Search

Проповеди

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[17-1] በብዙ ውሆች ላይ የተቀመጠችው የጋለሞታይቱ ፍርድ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 17፡1-18 ››

በብዙ ውሆች ላይ የተቀመጠችው የጋለሞታይቱ ፍርድ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 17፡1-18 ››
‹‹ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፡- ና በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፡፡ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ፡፡ በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ፡፡ ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በዕንቆችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፡፡ በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም፡- ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት ተብሎ ተጻፈ፡፡ ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት፡፡ ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ፡፡ መልአኩም አለኝ፡- የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ፡፡ ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፤ አሁንም የለም፤ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፡፡ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ፣ አሁንም እንደሌለ፣ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ፡፡ ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው፡፡ ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፡፡ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፡፡ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱም አለ፤ የቀረውም ገና አልመጣም፡፡ ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል፡፡ የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው፡፡ ከሰባቱም አንዱ ነው፡፡ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፡፡ ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ፡፡ እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፤ ሐይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፤ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ፡፡ አለኝም፡- ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች ወገኖችና ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብም፣ ቋንቋዎችም ናቸው፡፡ ያየሃቸው አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፡፡ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፡፡ በእሳትም ያቃጥሉአታል፡፡ እግዚአብሄር አሳቡን እንዲያደርጉ፣ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ፣ የእግዚአብሄርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና፡፡ ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፡- ና በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፡፡
በዚህ በዋናው ምንባብ ላይ የተነገረላት ጋለሞታ ሴትና አውሬው ማን እንደሆነ ማወቅ ምዕራፍ 17ን ለመተርጎምና ለመረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ በቁጥር 1 ላይ የተጠቀሰችው ‹‹ጋለሞታ›› የምታመለክተው የዓለምን ሐይማኖቶች ሲሆን ‹‹ሴቲቱ›› ደግሞ ዓለምን ታመለክታለች፡፡ በሌላ በኩል ‹‹አውሬው›› ጸረ ክርስቶስን ያመለክታል፡፡ ‹‹ብዙ ውሆች›› የዲያብሎስን አስተምህሮቶች ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በብዙም ውሃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ›› የሚለው ሐረግ እግዚአብሄር በብዙዎቹ የሰይጣን ትምህርቶች ላይ የተቀመጡትን የዓለም ሐይማኖቶች እንደሚፈርድባቸው ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 2፡- የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ፡፡
‹‹መሴሰን›› ራሱን እግዚአብሄርን ከመውደድ ይልቅ ይህንን ዓለምና በውስጡ ያሉትን ነገሮች መውደድን ያመለክታል፡፡ የዓለምን ነገሮች የሚመስሉ ምስሎችን መስራትና እነርሱን ልክ እንደ አምላክ ማምለክና መውደድ በእርግጥም የሴሰኝነት ምግባሮች ናቸው፡፡
‹‹የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ›› የሚለው ሐረግ የዚህ ዓለም መሪዎች ሕይወታቸውን የኖሩት በዓለም ሐይማኖቶች ሰክረው ነው ማለት ነው፡፡ የዓለም ሰዎች በሙሉም የዓለም ሐይማኖቶች ያቀረቡላቸውን እነዚህን ሐጢያቶች ጠጥተው በመስከር ሕይወታቸውን ኖረዋል፡፡
 
ቁጥር 3፡- በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ፡፡
‹‹በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ›› የሚለው ሐረግ የዚህ ዓለም ሕዝብ ቅዱሳንን ለማሳደድና ለመግደል ልቡን ከጸረ ክርስቶስ ጋር እንደሚያስተባብር ይነግረናል፡፡ ይህም የዓለም ሕዝብ ጸረ ክርስቶስ እንደሚያዝዘው የእርሱን ሥራዎች በመስራት የእግዚአብሄር ጠላት ባርያዎች እንደሚሆኑ ያሳየናል፡፡ አውሬው እግዚአብሄርን የሚቃወመው ጸረ ክርስቶስ ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ በብዙ ነገስታቶች ላይ ይሰለጥናል፡፡ በብዙ የዓለም ብሄረ መንግሥታቶች ላይም ይነግሳል፡፡
ነገር ግን ጸረ ክርስቶስ ዕብሪተኛ በመሆኑ እግዚአብሄርን ለመሳደብና የትዕቢት ቃሎችን ለመናገር አያመነታም፡፡ እርሱ ራሱ አምላክ ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በመናገር በዕብሪት ቃሎች እየደነፋ እግዚአብሄርን ይሳደባል፡፡ ራሱንም ልክ እንደ እግዚአብሄር ከፍ ያደርጋል፡፡ ሥልጣኑ በዓለምና በአህዛብ ነገሥተቶች ሁሉ ላይ ተዘርግቶ ይነግሳል፡፡
‹‹ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶችም ባሉበት›› በሚለው ሐረግ ውስጥ ‹‹ሰባቱ ራሶች›› እዚህ ላይ የሚያመለክቱት የዓለምን ሰባቱን ነገሥታት ሲሆን ‹‹አስሩ ቀንዶች›› ደግሞ የሚያመላክቱት የዓለምን መንግሥታቶች ነው፡፡
 
ቁጥር 4፡- ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በዕንቆችም ተሸልማ ነበር፤ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኩሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፡፡
‹‹ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጎናጽፋ፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በዕንቆችም ተሸልማ ነበር›› በሚለው ሐረግ ምንባቡ ከጸረ ክርስቶስ ጋር የሚዶልቱት ዓለማዊ ሐይማኖቶች እርሱን ንጉሣቸው አድርገው እንደሚያስቡት ይነግረናል፡፡ ስለዚህ እነርሱን የሚቃወሙ ሁሉ ሞት ሊፈረድባቸው የሚገባ መሆኑ ትክክል እንደሆነ ያስባሉ፡፡ እንዲያውም ቅዱሳንን በመቃወም በምግባሮቻቸው የሚያስቡዋቸውን አስተሳሰቦቻቸውን ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡
ይህንን ዓለም ዘላለማዊ የደስታ መንግሥት አድርጎ ለመሸላለምም ራሳቸውን በዓለም ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮችና ዕንቁዎች ውብ አድርገው ይሸልማሉ፡፡ ነገር ግን እምነታቸው ይበልጥ የሚማረከው በዚህ ዓለም ላይ ሲኖሩ ሳሉ ምን ያህል የስጋ ተድላዎች ማግኘት እንደቻሉ በማሰብ ላይ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የዚህን ዓለም ሕዝብ ሲመለከት የሚያየው በረከሱት ሐጢያቶቻቸው የተሞላውን ዓለም በመሆኑ ሁሉም በፊቱ የረከሱ ሆነው ይታያሉ፡፡
 
ቁጥር 5፡- በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም፡- ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት ተብሎ ተጻፈ፡፡
የዓለም ሐይማኖታዊ ሰዎች ራሳቸውን ልክ እንደ ልዕልት ለመሸላለም ቢሞክሩም ጋለሞታ ሆነው ይገለጣሉ፡፡ በአንድ በኩል ‹‹ባቢሎን›› የሚለው ስምዋ የጋለሞታይቱን በትዕቢት የተሞላ ጣዖታዊና ጨቋኝ ባህርይ ሲያሳየን በሌላ በኩል ‹‹እናት›› የሚለው ቃል በታሪክ ውስጥ ያሉት የጸረ ክርስቶስ ሐይሎች በሙሉ ምንጫቸው ሌላ ሳይሆን ዓለም ራሱ እንደሆነና ዓለም የሁሉም ዓይነት ጣዖት አምልኮና ብልሹነት ሥረ መሰረት እንደሆነ ያሳየናል፡፡
ይህ ዓለም በሚያብለጨልጩና ውብ በሆኑ ዕንቁዎች የተሸለመ ቢሆንም እግዚአብሄርን የሚቃወመውና በእነዚህ የዓለም ሕዝቦች ልብ ውስጥ የሚሰራው ጸረ ክርስቶስ ልክ እንደ እናታቸው ሆኖ ይሰራል፡፡ ስለዚህ ጌታ አምላካችን ሁሉንም በታላቁ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሊያጠፋቸው ወስኖዋል፡፡
 
ቁጥር 6፡- ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት፡፡ ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ፡፡
‹‹ቅዱሳን›› የሚያመለክቱት በመላው የቤተክርስቲያን ታሪክ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ያመኑትን የእምነት ሰዎች ነው፡፡ ‹‹የኢየሱስ ምስክሮች›› የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው በቅዱሳን መካከል ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅና አዳኛቸው የመሆኑን እውነት የመሰከሩትንና እምነታቸውን ለመጠበቅም በተለየ ሁኔታ ሰማዕት የሆኑትን ነው፡፡
ይህ ቁጥር ቅዱሳኖችን የሚያሳድዱትና የሚገድሉት የዚህ ዓለም የሐይማኖት ሰዎች እንጂ ሌሎች እንዳልሆኑ አበክሮ ይናገራል፡፡ እነርሱ የጸረ ክርስቶስ ግምባር ቀደም ሐይል ሆነው ይህንን ክፋት ይሰራሉ፡፡
እዚህ ላይ ዮሐንስ ሴቲቱን ባየት ጊዜ ‹‹እጅግ ትልቅ ድንቅ እንዳደነቀ› ተናግሮዋል፡፡ ይህ ዓለም በእርግጥም ጥያቄን የሚፈጥር ዓለም ነው፡፡ ቅዱሳን ዓለምን ለመጉዳት ምንም ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ሆኖም ይህ ዓለም ከጸረ ክርስቶስ ጋር በመዶለት ብዙ ቅዱሳንን ይገድላል፡፡ ይህ ዓለም እንግዳ እንጂ እንዴት ሌላ አንዳች ነገር ሊሆን ይችላል? የዚህ ዓለም ሰዎች እነዚህን ነገሮች በእርግጥም በቅዱሳን ላይ ያመጣሉ፡፡ ይህ ዓለም በጸረ ክርስቶስ ቁጥጥር ሥር ያለ በመሆኑ የእርሱ ባሮች የሆኑት የዓለም ሕዝቦች ቅዱሳኖችን ይዘው ይገድሉዋቸዋል፡፡
ስለዚህ እነርሱ በእርግጥም ለእኛ ባዕዳን መስለው ይታያሉ፡፡ የዓለምን ሰዎች በምንመለከትበት ጊዜ በእርግጥ በሆነ ሁኔታ ባዕድ መስለው አይታዩምን? ሰዎች በእግዚአብሄር አምሳል ተፈጥረው ሳሉ የጸረ ክርስቶስ ባሮች ሆነው ማንም ሰው ሳይሆን በእግዚአብሄር የሚያምኑ ብዙ ሰዎች እንዴት ሊገደሉ ይችላሉ? ለዚህ ምክንያቱ ዓለም የሰይጣን ባርያ መሆኑ ነው፡፡
 
ቁጥር 7፡- መልአኩም አለኝ፡- የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ፡፡
እዚህ ላይ ‹‹ሴቲቱ›› የምታመለክተው የዚህን ዓለም ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ጸረ ክርስቶስ ተብሎ ተጠራው አውሬ በዓለም ነገሥታቶችና በሕዝቦችዋ ሁሉ ላይ እንደሚነግስና በእነርሱ በኩልም እግዚአብሄርን የመቃወም፣ ቅዱሳንን የማሳደድና የመግደል ሥራዎቹን እንደሚሰራ ይነግረናል፡፡ ‹‹የአውሬው ምስጢር›› የሚያመለክተው በሰይጣን ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሰውን የጸረ ክርስቶስ ማንነት ነው፡፡ እርሱም የዚህን ዓለም ሕዝቦች የራሱ ያደርጋቸዋል፡፡
የዚህ ዓለም ሕዝብ ከጸረ ክርስቶስ ጋር በመዶለት ብዙ ቁጥር ያላቸውን የእግዚአብሄር ሕዝቦች በመፍጀት የሰይጣን መሳርያዎች ይሆናሉ፡፡ ይህ ዓለምና ጸረ ክርስቶስ አሁን ከዓይኖቻችን የተደበቁ የሰይጣን መሳርያዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን የታላቁ መከራ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ተኩል ሲያልፉ ይነሱና ቅዱሳንን ይገድላሉ፡፡
ይህ ዓለም በጣም ብዙ የሚያስቡ፣ የተማሩና ብልህ የሆኑ ፖለቲከኞች፣ ምሁራኖች፣ ፈላስፎችና ፕሮፌሰሮች እያሉበት ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ግራ የሚጋባ ሰው ይኖር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዓለም ከጸረ ክርስቶስ ጋር ስለሚያሴር እነዚህ ነገሮች ሁሉ የቅዱሳንን ዕልቂት ጨምሮ በተግባር የሚታዩ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም ለጸረ ክርስቶስ በማጎብደድ ቅዱሳኖችን የሚገድል መሆኑ የጸረ ክርስቶስን ምስጢር የሚፈታ ቁልፍ ነው፡፡
 
ቁጥር 8፡- ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፤ አሁንም የለም፤ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፡፡ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ፣ አሁንም እንደሌለ፣ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ፡፡
ይህ ቁጥር ጸረ ክርስቶስ ከጥንት ነገሥታቶች መካከል እንደተገኘና አሁን በዚህ ዓለም ላይ ባይኖርም ወደፊት በዓለም ላይ ብቅ እንደሚል ይነግረናል፡፡ የዚህ ዓለም ሕዝብም ጸረ ክርስቶስ ሲገለጥና ቅዱሳንን ሲግድል ሲያይ እጅግ እንደሚደነቁም ይነግረናል፡፡
ጸረ ክርስቶስ በዚህ ዓለም አዲስ ፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ ዓላማዎቹን ይተገብራል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ለሚኖረው ሕዝብ ምስጢራዊ ሆኖ ቢቀርም ነገር ድንቅ ሆኖ ይታያል፡፡ እርሱ የዚህን ዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የአስተሳሰብና የሐይማኖት ችግሮችን ወስዶ በችሎታው ሁሉንም ስለሚፈታቸው ብዙ ሰዎች እርሱን በመጨረሻው ዘመን ዳግመኛ እንደሚመጣው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስቡትና ይከተሉታል፡፡ ስለዚህ በዓለም ሕዝብ ዓይኖች ፊት አስገራሚ ሆኖ ይቀራል፡፡
 
ቁጥር 9፡- ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው፡፡ ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፡፡
ይህ ቁጥር ጸረ ክርስቶስ በዓለም ሕዝብ ላይ ለመሰልጠን የራሱን ሕጎች እንደሚደነግግና ዓላማዎቹን ለማስፈጸምም እነዚህን ሕጎች ለአስተዳደር አካሉ እንደሚያስተላልፍ ይነግረናል፡፡ የዓለም ሕዝብ የሚተባበርበት ምክንያት የጸረ ክርስቶስን ምልክት በመቀበልና እግዚአብሄርንና ቅዱሳንን በመቃወም ጸረ ክርስቶስ ባወጣው ሕጎች ሐይል ላይ እምነታቸውን በመጣል በሰይጣን አገዛዝ ሥር ለመሆን ነው፡፡
 
ቁጥር 10፡- ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፡፡ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱም አለ፤ የቀረውም ገና አልመጣም፡፡ ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል፡፡
ይህ ቁጥር እግዚአብሄርን የሚቃወሙት ነገሥታቶች ከዚህ ቀደም እንደተነሱት ነገሥታቶች ከዚህ ዓለም እንደሚወጡ ይነግረናል፡፡ የመጨረሻው የታላቁ መከራ ዘመን ሲመጣ የዚህ ዓለም መሪ ጸረ ክርስቶስ ሆኖ ይነሳና ቅዱሳኖችን ይፈጃል፡፡ ነገር ግን ጸረ ክርስቶስ የሚሆነው የዚህ ዓለም መሪ ስደት የሚቆየው እግዚአብሄር እንደፈቀደለት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 11፡- የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው፡፡ ከሰባቱም አንዱ ነው፡፡ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፡፡
ይህም ወደዚህ ዓለም የሚመጣው ጸረ ክርስቶስ የዓለም ነገሥታቶች የመጨረሻው ሆኖ እንደሚነሳ ይነግረናል፡፡ ጸረ ክርስቶስ ከዓለም ነገሥታቶች ውስጥ ብቅ ሲል የዘንዶውን ሥልጣን ስለተቀበለ፣ እንደ እግዚአብሄር ያለ ሐይልን ስለሚተገብርና ምልክቶችንና ተዓምራቶችን ስለሚያደርግ ብዙ የዓለም ሕዝቦች ይከተሉታል፡፡ የእግዚአብሄር ባሮችና ቅዱሳንም እንደዚሁ በጸረ ክርስቶስ ይገደላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚቆዩት ግን እግዚአብሄር እንደፈቀደው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ ጸረ ክርስቶስ በጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ይሰራል፡፡ ከዚያም ዳግመኛ ከዚያ ተፈትቶ ላይወጣ ወደ ሲዖል እሳት ይጣላል፡፡
 
ቁጥር 12፡- ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ፡፡
ይህ ቁጥር አስሩ መንግስታት መላውን ዓለም ለመግዛት ሥልጣናቸውን እንደሚያስተባብሩ ይነግረናል፡፡ እነዚህ አስር መንግሥታት በዚህ መንገድ ከተባበሩ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ከጸረ ክርስቶስ ጋር በመሆን ሥልጣናቸውን በዓለም ላይ ይተገብራሉ፡፡ ነገር ግን ቁጥሩ እነዚህ የዓለም ነገሥታት ጸረ ክርስቶስ የሚመራውን መንግሥት ገና እንዳልተቀበሉም ይነግረናል፡፡ ሆኖም በጣም በቅርቡ እነዚህ የዓለም ነገሥታቶች ለጥቂት ጊዜ የጨለማው ነገሥታት ሆነው ከአውሬው ጋር ይነግሳሉ፡፡ ነገር ግን ንግሥናቸው የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በጨለማው ግዛት ላይ የሚሰለጥኑት ለዚህ አጭር ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡
 
ቁጥር 13፡- እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፤ ሐይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፡፡
ጊዜው ሲደርስ የዚህ ዓለም ነገሥታቶች ሐይላቸውንና ሥልጣናቸውን ሁሉ ወደ ጸረ ክርስቶስ ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን፣ ቅዱሳኖችዋና የእርሱ አገልጋዮች በጸረ ክርስቶስ ክፉኛ ይሳደዳሉ፡፡ ሰማዕትም ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ጸረ ክርስቶስ ራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ሐይልና ሥልጣን ከአፉም በሚወጣው ሰይፍ ይጠፋል፡፡
 
ቁጥር 14፡- እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፤ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ፡፡
ሰይጣን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመዋጋት ቢሻም እርሱን አይችለውም፡፡ ቅዱሳኖችም እንደዚሁ ከእርሱ ጋር ታግለው ያሸንፉታል፡፡ እግዚአብሄር ለቅዱሳን በእምነታቸው ጸረ ክርስቶስን ተዋግተው የሚያሸንፉበትን ጉልበት ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ከጸረ ክርስቶስ ጋር በሚያደርጉት ትግል አይፈሩም፡፡ ነገር ግን በዘመን መጨረሻ በጌታ አምላካቸው በማመን በሰላምና በጸጥታ ይኖራሉ፡፡
ይህ የቅዱሳን ድል እምነታቸውን በመጠበቅና ሰማዕት በመሆን የሚያገኙት ነው፡፡ ይህ ጊዜ ሲመጣ ቅዱሳን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው እምነትና መንግሥተ ሰማይን ተስፋ በማድረግ በሚቀበሉት ሰማዕትነት ሰይጣንንና ጸረ ክርስቶስን አሸንፈው ትንሳኤያቸውንና ንጥቀታቸውን ያገኙና አዲሱን የክርስቶስን መንግሥት ተቀብለው ከዚያ በኋላ ለዘላለም በክብር ይኖራሉ፡፡
 
ቁጥር 15፡- አለኝም፡- ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች ወገኖችና ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብም፣ ቋንቋዎችም ናቸው፡፡
ዓለማዊ ሐይማኖቶች በሰይጣን ትምህርቶቻቸው ሕዝቡን ሁሉ አስተው ሰልጥነውበታል፡፡ ይህ ቁጥር በዓለማዊ ሐይማኖቶች ውስጥ የሚሰሩት የሰይጣን ትምህርቶች የዓለምን ሕዝቦችና ቋንቋዎች ሁሉ ሰርስረው እንደገቡና ተጽዕኖዋቸውም ሰዎችን እስከ ማጥፋት ሊደርስ የሚችል ከፍታ ላይ እንደደረሰ ይነግረናል፡፡
 
ቁጥር 16፡- ያየሃቸው አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፡፡ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፡፡ በእሳትም ያቃጥሉአታል፡፡
ይህ ቁጥር የዚህ ዓለም መንግሥታቶች የሐይማኖት ሰዎችን ለመግደልና ለማጥፋት ከጸረ ክርስቶስ ጋር እንደሚያበሩ ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር የዚህ ዓለም ሕዝብና ጸረ ክርስቶስ የሐይማኖት ሰዎችን እንደሚጠሉና እንደሚያንገላቱ፣ የዓለምን ሐይማኖቶችንም በሙሉ ከፊታቸው እንደሚያጠፉ ይነግረናል፡፡ የዓለም የሐይማኖት ሰዎች ቀደም ብለው በጸረ ክርስቶስ ድጋፍ ቅዱሳኖችን ቢገድሉም አሁን ደግሞ እነርሱ ራሳቸው በሰይጣንና በዓለማዊ ሰዎች ሊጠፉ ነው፡፡ በመጨረሻ ሰይጣን የዓለምን ሐይማኖቶች የተጠቀመው ራሱን አምላክ አድርጎ ለማኮፈስ ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 17፡- እግዚአብሄር አሳቡን እንዲያደርጉ፣ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ፣ የእግዚአብሄርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና፡፡
ይህም የዓለም ሕዝብ መንግስታቸውንና ሥልጣናቸውን ለሰይጣን እንደሚሰጡ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ በፈቃዳቸው ምልክቱን ስለሚቀበሉና የእርሱ ባሮች በመሆናቸው ስለሚኮሩ የጸረ ክርስቶስ ሕዝብ ይሆናሉ፡፡ የእርሱን ቅዱሳኖች እንዲያሳድዱ የሚፈቀድላቸው የእግዚአብሄር ቃል እስከፈቀደላቸው ጊዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡ በዚህ በተፈቀደው ጊዜ ወቅት ጸረ ክርስቶስ በልቡ ውስጥ ያለውን ክፋት ሁሉ በማፍሰስ እግዚአብሄርንና የእርሱን ቅዱሳን በነጻነት ይቃወማል፡፡
 
ቁጥር 18፡- ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት፡፡››
እግዚአብሄር እዚህ ላይ ይህ ዓለም ነገሥታቶችን ለመግዛትና ለመቆጣጠር አዳዲስ ሕጎችን እንደሚደነግግና የዓለም ነገሥታቶችም በእነዚህ አዳዲስ ሕጎች ገደብ ውስጥ ሆነው እንደሚተዳደሩ ይነግረናል፡፡ የዚህ ዓለም የበላይ ሥልጣን ራሱ ግለሰብ ይመስል በዓለም ነገሥታቶች ሁሉ ላይ ይሰለጥናል፡፡ በሌላ አነጋገር ዓለም ነገሥታቶችን በሙሉ አስሮ የማያፈናፍን ሕጎችን ያወጣል፡፡ በእነርሱ ላይ በመሰልጠንም ልክ እንደ አምላክ ይሆናል፡፡
‹‹ታላቂቱ ከተማ›› የምታመላክተው ጸረ ክርስቶስ የሚገዛበትን የፖለቲካ ተቋም ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው መጨረሻው ራሱ አምላክ ይመስል እግዚአብሄር የሰጠውን የዓለም ገዥ ሐይል ማገልገልና በእርሱ መገዛት ይሆናል፡፡ ሰዎች የሰይጣን ባርያዎች ስለሆኑ ይጠፋሉ፡፡
መዝሙረ ዳዊት 49፡20 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡›› ስለዚህ የዚህ ዓለም ሕዝብ አስቀድመው የሰይጣን ዕቅድ ምን እንደሆነ ማወቅ፣ በዚህ ዘመን ያሉ ቅዱሳን የሚሰብኩትን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አሁኑኑ ማመንና የሰይጣን ባሮች ከመሆን እርግማን አምልጠው የእርሱ ሕዝቦች በመሆን የእግዚአብሄርን ዘላለማዊ መንግሥት በረከት ለብሰው መኖር ይገባቸዋል፡፡