Search

Preken

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-10] ስሁት አስተምህሮቶች ‹‹ሮሜ 8፡29-30›› 

‹‹ሮሜ 8፡29-30›› 
‹‹ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፡፡ አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡››  
 
 
እነዚህ ምንባቦች እግዚአብሄር ሰዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለማዳን አስቀድሞ እንደወሰነ ይነግሩናል፡፡ ይህንን ለማድረግም እግዚአብሄር በክርስቶስ ጠራቸው፡፡ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፡፡ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሰረታውያን በሙሉ የታቀዱትና የተሰሩት በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ነው፡፡ የሮሜ መጽሐፍ የሚነግረን ይህንን ነው፡፡ ብዙ የሥነ መለኮት ምሁራንና ሐሰተኛ አስተማሪዎች ግን ይህንን ግልጽና ቀላል እውነት የራሳቸውን አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች ወደያዘ ተራ ትምህርት በመለወጥ በቅንነት እያሰራጩት ነው፡፡ አሁን ብዙ ሰዎች ይህንን እውነት በተሳሳተ መንገድ እንዴት እንደተረዱት ለመመርመር ትኩረታችንን ወደዚህ እናደርጋለን፡፡ 
 
አንዳንድ የሥነ መለኮት ምሁራን ከዚህ ምንባብ አምስት ዋና ዋና ትምህርቶችን ፈጥረዋል፡፡ 1) ቅድመ እውቀት 2) ቅድመ መወሰን 3) ውጤታማ ጥሪ 4) ጽድቅና 5) ክብር ናቸው፡፡ እነዚህ አምስት ትምህርቶች ‹‹የደህንነት ወርቃማ ሰንሰለት›› ተብለው በመጠራት እውነት ናቸው ተብለው ለምዕመናንና ለማያምኑ ሰዎች ተሰራጭተዋል፡፡ አባሎቻቸው ግን በእንከኖች የተሞሉ ናቸው፡፡ 
 
አምስቱም ትምህርቶች በሙሉ የሚናገሩት እግዚአብሄር ያደረገውን ብቻ ማለትም ‹‹እግዚአብሄር አንድን ሰው ቀድሞ አውቆታል፤ ቀድሞ መርጦታል፤ ቀድሞ ጠርቶታል፤ አጽድቆታል፤ አክብሮታል›› የሚሉትን ነው፡፡ አስቀድሞ የመወሰን ትምህርት እግዚአብሄር የሚያድናቸውን ሰዎች ከመወለዳቸው በፊት እንኳን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደመረጣቸው የሚናገር ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው አስቀድሞ የመወሰን እውነት ግን እግዚአብሄር ፍቅሩን በእነርሱ ላይ በማፍሰስ ሐጢያተኞችን ልጆቹ እንዳደረጋቸው ያስተምራል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ መንገድ ከመረጣቸው በኋላ ጠራቸው፤ አጸደቃቸው፤ አከበራቸውም፡፡ 
 
 

አስቀድሞ የመወሰንና የምርጫ ሥነ መለኮታዊ ትምህርቶች ስህተት፡፡ 

 
በክርስትና የሥነ መለኮት ትምህርት ውስጥ በጆን ካልቪን የታወጁትን ‹‹አምስቱን ታላላቅ ትምህርቶች›› ማግኘት እንችላለን፡፡ ከእነዚህ መካከል አስቀድሞ የመወሰን ትምህርትና የምርጫ ትምህርት ይገኛሉ፡፡ በቀጣዩ ውይይት ውስጥ የእነዚህን ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስህተቶች በመጠቆም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እመሰክራለሁ፡፡ 
 
የምርጫ ትምህርት ጆን ካልቪን ከተባለው የሥነ መለኮት ምሁር የመነጨ ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስለሆነው ምርጫ የተናገረው ከካልቪን ዘመን በፊት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የእርሱ የምርጫ ትምህርት ብዙዎችን ወደ ግራ መጋባት ነድቶዋቸዋል፡፡ ይህ የሐሰት ትምህርት የእግዚአብሄርን ፍቅር በመገደብ የሚያገልልና ተገቢ ያልሆነ እንደሆነ አድርጎም አብራርቶታል፡፡ በግልጽ አነጋገር የእግዚአብሄር ፍቅር ገደቦችም ሆኑ ወሰኖች የሉትም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ፍቅር ላይ እንደዚህ ያሉ ገደቦችን የሚጭን አስቀድሞ የመወሰን ትምህርት ስህተት እንጂ ሌላ አንዳች ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ እውነታው ግን ዛሬ በኢየሱስ የሚያምኑ ብዙ አማኞች ይህንን ትምህርት ተገቢና ትክክለኛ አድርገው መቀበላቸው ነው፡፡
 
የዚህ አስቀድሞ የመወሰን እሳቤዎች የብዙዎችን አእምሮ ተቆጣጥሮዋል፡፡ ምክንያቱም ትምህርቱ ለሚፈላሰፉ ሰዎች የሚስማማ በመሆኑ አእምሮዋቸውን በመቆጣጠር እንዲያምኑት አድርጓቸዋል፡፡ ትምህርቱ ከፍጥረት በፊትም ቢሆን እግዚአብሄር አንዳንዶችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አስቀድሞ በመወሰን የመረጣቸው ሲሆን ሌሎች ግን ከዚህ ምርጫ እንዲገለሉ አስቀድሞ ተወስኖባቸዋል ይላል፡፡ ይህ ትምህርት እውነት ቢሆን ኖሮ ያልተመረጡት ነፍሳቶች እግዚአብሄርን የሚቃወሙበት መሰረት ስለማይኖራቸው አመጸኛና ወገንተኛ አምላከ ይሆን ነበር፡፡ 
 
የዘመኑ ክርስትና በእነዚህ ትምህርቶች ምክንያት ትልቅ ግራ መጋባት ውስጥ ገብቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙ ክርስቲያኖች ‹‹ተመርጫለሁን?›› በማለት ግራ እየተጋቡ ይጨነቃሉ፡፡ መጨረሻቸውም በእግዚአብሄር ምርጫ ውስጥ ተካተው እንደሆነ ወይም ከዚያ ተገልለው እንደሆነ ለማወቅ መጓጓት ይሆናል፡፡ አስቀድሞ የመወሰን ትምህርት በኢየሱስ በሚያምኑ አማኞች መካከል ብዙ ግራ መጋባትን የፈጠረው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሄር በተሰጠው እውነተኛ የውሃና የመንፈስ ወንጌል ላይ ሳይሆን በምርጫቸው ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉና፡፡
 
ይህ ትምህርት የክርስትናን እውነት ወደ ሌላ የዓለም ሃይማኖት ቀይሮታል፡፡ አሁን ግን እነዚህን የተሳሳቱ ትምህርቶች የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሚመሰክረው ወንጌል ከክርስትናው ዓለም ውስጥ አውጥተን ለመጣል ጊዜው ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ አስቀድሞ የመወሰን ትምህርት ትክክል እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለራሳችሁ አይታችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻችሁ መዳን አለባችሁ፡፡ በእርግጥ በእግዚአብሄር የተመረጡት ሰዎች የእርሱን ጽድቅ የሚያውቁና የሚያምኑ ሰዎች ናቸው፡፡
 
 

እውነት የተናገረው አስቀድሞ መወሰንና ምርጫ፡፡ 

 
ኤፌሶን 1፡3-5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር በፊት ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን፡፡ በበጎ ፈቃዱ እንደወደደ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን፡፡›› በዚህ የኤፌሶን ምንባብ ውስጥ የተነገረው ምርጫ ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊት በክርስቶስ›› (ኤፌሶን 1፡4) ስለተመረጠው ምርጫ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድንም ሰው ከሐጢያት ከመዳን ጸጋ እንዳላገለለም ይነግረናል፡፡ 
 
ከዚህ ምንባብ አስቀድሞ የመወሰን ትምህርት በትክክል ስህተቱ ምን እንደሆነ ማረጋገጥ አለብን፡፡ የዚህ ትምህርት መሰረታዊ ስህተት የእግዚአብሄርን የምርጫ መስፈርት በአድልዎ ላይ መመስረቱ ነው፡፡ ማለትም ማን ይድናል ወይም አይድንም የሚለው መሰረት በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በእርሱ ግብታዊና በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡      
 
እምነታችን እንዲህ ባለ ቅድመ ሁኔታ አስቀደሞ የመወሰንና የምርጫዎች ስነ አመክንዮ ላይ ብንመሰርት በሚያቅበጠብጡን ጥርጣሬዎቻችንና ጭንቀቶቻችን እንዴት በኢየሱስ ልናምን እንችላለን? ካልቪኒዝም ጻድቁን አምላክ አመዛዛኝና ቅን ወዳልሆነ አምላክ የሚለውጥ የሐሰት ትምህርት ነው፡፡ ካልቪን እንዲህ ያለ ስህተት የሰራው ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ›› የሚለውን ሁኔታ ከእግዚአብሄር አስቀድሞ መወሰን ስላወጣው ነው፡፡ ስህተቱም ብዙዎችን ለማደናገርና ለማሳሳት አደገኛ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በግልጽ ‹‹እግዚአብሄር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደመረጠን›› (ኤፌሶን 1፡4) ይነግረናል፡፡ 
 
ካልቪናውያን እንደሚሉት እግዚአብሄር አምላካቸው ይሆን ዘንድ አንዳንዶችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መርጦ ሌሎችን ያለ ምንም ምክንያት ካገለለ ከዚህ የበለጠ ዘበት ምን ሊኖር ይችላል? ካልቪን እግዚአብሄርን በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ዓመጸኛ አምላክ አድርጎ ሳለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በሮሜ 3፡29 ላይ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ወይስ እግዚአብሄር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ ደግሞ አይደለምን? የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው፡፡›› እግዚአብሄር የእያንዳንዱ ሰው አምላክና የሁሉ አዳኝ ነው፡፡ 
 
ኢየሱስ የሁሉ አዳኝ ነው፡፡ እርሱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት በራሱ ላይ በመውሰድና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ ለሰው ሁሉ ቤዛነትን ሰጥቶዋል፡፡ (ማቴዎስ 3፡15) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ በመውሰድና እነዚህን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ተሸክሞ (ዮሐንስ 1፡29) በእኛ ፋንታ ለእነዚህ ሐጢያቶች በመኮነን (ዮሐንስ 19) እያንዳንዱን ሐጢያተኛ እንዳዳነ ይነግረናል፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡›› ኢየሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ሰው ሐጢያቶች በጥምቀቱ ወስዶ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅም ለሰው ዘር ሁሉ ከሙታን ተነሳ፡፡
 
እግዚአብሄር ማንን እንደጠራ ያለን መረዳት በቃሉ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ እንደዚያ ለማድረግ በሮሜ 9፡10-11 ላይ ያለውን ምንባብ እንመልከት፡- ‹‹ይህ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንዱ ከአባታችን ከይስሐቅ በጸነሰች ጊዜ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእዚአብሄር አሳብ ይጸና ዘንድ፡፡›› 
 
እዚህ ላይ ቃሉ ‹‹ከጠሪው›› የሆነ የእግዚአብሄር አሳብ ይጸና ዘንድ ይላል፡፡ ታዲያ እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ የጠራው ማንን ነው? እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን እንደጠራ ግልጽ ነው፡፡ እግዚአብሄር በኤሳውና በያዕቆብ መካከል ማንን ወደደ? ያዕቆብን ወደደ፡፡ እግዚአብሄር በራሱ ጽድቅ እንደተሞላው ኤሳው ያሉ አይነት ሰዎችን አልወደደም፡፡ ነገር ግን እንደ ያዕቆብ ያሉትን ሐጢያተኞች ጠርቶ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ዳግም እንዲወለዱ ፈቀደላቸው፡፡ እንደ ያዕቆብ ያሉትን ሐጢያተኞች በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለመውደድና ለመጥራት የመረጠው የእግዚአብሄር ጽድቅ ዋና ፈቃድ ይህ ነበር፡፡ 
 
አዳም የእያንዳንዱ ሰው አያት በመሆኑ ሁሉም የሐጢያተኛ ልጆች ሆነው ተወለዱ፡፡ በመዝሙረ ዳዊት 51 ላይ ዳዊት በእናቱ ማህጸን ውስጥ በነበረበት ስፍራ በሐጢያት እንደተጸነሰ ይናገራል፡፡ ሰዎች ሐጢተኞች ሆነው ስለተወለዱ ምንም ያህል ቆራጥ ውሳኔ ቢወስኑም ሐጢያቶችን ይሰራሉ፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስም በሕይወታቸው የሐጢያትን ፍሬዎች ማፍራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ማርቆስ 7፡21-23 የአፕል ዛፎች አፕሎችን ብቻ እንደሚያፈሩና የኮክ ፍሬዎችም ኮክን እንደሚያፈሩ ሁሉ ሰዎችም በሐጢያት ስለተወለዱ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሐጢያት ለመኖር እንደታሰሩ ይነግረናል፡፡
 
ያለ ፈቃዳችሁ ሐጢያትን የመስራት ልምምድ አላችሁ፡፡ ይህ የሆነበት ምከንያት እናንተ ከመጀመሪያውም ሐጢያተኞች ስለሆናችሁ ነው፡፡ ሰዎች ምንዝርናን፣ ዝሙትን፣ ስርቆትን፣ መጎምጀትን፣ ክፋትን፣ ተንኮልን፣ መዳራትንና ሌሎች እንዲህ ያሉ ሐጢያቶችን በአእምሮዋቸው ይዘው ተወልደዋል፡፡ ሰው ሁሉ ሕይወቱን በሐጢያት የሚኖረው ለዚህ ነው፡፡ ሐጢያት የተወረሰ ነው፡፡ እኛ ቅድመ አያቶቻችን ወደ እኛ ያስተላለፉዋቸውን ሐጢያቶች ይዘን ስለተወለድን በሐጢያት ለመኖር ተወስነናል፡፡ ኢየሱስን አዳኛችን አድርገን ማመንና በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን የሚያስፈልገን ለዚህ ነው፡፡ 
 
ይህ ማለት የእግዚአብሄር የመጀመሪያ ሥራ የሆነው አዳም ያበቃው በውድቀት ነው ማለት ነው? አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ዘር ልጆቹ ለማድረግ ስለወሰነ የመጀመሪያው ሰው በሐጢያት እንዲወድቅ ፈቀደ፡፡ እግዚአብሄር እኛን ለማዳንና በክርስቶስ ኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ልጆቹ ሊያደርገን በመሰረቱ ሐጢያተኞች እንድንሆን ፈቀደ፡፡ ስለዚህ ያለ ምንም ልዩነት ሐጢያተኞች ሆነን እንደተወለድን ማወቅ አለብን፡፡ 
 
ነገር ግን እግዚአብሄር የሰው ዘር ሐጢያተኞች እንደሚሆኑ በማወቅ ኢየሱስ ክርስቶስን ከፍጥረት በፊት ወደዚህ ምድር ሊልከው ወሰነ፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በእርሱ ላይ በመጫን በመስቀል ላይ እንዲሞት አደረገው፡፡ በሌላ አነጋገር ያመኑ ሁሉ ከሐጢያት የመዳንን በረከት አግኝተው የእግዚአብሄር ልጆች እንዲሆኑ ወሰነ፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ዘር የፈጠረበት እቅድና አሳብ ይህ ነበር፡፡ 
 
አንዳንድ ሰዎች የተሳሳተ መረዳትን ይዘው ‹‹ያዕቆብንና ኤሳውን ተመልከቱ፡፡ እግዚአብሄር አንዱን መርጦ ሌላውን አልተወውምን?›› ብለው ይጠይቁ ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ለመዳን ክርር የሚሉትን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ አልመረጣቸውም፡፡ እርሱ እያንዳንዱን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ልጆቹ ሊያደርግ በግልጽ መርጦዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ላይ ብቻ የምናተኩር ከሆነ እግዚአብሄር አንዱን ወገን ብቻ የመምረጡን አንደምታ ልናገኝ እንችላለን፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ግን እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለማዳን እንደ ያዕቆብ ያሉ ሰዎችን እንደመረጠ ያለ ምንም መሳሳት ማየት እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ማንን እንደጠራ ቃሉን በግልጽ መረዳትና ማመን አለብን፡፡ 
 
እግዚአብሄር ከኤሳውና ከያዕቆብ የጠራውና የወደደው ማንን ነው? እግዚአብሄር በድካሞች፣ በተንኮልና በዓመጻ የተሞላውን ያዕቆብን ሊወድደውና በእግዚአብሄር ጽድቅ ሊያድነው መረጠው፡፡ እናንተም እንደዚሁ እግዚአብሄር አብ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በጽድቅ የጠራችሁ በመሆኑ በዚህ እውነት ማመን አለባችሁ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የእግዚአብሄር ትክክለኛ ጽድቅ የመሆኑንም እውነት ማመን አለባችሁ፡፡
 
ታዲያ እግዚአብሄር እንደ ያዕቆብ ያሉ ሰዎችን ለምን መረጠ? እግዚአብሄር ያዕቆብን የመረጠው የዓመጸኛ ሰዎች ሁሉ ወኪል ስለነበር ነው፡፡ ያዕቆብ በእግዚአብሄር መጠራቱ ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ ጥሪ ነበር፡፡ ይህም ‹‹እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ለመመረጣችን›› ከእግዚአብሄር ቃል ጋር የሚስማማ ጥሪ ነው፡፡ ይህ ጥሪ ‹‹ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሄር አሳብ ይጸና ዘንድ›› ከሚለው የእውነት ቃል ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ 
 
ሐጢያተኞችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የማዳኑ መንገድ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በፍቅሩ መፈጸም ነበረበት፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ለሐጢያተኞች ያስቀመጠው የደህንነት ሕግ ይህ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ጽድቁን ሊያለብሳቸው ፈጽሞ የራስ ጽድቅ ያልነበራቸውንና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለጥሪው ምላሽ የሰጡትን እንደ ያዕቆብ ያሉትን ሰዎች ጠራ፡፡ 
 
እግዚአብሄር ራሳቸውን ያጸደቁትንና ጥሩ የሚመስሉትን ሰዎች ጠርቶዋልን? ወይስ የጠራቸው በድካሞች የተሞሉትንና የራስ ጽድቅ የሌላቸውን ነው? እግዚአብሄር የጠራቸው እንደ ያዕቆብ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ እግዚአብሄር በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ለሲዖል የታጩትን ሐጢያተኞች ጠርቶ አዳናቸው፡፡ እናንተ ከተወለዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሄር ክብር የጎደላችሁና ለሲዖል የታጫችሁ ሐጢያተኛ እንደነበራችሁ ማወቅ ያስፈልጋችኋል፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን በሙሉ ጠርቶ በጽድቁ አድኖዋቸዋል፡፡ 
 
የእግዚአብሄር ሕዝቦች በእርሱ ጽድቅ አምነው የጸደቁ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን በሙሉ ጠርቶ በኢየሱስ ሊያድናቸው አስቀድሞ ወሰነ፡፡ እግዚአብሄር የተናገረለት በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው አስቀድሞ መወሰንና እውነተኛ ምርጫ ይህ ነው፡፡ እውነተኛውን የእግዚአብሄር ምርጫ ለመረዳት በመጀመሪያ በብሉይ ኪዳን እንደተገለጠው ይህንን የምርጫ እውነት ታሪካዊ ዳራ መረዳት አለብን፡፡ 
                    
 
ከብሉይ ኪዳን የእግዚአብሄርን ምርጫ የሚመለከት ታሪካዊ ዳራ 
 
ዘፍጥረት 25፡21-26 ያዕቆብና ኤሳው ገና በእናታቸው በርብቃ ማህጸን ውስጥ ሳሉ ያለውን ታሪክ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ከሁለቱ መካከል ያዕቆብን መረጠ፡፡ ካልቪን የምርጫ ትምህርቱን የመሰረተው በዚህ ምንባብ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን የእርሱ መረዳት ከእግዚአብሄር ፈቃድ ያፈነገጠ እንደነበር በቅርቡ እናያለን፡፡ እግዚአብሄር ከኤሳው ይልቅ ያዕቆብን የወደደበት ምክንያት አለው፡፡ ይህ ምክንያት እንደ ኤሳው ያሉ ሰዎች በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍና ከመታመን ይልቅ በራሳቸው ብርታት በማመን መኖራቸው ሲሆን እንደ ያዕቆብ ያሉ ሰዎች ደግሞ በእግዚአብሄር ጽደቅ ላይ መደገፋቸውና መታመናቸው ነው፡፡ እኛ ‹‹በክርስቶስ የተመረጥነው›› (ኤፌሶን 1፡4) ለዚህ ነው፡፡ 
 
ያለ ኢየሱስና ከእግዚአብሄር ጽድቅ ውጭ የሆነ ‹‹ያለ ቅድመ ሁኔታ ምርጫ›› ሐሰተኛ የክርሰትና ትምህርት ነው፡፡ ይህ እሳቤ የዕድል ፈንታን አምላክ ወደ ክርስትና ውስጥ ከማስገባትና ከማመን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እውነቱ ግን እግዚአብሄር ሐጢያተኞቹን በሙሉ በእግዚአብሄር እንደመረጠ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ›› ሐጢያተኞችን በሙሉ ሊያድን ስለመረጠ ምርጫው እውነተኛው ምርጫ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያዕቆብን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መርጦ ኤሳውን ያለ ምንም ምክንያት አግልሎት ቢሆን ኖር የሚያዳላ አምላክ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ መረጠን፡፡ የጠራቸውን ለማዳንም የእግዚአብሄርን ጽድቅ በፈጸመው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዲወሰድና ክቡር ደሙን በመስቀል ላይ እንዲያፈስስ ኢየሱስን ወደ ምድር ላከው፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመረጠንና የወደደን እንዲህ ነው፡፡
 
የራሳችንን ሰብዓዊ አስተሳሰቦች ጥለን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ማመን አለብን፡፡ በፊደል እምነት ሳይሆን በመንፈሳዊ እምነታችን ማመን አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር አብ ሁላችንንም በኢየሱስ ክርስቶስ መርጦናል፡፡ ነገር ግን ካልቪን የእግዚአብሄርን ምርጫ ያስተናገደው እንዴት ነው? እውነተኛ እምነት የሚገኘው ሰው የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሲያውቅና ሲያምን ነው፡፡ የሰውን አስተሳሰብ እውነት አድርጎ ማመን እግዚአብሄርን ሳይሆን ጣዖትን እንደ ማምለክ ነው፡፡
 
በኢየሱስ አማካይነት በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን በተሳሳተው አስቀድሞ የመወሰን ትምህርት ከማመን በግልጽ የተለየ ነው፡፡ ኢየሱስ በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል መሰረት የማናውቀውና የማናምነው ከሆነ ማሰብ ከማይችሉት ተራ እንስሶች የተለየን አይደለንም፡፡ እኛ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ›› በእግዚአብሄር የጽድቅ ማህተም የእግዚአብሄር ልጆች ሆነን ተመርጠናል፡፡ እምነታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሰረት መመርመር ይገባናል፡፡
 
ከአምስቱ የካልቪናውያን ትምህርቶች አንዱ ‹‹ውሱን ስለሆነ ስርየት›› ይናገራል፡፡ ይህ ትምህርት ከብዙዎቹ የዓለም ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ ከእግዚአብሄር ደህንነት ተገልለዋል ይላል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ጽድቅና ፍቅሩ እንዲህ ቅንነት የጎደለው አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ‹‹ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲመጡ እንደሚፈልግ›› (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡4) ይነግረናል፡፡ የደህንነት በረከት ለአንዳንዶች ተሰጥቶ ለሌሎች ያልተፈቀደ ውሱን በረከት ከሆነ በኢየሱስ ማመናቸውን እርግፍ አድርገው የሚተዉ ብዙ ሰዎች ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል ተመልሰው ከሐጢያቶቻቸው በመዳን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛቸው አድርገው በማወቅና በማመን የዘላለምን ሕይወት መኖር አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ሁሉ በጽድቁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አድኖዋል፡፡
 
እግዚአብሄር በእርግጥ አንዳንዶችን ወዶ ሌሎችን ጠልቶ ከሆነ ሰዎች ጀርባቸውን ለእግዚአብሄር ይሰጣሉ፡፡ እግዚአብሄር አሁኑኑ እዚህ እንደቆመ እንገምት፡፡ እግዚአብሄር በስተ ቀኙ የቆሙትን ለደህንነት ቢመርጥና በስተ ግራው የቆሙትን ደግሞ ያለ ምክንያት ለሲዖል ቢመርጥ ይህ ትክክል ይሆናልን? በስተ ግራው ያሉት በእግዚአብሄር ላይ ከመነሳት በቀር ምርጫ አይኖራቸውም፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ከሆነ በዚህ ዓለም ላይ እርሱን እውነተኛ አምላክ አድርጎ የሚያገለግለውና የሚያመልከው ማነው? ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተጠሉት ሰዎች ያምጹና እነርሱም በበኩላቸው እግዚአብሄርን ይጠሉታል፡፡ የዚህ ዓለም ወንጀለኞች እንኳን የራሳቸው የሆኑ ሥነ ምግባሮችና አመዛዛኝነት አላቸው ይባላል፡፡ ታዲያ ፈጣሪያችን እንዴት እንዲህ ቀናነት ሊጎድለው ይችላል? እንዲህ ባለ ቀናነት በጎደለው አምላክስ ማን ያምናል?
 
አባታችን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ በሚገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ ሐጢያተኞችን ሁሉ ለማዳን ወሰነ፡፡ ውሱን ስርየት የሚለው የካልቪናውያን ትምህርት ከእግዚአብሄር ጽድቅ ጋር ምንም የማይገናኘው ለዚህ ነው፡፡ ከእነዚህ የተሳሳቱ ትምህርቶች የተነሳ ግን ብዙ ሰዎች በራሳቸው የተሳሳቱ መረዳቶች በተሳሳተ መንገድ በእግዚአብሄር በማመናቸው ወይም ከእርሱ በመራቃቸው መሳሳታቸውን እየቀጠሉ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ 
             
 
እውነት አልባ ሙቪ (ተንቀሳቃሽ ሲኒማ)፡፡ 
 
‹‹ዘ ስታንድ›› የሚል ርዕስ ያለው የስቴፈን ኪንግ ልብ ወለድ ከተወሰኑ ዓመታቶች በፊት በአጭር ተከታታይ የቴሌቪዥን ተውኔት ላይ ቀርቦ በመላው ዓለም ታዋቂነትን አትርፎ ነበር፡፡ የልብ ወለዱ መቼት እንዲህ ይገለጣል፡፡ በ1991 ዓ.ም አሜሪካ በመቅሰፍት ትመታና ተላላፊ በሽታውን ‹‹መቋቋም›› ቻሉ፡፡ ጥቂት ሺህ ሰዎች ብቻ በሕይወት ይተርፋሉ፡፡ ከትሩፋኑ ውስጥ እግዚአብሄርን በደመ ነፍስ የሚያገለግሉ ሰዎች በቡልደር ቺካጎ ሲገናኙ ‹‹ጨለማውን ሰው›› የሚያመልኩት ደግሞ ወደ ላስ ቬጋስ ኔቫዳ ነጎዱ፡፡ ሁለቱ ቡድኖችም በተናጥል አንዱ ሌላውን እስኪያጠፋ ድረስ ማህበረሰቦችን እንደገና ገነቡ፡፡
 
ከትሩፋኑ መካከል ስቱዋርት የሚባል ወጣት የዓለም መጨረሻ እንደደረሰ በተደጋጋሚ ሕልም ያልማል፡፡ አቢጋይል የምትባል አሮጊት ሴትም በሕልሞቹ እግዚአብሄር አስቀድሞ እንደመረጠው በማስታወስ ወደሆነ ቦታ እንዲሄድ ትነግረዋለች፡፡ በዚህ ፊልም ውስጥ እግዚአብሄር ይህንን ወጣት አዳነው፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሄር ወይም በኢየሱስ ሳያምን እንኳን ከፍጥረት በፊት እግዚአብሄር አስቀድሞ ወስኖታልና፡፡
 
ታዲያ እግዚአብሄር በኢየሱስ የማያምኑትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ያድናቸዋልን? አያድናቸውም፡፡ እግዚአብሄር በእርሱ ጽድቅ የሚያምኑትን ከሐጢያቶቻው ለማዳን ሰዎችን ሁሉ አስቀድሞ ወስኖዋቸዋል፡፡
 
የዚህ ፊልም ታሪክ በካልቪን አስቀድሞ የመወሰንና የምርጫ ትምህርቶች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህ ፊልም የአንድን የስነ መለኮት ምሁር ትምህርት አንድ ክፍል የሚናገር ተራ ታሪክ ነው፡፡ እግዚአብሄር አንዳንድ ሰዎችን ወደ ሲዖል ለመወርወርና ሌሎችን ለደህንነት ለመምረጥ እንዴት በግብታዊነት ሊወስን ይችላል? እግዚአብሄር ጻድቅ ስለሆነ እያንዳንዱን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አስቀድሞ በመወሰን መርጦዋል፡፡ ከእርሱ የጽድቅ ደህንነት የተገለለ ማንም የለም፡፡ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር አስቀድሞ ውሳኔና ምርጫ ትርጉም የለሽና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭም ነው፡፡ በጣም ብዙ የሥነ መለኮት ምሁራን እግዚአብሄር አንዳንዶችን ሲመርጥ ሌሎችን ትቶዋቸዋል በማለት መቀጠላቸው አሳዛኝ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር አጽናፈ ዓለማትን ከመፍጠሩ በፊትም ቢሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያተኞችን ሁሉ ለማዳንና በጽድቁም ልጆቹ ለማድረግ አቅዶ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ሐጢያተኞችን በሙሉ በኢየሱስ ወንጌል አማካይነት መርቶዋል፡፡ ታዲያ እንዴት ታምናላችሁን?     
 
ጥልቅ በሆኑ ተራራዎች ውስጥ ተቀምጠው የሚያሰላስሉ የቡዲስት መነኮሳት ከእግዚአብሄር ምርጫ እንደተገለሉ ታምናላችሁን? የእግዚአብሄር አስቀድሞ ውሳኔና ምርጫ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወሰን የሌለው ከሆነ የእርሱን ቃል መስበክም ሆነ በቃሉ ማመን አያስፈልገንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ያለ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመዳን አስቀድመው ከተወሰኑና ሌሎችም ከተገለሉ ሐጢያተኞች ፈጽሞ በኢየሱስ ማመን አያስፈልጋቸውም፡፡ በመጨረሻም ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ እኛን ከሐጢያቶቻችን ማዳኑም እንዲህ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ በሚገኘው የአምላክ ጽድቅ ንስሐ ቢገቡና አእምሮዋቸውን ወደ እግዚአብሄር ቢመልሱ በኢየሱስ ለማያምኑት ለእነዚህ የቡዲስት መነኮሳትም እንኳን ደህንነትን ፈቅዶላቸዋል?
 
በዚህ ዓለም ላይ በኢየሱስ እያመኑ ሕይወታቸውን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በሁለት ቡድኖች ብንከፍላቸው አንዱ ቡድን እንደ ኤሳው ያሉ ሲሆኑ ሌላው ቡድን ደግሞ እንደ ያዕቆብ ያሉ ናቸው፡፡ እንደ ያዕቆብ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን ለሲዖል እንደታጩ ሐጢያተኞች አድርገው ስለሚቆጥሩ በኢየሱስ በተሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ድነዋል፡፡ ሌላው ቡድን በኢየሱስ ላይ ባላቸው እምነት የራሳቸውን ጥረቶች በማከል በሰማይ በሮች አልፈው ለመግባት የሚሞክሩ እንደ ኤሳው ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡
 
እናንተ ማንን ትመስላላችሁ? ያዕቆብን ወይስ ኤሳውን? በእግዚአብሄር ጽድቅ ታምናላችሁን? ወይስ በተሳሳተው የአስቀድሞ መወሰን ትምህርት ታምናላችሁ? በእነዚህ ሁለት እምነቶች መካከል ያላችሁ ምርጫ መጨረሻችሁ የት እንደሚሆን -- ሰማይ ወይም ሲዖል -- ይወስናል፡፡ እነዚህን የተሳሳቱ ትምህርቶች ጥላችሁ በእግዚአብሄር ጽድቅ በተነገረው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን ከእርሱ ጋር ሰላም ለመፍጠር የእግዚአብሄርን ጽድቅ መቀበል አለባችሁ፡፡ ከሐጢያቶቻችን ፈጽሞ የሚያድነንና የዘላለምን ሕይወት የሚሰጠን ይህ እምነት ብቻ ነው፡፡