Search

ЧЗВ за Християнската Вяра

Тема 1: Новорождението от водата и Духа

1-25. በወንጌል ውስጥ የኢየሱስን ጥምቀት የማዳን ግዴታ አድርጎ መረዳት በመስቀል ላይ የሆነውን የእርሱን ሞት ከንቱ የሚያደርገው አይመስልህምን?

የኢየሱስ ጥምቀትና የመስቀል ላይ ሞቱ በእኩል ደረጃ ለማዳን አስፈላጊ ናቸው።

አንዱ ከሌላው ይበልጥ አስፈላጊ ነው ማለት አንችልም። ነገር ግን ችግሩ ዛሬ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች የሚያውቁት ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን ብቻ መሆኑ ነው። እነርሱ ኃጢአቶቻቸው እንደተነሱ እርሱ በመስቀል ላይ ስለሞተ እንደሆነ ያምናሉ፤ ነገር ግን ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ያስወገደው በመስቀል ላይ ብቻ አይደለም። እርሱ በመጥምቁ ዮሐንስ ስለተጠመቀና የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ በጀርባው ስለተሸከመ የመስቀል ላይ ሞቱ በተግባር የከፈለው የኃጢአቶቻችን ሁሉ ፍርድ ነው።
ያለ ኢየሱስ ጥምቀት በመስቀሉ ብቻ ማመን እጆችን በላዩ ላይ ሳይጭኑ ለጌታ መሥዋዕትን እንደ ማቅረብ ነው። እንዲህ አይነት መሥዋዕቶችን ያቀረቡ ሰዎች ከኃጢአቶቻቸው መዳን አይችሉም፣ ምክንያቱም መሥዋዕቱ እግዚአብሔር አምላክ ሊቀበለው የማይችለው ሕገወጥ መሥዋዕት ነው። እግዚአብሔር ከመገናኛው ድንኳን ሆኖ ሙሴን በመጥራት እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፥ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል። እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል” (ዘሌዋውያን 1፡3-4)።
ጌታ ጻድቅና ሕጋዊ ነው። ኃጢአቶቻችንን ለማጥራት ፍትሐዊና ትክክለኛ የሆነ የመሥዋዕት ሥርዓትን አቋቁሟል። ሕጋዊ መሥዋዕት ስናቀርብ መሥዋዕቱ ለእኛ ስርየትን ያመጣልን ዘንድ በጌታ ተቀባይነት ያገኛል። ያለ እጆች መጫን ምንም መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ልክ እንደዚሁ በኢየሱስ ላይ ካለን እምነት የእርሱን ጥምቀት ብንገድፍ በዚህ አይነቱ እምነት ከሁሉም ኃጢአቶቻችን መንጻት አንችልም።
የዘመኑ ክርስቲያኖች ከሚያምኑባቸው እጅግ የተለመዱ ስህተቶች አንዱ ጌታ ፍቅር ስለሆነ ኢየሱስን አዳኛቸው አድርገው በመመስከር ብቻ መዳን የሚችሉ መሆናቸው ነው። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል” (የሐዋርያት ሥራ 2፡21፣ ሮሜ 10፡13)፤ ነገር ግን ደግሞም እንዲህ ይነግረናል፦ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” (ማቴዎስ 7፡21)።
ኢየሱስ አዳኛችን እንደሆነ ለመመስከር እግዚአብሔር ያቋቋመውን የመዳን ሕግ ማወቅ አለብን። በኢየሱስ ስም በማመን ብቻ መዳን የምንችል ብንሆን ኖሮ ቅዱሳት መጽሐፍት ስለ ብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ሥርዓትና በማቴዎስ 7፡21-23 ላይም ዓመጻን ስለሚያደርጉ ሰዎች የሚጽፉበት ምንም ምክንያት ባልኖራቸውም ነበር።
ነገር ግን አስገራሚና ፍጹም የሆነው የጌታ የመዳን መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተመዝግቦዋል። በእርግጥም ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 3 እና 4 በግልጽ ማየት እንችላለን፣ አንድ ኃጢአተኛ የኃጢአትና የሰላም መሥዋዕቶችን ሲያቀርብ ኃጢአቶቹን ወደ መሥዋዕቱ ለማስተላለፍ እጆቹን በራሱ ላይ መጫን፣ ከዚያም ማረድና ደሙን መርጨት እንደነበረበት። ያለ እጆች መጫን መሥዋዕትን ማቅረብ ወይም ጉድለት ያለበትን መሥዋዕት ማቅረብ ስርየትን የማያስገኝ በጣም ሕገወጥ ነው።
የብሉይና የአዲስ ኪዳናት ቃሎች እርስ በርሳቸው የሚጣጣሙ ተመሳሳይ ነገሮች አሏቸው (ኢሳይያስ 34፡16)። ኢየሱስ በዮርዳኖስ የተቀበለው ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ኃጢአተኛ ለኃጢአት በሚቀርበው መሥዋዕት ራስ ላይ ከሚጭናቸው እጆቹ ጋር እኩል ነው። ኢየሱስ በዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “አሁንስ ፍቀድልኝ፥ እንደዚህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” (ማቴዎስ 3፡15)።
እዚህ ላይ “ጽድቅን ሁሉ” ማለት “ፍትህና ትክክለኛነት” ማለት ነው። ይህ ማለት ኢየሱስ በዚያ ዘዴ ለሰው ዘር ኃጢአት መሥዋዕት መሆኑ ተገቢ ነው ማለት ነው። የዓለምን ኃጢአቶች በሙሉ ለመውሰድ በእጆች መጫን መልክ በመጥምቁ ዮሐንስ መጠመቁ ለእርሱ ተገቢ ነበር። ይህም እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በመሠረተውና በእጆች መጫንና ደም በተዋቀረው የመሥዋዕት ሥርዓት መሠረት እጅግ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተፈጸመ።
በመስቀሉ ብቻ ማመን ማለት በውጤቱ የእርሱ ሞት ከኃጢአቶቻችን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ማለት ነው፣ ምክንያቱም ኃጢአቶቻችን ያለ ኢየሱስ ጥምቀት ፈጽመው ወደ እርሱ መተላለፍ አይችሉም ነበርና። የዚህ ውጤቱም የእርሱን ደም ኃጢአትን እንደማያነጻ መቁጠር ነው (ዕብራውያን 10፡29)።
ስለዚህ የእርሱ ደም በምዕመናን ልብ ውስጥ ያሉትን ኃጢአቶች በትክክል ለማንጻት ብቃት የሚኖረው በመጥምቁ ዮሐንስ በእጆች መጫን አማካይነት ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ ኃጢአቶቻቸው በሙሉ በእርሱ ላይ እንደተጫኑ ሲያምኑ ብቻ ነው። ስለዚህ ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ በውሃና በደም የመጣው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚያምን ሰው ዓለምን እንደሚያሸንፍ መስክሮዋል። ኢየሱስ የመጣው በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አይደለም (1ኛ ዮሐንስ 5፡4-6)።
ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱሳት መጻህፍት ሁሉ ውስጥ እርሱን የሚመለከቱትን ነገሮች ለደቀ መዛሙርቱ አብራርቷል። እርሱ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለው የኃጢአት መሥዋዕት ራሱ እንደነበር አሳየ። ዳዊት ስለ እርሱ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ” (መዝሙረ ዳዊት 40፡7-8፣ ዕብራውያን 10፡7)።
በውጤቱም የእርሱ ጥምቀት መስቀሉን አያሽርም፣ ነገር ግን በእውነቱ የመስቀሉን ትርጉም የሚያጠናቅቅና የሚፈጽም የጌታ ወንጌል አስፈላጊ ክፍል ነው። ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ክቡር ደም እስከሌለ ድረስ ቤዛነት ልናገኝ እንደማንችል ያስተምረናል። መዳን ማለት በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ከሁሉም ኃጢአቶች ሙሉ በሙሉ መንጻትና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል ማለቴ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፡8፣ የሐዋርያት ሥራ 2፡38)።