Search

คำสอน

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-29] የፍርዱ የደረት ኪስ፡፡ ‹‹ዘጸዓት 28፡15-30››

የፍርዱ የደረት ኪስ፡፡
‹‹ዘጸዓት 28፡15-30›› 
‹‹ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን የደረት ኪስ ሥራው፤ እንደ ኤፉዱም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊውም፣ ከቀይ ግምጃም፣ ከጥሩ በፍታም ሥራው፡፡ ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ ትክክልና ድርብ ይሆናል፡፡ በአራት ተራ የሆነ የዕንቁ ፈርጥ አድርግበት፤ በፊተኛው ተራ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ በሁለተኛውም ተራ በሉር፣ ሰንፔር፣ አልማዝ፤ በሦስተኛውም ተራ ያክንት፣ ኬልቄዶን፣ አሜቴስጢኖስ፤ በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፣ መረግድ፣ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ይደረጋሉ፡፡ የዕንቆቹም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች አሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ይቀረጹ፤ ስለ አሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ፡፡ ለደረቱ ኪስም የተጎነጎኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው፡፡ ለደረቱ ኪስም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አድርጋቸው፡፡ የተጎነጎኑትንም ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታገባቸዋለህ፡፡ የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው ታደርጋቸዋለህ፡፡ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሥራ፤ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ፡፡ ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ በኤፉዱም ፊት ከጫንቃዎቹ በታች በብልሃት ከተጠለፈ ኤፉድ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ፡፡ የደረቱም ኪስ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉድ ቋድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል፡፡ አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሄር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም፡፡›› 


አሁን ትኩረታችንን ሊቀ ካህኑ ለእስራኤል ሕዝብ ፍርድ ወደሚቀበልበት የደረት ኪስ እንመልስ፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ የፍርዱ ደረት ኪስ ርዝመቱና ስፋቱ አንድ ስንዝር ሆኖ አራት ማዕዘን ቅርጽ ባለው ድርብ ጨርቅ እንደተሠራ ይነግረናል፡፡ ማጉ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበር፡፡ በዚህ ጨርቅ ላይ በእያንዳንዱ ተራ ሦስት ሆነው በጠቅላላው አራት ተራ ያላቸው አሥራ ሁለት የከበሩ ድንጋዮች ተደርገውበታል፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን በፍርዱ ደረት ኪስ ላይ ኡሚምንና ቱሪምን እንዲያደርግ ነግሮታል፡፡ እዚህ ላይ ኡሚምና ቱሪም ‹‹ብርሃንና ፍጽምና›› ማለት ነው፡፡

 
የሊቀ ካህኑ ፍርድ መለኪያ፡፡ 


እንደምናውቀው እያንዳንዱ ፍርድ ውሳኔ ሊሰጠው የሚችለው ጉዳዩ ተዛማጅ ከሆኑ መለኪያዎችና ከሕጎችና ከደንቦች ጋር ከተመሳከረ በኋላ ነው፡፡ ታዲያ ሊቀ ካህኑ ለሕዝቡ የሚፈርደው በምን መለኪያዎች ላይ ተመርኩዞ ነው? እርሱ ሕዝቡ ላይ መፍረድ የነበረበት በደረቱ ኪስ ላይ ባሉት ‹‹ኡሪምና ቱሚም›› ማለትም ‹‹ብርሃንና ፍጽምና›› ነው፡፡ በትክክል እንዲፈርድ የሚያስችለው መሠረታዊ እምነት የፍርዱ ደረት ኪስ በተሠራባቸው አምስት ማጎች በተገለጠው እውነት ላይ ያለው እምነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሊቀ ካህኑ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፍርድን የሚሰጠው ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ በተሠራው እውነት በሚያምነው እምነት ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር የሊቀ ካህኑ ፍርድ መለኪያ ለደረቱ ኪስ ጥቅም ላይ በዋሉት በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውና ‹‹ብርሃንና ፍጽምና›› የሆነው እውነት ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ በአምስቱ ማጎች በተገለጠው እውነት በማመን ውሳኔዎቹ በመንፈሳዊ ደረጃ ትክክል ቢሆኑ ወይም ባይሆኑ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አሳሪ የሆኑ ውሳኔዎችን መወሰን ይችላል፡፡
የደረቱ ኪስ በእያንዳንዱ የሊቀ ካህን ልብ ላይ ይውላል፡፡ በውስጡም ኡሪምና ቱሚም ይደረጋሉ፡፡ ይህም በሊቀ ካህኑ ልብ ውስጥ የብርሃንና የፍጽምና እውነት በጽናት ስለተተከለ ሁልጊዜም የእስራኤልን ሕዝብ መምራትና እምነታቸው ትክክል ይሁን ወይም አይሁን፤ በእግዚአብሄር የመሥዋዕት ስርዓት መሠረት መሥዋዕቶችን አቅርበው ይሁን ወይም አይሁን፤ የእርሱን ትዕዛዛቶች ተከትለው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ መፍረድ እንደሚችል ያመለክታል፡፡
ዛሬ እኛ የእግዚአብሄር ንጉሣዊ ካህናት የሆንን ያንኑ ተመሳሳይ መለኪያ መያዝና በዚህ ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች መፍረድ አለብን፡፡ ሰዎች ለደረቱ ኪስ ጥቅም ላይ በዋሉት አምስቱ ማጎች በተገለጠው እውነት የሚያምኑ ከሆኑ በእግዚአብሄር ፊት የዓለም ብርሃን ሊሆኑ እንደሚችሉ የማያምኑ ከሆኑ ደግሞ እንደሚኮነኑ ተመሳሳይ ወደሆነ ድምዳሜ ላይ መድረስ አለብን፡፡
አንዳንዶች ወደ ተራራ ጫፍ ለመድረስ ብዙ መንገዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመከራከር በዚህ ቃል ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ ተራራ ወጭዎች ‹‹ባለፈው ጊዜ በጣም ቀላሉን መንገድ መርጠሃል፡፡ እኔ ግን ይህንን ተራራ ለማሸነፍ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ሸንተረር የምሥራቁን መንገድ እይዛለሁ›› ይሉ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው፤ ተራራ ወጭዎችን በሚመለከት እንዲህ ያለ አማራጭ መንገድ በጣም አለ፡፡ ነገር ግን ወደ እኛ መንፈሳዊ ክልል ስንመጣ መከራከር ወይም ማመቻመች አይቻልም፡፡ ብቸኛው መለኪያ እግዚአብሄር ያስቀመጠው ነው፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ፊት የዓለም ብርሃን ለመሆን ብዙ ዘዴዎች የሉም፡፡ ነገር ግን አንድ መንገድ ብቻ አለ፡፡ ይህም መንገድ የደረቱ ኪስና ኤፉዱ በተሠሩበት ጥሬ ዕቃዎች በወርቁ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውን የሚያበራ የደህንነት እውነት ማወቅና ማመን ከዚያም የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብሎ የራሱ የእግዚአብሄር ልጆች መሆን ነው፡፡
እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ደምስሶ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ጻድቃን እንዳደረገን በማመን ካልሆነ በስተቀር የዓለም ብርሃን ለመሆን ሌላ መንገድ የለም፡፡ ሐጢያተኞች፣ ጻድቃን፣ ፍጹማን ያልሆኑ ፍጹማን መሆን የሚችሉት ሊቀ ካህነት ለሚለብሱዋቸው ልብሰ ተክህኖዎች ጥቅም ላይ በዋሉት ጥሬ ዕቃዎች እውነት በማመን ብቻ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በእግዚአብሄር ፊት ድነን እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ፍርድ በተሰጠን ጊዜ የሚፈረድብን የሚያበራ የእውነት ብርሃን በሆነው የውሃና የመንፈስ ቃለ ወንጌል ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡
ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲዖል እንሄድ እንደሆነ በእግዚአብሄር ፊት በትክክል እንዲፈረድብን የምንፈልግ ከሆነ የፍርዱን ደረት ኪስ ለመሥራት ጥቅም ላይ የዋሉትን ጥሬ ዕቃዎች የሚያውቅና የሚያምን ይህ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሌሎችን አይተን ከሙሉ ልባቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያምኑ እንደሆነ ለይተን ለማወቅ በመጀመሪያ እኛ ራሳችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ እኛ መረዳት የሚገባን ነገር ቢኖር በወርቁ፣ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠው እውነት የሐጢያቶችን ስርየት በሚመለከት ትክክለኛ ወደሆነ ፍርድ ላይ በግልጥ መድረስ የሚያስችለን መሆኑን ነው፡፡ ስለ ትክክለኛው ፍርድ የሚመሰክረው ይህ እውነት ነው፡፡ አሁን ይህንን መረዳት ቻላችሁን?
ታዲያ ዛሬ በሐጢያቶች ስርየት ላይ ትክክለኛውን ፍርድ መስጠት የሚችለው ማነው? ዘላለማዊው የሰማይ ሊቀ ካህን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በስጋው ላይ በመውሰድ፣ በመስቀል ላይ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ ለዘላለም አድኖናል፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት መሠረት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ሁሉ የንጉሥ ካህን ሊሆንና ሰዎችን በትክክል የመፍረድ መብት ሊኖረው ይችላል፡፡ አሁን እኛ ዳግመኛ የተወለድን ሰዎች ያልዳኑትን እግዚአብሄር በሰጠው መለኪያ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የመፍረድ ሐላፊነት አለብን፡፡ እኛም የበላይ ዳኛ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ይህንን ሐላፊነት በታማኝነት መፈጸም ይገባናል፡፡
በእኛ በመንፈሳዊ ካህናቶች የሚሰጠውን ውሳኔ የማይወዱ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹እናንተ አምላክ አይደላችሁም! ልክ እንደ እኔ ደካማ ሰብዓዊ ፍጡር ሆናችሁ ሳላ የሐጢያቶቼን ስርየት መቀበሌን ወይም አለመቀበሌን እንዴት ልትወስኑ ትችላላችሁ? ለሐጢያተኞች ትክክለኛውን ፍርድ መስጠት የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው! ማን ነን ብላችሁ ታስባላችሁ? እንደዳንኩ ወይም እንዳልዳንኩ እንዴት ለመወሰን ደፈራችሁ? ይህንን የሚያውቀው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ አምላክ ናችሁ? እናንተ ከሌላው ሰው ሁሉ ይልቅ የተሻልን ነን ብላችሁ ታስባላችሁን?››
ነገር ግን የመንፈሳዊ ካህናቶች ውሳኔዎች ስህተት የሌለባቸው ከጌታ ዘንድ እንዲህ ያለ መብት ስለተሰጣቸው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ካህናት ትክክለኛውና ስህተቱ ምን እንደሆነ በሚወስኑበት ጊዜ በዚህ ውሳኔ ማመን ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛ ውሳኔ ነውና፡፡ የበሽተኞቻቸውን ሕመም ማከም የሚችሉት ሐኪሞች እንደሆኑ ሁሉ ነፍሳቶችን መርምረው ገናም ሐጢያተኞች እንደሆኑ ወይም ጻድቃን እንደሆኑ መወሰን የሚችሉት መንፈሳዊ ካህናት ናቸው፡፡ 
እኛ መንፈሳዊ ካህናት መሆን የምንችለው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በሚያምነው እምነት ነው፡፡ እነዚህ መንፈሳዊ ካህናት ሐጢያቶቻቸው ሁሉ ተወግደውላቸው በእውነት ወንጌል በማመን መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ካህናት የሆኑ ሐጢያተኞችን ከጻድቃን ለይተው ማወቅ ይችላሉ፡፡ እኛ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠውን ወንጌል በመስማታችንና በማመናችን አሁን ሐጢያተኞችን መፈወስና ወደ ክርስቶስ መምራት ችለናል፡፡ 


ሰዎች ክህነታቸውን ሲቃወሙ በድፍረት መቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡ 

ሐጢያተኞች በራሳቸው አስተሳሰቦች ጻድቃን የሰጡትን የትክክለኛ ፍርድ ሥልጣን ሊቀንሱ ይሞከራሉ፡፡ ነገር ግን የከፋው ነገር አስቀድመን ዳግመኛ የተወለድን ብንሆንም ስለ ክህነታችን የማናምን መሆናችን ነው፡፡ እኛ ዳግመኛ የተወለድን ሌሎችን ስንፈርድ ‹‹እንዲያው በአጋጣሚ ዕብሪተኛ ሆኜ ይሆን? እዚህ ላይ ስህተት ሰርቼ ይሆን?›› ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ስህተት የለም፡፡ ምክንያቱም ይህንን መንፈሳዊ ፍርድ በትክክል መስጠት የሚችሉት በመንፈሳዊ መልኩ የእግዚአብሄር ካህናት የሆኑት ብቻ ናቸውና፡፡ ስለዚህ እኛ ዳግመኛ የተወለድን ሐጢያተኞች በእነርሱ ላይ ለመፍረድ ያለንን ሥልጣን በሚቃወሙበት ጊዜ በድፍረት ልንቋቋማቸው ይገባናል፡፡ ኢየሱስ ‹‹ሐጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል›› (ዮሐንስ 20፡23) በማለት እንዲህ ያለውን መብት ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቶዋቸዋል፡፡ 
በመላው ዓለም በክርስቲያን የሥነ ጽሁፍ አገልግሎታችን አማካይነት የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበሉ ብዙ ቅዱሳኖች አሉ፡፡ ሌሎችን የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብለው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ በመንፈሳዊ መልኩ ለመለየት ይችሉ ዘንድ እግዚአብሄር ከዚህ የሐጢያቶች ስርየት ጋር አብሮ የመንፈስ ቅዱስን ሐይል ሰጥቶዋቸዋል፡፡ ወርቁ፣ ሰማያዊው፣ ሐምራዊው፣ ቀዩ ማግና ጥሩው በፍታ ምን እየነገራቸው እንደሆነ የሚያውቁና የሚያምኑ ሌሎችን በእምነት ይፈርዳሉ፡፡ እግዚአብሄር በእነዚህ ካህናት አማካይነት ሰዎችን ከሐጢያቶቻቸውና ከኩነኔ አድኖዋቸዋል፡፡ በመንፈሳዊ መልኩ የእግዚአብሄር ልጆች የሆንነው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ነው፡፡
የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን በኋላ መንፈሳዊ ካህናት ሆነናል፡፡ ስለዚህ የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበሉትንና ያልተቀበሉትን የመፍረድ መብት አለን፡፡ ሐጢያተኞችን በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ወደ ሲዖል እየተጓዙ እንደሆኑና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት መቀበል እንደሚኖርባቸው ያለ ማመንታት ልንነግራቸው ይገባናል፡፡ አስቀድመው ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ የተወለዱትም ወዳጅ ምዕመናኖቻችን በትክክለኛው ጎዳና እንዲጓዙ ልንፈርድባቸው ይገባናል፡፡
እኛ መንፈሳዊ ካህናት የሆንን ገና የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያልተቀበሉትን ሐጢያተኞች መፍረዳችን ትክክለኛ አይደለም ብላችሁ ማሰብ የለባችሁም፡፡ በሌላ አነጋገር እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ሐጢያተኞች መሆናቸውን ማወቅ ዕብሪት እንደሆነ አድርጋችሁ ማሰብ አይገባችሁም፡፡ በአንጻሩ እኛ መንፈሳዊ ካህናት ሆነን ሁልጊዜም የፍርዱን የደረት ኪስ በደረቶቻችን ላይ ስለምንሸከም ሐላፊነቶቻችንን ይበልጥ በትጋት መወጣት አለብን፡፡ ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ ገለል አድርገን እግዚአብሄርን በመወከል እነዚህ ሐጢያተኞች በሲዖል መኮነን ያለባቸው የመሆኑን ውሳኔ መስጠት አለብን፡፡ ያን ጊዜ እነዚህ ሐጢያተኞች መንፈሳዊ ካህናት የፈረዱትን ፍርድ የእግዚአብሄር ፍርድ አድርገው ይገነዘቡታል፡፡ ይህንን ፍርድ ይቀበላሉ፡፡ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው ሐጢያትን የሚያስወግድ የእግዚአብሄር ጸጋ ያምኑና ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይድናሉ፡፡ ፍርድ በእምነት ከተፈረደ ትክክለኛ ፍርድ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡
ታዲያ ሌሎች የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብለው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ መወሰን የምንችለው በምን መስፈርት ነው? ይህንን መወሰን የምንችለው በአምስቱ የወርቅ፣ የሰማያዊ፣ የሐምራዊ፣ የቀይ ማግና የጥሩ በፍታ ማጎች በሚያምነው እምነት ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እኛ ንጉሣዊ ካህናት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ በመመሥረት ሌሎችን መፍረድ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፤ በመስቀል ላይ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ በዚህም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አስወግዶ የእነዚያን ሐጢያቶች ኩነኔ ሁሉ ተሸከመ፡፡ በዚህ እውነት የሚያምኑ የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብለዋል፡፡ በዚህ እውነት የማያምኑ ሐጢያተኞች በመሆናቸው ሊፈረድባቸው ይገባል፡፡
የጻድቃን ፍርድ መለኪያ ማለትም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ተገቢ ሕይወት ኖረዋል ወይስ አልኖሩም የሚለው የሚወሰነው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዴት በሚገባ አገልግለዋል በሚለው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለሁሉም ፍርዶች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያምናል ወይስ አያምንም የሚለው ጥያቄ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን መሠረታዊ መለኪያ ያዋቅራል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት በዚህ እውነተኛ ወንጌል የማያምን ማንኛውም ሰው ሐጢያተኛ ሆኖ ይቀራል፡፡ ከአራቱ የብሉይ ኪዳን ማጎች ማለትም ከሰማያዊው፣ ከሐምራዊው፣ ከቀዩ ማግና ከጥሩ በፍታ እምነቱ ወይም እምነቷ አንዱን እንኳን አውጥቶ የሚተው ማንኛውም ሰው ለዘላለም ከሐጢያቱ ያልዳነ ሆኖ ይቀራል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄር ደህንነት በእነዚህ በአራቱ ማጎች ማመንን ይጠይቃል፡፡
በዛሬዎቹ ክርስቲያኖች መካከል በመስቀሉ ደም በማመን ብቻ ዳግመኛ እንደተወለዱ የሚናገሩ ብዙዎች አሉ፡፡ በመስቀሉ ደም ብቻ የሚያምኑትን የእነዚህን ክርስቲያኖች እምነት ስንመረምር እምነታቸው ብቁ እንዳልሆነ መደምደም እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እምነታቸው ሰማያዊውን ማግ (የኢየሱስን ጥምቀት) አውጥቶ በመጣሉ የፈጠራ እምነት ነውና፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የሰውን ዘር ሐጢያቶች መውሰድ ችሎዋልን? ኢየሱስ የተሰቀለው፣ ደሙን ያፈሰሰውና በመስቀል ላይ የሞተው አስቀድሞ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቁ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስለወሰደ ነው፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ ባይጠመቅ ኖሮ የዓለም ሐጢያቶች እንዴት ወደ እርሱ መሻገር ይችሉ ነበር? ክርስቶስ የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ተሸክሞ የተሰቀለውና ደህንነታችንንም ለመፈጸም እስከ ሞት ድረስ ደሙን ያፈሰሰው ሐጢያቶቻችን በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ በመሻገራቸው ነበር፡፡
ኢየሱስ የተሰቀለው በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠምቆ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በመውሰዱ ነው፡፡ ነገር ግን በእርሱ ጥምቀት ባይሆን ኖሮ ሐጢያቶቻችንን ሊወስድ የሚችል ሌላ ማን ይገኝ ነበር? የእግዚአብሄር አብን ፈቃድ ለመፈጸምስ ማንን በመስቀል ላይ ያንጠለጥል ነበር? በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ አስቀድሞ ሐጢያቶቻችንን ባይወስድ ኖሮ እንዴት በመስቀል ላይ ይሞት ነበር? ጉዳዩ ይህ አይደለምን? ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ ባይጠመቅ ኖሮ ሐጢያቶቻችሁ ሁሉ አሁንም በልባችሁ ውስጥ እንዳሉ ይቀሩ ነበር፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ የዓለምን ሐጢያቶች ባይወስድ ኖሮ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ የሚሞትበት ምክንያቱ ምንድነው?

 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ባለማወቅ የሚነሱ ጥያቄዎች፡፡ 

‹‹ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ መውሰዱ እውነት ከሆነ ይህ ማለት ኢየሱስ በስጋው ላይ ሐጢያቶች አሉበት ማለት ነው፡፡ ነገሩ ይህ ከሆነ ይህ ሐጢያተኛ የሆነው ኢየሱስ እንዴት የሐጢያተኞች አዳኝ ሊሆን ቻለ?›› ብለው የሚጠይቁ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡
ይህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ፈጽሞ ካለማወቅ የመነጨ አሰልቺ ጥያቄ ነው፡፡ ኢየሱስ ሲጠመቅ የሰውን ዘር ሐጢያቶች የወሰደው በስጋው ላይ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የዓለምን ሐጢያቶች የወሰደው በመንፈሱ ላይ አይደለም፡፡ የተጠመቀው ኢየሱስ መለኮታዊ ተፈጥሮ ፍጹም ቅዱስ ነበር፡፡ የተጠመቀው በስጋው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የዓለምን ሐጢያቶች የወሰደው በስጋው ላይ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ የተሰቀለው፣ ለሐጢያቶች ሁሉ የተኮነነው፣ ደሙን ያፈሰሰውና በመስቀል ላይ የሞተው በአጥማቂው ዮሐንስ ስለተጠመቀ ነው፡፡ ኢየሱስ በራሱ በዚህ ዓለም ላይ ፈጽሞ ሐጢያት አልሠራም፡፡ (2ኛ ቆሮንቶሰ 5፡21) ነገር ግን ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች ስለወሰደ እነዚህ የዓለም ሐጢያቶች በስጋው ላይ ተጫኑ፡፡ ነገሩ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ አዳኛችን ሊሆን ባልቻለም ነበር፡፡
ለእነዚህ አላዋቂ ሰዎች በትክክል ልነግራቸው የምፈልገው ነገር ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች የወሰደው በመስቀል ላይ አለመሆኑን ነው፡፡ ይህንን ደግሜ ልነግራችሁ፡- ‹‹ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ ሲጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰዱ ነው፡፡›› ይህ አውነት ካልሆነ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች ለመውሰድ ሌላ ዕድል ባልኖረው ነበር፡፡ በጥቅል አነጋገር ኢየሱስ የሐጢያተኞች ሁሉ የመሥዋዕት በግ ቢሆንም በልቡ ውስጥ ፈጽሞ ሐጢያት አልነበረበትም፡፡ ኢየሱስ ከውልደቱ ጀምሮ ሐጢያት አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ ወደ ስጋው የተሻገሩትን የዓለም ሐጢያቶች ተቀበለ፡፡ ኢየሱስ ለዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ሕጋዊ መሥዋዕት የሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ በጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ ደሙን አፍስሶ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ከዚያም ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡ እውነተኛ አዳኛችንም ሆነ፡፡ እንዲህ በማድረጉም የሐጢያትን ኩነኔ ሁሉ ተሸከመ፡፡ ስለዚህ አሁንም ድረስ በልባችሁ ውስጥ ሐጢያት ካለ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምነው እምነት ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ መዳን አለባችሁ፡፡
 


የተበረዘው ክርስትና ታሪክ፡፡ 


በጥንቷ የቤተክርስቲያን ዘመን እንደ ጳውሎስና ጴጥሮስ ያሉ ሐዋርያትና የጥንት ቅዱሳን መንፈሳዊ ካህናት መሆንና መሥራት የቻሉት በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደም በማመን ነበር፡፡ ከታሪክ አንጻር ስንናገር የጥንቷ ቤተክርስቲያን ክፍለ ጊዜና የቤተክርስቲያን አባቶች ዘመን ካለፈ በኋላ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት መበረዝ ጀመረ፡፡ በ313 ዓ.ም የወጣው የሚላን ድንጋጌም ይህንን የመበስበስ ሒደት አፋጠነው፡፡ ዛሬ ክርስቲያን የሆኑ ሐጢያተኞች የፈለቁት ከዚህ ብረዛ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እጅግ ብዙ የስም ክርስቲያኖች ተነስተዋል፡፡ በመስቀሉ ደም ብቻ አያምኑም፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት እንደተቀበሉም ይናገራሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠው ወንጌል ተደብቆ ቀርቷል እንጂ አልተሰበከም፡፡ ክርስትናን እንደ አንድ ተራ የዚህ ዓለም ሐይማኖት አድርገው ብቻ የሚመለከቱ ብዙ ክርስቲያኖች መነሳታቸው የሚረብሽ እውነታ ነው፡፡
መንፈሳዊ ካህናት እንድንሆን ባስቻለን እምነት ላይ ተመርኩዘን የዘመኑን ክርስቲያኖች ስንፈርድ ብዙዎቹ የሐጢያቶችን ስርየት እንዲቀበሉ የሚፈቅድላቸውን ደህንነት በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸውንና ማጣመማቸውን ማየት እንችላለን፡፡ የዘመኑ ክርስትና የቤተክርስቲያን ድርጅቶች የእምነት መምርያ ሁሉ አንዱ ከሌላው ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ማየት እንችላለን፡፡ የሚለያዩት በቤተክርስቲያን ድርጅቶቻቸው ስሞች ብቻ ነው፡፡ እምነቶቻቸውን በሚመለከትም ሁሉም በመስቀሉ ደም በማመን ብቻ እንደሚድኑ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ልቦቻቸው በውኑ ከሐጢያት አልነጹም፡፡ የእግዚአብሄርን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ሳያውቁ ራሳቸውን ጥሩ ክርስቲያኖች ነን ብለው ያስባሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው በመስቀሉ ደም ቢያምኑም አሁንም ድረስ በንስሐ ጸሎቶቻቸው ብቻ የተወጠሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ እንዲያስወግዱ የሚያስችላቸውን እውነት ገናም አላወቁምና፡፡ በሌላ አነጋገር ገናም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሐይል ሳያውቁ ሐጢያቶቻቸውን ለማንጻት የሚሞክሩ ሰዎች አሉ፡፡
እኛ እንደገና ይህንን እውነተኛውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በመላው ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እያሰራጨን ያለነው ለዚህ ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት ስለማያውቁ ለመገናኛው ድንኳን መሥሪያ ቁሳ ቁሶች ሆነው ጥቅም ላይ በዋሉት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠውን ይህንን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ለእነርሱ መስበክ እንዳለብን ተረድተናል፡፡ ሁላችንም ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰድ፣ በመስቀል ላይ በመሰቀልና በመሞት የሐጢያትን ኩነኔ ሁሉ እንደወሰደ በዚህ ዓለም ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እየሰበክን ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለማያውቁ ለእነዚህ ሰዎች ይህንን ወንጌል የማሰራጨት ዕዳ አለብን፡፡ ስለዚህ ወደ ማመን ይመጡ ዘንድ ይህንን እውነተኛ ወንጌል የሚሰሙበትን ዕድል የመስጠቱን አስፈላጊነት ተገንዝበናል፡፡
በአንዳንድ አገሮች የክርስትና እምነት ታሪክ 1,000 ወይም 2,000 ዓመታቶችን ያስቆጠረ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች አሁንም ድረስ ስለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል ግልጥ የሆነ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በተገለጠው የወንጌል እውነት ላይ ተመሥርተን ስንፈትናቸው ወደኋላ ተመልሰው ገና ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው መቀበል ያለባቸው ብዙዎች አሉ፡፡ እዚህ ላይ ለማለት እየሞከርሁ ያለሁት ምንም ያህል ለረጅም ጊዜ በኢየሱስ ቢያምኑም አሁንም ድረስ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ካልተቀበሉ እንደገና በትክክል ኢየሱስን እንዲቀበሉ ልንመራቸው የሚገባን መሆኑን ነው፡፡ በአስቸኳይ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ልናስተምራቸው ይገባናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ልክ እኛ ያሰብነው አሳብ ነበረው፡፡ እርሱ እንዲህ አለ፡- ‹‹ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፡፡ ግድ ደርሶብኝ ነውና፡፡ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 9፡16)
 


ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያተኞችን ሁሉ ለማዳን የሰው ስጋ ለብሶ የመጣ አምላክ ነው፡፡ 


አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሄር ልጅና የእነርሱ አዳኝ እንደሆነ ቢያምኑም ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ አያምኑም፡፡ በክርስቶስ የሐምራዊው ማግ አገልግሎት አያምኑም፡፡ እነዚህ ሰዎች በእርግጥም ይጠፋሉ፡፡ ምክንያቱም በልቦቻቸው ውስጥ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ውስጥ የተገለጠውን ምሉዕ እውነት የሚያምን እምነት ስለሌላቸው የሐጢያቶችን ስርየት አልተቀበሉምና፡፡ ጌታ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ እንደደመሰሰላቸው በልባቸው የማያምኑ በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የለም፡፡ ምክንያቱም ሐጢያቶቻቸው መንጻታቸውን የሚመሰክርላቸው ቃል የላቸውምና፡፡
ኢየሱስን የእኛ ‹‹ጌታ›› ብለን ስንጠራው እዚህ ላይ ‹‹ጌታ›› የሚለው ቃል አለቃ ማለት ሲሆን ኢየሱስ ራሱ አምላክ እንደሆነ እንደምናምን ያመለክታል፡፡ ይህንን ለማብራራት ሁልጊዜ የሚከተለውን ምሳሌ እጠቀማለሁ፡፡ ሰዎች ሲጸንሱ ሌሎች ሰዎችን ይወልዳሉ፡፡ ውሾች ሲጸንሱ ትንንሽ ውሾችን ይወልዳሉ፡፡ ወፎች ወፎችን ይወልዳሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የተለያዩ የዝርያ ዓይነቶች እንዳሉ ሁሉ እግዚአብሄር አብም አንድያ ልጁን ወለደ፡፡ ያም ልጅ እንደዚሁ አምላክ ነው፡፡ (መዝሙረ ዳዊት 2፡7) እርሱ በባህሪው በእርግጥም ከራሱ ከእግዚአብሄር ጋር የሚተካከል ነበር፡፡ (ፊልጵስዩስ 2፡6) ነገር ግን ራሱን ባዶ አድርጎ እንደ እኛ እንደ ሰዎች ሆነ፡፡ ከሐጢያት ሊያድነንም ወደዚህ ምድር መጥቶ ተጠመቀ፡፡ በመስቀል ላይም ሞተ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ እውነተኛ አዳኛችን በመሆንም እውነተኛውን የደህነነት እምነት ሰጠን፡፡
ሆኖም ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የሚክዱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ኢየሱስ በጥንት ዘመን ከተገለጡት ከአራቱ ጠቢባን ሰዎች አንዱ እንደሆነ በይፋ ያስተምራሉ፡፡ ይህ እሳቤ የመነጨው ከቤተክርስቲያን አባቶች ነው፡፡ ከእምነት አባቶቻቸው እውነተኛውን ወንጌል በመስማታቸው አንዳንዶቹ ጠንካራ እምነት ይዘው ሰማዕት በመሆን ስለ እምነታቸው ሲመሰክሩ ሌሎች ግን የኢየሱስን መለኮታዊነት ክደዋል፡፡ አንዳንድ የቤተክርስቲያን አባቶች ኢየሱስን የእግዚአብሄር ልጅ እንጂ ራሱ አምላክ አይደለም ብለው በመከራከር የጽሁፍ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡
በቅርቡ ብዙ የቃለ እግዚአብሄር ምሁራን ሐይማኖታዊ ጋርዮሽን መደገፍ ጀምረዋል፡፡ ሰዎች ከክርስትና ውጭ በተለያዩ ሐይማኖቶች ቢያምኑም ከሐጢያት ድነው ሰማይ መግባት ይችላሉ የሚሉ አመለካከቶች አሉዋቸው፡፡ እንዲህ ያለውን ቃለ አምነት በቅድሚያ ያወጀችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ እነዚህ የስም ክርስቲያኖች ይህንን አመለካከት የሚደግፉት እነርሱ ራሳቸው ኢየሱስ ራሱ አምላክና ፈጣሪ እንደሆነ ስለማያምኑ ነው፡፡ ቃሉ እንደሚናገረው በእርሱ ለማመን ይፈለጋሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን እውነተኛውን እምነት እንዲሀ ባለ የሐሰት ትምህርት ላይ መመሥረት አይችሉም፡፡ እነርሱ ቤቶቻቸውን በአሸዋ ላይ የገነቡ ሞኞች ናቸው፡፡ (ማቴዎስ 7፡26) እነርሱ ሁሉን ነገር ከሌሎች ሐይማኖቶች መማር ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ምዕራባውያን ቤተክርስቲያናት በሳምንት አንድ ቀን የቡዲዝምን የተመስጦ መርሃ ግብሮች እየተለማመዱ ነው፡፡ ከስብዕና አመለካከት አንጻር እንዲህ ያለ መርሃ ግብር ያማረና ይበልጥ የሰለጠነ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ራሱ አምላክ እንደሆነ የማያምን ማንኛውም ሰው ከሐጢያት ሊድን አይችልም፡፡
እናንተስ? የምታምኑት እንዴት ነው? ዘፍጥረት 1፡1-3 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ ምድርም ባዶ ነበረች፤ አንዳችም አልነበረባትም፡፡ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበር፡፡ የእግዚአብሄርም መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍፎ ነበር፡፡ እግዚአብሄርም ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ፡፡›› እግዚአብሄር በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን በቃሉ ፈጠረ፡፡ ቃሉ ገና ከመጀመሪያውም ነበረ፡፡ ይህ ቃልም እግዚአብሄር ነበረ፡፡ ስለዚህ ዓለም የተፈጠረው ስጋ ለብሶ በመጣው ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 1፡1፤ ዮሐንስ 1፡10) ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ማለትም የቃሉ አምላክ ነበር ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን አጽናፈ ዓለም የፈጠረ ፈጣሪና እኛን ለማዳን ወደዚህ ምድር የመጣ አዳኝ ነው፡፡ ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይን የክብር ዙፋን ትቶ የሰው ስጋ በመልበስ በግሉ ወደዚህ ምድር የመጣ አምላክ መሆኑን ማመናችን ትክክል ነው፡፡
እግዚአብሄር ራሱ በባሮቹ አማካይነት ስለ መሲሁ መምጣት ተንብዮ ነበር፡፡ በእነዚህ ትንቢቶች መሠረትም አዳኙ በድንግል ማርያም ማህጸን ውስጥ ተጸንሶ የሰው ስጋ ለበሰ፤ ማለትም በሰው አካል ውስጥ የተጸነሰውና የተወለደው እርሱ ራሱ አምላክ ነበር፡፡ 30 ዓመት ሲሞላው የሰማይ ሊቀ ካህን በመሆን ሐጢያቶቻችንን በሙሉና የሰውን ዘር ሁሉ ሐጢያቶች በጥምቀቱ በስጋው ላይ ወሰደ፡፡ ከዚያም በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ከሙታንም ተነሳ፡፡ በዚህም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ፈጽሞ አዳነን፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ እውነተኛና ዘላለማዊ አዳኛችን ሆነ፡፡
ኢየሱስ በመሠረታዊ ማንነቱ ከእግዚአብሄር አብ ጋር የሚተካከል ራሱ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ በመሠረቱ ከእግዚአብሄር አብ ጋር እኩል የሆነው ይህ ኢየሱስ ያው አምላክ ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስም አባት እንደዚሁ አምላካችን ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱም አምላካችን ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ነውና፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን ሆነን የተፈጠርነውም በእርሱ ነው፡፡ እግዚአብሄር በዘፍጥረት 1፡26 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፡፡›› እግዚአብሄር ሰውን በራሱ አምሳል ሲፈጠረው ኢየሱስ ክርስቶስም እዚያው ነበር፡፡ የፈጠረን እርሱ ነው፡፡ የፈጠረንና ከሐጢያት ያዳነን እርሱ ነው፡፡ ሊያድነን የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አዳኛችን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደህንነትን ስለሰጠንና እርሱ ራሱም አምላክ ስለሆነ የደህንነታችን ጌታ አድርገን እናምነዋለን፡፡ ስለዚህ እናንተና እኔ ከእንግዲህ ወዲያ ግራ በመጋባት መቅበዝበዝ አይገባንም፡፡ ነገር ግን አዳኝ ሆኖ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በመጣው ጌታ አምላክ በልባችን ማመን ይገባናል፡፡
ልቦቻቸው አሁንም በሐጢያት ተሞልተወ ሳሉ የእግዚአብሄር ልጆች ስለመሆናቸው ክርር የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ልቦቻቸው ሐጢያት እያለባቸው በእርግጥ የእግዚአብሄር ሕዝብ መሆን ይችላሉን? በእርግጥ አይችሉም! ክርስቲያን መሆናቸው ወይም አለመሆናቸው ምንም ማለት አይደለም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ባለማወቃቸው ምክንያት የሐጢያቶችን ስርየት ያልተቀበሉ ከሆኑ ማናቸውም ሰማይ መግባት አይችሉም፡፡ ነገር ግን በዚህ በመላው ዓለም ላይ በሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ የዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡
ታዲያ ትክክለኛውንና እውነተኛውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ለእነዚህ ሰዎች ማሰራጨት ያለበት ማነው? እኛ ማለትም እናንተና እኔ ለእነርሱ ትክክለኛውን ውሳኔ መወሰንና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እውነት ለእነርሱ መስበክ አለብን፡፡ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተገለጠው ወንጌል አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ተሰብኮ ሙሉ በሙሉ የሚተው ዓይነት እውነት አይደለም፡፡ ጌታችን እስኪመለስ ድረስ ስርጭቱን መቀጠል ያለበት ትክክለኛ የደህንነት እውነት ነው፡፡
የሐጢያቶችን ስርየት እንድትቀበሉ የሚያስችላችሁን ይህንን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ታውቁታላችሁን? ሰዎች ሐጢያት ካለባቸው የእግዚአብሄር ልጆች አይደሉም፡፡ የመገናኛው ድንኳን ቁሳ ቁሶች ሆነው ጥቅም ላይ በዋሉት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው የወንጌል እውነት የሚያምን እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እስከ ዓለም ፍጸሜ ደረስ ማሰራጨት አለብን፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመስበክ በጣም እናፍር ይሆን? በጥንት ዘመን እግዚአብሄር ባሮቹን ‹‹ውጡና ትንቢት መናገራችሁን ቀጥሉ›› ብሎ ሲነግራቸው ያንን በማድረግ ይቀጥሉ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ኢሳይያስን ‹‹ራቁትህን ሆነህ ትንቢት ተናገር›› ብሎ በነገረው ጊዜ ራቁቱን ሆኖ በመውጣት ትንቢት ተናገረ፡፡ (ኢሳይያስ 20፡2-5) በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በተገለጠው መሠረት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለሰዎች ሁሉ ስንሰብክ ከእግዚአብሄር ቁጣ ማምለጥ ይችላሉ፡፡ ወንጌልን በማሰራጨት መቀጠል የሚገባን ለዚህ ነው፡፡
እናንተስ? ልባችሁ እውነተኛውን ደህንነት የሚያመጣው የእውነት ቃል አለው? በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች የሐጢያቶችን ስርየት የሚሰጠው ቃል ከሌላቸውና አሁንም የሰይጣን ከሆኑ እንዴት ዝም ብላችሁ መቀመጥ ያስችላችኋል? መቀመጥ የለባችሁም፡፡ በመላው ዓለም ብዙ አጋሮች አሉን፡፡ እነርሱ የሐጢያቶችን ስርየት በሚያስገኘው ወንጌል በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በግልጥ ያምናሉ፡፡ አንዳንዶቹ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለጓደኞቻቸው በመንገራቸው ስደት እንደገጠማቸው ነግረውናል፡፡ ‹‹አሁንም በልቦቻችሁ ውስጥ ሐጢያት ስላለ የእግዚአብሄር ሕዝብ አይደላችሁም፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያለማመን ዕዳ ይዛችሁ በረከሱት ሐጢያቶቻችሁ ምክንያት ወደ ሲዖል እየሮጣችሁ ነው፡፡ እናንተ ‹ወንድሜ› ብላችሁ ብትጠሩኝም እኔ ግን ‹ወንድም› ብዬ ልጠራችሁ አልችልም፡፡ ምክንያቱም እኔ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ እናንተ ሐጢያተኛ አይደለሁምና›› በማለት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ጠላቶች አሸንፈዋቸዋል፡፡
በዚህ መንገድ ምላሽ እንዲሰጡ ፈጽሞ ምሪት አልሰጠናቸውም፡፡ በውስጣቸው ያለው መንፈስ ቅዱስ ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሳያቸው፡፡ መዋከብ አያስፈልጋችሁም፡፡ ምክንያቱም ሌሎችን ሁሉ ልትፈርዱ የምትችሉበትን መለኪያ የያዘ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በልቦቻችሁ ውስጥ አለና፡፡ የሌሎችን የሐጢያቶች ስርየት በትክክል ማወቅ የምትችሉበት ይህ ችሎታ ለእናንተ የተሰጠው በተለይ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በተገለጠው የወንጌል እውነት ስላመናችሁ ነው፡፡ ጌታ በእነዚህ በሦስቱ የሰማያዊ፣ የሐምራዊና የቀይ ማጎች ቀለማት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንዳዳነንና ጻድቃን እንዳደረገን በሚናገረው እውነት በማመን በእግዚአብሄር ፊት መቆም ይገባናል፡፡
 

ትክክለኛውን የደህንነት መለኪያ በትር እንጠቀም፡፡ 

የእግዚአብሄርን ቃል ‹‹ቀኖና›› ብለን እንጠራዋለን፡፡ ‹‹ቀኖና›› የሚለው ቃል የተገኘው ቋኔ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃልና ካኖን ከሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ሁለቱም የሚያመለክቱት መለኪያ በትርን ነው፡፡ አንድን ነገር መለካት ስንፈልግ በትክክል ለመለካት ማስመሪያ ወይም መለኪያ በትር መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ልክ እንደዚሁ የአንድን ሰው መንፈሳዊ አቋም ማለትም ግለሰቡ ዳግም ተወልዶ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ማወቅ በምንፈልግበት ጊዜ ያንን ግለሰብ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የመለኪያ በትር ልንመረምረው ይገባናል፡፡ አንድ ልብስ ሰፊ የደንበኞቹን መጠን ለመለካት ሜትሩን እንደሚጠቀም ሁሉ ያ ግለሰብም በእርግጥ ከሐጢያት ድኖ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ መመርመር አለብን፡፡ ይህንን የምናደርግበት መንገድ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው እውነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በዚህ የእግዚአብሄር ቃል ላይ በመመርኮዝ የግለሰቡን እምነት እያንዳንዱን ክፍል መንቀስና ከመለኪያው በታች ያለው ምን እንደሆነና ከመለኪያው የሚበልጠውም ምን እንደሆነ በግልጥ መለየት ይገባናል፡፡
በተለይም እምነታችንን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የመለኪያ በትር ማለትም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚገባ መፈተሽ ያስፈልገናል፡፡ አንድ ሰው በኢየሱስ የሚያምነው በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ብቻ ከሆነ እምነቱ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳሉት የንጉሥ ካህናት በእግዚአብሄር ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ከሐጢያቶቹ መላቀቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው ምሉዕ የደህንነት እውነት ማመን አለበት፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ሁሉ ከሐጢያት ለማዳን ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ በጥምቀቱም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እንደወሰደ፣ በመስቀል ላይ እንደሞተ፣ ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳና እውነተኛ አዳኛችን እንደሆነ ሁላችንም ማመን አለብን፡፡ ሁላችንም ይህ እውነተኛ የፍርድ መለኪያ ሊኖረን ይገባል፡፡ ሰዎች ሐጢያተኞች ወይም ጻድቃን መሆናቸውን መወሰን እንችል ዘንድም መለኪያው በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ይህንን በዘፈቀደ በራሳችን ዕውቀትና ስሜቶች ላይ ተመርኩዘን ልናደርገው አንችልም፡፡ መንፈሳዊ ካህናት ለሕዝባቸው የሐጢያት ቁርባን የማቅረብ ሐላፊነታቸወን እንዲፈጽሙ የሚጠቅማቸው ሥራ ይህ ነው፡፡
አሁን በዚህ ዘመን እናንተና እኔ እንዲህ ባለ ትክክለኛ መለኪያ በዓለም ሕዝብ ሁሉ ላይ መፍረድ አለብን፡፡ ይኸው መለኪያ ለሁሉም ለልጆቻችን፣ ለሚስቶቻችን፣ ለባሎቻችን፣ ለአባቶቻችን፣ ለእናቶቻችን፣ ለአማቾቻችንና ለልጅ ልጆቻችን በእኩል ደረጃ ያገለግላል፡፡ የሌሎችን እምነት በእግዚአብሄር ቃል መሠረት ለይተን ማወቅ ይገባናል፡፡ ካህናት የሆኑ የፍርዱን መለኪያ በትር በእያንዳንዱ ሰው ልብ ላይ ማኖር አለባቸው፡ ‹‹በኢየሱስ የሰማያዊ፣ የሐምራዊ፣ የቀይ ማግና የጥሩ በፍታ እውነት ታምናለህን? እንደዚህ የምታምን ከሆነ ድነሃል፡፡ የማታምን ከሆነ ግን አልዳንክም፡፡›› ልክ እንደዚህ ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ልናደርገው የሚገባን ትክክለኛ ነገር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ሊቀ ካህኑ ያደረገው ይህንን ከሆነ የዘመኑ መንፈሳዊ ካህናት እናንተና እኔም ያለ ምንም መሰናክል ይህንኑ ማድረግ አለብን፡፡ የእርሱ ካህናት ሆነን ማድረግ የሚገባንን የማናደረግ ከሆንን ፈጽሞ በእግዚአብሄር ከመወቀስ ማምለጥ አንችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ለሰው ወንጌል የሚሰበክበት መንገድ ያ አይደለም፡፡ ወንጌልን መስበክ ያለባችሁ እንዲህ ነው! እኛ ልክ እንደ እናንተ ለሰዎች ወንጌልን የምንሰንብክ ቢሆን ኖሮ ማን በኢየሱስ ያምን ነበር?›› ይላሉ፡፡
በቲዎሎጂ (ነገረ መለኮት) ‹‹ወንጌልን የመስበክ ጥበብ›› ተብሎ የሚጠራ ኮርስ አለ፡፡ ወንጌል እንዴት እንደሚሰበክ መመሪያን ይሰጣል፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹የወዳጅነት ስብከተ ወንጌል›› የሚለው ቃል በመስክ ከተሰማራ ከእያንዳንዱ ሰባኪ አፍ የማይጠፋ ሐረግ ነበር፡፡ ይህንን የሚያቀነቅኑ አቀንቃኞች አሁንም ድረስ ሰዎችን በወንጌል ልንደርሳቸው በምንሞክርበት ጊዜ በመጀመሪያ ጓደኞች ልናደርጋቸውና ቀስ በቀስ ወደ ቤተክርስቲያን ልንመራቸው ይገባናል እያሉ ያስተምራሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ በእነርሱ የወንጌል ስርጭት ጥረቶች አማካይነት ግለሰቡ በኢየሱስ ለማመን ሲወስን ክርስቶስ ወደዚህ ግለሰብ ልብ ውስጥ እንዲገባና እርሱ ወይም እርስዋ እንዲድኑ ያ ግለሰብ ኢየሱስን የመቀበል ጸሎት ተብሎ የሚጠራውን እንዲደግም እንደሚያደርጉትም ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን የዚህ አቀራረብ የመጨረሻው ውጤት ምንድነው? ሐጢያቶች ከእነዚህ አዲስ የተለወጡ ሰዎች ልቦች ውስጥ ይጠፋሉን? እንደዚያ አይሆንም፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ፤ ነገር ግን አሁንም ሐጢያት አለባቸው፡፡ በሌላ አነጋገር አዲስ የተለወጡት ሰዎች ሌላ የክርስትና ሐይማኖት ተለማማጅ ብቻ ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች በዚህ መንገድ እንዲያምኑ ካደረጓቸው በኋላ አስራቶችና የምስጋና ስጦታዎች እንዲሰጡ ያደርጉዋቸዋል፡፡ በመጨረሻም ክርስቲያኖች ቢሆኑም ከእግዚአብሄር ፍርድ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም አሁንም ሐጢያት አለባቸውና፡፡
እነርሱ ‹‹ገና እንዳገኛችኋቸው ሰዎችን እንዴት ሐጢያት እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸው ትጠይቁዋችኋላችሁ? በሚገባ ሳታውቁዋቸው እንደዳኑ ወይም እንዳልዳኑ ፍርዳችሁን በመስጠት እንዴት የደህንነትን ጉዳይ ፈጥናችሁ ታነሳላችሁ?›› በማለት የወንጌል ስርጭት ዘዴያችን ስህተት መሆኑን ይነግሩናል፡፡ በእርግጥ የተናገሩትን ነገር ማጤን ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም ልናድነው የምንፈልገው ነፍስ በአነጋገራችን በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል ስብዕና ያለው ነውና፡፡ ነገር ግን ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ለምንገናኛቸው አላማኒዎች የደህንነትን ወንጌል መስበከ አለብን፡፡ ምንም ያህል የቅርብ ወዳጆቻችን ብናደርጋቸውም ፈጥነንም ይሁን ዘግይተን ወንጌልን ልንሰብክላቸው ስለሚገባን ወንጌልን በእምነት የመስበክን ዕድል ልናጣ አይገባንም፡፡ ለምን? ምክንያቱም ስለዚህ እውነት እስከ መጨረሻው ድረስ ካልነገርናቸው ወንጌልን በትክክል እያሰራጨን አይደለንም፡፡ 
ስለዚህ በወንጌል ስብከታችን መጀመሪያ ወይም መጨረሻ ላይ ሰዎችን ሁሉ ‹‹በልባችሁ ውስጥ ሐጢያት አለ?›› ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ መልሱ አዎ ከሆነ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ልንሰብክላቸው ይገባናል፡፡ ስለ ድፍረታችን በእነርሱ ልንወቀስ እንችላለን፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን መንፈሳዊ ካህናት ስለሆንን የውሃውንና የመንፈሱን የወንጌል መለከት ለሰዎች ሁሉ በግልጥ የማስተጋባት ክቡር ሐላፊነት አለብን፡፡ 
 


አንድ ጌታ፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንድ እግዚአብሄር፡፡ 


እኛ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጻ ወጥተናል፡፡ የሕይወታችን ዓላማም በመላው ዓለም ወንጌልን በማሰራጨት ላይ ያረፈ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሚሰብኩት ወንጌላውያን ጋር የሚመሳሰሉ ሐላፊነቶች ስለተሰጡን አብረን እንሠራለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ለምንድነው? ተመሳሳይ በሆነ አምላክ ስለምናምን፣ ተመሳሳይ የሆነ የዘላለም ሕይወት ስለተቀበልንና ተመሳሳይ በሆነ ክብር ስለምንደሰት ነው፡፡ ሁላችንም እርስ በርሳችን የተለያየን ነን፡፡ እያንዳንዳችን የራሳችን የሆኑ ስብዕናዎችና ባህሪዎች አሉን፡፡ ነገር ግን ራሳችንን የለየነውና እርስ በርሳችን የተባበርነው ሕይወታችንን ለእግዚአብሄር ለመኖር ነው፡፡
እግዚአብሄር የዘመኑ ካህናት በሆኑት ልቦች ላይ የፍርዱን የደረት ኪስ አድርጓል፡፡ የደረቱ ኪስም ‹‹በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረት ኪሱን ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል፡፡›› (ዘጸዓት 28፡28) ይህ ሐረግ በምንወስነው በእያንዳንዱ ነገር ላይ የኢየሱስ ጥምቀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ደግሞ ያተኩርበታል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም እንደዚሁ ‹‹አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ ሐይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት፣ ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ›› (ኤፌሶን 4፡4-5) በማለት የኢየሱስን ጥምቀት አስፈላጊነት ይናገራል፡፡
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን አለማመናቸው ላይ ተመርኩዘን ሰዎች መዳን አለመዳናቸውን የመፍረድ ሐላፊነት አለብን፡፡ ገና የሐጢያቶችን ስርየት ለሚቀበሉ ወንጌልን መስበክ አለብን፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት ለተቀበሉትም ዕውቅናን መስጠትና በእምነታቸው እንዲያድጉ መርዳት አለብን፡፡ ከሐጢያቶቻችን ነጻ ወጥተን ሳለን በመንፈሳዊ መልክ የፍርዱን ደረት ኪስ መልበስ ወይም አለመልበሳችን ትክክል ነውን? በሌላ አነጋገር በአንድ ሰው ላይ የሰጠነውን ትክክለኛ ፍርድ ማስወገድ ትክክል ነውን? ትክክል አይደለም፡፡ ገና ላልዳነው ለእያንዳንዱ ሰው በመላው ዓለም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ አለብን፡፡
 

ታዲያ በስጋችን ፍጹማን ነን? 

በሐጢያተኞች ላይ ስንፈርድ የምንፈርደው ምግባሮቻቸውን አይደለም፡፡ በፋንታው ለይተን የምናውቃቸው በዚህ የእውነተኛው ወንጌል ብርሃንና በእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡ ለእነርሱ እውነተኛው ብርሃን ምንድነው? ለእነርሱ ብርሃኑ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የእግዚአብሄር ልጆች መሆን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ለዚህ ዓለም ብርሃን ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ ማለት ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቻቸው ነጻ የወጡ በምግባሮቻቸው ፍጹማን ናቸው ማለት ነውን? በእርግጥም በልቦቻቸው ፍጹማን ናቸው፡፡ በስጋቸው ግን ፈጽሞ ደካሞች ናቸው፡፡
በስጋችን ሁላችንም ራስ ወዳዶች፣ ብቁዓን ያልሆንንና ደካሞች ነን፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ግን የእርሱ ፍጹማን ሕዝብ ነን፡፡ ምግባሮቻቸው ብቁ ያልሆኑ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው ወይስ አይደሉም? እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምናምን መንፈሳዊ ደህንነታችን ፍጹም የሆነልን የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ በሌላ አነጋገር ፍጹማን የሆኑት በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በማመን የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበሉ ሰዎች ምግባሮች ሳይሆኑ ደህንነታቸው ነው፡፡ ያዳነን እምነታችን ፍጹም ስለሆነ በእግዚአብሄር ጸጋ እርስ በርሳችን መወያየት እንችላለን፡፡ ውሳኔያችን ላይ የደረስነው ትክክለኛ በሆነው የሰማያዊ፣ የሐምራዊና የቀይ ማግ እውነት በመሆኑ እምነታችንና ፍርዳችን ፈጽመው የተሳሳቱ አይደሉም፡፡
እግዚአብሄር ይህንን የፍርድ መለኪያ ሁልጊዜም በካህናቶቹ ላይ እንድናደርግ ነግሮናል፡፡ የዚህን ዓለም ሕዝብ በሙሉ በልቦቻችን መያዝ አለብን፡፡ ነፍሳቸውን ማቀፍ፣ ለእነርሱ መጸለይና የውሃውንና የመንፈሱንም ወንጌል በትክክል ለእነርሱ ማሰራጨት አለብን፡፡ ሁልጊዜም የፍርዱን ደረት ኪስ በልቦቻችን ውስጥ መያዝ ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ዛሬም፣ ነገም፣ ሁልጊዜም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንሰብክላቸው ዘንድ ሐጢያተኞችን ሁሉ ሐጢያት የሞላባቸው ስለመሆናቸው መፍረድ አለብን፡፡
ይህ የእምነት እውነት በልባችሁ ውስጥ ይገኝ ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡ ይህ እውነት በልቦቻችሁ ውስጥ ካለ ሁሉን የመፍረድ መብት ተሰጥቶዋችኋል ማለት ነው፡፡ በዚህ የእውነት ቃል ታመኑ፡፡ በዚህ መንገድ ሁልጊዜም በእግዚአብሄር ቃል ላይ ተመርኩዛችሁ ፍርድን ስጡ፡፡ ሁልጊዜም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሙሉ ልባችሁ አምናችሁ አሰራጩት፡፡
እኔ በየቀኑ በልቤ ላይ ያለውን ይህንን የፍርድ ደረት ኪስ በማስታወስ በእግዚአብሄር ፊት እያንዳንዱን ነገር እፈርዳለሁ፡፡ ወንጌልን በማሰራጨትም እቀጥላለሁ፡፡ በእርግጥ ድግግሞሽ ወንጌልን ለማሰራጨት እጅግ ውጤታማው መንገድ ነው፡፡ እኛ እንረሳለን፡፡ ፔዳጎጂስቶች በድግግሞሽ የሚሰጥ ሥነ ትምህርት እጅግ ትውፊታዊና ውጤታማ የሥነ ትምህርት መንገድ እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ የቋንቋ ምሁር አንድ ሕጻን ልጅ ቃሉን ከአንድ ሺህ ጊዜያቶች በላይ በመደጋገም በትክክል ሊናገረው እንደሚችል ገልጦዋል፡፡ ልክ እንደዚሁ የውሃውንና የመንፈሱን ቃል እውነት በቀጣይነትና በተደጋጋሚ ስናሰራጭ በልባችን ውስጥ ይታተማል፡፡ እኔ ሰዎች መጽሐፎቻችንን በሚያነቡበት ጊዜ የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት በግልጥ እንዲረዱትና እንዲያኑበት ይህንን የወንጌል እውነት በተደጋጋሚ ጽፌያለሁ፡፡ ይህንን የእውነት ወንጌል መስበካችንን የምንቀጥለው ለዚህ ነው፡፡
ወንድሞችና እህቶች እኛ ቅዱሳን እርስ በርሳችን ስለ እምነታችን መመስከር አለብን፡፡ እምነታችንን ስንመሰክርና የእግዚአብሄርን ጸጋ እርስ በርሳችን ስንከፋፈል ልቦቻችን በእርግጥም እርስ በርሳቸው ይገናኛሉ፡፡ የተሳሳተ ዕውቀት ወይም መረዳት ይዘን ከሆነም ሊስተካከል ወይም ሊሻሻል ይችላል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደግ የምንችለው በዚህ አማካይነት ነው፡፡ እምነታችን ሲያድግ የእምነት ሕይወታችንም ወደፊት ይገሰግሳል፡፡ ስህተት የሆነ ነገር ምን ያህል ጊዜ አስበናል? ቀደም ያለው ዕውቀታችን ምን ያህሉ የተሳሳተ ነው? በተጨባጭ ሲታይ ምን ያህሉ ክፍል በጽንሰ አሳብ ላይ የተመሠረተ ነው? የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከማወቃችን በፊት የነበሩን አመኔታዎቻችን ሁሉ በጽንሰ አሳብ ላይ የተመሠረቱ ብቻ ነበሩ፡፡ 
ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱ ከያዘው ወንጌል ውጭ አንዳች ሌላ ወንጌል የሚሰብክ ማንኛውም ሰው የተረገመ እንደሆነ ተናግሮዋል፡፡ (ገላትያ 1፡6) ጳውሎስ ከእግዚአብሄር እውነት ውጭ የሚያውቀውን ሁሉ እንደ አቧራ እንደቆጠረውም ተነግሮዋል፡፡ ነገር ግን በዘመኑ ከርስትና ውስጥ ረብ የለሽ በሆነው ሐይማኖታዊ ዕውቀታቸው የሚኩራሩ ብርቱዎች ይሆናሉ፡፡
በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በማመን የዳንን ሰዎች እርስ በርሳችን ስለምንግባባ በልቦቻችን መስማማት እንችላለን፡፡ በዚህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አናፍርም፡፡ ምክንያቱም ይህ እውነት ከዘላለማዊው የሲዖል ቅጣት አድኖናልና፡፡ በፋንታው በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ውስጥ የተደበቀውን የወንጌል እውነት ያለ ምንም ማመንታት ለዓለም ሁሉ እንሰብካለን፡፡ በአስቸኳይ ልንፈጽመው የሚገባን ተልዕኮ ይህ ነው፡፡
ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቸኛው እውነት እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳውቅ እጅግ ደንግጫለሁ! ‹‹አሃ ይኸው ነው! ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ አላወቅሁትም ነበር፡፡ በመላው ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይህንን ያውቃሉን? የቃለ እግዚአብሄር ምሁራንስ ስለዚህ ነገር ይናገራሉን?›› ከቃለ እግዚአብሄር ምሁራን መካከል ይህንን እውነት ያወቀና የሰበከ አንድ ሰው ባገኝ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ስለዚህ በውስጣቸው ጥቂት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ፍንጭ እንዳለ ለማግኘት በክርስትና ውስጥ ያሉትን የቃል እግዚአብሄር ትምህርት ቤት ቅርንጫፎች ሁሉ እስከምችለው ድረስ መረመርሁ፤ ነገር ግን ከንቱ ልፋት ነበር፡፡
ይህንን የወንጌል እውነት ከተረዳሁ በኋላ መጀመሪያ የጸለይሁት ጸሎት የሚከተለው ነበር፡- ‹‹ጌታ ሆይ በዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምናለሁ፡፡ በጥምቀትህ ሐጢያቶቼን ሁሉ እንደወሰደህ፣ በመስቀል ላይ እንደሞትህ፣ ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳህና አሁን እንዳዳንከኝ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ጌታ ሆይ በዚህ ዓለም ሁሉ ላይ የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ገና ይህንን እውነት አላወቁም፡፡ ይህንን እውነት በመላው ዓለም ላሰራጨው፡፡ የቀድሞውን ወንጌል ልክ ባለበት ሁኔታ እንድሰብከው ፍቀደልኝ፡፡››
አብራችሁን ከምትሠሩት ከእናንተ ሠራተኞቼ ጋር መገናኘቴ ድንቅ የሆነ በረከት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የማይሰሙና የማያምኑ አንድ ሺህ ሰዎችን ከመገናኘትና ከማስተማር ይልቅ እግዚአብሄርን ከሚሹ ጥቂት እውነት ፈላጊዎች ጋር መገናኘት የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት ለእነርሱ መስበክ፣ በእርሱ በማመንና ልክ እንደዚህ ከእነርሱ ጋር አብሮ ማገልገል በጣም የተሻለ ነው፡፡ ሁላችሁም በቃሉ ስለምታምኑ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ!
በዚህ ዓለም ላይ እንደ እናንተና እንደ እኔ ደስ የሚላቸው ሰዎች ጥቂቶች መሆናቸው እውነት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እንደ እኛ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ያሉት ማነው? እነዚህ ነገሮች ሁሉ በትክክል የተገኙት ከእውነት አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን የከበሩ በረከቶች ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ያሉ በረከቶችን ሰጥቶን ሳለ፣ እግዚአብሄር እንዲህ ያለ ክቡር ደህንነት ሰጥቶን ሳለና እግዚአብሄር እንዲህ ያለውን የከበረ ክህነት ሰጥቶን ሳለ እንዴት ለእርሱ ወንጌል አንሠራም? እንዴት ሐጢያተኞችን አንፈረድም? የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌልስ እንዴት አናሰራጭም? ወንጌልን ስናሰራጭስ እንዴት የሐጢያቶችን ስርየት ያገኙትን ካላገኙት መለየት አንችልም? እግዚአብሄር ሰማያትንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ ብርሃንን ከጨለማ እንደለየ ሁሉ እኛም በግልጥ ሐጢያተኞችን ከጻድቃን እንለያለን፡፡ እግዚአብሄር እውነትን ከውሸት ጋር ስንቀላቅል አይደሰትም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አለ፡- ‹‹የዘራኸው ዘርና ከወይኑ የወጣው አንድ ሆነው እንዳይጠፉብህ በወይንህ ቦታ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፡፡ በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ፡፡ ከተልባ እግርና ከበግ ጠጉር በአንድነት የተሠራ ልብስ አትልበስ፡፡›› (ዘዳግም 22፡9-11) ሐጢያተኞችን መለየትና በግልጥ ፍርዳቸውን መስጠት የሚኖርብን ለዚህ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ቃል የሰሙ ከምርጫዎቻቸው ጋር ባይስማማም እውነት መሆኑን ያምኑበት ዘንድ ጊዜው አሁን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል የሚያምኑ በጸጋው የዓለም ብርሃን ይሆናሉ፡፡ የማያምኑ ግን ከጨለማ ማምለጥ አይችሉም፡፡ ኡሪምና ቱሪም ማለትም ‹‹ብርሃንና ፍጽምና›› የሆነው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመናችን ነው፡፡ እኛ በእግዚአብሄር ሙሉ በሙሉ ከሐጢያት የዳንን ሰዎች ሆነናል፡፡
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄር ልጆች ሆናችኋልን? በዚህ ዓለም ላይ የነገሥታት ንጉሥ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይድረሰውና አሁን የንጉሥ ክህነትን ሥራዎች እየሠራን ሕይወታችንን በመኖር ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን የደህንነት ወንጌል ስለሰጠን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ሳለ የንጉሣዊ ክህነት ተግባሮቻችንን በስኬት እንድናከናውን ያስችለን ዘንድ ወደ እግዚአብሄር እጸልያለሁ፡፡ 
ሐሌሉያ! አምላካችንን ለዘላለም አመሰግነዋለሁ፡፡