Search

Bài giảng

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 16] እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ፡፡

ጳውሎስ በማጠቃለያው በሮሜ ላሉት ቅዱሳኖችና ለእኛ እርስ በርሳችን ሰላም እንድንባባል ተናገረ፡፡ በዚህ ዘመን ከሙሉ ልባችን በጌታ ሰላም የምንለው ማንን ነው? የእግዚአብሄርን ቃል በመላው ዓለም የሚሰብኩትን አገልጋዮችና ምዕመናኖች በደስታ ሰላም ልንላቸው እንችላለን፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መጽሐፎች በማንበብ ከዳኑት ጋር ሕብረት ማድረግ እንችላለን፡፡ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ሰላም የምንላቸው ቤተክርስቲያኖች፣ ምዕመናኖችና የእግዚአብሄር አገልጋዮች አሉን፡፡
 
ሁሉም በውሃውና በመንፈሱ ወንገል ስለማያምን ጻድቃን ሁሉንም ሰላም ማለት አይችሉም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ በደስታ ሰላም የምንላቸው በጣም ብዙ ሰዎች የሉም፡፡ ያን ያህል ሰላም የምንላቸውና በአንድ ዓይነት እምነት ሕብረት የምናደርግባቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች አለመኖራቸው ያሳዝናል፡፡ በዓለማውያን ቤተክርስቲያኖች ውስጥ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ነን እያሉ ከሚያስመስሉ ሐጢያተኞች ጋር ሕብረት ማድረግ አንችልም፡፡
 
ሐጢያትና መንፈስ ቅዱስ አብረው መኖር እንደማይችሉ ሁሉ ሐጢያተኞችና ጻድቃንም እርስ በርሳቸው ሰላምታ ሊለዋወጡ አይችሉም፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ለእግዚአብሄር መንፈሳዊ አምልኮን ሊያቀርቡና ለመንፈሳዊ ነገሮች ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ገና የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያልተቀበሉ ሐጢያተኞች የእግዚአብሄርን ሕግ በመጠበቅ ለመዳን ስለሚሞክሩ ከጻድቃን ጋር መንፈሳዊ ሕብረት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ እንስሳና ሰው እርስ በርሳቸው መነጋገር እንደማይቻላቸው ሁሉ ጻድቃንም ከሐጢያተኞች ጋር መንፈሳዊ ሕብረት ማድረግ አይቻላቸውም፡፡
 
ጳውሎስ መንፈሳዊ ሕብረት ያደረገባቸው ብቸኞቹ ሰዎች እንደ እርሱ ዓይነት እምነት ከነበራቸው ጋር እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ አንድ ሰው ከጳውሎስ ጋር ሕብረት አደረገ ማለት ጳውሎስ የግለሰቡን እምነት ደገፈ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ዛሬ ወደ አንድ ክልል ብሄድ ልጎበኘውና ሰላም ልለው የሚገባኝ ማንን ነው?›› ብዬ አሰብሁ፡፡ ወደ ሶኮቾ ብሄድ የሶኮቾን ቤተክርስቲያን እንደሚሆን፣ ወደ ጋንግኑንግ ብሄድ ደግሞ የጋንግኑንግን ቤተክርስቲያን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የእግዚአብሄርን አገልጋዮችና ምዕመናኖች ማግኘትና ከእነርሱ ጋር ሕብረት በማድረግ እንጀራ መቁረስ እችላለሁ፡፡ እዚያ ያሉትን ወንድሞቼንና እህቶቼን ቤቶችን መጎብኘትና ሰላም ማለትም እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ሰላም ማለት የምችላቸው ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትንና በመንፈስ ቅዱስ ተመሳሳይ እምነትን የሚጋሩትን ብቻ ነው፡፡
 
ጳውሎስ እምነታቸውን የደገፈላቸው ሰዎች ምንኛ የተባረኩ እንደነበሩ ማየት እንችላለን፡፡ እርስ በርሳችን ያለንን እምነት የሚያረጋግጠውና እርስ በርሳችን ሰላም እንድንባባል ያደረገን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ምንኛ ታላቅ ነው፡፡ እርስ በርሳችሁ ሰላም እንድትባባሉ በፈቀደላችሁ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እምነት አላችሁን? ያለ ምንም ጥርጥር ምንም ሐጢያት እንደሌለባችሁ በታማኝነት ለእግዚአብሄር መናዘዝ ትችላላችሁን?
 
ቻይናን በጎበኘሁ ጊዜ በዚያ ያሉትን ወዳጅ ምዕመናኖች ሰላም የማለት ዕድል ነበረኝ፡፡ በሔራን ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚኖረውን አንድ ወንድም ጎበኘሁ፡፡ በቀጣዩ ጠዋት ከእንቅልፋችን እንደነቃን ወዲያውኑ ትልቅ ቁርስ አዘጋጀልን፡፡ በቤተሰብ ደረጃ ተሰብስበን እንደምንቀመጥበት ባለ በአንድ ሰፊ ጠረጴዛ ተቀምጠን በዚያ ከሚገኙ ምዕመናን ጋር ያማረ ሕብረት አደረግን፡፡ ቀረብ ባለች ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ወንጌላዊም እኛን ለማየት በጣም ጓጉቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ጎበኘነው፡፡ ከእርሱም ጋር እንደዚሁ ሕብረት አደረግን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምነውን ሰው ሁሉ ሰላም ማለት እንችላለን፡፡
 
አሜሪካን ብጎበኝ የምሄደው የት ነው? በፍለሺንግ ኒውዮርክ የሚገኘውን መጋቢ ሳንቻን ሊንና ባለቤቱን እጎበኛለሁ፡፡ በዚያ ያሉትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለማግኘትም ኒው ላይፍ ሚሽንን እጎበኛለሁ፡፡ በሩሲያም ከጥቂት ዓመታት በፊት የጎበኘኋት ዳግም የተወለደች ቤተክርስቲያን አለች፡፡ በጃፓን በቶክዮ የሚገኘውን የሴት ዲያቆኒትን የሶን-ፓርክን ቤት እጎበኛለሁ፡፡
 
እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለን እምነታችን የዳንን ጻድቃን ነን፡፡ የዳንነው በሥጋችን ክንውኖች ሳይሆን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባለን እምነታችን አማካይነት በተቀበልነው የእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡
 
ማየት እንደምትችሉት ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 16 ላይ ሰላምታ ያቀረበላቸው ሰዎች ዝርዝር እንዳለ ሁሉ ጻድቃኖች ሰላም የሚሉዋቸው ሰዎች አሉ፡፡ ጳውሎስ እንዳደረገው እያንዳንዱን ክርስቲያን ሰላም ማለት አንችልም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ትክክለኛ እምነት የላቸውምና፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚያውቁትንና የሚያምኑትን ብቻ ሰላም ማለት እንችላለን፡፡ ሰላም የምንልበትንና ሰላም የምንባልበትን እምነት ስለሰጠን እግዚአብሄርን ከማመስገን ልንቆጠብ አንችልም፡፡
                        
 

ጳውሎስ ከእነዚህ ሰዎች እንድንርቅ አስጠንቅቆናል፡፡ 

 
ከቁጥር 17 ጀምሮ ጳውሎስ የሰጠን ሁለተኛው ምክር ለሆዳቸው ብቻ ከሚያገለግሉ ሰዎች መራቅ ያለብን መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፡፡ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ፡፡›› (ሮሜ 16፡17-18) ክርስቶስን ሳይሆን ሆዳቸውን የሚያገለግሉ ሰዎች አሉ፡፡ በምዕመናን መካከል ሁከትን የሚፈጥሩና ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግር የሚያታልሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎችን መሸሽ እንጂ ሰላም ማለት የለብንም፡፡
 
ጳውሎስ ከእነዚህ ሰዎች እንድንርቅ አስጠንቅቆናል፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ደስታ በቤተክርስቲያን ውስጥ መለያየትን መፍጠር በእግዚአብሄር ከልባቸው የሚያምኑትንም ማሰናከልና የራሳቸውን ሆድ ለመሙላትም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ማከማቸት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አጭበርባሪ ክርስቲያን መሪዎች ተከታዮቻቸውን ሕጉን ፈጽሞ እንዲታዘዙ በማስተማር ሰዎችን ከሕግ በታች አድርገው ለማፈን ይፍጨረጨራሉ፡፡ በኢየሱስ ስም ሆዳቸውን ብቻ የሚሞሉ የዋሆችን ያስታሉ፡፡ እነርሱን ሰላም ማለት አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ወደ አገልግሎት የገቡት የራሳቸውን ሆድ ለመሙላት ብቻ ነው፡፡
     
 

የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ለመላው ሕዝብ መሰራጨት አለበት! 

 
በሦስተኛ ደረጃ ጳውሎስ ወንጌልን ለሕዝቦች ሁሉ የማዳረስን አስፈላጊነት ተናግሮዋል፡፡ ቁጥር 26 እንዲህ ይላ፡- ‹‹…አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻህፍት የዘላለም እግዚአብሄር እንዳዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ…›› ጳውሎስ የሰበከው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ሕዝቦች ሁሉ በእርግጥም ሊያምኑበትና ሊታዘዙት የሚገባ ወንጌል ነው፡፡ ጳውሎስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሚያምኑት ጋር ቤተክርስቲያን የተከለባቸው አብዛኞቹ ክልሎች አሁን እስላማዊ ክልሎች መሆናቸው በጣም ያሳዝናል፡፡
 
በወቅቱ ጳውሎስ ወደ እነዚህ ክልሎች ሄዶ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በያዘው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በሚያምኑ ምዕመናኖች መካከል እዚያው የቤተክርስቲያን መሪዎችንም ሾሞዋል፡፡ ይህም በሚሽን ትምህርት ቤታችን ውስጥ ስልጠና ከሰጠናቸው በኋላ ሰራተኞችን ወደ ቤተክርስቲያናችን ከምንልክበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ቤተክርስቲያኖች እምነታቸውን ‹‹በአንድ ጌታ፣ በአንድ ሃይማኖት፣ በአንዲት ጥምቀት›› (ኤፌሶን 4፡5) ጠብቀው የቆዩ ቢሆኑም ወንጌልን በጽሁፍ መዝግበው ባላማስቀመጣቸው በወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት ጠብቀው ማቆየት ተሳናቸው፡፡
 
በአሁኑ ጊዜ መጽሐፎቻችንን ወደ ቱርክ ቋንቋ በመተርጎም ሂደት ላይ ነን፡፡ በቱርክ የሚኖር አንድ ሰው በእንግሊዝኛ መጽሐፎቻችን ተነክቶ ሊተረጉማቸው ፈቃደኛ ሆንዋል፡፡ እኛ በአሁኑ ጊዜ በአንድ ወቅት ጳውሎስ ራሱ ወንጌልን በሰበከበትና የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያኖች በተከለበት ስፍራ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰራጨት ጀምረናል፡፡ እኛም ጳውሎስ በጎበኘው በዚያው ክልል የሰበከውን ያንኑ ተመሳሳይ ወንጌል እየሰበክን ነው፡፡ ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል አሕዛቦች ሁሉ እርሱን በማመንና በመታዘዝ ብቻ ሊድኑበት የሚችሉበትን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ነው፡፡
 
ጳውሎስ በሮሜ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በሮሜ ለሚገኙት ቅዱሳን እርስ በርሳቸው ሰላም እንዲባባሉ፣ ለሆዳቸው ከሚያድሩት እንዲርቁና የውሃውንና የመንፈሱንም ወንጌል ለአሕዛቦች ሁሉ እንዲያሰራጩ ነገራቸው፡፡
       
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ያበረታናል፡፡ 
 
ጳውሎስ የጠቀሰው አራተኛው ነገር ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የሚያጸናን የእግዚአብሄር ጥበብ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደተሰበከ ከዘላለም ዘመናት የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻህፍት የዘላለም እግዚአብሄር እንዳዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምስጢር እንደተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን አሜን፡፡›› (ሮሜ 16፡25-27) በሮሜ የነበሩትን ቅዱሳን ያበረታቸው ምን ነበር? በሮሜ የነበሩትን ቅዱሳን ሊያበረታቸው የቻለው የጳውሎስ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነበር፡፡ ይህ ወንጌል የእግዚአብሄርም ጥበብ ነው፡፡ 
 
እግዚአብሄር በሰጠን ወንጌል ውስጥ የእርሱ ጥበብ አለ፡፡ ይህ ወንጌል በጉድለቶች የተሞሉትን ሰዎች ሳይቀር የሁሉንም ሐጢያቶች የመውሰድ ሐይል አለው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ምንም ያህል ደካሞችና በጉድለቶች የተሞሉ ቢሆኑም ሐጢያት አልባ ብቻ ሳይሆኑ የዚህ ወንጌል ሰባኪዎችም ተደርገዋል፡፡ ምሉዕ ፍጡራን ሊያደርገን የሚችለው የእግዚአብሄር ጥበብና ከዚያ የሚመጣው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ የሰውን ነፍስ፣ ልብ፣ አስተሳሰቦችና ሰውነት ከሚያበረታው ከዚህ ወንጌል ውጪ ሌላ እውነት የለም፡፡
 
ጳውሎስ ወንጌልን እንዲያው በሌጣው ‹‹ወንጌል›› ብሎ አልጠራውም፡፡ ነገር ግን ‹‹ወንጌሌ›› ብሎ ጠራው፡፡ ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ውስጥ የተገለጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በብሉይ ኪዳን ውስጥ ባሉት ነቢያት አማካይነት ተገልጦ በአዲስ ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በተፈጸመው ወንጌል ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ጳውሎስ ‹‹የእርሱ ወንጌል›› በነቢያ መጻህፍት ውስጥ በምስጢር ተሰውሮ በተቀመጠው መገለጥ መሰረት እንደታየ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡
 
ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በብሉይ ኪዳን ፔንታቱክ በተለይም በዘሌዋውያን የመስዋዕት ስርዓት ውስጥ የተገለጠና የእግዚአብሄር ጽድቅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ፣ በመስቀል ላይ ሞቱና በትንሳኤው በአዲስ ኪዳን የተፈጸመ ወንጌል ነው፡፡ ጳውሎስ ‹‹እንደ ወንጌሌ ሊያበረታችሁ ለሚችለው ለእርሱ›› ክብር ይሁን ያለው ለዚህ ነው፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የእግዚአብሄርን ቅዱሳንና አገልጋዮች ያበረታል፡፡ በዚህ ወንጌል አማካይነት እምነታችን፣ ነፍሳችን፣ አስተሳሰባችን፣ አእምሮዋችንና አካላችን ይበረታሉ፡፡ እምነታችን ሊበረታ የሚችለው እንዴት ነው? ሁልጊዜ ደካሞች እንደመሆናችን በርትተን እንድንቆም የሚያደርገን ምንድነው? 
እምነታችን እየበረታ የሚሄደው በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደውን የክርስቶስን ደህንነት ስለተቀበልን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት የለብንም ማለት የምንችለው ልባችን ከእንግዲህ ስለማያፍርና በዚህ በማያፍር መንፈሳዊ እምነትም አሁንም ድረስ በሐጢያት ለታሰሩት ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰራጨት ስለምንችል ነው፡፡
 
 
የመጨረሻ ምክሮች፡፡ 
 
ጳውሎስ እንዲህ በማለት ምዕራፍ 16ን በማጠቃለያ ጸሎት ያጠናቅቀዋል፡፡ ‹‹ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን አሜን፡፡›› እግዚአብሄርን በአያሌው የሚያከብረው ምንድነው? በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሄርን ጽድቅ መስበክ እግዚአብሄርን በአያሌው ያከብረዋል፡፡ እኛም ወንጌልን ከሙሉ ልባችን ስንሰብክ እንከብራለን፡፡
 
በሮሜ 16 ላይ ያለው የጳውሎስ መልዕክት መሰረተ አሳብ እነዚህ ናቸው፡፡ እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ፤ ለሆዳቸው ብቻ ከሚያድሩ ራቁ፤ ወንጌልን ለአሕዛቦች ሁሉ አሰራጩ፡፡ ጳውሎስ በሮሜ ላለችው ቤተክርስቲያን የሰጠው የመጨረሻው ምክር ይህ ነው፡፡ ጳውሎስ የሰበከው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እኛን በሁሉም መንገድ የማበርታት አቅም አለው፡፡ የምናምነው ይህንን ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምነው እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ሐዋርያቶች ከነበራቸው የእኛም ቤተክርስቲያን አሁን ከምታምነው እምነት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
 
ተመሳሳይነቱ ይታወቃችኋልን? መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብና ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የኖሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ስብዕናዎች ያላቸው ያንኑ እምነት እንዳለን ስረዳ ተገርሜያለሁ፡፡
 
በየቀኑ ወንጌልን ለምን ያህል ሰዎች እንደምናጋራ አስባችኋልን? በአንድ ቀን ከሁለት ሺህ ለማያንሱ ሰዎች ወንጌልን እናካፍላለን፡፡ በየአገሩ የሚኖሩ እንደ አዲስ ዳግም የተወለዱ ቅዱሳን ወንጌልን ለጎረቤቶቻቸው ቢሰብኩ እነዚህ ሁለት ሺህ ሰዎች ፈጥነው ወደ አስር ሺህ ይበዛሉ፡፡ አስር ሺህዎቹም ሰዎች ወደ ሃያ ሺህ ለማደግ አንድ ጊዜ ብቻ ወንጌልን መስበክ ይኖርባቸዋል፡፡ ማየት እንደምትችሉት ወንጌልን ለመላው ዓለም መስበክ የማይቻል ሥራ አይደለም፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ የተጻፉት መጽሐፎቻችን ቁልፍ ገጽታ መጠራቀማቸው እንጂ አለመጥፋታቸው ነው፡፡ የሚያነቡዋቸው ሰዎች ምንም ያህል ቢበዙም ትርጉሞቻቸው አይቀየሩም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የያዘ መጽሐፍ ሲኖር ብዙ ሰዎች እየተዋሱ ያነቡታል፡፡ የእግዚአብሄርም ወንጌል ይሰራጫል፡፡ ወንጌል በመላው ዓለም የሚዳረስበት ቀን በጣም ሩቅ አይደለም፡፡
 
በእምነታችሁ ያገኛችሁት የእግዚአብሄር ጽድቅ ባደጉት አገሮች የሚኖሩት ሰዎች እንኳን የማያውቁት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡ ለመላው ዓለም የምናሰራጨው እውነተኛው ወንጌል ይህ ዓለም የማያውቀው ምስጢር ነው፡፡ ስለዚህ የደህንነትን ምስጢር በሐጢያቶቻቸው ለተጨነቁ ሰዎች ሁሉ በጉጉት መግለጥ እንሻለን፡፡ ይህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ የታየው የእግዚአብሄር ጽድቅ በጣም ግልጽ ስለሆነ ይህንን ወንጌል የሚቀበሉ ሁሉ እግዚአብሄርን ያመሰግናሉ፤ ያከብሩማል፡፡
 
አንዳንድ ሰዎች በተደጋጋሚ ስለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መናገራችን እንግዳ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ምንም ያህል ብዙ ጊዜ ብንደጋግመውም አሁንም በነፍሳችን ውስጥ ደስታንና ምስጋናን ይጭራል፡፡ አሁንም ድረስ በሐጢያት የታሰሩ እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች ስላሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ደጋግመን ለመላው ዓለም እንሰብካለን፡፡ ይህ ወንጌል ጳውሎስን ጨምሮ በሐዋርያቶች የተሰጠ ያው ወንጌል ስለሆነ ነፍሳቶች ሁሉ በዚህ ወንጌል ማመን ይገባቸዋል፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስማትና በልባችን ጽላት ላይ መጻፍ ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም ለእያንዳንዱ ክርስቲያን አስፈላጊ ነው፡፡
 
በታተሙና በኤሌክትሮኒክ መጽሐፎች እንደዚሁም በድረ ገጽ ወንጌልን በቀን ከሁለት ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች እንሰብካለን፡፡ የእውነት ዘር በጥሩ አፈር ላይ ከወደቀ ከተዘራው በላይ ሰላሳ፣ ስልሳ ወይም መቶ ፍሬ ማፍራት ይችላል፡፡ አንድ ሰው ለብዙ ሰዎች ወንጌልን መስበክ ይችላል፡፡ እነዚህም ሰዎች እያንዳንዳቸው ለተጨማሪ ብዙዎች ወንጌልን በመስበክ ወንጌልን እጅግ ብዙ ቁጥር ላለው ሕዝብ ማሰራጨት ይችላሉ፡፡
 
ወንጌላችን በቀን ከሁለት ሺህ ለሚበልጥ ሕዝብ እንደሚሰራጭ ስንሰማ ልባችን በእግዚአብሄር ጽድቅ ይሞላል፡፡ ይህንን ወንጌል ለመላው ዓለም እንድናሰራጭ መንገዱን ስለከፈተልን እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሄር የአገልጋዮቹን እምነት ጨምሮ እንዲያበረታ እጸልያለሁ፡፡
                   
አሁን በመላው እየተሰራጨ ያለው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አዲስ የደህንነት እውነት ምልክት ነው፡፡ ይህ ወንጌል መንፈስ ቅዱስን ለመቀበልና ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ለመግባት ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ ዓለማዊ ሐይማኖቶችን ምንም ያህል አበክራችሁ ብትመረምሩም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማግኘት አትችሉም፡፡
 
በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት በእርሱ ጽድቅ ማመን ስለሚችሉ እግዚአብሄርን ያመሰግናሉ፡፡ መጽሐፋችንን የሚያነቡ ሁሉ ‹‹አሃ! ኢየሱስ ከሐጢያቶቼ ያዳነኝ እንደዚህ ነው!›› በማለት ይደሰታሉ፡፡ ምክንያቱም ይህንን ወንጌል ከዚህ በፊት በጭራሽ አልሰሙምና፡፡
 
ከሐጢያት ባርነት ነጻ ለመውጣትና መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ማብቂያ የሌለው ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመጨረሻ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሲያውቁና ሲቀበሉ ሙሉ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታና የአእምሮ ሰላምን ያገኛሉ፡፡ ከዚህች ቅጽበት ጀምሮም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በዓለም ላይ ለእያንዳንዱ ሕዝብ ይሰራጫል፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በመላው ዓለም እየተሰራጨ በመሆኑ ልቤ በደስታ ተሞልቷል፡፡ ወንጌልን ባገለግልም አሁንም ቢሆን በድክመቶችና በጉድለቶች የተሞላሁ እንደሆንሁ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስለማምንና የእግዚአብሄርን ጽድቅ ስለማውቅ ወንጌሉን በማገልገል እቀጥል ዘንድ ከጌታ ዘንድ ሁልጊዜም አዲስ ብርታትን እቀበላለሁ፡፡ አሁን ወንጌል ብዙ አገሮችን አዳርሶዋል፡፡ ብዙ ሰዎች መጽሐፎቻችንን አንብበው እንዲህ ባለው ፍጹም ወንጌል ተገርመዋል፡፡
 
በመላው ዓለም በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምኑ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የዳኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ድክመቶች ቢኖሩብንም ሙሉና ፍጹማን ሆነን የቆምነው የእግዚአብሄር ጽድቅ በሆነው ጌታችን ስለምናምን ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሄር ሰራተኞች ነን፡፡ ሥጋዊ ሆዳችንን ለመሙላት ብቻ አንሻም፡፡ ነገር ግን እውነተኛውን ወንጌል ለመላው ዓለም ሁሉ እናሰራጫለን፡፡ ብዙ ጻድቃን ምዕመናኖች ወንጌልን በመላው ዓለም ለማሰራጨት ጥሪያችንን ተቀብለው እንዲነሱ እባርካለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ፡፡
 
እኛም እንደ ጳውሎስ ጌታ መቼም ይምጣ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እናሰራጫለን፡፡ ለዚህ ታላቅ ተልዕኮ በርትተን አብረን እንሥራ፡፡ ወንጌልን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ስናሰራጭ ጌታ በተስፋው መሰረት መጥቶ ወደ ቤታችን ይወስደናል፡፡ ጳውሎስ የመከረንን ምክር በጥንቃቄ ማድመጥ፣ እርስ በርሳችን ሰላም መባባልና መደጋገፍ ይገባናል፡፡ የምግባር ጉድለቶች ቢኖሩብንም በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ ባለን እምነታችን መንፈሳዊ ብርታት እናገኛለን፡፡ በእርግጥ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያለን እምነት ምንኛ ያማረና እርግጠኛ እንደሆነ ወደ ማወቅ ደርሰናል፡፡ እኛ በእርግጥም የእግዚአብሄር ፍጹም ጽድቅ በሆነው ጌታችን የምናምን ምዕመናኖች ነን፡፡
 
ይህንን ዓለም በእግዚአብሄር ጽድቅ ላይ ባለን እምነታችን ስንመለከተው ብዙ የሚሰራ ነገር እንዳለ እንረዳለን፡፡ ሁላችንም ወንጌልን በዚህ ዓለም ላይ በማሰራጨትና የእግዚአብሄር ጽድቅ በሆነው ክርስቶስ በማመን እግዚአብሄርንም በማመስገን ሕይወታችንን መኖር እንችላለን፡፡
 
ሃሌሉያ! የእግዚአብሄር ጽድቅ የሆነውን ጌታችንን ለዘላለም አመሰግነዋለሁ!