Search

คำสอน

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 4-2] እነዚያ ሰማያዊ በረከትን በእምነት የተቀበሉ፡፡ ‹‹ ሮሜ 4፡1-8 ››

‹‹ ሮሜ 4፡1-8 ››
‹‹እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ዘንድ አይደለም፡፡ መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሄርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ ለሚሰራ ደመወዝ እንደ እዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡ ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡ እንደዚህ ዳዊት ደግሞ እግዚአብሄር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቆጥረለት ስለ ሰው ብጽዕና ይናገራል፡፡ እንዲህ ሲል፡- አመጻቸው የተሰረየላቸው ሐጢአታቸውም የከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡ ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› (ሮሜ 4፡1-8)
 
 

ሐጢያታቸው የተሰረየላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡

 
በዚህ ዘመን ብዙ ነፍሳቶችን በማዳኑ ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ ምዕራፍ 4 ላይ ስለተባረኩ ሰዎች ይናገራል፡፡ ስለዚህ ስለተባረኩ ሰዎች መናገር እወዳለሁ፡፡
 
‹‹እንደዚህ ዳዊት ደግሞ እግዚአብሄር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቆጥረለት ስለ ሰው ብጽዕና ይናገራል፡፡ እንዲህ ሲል፡- አመጻቸው የተሰረየላቸው ሐጢአታቸውም የከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡ ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› (ሮሜ 4፡6-8) መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሄር ፊት ስለተባረኩ ሰዎች ይናገራል፡፡ ሐጢያቶቻቸው በእግዚአብሄር ፊት የተሰረየላቸውና ጌታ ሐጢያትን የማይቆጥርባቸው ሰዎች በእርግጥም የተባረኩ ናቸው፡፡
ወደ ቅዱሳት መጻህፍት ጠልቀን ከመግባታችን በፊት አሁን ያለንበትን ሁኔታ እንዳለ እንመረምር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት አግኝተው ስለተባረኩ ሰዎች ይናገራል፡፡ ስለዚህ እኛም መባረክ ይገባን እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እናስብ፡፡
 
በዚህ ዓለም ላይ ሐጢያት የማይሰራ አንድም ሰው የለም፡፡ የሰው ዘር በኢሳይያስ 44፡22 ላይ እንደተጻፈው እንደ ደመና የበዛ ሐጢያት ይሰራል፡፡ ያለ ኢየሱስ ጸጋ ማንም ሰው የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማስወገድ አይችልም፡፡
 
ጌታ የሐጢያቶችን ስርየት በሰጠን የኢየሱስ ጥምቀትና የመስቀል ደሙ ከሐጢያቶቻችንና ከእግዚአብሄር ፍርድ ነጻ አውጥቶናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ባቀረበው መስዋዕት አሁን በሕይወት መኖር ችለናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ፈጽሞ ሐጢያት ያልሰራ ሰው ሊኖር ይችላልን? ሰው የሐጢያት ስርየትን የተቀበለ ቢሆን ወይም ባይሆን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሐጢያት መስራቱ አይቀርም፡፡ ሳናውቀው እንኳን በየጊዜው ሐጢያቶችን የምንሰራ በመሆናችን በሐጢያቶች ምክንያት ፍርድን ለመቀበል ታጭተናል፡፡
 
ቅንጣት ያህል መጠን ያለው ሐጢያት ያለበት ሰው ወደ ሲዖል የሚወርድ የመሆኑን እውነታ አምናለሁ፡፡ ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሐጢያት ደመወዝ ሞት ነው ይላልና፡፡ (ሮሜ 6፡23) የሐጢያት ደመወዝ ምንም ይሁን መከፈል አለበት፡፡ ሐጢያቶች ይቅርታን የሚያገኙት ሰው ዋጋውን ከከፈለ በኋላ ብቻ ነው፡፡ ሐጢያት የሚያመጣው ፍርድን ብቻ ነው፡፡
 
የምንኖረው በሁሉም አይነት ሐጢያቶች፣ ትልቅና ትንሽ በድንቁርና በሚሰሩ ሐጢያቶች፣ በእውቀት በሚሰሩ ሐጢያቶች፣ በድካም በሚሰሩ ሐጢያቶች ውስጥ ነው፡፡ ጠንከር ባለ አነጋገር የምናቀርባቸው ጥሩ ማማኻኛዎች ቢኖሩንም በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያቶቻችንን ከማመን በቀር ሌላ ማድረግ አንችልም፡፡ በዚህ እሳቤ ትስማማላችሁን? ሐጢያቶቻችን በሙሉ ይቅር ቢባሉም ሐጢያቶቻችንን ለማመን እምቢተኞች መሆን ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው አመኔታ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ማመን አለበት፡፡
 
 
ጌታን ማመስገን የሚችለው ጻድቅ ብቻ ነው፡፡
 
ሐጢያቶቻቸውና በደሎቻቸው አስቀድመው ይቅር የተባሉላቸውና የተከደኑላቸው ጻድቃን ሐጢያት አልባ ናቸው፡፡ እግዚአብሄርንም ያመሰግናሉ፡፡ በፊቱ በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ በእያንዳንዱ ሰዓትና ደቂቃ እግዚአብሄርን ከማመስገን በቀር ሌላ ማድረግ የምንችለው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሐጢያቶቻችን እንደ ደመና ቢበዙም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለወሰደውና በእኛ ምትክም በመስቀል ላይ ፍርድን ለተቀበለው ጌታ ምስጋናን እናቀርባለን፡፡
 
ጌታ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ባይስድና የሐጢያት ዋጋ ለመክፈል ባይሰቀልና ባይሞት ኖሮ በድፍረት አባታችን ብለን ልንጠራው እንችል ነበር? ጌታን እንዴት ልናመሰግነው እንችላለን? የእግዚአብሄርን ስም እንዴት ልናመሰግንና ለደህንነት ስጦታው ምስጋናን ልንሰጠው፣ እንደዚሁም እርሱን ልናከብር እንዴት እንችል ነበር?
 
እኛ ቅዱሳኖች ሐጢያቶቻችን አስቀድመው ስለተደመሰሱ ጌታን ልናመሰግነውና በዚህ ጊዜም ልናወድሰው እንችላለን፡፡ ክርስቶስ መስዋዕት ስለሆነልንና ቅንጣት የሚያህሉ ሐጢያቶችን ጨምሮ ጌታ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ ልናመሰግነው እንችላለን፡፡
 
ለሐጢያቶቻችን ይቅርታን ብናገኝም በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ሳለ በምግባሮቻችን ፍጹማን መሆን አንችልም፡፡ ሁላችንም ደካሞች ነን፡፡ ነገር ግን እኛ ጻድቃን እንደ መሆናችን በጸጋው የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ዋጋ በሙሉ የከፈለውን ጌታን እናመሰግናለን፡፡ በጨለማ ውስጥ ናችሁን? ምንም አይነት ጨለማ ይኑር በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት እንደሰራን ብንናዘዝና እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደው ጌታ ብናምን የጌታ እውነት እርሱን እንድናመሰግንና እንድናወድስ ይፈቅድልናል፡፡ እኛ በጸጋውና ሐጢያቶቻችንን ይቅር በማለቱ ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስን የምናመሰግን ቅዱሳን ሆነናል፡፡ ከዚህም በላይ በልባችን የሐጢያቶች ስርየትን ጸጋ ከተቀበልን በኋላ እግዚአብሄርን የምናመልክ ሰዎች ሆነናል፡፡
 
 
ያለ ሥራ ከጸደቅን ይህ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡
 
‹‹እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ዘንድ አይደለም፡፡ መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሄርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ ለሚሰራ ደመወዝ እንደ እዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡ ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› (ሮሜ 4፡1-5)
 
የሰው ሐጢያት የሚሰረየው ዋጋው ከተከፈለ በኋላ ብቻ ነው፡፡ ሕሊናችሁ ንጹህ ለመሆኑ እርግጠኞች ናችሁን? ሐጢያቶቻችን ምንም አይነት ይሁኑ ሕሊናችን ሊነጻ የሚችለው የሐጢያት ዋጋ ከተከፈለ በኋላ ብቻ ነው፡፡ እኛ ሐጢያተኞች ከመሞት በስተቀር ሌላ ምርጫ አልነበረንም፡፡ ነገር ግን ጌታ ለሐጢያቶቻችን ሞተ፡፡ ስለዚህ ሐጢያተኞች ድነው ጸደቁ፡፡
 
ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 4 ላይ በእግዚአብሄር ቃል ያመነውን የእምነት አባት አብርሃምን እንደ ምሳሌ በመጠቀም በዮርዳኖስ ወንዝ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በወሰደውና ለሐጢያቶቻቸው ይኮነን ዘንድ በተሰቀለው በኢየሱስ ክርስቶስ እንደዳኑ ይናገራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም በእግዚአብሄር ስላመነ እንደጸደቀ ይናገራል፡፡ እርሱ የዳነው በራሱ ምግባሮች ሳይሆን በእግዚአብሄር ቃል ላይ ባለው እምነት ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ጻድቅ አድርጎ ቆጠረው፡፡ አብርሃም በእግዚአብሄር ቃሎች በማመን ደህንነትን አግኝቶ ለሚያምኑ ሁሉ አባት ሆነ፡፡ በእግዚአብሄር ኪዳን በማመን ጸደቀ፡፡
ከሐጢያት መዳንና ለእኛ ለሐጢያተኞች የተሰጠን የእግዚአብሄር ጸጋ ምንድነው? ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ ስለዚህ ነገር እናስብ፡፡ ‹‹ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ዕዳ እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡›› (ሮሜ 4፡4) (ሮሜ 4፡4) ይህ ቁጥር እኛን ከሐጢያቶች ሁሉ ስላዳነን የእግዚአብሄር ማዳን ይናገራል፡፡ ስለ ሐጢያቶች ስርየት ያወራል፡፡ ‹‹ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡›› ሰው ለሰራው ሥራ ደመወዝ የሚቀበል ከሆነ ደመወዙን የሚቆጠረው እንደ ጸጋ ነው ወይስ እንደ ዕዳ? ሐዋርያው ጳውሎስ አብርሃምን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ደህንነትን ያብራራል፡፡ ሥራ የሰራ ሰው ለሰራው ሥራ ደመወዝ መቀበሉ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ፍጹም ሕይወትን ባንኖርም እንደ ቅዱሳን ሆነን ከጸደቅን ይህ የእግዚአብሄር ስጦታ እንጂ በራሳችን ጥረቶች የተገኘ አይደለም፡፡
 
‹‹ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡›› (ሮሜ 4፡4) በሐጢያቶች ይቅርታ አማካይነት የሚገኘው ጽድቅ ከጌታ ጥምቀትና ከፈሰሰው የመስዋዕት ደሙ የሚመጣ ነው፡፡ ደህንነት የተገኘው በጸጋና በሐጢያቶች ስርየት ስጦታ አማካይነት ነው፡፡ ሰው ከሐጢያት ሊቆጠብ ስለማይችል ሐጢያት እንደሰራ ያምን ዘንድ ተገደደ፡፡ ሰዎች ምንም ያህል የሚያምኑዋቸው ትምህርቶች ቢኖሩ ወይም ለሐጢያቶቻቸው ምንም ያህል አጠንክረው ቢጸልዩ ሐጢያቶቻቸውን ማንጻት አይችሉም፡፡
 
ሐጢያተኞች ሐጢያቶቻቸውን ማንጻት የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻቸውን እንደወሰደና ለሐጢያቶች ይፋ የሆነ ፍርድ ለመቀበል እንደተሰቀለ በሚናገረው ደህንነት በማመን ነው፡፡ ሐጢያተኞች ራሳቸው በፈጸሙት ማናቸውም አይነት መስዋዕት ለሐጢያቶቻቸው ዋጋ የመክፈል ብቃቶች የላቸውም፡፡ ሐጢያተኞች ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር በሐጢያቶች ይቅርታ አማካይነት በተገኘው ደህንነት ማመን ነው፡፡ ሊደገፉበት የሚችሉበት ብቸኛው ነገር የእግዚአብሄር ጸጋ ነው፡፡
 
ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እጅግ በሚያመች መንገድ ወሰደ፡፡ ራሱን በመስቀል ላይ መስዋዕት በማድረጉም ሐጢያተኞች ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ዳኑ፡፡ ይህ በሰይጣን ማታለያዎች፣ በድካሞቻችን ምክንያት የምንሰራቸውን ጥቃቅን ሐጢያቶችና እንደ ግዙፍ ተራራ የተለቁትን ሐጢያቶች ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ሐጢያተኞች በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ደም በማመን ደህንነትን ተቀብለዋል፡፡ እኛ ሐጢያተኞች የነበርን ሰዎች በእግዚአብሄር ነጻ የደህንነት ስጦታ አሁን ጸድቀናል፡፡
 
 
የሐጢያት ስርየት የሚሰጠው በጸጋና በስጦታ ብቻ ነው፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ ሐጢያተኛ እንዴት ከሐጢያቶቹ ሁሉ እንደሚድን ይናገራል፡፡ ‹‹ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡›› እርሱ የደህንነትን ጸጋ ከዚህ ዓለም ሥራ ጋር በማነጻጸር አብራርቶታል፡፡ አንድ ሐጢያተኛ በእግዚአብሄር ፊት ከሰራ በኋላ ከሐጢያቶቹ እንደዳነ የሚናገር ከሆነ ይህ የተገኘው ከእግዚአብሄር ስጦታ ሳይሆን ከራሱ ሥራዎች ነው፡፡ የሐጢያቶች ስርየት የሚሰጠው በጸጋና እንደ ስጦታ ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጸጋ ውስጥ ከምግባሮቻችን አንዳቸው አልተካተቱም፡፡ የተቀበልነው ከሐጢያት መዳን እግዚአብሄር ለእኛ የሰጠን ስጦታ ነበር ወይስ አልነበረም? አዎ ነበር፡፡ በሐጢያቶቻችን ከመጥፋት በቀር ሌላ ምርጫ አልነበረንም፡፡ ነገር ግን አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ የሞትን ደመወዝ ከፍሎ ለእኛ በመሞቱ እውነታ በማመን ከሐጢያቶቻችን ድነናል፡፡ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በስቅለት በመሸከምም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከኢየሱስ የደህንነት ጸጋ የመነጩ ናቸው፡፡ ይህ ስጦታ ነው፡፡ ነጻ ስጦታ ነው፡፡ ሐጢያተኞች በእግዚአብሄር ፍቅር ድነዋል፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወስዶ በስቅለቱም ሐጢያተኞችን በዓለም ላይ ካሉት ሐጢያቶች ሁሉና ከእግዚአብሄር ፍርድ ሁሉ አዳናቸው፡፡
 
‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢያተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› (ሮሜ 4፡5) ቀደም ብለን ስለሚሰራ ሰው ተነጋግረናል፡፡ ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ›› የሚለው ሐረግ ጻድቅ ለመሆን ሰናይ ምግባሮችን የማይሰሩ ሰዎችን ያመለክታል፡፡ ጳውሎስ ‹‹ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል›› በማለት የቁጥሩን ቀሪ ክፍል ይቀጥላል፡፡
 
እርሱ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማብራራት ሐጢያተኛውን እንደ ምሳሌ ተጠቅሞዋል፡፡ ሐጢያተኛ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ‹‹ሐጢያተኛ›› የሆነ ሰው እግዚአብሄርን የማይፈራና እስከ መጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ ብልሹ ሕይወትን የሚኖር ሰው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጻድቅ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ቃል እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት የሚሰራን ሰው የሚጠቁም ነው፡፡ ሰዎች በሐጢያት ተሞልተው መወለዳቸው እውነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሐጢያቶቻቸው ምክንያት የእግዚአብሄርን ፍርድ ለመቀበል የታጩ መሆናቸው የሰዎች እውነተኛ ባህርይ ነው፡፡
 
ነገር ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፎዋል፡- ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ›› የሚለው ሐረግ ‹‹ጻድቅ ባይሆንም›› ማለት ነው፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ፊት ጻድቅ ነን? --አይደለንም፡፡--
 
እግዚአብሄር ለእኛ ለሐጢያተኞች እንዲህ ይለናል፡- ‹‹እናንተ ሐጢያት የለባችሁም፡፡ እናንተ ጻድቅ ናችሁ፡፡›› ጌታ የሐጢያቶቻችንን ዋጋ በሙሉ ወስዶ ከፍሎዋል፡፡ ኢየሱስ አስቀድሞ የሐጢያቶችን ዋጋ ፈጽሞ እንደከፈለ ታምናላችሁን? የአማኙ እምነት ለጽድቅ ይቆጠርለታል፡፡ ‹‹እናንተ ትክክል ናችሁ፡፡ እናንተ በእርግጥም በዚህ ታምናላችሁ፡፡ እናንተ የእኔ ጻድቅ ሕዝብ ናችሁ፡፡ እኔ በአጥማቂው ዮሐንስ ስጠመቅና በመስቀል ላይም ለሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ስኮነን ስለደመሰስኩት ሐጢያት የለባችሁም!››
 
ሰው ሐጢያተኛ ቢሆንም እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀት የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ አስወግዶዋል፡፡ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን ልኮ በጥምቀቱ ሐጢያቶችን ወሰደ፡፡ በሐጢያተኞችም ፋንታ ተሰቀለ፡፡ እግዚአብሄር የሐጢያት ደመወዝ ሞት ነው የሚለውንና የእግዚአብሄርን የፍቅር ሕግ ሁለቱንም ሕጎች በአንድ ጊዜ ፈጸመ፡፡ ሐጢያተኞችንም ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው፡፡
 
እግዚአብሄር ኢየሱስ በሐጢያተኞች ፋንታ በጽድቅ ምግባሩ አማካይነት የዚህን ዓለም ሐጢያቶች ሁሉ በዮርዳኖስ ወንዝ እንደወሰደ ለሚያምኑ ሰዎች ‹‹አዎ እናንተ ሐጢያት አልባ ናችሁ፡፡ ልጄ አድኖዋችኋል፡፡ እናንተ ድናችኋል›› ይላቸዋል፡፡ ስለዚህ ባይጸድቁም ጸድቀዋል፡፡ በጌታ ደህንነት ላይ ያላቸውን እምነት ሲመለከት ሐጢያተኞች ቢሆኑም እግዚአብሄር እነርሱ የእርሱ ሐጢያት አልባ ሕዝብ እንደሆኑ ተናግሮዋል፡፡ ጌታ ሐጢያቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ጻድቃን እንደሆንን ይጠይቀናል፡፡ ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› በጎ ምግባሮችን እናደርጋለን? እኛ ጥሩ ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ነገር ግን ለሐጢያት ብቻ የምንተጋ ነን፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር ራሱ በደህንነት ስጦታ አድኖናል፡፡ እኛ በጌታ ማዳን ማለትም በኢየሱስ ጥምቀትና ሞት እናምናለን!
 
 
በጌታ ማዳን ላይ ባለን እምነት መኖር አለብን፡፡
 
በፈቃዱ የእኛን የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ዋጋ በሙሉ እንዴት እንደከፈለ በማወቅ ለፍቅር ስጦታውና እኛን ከሐጢያቶቻችን ላዳነን ጸጋው ጌታን እናመሰግነዋለን፤ እናወድሰዋለን፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኞች መሆናችንን በማመናችን በጥምቀቱና በመስቀሉ አማካይነት የሐጢያቶቻችንን ዋጋ በመክፈሉ በበቂ ሁኔታ አላመሰገንነውም፡፡ ነገር ግን ጻድቅ እንደሆንን የምናስብ ከሆንን የእግዚአብሄርን ጸጋ ማመስገን አንችልም፡፡
 
ሐጢያተኛውን በሚያጸድቅ የሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡ ጻድቅ በሚያደርጋቸው የኢየሱስ ቤዛነትና ፍርድ የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን ስጦታዎች ይቀበላሉ፡፡ ሰዎች የጽድቅ ሕይወትን ለመኖር በሚሞክሩበት ጊዜ ብዙ ስህተቶችን ስለሚሰሩ በእግዚአብሄር ፊት ጻድቅ አይደሉም፡፡
 
ሰዎች ሐጢያት ከመስራት መቆጠብ አለመቻላቸው ሐጢያተኝነታቸውን ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ ሐጢያተኛ ብሆንም በእግዚአብሄር ደህንነት በማመን እኖራለሁ፡፡ በእምነት መኖር ማለት እንደፈለጉ እንደፈለጉ መኖር ማለት አይደለም፡፡ በእምነት የጸደቀ ሰው የሚኖርበት የተወሰነ የሕይወት መንገድ አለ፡፡
 
ዳግም የተወለዱ ሰዎች በእያንዳንዲቷ ቀን የኢየሱስ የደህንነት ወንጌል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምን? ምክንያቱም በምድር ላይ ምግባሮቻቸው ጥሩ ስላልሆኑ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ሐጢያት ከመስራት መቆጠብ አይችሉም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ኢየሱስ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንደወሰደ የሚናገረውን የምስራች መስማት ይኖርበታል፡፡ ጻድቅ ሰው በየቀኑ ወንጌልን መስማትና ማሰላሰል አለበት፡፡ ያን ጊዜ መንፈሳቸው በሕይወት መኖር ይችላል፡፡ ልክ እንደ ጸሐይ ወቅትም በተደጋጋሚ እየጠነከሩ ይሄዳሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› ይህ መልዕክት ለማነው? ይህ እምነት የታቀደው እናንተንና እኔን ጨምሮ በዚህ ዓለም ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ነው፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም እንዴት እንደጸደቀ በዝርዝር ይነግረናል፡፡ ለሚሰራ ሰው የእግዚአብሄር ደህንነት አይመሰገንም፡፡ በፋንታው ተቀባይነት ያጣል፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ስለ ወንጌል አያመሰግንም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቁጥር 4 የሚያብራራው የሚሰራን ማለትም መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ሰናይ ምግባሮችን ለማድረግ የሚሞክርን ሰው ነው፡፡ የዚህ አይነት ሰው በፍጹም ስለ ኢየሱስ መስዋዕት አያመሰግንም፡፡ ለምን? በየቀኑ ለሚሰራቸው ሐጢያቶች ይቅርታን ያገኝ ዘንድ የንስሐ ጸሎቶችን እያቀረበ ብዙ ሰናይ ምግባሮችን ስለሚሰራና ስለሚያደርግ ጥረቶቹ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሒያቶቹን ስርየት እንዲቀበል እየሰሩ መሆናቸውን ያስባል፡፡ ከዚህ የተነሳ ፍጹም የሆነውን ይህንን የወንጌል ጸጋ አያመሰግንም፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው በትክክል የእግዚአብሄርን የደህንነት ስጦታ መቀበል አይችልም፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› (ሮሜ 4፡5) ይህ ማለት እግዚአብሄር ሐጢያተኞች የነበሩትንና በራሳቸው ምግባሮች ሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ማግኘት ያልቻሉትን ሰዎች ፈጽሞ አድኖዋቸዋል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጸጋ የሐጢያቶችን ስርየት በመቀበል ለዳኑ ጻድቃን ተገልጦዋል ማለትም ነው፡፡
 
 
የሚሰራ ሰው ጸጋውን እንደ ጸጋ አይቆጥረውም፡፡
 
ሮሜ 4፡5 አብርሃም እንዳደረገው እግዚአብሄርን ለሚያውቅና በቃሎቹ ለሚያምን ሰው የተጻፈ ነው፡፡ እኛ ሐጢያተኛውን ባዳነው ጌታ እናምናለን፡፡ በክርሰቲያኖች መካከል ሁለት አይነት ሰዎች አሉ፡፡ ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ለማግኘት አሁንም ድረስ የሚሰሩና ከሐጢያቶቻቸው ሙሉ በሙሉ የዳኑ ናቸው፡፡ በቁጥር 4 እና 5 ላይ እንደተጻፈው ‹‹የሚሰራ›› እና ‹‹ደመወዝን እንደ ጸጋ የማይቆጥር›› ሰው የሐጢያቶች ስርየት የሚያስገኘውን ጸጋ አይቀበልም፡፡ ምክንያቱም እርሱ በኢየሱስ ካመነ በኋላ ወደ እግዚአብሄር የሚቀርበው በሥራ ነውና፡፡
 
ሰዎች ምግባሮቻቸውን በእግዚአብሄር ፊት ስለሚያቀርቡ ሐጢያተኞች ሆነው ይቀራሉ፡፡ የጽድቅ ትምህርት አማኝ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ጥቂት በጥቂት በሒደት ሊቀደስ ይችላል ይገባዋልም የሚል የክርስትና ትምህርት ነው፡፡ ይህ ትምህርት ምዕመናኖች የሐጢያቶችን ስርየት ስጦታ እንዳይቀበሉና ከእግዚአብሄር ጋር እንዲጣሉ መርቶዋቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ቀስ በቀስ ይጸድቃል ብሎ አይናገርም፡፡ የሐጢያቶችን ይቅርታ ለማግኘት በመጸለይ፣ ጥሩ ነገርን በማድረግ ወይም የራሳቸውን ቆሻሻ በማንጻት ቀስ በቀስ ለመቀደስ የሚሞክሩ ሰዎች የሚሰሩ ሰዎች ናቸው፡፡ የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው ሲዖል ሊወርዱ የሚገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሊጸድቁ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄርን ጸጋ ንቀዋልና፡፡
 
ማናችንም ጻድቃን አይደለንም፡፡ ነገር ግን በዚህች ቅጽበት እጅግ ብዙ ሰዎች በተሳሳተ አቅጣጫ እየነጎዱና እያመኑ ነው፡፡ ኢየሱስ ያለፉ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ እንዳነጻላቸው በማወቅ በየቀኑ ለሚሰሩዋቸው ሐጢቶች ንስሐ በሚገቡበት ጊዜ ይቅር እንደሚባሉ ያምናሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ጥቂትም ቢሆን ጻድቅ እንደሆኑ ስለሚያስቡ ነው፡፡ በኢየሱስ ፊት በጎነታቸውንና ንጽህናቸውን ያሳያሉ፡፡ በመጨረሻም የእግዚአብሄር ስጦታ የሆነው የሐጢያቶች ስርየት ያመልጣቸዋል፡፡
 
 
የተባረከው ማነው?
 
ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የዳኑ ቅዱሳኖች በኢየሱስ በማመን ይጸድቃሉ፡፡ መጽደቅ የሚችለው ሰው ምን አይነት ሰው ነው የሚለው ጥያቄ መልሱ የሚከተለው ነው፡፡ ድካሞቹን በሚገባ የሚያውቅና ለሐጢያቶቹም የንስሐ ጸሎቶችን የማያቀርብ ሰው ከሌሎቹ ከብዙዎቹ መካከል በእምነት ለመጽደቅ የተቃረበ ነው፡፡ ጥሩ ምግባሮች በማድረግ፣ ጸሎቶችን በማቅረብ፣ በጎነትን በመፈጸም ያልተካኑና በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብቻ ከኢየሱስ የሐጢያቶች ስርየት ስጦታ ይቀበላሉ፤ ይጸድቃሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ጥሩ ነገሮች አላደረጉም፡፡
እነርሱ ያደረጉት ብቸኛው ነገር ‹‹ሐጢያት ሰርቻለሁ፡፡ እኔ ስሞት ወደ ሲዖል ከመውረድ በቀር ሌላ ምርጫ የሌለኝ ሐጢያተኛ ነኝ›› በማለት ሐጢያቶቻቸውን በቅንነት ማመን ነው፡፡ ያን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የፈጸመውን የተሟላ የደህንነት ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ጌታ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ለመውሰድ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ የመጠመቁንና የመሰቀሉን እውነታ ማመን ሐጢያተኞች በልባቸው ከሐጢያቶች ሁሉ እንዲድኑ ያስችላቸዋል፡፡ እነርሱ የእግዚአብሄር ልጆች በመሆን በረከት ተሸፍነዋል፡፡ ሐጢያተኞች በእርሱ ፊት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የዳኑበት መዳን የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ከጥፋት ስላዳነኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግናለሁ፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ በቁጥር 6 ላይ ‹‹ከሕግ ውጪ›› በእግዚአብሄር የተባረከን ሰው ያብራራል፡፡ ‹‹መስራትን›› በሚመለከት ቀጣዮቹን ሶስት ክፍሎች ያብራራል፡፡ በመጀመሪያ ‹‹የሚሰራ›› ከዚያም ‹‹የማይሰራ›› በመጨረሻም ‹‹ያለ ሥራዎች፡፡›› መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንደዚህ ዳዊት ደግሞ እግዚአብሄር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቆጥረለት ስለ ሰው ብጽዕና ይናገራል፡፡ እንዲህ ሲል፡- አመጻቸው የተሰረየላቸው ሐጢአታቸውም የከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡ ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› (ሮሜ 4፡6-8) ‹‹በጌታ መቆጠር›› ማለት ሰው ሐጢያት ቢኖርበትም እግዚአብሄር ሐጢያት አልባ አድርጎ ይቆጥረዋል ማለት ሳይሆን ግለሰቡ በእርግጥም ሐጢያት የለበትም ማለት ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ስለ ሰው ዘር ብጽዕና ይናገራል፡፡ ለሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ያገኙ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፡፡ አይደሉምን? ከእኛ የበለጠ ደስተኛ የሆነ ሰው የለም፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት ካገኘ ሰው የበለጠ ደስተኛ ሰው የለም፡፡ ይህ ማለት ቅንጣት ታሀል ሐጢያት ያለበት ሰው እንኳን በእግዚአብሄር ይፈረድበታል፤ በጭራሽ ደስተኛም አይሆንም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ጻድቃን ደስተኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የሐጢያቶችን ስርየት አግኝተዋልና፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ይል፡- ‹‹ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› (ሮሜ 4፡8)
 
‹‹ሐጢያቶቹ የተከደኑለት›› ማለት ጌታ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ደምስሶዋል ማለት ነው፡፡ ዳዊትም እንደዚሁ ‹‹አመጻቸው የተሰረየላቸው ብጹዓን ናቸው›› ብሎዋል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ በየቀኑ ሐጢያቶችን ቢሰሩም ሐጢያቶቻቸው ይቅር የተባለላቸው ሰዎች ብጹዓን ናቸው፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበሉ ጻድቃን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ከዕድሜ ልክ ሐጢያቶች ድነዋል፡፡ ጻድቃን በእርግጥም ደስተኞች ናቸው፡፡
 
 
ሐጢያቶቻቸው የተከደኑላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡
 
ሁለተኛ ደስተኛ ሰው ምን አይነት ሰው ነው? እኛ ሁልጊዜ ሐጢያት እንሰራለን፡፡ ነገር ግን የሐጢያት መከደን ኢየሱስ በጥምቀቱና በስቅለቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶዋል ማለት ነው፡፡ እንግዲያስ እግዚአብሄር አብ ይፈርድብናልን? የሐጢያተኞች ሐጢያቶች በሙሉ ተከድነዋልን? እርሱ በእኛ ውስጥ ስለሆነ፣ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደ፣ በመስቀል ላይ ደሙን ስላፈሰሰና ለእኛ ስለሞተ አይደረድብንም፡፡
 
ሐጢያቶቻቸው የተከደኑላቸው ሰዎች ብጹዓን ናቸው፡፡ የሐጢያት ደመወዝ የሆነው ሞት አይመለከተንም፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ በጥምቀት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወስዶዋልና፡ ሐሌሉያ! እኛ ደስተኞች ነን፡፡ ሐጢያት አለብን? የለብንም፡፡ በውሃና በደም የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን የማያውቁም ሆነ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ እንደተላለፉ የማያውቁ ሰዎች በኢየሱስ በትጋት ቢያምኑም ሁልጊዜም ሐጢያት አለባቸው፡፡
 
ነገር ግን ስለ ደህንነት እውነት የሚያውቁና በዚያም የሚያምኑ ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ሐጢያቶቻቸው የተከደኑላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እርሱ ያስተላለፉ ሰዎች ብጹዓን ናቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ በተጨባጭ ደስተኛ ማነው? ድካሞች ቢኖሩባቸውም አዳኝ ያላቸው ሰዎች የተባረኩ ናቸው፡፡ እጅግ ቅንጣትዋን ሐጢያት እንኳን ሳይቀር ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ በወሰደውና በእነርሱ ምትክም ተፈርዶበት በተሰቀለው አዳኝ በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች የተባረኩ ናቸው፡፡
 
 
ጌታ ሐጢያቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡
 
በደህንነት እውነት የሚያምኑና በውስጣቸውም መልካም እረኛ ያላቸው ሰዎች ብጹዓን ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ዳዊት እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› (ሮሜ 4፡8)
 
ደካሞች ብንሆንም የሐጢያቶችን ስርየት ያገኘን ሰዎች ጻድቅ ነን፡፡ በእምነት ብንጸድቅም ሥጋችን አሁንም ድረስ ደካማ ነው፡፡ ጌታችን በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወስዶዋልን? ጌታ የምንኮነን ሰዎች አድርጎ ይመለከተናልን? አይመለከተንም፡፡ እኛ ብቃት የሌለንና ደካሞች ብንሆንም እግዚአብሄር እንኮነን ዘንድ አይፈቅድም፡፡ ጌታ ሐጢያትን የማይቆጥርብን ለምንድነው? አስቀድሞ የሐጢያትን ዋጋ ስለከፈለና ለእኛ ሲል ስለተኮነነ ነው፡፡ ጌታ በእምነት የጸደቀውን ሰው ሐጢያቶች አያስታውስም፡፡ በግለሰቡ ላይም አይፈርድም፡፡
 
በእምነት የጸደቀ ሰው ብጹዕ ነው፡፡ ከውሃና ከመንፈስ የተወለደ ሰው ብጹዕ ነው፡፡ (ዮሐንስ 3፡5) እኛ እግዚአብሄር እንዳዳነንና እንደባረከን በመርሳት ብዙውን ጊዜ ዓለማዊ ነገሮችን እንሻለን፡፡ የእርሱን ጸጋ በምናጣበት ጊዜ የእግዚአብሄር ጠላት እንሆናለን፡፡ የእግዚአብሄርን ጸጋ በልቦናችን ውስጥ መያዝ አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ደህንነት በምዕመናን ውስጥ ይኖራል፡፡
 
የእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ ሐጢያቶቻቸው በተደመሰሱላቸው ሰዎች ውስጥ ያድራል፡፡ በእግዚአብሄር የማይፈረድባቸው ጻድቃን ናቸው፡፡ በዚህ ዓለምና በመንግሥተ ሰማይ እግዚአብሄር የማይፍድባቸው ሰዎች ብጹዓን ናቸው፡፡ ለምን? በእግዚአብሄር ጸድቀዋል፡፡ የእርሱን ፍቅር ተቀብለዋል፡፡ የእርሱም ልጆች ሆነዋናል፡፡
 
 
በእምነት ተባርከናል፡፡
 
በእምነት የጸደቁ ሰዎች ብፁዓን ናቸው፡፡ ዳግም የተወለዱ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ጸድቀዋልን? -- አዎ -- ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጥም ጸልዩ፡፡ በሁሉ አመስግኑ፡፡›› (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡16-18) ምክንያቱም እርሱ የእምነት አባት የአብርሃም ዘር በመሆኑ በእምነት ተባርኮዋልና፡፡ እኛም እንደዚሁ የአብርሃም ዘሮች ነን፡፡ አብርሃምም የዳነው ልክ እንደ እኛ በእግዚአብሄር ቃል በማመኑ ነው፡፡ እግዚአብሄር አብርሃምን እንዲህ አለው፡- ‹‹አብራም ሆይ አትፍራ፡፡ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፡፡ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው፡፡›› (ዘፍጥረት 15፡1)
 
አብርሃም ግን እንዲህ አለ፡- ‹‹እግዚአብሄር አምላክ ልጅ እንደሌለኝ ታያለህ፡፡ ምን ትሰጠኛለህ? የቤቴም መጋቢ ይህ የደማስቆ ልጅ ኤሊዔዘር ነው፡፡›› ከዚያም እንዲህ አለ፡- ‹‹ተመልከት፤ ልጅ አልሰጠኸኝም፡፡ በቤቴ የሚወለደው እርሱ እንደሚወርሰኝ የታወቀ ነው!›› ከዚያም እግዚአብሄር ወደ ውጭ አወጣውና እንዲህ አለው፡- ‹‹ሰማይን ቀና ብለህ ተመልከት፡፡ ልትቆጥራቸው የምትችል ከሆነ ከዋክብቶችን ቁጠር፡፡ ዘርህም እንዲሁ ይሆናል›› አለው፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ አምናለሁ፡፡›› በዚህም አብርሃም በእግዚአብሄር ቃሎች አመነ፡፡
 
አብርሃም እንዳደረገው በዚህ ዓለም ላይ በእግዚአብሄር ቃል ማመን ትችላላችሁን? ሰዎች ይህንን ማድረግ የሚያዳግታቸው አይመስልምን? የአብርሃም ሚስት በጣም ከማርጀቷ የተነሳ ልጅ መውለድ አትችልም ነበር፡፡ ነገር ግን አብርሃም ጥቂት ተስፋ ባለበት ወቅት በእግዚአብሄር ቃል አመነ፡፡ ስለዚህ አብርሃም በእግዚአብሄር ፊት ለጽድቅ ተቆጠረለት፡፡
 
ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ደምስሶዋል፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ በደሙ ስለ እኛ ተኮነነ፡፡ የሐጢያቶችን ስርየትና የእግዚአብሄርን ደህንነት በመቀበል የአብርሃም ዘሮች ሆነናል፡፡ ሌሎች ባላመኑ ጊዜ እኛ በጣም ሐጢያተኞች ነበርንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የእግዚአብሄር ሞኝነት ከሰዎች ይጠበባልና፤ የእግዚአብሄርም ድካም ከሰዎች ይበረታልና፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡25) እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀት (ውሃ) እና በመስቀሉ (ደም) ባላቸው እምነት በእግዚአብሄር ወንጌል የሚያምኑትን ልጆቹ አድርጎዋቸዋል፡፡ ይህ ለሰው ዘር ሞኝነት ይመስል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ደህንነትና የሐጢያቶች ስርየት ጥበብ እንደዚህ ናቸው፡፡ ይህ ከሰዎች እይታ አንጻርም ቢሆን ሞኝነት ይመስል ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር ግን ሐጢያተኞችን ሁሉ ነጻ በሆነው ስጦታው አድኖዋቸዋል፡፡
 
ኢየሱስ በአራቱም የምድር ማዕዘናት ከሚገኙ አስር ሺህ ሰዎች አንዳቸውን ጠርቶ ባረካቸው፤ አዳናቸው፡፡ በእነርሱ በኩልም ምስጋናን ተቀበለ፡፡ እኛ ተባርከናል ወይስ አልተባረክንም? --አዎ ተባርከናል፡፡ -- ይህ የሆነው እናንተ በሰራችኋቸው ሥራዎች እንዳልሆነ አስታውቁ፡፡ እግዚአብሄር በሰጠን በረከቶችና በቃሎቹ በኩል በሰጠን እምነት በማመናችን ተባርከናል፡፡ እግዚአብሄር በውሃ፣ በደምና በመንፈስ በመምጣት ልጆቹ አድርጎናል፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 5፡4-8) ፍቅሩንም ሰጥቶናል፡፡
 
በምድር ላይ በብዙ ድካሞች ውስጥ ብንኖርም ተባርከናል፡፡ እኔ ጌታን ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ እርሱ እኛ ሐጢያተኞች ለቅድስናችን መስራት በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ እንኳን እነዚያን የከበሩ በረከቶች ሰጥቶናል፡፡ ሐጢያትን አልቆጠረብንም፡፡ ዓመጻችንን ሁሉ ይቅር ብሎዋል፡፡ በደህንነት የተባረክነው እምነት አማካይነት ብቻ ነው፡፡