Search

Bài giảng

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-31] የሊቀ ካህኑን ልብሰ ተክህኖ ለመሥራት ጥቅም ላይ የዋሉት ጥሬ ዕቃዎች፡፡ ‹‹ዘጸዓት 28፡1-14››

የሊቀ ካህኑን ልብሰ ተክህኖ ለመሥራት ጥቅም ላይ የዋሉት ጥሬ ዕቃዎች፡፡
‹‹ዘጸዓት 28፡1-14›› 
‹‹አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፡፡ አሮንን፣ የአሮንንም ልጆች ናዳብን፣ አብዩድንም፣ አልዓዛርንም፣ ኢታምርንም አቅርብ፡፡ የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት፡፡ አንተም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር፡፡ የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፣ ኤፉድም፣ ቀሚስም፣ ዝንጉርጉር ሸሚዝም፣ መጠምጠሚያም፣ መታጠቂያም፡፡ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ፡፡ ወርቅንም፣ ሰማያዊና ሐምራዊ፣ ቀይም ግምጃ፣ ጥሩም በፍታ ይወስዱ፡፡ ኤፌዱንም በብልሃት የተሠራ በወርቅና በሰማያዊ፣ በሐምራዊውም፣ በቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ያድርጉ፡፡ ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን፡፡ በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉድ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ግምጃም፣ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን፡፡ ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላው ቅረጽ፡፡ በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማህተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ፤ በወርቅም ፈርጥ አድርግ፡፡ የእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቁዎች በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሄር ፊት ይሸከማል፡፡ የወርቅም ፈርጦች ሁለትም ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጎነጎነም ገመድ አድርግ፤ የተጎነጎኑትንም ድሪዎች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል፡፡›› 


አሁን ትኩረታችን የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖዎች ሲሠሩ ጥቅም ላይ ወደዋሉት ጥሬ ዕቃዎች እናድርግ፡፡ ኤፉድ ሊቀ ካህኑ ከሚለብሳቸው ልብሶች መካከል የተለየ ልብስ ነበር፡፡ ይህ ኤፉድ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበር፡፡ ይህ የሊቀ ካህኑ የተቀደሰ ልብስ እነዚህን አምስት ማጎች በጥልፍ አሠራር በሚሠራ ባለሙያ የተሠራ ነበር፡፡
እዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው የወርቅ ድሪ ስለ እውነተኛው እምነት ይነገራል፡፡ ለሊቀ ካህኑ ልብሶች ጥቅም ላይ የዋለው ሰማያዊ ማግ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ለመውሰድ ከአጥማቂው ዮሐንስ ሊቀበለው የነበረውን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ (ማቴዎስ 3፡15) ሐምራዊው ማግ ስለ ነገሥታት ንጉሥ ይናገራል፡፡ ቀዩ ማግም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ኩነኔ በተሸከመ ጊዜ ስለከፈለው መሥዋዕትነት ይናገራል፡፡ ለሊቀ ካህኑ ልብሶች ጥቅም ላይ የዋለው ነጩ በፍታ የእያንዳንዱን ሰው ሐጢያቶች በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የደመሰሰውን የእግዚአብሄር ጽድቅ ይገልጣል፡፡
ከሊቀ ካህናቱ ተግባራቶች መካከል እጅግ አስፈላጊው ለእግዚአብሄር መሥዋዕቶችን የማቅረብ ተግባር ነበር፡፡ ሊቀ ካህኑ በመሥዋዕቱ ስርዓት መሠረት ይህንን መሥዋዕቶችን ለእግዚአብሄር የማቅረብ ተግባር በመፈጸም የሚያገለግለው እግዚአብሄርን ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ከሐጢያቶቻቸው እንዲድኑም ያግዛቸዋል፡፡ ከሊቀ ካህኑ ተግባራቶች ሁሉ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እግዚአብሄርን ለማገልገልና ለማምለክ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ነበር፡፡
ይህንን ነጥብ ለማስረገጥ በዘጸዓት 32 ውስጥ የተነገረውን አንድ ታሪክ ላስታውሳችሁ፡፡ ሙሴ አስርቱን ትዕዛዛት ለመቀበል ወደ ሲና ተራራ በወጣ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ከተራራው ሳይወርድ እንደዘገየ አይተው አሮንን እንዲህ አሉት፡- ‹‹ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅምና ተነስተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፡፡›› (ዘጸዓት 32፡1) አሮንም ከእስራኤሎች የወርቅ አምባሮችን፣ ጉትቾችንና ቀለበቶችን ወስዶ ጥጃ ሠራላቸው፡፡ ያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አለ፡- ‹‹እስራኤል ሆይ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው፡፡›› (ዘጸዓት 32፡4) አሮንም ይህንን አይቶ በጥጃው ፊት መሠውያን በመሥራት ቀጣዩን ቀን ለየሆዋ አምላክ የበዓል ቀን አድርጎ አወጀ፡፡
በቀጣዩ ቀን የእስራኤል ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕትና የደህንነት መሥዋዕት አቀረቡ፡፡ ከዚያም ተቀምጠው በሉ፤ ጠጡም፤ ሊዘፍኑም ተነሡ፡፡ ይህ በእግዚአብሄር ፊት ታላቅ ሐጢያት ሆነና የእስራኤል ሕዝብ የእርሱን የፍርድ ቁጣ ተጋፈጡ፡፡ ይህንን ኩነት በአእምሮዋችን መያዝ አለብን፡፡ ሊቀ ካህኑ አሮን ደካማ ጎን ነበረው፡፡ ይህም ቢሆን ሊቀ ካህን እንደመሆኑ ለእርሱ እግዚአብሄርን ማገልገል እጅግ አስፈላጊ ተግባሩ መሆኑን ሳይረሳ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መታዘዝ ነበረበት፡፡ አሮን ግን ሊቀ ካህን ሆኖ ማከናወን የሚገባውን ተግባራት በመፈጸም ረገድ ታማኝ መሆን ተሳነው፡፡ እርሱ የሊቀ ካህንን ተግባራቶች ለመፈጸም ሕዝቡ ቢከተለውም ባይከተለውም በእግዚአብሄር በተመሠረተው የመሥዋዕት ስርዓት መሠረት የሚቃጠል መሥዋዕትና የደህንነት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረበት፡፡
በአጭሩ ሊቀ ካህኑ አሮን ማገልገል የነበረበት እግዚአብሄርን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ መጋቢዎች የሚያገለግሉት እግዚአብሄርን ሳይሆን ሰዎችን ነው፡፡ ብዙዎቹ የዘመኑ ካህናት እንዲህ ያሉ የተዛቡ እሳቤዎችን መቀበላቸውን ሳስብ በጣም አዝናለሁ፡፡ ነገር ግን ክፉኛ አልጨነቅም፡፡ ምክንያቱም በእነርሱ መካከል አሁንም ድረስ ትክክለኛ ካህናት ይገኛሉና፡፡ ካህናት የሕዝቡን ሐጢያቶች ለማስተሰረይ በመሥዋዕቱ ሥርዓት መሠረት ለእግዚአብሄር መሥዋዕቶችን በትክክል የማቅረብን ሐላፊነት መፈጸም አለባቸው፡፡
እግዚአብሄር ለሙሴ እንዲህ ሲል የተናገረበትን ምንባብ ለየት ያለ ትኩረት ልንሰጠው ይገባናል፡፡ ‹‹አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፡፡ አሮንን፣ የአሮንን ልጆች ናዳብን፣ አብዩድንም፣ አልዓዛርንም፣ ኢታምርንም አቅርብ፡፡›› (ዘጸዓት 28፡1) አሮን እግዚአብሄርን በመጀመሪያና በቅድሚያ ያገለግል ዘንድ እግዚአብሄር በተለየ መንገድ የተሠራውን የሊቀ ካህን ልብሰ ተክህኖ አለበሰው፡፡ ዛሬ የሚያገለግል እያንዳንዱ ካህን ይህንን መርሳት የለበትም፡፡ የሊቀ ካህኑ ልብሰ ተክህኖ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ፡፡
 


የሊቀ ካህኑን ተግባራቶች ለመፈጸም፡፡


በስርየት ቀን ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ የእስራኤሎችን ሐጢያቶች ለማስወገድ እጆቹን በራሱ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ ወደ መሥዋእቱ እንስሳ አሻግሮ ደሙን ያፈስሰዋል፡፡ ከዚያም በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ በስርየት መክደኛው ላይም ይረጨዋል፡፡ ልክ እንደዚሁ እውነተኛው የሰማይ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ የሰውን ዘር ሐጢያቶች የወሰደበትን ጥምቀት ተቀበለ፡፡ ደሙን አፍስሶ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነስቶ ለሚያምኑት የደህንነትን ድል አቀዳጃቸው፡፡
አሮን ሊቀ ካህን ሆኖ እግዚአብሄርን ሲያገልግል ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠራውንና ‹‹ኤፉድ›› ተብሎ የሚጠራውን ልብስ መልበስ ነበረበት፡፡ እግዚአብሄር በዚህ የሊቀ ካህኑ ልብስ የሐጢያትን ስርየት ለማግኘት እንደምን መሥዋዕቶቻችንን ማቅረብ እንደሚገባን እያስተማረን ነው፡፡ የሊቀ ካህኑ ልብሶች በተሠሩባቸው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ውስጥ ያለው ጥልቅ ትርጉም ለመረዳት በእግዚአብሄር ጽድቅና በፍቅሩ የተፈጸመውን የሐጢያቶች ስርየት ማወቅ አለብን፡፡
ለሊቀ ካህኑ ልብሶች ጥቅም ላይ በዋሉት በአምስቱ ማጎች አማካይነት እግዚአብሄር ከዓለም ፍጥረት በፊት ዘላለማዊው የሐጢየት ስርየት በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተመሠረተ አሳይቶናል፡፡ (ኤፌሶን 1፡4) ስለዚህ እኛ የካህናትን ተግባሮች በሚገባ ለማከናወን በመጀመሪያ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ውስጥ ያለውን የሐጢያት መወገድ ምስጢር መረዳትና በእርሱም ማመን አለብን፡፡ ይህ እግዚአብሄር አብ በክርስቶስ የመሠረተው ቀደምት የደህንነት ዕቅድ ነው፡፡
ሊቀ ካህኑ ክህነታዊ ተግባራቶቹን በሚገባ ለመፈጸም በተገቢው መንገድ ለእግዚአብሄር መሥዋዕቶችን ማቅረብ ነበረበት፡፡ ያም ማለት የሕዝቡን ሐጢያቶች ለማስተሰረይ እጆቹን በመሥዋዕቱ እንስሳ ራስ ላይ መጫንና በመሥዋዕቱ ስርዓት መሠረት በትክክለኛው መንገድ ሐጢያቶቻቸውን ወደ እንስሳው ማሻገር ነበረበት፡፡ ሊቀ ካህኑ በስርየት ቀን እጆቹን በመሥዋዕቱ እንስሳ ራስ ላይ ይጭንና ጉሮሮውን በመቁረጥ ደሙን ያፈስሰዋል፡፡ በዚህ እጆች መጫን እስራኤሎች ዓመቱን ሙሉ የሠሩዋቸው ሐጢያቶች በሙሉ ወደ መሥዋዕቱ ይሻገራሉ፡፡ በሚፈስሰው ደሙም ሐጢያቶቻቸው ሁሉ ስርየትን ያገኛሉ፡፡ ከዚያም ይህ መሥዋዕት ይጠናቀቅ ዘንድ ደሙን ይረጨዋል፡፡ ስጋውንም ያቃጥለዋል፡፡
በዚህ ነጥብ ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ ሊቀ ካህኑ የመሥዋዕቱ እንስሳ በእሳት ከመቃጠሉ በፊት ሐጢያቶቻቸው ቀደም ብለው ወደ እንስሳው እንደተሻገሩና የሐጢያቶቻቸው ስርየትም በእጆች መጫንና በእንስሳው ደም መፍሰስ አማካይነት መፈጸሙን ለሕዝቡ ማስተማር ነበረበት፡፡ የእያንዳንዱ ሊቀ ካህን እጅግ ትልቁ ተግባር ይህ ነበር፡፡ ሊቀ ካህኑ ለእውነት መቆም የነበረበት ሰው ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ታማኝ ሞግዚት መሆን ነበረበት፡፡ ምንም እንኳን ሊቀ ካህኑ እንደ ማንኛውም ተራ የእስራኤል ሕዝብ ደካማ ሰብዓዊ ፍጡር ቢሆንም በመሥዋዕቱ ስርዓት ውስጥ በተገለጠው እውነት በማመንና እነርሱን ወክሎ ለእግዚአብሄር መሥዋዕቶችን በማቅረብ ሕዝቡ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያገኙ ዘንድ አስችሎዋቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም ደካማ ፍጡራን ብንሆንም የሰማይ ሊቀ ካህን ለእኛ ባደረገው ነገር በማመንና የሐጢያቶቻችንን ስርየት በመቀበል ከእግዚአብሄር ጋር መመላለስ እንችላለን፡፡
በመገናኛው ድንኳን ስርዓት ውስጥ የተገለጠው ይህ የመሥዋዕት ስርዓት ከእግዚአብሄር የመጣ የደህንነት ጥበብ ነው፡፡ እኛን ከሐጢያት ያዳነን የእግዚአብሄር ጥበብ የሊቀ ካህኑ ልብሶች በተሠሩበት በወርቁ፣ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ውስጥ ተካቷል፡፡ ሊቀ ካህኑ ተግባሮቹን በስኬት ለማጠናቀቅ የሰውን ዘር ሐጢያት አልባ ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ እግዚአብሄር የመሠረተው የመሥዋዕት ስርዓት መሆኑን ማስተማር አለበት፡፡ እኛ የዘመኑ የንጉሥ ካህናት ስለሆንን (1ኛ ጴጥሮስ 2፡9) ሁልጊዜም ኢየሱስ ወደዚህ መጥቶ በጥምቀቱ የዓለምን ሐጢያቶች ለአንዴና ለመጨረሻ እንደወሰደ፣ ደሙን እንዳፈሰሰና በእኛ ፋንታም እንደሞተ፣ እንደተቀበረና ዳግመኛም ከሙታን እንደተነሳ እውነቱን መመስከር አለብን፡፡
ሰብዓዊ ፍጡራን የራሳቸውን ሐጢያቶች መደምሰስ ይችላሉን? የዚህ ዓለም ሐይማኖቶች የሰውን ዘር ሐጢያቶች ማስወገድ ይችላሉን? ሐጢያቶቻችን መወገድ የሚችሉት ሊቀ ካህኑ ባስተማረን የኢየሱስ ጥምቀትና ደሙ ባዋቀሩት የደህንነት እውነት ብቻ ነው፡፡ የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስርየት መቀበል የምንችለው በእግዚአብሄር በተመሠረተው የደህንነት ወንጌል ብቻ ነው፡፡ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ማስወገድ የሚችለው የሰማዩ ዘላለማዊ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነወ፡፡ በሌላ አነጋገር ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ስጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣቱና በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠምቆ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰዱ የእኛን የሐጢያተኞቹን ሐጢያቶች በሙሉ ለማስወገድ በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ ጌታ በመስቀል ላይ በመሰቀል፣ ደሙን በማፍሰስና በመስቀል ላይ በመሞት የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ኩነኔ የተሸከመው ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ ስለወሰደ ነው፡፡ በዚህ የጽድቅ ድርጊትም የሰውን ዘር ከሐጢያት የማዳን ሥራውን አጠናቀቀ፡፡ (ሮሜ 5፡18) ኢየሱስ ስለ እኛ በፈጸመው ሥራ ባይሆን ኖሮ ፈጽሞ መዳን ባልቻልንም ነበር፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ፈጽሞ በመደምሰስ የቅዱስ አምላክ ልጆች ያደረገን ይህ የሰማይ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
የሰማዩ መንፈሳዊ ሊቀ ካህን አስቀድሞ ለሐጢያቶቻችን ስርየት ስለተወሰነው የአብ ዕቅድ ሁሉ ያውቅ ነበር፡፡ ጌታ እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡- ‹‹እኔ አልፋና ዖሜጋ፣ መጀመሪያውና መጨረሻው፣ ፊተኛውና ኋለኛው ነኝ፡፡›› (ዮሐንስ ራዕይ 22፡13) ጌታ የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን በሚገባ ስለሚያውቅ በመሥዋዕቱ ስርዓት ውስጥ በተገለጡት ተስፋዎች መሠረት ደህንነታችንን ፈጸመ፡፡ በሐጢያቶቻችንና በድካሞቻችን ፈጽሞ እንዳንኮነንና እንዳንጠፋም አስችሎናል፡፡ የሰማዩ ሊቀ ካህን በጥምቀቱ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በመውሰድና ደሙን አፍስሶ በመደምሰስ ስለ እኛ ፍጹም የሆነውን ደህንነት ፈጸመ፡፡ የእግዚአብሄር ጥበብ ሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው የሚድኑበትን ደህንነት አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ይህም በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ተፈጽሞዋል፡፡ እግዚአብሄር አብ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ውስጥ በተገለጠው እውነት አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊውን የሐጢያቶች ስርየት አቀደ፡፡ በዚህ እውነት የሚያምኑ ምዕመናን ሁሉም ይህንን ፍጹም ደህንነት እንዲቀበሉ ፈቀደላቸው፡፡
 


የሊቀ ካህኑ የኤፉድ መታጠቂያ፡፡ 


ከሊቀ ካህኑ ልብሶች መካከል የኤፉድ መታጠቂያ ይገኝበታል፡፡ ሊቀ ካህኑ ኤፉዱን ለመታጠቅ በወገቡ ላይ የሚያደርገው ይህ መታጠቂያ የተሠራው ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ነበር፡፡ መታጠቂያ ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ‹‹ብርታትን›› ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በመጣው ደህንነት የሚያምነው እምነት እኛን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የማዳን ሐይል እንዳለው ይነግረናል፡፡ የሚያምነውን ሰው ሁሉ የሚያድነው የእግዚአብሄር ሐይል ይህ እውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ (ሮሜ 1፡16) ስለዚህ እዚህ ላይ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ከተገለጠው ውጭ በሌላ በማናቸውም አስመሳይ ወንጌሎች ማመን ከንቱ ልምምድ ነው፡፡
ብዙ ጉድለቶች ያሉባቸውም እንደዚሁ ጌታ በሰጠው በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ፈጽመው ከሐጢያቶቻቸው መንጻት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ በእግዚአብሄር በተፈጸመው በዚህ የሐጢያቶች ስርየት እውነት ወደ ኢየሱስ ተሻግረዋልና፡፡ (ማቴዎስ 3፡15፤ ዘሌዋውያን 16፡1-22) ስለዚህ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጡት እነዚህ የኢየሱስ የጽድቅ ሥራዎች እንዳዳኑዋቸው የሚያምኑ ሰዎች የስጋቸው የፈቃድ ሐይል ደካማም ቢሆን እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሰማዩ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስንኖር ከእግዚአብሄር ፍቅር ማን ሊለየን ይችላል? በእግዚአብሄር ደህንነት ላይ ያለን እምነት የተፈጸመው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው እውነት በሚያምነው እምነታችን ነው፡፡
ካህናት ክህነታዊ ተግባሮቻቸውን ሲያከናውኑ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በግልጥ የተብራራውን የመሥዋዕቱን ስርዓት የማይታዘዙ ማናቸውንም የሐሰት ወንጌሎች መታገስ የለባቸውም፡፡ እነዚህን አስመሳይ ወንጌሎች የሚሰብኩ ሰዎች ስብከቶቻቸውን ምንም ያህል አፍ በሚያስከፍት መንገድ ቢያቀርቡም ማንንም መርዳት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሄርን እውነተኛ የውሃና የመንፈስ ወንጌል እየመሰከሩ አይደሉምና፡፡ ስለዚህ አጭበርባሪዎችና ደሞዝተኞች ናቸው፡፡ የሰማዩን ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን ማመንን በሚመለከት በመገናኛው ድንኳን ስርዓት ውስጥ የተገለጠውን እጆችን የመጫንና ደምን የማፍሰስ የመሥዋዕት ስርዓት ከመቀበል መጉደል የለብንም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ አስመሳይ ወንጌሎች እንዳሉ መረዳት አለብን፡፡ ሰባኪው ማንም ይሁን የሚሰብከው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሆነ ልናዳምጠውና ትምህርቶቹን ሁሉ ልንቀበል ይገባናል፡፡
ኤፉዱና መታጠቂያው የተሠሩበት አምስቱ ጥሬ ዕቃዎች እውነተኛ ደህንነታችንን ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር በሰጠው የመሥዋዕት ስርዓት መሠረት በትክክል ሲቀርብ ለሐጢያተኞች የሐጢያት ስርየትን በሚያመጣው የመሥዋዕት እንስሳ የተገለጡ ጥሬ ዕቃዎች ናቸው፡፡ ይህም በዋናነት እጆችን መጫንና ደምን ማፍሰስን ያካትታል፡፡ እነዚህ ጥሬ ዕቃዎች ውለው አድረው በአዲስ ኪዳን ውስጥ በኢየሱስ ጥምቀትና ባፈሰሰው ደሙ ራሳቸውን ገልጠዋል፡፡ በዚህ ኢየሱስ ለሚያምኑ የሐጢያቶችን ስርየት ሰጠ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከልቡ የሚያምን ሁሉ የሐጢያቶች ስርየትና የዘላለም ሕይወት ይቀበላል፡፡ ይህ እውነት የዘመኑ ሊቀ ካህን ተግባራቶች በአደራ ለተሰጣቸውና በትክክል ዳግመኛ ለተወለዱ ሁሉ ተነግሮዋል፡፡
ምድራዊው ሊቀ ካህን እጆቹን በመሥዋዕቱ እንስሳ ራስ ላይ በመጫን የሕዝቡን ሐጢያቶች አሻገረ፡፡ ከዚያም ጉሮሮውን ቆርጦ ደሙን አፈሰሰ፡፡ ደሙንም በስርየት መክደኛው ላይ ረጨው፡፡ በዚህም በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛውን ወንጌል የመደገፉን ክህነታዊ ሐላፊነቶች ፈጸመ፡፡ የሰማዩ ሊቀ ካህን ግን የዓለምን ሐጢያቶች በስጋው ለመውሰድ ተጠመቀ፡፡ ስጋውን አሳልፎ በመስጠት፣ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስና ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት የሕዝቡን ሐጢያቶች በሙሉ ደመሰሰ፡፡ እንዲህ በማድረጉም ሕዝቡ ከሐጢያቶቻቸው እንዲነጹ አስቻላቸው፡፡ የእግዚአብሄርንም ፈቃድ ፈጸመ፡፡ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ የሚያስወግደው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህንን ወንጌል ሲያራጩና ክህነታዊ ተግባሮቻቸውን በስኬት ሲያከናውኑ ነው፡፡
ዛሬ ክርስትና በብዙ ችግሮች ከተተበተበባቸው ምክንያቶች አንዱ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሳያውቁ ክህነታዊ ተግባሮቻቸውን በሚገባ እየፈጸሙ እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ መንፈሳዊ አጭበርባሪዎች በውስጡ ስላሉ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛ ካህናት የመሆኛው መንገድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማመን ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ተገቢውን የሐጢያት መሥዋዕቶች ማቅረብና ሌሎችን ከልባቸው መውደድ የሚችሉት ይህ እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የተቋቋመችው ለምንድነው ብላችሁ ታስባላችሁ? የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የተቋቋመችው የውሃውንና የመንፈሱ ወንጌል ለሐጢያተኞች ለማሰራጨት ነው እላለሁ፡፡ እግዚአብሄርን የምናገለግለውና በእርሱ አምሳል የተፈጠሩትን ነፍሳቶች ሁሉ የምንወደው በዚህ መንገድ ነው፡፡
 


በዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወቅ አለበት፡፡


በመላው ዓለም ያለው የዘመኑ ክርስትና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማመን አለበት፡፡ ጌታችን እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፡፡…እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡›› (ማቴዎስ 5፡13-14) እኛ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምናምን ሰዎች የዓለም እውነተኛ ብርሃንና መንፈሳዊ ጨው ነን፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚያውቁና የሚያምኑ ሰዎችን የሚጠቅሙና የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እንዲቀበሉ የሚያስቸሉዋቸው መንፈሳዊ ካህናት ናቸው፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል ይህንን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንኳን ሳያውቁ ክህነታዊ ተግባሮቻቸውን እየፈጸሙ እንደሆኑ የሚናገሩ መጋቢዎች ከደመወዝተኛነት የዘለሉ አይደሉም፡፡ ደመወዝን ለማግኘት ብቻ ክህነታዊ ተግባሮቻቸውን የሚያከናውኑ ሰዎችን የስም ክርስቲያኖች ሊያደርጉዋቸው ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተከታዮቻቸው ሁሉ ውስጥ የሚገኙትን ሐጢያቶች ማስወገድ አይችሉም፡፡
እውነተኛ ካህናት ሐጢያቶቻቸው ስርየትን ያገኙ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት አልባ ሆነው የቆሙ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር እያንዳንዱን ሰው ከሐጢያቶቹ ሁሉ ሊያነጻው የቻለው ክህነታዊ ተግባራቱን በመሥጠትና የሕዝቡን ሐጢያቶች በሙሉ የሚያነጻውን ሕጋዊ መሥዋዕት እንዲያቀርብ በማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰው ዘር የእርሱን የደህንነት ሥራዎች እንዲያውቅ፣ በእነዚህ ሥራዎችም እንዲያምንና ወደ እርሱ ተመልሶ የጽድቅ ሕይወትን እንዲኖር የሚያስችለው በእነዚህ ካህናቶች ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውንና የቀዩን ማግ ምስጢር እንዲገነዘብና ይህንን እውነት እንዲያሰራጭ የማድረግ ሐላፊነትና ተግባር ያለባቸው ካህናቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊው ክህነትም እንደ ውሃውና እንደ መንፈሱ ወንጌል በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
እግዚአብሄር መንፈሳዊ ክህነታችንን ሐይል በተሞላበት ሁኔታ መፈጸም እንችል ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ቃለ ወንጌል ሰጥቶናል፡፡ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው እውነተኛ ወንጌል የሚያምነውን ይህንን እምነት (የወርቅ ድሪ) ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ ሊቀ ካህኑ የሚለብሳቸውን ልብሰ ተክህኖዎች በምናጠናበት ጊዜ የሰው ዘር የሐጢያት ስርየት እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ መረዳት እንችላለን፡፡ የሊቀ ካህኑን ልብሰ ተክህኖዎች በጥልቀት ስንመረምር የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በሚገባ ግልጥ ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ዘር ከሐጢያቶቹ ያዳነው ውሸታሞች ባሰራጩት አስመሳይ ወንጌሎች አይደሉም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከሐጢያት ለማዳን ያቀደው ከዓለም ፍጥረት በፊት ነው፡፡ ይህንን ዕቅድም በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ባፈሰሰው ደሙ በትክክል ፈጸመው፡፡
ሊቀ ካህናቱ ከሚለብሱዋቸው ልብሶች መካከል በጥልፍ ጥበብ የተሠሩ ሸሚዞችና የበፍታ ሱሪዎች ይገኙበታል፡፡ እኛም ብንሆን የውስጥ ሱሪዎችን እንለብሳለን፡፡ ነገር ግን እነዚህ የሊቀ ካህኑ ልብሶች እኛ ከምንለብሳቸው የውስጥ ሱሪዎች የተለዩ ነበሩ፡፡ የሊቀ ካህኑ ሸሚዝ እስከ ጉልበት የሚደርስ ረጅም ልብስ ነበር፡፡ ከጥሩ የበፍታ ማግ የተሠራ ስለሆነም በቀላሉ አየር ያስገባ ነበር፡፡ ካህናት የሚቃጠል መሥዋዕቶችን ሲያቀርቡ የመሥዋቶቹን ብልቶች ወደሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ በማምጣት ያቀጥሉዋቸው ነበር፡፡ ይህ መሠውያ በአንጻራዊ መልኩ ከፍ ያለ ስለነበር ወደሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ በሚቀርቡበት ጊዜ የካህናቱ ሐፍረተ ስጋዎች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ሙሴን ሐጢያት ሆኖባቸው እንዳይሞቱ የሊቀ ካህኑን ሐፍረተ ስጋ በሚገባ የሚሸፍኑ ሸሚዝና የበፍታ ሱሪዎችን እንዲሠራ አዘዘው፡፡
 የሊቀ ካህኑ ልብሶች ምን ያህል ያማሩ ነበሩ? በደረቱ ላይ የሚደረገው የደረት ኪስ በአሥራ ሁለት የከበሩ ድንጋዮች ያብረቀርቅ ነበር፡፡ በጫንቃው ላይ ያሉት ማሠሪያዎችም እንደዚሁ የከበሩ ድንጋዮች ነበሩባቸው፡፡ የደረቱ ኪስ ልክ እንደተጎነጎነ ድሪ ከንጹህ ወርቅ በተሠሩ ሁለት ፈርጦች ከጫንቃው ማሠሪያዎች ጋር ይያያዛሉ፡፡ ከኤፉዱ እንዳይለያይም ከኤፉዱ ማሠሪያ ጋር ይታሰራል፡፡ ስለዚህ ሊቀ ካህኑ ሲንቀሳቀስ እነዚህ ከንጹህ ወርቅ የተሠሩት የተጎነጎኑት ድሪዎች ወደፊትና ወደ ኋላ እየተወዛወዙ ያብረቀርቃሉ፡፡ ከዚህም በላይ በፍርዱ ደረት ኪስ ላይ ያሉት አስራ ሁለቱ የከበሩ ድንጋዮችም እንደዚሁ ያብረቀርቃሉ፡፡ በሁለቱ የጫንቃ ማሠሪያዎች ላይ ያሉት ሁለቱ ትላልቅ የከበሩ ድንጋዮችም እንደዚሁ ያብረቀርቃሉ፡፡ ከጥሩ በፍታ የተሠራው መጠምጠሚያ የተደረገበት ራስም በወርቁ ምልክት እንደ ወርቅ ያብረቀርቃል፡፡
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ምን ያህል ወርቅ ነበር? ሳንቆቹ ሁሉ በወርቅ የለበጡ ነበሩ፡፡ የስርየት መክደኛው፣ መቅረዙ፣ የሕብስቱ ገበታና እንደዚህ ያሉት ብዙዎቹ የቅድስቱ ስፍራ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፡፡ የመገናኛው ድንኳን በአጭሩ ዕጹብ ድንቅ ነበር፡፡ ልክ እንደዚሁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት ስንገባ ይህ ግዛት ምን ያህል ያማረ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ የመገናኛው ድንኳን ከውጭ ሲታይ ያን ያህል ማራኪ ላይመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ የመገናኛው ድንኳን ላይ የፈሰሰውን የወርቅ መጠን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው የዚህ ወርቅ ጠቅላላ መጠን ከአንድ ቶን በላይ እንደሆነ ያውቃል፡፡ በመገናኛው ድንኳን ላይ የፈሰሰው ጠቅላላ ወርቅ ሃያ ዘጠኝ መክሊትና ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበር፡፡ (ዘጸዓት 38፡24) ይህንን በዛሬው መለኪያ ስናሰላ ከአንድ ቶን በላይ ወይም እዚያ አካባቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አንድ መክሊት ወይም ኪካር (= 3,000 ሰቅል) 42 ኪሎ ግራም ይመዝናልና፡፡
ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠሩትን የእምነት ልብሶች አዘጋጅታችኋልን? እዚህ ላይ የወርቁ ድሪ እምነትን ያመለክታል፡፡ ሰማያዊው ማግ ኢየሱስ የተቀበለውን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ሐምራዊው ማግ ኢየሱስ ራሱ አምላክ የመሆኑን መለኮታዊነት ያመለክታል፡፡ ቀዩ ማግ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰዱ ክቡር ደሙን በመስቀል ላይ ማፍሰስ እንደነበረበት ይነግረናል፡፡ ጥሩው በፍታ ደግሞ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ስለሚገልጠው የእግዚአብሄር ቃል ይናገራል፡፡ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በርና በሊቀ ካህኑ ልብሶች ላይ ጥቅም ላይ የዋሉት ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ እግዚአብሄር ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደደመሰሰ ይነግሩናል፡፡
 

 
ይህንን እውነት አምነን በእግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ስርየት መቀበል እንችላለን፡፡ 


በእግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ በሊቀ ካህኑ ልብሶችና እንደዚሁም በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር በተገለጡት ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ጥሩ በፍታ ውስጥ ያለውን የደህንነት እውነት የሚያምን እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሊቀ ካህኑ በስርየት ቀን መሥዋዕቱን ሲያቀርብ በመሥዋዕቱ እንስሳ ራስ ላይ እጆቹን መጫንና ጉሮሮውን ቆርጦ ደሙን ማፍሰስ ነበረበት፡፡ በዚህ እጆችን መጫን የሕዝቡ ሐጢያቶች በሙሉ ወደዚያ የመሥዋዕት እንስሳ ይሻገራሉ፡፡ በዚህ የደም መፍሰስም እነዚያ ሐጢያቶች በሙሉ ይወገዳሉ፡፡ ይህ እምነት የሌለው ሰው ወደ እግዚአብሄር መቅረብ አይችልም፡፡ ያለዚህ እምነት ለእግዚአብሄር መሥዋዕቶችን ለማቅረብ መሞከር ፈጽሞ ኩሸት ነው፡፡ የመሥዋዕቱ ስርዓትና የመገናኛው ድንኳን ቁሳ ቁሶች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሚያምነው እምነት ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ ሊቀ ካህኑ በእግዚአብሄር ፊት መቅረብ የሚችለውና ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ የሚደመስሱትን መሥዋዕቶች በማቅረብ ለሕዝቡ ክህነታዊ ተግባራቶቹን የሚፈጽመው እግዚአብሄር በተናገረው ቃል ላይ ባለው እምነቱ ነው፡፡
ታዲያ እምነታችን እንዴት ነው? በዚህ ዘመን ይህንን እውነት አውቀን በማመን በእግዚአብሄር ፊት የምንኖር እናንተ እኔ የንጉሥ ካህናት ነን፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 2፡9) እምነታችሁ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በተገለጠው የመሥዋዕት ስርዓት ከሚያምነው እምነት ጋር ተመሳሳይ ነውን? እውነተኛው እምነት በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተነገረው እውነተኛ ወንጌል የሚያምን እምነት መሆን አለበት፡፡ ውጫዊ የሆኑት የእምነት ገጽታዎች በየጊዜው ሊለዋወጡ ይችላሉ፡፡ የእውነተኛ እምነት ይዘት ግን ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሄር ማረጋገጫን የሰጣቸው ካህናት በመሥዋዕቱ ስርዓት መሠረት መሥዋዕቶቹን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ኤፉዱ ‹‹በጥልፍ ሥራ የተሠራ›› ነው ሲል ጥርት ብሎ የተጠለፈ የጥልፍ ሥራ ነው ማለቱ ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ ከአምስቱ ዝርዝር ማጎች አንዱም ያጎደለበትንና ሙሉ በሙሉ በጥልፍ ሥራ የተሠራውን ኤፉድ መልበስ ነበረበት፡፡ ካህናት የሆኑ ሰዎች በቅድሚያ ቅድስናን ለብሰው በእግዚአብሄር ፊት የሚቀርቡና ለሌሎች የሐጢያቶችን ስርየት መሥዋዕት የሚያቀርቡት በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ከልብ በሚያምን እምነት ነው፡፡ 
ታዲያ እምነታችሁ እንዴት ነው? የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በትክክል አውቃችሁ ታምኑበታላችሁን? ራሱን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በገለጠው እውነት የሚያምነው የብሉይ ኪዳን ካህናት እምነት በአዲስ ኪዳን ዘመን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሚያምነው እምነት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ እምነት ማንም ሊለውጠው የማይችለው ፍጹም የሆነ የደህንነት እምነት ነው፡፡ ማንም ሰው ይህ እምነት ሳይኖረው በእግዚአብሄር ፊት መቅረብም ሆነ ቅዱስ ወንጌሉን ማሰራጨት አይችልም፡፡ ይህ ማለት በዚህ እውነተኛ ወንጌል የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያላገኙ ሰዎች ለሌሎች ክህነታዊ ተግባሮቻቸውን ሊፈጽሙ አይችሉም ማለት ነው፡፡
በድረ ገጻችን አማካይነት ከብዙ ሌሎች አገሮች ዜናዎችን እንሰማለን፡፡ ሰዎች በነጸ በሚሰራጩት የክርስቲያን መጽሐፎቻችን አማካይነት የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እየተቀበሉ እንደሆነ ከፔሩ እስከ ቻይና ከዩጋንዳ እስከ ሆላንድ ድረስ ከመላው ዓለም ሁሉ እንሰማለን፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በያዙት በእነዚህ መጽሐፎች አማካይነት ገና ያልተገናኘናቸው ሰዎች እንኳን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እያገኙ ነው፡፡ በእያንዳንዱ አገር ያሉ ሰዎች የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ተቀብለው እነርሱም በተራቸው ከእኛ ጋር አብረው ሠራተኞች በመሆን ወንጌልን ቢያሰራጩ ምን ያህል ታላላቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር? በነጻ የሚታደሉት የክርስቲያን መጽሐፎቻችን በእያንዳንዱ አገር ቢገቡ በመላው ዓለም የሚገኙ ብዙ ሰዎች ከልብ ዳግመኛ ለመወለድ አያዳግታቸውም ነበር፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ እጅግ ብዙ ነፍሳቶች በአሁኑ ጊዜ መጽሐፎቻችንን በማንበብ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እያገኙ ነው፡፡ ስለዚህ ለክህነታዊ ተግባሮቻችን ታማኝ መሆንና በመገናኛው ድንኳን ስርዓት ውስጥ የተገለጠውን ይህንን የደህንነት እውነት እምነት ማሰራጨታችንን መቀጠል አለብን፡፡
ውድ ወዳጅ ምዕመናን እውነተኛውን ወንጌል በመላው ዓለም ማሰራጨት የምትችሉት ሐጢያት አልባና ቅዱስ ስትሆኑ ብቻ እንጂ ከዚያ በፊት አይደለም፡፡ እኛ ካህናቶች ለመሆን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በተገለጡት አራት እውነቶች የሚያምን እምነት መያዝና ያንንም እምነት ማሰራጨት አለብን፡፡ ራሱ እውነተኛ የሆነው ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ አስወግዶዋል፡፡ ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቅና ደሙን በማፍሰስ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አንጽቶናል፡፡ በእኛ ፋንታም የእነዚህን ሐጢያቶች ኩነኔ በሙሉ በይፋ በመሸከም የሚያምኑትን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ አድኖዋቸዋል፡፡ ጻድቃንና ሐጢያት አልባ በሚያደርገን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የሚያምን ማንኛውም ሰው እነዚህን የተቀደሱ ልብሶች መልበስ ይችላል፡፡ እነዚህን ልብሶች ለብሰን ወደ እግዚአብሄር ስንቀርብ፣ ወደ እርሱ ስንጸልይ፣ የእርሱን ረድኤት ስንጠይቅና ስናገለግለው ያን ጊዜ ይህንን ወንጌል በማሰራጨት ክህነታዊ ተግባሮቻችንን መፈጸም እንችላለን፡፡
በዚህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻችሁን ስርየት ተቀብላችኋልን? ይህንን የወርቅ ድሪ የሚመስል እምነት በልባችሁ ውስጥ ይገኛልን? ይህንን የወንጌል እውነት ለራሳችን ብቻ ማወቁ በቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሙሉ ልባችንም ደግሞ ልናምንበት ይገባናል፡፡ በሊቀ ካህኑ ልብሶችና በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር ላይ ጥቅም ላይ በዋሉት በእነዚህ አራት ማጎች ውስጥ ከሚገኙት እውነቶች አንዳቸውንም መተው የለብንም፡፡ እያንዳንዳቸው በእምነታችን ውስጥ መገኘት አለባቸው፡፡ ዛሬ አስመሳይ ምዕመናን እነማን ናቸው? ተመሳሳይ የሚመስል ነገር ግን በሚገባ ሲመረመር ይዘቱ በጣም የተለየ የሆነ ነገር አስመሳይ ተብሎ ይጠራል፡፡ አስመሳይ ወንጌሎችስ እንዲህ አይደሉምን? በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ፋንታ በሌሎች አስመሳይ ወንጌሎች የሚያምኑ ሰዎች አጭበርባሪ እምነት የያዙ ሰዎች ናቸው፡፡
 

መንፈሳዊ ወታደሮች ሆናችሁ እምነታችሁን ተከላከሉ፤ ጦርነታችሁንም ተዋጉ፡፡ 

ለጊዜውም ቢሆን እውነተኛ ጋዜጠኞች እንደሆኑ የሚያስመስሉ ብዙ አስመሳይ ሪፖርተሮች የሰዎችን ገንዘብ ማጭበርበር ችለዋል፡፡ እነዚህ አጭበርባሪ ጋዜጠኞች አስመሳይ ማረጋገጫዎችን በመያዝ እውነተኛ ጋዜጠኖች በመምሰል ረገድ የተሳካላቸው ስለነበሩ ብዙ ሰዎች በእነርሱ ተጭበርብረዋል፡፡ ዛሬ እውነተኛውን ወንጌል የሚመስል አንዳች ሌላ አስመሳይ ወንጌል የሚያሰራጩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እርግጥ ነው፡፡ እውነቱ ግን እነዚህ ወንጌሎች ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል የተለዩ መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ወንጌል ከማመናችን በፊት የሰማያዊውን? የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እያንዳንዱን ክፍል የያዘ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማየት የተለየ ትኩረት በመስጠት በሚገባ ልንመረምረው ይገባል፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን የሊቀ ካህኑን ልብስ አንዲት ማግ ሳይቀንስ ሁሉንም በጥልፍ አሠራር እንዲሠራ አዘዘው፡፡ ይህ ማለት የዘመኑ ካህናትም እምነታቸውን በሚመለከት ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል አንዲት ነገር እንኳን ማስቀረት የለባቸውም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር በእነዚህ በአራቱ ማጎች በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ደህንነታችንን እንደፈጸመው የማናምን ከሆነ በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረን አይችልም፡፡ 
የአንድ ሰው እምነት የምር እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለይተን የምናውቀው እንዴት ነው? ሊቀ ካህኑ የሚለብሳቸውን ልብሶች ቀለማት ስንመለከት ዛሬ ሙሉ የሆነ እምነት ያላቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ እንደሆኑ መረዳት እንችላለን፡፡ አንድ ሰው ልክ እንደ እነዚህ ሰዎች በእውነተኛው ወንጌል ቢያምን ይህንን ግለሰብ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቹ የነጻ ሰው አድርጋችሁ ልትቆጥሩት ትችላላችሁ፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት በሚያመለክተው በሰማያዊው ማግ እውነት ሳያምኑ በመስቀሉ ደም ብቻ በማመን እምነታቸው ሙሉ እንደሆነ የሚያስቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ፍጹም በሆነው ወንጌል አያምኑም፡፡ እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛውን ወንጌል ስለማያውቁ ስለ መንፈሳዊው የሐጢያቶች ስርየት መስበክ አይችሉም፡፡
ውድ ወዳጅ ምዕመናን በአስመሳይ ወንጌሎች የሚያምኑትን ሰዎች እምነት በእውነተኛው ወንጌል ከሚያምኑት ሰዎች እምነት ለይታችሁ ማወቅ መቻል አለባችሁ፡፡ በዚህ ምድር ላይ በእነዚህ አስመሳይ ወንጌሎች የሚያምኑ ብዙ መጋቢዎች አሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን የሊቀ ካህኑ ልብሶች ከአምስት ጥሬ ዕቃዎች የተሠሩ ነበሩ፡፡ እኛ የሐጢያቶች ስርየት ያገኘነው ይህ እምነት ስላለን ነው፡፡ በሰይጣን ላይ መንፈሳዊ ውጊያችንን የምናፋፍመው ለዚህ ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ጉዳይ በኤፌሶን መጽሐፍ ውስጥ ገልጦታል፡፡ ወደ ኤፌሶን 6፡10-18 እንሂድ፡- ‹‹በቀረውስ በጌታና በሐይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ፡፡ የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡ መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፤ በሰማያዊም ስፍራ ካሉ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም ሁሉን ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፡፡ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፡፡ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡ የመዳንንም ራስ ቁር፣ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፡፡ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየጸለያችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፡፡››
 ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ እንቃወም ዘንድ›› ‹‹በጌታና በሐይሉ ችሎት እንድንበረታ›› እና ‹‹የእግዚአብሄርን ጦር ዕቃ ሁሉ እንድንለብስ›› እየነገረን ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ዕቃ ጦር ሁሉ ምንድነው? የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጳውሎስ የእግዚአብሄርን ቃል በማመን፣ በመልበስና አጥብቀን በመያዝ እነዚህን አስመሳይ እምነቶች እንድንዋጋ እየነገረን ነው፡፡ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፤ በሰማያዊም ስፍራ ካሉ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ዓለም ገዦች፣ የዚህ ዓለም ወገን ከሆኑትና ከዲያብሎስ ክፉ መናፍስት ጋር እንድንዋጋ እየመከረን ነው፡፡
ጳውሎስ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም ሁሉን ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሄርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፡፡ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፡፡ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡ የመዳንንም ራስ ቁር፣ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡›› ጳውሎስ ይህን የሚነግረን እኛ እነዚህን ነገሮች አድርገን ከፈጸምን በኋላ በእግዚአብሄር ፊት መቆም እንችል ዘንድ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስለምናምን የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብለን ከእርሱ ጋር በዘላለም ሕይወት ለመደሰት በፊቱ እንቆማለን፡፡
ሁላችንም በስጋችን ደካሞች ነን፡፡ ስለዚህ የእምነትን መታጠቂያ መታጠቅ አለብን፡፡ ጳውሎስ የጽድቅን ጥሩር መልበስ እንዳለብን ሲነግረን በዚህ ወንጌል ከሙሉ ልባችን ማመን እንደሚገባን መናገሩ ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ ከደረቱ በላይ ባለው የደረት ኪስ ላይ አሥራ ሁለት የከበሩ ድንጋዮችን እንደለበሰና በእያንዳንዱ ድንጋይ ላይም በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ውስጥ ያለው የእያንዳንዱ ነገድ ስም እንደተቀረጸበት ሁሉ እኛም ሰዎችን ሁሉ በልቦቻችን ላይ መሸከምና ወደ ክርስቶስ መምራት እንዳለብን እየነገረን ነው፡፡ ሊቀ ካህኑ በደረቱ ኪስ ላይ ያሉትን እነዚህን አሥራ ሁለቱን የከበሩ ድንጋዮች በመያዙና በደረቱ ላይ በመሸከሙ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በልቡ ላይ ተሸክሞዋቸዋል፡፡
እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ወገባችሁንም በእምነት ታጥቃችሁ›› እንዳለ ሁሉ እኛም በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የሚያምነው እውነት በትክክልና በተጨባጭ ሊኖረን ይገባል፡፡ ድካሞቻችንን ሳንፈራ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ላይ ያለንን እምነታችንን ከልባችን አጥብቀን ከያዝን ልቦቻችን ይጠነክራሉ፡፡ በማይናወጠው እምነታችን ላይ ጸንተን መቆም የምንችለው በዚህ እምነት ነው፡፡ ስለዚህ የጽድቅን ጥሩር ለብሰን በአእምሮዋችንና በልባችን ልናምንበት ይገባናል፡፡ ይህንን እውነተኛውን ወንጌል በጭንቅላታችን ብቻ ማወቁ በቂ አይደለም፡፡ በልቦቻችን ውስጥም ደግሞ ልናምነው ይገባናል፡፡
በሰላም ወንጌል መዘጋጀት ወንጌልን የምናሰራጭባቸውንም ጫማዎች መጫማት አለብን፡፡ እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ሰላምን ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር ሰላምን በሰጠንና ወንጌልን በማገልገል ሕይወታችንን እንድንመራ በሚያደርገን በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል እንድናምን ነግሮናል፡፡ 
እግዚአብሄር ‹‹የእምነትን ጋሻ›› እንድናነሳና ‹‹የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ እንድናጠፋ›› ነግሮናል፡፡ በጥንት ዘመን ብዙውን ጊዜ በጦርነት ላይ የሚሰማሩት የመጀመሪያ ምርጥ መሣርያዎች የሚንበለበሉ ፍላጾች ነበሩ፡፡ ጳውሎስ ሰይጣን የሚያጠቃን እንደዚህ መሆኑን እየነገረን ነው፡፡ ዲያብሎስ ‹‹ማን ነኝ ብላችሁ ነው የምታስቡት? ከልቦቻችሁ ውስጥ ብቅ የሚሉት አስተሳሰቦቻችሁና ምግባሮቻችሁ በሙሉ የረከሱ ናቸው፡፡ ታዲያ ወንጌልን ለማሰራጨት ታስባላችሁን? ይህ ምን ዓይነት የማይረባ ነገር ነው? በጣም እንደታበያችሁ አታስቡምን? በመጀመሪያ ለምን ራሳችሁን አታስተካክሉም?›› በማለት ጥቃቱን በድካሞቻችንና በአለመብቃቶቻችን ላይ ለይቶ ያነጣጥራል፡፡ በእነዚህ የሚንበለበሉ ፍላጾች ተመታችሁ ከዚህ ጥቃት የተነሳ ‹‹ትክክል ነህ›› በማለት ከተማረካችሁ ራሳችሁን ‹‹ራሴን እንኳን በትክክል መምራት የማልችል ምን ዓይነት ካህን ነኝ?›› በማለት መጠየቅ ይገባችኋል፡፡ ይህ በእናንተ ላይ ከደረሰ ነፍሳችሁ ትሞታለች፡፡ እናንተም በመንፈሳዊ ሕይወታችሁ ትሞታላችሁ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁሉም በላይ የእምነትን ጋሻ እንድናነሳ የነገረን ለዚህ ነው፡፡ ሰይጣን በድካሞቻችን እንድንወድቅ ያደርገን ዘንድ በልቦቻችን ውስጥ ሊተክላቸው ከሚሞክራቸው ከእነዚህ ስጋዊ አስተሳሰቦች የሚከልለን ምንድነው? በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የሚያምነው የማይናወጠው እምነት ነው፡፡ የእምነት ጋሻ ይህ ነው፡፡
የሚንበለበሉት ፍላጾች ማንንም ሳይለዩ በእኛ ላይ በሚዘንቡበት ጊዜ ጌታችን በዚህ እምነት እንድናጠፋቸው ነግሮናል፡፡ ‹‹ጌታ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ጻድቅ አድርጎኛል፡፡ በዚህም ከሙሉ ልቤ አምናለሁ፡፡›› እነዚህን የሚንበለበሉ ፍላጾች፣ በሰይጣን የታቀዱትን ዕቅዶችና ጥቃቶች ሁሉ ማስወገድ የምንችለው በዚህ እምነት ነው፡፡
ደካማ ናችሁን? በእርግጥም ስጋችሁ ደካማ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም በእግዚአብሄር ጸጋና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምነው እምነት ማከናወን አለባችሁ፡፡ በመጀመሪያ የሐጢያቶችን ስርየት ከተቀበላችሁ በኋላ በእምነት ጥቃቅን ጉዳዮችን መጋፈጥ ትችላላችሁ፡፡ በኋላ ግን በእምነት ብቻ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በማንኛውም መንገድ ሊፈቱ የማይችሉ ብዙ ችግሮች በሮቻችሁን ያንኳኳሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ ድካሞቻችሁ በጥቂቱ ብቻ ይገለጡ ይሆናል፡፡ ጊዜ እየነጎደ ሲሄድ ግን እነዚህ ድካሞች በከፍተኛ ደረጃና ይበልጥ ስለታማ ሆነው መገለጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ውሎ አድሮም በጣም ብዙ በሆኑ ድካሞች ስለምትጥለቀለቁ ራሳችሁን እንደትጠሉ ያደርጉዋችኋል፡፡
ሰይጣን በእናንተ ላይ ከፍተኛ ጥቃት የሚሰነዝረው በእርግጥ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት ተቀብላችሁ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ መጠራጠር በምትጀምሩባቸው በእነዚህ ወቅቶች ነው፡፡ ስለዚህ በእምነታችሁ ድካሞቻችሁን ማሸነፍ አለባችሁ፡፡ በሌላ አነጋገር በድካሞቻችሁ ምክንያት ራሳችሁን ወደ ማጥፋት የሚመሩዋችሁ እንዲህ ያሉ ስጋዊ አስተሳሰቦች እንዳይኖሩዋችሁ ራሳችሁን መከላከል አለባችሁ፡፡ በእምነት ጋሻ የሰይጣንን ጥቃት መቀልበስና ‹‹ሰይጣን ከእኔ ዞር በል! ሮሜ 1፡17 እንደሚለው ጻድቅ በእምነት ይኖራል፡፡ እኔ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩብኝም በእግዚአብሄር ጽድቅ ባለኝ እምነት አሁንም ጻድቅ ነኝ›› ብላችሁ መጮህ አለባችሁ፡፡ ጻድቅ በእምነት መኖር አለበት፡፡
በዚህ ዓለም ላይ በራሳችን የምንኮራበት አንዳች ነገር አለ? በዓለማዊ መንገድ የምንኮራበት ምንም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በዓለም ሰዎች ፊት አሁንም በድፍረት ልንናገረው የምንችለው ነገር አለን፡፡ የዓለም ሰዎች ‹‹እናንተ ጻድቅ ከሆናች እኔም ደግሞ ጻድቅ ነኝ›› ይሉዋችሁ ይሆናል፡፡ እናንተም እንዲህ ብላችሁ ልትመልሱላቸው ይገባል፡- ‹‹እናንተ ጻድቅ ከሆናችሁ እኔ ደግሞ የጽድቅ ሁሉ እናት ነኝ፡፡›› ማስተዋል ሳይኖራቸው ጉድለቶቻችንን በመሳብ የሚያጠቁን ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹አንተ ጥሩ ተማሪ አይደለህም፡፡ ይህንን ማድረግ አትችልም፤ ያንን ማደረግ አትችልም፡፡›› በዚህ መንገድ ቢያጠቁንም ፈጽሞ የምንጨነቅበት ምክንያት የለንም፡፡ ‹‹ትክክል ናችሁ፡፡ እኔ እዚያ ላይ ጥሩ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በዚህ በእውነተኛው ወንጌል አምናለሁ፡፡ ይህ ወንጌል ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ሰማያዊው ማግ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ሐምራዊው ማግ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ቀዩ ማግ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ጥሩው በፍታ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ቀደምት የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተመልከቱ፡፡ ትርጉማቸውን ለማወቅ ቢያንስ አራት ዕሁዶች ይወስዱባችሁ ይሆናል፡፡ አይደለም፤ በእርግጥ ከዓመት በኋላ እንኳን ምስጢሩን መረዳት ከቻላችሁ ዕድለኞች ናችሁ፡፡ እነርሱን ከማስተዋላችሁ በፊት ምናልባት 500 ትውልዶች ይፈጅባችሁ ይሆናል፡፡ የወርቁ ድሪ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ከእናንተ በተቃራኒ እኔ እነዚህን ነገሮች አውቄ አምንባቸዋለሁ፡፡›› ስለዚህ በእምነታችሁ የሰይጣንን ጥቃቶች ሁሉ በድፍረት መቀልበስ አለባችሁ፡፡ ጠንካራ እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ በዚህ እምነትም ዲያብሎስን ማሸሽ አለባችሁ፡፡
‹‹ደካማ ብሆንም አሁንም የእግዚአብሄርን ወንጌል አገለግላለሁ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማገልገል እግዚአብሄርን ማገልገል ነው፡፡ ጉድለት ቢኖርብኝም በእግዚአብሄር መንግሥት ውስጥ አሁንም ንጉሥ ነኝ፡፡ ወንጌልን ባላሰራጭ ሁላችሁም ፍጻሜያችሁ ሲዖል ይሆናል፡፡›› ወንድሞችና እህቶች ሁላችሁም እንዲህ ያለ ደፋር እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ይህ እምነት በጉልበት የምታገኙት ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር የሰጠን ነገር ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር ይህንን በእምነት መቀበል ነው፡፡ ይህንን እምነት በማመን ተቀብላችኋልን?
በኤፌሶን 6፡17 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹የመዳንን ራስ ቁር እንድንለብስ›› መክሮናል፡፡ የራስ ቁር (መከላከያ) ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደል? የመካከለኛውን ዘመን አርበኞች ታስታውሳላችሁን? ከብረት የተሠሩ የብረት ቆቦችን አድርገው በፈረስ ላይ በመሆን እርስ በርሳቸው በጉግስ ይጫወቱ ነበር፡፡ ፊቶቻቸውን የሚሸፍኑትን እነዚህን የራስ ቁሮች በመልበሳቸው ዓይኖቻቸው ላይ እስካልተወጉ ድረስ ቁስሎቻቸው ለሞት የሚያደርሱ ክፉ አይሆኑም ነበር፡፡ እነዚህን የጉግስ ጥቃቶች የቀለበሱላቸውና የከለሉላቸው እነዚህ በልዩ መንገድ የተሠሩ የራስ ቁሮች ነበሩ፡፡ ልክ እንደዚሁ የመዳን ራስ ቁርም እንዲህ ያለውን ሚና ይጫወታል፡፡
ስለዚህ በጭንቅላቶቻችን ውስጥ ያለው የእውነት ዕውቀትም እንደዚሁ ፍጹም መሆን አለበት፡፡ የወንጌል እውነት በዕውቀታችን በሚገባ የተደራጀ መሆን አለበት፡፡ ‹‹ይህ እውነት ነው ወይስ አይደለም? ይህ ትክክል ነው ወይስ ስህተት?›› በዚህ ሁኔታ እርግጠኛ ባለመሆናችን ከምንባዝን ግንዛቤያችን በአእምሮዋችን ውስጥ በሚገባ የጠራ መሆን አለበት፡፡ ‹‹ጌታ በሰማያዊው? በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ፈጽሞ ጻድቅ አድርጎኛል፤ በዚህ አምናለሁ፡፡›› ሰይጣን ሊገባበት የሚሞክርበትን ቀደዳ መሸፈን የምንችለው ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው፡፡ ይህም ራሳችንን በመዳን ቁር ይሸፍንልናል፡፡ ትክክለኛ በሆነው የእውነት ዕውቀት ማመን አለብን፡፡
ጳውሎስ የመንፈስን ሰይፍ እንድንይዝም ነግሮናል፡፡ ይህ የመንፈስ ሰይፍ የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ቃሉን ስንማር፣ ስናውቅና ስናምንበት ትልቅ መሣርያ የያዝን ያህል ነው፡፡ ሰይጣን በሌሎች ሰዎች፣ በገንዘብ፣ በተቃራኒ ጾታና በድካሞቻችን አማካይነት በሸር ያጠቃናል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ቃል ላይ ባለን እምነት ሁሉንም ማክሸፍ እንችላለን፡፡
በኤፌሶን ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን አምሳያ ከሊቀ ካህኑ ልብሶች ወስዶ በመጠቀም እውነተኛ እምነት ምን እንደሆነ በዚህ መንገድ አብራርቶልናል፡፡ ‹‹የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ፡፡›› በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር እኛን ጻድቃን ያደረገበትን የእውነት ጥሩር እንድንለብስ እየነገረን ነው፡፡ ጳውሎስ ‹‹የእምነትን ራስ ቁርና የመንፈስን ሰይፍ እንድንወስድ›› ነግሮናል፡፡ ይህንን ምሳሌ በመጠቀም የተሟላ የእውነት ዕውቀት በመያዝና በእግዚአብር ቃል በማመን ሰይጣንን እንድንዋጋው፣ እንድንመታውና እንድናሽንፈው እየነገረን ነው፡፡ እምነታችንን የሚተናኮሉትን ክፉ ዕንቅፋቶች በሙሉ ያለ ምንም ማመንታት እንድናወድማቸው እየነገረን ነው፡፡ አስመሳይ ወንጌሎችን የያዙ ሰዎች በአንድ ክፍል ብቻ ማለትም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙና የእግዚአብሄር ልጅ በመሆኑ መለኮታዊ ባህርያቶች በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንደነጹ ይናገራሉ፡፡ እኛ ይህንን አጭበርባሪ እምነት መናቅና በግልጥ ማስወገድ አለብን፡፡
በሰማያዊው ማግ አገልግሎቱ ሳያምን በኢየሱስ የሚያምን እምነት እውነተኛ ያልሆኑ ልብሶች የለበሰን ሊቀ ካህን ይመስላሉ፡፡ ሆኖም በዚህ ዓለም ላይ እውነተኛውን ማግ ከእምነታቸው አውጥተው የጣሉ በጣም ብዙ አጭበርባሪ ክርስቲያኖች ያሉ በመሆናቸው ሁሉንም ልንቆጥራቸው አንችልም፡፡ ነገር ግን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመጽሐፎቻችን ውስጥ በማስቀመጥ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የመጣውን ይህንን የምናምንበትን ወንጌል እንመሰክራለን፡፡ ሰዎች ቢያምኑበት ወይም ባያምኑበት መጽሐፎቻችን ትክክለኛውን የእግዚአብሄር ቃል እንዲይዙ ያደረግነው ቢያንስ እውነቱን እንዲያነቡት፣ እንዲያውቁትና እንዲያምኑበት ዕድል ለመስጠት ነው፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሄር በመሆኑና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስም ሐጢያቶቻችንን እንዳስወገደ ብቻ የሚያምኑ ሰዎች ሌሎችንና ራሳቸውንም ሳይቀር በማሳት የእምነታቸውን መሠረት በስሜቶቻቸው ላይ የማኖር ዝንባሌ አላቸው፡፡ ነገር ግን እኛ በእውነት የምናምን ሰዎች ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ፈጽሞ ያዳነን በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰሱ መሆኑን እናውቃለን፤ እናምናለን፤ እንሰብክማለን፡፡
አሁን የሊቀ ካህኑ ልብሶች ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተሠራ እንደነበር ታምናላችሁን? ሙሉ በሙሉ ቅድስናን የለበሱ ከእነዚህ ከአምስቱ ማጎች የተሠሩትን እነዚህን ልብሶች የለበሱ ናቸው፡፡ በወርቁ፣ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በመጣው የሐጢያት ስርየት በልባቸው የሚያምኑ በእርግጥም ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ እንደዳኑ የሚያምኑ እውነተኛ የእምነት ሰዎችና መንፈሳዊ ካህናት ናቸው፡፡
አሁን መንፈሳዊ ካህናት የሆኑ ሰዎች ፈጽሞ መርሳት የማይኖርባቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም የእውነተኛው ወንጌል ጥላው የሆነው የሰማያዊው፣ የሐምራዊው፣ የቀዩ ማግና የጥሩው በፍታ አንደምታ ነው፡፡ የሐጢያት ስርየትን የተቀደሱ ልብሶች የምንሠራው፣ በእምነት የምንለብሳቸውና በእግዚአብሄር ፊት የምንቀርበው በእነዚህ በአምስቱ እምነቶች ነው፡፡ ይህም ስለ እውነተኛው እምነታችን ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ለብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካህን እንዳደረገው በዚህ እውነት በሚያምነው እምነታችን ልቦቻችንን ቅዱስ አድርጎዋቸዋል፡፡ በዚህ እወነት በማመን ሁላችንም በእግዚአብሄር ፊት ካህናት ሆነናል፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የምናገለግል የንጉሥ ካህናት ነን፡፡
ወንድሞችና እህቶች በዚህ እውነት የሚያምን እምነት እንዲኖራችሁ እጠይቃችኋለሁ፡፡ በዚህ እምነትም ሰይጣንን ተዋግታችሁ ክህነታዊ ተግባራቶቻችሁን ፈጽሙ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ ሁላችሁም ለዘላለም ክህነታዊ ተግባሮቻችሁን በታማኝነት እንድትፈጽሙ ተስፋ በማድረግ እጸልያለሁ፡፡ ይህንን የምለው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ወንጌል ማመን ካቆማችሁ ክህነታችሁ ከእናንተ ስለሚወሰድ ነው፡፡ ሁለችሁም በእውነተኛው ወንጌል ላይ ባላችሁ የማይናወጥ እምነታችሁ ይበልጥ ታማኝ ካህናት ትሆኑ ዘንድ እጸልያለሁ፡፡ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን ወንጌል እንዳትተዉት፣ እምነታችሁን እንድትከላከሉና ለዘላለምም ክህነታዊ ተግባሮቻችሁን እንድትፈጽሙ ሁላችሁም እስከ ፍጻሜ ድረስ በእውነተኛው ወንጌል እንደምታምኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡