Search

คำสอน

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[1-1] የእግዚአብሄርን መገለጥ ቃል ስሙ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 1፡1-20 ››

የእግዚአብሄርን መገለጥ ቃል ስሙ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 1፡1-20 ››
‹‹ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባርያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአበሄር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፡፡ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባርያው ለዮሐንስ አመለከተ፡፡ እርሱም ለእግዚአብሄር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ፡፡ ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡም የተጻፈውን የሚጠብቁት ብጹዓን ናቸው፡፡ ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ካለውና ከነበረው፣ ከሚመጣውም፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣ ከታመነውም ምስክር፣ ከሙታንም በኩር፣ የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ ለወደደን፣ ከሐጢአታችንም በደሙ ላጠበን፣ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት ላደረገን ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ሐይል ይሁን አሜን፡፡ እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፡፡ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፡፡ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡ አዎን፤ አሜን፡፡ ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል፡፡ እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግስት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሄር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ፡፡ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡ በኋላዬም የመለከትን ድምጽ የሚመስል ታላቅ ድምጽ ሰማሁ፡፡ እንዲሁም የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰርምኔስ፣ ወደ ጴርጋሞንም፣ ወደ ትያጥሮንም፣ ወደ ሰርዴስም፣ ወደ ፊላደልፊያም፣ ወደ ሎዶቅያም፣ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ፡፡ የሚናገረኝንም ድምጽ ለማየት ዘወር አልሁ፡፡ ዘወርም ብዬም ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፡፡ በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፡፡ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው፤ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር፡፡ ራሱና የራሱም ጠጉር እንደ በረዶ ነጭ ነበሩ፡፡ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፡፡ እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበረ፡፡ ድምጹም እንደ ብዙዎች ውሃዎች ድምጽ ነበር፡፡ በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፡፡ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፡፡ ፊቱም በሐይል እንደሚያበራ እንደ ጸሐይ ነበር፡፡ ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ስር ወደቅሁ፡፡ ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፤ እንዲህም አለኝ፡- አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፡፡ ሞቼም ነበርሁ፡፡ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፡፡ የሞትና የሲዖልም መክፈቻ አለኝ፡፡ እንግዲህ ያየኸውን፣ አሁንም ያለውን፣ ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ፡፡ በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምስጢር ይህ ነው፡፡ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላዕክት ናቸው፡፡ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡›› 
 
 

ትንተና፡፡

 
ቁጥር 1፡- ‹‹ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባርያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአበሄር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፡፡ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባርያው ለዮሐንስ አመለከተ፡፡››
የራዕይ መጽሐፍ የተጻፈው እያሽቆለቆለ በነበረው የሮማውያን ንጉሠ ነገሥት የዶሚታን የአገዛዝ ዓመታቶች (በ95 ዓ.ም አካባቢ) በስደት በተላከበት የኤጅያን ባህር ደሴት በፍጥሞ ቆይታው ወቅት ለእርሱ የተሰጠውን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በመዘገበው በሐዋርያው ዮሐንስ ነበር፡፡ ዮሐንስ ወደ ፍጥሞ የተሰደደው ለእግዚአብሄር ቃልና ለኢየሱስ ምስክር ስለመሰከረ ነበር፡፡ ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስና በመላዕክቶቹ ምሪት አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን የእግዚአብሄርን ግዛት የተመለከተው በዚህ ደሴት ላይ ነው፡፡
ይህ ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ›› ምንድነው  የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ማለት እግዚአብሄር በወኪሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በዚህ ዓለምና ወደፊት በሚመጣው የእግዚአብሄር መንግሥት ላይ የሚሆነውን ይገልጥልናል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ በመሰረታዊነት ማነው? እርሱ ፈጣሪ አምላክና የሰውን ዘር ከዓለም ሐጢያቶች ያዳነ አዳኝ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው አዲስ መንግስት አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ ስለሚመጣው አዲስ ዓለም ሁሉን የሚያሳየን ገላጭና የእግዚአብሄር አብ ወኪል ነው፡፡ ዮሐንስ በመዘገበው የመገለጥ ቃል አማካይነት ኢየሱስ አሮጌውን ዓለም እንዴት እንደሚያጠፋውና አዲሱን ዓለም እንዴት እንደሚጀምረው ማየት እንችላለን፡፡
 
ቁጥር 2፡- ‹‹እርሱም ለእግዚአብሄር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ፡፡››
ዮሐንስ በተለይ ስለ እውነት ቃል የመሰከረው ኢየሱስ የእግዚአብሄር ወኪል ሆኖ ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ስላየ ነው፡፡ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚፈጸመውን አየ፤ ሰማም፡፡ ስለዚህ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ መመስከር ቻለ፡፡
 
ቁጥር 3፡- ‹‹ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡም የተጻፈውን የሚጠብቁት ብጹዓን ናቸው፡፡››
እዚህ ላይ በዮሐንስ የተመሰከረውን የእግዚአብሄር ቃል የሚያነቡና የሚሰሙ ብጹዓን ናቸው ተብሎዋል፡፡ ብጹዓን እነማናቸው? በመጀመሪያና በቀዳሚነት በእግዚአብሄር ቃል ላይ ባላቸው እምነታቸው አማካይነት ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ድነው የእግዚአብሄር ሕዝብ የሆኑ ምዕመናን ናቸው፡፡ ሊባረኩ የሚችሉት ቅዱሳን ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በዮሐንስ የተመሰከረውን -- በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ -- የእግዚአብሄር ቃል ምስክር የሚያነቡ፣ የሚሰሙና የሚጠብቁ እነርሱ ናቸውና፡፡ በዚህ መንገድ የእግዚአብሄር ቅዱሳን የሆኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል በመስማትና በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት በመጠበቅ የሰማይን በረከቶች ይቀበላሉ፡፡
እግዚአብሄር በዮሐንስ አማካይነት በዚህ ምድርና በሰማይ የሚመጣውን ሁሉ የእውነት ምስጢር አስቀድሞ ባይግረን ኖሮ ቅዱሳን ይህንን እንዴት ሊሰሙትና ሊያዩት ይችሉ ነበር? ዓለም እያለፈባቸው ያሉትን ለውጦች ሁሉ አስቀድሞ የማወቅና የማመን በረከትስ እንዴት ይኖራቸው ነበር? እግዚአብሄር በዮሐንስ አማካይነት ይህችን ምድርና ሰማይን ስለሚጠብቀው ነገር ሁሉን ስላሳየን ምስጋናንና ክብርን እሰጠዋለሁ፡፡ በዘመናችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሄር የመገለጥ ቃል በራሳቸው ዓይኖች ማየትና ማንበብ የሚችሉ ሰዎች በእርግጥም ብጹዓን ናቸው፡፡
 
ቁጥር 4፡- ‹‹ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ካለውና ከነበረው፣ ከሚመጣውም፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣››
ዮሐንስ እዚህ ላይ ደብዳቤውን ለሰባቱ የእስያ ቤተክርስቲያኖች እንደሚልክ ይናገራል፡፡ ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት በግዞት በነበረበት ወቅት እግዚአብሄር የሰጠውን ትንቢቶችና መገለጦች ከመዘገበ በኋላ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት እንደዚሁም በመላው ዓለም ለሚገኙ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ላከ፡፡
 
ቁጥር 5፡- ከታመነውም ምስክር፣ ከሙታንም በኩር፣ የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ ለወደደን፣ ከሐጢአታችንም በደሙ ላጠበን፣››
ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የታመነው ምስክር›› ብሎ የጠራው ለምንድነው? ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ በሐጢያት የታሰሩትንና ለጥፋት የታጩትን ሰዎች ሁሉ ለማዳን በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ ወስዶ በሕይወቱ የሐጢያትን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ በሦስት ቀናቶች ውስጥም ከሙታን ተነሳ፡፡ ይህንን ሁሉ ያደረገው ምዕመናኖችን ለማዳንና ሐጢያቶቻቸውን ለማንጻት ነው፡፡ የዓለምን ሐጢያተኞች በሙሉ ከሐጢያቶቻቸው ያዳነው ኢየሱስ ራሱ እንጂ ሌላ ስላልሆነ ለዚህ ደህንነት ሕያው የሆነው ምስክር ክርስቶስ ነው፡፡
ዮሐንስ ‹‹ከሙታን በኩር›› በማለት ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም በመምጣትና የሕጉን መጠይቆች በሙሉ በመፈጸም በኩር እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር በጥምቀቱ ሐጢያቶችን በሙሉ በመውሰድ፣ በመስቀል ላይ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት የሐጢያትን ደመወዝ ከፈለ፡፡ ክርስቶስ ‹‹ስለወደደንና በደሙ ስላጠበን›› እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ነጻ አውጥቶዋቸዋል፡፡
 
ቁጥር 6፡- ‹‹መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት ላደረገን ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ሐይል ይሁን አሜን፡፡››
ኢየሱስ የእግዚአብሄር አብ ወኪል ሆኖ በሥጋና በደም ወደዚህ ዓለም በመምጣት ሐጢያተኞችን በጥምቀቱና በመስቀሉ ደሙ አዳናቸው፡፡ ክርስቶስ በእነዚህ የጸጋ ምግባሮች አንጽቶን የእግዚአብሄር ሕዝብና ካህናት አደረገን፡፡ እነዚህን አስገራሚ የጸጋ በረከቶቹን ለሰጠን አብና የእርሱ ወኪልና አዳኝ ለሆነው ወልድ ክብር፣ ምስጋናና ውዳሴ ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁንላቸው! ክርስቶስ ሥጋ የለበሰበት ዓላማ ለአባቱ የእግዚአብሄር መንግሥት ሕዝብና ካህናት እንድንሆን ለማድረግ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም ለምንኖርበት ለመንግሥተ ሰማይ ‹‹ነገሥታቶች›› ተደርገናል፡፡
 
ቁጥር 7፡- ‹‹እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፡፡ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፡፡ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡ አዎን፤ አሜን፡፡››
እዚህ ላይ ክርስቶስ ከደመናት ጋር እንደሚመጣ ተነግሮዋል፡፡ እኔም ይህንን በሚገባ አምነዋለሁ፡፡ ይህ የሳይንስ ልብ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም ከሰማይ ወደ ምድር እንደሚመለስ የተነገረ ትንቢት ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የወጉትም›› ያዩታል ይላል፡፡ እነዚህ እነማን ናቸው? እነዚህ ይህ ቃል ሁሉንም ሊያድናቸው ሐይል ያለው ሆኖ ሳለ የውሃውንና የመንፈሱን ቃል ከብዙዎቹ የዓለም ሃይማኖታዊ ትምህርቶች እንደ አንዱ ብቻ አድርገው የተመለከቱ ሰዎች ናቸው፡፡
ክርስቶስ ሲመጣ በአለማመናቸው የወጉት ሰዎች በእርግጥም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፡፡ ምክንያቱም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በእርግጥም ከሐጢያቶቻቸው የሚያድናቸው የቤዛነትና የደህንነት ወንጌል መሆኑንና ኢየሱስም የዓለምን ሐጢያቶች ለመውሰድ በዮሐንስ መጠመቁን በሚረዱበት ጊዜ በጣም ይረፍድባቸዋልና፡፡
 
ቁጥር 8፡- ‹‹ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል፡፡››
ዮሐንስ ‹‹አልፋና ዖሜጋ›› ሲል ጌታችን የመላው ዩኒቨርስና የሰው ዘር ታሪክ የመነጨበት ጅማሬና ፍጻሜ ያለው የፍርድ አምላክ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ጌታ ጻድቃንን ሊሸልም ሐጢያተኞችን ደግሞ ሊፈርድ ይመጣል፡፡ እርሱ የሕዝቡን ሐጢያቶች የሚፈርድና በጽድቁ የሚያምኑትንም ሰዎች ጽድቅ የሚሸልም ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡
 
ቁጥር 9-10፡- ‹‹እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግስት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሄር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ፡፡ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡ በኋላዬም የመለከትን ድምጽ የሚመስል ታላቅ ድምጽ ሰማሁ፡፡››
‹‹ወንድም›› የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የሚውለው አብረው ያሉ ምዕመናኖች እርስ በርሳቸው ሲጠራሩበት ነው፡፡ ዳግም በተወለደች የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ቤተሰብ የሆኑ ሰዎች እርስ በራሳቸውን ወንድሞችና እህቶች ብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ ስያሜዎች የተሰጡን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመናችን ነው፡፡
እዚህ ላይ ‹‹የጌታ ቀን›› የሚያመላክተው ኢየሱስ ከሙታን የተነሳበትን ከሰንበት በኋላ ያለውን ቃል ነው፡፡ ኢየሱስ የተነሳው በዚህ የሳምንቱ ቀን ነው፡፡ እሁድን ‹‹የጌታ ቀን›› ብለን የምንጠራው ለዚህ ነው፡፡ ይህ ቀን የሕጉን ዘመን ቀን ፍጻሜና አዲሱን የደህንነት ዘመን ጅማሬ ያመላክታል፡፡ እንደዚሁም ጌታችን በትንሳኤው መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነች ነግሮናል፡፡
 
ቁጥር 11፡- ‹‹እንዲሁም የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰርምኔስ፣ ወደ ጴርጋሞንም፣ ወደ ትያጥሮንም፣ ወደ ሰርዴስም፣ ወደ ፊላደልፊያም፣ ወደ ሎዶቅያም፣ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ፡፡››
ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ አማካይነት ያየውን ጽፎ በእስያ ወዳሉት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት በደብዳቤዎች ላከ፡፡ ይህም እግዚአብሄር በፊቱ በተመላለሱት ባሮቹ በኩል ለመላው ቤተክርስቲያን እንደሚናገር ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 12፡- ‹‹የሚናገረኝንም ድምጽ ለማየት ዘወር አልሁ፡፡ ዘወርም ብዬም ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፡፡››
የእግዚአብሄር ቅዱስ መጽሐፍ በሐዋርያቶች ዘመን ስላልተጠናቀቀ ለደቀ መዛሙርት ምልክቶችንና ራዕዮችን ማሳየት አስፈላጊ ነበር፡፡ ዮሐንስ የእግዚአብሄርን ድምጽ ለመስማት ዘወር ሲል ‹‹ሰባት የወርቅ መቅረዞችን›› አየ፡፡ እዚህ ላይ መቅረዞቹ የሚያመለክቱት የእግዚአብሄርን አብያተ ክርስቲያኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል መገለጥ የሚያምኑ ቅዱሳኖችን ጉባኤዎች ነው፡፡ እግዚአብሄር በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ጌታ ነበር፡፡ እርሱ ለቅዱሳኖች ሁሉ እንክብካቤን የሚያደርግ እረኛ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡
 
ቁጥር 13፡- ‹‹በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፡፡ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው፤ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር፡፡››
ዮሐንስ ያየው ‹‹በሰባቱ መቅረዞች መካከል የሰው ልጅ የሚመስለው›› ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክት ነው፡፡ ኢየሱስ የቅዱሳን እረኛ እንደ መሆኑ በጥምቀቱና በስቅለቱ የእውነት ቃል የሚያምኑትን ሁሉ ይጎበኛል፤ ያናግራልም፡፡ ዮሐንስ ክርስቶስን ሲገልጠው ‹‹እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀው›› ማለቱ ጌታችን የእግዚአብሄር አብ ወኪል በመሆን ያለውን ማዕረግ ያመለክታል፡፡
 
ቁጥር 14፡- ‹‹ራሱና የራሱም ጠጉር እንደ በረዶ ነጭ ነበሩ፡፡ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፡፡››
ጌታችን ፍጹም፣ ቅዱስ፣ ባለ ግርማና የከበረ ነው፡፡ ‹‹ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ›› ማለት እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደ መሆኑ የሁሉም ቅን ፈራጅ ነው ማለት ነው፡፡
 
ቁጥር 15፡- ‹‹እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበረ፡፡ ድምጹም እንደ ብዙዎች ውሃዎች ድምጽ ነበር፡፡››
ኢየሱስ ማን እንደሆነ ይመስለናል? ቅዱሳን እርሱ ሙሉ በሙሉና ፍጹም አምላክ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ጌታችን ሁሉን ቻይ ነው፡፡ ድክመት የለበትም፡፡ ነገር ግን በዚህ ምድር ላይ ሲኖር የድካሞቻችን ተካፋይ በመሆኑ ስለ ገጠመኞቻችንና ሁኔታዎቻችን ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ ስላለው በተሻለ ሊያግዘን ይችላል፡፡ ድምጹ እንደ ብዙዎች መሆኑ ጌታችን ምን ያህል ቅዱስና ሁሉን ቻይ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በጌታችን ውስጥ አንድም የእንከን ወይም የድክመት ምልክት የለም፡፡ እርሱ በቅድስናው፣ በፍቅሩ፣ በግርማውና በክብሩ ብቻ የተሞላ ነው፡፡
 
ቁጥር 16፡- ‹‹በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፡፡ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፡፡ ፊቱም በሐይል እንደሚያበራ እንደ ጸሐይ ነበር፡፡››
‹‹በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት›› ማለት ጌታ የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ይጠብቃል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ከአፉ የሚወጣው ‹‹በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ›› ኢየሱስ በእግዚአብሄር የሥልጣንና የሐይል ቃል የሚሰራ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጌታችን ‹‹በሐይል እንደሚያበራ ጸሐይ›› ቃለ አምላክና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡
 
ቁጥር 17፡- ‹‹ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ስር ወደቅሁ፡፡ ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፤ እንዲህም አለኝ፡- አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ነኝ፡፡››
ይህ ቁጥር እኛ በእግዚአብሄር ፊት ምን ያህል ደካሞችና ጨለማዎች እንደሆንን ያሳየናል፡፡ ጌታችን ሁልጊዜም ሁሉን ቻይና ፍጹም ነው፡፡ ራሱንም ለእግዚአብሄር ባሮች አንዳንድ ጊዜ እንደ ጓደኛ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኮስተር ያለ የፍርድ አምላክ ሆኖ ይገልጣል፡፡
 
ቁጥር 18፡- ‹‹ሕያውም እኔ ነኝ፡፡ ሞቼም ነበርሁ፡፡ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፡፡ የሞትና የሲዖልም መክፈቻ አለኝ፡፡››
ጌታችን ለዘላለም ሕያው ነው፡፡ የእግዚአብሄር አብ ወኪል በመሆኑም የሰማይ ሥልጣን አለው፡፡ የሰው ዘር አዳኝና ፈራጅ እንደመሆኑ በዘላለም ሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ ነው፡፡
 
ቁጥር 19፡- ‹‹እንግዲህ ያየኸውን፣ አሁንም ያለውን፣ ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ፡፡››
የእግዚአብሄር ባሮች የአሁኑንና የወደፊቱን የእግዚአብሄር ዓላማና ሥራዎች የመመዝገብ ሐላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ጌታ ለዮሐንስ የገለጠለትን የዘላለም ሕይወት የምታገኘውን የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን እምነትና ወደፊት የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ በእምነት እንዲያሰራጭ ነገረው፡፡ እግዚአብሄር በዮሐንስ አማካይነት እኛም እንድናደርገው ያዘዘን ይህንኑ ነው፡፡
 
ቁጥር 20፡- ‹‹በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምስጢር ይህ ነው፡፡ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላዕክት ናቸው፡፡ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡››
‹‹የሰባቱ ከዋክብቶች ምስጢር›› ምንድነው? እግዚአብሄር በባሮቹ አማካይነት እኛን የራሱ ሕዝብ በማድረግ መንግሥቱን መገንባት ነው፡፡ ‹‹የወርቁ መቅረዞች›› የሚያመለክቱት እግዚአብሄር ለሰው ዘር በሰጠው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባመኑት ቅዱሳኖች በኩል የተገነቡትን አብያተ ክርስቲያኖች ነው፡፡
እግዚአብሄር በባሮቹና በአብያተ ክርስቲያኖቹ አማካይነት ዓላማው ምን እንደሆነና ይህች ዓለምም ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት ለምዕመናን አሳይቷል፡፡ ለዮሐንስ ባሳየውና እንዲመዘገብ ባደረገው የራዕይ ቃል አማካይነት እኛም ደግሞ የእርሱን ሥራዎች በዓይኖቻችን እናያለን፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች በሙሉ ለገለጠልን መለኮታዊው ቸርነት እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፤ አወድሰውማለሁ፡፡