Search

คำสอน

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-11] ሕይወታችሁን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ አድርጎ ለመጠበቅ ‹‹ ኤፌሶን 5፡6-18 ››

ሕይወታችሁን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ አድርጎ ለመጠበቅ
‹‹ ኤፌሶን 5፡6-18 ››
‹‹ከዚህ የተነሳ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሄር ቁጣ ይመጣልና፡፡ ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ፡፡ እንግዲህ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች አትሁኑ፡፡ ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፡፡ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፡፡ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁን ግለጡት እንጂ፡፡ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፡፡ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና፡፡ ስለዚህ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል፡፡ እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፡፡ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ፡፡ መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ማባከን ነውና፡፡››
 
 
ሕይወታችንን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ አድርገን ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለብን?
ራሳችንን መተው፣ መስቀሉን መሸከምና ክፉ መሻቶቻችንን ማሸነፍ ወንጌሉን ለመስበክ ራሳችንን መስጠት አለብን፡፡
 
‹‹በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት››  ወንጌልን ለመስበክ ራሳችንን አሳልፈን መስጠት አለብን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንዲኖር የሚያደርገውን በረከት አስቀድመን መቀበል ይኖርብናል፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል የዚህ አይነት እምነት ሊኖረን ማለትም እግዚአብሄር በሰጠን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ ይህ እምነት ሲኖረን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንዲኖር የሚያደርገውን በረከት እንቀበላለን፡፡
ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ይሻሉን? በእርግጥም ይሻሉ፡፡ ታዲያ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ይህንን ሕይወት መኖር የማይችሉት ለምንድነው? የገዛ ራሳቸው ችግሮች ከእግዚአብሄር ሥራዎች ስለሚበልጡባቸው ማለትም ከእርሱ ጋር መጓዝ ስለማይችሉ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን ሕይወት ጠብቆ ለማቆየት የእግዚአብሄርን ቃሎች መማርና ማመን ይገባናል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ምን አይነት ሕይወትና እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ለማወቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡፡  
 
 

አንዳንድ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የማይችሉበት ምክንያት ምንድነው?

 
በመጀመሪያ ራሳቸውን መተው ስለማይችሉ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከጌታ ጋር መጓዝ የሚችሉት ራሳቸውን የተዉ ብቻ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን ሕይወት መኖር በራስ ሐይል ስለማይቻል እያንዳንዱ ሰው ራሱን ለመተው የዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እምነት መያዝ አለበት፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸውም ቢሆኑ ለእግዚአብሄር መንግሥት የማያስቡ ከሆኑ ራሳቸውን መተው አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማገልገል አለብን፡፡ አንድ ሰው ራሱን መተውና የጽድቅ አገልጋይ ሆኖ መኖር የሚችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ማቴዎስ 16፡24-26 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፡- እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡ ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፡፡ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?››
ዳግም የተወለዱ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የማይችሉት የሥጋቸውን ፍትወቶች መካድ ስለተሳናቸው ነው፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸውም ቢሆኑ መንፈስ ቅዱስን መከተል የሚችሉት የሥጋቸውን ፍትወቶች ሲክዱ ብቻ ነው፡፡ ጌታ እንዲህ አለ፡- ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡››
ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው፤ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው፡፡ በመንፈስ መመላለስ የሚፈልጉ ሰዎች የሥጋ ሕይወታቸውን መተው አለባቸው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወት ጠብቀው ማቆየት የሚችሉት ይህንን መሥዋዕትነት ለመክፈል የሚደፍሩ ብቻ ናቸው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት እውነት ይህ ነው፡፡  
መከተል የምትፈለጉት ማንን ነው ጌታን ወይስ ዓለምን? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ወይም የፍትወት ሕይወት የእናንተ የሚሆነው በምርጫችሁ ነው፡፡ በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የምትፈልጉ ከሆነ ምርጫው የእናንተ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነንና ዘለቄታዊውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሰጠን፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን የመኖሩ ውሳኔ የእናንተ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት በእግዚአብሄር አስቀድሞ የተወሰነ ወይም በዕጣ ፈንታ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምኑ ሰዎች ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡  
 
 

በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ለመኖር ፈቃድ ሊኖራችሁ ይገባል

 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር ውዴታው ካላችሁ እግዚአብሄር ይፈቀድላችኋል፤ ያግዛችኋል፤ ይባርካችሁማል፡፡ ነገር ግን ያንን የምትፈልጉ ከሆነ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን የመኖር ፍላጎታችሁን እርግፍ አድርጋችሁ መተው አለባችሁ፡፡ 
ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል የምትችሉት በገዛ ፈቃዳችሁ ሳይሆን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖርና እርሱንም ጠብቆ ለማቆየት የሚቻለው ሙሉ በሙሉ በእናንተ ውዴታ ብቻ ነው፡፡ 
ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን ሕይወት መኖር የምትፈልጉ ከሆነ የገዛ ፈቃዳችሁን መመርመርና የእግዚአብሄርን እርዳታ መለመን ያስፈልጋችኋል፡፡ በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር የምንፈልግ ከሆነ እግዚአብሄር ይባርከናል፡፡ መሻታችንንም ይፈጽምልናል፡፡ ነገር ግን ግባችን ላይ ለመድረስ የሥጋን ፍትወቶች መካድ አለብን፡፡  
ሁለተኛ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን ሕይወት ለመኖር የራሳችንን መስቀሎች መሸከም አለብን፡፡ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎችም ውስጥ ቢሆን በእግዚአብሄር ፈቃድ መኖርና መመላለስ አለብን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ የጽድቅ ሕይወት መኖር ማለት ይህ ነው፡፡ 
ሦስተኛ ጌታ እንዲህ አለ፡- ‹‹ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፡፡ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?›› ይህ ማለት ጌታን መከተል ለሕይወታችን አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ በእርግጥም እርሱን የምንከተል ከሆነ መንፈሳችንና ሥጋችን ጤናማ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን እርሱን የማንከተለውና የገዛ ራሳችን ሕይወት የምንኖር ከሆነ መንፈሳችንና ሥጋችን ይሞታሉ፡፡ 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር የማንችለው ለምንድነው? የሥጋ ፍትወት የሆኑትን አስተሳሰቦቻችንን ስለማንክድ ነው፡፡ ኢየሱስን ስንከተል መንፈስ ውስጣዊ ማንነታችንን ስለሚያበረታው በትልቅ ጉልበት ሊመራን ይችላል፡፡
በኤፌሶን 5፡11-13 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁን ግለጡት እንጂ፡፡ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፡፡ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና፡፡›› ክርስቲያኖች ፍሬያማ ካልሆኑ የጨለማ ሥራዎች ጋር መተባበር የለባቸውም፡፡ ነገር ግን ራሳችንን ፍሬ አልባ ከሆኑ የጨለማ ሥራዎች ጋር ስናስማማ እግዚአብሄር እነዚያን ሥራዎች እንድናጋልጥ ይነግረናል፡፡ በጨለማ ሥራዎቻችን ልንነቀፍ ይገባናል፤ ምክንያቱም በሥውር ስለተሰሩት የጨለማ ሥራዎች መናገር እንኳን አሳፋሪ ነው፡፡ የተገለጡት ነገሮች ሁሉ ግን በብርሃን ይገለጣሉ፡፡  
ስለ እነዚህ አሳፋሪ ነገሮች መናገርና እነርሱን ማጋለጥ የሚችለው ማነው? ሌሎች ወንድሞቻችሁ ወይም እህቶቻችሁና የእግዚአብሄር ባሮች ማያጋልጡዋቸው ከሆነ እናንተው ራሳችሁ ልታጋልጡዋቸው ይገባል፡፡ የተገለጠው ሁሉ ወደ ብርሃን ይወጣልና ተብሎ ተነግሮዋል፡፡ ስለዚህ ክፉ ሥራዎቻችን ትክክል እንዳልሆኑ ማመንና በመሪያችን አማካይነት ራሳችን ፍሬያማ ያልሆኑትን የጨለማ ሥራዎች ለማጋለጥ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ይኖርብናል፡፡  
በዚህ ዓለም ላይ የተገለጡ ነገሮች ሁሉ እንደተነቀፉት ያበቃሉ፡፡ በእግዚአብሄር ዓለም ውስጥ ግን የተገለጡ ነገሮች ሁሉ ወደ ብርሃን ይወጣሉ፡፡ ምክንያቱም ሁሉን ይፋ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፡፡ እኛ ፍጹማን ስላልሆን በዚህ ዓለም ላይ በዕውር ድንበር ብዙ ሐጢያቶችን እንፈጽማለን፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ቃሎች ብርሃን በላያችን ላይ ስናበራ የተወሰኑ ሐጢያቶችን ወደ ማወቁ እንመጣና ሐጢያት መሆናቸውን እንቀበላለን፡፡ ለእግዚአብሄር ማለቂያ የሌለው ምስጋና የምንሰጠው ለዚህ ነው፡፡
ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንንና በደሎቻችንን ሁሉ ስላስወገደ፣ ኢየሱስ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜም ጽድቅ ሁሉ ስለተፈጸመ በእግዚአብሄር ጽድቅ በኩል በብርሃን መገለጥ እንችላለን፡፡ የሰው ዘር የፈጸማቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሐጢያቶች ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ ወደ ኢየሱስ ተሻግረዋል፡፡ እርሱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶ ለእነዚያ ሐጢያቶች ለመኮነን በመስቀል ላይ የሞተና የተነሳ የእግዚአብሄር በግ ነው፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ይቅር አለ፡፡ ‹‹ተፈጸመ›› (ዮሐንስ 19፡30) ባለ ጊዜ የሰው ዘር ሁሉ ዳነ፡፡ እኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው ነገር በእምነት ተቀድሰናል፡፡ ሐጢያቶቻችን ይቅር ስለተባሉ እንደገና ወደ ብርሃኑ ወጥተን እግዚአብሄርን በጽድቅ መከተል እንችላለን፡፡  
 
 
እግዚአብሄር ዘመኑን እንድንዋጅ ነገረን 
 
ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር ከፈለግን ዘመኑን መዋጀት እንዳለብን ተናገረ፡፡ ኤፌሶን 5፡16-17 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ፡፡›› በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ከፈለግን ዘመኑን መዋጀትና ሞኞች አለመሆን ይኖርብናል፡፡ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አውቀን ልናደርገው ይገባናል፡፡ ይበልጥ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ --ለሥጋችን ታማኝ የሆነ ሕይወት ወይስ ለእግዚአብሄር የተሰጠ ሕይወት --መወሰን አለብን፡፡    
ዳግም ከተወለድን በኋላ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይኖራል፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን ማለት አለቃችን እግዚአብሄር ነው፤ ንጉሣችንም እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ መድህናችን እርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ሙሉ በሙሉ አምላካችን መሆኑን አምነን መቀበል አለብን፡፡ እርሱ ብቸኛው አለቃችን ነው፡፡ እርሱ የፈጠረኝ፣ ሐጢያቶቼን ሁሉ ይቅር ያለኝና የባረከኝ ጌታዬ ነው፡፡ በሕይወቴና በሞቴ፣ በበረከቶቼ ወይም በዕርግማኖቼ ላይ ሥልጣን ያለው ንጉሤ እርሱ ነው፡፡ በዘመናችን ሁሉ እንታዘዘው ዘንድ ጌታ ራሱ አለቃና አምላክ መሆኑን ማመን አለብን፡፡   
ፊልጵስዩስ 2፡5-11 ምን እንደሚል እንመልከት፡- ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡ እርሱ በእግዚአብሄር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሄር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር ነገር አልቆጠረውም፡፡ ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፤ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳን የታዘዘ ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሄር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፡፡ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፡፡ ይህም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሄር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፡፡››   
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡›› እርሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ይህ እንደነበር ተናገረ፡፡ ጳውሎስ  የኢየሱስ የሆነው ‹‹ይህ አሳብ›› ፈጣሪ አምላክና በእግዚአብሄር ፈቃድ መሰረት ሕዝቡን ከሐጢያቶች ለማዳን ወደዚህ ዓለም የመጣው የኢየሱስ አሳብ እንደነበር መናገሩ ነበር፡፡ ጌታ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በዮሐንስ በኩል በሆነው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስወገደ፡፡ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜም የዓለም ሐጢያቶች ከእርሱ ጋር ተወገዱ፡፡ ከዚያም በሦስተኛው ቀን ተነሳና መድህናችን ሆነ፡፡ 
ፈጣሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው እኛን ለማዳን ነበር፡፡ እርሱ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳየ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በፊቱ ተንበርክኮ ፈጣሪ ሆኖ ሳለ ራሱን እንደ ተፈጣሪ ዝቅ በማድረግ የሐጢያት ይቅርታን የሰጠንን ፍቅሩን ማመስገን ይኖርበታል፡፡ ፍጥረታት ሁሉ እርሱ እውነተኛ አዳኛቸው መሆኑን መመስከር ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ የፍጥረት ጌታ ብቻ ሳይሆን ለእኛ የተሰጠው ልክ ለሽ ጽድቅ ጌታም ጭምር እንደሆነ እንድንመሰክር አደረገን፡፡ 
እኛ በእግዚአብሄር የምናምንና ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያለን ሰዎች ‹እግዚአብሄር እውነተኛ አለቃዬ ነው› ብለን ማመንና የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በልባችን ውስጥ መያዝ አለብን፡፡ አለቃችን ራሳችን ሳንሆን የፈጠረንና ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ማመን አለብን፡፡ እርሱ አዲስ የተባረከ ሕይወት እንድንኖር የሚያደርገንና ሁሉን ለእኛ በማዘጋጀትም ለእኛ የሚሰራልን አለቃችን እንደሆነም ደግሞ ማመን አለብን፡፡
ዳግም ከተወለዱ በኋላ ጌቶቻቸውን መቀየር የማይፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ነገር ግን የራሳቸው ጌታ ራሳቸው መሆናቸውን የሚያምኑ ብዙዎች አሉ፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው ነገር ግን የራሳቸው ጌቶች እንደሆኑ ድርቅ የሚሉ ብዙዎች አሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት እግዚአብሄርን የመከተል ሕይወት ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ሕይወት በአንድ ቀን የሚገኝ ሳይሆን ኢየሱስ የሕይወታችን ጌታና እኛንና በአጽናፈ ዓለማት ውስጥ ያሉትን ሌሎች ፍጥረቶች ሁሉ የፈጠረ ጌታ መሆኑን በማመን ብቻ የሚመጣ ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ያዳነንንና በመንግስተ ሰማይ ውስጥ የዘላለም ሕይወት የሰጠንንና ጌታችን፣ አለቃችንና አምላካችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል እምነት ያስፈልገናል፡፡
እውነቱን በአእምሮዋችን መያዝ ያስፈልገናል፡፡ ብዙ ሰዎች የራሳቸው ጌቶች ሆነው ሕይወታቸውን ይኖራሉ፡፡ በራሳቸው ሕይወት ላይ ይሰለጥናሉ፡፡ አሁን ግን ጊዜው ጌቶችን የመቀየር ነው፡፡ እኛ አሁን እግዚአብሄርን አውቀናል፡፡ ስለዚህ ዋናው አለቃችን ጌታ ነው፡፡
ሁላችንም በልቦቻችን ውስጥ ሐጢያት ስላለብን ለስህተታችን በሲዖል ልንኮነን ይገባናል፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመናችን እግዚአብሄርን አገኘነው፡፡ እግዚአብሄር አብዝቶ ስለወደደን ወደዚህ ዓለም መጣ፤ ሐጢያቶቻችንን እውነተኛ መድህናችን ይሆን ዘንድ በዮሐንስ በመጠመቅና  በመስቀል ላይ በመሞት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስወገደ፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ባለን እምነት የተነሳም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጻ ወጣን፡፡ በሌላ አነጋገር ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ተቀበልን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም፡፡›› (ሮሜ 8፡9) የእርሱን ቤዛነት ማለትም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ በተቀበልን ጊዜ የእግዚአብሄር ልጆች ሆንን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ አምላክ ነው፡፡ እኛም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መሰረት በእግዚአብሄር ጽድቅ መመላለስ አለብን፡፡ እንደዚህ ለመኖር የራሳችን ጌታ መሆናችንን ማቆም አለብን፡፡ ኢየሱስን አግኝተን በእርሱ ከዳንን በኋላ አንዱና ብቸኛው ጌታችን ልናደርገው ይገባናል፡፡  
 
 
በልባችን ውስጥ ያሉትን ዙፋኖች ለኢየሱስ ማስረከብ አለብን 
 
እኛ ራሳችንን የሕይወታችን ጌቶች አድርገን የምንመለከት ከሆንን ጌታን መከተል አንችልም፡፡ እግዚአብሄር እንድናገለግለው ሲያዘን የራሳችን ጌቶች ካልሆንን ያለ ምንም መዘግየት ‹‹እሺ›› እንላለን፡፡ አለበለዚያ ግን ‹‹ለምን አደርግልሃለሁ?›› ልንል እንችላለን፡፡ የራሱ ጌታ የሆነ ሰው ‹‹እርሱ የሚፈልገውን እንዳደርግለት እንደ ውለታ አድርጎ ሊጠይቀኝ ይገባል›› ብሎ ስለሚያስብ እግዚአብሄር እንዲያደርግ የሚፈልገውን ለማድረግ እምቢተኛ ነው፡፡ እንደዚህ ላለ ሰው የእግዚአብሄር መመሪያዎች ከንቱና አሰልቺ ቃሎች ናቸው፡፡    
ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የእርሱን ትዕዛዝ መታዘዝ አለብን፡፡ እኛ ወደ ዕርድ ስፍራ እንደሚጎተቱ እንስሶች አይደለንም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን በፈቃዳችን መከተል ይገባናል፡፡ በጽድቅ መንገድ የሚመራንን አዳኛችን የሆነውን አምላክ መከተል ይገባናል፡፡ እግዚአብሄር በደህንነት የባረከን ጌታ ነው፡፡ ጌታችን አድርገን የምናገለግለውና ሕጎቹን የምንጠብቅ ከሆንን በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ እንችላለን፡፡ እናንተና የቤተሰባችሁ አባሎች ንግሥናውን ለኢየሱስ ካስረከባችሁና እርሱን ከሁሉ በላይ አድርጋችሁ ካስቀመጣችሁት በሕይወታችሁ ውስጥ ጸጋና በረከት ይመጣል፡፡  
አንድ ሰው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ማዕበል ውስጥ እየቀዘፈ ሳለ ኢየሱስ ከበስተኋላው ቆሞ የሚያሳዩትን ሥዕሎች አይታችሁ ይሆናል፡፡ በሕይወታችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች እየተቆጣጠርናቸው እንደሆነና የጌታን ሥራ እየሰራን ሲመስለን እየመራን ያለውና እጆቻችንን የያዘን ግን በእርግጥም ኢየሱስ ነው፡፡ ሕይወታችንን የሚቆጣጠረው ሁሉን ቻዩ አምላክ ነው፡፡ እርሱ አዳነን፡፡ እርሱ ከሰይጣን ይጠብቀናል፤ ይመራናል፤ በእኛም ላይ ይሰለጥናል፡፡
እርሱ ጌታችን ስለሆነ ሊቆጣጠረንና ሊባርከን ይችላል፡፡ ነገር ግን እርሱን እንደ ጌታችን አድርገን ካልተቀበልነው የጌትነቱን ሚና አይጫወትም፡፡ እርሱ የስብዕና አምላክ ስለሆነ የእርሱን ፈቃድ እንድንታዘዝ አያስገድደንም፡፡ እርሱ ሁሉን የሚችል አምላክ ቢሆንም እኛ እርሱን ጌታችን አድርገን ለማገልገልና እርዳታን ለመጠየቅ ፈቃደኞች እስካልሆንን ድረስ አንዳች ነገር አያደርግልንም፡፡
 

ነገሮችን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ 
 
እርሱ በእኛ ላይ ይሰለጥን ዘንድ ሁሉንም ነገሮች በእርሱ ላይ ጣሉ፡፡ አገልግሉት፡፡ እርሱ አለቃችን መሆኑንም እመኑ፡፡ እኛ ከፍጽምና የራቅን ስለሆንን ሁሉንም ነገሮች በእርሱ ላይ መጣልና ሐላፊነቱን ሁሉ ወደ እርሱ ማሻገር አለብን፡፡ ቤተሰባችንን፣ የቀን ተቀን ሕይወታችንንና ሌላውን ነገር ሁሉ አንድ ጊዜ በእርሱ ላይ ከጣልን ከእግዚአብሄር ጥበብን እንቀበልና እግዚአብሄር በሰጠን እምነትና ሐይል ችግሮችን ሁሉ በመቋቋም እርሱ እንደሚፈልገው መኖር እንችላለን፡፡   
ያን ጊዜ ችግሮቻችን የጌታችን ይሆናሉ፡፡ ይህ ማለት ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነውን ኢየሱስን ብንከተል ሐላፊነቱን ስለ እኛ ይወስዳል ማለት ነው፡፡ እኛም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን በመኖር በእርሱ ውስጥ ባለው ሰላም እንደሰታለን፡፡ ታማኝ ክርስቲያኖች በመሆንም በእግዚአብሄር ፊት ተንበርክከን ጌታችንን ማገልገል ይገባናል፡፡   
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ለመኖር ምን አይነት እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ፊልጵስዩስ 3፡3 የሚናገረውን እንመልከት፡- ‹‹እኛ በመንፈስ እግዚአብሄርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹ግርዘት›› ማለት እግዚአብሄርን በመንፈስ ማምለክ በክርስቶስ ኢየሱስ መደሰትና በሥጋ አለመታመን ማለት ነው፡፡  
በግርዘት መኖር ማለት በልባችን ውስጥ ያለውን ሐጢያት በሙሉ ቆርጠን በዮሐንስ ወደተጠመቀው ኢየሱስ ማሻገር ማለት ነው፡፡ በመንፈስ የሚመሩ ሕይወታቸውን ለመንፈስ ይሰጣሉ፡፡ እግዚአብሄርን ያገለግላሉ፡፡ ‹‹ኢየሱስ ይህንን ክቡር ሕይወት እንድኖር መራኝ፡፡ ጻድቅ አደረገኝ፤ ባረከኝም፡፡ እርሱን ለማገልገል የሚያስፈልገኝን ጸጋ ሰጠኝ›› በማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ይደሰታሉ፡፡ እንደዚህ ሆነን መኖር ያስፈልገናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ይህ ነው፡፡ ‹‹እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሄር ክብር አድርጉት፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 10፡31)      
ፊልጵስዩስ 3፡13-14 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፡፡ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሄርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ፡፡›› እግዚአብሄር ከኋላችን ያሉትን ነገሮች እንዳለፉ ቆጥረን ከፊት ለፊታችን ወዳሉት ነገሮች እንድንዘረጋና ወደ ግባችን መፍጠን እንዳለብን ነገረን፡፡ የጽድቅ ምግባሮቻችን ወይም የተሳሳቱ ድርጊቶቻችን ምንም ይሁኑ ከኋላችን ያሉትን እነዚያን ነገሮች መርሳትና ከፊት ለፊታችን ወዳሉት ለመዘርጋት መሞከርና ወደ ግባችን መፍጠን አለብን፡፡ ይህ ግብ በእርሱ አምነን ኢየሱስ ክርስቶስን አጥብቀን በመያዝ ፈቃዱን ማገልገል ነው፡፡
እኛ ከፍጽምና የራቅን ስለሆንን በሥጋ ስንታለል ለመውደቅ እናዘነብላለን፡፡ ሆኖም ወደ እግዚአብሄር በመመልከትና በእምነት ከድካሞቻችንና ከበደሎቻችን ሁሉ መላቀቅ እንችላለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ሐጢያቶቻችን ሁሉ ወደ እርሱ ተሻገሩ፡፡ እርሱ በትንሳኤ አማካይነት መድህናችን በሆነ ጊዜ በእርሱ ማመናችን ምስጋና ይግባውና አዲስ ሕይወት ተሰጠን፡፡ ስለዚህ ከኋላችን ያሉትን እነዚያን ነገሮች በሙሉ ረስተን ወደፊት ወዳሉት ነገሮች በመዘርጋት ወደ ግባችን መፍጠን አለብን፡፡  

 
 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት
 

ከፊት ለፊት ወዳሉት ነገሮች መዘርጋትና ከፍ ወዳለው ግብ መፍጠን አለብን፡፡ ሸክም ሆነውባችሁ ከሆነ ያለፉትን ነገሮች ሁሉ በተቻለ ፍጥነት መርሳት እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከድካሞቻችን የተነሳ ሊከወኑ የማይችሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ብዙም የሚያሳስቡ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አስፈላጊው ነገር ወደፊት ያለው ነውና፡፡ ወደፊት ያለው ነገር በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ንጉሥነታችንን በእምነት አማካይነት ለኢየሱስ ክርስቶስ መስጠትና በእርሱ መመራት ይገባናል፡፡ ወደፊት እንዴት እንደምንኖርና እርሱን የሚያስደስተውን ለማድረግ እንዲወስንልን መፍቀድ አለብን፡፡
 
 
ደቀመዛሙርት እንደኖሩት መኖር አለብን 
 
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር የምንችለው በሐጢያት ስርየት ላይ ጠንካራ እምነት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-10ን እንመልከት፡- ‹‹እንግዲህ ልጄ ሆይ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ፡፡ ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ለሌሎችም ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ፡፡ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ አብረኸኝ መከራ ተቀበል፡፡ የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም፡፡ ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል የድሉን አክሊል አያገኝም፡፡ የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል፡፡ የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ፡፡ በወንጌል እንደምሰብከው ከሙታን የተነሳውን ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፡፡ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራን እቀበላለሁ፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ግን አይታሰርም፡፡ ስለዚህ እነርሱም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ፡፡›› 
ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንደነገረው መንፈስ ቅዱስም ለእኛ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ፡፡ ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ለሌሎችም ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ፡፡››
‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ፡፡›› እዚህ ላይ በጸጋ መበርታት ማለት በእርሱ በማመንና እርሱን አጥብቀን በመያዝ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለንን እምነት ማጠንከር ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ሊወሰድ ወደዚህ ዓለም መጣ፤ በመስቀል ላይም ሞተ፤ ከሙታንም ተነስቶ መድህናችን ሆነ፡፡ ይህ ማለት እኛ በጸጋው መበርታትና እርሱን ማመስገን አለብን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር አዳነን፡፡ ስለዚህ ደህንነትን የእግዚአብሄር ስጦታ አድርገን በእምነት አማካይነት መቀበል ይኖርብናል፡፡ ይህ በሐጢያቶች ስርየት የሚገኘው ደህንነት ነው፡፡ በየቀኑ የማለዳ ጸሎቶችን ከማድረግ ወይም ለቤተክርስቲያን ግንባታ ገንዘብን ከመለገስ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ደህንነትን በመቀበል ረገድ ከሚያመጡት ጥቅም ይልቅ የሚያደርሱት ጉዳት ይበልጣል፡፡    
በሐጢያት ይቅርታ በኩል ደህንነታችንን አገኘን ማለት ምግባሮቻችን ምንም ይሁኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለመሸከም ተጠመቀና ከዚያም መተላለፎቻችንን በሙሉ ለመደምሰስ በመስቀል ላይ ሞተ ማለት ነው፡፡ እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳንም ተነሳ፡፡ መጋቢዎችም ልክ እንደ ምዕመናን ይህንን የወንጌል እውነት በማመን ሐጢያቶቻቸው ይቅር ተብለዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከሙሉ ልቡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ማንኛውም ሰው የሐጢያትን ይቅርታ ይቀበላል፡፡ ስለዚህ በደህንነት ጸጋ መተማመን ሊኖረንና እምነታችንን ልናበረታ እንችላለን፡፡  
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት የምንፈልግ ከሆነ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለን እምነት መበርታት አለብን፡፡ በሕይወታችን ውስጥ መስፈርቱን ከማሟላት የምንጎድልባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ድካሞችም አሉብን፡፡ በደህንነት ጸጋ መበርታት ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ስንኩልነታችን በሚገለጥበት ጊዜ ሁሉ ለራሳችን ‹‹እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አዳነኝ፡፡ ኢየሱስ በውሃና በመንፈስ አማካይነት ሐጢያቶቼን በሙሉ ይቅር አለ›› በማለት እምነታችንን ማሰላሰል ይኖርብናል፡፡ በዚህ ወንጌል በማመን ጻድቅ እንሆናለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታም ራሳችንን እናበረታለን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነን ብርቱ ሆንን፡፡ በእምነታችንም የተባረክን ሰዎች ሆንን፡፡
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሄር ክብር አድርጉት፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 10፡31) ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ማለት ሕይወታችንን ለእግዚአብሄር ቀድሰን መስጠት አለብን ማለት ነው፡፡ ‹‹የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ›› የእርሱን ሥራ ለመስራት መብላት መጠጣትና በእግዚአብሄር ብርቱ መሆን አለብን፡፡ ወንጌልን ለመስበክ ለጤናችን ጥሩ ነገሮችን መብላት አለብን፡፡  
‹‹የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም፡፡›› (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡4) ወንጌልን ለመስበክ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መምራት አለባችሁ፡፡ ወንጌልን የሚሰብክ ሕይወት ስንመራ የታመነ ሕይወትን እንኖራለን፡፡ ልክ እንደዚህ በእምነት መኖር አለብን፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ጠብቃችሁ ለማቆየት የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁን ለጌታ ቀድሳችሁ መስጠት፣ እርሱን ማገልገል፣ ገንዘባችሁንም ለወንጌል መጠቀምና ደስታችሁንና ሐዘናችሁን ከእግዚአብሄር ጋር መጋራት ይኖርባችኋል፡፡ የዚህ አይነት ሕይወት መምራት ከፈለግን ወንጌልን ለማገልገል ጠንካራ ፈቃድ ይዘን መኖር አለብን፡፡   
ብዙ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ የራሳቸውን ሕይወት ኖረዋል፡፡ የራሳቸው አለቃ ለመሆንም ግድግዳዎችን አቆሙና ንብረታቸውን አከማቹ፡፡ ሆኖም አሁን እግዚአብሄርን አንድና ብቸኛ አለቃ አድርገን ልንሾመው ይገባናል፡፡ ጌታ እንዲህ አለ፡- ‹‹የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም፡፡›› የበጎ ወታደርን ሕይወት መኖር ማለት ሕጎችን መታዘዝ ማለት ነው፡፡ የእርሱ ታማኝ ወታደሮች ሆነን ለእርሱ የምንኖር ከሆንን ጌታ ችግሮቻችንን ያቃልልልናል፤ ይመራንማል፡፡ አስቀድመን የእግዚአብሄርን መንግሥትና ጽድቁንም እንድንሻ ይነግረናል፡፡ (ማቴዎስ 6፡33)     
በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ውሸት የሆነ ነገር የለም፡፡ እርሱን ከተከተልነው የቃሉን እውነተኛነት እንለማመዳለን፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ በልባችሁ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሊኖር እንደሚገባ አስታውሱ፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሌለው ሰው የራሱን ዙፋን ለእግዚአብሄር አሳልፎ ሊሰጥ አይችልም፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያለበት ሰው ግን የልቡን ዙፋን ለእግዚአብሄር ስለሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ይለማመዳል፤ በልቡ ውስጥም ሰላምና ሐሴት ይኖራል፡፡
ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ለእናንተ እውነተኛ ሊሆን የሚችለው ውብ የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ስትረዱና ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትና የተባረከ ሕይወት እንዲኖራችሁ ከፈለጋችሁ እግዚአብሄርን እንደንጉሥ ልታገለግሉትና ለመንግሥቱም በጎነት ልትኖሩ ይገባል፡፡ ያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትሞላላችሁ፤ ልባችሁም ይትረፈረፋል፡፡ የተባረከው ሕይወታችሁም በእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ ልጆች የመሆንን በረከቶች በማሸነፍ ተጠብቆ ይቆያል፡፡ 
በጌታ በማመን የሐጢያት ደህንነትና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት መኖር እንደሚኖርባቸው የሚናገረውን መልዕክት አቅርቤያለሁ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወት አብራርቻለሁ፡፡ የዚህ አይነቱ ሕይወትም እንዴት ተጠብቆ እንደሚቆይ ገልጫለሁ፡፡ 
ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ላለው ሰው ዳግም መወለድ የመጨረሻው አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን በመኖር መቀጠል ይኖርበታል፡፡ መንፈሳችንና ሥጋችን ሊባረኩ የሚችሉት የዚህ አይነት ሕይወት ስንኖር ብቻ እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅና ማመን አለብን፡፡
የዚህ አይነቱ ሕይወት በዘፈቀደ የሚሆን አይደለም፡፡ ጌታችንን አለቃችን አድርገን በማመን በልባችን ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ስንሰጠው ብቻ የሚሆን ነው፡፡ እግዚአብሄር አድኖናል፡፡ ወንጌልን የምናገለገልበትን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትም ሰጥቶናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወት ጠብቀን ማቆየት እንችል ዘንድ ሥራውን የምንሰራበትን ስፍራ ሰጥቶናል፡፡     
ራሳችሁን ለእርሱ ቀድሳችሁ ሕይወታችሁን ለእርሱ ልትኖሩ ይገባል፡፡ ይህንን ውብ ወንጌል በመስበክ አገልግሉት፡፡ ያን ጊዜ ልባችሁ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል፡፡ ሐሴትና ጸጋም ከውስጣችሁ ይፈልቃል፡፡ እርሱ በሚመለስበት ቀንም በእግዚአብሄር ፊት በኩራት ቆማችሁ ሽልማቱን በመቀበል ትባረካላችሁ፡፡ እናንተና እኔ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወት ማድነቅ አለብን፡፡ የዚህ አይነቱን ሕይወት በእምነት ለመኖር መጣር አለብን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን ሕይወት ጠብቀን ማቆየት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር የልባችሁን ዙፋን ለቃችኋልን? እርሱ በልባችሁ ውስጥ ዋናውን ስፍራ እንዲይዝ እንደምትፈቅዱለት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን ለመኖር ፈቃድ ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወትን መኖር ትችሉ ዘንድ የሚባርካችሁ ያን ጊዜ ነው፡፡