Search

Bài giảng

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[6-2] የሰባቱ ማህተሞች ዘመኖች፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 6፡1-17 ››

የሰባቱ ማህተሞች ዘመኖች፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 6፡1-17 ››
 
እያንዳንዱ የራዕይ ምዕራፍ ርዕሰ ጉዳይ እንደሚከተለው በአጭሩ ሊጠቃለል ይችላል፡፡
ምዕራፍ 1 -- የራዕይ ቃል መግቢያ
ምዕራፍ 2-3 -- በእስያ ላሉት ለሰባቱ ቤተክርስቲያኖች የተጻፉ ደብዳቤዎች
ምዕራፍ 4 -- በእግዚአብሄር ዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ
ምዕራፍ 5 -- የእግዚአብሄር አብ ወኪል ሆኖ በዙፋን ላይ የተቀመጠው ኢየሱስ
ምዕራፍ 6 -- በእግዚአብሄር የተወሰኑት ሰባቱ ዘመናቶች
ምዕራፍ 7 -- በታላቁ መከራ ወቅት የሚድኑት ሰዎች
ምዕራፍ 8 -- ሰባቱን መቅሰፍቶች የሚነፉት መለከቶች
ምዕራፍ 9 -- የጥልቁ ጉድጓድ መቅሰፍቶች
ምዕራፍ 10 -- ንጥቀት መቼ ይሆናል?
ምዕራፍ 11 -- ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ ነቢያቶች እነማን ናቸው?
ምዕራፍ 12 -- ታላቅ መከራ የሚገጥማትየእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን
ምዕራፍ 13 -- የጸረ ክርስቶስ መነሳትና የቅዱሳን ሰማዕትነት
ምዕራፍ 14 -- የቅዱሳን ትንሳኤ ንጥቀትና በአየር ላይ እግዚአብሄርን ማመስገናቸው
ምዕራፍ 15-16 -- የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ጅማሬ
ምዕራፍ 17 -- በብዙ ውሆች ላይ የተቀመጠችው የታላቂቱ ጋለሞታ ፍርድ
ምዕራፍ 18 -- የባቢሎን መውደቅ
ምዕራፍ 19 -- ሁሉን በሚችል አምላክ የሚተዳደርመንግሥት
ምዕራፍ 20 -- የሺህው ዓመት መንግሥት
ምዕራፍ 21 -- ሰማያዊቷ ቅድስት ከተማ
ምዕራፍ 22 -- የሕይወት ውሃ የሚፈልቅበት አዲስ ሰማይና ምድር
 
ከመጀመሪያው ምዕራፍ ጀምሮ እያንዳንዱ የራዕይ ቃል ምዕራፍ ርዕሰ ጉዳይ አለው፡፡ ሲብራሩም ሁሉም እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ድረስ እርስ በርሳቸው ይያያዛሉ፡፡ ልክ በሮሜ ውስጥ ምዕራፍ 1 መግቢያ፣ ምዕራፍ 2 ለአይሁድ የተነገረ የእግዚአብሄር ቃል፣ ምዕራፍ 3 ለአሕዛቦች የተነገረ የእርሱ ቃል እንደሆነ ሁሉ የራዕይም ቃል እንዲሁ ለእያንዳንዱ ምዕራፍ ርዕስ አለው፡፡
 
በመላው ቃል ላይ ተመርኩዤ ራዕይን የማብራራው በጣም ብዙ ሰዎች ራዕይን በሁሉም ዓይነት መላ ምቶች ስለተነጋገሩበት ነው፡፡ ራዕይን በእነዚህ ግምቶች ላይ አተኩራችሁ የምትገነቡት ከሆነ ከበድ ያሉ ስህተቶችን ከመስራት አታመልጡም፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በመንፈስ ቅዱስ በተመሩ የእግዚአብሄር ሰዎች በመሆኑ ፈጽሞ እርማት የሚያስፈልገው ምንም ነገር የለም፡፡ በአንጻሩ ዓለማዊ መጽሐፎች የደራሲዎቹ መጣጥፍ ምንም ያህል ጥሩና በዕውቀት የተሞላ ቢሆንም ስህተቶች ስላሉባቸው ብዙ እርማቶች ያስፈልጉዋቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ግን ለሺህ ዓመታቶች ሲወርድ ሲዋረድ ቢመጣም ፈጽሞ አልተለወጠም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ለብዙ ዓመታቶች ሲተላለፍ ቢቆይም ስህተት ሳይገኝበት ቀርቷል፡፡ ምክንያቱም የተጻፈው ልባቸው በመንፈስ ቅዱስ በተነዱ የእግዚአብሄር ባሮች ነበርና፡፡
 
እግዚአብሄር ሊነግረን የፈለገው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተሰወረ ብዙዎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሃይማን ሆነን ቀርተናል፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ገና ከፍጥረት ጀምሮ አንድ ጊዜ እንኳን አልተለወጠም፡፡ ሆኖም ብዙ ሰዎች ደካማ የሆነ የእግዚአብሄር ቃልና የዕቅዱ መረዳት ስላላቸው መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው አስተሳሰቦች መተርጎም ጀመሩ፡፡
 
እግዚአብሄር ምስጢሮቹን እንዲያው ለማንም ሰው ስለማይገልጥ እርሱን ሳያመልኩና እንደ ቃሉ ሳያምኑ የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ እየጠሩ ስስታቸውን ብቻ ለመሙላት የሚሞክሩ ሰዎች ከቶውኑም እውነትን ማየት አይችሉም፡፡ በሌላ አነጋገር ሐጢያት ያባቸው ሰዎች ምንም ያህል በርትተው ቢሞክሩም ፈጽሞ የራዕይን ቃል መረዳት አይችሉም፡፡ ሁሉም ዓይነት ስህተቶች የተሰሩት ቃሉን የመረዳት አቅም ስለሌላቸው ነው፡፡ አንዳንዶች ስለ ዘመኑ መጨረሻ ዋጋ በሌላቸው ምናቦች በማመን፣ እነርሱን በማጥናትና የኢየሱስን ዳግመኛ ምጽዓት ጊዜም ሳይቀር በማወጅ ወድቀዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ስሜት በመተርጎም በሒደት ሁሉንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስህተቶችን ሰርተዋል፡፡
 
እኛ በምናውቃቸው የሥነ መለኮት ምሁራን መካከል የእነርሱ ወኪሎች የሆኑት አብርሃም ኩይፐርና ሊዊስ ቤርክሆፍ የሺህ ዓመት መንግሥት የሚባል ነገር የለም ብለው ሲያቀነቅኑ ሲ. አይ. ስኮፊልድም ከቅድመ መከራ በፊት ንጥቀት ይሆናል የሚለውን ጽንሰ አሳብ ይዞዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሊቃውንቶች የያዙዋቸው መላ ምቶች ሁሉም በራሳቸው አስተሳሰቦች ላይ የተመሰረቱ የተሳሳቱ ትምህርቶች ናቸው፡፡
 
በመጀመሪያ በአክራሪዎች የሚቀነቀነው የሺህ ዓመት መንግሥት የለም የሚለው ትምህርት የተለየ የሺህ ዓመት መንግሥት የሚባል ነገር የለም፤ ይህ መንግሥትም አሁን በዚህ ምድር ላይ በሚኖሩ ቅዱሳን ልብ ውስጥ ተፈጽሞዋል በማለት ይከራከራል፡፡ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም የሚሉ ሰዎች ወደፊት በተጨባጭ የሚመሰረተውን የሺህ ዓመት መንግሥት ይክዳሉ፡፡ ይህ ‹‹መላ ምት›› የሺህውን ዓመት መንግሥት በተምሳሌታዊ አገባብ በመተርጎም ቅዱሳን እስከ ኢየሱስ ምጽዓት ድረስ የሚቆዩበትን ዘመን የሺህው ዓመት መንግሥት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ነገር ግን የሺህ ዓመት መንግሥት የለም በሚለው ትምህርት ውስጥ የሺህው ዓመት መንግሥት ያለ ምንም ታላቅ መከራ ቀድሞውኑም በቅዱሳን ልብ ውስጥ ተግባራዊ ሆንዋል የሚለው አተረጓጎም በጣም የተሳሳተ ነው፡፡
 
ነገር ግን በስኮፊልድ የተብራራው የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም ከሚለው መላ ምት ይልቅ በመላው ዓለም በስፋት ተሰራጭቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ‹‹የቅድመ መከራ ንጥቀት›› ትምህርት የራሱን የእግዚአብሄርን ዕቅድ ለውጦታል፡፡ እግዚአብሄር ዩኒቨርስን ከመፍጠሩ በፊት ሰባት ዘመኖችን አቅዶዋል፡፡ በጊዜ ሒደት ውስጥም ሁሉን ነገር በዕቅዱ መሰረት ፈጽሞታል፡፡ ነገር ግን በራዕይ 6 ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሄር ዕቅድ የማያውቁ ሰዎች ይህንን የተሳሳተ የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ አፈለቁ፡፡ በአሕዛቦች መካከል ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ይነጠቃሉ፤ ከእስራኤል ሕዝብ አንዳንዶቹም በሰባቱ ዓመት የመከራ ዘመን ይድናሉ በማለት ይከራከራሉ፡፡
 
ይህ ጽንሰ አሳብ ብዙ ሰዎችን ትልቅ ግራ መጋባት ውስጥ የከተተ ትምህርት ሆኖ ቀርቷል፡፡ በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ መሰረት የቅዱሳን ንጥቀት የሚሆነው ከታላቁ መከራ በፊት ከሆነ በራዕይ 13 ላይ እንደተመዘገበው የቅዱሳን ስደትም ሆነ ሰማዕትነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ የሚያምኑ ምዕመናን ከዚህ የቅድመ መከራ ንጥቀት ትምህርት ውስጥ ወጥተው ንጥቀታቸው የሚመጣው በታላቁ መከራ አጋማሽ ላይ የመሆኑን እውነት በማመን እምነታቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡
የራዕይ ቃል እግዚአብሄር ዓለምን በሰባቱ ዘመኖች ሕግ መሰረት እንደሚመራ ይገልጥልናል፡፡ በራዕይ 6 ላይ እንደተብራራው እግዚአብሄር በወሰናቸው የሰባቱ ዘመኖች ዕቅድ ትኩረት ውስጥ አልፈን ማየት አለብን፡፡ ሰዎች ግራ ተጋብተዋል፡፡ እምነታቸውም አልተረጋጋም፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጡትን የእነዚህን ሰባት ዘመኖች እውነት አያውቁምና፡፡ ስለዚህ በራዕይ 6 ላይ በተጻፈው መሰረት ማመን አለብን፡፡ እንደዚያ ለማድረግ ጥቂቶቹንና የተገነጣጠሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመመልከት በከፊል አገባብ ከማሰብ ይልቅ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የመሰከረውን የሰባቱን ዘመኖች ምስጢረ ቃል ማመን አለብን፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ከሰዎች እንደተሰወረ ሁሉ የእግዚአብሄርም ሰባቱ ዘመኖች እንዲሁ ተሰውረዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የራዕይን ቃል ለመረዳት ቢሞክሩና በራሳቸው አስተሳሰቦች ላይ በማተኮር ብዙ ጽንሰ አሳቦችን ቢያቀርቡም የራዕይ ቃል አሁንም ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ይህም የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እስከ አሁን ደረስ ከመደበቁ እውነታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን የክርሰቶስን ምጽዓት፣ የቅዱሳንን ንጥቀት ወይም የሺህውን ዓመት መንግሥት በሚመለከት ሊቃውንቶች እስከ አሁን ደረስ የደረሱባቸው ጽንሰ አሳቦች በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎችን አልጠቀሙዋቸውም፡፡
የራዕይን ቃል ለመረዳት ምዕራፍ 6ን መረዳት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ የራዕይን ቃል በሙሉ ለመፍታትና ለመረዳት ቁልፍ ነው፡፡ ነገር ግን የራዕይን ምሉዕ ቃል ከመረዳታችን በፊት ራሳችንን ማስታወስ ያለብን አንድ ነገር አለ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁና ሳያምኑ ራዕይን መረዳት አይቻልም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ሊስተዋል የሚችለው በመጀመሪያ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስታውቁና ስታምኑ ብቻ ነው፡፡
 
የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በዓለም ላይ የሚወርዱት የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በዓለም ላይ የሚወርዱት በራዕይ 8 ላይ እንደተመዘገበው ‹‹ሰባተኛውን ማህተም በፈታ ጊዜ›› ነው፡፡ ይህም በራዕይ 6 ላይ በተመዘገበው በአራተኛው ዘመን በሐመሩ ፈረስ ዘመን የሚገለጡትን ሁነቶች ያብራራል፡፡ ስለዚህ አስቀድማችሁ እግዚአብሄር የወሰናቸውን ሰባቱን ዘመኖች ሳትረዱ የሰባቱን መለከቶች መቅሰፍቶች መረዳት አትችሉም፡፡ የራዕይን ቃል በሙላቱ ለመረዳት በመጀመሪያ እግዚአብሄር የሰጠንን የወሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወቅና ማመን አለብን፡፡
 
በራዕይ 6 ላይ ያለው የእግዚአብሄር ቃል እግዚአብሄር የሰውን ዘር በፈጠረ ጊዜ የነደፈውን ጠቅላላ ንድፍ ዝርዝር ያቀርባል፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ዘር ጅማሬና ፍጻሜ በሰባት የተለያዩ ዘመኖች ከፋፍሎታል፡፡
 
እነዚህም በመጀመሪያ የአምባላዩ (ነጩ) ፈረስ ዘመን፣ ሁለተኛ የዳማው (ቀዩ) ፈረስ ዘመን፣ ሦስተኛ የጉራቻው (ጥቁር) ፈረስ ዘመን፣ አራተኛ የሐመሩ ፈረስ ዘመን፣ አምስተኛው የቅዱሳን ሰማዕትነትና ንጥቀት ዘመን፣ ስድስተኛው የዓለም ጥፋት ዘመን፣ ሰባተኛው የሺህው ዓመት መንግሥትና የአዲሱ ሰማይና ምድር ዘመን ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ዘር ያለውን ዕቅዱን በእነዚህ ሰባት ዘመኖች እንደከፋፈለ አምነን እንታዘዛለን፡፡ አሁን ዓለም ያለው በጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ነው፡፡ የአምባላዩንና (ነጩን) የዳማውን (ቀዩን) ፈረሶች ዘመን አልፎዋቸዋል፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ አሁን እኛ እየኖርንበት ያለው ዘመን የረሃብ ዘመን እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን የሐመሩም ፈረስ ዘመን እየቀረበን ነው፡፡ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ የቅዱሳን ሰማዕትነት ዘመን ይጀምርና ወደ ሰባቱ የታላቁ መከራ ዓመት እንገባለን፡፡ ይህ የመከራዎችና ሰማዕትነት ዘመን የሐመሩ ፈረስ ዘመን ነው፡፡
 
‹‹አራተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምጽ፡- መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ፡፡ እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፡፡ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ፡፡ ሲዖልም ተከተለው፡፡ በሰይፍና በራብም፣ በሞትም፣ በምድርም አራዊት ይገደሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛው እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹በምድርም አራዊት ይገደሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛው እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው›› የሚለው ምንባብ ጸረ ክርስቶስ በሐመሩ ፈረስ ዘመን እንደሚመጣና ቅዱሳኖችን ሰማዕት እንደሚያደርጋቸው የሚጠቁም ነው፡፡
 
በሐመሩ ፈረስ ዘመን ወቅት የሚገለጡት ሁነቶች በራዕይ 8፡1-7 ላይ ተመዝግበዋል፡፡ ‹‹ሰባተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ እኩል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ፡፡ በእግዚአብሄርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፡፡ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው፡፡ ሌላም መልአክ መጣና የወቅር ጥና ይዞ በመሰውያው አጠገብ ቆመ፡፡ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰውያ ላይ ለቅዱሳን ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው፡፡ የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሄር ፊት ወጣ፡፡ መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰውያውን እሳት ሞላበት፡፡ ወደ ምድርም ጣለው፡፡ ነጎድጓድና ድምጽም፣ መብረቅም፣ መናወጥም ሆነ፡፡ ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላዕክት ሊነፉ ተዘጋጁ፡፡ ፊተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፡፡ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የለመለመም ሣር ሁሉ ሁሉ ተቃጠለ፡፡››
 
በራዕይ 8 ላይ ያለው የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ማብራሪያ በራዕ 6 ላይ የተመዘገበውን የሐመር ፈረስ ዘመን እውነት በዝርዝር ያብራራል፡፡ ይህ ቃል በሐመሩ ፈረስ ዘመን የሚገለጡትን የጸረ ክርስቶስን መገለጥ፣ የሰባቱን ማህተሞች መቅሰፍቶችና ሰባቱን ጽዋዎች በዝርዝር መዝግቦዋል፡፡
 
በሌላ በኩል ምዕራፍ 4 እና 5 ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለምና በሚመጣው ሁሉ ላይ አምላክ ሆኖ እንደሚገለጥና የአብ ሙሉ ዕቅድም አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚፈጸም ይነግረናል፡፡ ስለዚህ በራዕይ 4 እና 5 አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም ምን ያህል ብርቱና እንዴት ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
 
ራዕይ 8 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላዕክት ሊነፉ ተዘጋጁ፡፡ ፊተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፡፡ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የለመለመም ሣር ሁሉ ሁሉ ተቃጠለ፡፡›› የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ የዓለም ደን ሲሶው ይቃጠላል፡፡ ይህ ውድመትም ተጨማሪ መቅሰፍቶችን ያስከትላል፡፡
 
የመጀመሪያው መለከት መቅሰፍት የዛፎችን ሲሶ ያቃጥላል፡፡ ይህ ውድመት ዓለምን ሲመታው ቀሪዎቹ ደኖችም በዓለም ሲሶ ላይ የሚወርደው ግዙፍ እሳት በሚያመጣቸው የብክለት ተጽዕኖዎች ስለሚወድሙ ጢሱ ጸሐይ ወደ ምድር እንዳትደርስ ያግዳታል፡፡ ሰብሎችም ይሞታሉ፡፡ መላው ዓለምም በታላቅ ረሃብና ቀጣና ውስጥ ይወድቃል፡፡
 
በዚህ የረሃብ ዘመን የአንድ ቀን ሥራ ደመወዝ የሚገዛው አንድ እርቦ ስንዴ ወይም ሶስት እርቦ ገብስ ብቻ ነው፡፡ አሁን ዓለም በቅርቡ የሚመጣውን ይህንን እንግዳ የሆነ ረሃብና ቀጣና እየጠበቀ ነው፡፡ ይህ የዓለም ረሃብ በሥጋዊና በመንፈሳዊ መንገዶች ይመጣል፡፡ መንፈሳዊ ረሃብ ቀድሞውኑም በዛሬው ዘመን ላይ አለ፡፡
 
የዘመኑ ቤተክርስቲያኖች መንፈሳዊውን እንጀራና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሕይወት ከዓለም ጋር መጋራት በማይችሉ ተራ ክርስቲያኖች ብቻ የተሞሉ ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ያሉ ሰዎች ከአውሮፓ እስከ እስያና አሜሪካ አህጉር ድረስ አሁን ሁሉም እየኖሩ ያሉት በጥፋታቸው ዘመን ውስጥ ነው፡፡ በዛሬው በዘመኑ ክርስትና ውስጥ ለተራቡት ነፍሳቶች መንፈሳዊ እንጀራ የሚያቀርቡት ጥቂቶች ናቸው፡፡
 
የሐመሩን ፈረስ ዘመን ጸረ ክርስቶስ የሚገለጥበት ዘመን አድርገን እንገልጠዋለን፡፡ በዚህ ዘመን የተፈጥሮ ጥፋቶች የእንጀራና የውሃ እጥረት ስለሚያስከትሉ ይህንን ታላቁን ረሃብ ተቋቁሞ ማለፍ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ዓለም በሳይንሳዊ እመርታው ቢቀጥልም የኑሮ ደረጃው ከዚህ በፊት ታይቶ ወደማያውቅ እጅግ አስከፊ ወደሆነ ድህነት ይወርዳል፡፡ እንዲህ ባለ ዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ኑሮዋቸውን ለመቀጠል በውስጣቸው የሚቀር አንዳች ፍላጎት ይኖራቸዋልን?
በዚህ የመከራ ዘመን ውስጥ ሁላችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ሰማዕትነታችንን መቀበልና እግዚአብሄርን ማክበር አለብን፡፡ እንዲህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ቅዱሳን በሰማዕትነታቸው ለእግዚአብሄር ክብርን ሁሉ ይሰጣሉ፡፡ እግዚአብሄርም በምላሹ እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት የሆኑትን ወደ ሰማይ በመውሰድ በበጉ ሰርግ እራት ላይ ይጋብዛቸዋል፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሄር መንግሥት አገልጋይ እንደሆነ ተናግሮዋል፡፡ ሐዋርያት ብዙዎች ወደ ሺህው ዓመት መንግሥት ይገቡ ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰብከዋል፡፡
 
በታላቁ መከራ ወቅት በእስራኤሎች መካከል ሰማዕት የሚሆኑና ኢየሱስን በማመናቸው የሚነጠቁ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን በሐመሩ ፈረስ ዘመን ማለትም በታላቁ መከራ ዘመን ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ታላቁ መከራ ሲመጣ በዚህ ዓለም ያለ እያንዳንዱ ሰው በውድመት የተመታችውን ዓለም ስርዓት ማስያዝ የሚችል ሰው ይፈልጋል፡፡ አውዳሚ የሆኑ የተፈጥሮ ጥፋቶች የተከሰቱትን ችግሮች የሚፈታና እየገጠሙዋቸው ያሉትን ብዙዎቹን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ሐይማኖታዊ ችግሮች የሚያቃልል ሰው ይናፍቃሉ፡፡ ጸረ ክርስቶስ ብቅ የሚለው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
 
በቅርቡ አንዲት ጃፓናዊት ደራሲ የሮም ንጉሠ ነገሥታቶችን የሚያወድስ ዘ ስቶሪ ኦፍ ዘ ሮማንስ (የሮማውያን ታሪክ) የሚል ርዕሰ ያለው ተከታታይ መጽሐፎችን ጽፋለች፡፡ የደራሲው ዋናው መከራከሪያ ዓለም አምባገነን ሥልጣን ያለው መሪ በቶሎ ያስፈልገዋል የሚል ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችም ከእርስዋ ጋር ተስማምተዋል፡፡ በታላቁ መከራ ወቅት ሰዎች የራሳቸው ግዛት ያላቸውን ብዙ መሪዎች ሳይሆን ዓለምን በብረት ጡጫ መግዛት የሚችል አንድ በመላው ዓለም ላይ የሚሰለጥን ሐያል የዓለም ገዥ ይፈልጋሉ፡፡
 
በአሁኑ ጊዜ ዓለም በብዙ አገረ መንግሥታቶች ተከፋፍላለች፡፡ እያንዳንዳቸውም የራሳቸው መሪ አላቸው፡፡ በመጨረሻው ዘመን ግን ሰዎች ችግሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ የሚፈታላቸው አንድ ግርማ ሞገስ ያለው የዓለም መሪ ይፈልጋሉ፡፡ አሁን ዓለም ይህንን መሪ ማለትም በመላው ዓለም ላይ የሚነግሰውን ጸረ ክርስቶስ ይጠብቃል፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ ጸረ ክርስቶስ በታላቅ ሐይል ይገለጥና በዓለም ላይ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በአገዛዙ ሥር እንደሚያስገዛው ይነግረናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ እሳት በምድር ላይ ዘንቦ የዓለምን ዛፎች ሲሶ እንደሚያቃጥልም ይነግረናል፡፡ ይህ ዘመን ሲመጣ ጸረ ክርስቶስ በምድር ላይ ይገዛል፡፡ ያለ እርሱ ምልክትም ማንም ምንም ነገር መሸጥ ወይም መግዛት አይችልም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ምልክቱን ለመቀበልና ጣዖቱን ለማምለክ አሻፈረኝ ስለሚሉ ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ከዚያም ትንሳኤን አግኝተው ይነጠቃሉ፡፡ የሐመሩ ፈረስ ዘመን እንዲህ ሲጠናቀቅ የሺህው ዓመት መንግሥት ይጀምራል፡፡
 
ጌታ የዚህ ዓለም ጥፋትና ታላቁ መከራ እንደ ሌባ እንደሚመጣ ነግሮናል፡፡ ስለዚህ አሁን የታላቁን መከራ ችግሮችና ጥፋት ሁሉ ማሸነፍ የሚችል እምነት ማዘጋጀት አለብን፡፡ ይህ ዝግጅት ተግባራዊ መሆን የሚችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ የማይዘጋጁ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስለማያምኑ መቅፍቶችና ጥፋት ሁሉ ይወርድባቸዋል፡፡
 
ስለዚህ የዛሬው ዘመን የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን መሆኑን በግልጽ መረዳት አለብን፡፡ ያ የመጨረሻው ቀን ከመምጣቱ በፊት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና ለወደፊቱ መዘጋጀት አለብን፡፡
 
አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በሰማዕትነታቸው ይነጠቃሉ፡፡ ባለጠጎች የሆኑ ሰዎች በምቾት መኖራቸውን አይቀጥሉም፡፡ ድሆች የሆኑ ሰዎችም በድህነታቸው አይቀጥሉም፡፡ ስለዚህ አሁን በእኛ ላይ እየሆኑ ባሉት ነገሮች ማዘንም ሆነ መመካት የለብንም፡፡ ምክንያቱም የሐመሩ ፈረስ ዘመን ቅርብ እንደሆነና ያን ጊዜም ቅዱሳን ሁሉ ሰማዕት ሊሆኑ እንደሚችሉ እናምናለንና፡፡
 
በየጊዜው በራሳቸው መንገድ ክርስቶስ የሚመጣበትን ጊዜ በመተንተን ታላቅ ግራ መጋባትን ፈጥረው ለጌታ ዳግመኛ ምጽዓት የራሳቸውን ቀንና ሰዓት እያወጁ ብዙዎችን በእነዚህ አባባሎች የሚያስቱ አንዳንድ ሰዎችን በዙሪያችን እናያለን፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ሰባተኛው መለከት እስከሚነፋ ድረስ የክርስቶስ ምጽዓት አይሆንም፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በማስላትና ጌታ የሚመለስበትን የራሳችንን ቀን የመወሰን ስህተትን በፍጹም መስራት የለብንም፡፡
 
ክርስቶስ የሚመጣበትን ቀን በሕልማቸው ወይም በራዕያቸው እንዳዩ የሚናገሩትን ሰዎችም ልንጠነቀቃቸው ይገባናል፡፡ ሕልሞቻቸው ከሕልሞች የዘለሉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር የንጥቀቱ የጊዜ ወሰን በትክክል መቼ እንደሚሆን በቃሉ በኩል ስለነገረን ማመን ያለብን ቃሉን ብቻ ነው፡፡
 
በራዕይ 6 ላይ ያለው አራተኛው የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ ሰማዕታት ከሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ጋር ይነሳሉ፡፡ የቅዱሳን ትንሳኤና ንጥቀትም ይመጣል፡፡
 
አሁን እኛ እየኖርን ያለነው እግዚአብሄር በወሰናቸው ሰባት ዘመኖች በሶስተኛው ዘመን መሆኑን መገንዘባችን ለእኛ አስፈላጊ ነው፡፡ የዛሬው ዘመን የጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ይህንን ስናደርግ አሁኑኑ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ዘሮች መዝራት እንችላለን፡፡ አሁን ዘሮችን በመትከል የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣ መከሩን መሰብሰብ እንችላለን፡፡
 
እግዚአብሄር በፈጠረው የተፈጥሮ ዓለም ውስጥ በሳምንት ውስጥ የሚበቅሉ፣ የሚያብቡና የሚያፈሩ ሰብሎች አሉ፡፡ የሐመሩ ፈረስ ዘመን ሲመጣም አሁን እኛ በምንሰብከው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የዳኑ ሰዎች ልክ እንደ እነዚህ የበረሃ ተክሎች ሰማዕት ይሆኑና ጌታ በፈቀደልን ትንሳኤያችንና ንጥቀታችን ውስጥ ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ በመከራው ዘመን ከአሁኑ ይልቅ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመናቸው ሰማዕት የሚሆኑ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡
 
የራዕይ ቃል ማብራሪያውን በሕዝበ እስራኤል ደህንነት አይገድበውም፡፡ የራዕይ ዘመን ለእስራኤሎች ብቻ የተጠበቀ ነው ብሎ የሚያምን ማንኛውም ሰው ከባድ ስህተት እየሰራ ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም የራዕይ ዘመን ሲመጣ በጣም ብዙ አሕዛቦች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ይድኑና እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት ይሆናሉና፡፡ የራዕይ ቃል ዕውቀታቸው ትክክል መሆኑ ወይም አለመሆኑ በእምነታችሁ ላይ ትልቅ ልዩነትን ያመጣል፡፡
 
ስለዚህ የዘመኑ ክርስቲያኖች በቅድመ መከራ ንጥቀት ማመናቸው በአጭሩ ስህተት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳን ሰማዕትነት የሰባቱ ዓመት ታላቅ መከራ አጋማሽ ጥቂት አለፍ እንዳለ መሆኑንና ንጥቀታቸውም ይህ ከሆነ በኋላ ወዲያውኑ እንደሚመጣ ይነግረናል፡፡ የራዕይን ቃል ልክ እንደተጻፈው ምዕራፍ በምዕራፍና ቁጥር በቁጥር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ክልል ውስጥ መፍታት አለብን፡፡ እንዲህ ስናደርግ ትክክል የሆነ የራዕይ ቃል ዕውቀት ይኖረናል፡፡
 
ራዕይ 7 በአሕዛቦች መካከል እጅግ ብዙ ሰዎችም እንደዚሁ በእምነታቸው ደህንነትን ተቀብለው ሰለ እምነታቸው ደህንነትን ተቀብለው ስለ እምነታቸው ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን እንደተጻፈው ማመን አለብን፡፡ እግዚአብሄር በወሰናቸው በሰባቱ ዘመኖች እንጂ በቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብም ሆነ የሺህ ዓመት መንግሥት የለም በሚለው ጽንሰ አሳብ ማመን የለብንም፡፡
 
የራዕይ ቃል ምዕራፍ 1 መግቢያ ነወ፡፡ ምዕራፍ 2 እና 3 የቅዱሳንን ሰማዕትነት ያብራራሉ፡፡ ምዕራፍ 4 ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነና በእግዚአብሄር ዙፋን ላይ እንደተቀመጠ ይነግረናል፡፡ ምዕራፍ 5 እንዴት የእግዚአብሄር አብን ፈቃድ እንደሚፈጽም ያሳየናል፡፡ ምዕራፍ 6 በእግዚአብሄር የታቀደውን የሰባቱን ዘመኖች ጠቅላላ ንድፍ ያቀርባል፡፡ እነዚህ ሁሉ ዕቅዶች በራዕይ ቃል ውስጥ ተፈትተዋል፡፡
 
የራዕይ ቃል ‹‹ከእንግዲህ ወዲያ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብጹዓን ናቸው›› ብሎ እንደሚነግረን ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱሳን የሚኖሩት ትንሳኤንና የሺህ ዓመቱን መንግሥት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡
 
ዮሐንስ ራዕይ 8፡10-11 ሌላ መቅሰፍትን ያብራራል፡- ‹‹ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፡፡ የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፡፡ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፡፡ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡›› እዚህ ላይ በዚህ ወቅት እንደ ችቦ የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ እንደወደቀ ይናገራል፡፡ ይህ እንደ ችቦ የሚቃጠለው ታላቅ ኮከብ ተወርዋሪ ኮከብን የሚያመለክት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሰማያት ሲናወጡ ከዋክብቶች እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ፡፡ ስበርባሪዎቻቸውም በምድር ላይ ይወድቃሉ፡፡
 
ዮሐንስ ራዕይ 8፡12-13 ሌላ መቅሰፍትን በማብራራት ይቀጥላል፡- ‹‹አራተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ የጸሐይ ሲሶና የጨረቃም ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፡፡ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ እንዲሁም የሌሊት፡፡ አየሁም አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምጽ፡- ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምጽ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፣ ወዮላቸው፣ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ፡፡›› ይህም የዓለም ሲሶ ይጨልምና ቀኖች ወደ ምሽቶች እንደሚቀየሩ ይነግረናል፡፡
 
 የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች እንዲህ ሲጀምሩ እናንተና እኔ በእነዚህ ውስጥ መኖራችን በሚገባ የተረጋገጠ ነው፡፡ ሕያዋን ቅዱሳን ግን ፈጥነው ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ በእምነታቸውም ሰይጣንን ያሸንፋሉ፡፡
 
 በራዕይ 6 ውስጥ የተገለጡትን ሰባቱን ዘመኖች በግልጽ ካወቃችሁ በዛሬው ዘመን ምን ማድረግ እንደሚገባችሁና ምን ዓይነት እምነት እንደሚያስፈልጋችሁ ግልጽ የሆነ ዕውቀት ይኖራችኋል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በራዕይ ዘመን ሰማዕት ስለሚሆኑ ይህንን ዘመን መጋፈጥ ያለባቸው የእግዚአብሄርን መንግሥት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ቅዱሳኖች በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ በመጨረሻው ዘመን በእምነታቸው ለሰማዕትነታቸው መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ይህንን እምነት በማሰራጨትም የእግዚአብሄርን መንግሥት ለማስፋፋት ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡
 
 እግዚአብሄር የወሰናቸውን ሰባቱን ዘመኖች አውቃችሁ ታምኑባቸዋላችሁን? አሁን እየኖርን ያለነው በጉራቻው (ጥቁሩ) ፈረስ ዘመን ላይ እንደሆነ መረዳት ትችላላችሁን? አሁን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የማታውቁም ሆነ የማታምኑ ከሆናችሁ በምድር ላይ ከሚመጡት መከራዎች ማምለጥ አትችሉም፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ መዘጋጀት አለባችሁ፡፡ መከራዎችን የሚያሸንፍ እምነት ሊኖራችሁ እንዲችል በመጀመሪያ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ስርየትን ማግኘትና መንፈስ ቅዱስን ስጦታ አድርጋችሁ በመቀበል በሺህው ዓመት መንግሥት ውስጥ ገብታችሁ ለመኖር መዘጋጀት አለባችሁ፡፡
 
አሁኑኑ ተዘጋጁ፡፡ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በሚመጡበት ጊዜ ብቻ ለማመን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለማስተላለፍ አቅዳችሁ ከሆነ ብዙ መከራዎች ይገጥሙዋችኋል፡፡ የእግዚአብሄር ሕዝብ ሆናችሁ ዳግመኛ ለመወለድና ለወደፊቱ ለመዘጋጀት በዚህች ቅጽበት በውሃውና መንፈሱ ወንጌል ታምኑ ዘንድ ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡
እግዚአብሄር የወሰናቸው ሰባቱ ዘመኖች፡-
 
1.    አምባላይ (ነጭ) ፈረስ፡- የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ጅማሬና ቀጣይነት
2.    ዳማ (ቀይ) ፈረስ፡- በሰይጣን ዘመን መምጣት የሰላም መጥፋት ዘመን
3.    ጉራቻ (ጥቁር) ፈረስ፡- የሥጋዊና የመንፈሳዊ ረሃብ ዘመን ማለትም የአሁኑ ዘመን
4.    ሐመር ፈረስ፡- በጸረ ክርስቶስ መምጣት ቅዱሳኖች ሰማዕት የሚሆኑበት ዘመን
5.    የቅዱሳን ትንሳኤና ንጥቀት እንደዚሁም የበጉ ሰርግ እራት ዘመን
6.    የመጀመሪያው ዓለም የሚጠፋበት ዘመን
7.    ጌታና ቅዱሳኖች የነገሱበት የሺህው ዓመት መንግሥትና የአዲስ ሰማይና ምድር ዘመን
 
እግዚአብሄር የወሰናቸው ሰባቱ ዘመኖች እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህን ዘመኖች በግልጽ የሚያውቁና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች በመጨረሻው ዘመን ለመኖር እምነታቸውን ያዘጋጁ ሰዎች ናቸው፡፡ እናንተም ደግሞ እግዚአብሄር የወሰናቸውን እነዚህን የእውነተኛ እምነት ዘመኖች ለይታችሁ ማወቅ እንድትችሉ ተስፋዬም ጸሎቴም ነው፡፡