Search

คำสอน

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 2-1] የሮሜ መግቢያ ምዕራፍ 2

በዚህ ዓለም ላይ በእግዚአብሄር የሚያምኑ ሁለት የሕዝብ ቡድኖች ብቻ አሉ፡፡ እነርሱም አይሁዶችና ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት የሕዝብ ቡድኖች መካከል የመጀመሪያው ቡድን በኢየሱስ ሲያምን ሁለተኛው ቡድን ግን አያምንም፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ የማያምኑትን ሕዝቦች እምነት ከንቱ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች የሚገጥማቸው እጅግ ከበድ ያለ ችግር በኢየሱስ ቢያምኑም ገና ከሐጢያቶቻቸው ያልተላቀቁ መሆናቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ርዕስ በምዕራፍ 2 ላይ አንስቶታል፡፡ ይህ ለአይሁዶችና ለግሪኮች ብቻ ሳይሆን ለዛሬዎቹ ክርስቲያኖችም ነው፡፡
 

 
አይሁዶች በቀላሉ ሌሎችን ይኮንናሉ፡፡

 
ሐዋርያው ጳውሎስ ተመሳሳይ እምነቶች ያሉዋቸውን አይሁዶችና ክርስቲያኖች ገስጾዋቸዋል፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 2፡1 ላይ ‹‹አንተ የምትፈርድ ሰው›› በማለት አይሁድ ወይም ክርስቲያን በመሆናቸው በላጭነት ስሜት የሰከሩትን ይገስጻቸዋል፡፡ በእግዚአብሄር ካመኑ በኋላ ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች በልቦቻቸው ውስጥ ባለው የሕሊና ሕግ ስህተቱ ምን እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ሌሎችን እንዳይሰርቁ የሚነግሩዋቸው ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው ያመነዝራሉ፡፡ የጌታንም ቃሎች አይጠብቁም፡፡ ሆኖም ራሳቸውን በእግዚአብሄር የሚያምኑ አማኞች አድርገው በመቁጠር ሌሎችን በእግዚአብሄር ትዕዛዛት ይመራሉ፡፡ እነዚህ በአይሁዶችና በክርስቲያኖች መካከል ያሉ ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች ናቸው፡፡
 
በእግዚአብሄር የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን ሕግ እንደሚጠብቁ በመመካት ሌሎች ጣዖታትን እንዳያመልኩ ወይም እንዳይገድሉ ይነግሩዋቸዋል፡፡ ስለዚህ የእርሱን ሕጎች በመጣስ እግዚአብሄርን ያሳፍራሉ፡፡
 
የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሳያውቁ በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ኢየሱስ አዳኛቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን እምነታቸው በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቀድሞውኑም ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ የደመሰሰውን የእግዚአብሄርን እውነተኛ ጽድቅ ይቃወማሉ፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምኑትን እውነተኛ ምዕመናን እየተቃወሙ ያሉት እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን አያውቁም፡፡ ብዙ ሰዎች የኢየሱስን ፍቅር ወይም መንፈሳዊ ግርዘት ሳያውቁ ራሳቸውን ክርስቲያኖች ብለው ይጠራሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የያዘውን ወንጌል ግን ይንቃሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንደሚከተሉ ይናገራሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኢየሱስን አልተቀበሉትም፡፡ ኢየሱስ ራሱን የእግዚአብሄር ልጅ በማድረጉ ተሳድቦዋል ብለው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ እንዳይደለ በስውር አይሁዳዊ የሆነ ግን እውነተኛ አይሁዳዊ እንደሆነ ተናግሮዋል፡፡ እነርሱ የእግዚአብሄር ሕዝብና የእግዚአብሄር መንግሥት አካል ነን ይላሉ፡፡ ነገር ግን አይሁዶች አዳኛቸውን ኢየሱስን ክደው ሳለ እንዴት በእግዚአብሄር ሊያምኑ ይችላሉ?
 
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፡፡›› (ሮሜ 2፡29) በመንፈሳዊ ግርዘት የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሄር የሚያምኑ እውነተኛ ምዕመናን ናቸው፡፡ እነርሱ በእምነት ጸድቀዋል፡፡
 
በእግዚአብሄር የሚያምኑ ምዕመናን ሙገሳና ምስጋና የሚቀበሉት ከማነው? ጳውሎስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሄር ነው እንጂ ከሰው አይደለም፡፡›› (ሮሜ 2፡29) በእግዚአብሄር ጽድቅ የምናምን ከሆነ የእርሱን ምስጋና እናገኛለን፡፡ ከእርሱ ዘንድም ሽልማትን እንወስዳለን፡፡ በኢየሱስ በግልጥ እያመናችሁ በልባችሁ ውስጥ ሐጢያትን ከያዛችሁ በእግዚአብሄር ጽድቅ በተጨባጭ አላመናችሁም፡፡ በእርሱ ላይ እያላገጣችሁ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያምን ሰው የሚቀበለውን ፍርድ ትቀበላላችሁ፡፡
 
የእግዚአብሄርን እውነት ቸል የሚሉ እነማናቸው? እነርሱ ከእግዚአብሄር ቃል ይልቅ የሰዎችን ቃል አጥብቀው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እነርሱ በክርስትና ውስጥ ራሳቸውን በተለያዩ አንጃዎች አደራጅተው እግዚአብሄርን ይቃወማሉ፡፡ በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን አይነት ፍርድ እንደሚወርድባቸው መገመት ትችላላችሁን?
 

 
እግዚአብሄርን የሚቃወሙ ሰዎች የሚደርስባቸው ቅጣት፡፡

 
ቁጥር 8 እና 9 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለአመጻ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቁጣና መቅሰፍት ይሆንባቸዋል፡፡ ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፡፡ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፡፡››
 
ክፋትን በሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ጭንቀት›› የሚለው አገላለጽ የሲዖል ቅጣትን የሚያሳይ ነው፡፡ ክፋትን የሚያደርጉ ሰዎች መከራና የሲዖል ጭንቀት ይገጥማቸዋል፡፡
 
እግዚአብሄርን የሚንቁ ሰዎች ምን አይነት እርግማን ይደርስባቸዋል? እግዚአብሄር ፍቅሩን በሚንቁ ላይ አስፈሪ ፍርድ ይልክባቸዋል፡፡ ከመንፈሳዊ ግርዘት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ፍቅር የሚቃወሙ ሰዎች በአካልና በአእምሮ እንዴት በሰላም ይኖራሉ ብላችሁ ታስባላችሁ? አንዳንድ ሰዎች አሁን ብልሹ ሕይወትን ይኖሩና ይሞታሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቁጣ የሚገባቸው ናቸውና፡፡ እነርሱ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ስለተቃወሙ በልባቸው ውስጥ እውነተኛ እርካታ የላቸውም፡፡ ከመንፈሳዊ ግርዘት የሚገኘውን ፍቅር አያውቁም፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ቢሄዱና በኢየሱስ እንደሚያምኑ ቢናገሩም አሁንም ድረስ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ስላላገኙ ይቸገራሉ፡፡
 
ይህንን ምስጢር በኢየሱስ ስላመናችሁ ብቻ ልታውቁት አትችሉም፡፡ ይህንን የሚያውቁት በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑት ብቻ ነው፡፡ እናንተ በተሳሳተ መንገድ በእግዚአብሄር የምታምኑ አማኞች የእግዚአብሄር ጽድቅ የሆነውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መረዳትና ማመን እንዳለባችሁ ትመከራላችሁ፡፡ ያን ጊዜ ከመከራና እርግማን ራሳችሁን ነጻ ማውጣት ትችላላችሁ፡፡
 
አንድ ሰው በኢየሱስ እያመነ በልቡ ውስጥ ሐጢያት እንዳለ የሚናገር ከሆነ ይህ ማለት በተሳሳተ መንገድ ስላመነ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሚለግሰው እውነተኛ ወንጌል ማመን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ሰዎች በየትኛውም የእምነት ድርጅት ውስጥ በሆነው በኢየሱስ ቢያምኑም በእርሱ እናምናለን እያሉ በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት ይዘው ከሆነ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ቸል የማለትን ሐጢያት እየሰሩ ነው፡፡ በእግዚአብሄር የማመን ትክክለኛው ውጤት ምንድነው? ኢየሱስ በእውነት አዳኛችሁ እንደሆነ የምታምኑ ከሆነ በእርግጥም ሐጢያት አልባ ትሆናላችሁ፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ካመናችሁ በኋላ እንኳን በልባችሁ ውስጥ ሐጢያት ካለ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሚገባ አልተረዳችሁትም ማለት ነው፡፡
 
ሐጢያተኞችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ያዳነው አስቀድሞ በሥጋ በመምጣት ሐጢያተኞችን አድኖ የምዕመናን ሁሉ አዳኝ ሆንዋል፡፡ ታዲያ በውሃውና በመንፈስ ቅዱስ ከልቡ የሚያምን ሰው ሐጢያት ሊኖርበት ይችላልን? መጀመሪያ በኢየሱስ ካመነበት ቅጽበት ጀምሮ በእግዚአብሄር ጽድቅ ከልቡ ያመነ ሰው ሐጢያት አይኖርበትም፡፡ ልቡ ሐጢያት የሚሰራው ቢያንስ በኢየሱስ ያመነ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ቸል ስለሚል ነው፡፡
 
ስለዚህ አሁኑኑ ግትርነታችሁን መተው አለባችሁ፡፡ ‹‹ኢየሱስን በተሳሳተ መንገድ አምኜዋለሁ! ታዲያ ኢየሱስን ማወቅና ማመን የሚገባኝ በምን መንገድ ነው? መስቀሉ ኢየሱስን በማመን ረገድ አስፈላጊ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ የእርሱ ጥምቀትም ደግሞ እንደዚሁ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለና በይፋ እንደተኮነነ ወደ መረዳት ደርሻለሁ፡፡›› እናንተም እነዚህን እውነቶች ተረድታችሁ ልታምኑባቸው ይገባችኋል፡፡
 
ስለዚህ ጌታን በመቃወም ግትሮች የሆኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን መቅሰፍት ይቀበላሉ፡፡ ውጤቱም ወደ ሲዖል እሳት መጣል ነው፡፡ ማቴዎስ 7፡22 እንዲህ የሚለው ለዚህ ነው፡- ‹‹በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም፤ በስምህ አጋንንትን አላወጣንምን፤ በስምህስ ብዙ ተዓምራትን አላደረገንምን? የሉኛል፡፡›› ጌታ ዳግም ሲመጣ ላይ ላዩን በኢየሱስ እንደሚያምኑ የሚያስመስሉ፣ በእግዚአብሄር ጽድቅ የማያምኑና በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያቶች ያሉባቸው ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ይኮነናሉ፡፡ ጌታን እንዲህ ይሉታል፡- ‹‹በአንተ በሚገባ አላመንሁምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣሁምን? በልሳንስ አልተናገርሁምን? ጌታ ሆይ አላገለገልሁህምን?››
 
ጌታ ግን እንዲህ ይላቸዋል፡- ‹‹ከቶ አላወቅኋችሁም፡፡ እናንተ አመጸኞች ከእኔ ራቁ! (ይህ በእግዚአብሄር ጽድቅ የማያምኑትን ይጠቁማል፡፡) ጥምቀትን በመቀበልና በመስቀል ላይ በመሞት ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ እንደደመሰስሁ ሳታምኑ እንዴት በእኔ እንደምታምኑ ልትናገሩ ትችላላችሁ? ውሸታሞች ናችሁ፡፡ ለዘላለም በሚነደው እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፡፡ ሐጢያታችሁ የሐሳዊ ነቢይ ሐጢያት ነው፡፡ ብዙ ሰዎችንም ወደ ሲዖል ልኮዋል፡፡›› በእርሱ ጽድቅ የማያምኑና ግትርነታቸውን የማይተዉ ሰዎች አስፈሪውን የእግዚአብሄር ቁጣ ይቀበላሉ፡፡
 
ለዚህ አይነቱ እምነት እጅግ ትልቁ ምሳሌ የአይሁዶች እምነት ነው፡፡ እነርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመጣው የእግዚአብሄር ጽድቅ አያምኑም፡፡ በፕሮቴስታንቶች መካከል እንኳን የንስሐ ጸሎቶችን በሚያቀርቡበት ጊዜ ሁሉ በየቀኑ የሚሰሩዋቸው ሐጢያቶች ይቅርታን ያገኛሉ የሚሉ ብዙ ግትር ክርስቲያኖች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሄር ቁጣ ለማምለጥ በእርሱ ጽድቅ ያለማመን ግትርነታቸውን መተው አለባቸው፡፡
 
እነርሱ በየቀኑ ንስሐ በሚገቡበትና የእርሱን ይቅርታ ለማግኘት በሚጸልዩበት ጊዜ ሁሉ የሰሩዋቸውን ወንጀሎች ኢየሱስ ይቅር ይላቸዋልን? አይላቸውም፡፡ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ሊቀ ካህንና የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የነበረው አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስን ከ2,000 ዓመታት በፊት አጠመቀው፡፡ እርሱም በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ በዚህም የእግዚአብሄርን ጽድቅ ፈጸመ፡፡ በአንድ ጊዜም የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ደመሰሰ፡፡
 
ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን የት ወሰዳቸው? ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ በራሱ ላይ ተሸከመ፡፡ በመስቀል ላይ ደሙን ለማፍሰስና ለሁሉም ሐጢያቶች በይፋ ፍርድን ለመቀበል ወደ ጎልጎታ በመሄድ አማኞችን ለዘላለም ከሐጢያት አድኖዋቸዋል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን የሆኑ ሐጢያተኞች ሁሉ አሁንም ድረስ ግትሮች ናቸው፡፡ በእግዚአብሄርም ጽድቅ አያምኑም፡፡ ልቦቻቸው በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደም አስቀድሞ ከሐጢያቶች ሁሉ ነጽቶ ከሆነ እስኪሞቱ ድረስ ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን መለመን ለምን አስፈለጋቸው? እነርሱ ግትሮች ናቸው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀትም እንደዚሁ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት ማመንና የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡
 
እያንዳንዱ ሰው ግትር ነው! በእግዚአብር ፊት ግን የእርሱን ጽድቅ የመናቃችሁን ግትርነት መተው ይገባችኋል፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምኑ ሰዎች ቃሎቹን ማመንና መታዘዝ አለባቸው፡፡ እኔም ደግሞ በጣም ግትር ሰው ነኝ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ፊት ግትርነቴን ትቼ በጸጋው ጻድቅ ሆኛለሁ፡፡
 
እውነተኛ ንስሐ የራስን ግትርነት ትቶ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በአእምሮ በመቀበል የሐጢያቶችን ስርየት መቀበል ነው፡፡ ይቅርታን ከተቀበልን በኋላ በእግዚአብሄር ፊት በመንፈሳዊ ሁኔታ የተሻለ ሕይወትን ለመኖር በመሞከር የተሳሳቱ መንገዶቻችንን መቀየርና ስህተቶቻችንን ማመን አለብን፡፡ ዳግም በተወለደ ጻድቅ ትክክለኛ ሕይወት ውስጥ ንስሐ የሚባለው ስህተቶችን ማመን ነው፡፡
 
በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የማያውቁ ሰዎች ይጠፋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግትር የሆኑ መንገዶቻቸውን መተው፣ ንስሐ መግባትና የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ለማግኘትም በኢየሱስ ጥምቀትና መስቀል ማመን አለባቸው፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 3፡19) ጌታ ይህንን ትዕዛዝ የሰጠን በእርሱ ጽድቅ በማመን በአንድ ጊዜ የሐጢያቶችን ስርየት እንድናገኝ ነው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በስቅለቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንዳነጻ በሚናገረው እውነት በማመን ፈጽሞ ጻድቃን ሰዎች እንድንሆንና የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅርታ እንድናገኝ እግዚአብሄርንና ቃሎቹን ማድመጥ ይኖርብናል፡፡ አንድ ሰው በእግዚአብሄር ጽድቅ ሲያምን ሐጢያቱ ሁሉ ይቅር ይባልና መንፈስ ቅዱስን በስጦታ መልክ ይቀበላል፡፡ የኢየሱስ ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት ሁሉ በእግዚአብሄር ጽድቅ አምነው በአንድ ጊዜ የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብለዋል፡፡ እናንተም ደግሞ በእግዚአብሄር ፊት ግትሮች መሆን የለባችሁም፡፡ በትክክለኛ ወቅቶች ግትሮች መሆን ይኖርባችኋል፡፡ መንፈሳዊውን ግርዘት በሚገባ የማታስተውሉ ከሆነ ልትማሩትና ልታምኑት ይገባችኋል፡፡ ግትር ሆኖ መቅረት ትክክል አይደለም፡፡ ንስሐ መግባትና ማመን ይኖርባችኋል፡፡
 
ሰዎች የመንፈሳዊ ግርዘትን እውነት ሳያውቁ እውነትን ይንቃሉ፤ ያላግጡበትማል፡፡ ‹‹ያ ስህተት ነው! ሰው በየቀኑ ሐጢያቶችን እየሰራ እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? ገናም በሐጢያት የተሞሉ ቢሆኑም እግዚአብሄር በኢየሱስ የሚያምኑ ምዕመናኖችን ጻድቃን ብሎ እንደጠራቸው ታውቃላችሁ፡፡ ይህ የመንጻት ትምህርት ነው፡፡ ጻድቃን ተብላችሁ የተጠራችሁት በእርግጥ በልባችሁ ውስጥ አንዳች ሐጢያት ስለሌለባችሁ አይደለም፡፡›› ነገር ግን ይህ በጣም የተሳሳተ ትምህርት እንደሆነ ማወቅ ይገባችኋል፡፡
 
እግዚአብሄር በመጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያቶችን ስርየት በሚሰጠን የመንፈሳዊ ግርዘት ወንጌል አማካይነት ‹‹ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ ደምስሻለሁ፡፡ አሁን ሐጢያት አልባ ናችሁ፡፡ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ስለወሰድሁ ጻድቃን ናችሁ›› ይላል፡፡ ‹‹በጽድቄ ታምናላችሁን? በመንፈሳዊ ግርዘት ቃሎች የምታምኑ ከሆናችሁ ያን ጊዜ ከሕዝቦቼ አንዱ ናችሁ፡፡ ሐጢያት አልባም ናችሁ›› ይላል፡፡ እግዚአብሄር ፍጹም ስለሆነው ማዳኑ ተናግሮዋል፡፡ የስም ክርስቲያኖች ግን በመንፈሳዊ ግርዘት በሚያምኑ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ይሳለቃሉ፤ ያፌዛሉም፡፡ ‹‹ሰው ያለ ማቋረጥ ሐጢያቶችን እየሰራ ሳለ እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? አንድን ሰው ‹ሐጢያት አልባ› ብላችሁ ልትጠሩት የምትችሉት በመንጻት ትምህርት አማካይነት ብቻ ነው፡፡ አንድን ሰው እንዴት ሐጢያት አልባ ነው ብለን ልናስብ እንችላለን? ሰው በየቀኑ ሐጢያትን ከመስራት በቀር ሌላ ማድረግ አይችልም›› ይላሉ፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ ስለማያምኑ እንደዚህ በመሳለቅ ግትሮች ሆነው ይቀራሉ፡፡
 
እግዚአብሄር ግን በጎን በማድረግ ለሚታገሱ የዘላለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል፡፡ በጎን በማድረግ የታገሱ ክብርን፣ ምስጋናንና የማይጠፋን ሕይወት የሚሹ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆናሉ፡፡ እንዲህ የማያደርጉ ግን ቅጣትን ይቀበላሉ፡፡ ኢየሱስ ከልባቸው ለዘላለም ለመኖር ለሚሹና ሐጢያት አልባ ሕይወት ላላቸው ሰዎች የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፡፡
 
‹‹ጌታ ሆይ በሕሊናዬ አንዳች የማላፍርበት ሕይወትን እንድኖር ከልቤ የምሻው በሐጢያት ስርየት ማመን ነው፡፡ የአንተ ልጅ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ በአንተ ጽድቅ ማመንና አንተን ማስደሰት እፈልጋለሁ፡፡ ሐጢያት አልባ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ እባክህ ከሐጢያቶቼ ሁሉ አድነኝ፡፡›› የእግዚአብሄርን የጽድቅ ደህንነት የሚሹና ለሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች የእግዚአብሄር አምላክን የጽድቅ ወንጌል ለእነርሱ በመስጠት ፍላጎቶቻቸውን ሁሉ ያዳምጣል፡፡ ሐጢያቶቻቸውንም ሁሉ ይቅር ይላቸዋል፡፡ ለዘላለም ለመኖር ለሚፈልጉ ሰዎች እግዚአብሄር የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፡፡
 

 
መንፈሳዊ ግርዘት ምንድነው?

 
መንፈሳዊ ግርዘት ማለት በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት የተፈጸመ የሐጢያቶች ስርየት ነው፡፡ የበጉ ደም በይፋ የተገለጠ ፍርድ ነው፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁን የዓለም ሐጢያቶች ወደ ኢየሱስ መተላለፋቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ክርስትና ብሉይ ኪዳንን ቸል ማለት አይችልም፡፡ ምክንያቱም እንደዚያ የሚያደርግ ከሆነ በአዲስ ኪዳን ሊያምን አይችልምና፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊው ግርዘትና በፋሲካ የፈሰሰው የበጉ ደም በጣም የተሳሰሩ እንደሆኑ ማግኘት እንችላለን፡፡
 
በ1ኛ ዮሐንስ 5፡6 ላይ ኢየሱስ ‹‹በውሃው ብቻ ሳይሆን በውሃውና በደሙ›› እንደመጣ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በውሃ ወይም በደም ብቻ አልመጣም፡፡ እርሱ የመጣው በሁለቱም ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ለመዳን በውሃው በደሙና በመንፈሱ ቃሎች ማመን ይኖርባችኋል፡፡
 
ዘጸአት ምዕራፍ 12ን ሳነብ ስለ መንፈሳዊ ግርዘት አንዳንድ ጥያቄዎች ነበሩብኝ፡፡ ዘጸአት ምዕራፍ 12 ምን ማለት ነው? ምዕራፉን በሙሉና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተዛማጅ የሆኑትን ምንባቦች በሙሉ ደጋግሜ በጥንቃቄ ተመለከትሁ፡፡ እስራኤሎች በፋሲካው በዓል ላይ መሳተፍ የቻሉት ግርዘትን ስለተቀበሉ እንደነበር ተረዳሁ፡፡ በአዲስ ኪዳንም ኢየሱስ ዝም ብሎ በመስቀል ላይ ላይ ደሙን እንዳላፈሰሰ ተናግሮዋል፡፡ እርሱ ደሙን ያፈሰሰው በዮሐንስ በመጠመቁ ነበር፡፡
 
እግዚአብሄር ሕጋዊ ለሆነው የፋሲካ በዓል ለእስራኤሎች ሁለት ስርዓቶችን እንደሰጣቸው ተናግሮዋል፡፡ አስቀድመው ግርዘትን እንዲቀበሉና ከዚያም የፋሲካውን ጠቦት ሥጋ እንዲበሉ! በብሉይ ኪዳን መንፈሳዊው ግርዘት ይህ ነበር! በአዲስ ኪዳን ሐጢያቶቻችን በዮሐንስ ጥምቀት ወደ ኢየሱስ እንደተላለፉና እርሱም በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰ ተናግሮዋል፡፡ እነዚህን እውነታዎች መቀበል ውጤቱ የመንፈሳዊ ግርዘትን እውነት መቀበል እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ የዓለምን ሐጢያቶች የተሸከመውና በእኛ ፋንታም ፍርድን ለመቀበል በመስቀል ላይ መሞት የነበረበት ለዚህ ነው፡፡
 
ይህንን እውነት በልባችሁ በመቀበል ከሐጢያቶቻችሁና ከበደሎቻችሁ ሁሉ መዳንን ትለማመዳላችሁ፡፡ አንድ ሰው ከሐጢያቱ ሁሉ ለመዳን ከፈለገ መንፈሳዊ ግርዘትን ሊሰጠው በሚችለው በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ያስፈልገዋል፡፡ ሰዎች ይህንን እውነት መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እናንተ አንባቢያን የሐጢያቶችን ስርየት በሚመለከት የብሉይ ኪዳኑ መንፈሳዊ ግርዘትና የአዲስ ኪዳኑ የኢየሱስ ጥምቀት እውነት እንደሚጣመሩ መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ኢየሱስ ፍርድን የተቀበለው ሐጢያት ስለሰራ አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ለሰው ዘር በመስቀል ላይ የሞተው ስለተጠመቀና የዓለምን ሐጢያቶች በሥጋው ስለተሸከመ ነበር፡፡ መንፈሳዊ ግርዘትን የተቀበሉ ሰዎች እምነት ይህ ነው፡፡
 
በመንፈሳዊ ግርዘት አማካይነት በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች በኢየሱስ ከልባቸው ስለሚያምኑ ሐጢያት የለባቸውም፡፡ በኢየሱስ ያመኑ ከእግዚአብሄር ዘንድ መንፈሳዊ ግርዘትን ላልተቀበሉ ሰዎች አዝንላቸዋለሁ፡፡ እነርሱ ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደ የመሆኑን እውነት ማመን ይኖርባቸዋል፡፡
 
የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በመስቀሉ ብቻ እንጂ በጥምቀቱ የማያምኑ መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምን እምነት የላቸውም፡፡ እግዚአብሄር በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ የነገረንን ማመን እንዳለብን ማወቅ ይኖርባችኋል፡፡
 
የስነ መለኮት ምሁራን አስተምህሮቶችና ትምህርቶች ምንም ይሁኑ ልንጥላቸው ይገባናል፡፡ ማመን ያለብን ወደ እርሱ ጽድቅ የሚመሩንን የእግዚአብሄር ቃሎች ብቻ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የእርሱ ጽድቅ የሌለባቸው ቃሎች በእርግጥም የእግዚአብሄር ቃሎች ስላልሆኑ ነው፡፡ መንፈሳዊ ግርዘት የሌለበት ወንጌል የተሟላ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ስለ ግርዘት በአዲስ ኪዳን ደግሞ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በብሉይ ኪዳን ስለ ግርዘትና ስለ ፋሲካው ደም የተናገረው በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ ጥምቀትና ከደሙ ጋር ይዛመዳል፡፡ መንፈሳዊ ግርዘትን ለማግኘት በዚህ እውነት ማመን አለብን፡፡ ነገር ግን በዚህ እውነት የማናምን ከሆንን ከእግዚአብሄር መንግሥት እንገለላለን፡፡
 
የእግዚአብሄር ጽድቅ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ብቻ ተፈጽሞዋልን? እንደዚያ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ የተፈጸመው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ግርዘትን በልቦቻችን ውስጥ የተቀበልነው በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ብቻ ሳይሆን ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱም ነው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባደረገው የስርየት ሞቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በተጨባጭ ስለደመሰሰ መንፈሳዊ ግርዘትን ማግኘት ችለናል፡፡
 
 
ግርዘት ማለት ቆርጦ መጣል ማለት ነው፡፡
 
ኢሳይያስ መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመቁሰልና በመምታት የሐጢያቶቻችንን ፍርድ በይፋ እንደሚቀበል ተንብዮአል፡፡ ስለዚህ ከመቀጠላችን በፊት አንድ ነገር ማወቅ ይኖርበናል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለምን መሰቀል አስፈለገው?
 
በብሉይ ኪዳን አንድ ሐጢያተኛ ሐጢያቶቹን ለማሻገር እጆቹን ለመስዋዕት በቀረበው ጠቦት ራስ ላይ መጫንና ጠቦቱን ማረድ ነበረበት፡፡ ከዚያም ካህኑ ለሐጢያት መስዋዕት ሆኖ ከቀረበው እንስሳ ደም በጣቱ የተወሰነውን ይወስድና በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ የቀረውን ደም ከመሰውያው በታች ያፈስሰዋል፡፡ (ዘሌዋውያን 4፡27-30) የብሉይ ኪዳን ዘመን ሐጢያተኛ ከሐጢያቶቹ መንጻት የሚችለው በዚህ መንገድ ነበር፡፡ እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን የእግዚአብሄር በግ ሆኖ የመጣው ኢየሱስ (ዮሐንስ 1፡29) የሰውን ዘር ሐጢያቶች ለመውሰድ በብሉይ ኪዳን ይደረግ እንደነበረው በራሱ ላይ እጆች ሊጫኑበት አይገባውምን?
 
ታዲያ ጌታ የዓለምን ሐጢያቶች የወሰደው መቼና እንዴት ነበር? ይህ ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ባጠመቀበት በማቴዎስ 3፡13-17 ላይ አልተገለጠምን? ይህም በብሉይ ኪዳን በዘሌዋውያን ውስጥ ሐጢያተኛው ሐጢያቶቹን ለማስተላለፍ ‹‹እጁን በሐጢያት ቁርባኑ ራስ ላይ ይጭናል›› (ዘሌዋውያን 1፡4፤3፡8፤4፡29) ከሚለው ጋር የሚዛመድ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሊቀ ካህኑ እጆቹን በጠቦቱ ራስ ላይ ጭኖ የእስራኤሎችን ሐጢያቶች በሙሉ ማሻገር ነበረበት፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡21) ከዚያም ከደሙ የተወሰነውን ይወስድና በሚቃጠለው መስዋዕት መሰዊያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ የቀረውን ደም ደግሞ ከመሰዊያው በታች ያፈስሰዋል፡፡ እነርሱም በዚህ መንገድ የሐጢያቶችን ስርየት ይቀበላሉ፡፡
 
ልክ በዚሁ መንገድ እኛም ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ የሐጢያቶቻችንን ስርየት አግኝተናል፡፡ እግዚአብሄር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊሰጠን የፈለገው የአምላክ ጽድቅና መንፈሳዊ ግርዘት ይህ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛ በእግዚአብሄር ጽድቅ የምናምን ሰዎች ኢየሱስ በዮሐንስ በመጠመቁና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰሱ ሐጢያቶቻችን ተወግደዋል፡፡ በአዲስ ኪዳን የኢየሱስን ጥምቀት ትርጉም ከብሉይ ኪዳን ግርዘት ጋር አያይዘን ስናስተውለው በእግዚአብሄር ጽድቅ ወደ ማመኑ እንመጣለን፡፡ በልቦቻችንም መንፈሳዊውን ግርዘት በትክክል ወደ መቀበል እንመጣለን፡፡
 
 
በአዲስ ኪዳን እውነተኛው መንፈሳዊ ግርዘት፡፡
 
ማቴዎስ 3፡13-15ን እንመልከት፡- ‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡››
 
አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ አጠመቀው፡፡ እጆቹን በኢየሱስ ራስ ላይ ጭኖ አጠመቀው፡፡ (በግሪክ ማጥመቅ ማለት ‹‹ባፕቲዞ›› ሲሆን ፍቺውም ከውሃ ስር ማጥለም ወይም ማጥለቅ ነው፡፡)
 
ኢየሱስ ለሐጢያቶቻችን በመስቀል ላይ ይሞት ዘንድ በመጀመሪያ በጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻችንን መውሰድ ነበረበት፡፡ እርሱ ለምን ተጠመቀ? እርሱ የተጠመቀው የእግዚአብሄር ጽድቅ ሁሉ መፈጸም ይችል ዘንድ ነው፡፡ እርሱ በጥምቀት አማካይነት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በመውሰድ አምላካችንና አዳኛችን መሆኑ ትክክልና ተገቢ ነበር፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ተሸክሞ በመስቀል ላይ መሞቱ ተገቢ ነበር፡፡
 
ኢየሱስ በአገልግሎት ሕይወቱ ያደረገው የመጀመሪያው ነገር ጥምቀትን መቀበል ነበር፡፡ በግሪክ ‹‹ባፕቲዝማ›› የሚለው ጥምቀት ‹‹መታጠብን፣ መቀበርን፣ ማስተላለፍንና ማሻገርን›› ያመለክታል፡፡ በብሉይ ኪዳን ሰባተኛው ወር 10ኛው ቀን ለእስራኤሎች የስርየት ቀን ነበር፡፡ አሮንም የእስራኤሎችን ሐጢያቶች በሙሉ ለማስተላለፍ እጆቹን በመስዋዕቶቹ ፍየሎች ላይ ይጭን ነበር፡፡ ከሁለቱ ፍየሎች አንዱ ለእግዚአብሄር የቀረበ ሲሆን ሌላው ደግሞ በእስራኤሎች ፊት የማስተሰርያ መስዋዕት ሆኖ የቀረበ ነው፡፡ (ዘሌዋውያን 16) በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ተቀበለ፡፡ 
ኢየሱስ በተጠመቀ ማግስት ዮሐንስ ጣቱን ወደ እርሱ ቀስሮ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ›› ሲል ተናገረ፡፡ (ዮሐንስ 1፡29)
 
መንፈሳዊ ግርዘት በደሙ በማመን ብቻ ሊገኝ እንደማይችል ማመን አለባችሁ፡፡ 
ከ1ኛ ዮሐንስ 5፡4 ጀምረን እንመልከት፡- ‹‹ከእግዚአብሄር የተወለደ ሁሉ አለምን ያሸንፋልና፤ አለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው፡፡ ኢየሱስም የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር አለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውሃና በደም የመጣ ይህ ነው፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውሃውና በደሙ እንጂ በውሃው ብቻ አይደለም፡፡ መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው፡፡ የሚመሰክሩት መንፈሱና ውሃው ደሙም ሦስት ናቸውና፡፡ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ፡፡ የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሄር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፡፡ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሄር ምስክር ይህ ነውና፡፡ በእግዚአብሄር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፡፡ በእግዚአብሄር የማያምን እግዚአብሄር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል፡፡ እግዚአብሄር የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው፡፡ ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ ልጁ የሌለው ሕይወት የለውም፡፡›› (1ኛ ዮሐንስ 5፡4-12)
 
የመንፈሳዊ ግርዘት ማረጋገጫው ምንድነው? የኢየሱስን ጥምቀትና ደሙን ደህንነታችን አድርገን የምናምንበት እምነት ነው፡፡ ዓለምን ድል ያደረገው ውሃውና ደሙ ነው፡፡ ‹‹በውሃና በደም የመጣ ይህ ነው፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውሃውና በደሙ እንጂ በውሃው ብቻ አይደለም፡፡ መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው፡፡ የሚመሰክሩት መንፈሱና ውሃው ደሙም ሦስት ናቸውና፡፡›› እግዚአብሄር አምላካችንና አዳኛችን መሆኑን የሚያሳዩት እነዚህ ምስክሮች እግዚአብሄር የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም እንደመጣ፣ በጥምቀቱ አማካይነትም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በሥጋው እንደወሰደ፣ በእኛ ፋንታም ደሙን በመስቀል ላይ እንዳፈሰሰና በዚህም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንዳዳነን ይመሰክራሉ፡፡
በአዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ግርዘቱ ወንጌል ውሃውንና ደሙን የያዘ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውሃው ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት ሲያመለክት ደሙ ደግሞ በመስቀል ላይ የሆነውን ሞቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ከብሉይ ኪዳን ግርዘት ጋር ይዛመዳል፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁ ሐጢያቶቻችን በጥምቀት ወደ እርሱ እንደተሻገሩ ማረጋገጫ ነው፡፡ በእውነት የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ቆመው ‹‹አምላኬ አንተ አዳኜ ነህ፡፡ በጽድቅህ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ሐጢያት የለብኝም፡፡ እኔ የአንተ እንከን አልባ ልጅ ነኝ፡፡ አንተም አምላኬ ነህ›› ማለት ይችላሉ፡፡ እንደዚህ በእርግጠኝነት እንድትጮሁ የሚያደርጋችሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መሰረት ምንድነው? የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሚያዋቅረው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ላይ ያላችሁ እምነት ነው፡፡ በክርስቶስ ደም ብቻ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የራሴ ጽድቅ አድርጌ መቀበል የሚቻል አይደለም፡፡ ይህንን የሚፈጥሩት ጥምቀቱና ደሙ ናቸው፡፡ 
የኢየሱስ ጥምቀት በደህንነታችን ውስጥ ስላለው አስፈላጊነት የሚናገረውን ምንባብ እንመልከት፡፡ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 የዚህ እውት ማረጋገጫ ነው፡፡ ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውንን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡›› 
አሁን ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ደህንነታችን የማያጠራጥር ማስረጃ እየተናገረ ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ግርዘትን የሚያመለክት ነበር፡፡ ገባችሁ? በብሉይ ኪዳን እስራኤሎች በግርዘት ሸለፈታቸውን ቆርጠው እንደጣሉ ሁሉ ኢየሱስም በአዲስ ኪዳን በዮሐንስ ተጠምቆ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰድ መንፈሳዊ ግርዘትን እንድንቀበል አስቻለን፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም የእግዚአብሄርን ጽድቅ ፈጠሩ፡፡ መንፈሳዊ ግርዘትና ጥምቀት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ለሁላችንም መንፈሳዊ ግርዘትን እንደሚያመለክት መረዳት ይኖርባችኋል፡፡
 
‹‹ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡›› የእግዚአብሄርን ጽድቅ የምንቀበለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንደተጠመቀና ለሐጢያቶቻችንም በመስቀል ላይ እንደሞተ በማመን ነው፡፡ ማቴዎስ 3፡15 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በኢየሱስ ራስ ላይ ስለተጫኑ የሐጢያተኞች ሐጢያቶች ፈጽመው ተደምስሰዋል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመንም እያንዳንዱ ሐጢያተኛ ጻድቅ ይሆናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ከተሸከመ በኋላ በመስቀል ላይ የፍርድ ደሙን አፈሰሰ፡፡ የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በዚህ መንገድ ተሰርየዋል፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች እንደወሰደና በእኛ ፋንታም በይፋ እንደተፈረደበት ማመን ለምዕመናን የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሚያመጣው እውነት ማመን ማለት ነው፡፡ በዚህ እውነት እመኑ፡፡
 
ዮሐንስ 1፡29 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ፡፡›› ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ ፈጣሪያችን በመሆኑም የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰድ የግርዘት ተስፋውን ፈጸመ፡፡ በልባችን ውስጥ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሆነውን መንፈሳዊ ግርዘት የሚያመጣው እውነተኛው እምነት ይህ ነው፡፡ ኢየሱስ እውነተኛው ጽድቃችን ነው፡፡ ኢየሱስን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ መንፈሳዊ ግርዘትን እንድንቀበል ላስቻለን ጥምቀቱና ደሙ እርሱን ማመስገን አለብን፡፡
 
1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ይቀጥላል፡- ‹‹የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡›› የአንድ ሰው የሥጋ እድፍ ኢየሱስን እውነተኛ አዳኙ አድርጎ ስላመነ ብቻ አይወገድም፡፡ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት መቀበል የምትችሉት ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ወደ ኢየሱስ መተላለፋቸውን በማመን ነው፡፡ ኢየሱስን አዳኛችሁ አድርጋችሁ መቀበል የሐጢያት ስርየትን በልባችሁ ውስጥ ያስቀምጣል፡፡ ይህ በምዕመኑ ልብ ውስጥ ይሆናል፡፡ አዳኙን በልባችሁ ስታምኑት ሥጋችሁ አሁንም የረከሰና ሐጢያቶችን የሚሰራ ቢሆንም ከሐጢያታችሁ ትነጻላችሁ፡፡ ነገር ግን ሐጢያት የለም፡፡ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ እንደተላለፉና በልባችሁ ውስጥም ምንም ሐጢያቶች እንደሌሉ በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ትቀበላላችሁ፡፡
  
 
እውነትን የራሳችሁ ለማድረግ በእርሱ ማመን አለባችሁ፡፡
 
ዮሐንስ 1፡12 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡›› 
የተቀበላችኋቸው ቃሎች ምንድናቸው? የእግዚአብሄር ልጅ የሰራቸውን ነገሮች መቀበል ይኖርባችኋል፡፡ የእግዚአብሄር ሥራ ምን ነበር? የእግዚአብሄር ልጅ በሐጢያተኛ ሥጋ ምሳሌ ወደ ምድር መጣ፡፡ ሰላሳ ዓመት ሲሆነው ሐጢያቶቻችን ይደመሰሱ ዘንድ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ሊወስድና መንፈሳዊ ግርዘትን ሊሰጠን ተጠመቀ፡፡ ከዚያም የእግዚአብሄር በግ ሆኖ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ለእኛም ስርየትን ሰጠን፡፡ ጌታ ለሐጢያተኞች ሁሉ የዘላለም የሐጢያት መስዋዕት በመሆን ለዘላለም አዳነን፡፡ ይህ እውነተኛ እምነት ነው፡፡ በዚህ እውነት በማመን ጻድቃን እንሆናለን፡፡
 
በክርስቶስ ደም ብቻ መንፈሳዊ ግርዘትን መቀበል እንችላለን? አንችልም፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ሐጢያቶችን ከእኛ አስወግዶዋል፡፡ ለሐጢያተኞች ደሙን በማፍሰስ በመስቀል ላይ የተቀበለው ፍርድም ለእናንተና ለእኔ በይፋ የተቀበለው ፍርድ ነበር፡፡ በእግዚአብሄር የጽድቅ ወንጌል ማለትም በኢየሱስ የጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው የደሙ ወንጌል በማመናችን ከሐጢያት ድነናል፡፡ ከፍርድም ነጻ ሆነናል፡፡ ኢየሱስን አዳኝ አድርጎ መቀበል በሐጢያተኛው ልብ ውስጥ ያሉትን ሐጢያቶች በሙሉ መደምሰስ ይችላል፡፡ በልቦቻችሁ ውስጥ መንፈሳዊውን ግርዘት ተቀበሉ፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር ጽድቅ የእናንተ ይሆናል፡፡
 
 
እውነተኛ መንፈሳዊ ግርዘት በልብ ውስጥ መከናወን አለበት፡፡
 
በሮሜ ምዕራፍ 2 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› ልባችሁን የምትገረዙት እንዴት ነው? ኢየሱስ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር እንደመጣ፣ ‹‹የዓለምን ሐጢያቶች›› በሙሉ ለመውሰድ እንደተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰና ዘላለማዊ አዳኛችን ይሆን ዘንድም ዳግመኛ ከሙታን እንደተነሳ በማመን ይቻላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ልብ መገረዝ እንዳለበት ተናግሮዋል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት በማመን በልባችሁ መገረዝ ትችላላችሁ፡፡ በልባችሁ መንፈሳዊ ግርዘትን መቀበል ከፈለጋችሁ በኢየሱስ ጥምቀት እመኑ፡፡ ያ ጊዜ በእርግጠኝነት ከእግዚአብሄር ልጆች አንዱ ትሆናላችሁ፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ከሐጢያቶቹ ሁሉ እንዳዳነው የሚያምን ሰው ጻድቅ ነው፡፡
 
ኢየሱስ 29 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ቤተሰቡን እየረዳ የግል ሕይወቱን ኖረ፡፡ 30 ዓመት ሲሆነው ግን የአገልግሎት ሕይወቱን መኖር ጀመረ፡፡ በአገልግሎት ሕይወቱ ወቅት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በመደመሰስ ሐጢያተኞችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው፡፡ መጀመሪያ ያደረገው ነገር ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳንና ጻድቃን ለማድረግ መጠመቅ ነበር፡፡ ‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ ከዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡›› (ማቴዎስ 3፡13) ኢየሱስ ለምን ሊጠመቅ ሞከረ? እርሱ ይህንን ያደረገው የሐጢያተኛውን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ የጥምቀቱን እውነተኛ ትርጉም መሳት የለብንም፡፡ ጥምቀት ሐጢያቶችን በማስተላለፍ ማስወገድ ነው፡፡ ኢየሱስም የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ለመውሰድ ሲል ዮሐንስ እንዲያጠምቀው የጠየቀው ለዚህ ነው፡፡
ኢየሱስን ያጠመቀው ዮሐንስ ማነው? ዮሐንስ የሰው ዘር ሁሉ ወኪል ነበር፡፡ ይህ በማቴዎስ 11፡11-14 ላይ በሚገባ ተብራርቷል፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል፡፡ ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል፡፡ ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፡፡ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፡፡››
 
ከአጥማቂው ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ የእግዚአብሄር ኪዳን ዘመን አብቅቷል፡፡ ይህ የሆነው የአምላክን ተስፋዎች መፈጸም የነበረበት ሰው ኢየሱስ በመምጣቱ ነው፡፡ ታዲያ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉትን የተስፋ ቃሎች መፈጸም የነበረባቸው ሰዎች እነማን ነበሩ? ኢየሱስና አጥማቂው ዮሐንስ ነበሩ፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ሐጢያቶችን ወደ ኢየሱስ አስተላለፈ፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ሐጢያቶችን በሙሉ በአዲስ ኪዳን ወደመጣው የእግዚአብሄር በግ ለማስተላለፍ የተላከ የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነበር፡፡ ዮሐንስ በመስዋዕቱ ሕግ ውስጥ በተደነገገው ሕጋዊ መንገድ መሰረት እጆቹን በኢየሱስ ራስ ላይ በመጫን ተግባሩን ፈጸመ፡፡ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ተቆርጠው ወደ ኢየሱስ ተላለፉ፡፡ እግዚአብሄርም ‹‹እንዲህ›› በሰው ዘር ልቦች ውስጥ መንፈሳዊ ግርዘትን ሰጠ፡፡
 
የኢየሱስን ጥምቀትና ደሙን ስርየታችሁ አድርጋችሁ አጥብቃችሁ ያዙ፡፡ ኢየሱስ ቀድሞውኑም የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወስዶዋል፡፡ ፍርድንም ሁሉ ተሸክሞዋል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል ኢየሱስ መጠመቁንና ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለማንጻትም ደሙን ማፍሰሱን የሚናገር እውነት ነው፡፡ አሁን የእግዚአብሄርን ጽድቅ በልቦቻችን ውስጥ በመቀበል የሐጢያቶችን ስርየት ማግኘት እንችላለን፡፡ ይህንን ብትቀበሉ ‹‹የአብርሃም ልጅ የዳዊት ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ›› ወደሚለው መግባት ትችላላችሁ፡፡ አስቀድመው የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን የማያወቁና አሁንም ድረስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ያሉም አሉ፡፡ ጸሐይ ትጠልቃለች፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት እመኑና ወደ እርሱ ግቡ፡፡ በጥምቀት የምታምኑበት እምነት ለሰርጉ ድግስ የተዘጋጀ ዘይታችሁ ይሆናል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ ላይ ደም በማመን ብቻ ዳግመኛ የሚመጣልንን ጌታ ኢየሱስ ለመገናኘት ዘይታችሁን ታዘጋጁ ዘንድ ምስጢሩን እንደምታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
 
ኢየሱስ የእያንዳንዱን ሰው ሐጢያቶች ለመደምሰስ ሲል ጥምቀትን ተቀበለ፡፡ ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅና ራሱም አምላክ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪያችን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች አድርጎ ሊቀበለን በአባቱ ፈቃድ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ሁሉ የሚናገሩት ስለ ማነው? የሚተነብዩት ስለ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱ ወደ ምድር መጥቶ ሐጢያቶቻችንን እንዴት እንደሚወስድና እንደሚያስወግድ የሚናገሩ ትንቢቶች ነበሩ፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያሉት ትንቢቶች እንደተናገሩት ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ወደ ምድር በመምጣት በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወሰደ፡፡ ከአዳምና ከሄዋን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሰው ድረስ ያሉትን የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ተሸከመ፡፡
 
በልቦቻችሁ መንፈሳዊ ግርዘትን ተቀበሉ፡፡ ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› (ሮሜ 2፡29) በኢየሱስ ጥምቀት ስታምኑ ወዲያውኑ የልብ ግርዘትን ትቀበላላችሁ፡፡ የልብ ግርዘት ማለት ሐጢያቶቻችን በሙሉ በእርሱ ጥምቀት ወደ እርሱ መተላለፋቸውን ስንቀበል በልቦቻችን ውስጥ ያሉት ሐጢያቶች መወገድ ማለት ነው፡፡ የልብ ግርዘትን ተቀብላችኋልን? በልብ ግርዘት በማመን ‹‹ሐጢያቶች በሙሉ በእምነት ይነጻሉ፡፡››
 
 
በእርግጥ የመንፈሳዊ ግርዘትን እውነት በልባችሁ ተቀብላችኋልን?
 
ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ከተጠመቀና በመስቀል ላይ ከሞተ 2,000 ዓመታት ሆነውታል፡፡ እኛ ይህንን እውነት መቀበልና በልቦቻችን ውስጥ ማኖር ያለብን ዛሬ ነው፡፡ ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው፡፡›› እውነትን በማመን በአእምሮዋችንና በልቦቻችን ግርዘትን መቀበል እንችላለን፡፡ ሁላችንም በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ደህንነትን ተቀብለናል፡፡ በምድር ላይ የእግዚአብሄር ፍርድ ቢመጣም አንፈራም፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄር ፍርድ አይወርድባቸውም፡፡ የእግዚአብሄር ፍርድ የሚወርደው በልቦቻቸው ውስጥ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ባልተቀበሉት ሰዎች ላይ ነው፡፡
 
ዛሬ ክርስቲያኖች በኢየሱስ እያመኑ የሚሳሳቱት ለምንድነው? ለምን በጭንቀት ይኖራሉ? ለደህንነታቸው በኢየሱስ ደም ብቻ ስለሚያምኑ ነው፡፡ አሁን እግዚአብሄርን በግትርነታችሁ እንዳሰቃያችሁት አምናችሁ ኢየሱስ በዮርዳኖስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደ ወደ መሆኑ እውነት መመለስ ይገባችኋል፡፡ ያን ጊዜ በልባችሁ ውስጥ መንፈሳዊ ግርዘት ይከናወናል፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ የምታምኑ ከሆነ በልባችሁ ውስጥ መንፈሳዊ ግርዘት ይከናወናል፡፡ ከእግዚአብሄር ሕዝብም አንዱ ትሆናላችሁ እንጂ የእግዚአብሄር ፍርድ አያገኛችሁም፡፡ በመካከላችሁ በኢየሱስ እያመኑ በኢየሱስ ደም ላይ ብቻ ጥገኛ የሆኑ ሰዎች ካሉ ጥያቄ ልጠይቃቸው እወዳለሁ፡፡ መንፈሳዊ ግርዘታችሁና የእግዚአብሄር ጽድቅ በመስቀሉ ደም ብቻ የተገኙ ናቸውን? ደህንነታችን የተፈጸመው በደም ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ጥምቀት፣ በደሙና በመንፈስ ነው፡፡
 
 
ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ የሚደረሰው ከክርስቶስ ጋር በመቆራኘት ነው፡፡
 
ሮሜ 6፡3-8ን እናጥና፡- ‹‹ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፡፡ ከእንግዲህስ ወዲያ ለሐጢአት እንዳንገዛ የሐጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን፡፡ የሞተስ ከሐጢአቱ ጸድቋልና፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፡፡››
 
ቁጥር 5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፡፡›› መጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያት ደመወዝ ሞት እንደሆነ ማለትም ሐጢያት ያለበት ሰው ሁሉ እንደሚጠፋና ወደ ሲዖል እንደሚወርድ ይናገራል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ እውነት ሙሉ በሙሉ ከማመናችሁ በፊት ሁላችሁም ሐጢያት አልነበረባችሁምን? አዎ፡፡ ኢምንት የምታክል ሐጢያት ብትኖርባችሁ እንኳን ወደ ሲዖል ትወርዳላችሁ፡፡ ‹‹በእሳትና በዲን የሚቃጠለውን ባህር›› (ዮሐንስ ራዕይ 21፡8) ፍርድም ትቀበላላችሁ፡፡ ለሐጢያቶቻችን ሞት የሆነውን ዋጋ መክፈል ቢኖርብን ኖሮ ፈጽሞ ከሐጢያቶቻችን መዳን ባልቻልንም ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ምድር በመላክ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስተላለፈለት፡፡ በእኛ ፋንታም እርሱን ኮነነው፡፡
 
እግዚአብሄር አብዝቶ ስለወደደን ሁላችንንም አዳነን፡፡ እግዚአብሄር አብ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም በመላክ በጥምቀት አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ልጁ አስተላለፈ፡፡ ለሐጢያቶች ስርየትን ለመስጠትም ደሙን ያፈስስ ዘንድ በምስማር ተቸነከረ፡፡ በዚህ ማመን ከኢየሱስ ጋር አንድ መሆን ነው፡፡ የሐጢያት ደመወዝ ሞት ነው፡፡ ሁላችንም በልቦቻችን ውስጥ ሐጢያቶች ስለነበሩብን በእነዚያ ሐጢያቶች ምክንያት ወደ ሲዖል መውረድ ይጠበቅብን ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ሲዖል ለመውረድ በታጨነው በእኛ ፋንታ ኢየሱስ በዮርዳኖስ በመጠመቅና በመስቀል ላይ በይፋ በመቀጣት ሐጢያቶችን አስወገደ፡፡ ስለዚህ የእርሱ ሞት የእኛ ሞት ሆነ፡፡ ምክንያቱም የእርሱ ጥምቀት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶዋልና፡፡
 
ብዙ ሰዎች ዛሬም ‹‹በሃይማኖታዊ›› መንገድ በኢየሱስ ያምናሉ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ይቅርታን እየለመኑ ሐጢያቶቻቸውን ሲናዘዙ በእንባዎቻቸው ይታጠባሉ፡፡ አሁኑኑ ይህንን ማድረግ አቁሙና በእግዚአብሄር ጽድቅ እመኑ፡፡ በልባችሁ የእግዚአብሄርን ሰላም ታገኛላችሁ፡፡ ኢየሱስ እኛን ለማዳን ሲል ተጠመቀ፡፡ በመስቀል ላይም ሞተ፡፡ በዚህ ወንጌል እንደምታምኑ ስፋ አደርጋለሁ፡፡
 
እግዚአብሄር በሙሴ በኩል ስለ ሐጢያቶች ስርየት አስተምሮናል፡፡ ሙሴ ወደ ግብጽ ሄዶ የእርሱን ሕዝብ እስራኤሎችን ነጻ እንዲያወጣ የተነገረውን የእግዚአብሄር ትዕዛዝ ተቀበለ፡፡ ስለዚህ ከሚስቱና ከልጁ ጋር በአህያ ተጭነው ወደ ግብጽ ሄዱ፡፡ በዚያ ሌሊት የእግዚአብሄር መልዕክተኛ ተገልጦ ሙሴን ሊገድለው ሞከረ፡፡ በዚያን ጊዜ ሚስቱ ሲፓራ ፈጥና የባልጩት ድንጋይ በመውሰድ የልጅዋን ሸለፈት ገርዛ በሙሴ እግሮች ፊት ጣለችውና ‹‹አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ›› (ዘጸአት 4፡25) አለችው፡፡
 
በዚህ ምንባብ ውስጥ ያለው እውነት ይህንን ይመስላል፡፡ ግርዘትን ባይቀበል የሙሴም ልጅ እንኳን ከእግዚአብሄር ሕዝብ እንደ አንዱ ባልተቆጠረም ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ሊገድለው ሆነ፡፡ እግዚአብሄር እስራኤሎች ባይገረዙ ኖሮ የእርሱ ሕዝብ ሆነው እንደማይቆጠሩ ተናግሮዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ግርዘት ከእግዚአብሄር ሕዝብ አንዱ የመሆን ምልክት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሙሴ ይህንን እንዲገነዘብ ፈለገ፡፡ ስለዚህ የሙሴ ሚስት የልጅዋን ሸለፈት በፍጥነት በመግረዝ ‹‹አንተ የደም ሙሽራ ነህ›› ብላ ጣለችው፡፡ እግዚአብሄር በልጁ አለመገረዝ ምክንያት ሙሴን ሊገድለው ሞከረ፡፡
 
ግለሰቡ የአብርሃም ዘር ቢሆን እንኳን ካልተገረዘ ከእስራኤሎች መካከል ይቆረጣል፡፡ የፋሲካውን ጠቦት ሥጋ መብላትና የበሩን ጉበንና መቃን በበጉ ደም መቀባት የሚችለው የተገረዘ ብቻ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ መሳተፍ የሚችሉትም በመንፈሳዊ ግርዘት የተገረዙ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ እምነት የሌላቸው ሰዎች ፈጽሞ ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ መግባት ስለማይችሉ በእግዚአብሄር ክብር ውስጥ ተሳታፊ ናቸው፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ አይሁድ ነበር፡፡ በስምንት ቀኑ ተገረዘ፡፡ በገማልያል እግር ስር ተቀምጦም አደገ፡፡ በብሉይ ኪዳን የተካነ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ለምን መጠመቅና በመስቀል ላይ ለምን መሞት እንደነበረበት በሚገባ ተረድቷል፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በብዙ ማረጋገጫ መስበክ ቻለ፡፡ ‹‹መገረዝም የልብ መገረዝ ነው›› (ሮሜ 2፡29) ያለው ለዚህ ነው፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ስለ ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት መናገሩ እርግጥ ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን የመውሰድ መንፈሳዊ ግርዘታችንን ቢፈጽምም በመስቀል ላይ ባይሰዋ ኖሮ ማለትም ፍርድን ባይቀበል ኖሮ መዳን ባልቻልንም ነበር፡፡ ጳውሎስ በተደጋጋሚ ስለ መስቀሉ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ መስቀሉ የመንፈሳዊ ግርዘታችን ድምዳሜና ፍጻሜ መሆኑን በአእምሮዋችሁ መያዝ ይኖርባችኋል፡፡ ነገር ግን ዛሬ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ሞቱ መካከል ስላለው ግንኙነት ቅንጣት ያህል እሳቤ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ለሲዖል ይኮነናሉ፡፡ በመንፈሳዊ ግርዘት የማመኑ ሐይል በሚገባ ለትውልዶች ቢተላለፍ ኖሮ የዘመኑ ክርስትና እንደዚህ አይሆንም ነበር፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን ለመጀመሪያ በተገናኙት ጊዜ በጣም አመስግነዋል፡፡ ነገር ግን ሊቋቋሟቸው በማይችሉዋቸው ድካሞች ተስፋ በመቁረጥ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የከፉ ሐጢያተኞች ይሆናሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢየሱስ ካመኑ በኋላ አስር ዓመታት አልፈው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የከፉ ሐጢያተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በኢየሱስ ካመኑ በኋላ እንኳን ሐጢያተኞች ሊሆኑ ይችላሉን?
 
‹‹♪ማልቀስ አያድነኝም! ♫ፊቴ በእንባዎች ቢታጠብም ♫ፍርሃቶቼን መቋቋም አይችሉም፡፡ ♫የዓመታት ሐጢያቴን ሊያነጹልኝ አይችሉም! ♫ማልቀስ አያድነኝም!...♪በክርስቶስ ያለኝ እምነት አያድነኝም! ♫በሚያለቅሰው ልጅህ ልታመን፡፡ ♪እርሱ በሰራው ሥራ ልታመን፡፡ ♪አቤቱ እርዳኝ፡፡ ወደ ክንዶች እሮጣለሁ፡፡ ♪በክርስቶስ ማመን ያድነኛል♪፡፡››
 
‹‹ማልቀስ አያድነኝም፡፡ በክርስቶስ ማመን ያድነኛል›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ግን በቃል ብቻ ነው፡፡ ሐጢያት በሚሰሩበት ጊዜ ሁሉ እንባቸውን እያፈሰሱ ይጸልያሉ፡፡ ‹‹አምላኬ እባክህ ይቅር በለኝ፡፡ አሁን ይቅር የምትለኝ ከሆነ ከአሁን ጀምሮ ጥሩ እሆናለሁ፡፡›› አንድ ክርስቲያን ሐጢያት ሲሰራ ይናዘዛል፡፡ ያለቅሳል፡፡ እነርሱ ይቅርታም ይጠይቃሉ፡፡ ያን ጊዜ ጥሩ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ለዓመታቶች ያህል የሚደጋግም ሰው በጸጸት ‹‹ለምን ቀደም ብዬ በኢየሱስ አመንሁ? በእርሱ ማመን የነበረብኝ 80 ዓመት ሲሆነኝ ነበር፡፡ በጣም በለጋነት ዕድሜዬ አምኛለሁ›› የሚል ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ ይህ የሆነው እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መኖር ስለሚጠበቅበት ነው፡፡ ነገር ግን አልኖረም፡፡
 
እያንዳንዱ ሰው ለሚሰራው ሐጢያት ፍርድ ሊኖር ይገባል፡፡ ኢየሱስ የተጠመቀው፣ በመስቀል ላይ የተኮነነውና የከበረውን ደሙን ያፈሰሰው እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን ነው፡፡ በሶስት ቀንም ከሙታን ተነሳ፡፡ እግዚአብሄር አብ ኢየሱስን እንደገና ወደ ሕይወት መለሰው፡፡ በመንፈሳዊ ግርዘት የሚያምን ሰው ወንጌልን የማሰራጨት ሕይወት ሊኖር ይችላል፤ ይኖርማል፡፡ መንፈሳዊ ግርዘት እኛ የእግዚአብሄር ልጆች እንደምንሆን የሚያሳይ ማስረጃና የእግዚአብሄርም ጽድቅ ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ሐጢያቶቻችን ወደ እርሱ ለመተላለፋቸው ማስረጃ ሲሆን በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ክቡር ደሙ ደግሞ ይፋ ፍርድን በመቀበል የሐጢያቶቻችንን ደመወዝ በሙሉ ለመክፈሉ ማስረጃ ነው፡፡
 
በኢየሱስ እያመናችሁ በልባችሁ ሐጢያተኞች ሆናችሁ ቀርታችኋልን? ያ መናፍቃን እምነት ነው፡፡ ቲቶ 3፡10 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መለያየትን የሚያነሳ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ሐጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሰጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ፡፡›› መናፍቅ የሆነ እምነት ያላቸው ሰዎች በራሳቸው ላይ የፈረዱ ሐጢያተኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሞት ቢያስፈራራቸውም እንኳን ሐጢያተኞች በመሆናቸው የሚጸኑ ናቸው፡፡ እነርሱ የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን ለመቀየር በጣም ትሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ለእነዚህ ሐጢያተኞች ‹‹መናፍቅ ነህ፤ የእኔ ልጅ አይደለህም፡፡ ወደ ዘላለም የሲዖል እሳት ትወረወራለህ›› ይላቸዋል፡፡
 
በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወይም የኢየሱስን ጥምቀትና ደም መንፈሳዊ ግርዘት ያልተቀበሉ ሰዎች መናፍቅ ክርስቲያኖችና በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኝነታቸውን ከመናዘዝ በቀር ሌላ ማድረግ የማይችሉ ታላላቅ ሐጢያተኞች ናቸው፡፡ በኢየሱስ ጽድቅ የማያምኑ ሐጢያተኞች ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገቡ አይችሉም፡፡
 
በኢየሱስ ካመኑ በኋላ ጻድቃን የሆኑ ሰዎች በልቦቻቸው ውስጥ መንፈሳዊ ግርዘትን ለመቀበላቸው ማስረጃ አላቸው፡፡ ማስረጃዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡ ኢየሱስ የሰው ሥጋ ለብሶ የመጣ አምላክ ነው፡፡ እርሱ ተጠምቆ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶዋል፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ለመውሰድ ወደ ምድር መጣና በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ በመንፈሳዊ ግርዘት የሚያምኑትን ሰዎች እምነት ፍጹም ለማድረግም በመስቀል ላይ ፍርድን ተቀበለ፡፡ በሦስት ቀናት ከሙታን ተነሳ፡፡ ሕያው አዳኛችንም ሆነ፡፡ ትክክለኛው የእግዚአብሄር የደህንነት ጽድቅ በደም ብቻ የሆነው ሳይሆን በውሃ፣ በደምና በመንፈስ የሆነው ነው፡፡ እርሱ ለእኛ ፍጹም የሆነ ደህንነት እንደሰጠን የሚመሰክሩት የመንፈሳዊ ግርዘት አሳማኝ ማስረጃዎች እነዚህ ናቸው፡፡
 
ውድ ክርስቲያኖቼ ደህንነታችን የተከናወነው በኢየሱስ ደም ብቻ ሳይሆን በውሃው፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ መሆኑን በልቦቻችሁ ተቀበሉ፡፡ እግዚአብሄር የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ቆርጦ በመጣል ኩነኔን ፈጽሞ ከእኛ አስወግዶዋል፡፡ እርሱ ቆርጦ የጣለው የእኔን ሐጢያቶች ብቻ ሳይሆን ከአዳም ሐጢያት ጀምሮ በምድር ላይ የሚቀረው የመጨረሻ ሰው እስከሚሰራቸው ድረስ ያሉትን ሐጢያቶችም ጭምር ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ በጥምቀቱና በደሙ አስወግዶዋቸዋል፡፡ መንፈሳዊ ግርዘትን መቀበል በውሃውና በደሙ በመጣው በኢየሱስ በተፈጸመው የእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምነውን ማንኛውንም ሰው ያድነዋል፡፡
የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ኢየሱስ በዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ተቆርጠው ተጥለዋል፡፡ አሁን በመንፈሳዊው ግርዘት የሚያምኑ ሰዎች በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት ሊኖርባቸው አይችልም፡፡ ኢየሱስ ዳግመኛ ከሙታን ተነስቶ በሐጢያት የሞቱትን ነፍሶቻችንን በጽድቁ ሕያው አድርጎዋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀት፣ በደሙና በመንፈሱ ወንጌል እኛን እየፈለገ ነው፡፡ አሁን እኛ በመንፈሳዊ ግርዘት ለሚያምኑ ሰዎች እግዚአብሄር ከፍጥረት በፊት በኢየሱስ ያቀደው እቅድ ነበር፡፡ አሁን እናንተ በእግዚአብሄር ጽድቅ የምታምኑ መንፈሳዊ ግርዘትንም ደግሞ ተቀብላችኋል፡፡