Search

Проповеди

ርዕስ 3፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል

[3-3] ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፡1-12)

ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፡1-12)
(1ኛ ዮሐንስ 5፡1-12)
“ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን። ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፦ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።”
 
 
ኢየሱስ የመጣው በምንድነው?
በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ
 
ኢየሱስ በውሃ መጥቷልን? አዎን መጥቶዋል። በጥምቀቱ መጥቷል። ውሃው የሚያመላክተው በዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ የሆነውን የኢየሱስ ጥምቀት ነው። ይህም የዓለምን ኃጢያቶች በሙሉ የወሰደበት የቤዛነት ጥምቀት ነበር።
ኢየሱስ በደም መጥቶዋልን? አዎን መጥቶዋል። እርሱ የሰው ሥጋ ለብሶ መጣና የዓለምን ኃጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ ተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስም የኃጢያትን ደመወዝ ሁሉ ከፈለ። ኢየሱስ የመጣው በደም ነው።
ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ መጥቶዋልን? አዎ መጥቶዋል። ኢየሱስ እግዚአብሔር ነበር፣ ነገር ግን የኃጢአተኞች አዳኝ ለመሆን በሥጋ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ መጣ።
ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ እንደመጣ አያምኑም። ኢየሱስ በእርግጥም የነገሥታት ንጉሥና የአማልክቶች እግዚአብሔር መሆኑን የሚያምኑ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። አብዛኛው ሕዝብ አሁንም ድረስ ‘ኢየሱስ በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ወይስ የሰው ልጅ?’ ጥርጣሬ አላቸው። ብዙዎች፣ የሥነ መለኮት ምሁራንና አገልጋዮችን ጨምሮ፣ ኢየሱስን እግዚአብሔር፣ አዳኝ፣ እና ፍጹም ሕላዌ ከመሆን ይልቅ እንደ ሰው ያምናሉ።
እግዚአብሔር ግን ኢየሱስ የነገሥታት ንጉሥ፣ እውነተኛ እግዚአብሔርና እውነተኛ አዳኝ መሆኑን የሚያምን ማንኛውም ሰው ከእርሱ እንደተወለደ ተናግሮዋል። እግዚአብሔርን የሚወዱ ሰዎች ኢየሱስንም ይወዳሉ፣ በእውነት በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎችም በተመሳሳይ መንገድ በኢየሱስ ይወዳሉ።
ሰው ዓለምን ማሸነፍ አይችልም። ስለዚህ ሐዋርያው ዮሐንስ ዓለምን ማሸነፍ የሚችሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ብቻ እንደሆኑ ነገረን። ታማኞች ዓለምን ማሸነፍ የሚችሉት በኢየሱስ ውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ እምነት ስላላቸው ነው። ዓለምን የማሸነፊያው ሐይል ከሰው ፈቃድ፣ ጥረት ወይም የጋለ ስሜት ሊፈልቅ አይችልም።
“በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም” (1ኛ ቆሮንቶስ 13፡1-3)። እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘ፍቅር’ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ የመጣውን ኢየሱስን ማለት ነው።
 
 
በውሃውና በደሙ የሚያምን ሰው ብቻ ዓለምን ሊያሸንፍ ይችላል
 
ዓለምን ማሸነፍ የሚችለው ማነው?
በኢየሱስ ጥምቀት፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ቤዛነት የሚያምን ሰው ነው
 
1ኛ ዮሐንስ 5፡5-6 እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ።”
አጋር ክርስቲያኖች ሰይጣንንና ዓለምን ያሸነፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። በኢየሱስ ውሃ፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ቃል የሚያምኑ ሰዎችም እንደዚሁ ዓለምን ማሸነፍ ይችላሉ። ኢየሱስ ዓለምን ያሸነፈው እንዴት ነበር? በውሃው፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ቤዛነት አማካይነት ነበር።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ውሃ’ የሚያመለክተው ‘የኢየሱስን ጥምቀት’ ነው (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)። ኢየሱስ በሥጋ ወደዚህ ዓለም መጣ። የዓለምን ኃጢአተኞች ለማዳን መጣ፤ የኃጢአተኞችን ሁሉ ኃጢአቶች ለመውሰድም ተጠመቀና እነዚያን ኃጢአቶች ለማስተሰረይ በመስቀል ላይ ሞተ።
በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም እርሱ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም የመምጣቱን እውነታ የሚያመለክት ነው። እርሱ ኃጢአተኞችን ለማዳን በሰው ሥጋ ምሳሌ መጣ፣ በውሃም ተጠመቀ። ስለዚህ ኢየሱስ በውሃና በደም ወደ እኛ መጣ። በሌላ አነጋገር የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ በጥምቀቱ ውሃና በሞቱ ደም ወሰደ።
ሰይጣን ዓለምን የገዛው እንዴት ነበር? ሰይጣን የሰው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል እንዲጠራጠር በማድረግ በልቦቻቸው ውስጥ የአለመታዘዝ ዘሮችን ተከለ። በሌላ አነጋገር ሰይጣን እነርሱን የእግዚአብሔርን ቃል እንዳይታዘዙ በማሳት ሰዎችን የእርሱ አገልጋዮች አድርጎ ለወጣቸው።
ሆኖም ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መጣና በጥምቀቱ ውሃና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ የሰዎችን ኃጢአቶች በሙሉ ደመሰሰ። እርሱ ሰይጣንን አሸነፈና የዓለምንም ኃጢአቶች በሙሉ ደመሰሰ።
ይህ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአተኞች አዳኝ ስለነበር ነው። በውሃና በደም ስለመጣም አዳኛችን ሆነ።
 
 

ኢየሱስ በቤዛነት ጥምቀቱ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ወሰደ

 
የኢየሱስ ዓለምን ማሸነፍ ምን ማለት ነው?
ይህ ማለት የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ወስዶዋል ማለት ነው።
 
ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ለመውሰድ ስለተጠመቀና እነርሱንም ለማስተሰረይ ስለሞተ ከኃጢአቶቻችን ሁሉ ሊያድነን ቻለ። ኢየሱስ የሰዎች ሁሉ ወኪል በሆነው በመጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ስለተጠመቀ የዓለም ኃጢአቶች በሙሉ ወደ እርሱ ተላልፈዋል። የኃጢአትን ደመወዝ ለመክፈልም በመስቀል ላይ ሕይወቱን ሰጠ። እርሱ በሞቱና በትንሳኤው የሰይጣንን ሐይል አሸነፈ። እርሱ የኃጢአቶቻችንን ደመወዝ በሞቱ ከፈለ።
 
 

ኢየሱስ በጥምቀቱ ውሃና በመስቀሉ ደም ወደ ኃጢአተኞች መጣ

 
ሐዋርያው ዮሐንስ ቤዛነት በውሃ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በውሃውና በደሙ የሚገኝ እንደሆነ ተናገረ። ስለዚህ ኢየሱስ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ስለወሰደና ኃጢአቶቻችንንም ለዘላለም ስላስወገደ ኃጢአተኞች በሙሉ በእርሱ በማመንና ለቃሎቹ ታማኝ በመሆን ከኃጢአት ይድናሉ።
 
ኢየሱስ የሰይጣንን ሐይል ያሸነፈው እንዴት ነበር?
በጥምቀቱ፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ
 
ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ወሰደ። እርሱ በዮርዳኖስ ጥምቀቱ ኃጢአቶቻችንን ሁሉ ወሰደ፣ በመስቀል ላይም የእነዚያን ኃጢአቶች ዋጋ ከፈለ፤ በሞቱ ለኃጢአቶቻችን ከፈለ። ‘የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው’ (ሮሜ 6፡23) የሚለው የእግዚአብሔር ጻድቅ ሕግ ትንቢትም ተፈጸመ።
ኢየሱስ ዓለምን ማሸነፍ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ዓለምን የሚያሸንፈው እምነት ኢየሱስ በውሃውና በደሙ በለገሰን የቤዛነት ወንጌል የሚያምን እምነት ነው። እርሱ በሥጋ መጥቶ በጥምቀቱ ውሃና በመስቀል ላይ ሞቱ መዳንን መሠከረ።
ኢየሱስ ዓለምን ማለትም ሰይጣንን አሸነፈ። የጥንቷ ቤተክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ለሮም ንጉሠ ነገሥት ወይም ለማናቸውም የዚህ ዓለም ፈተናዎች ሳያጎበድዱ በሰማዕትነት ፊት እንኳን ጸንተው ቆሙ።
ይህ ሁሉ ኢየሱስ በውሃና (እርሱ የዓለምን ኃጢአቶች ለመውሰድ ተጠምቆዋል) በመስቀል ላይ በደሙ (በሞቱ የኃጢአቶቻንን ሁሉ ደመወዝ ከፍሎዋል) መጣ የሚል እምነታቸው ውጤት ነበር።
ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ መጣ (የሰው ሥጋ ለብሶ መጣ)፣ እና ቤዛነትን የምናገኝ ሁሉ ዓለምን ማሸነፍ እንችል ዘንድ የኃጢአተኞችን ኃጢአቶች በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ወሰደ።
 
 
ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)
 
የመዳን ምሳሌ ምንድነው?
የኢየሱስ ጥምቀት
 
በ1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ላይ እንዲህ ተባለ፦ “ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፣ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው።” ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ አዳኝ እንደነበርና በውሃ ጥምቀትና በደም እንደመጣ መሰከረ።
ከዚህ የተነሣ በውሃና በደም በመጣው ኢየሱስ ማመን አለብን። የኢየሱስ ጥምቀት ውሃም እንደዚሁ የመዳናችን ምሳሌ እንደሆነ ማወቅ ይገባናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ የጥምቀት ‘ውሃ’ ‘ደም’ እና ‘መንፈስ ቅዱስ’ በቤዛነት ውስጥ ‘ወሳኝ ጉዳዮች’ እንደሆኑ ነገረን።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳቸውም የኢየሱስን ጥምቀት ሳያምኑ በመስቀሉ ደም ብቻ አላመኑም። በደሙ ብቻ ማመን ማለት የእውነተኛውን እምነት ግማሽ ብቻ መያዝ ማለት ነው። በግማሽ ወይም ባልተሟላ እውነት ላይ የተመሠረተ እምነት ከጊዜ ጋር ይደበዝዛል። ነገር ግን በውሃው፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች እምነት ከጊዜ ጋር እየጠነከረ ይሄዳል።
ሆኖም በዚህ ዘመን በዓለም ላይ የመስቀሉ ደም ወንጌል ድምጽ ብቻ እየጠነከረና እየጠነከረ እየሄደ ነው። ይህ ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሰዎች የእውነትን ቃል፣ ማለትም የውሃውንና የመንፈስ ቅዱስን ቤዛነት ስለማያውቁ፣ ዳግም ሊወለዱ አይችሉም።
በአንድ ወቅት የምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት የአጉል እምነት ሰለባ ሆኑ። ለተወሰነ ጊዜ የበለፀጉ ይመስሉ ነበር፣ የሰይጣን አገልጋዮች ግን እምነታቸውን ወደ አጉል እምነት ለመቀየር ረድተዋል።
አጉል እምነት አንድ ሰው በወረቀት ወይም በእንጨት ላይ መስቀልን ከሳለ ዲያብሎስ እንደሚሸሽ እና በኢየሱስ ደም ካመነ ሰይጣን እንደሚባረር ማመን ነው። ሰይጣን በእነዚህና በሌሎች የአጉል እምነት አመኔታዎች አማካይነት ሰዎች ማመን ያለባቸው በኢየሱስ ደም ብቻ እንደሆነ እንዲያምኑ አሳታቸው። ሰይጣን ኢየሱስ ለኃጢአተኞች ደሙን እንዳፈሰሰ በመናገር ደሙን እንደሚፈራ ያስመስላል።
ነገር ግን ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት እውነተኛውን የኢየሱስ ጥምቀት ወንጌልና የመስቀሉን ደም መሰከሩ። ሆኖም በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች የሚመሰክሩት ምንድነው? የሚመሰክሩት የኢየሱስን ደም ብቻ ነው።
እኛ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፉት ቃሎች ልናምንና በመንፈስ ቅዱስ፣ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ መዳን ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል። የኢየሱስን ጥምቀት ችላ ብለን ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተልን የመሆኑን እውነታ ብቻ የምንመሰክር ከሆነ መዳናችን የተሟላ ሊሆን አይችልም።
 
 
ለእግዚአብሔር መዳን ‘የምስክርነት ቃል’
 
እግዚአብሔር እንዳዳነን ማረጋገጫው ምንድነው?
ውሃው፣ ደሙና መንፈስ ቅዱስ
 
1ኛ ዮሐንስ 5፡8 ላይ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና።” በመጀመሪያው መንፈስ ቅዱስ ነው፣ ሁለተኛው የኢየሱስ ጥምቀት ውሃ ነው፣ ሦስተኛው የመስቀሉ ደም ነው። እነዚህ ሦስቱ ነገሮች በሙሉ አንድ ናቸው። ኢየሱስ ከኃጢአታችን ሊያድነን ወደዚህ ዓለም መጣ። እርሱ ከሦስቱ ከጥምቀት፣ ከደምና ከመንፈስ ቅዱስ ሁሉ ጋር ብቻውን ይህንን አደረገ።
“የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና።” እግዚአብሄር እንዳዳነን የሚያረጋግጡ ሦስት ነገሮች አሉ። እነዚህ የሚመሰክሩት ሦስት ነገሮች የኢየሱስ ጥምቀት ውኃ፣ ደሙና መንፈስ ቅዱስ ናቸው። እነዚህ ሦስት ነገሮች ኢየሱስ በዚህ ዓለም ላይ ለእኛ ያደረጋቸው ናቸው።
ከእነዚህ ሦስት ነገሮች አንዱ እንኳን ቢጎድል መዳን ሙሉ አይሆንም ነበር። የሚመሰክሩት ሦስት ናቸው፦ እነርሱም መንፈስ፣ ውሃና ደም ናቸው።
በሥጋ ወደ እኛ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር፣ መንፈስና ወልድ ነው። እርሱ በሰው ሥጋ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ወደዚህ ዓለም ወረደ፣ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ለመውሰድ በውሃ ውስጥ ተጠመቀ። ኃጢአቶችን ሁሉ በሥጋው ወሰደና በመስቀል ላይ እስከ ሞት ድረስ በመድማት እኛን ኃጢአተኞችን አዳነን። እርሱ ሙሉ በሙሉ ለኃጢአቶቻችን ከፈለ። ይህ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ የሆነ የተሟላ የቤዛነት ወንጌል ነው።
ከእነዚህ አንዱ እንኳን ቢጎድል እኛን ከኃጢአቶቻችን ሁሉ ያዳነንን የእግዚአብሔርን መዳን እምቢኝ ማለት ይሆን ነበር። ሆኖም ዛሬ ብዙሃኑ ምዕመናን የሚመሰክሩትና የሚያምኑት የደሙንና የመንፈስ ቅዱስን ወንጌል ብቻ ነው።
ሐዋርያው ዮሐንስ ግን ሦስት የሚመሠክሩ ነገሮች እንዳሉ ተናግሮዋል፦ እነርሱም የኢየሱስ ጥምቀት ውሃ፣ በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደምና መንፈስ ቅዱስ ናቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ በምስክርነቱ በጣም ግልጽ ነበር።
ኃጢአተኛውን የሚዋጀው እምነት የመንፈስ ቅዱስ፣ የውሃውና የደሙ እምነት ነው። ሰው ዓለምን እንዲያሸንፍ የሚያስችለው እምነት የት ነው? እዚሁ ነው። በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ በመጣው ኢየሱስ ማመን ነው። በዚህ እመኑና መዳንንና የዘላለምን ሕይወት ተቀበሉ።
 
ያለ ኢየሱስ ጥምቀት የእግዚአብሔር መዳን ፍጹም ነው?
አይደለም
 
ዳግመኛ ከመወለዴ ከረጅም ጊዜ በፊት እኔም ደግሞ በመስቀሉ ደምና መንፈስ ቅዱስ ብቻ ያመንሁ ክርስቲያን ነበርሁ። እርሱ እኔን ከኃጢአቶቼ ሁሉ ለማዳን መንፈስ ቅዱስ ሆኖ እንደመጣና በመስቀል ላይም ለእኔ እንደሞተ አመንሁ። ያመንሁት በእነዚህ ሁለት ነገሮች ብቻ ነበር፣ ይህን ግማሽ እምነት ለሰዎች ሁሉ ለመስበክ በቂ ትዕቢተኛ ነበርሁ።
ኢየሱስ እንዳደረገው ለሰዎች ልሠራና ልሞት ሚሽነሪ እሆን ዘንድ የሥነ መለኮት ትምህርት ለመማር እቅድ ነበረኝ። ታላላቅ ነገሮችን ሁሉ አቅጄ ነበር።
ነገር ግን ያመንሁት በሁለት ነገሮች ብቻ ስለነበር በልቤ ውስጥ ሁልጊዜም ኃጢአት ነበረ። ከዚህ የተነሳ ዓለምን ማሸነፍ አልቻልሁም። ከኃጢአትም ነጻ መሆን አልቻልሁም። በደምና በመንፈስ ቅዱስ ብቻ አምኜ በነበረ ጊዜ በልቤ ውስጥ ገናም ኃጢአት ነበረብኝ።
በኢየሱስ ያመንሁ ብሆንም ገናም በልቤ ውስጥ ኃጢአት የነበረበት ምክንያቱ ስለ ውሃው ማለትም ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ስለማላውቅ ነበር። በኢየሱስ ጥምቀት ውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ባለኝ የተሟላ እምነት እስከምድን ድረስ መዳኔ የተሟላ አልነበረም።
የሥጋ ኃጢአቶችን ማሸነፍ ያልቻልኩበት ምክንያት የኢየሱስን ጥምቀት ትርጉም ስለማላውቅ ነበር። አሁንም እንኳን ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ያምናሉ፣ ነገር ግን አሁንም የሥጋ ኃጢአቶችን ይሠራሉ። አሁንም ድረስ በልባቸው ውስጥ ኃጢአቶች አሉ፣ ለኢየሱስ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር ለማነቃቃትም ይሞክራሉ።
እነርሱ የመጀመሪያውን የግለት ስሜታቸውን ማነቃቃት አይችሉም፣ ምክንያቱም በውሃው ሙሉ በሙሉ ከኃጢአቶቻቸው በጭራሽ አልነጹም። ኃጢአቶቻቸው በሙሉ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እርሱ እንደተላለፉ አይገነዘቡም፣ ከውድቀት በኋላም እንደገና እምነታቸው እንዲያገግም ማድረግ አይችሉም።
ይህንን ለሁላችሁም ግልጽ ማድረግ እወዳለሁ። በኢየሱስ ስናምን በእምነት መኖርና ዓለምን ማሸነፍ እንችላለን። ሆኖም እንኳን ደካማ ብንሆንም፣ በዚህ ዓለም ላይ ምንም ያህል ብዙውን ጊዜ ኃጢአት ብንሠራም በጥምቀቱ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነጻ ያደረገንን ኢየሱስን አዳኛችን አድርገን እስካመንን ድረስ በድል አድራጊነት መቆም እንችላለን።
ነገር ግን የጥምቀቱን ውሃ ሳናምን በኢየሱስ የምናምን ከሆነ፣ ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣት አንችልም። ሐዋርያው ዮሐንስ ዓለምን የሚያሸንፈው እምነት በጥምቀት ውሃ እና ደምና መንፈስ ቅዱስ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ እምነት እንደሆነ ነገረን።
እግዚአብሄር በጥምቀትና በደሙ የሚያምኑትን ሰዎች ለመዋጀት አንድያ ልጁን ላከ። ኢየሱስ በጥምቀቱ ኃጢአቶቻችንን ሁሉ አስወገደ። የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ (በሰው ሥጋ) ወደ እኛ መጣ። ከዚያም የኃጢአትን ደመወዝ ለመክፈል በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ። በዚህም ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአት አርነት አወጣ።
ዓለምን ወደ ማሸነፍ የሚመራን እምነት የሚመጣው ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአቶች ሁሉ ነጻ ባወጣን በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ የመጣ የመሆኑን እውነት ከማመን ነው።
የኢየሱስ ጥምቀት ውሃና የመስቀሉ ላይ ደም ባይኖሩ ኖሮ እውነተኛ መዳንም ባልኖረ ነበር። አንዱ ወይም ሌላው ባይኖር እውነተኛ መዳን ሊኖረን ባልቻለም ነበር። ያለ ውሃው፣ ደሙና መንፈሱ ቅዱስ እውነተኛ መዳን ላይ መድረስ አይቻልም። ስለዚህ በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ ቅዱስ ማመን ይኖርብናል። ይህንን እወቁ፣ እውነተኛ እምነትም ይኖራችኋል።
 
 
የውሃው፣ የደሙና የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት የሌለው መዳን እውነተኛ መዳን እንዳልሆነ እነግራችኋለሁ
 
ለመዳን የሚመሰክሩት ሦስቱ አስፈላጊ ነገሮች ምንድናቸው?
ውሃው፣ ደሙና መንፈስ ቅዱስ
 
አንድ ሰው የላይኛውን ጥያቄ እንዲህ ብሎ ያስበው ይሆናል፦ “ኢየሱስ አዳኜ ነው። በመስቀሉ ላይ ደም አምናለሁ፣ ሰማዕት ሆኜ መሞትም እፈልጋለሁ። በልቤ ውስጥ ኃጢአት ቢኖርም በኢየሱስ አምናለሁ። በትጋት ንስሐ ገብቻለሁ፣ በየቀኑም ጥሩ፣ ቀናና መሐሪ በሆነ መንገድ ለመሥራት ጥረት አድርጌአለሁ። ሕይወቴንና ያለኝን ዓለማዊ ሐብት በሙሉ ለአንተ ሰጥቻለሁ። ትዳር አልመሠረትኩም። እግዚአብሔር እንዴት ሊያውቀኝ አይችልም? ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞቶልኛል። ቅዱሱ እግዚአብሔር የሆነው ኢየሱስ ሰው ሆኖ በመውረድ በመስቀል ላይ ለእኛ ሞቷል። በአንተ አመንሁ፣ ለአንተም መሥዋዕት ሆንሁ፣ ለአንተም በታማኝነት ሥራዬን ሠራሁ። ብቁ ባይሆንም እና አሁንም በልቤ የተወሰነ ኃጢአት ቢኖረኝም፣ ለዛ ኢየሱስ ወደ ገሃነም ይልካኛል? አይ፣ አይሰደኝም።”
በዚህ መንገድ የሚያስቡ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ለመውሰድ እንደተጠመቀ አያምኑም። በኢየሱስ የሚያምኑ ገናም ኃጢአት ያለባቸው እነዚህ ሰዎች የት ይሄዳሉ? ወደ ገሃነም ይሄዳሉ። እነርሱ ኃጢአተኞች ናቸው!
እንዳሻቸው የሚያስቡና እግዚአብሔር እንደ እነርሱ ማሰብ እንዳለበት የሚገምቱ ሰዎች ወደ ገሃነም ይሄዳሉ። ከዚህም በላይ አንዳንዶች ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ኃጢአቶችን በሙሉ ስለወሰደ በዓለም ላይ ኃጢአት የለም ይላሉ። ይህ ግን ስለ ደሙና መንፈስ ቅዱስ ብቻ መናገር ነው። ይህ ሰዎችን ሙሉ ወደሆነ ቤዛነት የሚመራ እምነት አይደለም።
ኢየሱስ በጥምቀቱ ኃጢአቶቻችንን እንደወሰደ፣ በኃጢአቶቻችን ምክንያት ለመፍረድ በመስቀል ላይ እንደሞተ፣ እና ከሞቱ በኋላ በሦስተኛው ቀን እንደተነሳ ማመን ይገባናል።
ይህ እምነት ሳይኖር የተሟላ መዳን አይገኝም። ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ ሞተ፣ ተነሣም። ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ መጣ። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአቶች ሁሉ አስወገደ።
የሚመሰክሩ ሦስት ዋና ነገሮች አሉ፦ እነርሱም መንፈስ ቅዱስ፣ ውሃና ደም ናቸው።
በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነና የሰው ሥጋ ለብሶ እንደወረደ ይመሰክራል።
ሁለተኛው ነገር ‘የውሃው’ ምስክር ነው። ውሃው ኃጢአቶቻችን ወደ ኢየሱስ የተላለፉበት በዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ የሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ነው። ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ኃጢአቶቻችን በሙሉ ወደ እርሱ ተላልፈዋል (የማቴዎስ ወንጌል 3፡15)።
ሦስተኛው ምስክር ‘ደም’ ነው፣ ይህም አዲስ ሕይወትን የሚያመለክትና ኢየሱስ የኃጢአቶቻችንን ፍርድ በኛ ፋንታ የሚቀበልበትን ይወክላል። ኢየሱስ ስለ እኛ ሞተ፣ በእኛ ምትክ የአባቱን ፍርድ ተቀበለ፣ ከሞቱም በኋላ በሦስተኛው ቀን ተነሣ።
እግዚአብሔር አብ ለቤዛነታችን ምስክር ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን በልጁ ጥምቀትና ደም በሚያምኑ ሰዎች ልቦች ውስጥ ልኮዋል።
ዳግም የተወለዱት ሰዎች ዓለምን የሚያሸንፉበት የመዳን ቃል አላቸው። ቤዛነትን ያገኙት ሰይጣንን፣ የሐሰተኛ ነቢያቶችን ውሸቶችና መሰናክሎች ወይም ያለ ማቋረጥ የሚያጠቁዋቸውን የዓለም ግፊቶች ያሸንፋሉ። እኛ ይህ ሐይል ሊኖረን የቻለበት ምክንያት በልባችን ውስጥ ሦስት ነገሮች ስላሉን ነው፦ እነርሱም የኢየሱስ ውሃ፣ ደሙና መንፈስ ቅዱስ ናቸው።
 
ዓለምንና ሰይጣንን የምናሸንፈው እንዴት ነው?
በሦስቱ ምስክሮች በማመን
 
በመንፈስ ቅዱስ፣ በውሃና በደም ስለምናምን ሰይጣንንና ዓለምን ማሸነፍ እንችላለን። በኢየሱስ ጥምቀትና ደም የሚያምኑ ሰዎች የሐሰተኛ ነቢያቶችን ሁሉ ማሸነፍ ይችላሉ። በምናሸንፍበት በዚህ ሐይል ላይ ያለን እምነታችን ያረፈው በውሃው፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ነው። በዚህ ታምናላችሁን?
በኢየሱስ ጥምቀት፣ በደሙ እና ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና አዳኛችን መሆኑን በማመን በኩል በሚገኘው ቤዛነት ላይ እምነት ከሌላችሁ ዳግም ልትወለዱም ሆነ ዓለምን ልታሸንፉ አትችሉም። በልባችሁ ውስጥ ይህ እምነት አለ?
በልባችሁ ውስጥ መንፈስ ቅዱስና ውሃው አሉ? ኃጢአቶቻችሁ በሙሉ ወደ ኢየሱስ እንደተላለፉ ታምናላችሁ? በልባችሁ ውስጥ በመስቀል ላይ ደም አለ?
በልባችሁ ውስጥ የኢየሱስ ጥምቀት ውሃ ካለ፣ እንዲሁም ኢየሱስ ለእናንተ በመስቀል ላይ እንደሞተና ለእናንተ ፍርድን እንደተቀበለ የምታምኑ ከሆነ አለምን ታሸንፋላችሁ።
ሐዋርያው ዮሐንስ ዓለምን ያሸነፈው እነዚህ ሁሉ ሦስት አስፈላጊ ነገሮች በልቡ ውስጥ ስላሉ ነበር። እርሱም በሥራቸው መሰናክሎችንና ዛቻዎችን ለሚታገሱት በእምነት ወንድሞቹ ሁሉ ስለ ቤዛነት ተናግሯል። እርሱ እንዲህ በማለት መሰከረ፦ “እናንተም ደግሞ ዓለምን ማሸነፍ የምትችሉት እንደዚህ ነው። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ፣ በውሃና በደም መጣ። እርሱ ዓለምን እንዳሸነፈ በመንፈስ ቅዱስ፣ በውሃና በደም የሚያምኑ ሰዎችም ዓለምን ማሸነፍ ይችላሉ። እምነት ያላቸው ዓለምን የሚያሸንፉበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው።”
በ1ኛ ዮሐንስ 5፡8 ላይ እንዲህ ይላል፦ “የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፦ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ።” ብዙዎች አሁንም ስለ ደምና መንፈስ ቅዱስ ይናገራሉ፣ ነገር ግን የኢየሱስን የጥምቀት ውሃ ይተዋሉ። ‘ውሃውን’ ካስወገዱ፣ አሁንም በሰይጣን ተታልለዋል። ከራሳቸው የራስ-ማታለል ጀርባ መውጣትና ንስሐ መግባት አለባቸው፤ የኢየሱስን ጥምቀት በመቀበል፣ በ‘ውሃው’ ማመን ለዳግም መወለድ አስፈላጊ ነው።
ማንም ሰው በኢየሱስ ውሃና ደም ሳያምን ዓለምን ማሸነፍ አይችልም። ደግሜ እላችኋለሁ ማንም አይችልም! የኢየሱስን ውሃና ደም እንደ ብርቱ መሣሪያዎቻችን አድርገን በመጠቀም መዋጋት ይኖርብናል። የእርሱ ቃል የመንፈስ ቅዱስ ሰይፍ ብርሃንም ነው።
አሁንም ድረስ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ባነጻው የኢየሱስ ጥምቀት የማያምኑ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። አሁንም ድረስ በሁለት ነገሮች ብቻ የሚያምኑ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ኢየሱስ ‘ተነስተው እንዲያበሩ’ ሲነግራቸው ፈጽሞ ማብራት አይችሉም። አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ኃጢአት አለባቸው። በኢየሱስ ቢያምኑም አሁንም መጨረሻቸው ገሃነም ነው።
 
 
ሰዎች መስማት፣ ማመንና መዳን እንዲችሉ የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ወንጌል በእርግጠኝነት መመስከር አለበት
 
በኢየሱስ ጥምቀት ላይ ያለን እምነት የዶግማ ዓይነት ብቻ ነውን?
አይደለም፣ ዶግማ አይደለም። እውነቱን ነው።
 
ወንጌልን ስንመሰክር ግልጽ መሆን አለበት። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ፣ በጥምቀትና (ኃጢአቶቻችንን በሙሉ በወሰደበት) በደም (ለኃጢአቶቻችን ሁሉ ዋጋ በከፈለበት) መጣ። በእነዚህ በሦስቱ ሁሉ ማመን አለብን።
ካለመንን እየሰበክን ያለነው ወንጌልን ሳይሆን ቀለል ያለ ሐይማኖትን ነው። በዚህ ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ክርስትናን እንደ ሐይማኖት ይጠሩታል። ነገር ግን ክርስትና እንደ ሐይማኖት ሊመደብ አይችልም። ክርስትና በእውነት ላይ የተመሠረተ የቤዛነት እምነት፣ ወደ እግዚአብሔር ቀና ብሎ የመመልከት እምነት ነው። ሐይማኖት አይደለም።
ሐይማኖት በሰው የተፈጠረ ነገር ሲሆን፣ እምነት ግን እግዚአብሔር የሰጠንን መዳን ወደ ላይ ተመልክቶ የሚያይ ነው። ይህ ነው ልዩነቱ። ይህንን እውነት ችላ ካላችሁ ክርስትናን እንደ ሌላ ሐይማኖት ብቻ ትቆጥሩታላችሁ፣ በሞራልና በሥነ ምግባር አማካኝነትም ትሰብካላችሁ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ላይ ሐይማኖትን ለመመሥረት አልመጣም። እርሱ ፈጽሞ ክርስትና የሚባል ሐይማኖት አልመሠረተም። ክርስትና ሐይማኖት ነው ብላችሁ የምታምኑት ለምንድነው? ሁሉም አንድ አይነት ከሆነ ለምን በቡድሃ ሐይማኖት አታምኑም? ይህንን በማለቴ የተሳሳትሁ ይመስላችኋል?
አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን እንደ ሐይማኖት አድርገው ያምናሉ፣ በመጨረሻም እንዲህ ይላሉ፦ “ልዩነቱ ምንድነው? መንግሥተ ሰማያት፣ ኒርቫና፣ ገነት… ሁሉም አንድ ዓይነት ነገር ናቸው፣ ስሞቻቸው ብቻ ነው የተለያየው። በመጨረሻ ሁላችንም አንድ ቦታ ላይ እንደርሳለን።”
አጋር ክርስቲያኖች በእውነት ላይ ጸንተን መቆም አለብን። ‘ተነስተን ማብራት’ አለብን። ያለ ምንም ማመንታት እውነቱን መናገር መቻል አለብን።
አንድ ሰው “ያ ወደ ሰማይ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ሊሆን አይችልም” ሲል እናንተ ግልጽ በሆነ መንገድ “አይደለም! ብቸኛው መንገድ ያ ነው፤ ሰማይ መሄድ የምትችለው በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ስታምን ብቻ ነው” ልትሉት ይገባችኋል። ሌሎች ነፍሳቶች የቤዛነትን ቃል እንዲሰሙ፣ ዳግም እንዲወለዱና ሰማይ እንዲገቡ በጣም ብሩህ ሆናችሁ ማብራት ይገባችኋል።
 
 
ትክክለኛ እምነት ይኑራችሁ፦ የኢየሱስን ጥምቀትና የደሙን ቤዛነት የማያውቁ፣ ኢየሱስን አንድ ወገን ፍቅር የሚወዱ ሰዎች ይጠፋሉ
 
በኢየሱስ ቢያምኑም የሚጠፉት እነማን ናቸው?
በኢየሱስ ጥምቀት የማያምኑት ሰዎች ናቸው
 
ኢየሱስን በዘፈቀደ ስለማመን መናገር ለኢየሱስ ምላሽ የማይሰጥ ፍቅር መያዝና እውነትን እንደ ተራ ሐይማኖት የመቁጠር ያህል ነው።
ፓስፊክን የሚያቋርጥ አንድ መርከብ ሰምጦ ጥቂት የተረፉ ሰዎች በጎማ መንሳፈፊያ ላይ ሲንሳፈፉ ቆዩ። የአደጋ ጥሪ ምልክትም ላኩ፣ ነገር ግን በማዕበል የሚናጠው ባህር ሌሎች መርከቦች እነርሱን ለማዳን እንዳይመጡ ከለከላቸው። ከዚያም በምትኩ አንዲት ሔሊኮፕተር መጣችና ገመድ ወረወረች።
ከእነርሱ አንዱ ገመዱን በሰውነቱ ላይ በመጠምጠም ፋንታ በእጆቹ ይዞት ቢቀር፣ ከኢየሱስ ጋር ምላሽ በማይሰጥ ፍቅር ውስጥ እንደወደቀ ሰው ይሆናል፤ እንደፈለገ በእግዚአብሔር ያምናል፣ ነገር ግን ገና አልዳነም። እርሱ አሁንም ደህንነት የለውም፣ ነገር ግን እንዲህ ይላል፦ “አምናለሁ። አድነኝ። አምናለሁ፣ ስለዚህ እድናለሁ ብዬ አስባለሁ።”
የኢየሱስን ጥምቀትና የደሙን እውነት የማያስተውል ሰው ገመዱን ብቻ በመያዝ እንደሚድን ያምናል።
ነገር ግን ወደ ላይ ሲጎተት፣ እጆቹ በገመዱ ላይ ያላቸውን መያዝ ያጣሉ። በራሱ ኃይል ብቻ ይይዛል። ያ ኃይል ሲያልቅ፣ መያዙን ያጣልና ወደ ውቅያኖሱ ተመልሶ ይወድቃል።
ይህ ከኢየሱስ ጋር ምላሽ በማይሰጥ ፍቅር ውስጥ መሆን ምን እንደሚመስል ነው። ብዙዎች በእግዚአብሔርና በኢየሱስ እናምናለን፤ በመንፈስ ቅዱስ በመጣው ኢየሱስ እናምናለን ይሉ ይሆናል፣ ይህ ግን የሙሉ ስሌቱ አንድ ክፍል ብቻ ነው። እነርሱ ፍጹም በሆነው ወንጌል በእውነት ማመንም ሆነ በውስጡ መኖርም አይችሉም፣ ስለዚህ በእርሱ እንደሚያምኑ ደጋግመው ለመናገር ራሳቸውን ያስገድዳሉ።
ማመንና ለማመን መሞከር ተመሳሳይ ነገር አይደለም። እነርሱ ኢየሱስን እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚከተሉት ይናገራሉ፣ ነገር ግን በልቦቻቸው ውስጥ በቀሩት ኃጢአቶች ምክንያት በመጨረሻው ቀን ይጣላሉ። ኢየሱስ በጥምቀቱ፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ እንደመጣ ሳያውቁ ይወዱታል። ኢየሱስን የሚወዱት ስለ ደሙ ብቻ ከሆነ ገሃነም ይወርዳሉ።
ነፍሳችሁን እውነተኛ ወንጌል በሆነው የጥምቀት ውሃና በመስቀሉ ደም ቃል እሰሩዋት። ኢየሱስ የመዳንን ገመድ ወደ ታች ሲወረውር ራሳቸውን በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ የሚያስሩ ሰዎች ይድናሉ።
በሔሊኮፕተሩ ላይ ያለው ነፍስ አድን ሰው በድምጽ ማጉያ “እባካችሁ በጥንቃቄ አድምጡኝ። ገመዱን ወደ ታች ስወረውር፣ ከክንዶቻችሁ በታች በደረታችሁ ዙሪያ አስሩት። ከዚያም እንዳላችሁ ቆዩ። ገመዱን በእጆቻችሁ ይዛችሁ አትንጠልጠሉ። በደረታችሁ ዙሪያ አስሩትና ዘና በሉ። ያን ጊዜ ትድናላችሁ” በማለት ጮኸ።
እርሱ እነዚህን መመሪያዎች ከሰጠ በኋላ የመጀመሪያው ሰው መመሪያዎቹን ተከትሎ ራሱን በገመዱ አሰረና ዳነ። ሌላው ሰው ግን “አትጨነቅ። እኔ በጣም ጠንካራ ነኝ። በጤና ክለብ እየተለማመድኩ ነበር። ጡንቻዎቼን ማየት ትችላለህን? ለብዙ ማይሎች ተንጠልጥዬ መቆየት እችላለሁ” አለ። ከዚያም ገመዱ ወደ ላይ ሲሳብ፣ በእጆቹ ይዞ ተንጠለጠለ።
በመጀመሪያ ሁለቱም ሰዎች ወደ ላይ ተጎትተው ነበር። ነገር ግን ልዩነት አለ። አንዱ ሰው መመሪያዎቹን አድምጦ በደረቱ ዙሪያ ገመዱን አሰረና ያለ ምንም እንቅፋት ወደ ላይ ተጎተተ። ወደ ላይ ሲጎትት ሕሊናውን ስቶ እንኳን ቢሆን የሆኖ ሆኖ ወደ ላይ ተጎትቷል።
በጉልበቱ የተኩራራው ሰው ጉልበቱ ስለደከመ በመጨረሻ ጉልበቱ ስለሟጠጠ መያዙን አጣ። ለማዳመጥ ፈቃደኛ ስላልሆነና መመሪያዎቹን ችላ ስላለ ሞተ።
ማንም ሰው ሙሉ ቤዛነት ያገኝ ዘንድ ነፍሳትን ሁሉ ከኃጢአት ባዳነው በኢየሱስ የጥምቀት ውሃና ደም ቤዛነት ማመን አለበት። መዳን የሚሰጠው ከሙሉ ልባቸው በቃሉ ለሚያምኑ ሰዎች ነው፦ “እኔ ከመጥምቁ ዮሐንስ በተቀበልሁበት ጥምቀቴና በመስቀል ላይ እስከ ሞት ድረስ ባፈሰስሁት ደሜ ሙሉ በሙሉ አደንኋችሁ።”
በደሙ ብቻ የሚያምኑ ሰዎች “አትስጋ አምናለሁ። የኢየሱስን ደም እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ አመሰግናለሁ። ኢየሱስን እስከ መጨረሻው ድረስ እከተለዋለሁ፣ አለምንና የቀሪ ሕይወቴን ኃጢአቶች በሙሉ ለማሸነፍ በደሙ ላይ ያለኝ እምነቴ ብቻውን በቂዬ ነው” ይላሉ።
ሆኖም ይህ በቂ አይደለም። እግዚአብሔር እንደ ሕዝቡ የሚመሰክርላቸው ሰዎች በሦስቱ ነገሮች በሙሉ የሚያምኑ ናቸው፦ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እንደመጣና፣ እንደተጠመቀ (ኢየሱስ በዮርዳኖስ ጥምቀቱ ኃጢአቶችን ሁሉ ወስዶዋል)፣ የኃጢአቶችን ሁሉ ደመወዝ ለመክፈል በመስቀል ላይ እንደሞተ፣ እና ከሙታን እንደተነሣ።
መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው በሦስቱም ነገሮች በሙሉ በሚያምኑት ሰዎች ላይ ብቻ ነው፣ ለእነርሱም ይመሰክራል። “አዎ፣ እኔ አዳኛችሁ ነኝ። በውሃና በደም አዳንኳችሁ። እኔ አምላካችሁ ነኝ።”
ነገር ግን እግዚአብሔር በሦስቱም በሙሉ ለማያምኑ ሰዎች መዳንን አይሰጣቸውም። አንድ ነገር ብቻ ቢጎድልም እንኳን፣ እግዚአብሔር “አይደለም፣ አልዳናችሁም” ይላል። የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሁሉ በሦስቱም በሙሉ አመኑ። ኢየሱስ የእርሱ ጥምቀት የመዳን ምስክር፣ ደሙም ፍርድ እንደሆነ ተናግሮዋል።
 
 
ሐዋርያቱ ጳውሎስና ጴጥሮስም እንዲሁ ስለ ኢየሱስ ጥምቀትና ደም ሁለቱንም መሰከሩ
 
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመሰከሩት ስለ ምንድነው?
ስለ ኢየሱስ ጥምቀትና ደም
 
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ተናግሮዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት ምን ያህል ጊዜ እንደተናገረ እናይ። በሮሜ 6፡3 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” በ6፡5 ላይም እንዲህ ይላል፦ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።”
በገላትያ 3፡27 ላይም እንዲህ ይላል፦ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።” የኢየሱስ ሐዋርያት በሙሉ ስለ ‘ውሃው’ ማለትም የኢየሱስ ጥምቀት መሰከሩ። “ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል” (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)።
 
 

የጌታ የቤዛነት መዳን የመጣው በኢየሱስ ውሃና ደም አማካኝነት ነው

 
እግዚአብሔር ጻድቅ ብሎ የሚናገረው ማንን ነው?
በልቦቻቸው ውስጥ ምንም ኃጢአት የሌለባቸውን
 
ኢየሱስ ለሰው የለገሰው ቤዛነት የኢየሱስ ውሃ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ቤዛነት ነው። እኛም በዚያ ቤዛነት ተነሥተን ማብራት አለብን። እንዴት? እነዚህን ሦስት ነገሮች በመመስከር ነው።
“ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ” (ኢሳይያስ 60፡1)። እግዚአብሔር ብርሃኑን በእኛ ላይ አበራና እኛም እንድናበራ ይነግረናል። ይህንን ትዕዛዝ መታዘዝ አለብን።
እኛ ወንጌልን በሙሉ ሐይል መስበክ ይኖርብናል። ነገር ግን አሁንም ድረስ በጣም ብዙ ሰዎች አያዳምጡም። በኢየሱስ እመኑ ትቤዘናላችሁ። ጻድቃን ትሆናላችሁ። ገናም ኃጢአት በልባችሁ ውስጥ ካለ ገና ጻድቃን አልሆናችሁም። የዓለምን ኃጢአትም ገና አላሸነፋችሁም።
በኢየሱስ ውሃ (የኢየሱስ ጥምቀት) የማታምኑ ከሆነ በልባችሁ ውስጥ ያለውን ኃጢአት በጭራሽ ማስወገድ አትችሉም። በኢየሱስ ደም የማታምኑ ከሆነ በጭራሽ ከፍርድ ማምለጥ አትችሉም። በመንፈስ ቅዱስ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ የማታምኑ ከሆነ በጭራሽ መዳን አትችሉም። በሦስቱ ምስክርነቶች እስካላመናችሁ ድረስ በጭራሽ ሙሉ በሙሉ ጻድቃን ልትሆኑ አትችሉም።
ያልተሟላ ጽድቅ የሚመራው ወደ ‘ጽድቅ ተብዬ’ ብቻ ነው። ማንም ሰው ገና ኃጢአት እንዳለበት እያለ ራሱን ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ፣ እርሱ ገና በኢየሱስ ውስጥ አይደለም። በዚህ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ‘ጽድቅ ተብዬ’ ነገር አማካይነት ቤዛነት ላይ ለመንጠልጠል ይሞክራሉ። እነርሱ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብዙ የማይረቡ ጽሁፎችን ጽፈዋል።
እግዚአብሔር አሁንም ድረስ በልቡ ውስጥ ኃጢአት ያለበትን ሰው ኃጢአት አልባ ብሎ ይጠራዋልን? እግዚአብሔር ያንን አያደርግም። እግዚአብሔር ያየውን ያንን ይናገራል። እርሱ ሁሉን ቻይ ነው፣ ነገር ግን ፈጽሞ ሊዋሽ አይችልም። ሰዎች የጽድቅን እውነተኛ ትርጉም አይረዱትም። አንድን ነገር ‘ንጹህ’ ነው ብለን የምንጠራው ንጹህ ሲሆን ብቻ ነው። ኃጢአት እያለ ‘ንጹህ’ ብለን አንናገርም።
በልባችሁ ውስጥ ኃጢአት እያለ በኢየሱስ ጻድቃን ተብላችሁ እንደተጠራችሁ ታስቡ ይሆናል። ያ ስህተት ነው።
ኢየሱስ ጻድቃን ብሎ የሚያውጀው እርሱን በመንፈስ የመጣ፣ በውሃ የመጣ (በተጠመቀ ጊዜ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ወስዶዋል)፣ እና በደም የመጣ (በሥጋ መጥቶ ስለ እኛ ሞተ) አድርገን ስናምነው ብቻ ነው።
አጋር ክርስቲያኖች ‘ጽድቅ ተብዬ’ ነገር ከውሃውና ከደሙ ወንጌል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ‘ተብዬ’ ወይም ‘ጻድቅ ተብሎ መጠራት’ የሰው ልጅ የፈጠረው ትምህርት ነው። በልባችሁ ውስጥ ኃጢአት እያለባችሁ እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ ይቆጥራችኋልን? እግዚአብሔር አንድ ሰው በኢየሱስ በጽኑ ቢያምንም በልቡ ውስጥ ኃጢአት ካለው ጻድቅ አድርጎ አይቆጥረውም። ኢየሱስ በፍጹም አይዋሽም።
ሆኖም እርሱ በልቡ ውስጥ ኃጢአት ያለበትን ሰው ጻድቅ አድርጎ እንደሚቆጥረው አሁንም ታስባላችሁን? ያ ሰዎች የሚያስቡት እንጂ እግዚአብሔር የሚያስበው አይደለም። እግዚአብሔር ውሸቶችን ይጠላል። ‘በመንፈስ ቅዱስ’ እና ‘በደም’ ብቻ እያመናችሁ እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ ይቆጥራችኋልን? በጭራሽ አይደለም።
እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ የሚቆጥራቸው አንድ ዓይነት ሰዎች ብቻ አሉ። እነርሱም በልቦቻቸው ውስጥ ምንም ኃጢአቶች የሌሉባቸውን ሰዎች ነው። እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ የሚቆጥራቸው እነዚህን ሦስት ነገሮች በሙሉ የሚያምኑትን ብቻ ነው፦ አምላክ የሆነው ኢየሱስ በሥጋ ወደ ዓለም እንደመጣ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ እንደተጠመቀ፣ እና ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ለማጥፋት በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰ።
እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ የሚቆጥራቸው በቤዛነት የምሥራች የሚያምኑትን ብቻ ነው። ትክክለኛ አመኔታ ያላቸው እነርሱ ናቸው። እነርሱ እርሱ ለእኛ ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ አምነዋል። ኢየሱስ እንደመጣ፣ ኃጢአቶቻችንን ለመውሰድ እንደተጠመቀ፣ በመስቀል ላይ በመሞትም ስለ እኛ ፍርድን እንደተቀበለና ከሙታንም እንደተነሣ ያምናሉ።
እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተደረጉት ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሣ ነው። ኢየሱስ ከሰማይ ወርዶ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፡28)። ይህንን ያደረገው ኃጢአቶቻችንን በመውሰድ ነው።
እግዚአብሔር በኢየሱስ ደም ብቻ የሚያምኑትን አይቀበላቸውም። በኢየሱስ ደም ብቻ የሚያምኑ ሰዎች አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ኃጢአት አለባቸው።
ኢየሱስ የተቤዙ አድርጎ የሚያውቃቸው እነማንን ነው? “ወደዚህ ምድር በወረድሁና በመጥምቁ ዮሐንስ በተጠመቅሁ ጊዜ ኃጢአቶቻችሁን ሁሉ ወሰድሁ። የዓለም ኃጢአቶች በሙሉ ወደ እኔ እንደተላለፉ እመሰክራለሁ። በመስቀል ላይም የኃጢአቶችን ዋጋ ከፈልሁ። እንዲህም አዳንኋችሁ።” በኢየሱስ ጥምቀት፣ በደሙና እግዚአብሔር በመሆኑ እውነታ ማመን ሁሉም ለመዳን አስፈላጊ ናቸው።
ኢየሱስ በሦስቱም በሙሉ ለሚያምኑ ሰዎች እንዲህ ይላል፦ “አዎ ድናችኋል። እናንተ ጻድቃንና የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ።” በኢየሱስ ጥምቀት በደሙና በመንፈስ ቅዱስ በአንድ ላይ የምታምኑ ከሆነ ትድናላችሁ። በኢየሱስ ደምና መንፈስ ብቻ የሚያምኑ ሰዎች አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ኃጢአት አለ።
በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ አንድ እውነት ብቻ አለ። ፍትህ፣ ታማኝነት፣ ፍቅርና ደግነት አለ። አንድም የውሸት ነጥብ የለም። ውሸቶችና ተንኮሎች በመንግሥተ ሰማይ አይኖሩም።
 
‘ህግ አልባነትን የሚፈጽም’ ማነው?
በኢየሱስ ጥምቀት የማያምን ሰው
 
“በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን፥ ይሉኛል” (ማቴዎስ 7፡22)።
እግዚአብሄር እነዚያን የሰው ሥራዎች በፍጹም አይቀበላቸውም። “የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” (ማቴዎስ 7፡23)።
“ሁለት ቤቶችን አቀረብኩልህ። ሕይወቴንም እንኳን ለአንተ ሰጠሁ። አታየኝምን? እኔ እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሴ ድረስ ፈጽሞ አልካድኩህም። አታየኝምን?” 
“ስለዚህ በልብህ ውስጥ ኃጢአት አለን?” 
“አዎ ጌታ፣ ሆይ ጥቂት አለኝ።” 
“እንግዲያውስ ከእኔ ራቅ። ማንም ኃጢአተኛ እዚህ እንዲገባ አይፈቅድለትም።” 
“ነገር ግን ሰማዕት ሆኜ ሞቻለሁ!”
“‘ሰማዕት ሆኜ ሞቻለሁ’ ስትል ምን ማለትህ ነው? የሞትከው በግትርነትህ ብቻ ነው። ጥምቀቴንና ደሜን እውቅና ሰጥተሃልን? አንተ ሕዝቤ እንደሆንህ ፈጽሞ መስክሬአለሁን? አንተ ሕዝቤ እንደሆንህ ለልብህ መስክሬአለሁን? አንተ በእኔ ጥምቀት አላመንህም፣ እኔም አንተ ሕዝቤ እንደሆንህ ፈጽሞ አልመሰከርኩም፣ ነገር ግን እምነትህ ላይ ተንጠልጥለህ ለዚያ አመኔታህ ሞትክ። መቼ ነው እኔ ለአንተ የመሰከርኩት? ይህንን በራስህ ላይ ያመጣኸው አንተው ነህ። የራስህን ቤዛነት ለማግኘት ወደድህና ብቻህንም ሞከርህ። ገባህ? አሁን መንገድህን ቀጥል።”
ኢየሱስ ተነሥተን እንድናበራ ነገረን። የተዋጁ ሰዎች በብዙ ውሸታም ክርስቲያኖችና በብዙ ሐሰተኛ ነቢያቶች ፊት ይሸማቀቁናብሩህ ሆነው ማብራት ይሳናቸው ይሆናል! ነገር ግን ትንሽ ነበልባል ትልቅ እሳት ማስነሣት ትችላለች። አንድ ሰው በድፍረት ተነሥቶ እውነትን ቢመሰክር መላው ዓለም ይበራል።
በኢሳይያስ 60፡1-2 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ብርሃንሽ መጥቶአልና የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ አብሪ። እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።”
የውሸትና የሐሰት ወንጌል ጨለማ ምድርን ስለሚሸፍን፣ እግዚአብሔር ተነሥተን እንድናበራ አዘዘን። ኢየሱስን ሊወዱት የሚችሉት በእርሱ የሚያምኑት ብቻ ናቸው። ያልተዋጁ ሰዎች ፈጽመው ኢየሱስን መውደድ አይችሉም። እነርሱ እንዴት ኢየሱስን ሊወዱ ይችላሉ? እነርሱ ስለ ፍቅር ብቻ ያወራሉ፣ ነገር ግን እስካላመኑ ድረስ እርሱን በእውነት ሊወዱት ፈጽሞ አይችሉም።
 
 
ለኃጢአተኞች መዳን ምስክሮች የሚሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ
 
በልባችን ውስጥ ያለው የመዳን ምስክር ምንድነው?
የኢየሱስ ጥምቀት
 
“የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፦ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ።” ኢየሱስ ወደ ምድር መጣና በውሃና በደም ሥራውን ሰራ። ይህንን አደረገና አዳነን።
“የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም” (1ኛ ዮሐንስ 5፡9-12)።
ዳግም የተወለዱት የሰዎችን ምስክርነት ይቀበላሉ። እኛ ጻድቃን እንደሆንን እውቅና ይሰጠናል። ቤዛነትን ያገኙ ዳግም የተወለዱ ሰዎች ስለ ቤዛነት እውነት ሲናገሩ፣ ሰዎች ሊቃወሙት አይችሉም። ይቀበሉታል። እነርሱ እኛ በትክክል እንደምናምንና በእምነታችንም ትክክል እንደሆንን ይናገራሉ። እንዴት ዳግም እንደተወለድን ብንነግራቸው የምንመሰክረውን እውነተኛ ወንጌል ማንም መቃወም አይችልም። እነርሱ እኛ ትክክል እንደሆንን ይናገራሉ። እኛ ዳግመኛ የተወለድን የሌሎችን ምስክርነት እንቀበላለን።
ነገር ግን ይህ ምንባብ እንደዚህም ደግሞ ይላል፦ “የእግዚአብሔር ምስክር ይበልጣል፤ የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና።” ቃሉ የእግዚአብሔር ምስክር ስለ ልጁ ነው ይላል። ትክክል? የእግዚአብሔር ልጅ ምስክር ምንድነው? እግዚአብሔር እንዳዳነን ምስክሩ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ፣ በቤዛነት ውሃና በመስቀል ላይ ደሙ መምጣቱ ነው። እግዚአብሔር እኛን ያዳነበት መንገድ ይህ እንደሆነና እኛም በዚህ ስለምናምን የእርሱ ልጆች እንደሆንን ይመሰክራል።
“በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።”
ይህ ምንባብ የዳኑት እነማን እንደሆኑ በግልጽ ይነግረናል። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሰው በራሱ ውስጥ ምስክር እንዳለው ይናገራል። በልብህ ውስጥ ምስክር አለህ? ይህ በአንተም በእኔም ውስጥ አለ። ኢየሱስ ስለ እኛ ወደ ምድር መጣ። (እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በማርያም ሰውነት በኩል በሥጋ መጣ።) 30 ዓመት ሲሆነው ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ለመውሰድ ተጠመቀ። ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ይዞ በመስቀል ላይ ተፈረደበት። የዘላለም ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ በሦስተኛው ቀን ተነሣ። ኢየሱስ ያዳነን እንዲህ ነው።
እርሱ ትንሣኤን ባያገኝ ኖሮ ምን ይከሰት ነበር? እንዴት በመቃብር ውስጥ ሆኖ ለእኔ ሊመሰክር ይችል ነበር? ይህ ነው እርሱ አዳኜ የሆነበት ምክንያት። የምናምነውም ይህንን ነው።
እርሱ እንዳለው ሁሉ፣ በጥምቀቱና በደሙ አድኖናል። እኛም ስለምናምን እናንተና እኔ ድነናል። ምስክሩ በእኔም ውስጥ በእናንተም ውስጥ አለ። የዳኑ ሰዎች የእርሱን የጥምቀት ‘ውሃ’ ፈጽሞ ቸል ሊሉት አይችሉም። እርሱ እኛን ለማዳን ያደረጋቸውን ነገሮች በፍጹም አንገድፋቸውም።
“አሁንስ ፍቀድልኝ፥ እንደዚህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” (ማቴዎስ 3፡15)። ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ ባጠመቀው ጊዜ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ በዮርዳኖስ እንደወሰደ ፈጽሞ አንክድም። የተዋጁ ሰዎች የኢየሱስን ጥምቀት ‘ውሃ’ በፍጹም ሊክዱት አይችሉም።
 
 
የሚያምኑ ነገር ግን ያልተዋጁ ሰዎች የኢየሱስን ጥምቀት እስከ መጨረሻው ድረስ ይክዱታል
 
እግዚአብሔርን ሐሰተኛ የሚያደርገው ማነው?
በኢየሱስ ጥምቀት የማያምን ሰው ነው
 
ሐዋርያው ዮሐንስ “በእግዚአብሔር የማያምን እርሱን ሐሰተኛ አድርጎታል” ባለ ጊዜ እንዴት ትክክል ነበረ። ሐዋርያው ዮሐንስ አሁን እዚህ ቢኖር ኖሮ ለእኛ ለክርስቲያኖች ምን ይነግረን ነበር? እርሱ ምናልባት ‘ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ወስዷልን?’ ብሎ ይጠይቀን ነበር።
መጥምቁ ዮሐንስም አሁን በኖረ ኖሮ፣ ኢየሱስ እኛን በጥምቀቱ ስለተቤዠበት ወንጌል አይመሰክርምን? “እርሱ በእኔ በተጠመቀ ጊዜ ኃጢአቶቻችሁ ወደ ኢየሱስ ራስ አልተላለፉምን፣ እርሱስ ኃጢአቶቻችሁን አልተሸከመምን?” ስለዚህ እርሱ “ኢየሱስ ሁላችንንም ለማዳን እንደተጠመቀ” በግልጽ ይመሰክር ነበር።
በእግዚአብሔር የማያምኑ ማለትም እኛን ለማዳን ባደረገው በእያንዳንዱ ነገር የማያምኑ ሰዎች እርሱን ውሸታም ያደርጉታል። እኛ ኢየሱስ ሲጠመቅ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ወሰደ ስንል እነርሱ “ኦ ውድዬ! እርሱ ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ሊወስድ አይችልም! እርሱ የወሰደው የመጀመሪያውን ኃጢአት ብቻ ነው፣ ስለዚህ የቀን ተቀን ኃጢአቶቻችን በሙሉ አሁንም ድረስ አሉ” ይላሉ።
እነርሱ ‘ለመዳን በየቀኑ መናዘዝና የአሁኑን ኃጢአቶች የንስሐ መግለጽ አለብን’ ብለው ይሟገታሉ። የሚያምኑት ይህንን ነው። እናንተስ የምታምኑት ይህንን ነውን? ኃጢአቶቻችን በኢየሱስ ጥምቀት እንደተወገዱ የማያምኑ ሰዎች እግዚአብሔርን ውሸታም ያደርጉታል።
 
 
ኢየሱስ ሲጠመቅና በመስቀል ላይ ሲደማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዋጀን
 
የሚዋሸው ማነው?
በኢየሱስ ጥምቀት የማያምን ሰው
 
ኢየሱስ ተጠመቀና ኃጢአቶችንም ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ወሰደ። እግዚአብሔር በኢየሱስ ጥምቀትና ደም የሚያምኑትን ሰዎች ያድናል፣ የማያምኑትን ግን ይተዋቸዋል። እነርሱ ገሃነም ይወርዳሉ። ስለዚህ መዳናችን ወይም አለመዳናችን የተመሠረተው በምናምነው ነገር ላይ ነው። ኢየሱስ ከዓለም ኃጢአቶች ሁሉ አዳነን። የሚያምኑ ሰዎች ይድናሉ፣ የማያምኑ ሰዎች ግን እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ስላደረጉት አይድኑም።
ሰዎች ገሃነም የሚወርዱት በድክመቶቻቸው ምክንያት ሳይሆን ስለማያምኑ ነው። “በእግዚአብሔር የማያምን እርሱን ሐሰተኛ አድርጎታል” (1ኛ ዮሐንስ 5፡10)። ኃጢአቶቻቸው በሙሉ ወደ ኢየሱስ እንደተላለፉ የማያምኑ ሰዎች አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ኃጢአት አለባቸው። ኃጢአት እንደሌለባቸው ሊናገሩ አይችሉም።
አንድ ጊዜ አንድ ዲያቆን አገኘሁና ጠየቅሁት፦ “ዲያቆን፣ በኢየሱስ ባምን ኃጢአቶቼ ይሄዳሉን?” 
“በእርግጥ እንዲሁ ይሆናል።”
“እንግዲያውስ ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ወስዶ ተፈጸመ ስላለ ድነሃል። ይህ ትክክል አይደለምን?” 
“አዎ ድኛለሁ።”
“እንግዲያውስ ያለ ኃጢአት መሆን አለብህ።” 
“አዎ ነኝ።” 
“እንደገና ኃጢአት ብትሠራ ምን ይከሰታል?” 
“እኛ ሰዎች ብቻ ነን። እንዴት ዳግመኛ ኃጢአት ላንሠራ እንችላለን? ስለዚህ በየቀኑ ንስሐ መግባትና ኃጢአቶቻችንን ማጠብ አለብን።”
ይህ ዲያቆን ምሉዕ የሆነውን የቤዛነት እውነት ባለማወቁ አሁንም ድረስ በልቡ ውስጥ ኃጢአት አለ።
እርሱን የመሰሉ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚያፌዙና ሐሰተኛ የሚያደርጉት ናቸው። እግዚአብሔር የሆነው ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ማስወገድ ይሳነዋልን? በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው። ኢየሱስ ኃጢአቶችን በሙሉ ባያስወግድ ኖሮ እንዴት የመዳን እግዚአብሔር ሊሆን ይችል ነበር? እግዚአብሔርስ በእርሱ እንድናምን እንዴት ሊነግረን ይችል ነበር? እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ልታደርጉት ነውን? ያንን እንዳታደርጉ እመክራችኋለሁ!
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን እንዳናላግጥ ይነግረናል። ይህም ማለት እግዚአብሔርን ውሸተኛ አታድርጉት እና አታታሉትም። እግዚአብሔር እንደ እኛ አይደለም።
ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ቤዛነት ወንጌል በግልጽ ነግሮናል። ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ለእኛ ባደረጋቸው ነገሮች (ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ በመምጣቱ እውነታ) ማመን አይፈልጉም።
የተነገራቸውን የማያምኑ ሰዎች ካሉና እግዚአብሔር ያደረገልንን ነገሮች በሙሉ የሚያምኑ ሰዎች ካሉ (በእግዚአብሔር ፊት “እኔ ጻድቅ ነኝ” የሚሉ ሰዎችና፣ “እኔ ኃጢአተኛ ነኝ” የሚሉ ሌሎች) እውነትን እየተናገሩ ያሉት የትኞቹ ናቸው?
እግዚአብሔር ባደረጋቸው ነገሮች የማያምኑ፣ የውሃውን፣ የደሙንና የመንፈስ ቅዱስን ምስክር የማይቀበሉ ሰዎች እየዋሹ ነው። እነዚህ ሰዎች ሐሰተኛ እምነት አላቸው። የማያምኑ ሰዎች እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ያደርጉታል።
እግዚአብሔርን ሐሰተኛ አታድርጉት። ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጥቶ እንዲህ (በመጠመቅ) ጽድቅን ሁሉ ፈጸመ (የዓለምን ኃጢአቶች ወሰደ)።
 
 
ሐሳዊ ነፍስ የኢየሱስን ጥምቀትና ቅድስናውን ትክዳለች
 
ሰይጣንና ዲያብሎስ የሚክዱት ምንድን ነው?
የኢየሱስን ጥምቀትና ቅድስናውን
 
በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ምዕመን በውስጡ ምስክር አለው። የተቤዠ ሰው ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ኃጢአቶቹ ወደ እርሱ እንደተላለፉና በኢየሱስ ውሃና ደም እንደዳነ ያምናል። እነርሱ ኢየሱስ ማርያም ሰውነት በኩል ወደዚህ ዓለም እንደተወለደ፣ በመስቀል ላይ ከመሞቱም በፊት በዮርዳኖስ እንደተጠመቀና ትንሳኤን እንዳገኘ ያምናሉ።
ጻድቃን በልቦቻቸው ውስጥ ምስክር አላቸው። የመዳናችን ማረጋገጫው በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ በመጣው በኢየሱስ ላይ ያለን እምነታችን ነው። ምስክሩ በውስጣችሁ አለ። ‘በራሳችሁ ውስጥ ምስክር ይኑራችሁ።’ እላችኋለሁ፦ በውስጣችሁ የድኅነት ማረጋገጫ የሆነው ምስክር ከሌለ ይህ ድኅነት አይደለም፤ የድኅነት ማረጋገጫ በውስጣችሁ ነው።
ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ አለ፦ “በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው” (1ኛ ዮሐንስ 5፡10)። በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደም ብቻ ማመን ምስክር መያዝ ነውን? ወይስ በውሃ ማመን እንጂ በደም አለማመን ነውን? በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሦስቱን ምስክሮች በሙሉ ማመን አለባችሁ።
ኢየሱስ ‘ድናችኋል’ ብሎ የሚመሰክርላችሁ ያን ጊዜ ብቻ ነው። ከሦስቱ በሁለቱ (ደምና መንፈስ ቅዱስ) ብታምኑ ምስክር እንደሚኖራችሁ እየተናገራችሁ ነውን? ይህ በራሳችሁ መንገድ በእግዚአብሔር ማመን ይሆን ነበር። ይህ ‘ለራሳችሁ መመስከር’ ይሆን ነበር።
እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ከሦስቱ በሁለቱ ብቻ የሚያምኑ በጣም ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ አሉ። እነርሱ እንደዳኑ ይመሰክራሉ፣ ስለዚሁም መጽሐፎችን ይጽፋሉ። እንዴት አንደበተ ርቱዕ ናቸው! ይህ በጣም አስከፊ ነው። ራሳቸውን ‘ወንጌላውያን’ ብለው ይጠራሉ። እነርሱ ‘ወንጌላውያን’ ብቻ ሳይሆኑ ‘ሐይማኖተኞች’ እንደሆኑ ያስባሉ። በ‘ውሃው’ የማያምኑ አሉ፣ ነገር ግን አሁንም በድኅነታቸው ይመካሉ! እንዴት ሎጂካል ይሰማሉ! ነገር ግን የእግዚአብሔር ምስክር የላቸውም። ይህ መላ ምት ብቻ ነው።
ይህንን እንዴት ድኅነት ብላችሁ ልትጠሩት ትችላላችሁ? የእግዚአብሄርና የሰዎች ምስክር ያላቸው በመንፈስ ቅዱስ፣ በውሃና በደም በመጣው ኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና” (1ኛ ተሰሎንቄ 1፡5)። ሰዎች በኢየሱስ ደም ብቻ ሲያምኑ ሰይጣን ይደሰታል። “ኦ እናንተ ሞኞች በእኔ ተታላችኋል… ሃ-ሃ!” የኢየሱስን ደም ሲያመሰግኑ ሰይጣን ይሸሻል ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። እነርሱ ሰይጣን መስቀሉን ይፈራ ይሆናል ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ሰይጣን ሥራው ማስመሰል ብቻ እንደሆነ በአእምሮዋችሁ ልትይዙ ይገባል። በዚህ መሞኘት አይገባንም።
አጋንንት አንድን ሰው ሲገባ፣ ያ ሰው ሊረብሽና በአፉ አረፋ ሊያወጣ ይችላል። ይህ ለዲያብሎስ አስቸጋሪ ተግባር አይደለም። ዲያብሎስ ሰው ማንኛውንም ነገር እንዲያደርግ የሚያስችለው ሐይል አለው። ዲያብሎስ አእምሮውን ጥቂት ብቻ መጠቀም አለበት። እግዚአብሔር ለዲያብሎስ ከመግደል ሥልጣን ውጭ ሁሉንም አይነት ሥልጣኖች ሰጥቶታል። ዲያብሎስ አንድን ሰው እንደ ዛፍ ቅጠል እንዲንቀጠቀጥ፣ እንዲጮህና በአፉም አረፋን እንዲደፍቅ ሊያደርገው ይችላል።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ ምዕመናን “በኢየሱስ ስም ውጣ! ውጣ!” እያሉ ይጮሃሉ። ሰውየውም ወደ መልካም አእምሮው ሲመለስና ወደ መደበኛ ሁኔታው ሲመጣ፣ የኢየሱስ ደም እንደሆነ ሐይሉን የነበረው ይላሉ። ይህ ግን የደሙ ሐይል አይደለም። ይህ የዲያብሎስ ‘ማስመሰያ’ ብቻ ነው።
ሰይጣንና ዲያብሎስ በጣም የሚፈሩት በጥምቀቱ ያነጻን፣ በደሙም ስለ እኛ ፍርድን የወሰደውና በሦስተኛው ቀን የተነሣውን ኢየሱስ የሚያምኑትን ሰዎች ነው። ሰይጣን የኢየሱስን ጥምቀትና የደሙን ድኅነት የሚመሰክር ሰው አካባቢ ሊቆይ አይችልም።
እንደምታውቁት፣ የካቶሊክ ካህናቶች አንዳንድ ጊዜ ሰይጣንን ያባርራሉ። ይህንን በፊልሞች ውስጥ አይተናል። በ‘ዘ ኦሜን’ ፊልም ውስጥ፣ አንድ ካህን የእንጨት መስቀል ይይዛል እና ያወዛውዘዋል፣ ነገር ግን ካህኑ ይሞታል። ዳግም የተወለደ ሰው በዚህ መልኩ አይሸነፍም።
እርሱ ስለ ኢየሱስ ውሃና ደም በድፍረት ይናገራል። ዲያብሎስ ሊያሰቃየው ሲሞክር ዲያብሎስን “ኢየሱስ ኃጢአቶቼን በሙሉ እንደወሰደ ታውቃለህን?” ብሎ ይጠይቀዋል። ዲያብሎስ ከዚያ ይሸሻል። ዲያብሎስ ‘ዳግም በተወለደ ሰው’ ዙሪያ መሆንን ይጠላል። አንድ ‘ዳግም የተወለደ’ ሰው እዚያ ከተቀመጠ ዲያብሎስ ሊሸሽ ይሞክራል። በእግዚአብሔር የማያምኑ እርሱን ሐሰተኛ እንደሚያደርጉት ይነገራል። እነርሱ በልጁ ምስክር፣ በውሃውና በደሙ ምስክር አያምኑም።
 
የእግዚአብሔር ልጅ ምስክርነት ምንድነው?
ጥምቀቱ፣ ደሙ እና መንፈስ ቅዱስ
 
የእግዚአብሔር ልጅ ምስክር ምንድነው? እርሱ በመንፈስ መጥቶ በውሃ ኃጢአታችንን ያስወገደ መሆኑ ነው። የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደና በመስቀል ላይ ለእኛ ደሙን አፈሰሰ። ያ የውሃ፣ የደምና የመንፈስ ቅዱስ ቤዛነት አይደለምን?
ሰዎች የቤዛነት ወንጌል በሆነው በእውነተኛው የውሃና የደም ወንጌል ስለማያምኑ በእግዚአብሔር ፊት ይዋሻሉ። አመኔታዎቻቸው ውሸት ናቸው፣ እነርሱም እነዚህን ውሸቶች በከንቱ ያሰራጫሉ።
ወደ 1ኛ ዮሐንስ 5 እንመለስ። በ11ኛው ቁጥር ላይ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።” ይህ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን እና ይህ ሕይወት በተቀበለው ሰው ውስጥ እንዳለ ይነግረናል። እንዲሁም ይህ ሕይወት በእግዚአብሔር ልጅ ውስጥ ነው።
የዘላለምን ሕይወት የሚያገኙ ሰዎች በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመን የተዋጁ ሰዎች ናቸው። የተዋጁት የዘላለምን ሕይወት አግኝተው ለዘላለም ይኖራሉ። የዘላለምን ሕይወት ተቀብላችኋልን?
በ12ኛው ቁጥር ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ልጁ ያለው ሕይወት አለው፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።” በሌላ አነጋገር ወልድ በምድር ላይ ባደረጋቸው ነገሮች በጥምቀቱ፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሣኤው የሚያምን ሰው የዘላለም ሕይወት አለው። ነገር ግን ከእነዚህ አንዱን እንኳን የሚያስወግድ ሰው ሕይወት አይኖረውም፣ አይዋጅምም።
ሐዋርያው ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኢየሱስ ባደረጋቸው ነገሮች በውሃው፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ባላቸው እምነት ላይ ተመሥርቶ ለየ። እነዚህ ነገሮች እነርሱ በውስጣቸው ቃሉ እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው ይነግሩናል። እርሱ የዳኑትን በኢየሱስ የጥምቀት ውሃ፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ባላቸው አመኔታ ይለያቸዋል።
 
 
ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች በግን ከፍየል መለየት አይችሉም
 
የተዋጁትን ካልተዋጁት መለየት የሚችለው ማነው?
ዳግም የተወለደው ብቻ መለየት ይችላል
 
ሐዋርያው ዮሐንስ የተዋጁትን ጻድቃን ሰዎች በግልጽ ለያቸው። ሐዋርያው ጳውሎስም ደግሞ ይህንኑ አድርጓል። የእግዚአብሔር አገልጋዮች በበግ እና በፍየል መካከል መለየት የሚችሉት እንዴት ነው? እውነተኛ የሆኑትን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ከአስመሳዮች መለየት የሚችሉት እንዴት ነው? በውሃውና በኢየሱስ ደም በማመን የተዋጁ ሰዎች የማየት ሐይል ይቀበላሉ።
አንድ ሰው መጋቢ፣ ወንጌላዊ ወይም ሽማግሌ ቢሆን የተዋጁትን ሰዎች መለየት የማይችል ከሆነ ወይም በበግ እና በፍየል መካከል ልዩነት ማድረግ የማይችል ከሆነ፣ እርሱ ራሱ አልተዋጀም፣ በውስጡም ሕይወት የለውም። ነገር ግን በእውነት የተዋጁ ሰዎች ልዩነቱን በግልጽ ማየት ይችላሉ። በውስጣቸው ሕይወት የሌላቸው ሰዎች ልዩነቱን ማየትም ሆነ መቀበል አይችሉም።
በጨለማ ውስጥ ቀለማቶችን መለየትን ይመስላል። አረንጓዴ አረንጓዴ፣ ነጭም ነጭ ነው። ነገር ግን ዓይኖቻችሁን ብትጨፍኑ ቀለማቶችን ማየትም ሆነ ማወቅ አትችሉም።
ዓይኖቻቸው የተገለጡ ሰዎች ግን በቀለም ውስጥ ያለችውን በጣም ኢምንት ልዩነት እንኳን ማወቅ ይችላሉ። የትኛው አረንጓዴ የትኛው ደግሞ ነጭ እንደሆነ መናገር ይችላሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ በተዋጁትና ባልተዋጁት ሰዎች መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት አለ።
እኛ የቤዛነት ወንጌል የሆነውን የውሃውን፣ የደሙንና የመንፈስ ቅዱስን ወንጌል መስበክ ይኖርብናል። ተነስተን ማብራት አለብን። እውነተኛውን እምነት ለማሰራጨት ሰዎችን በዙሪያችን ስንሰበስብ በሰው ቃል አንናገርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 1ኛ ዮሐንስ 5 የዚህን ትርጉም ያብራራል። ግራ መጋባት እንዳይኖር ደረጃ በደረጃ ልናብራራው ይገባናል።
የምናስፋፋው ቃል ማለትም የኢየሱስ የውሃው፣ የደሙና የመንፈስ ቅዱስ ቃል የቤዛነት ብርሃን ነው። የኢየሱስን ‘ውሃ’ ለሰዎች ለማስተዋወቅ ብሩህ ሆነን ማብራት አለብን። የኢየሱስን ‘ደም’ ማሳወቅ ብሩህ ሆኖ ማብራት ነው። በምድር ላይ ይህንን እውነት የማያውቅ ሰው እንዳይኖር በጣም ግልጽ ልናደርገው ይገባናል።
የተዋጁ ሰዎች ተነስተው የማያበሩ ከሆነ ብዙ ሰዎች ቤዛነትን ሳያገኙ ይሞታሉ፣ እግዚአብሄርም አይደሰትም። እኛንም ሰነፍ አገልጋዮች ብሎ ይጠራናል። እኛ የኢየሱስን የውሃና የደም ወንጌል ማስፋፋት አለብን።
ራሴን ብዙ ጊዜ የምደጋግመው የኢየሱስ ጥምቀት ለደህንነታችን በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ለልጆች ስንናገር ማስተዋላቸውን ለማረጋገጥ ስንል እያንዳንዱን ነጥብ በመደጋገም ነገሮችን ደጋግመን ማብራራት ይኖርብናል።
አንድ መሃይም የሆነን ሰው ለማስተማር ስንሞክር ምናልባት የምንጀምረው ከሆሄ ነው። ከዚያም ቀስ በቀስ በዚህ ሆሄ እንዴት ቃላቶችን መጻፍ እንደሚችል እናስተምረዋለን። ‘ቅጣት’ የሚለውን አይነት ቃል መጻፍ ሲችል የእነዚህን ቃላቶች ትርጉም ልናብራራለት እንጀምራለን። ይህ በትክክል ሰዎች በእውነት እንዲረዱ ለማረጋገጥ ስለ ኢየሱስ ልንናገር የሚገባን መንገድ ነው።
የኢየሱስን ጥምቀት በግልጽ ማብራራት ይገባናል። እርሱ በውሃ፣ በደምና በመንፈስ ቅዱስ ወደዚህ ዓለም መጣ። ኢየሱስን አዳኛችሁ አድርጋችሁ በማመን እንድትድኑ እጸልያለሁ።
የውሃውና የመንፈሱ ቤዛነት የሚመነጨው በኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ ደሙና ኢየሱስ አምላክና አዳኛችን በመሆኑ አመኔታ ላይ ካለን እምነት ነው። 
 
ይህ ስብከት በየኤሌክትሮኒክ መጽሐፍት ቅርጸት ደግሞ ይገኛል። ከዚህ በታች ባለው የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ጠቅ ያድርጉ።
በውኑ በውሃውና በመንፈስ ቅዱስ ዳግም ተወልዳችኋልን? [አዲስ የተሻሻለ እትም]