Search

Bài giảng

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[5-1] የእግዚአብሄር አብ ወኪል ሆኖ በዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 5፡1-14 ››

የእግዚአብሄር አብ ወኪል ሆኖ በዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 5፡1-14 ››
‹‹በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማህተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ፡፡ ብርቱም መልአክ፡- መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማህተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምጽ ሲያውጅ አየሁ፡፡ በሰማይም ቢሆን፣ በምድርም ላይ ቢሆን፣ ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ፡፡ ከሽማግሌዎቹም አንዱ፡- አታልቅስ፤ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማህተሞች ይፈታ ዘንድ ድል ነስቷል አለኝ፡፡ በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፡፡ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት፡፡ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሄር መናፍስት ናቸው፡፡ መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው፡፡ መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፡፡ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ፡፡ መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማህተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፡፡ ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሄር ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጀተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፡፡ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስ ቅኔ ይዘምራሉ፡፡ አየሁም በዙፋኑም፣ በእንስሶቹም፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላዕክትን ድምጽ ሰማሁ፡፡ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበረ፡፡ በታላቅ ድምጽም፡- የታረደው በግ ሐይልና ባለጠግነት፣ ጥበብም፣ ብርታትም፣ ክብርም፣ ምስጋናም፣ በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ፡፡ በሰማይና በምድርም፣ ከምድርም በታች፣ በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ በረከትና ክብር፣ ምስጋናም፣ ሐይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ፡፡ አራቱም ሽማግሌዎች አሜን አሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ፡፡›› 
               
 

ትንታኔ፡፡  

 
ቁጥር 1፡- ‹‹በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማህተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ፡፡››
እዚህ ላይ እግዚአብሄር በቀኝ እጁ በሰባት ማህተሞች የተዘጋ መጽሐፍ እንደያዘ ይናገራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ቀኝ እጅ መጽሐፉን መውሰዱ ኢየሱስ የሰማይ ሥልጣን ሁሉ እንደተሰጠው የሚያሳይ ፍቺ አለው፡፡
 
ቁጥር 2-4 ‹‹ብርቱም መልአክ፡- መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማህተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምጽ ሲያውጅ አየሁ፡፡ በሰማይም ቢሆን፣ በምድርም ላይ ቢሆን፣ ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ፡፡››
በዓለም ላይ መፍረድ፣ አዲስ ሰማይና ምድር መፍጠርና የእግዚአብሄር አብ ወኪል ሆኖ በዚያ ከቅዱሳን ጋር መኖር የቻለ ከኢየሱስ በቀር ማንም የለም፡፡
 
ቁጥር 5፡- ‹‹ከሽማግሌዎቹም አንዱ፡- አታልቅስ፤ እነሆ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማህተሞች ይፈታ ዘንድ ድል ነስቷል አለኝ፡፡››
እዚህ ላይ ‹‹ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር›› የሚለው ሐረግ ኢየሱስ ክርስቶስ የአብን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም የተገባና የሚችል ሁሉን ቻይ አምላክና የነገሥታት ንጉሥ የመሆኑን እውነታ ያጎላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አምላክና የአብን ዕቅድ የሚፈጽም የእግዚአብሄር ወኪል ነው፡፡
 
ቁጥር 6፡- ‹‹በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፡፡ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት፡፡ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሄር መናፍስት ናቸው፡፡››
ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሄር አብ ሥልጣንን ሁሉ በሰማይና በምድር ከተቀበለ በኋላ ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ቻይ አምላክ ሆንዋል፡፡ እርሱ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድረ የመጣ፣ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ የወሰደና እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን ለእነዚህ ሐጢያቶች የሞተ አምላክ ነው፡፡
 
ቁጥር 7፡- ‹‹መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደ፡፡››
ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ለመሆን ስለበቃ መጽሐፉን ከአብ መውሰድ ቻለ፡፡ ይህ ማለት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጌታችን የእግዚአብሄርን ሥራዎች በሙሉ ይፈጽማል ማለት ነው፡፡
 
ቁጥር 8፡- ‹‹መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፡፡ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ፡፡››
ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ሥራው 24ቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች ያቀረቡዋቸውን የቅዱሳን ጸሎቶች መስማት የሆነውን እግዚአብሄር አብን ወክሎ ይሰራል ማለት ነው፡፡
  
ቁጥር 9፡- ‹‹መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማህተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፡፡ ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሄር ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጀተህ፡፡››
እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ወኪል ከሆነ በኋላ በሰማይ አገልጋዮች ይመሰገናል፡፡ የሰማይ አገልጋዮች በዚህ ምድር ላይ ሐጢያተኞችን ከዓለም ሐጢያቶች በማዳኑ ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገኑት፡፡ ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ ሐጢያተኞችን ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ ለማዳን በዮሐንስ ተጠምቆ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ የራሱን ደም የሐጢያት ዋጋ አድርጎ በመክፈልም እነዚህን ሐጢያተኞች ለአብ ዋጃቸው፡፡ የሰማይ አገልጋዮች አምላካቸው የሆነውን የእርሱን የጽድቅ ሥራዎች የሚያመሰግኑት ለዚህ ነው፡፡
 
ቁጥር 10፡- ‹‹ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፡፡ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስ ቅኔ ይዘምራሉ፡፡››
የእግዚአብሄር አብ ወኪል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳኖችን የእግዚአብሄር መንግሥት ሕዝብና ካህናት አደረጋቸው፡፡ በመንግሥቱም ላይ አነገሳቸው፡፡ ስለዚህ ከሰማይ አገልጋዮች ክብርንና ምስጋናን ሁሉ ይቀበል ዘንድ ይበልጥ ብቁ ሆነ፡፡
 
ቁጥር 11-12፡- ‹‹አየሁም በዙፋኑም፣ በእንስሶቹም፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላዕክትን ድምጽ ሰማሁ፡፡ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበረ፡፡ በታላቅ ድምጽም፡- የታረደው በግ ሐይልና ባለጠግነት፣ ጥበብም፣ ብርታትም፣ ክብርም፣ ምስጋናም፣ በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ፡፡››
ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በሥጋው ስለወሰደ ደሙን አፈሰሰ፡፡ አብን የሚወክል ሆኖ በሰማይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ ሐይል፣ ባለጠግነት፣ ጥበብ፣ ብርታት፣ ክብርም፣ ምስጋናም፣ በረከትም ይቀበል ዘንድ ተገባው፡፡ በሰማይ አገልጋዮችና በመላዕክቶች ታጅቦም ምስጋናንና ስግደትን ሁሉ ተቀበለ፡፡ ሐሌሉያ! እግዚአብሄር ይመስገን! በእግዚአብሄር ዙፋን ዙሪያ አራቱ እንስሶችና 24ቱ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ የእርሱ ክብር ማለቂያ ስለሌለው ነፍሳቶችን ሁሉ ከሐጢያት ያዳነውን እግዚአብሄርን አመሰገኑ፡፡
 
ቁጥር 13-14፡- ‹‹በሰማይና በምድርም፣ ከምድርም በታች፣ በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ በረከትና ክብር፣ ምስጋናም፣ ሐይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ፡፡ አራቱም ሽማግሌዎች አሜን አሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ፡፡››
በመጨረሻም የእግዚአብሄር ወኪል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ አገልጋዮች ምስጋናንና ስግደትን ሁሉ የሚቀበል አምላክ ሆኖ ከፍ አለ፡፡ የሰማይ አገልጋዮች በሙሉ በረከትን፣ ውዳሴንና ክብርን ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሰጡት፡፡ እግዚአብሄር ይህ የሚገባው መሆኑ እጅግ አስገራሚና የሚያስመሰግን ነበርና፡፡ በሰማይና በምድር ያሉ ቅዱሳን ሁሉ የእግዚአብሄር አብ ወኪል ዙፋን ላይ ለተቀመጠው ለእርሱ ክብርንና ውዳሴን መስጠት አለባቸው፡፡