Search

Preken

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 2-3] መገረዝ የልብ ነው፡፡ ‹‹ ሮሜ 2፡17-29 ››

‹‹ ሮሜ 2፡17-29 ››
‹‹አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ፣ በእግዚአብሄርም ብትመካ፣ ፈቃዱንም ብታውቅ፣ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ፣ በሕግም የእውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ የዕውሮች መሪ፣ በጨለማም ላሉ ብርሃን፣ የሰነፎችም አስተማሪ፣ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሄርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሄር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደተጻፈ ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፡፡ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለመገረዝ ሆኖአል፡፡ እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ስርአት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቆጠርለትምን? ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል፡፡ በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፡፡ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም አይደለምና፡፡ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፡፡ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፡፡ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሄር ነው እንጂ ከሰው አይደለም፡፡››
 
 

በልባችን መገረዝ አለብን፡፡

 
‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› በልባችን መዳን አለብን፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- ‹‹መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፡፡ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሄር ነው እንጂ ከሰው አይደለም፡፡›› (ሮሜ 2፡9) በልቦቻችን ውስጥ የሐጢያቶች ስርየት ሊኖረን ይገባል፡፡ በልቦቻችን ውስጥ የሐጢያት ይቅርታ ከሌለን ዋጋ የለውም፡፡ ሰው ‹‹ውስጣዊ ማንነትና ውጫዊ ማንነት›› ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው በውስጡ የሐጢያትን ስርየት መቀበል አለበት፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ለአይሁዶች እንዲህ አላቸው፡- ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› ታዲያ አይሁዶች የገረዙት ምንድነው? እነርሱ የሥጋቸውን ክፍል ገረዙ፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹መገረዝ የልብ መገረዝ ነው፡፡›› አይሁዶች በውጫዊ መልኩ ተገረዙ፡፡ ጳውሎስ ግን መገረዝ የልብ መገረዝ ነው ይላል፡፡ የእርሱ ልጆች ስንሆን እግዚአብሄር በልቦቻችን ውስጥ ይናገራል፡፡
 
ጳውሎስ የተናገረው ስለ ውጫዊ መገረዝ ሳይሆን በልብ ስለሚሆን መገረዝና የሐጢያት ስርየት ነው፡፡ ለዚህ ‹‹የማያምኑ ቢኖሩስ?›› (ሮሜ 3፡3) ሲል ‹‹አንዳንዶች በልባቸው ባያምኑ›› ማለቱ ነው፡፡ እርሱ የተናገረው ስለ ውጫዊ ማመን ሳይሆን ‹‹በልብ ስለለሚደረግ ማመን›› ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ማለቱ እንደሆነና የሐጢያት ስርየትም ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ በእግዚአብሄር ቃል አማካይነት የሐጢያትን ስርየት በልቦቻችን ውስጥ እንዴት ማግኘት እንዳለብንም መማር አለብን፡፡
 
‹‹የማያምኑ ቢኖሩስ?›› ማለት ‹‹አይሁዶች በሥጋ የአብርሃም ዝርያዎች ቢሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛቸው አድርገው ባያምኑስ?›› ማለት ነው፡፡ አለማመናቸው የእግዚአብሄርን ታማኝነት ያስቀራልን? እግዚአብሄር የአብርሃምን ዘሮች ጨምሮ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የመደምሰሱ እውነታ ዋጋ ያጣልን? በፍጹም! በሥጋ የአብርሃም ዘሮች የሆኑት አይሁዶች እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስን በጥምቀቱና በስቅለቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች ያስወገደ አዳኝ የእግዚአብሄር ልጅ አድርገው ቢያምኑ መዳን እንደሚችሉ ጳውሎስ ተናግሮዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሆነው የእግዚአብሄር ማዳንና ጸጋ ከንቱ ሊሆን እንደማይችልም ተናግሮዋል፡፡
 
ሮሜ 3፡3-4 እንዲህ ይላል፡- ‹‹የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሄርን ታማኝነት ያስቀራልን? እንዲህ አይሁን፡፡ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድም በገባህ ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሄር እውነተኛ ይሁን፡፡›› ጌታ በቃሉ ተስፋ ሰጠ፡፡ ተስፋውንም ራሱ በመፈጸም ምዕመናኖችን ቀደሰ፡፡ እግዚአብሄር ጽድቁን ለማሳየትና በተፈረደበት ጊዜ ተስፋ የሰጠውን ለመፈጸም በቃሉ አማካይነት የሚያምኑትን ሊያጸድቃቸው ፈለገ፡፡ እኛም በልባችን የሐጢያት ስርየትን የተቀበልን በቃሉ ሊፈረድብን እንሻለን፡፡ በተፈረደብን ጊዜም በቃሉ ድል መንሳት እንፈልጋለን፡፡
 
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ውጪው ማንነትና ስለ ውስጡ ማንነት ይናገራል፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ‹‹ውጫዊና ውስጣዊ ማንነቱ›› ይናገራል፡፡ እኛም ውጫዊ ማንነትና ውስጣዊ ማንነት ያለን ሲሆን እነርሱም ሥጋና መንፈስ ናቸው፡፡ እኛም ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ ነን፡፡ አሁን ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ይናገራል፡፡
 
ሮሜ 3፡5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ነገር ግን አመጻችን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚያስረዳ ከሆነ ምን እንላለን?›› ጳውሎስ ውጫዊ ማንነቱ ንጹህ ስለመሆኑ መናገሩ አይደለም፡፡ የእርሱ ሥጋ ቆሻሻና እስኪሞት ድረስ ሐጢያት በመስራት የሚቀጥል ነው፡፡ ይህ በዓለም ላይ የሚኖረውን ሕዝብ ሁሉ ይጨምራል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እነዚያን ሕዝቦች ካዳነ ጽድቁን አያሳይምን? ውጫዊ ማንነታቸው ደካማ ቢሆንም እግዚአብሄር ሰብዓዊ ፍጡራንን ካዳነ ጽድቅ አይደለምን? ስለዚህ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቁጣን የሚያመጣ እግዚአብሄር አመጸኛ ነውን? እንደ ሰው ልማድ እላለሁ እንዲህ አይሁን፡፡ እንዲህ ቢሆን እግዚአብሄር በዓለም እንዴት ይፈርዳል?›› (ሮሜ 3፡5-6) ጳውሎስ እኛ የዳንነው ውጫዊ ማንነታችን ንጹህ ስለሆነ እንዳይደለ ያብራራል፡፡
 
እኛ ውጫዊና ውስጣዊ ማንነቶች አሉን፡፡ ሆኖም ጳውሎስ ‹‹የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሄርን ታማኝነት ያስቀራልን? መገረዝ የልብ ነው›› በማለት በልብ ጉዳይ ላይ ያተኩራል፡፡ እምነታችን ሐጢያት በሚሰራውና ድካሞች ባሉበት ውጫዊ ማንነት ላይ በመመስረት አንድ ጊዜ ጻድቅ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ሐጢያተኛ የምንሆን ከሆነ ይህ እውነተኛ እምነት አይደለም፡፡
 
 

ውጫዊው ሰው እስኪሞት ድረስ ሁልጊዜም ሐጢያት ይሰራል፡፡

 
ሐዋርያው ጳወሎስ ተስፋውን በውጫዊ ማንነቱ ላይ አላደረገም፡፡ ሐጢያቶቻቸው የተደመሰሱላቸውም ሰዎች ውጫዊና ውስጣዊ ማንነቶች አሉዋቸው፡፡ ውጫዊ ማንነታቸውን ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል? ተስፋ ከመቁረጥ በቀር ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ እስቲ ውጫዊ ማንነታችንን እንመልከት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥሩዎች ነን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ክፉዎች ነን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ውጫዊው ማንነታችን ከክርስቶስ ጋር እንደተሰቀለ ይናገራል፡፡ ውጫዊው ማንነታችን ሞቶዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የውጫዊ ማንነታችንን ሐጢያቶች በሙሉ ይቅር ብሎዋል፡፡
 
እኛ የዳንን ሰዎች ራሳችንን በምንመለከትበት ጊዜ በተደጋጋሚ በውጫዊ ማንነታችን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ውጫዊ ማንነታችን ጥሩ ሲሆን ተስፈኞች እንመስላለን፡፡ ነገር ግን እንደጠበቅነው ሳይሆን ሲቀር ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ በውጫዊ ማንነታችን ተስፋ ስንቆርጥ እምነታችን እንደተፈረካከሰ ወደ ማሰቡ እናዘነብላለን፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ውጫዊ ማንነታችን ቀድሞውኑም ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎዋል፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያገኙትም ቢሆኑ በሥጋዊ አካሎቻቸው ሐጢያትን ይሰራሉ፡፡ ያ ግን ሐጢያት ነውን? አዎ ሐጢያት ነው፡፡ ነገር ግን የሞተ ሐጢያት ነው፡፡ ሐጢያቶቹ ከጌታ ጋር ወደ መስቀል ስለተወሰዱ ያም ሐጢያት ሞቷል፡፡ ውጫዊው ሥጋ የሚሰራው ሐጢያት የከፋ ችግር አይደለም፡፡ የከፋው ነገር ልቦቻችን በጌታ ፊት ቀና አለመሆናቸው ነው፡፡
 
 
እግዚአብሄርን በልባችን ማመን አለብን፡፡
 
ጻድቁ የሐጢያት ስርየትን ከማግኘቱ በፊት ብዙ ሐጢያቶች ይገለጣሉ፡፡ ስለዚህ የደህንነታችንን መሰረት በየቅጽበቱ ሐጢያት በሚሰራው ውጫዊ ሰው ላይ የምናደርግ ከሆንን የእግዚአብሄር ደህንነት እንከን ያለው ይሆናል፡፡ እምነታችንን በውጫዊው ሥጋ ምግባሮች ላይ የምንመሰርት ከሆነ እምነታችን አብርሃም ይዞት ከነበረው የእግዚአብሄር እምነት ያፈነግጣል፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹መገረዝም የልብ ነው፡፡›› እኛ የምንቀደሰውና ጻድቃን የምንሆነው በውጫዊው ሰዋችን ምግባሮች ሳይሆን በልብ በማመን ነው፡፡ ቅድስና ውጫዊው ማንነታችን እግዚአብሄር የተናገረውን በማመን ወይም ባለማመኑ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ይህንን አስተዋላችሁትን? ችግሩ ውጫዊና ውስጣዊ ማንነት ያለንና እነርሱም የተቆራኙ መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በውጫዊው ሰው ላይ የበለጠ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ውጫዊው ማንነታችን ጥሩ ነገር ሲያደርግ እንመካለን፡፡፡ ጥሩ ነገር ካላደረገ ግን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ጳውሎስ ይህ ትክክለኛ እምነት አይደለም ይላል፡፡
 
‹‹መገረዝም የልብ ነው፡፡›› ተጨባጩ እውነት ምንድነው? በልባችን የምናውቀውና የምናምነው እንዴት ነው? በማቴዎስ 16 ላይ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- ‹‹ሰዎች እኔ ማን እንደሆንሁ ይላሉ?›› ያን ጊዜ ጴጥሮስ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሄር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› በማለት እምነቱን መሰከረ፡፡ ጴጥሮስ በልቡ እንደዚያ አመነ፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው፡- ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን የሰማይ አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና የተባረክህ ነህ፡፡›› ኢየሱስ የጴጥሮስ እምነት ትክክለኛ እምነት እንደነበር ተናግሮዋል፡፡
 
አብርሃም ልጅ አልነበረውም፡፡ እግዚአብሄርም ልጅ እንደሚሰጠውና የብዙ አሕዛቦች አባት እንደሚሆን ቃሉንና ተስፋውን ሰጠው፡፡ እግዚአብሄርም ለእርሱና ከእርሱም በኋላ ለዘሮቹ አምላክ እንደሚሆንም ነገረው፡፡ እግዚአብሄር ለአብርሃም በእርሱና በአብርሃም መካከል ለሚሆነው ቃል ኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ ቤተሰቡና ዘሮቹ ሁሉ እንዲገረዙም ነገረው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹በሥጋችሁ መገረዝ ላይ ያሉት ጠባሳዎች እኔ አምላካችሁ ለመሆኔ ኪዳን ነው›› አለው፡፡ አብርሃም ኪዳኑን በልቡ አመነ፡፡ እግዚአብሄር የእርሱ አምላክ እንደሚሆን አመነ፡፡ በልቡም ባረከው፡፡ እግዚአብሄር ከእርሱም በኋላ ለዘሮቹ አምላክ እንደሚሆንም አመነ፡፡ በራሱ በእግዚአብሄርም አመነ፡፡
 
 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባችን በማመን ጻድቃን ሆነናል፡፡
 
እግዚአብሄር አምላካችን አዳኛችን መሆኑን በልባችን ስላመንን ጻድቃን ሆነናል፡፡ በልቦቻችን በማመን ድነናል፡፡ በሌላ አንዳች ነገር አልዳንም፡፡ እግዚአብሄር አምላካችን እንደሆነና በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደደመሰሰ በማመናችን ጻድቃን ሆነናል፡፡ በልባችን ማመን ያድነናል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና፡፡›› (ሮሜ 10፡10)
 
በዚህ ጊዜ ግልጽ ልናደርገው የሚገባው ነገር ጻድቃን የተደረግነው በሥጋችን ሰናይ ምግባሮች ሳይሆን በልቦቻችን በማመናችን መሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስ ‹‹ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ ነገር ግን አንድ ቅድመ ሁኔታ አለ፡፡ ልጄ የምትሆኑት ሐጢያት ማድረግ ስታቆሙ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ከተሳናችሁ ልጄ አትሆኑም›› በማለት በውጫዊ ማንነታችን ላይ ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጥ ጻዳቃን ባልሆንን ነበር፡፡
 
በልቦቻችን በማመን ጻድቃኖች ሆነናል፡፡ እግዚአብሄር በውጫዊ ማንነታችን ላይ ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጥ ኖሮ ጻድቃን መሆን እንችል ነበርን? እግዚአብሄር በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ፣ በመሰቀልና በእናንተ ፋንታ በመኮነን ሐጢያቶቻችሁን ወስዶ እንዳዳናችሁ ታምናላችሁን? ይህንን የምታምኑት እንዴት ነው? በልባችሁ አታምኑትምን? እግዚአብሄር ‹‹ትናንሽ ድካሞቻችሁን ይቅር እላለሁ፡፡ ትላልቆቹን ግን ይቅር አልልም፡፡ ይህንን ቅድመ ሁኔታ የማታሟሉ ከሆናችሁ ደህንነታችሁን እሰርዘዋለሁ›› ቢል ኖሮ ፈጽሞ መዳን ትችሉ ነበርን?
 
 

ውጫዊውን ሰው ከውስጣዊው ሰው መለየት አለብን፡፡

 
ውጫዊው ሰው ማለትም ሥጋችን ሁልጊዜም ደካማ ነው፡፡ በራሱ ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ ሊደርስ አይችልም፡፡ እኛ ጻድቃን የሆንነው በእግዚአብሄር ፊት በልቦቻችን በማመን ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ በልቦቻቸው የሚያምኑትን እንደሚያድናቸው ተስፋ ሰጥቶአልና፡፡ እግዚአብሄር ያደረገውንና ኢየሱስም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደና እንደደመሰሰ የሚያምነውን እምነታችን በማየት ጻድቅ ልጆቹ አድርጎናል፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ኪዳን ነው፡፡ እርሱም ተስፋውን በመፈጸም አድኖናል፡፡
 
እግዚአብሄር በልቦቻችን ውስጥ እምነትን ሲያይ እኛም የእርሱ ሕዝብ እንደምንሆን ይናገራል፡፡ ውጫዊ ማንነታችንን ከውስጣዊው ማንነታችን መነጠል አለብን፡፡ የደህንነት መለኪያችንን የውጫዊው ሥጋ ምግባሮች አድርገን የምናስቀምጥ ከሆንን በዓለም ላይ ያለ ማንም ሰው የሐጢያት ስርየትን ሊያገኝ አይችልም፡፡ ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› የዳንነው በልቦቻችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን ነው፡፡ ይህንን ተረድታችኋልን? ‹‹ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና፡፡›› (10፡10) ሐዋርያው ጳውሎስ ውጫዊውን ሰው ከውስጣዊው ሰው በግልጽ ነጥሎታል፡፡
 
ውጫዊው ሰዋችን ከውሻ ትፋትም የከፋ ነው፡፡ አይረባም፡፡ አብርሃምን ምሳሌ አድርገን መጠቀም አያስፈልገንም፡፡ ራሳችሁን ተመልከቱ፡፡ የማይረባውን ሥጋችሁን ተመልከቱት፡፡ ሥጋ ከፍ ያለ ማህበራዊ ሥልጣን ለመያዝና በከበሬታ ለመኖር በመሞከር ሸፍጥን ይጠቀማል፡፡ ሥጋ ሁልጊዜም የራሱን ፍላጎት ከማሟላት በስተቀር ሌላ አንዳች የሚያደርገው ነገር የለምን? ሥጋ በሚያስበውና በሚሰራው ነገር ቢፈረድበት ኖሮ በቀን ውስጥ ከአስራ ሁለት ጊዜ በላይ ይፈረድበት ነበር፡፡ ሥጋ የእግዚአብሄር ተቃዋሚ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ትኩረት የሚያደርገው በውስጣዊው ሰዋችን ላይ ብቻ ነው፡፡ ስለ ውጫዊው ሰው አይገደውም፡፡ ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን በልባችን በተጨባጭ ማመናችንን ሲያይ ያድነናል፡፡ ከሐጢያቶቻችን በሙሉ እንዳዳነንም ይነግረናል፡፡
 
 
በራሳችን እሳቤዎች ፈጽሞ መዳን አንችልም፡፡
 
እስቲ አስተሳሰቦቻችንን እንመልከት፡፡ በአስተሳሰቦቻችን ብቻ ማመን እንደምንችል እናስባለን፡፡ ‹‹እግዚአብሄር ስላዳነኝ ድኛለሁ›› ብለን በማሰብ በሥጋ አስተሳሰቦች ማመን እንችላለን፡፡ ነገር ግን በአስተሳሰቦቻችን መዳን አንችልም፡፡ የሥጋ አሳብ በየጊዜው ይለዋወጣል፡፡ ሁልጊዜም ክፉ ነገርን ያደርጋል፡፡ ይህ እውነት ነውን? የሥጋ አእምሮ የሚያስባቸው እሳቤዎች እንደ ፍትወቱ ይህንንና ያንን ማድረግ ይፈልጋል፡፡
 
አንድ ሰው እምነቱን በእሳቤዎቹ ላይ አደረገ እንበል፡፡ አሁን የያዘው አስተሳሰብ ከቀድሞው አስተሳሰብ ማለትም ‹‹ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሐጢያቶችን ሁሉ ከመውሰዱ›› ጋር በመስማማቱ ሊመካ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሥጋ አስተሳሰቦች የጸኑ ስላይደሉ አንድ ጊዜ በደህንነት ላይ ያለውን ደካማ አስተሳሰብ ቅንጣት የምታህል ጥርጣሬ ከወረረችው ዳግመኛ በደህንነቱ ሊመካ አይችልም፡፡ በሥጋ እሳቤ ላይ ተመስርቶ በተሳሳተ መንገድ የተገነባ እምነት በጥርታሬ ምት ይወድቃል፡፡
 
የእምነታችንን መሰረት በራሳችን አስተሳሰቦች ላይ ከጣልን በእርሱና በእውነት ከልብ ማመን አንችልም፡፡ እንደዚህ ያለ እምነት በአሸዋ ላይ እንደተሰራ ቤት ነው፡፡ ‹‹ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፡፡ ወደቀም፡፡ አወዳደቁም ትልቅ ሆነ፡፡›› (ማቴዎስ 7፡27)
 
ስለዚህ በአስተሳሰቦች የሚያምን ሰው እምነት በእግዚአብሄር ቃል ላይ ከተመሰረተ እምነት በጣም የራቀ ነው፡፡ እግዚአብሄር ‹‹በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድም በገባህ ጊዜ ትረታ ዘንድ›› (ሮሜ 3፡4) ብሎዋል፡፡ ደህነንታችን በእግዚአብሄር ቃል ላይ መመስረት አለበት፡፡ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፡፡ ቃል በሰዎች አምሳል ሆኖ ወደ ምድር መጣ፡፡ ኢየሱስ አዳነን፡፡ በምድር ላይም 33 ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ እርሱ አስቀድሞ ለባሮቹ የነገራቸው የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ የሆነውን የተስፋ ቃል ይጽፉ ዘንድ ሐዋርያቶቹን መራቸው፡፡ እግዚአብሄር የተናገረውን ጽፎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀመጠው፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ ውስጥና ከቃሉ ጋር ተገለጠ፡፡ በቃሉ ተናገረ፡፡ በቃሉም አዳነን፡፡
 
‹‹አንዳንድ ጊዜ የዳንሁ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን የጌታን ማዳን ማመን አልችልም›› ብለን እያሰብን በእግዚአብሄር ቃል ሳናምን በአስተሳሰቦቻችን መዳን አንችልም፡፡ ምክንያቱም አስተሳሰቦቻችን ሁልጊዜም ስለሚቀያየሩ ሁሌም እውነተኛ አይደሉምና፡፡
 
ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ መገረዝም የልብ ነው ይላል፡፡ የእርሱን ጽድቅ በልባችን እናምነዋለን፡፡ ልባችሁ ቃሉን ሲያምን እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይህን ቃል እንደገባና ኪዳኑንም እንደፈጸመ በግልጽ ይመሰክራል፡፡ በአዲስ ኪዳንም በዚህ አይነት መንገድ በቃሉ አዳነን፡፡ ቃሎቹን በልባችን በማመን ድነን የእግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡
 
 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባችን በማመን ከሐጢያቶቻችን ድነናል፡፡
 
ልባችን በእግዚአብሄር በማመኑ በእምነት ድነናል፡፡ የሥጋ አእምሮ አስተሳሰባችን ግን እርሱን አያምነው ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች የሆንነው በልቦቻችን በማመን እንጂ በውጫዊው ሰው ምግባሮች ወይም አስተሳሰቦች በማመን አይደለም፡፡ ቃሉን በልባችን በማመናችን የእግዚአብሄር ልጆች እንደሆንን ግልጽ ነው፡፡ በልባችሁ ታምናላችሁን? ኢየሱስ አዳኛችሁ እንደሆነ ከልባችሁ ታምናላችሁን? በእግዚአብሄር ልጅ የሚያምን ሰው በራሱ ምስክር አለው፡፡ ኢየሱስ ፈጽሞ እንዳዳናችሁ የራሳችሁ የተሞክሮ ምስክር ሳይሆን የቃሉ ምስክር አላችሁን? በልባችሁ ውስጥ የእግዚአብሄር ቃል አለን? እወነተኛ እምነት መያዝ ማለት በእምነት መዳን ማለት ነው፡፡
 
የእግዚአብሄርን ቃል በልባችን በማመን የሐጢቶቻችንን ስርየት እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን የውጫዊው ሰዋችንን ድካሞች በምንመለከትበት ጊዜ በተደጋጋሚ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ያን ጊዜ በእግዚአብሄር ላይ ካለን እምነት ለማፈግፈግ እንቸኩላለን፡፡ እውነትን በሙላት ያልተረዳ ሰው ግራ መጋባት ውስጥ ያለ ሰው ነው፡፡ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የእምነታቸውን መለኪያ በምግባሮቻቸው ላይ አድርገውታል፡፡ ያ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እምነታችንን በራሳችን አስተሳሰቦች መለካት የለብንም፡፡ እምነታችንን በሥጋችን ላይ ማኖር የለብንም፡፡ ምክንያቱም ሥጋ ጥቅም የለውምና፡፡ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ሰው የሚጸድቀው በእግዚአብሄር ቃል በልቡ ሲያምን እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ በእምነት ብቻ እንጂ በአስተሳሰቦች ወይም በምግባሮች አንድንም፡፡ ሐጢያት መስራታችን ወይም ጥሩ ማድረጋችን ከእግዚአብሄርና ከክብሩ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡
 
ስለዚህ እውነተኛ እምነት ማለት የእግዚአብሄርን ቃል ማለትም የደህንነትን እውነት በልብ በማመን መዳን ማለት ነው፡፡ ልባችን ሲሳሳት እምነታችንም ይሳሳታል፡፡ ልባችን ትክክል ሲሆን እምነታችንም ትክክል ይሆናል፡፡ ትክክለኛ ባህርይ የሚመጣው ከትክክለኛ እምነት ነው፡፡ እምነት ሲደክም የተሳሳተ ባህርይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን እግዚአብሄር እግዚአብሄር ልብን ይመረምረዋል፡፡፡ እግዚአብሄር ልብ ትክክል ወይም የተሳሳተ እንደሆነ ይመለከታል፡፡ እግዚአብሄር በልባችን የምናምን መሆን ወይም አለመሆናችንን ይመለከታል፡፡ ገባችሁ? እግዚአብሄር ልባችንን ሲመለከት ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን እናምነው እንደሆነ ይመለከታል፡፡ በልባችሁ ታምናላችሁን?
 
እግዚአብሄር እኛን ሲመለከት በልባችን እናምን እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያጤናል፡፡ ልባችንን ይመለከታል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ልባችንን መመርመር አለብን፡፡ መገረዝ የልብ ነው፡፡ በልባችሁ ታምናላችሁን? እግዚአብሄር ልብን ይመለከታል፡፡ በእርግጥ እውነትን እናውቅ እንደሆነና ያንንም መከተል እንፈልግ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ መከተልና ባቃሉ ማመን እንፈልግ እንደሆነ ይመለከታል፡፡
 
 
ዳግም በመወለድ ትክክለኛ ጊዜ ላይ ትልቅ ትኩረት የሚያደርግ የሐይማኖት ቡድን አለ፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረገው ነገር ትክክለኛ እውቀት መያዝና ይህንኑም በልባችሁ ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች እንዳልዳኑ የሚናገር አንድ የሃይማኖት ቡድን አለ፡፡ እኔን እንዲያስተውሉኝና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዲያስተምሩ እፈልጋለሁ፡፡ ሐጢያቶቻችሁ ተደምስሰዋልን? አሜን፡፡ ይህንን በልባችሁ ታምናላችሁን?
 
ነገር ግን እምነቶቻችን ትክክል እንዳልሆኑ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ እኛ በሳይንስ የተረጋገጠውን ብቻ እንጂ የተጻፈውን ቃል ማመን እንደሌለብን ይገራሉ፡፡ ፍጹም የሆነ ደህንነትና ፍጹም እምነት ያ ነው ይላሉ፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው ዳግም የተወለደበትን ትክክለኛ ጊዜ (ሰዓት፣ ቀንና ወር) ማወቅ አለበት ይላሉ፡፡ ወንድም ሃዋንግ ከእነርሱ አንዱ ከሆነው ጋር በተገናኘ ጊዜ ግለሰቡ ወንድም ሃዋንግን ዳግም የተወለደው መቼ እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡ ስለዚህ ወንድም ሃዋንግ ትክክለኛውን ቀንና ሰዓት እንደማያውቅ ነገር ግን ባለፈው ዓመት በአንድ ወቅት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግም እንደተወለደ መለሰለት፡፡ ያን ጊዜ ወንድም ሃዋንግ እንዳልዳነ ነገረው፡፡
 
መቼ ዳግም እንደተወለድን ብናሰላስል ትክክለኛውን ሰዓት፣ ቀን፣ ወርና ዓመት መናገር እንደምንችል እርግጥ ነው፡፡ ማለዳ፣ ቀትር፣ በምሳ ሰዓት ወይም በእራት ሰዓት እንደሆነም መናገር እንችላለን፡፡ ነገር ግን ደህንነት በልብ የማመን ጉዳይ ነው፡፡ ትክክለኛውን ጊዜ ባታውቁትም ግድ የለም፡፡
 
 
መገረዝ የልብ መገረዝ ነው፡፡
 
ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ ለእነዚያ ሐጢያቶች በመኮነን በእኛ ፋንታ ተሰቀለ፡፡ ስለ መተላለፋችንም ቆሰለ፡፡ ስለ በደላችንም ደቀቀ፡፡ እርሱ የውጫዊና የውስጣዊ ማንነታችንን ሐጢያቶች በሙሉ አስወገደ፡፡ መንፈሳችንም ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በቅናት እንዳልዳንን ቢነግሩንም አሁን እርሱ እንደሚወደው ጌታን መከተል እንችላለን፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውጫዊው ሰው ምን ይላል? የሐጢያት ስርየትን ከተቀበልን በኋላ ብዙ ድካሞች የሚገለጡ ይመስላል፡፡ ድካሞቻችን በሙሉ ገና አልተገለጡም፡፡ ብዙ አለመብቃቶችም ይገለጣሉ፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር አምላካችን እንደሆነና ኢየሱስም በጥምቀቱ አማካይት በዮርዳኖስ ወንዝ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደና እንደተሰቀለ የምናምን ከሆንን እንድናለን፡፡
 
እኛ ዳግም በተወለዱበት ቀን ላይ ትኩረት ከሚያደርጉና በሳይንስ የተረጋገጠውን ብቻ ከሚያምኑ ጋር አንፎካከርም፡፡ እነርሱ እንዳልዳኑ ግልጽ ነው፡፡ ጻድቃን ለመሆን በልባችን እናምናለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እንደሆነ ታምናላችሁን? አሜን፡፡ እምነት የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ጌታ ልቦቻችንን ይመራል፡፡ ጌታ እኛ የእርሱ ጻድቅ ልጆች እንደሆንንና እምነታችንም እውነተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እርሱ ልባችንን ይባርካል፡፡ በእምነትም በልባችን እንድንከተለው ይፈልግብናል፡፡ በልባችን አምነን ከእርሱ ጋር በምንጓዝበት ጊዜ እግዚአብሄር ይመራናል፤ ይባርከንማል፡፡
‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› በልባችን በማመን ድነናል፡፡ በምድር ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ወንጌልን በልባቸው በማመናቸው እንደዳኑ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በእምነታቸው ላይ ምግባሮችን እንደሚጨምሩ የታወቀ ነው፡፡ የውጫዊውን ሰው ምግባሮች የእምነታቸው መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቱዋቸዋል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ወደ ደህንነት እንደማይመራቸው ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም በልብ ማመንንና የራሳቸውን ሰናይ ምግባሮች አብረው ይደባልቁዋቸዋልና፡፡
 
ከዚህ የተነሳ ውጫዊው ሰው ምን ያህል ጥሩ ነገር እንደሚያደርግና እንዴት ብዙውን ጊዜ የንስሐ ጸሎቶችን እንደሚያቀርቡ ይጨነቃሉ፡፡ ከሐጢያቶቻቸው እንደዳኑ ቢያስቡም ከደህንነት የራቁ ናቸው፡፡
 
 
እግዚአብሄር ልብን ይመለከታል፡፡
 
በልባችን ጻድቃን ለመሆን እናምናለን፡፡ ይህ ከውጫዊው ሥጋ የተነጠለና ከምግባሮቻችን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ደህንነት ራሱ ከምግባሮቻችን ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም፡፡ ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ እንደተደመሰሱ ከተማራችሁ በኋላ ተጽናናችሁን? ጌታን በደስታ ማገልገል ትፈልጋላችሁን? ወንጌልን በደስታ ትሰብካላችሁን? በእርሱ ያማረ ሚሽን ውስጥ ራሳችሁን ማሳተፍ ትፈልጋላችሁን? ልብ አመስጋኝና ደስተኛ ሆንዋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር የልብ እምነታችንን ተቀብሎታልና፡፡ ስለዚህ ልብ በእግዚአብሄር ፊት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡