Search

דרשות

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-4] እነዚያ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር ተመሳሳይ የሆነ እምነት ያላቸው ሰዎች ‹‹ የሐዋርያት ሥራ 3፡19 ››

እነዚያ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር ተመሳሳይ የሆነ እምነት ያላቸው ሰዎች
‹‹ የሐዋርያት ሥራ 3፡19 ››  
‹‹እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ ሐጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም፡፡››
 
 
ሐዋርያት የነበራቸው እምነት ምን አይነት ነበር?
እነርሱ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም አመኑ፡፡
 
የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት እምነት ስንመለከት ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ካገኙ በኋላ የነበራቸው እምነት መንፈስ ቅዱስን ከማግኘታቸው በፊት ከነበረው እምነት ጋር በጣም የተለያየ ነበር፡፡ ሥጋቸው የተለየ አልነበረም፡፡ ነገር ግን  መንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉ በኋላ ሕይወታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ሙሉ በሙሉ ተለውጦዋል፡፡
እኔ የምኖርበት ከተማ የሚያምሩ ተራሮችና ሐይቆች ያሉበት ነው፡፡ እነዚህን ልብ የሚመስጡ ተፈጥሮዎች ስመለከት በእርካታና በመደነቅ ስለምሞላ እግዚአብሄርን እንደ እነዚህ ስላሉት ፍጥረቶች ከማመስገን በቀር የማደርገው አንዳች ነገር የለም፡፡ አንጸባራቂው ኩልል ያለ ንፁህ ውሃ በጸሐይ ብርሃን ሲያብረቀርቅ ልቤን ሙሉ ስለሚያደርገው በዙሪያዬ ያለው አለም ልክ ወርቅ ይመስለኛል፡፡  
ነገር ግን እንደዚህ ያለ ማራኪ ውበት ራሱን የማይገልጥባቸው ስፍራዎችም አሉ፡፡ ሰማይ ጥርት ብሎ የሚታይባቸው ስፍራዎችም አሉ፡፡ ነገር ግን የፀሐይ ብርሃን የሚያርፍበት ውሃ ይበልጥ ቆሻሻ ሆኖ ይታያል፡፡ እንደዚህ ባለው ትዕይንት ውስጥ ብሩህ ነጸብራቅ አይኖርም፡፡ እንደዚህ ያለውን ሐይቅ ስመለከት ሐጢያቶቼን ስላነጻውና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ስለሰጠኝ ውብ ወንጌሉ ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡
በቆሻሻ የተሞላ ሐይቅ ብርሃንን ማንጸባረቅ እንደማይችል ሁሉ እኛም የሐጢያተኛ ተፈጥሮዋችን ባለ ዕዳ ሆነን ከእግዚአብሄር ብርሃን የራቅንና ወደማይታወቅ ዕጣ ፈንታ የምንነጉድ ሰዎች እንሆን ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በልቦቻችን ውስጥ ሲያድር የእግዚአብሄር ልጆች ሆነን እንገለጥና ወንጌልን ለሌሎች ሰዎች የምናስተምር እንሆናለን፡፡ እኛ የእርሱን ብርሃን ስለተቀበልን እንደ ብርሃን እናበራለን፡፡  
ልክ እንደዚሁ ከኢየሱስ ትንሳኤ በኋላ የእርሱ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የብርሃን ልጆችና ሐዋርያት ሆኑ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ለሁሉም ታላቅ በረከት ስለሆነ ብዙ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይመኛሉ፡፡ 
 
 

የሐዋርያው ጳውሎስ እምነት
 

ጳውሎስ ምን አይነት እምነት ነበረው? ጳውሎስ ስለ እምነቱ ሲመሰክር በወቅቱ እጅግ ታላላቅ ከነበሩት የሕግ አስተማሪዎች አንዱ በሆነው በገማልያል እግር ስር ሆኖ የአባቶቹን ሕግ አጥብቆ እንደተማረ ተናግሮዋል፡፡ ነገር ግን ሕጉን እየጠበቀ እንኳን ከሐጢያቶቹ መዳን እንዳልቻለ እንዲያውም የመድሃኒታችን የኢየሱስ አሳዳጅ እንደነበር ተናዞዋል፡፡ አንድ ቀን በደማስቆ መንገድ ላይ ከኢየሱስ ጋር ተገናኝቶ የእርሱ ወንጌል ወንጌላዊ ሆነ፡፡ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ፣ የአለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለማንጻት በዮሐንስ እንደተጠመቀና የእነዚያን ሐጢያቶች ፍርድ ለመውሰድም በመስቀል ላይ እንደደማ አመነ፡፡ በሌላ አነጋገር ጳውሎስ በልቡ ውስጥ በሐጢያት ይቅርታ እምነቱ ነበረው፡፡ 
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በዮሐንስ የተጠመቀውና በመስቀል ላይም ደሙን ያፈሰሰው ለሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይቅርታን ለመስጠት እንደሆነ አመኑ፡፡ ጳውሎስም ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ተመሳሳይ እምነት ስለነበረው ከሐጢያቶቹ በሙሉ ድኖዋል፡፡
ጳውሎስ በገላትያ 3፡27 ላይ እንዲህ ተናግሮዋል፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡›› በዚህም የኢየሱስ ጥምቀት መዳኛው መሆኑን አመነ፡፡ ጴጥሮስም እንደዚሁ በ1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ላይ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡›› ጴጥሮስ በዚህ ጥቅስ አማካይነት የኢየሱስን ጥምቀት ውብ ወንጌል ገለጠ፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዮሐንስ ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዳነጻ አምነዋል፡፡ ለሐጢያቶቻቸውም ይቅርታን አግኝተዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም በዚህ እውነት በማመናቸው ዳግመኛ ከሕግ እርግማን በታች አይደሉም፡፡   
እነርሱ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አምነዋል፡፡ ይህ እምነት ለደቀ መዛሙርቱ የተቃና ብቃት አስፈላጊ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ 1፡21-22 ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር የትንሳኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል፡፡›› የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን የተጀመረው በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት በማመን ነው፡፡ 
የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ ለማግኘት የሚያስፈልገን እውነት በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን ነው፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡›› (ገላትያ 3፡27) ጳውሎስም እንደዚሁ በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አምኖዋል፡፡   
ቲቶ 3፡5ን እንመልከት፡- ‹‹እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹ለአዲስ ልደት የሚሆነው መታጠብ››  የሚለው ሐረግ የሚያመላክተው ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀ ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ መንጻታቸውን ነው፡፡ እናንተም የሐጢያቶቻችሁን ይቅርታ ለማግኘት በዮሐንስ በኩል በሆነው ጥምቀቱ ወደ ኢየሱስ መሻገሩን በሚናገረው ውብ ወንጌል ማመን ያስፈልጋችኋል፡፡ ኢየሱስ የተሰቀለውና እስከ ሞት ድረስ ደሙን ያፈሰሰው በጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስለወሰደ ነበር፡፡ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት በዚህ እውነት ማመን ብቻ በቂ ነው፡፡ ጳውሎስም እንደዚሁ በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመኑን ተናግሮዋል፡፡    
ዕብራውያን 10፡21-22ን እንመልከት፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእግዚአብሄርም ቤት ላይ የሆነ ትልቅ ካህን ስላለን ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውሃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹በጥሩ ውሃ ታጥበን›› የሚለው ሐረግ የሚያመላክተው የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ያነጻውን የኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ 
ስለዚህ በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ውስጥ የውቡ ወንጌል ዋና ዋና ክፍሎች የእርሱን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ መሆኑን ማግኘት እንችላለን፡፡ እናንተም ደግሞ ጳውሎስ የነበረውን አይነት እምነት መጋራት አለባችሁ፡፡ 
ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ መንጻታቸውን ሳያውቁ በከንቱ በእርሱ ያምናሉ፡፡ አንዳንድ የነገረ መለኮት ምሁራን ሰዎች የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ለማግኘት በውሃ መጠመቅ አለባቸው ብለው ይከራከራሉ፡፡ ይህ አባባል የመነጨው ምናልባትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን እውነተኛውንና ውቡን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ካለማወቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ሐጢያቶቻችን በውሃ ውስጥ ስንጠመቅ በተደረገ ተራ ስርዓት ብቻ ይቅርታን ሊያገኙ አይችሉም፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ላይ ያለን እምነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያነጻናል፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ የሚያገኙት በውቡ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡ በእርሱ ደም በማመናቸው ፍርዳቸው በሙሉ ተሰርዞዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችሉት ይህ እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡  
‹‹ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውሃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፡፡›› (ዕብራውያን 10፡22) የዕብራውያን ጸሐፊ በተረዳንበት እምነት በእውነተኛ ልብ ወደ እግዚአብሄር እንድንቀርብ ይነግረናል፡፡ እናንተም ደግሞ በውቡ ወንጌል በተረዳችሁበት እምነት በእውነተኛ ልብ ወደ እርሱ መቅረብ ይኖርባችኋል፡፡   
ዛሬ ክርስቲያኖች ከልባቸው መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የሚያድረው ሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ባገኘባቸው ሰዎች ውስጥ ነው፡፡  ብዙዎች ይህንን ስለማያውቁ በውቡ የኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ወንጌል ሳያምኑ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ይመኛሉ፡፡ በኢየሱስ እያመኑ በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ የማያምኑ መንፈስ ቅዱስን ሊቀበሉ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ንጹህ ልብ የላቸውምና፡፡ 
ጳውሎስ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ስላመነ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ፡፡ ይህንን እምነት በማሰራጨቱም እንደ መናፍቅ ተቆጥሮ ተሳደደ፡፡ ሆኖም መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ ስላደረ እስከ መጨረሻው ድረስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰራጨት ቻለ፡፡ ‹‹ሐይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ፡፡›› (ፊልጵስዩስ 4፡13) ለዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ጳውሎስ ወደ እግዚአብሄር እስኪሄድ ድረስ እግዚአብሄርን እያገለገለ በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ስር ሆኖ ሕይወቱን ኖረ፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችሉት የጳውሎስ አይነት ተመሳሳይ እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ 
እስቲ የጳውሎስን እምነት እንመልከት፡፡ ቆላስያስ 2፡12 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ፤ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሄር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ፡፡›› ጳውሎስ በዮሐንስ በተጠመቀው በኢየሱስ በማመኑ ሐጢያቶቹ በሙሉ ይቅር ተባሉለት፡፡ 
 
 

ክርስትና ከጥንት ዘመን ጀምሮ እንዴት ሊለወጥ ቻለ?

 
በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለች በኋላ ደቀ መዝሙር የሆነች አንዲት እህት የሰጠችውን ምስክርነት እንመልከት፡፡ 
‹‹ዕድሜዬ እየገፋ ቢሆንም ልጅ መውለድ ግን አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ በጸሎት አማካይነት የእርሱን በረከት ለማግኘት ከአንዱ ቤተክርስቲያን ወደ ሌላው ቤተክርስቲያን ነጎድሁ፡፡ ብቻዬን ቤቴ ውስጥ ተቀምጬ እንኳን ቢያንስ ለአንድና ለሁለት ሰዓት ያህል እጸልይ ነበር፡፡ ይህ ሐይማኖታዊ ልምድ የቀን ተቀን የሕይወቴ ክፍል ሆነ፡፡
በራሴ መንገድ የዚህ አይነቱን ሐይማኖታዊ ሕይወት እየመራሁ
ሳለሁ አንዲት በዕድሜ የገፋች ሴት አገኘሁ፡፡ እግዚአብሄር ልጅ እንዲሰጠኝ የምለምን ከሆንሁ እርስዋ እጆችዋን በእኔ ላይ ጭና የምትጸልይልኝን ጸሎት ለመቀበል መሞከር እንደሚኖርብኝ ነገረችኝ፡፡ ይህች ሴት የእግዚአብሄር መልዕክተኛ እንደሆነች ከሆነ ቦታ ሰምቼ ስለነበር እጆችዋን በራሴ ላይ እንድትጭን ፈቀድሁላት፡፡ በዚያች ቅጽበት ከዚህ ቀደም ተሰምቶኝ የማያውቅ ልምምድ ተሰማኝ፡፡ ምላሴ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ በልዩ ቋንቋ ተናገርሁ፡፡ ወደላይ የሚገፋኝ አንድ እንግዳና የጋለ ሐይል ተሰማኝ፡፡
ይህንን ልምምድ መንፈስ ቅዱስን የመቀበሌና የጸሎቶቼ መልስ አድርጌ ተቀበልሁት፡፡ እጆችዋን በራሴ ላይ የጫነችው ሴት ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለችው ስጦታ ያላት ይመስል ስለነበር ትንቢት መናገርና መፈወስ ትችል ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በቅጡ አልተማረችም፡፡ ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስን ሐይል በመጠቀም በርካታ መጋቢዎችና ምሁራን በእጆች መጫን አማካይነት መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ረድታቸዋለች፡፡  
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ ያሉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርሁ፡፡ ከእነዚህ አንዱ  3‹‹ተሐድሶ/መነቃቃት›› ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ባደረግሁዋቸው ጸሎቶች በአንዱ በመላው ሰውነቴ ውስጥ የመንቀጥቀጥ ስሜት ተሰማኝ፡፡ ልቤም ለእግዚአብሄርና ለባልንጀሮቼ ባለኝ ፍቅር ነደደ፡፡ ይኸው ተመሳሳይ ነገር ሌሎችንም ገጥሞዋቸዋል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ይስቱ በልሳንም ይናገሩ ነበር፡፡ በዚያ ስፍራ በአጋንንት የተያዙ ሰዎች ስለነበሩ የዚህ ስብሰባ መሪ አጋንንቶችን አስወጣ፡፡
 
[3] እውነተኛ ተሐድሶ ተፈጥሮአዊና የክርስትና ሕይወት ክፍል ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ዕድገትን በመንፈስ ቅዱስ በማረጋገጥ ያስገኛል፡፡ ሆኖም በቅርብ ዓመታት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ‹‹ተሐድሶ›› የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን የመንፈስ ጥንካሬ የሚያመለክት እንዳልሆኑ የተለያዩ ሐሳቦች ይሰነዝራሉ፡፡ እነርሱ የሚሉት ‹‹ተሐድሶ›› ብዙውን ጊዜ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች የሚከሰቱበትንና በተለያዩ መንፈሳዊ ዕይታዎች የሚገለጡ የሚመስሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ ምንጮች የሚወሰዱ ናቸው፡፡
እነዚህ በተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ስም የሚሰብኩና የሚሰራጩ ትክክለኛና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑና የሐሰት ትምህርት ተከታዮችና መሪዎች ብዙ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ትክክለኛ ትርጉም እንዳይረዱና መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እንዳይችሉ አድርገዋቸዋል፡፡ እነዚህም ሰዎች የውቡን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ትክክለኛ ትርጉም እንዳይረዱና በስህተት እንዲመለከቱት አድርገዋል፡፡ 
 
የዚህ ተሐድሶ/መነቃቃት እንቅስቃሴ አላማ ሰዎች እንደ መንቀጥቀጥ፣ ትንቢትን እንደ መናገር፣ አጋንንቶችን እንደ ማስወጣትና በልሳን እንደ መናገር ባሉ ነገሮች አማካይነት መንፈስ ቅዱስን እንዲለማመዱ መርዳት ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ልምምዶች ሁሉ ቢኖሩም ሐጢያት ነበረብኝ፡፡ በልቤ ውስጥ ያሉት ሐጢያቶችም ፍርሃትና ሐፍረት እንዲሰማኝ አድርገውኛል፡፡    
ስለዚህ በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ የሐጢያትን ችግር መፍታት እችል ዘንድ ከልቤ ጸልያለሁ፡፡ ሐጢያት እንደሰራሁ ብናዘዝም ሰዎች ግን እንደ መልአክ ይመለከቱኝ ነበር፡፡ ጥሩ እምነት አለኝ ብዬ አሰብሁ፡፡ ነገር ግን ተሳስቼ ነበር፡፡ ስህተቴን ባልረዳ ኑሮ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት የሚያስችለኝ ዕድል ማግኘት አልችልም ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሚያሰራጩት ጋር ተገናኘሁና በእግዚአብሄር ቃሎች በማመን ለሐጢያቶቼ ሁሉ ይቅርታን አገኘሁ፡፡ አሁን በትክክል ደስተኛ ነኝ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምናለሁ፡፡ መንፈስ ቅዱስን አግኝቻለሁ፡፡ እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ በዚህ ወንጌል በማመን መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ ጌታችንን አመሰግነዋለሁ፡፡››
እዚህ ላይ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እንደሚያስፈልገን ተምረናል፡፡ ለሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ይቅርታን ለማግኘት ከፈለጋችሁ በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀት ማመን አለባችሁ፡፡ ኤፌሶን 4፡5ን እንመልከት፡- ‹‹አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንዲት ጥምቀት፡፡›› እዚህ ላይ የምናምንበት አንድ ጌታና አንድ ጥምቀት እንዳለ ይናገራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት እንችል ዘንድ በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አለብን፡፡ ካላመንን መንፈስ ቅዱስ ጨርሶ በውስጣችን አያድርም፡፡  
በአንድ ወቅት የቅድስናና የንጽህና እንቅስቃሴ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ እንደሚረዳቸው የተማሩና በዚያም ያመኑ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከእንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ጋር ብንቀላቀል መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ያድራል ብላችሁ ታስባላችሁን? ይህ የሚቻል ቢሆን ኖሮ እምነቱን ለመጠበቅ ጠቢብ ትሆኑ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ምክንያት በእናንተ ላይ የሚወርድ ከሆነ ኢየሱስ ወርዶ ከሐጢያቶቻችን ባላዳነን፤ በዮሐንስ መጠመቅና በመስቀል ላይ መሰቀልም ባላስፈለገው ነበር፡፡ 
መንፈሰ ቅዱስን መቀበል ለሐጢያቶቻችሁ ይቅርታን ባመጣላችሁ በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመናችሁ የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ሐጢያቶቻቸው ለነጹላቸውና በእውነተኛው ወንጌል ይቅርታን ላገኙ የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ 
በዚህ ዘመን በተሐደሶ/መነቃቃት እንቅስቃሴ በሚኩራሩት መካከል አድካሚ የንስሐ ጸሎቶች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል እንደሚያስችሉዋቸው የሚያምኑ አንዳንዶች አሉ፡፡ አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ሐጢያት ቢኖርበትም እንኳን ለንስሐ ከጸለየ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል ይላሉ፡፡  
በመላው ዓለም የተሰራጨው የጴንጤ ቆስጤ ካራዝማቲክ እንቅስቃሴ የጀመረው በ1800ዎቹ አመታት በአሜሪካ ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ብቅ ያለው የሰዎች ስነ ምግባርና ሞራል ከዘቀጠበት ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ነበር፡፡ እንቅስቃሴው የብዙ ሰዎች ልቦች ከታላቁ የገንዘብ ቀውስ የተነሳ ባዘነበት ወቅት ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሄር ቃሎች ላይ የተመሰረተው እምነት አሽቆለቆለ፡፡ አዲስ ሐይማኖታዊ እንቅስቀሴም ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስን (እግዚአብሄርን) በተጨባጭ በመለማመድ ላይ ያነጣጠረው የጴንጤ ቆስጤ ካራዝማቲክ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን ስራዎች በአይን ማየትና የእግዚአብሄርን ቃሎች ሐይል በአካልና በአእምሮ መለማመድን ያቀፈ እንቅስቃሴ ነበር፡፡   
ነገር ግን በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ አደገኛው እንከን ምዕመናንን ከእግዚአብሄር ቃሎች ማራቁና አካላዊ በረከቶችን ለማግኘት የሚተጋ ሐይማኖት ሆኖ መቅረቱ ነው፡፡ በውጤቱም የዚህ የአዲሱ እንቅስቃሴ ተከታዮች የጥንቆላ አጃቢዎች ሆኑ፡፡ ዛሬም እንኳን በጴንጤ ቆስጤ ካራዝማቲክ እንቅስቃሴ የሚኩራሩ አንድ ሰው በኢየሱስ እምነት ካለው ባለጠጋ ይሆናል፤ ከደዌው ይፈወሳል፤ በነገር ሁሉ የተሳካለት ይሆናል፤ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል፤ በልሳን ይናገራል፤ ሌሎችን የሚፈውስበት ሐይልም ይኖረዋል ብለው ያምናሉ፡፡ የጴንጤ ቆስጤ ካራዝማቲክ እንቅስቃሴ በመላው ዓለም ተሰራጭቷል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ሰዎች በውቡ ወንጌል ላይ ባላቸው እምነትና መንፈስ ቅዱስን በመቀበል አቅማቸው ላይ ጋሬጣ ሆንዋል፡፡
የዘመኑ ክርስትና የመነጨው ከ500 አመታቶች በፊት በሉተርና በካልቪን ነው፡፡ ነገር ግን በክርስትና ድንበሮች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ጥናት በጽኑ አልጠለቀም፡፡ ችግሩ ዘመናዊው ክርስትና ከጀመረበት ጅማሬ አንስቶ ብዙ ክርስቲያኖች የእርሱን ጥምቀትና የመስቀል ላይ ሞቱን ፋይዳ ሳይገነዘቡ በኢየሱስ ማመናቸው ነው፡፡ ነገሮችን ይበልጥ ውስብስብ ለማድረግም ሰዎች በተሳሳቱ የክርስትና ትምህርቶችና በአካላዊ ልምምዶች ላይ ብዙ ማተኮር ጀመሩ፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ኢየሱስ በዮሐንስ የተጠመቀው የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ እንደሆነ፣ የተሰቀለውም ለእነዚያ ሐጢያቶች ፍርድን ይቀበል ዘንድ እንደነበር በሚናገረው ውብ ወንጌል ማመን አለባቸው፡፡ የዚህ አይነቱ እምነት መንፈስ ቅዱስን እንድትቀበሉ ያደርጋችኋል፡፡ 
ዛሬ ክርስትና እንደዚህ የወደመው ሰዎች ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን ቸል በማለታቸው ነው፡፡ ኢየሱስ እውነትን እንድናውቅ ነግሮናል፡፡ በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን ማለት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ከፈለጋችሁ ዮሐንስ ኢየሱስን ባጠመቀው ጊዜ ሐጢያቶቻችሁ ወደ እርሱ የተሻገረ መሆኑንና ደሙም ለሐጢያቶቻችን ይቅርታ የተከፈለ ፍርድ እንደነበር እመኑ፤ ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቀበላላችሁ፡፡ 
ብዙ ሰዎች የቤዛነት ወንጌል አድርገው የሚያምኑት የኢየሱስን ደም ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ደም ብቻ የምታምኑ ካላችሁ ከሐጢያት ነጻ ትወጣላችሁን? እንደዚህ ሊሆን እንደሚችል የምታምኑ ከሆነ ምናልባትም ስለ እውነተኛው የኢየሱስ ጥምቀት ያላችሁ እውቀት ያልጠራ ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ አሁንም በልባችሁ ውስጥ ሐጢያት አለ፡፡ ከሐጢያቶቻችሁ መዳንና መንፈስ ቅዱስን መቀበል የምትችሉት የኢየሱስን ጥምቀትና ደሙን እንደ አንድ እምነት በአንድ ላይ ስታቆራኙዋቸው ብቻ ነው፡፡ አለምን እንድናሸንፍ የሚረዳን ብቸኛው እውነተኛ ወንጌል ይህ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ‹‹የሚመሰክሩት መንፈሱና ውሃው ደሙም ሦስት ናቸው፡፡ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ፡፡›› (1ኛ ዮሐንስ 5፡8) ስለዚህ እግዚአብሄር እኛን ከሐጢያቶቻችን ለማዳን ባለው ፍላጎት ዮሐንስ ኢየሱስን እንዲያጠምቀውና ከዚያም እንዲሰቀል አደረገው፡፡  
ብዙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቢያምኑም የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ የማይቀበሉት በዮሐንስ በኩል በሆነው የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በተከናወነው ውብ ወንጌል ስለማያምኑ ነው፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ነገሮች የሚያምኑ ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ያገኛሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በልቦቻቸው ውስጥ ያድራል፡፡ 
ሰዎች ሐጢያቶቻቸው እንደነጹ ሲያውቁ ልባቸው ልክ እንደ ዕረፍት ውሃ ሰላማዊና በእርካታ የተሞላ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሰው ልብ ውስጥ ባደረበት ቅጽበት ሰላም ልክ እንደ ወንዝ በልቡ ውስጥና ከልቡ ውጪ ይፈሳል፡፡ መንፈስ ቅዱስን የመቀበያውን ወንጌል ስናሰራጭ በዚህ እውነት በማመንና በመንፈስ በመመላለስ ጌታችንን እንገናኘዋለን፡፡ ልባችን ከዚህ ቀደም የዚህ አይነት ሰላም ኖሮት አያውቅም፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ኑሮዋችን ሰላማዊ ይሆናል፡፡ ልባችንም ፍጹም ደስተኛ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውብ ወንጌል መራቅ አንችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን እንድናሰራጭ በማነቃቃትና በዚህ የሚያምኑ ሰዎችንም መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ በመፍቀድ ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ይሆናል፡፡
እኛ በውቡ የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ውብ ወንጌል በማመናችን በመንፈስ ቅዱስ ተባርከናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ማመን አለባችሁ፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ በዮሐንስ መጠመቁንና ለሐጢያቶቻቸውም ይኮነን ዘንድ በመስቀል ላይ መሞቱን በሚናገረው የእግዚአብሄር ቃል የማመንን ሒደት መጀመር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን ሲያደርጉ በመጨረሻ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ፡፡