Search

דרשות

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[4-2] ኢየሱስ አምላክ ነው፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 4፡1-11 ››

ኢየሱስ አምላክ ነው፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 4፡1-11 ››
 
በራዕይ 4 ቃል አማካይነት የእኛ ኢየሱስ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን፡፡ በዚህ ዕውቀትም እምነታችን ይጠነክራል፡፡ በቃሉ አማካይነት የተገኘው ዕውቀት ወደ እምነት ተለውጦ በልባችን ውስጥ ሲተከል የእርሱ መምጫ ጊዜ በሚቃረብበትና ጸረ ክርሰቶስም ተገልጦ በእኛ ላይ በሚዝትበት ጊዜ በጌታ ላይ ባለን ብርቱ እምነት ሰይጣንን ተዋግተን ማሸነፍ እንችላለን፡፡
 
ለመጀመሪያዎቹ የታላቁ መከራ የሶስት ዓመት ተኩል መከራዎች መዘጋጀት እንችል ዘንድ አሁን እምነታችንን እየተንከባከብን ነው፡፡ ይህንን እንክብካቤ ሳናደርግ ቀኑን የምንጋፈጥ ከሆነ በእርግጠኝነት እምነታችንን እናጣለን፡፡ ነገር ግን ብርቱ እምነትን ካዘጋጀን በቀጣዩ ቅጽበት ብንሞትም ያዳነን እግዚአብሄር እንደሆነና እኛም እርሱን ሊቋቋመው ከማይችለው ሰይጣን በእጅጉ የሚበልጠው የሁሉን ቻዩ አምላክ ልጆች መሆናችንን በድፍረት እናውጃለን፡፡
 
እንዲህ ለማድረግ ግን በመጀመሪያ ጌታ ሁሉን ቻይ መሆኑንና እኛም የእርሱ ልጆች መሆናችንን ከሙሉ ልባችን ማመን አለብን፡፡ ከእግዚአብሄር አብ ጋር እኩል የሆነው ጌታችን ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ ምን ያህል ዝቅ አለ? እርሱ የሰው ሥጋ ለብሶ የእርሱ ፍጡር ከሆንነው ከእኛም ዝቅ ብሎ ወደ ምድር መጣ፡፡ ጌታ እንዲህ ባለ ውርደት ሳይሆን ከዓለም መሪዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሐይልና ሥልጣን መጥቶ ቢሆን ኖሮ ይፈጠር ነበር? ሐያላን የሐያላን ወዳጆች መሆናቸውና ሥልጣናቸውን በምስኪኑ፣ በተዋረደውና በደካማው ላይ የሚጠቀሙ መሆናቸው የተለመደ ነው፡፡ ጌታ ግን ከእኛ በታች ሆኖ የባርያን መልክ ይዞ ወደዚህ ምድር በመምጣት ከምስኪኖችና ከደካሞች ጋር በመወዳጀት ከሐጢያቶቻቸው አድኖዋቸው የራሱ ሕዝብ አደረጋቸው፡፡
እግዚአብሄር መልካም እረኛና መሐሪ ጌታ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ልጆቹ የምንሆንበትን ክብር ስለሰጠን ይህንን መሐሪና መልካም እረኛ የምናመሰግነው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ ሳለን ለሰጠን ጸጋውና በረከቶቹ ጌታን ከልባችን እናመሰግነዋለን፡፡ ወደ መንግሥቱ ስንገባም ለሥልጣኑና ለክብሩ እያመሰገንነው እንቀጥላለን፡፡ ጌታን በድምጻችን ለማመስገን መተባበር ትልቅ በረከት ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታን ማመስገን የሚችሉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸውና፡፡ እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑ ብቻ የተሰጠው ይህ ትልቅ በረከት ተሰጥቶናል፡፡ እኛ የዚህ ባለ ግርማ ሞገስ አምላክ ሕዝቦችና አገልጋዮቹ መሆናችንን በፍጹም መርሳት የለብንም፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ እንጂ አምላክ አይደለም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሰዎችን እንደሚወልዱና እንስሶችም እንስሶችን እንደሚወልዱ የእግዚአብሄር ልጅም አምላክ ነው፡፡ ሰዎች ውሻ መውለድ እንደማይችሉ ሁሉ የሁሉን ቻዩ አምላክ ልጅም ሰው፤ የእርሱ ተራ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ኢየሱስ አምላክ መሆኑን የማይገነዘቡ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ እንዳዳነን የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡
 
ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ማመን አለብን፡፡ (ዮሐንስ 1፡1) እግዚአብሄር አብ ለኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን አዘጋጅቶ ሥልጣኑን ሁሉ ለነበረው፣ ላለው በፍርድ ቀን ለሚመጣውና ለዘላለም ለሚኖረው ለእርሱ ለኢየሱስ ባስተላለፈለት ጊዜ በእግዚአብሄር ሥልጣን በፍጥረት፣ በደህንነትና በፍርድ አምላክ ግርማ ሞገስ በሁሉም ላይ ሊሰለጥን በእርሱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ፡፡ እኛ በጌታ በማመን የእርሱ ልጆች ስለሆንን ወደ መንግሥቱ እንገባለን፡፡ ለዘላለምም እንኖራለን፡፡ የምናምንበት ኢየሱስ አምላክ ነው፡፡ እኛም ከእርሱ ዘንድ ደህንነታችንን ያገኘን የእግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡
 
ዳግመኛ የተወለዱት የእግዚአብሄር ቅዱሳኖች፣ ሰራተኞችና አገልጋዮች ሊኮሩ ይገባል፡፡ እኛ በዚህ ምድር ላይ ያለን ጥሪት ትንሽ ቢሆንም በመላው ዩነቨርስ ላይ የሚገዙ የእግዚአብሄር ልጆች በመሆናችን እንደ ንጉሥ ልንኮራ ይገባናል፡፡ ሁሉን የሚችለው አምላክ ከዓለም ሐጢያቶች ስላዳነንና ልጆቹ ስላደረገን አመሰግነዋለሁ!
 
በሰማይ ያሉት 24ቱ ሽማግሌዎች ለእግዚአብሄር ያቀረቡት ምስጋና በዚህ ምድር ላይ ባደረገው ነገር ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ሁሉን ስለፈጠረና በፈቃዱም ስለተፈጠሩ እግዚአብሄር ክብርን፣ ውዳሴንና ሐይልን ሊቀበል የሚገባው መሆኑን የሚገልጥ ምስጋና አቀረቡ፡፡
 
እዚህ ላይ እኛ በሚገባ መረዳት የሚኖርብን ነገር በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና እርሱም አምላክ መሆኑን ነው፡፡ እኛ የምናምንበት ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ያዳነን እውነተኛው አምላክ ነው፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ሥልጣን ሁሉ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ የሚሰጠውም በአዳኝ አምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ በዙፋን ላይ ተቀምጦ ፍርድ ሲሰጠን ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉላቸው ሰዎች ወደ አዲሱ ሰማይና ምድር ይገባሉ፡፡ ስሞቻቸው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የማይገኙ ሰዎች ወደ እሳት ይጣላሉ፡፡
 
ስለዚህ በኢየሱስ አለማመን በእግዚአብሄር አለማመን ነው፡፡ በእግዚአብሄር አለማመንም እግዚአብሄርን መቃወም ነው፡፡ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ፣ አዳኝ እንደሆነና የሰማይ ንጉሥ እንደሆነ የማያምኑ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት አስፈሪ ፍርድ የሚገጥማቸው ለዚህ ነው፡፡
 
በእግዚአብሄር ከሚያምኑ መካከል ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ቢሆንም ራሱ አምላክ አይደለም የሚል የተሳሳተ እምነት ያለው የየሆዋ ምስክሮች ተብሎ የሚጠራ ቡድን አለ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አምላክ ባይሆን ኖሮ ከሐጢያቶቻችን ሊያድነን ባልቻለም ነበር፡፡ ምክንያቱም ፍጹም የሆነ ደህንነት ሊሰጠን የሚችለው ራሱ ፍጹም የሆነ ብቻ ነውና፡፡
 
እኛ በጣም ደካሞች ስለሆንን ልባችን በሚለዋወጡት ሁኔታዎች በቀላሉ ይቀያራል፡፡ ደካሞች ብንሆንም ኢየሱስ ክርስቶስን ለዘላለም የምናመሰግነው ለዘላለም የሚኖረውና ለዘላለም ፍጹም የሆነው ኢየሱስ የሐጢያተኞች አዳኝ ስለሆነ ነው፡፡ ጌታን ማመስገን የሚችሉት ሐጢያቶችን በሙሉ ባስወገደው ፍጹም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የዳኑ ብቻ ናቸው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ በአስተሳሰባችንና በአእምሮዋችን ውስጥ ያለው እምነታችን ከቶውኑም ከዓለማዊ ሐይማኖቶች ጋር የሚመሳሰል እምነት መሆን የለበትም፡፡ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ስናውቅና ስናስብ፣ በእርሱ ያለን እምነታችንም ትክክለኛ ሲሆን እውነተኛውን አምላክ እንለማመደዋለን፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ አምላካችን መሆኑን በሚያምነው እምነታችን ልንኖር ይገባናል፡፡ በዚህ እምነትም ጠላቶቻችንን ተዋግተን ማሸነፍ እንችላለን፡፡ በሌላ አነጋገር በአምላካችን በኢየሱስ ስናምን ይህ እምነት ሰይጣንን ስለሚያንቀጠቅጠው ጸንተን እንድንቆምና የዘመን መጨረሻዎቹን መከራዎችና ችግሮች እንድናሸንፍ ያስችለናል፡፡ በሌላ በኩል ኢየሱስ አምላካችን መሆኑን የማናምን ከሆንን ሰይጣን ይስቅብናል፡፡ ከእምነታችንም ያርቀናል፡፡
 
ኢየሱስ ዙፋኑን ከእግዚአብሄር አብ ከተቀበለ በኋላ አምላካችን ሆኖ በዚህ ዙፋን ላይ ተቀመጠ፡፡ ኢየሱስ በመላው ዩኒቨርስ ላይ የሚገዛ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ በራዕይ ቃል አማካይነት እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ የእግዚአብሄርን ሥልጣንና ሐይል ሁሉ ከአብ ተቀብሎዋልና፡፡
 
በዚህ እውነት ላይ ያላችሁ እምነት ሰይጣንን በድፍረት ድል እንድትነሱት ያስችላችኋል፡፡ እኛ የእርሱ ልጆች በመሆናችን የእግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ሐይል ከጀርባችን ስላለ ማንም አያሸንፈንም፡፡ የዘመኑን መጨረሻም በድፍረትና በጀግንነት ማሸነፍ እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ስላደረገው ነገር ሁሉ አመሰግነዋለሁ፤ አውድሰውማለሁ!