Search

Sermons

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-6] መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ እንደሚኖር እመኑ፡፡ ‹‹ ማቴዎስ 25፡1-12 ››

መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ እንደሚኖር እመኑ፡፡
‹‹ ማቴዎስ 25፡1-12 ››
‹‹በዚያን ጊዜ መንግስተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች፡፡ ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ፡፡ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮዋቸው ዘይት ያዙ፡፡ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ፡፡ እኩለ ሌሊትም ሲሆን እነሆ ሙሽረው ይመጣል ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ፡፡ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሱና መብራታቸውን አዘጋጁ፡፡ ሰነፎቹም ልባሞቹን፡- መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው፡፡ ልባሞቹ ግን መልሰው፡- ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው፡፡ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፡፡ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፤ ደጁም ተዘጋ፡፡ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቆነጃጅት መጡና፡- ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ክፈትልን አሉ፡፡ እርሱ ግን መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ አላውቃችሁም አለ፡፡››
 
 

መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው ቆነጃጅት የተመሰሉት እነማን ናቸው?

 
መንፈስ ቅዱስ የሚመጣው ለማን ነው?
በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ባገኙት ላይ ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ምንባቦች ላይ አምስት ልባም አምስት ሰነፍ ቆነጃጅት አሉ፡፡ አምስቱ ሰነፍ ቆነጃጅት አምስቱን ልባም ቆነጃጅት ከዘይታቸው የተወሰነውን እንዲካፍሉዋቸው ጠየቋቸው፡፡ ልባሞቹ ግን ሰነፎቹን ቆነጃጅቱ እንዲህ በማለት ጠየቁዋቸው፡፡ ‹‹ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው፡፡›› ስለዚህ ሰነፎቹ ቆነጃጅት ዘይት ለመግዛት ሲሄዱ ከመብራቶቻቸው ጋር ዘይት የነበራቸው አምስቱ ልባሞች ወደ ሠርጉ ገቡ፡፡ ለጌታችን ዘይት ማዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው? ማድረግ የምንችለው ብቸኛው ነገር በልባችን ውስጥ ያለውን የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ አግኝተን እርሱን መጠበቅ ነው፡፡         
በሰዎች መካከል ሁለት አይነት እምነትን ልናገኝ እንችላ ለን፡፡ አንደኛው በሐጢያቶች ይቅርታ ወንጌል እምነት ነው፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስን ወደ መቀበል ይመራል፡፡ ሌላኛው  የሐጢያቶች ይቅርታ ቢገኝም ባይገኝም ቸልተኛ ሆኖ ለሐይማኖታዊ ስርአቶች ታማኝ መሆን ነው፡፡ 
ለገዛ ራሳቸው የሐይማኖት ትምህርቶች ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ውብ የሆነው ወንጌል ሸክም ነው፡፡ ሙሽራው በሚመጣበት ጊዜ ዘይት ሊገዙ እንደሄዱት ሰነፍ ቆነጃጅት መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ተስፋ ከአንዱ የአምልኮ ቤት ወደ ሌላው የአምልኮ ቤት የሚንከራተቱ ሰዎች እያታለሉ ያሉት ማንንም ሳይሆን ራሳቸውን ነው፡፡ እንደ እነዚህ አይነት ሰዎች ከፍርዱ ቀን በፊት በልባቸው ውብ የሆነውን ወንጌል ማመን ያለባቸው የመሆኑን እውነታ አያውቁም፡፡ እግዚአብሄርን በቅንአታቸው በማስደነቅ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ይመኛሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በርካታ ጥረቶችን ያደረገ ዲያቆን የሰጠውን ምስክርነት እንመለከታለን፡፡ ይህ ምስክርነት እናንተን ይጠቅማችኋል፡፡
‹‹መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ብዙ ነገር አደረግሁ፡፡ ራሴን ለገዛ እምነቴ በትጋት ባስገዛ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እችላለሁ ብዬ ስላሰብሁ ከአንድ የጸሎት ቤት ወደ ሌላው የጸሎት ቤት ተንከራተትሁ፡፡ ከእነዚህ የጸሎት ቤቶች በአንዱ የነበሩ ሰዎች የአገልግሎቱ ክፍል በመሆኑ በኤሌክትሪክ ፒያኖና በከበሮ ይታጀቡ ነበር፡፡ ስብሰባውን የሚመራው መጋቢ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚፈልጉትን አንድ በአንድ ጠርቶ የግለሰቡን ግምባር በእጁ ሲመታው በልሳን መናገር ጀመረ፡፡ ድምጽ ማጉያ ይዞ ዙሪያውን እየሮጠም ‹‹እሳትን፣ እሳትን፣ እሳትን ተቀበሉ›› እያለ በመጮህ በሰዎች ላይ እጆቹን ይጭንና አንዳንዶች እንዲንቀጠቀጡና ራሳቸውን እንዲስቱ ያደርግ ነበር፡፡ ይህ ምግባር መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ጥርጣሬዎች ነበሩኝ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ስብሰባዎች ሱሰኛ ሆኜ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አልተሳካልኝም፡፡
ከዚያ ልምምድ በኋላ ወደ ተራሮች ሄጄ አንድ ዛፍ ላይ ተጠምጥሜ ሌሊቱን በሙሉ ሳለቅስና ስጸልይ አደርሁ፡፡ በዋሻ ውስጥ ሆኜ ለመጸለይም ሞክሬያለሁ፡፡ ያም ቢሆን የሚሰራ አልሆነም፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሊቱን በሙሉ ለ40 ቀናት ለመጸለይ ሞከርሁ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን አልተቀበልሁም፡፡ ከዚያም አንድ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ወደተደረገ ሴሚናር ተጋበዝሁ፡፡ ሴሚናሩ በሳምንት አንድ ጊዜ ሲሆን የቆየውም ለሰባት ሳምንት ነበር፡፡
ሴሚናሩ ያተኮረው በእግዚአብሄር ፍቅር፣ በመስቀሉ፣ በኢየሱስ ትንሳኤ፣ እጆችን በመጫን፣ በመንፈስ ፍሬና በመንፈሳዊ ዕድገት ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ሴሚናሩ ሊጠናቀቅ አቅራቢያ በሴሚናሩ ላይ የሰበከው ሰባኪ እጆቹን በራሴ ላይ ጭኖ መንፈስ ቅዱስን እንድቀበል ጸለየልኝ፡፡ እንደነገረኝም አደረግሁ፡፡ ዘና ብዬ እጆቼን ወደ ሰማይ በማንሳት በተደጋጋሚ ‹‹ላ-ላ-ላ-ላ›› እያልሁ ጮህሁ፡፡ ድንገት ‹‹ላ-ላ-ላ-ላ›› እያልሁ ስጮህ እንግዳ በሆነ ቋንቋ በብቃት መናገር ጀመርሁ፡፡ መንፈስ ቅዱስን በመቀበሌም ብዙ ሰዎች እንኳን ደስ አለህ አሉኝ፡፡ ነገር ግን በቤት ውስጥ ብቻዬን ሆኜ ሳለሁ ፈራሁ፡፡ ስለዚህ ለሴሚናሩ ፈቃደኛ ሰራተኛ ሆኜ መስራት ጀመርሁ፡፡ በተቻለኝ መጠን ብዙ ስራ ለመስራት ፈቃደኛ መሆን እንዳለብኝ በማሰብ አገልግሎቶቼን ለማበርከት በአገሪቱ ዙሪያ ተጓዝሁ፡፡ በአንዳንድ በሽተኞች ላይ እጆቼን ስጭን ከሕመማቸው የተፈወሱ መሰሉ፡፡ ነገር ግን ወዲያው በሕመም ይሰቃዩ ነበር፡፡ ከዚያም ራዕዮችን ማየት ጀመርሁ፡፡ ትንቢት መናገርም እንደምችልም አወቅሁ፡፡ አስገራሚው ነገር የተናገርኋቸው ትንቢቶች እውን መሆናቸው ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየቦታው እየተጠራሁ ልክ እንደ አንድ አዋቂ ሰው መስተናገድ ጀመርሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም መፍራቴን አላቆምሁም፡፡ ከዚያም አንድ ቀን ‹‹እንደዚህ ሆነህ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ አትንከራተት፡፡ በፋንታው ወደ ቤተሰብህ ሄደህ ደህንነትን እንዲያገኙ እርዳቸው›› የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ ሆኖም ደህንነት ምን እንደሆነ አላወቅሁም፡፡ የማውቀው ነገር ቢኖር ሌሎች የነገሩኝን ብቻ ነበር፡፡ ያም ይህንን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ካልተጠቀምሁበት እግዚአብሄር እንደሚነጥቀኝ የሚገልጥ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ችሎታዎቼን መጠቀም አስፈራኝ፤ ነገር ግን እንደዚያ ማድረግ አላቆምሁም፡፡
አንድ ቀን አንዲት ሴት ጠንቋይ በኢየሱስ ማመን እንደምትፈልግ ሰማሁ፡፡ ስለዚህ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ጎበኘናት፡፡ እንደምንጎበኛት ቀደም ብለን አልነገራትም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህች ሴት ጠንቋይ ከበርዋ ውጪ ሆና ትጠብቀን ስለነበር ‹‹እንደምትመጡ አውቅ ነበር›› አለችኝ፡፡ ከዚያም ድንገት ‹‹በምስራቁ ጥንቆላና በምዕራቡ ጥንቆላ መካከል ምንም ልዩነት የለም›› በማለት በላያችን ላይ ውሃ መድፋት ጀመረች፡፡ ወደ እኛ እየጠቆመችም ‹‹የኢየሱስ ጠንቋዮች›› ብላ እየጠራችን ‹‹ይህ ሰው ፈርቷል፤ ያኛው ግን አልፈራም›› አለች፡፡ ያቺ ሴት ጠንቋይ የተናገረችው ነገር ጭንቅላቴን ነካኝ፡፡ ሳደርገው የነበረው ነገር ሁሉ ጠንቋይ ከሚያደርገው የተለየ እንዳልነበረ ማሰብ ጀመርሁ፡፡ ያደረግሁት ነገር በሙሉ መንፈስ ቅዱስን አላመጣልኝም፡፡ ምክንያቱም አሁንም ድረስ በልቤ ውስጥ ሐጢያት ነበርና፡፡››
ከዚህ ምስክርነት መንፈስ ቅዱስን መቀበል ከእኛ ችሎታዎች በላይ መሆኑን እንማራለን፡፡ እንደዚህ ያለው እምነት በእግዚአብሄር ወንጌል ላይ የተመሰረተ ስላልሆነ የዚህ አይነት ሐይማኖታዊ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች በመብራታቸው ውስጥ ዘይት የላቸውም፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው መብራት የሚያመላክተው ቤተክርስቲያንን ሲሆን ዘይቱ የሚያመላክተው ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስን ሳይቀበሉ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ይሁንም አይሁንም ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ሞኞች መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡
ሰነፎቹ ቆነጃጅት ሐይማኖታዊ ግለታቸውንና ቅንአታቸውን በየቀኑ ማንደድ ይመኛሉ፡፡ በሌላ መንገድ ስናስቀምጠው ሰነፎቹ ቆነጃጅት ለእግዚአብሄር ካላቸው ዕውር ቅንአት ጋር አብረው ስሜቶቻቸውን ያነድዳሉ፡፡ ስሜቶቻችን 20 ሳንቲ ሜትር ርዝማኔ ቢኖራቸውና 1 ሳንቲ ሜትር ለማንደድ የሚወስድብን ጊዜ አንድ ቀን ቢሆን ስሜቶቻችንን በሙሉ በእሳት ለማንደድ የሚወስድብን 20 ቀናት ብቻ ነው፡፡ ከእምነታቸው ጀርባ ያሉት ስሜቶች ጥንካሬ የሚያገኙት በማለዳ ጸሎቶች፣ ሌሊቱን ሁሉ በሚደረጉ ጸሎቶች፣ በጾምና በጸሎት እንደዚሁም በመነቃቃት ስብሰባዎች ነው፡፡ ነገር ግን ስሜቶቻቸው በዕድሜ ዘመናቸው ሁሉም ይነዳሉ፡፡ እነርሱ በዚህ ማለቂያ የሌለው ስሜቶቻቸውን የማቀጣጠል ሒደት ተጠምደዋል፡፡
ስሜቶቻቸው የሚቀጣጠሉት በኢየሱስ ስም ነው፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው ስሜቶቻቸውን ያቀጣጥላሉ፡፡ ነገር ግን ልባቸው አሁንም በውዥንብር ውስጥ ያለ በመሆኑ ሌላ አንዳች ነገር ይፈልጋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት እምነታቸው የመጣው ከአካላዊ ልምምዶች ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ነበልባሉ እንዳይጠፋ እነዚህን ስሜቶች በየጊዜው ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሆኖም በዚህ አይነቱ እምነት መንፈስ ቅዱስን መቀበል አይችሉም፡፡ ስሜቶቻቸውን ማንደድ መንፈስ ቅዱስን ወደ መቀበል አይመራቸውም፡፡
ሁላችንም በእግዚአብሄር ሙሉ ሕልውና ፊት መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል እውነተኛውን እምነት ማዘጋጀት አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ብቃት የሚኖረን ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ብቁ የሚያደርገንን እምነት የምናገኘው እንዴት ነው? እውነቱ ያለው በዮርዳኖስ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በተፈጸመው ውብ ወንጌል ላይ ነው፡፡
እግዚአብሄር እኛን ‹‹የክፉ አድራጊ ዘር›› (ኢሳይያስ 1፡4) በማለት ጠቁሞናል፡፡ ይህንን ማመን አለብን፡፡ ሰዎች በመጀመሪያ የተወለዱት 12 አይነት ሐጢያቶችን ይዘው ነው፡፡ (ማርቆስ 7፡21-23) ሰብአዊ ፍጡራን ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ እስከሚሞቱበት ጊዜ ድረስ ሐጢያትን ከመስራት አይታቀቡም፡፡ 
በዮሐንስ 1፡6-7 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ከእግዚአብሄር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፡፡ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፡፡›› መጥምቁ ዮሐንስ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ›› (ዮሐንስ 1፡29)   በማለት ኢየሱስን አጠመቀውና የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ወደ እርሱ አስተላለፈ፡፡ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማጥመቁ ምስጋና ይሁንና እኛ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ዳንን፡፡ ዮሐንስ ኢየሱስን ባያጠምቀውና የአለምን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደ የእግዚአብሄር በግ መሆኑን ባያውጅ ኖሮ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ከራሱ ጋር አብሮ መስቀል ላይ መውሰዱን ማወቅ ባልቻልን ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበልም መንገዱን ማወቅ ባልቻልንም ነበር፡፡ ነገር ግን ምስጋና ለዮሐንስ ምስክርነት ይሁንና ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ መውሰዱንና እኛም መንፈስ ቅዱስን መቀበል መቻላችንን ወደ መረዳት መጣን፡፡  
በዚህ እምነት ሙሽራውን ኢየሱስን ለመቀበል ሙሉ በሙሉ የተዘጋጁ ሙሽሪቶች ሆነናል፡፡ እኛ በኢየሱስ ያመንንና መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ሙሉ በሙሉ የተዘጋጀን ቆነጃጅት ነን፡፡
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሙሉ ልባችሁ ታምናላችሁን? ኢየሱስ ክርስቶስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ እንደወሰደ ታምናላችሁን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› (ሮሜ 10፡17) መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ሲባል ኢየሱስ በዮሐንስ እንደተጠመቀና በመስቀል ላይ እንደሞተ ማመን አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ሊመጣ የሚችለው ኢየሱስ ሰብአዊ ፍጡር ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት በዮሐንስ እንደተጠመቀ በመስቀል ላይ እንደሞተና እንደተነሳ በመረዳት ነው፡፡
ዛሬም እንኳን ሁለት አይነት የምዕመናን ቡድኖች አሉ፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ታሪክ ላይም ያሉት አስሩ ቆነጃጅት ሁለት ቡድኖች ነበሩ፡፡ እናንተ ከየትኛው ወገን ናችሁ? በውሃና በመንፈስ በማመን መንፈስ ቅዱስን መቀበል አለባችሁ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን እየሄዳችሁ ገናም መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድባችሁ እየጠበቃችሁ ነውን? መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል እውነተኛውን ወንጌል ማወቅ አለባችሁ፡፡
መንፈስ ቅዱስን መቀበል የምንችለው በምን አመኔታዎች ነው? በጋለ ስሜት ተነስታችሁ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ትችላላችሁን? ራሳችሁን በሳታችሁበት ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ትችላላችሁን? በአክራሪ ሐይማኖቶች በማመን መንፈስ ቅዱስን መቀበል ትችላላችሁን? የሐጢያቶቻችሁን ይቅርታ ለማግኘት ያለ ማቋረጥ ትጸልያላችሁን? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከውሃ ሲወጣ የእግዚአብሄር መንፈስ በርግብ አምሳል እንደወረደበት ይናገራል፡፡ እርሱ የተጠመቀው ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመሸከምና የሐጢያቶቻችንን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል እንደተሰቀለ ሊነግረን ነው፡፡  
እኛ መዳን እንድንችልና መንፈስ ቅዱስንም እንድንቀበል ኢየሱስ የአለምን ሐጢያት ለመሸከም በዮሐንስ ተጠመቀና በመስቀል ላይ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ተፈረደበት፤ ከሙታንም ተነሳ፡፡ የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ ለማግኘት በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ጥምቀት በማመን በነጻነው ላይ ልክ እንደ ርግብ በሰላማዊ መንገድ እንደሚወርድብን ከኢየሱስ ጥምቀት ማየት እንችላለን፡፡ (ማቴዎስ 3፡13-15)
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ ግለሰቡ በሐጢያት ይቅርታ ሲያምን መንፈስ ቅዱስ ልክ እንደ ሰላማዊ ርግብ ይወርድበታል፡፡ ቀደም ብለው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ይህ ተግባራዊ ሊሆን የቻለው በእምነት በኩል ባገኙት የሐጢያት ይቅርታ እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሙሉ ልባቸው በሐጢያት ይቅርታ በሚያምኑት ላይ ይወርዳል፡፡ 
ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት በሚሰጡት በሕብስቱና በወይኑ መጣ፡፡ (ማቴዎስ 26፡26-28፤ ዮሐንስ 6፡53-56) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ከውሃው ሲወጣ እንዲህ የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ፡- ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡›› (ማቴዎስ 3፡17)
እግዚአብሄርን እንደ ስላሴ ማመን ቀላል ነው፡፡ እግዚአብሄር የኢየሱስ አባት ሲሆን ኢየሱስም የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ እግዚአብሄር ነው፡፡ ስላሴ ለእኛ አንድ አምላክ ነው፡፡
በመስቀሉ በማመን ብቻ ወይም ራሳችሁን በጽድቅ ስራዎች በመቀደስ በጭራሽ መንፈስ ቅዱስን እንደማትቀበሉ ማወቅ አለባችሁ፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የምትችሉት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በእርሱ ላይ ለመጫን ዮሐንስ ኢየሱስን እንዳጠመቀውና ለሐጢያቶቻችን ስርየት ለመስጠትም በመስቀል ላይ እንደሞተ ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ እውነት ምንኛ ቀላልና ግልጽ ነው! የሐጢያት ይቅርታንና መንፈስ ቅዱስን መቀበል አዳጋች አይደለም፡፡   
እግዚአብሄር ቀለል ባሉ ቃሎች ተናግሮናል፡፡ የአንድ ተራ ሰው የማሰብ ችሎታ ከ110-120 አካባቢ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ወንጌል ተራ ሰው ሊያስተውለው ቀላል ነው፡፡ በ4 ወይም 5 የዕድሜ ክልል ላሉ ልጆችም እንኳን ውብ የሆነውን ወንጌል መረዳት አያስቸግራቸውም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ስለ መንፈስ ቅዱስ በጣም ውስብስብ በሆነ መንገድ ቢነግረን ኖሮ እናስተውለው ነበርን? እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅር አለን፡፡ በእርሱ ላመኑትም መንፈስ ቅዱስን ስጦታ አድርጎ ሰጣቸው፡፡
እግዚአብሄር በእጆች መጫን ወይም በንስሐ ጸሎቶች መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንደማንችል ነገረን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በፆም ወይም ራስን በመስጠት ወይም ሌሊቱን ሁሉ በተራሮች ላይ ሆኖ በመጸለይ አይሰጥም፡፡ መንፈስ ቅዱስን በውስጣችን እንድንቀበል የሚረዳን እምነት ምን አይነት ነው? ኢየሱስ ወደ አለም መጥቶ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመውሰድ የመጠመቁን፣ በመስቀል ላይ የመሞቱንና የመነሳቱን እውነታ የሚያምን እምነት ነው፡፡
 
 

በእርግጥ በዚህ ማመን ይኖርብናልን?

 
የሐጢያቶችን ይቅርታ ማግኘትና ከዚያም መንፈስ ቅዱስን መቀበል ያለብን ለምንድነው? የእግዚአብሄር መንግስት ዜጎች ለመሆን የእርሱ መንፈስ ያስፈልገናል፡፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ኢየሱስ አዳኛችን አድርገን ማመን፣ በጥምቀቱና በደሙ ማመን ያስፈልገናል፡፡ በመጨረሻም ለሐጢያቶቻችን ይቅርታን ማግኘት አለብን፡፡
እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ላገኙት የሚሰጠው ለምንድነው? የራሱ ሕዝብ አድርጎ ሊያትማቸው ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ተመስርተው በኢየሱስ የሚያምኑትን ለማተም መንፈስ ቅዱስን ዋስትና አድርጎ ሰጠ፡፡    
በጣም ብዙ ሰዎች የተሳሳተ አይነት እምነት ይዘዋል፡፡ በኢየሱስ ጥምቀት አምኖ መንፈስ ቅዱስን መቀበል በጣም ቀላል ነው፡፡ ቀደም ብሎ መንፈስ ቅዱስን ለተቀበልነው ይህ ቀላል ነው፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ላላገኙት ግን የማይቻል ነው፡፡ እውነቱን አያውቁም፡፡ በፋንታው መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አክራሪ በሆኑ ድርጊቶች ራሳቸውን በሐይማኖታዊ ኮማ ውስጥ ማስመጥ በመሳሰሉ ሌሎች መንገዶች መንፈስ ቅዱስን ይሻሉ፡፡ እውቀት አልባዎች ስለሆኑ ሰይጣን በዘራቸው ዘሮች ተወናብደው በባዕድ አምልኮ ሐይማኖቶች ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ፡፡ 
መንፈስ ቅዱስ የሚያድረው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አምነው የሐጢያት ይቅርታን በተቀበሉት ላይ ነው፡፡ ‹‹ሐጢያት የለብኝም›› ብለው መናገር የሚችሉት በእግዚአብሄር ማዳን የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡ አንድ ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምን ከሆነ ሐጢያት የለብኝም ማለት አይችልም፡፡ እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አምነው የሐጢያት ይቅርታን ለተቀበሉት ልጆቹ መንፈስ ቅዱስን ዋስትና አድርጎ ሰጥቶዋቸዋል፡፡
የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደወሰደ የመሰከረው ማነው? ኢየሱስ፣ የእርሱ ደቀ መዛሙርትና መንፈስ ቅዱስ የመሰከሩት ይህንኑ ነው፡፡ ሰዎችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ያቀደው ማነው? ቅዱስ አባት ነው፡፡ ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ያደረገው ማነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ለመሆኑ በመጨረሻ ዋስትና የሰጠው ማነው? መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡  
እግዚአብሄር የራሱ ሕዝብ ሊያደርገን ፈለገ፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ሊያድነን ወሰነ፡፡ መለኮታዊው ስላሴ ፍጹም ስለሆነው ደህንነታችን ዋስትናን በመስጠት የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ እንዳገኘን አረጋገጠ፡፡ 
በማቴዎስ 3፡17 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡›› የእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ ያላቸው የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡ እነርሱ የእርሱ ልጆች ናቸው፡፡ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡›› ኢየሱስ ቀድሞውኑም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር አብ ‹‹ለሐጢያቶቻችሁ ይቅርታን ለማግኘት ከፈለጋችሁ የሰው ዘር ሐጢያት በሙሉ አንድያ ልጄ በሆነው በኢየሱስ ለዘላለም መወገዱን እመኑ፡፡ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ፡፡ ልጆቼም ሁኑ›› ብሎ ነግሮናል፡፡ በዚህ የሚያምኑ ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን አግኝተው የእግዚአብሄር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሆናሉ፡፡ ልጆቹ አድርጎ ያትማቸው ዘንድም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ለሐጢያቶቻችን ይቅርታን የምናገኘው በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ስናምን ብቻ ነው፡፡  
ሰዎች ልባቸውን ንጹህ ካላደረጉና በይቅርታው ወንጌል ካላመኑ የአዳም ሐጢያት ቀድሞውኑም ተወግዶዋል ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ተጨባጭ ለሆኑት ሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ለማግኘት ያለ ማቋረጥ የንስሐ ጸሎትን መጸለይ እንዳለባቸውም ደግሞ ያምናሉ፡፡ የእነዚህ አይነት አስተሳሰቦች ሰለባ ከሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ግራ የሚያጋባና የማይሰተዋል ይሆንባቸዋል፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት የተለዩ ልዩ ልዩ አይነት እምነቶችን ወደ ማመን ይመጣሉ፡፡ 
አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ የሚወርድባቸው ‹‹በጸሎት አማካይነት›› እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ አንጻር እውነት አይደለም፡፡ ይህ አሳማኝ ይመስል ይሆናል፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ከውሃው ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል እንደወረደበት ይናገራል፡፡ ይህ የሚያረጋግጥልን መንፈስ ቅዱስን መቀበል ከፈለግን የሚያስፈልገን ብቸኛው ነገር ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ በዮሐንስ እንደተጠመቀና ለእነዚያ ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ ተኮንኖ መድህናችን ለመሆን ከሙታን መነሳቱን ማመን መሆኑን ነው፡፡ 
እኛ በዚህ እውነት አምነን መንፈስ ቅዱስን ስንቀበል እግዚአብሄር ምን ይለናል? ‹‹አንተ ልጄ ነህ፡፡ በእርሱ ደስ የምሰኝብህ ውድ ልጄ ይህ ነው›› ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ወደፊት በኢየሱስ አምነው የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ለሚያገኙትም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ ይህ እውነት እኛን የእርሱ ልጆች ለማድረግ ከእግዚአብሄር የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡
ሰዎች ግን አሁንም ድረስ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ሌላ መንገድ ስለ መኖሩ ይናገራሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በማልቀሳችሁና በምድራዊ ጥረቶቻችሁ በእናንተ ላይ የሚወርድ ይመስላችኋልን? የእግዚአብሄር ስራዎች በፈቃዱ መሰረት ብቻ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ እርሱ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጠው የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ላገኙት ብቻ ነው፡፡ እርሱ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ ወስዶ ስለ እነርሱ ለመኮነን በመስቀል ላይ የተሰቀለው ልጄ እንዲጠመቅ አድርጌያለሁ፡፡ ልጄን መድህናችሁ እንዲሆን ሾሜዋለሁ፡፡ ልጄ የፈጸመውን የሐጢያት ይቅርታ ከተቀበላችሁ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እልክላችኋለሁ፡፡››
አባታችን የፈለገውን ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው ሳንባው እስኪፈነዳ ድረስ ሌሊቱን በሙሉ ተንበርክኮ ቢያለቅስም እግዚአብሄር የግድ መንፈስ ቅዱስን አይሰድለትም፡፡ ‹‹አንተ ገና እውነተኛውን እውቀት አልተቀበልህም፡፡ የተሳሳቱ እምነቶችን የሙጥኝ ብለህ መያዝህን ቀጥለሃል፡፡ እውነተኛውን እምነት እምቢ እስካልህ ድረስ መንፈስ ቅዱስ አይሰጥህም›› በማለት ይወቅሰዋል፡፡
በዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጆች የሚወስኑዋቸው ውሳኔዎች እንደ ሁኔታዎቹ ይቀያየራሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ሐጢያቶችን ይቅር ለማለትና መንፈስ ቅዱስን ለመስጠት ያጸናው ሕግ አይለወጥም፡፡ በተሳሳቱ እምነቶች ጥላ ስር ወድቃችሁ ከሆነ እንደገና ትክክለኛውን መንገድ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለማይታዘዙት ኢየሱስ የዕንቅፋት ድንጋይ እንደሆነ ይናገራል፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 2፡8)
በኢየሱስ እያመኑ ለምን እንደተጠመቀ የማያምኑ ሰዎች የቤዛነቱን ወንጌል የሚያምኑት በከፊል ስለሆነ ወደ ሲዖል መውረዳቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ በኢየሱስ ስታምኑ የሐጢያት ይቅርታ የሚገኝበት ወንጌል የተመሰረተበትን የኢየሱስን ጥምቀትና ደሙን ማወቅ ይኖርባችኋል፡፡ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስንም ትቀበላላችሁ፡፡
ኢየሱስ በምድር ላይ ስለኖረው ሕይወት እናስብ፡፡ ኢየሱስ ሰው ሆኖ የዚህን ዓለም ሐጢያት በሙሉ በጥምቀቱ ወሰደ፡፡ በመስቀል ላይም ሞተ፡፡ እኛን ከሲዖል እሳት ለማዳንም ለሐጢያቶቻችን ተኮነነ፡፡ በእርሱ የሚያምኑ መንፈስ ቅዱስን በስጦታ መልክ ይቀበላሉ፡፡
ስለዚህ ሁላችንም መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል እውነተኛውን መንገድ መከተል አለብን፡፡ የሚያስፈልገው ነገር እንደ እውነት ቃሎች ማሰብ ነው፡፡ ይህንን ስታደርጉ ኢየሱስ ይጠብቃችኋል፤ ይባርካችኋልም፡፡ ልባቸውን ባዶ አድርገው በቃሎቹ የሚያምኑ የሐጢያትን ይቅርታ አግኝተው በእውነቱ መኖር ይችላሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ይመራሉ፡፡ ከዚህም በላይ በመንፈስ ቅዱስ ዕርዳታ ሌሎችን ወደ ትክክለኛው መንገድ መምራት ይችላሉ፡፡በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በተከናወነው ቤዛነት እመኑ፡፡ በእምነት የምንከተለውና የሐጢያት ይቅርታን፣ የዘላለም ሕይወት በረከትንና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ሞቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደ የይቅርታ አምላክ ነው፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አንጽቶ በዚህ የወንጌል እውነት ለሚያምኑት መንፈስ ቅዱስን ሰጣቸው፡፡ እውነተኛውን እምነት በመያዝ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ትችላላችሁ፡፡