Search

Khotbah-Khotbah

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[10-2] የቅዱሳን ንጥቀት መቼ እንደሚሆን ታውቃላችሁን? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 10፡1-11 ››

የቅዱሳን ንጥቀት መቼ እንደሚሆን ታውቃላችሁን?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 10፡1-11 ››
 
አሁን ትኩረታችንን ንጥቀት መቼ ይሆናል? ወደሚለው እንመለስ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ንጥቀት የሚያወሩ ብዙ ምንባቦች አሉ፡፡ አዲስ ኪዳን ይህንን የሚያወሱ ብዙ ምንባቦች አሉት፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥም እንደዚሁ በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ ስለተነጠቀው ኤልያስና ከእግዚአብሄር ጋር በመጓዙ እግዚአብሄር ስለወሰደው ሄኖክ ማግኘት እንችላለን፡፡ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ስፍራዎች ላይ ስለ ንጥቀት ይናገራል፡፡ ንጥቀት ማለት ‹‹ማንሳት›› ማለት ነው፡፡ ይህም እግዚአብሄር በሐይሉ ሕዝቡን ወደ ሰማይ እንደሚያነሳ ያመለክታል፡፡
 
ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ግራ የሚያጋባውም እንደዚሁ ይህ የንጥቀት ጥያቄ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሕዝቡን የሚነጥቀው መቼ ይሆናል? የንጥቀትን ጊዜ አስመልክቶ የሚነሳው ጥያቄ በክርስትና ውስጥ ተዘውትረው ከሚጠየቁ በርካታ ጥያቄዎች አንዱ ነው፡፡
 
ወደ 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡4-17 ሄደን እግዚአብሄር በሐዋርያው ጳውሎስ በኩል የነገረንን እንመልከት፡- ‹‹ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሳ ካመንን እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሄር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል፡፡ በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፡፡ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፡፡ ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሄርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፡፡ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፡፡ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፡፡ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን፡፡››
 
በይሁዳ 1፡14 ላይም እግዚአብሄር እንዲህ ነግሮናል፡- ‹‹ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ ጌታ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ትንቢት ተናገረ፡፡›› በሌላ አነጋገር ቅዱሳኑ የመላዕክቱ አለቃ መለከት በሚነፋበት ጊዜ በአምላካችን ወደላይ ይነጠቁና ለጥቂት ጊዜ በአየር ላይ ይቀራሉ፡፡ ከዚያም ከጌታችን ጋር እንደገና ወደ ምድር ይወርዳሉ፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ስለ ንጥቀት ያብራራው ማብራሪያ ነው፡፡
 
ከላይ ያሉትን ምንባቦች አስቀድመን የተመለከትንበት ምክንያቱ ራዕይ 10 ንጥቀት መቼ እንደሚመጣ ስለነገረን ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስሁት የዚህ ምዕራፍ ዋናው ምንባብ የሚገኘው በቁጥር 7 ላይ ነው፡፡ ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል አለ፡፡›› ይህ ቁጥር ስለ ንጥቀት ያሉንን ጥያቄዎችና እንቆቅልሾች በሙሉ የሚመልስ ነው፡፡ ምክንያቱም ንጥቀት መቼ እንደሚሆን ይነግረናልና፡፡
 
እግዚአብሄር በራዕይ ለዮሐንስ ብርቱ መልአክን ላከለት፡፡ እርሱም ጌታ ወደዚህ ምድር የመጣ በሚያስመስል ድርጊት በዚህ መልአክ አማካይነት የሚያደርገውን ነገር አሳየው፡፡ ይህ መልአክ እጁን ወደ ላይ አንስቶ ‹‹ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፣ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፣ ባህርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ፡- ወደፊት አይዘገይም›› ብሎ ማለ፡፡ ከእንግዲህ አይዘገይም ማለት ዳግመኛ ለመዘግየት አንዳች ምክንያት አይኖርም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ‹‹ጊዜ የለም›› ማለት ነው፡፡ ደግሞ ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለበት ቀን እግዚአብሄር ለባሮቹ ለነቢያት እንደተናገረው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡
 
ከሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ዓለም ወደ ሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ውስጥ ይገባል፡፡ ያን ጊዜ ዳግመኛ ለዚህ ዓለም የሚቀር አንዳች ጊዜ እንደማይኖር መረዳት አለብን፡፡ ስለዚህ በቁጥር 7 ላይ ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል›› የሚለው ቃል የሚያመላክተው የንጥቀትን ዘመን ነው፡፡ ጳውሎስ በሌላ ቦታ ንጥቀት የሚሆነው በመላእክት አለቃ ድምጽና በእግዚአብሄር መለከት መነፋት እንደሆነ ተናግሮዋል፡፡ ጳውሎስ በአእምሮው የነበረው ይህ ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንጥቀትን በሚመለከት የቀረቡት ማመሳከሪያዎች ሁሉ የመነሻ ነጥባቸውም እንደዚሁ ይህ ነው፡፡
 
‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡›› ይህ ቃል የቅዱሳን ንጥቀት ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋበት ጊዜ እንደሚሆን እነርሱንም በአየር እንደሚነጥቃቸው ይነግረናል፡፡ የእግዚአብሄር ባሮች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለጠፉት ነፍሳቶች ሲያሰራጩና መንፈስ ቅዱስም እውነተኛውን ወንጌል በተቀበሉት ምዕመናን ልብ ውስጥ በተጨባጭ ሲወርድ እነርሱም በተጨባጭ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆናሉ፡፡ የእግዚአብሄር ምስጢር የሆነው ንጥቀት ቅዱሳንን ወደ አየር በመንጠቅ ተጨባጭ የሚሆን መሆኑ ለእኛ ነው፡፡
 
ከዚህ በኋላ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች የመጨረሻ መቅሰፍቶች በማፍሰስ ዓለምን ሙሉ በሙሉ ያጠፋል፡፡ ከክርስቶስ ጋር ለሺህ ዓመት የምንነግስበትንም የእግዚአብሄር መንግሥት በዚህች ምድር ላይ ያመጣል፡፡ ከዚያም ለዘላለም ወደምንኖርበት አዲስ ሰማይና ምድር ይወስደናል፡፡
 
እግዚአብሄር ስለ መጭው ንጥቀት ለዮሐንስ ከነገረው በኋላ ታናሺቱን መጽሐፍ እንዲበላና ዳግመኛ ትንቢት እንዲናገር አዘዘው፡፡ የእግዚአብሄር ባሮች በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ለሚኖሩት ቅዱሳን ሊያስተምሩዋቸው የሚገባው እጅግ ጠቃሚው ትምህርት የንጥቀቱን ሁነትና ትክክለኛ ጊዜውን ነው፡፡ እነዚህን ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሰረቱ ትክክለኛ አገባቦች ሊያስተምሩ ይገባቸዋል፡፡ የውሃውንና የመንፈሱንም ወንጌል በትክክል ማስተማር አለባቸው፡፡ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ የሚኖሩ የእግዚአብሄር ባሮችና ቅዱሳኑ ሊያደርጉዋቸው የሚገባቸው እነዚህን ነው፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን ሥራዎች እንደዚሁም የእርሱን ምስጢር ለእነርሱ መግለጡን ለቅዱሳን በአደራ ሰጥቶዋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር እንደማይዘገይ ነገር ግን ሁሉንም ነገር በተጨባጭ እንደሚፈጽም ነግሮናል፡፡
 
በምዕራፍ 11 ላይ ሁለት የወይራ ዛፎች ማለትም ሁለት ነቢያቶች ተገልጠዋል፡፡ በሁለት የወይራ ዛፎች የተመሰሉት እነዚህ ሁለት የእግዚአብሄር ባርያዎች እርሱን በመዋጋታቸው በጸረ ክርስቶስ ይገደላሉ፡፡ ነገር ግን በሦስት ቀናቶች ውስጥ እንደገና ከሙታን ይነሱና ይነጠቃሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር በተለያዩ አጋጣሚዎች ንጥቀት የሚሆነው በዚህ የጸረ ክርስቶስ ዘመን ቅዱሳን ሰማዕት በሚሆኑበት ጊዜ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡
 
አስቀድመን ማወቅ የሚገባን ቅዱሳን የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች የመጀመሪያዎቹ ስድስት መቅሰፍቶች እስከሚፈጸሙ ድረስ በዚህ ምድር ላይ ቀርተው በታላቁ መከራ ውስጥ የሚያልፉ መሆናቸው ነው፡፡ እግዚአብሄርም ቅዱሳንን ከእነዚህ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ይጠብቃቸዋል ማለትም እግዚአብሄር እስከ ስድስተኛው መቅሰፍት ድረስ ይጠብቃቸዋል፡፡ በመጨረሻ ግን ጸረ ክርስቶስ እግዚአብሄርን በመቃወም የሞት ሽረት ትግሉን በሚያደርግበት የጭካኔው መጨረሻ ላይ ይገድላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን የሚቀበሉት ሞት ሰማዕትነታቸው ነው፡፡ እምነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የጽድቅ ሞት ስለሚሞቱ ይህንን ‹‹ሰማዕትነት›› ብለን እንጠራዋለን፡፡ ስለዚህ ንጥቀት የሚሆነው ከዚህ ሰማዕትነት በኋላ መሆኑንና ይህንንም እምነት ለሌሎች መስበክ አለብን፡፡
 
ብዙ ሰዎች ንጥቀት የሚሆነው ከታላቅ መከራ በፊት ነው ወይስ በኋላ በሚል በአያሌው ግራ ተጋብተዋል፡፡ በቀድሞ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ክርስቶስ ከታላቅ መከራ በኋላ ይመጣል፤ ቅዱሳንም በዚህ የኢየሱስ ዳግመኛ ምጽዓት ይነጠቃሉ ብለው ማሰብ ያዘወትሩ ነበር፡፡ ዛሬ ግን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ንጥቀት የሚመጣው ከታላቁ መከራ በፊት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እነርሱ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ወይም የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እንደማይመለከቱዋቸው፤ በየቀኑ የሚኖሩትን ሰላማዊና ያማረ ሕይወት እየኖሩ እንደሚነጠቁ ያስባሉ፡፡ እኛ ግን በዚህ የሐሰት ትምህርት መታለል የለብንም፡፡ እነዚህ ሰዎች የንጥቀትን ጊዜ በሚመለከት ባላቸው ዕውቀትና ግንዛቤ ክፉኛ ተሳስተዋል፡፡ የመጨረሻው ዘመን በጣም እየቀረበ ሲመጣ አምልኮዋቸው ይደክማል፡፡ እምነታቸውም ይጠፋል፡፡
 
ንጥቀት የሚመጣው በታላቁ መከራ አጋማሽ ላይ ነው ብዬ ስነግራችሁ ይህንን የምነግራችሁ ይበልጥ ሐይማኖተኞች እንድትሆኑ አይደለም፡፡ በንጥቀቱ ዘመን ላይ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራችሁና ከቅድመ መከራ ንጥቀት የሐሰት ትምህርት እንድትሸሹ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በቁጥር 7 ላይ እንዲህ ሲል በዝርዝር ነግሮናልና፡- ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡›› የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲወርዱ ቀደም ካሉት የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በተቃራኒ አንዱ ሌላውን ተከትለው ያለ ማቋረጥ ይወርዳሉ፡፡ እኛ ቅዱሳኖች ይህንን መገንዘብ አለብን፡፡
 
ዮሐንስ ራዕይ 16፡1-2 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ለሰባቱም መላእክት ሄዳችሁ የእግዚአብሄርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምጽ ከመቅደሱ ሰማሁ፡፡ ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፡፡ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው፡፡›› በተከታታይ የሚወርዱት ቀጣዮቹ ጽዋዎች ይህንን የመጀመሪያ መቅሰፍት በመከተል ምንም የመለከቶች መነፋትም ሆነ አንዳች ሌላ ነገር ሳይኖር ሰባቱ መለከቶች አንዱ ሌላውን ተከትለው ጽዋዎቻቸውን ያፈስሳሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ሰባቱን ጽዋዎች በተከታታይ በማፍሰስ ይህንን ዓለም ሙሉ በሙሉ ያወድመዋል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ሁሉም ነገር በሰባተኛው መለከት መቅሰፍት ውስጥ በአንድ ላይ በተካተቱት በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች መውረድ ያበቃልና፡፡
 
የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በሚወርዱበት ጊዜ በአንዱና በቀጣዩ መቅሰፍት መካከል ቢያንስ የሆኑ ዕረፍቶች አሉ፡፡ በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ግን እንዲህ ያለ ዕረፍት የለም፡፡ እነዚህ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ለመጨረሻዋ ቅጽበት የተጠበቁ በመሆናቸው የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ከወረዱ በኋላ በመጨረሻ የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ጊዜ ዓለም ሁሉም ነገር ወደሚያበቃበት ፈጽሞ አዲስ ወደሆነ ደረጃ ይቀየራል፡፡
 
ዮሐንስ ራዕይ 11፡15-18 ይህንን የመዘገበው ለዚህ ነው፡- ‹‹ሰባተኛውም መልአክ ነፋ፤ በሰማይም የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሳል የሚሉ ታላላቅ ድምጾች ሆኑ፡፡ በእግዚአብሄርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሄር እየሰገዱ እንዲህ አሉ፡፡ ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሄር ሆይ ትልቁን ሐይልህን ስለያዝህ፣ ስለነገስህም፣ እናመሰግንሃለን፡፡ አሕዛብም ተቆጡ፤ ቁጣህም መጣ፡፡ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፡፡ ለባርያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ፡፡››
 
እዚህ ላይ ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋበት ጊዜ ‹‹የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሳል›› የሚሉ ታላላቅ ድምጾች እንደሆኑ ተነግሮዋል፡፡ ነገር ግን አንድም መቅሰፍት አልተጠቀሰም፡፡ ለምን? ምክንያቱም የሰባተኛውን መለከት መነፋት ተከትሎ ወዲያውኑ የሚመጣው ሰባተኛው መቅሰፍት ሳይሆን ንጥቀት ነውና፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ የሚኖሩትንና ቀድሞውኑም ያንቀላፉትን ቅዱሳን ያስነሳና ይነጥቃቸዋል፡፡ የእነርሱ ንጥቀት ሲያበቃ የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ያወርድና ዓለምን ሙሉ በሙሉ ያጠፋታል፡፡
 
ንጥቀታችን በትክክል መቼ እንደሚሆን ማወቅ ከፈለግን መመልከት የሚኖርብን በራዕይ 10፡7 ላይ የሚገኘውን የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሄር ለባሮቹ ለነቢያት እንደተናገረው የእግዚአብሄር ምስጢር በእርግጠኝነት ይፈጸማል፡፡ እዚህ ላይ የእግዚአብሄር ምስጢር የሚያመለክተው የማንንም ሳይሆን የቅዱሳንን መነጠቅ ነው፡፡
 
እዚህ ላይ ግልጽ የሆነ ግንዛቤና ትክከለኛ እምነት እንዲኖራችሁ ሌላ ምንባብ አቀርባለሁ፡፡ እንደገናም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነሆ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም፡፡ ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፡፡ መለከት ይነፋልና፤ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሳሉ፡፡›› (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-52) መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳን ትንሳኤ በመጨረሻው መለከት ወቅት እንደሚሆን በግልጽ አይናገርምን? መለከት ሲነፋ በክርስቶስ የሞቱ የማይበሰብሱ ሆነው ይነሳሉ፡፡ እኛም ለመነጠቅ በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፡፡
 
በምዕራፍ 10 ላይ የተገለጠው መልአክ የመጀመሪያዎቹን ስድስት መለከቶች ከሚነፉት ከሌሎቹ መለከቶች የተለየ በእግዚአብሄር የተላከ ብርቱ መልአክ ነው፡፡ ይህ ብርቱ መልአክ የሚያደርገውን ስንመለከት በአብዛኛው አምላክን ስለሚመስል እግዚአብሄር ነው ብለን ልንሳሳት እንችላለን፡፡ ‹‹በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፡፡ ፊቱም እንደ ጸሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፡፡ የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ፡፡ ቀኝ እግሩንም በባህር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፡፡ እንደሚያገሳም አንበሳ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጎድጓድ በየድምጻቸው ተነገሩ፡፡››
 
በሌላ አነጋገር ይህ መልአክ እግዚአብሄር ነው ብለን ልንሳሳት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ይህ ብርቱ መልአክ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በእርሱ ፋንታ ሆኖ ይፈጽማልና፡፡ ይህም እግዚአብሄር እነዚህን ነገሮች ሁሉ በዚህ ብርቱ መልአክ አማካይነት እንደሚያደርግ ይነግረናል፡፡ እግሮቹን በባህርና በምድር ላይ ያደረገው ይህ መልአክ ሁለቱንም እንደሚያጠፋና ነጎድጓዶቹ ሲመጡም እግዚአብሄር ከዩኒቨርስና ከሰው ዘር ፍጥረት ጀምሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ያቀደውን ነገር ሁሉ እንደሚያጠናቅቅም ይነግረናል፡፡
 
እኛ ቅዱሳኖች ከሰባቱ መቅሰፍቶች ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ስድስት መቅሰፍቶች ውስጥ ኖረን እናልፋለን፡፡ እስከዚያ ድረስም ወንጌልን መስበካችንን እንቀጥላለን፡፡ እግዚአብሄር ዮሐንስን ታናሺቱን መጽሐፍ ወስዶ እንዲበላትና እንደገናም ትንቢት እንዲናገር ነገረው፡፡ ይህ ቃል ግን በእናንተና በእኔ ላይም አነጣጥሮዋል ማለትም እኛም እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ በእምነታችን መቀጠልና መኖር አለብን፡፡ ሰባተኛው መለከት ሲነፋ መነጠቃችን የተረጋገጠ ስለሚሆን ይህንን የመነጠቃችንን እውነት መረዳት በእምነትም እርሱን አጥብቀን መያዝና ይህ ቀን እስኪመጣ ድረስም ቃሉን መስማትና መስበክ አለብን፡፡
 
ሰባተኛው መለከት እስከሚነፋ ድረስ ጸረ ክርስቶስ በዚህ መቅሰፍት ውስጥ በሥራው ይተጋል፡፡ ቅዱሳንም ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ወዲያውኑ ይነጠቃሉ፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ የሚያምኑ ብዙ ምዕመናን እምነት ከመሰረቱ በተናወጠበትና ጥንካሬውን ባጣበት በዚህ ዘመንም ቢሆን እናንተና እኔ አሁንም በእምነት መኖር አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር መነጠቃችን ሰባተኛው መለከት ከተነፋ በኋላ በትክክል እንደሚመጣ ማመንና ሕይወታችንንም በዚህ እምነት መኖር አለብን፡፡
 
በቅርቡ የሰባቱን መለከቶች መቅሰፍቶች በዓኖቻችን እናያለን፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ሰባተኛው ድረስ እነዚህን መቅሰፍቶች በዓይኖቻችን አይተን እንቆጥራቸዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ እኛ ቅዱሳን ሰማዕት የምንሆንበት ዘመን እንደቀረበ በውስጣችን ሲሰማን በእርግጥም ሰማዕት እንሆናለን፡፡ ይህ አፈ ታሪክም ሆነ ሳይንሳዊ ልብ ወለድ አይደለም፡፡ በራሳችሁ ስሜትም ልታምኑት ወይም ላታምኑት የምትችሉት ነገርም አይደለም፡፡ ይህ በትክክል በእናንተና በእኔ ላይ የሚሆን ነው፡፡
 
በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ መነጠቅን በግልጽ የሚያሳየው ቁጥር ራዕይ 10፡7 የቅዱሳን መነጠቅ ሰባተኛው መለከት በሚነፋበት ጊዜ እንደሚመጣና ዓለምም በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ወደ ፍጻሜ እንደሚመጣ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱሳኖችን ከነጠቀ በኋላ መላውን ዓለም ያጠፋዋል፡፡ ቅዱሳኖች ሁሉ ከተነጠቁ በኋላ ጌታን በአየር ላይ ያመሰግኑታል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ግን የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ይወርዳሉ፡፡ ዓለምንም ሙሉ በሙሉ ያወድሙዋታል፡፡ እነዚህ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲጠናቀቁ ቅዱሳን ከጌታ ጋር ሆነው ወደታደሰችው ምድር ይወርዳሉ፡፡ ያን ጊዜ የሺህ ዓመት መንግሥት የሆነው የክርስቶስ መንግሥት በዚህች ምድር ላይ ይመሰረታል፡፡
 
የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች በአብዛኛው የቅድመ መከራን ንጥቀት ይደግፋሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከእነርሱ አንዳንዶቹ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም የሚለውን ጽንሰ አሳብ እስከ ማቀንቀን ድረስ ርቀው ሄደዋል፡፡ ታዲያ የሺህው ዓመት መንግሥት እውነተኛ አይደለምን? በዚህ ዘመን እንደዚያ ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በኮርያ ውስጥ እጅግ ታላላቅ በሆኑ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ከ666 ምልክት እስከ ንጥቀት ድረስ በራዕይ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ነገር እውነተኛ ሳይሆን ተምሳሌት ነው ብለው እስከ መናገር ደርሰዋል፡፡ ጌታችን በአንድ ወቅት ‹‹የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?›› ብሎ እንደጠየቀው በዚህ በመጨረሻው ዘመን እውነተኛ ምዕመናን ማግኘት በእርግጥም አዳጋች ነው፡፡
 
ጌታ ግን ንጥቀታችን በእርግጥም ተጨባጭ እንደሚሆን ነግሮናል፡፡ ስንነጠቅ ጌታን በአየር ላይ እንገናኘውና እናመሰግነዋለን፡፡ እርሱም ይጠነቀቅልናል፤ ያጽናናንማል፡፡ ከእርሱም ጋር እንደገና ወደዚህ ምድር እንመለሳለን፡፡ ወደ ሺህው ዓመት መንግሥት በመምጣትም በታደሰው ነገር ሁሉ መካከል ትንሳኤን ባገኘውና በተለወጠው ሰውነታችን ከተለወጠው ሕይወታችን ወደተለወጠው በረከታችን በማለፍ አዲስ ሕይወትን እንኖራለን፡፡ በእግዚአብሄር ተሸፍነን እንዲህ ባለ ክብር ውስጥ እንኖራለን፡፡ እናንተና እኔ በዚህ እምነትና በዚህ ተስፋ መኖር አለብን፡፡ የሺህው ዓመት መንግሥት ሲጠናቀቅ ወደ አዲሱ ሰማይና ምድር ገብተን በዘላለማዊ ክብርና ግርማ ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር እንነግሳለን፡፡
 
ወደ ሺህው ዓመት መንግሥትና ወደ አዲሱ ሰማይና ምድር ስንገባ መላዕክቶች ሁሉ አገልጋዮቻችን ይሆናሉ፡፡ መንፈሳዊ ፍጡራን፣ እግዚአብሄርና ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠሩት መላው ዓለምና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ የማን ንብረት ይሆናሉ? ሁሉም የእኛ ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን የሚወርሱት ቅዱሳኖች እንደሆኑ የሚናገረው ለዚህ ነው፡፡ እናንተና እኔ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ የተወለድን ቅዱሳን ስለሆንን የእግዚአብሄር ወራሾችና ከክርስቶስ ጋርም አብረን ወራሾች ነን፡፡ ስለዚህ እናንተና እኔ በምድር ላይ ያሉትን መከራዎች በእምነት አሸንፈን የውርሳችንን ቀን በመናፈቅ ልንጸና ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄር ምርጥ ወታደሮች እንደ መሆናችንም የሚዋጋ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡
 
እግዚአብሄር እነዚህ ነገሮች ሁሉ ያለ አንዳች መዘግየት በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ነግሮናል፡፡ በሌላ አነጋገር በቅርቡ በጣም በእርግጠኝነት ይፈጸማሉ፡፡ ያን ጊዜ አንዳንዶች እግዚአብሄር ስለዚህ ጉዳይ ለምን በዝርዝር አልነገረንም ብለው ይገረሙ ይሆናል፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልሱ የአምላክን ሥራዎች መሰወር የእርሱ ጥበብ ነው የሚለው ነው፡፡ (ምሳሌ 25፡2፤ሉቃስ 10፡21)
 
የእግዚአብሄር ዕቅድ በዝርዝር ተጽፎ ቢሆን ኖሮ በዚህ ዓለም ላይ ለብዙ ውጥረት ምክንያት ይሆን ነበር፡፡ ያን ጊዜ ቅዱሳን እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ መኖር አይችሉም፡፡ አብዛኞቹ ቅዱሳኖች በማያምኑ ሰዎች ይገደላሉ፡፡ አንድም ቅዱስ አይተርፍም፡፡ ስለ መጨረሻው ዘመን የሚናገረው እያንዳንዱ ዝርዝር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢጻፍ ኖሮ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች ዳግመኛ የተወለዱትን ምዕመናኖች በሙሉ ያርዱዋቸው ነበር፡፡ እግዚአብሄር ዓላማዎቹን በመሰወር ለሚገባቸው ብቻ ገለጠ፡፡ ለቀሩት ግን ምስጢር አድርጎ ደበቀው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጥበብ ነው፡፡ እግዚአብሄር ዕቅዱን ለእኛ በመግለጥ እንድናውቀው የፈቀደልን በዚህ ዘመን ለሚኖሩ ቅዱሳን በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡
 
ዳግመኛ የተወለዱት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያናት አሁን ስለ መጨረሻው ዘመን በዝርዝር ይናገራሉ ማለት የመጨረሻዎቹ ቀናቶች እየቀረቡን ነው ማለት ነው፡፡ የመከራው ዘመን ስለተቃረበ ቅዱሳን እንዲጸኑና ይህንን እየተቃረበ ያለውን መከራ እንዲያሸንፉ ትክክለኛ የሆነ የዘመን መጨረሻ ዕውቀት ይኖራቸው ዘንድ የራዕይ ቃል ይሰበካል፡፡ ዳግመኛ የተወለዱትም ቢሆኑ አንዳች እውነት ሳይኖራቸው መከራውን ቢጋፈጡ ምን እንደሚያደርጉ ስለማያውቁ መከራው በተጨባጭ ሲመጣ ትልቅ ግራ መጋባት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ይህ ግራ መጋባት በራሳቸው ግለሰባዊ እምነት ላይ ብቻ ለሚደገፉ ሰዎች ይበልጥ ያይላል፡፡
 
ብዙ ያልተዘጋጁ ነፍሳቶች ባለማወቃቸውና ግራ በመጋባታቸው የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ በተሳሳተ አቅጣጫ መንጉድ ይጀምራሉ፡፡ ‹‹እግዚአብሄር የነገረህ ነገር አለ?›› ‹‹ስትጸልይ ራዕይ አላየህምን?›› ብዙዎች ከእግዚአብሄር ዘንድ ራዕዮችን ለመሻት ይነሳሳሉ፡፡ ብዙዎችም በመጨረሻው ዘመን እንዲህ ያሉ ራዕዮችን እንዳዩ ይናገራሉ፡፡ ቅዱሳን አላዋቂዎች ሆነው የሚቀሩ ከሆኑ በመጨረሻው ዘመን በሚኖሩ ቅዱሳን መካከል የሚነሳው የተለመደ ጥያቄ ይህ ይሆናል፡፡
 
እግዚአብሄር ግን እንዲህ ባለ መንገድ ፈጽሞ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ እንዲህ በማለት አዞናልና፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡›› በሌላ አነጋገር ቅዱሱ ሰው መስማት ያለበት መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያኖች በኩል የሚነገረውን ብቻ ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ቃል ዋስትና የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ የሚመሰክረው እውነትና ትክክለኛ የሆነውን ብቻ ስለሆነ የዓለምን ፍጻሜ የሚያበስሩት መቅሰፍቶች በሚመጡበት ጊዜ እኛ ቅዱሳኖች በመከራዎች አንገረምም፡፡ ነገር ግን በእምነት እንኖራለን፡፡ ያን ጊዜ አስቀድሞ የእውነትን ቃል ሰምተን በእምነት በልባችን ውስጥ ጽፈነዋልና፡፡
 
ዮሐንስ አስቀድሞ ወደፊት የሚሆነውንና የእግዚአብሄር ባሮችም ከዚህ የተጻፈ ቃል ክልል ሳይወጡ እውነቱን ለምን እንደሚሰብኩ የገለጠልን ለዚህ ነው፡፡ ትንቢት መናገር ማለት የሚመጣውን ነገር፤ የተጻፈውን የእግዚአብሄር ቃል ማወቅና መስበክ እንጂ ሌላ ማለት አይደለም፡፡ በሕልሞች ራዕዮችን ማየት ወይም ጸሎት ትንቢትን መናገር ማለት አይደለም!
 
መነጠቃችን በእርግጥም ፈጽሞ የማይቀርና እኛም የእግዚአብሄር ቅዱሳን መሆናችንን አትርሱ፡፡ መነጠቃችሁ ሲመጣ ለሺህ ዓመት ለመኖር ዳግመኛ ወደታደሰችው ምድር የምትወርዱና በአዲሱ ሰማይና ምድር ለዘላለም የምትኖሩ፣ በአየር ላይ ከክርስቶስ ጋር የምትሆኑ ቅዱሳን እንደሆናችሁም አትርሱ፡፡ ስለ ቅድመ መከራ ንጥቀት ወይም ስለ ድህረ መከራ ንጥቀት ሲናገሩ ወይም የሺህ ዓመት መንግሥት የሚባል ጨርሶ የለም ሲሉ አትስሙ፡፡ እዚህ ላይ እየተወያየንበት ያለውን ምንባብ በማሳየት እውነቱን ንገሩዋቸው፡፡ 1ኛ ተሰሎንቄ 4ን እና 1ኛ ቆሮንቶስ 15ን ልትጠቁሙዋቸውና ጌታ በመላዕክት አለቃ ድምጽና በመጨረሻው መለከት መነፋት እንደሚወርድና ቅዱሳኖች ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ በአየር ላይ እንደሚነጥቃቸውም ልትነግሩዋቸው ይገባችኋል፡፡ እምነታችሁን መጠበቅ የምትችሉት በዚህ ንጥቀት ስታምኑ ብቻ ነው፡፡
 
ንጥቀትን ለማግኘት በእምነት ሰማዕት መሆንና የሥጋ ትንሳኤ ሊኖር ይገባል፡፡ ንጥቀት ከትንሳኤ ጋር አብሮ ስለሚመጣ ትንሳኤን እንዳገኘን ወዲያውኑ ተነጥቀን በአየር ላይ ከፍ እንላለን፡፡ ስለዚህ ንጥቀትና ትንሳኤ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ትንሳኤ ተካፋይ መሆን ማለት በሺህው ዓመት መንግሥት ከጌታ ጋር መኖር ማለት ነው፡፡ መነጠቅ ማለትም እንደዚሁ በዚህ ምድር ላይ ለሺህ ዓመት ከጌታ ጋር መኖር ማለት ነው፡፡
 
የምንነጠቀው ለምንድነው? ምክንያቱም እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በማፍሰስ በዚህች ምድር ላይ ያለውን እያንዳንዱን ነገር ስለሚያጠፋ ነው፡፡ ልጆቹን ከእነዚህ የጥፋት መቅሰፍቶች ለማዳን ሲል አስቀድሞ ቅዱሳኖችን ይነጥቃቸዋል፡፡ ቅዱሳኖችን ከሐጢያተኞች ለመለየትና ልዩ መዳረሻዎቻቸውን ለማሳየት ሲል ቅዱሳኖችን ይነጥቃቸዋል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ማለትም በንጥቀታችን፣ በትንሳኤያችንና በሰማዕትነታችን ማመን አለብን፡፡
ለአንዳንዶች የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በዝርዝር ሲገለጥላቸው ለሌሎች ግን ሙሉ በሙሉ የተደበቀ ምስጢር ሆኖ ይቀራል፡፡ ልክ እንደዚሁ የቅዱሳን ሰማዕትነት፣ ትንሳኤ፣ ንጥቀትና በሺህው ዓመት መንግሥትና በአዲሱ ሰማይና ምድር ላይ መንገሳቸው ሁሉም የእግዚአብሄር ምስጢሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን ምስጢሮች የገለጠውና ያሳየው ዳግመኛ ለተወለዱት ብቻ ነው፡፡ በእነዚህ ምስጢሮች እንዲያምኑ በማድረግም በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንዲያልፉና በንጥቀትና በመንግሥተ ሰማይ ተስፋ በማድረግ መከራዎቻቸውን እንዲያሸንፉ አስችሎዋቸዋል፡፡
 
እናንተና እኔ የዚህ ዓይነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነት እምነት ሳይኖረን ማለትም እንደምንነጠቅ፣ በአዲስ ሰማይና ምድር እንደምንኖር፣ ጌታም በጸረ ክርስቶስ ስንገደል እንደሚያስነሳንና እንደሚነጥቀን፣ በአየር ላይ እንድንቆይ እንደሚፈቅድልንና ከዚያም ለሺህ ዓመት ከእርሱ ጋር ለመንገስ ወደዚህ ምድር እንደምንመለስ ሳናምን በዚህ በመጨረሻው ዘመን በሚገጥመን አስቸጋሪና አስጨናቂ ሕይወት ውስጥ መጽናት አንችልም፡፡
 
ቅዱሳን ውብ ሕልም አላቸው፡፡ ይህንን ሕልም እውን የሚያደርገው ጌታችን እንጂ ሌላ ማንም አይደለም፡፡ ይህ ተስፋ ከሌለን በዚህ አስጨናቂ ዓለም ውስጥ የምንኖረው በሐዘንና በመከራ ብቻ ይሆናል፡፡
 
ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለእርሱ በአደራ የተሰጠውን ውብ ነገር እንዲንከባከበው ነገረው፡፡ ይህ ወንጌል ውብ ነው፡፡ ሰማዕትነታችን፣ ትንሳኤያችንና ንጥቀታችንም ውቦች ናቸው፡፡ በሺህው ዓመት መንግሥትና በአዲሱ ሰማይና ምድር መኖርም እንደዚሁ ውብ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥሩና ውብ ነገሮች ናቸው፡፡ የቅዱሳንም ብቻ ናቸው፡፡ ሁሉም ምናቦች ወይም እሳቤዎች ሳይሆኑ ተጨባጭ እምነትና ተስፋ ናቸው፡፡ እነዚህ ጌታ የሰጠን ተስፋችንና እምነታችን ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁሉ በማመን የሺህው ዓመት መንግሥትና አዲሱ ሰማይና ምድር ወደ እኛ የሚመጡበትን ቀን ተስፋ በማድረግ በዚህ ዘመን መኖር አለብን፡፡
 
የምንነጠቀው እናንተና እኔ ነን፡፡ በጌታ ፊት ለመቆምና በሺህው ዓመት መንግሥትና በአዲሱ ሰማይና ምድር ላይ ለመንገስ የምንነጠቅበትን ቀን በመጠበቅ በእምነት መኖር አለብን፡፡
 
እግዚአብሄር ፈጥኖ እንደሚመጣ ነግሮናል፡፡ በሰባቱ ዓመት የታላቁ መከራ ክፍለ ጊዜ በመጀመሪያው አጋማሽ ወቅት የሚወርዱት መቅሰፍቶች ለዘብ ያሉና ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ናቸው፡፡ መቅሰፍቶቹ በሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ ውስጥ የሚዘልቁ ቢሆኑ ኖሮ ሰው እንዴት ሊቋቋማቸው ይችላል? የመጀመሪያዎቹ መቅሰፍቶች አጭር ናቸው፡፡ ጊዜ ወደ መጨረሻው ፍጻሜ እየተቃረበ ሲሄድ ብዙ የሚታይ ይኖራል፡፡ የሰባተኛው መለከት መቅሰፍት ሲመጣ አስደናቂ ወደሆነ መጠን ያድጋል፡፡
 
ሰይጣን የቅዱሳኖችን እምነት ለማናወጥ ሲሞክር ጥቂት የቤተክርስቲያን መሪዎችን በመግደል ምሳሌዎች አድርጎ ያቀርባቸዋል፡፡ ሰይጣን ‹‹እግዚአብሄርን የምትክድ ከሆነ ሕይወትህን አተርፍልሃለሁ!›› ይል ይሆናል፡፡ ዓለም ብትሻሻል እንኳን የሰይጣንን ስጦታ በሚመለከት ሁለት ጊዜ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ጌታ የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች እንደሚያወርድና በእነዚህ መቅሰፍቶች በመጡት ችግሮች ሁሉ ውስጥ እንደሚያልፍ በሚገባ የሚያውቅ ትክክለኛ አእምሮ ያለው ሰው እንዴት ጌታን ይክዳል? የዓለምን ፍጻሜ የሚያውቁ ቅዱሳን ጌታንም ሆነ እምነታቸውን አይክዱም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ያለ በመሆኑም ድፍረቱን ይሰጠናል፡፡
 
የእግዚአብሄር ዕቅዶች በሙሉ በመጨረሻው ዘመን ስለሚፈጸሙ ለመሰላቸት ቦታ የለም፡፡ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩት መቅሰፍቶች ሲጠናቀቁ ትንሳኤ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላም በአየር ላይ ከፍ የሚያደርገን ንጥቀት ይመጣል፡፡ የሥጋ ሰውነታችን ወደ መንፈሳዊ ሰውነት ሲለወጥና ጌታን ሲያመሰግን አስቡ፡፡ በእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ ከዚህ በፊት በዚህ ምድር ላይ ፈጽሞ ባልተለማመድነው ሙሉ፣ ልዩ፣ ውብና ያማረ በሆነ ዓለም ውስጥ መደሰት እንችላለን፡፡ መንፈሳዊ አካሎች ከጊዜና ከቦታ ወሰኖች ነጻ ስለሆኑ ወደምንፈልገው ማንኛውም ስፍራ መሄድ በምንችልበት ድንቅና ግሩም ዓለም ውስጥ እንኖራለን፡፡
 
እንዲህ ያሉ ታላላቅ በረከቶችን ስለሰጠን ለእግዚአብሄር እውነተኛ ምስጋናን አቀርባለሁ፡፡ በቃሉ አማካይነት ታላቁን መከራ፣ መቅሰፍቶቹን፣ ሰማዕትነታችንን፣ ትንሳኤያችንንና ንጥቀታችንን በዝርዝር ስለገለጠልን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ ልቦቻችን ሁልጊዜም ይህንን ዘመን በማወቅና በእርሱ በማመን እንዲኖሩም እጸልያለሁ፡፡