Search

Проповеди

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[10-1] የንጥቀቱ ጊዜ መቼ እንደሆነ ታውቃላችሁን? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 10፡1-11 ››

የንጥቀቱ ጊዜ መቼ እንደሆነ ታውቃላችሁን?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 10፡1-11 ››
‹‹ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጎናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፡፡ ፊቱም እንደ ጸሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፡፡ የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ፡፡ ቀኝ እግሩንም በባህር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፡፡ እንደሚያገሳም አንበሳ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጎድጓድ በየድምጻቸው ተነገሩ፡፡ ሰባቱ ነጎድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፡፡ ከሰማይም ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን ነገር በማህተም ዝጋው፤ አትጻፈውም የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ በባህርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፡፡ ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፣ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፣ ባህርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ፡- ወደፊት አይዘገይም፤ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል አለ፡፡ ከሰማይም የሰማሁት ድምጽ እንደገና ሲናገረኝና፡- ሂድና በባህርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ፡፡ ወደ መልአኩም ሄጄ፡- ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት፡፡ እርሱም፡- ውሰድና ብላት፤ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች፤ በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ፡፡ ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት፡፡ በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፡፡ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ፡፡ በብዙ ወገኖችና በአህዛብም፣ በቋንቋዎችም፣ በነገሥታትም ላይ እንደገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ፡፡››
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
የዚህ ምዕራፍ መሰረተ አሳብ የሚገኘው በቁጥር 7 ላይ ነው፡፡ ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡›› በሌላ አነጋገር በዚህ ጊዜ ንጥቀት ይሆናል፡፡
 
ቁጥር 1፡- ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጎናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፡፡ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፡፡ ፊቱም እንደ ጸሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፡፡
በምዕራፍ 10 ላይ የተገለጠው ብርቱ መልአክ ሊመጡ ያሉትን የእርሱን ሥራዎች የሚመሰክር የእግዚአብሄር ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡ ይህ መልአክ የተገለጠው የእግዚአብሄር ግርማ ሞገስና ሥልጣን ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡ እግዚአብሄር የዚህን ዓለም ባህሮች እንደሚያጠፋና ቅዱሳንንም ከሙታን አስነስቶ ወደ ሰማይ እንደሚነጥቃቸው ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡
 
ቁጥር 2-3፡- የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ፡፡ ቀኝ እግሩንም በባህር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፡፡ እንደሚያገሳም አንበሳ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጎድጓድ በየድምጻቸው ተናገሩ፡፡
እግዚአብሄር ሁሉን ነገር በእቅዶቹ መሰረት ያከናውናል፡፡ የመጨረሻው ቀን ሲመጣ ምድርንና ባህርን ያጠፋል፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታችን የመጀመሪያውን ባህርና የመጀመሪያውን ምድር ያጠፋል፡፡
ይህ ምንባብ እግዚአብሄር ያቀዳቸውን ነገሮች ሁሉ ለመፈጸምና ሥራዎቹን ለማጠናቀቅ ያለውን ጠንካራ ፈቃድ ያሳያል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰባት ቁጥር የምልዓትን ፍቺ ይዞዋል፡፡ እግዚአብሄር ሥራዎቹን ሁሉ አጠናቆ ባረፈ ጊዜ ይህንን ቁጥር ተጠቅሞበታል፡፡ ልክ እንደዚሁ ይህም ምንባብ እግዚአብሄር በመጨረሻው ዘመን ብዙዎችን ከጥፋታቸው እንደሚያድናቸው በሌላ በኩል ግን ይህንን ዓለም በእርግጠኝነት እንደሚያጠፋው ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 4፡- ሰባቱ ነጎድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፡፡ ከሰማይም ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን ነገር በማህተም ዝጋው፤ አትጻፈውም የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡
እግዚአብሄር የቅዱሳንን ንጥቀት ካልዳኑት ሰዎች ለመደበቅ ዮሐንስን ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን እንዳይጽፍ አዘዘው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሄር ሥራዎቹን ከማያምኑ ሰዎች ይደብቃል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የእግዚአብሄር ጠላቶች ስለሆኑ የእርሱን ቅዱሳን ይጠላሉ፤ ያሳድዳሉም፡፡
እግዚአብሄር ዓለምን በውሃ ባጠፋበት በኖህም ዘመን እንደዚሁ መጭውን የውሃ ጥፋት የገለጠው ለኖህ ብቻ ነው፡፡ ዛሬም እንደዚሁ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመላው ዓለም በመስበክ መንግሥተ ሰማይን በዚህ ለሚያምኑ ሰዎች ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን እውነተኛ እምነት ካላቸው ከእነዚህ ውጪ ንጥቀት መቼ እንደሚመጣ ለሌላ ለማንም ሰው አልገለጠም፡፡ እግዚአብሄር በመንግሥቱ ውስጥ ለጻድቃን የሚሆን አዲስ ዓለም ፈጥሮዋል፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥም ከእነርሱ ጋር አብሮ ሊኖር ይሻል፡፡
 
ቁጥር 5-6፡- በባህርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፡፡ ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፣ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፣ ባህርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ፡- ወደፊት አይዘገይም፡፡
በሁሉም ነገር ላይ የሚደረገው የመጨረሻው መሃላ በአንድ ሰው የራስ ስም ሳይሆን ታላቅ በሆነ አንድ ሰው የሚደረግ በመሆኑ እነዚህ ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሄር ሊማልባቸው ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩ ቅዱሳንና አስቀድመው የእርሱ ቅዱሳን ለሆኑት ለሁለቱም የመጨረሻው ዋስትና ሰጭ እግዚአብሄር ነው፡፡
እዚህ ላይ ብርቱው መልአክ በእርግጠኝነት ንጥቀት እንደሚመጣ ሁሉን በሚችለው አምላክ ይምላል፡፡ ይህ መሃላ እግዚአብሄር አዲስ ሰማይና ምድር እንደሚፈጥርና በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ከቅዱሳኑ ጋር እንደሚኖር ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር አዲሱን ዓለም የመፍጠር ሥራውን እንደማያዘገይ ነገር ግን ለቅዱሳኑ ሲል በቅርቡ እንደሚያጠናቅቀውም ያሳየናል፡፡
 
ቁጥር 7፡- ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል አለ፡፡
ይህ ቁጥር በመጨረሻዎቹ መከራዎች ውስጥ የመጨረሻው ሰባተኛው መለከት በሚነፋበት ጊዜ ቅዱሳን ሁሉ እንደሚነጠቁ ይነግረናል፡፡ በዚህ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች አብዝቶ የሚያስደንቃቸው የቅዱሳን ንጥቀት መምጣቱ ነው፡፡
ራዕይ 10፡7 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል አለ፡፡›› ‹‹ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል›› የሚለው ይህ ሐረግ ምን ማለት ነው? ይህ ማለት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነተኛ ወንጌል እንደመሆኑና በዚህ የሚያምን ማንኛውም ሰው ስርየትንና መንፈስ ቅዱስን በልቡ እንደሚቀበል ሁሉ የቅዱሳንም ንጥቀት እንደዚሁ ሰባተኛው መለከት በሚነፋበት ጊዜ በእርግጠኝነት ይመጣል ማለት ነው፡፡
ከሰባቱ መለከቶች የስድስተኛው መለከት መቅሰፍት ካበቃ በኋላ ጸረ ክርስቶስ በዓለም ላይ ተገልጦ ሥልጣኑን በማደላደሉ ሰው ሁሉ የአውሬውን ምልክት እንዲቀበል ስለሚጠይቅ ቅዱሳን ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ያንን ተከትሎ ወዲያውኑ ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ እምነታቸውን በመጠበቅ ሰማዕት የሆኑትና በሕይወት የተረፉት ቅዱሳን ትንሳኤን በማግኘት አብረው ይነጠቃሉ፡፡ ከዚያም የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች፤ በሰው ዘር ላይ የሚወርደው የመጨረሻው መቅሰፍት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ አይኖሩም፡፡ ከንጥቀታቸው በኋላ ከጌታ ጋር በሰማይ ይሆናሉ፡፡ ቅዱሳን ንጥቀታቸው የሚሆነው ሰባተኛው መልአክ የመጨረሻውን መለከት ሲነፋ መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም እንደዚሁ በ1ኛ ተሰሎንቄ ላይ ጌታ በሊቀ መልአክ መለከት ከሰማይ እንደሚወርድ ይነግረናል፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች ጌታ ንጥቀት በሚሆንበት ጊዜ ወደዚህ ምድር እንደሚመጣ ያስባሉ፡፡ ነገሩ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ንጥቀት ሲሆን ጌታችን አየር ላይ ይሆናል እንጂ ወደዚህ ምድር አይመጣም፡፡ በሌላ አነጋገር ቅዱሳንን ወደላይ በመውሰድና በአየር ላይ በመቀበል ንጥቀትን ይፈጽማል፡፡
ስለዚህ የእውነተኛ ቅዱሳን ንጥቀት በሚሆንበት ጊዜ ወደዚህ ምድር ይመጣል የሚል የተሳሳተ እሳቤ ያላቸው ክርስቲያኖች የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን መጣልና እውነትን አውቀው የቅዱሳን ንጥቀት ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋበት ጊዜ እንደሚመጣ በማስታወስ በዚህ እውነት በትክክል ማመን ይኖርባቸዋል፡፡
ስለዚህ የእውነተኛ ቅዱሳን ንጥቀት በሚሆንበት ጊዜ ጌታ ወደዚህ ምድር ይመጣል የሚል የተሳሳተ እሳቤ ያላቸው ክርስቲያኖች የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን መጣልና እውነትን አውቀው የቅዱሳን ንጥቀት ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋበት ጊዜ እንደሚመጣ በማስታወስ በዚህ እውነት በትክክል ማመን ይኖርባቸዋል፡፡
‹‹ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡›› እዚህ ላይ የእግዚአብሄር ምስጢር የሚያመለክተው ከሰባተኛው መለከት መነፋት ጋር አብሮ የሚመጣውን የቅዱሳን ንጥቀት መሆኑን መረዳት አለባችሁ፡፡ በአጭሩ እግዚአብሄር የመጀመሪያውን ዓለም አጥፍቶ ሁለተኛውን ዓለም ይመሰርታል፡፡ ይህም እግዚአብሄር በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን ዳግመኛ ከተወለዱት ጋር አብሮ የሚኖርበትና ሁሉን ቻዩ አምላክ ለሕዝቡ የገባቸውን ተስፋዎችም በታማኝነት የሚፈጽምበት ነው፡፡ ይህ ለቅዱሳን ራሱ ያስቀመጠው የዩኒቨርስ ሁሉ ፈጣሪ የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው፡፡
መልአኩ ሰባተኛው መለከት ሲነፋ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ይጠናቃሉ፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች የመጨረሻ መቅሰፍቶችም ይጀምራሉ፡፡ ቃሉ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል አለ፡፡›› ‹‹ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡›› እዚህ ላይ የእግዚአብሄር ምስጢር ቅዱሳን በሰባተኛው መልአክ መለከት የሚነጠቁ መሆናቸው ነው፡፡
አሁን ቅዱሳን በዚህች ምድር ላይ እየኖሩ ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱ አዲስና የተሻለ በሆነ ዓለም ላይ እንዲኖሩ ሰማዕት መሆን፣ ትንሳኤን ማግኘትና መነጠቅ አለባቸው፡፡ ከጌታ ጋር ወደ በጉ ሰርግ የሚጋበዙትና ለሺህ ዓመት ከእርሱ ጋር የሚነግሱት ያን ጊዜ ይሆናል፡፡ ከዚህ ሺህ ዓመት በኋላ ጸረ ክርስቶስ፣ ሰይጣንና የእርሱ ተከታዮች በሙሉ የእግዚአብሄርን ዘላለማዊ ፍርድ ይቀበላሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ቅዱሳን በሰማይ ዘላለማዊ ባርኮቶች ውስጥ ከጌታ ለመኖር ይባረካሉ፡፡ እግዚአብሄር ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋበት ጊዜ እነዚህን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጽም ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 8፡- ከሰማይም የሰማሁት ድምጽ እንደገና ሲናገረኝና፡- ሂድና በባህርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ፡፡
እግዚአብሄር ቅዱሳንና የእግዚአብሄር ባሮች የመጨረሻው ቀን እስኪመጣ ድረስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበካቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ይነግረናል፡፡ ይህ ወንጌል የሐጢያቶችን ስርየት፣ ሰማዕትነትን፣ ትንሳኤን፣ ንጥቀትንና የበጉን ሰርግ እራት የሚያወሳ እውነት ነው፡፡ ቅዱሳንና የእግዚአብሄር ባሮች እስከ መጨረሻው ድረስ ወንጌን ይሰብኩ ዘንድ በመጀመሪያ ታላቁ መከራ ከመምጣቱ በፊት በእምነታቸው የእግዚአብሄርን ቃል መመገብ አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ሁለት ዓይነት እምነቶችን ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያው ዳግመኛ የመወለጃ እምነት ሲሆን ሁለተኛው እውነተኛ እምነታችንን በመከላከል ሰማዕትነትን የምንቀበልበት እምነት ነው፡፡
 
ቁጥር 9፡- ወደ መልአኩም ሄጄ፡- ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት፡፡ እርሱም፡- ውሰድና ብላት፤ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች፤ በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ፡፡
ቅዱሳንና የእግዚአብሄር ባሮች በመጀመሪያ የእግዚአብሄርን ቃል መመገብ ከዚያም ይህንኑ ቃል ለብዙዎች ማሰራጨት አለባቸው፡፡ ይህ ቁጥር በእግዚአብሄር ቃል የሚያምኑ ሰዎች ልቦች የጣፈጡ ቢሆኑም ይህንን የእምነት ቃል ለጠፉት ነፍሳቶች መስበክ ያን ያህል ቀላል ሥራ ሳይሆን በመስዋዕትነቶች የታጀበ መሆኑን ያስተምረናል፡፡ እዚህ ላይ እግዚአብሄር እያሳየን ያለው ይህንን ነው፡፡
 
ቁጥር 10፡- በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፡፡ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ፡፡
ዮሐንስ በእምነት የእግዚአብሄርን ቃል በበላ ጊዜ ልቡ በደስታ ተሞላ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ቃል የተመሰከረለትን እውነት በዚህ እውነት ለማያምኑ ሰዎች ሲሰብክ ዮሐንስ ብዙ እክሎች ገጠሙት፡፡
 
ቁጥር 11፡- በብዙ ወገኖችና በአህዛብም፣ በቋንቋዎችም፣ በነገሥታትም ላይ እንደገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ፡፡
ቅዱሳን የእግዚአብሄርን በረከቶች የሚያገኙት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት መሆኑን ለእያንዳንዱ ሰው እንደገና ትንቢት መናገር አለባቸው፡፡ ጌታችን በመጨረሻው ዘመን ለዚህ ዓለም ያለው ዓላማ ሰው ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ወደ እግዚአብሄር ባርኮቶች ይመጣ ዘንድ መሆኑን ደግመው መተንበይ አለባቸው፡፡ እግዚአብሄር የሚያመጣው አዲስ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣና ወደዚያ መግባት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን መጽደቅ እንዳለበት የሚናገረው የእውነት ቃል እንዲሰብክ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ጌታችን መንግሥት እንዲገቡና እንዲኖሩ የሚፈቅድላቸው እምነት ይኖራቸው ዘንድ ቅዱሳንና የእግዚአብሄር ባሮች ይህንን ሥራ ለመስራት ከመጀመሪያው ጀምረው ሁሉንም እንደገና በመጀመር የእግዚአብሄርን ቃል መስበክ አለባቸው፡፡