Search

דרשות

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[16-2] ሰባቱ ጽዋዎች ከመውረዳቸው በፊት ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር… ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 16፡1-21 ››

ሰባቱ ጽዋዎች ከመውረዳቸው በፊት ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 16፡1-21 ››
 
ከሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ውስጥ የመጀመሪያው መቅሰፍት የቁስል መቅሰፍት፣ ሁለተኛው መቅሰፍት ባህር ወደ ደም የሚለወጥበት መቅሰፍት ሲሆን ሦስተኛው መቅሰፍት ንጹህ ውሃ ወደ ደም የሚለወጥበት መቅሰፍት ነው፡፡ አራተኛው መቅሰፍት ሰዎች በፀሐይ ሙቀት ተቃጥለው የሚሞቱበት መቅሰፍት ነው፡፡
 
ዋናው ምንባብ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹አራተኛውም ጽዋውን በጸሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት፡፡ ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሄርን ስም ተሳደቡ፡፡ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም፡፡›› ይህም እግዚአብሄር ፀሐይን ወደ ምድር እንደሚያስጠጋና ሕይወትን አቃጥሎ እንደሚገድል ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ይህ እንዲሆን ሲፈቅድ ከመሬት በታች ጥልቅ ዋሻ ቆፍረው እዚያ ቢደበቁም እንኳን ማናቸውም ከሚያቃጥለው የፀሐይ ሙቀት ማምለጥ አይችሉም፡፡ ለዚህ መቅሰፍት የተዘጋጁትን ከፍተኛ ብቃት ያላቸው የአየር መቅዘፊያዎችን በመጠቀም የእግዚአብሄርን መቅሰፍት ማቆም አይችሉም፡፡ ሁሉም ከመሞት በቀር ምርጫ አይኖራቸውም፡፡
 
የዚህ መቅሰፍት ጊዜ ሲመጣ በእነርሱ ላይ ምን እንደሚደርስባቸው ማሰብ እንችላለን፡፡ ቆዳቸው ይላጣል፡፡ ከውስጥ ያለው ሥጋቸውም የተቀቀለ ቀይ ሆኖ እየበሰበሰ ይወድቃል፡፡ ያን ጊዜ ሁሉም በቆዳ ካንሰር ይሞታሉ፡፡
 
ያም ሆኖ በሚያቃጥለው የፀሐይ ሙቀት እየሞቱ ሳሉ እንኳን ከሐጢያቶቻቸው ንስሐ አይገቡም፡፡ የእግዚአብሄር መቅሰፍት አስገራሚ ነው፡፡ በዚህ መቅሰፍት ውስጥ እያለፉ ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ያሉትም እነዚህ ሰዎች የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ እነርሱ ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ሲሉ የእግዚአብሄር መቅሰፍቶች ይቀጥላሉ፡፡
 
ዋናው ምንባብ እንዲህ ይላል፡- ‹‹አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፡፡ ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፡፡ ከስቃያቸውና ከቁስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም፡፡›› የዛሬውን ዓለም ስንመለከት አሁኑኑ በእግዚአብሄር ሊፈረድባቸው የሚገባቸው እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አንመለከትምን? ነገር ግን እግዚአብሄር ቁጣውን በትዕግስት አፍኖ በመያዙ እስከ አሁን ድረስ አልተፈረደባቸውም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ሳያምኑ ቢሞቱ ኖሮ እግዚአብሄር በማይሞቱ አካሎች ወደ ሕይወት ያመጣቸውና ለዘላለም በሚነደው የሲዖል እሳት ውስጥ ለዝንተ ዓለም ይሰቃያሉ፡፡
 
ይህ በሚሆንበት ጊዜ ስቃያቸው ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ እጅግ ታላቅ በመሆኑ መሞት ይፈልጋሉ፡፡ የሲዖል ስቃይ ግን ለዘላለም ይቆያል፡፡ እግዚአብሄር የሚፈርድባቸው ሰዎች መሞት የሚፈልጉበት ሞት ግን ከእነርሱ የሚሸሽበት ዘመን ይመጣል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር ለዘላለም ይፈርድባቸው ዘንድ ከመሞት ይከለክላቸዋልና፡፡
 
ስድስተኛው መቅሰፍት የአርማጌዶን መቅሰፍት ነው፡፡ ሰባተኛው መቅሰፍትም የታላቁ መሬት መናወጥና የታላቅ በረዶ የመጨረሻ መቅሰፍት ነው፡፡
 
ቁጥር 17-21 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ፡- ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ፡፡ መብረቅና ድምጽም፣ ነጎድጓድም፣ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ፡፡ ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፤ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ፡፡ ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሄር ፊት ታሰበች፡፡ ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራራዎችም አልተገኙም፡፡ በሚዛንም አንድ ታላንት (አንድ ታላንት ሦስት ፈረሱላ የሚያህል ነው) የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፡፡ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሄርን ተሳደቡ፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና፡፡››
 
የላይኛው ምንባብ እግዚአብሄር ሰባተኛውን ጽዋ ሲያፈስስ ፕላኔቷን ታላቅ የመሬት መናወጥ እንደሚመታት፣ መላው ዓለምም ለሦስት እንደሚከፈልና በዚህ ምድር ላይ ገናም የቆሙ ሕንጻዎች እንደሚፈራርሱና ከእነርሱ አንዱም እንደማይተርፍ ይነግረናል፡፡ ይህ ዓለም አሰቃቂ በሆነው የእግዚአብሄር ቁጣ ስለሚመታ ደሴቶችና ተራሮችም በሙሉ ይጠፋሉ፡፡ 
 
ይህ በሚሆንበት ጊዜ የሒማልያ ተራሮች ገናም ቆመው ይቀራሉን? በእርግጥም አይቆሙም! ታላላቅ ተራሮች በሙሉ በሕይወት ባሉ ሰዎች ዓይኖች ፊት ይወድማሉ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ተራራ ያለ ምንም ፍንጭ ተኖ ይጠፋል፡፡ ምንባቡ 100 ፓውንድ (45 ኪሎ) የሚመዝኑ ታላላቅ በረዶዎችም በዚህች ምድር ላይ እንደሚወርዱ ይነግረናል፡፡ በእነዚህ የመሬት መናወጦችና በረዶዎች ውስጥ አልፎ የሚተርፍ ሰው ሊኖር ይችላልን?
 
ዮሐንስ ራዕይ 18 የእግዚአብሄር ቁጣ በእርሱ ባላመኑትና ቃሉን ቸል ባሉት ላይ እንደሚወርድ ይነግረናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች መለኮት የሆኑ ይመስል ‹‹እኔን ፈጽሞ የእግዚአብሄር ቁጣ አይነካኝም፡፡ መቼም ቢሆን እርሱ በእኔ ላይ አይፈርድም›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ቁጣ በትክክል የሚወርደው በራሳቸው ትዕቢትና ዕብሪት በተሞሉ በእነዚህ ዓይነት ሰዎች ላይ ነው፡፡ ይህች ዓለም እግዚአብሄር በሚያፈስሳቸው በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በምትመታበት ጊዜ እንደምትጠፋ ማመን አለብን፡፡
 
 

በእግዚአብሄር ቃል ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ 

 
እግዚአብሄር ይህንን ዓለም እንደሚያጠፋው ነገሮናል፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም ለዘላለም አይቆይም፡፡ በመሆኑም እየተቃረበ የመጣውን ፍጻሜ የሚጋፈጡ ሁሉ በዚህ እውነት ይበልጥ በጽናት ማመንና መንፈሳዊ እምነታቸውን መከተል አለባቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ከመንፈሳዊ እንቅልፋቸው መንቃት አለባቸው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ሕይወታችሁን የኖራችሁት በምን ዓይነት እምነት እንደነበር አላውቅም፡፡ ነገር ግን ትኩረታችሁን በመጨረሻው ዘመን እየሆነ ባለው ነገር ላይ የማድረጉ፣ የመንቃቱና የማመኑ ጊዜ አሁን ነው፡፡ ስለዚህ በራዕይ ውስጥ የተተነበዩትን መቅሰፍቶች በትክክል ማወቅና ንቁ መሆን አለባችሁ፡፡
 
ጌታችን ይህች ምድር በቅርቡ በሰባቱ የእግዚአብሄር ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሥር እንደምትወድቅ ነግሮናል፡፡ ስለዚህ ሰዎች በሚገባ ባይቀበሉትም እንኳን ወንጌልን መስበካችንን እየቀጠልን ጌታን መጠበቅ አለብን፡፡
 
የዚህች ዓለም ዕጣ ፈንታ አሁን አደጋ ላይ ነው፡፡ የዛሬዋ ዓለም ከጦርነት ስጋት እስከ አልተረጋገጠ የአየር ጠባይ፣ የሥነ ምህዳር ማሽቆለልቆል፣ እየበዙ ባሉ ማህበራዊ ግጭቶችና ሁሉም ዓይነት በሽታዎች ድረስ ለሁሉም ዓይነት አደጋዎች የተጋለጠች ናት፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ይህ ዘመን የኖህን ዘመን እንደሚመስል ነግሮናል፡፡ ይህ ዘመን የኖህን ዘመን የሚመስል ነው ማለት ይህች ዓለም በአሁኑ ጊዜ ወደ መጨረሻው ዘመንዋ ገብታለች ማለት ነው፡፡ ሰዎች እንደ መብላት፣ መጠጣት፣ ማግባትና እንደዚህ ያሉ አስደሳች ጉዳዮች ባሉ የሥጋ ነገሮች ብቻ መደሰታቸው የመጨረሻው ዘመን ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ እነርሱ የእግዚአብሄርን ፍርድ ሊቀበሉ ይገባቸዋል፡፡ በኖህ ዘመንም እንደዚሁ እነዚህ ሰዎች ኖህ የነገራቸውን ስላላዳመጡ ከኖህና ከስምንት ቤተሰቡ ጋር ሁሉም ጠፉ፡፡ መጭው ዓለምም እንደዚሁ ይህንን የሚመስል ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ተስፋ የሰጣቸው አብዛኞቹ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጻፉት ይፈጸማሉ፡፡ ከእነዚህም 5 ከመቶ የሚሆኑት ገናም የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ የቀሩት ግን ሁሉም ቀደም ብለው ተፈጽመዋል፡፡ ጌታ ተስፋ የሰጠው የደህንነትና የመቤዠት ቃልም በሙሉ ተፈጽሞዋል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ፍርድ የሚጠብቀው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑትን ብቻ ነው፡፡ ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን የሚጠብቃቸው ጻድቃን ገብተው የሚኖሩበት የሺህው ዓመት መንግሥትና አዲስ ሰማይና ምድር ብቻ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር መሐሪ ነው፡፡ ከጻድቃንም ጎን ይቆማል፡፡ እግዚአብሄር ቁጣው ለሚገባቸው ሰዎች ቁጣውን በእርግጠኝነት ያወርድባቸዋል፡፡ ምህረቱ ለሚገባቸውም ምህረቱን እንደሚለግሳቸው በሚገባ የተረጋገጠ ነው፡፡
 
እነዚህ መቅሰፍቶች የሚወርዱት መቼ ነው? የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች የሚወርዱት የ666 ምልክት በዚህ ዓለም ላይ ታውጆ ቅዱሳኖች ከተቃወሙትና ሰማዕት ከሆኑ በኋላ ነው፡፡ የመጀመሪያው ትንሳኤ፣ የሺህው ዓመት መንግሥትና በታላቁ ነጭ ዙፋን ላይ የተቀመጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ይመጣል፡፡ ይህንን ተከትሎም ዘላለማዊው የሰማይ መንግሥት ይከፈታል፡፡ በእግዚአብሄር መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ዕውቀት ላይ መድረስ ያለብን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት ነው፡፡
 
ኢየሱስ ዳግመኛ ከሞት የመነሳቱን እውነታ ታምናላችሁን? ጌታ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱና በደሙ አማካይነት እንዳስወገደ ታምናላችሁን? ጌታችን የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በውሃውና በደሙ ወስዶ በሦስት ቀናት ውስጥ ዳግመኛ ከሙታን በመነሳት አሁን በአባቱ ዙፋን ቀኝ ተቀምጦዋል፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ሐጢያቶች በግልጽ ተወግዶዋል፡፡ ክርስቶስ ዳግመኛ ከሙታን እንደተነሳ እነርሱም ደግሞ ይነሳሉ፡፡
 
ስለዚህ ቅዱሳን ከጌታ ጋር ይከብራሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ለጌታ ብዙ መከራዎችን ይጋፈጣሉ፡፡ ሆኖም የዚህ ዘመን መከራዎች እነርሱን ከሚጠብቃቸው ክብር ጋር ሊነጻጸሩ የሚገባቸው አይደሉም፡፡ ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳኖችን የሚጠብቃቸው ብቸኛው ነገር ይህ ክብር ነውና፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ስለ ወደፊቱ መጨነቅ አይኖርባቸውም፡፡ ጻድቃን ማድረግ የሚኖርባቸው ነገር ቢኖር ቀሪ ሕይወታቸውን ለወንጌል መኖርና በእምነታቸው መኖር ነው፡፡ ራሳችንን ነፍሳቶችን ለማዳን ሥራ መቀደስና ዓለምንም መተው አለብን፡፡
 
 

ቀሪ ሕይወታችንን ለእግዚአብሄር እንቀድስ፡፡ 

 
በመካከላችን ወንጌልን የሚክድ ሰው ሊኖር ይችላል በማለት ተጨንቄአለሁ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚክድ ማንም ሰው በመጨረሻም ጌታን ራሱን ይክዳል፡፡ ደካሞች ብንሆንም ጌታ በፈጸመው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ካመንንና ከተከተልን ሁላችንም በእምነት መኖር እንችላለን፡፡ ቅዱሳን በራሳቸው ጥበብና ጉልበት ብቻ መኖር አይችሉም፡፡ እንደዚያ ቢያደርጉ ኖሮ መጨረሻቸው እምነታቸውን መካድና በገዛ ራሳቸው ላይ ጥፋትን ማወጅ ይሆን ነበር፡፡ ይህንን ለማስወገድ በእምነት መኖር አለብን፡፡
 
ጌታችን የሰው ዘር 666 ምልክትን እንዲቀበል ለምን ፈቀደ? ይህንን ያደረገው ስንዴውን ከገለባው ለመለየት ነው፡፡ ቅዱሳኖች እንዲነጠቁ ከመፍቀዱ በፊት እግዚአብሄር ሊያደርገው የሚገባው የመጀመሪያው ነገር ስንዴውን ከገለባው በግልጽ መለየት ነው፡፡
 
ቅዱሳኖች የሚዋጉት መንፈሳዊ ተጋድሎ አለ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን የእግዚአብሄርን ጠላቶች ከመዋጋት መሸሽ የለባቸውም፡፡ ሰይጣንን ለመዋጋት የሚያመነቱ ከሆኑ ሰይጣን ክፉኛ ያጠቃቸዋል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ሁሉ ለራሳቸውም ሲሉ እንኳን መንፈሳዊ ውጊያዎችን መዋጋት አለባቸው፡፡ ቅዱሳን የሚዋጉዋቸው መንፈሳዊ ውጊያዎች በሙሉ ተገቢ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቅዱስ እግዚአብሄርን ለመከተል ሰይጣንንና የእርሱን አገልጋዮች ማሸነፍ አለበት፡፡
 
ቅዱሳን ለእግዚአብሄር መንግሥት መዋጋት አለባቸው፡፡ ለእግዚአብሄር መንግሥትም መሰደድና በዓለም ሰዎች መጠላት አለባቸው፡፡ ቅዱሳን ለጌታ ይዋጉ ዘንድ የተሰጣቸው ዕድል በራሱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ለእግዚአብሄር የመዋጋቱ ይህ ዕድል ለእናንተ ተሰጥቶዋችሁ ከሆነ ለዚህ ዕድል እርሱን ልታመሰግኑት ይገባችኋል፡፡ እንዲህ ያለ ገድል መልካም ገደል ነው፡፡ ምክንያቱም ለእግዚአብሄር ጽድቅ የሚደረግ ተጋድሎ ነውና፡፡
 
እግዚአብሄር ጻድቃንን ይረዳል፡፡ በሕይወታችን ብዙ ቀኖች አልቀሩንም፡፡ የእኔ ተስፋና ጸሎት ሁላችንም ቀሪውን ዘመናችንን መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን እየተጋደልን በጌታ ፊት እስከምንቆም ድረስም መንፈሳዊ ሥራዎችን እየሰራን እንድንኖር ነው፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ምንም ቢናገሩም መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን መጋደል፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችን ማፍራትና እነዚህን ፍሬዎች በጌታችን ፊት ማኖር ይገባናል፡፡ ጌታችን የሚመጣበት ቀን ሲደርስ ጌታ ዕንባዎቻችንን ያብስና ዳግመኛ በማናለቅስበት፣ ዳግመኛ በማንሰቃይበትና ዳግመኛ ሐጢያት በማይገኝበት ስፍራ እንድንኖር ይፈቅድልናል፡፡
ሁላችንም በእምነት እንኑር፡፡ በዚህ እምነትም ሁላችንም ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንግባ፡፡