Search

Khotbah-Khotbah

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[2-9] በውሃውና በመንፈሱ ድናችኋልን? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡18-29 ››

በውሃውና በመንፈሱ ድናችኋልን?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡18-29 ››
 
የትያጥሮን ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄርን ሥራዎች በፍቅር፣ በእምነትና በትዕግስት አገለገለች፡፡ በጊዜ ሒደት ውስጥም ምግባሮችዋ እየተሻሻሉ ሄዱ፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ በክፉ ነቢይት የተጠቃች ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ በሌላ አነጋገር ስህተቶችዋ ከአባላቶችዋ አንዳንዶቹ ጣዖትን ለማድረግና ዝሙትን ለመፈጸም በዚህች ንስሐ ያልገባች ሐሳዊት ነቢይት መታለላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ጌታ የትያጥሮንን ቤተክርስቲያን ንስሐ እንድትገባና የቀደመውንም እምነቷን እስከ ፍጻሜው ድረስ አጥብቃ እንድትይዝ ጠየቃት፡፡ እምነታቸውን እስከ መጨረሻ ድረስ ለሚጠብቁትም በአሕዛቦች ላይ ሥልጣንንና የንጋት ኮከብን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል፡፡ 
 
 
የኤልዛቤል በኣል፡፡ 
 
ኤልዛቤል የንጉሥ አክዓብ ሚስት በሆነች ጊዜ አረማዊ የሆነውን አምላክዋን በኣልን ወደ እስራኤል ይዛ የመጣች አህዛብ ልዕልት ነበረች፡፡ (1ኛ ነገሥት 16፡31) በኣል ሰዎች ብልጽግናን ሲፈልጉ የሚሰግዱለት አረማዊ የጸሐይ አምላክ የፊንቄያውያን ጣዖት ነበር፡፡ የዚህ አምላክ ምስሎች ተቀርጸው ይሰገድላቸው ነበር፡፡ ተከታዮቹም ለቤተሰባቸውና ለምድሪቱ ፍሬያማነት ይጸልዩ ነበር፡፡ ይህ በመላው ዓለም ላይ ከሚገኘው ምድርንና ተፈጥሮን ከማምለክ ጥቅል የአረማውያን ምግባር ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለምሳሌ በአንድ ትልቅ ዓለት ላይ አማልክትን በማኖር ዓለቱን እንደ አምላክ ማምለክ ተፈጥሮአዊ ነገሮችን የማምለክ የተለመደ አረማዊ ምግባር ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ሐይማኖታዊ ምግባርና እምነት ፓንቴይዝምን (አምላክ በሁሉም ነገር ውስጥ ይገኛል) በያዙት ዘንድ ይታወቃል፡፡ 
 
ኤልዛቤል ይህንን አረማዊ ሐይማኖት በማስተዋወቅዋ በኣል ለሕዝበ እስራኤል አንድ ታላቅ አምላከ ጣዖት ሆነ፡፡ እውነተኛውን የሆዋ አምላክ ብቻ ማምለክ የለመደው ንጉሥ አክዓብ ከዚህች አረማዊ ሴት ጋር በመጋባቱ ምክንያት በኣልን አመለከ፡፡ ብዙ እስራኤላውያንም የእርሱን ዱካዎች ተከትለው እውነተኛውን አምላክ በመተው በበኣል አምልኮዋቸው ጣዖትን አመለኩ፡፡ 
 
እግዚአብሄር የትያጥሮን ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሐሳዊቷን ነቢይት እምነት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገባ በመፍቀዱ ነቀፈው፡፡ እግዚአብሄር ኤልዘቤልንና ተከታዮችዋን ንስሐ እንዲገቡ በማዘዝ ቢያምጹ ታላቅ መከራንና ጥፋትን እንደሚያመጣባቸው አስጠነቀቃቸው፡፡ 
 
ይህ ማለት እውነተኛዋ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ይቆጣጠርዋት ዘንድ ሐብትንና ቁሳዊ ንብረቶችን አትፈቅድም ማለት ነው፡፡ እስራኤሎች የጸሐይ አምላክ የሆነውን በኣልን ለልምላሜና ለብልጥግና ሲያመልኩ እንደነበረው የዘመኑ ምዕመናን ዓለምን አምላካቸው አድርገው ሊሰግዱለት አይችሉም ማለት ነው፡፡ 
 
3ኛ ዮሐንስ 1፡2 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወዳጅ ሆይ ነፍስህ እንደሚከናወን በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ፡፡›› የሐዋርያውን የዮሐንስን እምነት ስንመለከት የመጀመሪያ ትኩረቱ መንፈሳዊ ክንውንነት እንደነበር እናያለን፡፡ ዮሐንስ ለነፍሳት ክንውን ሁሉ የሚከተል እንጂ የሚቀድም ያልሆነ የሌሎች ነገሮችን ክንውንነት አስቦዋል፡፡ ታዲያ ይህ እምነት በዛሬው ዓለም ውስጥ እንዴት ተለወጠ? ይህ እምነት ዓለማው መከናወንን የእምነት ፊት መሪ በማድረግና ለመንፈሳዊ ደህንነት ማንኛውንም ሌላ ትኩረት ቸል በማለት የሥጋ ባርኮቶችን ብቻ የሚሻ የተበላሽ እምነት ሆነ፡፡ ብዙዎች በኢየሱስ የሚያምኑት ነፍሳቸውን ለማበልጠግ ሳይሆን አስቀድመው ሥጋቸውን ብቻ ለማበልጠግ ነው፡፡ 
 
በዙሪያችን ተከታዮቻቸው ላቀረቡት አምልኮ ብልጥግናንና ጤናን እንደሚሰጡ የሚናገሩ እንደ ሐሺሽ መርዛማ የሆኑ ብዙ የሐይማኖት አምልኮተ ሰቦች አሉ፡፡ የኤልዛቤል አምልኮተ በኣልም ልክ እንደዚህ ነበር፡፡ ሰዎች የገዛ ሥጋቸውን በብልጥግናና ልምላሜ ብቻ በመሻት እንዲህ ያሉ አምልኮተ ጣዖትን ተከትለዋል፡፡ 
 
በዛሬዎቹ ዳግመኛ የተወለዱ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ አንዳንዶች ጉባኤዎቻቸውን ለማስፋት የኤልዛቤልን እምነት ለማስተናገድ ያዘነብሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሥነ አመክንዮው በእግዚአብሄር መቅደስ ውስጥ ጣዖታትን ከማስቀመጥ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ 
 
ኤልዛቤል አረማዊውን አምላከ በኣል ያስገባችው ወደ እስራኤል ብቻ ሳይሆን ወደ የሆዋ መቅደስ ውስጥም ነበር፡፡ ከሐጢያት መዳንን ትቶ የሥጋን መከናወንና ዓለማዊ ትርፎችን የሚሻ የዚህ ዓይነቱ እምነት በእግዚአብሄር ፊት ጣዖታትን እንደማምለክ ሁሉ የተሳሳተ እምነት ነው፡፡ 
 
በመላው ዓለም የሚገኙ የዘመኑ ቤተክርስቲያኖች ‹‹ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ ተወግደዋል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ አስወግዶዋቸዋልና›› በማለት ከዮሐንስ 1፡29 ይሰብካሉ፡፡ እነርሱ ሰው በኢየሱስ ጥምቀት ባያምንም ደህንነት የሚገኘው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በእርሱ በማመን ብቻ ነው በማለት የኢየሱስን ጥምቀት እንደ ተራ ማጀቢያ አድርገውታል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት፤ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ የወሰደበት ጥምቀት በዘፈቀደ የምንጨምረው ወይም የምናስወጣው አንዳች አማራጭ ነገር አይደለም፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት ተራ የወንጌል ማጀቢያ አድርጎ ማስተናገድና ማመን በኣልን ከማምለክ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ 
 
ታዲያ እነዚህ ሰዎች ያለ ኢየሱስ ጥምቀት ወንጌልን የሚሰብኩት ለምንድነው? ይህንን የሚያደርጉት ተስፋቸው የሚገኘው በእግዚአብሄር መንግሥት ውሰጥ ሳይሆን በዚህ ምድር ላይ ባለው ዓለማዊ ብልጥግናቸው ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች አረማዊውን አምላከ በኣል ካመለኩት ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ 
 
ከዚህ ቀደም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ካመኑ በኋላ አሁን የመስቀሉን ደም ብቻ የሚሰብኩ ሰዎች አምልኮተ በኣል የሆነውን የጣዖት አምልኮ እንደ ማምለክ ያለ አስከፊ ሐጢያት አየሰሩ ነው፡፡ 
 
ማንም ሰው ግቡን በዚህ ዓለም ቁሳዊ ትርፎች ላይ በማስቀመጥ በትክክል ማገልገል አይችልም፡፡ መጋቢዎች የኢየሱስን ጥምቀት ትተው በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን ብቻ በመስበካቸው የዚህን ዓለም ምድራዊ ትርፎች ማካበት ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ እምነት እውነተኛ እምነት እንዳይደለ፤ የዚህ ዓይነቱ ስብከትም እውነተኛ ስብከት እንዳልሆነ እንዳልሆነ መገንዘብ አለባቸው፡፡ 
 
የራዕይን ምንባብ ስንመለከት የትያጥሮን ቤተክርስቲያን አገልጋይ ልክ ኤልዛቤል በኣልን እንዳመለከች በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በኣልን አንዳመለከ ማየት እንችላለን፡፡ 
 
ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ ከሆኑ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ መኖርም ሆነ በውስጣቸው መሥራት አይችልም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም›› እንዳለው ሰው የእግዚአብሄር ልጅ መሆን አለመሆኑ የሚወሰነው በልቡ ውስጥ ባለው የክርስቶስ መንፈስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ መንፈስ የሌላቸው ሰዎች እንደተረሱ ይነግረናል፡፡ 
 
 

የኢየሱስን ጥምቀት የሚያውቁና የሚያምኑ ሰዎች፡፡ 

 
ሰው የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በወሰደበት በኢየሱስ ጥምቀትና (ውሃ) በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሲያምን መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ ይኖራል፡፡ 
 
ነገር ግን ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምን ከሆነ ለኢየሱስ ሰማዕት ቢሆን እንኳን የራሱን ጽድቅ ለመፈጸም የሚሞክርበት ሰማዕትነት እንጂ እውነተኛ ሰማዕትነት አይሆንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በመስቀሉ ደም በማመን ብቻ መላውን ሕይወታቸውን ለሚሲዮን ሥራ ቀድሰው በመስጠት እየኖሩ ወንጌልን ለመስበክ እጅግ ራቅ ወዳለ የዓለም ማዕዘን ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዴም ለእምነታቸው ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ 
 
ሰዎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ብቻ ቢያምኑም በክርስቶስ ፍቅር ተነሳስተው እንዲህ ሰማዕት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ማቴዎስ 7፡23 እንደሚነግረን ጌታ ራሱ ሥራዎቻቸውንና መስዋዕትነታቸውን ሁሉ የማይቀበለው ከሆነ ይህ ምን ጥቅም ይኖረዋል? ለምሳሌ የሞርሞን ሚሲዮናውያን እንደሚያደርጉት ወንጌልን በጉጉትና በታማኝነት ቢያሰራጩ ምንም ማለት አይደለም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስላልሰበኩ እምነታቸውና ጥረቶቻቸው ሁሉ ከንቱ ይሆናሉ፡፡ 
 
እግዚአብሄር የትያጥሮንን ቤተክርስቲያን አገልጋይ የነቀፈው የኤልዛቤል እምነት ተከታዮች በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲያቆጠቁጡና እንዲያድጉ በመፍቀዱ ነበር፡፡ በዛሬው ዓለም ነፍሳቶችን የሚያታልሉ ልክ እንደዚህ ያሉ ብዙ የሐይማኖት መሪዎች አሉ፡፡ እውነተኛዋ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ውልደት፣ በጥምቀቱ፣ በስቅለቱ፣ በሞቱ፣ በትንሳኤውና በዕርገቱ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ትክክለኛ እምነት ሊኖራትና ወንጌልን ልታሰራጭ ይገባታል፡፡ አለበለዚያ እምነቷ ከንቱ ነው፡፡ 
 
ሐሰተኛ ነቢያቶች ለመዳን የእርሱን ጥምቀት አስፈላጊነት ባለመገንዘብ በመስቀል ላይ በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ማመን ብቻ በቂ ነው ይላሉ፡፡ ክርስትና የውሃውን እውነት ስለተወ ተበላሽቶ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሐይማኖቶች እንደ አንዱ ሆኖ ተቀይሮዋል፡፡ ክርስትና ከእንግዲህ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ደህንነትን ማምጣት ያልቻለው ለዚህ ነው፡፡ 
 
ክርስትና ያለ ኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ከፈሰሰው ደሙ ውጭ በዓለም ሥነ ምግባሮችና በጎነቶች ላይ ብቻ ወደሚያተኩር ተራ ሐይማኖት ተቀይሮዋል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን በሆኑባቸው በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ አሁን የምሥራቅ ሐይማኖቶች ገናና እየሆኑ ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም በሐይማኖት ላይ ያነጣጠረ እንዲህ ያለ ክርስትና በእግዚአብሄር የሚገኘውን የሐጢያቶች ስርየትና እውነተኛ እምነት መስጠት አልቻለምና፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰዎች ረቂቅ ባህርይ ወዳላቸው የምስራቃውያን ሐይማኖቶች ተስበው ለምዕራባውያን ሐይማኖቶች የተሻሉ አማራጮችን እንደሚያቀርቡ ያስባሉ፡፡ ክርስትና ግን ምዕራባዊም ምሥራቃዊም ሐይማኖት አይደለም፡፡ 
 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌልና የዘመኑን ክርስትና ሁኔታ ዳግመኛ ለማጤን ጊዜያችን አሁን ነው፡፡ እውነትን የያዘው ክርስትና አሁን ባለበት ሁኔታ ለምን እንደተበላሸና የዘመኑ ክርስትናም በብዙ ሰዎች ዓይን ለምን እንዲህ የማይረባና አስቸጋሪ እንደሆነ መጠየቅና ማሰብ አለብን፡፡ መልሱ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ ይገኛል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት እጅግ አስከፊው ነገር የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነተኛ ደህንነትን የሚያስገኝ እውነት መሆኑን አለመቀበል ነው፡፡ 
የዘመኑ ክርስትና የተመሰጠው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውበት ሳይሆን በዓለም ውበት ነው፡፡ በእስያ ያሉት ሰባቱ ቤተክርስቲያኖች በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ጌታን አገልግለዋል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደታየው እነርሱም እንደዚሁ በከፊል የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በስፋት እየተገፋ ሲወጣና በምትኩም የሕዝቡን ልብ አብዝቶ በሚይዘው ዓለም ወደ መተካቱ ሲመጣ ወደ ዓለም የተገለበጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ 
 
ቤተክርስቲያን የደህንነት እውነት የሆነውን በውሃና በመንፈስ ዳግመኛ የመወለድ ወንጌል መስበክ ትታ በምትኩ የመስቀሉን ደም ብቻ ብትሰብክ ምን ይፈጠራል? ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ዓለምን ብትከተል ፈጥና በዓለም ስለምትበላሽ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለመዳን የኢየሱስን ጥምቀት አለማወቅ ችግር የለውም ማለት ይጀምራሉ፡፡ እኔ ይህንን ጠቃሚ ነጥብ በእግዚአብሄር ቃል አማካይነት ዳግመኛ የምመረምረውና የማነሳው ለዚህ ነው፡፡ 
 
 

የኢየሱስ ጥምቀት ባለው ወንጌልና የእርሱ ጥምቀት በሌለው ወንጌል መካከል ያለው ልዩነት፡፡ 

 
እናንተና እኔ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስርየት ተቀብለናል፡፡ ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የጌታ እውነት ሲሆን የኢየሱስ ጥምቀት፣ በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደሙና መንፈስ ቅዱስ የደህንነታችን ማስረጃዎች ናቸው፡፡ 
 
1ኛ ዮሐንስ 5፡5-7 እና 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ‹‹ውሃ›› ማለትም ጥምቀት የደህንነታችን ምልክት እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ ይህ ኢየሱስ በጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ እንደወሰደ ከሚናገረው የማቴዎስ 3፡15 የደህንነት ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት ይህንን ያህል አስፈላጊ ሆኖ ሳለ የኢየሱስን ጥምቀት ቸል ብሎ በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደም ብቻ መስበክ እንዴት ምሉዕና ፍጹም ወደሆነ ደህንነት ሊመራን ይችላል? ከሐጢያት የዳኑ ሰዎች በቃሉ በማመን ግልጽ የሆነ የደህንነት መስመር ማስመር አለባቸው፡፡ ይህ መስመር ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንላቸው ራሳቸውን ደጋግመው ማስታወስ አለባቸው፡፡ 
 
ሰው ለደህንነቱ ግልጽ የሆነ የመለያ መስመር ካላሰመረ ይህ ማለት ግለሰቡ ገና አልዳነም ማለት ነው፡፡ ከሐጢያት መዳናችን የእምነታችን የዕድገት ደረጃ ብቻ ነው በሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ ከሐጢያት መዳን የመንፈሳዊ ማረጋገጫ ደረጃ ሳይሆን የእምነት ቤታችንን በዓለት ላይ የምንሰራበት እጅግ አስፈላጊው ደረጃ፤ የእምነታችን ዋናው መሰረት ነው፡፡ 
 
የደህንነትንም ጉዳይ የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ‹‹የቃለ እግዚአብሄር አቋሞች›› ጉዳይ ብቻም አይደለም፡፡ የቃለ እግዚአብሄር ትምህርቶች በየቤተክርስቲያኑ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት፤ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ የመውሰዱ እውነት ከእምነት ወደ እምነት ሊለያይ አይችልም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስንሰብክ ወሳኝ የሆነውን የኢየሱስን ጥምቀት አስፈላጊነት መተው የማንችለው ለዚህ ነው፡፡ 
 
የክርስቶስን ጥምቀት ትተን ኢየሱስን ‹‹የዓለምን ሐጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ›› አድርገን መስበክ ወይም ሰዎች በመስቀሉ ደም ብቻ አምነው ሊድኑ እንደሚችሉ መስበክ አንችልም፡፡ በክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም በማመን የሐጢያቶቻችንን ስርየት መቀበል አለብን፡፡ የሰው ሐጢያቶች በኢየሱስ ጥምቀት ሳያምን በመስቀሉ ደም ብቻ በማመን እንዴት ሊወገዱ ይችላሉ? ሰዎች በመስቀሉ ደም ብቻ ሲያምኑ የሕሊናቸውም ሐጢያቶች እንደዚሁ ይወገዳሉን? አይወገዱም!
 
ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሄርን ጽድቅ፣ ሐጢያቶቻችንንና ፍርዳቸውን መስክሮዋል፡፡ ሊኖረን የሚገባው እውነተኛ እምነት በዚህ የክርስቶስ ኑዛዜ እውነተኛ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ እምነት ነው፡፡ እውነተኛ ዕውቀት ስል ምን ማለቴ ነው? በእግዚአብሄር የሚፈረድባቸው ሐጢያቶቻችን ምን እንደሆኑ፣ የእርሱ ጽድቅ ምን እንደሆነና በእግዚአብሄር ፊት የተኮነነ እምነትም ምን ዓይነት እምነት እንደሆነ ግልጽ የሆነ መረዳት መያዝ ማለቴ ነው፡፡ እውነተኛ እምነት ከእውነተኛ ዕውቀታችን መብቀል የሚችለው እነዚህን በማወቅ ብቻ ነው፡፡ 
 
በወንጌል ስብከት ውስጥ የኢየሱስን ጥምቀት ወይም የመስቀል ላይ ደሙን ከተውን የምንሰብከው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አይሆንም፡፡ የእግዚአብሄርን እውነት በራሳችን ሰውኛ መደላድሎች ብናስተናግደውና ሰው ሁሉ በኢየሱስ በማመን ብቻ ሐጢያት አልባ መሆን እንደሚችል ብንሰብክ ሰባኪዎቹም ሰሚዎቹም ሐጢያተኞች ሆነው ይቀራሉ፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት በመስበክና በአለመስበካችን መካከል ያለው ልዩነት ነፍሳቶችን በማዳን ረገድ ሁሉንም ልዩነት ይፈጥራል፡፡ 
 
የሐዋርያቶችን እምነት ስንመለከት የመስቀሉን ደም ብቻ እንዳልሰበኩ እናያለን፡፡ ሁሉም የኢየሱስን ጥምቀትና የመስቀል ላይ ደሙን እንደ አንድ የደህንነት ሥራ አምነውታል፡፡ ኢየሱስ በመጀመሪያ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ በራሱ ላይ ሳይወስድ በመስቀል ላይ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አስወግዶዋል ብሎ መከራከር በሰውኛ አስተሳሰብ ከስነ አመክንዮ ውጭ ብቻ ሳይሆን ከውሃውና ከመንፈሱ እውነት ጋርም የሚስማማ አይደለም፡፡ እንዲህ ባለ ግማሽ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ከሐጢያቶቻቸው መዳን አይችሉም፡፡ 
 
የወንጌል ሰባኪው ሥራዎች፡፡ 
 
በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር መንፈሳዊ አጣማሪዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚሰብኩ ሰዎች ናቸው፡፡ የመንፈሳዊ ደህንነት አጣማሪዎች በጌታና በእርሱ ሙሽሪቶች መካከል መሸምገል አለባቸው፡፡ እነርሱ ማድረግ ያለባቸው የመጀመሪያው ነገር ጌታ ለእነርሱ ያደረገውን ለሐጢያተኞች መስበክ ነው፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻቸውን በራሱ ላይ ለመውሰድ እንደተጠመቀና ለእነዚህ ሐጢያቶችም በሙሉ በመስቀል ላይ እንደተኮነነ ሊያስተምሩዋቸው ይገባል፡፡ ሙሽሪቶቹ በዚህ ያምኑ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ በትክክል ማወቅ አለባቸው፡፡ ሙሽሪቶቹ ካመኑ የአጣማሪዎቹ ሚና በሙሉ ይፈጸማል፡፡ 
 
እዚህ ላይ ለመድረስ አጣማሪዎቹ ሙሽራው ማን እንደሆነና ምን እንዳደረገላቸው ለሙሽሪቶቹ ማብራራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ሙሽሪቶች ነገሩን በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ ነው፡፡ የሙሽሪቶቹ ልቦች ሙሽራው ለእነርሱ ያደረገላቸውን ሲገነዘቡ አጣማሪዎቹ ሙሽራው በውሃውና በደሙ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ የወሰደ የመሆኑን እውነታ ማስተማር አለባቸው፡፡ 
 
ሙሽሪቶቹ ሙሽራው ለእነርሱ ያደረገላቸውን ነገር በሙሉ ሲቀበሉ ያን ጊዜ እነርሱ የክርስቶስ ሙሽሮች ሆነው ይጠራሉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽሪቶች የሚሆኑ ሰዎች ሙሽራው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቤዛነት እንደገዛቸው መረዳት አለባቸው፡፡ ሙሽራው እነርሱን የራሱ ለማድረግ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በውሃውና በደሙ አንጽቶ እንደ በረዶ ነጭ በማድረግ የራሱ ሙሽሪቶች አድርጎ እንደተቀበላቸው መገንዘብ አለባቸው፡፡ 
 
ሙሽሪቶች ሙሽራውን ለዘላለም ሊያከብሩትና ሊያውቁት የሚችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የተቀበሉ ሰዎች ሁሉ ጻድቅ ናቸው፡፡ ጻድቃንም ሐጢያት አልባ ናቸው፡፡ ሐጢያት አልባዎችም የኢየሱስ ሙሽሪቶች ናቸው፡፡ ሙሽሮቹ እንዲህ ዓይነት እምነት ሲኖራቸው ከሙሽራው ጋር ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ ሙሽራውም በዕቅፉ ሊቀበላቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ሙሽሪቶቹ ለሰርጋቸው በሚገባ መዘጋጀት የሚችሉት መንፈሳውያኑ አጣማሪዎች ሙሽሪቶቹን በእውነት ቃል ሲያዘጋጁዋቸው ብቻ ነው፡፡ 
 
እንዲቃናላቸውም የመንፈሳዊው ደህንነት አጣማሪዎች ሙሽራው ምን ዓይነት ሙሽሪቶችን እንደሚፈልግ ማወቅ አለባቸው፡፡ ሙሽራችን ኢየሱስ ሐጢያት የለበትም፡፡ እርሱ ቅዱስ ነው፡፡ ኢየሱስ ነቁጥ የሌለባቸውን ሙሽሪቶች የሚፈልገው ለዚህ ነው፡፡ ይህ ሙሽሮችን ማስዋብ ማለት ሐጢያቶቻቸው በሙሽራው በተፈጸመው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ሙሉ በሙሉ ከነጻ በኋላ ነው ማለት ነው፡፡ ሐጢያቶቻቸው በከፊል ከነጹ በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው ቢሆን ኖሮ ሙሽራው አይቀበላቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም እርሱ የእርሱ ሙሽሪቶች ሙሉ በሙሉ ሐጢያት አልባ እንዲሆኑ ይፈልጋልና፡፡ ይህንን ሚና የሚጫወቱት የእግዚአብሄር አገልጋዮች የመንፈሳዊ ደህንነት አጣማሪዎች ናቸው፡፡ 
 
ስለዚህ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ሙሽሪቶቹን ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው ማዘጋጀታቸውን መቀጠል አለባቸው፡፡ በዚያው ጊዜም በዘመኑ ክርስትና ውስጥ በየስፍራው መንፈሳዊ ትርፎችን የሚበዘብዙና የሚዘርፉ ብዙ የሥጋ አጣማሪዎች እንዳሉ መረዳት አለብን፡፡ እነዚህ የሥጋ አጣማሪዎች በኢየሱስ ክርስቶስና ተቀባይነት ባጡት ሙሽሪቶች ይመታሉ፡፡ የሥጋ አጣማሪዎች መሆን የለብንም፡፡ 
 
 
የሰይጣንን ጥልቅ ነገር ማወቅ፡፡ 
 
በእግዚአብሄር አገልጋዮችና ሕዝቦች መካከልም ቢሆን የሰይጣንን ማታለል ጥልቀት የማያውቁ ብዙዎች አሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ሰይጣን ምን ያህል ሊያሰናክለን ጠንክሮ እንደሚጥር የማያውቁ ብዙዎች አሉ፡፡ እጅግ ብዙ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ሰይጣን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ምን ያህል እንደለወጠውና እንዳበላሸው፤ ምዕመናንም የእርሱን ሐሰተኛ እምነት ይከተሉ ዘንድ ምን ያህል እንዳሳታቸው ማወቅ ተስኖዋቸዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ በኢየሱስ የሚያምኑ ብዙ ምዕመናን መጨረሻቸው እውነተኛውን የውሃውንና መንፈሱን ወንጌል በመያዝ ፋንታ የተበላሸውን ወንጌል ይዘዋል፡፡ ነፍሳቸውም ከእግዚአብሄር ፍላጎት ውጭ ጠፍቷል፡፡ 
 
እግዚአብሄርን ‹‹የኤልዛቤልን ትምህርት አትከተሉ፡፡ እኔ እስክመጣ ድረስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌላችሁን አጥብቃችሁ እመኑ፤ ስበኩም፡፡ ያን ጊዜ በአህዛብ ላይ ሥልጣን እሰጣችኋለሁ›› ብሎ ነግሮናል፡፡ ነገር ግን በኤልዛቤል እምነት የተታለሉትን ወደ መከራ እንደሚጥላቸውና ዳግመኛ እንደሚቀርጻቸውም እግዚአብሄር ይነግረናል፡፡
 
ክርስቶስ የሚመጣበት ጊዜ ሲደርስ በኢየሱስ ደም ብቻ አምነው ደህንነትን የሰበኩ ሰዎች እምነታቸውን እንደሚክዱ እናያለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜም እምነታቸው ከእነርሱ በሚለየው በቀሩት ላይ የበላይነት ስሜት እየተሰማቸው ስለ እምነታቸው ለመኩራራት የሚያዘነብሉ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ግን በእነርሱ እምነትና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምኑ ሰዎች መካከል ይለያል፡፡ ‹‹ድል ለነሳውና እስከ መጨረሻውም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደተቀበልሁ በአህዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፡፡ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፡፡ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፡፡ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ፡፡›› 
ጌታችን ወደዚህ ምድር ሲመጣ ዳግመኛ ሳይወለዱ ጌታን የሚገናኙ ብዙ ክርስቲያኖች ይኖራል፡፡ እነርሱ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስላላመኑ ጌታን በልባቸው ውስጥ ባለው ሐጢያት ይገናኙታል፡፡ በአንጻሩ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ልባቸው ከሐጢያቶቻቸው የተሰረየላቸው ሰዎች በጌታ ምጽዓት ይለወጡና ከእርሱ ጋር ይነግሳሉ፡፡ እዚህ ላይ እንደተባለውም የጌታናየሕዝቡ ሥልጣን የሸክላ ዕቃን እንደሚሰባብር የብረት በትር ነው፡
 
እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት እስከ መጨረሻ ለሚጠብቁ በአህዛብ ላይ ሥልጣን እንደሚሰጣቸው በሚገባ የተረጋገጠ ነው፡፡ ጌታችን ይህ ሥልጣን እርሱ ከአባቱ ከተቀበለው ሥልጣን ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ጌታ በአህዛብ ላይ በሰጠን በዚህ ሥልጣን ለዘላለም እንድንነግስ እንደ ኤልዛቤልና በለዓም ያሉትን ሐሰተኛ ነቢያቶች ተዋግተን ማሸነፍ አለብን፡፡
 
 
በእውነት የሚገኝ ግልጽ ደህንነት! 
 
ጌታችን ሐጢያተኞችን ለማዳን ወደዚህ ምድር መጥቶ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ በዮሐንስ መጠመቅ ነበረበት፡፡ ጌታ ሐጢያቶቻችንን ለመውሰድ ስለተጠመቀ እነዚህን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ተሸከመ፡፡ በዚያም ሞተ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ እርሱ እነዚህን የጽድቅ ምግባሮች ያደረገው ለእኛ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር ሐጢያቶችን ሲፈጽምና ሲታገል ማየት አላስቻለውም፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ሊያድናችሁ የሚችል እውነት ነው፡፡
 
ጌታችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑ ሰዎች ሁሉ አዳኝ መሆን ችሎዋል፡፡ ጌታ በዮሐንስ መጠመቅ ስለነበረበት በዮሐንስ 1፡29 አና በዮሐንስ 19፡30 ላይ ለተመሰከረው ለዚህ አስገራሚ ውጤት ፍሬያማ መሆን ችሎዋል፡፡ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ!›› ‹‹ተፈጸመ፡፡›› በዚህ የእግዚአብሄር ቃል አማካይነት መዳናቸውን ያረጋገጡ ሰዎች በእርግጥ ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ እንደወሰደ ያውቃሉና፡፡ የራሳችንን ልብ ልንጠነቀቅና ልንመለከት ይገባናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማናምን ከሆንን ሐጢያቶቻችን በልባችን ውስጥ መኖራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
 
የኢየሱስን ጥምቀት ቸል ብለው በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ብቻ የሚያምኑ ሰዎችን ልብ ቀረብ ብለን ስንመለከት በልባቸው ውስጥ ያለው ሐጢያት ሊካድ እንደማይችል እናያለን፡፡ በተለይ አጥማቂው ዮሐንስ በኢየሱስ ላይ ላደረገው ጥምቀት የተለየ ትኩረት ማድረግና አጠንክረን ማመን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሄር ቃል ላይ የራሳችንን ዕሳቤዎች መጨመርም ሆነ ከቃሉ መቀነስ አንችልምና፡፡ ሐሰተኛ ወንጌሎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎችን እምነት የሚያወድሙ ስለሆኑ እነዚህን ሐሰተኛ ወንጌሎች ሁላችንም ልንዋጋቸው ይገባናል፡፡
 
ኢየሱስ ራሱ ‹‹ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ›› በማለት ነግሮናል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹እርሾው›› የሚያመለክተው መጠጥ ወይም እንጀራ ለመስራት ጥቅም ላይ የሚውለውን እርሾ ሳይሆን የኢየሱስን ጥምቀት ያልያዘውን ወንጌል ነው፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በጥምቀቱ በራሱ ላይ በመውሰድ የተሸከማቸው በመስቀል ላይ በመሰቀልና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት እውነተኛ አዳኛችን ለመሆን የመሆኑን እውነታ ማወቅና ማመን አለብን፡፡
 
ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰድና በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ በማስወገድ የራሱን ድርሻ ተወጣ፡፡ በሕዝቡ ወገን ግን ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ስለማያምኑ ሐጢያቶቻቸው መኖራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ለመውሰድ የተጠመቀ መሆኑን ባለማመናቸው ሐጢያቶቻቸው ሊደመሰሱ አልቻሉም፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ በአንድ ላይ በማመን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የሚያስወግድና እንደ በረዶ የሚያነጻ ወንጌል ነው፡፡
 
 
ድል የነሱትን ሰዎች እንሁን፡፡ 
 
ከዚህ ከዋናው ምንባብ የእግዚአብሄር ቃል ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን እንደተነገረ አይተናል፡፡ እግዚአብሄር ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን አገልጋይ በአህዛብ ላይ ሥልጣንን እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል፡፡ እያንዳንዱ ዳግመኛ የተወለደ ቅዱስ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ ተጠምዶ በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ይኖራል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ባለን እምነታችን ሁልጊዜም በዚህ ተጋድሎ ውስጥ ማሸነፍ አለብን፡፡ ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጀምረው አንድ ሰው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ከጀመረበት ቅጽበት ጀምሮ ነው፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ከእርሱ ጋር በሚያደርጉት ትግል ሰይጣንን ድል መንሳት አለባቸው፡፡ አንዳንዶቻችን በእግዚአብሄር ፊት እስከምንቆምበት ጊዜ ድረስ ከሰይጣን ጋር ተዋግተን ሐሰተኛ ወንጌሎችን እናሸንፋለን፡፡ ድል የሚነሱ ሰዎች ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቅ፣ በመስቀል ላይ በመሞትና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት ሐጢያቶቻችንን ሙሉ እንደወሰደ ያምናሉ፡፡ ሌሎች ምንም ቢሉም እነርሱ የሐጢያቶቻቸው መንጻት ስፍራ የዮርዳኖስ ወንዝ እንደሆነና ሐጢያቶቻቸው በሙሉም ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት ወደ ኢየሱስ እንደተላለፉ ባላቸው እምነት አይናወጡም፡፡
 
ጌታችን ሰይጣንን ተዋግተን እንድናሸንፈው አዞናል፡፡ ሥጋችን አንዳንድ ጊዜ ሊጨነቅና ሊደክም ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለን እምነት ከሐሰተኛ ወንጌሎች ጋር የሚያደርገውን ጦርነት በፍጹም ሊሸነፍ አይችልም፡፡
 
ጌታ እንዲህ ብሎ ይነግረናል፡- ‹‹በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፡፡ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ መንገደዱም የቀጠነ ነውና፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው፡፡›› (ማቴዎስ 7፡13-14) የብሉይ ኪዳን ነቢይ ኤልያስ ከ850 ከሚበልጡ የበኣል ካህናት ጋር ተዋግቶ አሸንፎዋል፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስም እንደዚሁ እርሱ ከሚያሰራጨው ወንጌል ውጭ ሌላ ወንጌል እንደሌለ ተናግሮዋል፡፡ (ገላትያ 1፡7) ይህ የጳውሎስ ወንጌል በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ከሚያምነው እምነት ውጭ ሌላ ወንጌል አልነበረም፡፡ በዚህ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ዳግመኛ ከተወለዱ በኋላ እንኳን አንዳንድ ጉድለቶች ቢኖሩባቸውም በልባቸው ውስጥ ለዘላለም ሐጢያት የለባቸውም፡፡ ጌታችን በውሃው ሐጢያቶቻችንን በሙሉ አንጽቶ በደሙ የእነዚህን ሐጢያቶች ፍርድ በሙሉ ተቀብሎዋል፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና የመስቀል ላይ ደሙ ለሚያምኑት ሰዎች ዘላለማዊ ቤዛነትን አምጥቶላቸዋል፡፡
 
ጌታ ለዳኑት ሰዎች እምነታቸውን የሚጠብቁበትን፣ እስከ መጨረሻ ድረስ የሚዋጉበትንና የሚያሸንፉበትን ሥልጣን ሰጥቶዋቸዋል፡፡