Search

Mahubiri

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 8-4] ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው፡፡ ‹‹ሮሜ 8፡4-11›› 

‹‹ሮሜ 8፡4-11›› 
‹‹እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትዕዛዝ ይፈጸም ዘንድ ሐጢአትን በሥጋ ኮነነ፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፡፡ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሄር ዘንድ ጥል ነውና፡፡ ለእግዚአብሄር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም ተስኖታልና፡፡ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሄርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም፡፡ እናንተ ግን የእግዚአብሄር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም፡፡ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም፡፡ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በሐጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል፡፡ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን፤ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ፡፡ በእግዚአብሄር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሄር ልጆች ናቸውና፡፡››
       
 
ከአገር ውጪ የሚከናወን ሚሽን በጽሁፍ አማካይነት ሲከወን ውጤታማ ነው፡፡ አሁን እያደረግን ያለነው ይህንን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስናነብ እንባረካለን፡፡ በቃሉ ስለምናምንም እምነታችን ያድጋል፡፡
  
ሰዎች ላለፉት አምስት መቶ ዓመታት በሒደት በመቀደስ ትምህርት፣ በመንጻት ትምህርትና በንስሐ ጸሎት መዳን ይቻላል በሚሉ ሌሎች የሐሰት ትምህርቶች በመታለል ሲሰቃዩ ነበር፡፡
 
ሮሜ 8፡3 እግዚአብሄር ሥጋ ስለደከመ ሕጉ ማድረግ ያልቻለውን ነገር እንዳደረገ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ልጁን በሐጢያተኛ ሥጋ ምሳሌ በመላክ ሐጢያትን በሥጋው ኮነነ፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያድነን ዘንድም በእርሱ ላይ ፈረደበት፡፡
ዛሬ የእግዚአብሄርን እውነት ለማግኘት ወደ ሮሜ 8፡4-11 እንሄዳለን፡፡ ሮሜ 8፡3-4 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከሥጋ የተነሳ ስለደከመ ለሕግ ያልተቻለውን እግዚአብሄር የገዛ ልጁን በሐጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በሐጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትዕዛዝ ይፈጸም ዘንድ ሐጢአትን በሥጋ ኮነነ፡፡›› በእርግጥ ጥያቄው ይህ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?
 
 

በመጀመሪያ እንደ ሥጋ ፈቃድ አለመመላለስ ምን ማለት ነው? 

 
ይህ ማለት የሥጋን ትርፎች አለመሻት ማለት ነው፡፡ በመንፈስ ምኞቶችና በሥጋ ፍትወቶች መካከል መለየትና የእግዚአብሄርን ቃል ከማይታዘዙ መራቅ ማለት ነው፡፡ ቁጥር 5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ፡፡›› ‹‹የሥጋ ነገር›› ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ቤተክርስቲያን እየሄዱ እንኳን የራሳቸውን ፍላጎቶች የሚከተሉ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡
 
በአጭሩ ለማስቀመጥ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ የሚካሄደውን ትርፍ የማጋበስ ንግድ ለማከናወን ሲሉ ቤተክርስቲያን መሄድ የለባቸውም ማለት ነው፡፡ ይህ እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መደበኛና ታማኝ ደንበኞችን ለማግኘት ተስፋ በማድረግ የንግድ ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ብዙ ሕዝብ ወደሚገኙባቸው ቤተክርስቲያኖች ይሄዳሉ፡፡ እነርሱ ቤተክርስቲያን የሚሄዱትና በኢየሱስ የሚያምኑት ለሥጋቸው ጥቅም ነው፡፡
 
ሌሎችም አሉ፡፡ በክርስትናው ማህበረሰብ ውስጥ ወገንተኝነትን የሚያስተምሩና ተከታዮቸቸው ቁሳዊ በረከቶችን ብቻ እንዲከተሉ የሚያስተምሩ ሰዎች እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩና ሐሳባቸውን በሥጋ ነገሮች ላይ የጣሉ ናቸው፡፡
 
በክርስትና ማህበረሰባችን ውስጥ ወገንተኝነትን በቀላሉ ማግኘት እንችላለን፡፡ እነዚህ ወገንተኞች ታዲያ እነማን ናቸው? እነዚህ በሃይማኖት ድርጅታቸው ታላቅነት ላይ ባላቸው የተዛባ እምነት ራሳቸውን የሚያታልሉ ሰዎች ናቸው፡፡ የእነርሱ አንጃ በእከሌና በእከሌ የተመሰረተ እንደሆነና እከሌና እከሌ የተባሉ የሥነ መለኮት ምሁራን እንዳላቸው፤ ትልቅና በዓለም ደረጃም በሰፊው የታወቁ ጠንካራ ወግና ወ.ዘ.ተ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የእነዚህን ሰዎች ከንቱነት ያዋቀሩትና እምነታቸውን የገነቡላቸው እነዚህ ትምክህቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እንዲህ ያለ እምነት ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡
 
ወገንተኞች በኢየሱስ የሚያምኑት ለሥጋቸው ጥቅም ነው፡፡ በሥጋ የሚኖሩ ሰዎች በቤተክርስቲያኖቻቸውና ትልልቅ ወደሆኑ ቤተክርስቲያኖቻቸው በመሄዳቸውም በቁሳዊ በረከት በመባረካቸው ይኮራሉ፡፡ አንዳንድ ቤተክርስቲያኖች ‹‹ሚስትህን ውደድ›› የሚሉ የጋራ የሆኑ ግቦች አሉዋቸው፡፡ ‹‹እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ›› ማለት እንግዲህ ይህ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኖች ግባቸው ሚስቶቻቸውን በመውደድ ላይ ሊሆን ይገባልን? አይገባም፡፡ ሚስቶቻችንን መውደድ የለብንም እያልሁ ነውን? አይደለም! ነገር ግን እነዚህ ግቦች ግሩምና የሚማርኩ ቢሆኑም የቤተክርስቲያናችን መሰረታዊ ዓላማ መሆን የለባቸውም፡፡
 
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሐሳባቸውን በሥጋ ነገሮች ላይ ያደርጋሉ፡፡ ዛሬ በጣም ብዙ አገልጋዮች የቤተክርስቲያን አባሎቻቸውን፣ ስጦታዎቻቸውንና ሕንጻዎቻቸውን መጠን በማሳደግ ላይ ብቻ የሚተጉ ሰዎች ሆነዋል፡፡ አሁን የእምነታቸው ዋና ዓላማ እነዚህ ሆነዋል፡፡ እጅግ ትልቁ ግባቸው ትልቅ፣ ሰፊና ቁመተ ረጅም ቤተክርስቲያን መገንባት ሆንዋል፡፡ ብዙ ተከታዮችን የሚስቡበት እነርሱን ወደ ሰማይ ለማድረስ እንደሆነና ሌሎች ምክንያቶችን ለይምሰል ቢናገሩም ዋናው ዓላማቸው ትልልቅ የቤተክርስቲያን ሕንጻዎችን ለመገንባት ገንዘብ መሰብሰብ ነው፡፡
 
ቤተክርስቲያኖቻቸው የሥጋን ነገር እንዲከተሉ ለማድረግ ተከታዮቻቸው የሃይማኖት አክራሪዎች እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው፡፡ አንዳንድ መጋቢዎች ጉባኤያቸውን አክራሪዎች፣ ወፈፌዎች፣ ስሁቶች በማድረግና ፈጽመው በተሳሳቱ ሰዎች በመሙላት ችሎታቸው ተሳክቶላቸዋል፡፡
 
 

እንደ እግዚአብሄር መንፈስ የሚኖሩ ሰዎች፡፡ 

 
ሆኖም በክርስቲያኖች መካከል እንደ እግዚአብሄር መንፈስ የሚመላለሱ ሰዎች መኖራቸው እርግጥ ነው፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች እንደ እግዚአብሄር ቃል ይኖራሉ፡፡ የራሳቸውን አስተሳሰቦች በመካድም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው መሰረት ይኖራሉ፡፡ እግዚአብሄር የሚደሰትበትን ያደርጋሉ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱንም ወንጌል ይሰብካሉ፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ የመንፈስን ነገርን እንደሚያስቡ ይናገራል፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ለሐጢያቶቻችን ሁሉ ይቅርታን ካገኘን ግድየለሽ ሆነን መኖር አይገባንም፡፡ ነገር ግን የመንፈስን ሥራ በማሰብ ልንኖር ይገባናል፡፡ በመንፈስ የሚኖሩ ሰዎች መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ፡፡ በእምነትም የመንፈስን ነገር ለማድረግ ይወጣሉ፡፡ የመንፈስን ነገር የሚከተሉ ሰዎች ብጹዓን ናቸው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስደስቱ ሌሎችን ከዓለም ሐጢያቶች የሚያድኑና በእምነት የሚኖሩ ሰዎች እነዚህ ናቸው፡፡ እኛ የሐጢያቶቻችንን ይቅርታ አግኝተናል፡፡ ስለዚህ የመንፈስን ነገር ማሰብና እንደ እርሱ ፈቃድ መኖር አለብን፡፡
 
የሕይወት ግባችን የመንፈስን ሥራ መፈጸም ነው፡፡ እርሱም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ ነው፡፡ የመንፈስን ነገር ማሰብ አለብን፡፡ የመንፈስን ነገር ምን ያህል ታስባላችሁ? እኛ መንፈሳዊውን ጦርነት እየተዋጋን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመንና እርሱንም በመስበክ የመንፈስን ነገር መለማመድ አለብን፡፡ ደካሞችና በጉድለቶች የተሞላን ብንሆንም ሁልጊዜም ጌታን የሚያስደስተውን ነገር ማሰብና አእምሮዋችንን በእግዚአብሄር ሥራ ላይ በማኖር የመንፈስን ሥራ ማከናወን አለብን፡፡ አንድ ሥራ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ጌታን የሚያስደስተውን ተጨማሪ ሥራ ደግመን ለመስራት መጣር ይገባናል፡፡
 
አሁን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሥነ ጽሁፍ ሥራ አማካይነት በመላው ዓለም ላይ እየሰበክን ነው፡፡ ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ሰዎች ድረ ገጻችንን በመጎብኘት በየቀኑ በነጻ የሚታደሉ የክርስቲያን መጽሐፎቻችንና የኤሌክትሮኒክስ መጽሐፎችን እየተቀበሉ ነው፡፡ እኛ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በዓለም ላይ በሚገኝ በእያንዳንዱ አገር ለሚኖረው ሰው ሁሉ ለመስበክ በእምነት እየተፍጨረጨርን ከእናንተ ጋር በእርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ወንጌልን በማገልገል ላይ ነን፡፡ የመንፈስን ነገሮች ባናስብ ኖሮ እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች ባልተሰጡን ነበር፡፡ የመንፈስን ነገር በማሰብ የእርሱን ሥራ አንድ በአንድ ማከናወን ይገባናል፡፡ ያን ጊዜ በምሳሌ ምዕራፍ 31 ላይ እንደምትገኘው መልካም ሴት መንፈሳዊውን ሙሽራችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እናስደስተዋለን፡፡
 
ቁጥር 8 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በሥጋ ያሉትም እግዚአብሄርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም፡፡›› ይህ የሚጠቁመው የሐጢያቶችን ይቅርታ ያልተቀበሉትን ሰዎች ነው፡፡ ‹‹ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሄር ዘንድ ጥል ነውና፡፡ ለእግዚአብሄር ሕግ አይገዛምና መገዛትም ተስኖታል፡፡ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሄርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም፡፡›› (ሮሜ 8፡7-8) ስለዚህ በውስጣቸው መንፈስ የሌላቸው ሐጢያተኞች የእግዚአብሄርን ሥራ መስራትም ሆነ እርሱን ማስደሰት አይችሉም፡፡
 
ሐጢያተኞች ለእግዚአብሄር ሕግ አይገዙም፡፡ ለእግዚአብሄርም ጽድቅ አይገዙም፡፡ እርሱንም ማስደሰት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስለማይኖር የእግዚአብሄርን ፈቃድ መረዳት አይችሉም፡፡ ጌታን የሚያስደስተው የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ይቅር ማለት ነው፡፡ እርሱ በሐጢያቶች ምስጋናና አምልኮ አይደሰትም፡፡
           
እግዚአብሄር ሐጢያተኞች ሲያመሰግኑት አይደሰትም፡፡ ሐጢያተኞች ምንም ያህል እጆቻቸውን አንስተው ቢያመሰግኑትና በአምልኮ ላይም እንባዎቻቸውን ቢያፈሱ እርሱን ሊያስደስቱት አይችሉም፡፡ ሐጢያተኛ ክርስቲያኖች በስሜቶች ሰክረው እግዚአብሄርን ሊያስደስቱት ይሞክራሉ፡፡ ሐጢያት ያለባቸው ሰዎች እግዚአብሄርን ማስደሰት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ሐጢያተኞች ናቸውና፡፡ ምንም ያህል ቢፍጨረጨሩ ሐጢያተኞች ጌታን በጭራሽ ማስደሰት አይችሉም፡፡ ጉዳዩ ጌታን ለማስደሰት ምን ያህል ፈቃደኞች ናቸው የማለት ነገር አይደለም፡፡ ጉዳዩ እነርሱ ጌታን ለማስደሰት የአለመቻላቸው ነገር ነው፡፡
 
ሰዎች ትላልቅ ቤተክርስቲያኖችን ቢገነቡ እግዚአብሄር ይደሰታልን? አይደሰትም፡፡ ወደ አንድ ትልቅ የቤተክርስቲያን ሕንጻ መዛወር የሚያስፈልግ ከሆነ ትልቅ ቤተክርስቲያን መገንባት ይኖርበታል፡፡ ለመገንባት ሲባል ብቻ ትልቅ ቤተክርስቲያን መገንባት ግን እግዚአብሄርን ፈጽሞ አያስደስተውም፡፡ 
 
ለምሳሌ በእኔ ከተማ ያለች ቤተክርስቲያን አዲስ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ለመገንባት በቅርቡ 3 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች፡፡ የቀደመው ሕንጻ ከእርሱ አጠገብ ቆሞዋል፡፡ አሁንም ድረስ ማራኪ ቅርጹንና ይዘቶቹን እንደያዘ ነው፡፡ የጉባኤው መጠን በአብዛኛው ከ200-300 ብቻ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያለ ቤተክርስቲያን መገንባቱ በእርግጥ አስፈላጊ ነበርን? የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በጡቦች አትገነባም፡፡ እግዚአብሄር እኛ የአምላክ ቤተመቅደስ እንደሆንንና የእግዚአብሄርም መንፈስ በጻድቃን ልብ ውስጥ እንደሚኖር ነግሮናል፡፡
 
አስፈላጊ ከሆነ ትልቅ ቤተክርስቲያን መገንባት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በራሱ ትልልቅ ቤተክርስቲያኖችን መገንባት ለእግዚአብሄር ክብርን ያመጣልን? አያመጣም፡፡ ብዙ ሰዎችን ቤተክርስቲያን ውስጥ መሰብሰብ ለእግዚአብሄር ክብርን ያመጣልን? አያመጣም፡፡ ያንን በማድረግ እግዚአብሄርን ማስደሰት አትችሉም፡፡ በሥጋ ያሉት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይችሉም፡፡
 
አንዳንድ ጊዜ የሥጋን ጥቅሞች ብቻ የሚያሳድዱ ጻድቃኖችም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ጌታን ማስደሰት አይችሉም፡፡ በጻድቃን መካከልም ልክ እንደ ሐጢያተኞች አሁንም ድረስ በሥጋ አስተሳሰቦቻቸው የታሰሩ አንዳንዶች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሄርን ማስደሰት አይችሉም፡፡ እነርሱ በተጨባጭ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጤናማ የሆነ የእምነት ሕይወትን አይኖሩም፡፡ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ያጉረመርማሉ፤ ይበሳጫሉ፡፡ ውለው አድረውም ከቤተክርስቲያን ይቀራሉ፡፡
ስለዚህ እኛ ጻድቃን የሆንን ሰዎች የሥጋን ትርፎች ብቻ የሚሻ ሕይወትን ሳይሆን ጻድቅ የሆነና እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወትን መኖር አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ሥራዎችና ጽድቁን ማሰብ፣ የጽድቁን ሥራዎች ማገልገልና ሰውነታችንን፣ እምሮዋችንንና ንብረቶቻችንን ሁሉ የእግዚአብሄር ጽድቅ ዕቃ ጦር አድርገን መጠቀም ይገባናል፡፤
     
 

በክርስቶስ መንፈስ ያሉ ሰዎች፡፡ 

 
ቁጥር 9ን በአንድ ላይ እናንብብ፡- ‹‹እናንተ ግን የእግዚአብሄር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም፡፡ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም፡፡››
 
በጳውሎስ መሰረት ይህ ምንባብ የሚለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ብናምን በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄር ጽድቅ ብናምንና ከሐጢያቶቻችን ብንድን በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ነን ነው፡፡ በልቡ ውስጥ መንፈስ ያለው ማንኛውም ሰው በክርስቶስ ነው፡፡ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ማንኛውም ሰው የእርሱ አይደለም፡፡
 
ስለዚህ እኛ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደለንም፡፡ እኛ በመንፈስ ያለንና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያት የዳንን ሰዎች በክርስቶስ ጻድቃን ሆነን እግዚአብሄርን የማስደሰት ችሎታ ያለን የጽድቅ ወታደሮች መሆናችንን መርሳት አይገባንም፡፡ በሥጋችን ድካም ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡ ደካሞች ብንሆንም የእርሱ በመሆናችንና በእርሱ ውስጥ በመኖራችን እምነት የእርሱ ሰራተኞች ሆነን እግዚአብሄርን ማስደሰት አለብን፡፡
   
ዳግም ከተወለድን በኋላ የሥጋችንን ትርፎች ብቻ መከተል እንዳልተፈቀደልን ማወቅ አለብን፡፡ ጻድቃን ለእግዚአብሄር ጽድቅ ብቻ ለመኖር የታጩ መሆናቸውን አውቀን መኖር ይገባናል፡፡ ቁጥር 10 ክርስቲያኖች እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባቸው ያሳየናል፡፡ ‹‹ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በሐጢአት ምክንያት የሞተ ነው፡፡ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው፡፡››
 
እኛና ሰውነታችን በሐጢያቶቻችን ምክንያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሰቀሉና መሞቱ እውነት ነው፡፡ በእግዚአብሄር የጽድቅ ሥራ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነናል፡፡ በዚህ ጽድቅ ምክንያት የጻድቃን መንፈስ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ የዘላለም ሕይወት!  የጸደቁ ሰዎች ከእንግዲህ ወዲያ ለሥጋቸው ብቻ እንዲኖሩ እንዳልተፈቀደላቸው ማወቅ ይገባናል፡፡ ዳግም ከተወለዱ በኋላ ለእግዚአብሄር ጽደቅ የማይኖሩ ሰዎች ከእግዚአብሄር በረከቶች በጣም የራቁ ናቸው፡፡
 
እኛ ለእግዚአብሄር ጽደቅ እንድንኖር ታጭተናል፡፡ ምናልባት አንዳንዶቻችሁ ዳግም ከተወለዳችሁ በኋላ ተስፋ በመቁረጥ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ በሥጋ ያሉት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይችሉም ይላል፡፡ እኔም ከእነርሱ አንዱ መሆን አለብኝ›› ብላችሁ አስባችሁ ይሆናል፡፡ ይህ ግን እውነት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የጽድቁ ወታደሮች እንሆን ዘንድ አድሶናል፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ የሚያስቡት ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ ሰለተረዱት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጻድቃኖችም ሰውነታቸው እንደ ሥጋ ፈቃድ ስለሚኖርና ደካሞች ስለሆኑ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መኖር ባይችሉም እውነቱ ግን መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ያለባቸው ሰዎች የእግዚአብሄርን ሥራዎች በመስራት የሚደሰቱ መሆናቸው ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ሥራዎች መስራት ደስተኞች፣ በሐሴት የተሞሉና የተደላደሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የእግዚአብሄርን ሥራ የማይሰራ ሕይወት እንቅስቃሴና ዓላማ የሌለው ርጉም ሕይወት ነው፡፡
 
የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ተቀብለን በእግዚአብሄር ጽድቅ ውስጥ መኖር ከጀመርን በኋላ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይኖራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደህንነትን በተቀበለ በማንኛውም ሰው ላይ ይመጣል፤ ይኖራልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚኖርባቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ? የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማገልገልና የጽድቅ ሥራውን ለመሥራት ይታጫሉ፡፡
 
በአጭሩ የሐጢያቶችን ይቅርታ አግኝተው የጸደቁ ሰዎች መኖር ያለባቸው በእምነት ብቻ ነው፡፡ ጻድቃን እምነታቸውን መጠበቅ የሚችሉት በእምነት ሲኖሩና የእግዚአብሄርን ሥራዎች ሲሰሩ ብቻ ነው፡፡ ከጸደቃችሁ በኋላ በዚህ ዓለም ላይ በሥጋችሁ እንደምትኖሩ የምታስቡ ከሆነ ለዚህ ምክንያቱ የሐጢያቶቻችሁን ይቅርታ መቀበላችሁንና ዕጣ ፈንታችሁም መለወጡን አለመረዳታችሁ ነው፡፡
 
የጻድቃን ዕጣ ፈንታ ተለውጦዋል፡፡ ዳግም ከመወለዳቸው በፊት ለዓለምና ለራሳቸው ኖረዋል፡፡ በሥጋ ፍላጎታቸው ሲኖሩ በነበረ ጊዜም ደስተኞች ነበሩ፡፡ ዳግም ከተወለዱ በኋላ ግን ዳግመኛ እንደዚያ መኖር አይቻልም፡፡ እኛ የሐጢያቶችን ይቅርታ ተቀብለናል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ብናገኝ ደስተኞች ነን? ሌሎች ነፍሳቶችን ከዚህ ዓለም ለማዳን ራሳችንን ቀድሰን ሰጥተን ሳለን በቁሳዊ ነገሮች ብቻ እንዴት ልንረካ እንችላለን?
 
በሌላ አነጋገር ስለ ሥጋ ነገሮችና ስለ መንፈስ ነገሮች አጥብቃችሁ እንድታስቡ እየጠቅኋችሁ ነው፡፡ እነዚያን ነገሮች ለማወቅ ስትሉ ልታደርጉዋቸው አያስፈልጋችሁም፡፡ እናንተ ማድረግ የሚኖርባችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ በጥብቅ ማሰብ ነው፡፡
 
እስከ አሁን ድረስ ቀደም ባለው የሮሜ የስብከት መጽሐፌ ከሮሜ ምዕራፍ 1 እስከ 6 ድረስ ሰብኬያለሁ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ከምዕራፍ 7 እስከ 16 ድረስ እሰብካለሁ፡፡ ተከታታይ በሆነው የክርስቲያን መጽሐፌ 5ኛና 6ኛ ቅጾች የሆኑት እነዚህ ሁለት የስብከት መጽሐፎቼ በመላው ዓለም ለሚገኙ ክርስቲያኖች ይሰራጫሉ፡፡ ተከታታይ በሆነው የክርስቲያን መጽሐፌ አማካይነት ብዙ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ ወደ ማወቅ እንደሚደርሱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቀደም ባሉት ሦስት የስብከት መጽሐፎቼ አማካይነት በእግዚአብሄር ደህንነት ላይ መሰረታዊ ስለሆኑት አስተምህሮቶች ተናግሬያለሁ፡፡ የመጀመሪያው ቅጽ ስለ ወንጌል ይናገራል፡፡ ሁለተኛው ቅጽ ስለ ሥነ መለኮት አስተምህሮቶች ጉዳይ ያወራል፡፡ ሦስተኛው ቅጽ ስለ መንፈስ ቅዱስና መንፈስን ለመቀበል ትክክለኛው መንገድ ምን ስለመሆኑ ያወራል፡፡ በሮሜ ላይ የተጻፉት እነዚህ አምስተኛና ስድስተኛ ቅጾችም ብዙዎቹ የሥነ መለኮት አስተምህሮቶች ምን ያህል የተሳሳቱ እንደሆኑ፣ ክርስቲያኖች በኢየሱስ እያመኑም ሐጢያቶች ለምን እንዳልተወገዱና የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የእግዚአብሄር ጽድቅ ሆኖ እንዴት እንደተገለጠ በስፋት ይናገራሉ፡፡
 
ወንጌል በዚህ መጽሐፍ አማካይነት በዓለም ላይ ይበልጥ በስፋት እንደሚሰራጭ አምናለሁ፡፡ የሦስተኛውን ቅጽ ሕትመት የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቅጾች ካተምንበት ጊዜ ጋር ስናነጻጽረው በወንጌል ስብከት ላይ የማይናቅ እመርታ ተከናውኖዋል፡፡ አሁን ከሦስተኛው ቅጽ በኋላ ብዙ ሰዎች ተከታታይ ከሆኑት የክርስቲያን መጽሐፎቼ የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ቅጾቼን እየጠየቁ ነው፡፡
 
እነዚህ ሁለቱ መጽሐፎች ከታተሙ በኋላ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ሐይል ምንኛ ታላቅ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄር የእርሱን ጽድቅ ወደ ማወቅ በመጡት ላይ ብዙ በረከቶችን አትረፍርፎ እንዲለግሳቸው እጸልያለሁ፡፡ እነርሱ የሮሜን መጽሐፍ እንዴት እንደሚረዱ ያውቃሉ፡፡ ይህ መጽሐፍ የሚስተዋለው የእግዚአብሄርን ጽድቅ የያዘውን ወንጌል በማመን ነው፡፡
 
ሁላችንም ተባብረን ለወንጌል እየሰራን ነው፡፡ እናንተም ደግሞ የእግዚአብሄርን ሥራ እየሰራችሁ አይደለምን? ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ወንጌልን የመስበኩን አገልግሎት እየደገፋችሁ ነው፡፡ እኛ በድርሻችን ታማኞች ስንሆንና ወንጌልን ስንሰብክ በመላው ዓለም የሚገኙ ብዙ ነፍሳቶች ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይድናሉ፡፡ ታዲያ ይህንን ክቡር ሥራ በዓለማዊ ሥራ ልንለውጠው እንችላለን?        
 
እኛ ጻድቃኖች ከእንግዲህ ወዲህ ለገዛ ሥጋችን ብቻ ለመኖር እንዳልታጨን ግልጽ ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ዕጣ ፈንታችን የእግዚአብሄርን ጽድቅ በመፈጸም፣ ነፍሳቶችን በማዳንና ለዚህ ጽድቅ በመኖር ተቃኝቷል፡፡ ይህንን አውቃችሁ ቀሪ ሕይወታችሁን ለእግዚአብሄር፣ ለእውነተኛው ወንጌልና በሐጢያት ለጠፉ ነፍሳቶች መኖር አለብን፡፡
 
በዚህ ክፍል ላይ የሮሜ መጽሐፍ እየተናገረ ያለው ይህንን ነው፡፡ ቁጥር 10 እና 11 እንመልከት፡- ‹‹ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በሐጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል፡፡››
 
ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ እኛ ማለትም ሰውነታችን ከረጅም ጊዜ በፊት በሐጢያቶቻችን ምክንያት መሞታችንን የሚናገር ነው፡፡ ነገር ግን መንፈሳችን ከእግዚአብሄር ጽድቅና ከእምነት የተነሳ ሕያው ሆንዋል፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምን ማንኛውም ሰው አዲስ ሕይወትን ያገኛል፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን አዲስ ሕይወትን አግኝተናል፡፡
 
ቁጥር 11 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል፡፡›› ይህ ማለት እርሱ በዓለም ፍጻሜ ትንሳኤን ይሰጠናል ማለት ነው፡፡ ከረጅም ጊዜ በፊት ለሥጋችንና ለሐጢያት ብቻ የኖርነው ሕይወት አሁን አልፎዋል፡፡ ዕጣ ፈንታችንም በቀሪው ዘመናችን ለእግዚአብሄርና ለጽድቁ ወደ መኖር ተቀይሮዋል፡፡
 
‹‹ጻድቃን ብዙውን ጊዜ የሚሉትን ለማለት እንደሚሰባሰቡ አያጠራጥርም›› ብላችሁ በማሰብ በጻድቃን ሕይወት ተሰላችታሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ ብትቆዩ አጠገባችሁ የተቀመጠው ዳግም የተወለደ ምዕመን ሲያዛጋ መስማት ወይም ምስጋናውንና ድምጹን ማድመጥም ቢሆን አእምሮዋችሁን ያድሰዋል፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያንና በምዕመናን ልብ ውስጥ ይሰራልና፡፡ አእምሮዋችሁ ይታደሳል፤ በልባችሁም አዲስ ብርታት ታገኛላችሁ፡፡ መንፈሳዊውን የሕይወት እንጀራም ትመገባላችሁ፡፡ ወጥታችሁ መንፈሳዊ ሥራዎችን ለመስራትም መንፈሳዊ ሐላፊነቶችን ትረከባላችሁ፡፤
 
በምዕመናን ስብሰባ ላይ ልትታደሱ ትችላላችሁ፡፡ ከዓለም የመለየታችሁ እውነታ ዕጣ ፈንታችሁ እንደተቀየረ ያሳያል፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር የሚያስቡት እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚመላለሱ የመንፈስን ነገር የሚያስቡት ለዚህ ነው፡፡ አሁን ጽድቅን ያገኘነው እኛ ዳግመኛ እንደ ሥጋ ፈቃድ አንኖርም፡፡ ጻድቃን ዳግመኛ የሐጢያት ባርያ መሆን አይፈልጉም፡፡ ቢያንስ እንደ መንፈስ ፈቃድ ለመመላለስ እንሻለን፡፡ የመንፈስንም ነገር እናስባለን፡፡ ጻድቃን የመንፈስን ነገር፣ ነፍሳቶችን  ለክርስቶስ የመመለስን ሥራ ይሰራሉ፡፡
 
የእግዚአብሄርን ሥራ ጠንክረን መስራት፣ የራሳችንን አስተሳሰቦች መካድና አእምሮዋችንን በዚህ ላይ ማድረግ አለብን፡፡ ቀሪውን ሕይወታችንን በዚህ መንገድ መኖር አለብን፡፡ ዕጣ ፈንታችሁ ለእግዚአብሄር ብቻ ትኖሩ ዘንድ ተቀይሮዋል፡፡ ምክንያቱም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ደህንነትን ተቀብላችኋልና፡፡ ይህንን እውነት እንደምታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
 
አዝናለሁ፤ ነገር ግን ዳግመኛ ወደ ዓለም ተመልሳችሁ የሐጢያት ባርያ መሆን አትችሉም፡፡ አሁን ወደ ዓለም የምትመለሱ ከሆናችሁ መጨረሻችሁ ሞት ይሆናል፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው፡፡ ሥጋዊ ፍላጎቶቻችሁን በመከተል የምትቀጥሉ ከሆናችሁ መንፈሳችሁ ይሞታል፡፡ አእምሮዋችሁ ይሞታል፡፡ አካላችሁም ይሞታል፡፡ እስራኤሎች ከወጡ በኋላ ወደ ግብጽ አልተመለሱም፡፡ ቀይ ባህርን ከተሻገሩ በኋላም ከግብጻውያን ጋር በመገናኘታቸው አልተደሰቱም፡፡ ልክ እንደዚሁ እኛም የጸደቅን ሰዎች ዳግመኛ ወደ ግብጽ መመለስም ሆነ መንፈሳዊ ከሆነ ግብጻዊ ጋር በመገናኘት ልንደሰት አንችልም፡፡ 
 
ጻድቅና ዳግም የተወለደ ሰው ወደ ዓለም ሄዶ ከሐጢያተኞች ጋር ቢኖር ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በመኮብለሉ ያብዳል፡፡ ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ርቋል፡፡ ስለዚህ የመንፈስን ነገር በማሰብ እንኑር፡፡
             
የእግዚአብሄር መንፈስ ነገሮች ማለት ምን ማለት ነው? የእግዚአብሄር ነገሮች አይደሉምን? የእግዚአብሄርን ወንጌል የማገልገል ነገሮች አይደሉምን? እኛ ግን ደካሞችና እንከን ያለብን ሰዎች አይደለንምን? እናንተ ደካሞች ናችሁ፡፡ እኔም ደካማ ነኝ፡፡ ደካሞችና እንከን ያለባችሁ ሆናችሁ ሳላችሁ የሐጢያቶችን ይቅርታ አልተቀበላችሁምን? በእርግጥ ተቀብላችኋል! መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ውስጥ አይኖርምን ? መልሱ ማያወላውል ይኖራል ነው!
 
ታዲያ እኛ የመንፈስን ነገር ማሰብ እንችላለን ወይስ አንችልም? በእርግጥ እንችላለን፡፡ ሁላችንም የመንፈስን ነገር ማሰብ እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር የመንፈስን ነገሮች ታደርጉ ዘንድ ዕጣ ፈንታችሁን እንደቀየረው ታውቃላችሁን? ይህንንስ ታምናላችሁን?
 
አሁን አእምሮዋችን ተቀይሮዋል፡፡ አእምሮዋችሁ በእርግጥ እንደተቀየረ የማታውቁ ከሆነ ችግር ይሆንባችኋል፡፡ አእምሮዋችሁን በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ አጽንታችሁ ማኖር አለባችሁ፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ቤታችሁ ትሆናለች፡፡ አብረዋችሁ ያሉት ምዕመናንም ወንድሞቻችሁ፣ እህቶቻችሁ፣ ወላጆቻችሁ፣ በመንፈስም ቤተሰቦቻችሁ ይሆናሉ፡፡ በቤተክርስቲያናችሁ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው ቤተሰባችሁ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደዚህ ካላሰባችሁ ይህንን ትምህርት እንደገና ለማጤንና አጥብቃችሁ ለማሰብ ጊዜው አሁ ነው፡፡
 
ቤተሰባችሁ የሥጋና የደም ቤተሰብ ብቻ እንደሆነ አታስቡ፡፡ ይህ የእናንተና የእያንዳንዱ ዳግም የተወለደ ሰው ቤት ነው፡፡ ሁላችሁም የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባል ናችሁ፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ መኖር የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ ስለ መንፈስ ማሰብ ሰላምን ማግኘት ነውና፡፡