Search

Mahubiri

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[11-2] የእስራኤል ሕዝብ መዳን ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 11፡1-19 ››

የእስራኤል ሕዝብ መዳን
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 11፡1-19 ››
 
እግዚአብሄር ሁለቱን ነቢያቶች ለእስራኤል ሕዝብ የሚልከው ለምንደነው? እግዚአብሄር ይህንን የሚያደርገው በተለይ የእስራኤልን ሕዝብ ለማዳን ዋናው ምንባብ እግዚአብሄር ሁለቱ ምስክሮች ለ1,260 ቀናት ትንቢት እንዲናገሩ እንደሚያደርግ ይነግረናል፡፡ ይህም እስራኤሎችን ለመጨረሻ ጊዜ ለማዳን ነው፡፡ እግዚአብሄር የእስራኤልን ሕዝብ በዚህ መንገድ የሚያድን መሆኑ የዓለም መጨረሻ መቃረቡን የሚያሳይ ነው፡፡
 
ቁጥር 2 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው፤ አትለካውም፡፡ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል፡፡›› ይህ ማለት አስከፊዎቹ መቅሰፍቶች በአሕዛቦች ላይ ሲወርዱ፣ የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ ሲጀምርና ቀስ በቀስ ታላቅ ግራ መጋባትንና መቅሰፍቶችን ሲያመጣ ከአሕዛቦች መካከል ወንጌል ሰምተው ያመኑ ሰማዕት ሲሆኑ እግዚአብሄር ሁለቱን ነቢያቶች ለእስራኤል ሕዝብ ያስነሳና ኢየሱስ አምላክና አዳኝ እንደሆነ በመመስከር እስራኤሎችን ያድናል ማለት ነው፡፡ ይህም እነዚህ የእግዚአብሄር ሥራዎች መሆናቸውን ይነግረናል፡፡
 
እኛ የቤተክርስቲያን መሪዎቻቸው የመጨረሻው ዘመን ሁለት ምስክሮች ናቸው ወይም የእነርሱ አንጃ መስራች ለመጨረሻው ዘመን ትንቢት የተነገረለት ኤልያስ ነው በሚል ለሳቱ ሰዎች ይህንን ቃል ማስተማር አለብን፡፡ ዓለማዊ ቤተክርስቲያኖች ስለ ራዕይ በሚናገሩበት ጊዜ ሁሉ ይህንን የሁለቱን የወይራ ዛፎች ምንባብ በአብዛኛው ይጠቀሙበታል፡፡ በእምነት ሕይወት ካገኘኋቸውና በመናፍቃውያን አምልኮተ ሰቦች ከተታለሉት ሰዎች ሁሉ የእርሱ አምልኮተ ሰብ መሪ እዚህ ላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ የወይራ ዛፎች አንዱ የመሆኑን እንግዳ አባባል ከመናገር የተቆጠበ አንድም ሰው የለም፡፡ እኔ የማውቀው እያንዳንዱ መናፍቅ ውሎ አድሮ እንደዚህ ዓይነቱን አባባል ተጠቅሞዋል፡፡
 
ነገር ግን የራዕይ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች እነዚህ መናፍቃን እንደሚሉዋቸው አይደሉም፡፡ እውነቱ እነዚህ ሁለቱ የወይራ ዛፎች በትክክል የሚያመለክቱት እግዚአብሄር እስራኤሎችን ለማዳን ከእነርሱ ውስጥ የሚያስነሳቸውን ሁለቱን ነቢያት ነው፡፡
 
ምዕራፍ 11 እግዚአብሄር የእስራኤልን ሕዝብ እንዴት እንደሚያድን በዝርዝር ይነግረናል፡፡ ልክ እንደ ሮሜ መጽሐፍ የራዕይ መጽሐፍም እያንዳንዱ ምዕራፍ የራሱ የሆነ የተለየ ርዕስ አለው፡፡ ይህ ምዕራፍ ስለምን እንደሚናገር የምንረዳው ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በማወቅ ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሕዛቦች ቅድስቲቱን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር እንደሚረግጡዋት አንብበው ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ሳያውቁ የአሕዛቦች ዘመን ያበቃል፤ በምትኩም እስራኤሎች የሚድኑበት ዘመን ይከፈታል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚድኑት እስራኤሎች ብቻ ይሆናሉ ይላሉ፡፡
 
ይህ ግን ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ምዕራፍ 7 ከአሕዛቦች የሚወጡ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ብዙሃኖች ከመከራው ድነው እንደሚወጡ ይነግረናል፡፡ ይህም ማለት በመከራው ውስጥ የሚድኑት እስራኤሎች ብቻ ሳይሆኑ አሕዛቦችም እስራኤሎችም ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ምዕራፍ 11 የሚነግረን እግዚአብሄር በመጨረሻው ዘመን የእስራኤልን ሕዝብ ለማዳን ሁለቱን ነቢያቶች እንደሚያስነሳ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት አሕዛቦች ከእንግዲህ ወዲህ አይድኑም ማለት አይደለም፡፡
 
አንዳንዶች ‹‹ምዕራፍ 7 በእግዚአብሄር የታተሙት እስራኤሎች ቁጥር ይህ እንደሆነ ስለሚነግረን 144,000 እስራኤሎች አልዳኑምን?›› ብለው ይጠይቁ ይሆናል፡፡ መታተም ማለት መዳን ማለት አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይቀበል የሚድን ማንም ሰው የለም፡፡ ደህንነት የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመምጣት አዳኛችን መሆኑን፣ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመውሰድም መጠመቁን፣ እነዚህን የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በመስቀል ላይ ተሸክሞ መሞቱንና ዳግመኛም ከሙታን መነሳቱን በማመን ብቻ ነው፡፡
 
እኛ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ በሐጢያት የታሰርን መሆናችንን ብናውቅም ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ፈጽሞ በማስወገድ አዳኛችን መሆኑን በማመን ድነናል፡፡ 144,000ዎቹ እሰራኤላውያን ቢታተሙም እግዚአብሄር የራሱን ሁለቱን ነቢያት በማስነሳት ወንጌሉን በእነርሱ በኩል ይሰብክላቸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር ቃሉ የሚለው ሁለቱ ነቢያት ወንጌልን ለእስራኤሎች ይሰብኩላቸውና ከእነርሱም 144,000 ይድናሉ ነው፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ የሚያዳላ ወይም የሚያገልል አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ሳያምን መዳን የሚችል ማንም የለም፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስን ሳታውቅ ‹‹ድነሃል፤ ነገር ግን አልዳንህም›› አይልም፡፡
 
በዋናው ምንባብ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለቱ የወይራ ዛፎች ማለትም ሁለቱ ነቢያት ጎልጎታ በሚባል ስፍራ ይገደላሉ፡፡ በድናቸው ሳይቀበር በአደባባይ ይተኛል፡፡ ኢየሱስን የማያምኑትም ሆነ የማይቀበሉ ሰዎች በእነርሱ ሞት ተደስተው እርስ በርሳቸው ስጦታዎችን ይለዋወጣሉ፡፡ ቁጥር 11 እና 12 ግን እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ከእግዚአብሄር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፡፡ በእግሮቻቸውም ቆሙ፡፡ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው፡፡ በሰማይም፡- ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምጽ ሰሙ፡፡ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ፡፡››
 
ይህም ጊዜው ሲደርስ እኛ ማለትም እናንተና እኔ ሰማዕት እንደምንሆን በቀጥታ ይነግረናል፡፡ ከሰማዕትነታችን በኋላም ወዲያው ትንሳኤያችንና ንጥቀት ይመጣል፡፡ ይህ ርዕሰ ጉዳይ በመላው የራዕይ መጽሐፍ ውስጥ መታየቱን ቀጥሎዋል፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በዚህ ምድር ላይ ሲወርዱ የተነጠቁት ቅዱሳን በአየር ላይ እግዚአብሄርን እንደሚያመሰግኑ የሚነግሩን ምንባቦችም ደግሞ አሉ፡፡
 
ምዕራፍ 14ም እንደዚሁ የደህንነት በኩራቶች ብቻ እንጂ ሌሎች ሊዘምሩት የማይችሉትን መዝሙር በመዘመር ጌታን ስለሚያመሰግኑት የዳኑ 144,000ዎች ይናገራል፡፡ ይህም የእስራኤል ሕዝብ ሲድኑ በየስፍራው ሰማዕት እንደሚሆኑና ከሰማዕትነታቸው በኋላም ወዲያውኑ ትንሳኤያቸውና ንጥቀታቸው እንደሚመጣ ይነግረናል፡፡
 
ይህ አሕዛቦችንም ይመለከታል፡፡ በመጨረሻው ዘመን እናንተና እኔ በሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ብዙ መከራዎች ውስጥ እናልፋለን፡፡ እግዚአብሄር ግን ከእነዚህ መቅሰፍቶች ይጠብቀናል፡፡ የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ ከመጀመሪያው የሦስት ዓመት ተኩል አጋማሽ አልፎ ሄዶ ጫፍ ላይ ሲደርስ የቅዱሳን ስደትም እንደዚሁ ጫፉ ላይ ይደርሳል፡፡ ነገር ግን ይህ የከፋ ስደት የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ቅዱሳንና የእግዚአብሄር ባሮች ወዲያውኑ ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ከሰማዕትነታቸው በኋላም ወዲያውኑ ይነጠቃሉ፡፡
 
ለምን? ራዕይ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በዚህ ምድር ላይ በሚወርዱበት ጊዜ ቅዱሳን አስቀድመው በሰማይ ሆነው እግዚአብሄርን እያመሰገኑ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራልና፡፡ ቃሉ ይህንን ድንቅ ብሎ ይገልጠዋል፡፡
 
ዮሐንስ ራዕ 10፡7 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምጹም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደሰበከላቸው የእግዚአብሄር ምስጢር ይፈጸማል፡፡›› ይህ የሚያመለክተው ሌላ ነገርን ሳይሆን በእግዚአብሄር የተሰወረውን ምስጢር ማለትም ንጥቀትን ነው፡፡ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ጌታ ራሱ በትእዛዝ፣ በመላዕከትም አለቃ ድምጽ፣ በእግዚአብሄርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፡፡››
 
ነገር ግን ጌታ ከሰማይ ይወርዳል ማለት ወዲያውኑ ወደዚህ ምድር ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ ከሰማይ ወደ አየር ይወርዳል፡፡ ያንቀላፉትን የሚያስነሳውና በሕይወት ያሉትን ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎችን የሚለውጠው የመጀመሪያው ትንሳኤ ሲመጣ ቅዱሳን ጌታን በአየር የሚቀበሉበት ንጥቀት ወዲያውኑ ተከትሎ ይመጣል፡፡ የበጉ ሰርግ እራት በአየር ላይ ከተከናወነና ይህ ዓለምም በዚህ ምድር ላይ በሚወርዱት በቀሩት የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች መውደሙ ከተጠናቀቀ በኋላ ጌታ ከእኛ ጋር አብሮ ወደታደሰችው ምድር ይወርድና ገናም በሕይወት ባሉት ፊት ይገለጣል፡፡
 
በራስ አስተያየቶች ላይ ተመስርቶ የራዕይን ቃልና መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም በጥፋት መንገድ ላይ መቆም ነው፡፡ ቃሉን በተገቢው መንገድ ሳይረዱ አንዳንድ የሥነ መለኮት ምሁራን ያቀረቡዋቸውን ተራ መላ ምቶች አምኖ እነዚህን አባባሎች ማቀንቀን ስህተት ነው፡፡
 
ወግ አጥባቂ በሆኑ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ ከፍተኛ ዕውቅናና ዝና ካላቸው የሥነ መለኮት ምሁራን መካከል እንደ ኤል. ቤርኮፍና አብርሃም ካይፐር ያሉት አንዳንድ ሊቃውንቶች ሺህ ዓመት የለም ይላሉ፡፡ ከቅድመ መከራ ንጥቀት፣ ከድህረ መከራ ንጥቅትና ሺህ ዓመት የለም ከሚሉት ጽንሰ አሳቦች ውስጥ በዚህ በመጨረሻው ሺህ ዓመት የለም በሚለው ትምህርት ማመን መጽሐፍ ቅዱስን ራሱን አለማመን ነው፡፡
 
ሰዎች በድህረ መከራ ንጥቀት ማመን ያዘወትሩ የነበረበት ዘመን አሁን አልፎዋል፡፡ በዚህ ዘመን ሁሉም ማለት ይቻላል በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ያምናል፡፡ ይህ ጽንሰ አሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክል አይደለም፡፡ ሆኖም ሰዎች ስለ ቅድመ መከራ ንጥቀት በሚነገራቸው ጊዜ ሁሉ አብዝተው ይወዱታል፡፡ ለምን? ምክንያቱም በዚህ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ መሰረት ክርስቲያኖች ስለ ሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ የሚጨነቁበት አንዳች ነገር አይኖርምና፡፡
 
ስለዚህ ምዕመናኖች ትኩስ ወይም በራድ ያልሆነ የእምነት ሕይወትን መኖራቸው ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ቤተክርስቲያኖችም የሚጨነቁት የጉባኤዎቻቸውን መጠን ለመጨመር ብቻ ነው፡፡ በዚህም የሰዎች እምነት ላልቷል፡፡ በታላቁ መከራ ውስጥ ስለ ማለፍ መጨነቅ እንደማያስፈልጋቸው ስለሚያስቡ እምነታቸው የዘመኑ መጨረሻ እየተቃረበ ሲሄድ ይበልጥ ብርቱ መሆን ሲገባው የታይታና ልል ሆንዋል፡፡ ሰዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ሺህ ዓመት የለም የሚለውን ማመን ያዘወትሩ ነበር፡፡ ከዚያም ለጥቂት ጊዜ በድህረ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ አመኑ፡፡ አሁን ደግሞ በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ያምናሉ፡፡
 
በ1830ዎቹ በሙዲ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቋም ውስጥ ፕሮፌሰር የነበረው ሬቨረንድ ስኮፊልድ የማመሳከሪያ መጽሐፍ ቅዱስን መጻፍ ጀመረ፡፡ ስኮፊልድ በዓለም ታዋቂ በነበረው ዝነኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ በዳርቢ ከፍተኛ ተጽዕኖ አድሮበት ነበር፡፡
 
ቀደም ብሎ የካቶሊክ ካህንና የስኮፊልድ መንፈሳዊ አስተማሪ የነበረው ዳርቢ እጅግ ብሩህ አእምሮ የነበረውና በስፋት የሚታወቅ ሰው ነበር፡፡ ስህተቶችዋን ከተረዳ በኋላ የካቶሊክን ቤተክርስቲያን ትቶ ከአንድ ትንሽ የክርስቲያን ጉባኤ ጋር በመቀላቀል የጉባኤው መሪ ሆነ፡፡ ዳርቢ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ማቋረጥ የሚያነብና የሚያጠና ቢሆንም ታላቁ መከራ ከንጥቀት በፊት ይሁን ወይም በኋላ ከራዕይ መጽሐፍ መረዳት አልቻለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ግልጽ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት በመሻት ጉዞ አደረገ፡፡
 
በዚህ ጉዞ ወቅት የኑማቶሎጂ መሪ ከነበረች ኮረዳ ሴት ጋር ተገናኘ፡፡ ይህች ልጃገረድ ንጥቀቱ ከታላቁ መከራ በፊት እንደሚሆን በራዕይ ማየቷን ተናገረች፡፡ የነገረችውን በማመንና ንጥቀት ከመከራው በፊት እንደሚመጣ በመቀበል ዳርቢ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቹን በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳቦች ደመደመ፡፡
 
ሆኖም በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በዋናነት የሚያምኑት በድህረ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ስለነበር የዳርቢ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ በደንብ ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡
 
ዳርቢ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ተጻፈው ስለ እስራኤል ሕዝብ መዳን እንደሆነና ይህም ከአሕዛብ መዳን ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ይናገር ነበር፡፡ ‹‹እንደገና ትንቢት ልትናገር ይገባሃል›› (10፡11) የሚለውንም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መሰበክ ሳይሆን እየመጣ መሆኑን የሚያውጀውን የመንግሥቱን ወንጌል ነው በማለት ተርጉሞቷል፡፡
 
ይህንን የዳርቢን መላ ምት እንደወረደ ተቀብሎ ይህንን የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ በማመሳከሪያ መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ በማስገባት በሰባቱ ዘመኖች ላይ የራሱን መላ ምት ፈጠረ፡፡ የስኮፊልድ አባባል በጊዜው ተቀባይነትን አግኝቶ ከጀርባ ታሪኩ ጋር በሚገባ በመገጣጠሙ በመላው ዓለም ሐይማኖተኞች መካከል ታላቅ መነሳሳት በማምጣት በሰፊው ተቀባይነትን አገኘ፡፡
 
እግዚአብሄር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ይላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ታሪክን በሰባቱ ማህተሞች በሰባት ዘመኖች በከፈለው በእግዚአብሄር ዙፋን ፊት በሰባት ማህተሞች የታተመውን መጽሐፍ በመውሰድ ሲከፍተው እናያለን፡፡
 
የመጀመሪያው ዘመን የነጩ ፈረስ ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን እግዚአብሄር ዩኒቨርስንና ሰውን ከፈጠረበት ቅጽበት ጀምሮ እኛን ለማዳን የወሰነበትና በዚያው መሰረትም በእርግጥ እኛን ያዳነበት ዘመን ነው፡፡ ዮሐንስ ራዕይ 6፡2 ‹‹አየሁም እነሆም አምባላይ ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፡፡ አክሊልም ተሰጠው፡፡ ድልም እየነሳ ወጣ ድል ለመንሳት›› ብሎ እንደነገረን ጌታ አሸንፎዋል፡፡ በማሸነፍም ይቀጥላል፡፡ ከፍጥረትም በፊት እንኳን ወንጌል አስቀድሞም ነበር፡፡ ደህንነትም ቀድሞውኑ ጀምሮዋል፡፡
 
ሁለተኛው ዘመን የሰይጣን ዘመን የሆነው የዳማው (ቀዩ) ፈረስ ዘመን ነው፡፡ ይህ ዲያብሎስ ከሰው ዘር ሰላምን በመውሰድ እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ፣ እርስ በርሳቸው እንዲጠላሉና በሐይማኖት ግጭቶች ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያደርግበት ዘመን ነው፡፡
 
ሦስተኛው ዘመን የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ሲሆን መንፈሳዊና ሥጋዊ ረሃብ የሚከሰትበት ዘመን ነው፡፡ አራተኛው ዘመን የሐመሩ ፈረስ ዘመን ማለትም የሰማዕትነት ዘመን ነው፡፡ አምስተኛው ዘመን የመነጠቅ ዘመን ነው፡፡ እግዚአብሄር ቅዱሳኖች የሚነጠቁበትን ዘመን ከዘመኖቹ አንዱ አድርጎታል፡፡ ስድስተኛው ዘመን ሰባቱ ጽዋዎች የሚፈሱበት ይህ ዓለም የሚጠፋበት ዘመን ነው፡፡ ቀጣዩ ዘመንም የሺህ ዓመት መንግሥትና የአዲስ ሰማይና ምድር ዘመን ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የዚህን ዓለም ጊዜ በሰባት ማህተሞች በታተመው መጽሐፍ ውስጥ ባሉት በእነዚህ ሰባት ዘመኖች ውስጥ አስቀምጦታል፡፡
 
ስኮፊልድ በሰባት ዘመናቶች የከፈለው የጊዜ ክፍልፋይ ከራሱ ያመነጨው ነው፡፡ በአንጻሩ በእግዚአብሄር እጅ በተያዘው ባለ ሰባት ማህተም መጽሐፍ አማካይነት በራዕይ 6 ውስጥ የተተነበዩት ሰባቱ ዘመኖች በራሱ በእግዚአብሄር የተወሰኑ ነበሩ፡፡ ሰዎች ግን ሰው ሰራሽ ስለሆነው የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ይናገራሉ፡፡ በዚህ የሚያምኑ ብዙ ሰዎችም ጌታን ከልባቸው ማመኑ አስፈላጊ እንዳልሆነ ደምድመዋል፡፡
 
እነርሱ በልባቸው ‹‹ታላቁ መከራ ከመምጣቱ በፊት ስለምንነጠቅ የሰባቱ ዓመት ታላቁ መከራ በሚመጣበት ጊዜ ቀደመን በእግዚአብሄር ፊት እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ምንም የምንጨነቅበት ነገር የለንም!›› ብለው ወስነዋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ከመከራው በፊት እንደምንነጠቅ ነግሮን ቢሆን ኖሮ በእርግጥም እምነታችንን ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ባልነበረም ወደ ቤተክርስቲያንም በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ መሄድ ብቻ በበቃን ነበር፡፡ እግዚአብሄር የነገረን ግን ይህንን አይደለም፡፡
 
‹‹ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ፡፡›› ‹‹እነርሱም አርባ ሁለት ወር ቅድስቲቱን ከተማ ይረግጡአታል፡፡›› ይህ የእግዚአብሄር ቃል በመከራው ዘመን አሕዛቦችም ደግሞ እንደሚድኑ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ያሰራጩ ዘንድ ሁለቱን ነቢያቶች ያስነሳል፡፡ የመከራው ዘመን ሲመጣ እርሱ በወሰነው የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ የመጀመሪያ ሦስት ዓመት ተኩል ሳያልፍ በእግዚአብሄር ፊት ሊቆም የሚችል ማንም የለም፡፡ እግዚአብሄር በዚህ ጊዜ ብዙ ሰማዕታት ከመከራው እንደሚወጡም ነግሮናል፡፡
 
አንድ ሰው በትክክል በኢየሱስ ያምን ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል መማርና በተጨባጭ ትክክል በሆነው ነገር ማመን አለበት፡፡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እያንዳንዱን ገጽ ሳያነቡ በራሳቸው የሚሰብኩና የሚያምኑ ከሆኑ መጨረሻቸው መናፍቃን መሆን ይሆናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እጅግ ብዙ የሐይማኖት ድርጅቶች ያሉበት ምክንያቱ ብዙ ሰዎች እምነታቸውን በራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ላይ በመመስረታቸው ነው፡፡
 
የእስራኤል ሕዝቦች መዳናቸው የእግዚአብሄር ዕቅድ በተስፋ ቃሉ መሰረት እንደሚፈጸም ይነግረናል፡፡ ይህም እንደዚሁ እግዚአብሄር ለእኛ ተናገረውን የተስፋ ቃል እንደማይቀለብስ ነገር ግን ሁሉንም እንደሚፈጽም ይነግረናል፡፡ እንዲህ ያለ ታላቅ ተስፋ ያለን ለዚህ ነው፡፡
 
ሁለቱ የእስራኤል ነቢያቶች ከሞቱ ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ተነስተው ወደ ሰማይ ያርጋሉ፡፡ ንጥቀት ይህ ነው፡፡ በታላቁ መከራ ውስጥ ሰማዕት የሆኑት እንዴት እንደሚነጠቁ ምሳሌን ያቀርባል፡፡ የራሳችንንም ንጥቀት እንደ ምልክት አድርጎ ያሳየናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰባተኛው መለከት ከተነፋ በኋላ ይህች ምድር የክርስቶስ መንግሥት እንደምትሆንና እርሱም በእርስዋ ላይ ለዘላለም እንደሚነግስ ይነግረናል፡፡ በኢየሱስ ክርቶስ የታመኑትም እንደዚሁ ከእርሱ ጋር አብረው ይነግሳሉ፡፡
 
እግዚአብሄር ቅዱሳኖችን ከነጠቀ በኋላ ይህችን ምድር ሙሉ በሙሉ ያጠፋታል፡፡ ጥፋቱ መቶ እጅ ስለመሆኑ አናውቅም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዝርዝር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈምና፡፡ እግዚአብሄር ግን በራዕይ 11፡18 ላይ ይህንን ነግሮናል፡- ‹‹ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሄር ሆይ ትልቁን ሐይልህን ስለያዝህ፣ ስለነገስህም፣ እናመሰግንሃለን፡፡ አሕዛብም ተቆጡ፤ ቁጣህም መጣ፡፡ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፡፡ ለባርያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ፡፡›› ታላቁ መከራ የሦስት ዓመት ተኩል ጣሪያውን ሲያልፍ ንጥቀቱ በእርግጠኝነት ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው የሦስት ዓመት ተኩል በትክክል ሲመጣ ሳይሆን እርሱን በጥቂቱ ካለፈ በኋላ መነጠቅ ይሆናል፡፡ መከራው ጣሪያው ላይ የሚደርሰው በሰባቱ ዓመት አጋማሽ ላይ ነው፡፡ የእስራኤል ሕዝቦች ቅዱሳን ሰማዕት የሚሆኑት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ንጥቀቱም ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ይመጣል፡፡ መነጠቅ ሲሆን ሁላችንም በአየር ላይ ከበጉ ሰርግ እራት ጋር እንተባበራለን፡፡
 
ማቴዎስ 25 እንደሚነግረን በአየር ላይ በበጉ ሰርግ እራት ላይ ስንሳተፍ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በዚህች ምድር ላይ ይወርዳሉ፡፡ በአየር ላይ ሆነን እግዚአብሄርን ስናመሰግንና በዚህች ምድር ላይ እየሆኑ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ስናይ ስለ ጸጋው እግዚአብሄርን አብዝተን እናወድሰዋለን፡፡
 
በራዕይ ቃል አማካይነት የመጨረሻዎቹ ቀናቶች ሲመጡ ዘመኑን ለይታችሁ በትክክል በቃሉ በማመን ሕይወታችሁን በእምነትና በትጋት እንድትኖሩና ለወደፊቱ እንድትዘጋጁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልይማለሁ፡፡ ከእርሱ ጋር በበጉ ሰርግ እራት ላይ በመካፈል ጌታን ለማመስገን ለማወደስና ለማምለክ እምነታችሁን ማዘጋጀት አለባችሁ፡፡
 
የራዕይ ቃል ዳግመኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባላችሁ እምነት በትጋትና በታማኝነት ልትኖሩ እንደሚገባችሁ ለልባችሁ እያስታወሰ በመጭዎቹ ቀናቶች ታላቅ መሪ መሆኑን እንዲያረጋግጥላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡