Search

דרשות

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[14-2] ቅዱሳን ለጸረ ክርስቶስ መገለጥ ምላሽ መስጠት የሚገባቸው እንዴት ነው? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 14፡1-20 ››

ቅዱሳን ለጸረ ክርስቶስ መገለጥ ምላሽ መስጠት የሚገባቸው እንዴት ነው?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 14፡1-20 ››
 
ጸረ ክርስቶስ በቅርቡ ወደፊት ሲገለጥ ድል ለማድረግ ቅዱሳን በጌታ ባላቸው እምነት ሰማዕት ለመሆን ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ ጸረ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ የሚተገብራቸውን ክፉ ዕቅዶች በሚገባ ማወቅ አለባቸው፡፡ ቅዱሳን እርሱን በእምነት መቃወምና ማሸነፍ የሚችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ሰዎች የስሙን ምልክት ወይም ቁጥሩን እንዲቀበሉ በማድረግ የክርስቲያኖችን እምነት ሊያጠፋ ይሞክራል፡፡
 
እርሱ የክርስቲያኖችን እምነት ለማጥፋት የሚሞክረው እግዚአብሄርን በመቃወምና የጻድቃንን እምነት በማፈራረስ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እንዳይቀበሉ ለመከላከል ስለሚሻ ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ ሰዎችን የእርሱ ባርያዎች በማድረግ እግዚአብሄርን እንዲቃወሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህም ጸረ ክርስቶስና በዚህ ምድር ላይ ገናም የቀሩ የእርሱ ተከታዮች ታላላቅ ቅጣቶችንና መቅሰፍቶችን ይቀበላሉ፡፡
 
ጻድቃን የእምነት ሕይወታቸውን መኖር ያለባቸው እግዚአብሄር በጠላቶቻቸው ላይ የሚያወርዳቸውን የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በግልጽ በመረዳት ነው፡፡ እግዚአብሄር በዘዳግም 32፡35 ላይ ‹‹በቀልና ፍርድ የእኔ ነው›› እንደሚል የልጆቹን ደም በእነርሱ ላይ ይበቀላል፡፡ ስለዚህ በቁጣችን ከምንሸነፍና ፍሬ የሌላቸውን ሥራዎቹን ከምንሰራ ይልቅ እምነታችንን መጠበቅና የድል ሕይወትን መኖር አለብን፡፡ እግዚአብሄር ከሰማዕትነታቸው በኋላ ገናም በዚህ ምድር ላይ የሚቀሩትን ሁሉ የሚያጠፋ የመሆኑን እውነት በማመን ቅዱሳን ጸረ ክርስቶስን መዋጋት አለባቸው፡፡
 
 

ፈጽሞ ሊረሳ የማይገባ የእውነት ቃል፡፡ 

 
የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የተቀበሉ ሁሉ ማስታወስ የሚገባቸው ነገር ቢኖር በጸረ ክርስቶስ ሰማዕት ከሆኑ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ትንሳኤን የሚያገኙትና የሚነጠቁት ሐጢያት የሌለባቸው ቅዱሳን ብቻ መሆናቸውን ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ የሚገለጥበትና ቅዱሳን ሰማዕት የሚሆኑበት ቀን ሲመጣ እያንዳንዱ የእግዚአብሄር ተስፋ እንደሚፈጸም መርሳት የለብንም፡፡
 
በምዕራፍ 14 ከቁጥር 14 ጀምሮ የእግዚአብሄር ቃል ቅዱሳን መነጠቃቸው በጣም የተረጋገጠ መሆኑንና የዚህ ንጥቀት ዘመንም ከሰማዕትነታቸው በኋላ ወዲያውኑ እንደሚመጣ ያስተምረናል፡፡
 
የእኛ ትንሳኤና ንጥቀት የሚመጣው ሰይጣን ሰዎች ምልክቱን እንዲቀበሉ ካደረገ በኋላ እንደሚሆን መርሳት የለብንም፡፡ ጸረ ክርስቶስ ሰማዕት ያደረጋቸው ጻድቃን የመጀመሪያው ትንሳኤና ንጥቀት ባርኮቶች ይጠብቁዋቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ጻድቃን እምነታቸውን ለመጠበቅ የተቀደሰውን ሰማዕትነታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ምክንያቱም የሰይጣንን ምልክት ለመቀበል አሻፈረን ይላሉና፡፡ ስለዚህ ሰማዕት የሚሆኑት ጻድቃኖች በዚህ ምድር ላይ በደከሙት ድካም ልክ ሽልማቶቻቸውን ይቀበላሉ፡፡ የእግዚአብሄርም ክብር ይጨመርላቸዋል፡፡
 
ለእናንተ የሚቀርቡዋቸው ወዳጅ ቅዱሳኖች ወይም ባሮች እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ ስለፈቀደላቸው እግዚአብሄርን ማመስገንና ለእርሱ ክብርን መስጠት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ሰማዕታቶች የተቀደሱ አካሎችን ይዘው በመነሳት በጌታ ይነጠቃሉና፡፡
 
 

እግዚአብሄርን ለሚቃወሙ ሰዎች የተዘጋጁት የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ምንድናቸው? 

 
ቁጥር 19 እንዲህ ይላል፡- ‹‹መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቆርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሄር ቁጣ መጥመቂያ ጣለ፡፡›› ሁልጊዜም የአምላክን ፍቅር የተቃወሙ ሰዎች ቅዱሳኖች ሰማዕትነታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከእግዚአብሄር ዘንድ የእርሱን አስፈሪ መቅሰፍቶች ለመቀበል ታጭተዋል፡፡ ምክንያቱም በምድር ላይ ያሉ ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመቀበል እምቢ ብለው ተቃውመውታልና፡፡ እነዚህ ሰዎች እነርሱን ከሐጢያት ለማዳን በውሃና በደሙ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ደህንነት ባለማመን የእግዚአብሄር ጠላቶች ሆነዋል፡፡ እነርሱ መቀበል ያለባቸው እግዚአብሄር የሚያወርዳቸውን የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ብቻ ሳይሆን ለዘላለምም አስፈሪውን የሲዖል ቅጣት መቅሰፍትም እንደዚሁ መቀበል አለባቸው፡፡
 
እነዚህ እግዚአብሄር በጌታ ባልተነጠቁት ላይ የሚያወርዳቸው ሰባቱ መቅሰፍቶች ናቸው፡፡ ቅዱሳን ሰማዕት ከሆኑ በኋላ እግዚአብሄር ያለ ርህራሄ በንጥቀት ውስጥ ሳይሳተፉ አሁንም ድረስ የሰይጣን ባሮች ሆነው በዚህ ምድር ላይ ለቀሩትና የእግዚአብሄርን ክብር በመሳደብ ለሚቀጥሉት ያዘጋጃቸውን እነዚህን የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ያወርዳል፡፡
 
ታዲያ እግዚአብሄር ጻድቃን ሰማዕት እንዲሆኑ የሚያደርገው ለምንድነው? ምክንያቱም ጻድቃን በዚህ ምድር ላይ ዳግመኛ ካልተወለዱት ጋር አብረው ቢቀመጡ ጊዜያቸው ሲደርስ የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ማውረድ ስለማይችል ነው፡፡ እግዚአብሄር ጻድቃንን ስለሚወድ የእርሱ ክብር ተካፋዮች ይሆኑ ዘንድ ሰማዕት እንዲሆኑ ይፈቅዳል፡፡ እግዚአብሄር የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ከመውረዳቸው በፊት ጻድቃን ሰማዕት የሚሆኑት ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ሰማዕት ለሆኑት ጻድቃን ትንሳኤንና ንጥቀትን ከሰጠ በኋላ እነዚህን መቅሰፍቶች በነጻነት በምድር ላይ ያወርዳቸዋል፡፡
 
 
የሺህው ዓመት መንግሥትና የቅዱሳን ሥልጣን፡፡ 
 
ጌታ ከቅዱሳኑ ጋር አብሮ ወደዚህች ምድር ዳግመኛ ሲመለስ የሺህው ዓመት መንግሥት ዘመን ይጀምራል፡፡ ማቴዎስ 5፡5 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹የዋሆች ብጹዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና፡፡›› ጌታ ከቅዱሳን ጋር አብሮ ወደዚህች ምድር ሲመለስ ‹‹ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ›› የሚለው የመዝሙረ ዳዊት 37፡29 ቃል በሙሉ ይፈጸማል፡፡
 
ጌታ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር አብሮ ወደዚህች ምድር ሲመለስ ይህችን ምድር የራሳቸው የሚያደርጉበትን ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በአስር ከተሞች፤ በሌሎች አምስት ተጨማሪ ከተሞችም ላይ እንዲገዙ ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ ጌታ ሲመለስ ይህችን ምድርና በእርስዋ ያለውን እያንዳንዱን ነገር ያድሳል፡፡ ቅዱሳንም ከእርሱ ጋር አብረው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለሺህ ዓመት በምድሪቱ ላይ እንዲነግሱ ያደርጋቸዋል፡፡
 
በዚህ ዘመን የሚኖሩ ጻድቃን ሊኖሩ የሚገባቸው በምን ተስፋ ላይ ነው? እነርሱ የክርስቶስ መንግሥት በዚህች ምድር ላይ የምትመሰረትበትን ቀን ተስፋ እያደረጉ መኖር አለባቸው፡፡ የጌታ መንግሥት ወደዚህች ምድር ስትመጣ ከእርሱ ንግሥና የሚፈልቁት ሰላም፣ ደስታና በረከቶች በመጨረሻ በምድር ላይ ይሆናል፡፡ በጌታ አገዛዝ ሥር ስንኖር ምንም ነገር አይጎድልንም፡፡ ነገር ግን ከልክ ባለፈ መትረፍረፍና ፍጽምና ውስጥ ብቻ እንኖራለን፡፡
 
የጌታ መንግሥት ወደዚህች ምድር ስትመጣ ጻድቃን ሲያልሙዋቸው የነበሩት ሕልሞችና ተስፋዎች በሙሉ ይፈጸማሉ፡፡ ጻድቃን በዚህች ምድር ላይ ለሺህ ዓመት ከኖሩ በኋላ ወደ ዘላለማዊው መንግሥተ ሰማይ ይገባሉ፡፡ በአንጻሩ ግን እግዚአብሄርን የተቃወሙ ሰዎች ዘላለማዊ ወደሆነው የእሳትና የዲን ባህር ውስጥ ተወርውረው ቀንና ሌሊት ዕረፍት እስከማይኖራቸው ድረስ ለዘላለም ይሰቃያሉ፡፡
 
ስለዚህ ጻድቃን የጌታን ቀን በመጠባበቅ በተስፋ መኖር አለባቸው፡፡ ጻድቃን ሁሉ ሰማዕትነት፣ ትንሳኤ፣ ንጥቀትና የዘላለም ሕይወት በሙሉ የእነርሱ እንደሆኑ መርሳት የለባቸውም፡፡ ይህንን የእውነት ቃል በልባችሁ ውስጥ በመያዝ እስከ አሁን የሰማችሁትን በጽናት አጥብቃችሁ የሙጥኝ በሉ፡፡
ጻድቃን ጌታ እስከሚመለስበት ቀን ድረስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመስበክና ተስፋቸውን በመንግሥተ ሰማይ ላይ በማኖር ይኖራሉ፡፡ ጻድቃን በእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ሥልጣንና በዚህች ምድር ላይ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የመስበክ ሥልጣን አላቸው፡፡
 
 
በዚህ ጨለማ ዘመን ውስጥ የሚኖሩ ቅዱሳን ምን ማድረግ አለባቸው? 
 
ይህ ዘመን የጨለማ ዘመን መሆኑ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ዘመን መኖርም ይበልጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለሐጢያተኞች መስበክና እነርሱን መንከባከብ አለብን፡፡ ጻድቃን በኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የእግዚአብሄርን ፍቅርና የሐጢያቶቻቸውን ስርየት በመላው ዓለም መስበክ አለባቸው፡፡ አሁን ጻድቃን ሊያደርጉት የሚገባቸው ይህንን ነው፡፡
 
የቀረበውን ይህንን ዕድል ካጡ ዳግመኛ ፈጽሞ ሊያገኙት አይችሉም፡፡ የዚህ ዓለም ፍጻሜ በጣም ሩቅ ስላልሆነ የውሃውናና የመንፈሱን ወንጌል አብዝተን መስበክና የጠፉትን ነፍሳቶችም በእግዚአብሄር መንግሥት ተስፋ ልንከባከባቸው ይገባናል፡፡ ጻድቃን ሊያደርጉት የሚገባቸው መልካም ነገር ይህ ነው፡፡
 
በዚህ ዓለም ውስጥ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ቃል ባይኖራቸውም እንኳን በኢየሱስ እንደሚያምኑና ጌታን እያገለገሉ እንደሚኖሩ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ እውነት ሳይኖራቸው የሐይማኖት ሕይወታቸውን የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ሐሳዊ ነቢያት ናቸው፡ እነዚህ ዋሾዎች በኢየሱስ ስም የምዕመናኖችን ቁሳዊ ሐብቶች የሚበዘብዙ አሳቾች ናቸው፡፡
 
ስለዚህ እኛ በእነዚህ ሐሳዊ ነቢያቶች ተታለው ሳሉ የእምነት ሕይወታቸውን ለመኖር የሚሞክሩትን ልናዝንላቸው ይገባናል፡፡ እነዚህ የስም ክርስቲያኖች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳይዙ የእምነት ሕይወታቸውን በመኖራቸው ሐጢያተኞች ሆነው ይቀራሉ፡፡ በኢየሱስ እንደሚያምኑ ቢናገሩም በእግዚአብሄር ሕግ እርግማን ውስጥ መኖራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እነርሱ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቢያምኑ በልባቸው ውስጥ ያሉት ሐጢያቶች በሙሉ ተወግደው እንደ በረዶ እንደሚነጹና የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታም እንደሚሰጣቸው እውነቱን ባለማወቅ ሁልጊዜም በሐጢያት ይኖራሉ፡፡
 
ነገር ግን በአንጻሩ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑና ይህንን የሚሰብኩ የእግዚአብሄር ባሮች በሰላም ይኖራሉ፡፡ የእግዚአብሄር ባሮችና የእርሱ ሕዝቦች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ይደሰታሉ፡፡ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች ሁሉ በአንድ ጊዜ በመውሰድና ለእነዚህ ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ በመኮነን የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዲወገዱ አድርጓል፡፡ በዚሁ የስርየት ደህንነት ባመንሁ ጊዜ ክፉኛ ያጎበጡኝ ሐጢያቶቼ በሙሉ ተወግደዋል፡፡ አሁን ጻድቅ ሆኛለሁ›› በማለት ይመሰክራሉ፡፡
 
በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ቅዱሳን በእነዚህ ምስክርነቶቻቸው ለእግዚአብሄር ክብርን ይሰጣሉ፡፡ ይህ እምነት ያላቸው ሰዎች በመጨረሻ ሰማይን ተስፋ ማድረግ ይችላሉ፡፡
 
 
የመጀመሪያው ትንሳኤ ለቅዱሳን የተቀመጠ ሁነት ነው፡፡ 
 
በቅርቡ ጌታ ፈጥኖ ወደዚህች ምድር ይመለሳል፡፡ በጣም በቅርቡ ጸረ ክርስቶስ የሚሆነው ሰው ይገለጥና በብዙ ሰዎች ቀኝ እጅ ወይም ግምባር ላይ ምልክቱን ያትማል፡፡ ይህ ጊዜ ሲመጣ የጌታ ዳግመኛ ምጽዓት፣ እንደዚሁም የቅዱሳን ሰማዕትነት፣ ትንሳኤና ንጥቀት ሁሉም እንደተቃረቡዋችሁ መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ይህ ቀንና ሰዓት ሲመጣ ለቅዱሳን የደስታ ቀን፤ ዳግመኛ ላልተወለዱ ሐጢያተኞች ግን የሐጢያት ፍርዳቸውን የሚቀበሉበት ቀን እንደሚሆን መገንዘብ ይገባችኋል፡፡
 
ቅዱሳኖች በሙሉ ሰማዕትነታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ትንሳኤን ያገኙና ከጌታ ጋር በበጉ ሰርግ እራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እናንተና እኔ በዚህ ጊዜ ሰማዕት ከሆንን አካሎቻችን ወዲያው ትንሳኤን አግኝተው ይነጠቃሉ፡፡ ከእኛ በፊት በነበሩት ቅዱሳን አካሎች ላይ የሆነው ነገር አካሎቻቸው ወደ አፈርነት ተቀይረው ይሁን ወይም ከእንግዲህ ወዲያ በእነርሱ ውስጥ የቀረ ቅርጽ አይኖር ይሆን ችግር የሚፈጥር አይደለም፡፡ ይህ ጊዜ ሲመጣ ቅዱሳን የአሁኑን ደካማ አካል ይዘው ሳይሆን ፍጹም የሆነ አካል ይዘው ይነሳሉ፡፡ ጻድቃን በዚህ ጊዜ ቅዱስ አካሎችን ይዘው በመነሳት ከጌታ ጋር ለዘላለም ይኖራሉ፡፡
 
አስቸጋሪ ወቅቶች ቢጠብቁንም ጸረ ክርስቶስ መጥቶ ሲያሳድደን አሁን በምናዳምጠው የእግዚአብሄር ቃለ በማመን እምነታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ መጠበቅ አለብን፡፡ እናንተና እኔ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስላመንን ሁላችንም በቅዱሳን ሰማዕትነት፣ በመጀመሪያው ትንሳኤያቸውና ንጥቀታቸው ውስጥ እንደምንሳተፍ መርሳት የለብንም፡፡
 
በዚህ እውነት ላይ ካላችሁ እምነት ፈቀቅ ማለት የለባችሁም፡፡ ጸረ ክርስቶስን የሚዋጋና የሚያሸንፍ ሕይወት ልትኖሩ ይገባችኋል፡፡ ይህ ቀን እስኪመጣ ድረስ እውነትን በማመን ከእኛ በፊት ከዳኑት ጋር አብረን የእግዚአብሄርን ቃል መያዝና ጌታን በእምነት መከተል አለብን፡፡
 
 
አሁንም እንኳን ሰዎችን የሚያስቱ ብዙ ዋሾዎች አሉ፡፡ 
 
አሁንም እንኳን እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው የሐሰት እምነትን እያስተማሩ ነው፡፡ በተለይም ለጉባኤዎቻቸው የቅድመ መከራን ንጥቀት ትምህርት በማቀነቀንና በማስተማር የሰባቱ ዓመት ታላቁ መከራ እንደማይመለከታቸው ለማሳመን የሚሞክሩ ብዙ ውሸታሞች አሉ፡፡
 
በአንጻሩ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳን ሰማዕትነትና ንጥቀት የመጀመሪያዎቹ ሦስት አመታት ተኩል መከራ ጥቂት ሲያልፍ እንደሚመጣ በግልጽ ይመሰክርልናል፡፡ በእነዚህ ውሸታሞች አንታለል፡፡ በፋንታው የታላቁ መከራ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ተኩል ሲቀርቡን ሁላችንም ሰማዕት እንደምንሆንና ከዚያ በኋላም ወዲያውኑ ትንሳኤ አግኝተን እንደምንነጠቅ አውቀን እንመን፡፡
 
ስለዚህ የሰባቱ ዓመት ታላቁ መከራ እንደማይመለከታቸው ከሚያስተምሩ ሐሳዊ ነቢያቶች መራቅ አለባችሁ፡፡ እውነተኛ ቅዱሳን ሰማዕትነታቸው፣ ትንሳኤያቸው፣ ንጥቀታቸውና የበጉ ሰርግ እራት ሁሉም የመከራው የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ተኩል ጥቂት እንዳለፈ እንደሚመጡ ያምናሉ፡፡
 
 
ታዲያ አሁን ሁላችንም መኖር የሚገባን እንዴት ነው? 
 
አሁን ጌታን ማለትም ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች የተሸከመውን፣ በመስቀል ላይ የደማውንና ዳግመኛ ከሙታን የተነሳውን ጌታ አዳኙ አድርጎ የሚያምን ማንኛውም ሰው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በልቡ ውስጥ ይሰተዋል፡፡
 
መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኩል የነገራችሁን በጆሮዎቻችሁ በመስማትና በልባችሁ በማመን በእግዚአብሄር ላይ ባላችሁ እምነት ልትኖሩ ይገባል፡፡ ቅዱሳን ሁሉ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በመመራት የእምነት ሕይወታቸውን መኖር አለባቸው፡፡ ማንም ብቻውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ አይችልም፡፡ መጠበቅም ሆነ ማገልገል አይችልም፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን አስቀድመው ዳግመኛ ለተወለዱት ቅዱሳን እንኳን በጣም አስፈላጊ የሆነችው ለዚህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ቤተክርስቲያኑንና የእርሱን አገልጋዮች እንዲህ አድርጎ በምድር ላይ አቁሞዋቸዋል፡፡ በእነርሱ አማካይነትም ጠቦቶቹን ይመግባል፡፡ በተለይ የዘመኑ መጨረሻ ይበልጥ እየቀረበን ሲመጣ የእግዚአብሄር ሥራዎች ይበልጥ ክቡርና ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ታማኝ ሕይወት እንድትኖሩ እጸልያለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ፡፡ የዘመኑ መጨረሻ እየቀረበ ሲመጣ ጻድቃን አብረው ለመቀመጥ፣ ለመጸለይ፣ ለመጽናናት፣ ለመያያዝ፣ እርስ በርስ ለመደጋገፍ፣ ለጌታ ለመኖርና በአንድ ልብና በአንድ ዓላማ ለመቀናጀት ይበልጥ ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡
 
እግዚአብሄር ለቅዱሳን ሰማዕትነትን፣ ትንሳኤን፣ ንጥቀትንና የዘላለም ሕይወትን ፈቅዶዋል፡፡ ሁላችንም ጸረ ክርስቶስን ተዋግቶ የሚያሸንፍ ሕይወትን በመኖር በእግዚአብሄር ፊት በታማኝነት እንቁም፡፡ ሐሌሉያ!