሽራው ይመጣል!›› በሚል ጩኸት ታጅቦ መጣ፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሱና መብራታቸውን አዘጋጁ፡፡›› ሰነፎቹ ሁልጊዜም ገልቱዎች ናቸው፡፡ ሙሽራው ከመምጣቱ በፊት ዘይታቸውን ማዘጋጀት ይገባቸው ነበር፡፡ ጧፉ ምንም ያህል የደከመ ቢሆንም ዘይት ያለው መብራት አይጠፋም፡፡
ዘይት የሌለው መብራት የያዙት ሰነፎቹ ቆነጃጅት ያበሩት ጧፉን ብቻ ነበር፡፡ ይህ ማለት የተቃጠሉት ልቦቻቸው ብቻ ነበሩ ማለት ነው፡፡ ‹‹ዳግም መወለድ ይኖርብኛል፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው የሚኖረውን ሕይወት መኖር አለብኝ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም መሞላት አለብኝ፡፡›› ልክ እንደዚህ ልቦቻቸውን በታማኝነት አነደዱ፡፡ እኛ ልጆች በነበርንበት ወቅት በምሽት ክፍሎቻችንን ለማብራት የምንጠቀመው በነጭ ጋዝ የሚሰሩ ኩራዞችን ነበር፡፡ መብራቱ አንድ የወረቀት ቁራጭ እንዲያቃጥል ከፈቀድን በቅጽበት ወረቀቱ ነዶ ያልቅ ነበር፡፡ እሳቱ ትንሽ ከፍ ያለና በጣም ብሩህ ነበር፡፡ ነገር ግን ወዲያው ይጠፋ ነበር፡፡
  
ወደ ሲዖል የሚወርዱት ሰነፎቹ ቆነጃጅት ያለ ዘይት የራሳቸውን ልቦች (ስሜቶች) የሚያነዱና ጌታን በተጨባጭ በሚገናኙበት ጊዜም የእምነት እሳታቸው የሚጠፋባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ የላቸውም፡፡ ‹‹♫ አንተ የምትነድ መንፈስ ና♫ ፡፡›› እነርሱ በትልቅ ጥድፊያ ውስጥ ናቸው፡፡ ሴቶችም በዳንስ ይቀልጣሉ፡፡ (ይህንን የመንፈስ ቅዱስ ዳንስ ብለው ይጠሩታል፡፡) ‹‹እባክህ ና›› እያሉም ጡቶቻቸውን ያዘልላሉ፡፡ እነርሱ ሰነፎችና ወፈፌዎች ናቸው፡፡ በአዳኙ ፊት አሁንም ድረስ ሐጢያት ያለብን ከሆንን ሰነፎች መሆን አለብን፡፡ በኢየሱስ ብናምንም በልቦቻችን ውስጥ ሐጢያት ካለብን ሰነፎቹን ቆነጃጅት እንመስላለን፡፡ በፍጹም ሰነፍ ቆንጆ አንሁን፡፡
 
 
ጌታ ሐጢያት ያለባትን ሙሽራ እንዴት ሊያገባ ይችላል?
 
ጌታ ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ ሙሽራው እግዚአብሄርና ሐጢያት የሌለበት የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሙሽራችን ነው፡፡ ሆኖም ሐጢያት እያለባችሁ እንዴት እግዚአብሄርን ልትገናኙት ትችላላችሁ? ሐጢያትን በልባችሁ ይዛችሁ እግዚአብሄርን ልትገናኙት ትፈልጋላችሁን? ይህንን ማድረግ በጣም ገልቱነትና ሞኝነት ነው፡፡
ሙሽራችን ኢየሱስ መጥቶ ሙሽሮችን እንዲቀድሱ አደረገ፡፡ ሙሽሮቹን በጥምቀቱ አማካይነት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ በማንጻት ጻድቃን አድርጎዋቸዋል፡፡ የእርሱ ሙሽሮች ይሆኑ ዘንድ መረጣቸው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ከእነርሱ አምስቱ ‹‹እባካችሁ ኑ›› አሉ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ አምስቱ ገናም በጨለማ ውስጥ ቆመው ነበር፡፡ ፊቶቻቸው ጨልመው ሳሉ እንዴት የሰርግ ስርዓቶች ሊኖሩዋቸው ይችላሉ? ሙሽራው መጥቶ ‹‹እንዴት ነበራችሁ?›› አላቸው፡፡ የኋለኞቹ አምስት ሙሽሮች ፊቶቻቸው በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ጨልመው ነበር፡፡ ሐጢያቶቻቸው በልቦቻቸው ውስጥ እዚህና እዚያ ተንጠልጥለው ስለነበር ጥልቅ በሆነ ሐዘን ውስጥ ነበሩ፡፡
  
በሐጢያቶችዋ ምክንያት የምታለቅስን ሙሽሪት ጌታ እንዴት ሊያገባት ይችላል? ‹‹ጌታ ሆይ እንዲህ አድርገህ ስለቀደስከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡›› የዚህ አይነት ሰው ደካማ ቢሆንም እንኳን በመንፈሳዊው ሙሽራ ደስተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙሽራው እርሱን/እርስዋን ወዶዋል፡፡ ከእርሱ/ከእርስዋ ድካሞችና ሐጢያቶችም አንጽቶዋቸዋል፡፡ ሙሽራ ሁልጊዜም ሙሽሪት መቆነጃጂያ እንድትጠቀም ይረዳታል፡፡ ልብሶችን፣ ምርጥ ሽቱዎችንና መቀባቢያዎችን ሁሉ ይልክላታል፡፡ ከዚያም ሙሽሪት ሙሽራውን ለመገናኘት ዝግጁ ትሆን ዘንድ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ትኳኳላለች፡፡
  
የእርሱ ሙሽሮች ሆነን ልንገናኘው እንችል ዘንድ እንዲመራን ጌታችን ሙሽራ ሆኖ ወደዚህ ዓለም ተላከ፡፡ ለሐጢያት ስርየት ይሆን ዘንድም በዮርዳኖስ ሥጋውን ሰጠን፡፡ ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፡፡ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን፡፡›› (ዮሐንስ 1፡14) በጌታ በማመን የጸጋ፣ የእውነትና የሐጢያት ይቅርታ ሙላት ይኖረን ዘንድ እርሱ ራሱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስወገደ፡፡ ሙሽራው በዮርዳኖስ ወንዝ የሙሽሪቶቹን ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደ፡፡ ጌታ በእነርሱ ፋንታ በመስቀል ላይ በመኮነን ሙሽሪቶቹን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳነ፡፡
 
 
መንፈስ ቅዱስን በገንዘብና በመከራዎች መግዛት እንችላለን?
 
ነገር ግን ሙሽራው ሊመጣ በተቃረበ ጊዜ ሰነፎቹ ቆነጃጅቶች መብራታቸው ሊጠፋባቸው ስለሆነ ልባሞቹን ከዘይታቸው እንዲያካፍሉዋቸው ጠየቁዋቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መጋራት እንችላለንን? የሐጢያት ይቅርታን በሰናይ ምግባሮች፣ በመከራ ወይም በገንዘብ መግዛት እንችላለንን? ልባሞቹ የመነቃቃት አገልግሎት ካላቸው ሰባኪዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲገዙ ነገሩዋቸው፡፡ ሰነፎቹም ከዚህ ቀደም ከእነርሱ መግዛታቸውን አሰቡ፡፡ ዘይቱን በገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ አሰቡ፡፡ ረብጣ ስጦታዎችና አገልግሎቶች፣ ትክክለኛ ወደሆኑ ቤተክርስቲያኖች መሄድና በተደጋጋሚ መጸለይ፣ አንዳች ነገር እንደሚሰጣቸው በማሰብ የሃይማኖትን ሕይወት በትጋት ኖረዋል፡፡
  
ነገር ግን ማንም ሰው ምንም ነገር ቢሆን ጌታ የሰጠውን የሐጢያት ስርየት ከምድር በሚገኝ በማናቸውም ነገር ሊገዛ አይችልም፡፡ ሰነፎቹ በጌታ ፊት ለመቆም እስኪመጡ ድረስ ስሜቶቻቸውን ለማንደድ ሞክረዋል፡፡ ከአምስቱ ሰነፍ ቆነጃጅት አንዱ ‹‹እከተልሃለሁ፤ ጸሎቶችን ለማድረግና የንስሐ ጸሎቶችን ለማድረስም ወደ ተራራ እወጣለሁ፡፡ እርሱን ለማገልገል እንሂድ፤ ወንጌልን ለመስበክ ከአገር ውጪ እንሂድ›› በማለት የሃይማኖት ሕይወትን ጀመረ፡፡    
  
በመጨረሻ ሙሽራው በታላቅ አጀብ መጣ፡፡ ሙሽራው ሲመጣ ሰነፎቹ ዘይት ሊገዙ ሄዱ፡፡ ነገር ግን የሐጢያት ይቅርታን ያገኙትና ዘይታቸውን (መንፈስ ቅዱስ) ያዘጋጁት ቆነጃጅቶች ወደ ሰርጉ ድግስ ገቡ፡፡ ሙሽራው ሁሉን ካዘጋጀ በኋላ ከሙሽሮቹ ጋር ተገናኘ፡፡ ከዚያም በሩን ቆለፈ፡፡ ኢየሱስ አምስቱን ቆነጃጅት የመረጠው እንዲያው በዘፈቀደ አልነበረም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹‹አምስት›› ቁጥር ‹‹ጸጋን›› የሚያመላክት ቁጥር ነው፡፡ አምስቱ ቆነጃጅት የሚያመላክቱት በጸጋ የሐጢያትን ስርየት ያገኙትንና በእርሱ ጸጋና የጽድቅ ምግባሮች የሚያምኑትን ነው፡፡ እነርሱ ሙሽራው ያደረገላቸውን አስተውለው ጻድቃን በሚያደርጋቸው በጌታ ጽድቅ አመኑ፡፡ ሌሎቹ ቆነጃጅት ግን ውለው አድረው መጥተው ‹‹ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ክፈትልን›› አሉት፡፡ እርሱ ግን ‹‹እውነት እላችኋለሁ አላውቃችሁም›› ብሎ መለሰ፡፡
  
 
የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል የምንችለው ሐጢያቶቻችን ሲደመሰሱ ብቻ ነው፡፡
 
ዘይት ያላዘጋጁ ጌታን ሊገናኙት አይችሉም፡፡ ጌታ ለመንግሥተ ሰማይ የሚቀበላቸው በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑትን፣ መንግሥተ ሰማይን የጠበቁትንና በልባቸው ውስጥም በተጨባጭ የሐጢያት ስርየትን ያገኙትን ነው፡፡ ጌታ የተስፋ ቃሎችን ተናግሮዋል፡- ‹‹ንስሐ ግቡ፤ ሐጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38) የሐጢያቶቻችንን ስርየት ከተቀበልን በኋላ ምን ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 2፡38) የእግዚአብሄርን የጽድቅ ወንጌል ስትቀበሉ በልባችሁ ውስጥ ያሉት ሐጢያቶች በተጨባጭ ይደመሰሱና መንፈስ ቅዱስ ወደ እናንተ ይመጣል፡፡ የእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ በአካለ ሥጋ ሊታወቀን አይችልም፡፡ ያም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ አለ፡፡ ሐጢያት የለብንም ማለት የምንችለው መንፈስ ቅዱስና የእግዚአብሄር ልብ በልቦቻችን ውስጥ ስላሉ ነው፡፡ በእርግጥም አሉ፡፡ የጌታን ጽድቅ የተቀበለ ሰው ደካማ ቢሆንም እንኳን ጻድቅ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን የጌታ ጽድቅ የሌለው ሰው ሐጢያተኛ ሆኖ ይቀራል፡፡
 
 
የእግዚአብሄር ጽድቅ በእርሱ ተገልጦዋልና፡፡ 
 
ጌታ በውሃና በደም መጣ፡፡ በጥምቀቱም ከሐጢያቶቻችን አዳነን፡፡ በተጠመቀና ደሙን በማፍሰስ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ይፋ የሆነ ቅጣት በተቀበለ ጊዜ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አስወግዶዋል፡፡ ሐዋርያቶቹ ዮሐንስ፣ ጴጥሮስና ጳውሎስ ስለዚህ ነገር ምን አሉ? እነርሱ ስለ ኢየሱስ ሥጋና ደም በጥቅሉ ተናግረዋል፡፡ ስለ ኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ስላፈሰሰው ደሙ ተናግረዋል፡፡ ማቴዎስ 3፡13-17 የኢየሱስን ጥምቀት በትክክል አብራርቶታል፡፡ ኢየሱስ ሐጢያተኞችን ሐጢያት አልባ ለማድረግና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለማንጻት በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡
  
1ኛ ጴጥሮስ 3፡21ን እንመልከት፡፡ ጴጥሮስ የእርሱ ጥምቀት የደህንነት ምሳሌ መሆኑን መስክሮዋል፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ እርሱም መላዕክትና ሥልጣናት ሐይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሄር ቀኝ አለ፡፡›› (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21-22)  
  
እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹ይህም ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡›› በሥጋው ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደበት የኢየሱስ ጥምቀት የመዳናችን ማረጋገጫ ሆንዋል፡፡ እርሱ ደሙን በመስቀል ላይ የማፍሰሱ እውነታ ለሐጢያቶቻችን የተኮነንን ለመሆናችን ማስረጃ ነው፡፡ ምን እያልሁ እንደሆነ ገብቶዋችኋልን? ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ (1ኛ ዮሐንስ 5፡6-9) እንደመጣ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም ተላከ፡፡ ሊቀ ካህኑ አሮን የሕዝቡን ሐጢያቶች ለማስተላለፍ እጆቹን በመስዋዕት እንስሶች ላይ በጫነበት ተመሳሳይ መንገድ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፡፡
  
ውሃ ማለትም ጥምቀት የሚያድነን ምሳሌ ነው፡፡ የሥጋን እድፍ ለማስወገድ እንዳልሆነ ተጽፎዋል፡፡ ይህ የሐጢያትን ስርየት ካገኘን በኋላ ሐጢያት አንሰራም ማለት አይደለም፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት በማመን የሐጢያትን ይቅርታ እንቀበላለን፡፡ ከዚያስ በሥጋ ሐጢያትን አንሰራም? አዎ እንሰራለን፡፡ ብዙ ሰዎች የሐጢያት ስርየትን በትክክል ሳይረዱ ቀርተው ‹‹በልብህ ውስጥ ሐጢያት ከሌለብህ እንደገና ሐጢያት አትሰራም›› የሚሉ ነገሮችን ይናገራሉ፡፡ ይህ የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በምድር ላይ መልካምን የሚሰራ ሐጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገገኝምና፡፡›› (መክብብ 7፡20) ሥጋ አሁንም ደካማ ነው፡፡ እስኪሞት ድረስም ደካማ ነው፡፡ እስኪሞት ድረስ ሐጢያት ይሰራል፡፡ ‹‹የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፡፡ ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡›› ሕሊናችን በእግዚአብሄር ፊት ወደ በጎ ሕሊና የሚለወጠው በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ላይ ባለን እምነት ነው፡፡ ሕሊናችን እግዚአብሄርን ጌታችንና አዳኛችን ብሎ መጥራት የሚችለው ጌታ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደ የመሆኑን እውነታ በማመን ነው፡፡
 
 
ለልቦቻችን መንፈሳዊው ምግብ የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ነው፡፡
 
የልብ ምግብ የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ነው፡፡ የልብ ምግብና ሐጢያቶቻችንን ያነጻው ምሳሌ የኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ጥምቀት የሚያድነን ምሳሌ እንደሆነ ተናገረ፡፡
  
1ኛ ጴጥሮስ 1፡22-23ን እንመልከት፡- ‹‹ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ዘላለም በሚኖር በእግዚአብሄር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡›› አሜን፡፡
  
እኛ ዳግም ተወልደናል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመንም የሐጢያቶቻችንን ስርየት ተቀብለናል፡፡ በተጻፈው የጌታ ቃል በማመን ዳግመኛ ተወልደናል፡፡ ‹‹በሕያውና ለዘላለም በሚኖር የእግዚአብሄር ቃል›› ዳግመኛ ተወልደናል፡፡ ሃሌሉያ! ዳግመኛ መወለድ የሚመጣው ሕያው በሆነውና ለዘላለም በሚኖረው ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል መለኪያን የሚያመላክት ቀኖና ነው፡፡ የደህንነት መለኪያ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ደህንነት የሚለካበት የመለኪያ በትር ፈጽሞ አይለወጥም፡፡
  
አጥማቂው ዮሐንስ በዮሐንስ 1፡29 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀው የእግዚአብሄር በግ በሥጋውና በደሙ ያዳነን እውነተኛ የሕይወት እንጀራ ነው፡፡
  
የእግዚአብሄርን ቃል በማመናችን ተቀድሰናል፤ ድነናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› ‹‹ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና፡፡›› (ሮሜ 10፡17፤1፡17) በወንጌል በማመን ጻድቅ መሆን እንችላለን፡፡
  
ተቀድሳችኋልን? --አሜን-- አንዳች ሐጢያቶች የሉባችሁምን? ይህ ወንጌል ነው፡፡ በግሪክ ‹‹ኢዋጂሊዮን›› የምሥራች ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ምንድነው? ጌታ ሥጋውንና ደሙን ለእኛ በመስጠት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ የደመሰሰበት እውነታ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ እንድንቀደስ ፈቅዶልናል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ሐጢያት የሌለበት ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ወስዶ ለሐጢያተኞች መሰቀሉ ነው፡፡ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ያነጻው ውሃው የኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ኢየሱስ በጥምቀቱና በስቅለቱ የዓለምን ሐጢያቶች የወሰደ በመሆኑ እውነታ አማካይነት የተሰጠ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ የእርሱን ጥምቀትና ሞት ይይዛል፡፡ መስቀሉም የመኮነናችን ምሳሌ ነው፡፡ በወንጌል ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሄር ጽድቅ ይህ ነው፡፡