Search

Kazania

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[7-1] በታላቁ መከራ ወቅት ማን ይድናል? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 7፡1-17 ››

በታላቁ መከራ ወቅት ማን ይድናል?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 7፡1-17 ››
‹‹ከዚህ በኋላም በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላዕክት አየሁ፡፡ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ፡፡ የሕያው አምላክ ማህተም ያለውም ሌላ መልአክ ከጸሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፡፡ ምድርንና ባሕርንም ሊጎዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላዕክት በታላቅ ድምጽ እየጮኸ፡- የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ አላቸው፡፡ የታተሙትንም ቁጥር ሰማሁ፡፡ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ፡፡ ከይሁዳ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ ታተሙ፡፡ ከሮቤል ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከጋድ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከአሴር ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከንፍታሌም ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከምናሴ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከስምዖን ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከሌዊ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከይሳኮር ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከዛብሎን ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከዮሴፍ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከብንያም ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፡፡ ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ፣ ከወገንም፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፡፡ በታላቅ ድምጽም እየጮሁ፡- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ፡፡ መላዕክቱም ሁሉ፣ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹም፣ በአራቱም እንስሶች ዙሪያ ቆመው ነበር፡፡ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፡፡ ለእግዚአብሄርም እየሰገዱ፡- አሜን በረከትና ክብር፣ ጥበብም፣ ምስጋናም፣ ውዳሴም፣ ሐይልም፣ ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን አሜን አሉ፡፡ ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፡- እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ፡፡ እኔም፡- ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ አልሁት፡፡ አለኝም፡- እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ዙፋን ፊት አሉ፡፡ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፡፡ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፡፡ ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፡፡ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፡፡ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፡፡ እግዚአብሄርም ዕንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ‹‹ከዚህ በኋላም በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላዕክት አየሁ፡፡ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ፡፡››
የመከራ ነፋሳቶች መንፈሳቸው ወይም አለመንፈሳቸው ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሄር ፈቃድ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ይህ ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ ምድር ላይ ታላቁን መከራ ከመፍቀዱ በፊት ከእስራኤል ነገዶች 144,000 ሊያድንና የራሱ ሕዝብ ሊያደርጋቸው ወስኖዋል፡፡
 
ቁጥር 2-3፡- ‹‹የሕያው አምላክ ማህተም ያለውም ሌላ መልአክ ከጸሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፡፡ ምድርንና ባሕርንም ሊጎዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላዕክት በታላቅ ድምጽ እየጮኸ፡- የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ አላቸው፡፡››
እዚህ ላይ እግዚአብሄር ምድርንና ባህርን እንዲጉዱ የተሰጣቸውን አራቱን መላዕክቶች 144,000 እስራኤሎች እስከሚታተሙ ድረስ ዓለምን እንዳይጎዱ ነገራቸው፡፡ ይህ ለእስራኤል ሕዝብ ያለውን የተለየ ጥበቃ የሚያሳይ ልዩ የእግዚአብሄር ትዕዛዝ ነበር፡፡
 
ቁጥር 4፡- ‹‹የታተሙትንም ቁጥር ሰማሁ፡፡ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ፡፡››
በእግዚአብሄር የታተሙ ሰዎች በመጨረሻው ዘመን ታላቅ መከራ ወቅት ከእግዚአብሄር ዘንድ የተለየ ጥበቃንና የእርሱን የደህንነት በረከት ይቀበላሉ፡፡
 
ቁጥር 5-9፡- ‹‹ከይሁዳ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ ታተሙ፡፡ ከሮቤል ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከጋድ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከአሴር ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከንፍታሌም ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከምናሴ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከስምዖን ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከሌዊ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከይሳኮር ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከዛብሎን ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከዮሴፍ ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፣ ከብንያም ነገድ አስራ ሁለት ሺህ፡፡ ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ፣ ከወገንም፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፡፡››
ይህ ቁጥር ከእስራኤል ሕዝብ መካከል የታተሙትን ቁጥር ይነግረናል፡፡ ከእያንዳንዱ የእስራኤል የእስራኤል ነገድ 12000 ሆነው የእግዚአብሄርን ልዩ ጸጋ ተቀባዮች ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሄር ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ለተወጣቱት 12,000 ደህንነትን በመስጠት የራሱ ሕዝብ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ልዩ ጸጋ ለእያንዳንዱ ነገድ በኩል ደረጃ ይሰጣል፡፡
እግዚአብሄር እያንዳንዱን የእስራኤል ነገድ በእኩል ደረጃ ስለወደደ ለሁሉም የእርሱ ሕዝብ የሚሆኑበትን ተመሳሳይ በረከት ሰጥቶዋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር እስራኤሎችን በዚህ ጸጋ ያለበሳቸው ለአብርሃምና ለዘሮቹ የተሰጠውን የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም ነው፡፡ በዚህም እግዚአብሄር ለሰው ዘር ቃል የገባውንና ያቀደውን ሁሉ ሲፈጸም ማየት ይቻላል፡፡
ይህ በታላቁ መከራ ወቅት እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው አሕዛቦችም እንደሚድኑና የእግዚአብሄር ሕዝብ እንደሚሆኑ ይግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር በአሕዛቦችም መካከል በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው የሚድኑና በመጨረሻው ዘመን ለእምነታቸው ሰማዕት የሚሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ እንኳን አሕዛቦችን የራሱ ሕዝቦች ለማድረግ እንደሚሰራ ማስታወስ አለብን፡፡
 
ቁጥር 10-11፡- ‹‹በታላቅ ድምጽም እየጮሁ፡- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ፡፡ መላዕክቱም ሁሉ፣ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹም፣ በአራቱም እንስሶች ዙሪያ ቆመው ነበር፡፡ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፡፡››
እግዚአብሄር በመጨረሻውም ዘመን እንኳን ማዳኑን ለእስራኤሎችና ለእኛ ለአሕዛቦች ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ስግደትን፣ ምስጋናንና ክብርን ሁሉ ሊቀበል የተገባው ነው፡፡ ምክንያቱም ለቅዱሳን የስግደታቸው ሁሉ ማዕከል ሌላ ሳይሆን እግዚአብሄር ብቻ ነውና፡፡
 
ቁጥር 12፡- ‹‹ለእግዚአብሄርም እየሰገዱ፡- አሜን በረከትና ክብር፣ ጥበብም፣ ምስጋናም፣ ውዳሴም፣ ሐይልም፣ ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን አሜን አሉ፡፡››
የእግዚአብሄር አገልጋዮች በሙሉ አምላክ ለሆነው ጌታ ምስጋናን ይሰጣሉ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ሁሉ ምስጋና ክብር መቀበሉ ተገቢ ነው፡፡
 
ቁጥር 13-14፡- ‹‹ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፡- እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ፡፡ እኔም፡- ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ አልሁት፡፡ አለኝም፡- እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ፡፡››
እግዚአብሄር ቅዱሳን ክቡር የሆነውን ሰማዕትነታቸውን እንዲያሸንፉና እውነተኛ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ የታላቁን መከራ ነፋስ ካስነሳ በኋላ የመጨረሻ መከሩን ይሰበስባል፡፡
የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመት ተኩል ሲያልፉ ቅዱሳን በጸረ ክርስቶስ ክፉኛ ይሰደዳሉ፡፡ እምነታቸውን ለመከላከልም ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ይህ የሰማዕትነት መከራ በታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ከማናቸውም ሌሎች መከራዎች የተለየ ደርዝ ያለው ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ በእግዚአብሄር የሚያምኑ ቅዱሳንን እምነት ፈጽሞ የሚጠይቅ ነው፡፡ ሰማዕትነት ለቅዱሳን ታላቅ ክብር ነው፡፡ ቅዱሳን ሁሉ በሰማዕትነታቸው በእግዚአብሄር ያላቸውን እምነት ይበልጥ በግልጽ ማሳየት ይችላሉ፡፡ በመጨረሻው ዘመን ታላቅ መከራ ውስጥ ቅዱሳን ሁሉ በሰማዕትነታቸው እምነታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ትንሳኤን አግኝተው በመነጠቅም በእግዚአብሄር ዙፋን ፊት ይቆማሉ፡፡
 
ቁጥር 15-16፡- ‹‹ስለዚህ በእግዚአብሄር ዙፋን ፊት አሉ፡፡ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፡፡ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፡፡ ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፡፡››
በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ደህንነት ላይ ያላቸውን እምነት ለመጠበቅ በመጨረሻው ዘመን ታላቅ መከራ ውስጥ ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለ እምነት ላላቸው ቅዱሳን ልዩ ጥበቃውንና በረከቱን ይሰጣቸዋል፡፡ በዕቅፉም ውስጥ ያስገባቸዋል፡፡
ቅዱሳን ከጸረ ክርስቶስ ጋር ተዋግተው ሰማዕት ከሆኑና ትንሳኤን ካገኙ በኋላ በእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ ዳግመኛ አይሞቱም ወይም በፍጹም አይሰቃዩም፡፡ ለእግዚአብሄር ልጆች በተሰጡት ባርኮቶች ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ፡፡ በእግዚአብሄር ዕቅፍ ውስጥ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች አንዳች አይጎድልባቸውም፡፡ ዳግመኛም ክፉ የሆነ ጉዳት ወይም ስቃይ አይደርስባቸውም፡፡ አሁን እነርሱን የሚጠብቃቸው ለዘላለም ለእነርሱ የሚሰጣቸው የእግዚአብሄር ልዩ ሽልማት፣ ፍቅርና ክብር ነው፡፡
 
ቁጥር 17፡- ‹‹በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፡፡ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፡፡ እግዚአብሄርም ዕንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፡፡››
እግዚአብሄር የቅዱሳን ዘላለማዊ እረኛ ይሆንና ዘላለማዊ በረከቶቹን ይሰጣቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ለጌታ ሲሉ ለተቀበሉት መከራና ሰማዕትነት ሁሉ ሽልማት ለመስጠት ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭ ይመራቸዋል፡፡ በእግዚአብሄር ዙፋን ፊትም ከጌታ ጋር እንጀራን እንዲቆርሱ ይፈቅድላቸዋል፡፡ በእርሱ ክብር ውስጥ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድም ለዘላለም በረከቶቹን ያለብሳቸዋል፡፡ ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ ሳሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስላመኑ፣ ለእግዚአብሄር ክብርም የአገልግሎት ሕይወትን ስለኖሩና ለስሙም ሰማዕት ስለሆኑ እንዲህ እምነታቸውን የጠበቁትን እግዚአብሄር በአዲሱ ሰማይና ምድር በክብሩ መካከል ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሐሌሊያ! ጌታችን ይመስገን!