Search

Preken

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-7] የጌታ ዳግም ምጽአትና የሺህው ዓመት መንግሥት ‹‹ሮሜ 8፡18-25›› 

‹‹ሮሜ 8፡18-25›› 
‹‹ለእኛ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሄርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና፡፡ ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፡፡ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፡፡ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሄር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን፡፡ እርሱም ብቻ  አይደለም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን፡፡ በተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡›› 
 
 
በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን የጸደቁ ሰዎች የሰማይን ክብር ተቀብለዋል፡፡ ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል ሲሉ መከራን የሚቀበሉት ሰዎችን ሁሉ በሰማይ ክብር ለመሸፈን ነው፡፡ ምዕመናን ራሳቸውን ለእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል ቀድሰው በመስጠት በምድር ላይ መከራን መቀበላቸውና የክርስቶስ መከራ ተካፋይ መሆናቸው ክቡርና ጽድቅ ነውና፡፡ 
 
ከልባችን ለምናከብረውና ለምናወድሰው አምላክ መከራን መቀበል ክብር አይደለምን? በእርግጥም ነው፡፡ የከበረ መከራ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች ለእርሱ ጽድቅ የሚሰቃዩት ለዚህ ነው፡፡ አሁን የምትሰቃዩት ለማነው? የምትሰቃዩት ለዓለምና ለሥጋችሁ ነውን? የዓለምን ስቃይ መቀበል ለነፍሳችሁ ምን ጥቅም አለው? ለእግዚአብሄር ጽድቅ መከራን ተቀበሉ፡፡ በእርሱም እመኑ፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር ክብር በእናንተ ላይ ይሆናል፡፡ 
 
 

ወደፊት የምንባረክበት ውርስ፡፡ 

 
ስለምንቀበለው ርስት እናስብ፡፡ በሰማይ የምንቀበለው ርስት በአዲሱ ሰማይና ምድር ከኢየሱስ ጋር የመንገስ ሽልማት ነው፡፡ በሺህው ዓመት መንግሥትና በዘላለማዊው የእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ የምንቀበለው ክብር በጣም ታላቅ በመሆኑ ልክ ሊኖረው አይችልም፡፡ የሚጠብቃቸውን ማወቅ የሚችሉትና ይህንን ክብር የሚቀበሉት ራሳቸው ዳግም የተወለዱ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ 
   
 
ማይወዳደረው ክብር፡፡ 
 
‹‹ለእኛ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡›› (ሮሜ 8፡18)  
ምዕመናኖች የሚቀበሉትን ክብር ከአሁኑ ዘመን ስቃያቸው ጋር ሲያወዳድሩት ክብራቸው ከስቃያቸው በጣም እንደሚልቅ ጳውሎስ ተናግሮዋል፡፡ ይህ ሙሉ በሙሉ እውነት ነው፡፡ እኛን የሚጠብቀን ክብር አሁን ከምንሸከመው ስቃይ በጣም እንደሚልቅ በሚገባ የተረጋገጠ ነው፡፡ 
 
 
የፍጥረት ናፍቆት፡፡ 
 
‹‹የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሄርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና፡፡ ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፡፡ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፡፡ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሄር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው፡፡›› (ሮሜ 8፡19-21) 
 
የእግዚአብሄር ፍጥረት በሙሉ ከሐጢያት ባርነት መፈታትን ይናፍቃል፡፡ ለመፈታትም የእግዚአብሄር መንግሥት በምድር ላይ መመስረት አለበት፡፡ እነዚህ ፍጥረቶች እንደዚሁ የእግዚአብሄር ልጆች የሺህው ዓመት መንግሥት ባለቤቶች እንዲሆኑ ይጠባበቃሉ፡፡ ስለዚህ ፍጥረታት ሁሉ የእግዚአብሄር ልጆች የአምላክን ክብር ለብሰው ከእርሱ ጋር የሚነግሱበትንና የእግዚአብሄር መንግሥት የሚመጣበትን ቀን ይጠብቃሉ፡፡ 
 
 
የሰውነታችንን ቤዛነት መጠባበቅ፡፡  
 
‹‹ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን፡፡ እርሱም ብቻ  አይደለም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን፡፡ በተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡›› (ሮሜ 8፡22-25) 
 
በእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ድነዋል፡፡ የእግዚአብሄር መንግሥት የሚመጣበትን ቀን በመከራቻቸው እየታገሱ ይጠባበቃሉ፡፡ እነርሱ ያለ ማቋረጥ ለወንጌል መከራን ይቀበላሉ፡፡ በመከራ አማካይነትም ለእግዚአብሄር መንግሥት ያላቸው ተስፋ ይበልጥ ቀና ይሆናል፡፡ ይህ ለእነርሱ ተፈጥሮአዊ ነው፡ የሚጠብቁት በሥጋ ዓይን የሚታየውን ተስፋ ሳይሆን የማይታየውን የእግዚአብሄር መንግሥትና የራሳቸውን መለወጥ ነው፡፡ 
 
በዛሬው ዓለም ሰዎችና ሌሎች ነገሮች ሁሉ በቃላት ሊገለጥ የማይችል የድካም ሕይወትን ይኖራሉ፡፡ ጊዜው እየነጎደ ሲሄድ ዓለም ይቀየራል፡ ቴክኖሎጂና ሥልጣኔም ሲያድግ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ያላቸው ተስፋ በልባቸው ውስጥ ያድጋል፡፡ ወደፊት በምድር ላይ ገነትን ማየት ይናፍቃሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ እድገት እያለ ሒደቱ ለምን እንደዘገየ ግራ በመጋባት ይጨነቃሉ፡፡ ይቀበጠበጣሉ፡፡ ስልቹ ይሆናሉ፡፡ ኮምፒውተሮች፣ አውቶሞቢሎችና ሌሎች የቴክኖሎጂና የሳይንስ ግኝቶች ቀጥለዋል፡፡ ነገር ግን የሰውን ሳቅ መስማት በጣም አዳጋች ነው፡፡ 
 
ለወደፊቱ የሰው ዘር ተስፋ አለን? መልሱ የሚያሳዝን የለም ነው፡፡ በዮሐንስ ራዕይ ቃል መሰረት እንደዚሁም በሳይንቲስቶች አመለካከት በውሃ ዕጥረት፣ በኦዞን ንጣፍ መሸንቆር፣ በድርቅና ብዙ ሰዎችም በጥማትና በሙቀት እንዲሞቱ በሚያደርገው የደን ጭፍጨፋ ጥፋቶች ይጠብቁናል፡፡ በልባችሁ እነዚህ ሁሉ ጥፋቶች እንደሚጠብቁን ይታወቃችኋልን?
 
እየኖርን ያለነው በሚያስደስት ዓለም ውስጥ ነውን? በአንዳንድ ሁኔታዎች የሚያስደስት ይመስል ይሆናል፡፡ በገንዘብ ሊገዛ የማይችል ነገር ምን አለ? ነገር ግን ንጹህ ውሃና ጽዱ አካባቢ ያስፈልገናል፡፡ ሆኖም የኦዞን ንጣፍ በመሳሳቱ ገዳይ የሆኑ ጨረሮች ከባቢ አየሩን ሰንጥቀው ያልፉ ዘንድ እየፈቀደ ነው፡፡ የአልትራ ቫዮሌት ጨረሮች ተክሎችን እየቀየሩና የሰዎችን ልብ እያወኩ ነው፡፡ ሰዎች ‹‹ይህ ዓለም ምን ይገጥመው ይሆን?›› በማለት በጣም እየተጨነቁ ነው፡፡ እኛ ዳግም የተወለድን ሰዎች ግን ከዓለም ሰዎች በተቃራኒ ለመጀመሪያው ትንሳኤና ለሺህ ዓመትም ከኢየሱስ ጋር ለመንገስ የሚያበቃን እምነት አለን፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ራሱ በጩኸት፣ በመላዕክት አለቃ ድምጽና በእግዚአብሄር መለከት ዳግመኛ ከሰማይ እንደሚወርድ ይነግረናል፡፡ (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16) ጥያቄው እርሱ የሚመጣው ‹‹መቼ›› ነው የሚለው ነው፡፡ ጌታችን በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ሰዎች ለመውሰድ እንደሚመጣ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ እኛም ያንን ቀን እየጠበቅን ነው፡፡ 
 
ዳግም የተወለዱ ሰዎች በዚህ ወንጌል ያምናሉ፡፡ ‹‹ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ሐጢያቶቼ ወደ እርሱ ተላልፈዋል፡፡ እኔም ጌታ በእኔ ምትክ ለሐጢያቶቼ የተፈረደበት አዳኝ እንደሆነ አምናለሁ፡፡›› እግዚአብሄር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደህንነትን ሰጥቶናል፡፡ እርሱ የራሱን ሕዝብ ከሙታን ለማስነሳትና በዚህ ምድር ላይ ለሺህ ዓመት እንዲነግሱ ለመፍቀድ ዳግመኛ ይመጣል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንባቢዎቹ መደርደር የሚገባው የሥዕል እንቆቅልሽን ይመስላል፡፡ 
 
ኢየሱስ በመጀመሪያ በመጣ ጊዜ ሐጢያተኞችን ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለመጥራት መጣ፡፡ በጥምቀቱም ሐጢያቶቻቸውን በሰውነቱ ተሸከመ፡፡ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም ስለ እነርሱ ተኮነነ፡፡ አሁን በሰማይ የሚኖረው ጌታ ዳግም ሲመጣ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑትን ሁሉ ለሺህ ዓመት ከእርሱ ጋር ይነግሱ ዘንድ ከሙታን ያስነሳቸዋል፡፡ 
    
 

የሺህው ዓመት መንግሥት፡፡  

 
በዚህ ዓለም ላይ ሌሎችን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡ እነርሱ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወንጌል ለእያንዳንዱ የጠፋ ነፍስ በማቅረብ ለክርስቶስ የሚማርኩ ብቸኛ ሰዎች ናቸው፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ለእግዚአብሄር ልጆች ወሮታን ይመልሳሉን? አይመልሱም፡፡ ታዲያ ማን ይመልሳል? ኢየሱስ ዳግመኛ ሲመጣ ዳግም የተወለዱትን ከሙታን በማስነሳትና ለሺህ ዓመት እንዲነግሱ በመፍቀድ ወሮታውን ይመልስላቸዋል፡፡ 
 
የሺህው ዓመት መንግሥት ለእኛ ዳግም ለተወለድን ምዕመናን ነው፡፡ ጌታችን ዳግም ሲመጣ ይህ የአሁኑ ዓለም ቢወደድም በአዲስ ዓለም እንኖራለን፡፡ እዚያም ከእርሱ ጋር እንድንነግሥና እስከፈለግነው ድረስ በደስታና በሐሴት እንድንኖር ይፈቅድልናል፡፡ 
 
ጳውሎስ በሮሜ 8፡23 ላይ እንዲህ ብሎዋል፡- እርሱም ብቻ  አይደለም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን፡፡›› እናንተም ያንን ቀን እየጠበቃችሁ ነውን? የመንፈሰ በኩራት ያለን እኛም ብንሆን የሰውነታችንን ቤዛነት በጉጉት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን፡፡ እግዚአብሄር ከሙታን እንደሚያስነሳን፣ ሰውነታችንን እንደሚለውጥና ከእርሱ ጋር እንድንኖር እንደሚፈቅድ ተናግሮዋል፡፡ እኛ ጻድቃን ሆነን ዳግም የተወለድን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእርሱን ዳግም ምጽአት ተስፋ እናደርጋለን፤ እንጠብቅማለን፡፡ 
 
እኛ በውስጣችን እንቃትታለን፡፡ ዳግም የተወለዱ ምዕመናን ይህ ዓለም ምን እንደሚሆን ያውቃሉ፡፡ ጠንቋዮች የወደፊቱን መተንበያቸው ምንም ማለት አይደለም፡፡ ዳግም የተወለዱ ምዕመናን ወደፊት ምን እንደሚሆን በትክክል ያውቃሉ፡፡ ዓለም እኛ በትክክል በተነበይነው መሰረት ቢለወጥ እንኳን አሁን ማንም አያምነንም፡፡ በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል ሰዎች ግን ያለ ምንም መኩራራት ይጠብቃሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የማያውቁ ሌሎች ሰዎች ቢያንጓጥጡዋቸውም በተስፋ ይኖራሉ፡፡ 
 
ስለዚህ የማያምኑ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ደህንነትን መቀበል አለባቸው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻቸውን እንደወሰደና በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተኮነነ ማመን አለባቸው፡፡ የመጨረሻው ቀን ሲመጣ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መግባት የሚችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ያን ጊዜ ወሮታችን ይመለሳል፡፡ የዘላለም ሕይወት ይኖረን ዘንድም ወደ መንግሥቱ ይገባሉ፡፡ 
አዝናችኋልን? ደክማችኋልን? ወይስ በሕይወታችሁ ረክታችኋል? ከመሞታችን በፊት ኢየሱስ እንዴት አዳኝ እንደሆነ በግልጽ ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ለሰማይ ኑሮዋችንም መዘጋጀት አለብን፡፡ ይህ ዓለም ሁሉም ነገር አይደለም፡፡ ይህንን እውነት በማወቅ ሰማይ ለመኖር መዘጋጀት አለብን፡፡ ጠቢብ የሚያደርገው ይህንን ነው፡፡ በየቀኑ በተድላ ትኖራላችሁን? እንደዚያ ከሆነ ሞኞች ናችሁ፡፡ በሌላ በኩል የተሻለውን ወይም ሰማያዊውን አገር የሚሹና ወደዚያ በመግባት ሕልማቸው እውን ይሆን ዘንድ የሚዘጋጁ ሰዎች ቤታቸውን በዓለት ላይ የመሰረቱ ጠቢብ ሰዎች ናቸው፡፡ 
               
 

በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ፡፡ 

 
እግዚአብሄር በራሱ አምሳል ፈጥሮን ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድንኖር ፈልጓል፡፡ ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን የተጠመቀውና ደሙንም ያፈሰሰው ለዚህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚኖሩ ሰዎች ከጌታ ጋር ይኖራሉ፡፡ ጌታም ለዚህ ወሮታውን ይከፍላቸዋል፡፡ ጌታችን ዕንባዎችን ከዓይናችን አብሶ ላለፍንባቸው ችግሮችና ብቸኝነት ሁሉ ወሮታውን ይከፍለናል፡፡ 
 
እግዚአብሄር ሁሉን ያድሳል፡፡ ጡት የሚጠባ ሕጻን እጁን በእፉኝት ጉድጓድ ላይ ጭኖ የማይነደፍበት አዲስ ዓለም እንዲመጣ ፈቅዶዋል፡፡ (ኢሳይያስ 11፡8) ያንን ቀን በትዕግስት ተስፋ እያደረግን የማይታየውን ማመንና በጉጉት መጠባበቅ አለብን፡፡ የሚታየውን እንጠብቃለን የምንል ከሆነ ሞኞች ነን፡፡ በሌላ አነጋገር የማይታየውን ተስፋ ብናደርግና በእግዚአብሄር ቃል ብናምን ያን ጊዜ ጠቢባን ነን፡፡ ከዳንን በኋላ አሁን በዓይናችን ባይታይም መምጣቱ የማይቀረውን ክብር እንጠብቃለን፡፡ 
 
እግዚአብሄር ከእኛ በላይ ይቃትታል፡፡ ነገር ግን አሁንም እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡ እኛ ሥጋችን ወደ መንፈሳዊ ሰውነት እንዲለወጥና ጊዜያችን ሲመጣም እንድንነግስ በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ በውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ምን ይላል? እንድንጠብቅ የሚያደርገን ምንን ነው? የሺህ ዓመቱን መንግሥት እንድንጠብቅ እያደረገን ነው፡፡ ጌታ ሰውነታችንን ለማደስና አብሮን ለመኖር እየጠበቀ ነው፡፡ እኛም ደግሞ ከእግዚአብሄር ጋር ለሺህ ዓመት አብረን ለመኖር እየናፈቅን ነው፡፡ 
 
ሃሌሉያ! ለጌታችን ምስጋና እናቀርባለን፡፡    
 
ክርስቲያኖች ሰማይን ተስፋ በማድረግና በተስፋቸው በመተማመን ይኖራሉ፡፡ ይህ መተማመን በስሜቶቻችን ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን በማይዋሸው የእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡