Search

布道

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-10] በመንፈስ ተመላለሱ! ‹‹ ገላትያ 5፡16-26፤6፡6-18 ››

በመንፈስ ተመላለሱ!
‹‹ ገላትያ 5፡16-26፤6፡6-18 ››
‹‹ነገር ግን እላለሁ፤ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፡፡ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፡፡ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም፡፡ በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም፡፡ የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው፡ እርሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንንም የሚመስል ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልሁ ይህንን የሚያደርጉ የእግዚአብሄርን መንግሥት አይወርሱም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ፡፡ በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ፡፡ እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ፡፡››   
‹‹ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል፡፡ አትሳቱ፤ እግዚአብሄር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፡፡ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል፡፡ ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት፡፡ እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ፡፡ እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደጻፍሁላችሁ እዩ፡፡ በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፡፡ ነገር ግን ስለ ኢየሱስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው፡፡ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳን ሕግን አይጠብቁም፡፡ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፡፡ በዚህም ስርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሄር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምህረት ይሁን፡፡ እኔ የኢየሱስን ማህተም በሥጋዬ ተሸክሜያለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ፡፡ ወንድሞች ሆይ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን አሜን፡፡››
 
 
በመንፈስ ለመመላለስ ምን ማድረግ አለብን?
ውቡን ወንጌል መስበክና መከተል አለብን፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ በጻፈው ደብዳቤ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጽፎዋል፡፡ በገላትያ 5፡13-14 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹ወንድሞች ሆይ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፡፡ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፡፡ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባርያዎች ሁኑ፡፡ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፡፡ እርሱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው፡፡››  
በአጭሩ መልዕክቱ ውብ በሆነው ወንጌል በማመናችን ስለዳንንና ከሐጢያት ነጻ ስለወጣን ይህንን አርነት የሥጋን ምኞት ለመፈጸም እንደ ዕድል ልንጠቀምበት ሳይሆን በፍቅር አማካይነት አንዳችን ሌላችንን ማገልገልና ውቡን ወንጌል መከተል አለብን የሚል ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ስላዳነን ወንጌልን መስበክ ተገቢያችን ነው፡፡ ጳውሎስ እንዲህም ደግሞ አለ፡- ‹‹ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተተንቀቁ፡፡›› (ገላትያ 5፡15)
 
 

በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት በመንፈስ ተመላለሱ

 
በገላትያ 5፡16 ላይ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ነገር ግን እላለሁ፤ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፡፡›› በቁጥር 22-26 ላይም እንዲህ አለ፡- ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ፡፡ በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ፡፡ እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ፡፡›› እዚህ ላይ ጳውሎስ  በመንፈስ የምንመላለስ ከሆንን የመንፈስን ፍሬ እንደምናፈራ ይነግረናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በመንፈስ እንድንመላለስ ይጠይቀናል፡፡ የምንኖረው ግን በሥጋ ነው፡፡
እኛ የሰው ልጆች የተወለድነው የመንፈስን ፍሬ ማፍራት ከማይችል ሥጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን በመንፈስ መመላለስ የምንፈልግ ብንሆንም ተፈጥሮዋችን ሊለወጥ አይችልም፡፡ በመንፈስ መመላለስና የመንፈስን ፍሬ ማፍራት የሚችሉት ውብ በሆነው ወንጌል በማመን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ ብቻ የሆኑት ለዚህ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ እንድንመላለስ ሲነግረን ሌሎችም ደግሞ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ያገኙ ዘንድ ውብ የሆነውን ወንጌል ልንሰብክላቸው ይገባናል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ውብ የሆነ ወንጌል የምንኖር ከሆንን የመንፈስን ፍሬ እናፈራለን፡፡ በሌላ አነጋገር ጉዳዩ ሰብአዊ ተፈጥሮን መለወጥ አይደለም፡፡ በዚህ ውብ የሆነ ወንጌል ስንመላለስ የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ደግነት፣ ቸርነት፣ ታማኝነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት እናፈራለን፡፡ የመንፈስ ፍሬ የዘላለም ሕይወት እንዲኖራቸው ሌሎችን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን ያግዘናል፡፡
 
 

የሥጋ ምኞትና የመንፈስ ፍላጎት ተቃርኖ

 
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛሉና፡፡ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም፡፡›› (ገላትያ 5፡17) እኛ ቤዛነትን ያገኘን በተመሳሳይ ጊዜ የሥጋና የመንፈስ ምኞት ስለያዝን እነዚህ ሁለት ነገሮች ሁሌም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ አንዳቸውም ልባችንን መሙላት አይችሉም፡፡    
መንፈስ ከልቦቻችን ጥልቅ ውብ የሆነውን ወንጌል እንድንሰብክና ጌታን እንድናገለግል ወደ መመኘት ይመራናል፡፡ የእግዚአብሄርን ውብ ወንጌል በመስበክ ሰዎችን ከሐጢያቶቻቸው እንድናድን ያግዘናል፡፡ 
በሌላ በኩል ግን ፍላጎቶቻችን የሥጋን ምኞት ስለሚያነሳሱ በመንፈስ መመላለስ አንችልም፡፡ ይህ በመንፈስና በሥጋ ምኞት መካከል የሚደረግ የዘላለም ግጭት ነው፡፡ አንድ ሰው በሥጋ ምኞት ሲቃጠል ፍጻሜው ሥጋን ማገልገል ይሆናል፡፡ ሥጋ በመንፈስ ላይ ይመኛል፡፡ ሁለቱም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ የምንፈልገውን ማድረግ አንችልም፡፡ 
ታዲያ በመንፈስ በመመላለስ ውስጥ ምን ይካተታል? እግዚአብሄርን የሚያስደስቱትስ ምን አይነት ነገሮች ናቸው? ውብ የሆነውን ወንጌል መስበክና መከተል ማለት በመንፈስ የመመላለስ ሕይወት እንደሆነ እግዚአብሄር ተናገረ፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትን መምራት ይችሉ ዘንድ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ላላቸው ሰዎች በመንፈስ የሚመላለሱበትን ልቦች ይሰጣቸዋል፡፡ በመንፈስ በመመላለስ የመንፈስን ፍሬ እንድናፈራ የሰጠን ትዕዛዝ ውብ የሆነውን ወንጌል በመስበክ ሌሎችን ከሐጢያቶቻቸው ለማዳን የተሰጠን ማደፋፈሪያና ትዕዛዝ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መመላለስ ማለት እግዚአብሄርን የሚያስደስት ሕይወት መኖር ማለት ነው፡፡
በመንፈስ ለመመላለስ ከሁሉ በፊት ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ በውስጣችን የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ከፈለግን በመጀመሪያ እግዚአብሄር በሰጠን ውብ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ ውብ የሆነውን ወንጌል ከልባችን ጥልቅ ካላመንን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስም መቀበልም ሆነ ከሐጢያት መዳንንም አናገኝም፡፡ ይህ ማለት በመንፈስ መመላለስ አንፈልግም ማለት ነው፡፡
መንፈስ ውብ የሆነውን ወንጌል እንድንሰብክ፣ ጌታን እንድናገለግልና ለእግዚአብሄር ክብር እንድናመጣ ፍላጎቱን ይሰጠናል፡፡ ይህ ፍላጎት የሚመጣው ለእግዚአብሄር ራሱን ቀድሶ ከሰጠና ውብ የሆነውን ወንጌል ለመላው ዓለም ከመስበክ ነው፡፡ ውብ የሆነውን ወንጌል ለመስበክ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ከሚያደርግ ልብ ውስጥም ይመነጫል፡፡ የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ካገኙ በኋላ ውብ በሆነው ወንጌል የሚያምኑና መንፈስ ቅዱስን የሚቀበሉ በመንፈስ ይመላለሳሉና ወንጌልንም ለመስበክ ራሳቸውን ይቀድሳሉ፡፡ ይህ ከላይ የተሰጣቸው መንፈሳዊ ውርሳቸው ነው፡፡ 
እነዚያ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው የሥጋ ምኞት ቢኖርባቸውም መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስለሚያድር መንፈስ ቅዱስን በመታዘዝ በመንፈስ ይመላለሳሉ፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ፡፡›› እርሱ ይህንን ሲል ሌሎችም ለሐጢያቶቻቸው ይቅርታን ያገኙ ዘንድ ኢየሱስ የሰጠንን ውብ ወንጌል መስበክ አለብን ማለቱ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በመንፈስ እየተመላለስን በሥጋ እንመላለሳለን፡፡ በሕይወታችን ውስጥ የሥጋ ምኞትና የመንፈስ ፍላጎት እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ፡፡ ነገር ግን በግልጽ ማወቅና መገንዘብ የሚገባን ነገር ቢኖር ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ያላቸው በመንፈስ የሚመላለስ ሕይወትን መኖር እንዳለባቸው ነው፡፡ በእግዚአብሄር በረከቶች የተሞላ ሕይወትን መኖር የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ያለ ሰዎች የመንፈስን ፍሬ ለማፍራት አሻፈረኝ ካሉ የሥጋን ፍሬ በማፍራት ፍጻሜያቸው ጥፋት ይሆናል፡፡ ፍሬያቸው ጠፊና አይረቤ ነው፡፡ በመንፈስ መመላለስ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው፡፡
‹‹በመንፈስ መመላለስ›› የሚለውን ሰምተናል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቻችን ‹‹መንፈስ ቅዱስ በውስጤ እንዳለ ስሜቱ ስለማይሰማኝ ይህንን እንዴት ማድረግ እችላለሁ?›› ብለን እናስብ ይሆናል፡፡ አንዳንዶቻችን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለይተን ማወቅ የምንችለው እግዚአብሄር ተገልጦ በቀጥታ ሲናገረን ብቻ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ መንፈስ ውብ ለሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የመኖርን ፍላጎት ይሰጠናል፡፡  
በሥጋ ስለምንመላለስ እርሱ በውስጣችን እንደሚኖር እርግጠኞች ሆነን እርሱነቱ የማይሰማን ጊዜ ይኖር ይሆናል፡፡ አንዳንዶች እርሱ በውስጣችን ያንቀላፋ መስሎ ሊሰማቸው ይችል ይሆናል፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ገናም በሥጋ የሚመላለሱ ናቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች ሥጋቸውን ብቻ የሚያዝናኑና እርሱ እንደነገራቸው የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ሥጋ ከሚጠይቃቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች የተነሳ ይቸገራሉ፡፡ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸውም እንኳን እንደ ሥጋቸው ምኞት ለመኖር ያዘነብላሉ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ የተለመደ ነው ብለው ያስባሉና፡፡
እግዚአብሄር በመንፈስ እንድንኖር ይነግረናል፡፡ ይህ ማለት ውብ የሆነውን ወንጌል ማገልገል ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል ቀድሰን መስጠት አለብን ማለትም ጭምር ነው፡፡ በወንጌል መደሰትና በእርሱም መኖር በመንፈስ መመላለስ ማለት ነው፡፡ በመንፈስ መመላለስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በመማር እንደዚያ መኖር ይኖርብናል፡፡ በመንፈስ እየተመላለሳችሁ ነውን?
 
 

ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሌለው በመንፈስ መመላለስ ይችላልን?

 
ዳግም ያልተወለዱ በመንፈስ መመላለስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡ በዚህም ብዙ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ይሞክራሉ፤ በራሳቸው መንገድም ይሹታል፡፡ መንፈስ ቅዱስን የመሻቱ ድርጊት በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ 
ለምሳሌ ሰዎች ለአገልግሎት በተወሰኑ ጸሎት ቤቶች ሲሰበሰቡ አገልጋዩ ድምጹን ከፍ አድርጎ ይፀልያል፡፡ እያንዳንዱ ሰውም የጌታን ስም ጮክ ብሎ መጥራት ይጀምራል፡፡ አንዳንዶችም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ይመስል በልሳን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ማንም ራሳቸውም እንኳን ምን እየተናገሩ እንደሆነ አያውቁም፡፡ ወዲያም ከእነርሱ አንዳንዶቹ መሬት ላይ ይወድቃሉ፡፡ አካላቸውም በልቅ ስሜት መንቀጥቀጥ ይጀምራል፡፡ እነርሱ በእርግጥም በአጋንንቶች ተይዘዋል፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ይመስላቸዋል፡፡ ከዚያም ሰዎች ‹‹ጌታ፤ ጌታ!›› እያሉ ሲጮሁም ሁካታ ይፈጠራል፡፡ ጌታን ይጠራሉ፡፡ ዕንባቸውን ያፈሳሉ፡፡ እጆቻቸውንም ያጨበጭባሉ፡፡ ይህ ክስተት ብዙውን ጊዜ ‹‹በመንፈስ ቅዱስ›› መሞላት ተብሎ ይጠራል፡፡
ሰባኪው ምስባኩን እየደለቀ በልሳን ይናገራል፡፡ ሰዎችም ‹‹ጌታ! ጌታ!›› እያሉ ይጮሃሉ፡፡ እነርሱ የዚህ አይነቱን ሁኔታ ይወዱታል፡፡ አንዳንዶችም ባልተቀደሰው ቅዠታቸው በኤደን ገነት ውስጥ የነበረውን መልካሙንና ክፉውን የሚያስታውቀውን ዛፍና የኢየሱስን ፊት በራዕይ እንዳዩ ይናገራሉ፡፡ እነርሱ እነዚህን ነገሮች መንፈስ ቅዱስን የመቀበያና በእርሱ ተሞልተው ከእርሱ ጋር የሚመላለሱባቸው መንገዶች አድርገው በተሳሳተ መንገድ ያስቡዋቸዋል፡፡ የተዛነፉት ድርጊቶቻቸው የመጡት ስለ እግዚአብሄር ቃልና ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሳሳቱ እሳቤዎችን በመያዛቸው ነው፡፡
‹‹በመንፈስ መመላለስ፡፡›› እግዚአብሄር ዳግም ለተወለዱት የሚነግራቸው ይህንን ነው፡፡ ይህ ማለት እርሱን የሚያስደስቱትን ነገሮች ማድረግ ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ የሥጋን ስራዎች ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ጋር አነጻጽሮታል፡፡ እርሱ እንዲህ አለ፡- ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡›› (ገላትያ 5፡22-23)    
‹‹በመንፈስ መመላለስ›› ማለት ውብ የሆነውን ወንጌል መስበክና ሌሎችን ከሐጢያቶቻቸው ማዳን ማለት ነው፡፡ ይህንን የምናደርግ ከሆነ የመንፈስን ፍሬ ማፍራት እንችላለን፡፡ የመንፈስ ፍሬዎች ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ የውሃት፣ ደግነት፣ ቸርነት፣ ታማኝነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት ናቸው፡፡ ይህንን ፍሬ ማፍራት የምንችለው ውብ በሆነው ወንጌል ስናምን ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን መስዋዕት አድርጎ ውብ የሆነውን ወንጌል ሲያገለገልና ሲሰብክ ያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ መንፈሳዊ ሕይወትን መኖር ይችላል፡፡   
የመንፈስ ፍሬ እንደመሆኑ ‹‹ቸርነት›› ማለት መልካም ምገባሮችን ማድረግ ማለት ነው፡፡ በጎነት ማለትም ደግሞ ነው፡፡ ውብ ለሆነው ወንጌል በጎነትን ይዞ መቆየትና ለሌሎች ጥቅም አንዳች ነገርን ማድረግ ቸርነት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት እጅግ የላቀው በጎነት ወንጌልን ለሌሎች ጥቅም መስበክ ነው፡፡ 
‹‹ደግነት›› ለሰዎች መራራት ነው፡፡ ለሌሎች የሚራራ ሰው፤ ወንጌልን በትዕግስትና በደግነት የሚያገለግል ሰው ሰላም ይኖረዋል፡፡ በመንፈስ የሚመላለስ ሰው የጌታ ሥራ ተከናውኖ ሲመለከት ይደሰታል፤ የእርሱን ሥራ መስራትም ይወዳል፤ ሌሎችን ይወዳል፡፡ በነገሮች ሁሉም ታማኝ ነው፡፡ ማንም እንዲህ እንዲያደርግ ባያስገድደውም ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያለው ሰው ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በሥራው ታማኝ ይሆናል፡፡ እርሱ ጨዋ ነው፤ ራሱንም ይቆጣጠራል፡፡ የመንፈስ ፍሬ አለው፡፤ በውስጡ መንፈስ ቅዱስ ያለው ሰው በመንፈስ መመላለስ ይኖርበታል፡፡ የመንፈስን ፍሬ ማፍራት የሚችለው እንደዚህ ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡  
በመንፈስ የምትመላለሱ ከሆነ የመንፈስንም ፍሬ ማፍራት ትችላላችሁ፡፡ እንደዚያ የማታደርጉ ከሆነ ግን ፍጻሜያችሁ የሥጋን ምኞት ማድረግ ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 5፡19-21 ላይ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው፡ እርሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንንም የሚመስል ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልሁ ይህንን የሚያደርጉ የእግዚአብሄርን መንግሥት አይወርሱም፡፡››  
 
 
የሥጋ ሥራዎች የተገለጡ ናቸው
 
የሥጋ ሥራዎች የተገለጡ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የሥጋ ሥራ ‹‹ምንዝርና›› ሲሆን ይህ ማለት ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ዝሙት›› ነው፡፡ ሦስተኛው ‹‹ርኩሰት›› ነው፡፡ አራተኛው ‹‹መዳራት›› ሲሆን ይህ ማለት ፍትወት ማለት ነው፡፡ አምስተኛው ‹‹ጣዖትን ማምለክ›› ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄርን ከማገልገል ይልቅ ጣዖታትን ማገልገል ማለት ነው፡፡ ስድስተኛው ‹‹ጥንቆላ›› ነው፡፡ ሰባተኛው ‹‹ጥላቻ›› ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሌለው ሰው በሥጋ ቢመላለስ ሐጢያተኛ በሆነው ተፈጥሮው ምክንያት ለሌሎች ያለውን ጥላቻ ያሳያል፡፡ ስምንተኛው ‹‹ጠብ›› ነው፡፡ ይህ ማለት ከጓደኞቻችን ወይም ከቤተሰባችን ጋር መጋጨት ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ቅንአት፣ ቁጣና ራስ ወዳድነት›› ናቸው፡፡
አስረኛው ‹‹መለያየት›› ነው፡፡ አንድ ሰው በሥጋ ብቻ የሚመላለስ ከሆነ የቤተክርስቲያንን ሥራ መስራት ስለሚያዳግተው ውሎ አድሮ በገዛ ፈቃዱ ከቤተክርስቲያን ለቆ ይወጣል፡፡ አስራ አንደኛው ‹‹መናፍቅነት›› ነው፡፡ በሥጋ የሚመላለስ ሰው ይህንን የሚያደርገው የገዛ ፈቃዱን ለማርካት ነው፡፡ ነገር ግን ያ ሕይወት ከእግዚአብሄር ፈቃድ በጣም የተለየ ስለሆነ ውሎ አድሮ ውብ ከሆነው ወንጌል ይርቃል፡፡ ኑፋቄ ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማፈንገጥ ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል የሚያምንና በመንፈስ የሚመላለስ ሰው  ከእግዚአብሄር ፈቃድ አይርቅም፡፡ ‹‹ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነትና እነዚህን የመሰሉ ሁሉ›› የሥጋ ሥራዎች ናቸው፡፡ በሥጋ የሚመላለሱ ብቻ እነዚህን ነገሮች ያደርጋሉ፡፡ ጌታ ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ እኛ ዳግም የተወለድን በመንፈስ መመላለስ ይኖርብናል፡፡
ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ያለው የሥጋ ምኞት ብቻ ነው፡፡ ‹‹በዝሙት፣ በርኩሰት፣ በመዳራትና በጣዖት አምልኮ›› የሚጠመዱት ለዚህ ነው፡፡ ዳግም ያልተወለዱ ሐሰተኛ አገልጋዮች ብዙ ገንዘብ እንዲለግሱዋቸው ተከታዮቻቸውን ለማሳመን ሲሉ በእነርሱ ላይ ‹‹ጥንቆላን›› ይተገበራሉ፡፡ ብዙ ገንዘብ ለሚሰጡትም አስፈላጊ የሆኑ ሐላፊነቶችንና በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን ቁልፍ ቦታ ይሰጡዋቸዋል፡፡ በሥጋ የሚኖሩ ለሌሎች ያላቸውን ‹‹ጥላቻ›› ይገልጣሉ፡፡ ቤተክርስቲያኖችን ወደ ብዙ የሐይማኖት ድርጅቶች ይከፋፍላሉ፤ ስለ ራሳቸው የሐይማኖት ድርጅትም ይኩራራሉ፤ ሌሎቹንም መናፍቃኖች አድርገው ሳንሱር ያደርጉዋቸዋል፡፡ ‹‹ጠብ፣ ምቀኝነት፣ ቁጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ቅንአት›› ዳግም ባልተወለዱ ሰዎች ልቦች ውስጥ አሉ፡፡ እኛ ቅዱሳን የሆንን በሥጋ የምንመላለስ ከሆነ የሚገጥመን ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡    
  
 
መንፈስ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖችን የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ እንዲያፈሩ ያደርጋል
 
ዳግም የተወለዱ መኖር ያለባቸው ውብ የሆነውን ወንጌል ለመስበክ መሆን አለበት፡፡ ጌታን ብቻችንን ሆነን መከተል ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ውብ የሆነውን ወንጌል የማገልገሉን ሥራ መስራት ያለብን ከእግዚአብሄር  ቤተክርስቲያን ጋር በመቆራኘት ነው፡፡ አብረን መጸለይና ውብ በሆነው የመንፈስ ወንጌል የሚመላለስ ሰው ለመሆን ጉልበቶቻችንን ቀድሰን መሰጠት አለብን፡፡ በመንፈስ የሚመላለሱ ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመስበክ መኖር አለባቸው፡፡ በሌላ አነጋገር በሥጋ መመላለስ ማለት ለራስ ብቻ የመኖር ሕይወት ማለት ሲሆን በመንፈስ መመላለስ ማለት ደግሞ የሌሎችን ነፍስ ለማዳን መስራት ማለት ነው፡፡ ብዙ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች የዚህ አይነት ውብ ሕይወት እየኖሩ ነው፡፡ ለሌሎች በጎነት ይኖራሉ፡፡ 
ውብ የሆነውን ወንጌል ሰምተው እንኳን የማያውቁ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዓለም ዙሪያ አሉ፡፡ እኛ በአፍሪካና በእስያ የሚኖሩትን ሕዝቦች እንወዳቸዋለን፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በተበታተኑት ደሴቶች የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው እንወደዋለን፡፡ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ጋር በማስተዋወቅም ፍቅራችንን ልናሳያቸው ይገባናል፡፡
በመንፈስ መመላለስ አለብን፡፡ ይህንን የሚቃወም ሕግ የለም፡፡ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም፡፡›› (ገላትያ 5፡22-23) ይህንን ሊቃወም የሚችል አንዳች ሕግ አለን? የለም፡፡ ልንታዘዘው የሚገባን የመንፈስ ሕግ ይህ ነው፡፡ ጳውሎስ በመንፈስ እንድንመላለስ ነገረን፡፡ ጌታችን ለእኛ ለሐጢያተኞቹ ሕይወቱን እንደሰጠ ሁሉ እኛም ወንጌልን ለሌሎች መስበክ አለብን፡፡ ሌሎችን ከሐጢያቶቻቸው ማዳን በመንፈስ መመላለስ ነው፡፡ በመንፈስ መመላለስ ይኖርብናል፡፡ 
ጳውሎስ በገላትያ 5፡24-26 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ፡፡ በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ፡፡ እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ፡፡›› በመንፈስ ለመመላለስ የምንኖር ከሆነ የጠፉ ነፍሳቶችን ለማዳን መኖር አለብን፡፡ የመንፈስን ሥራ ልናደርግና ከእርሱ ጋር ልንመላለስ ይገባናል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ካለው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን እንድንኖር ይመራናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የፍቅር ንጉሥ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፍቅሩ መሳሪያዎች አድርጎ ይጠቀምብናል፡፡     
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹‹የኢየሱስ ክርስቶስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ፡፡›› (ገላትያ 5፡24) እርሱ ዳግም የተወለዱት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው እንደሞቱም ተናገረ፡፡ በእርግጥ ዳግም የተወለዱት አስቀድመው ከኢየሱስ ጋር አብረው ሞተዋል፡፡ ይህንን አልተረዳነውም፡፡ ነገር ግን እርሱ የሐጢያቶቻችንን ዋጋ ለመክፈል በተሰቀለ ጊዜ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሞተናል፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቀለ ማለት እናንተና እኔም በመስቀል ላይ አብረን ከእርሱ ጋር ሞተናል ማለት ነው፡፡ የእርሱ ሞት የእኛ ሞት ነበር፡፡ የእርሱ ትንሣኤም የእኛን ዋስትና ያለው ትንሣኤ የሚያመላክት ነው፡፡ እናንተና እኔ በእምነታችን አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ኖረን ሞተናል፡፡ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ እምነታችን በመንፈስ እንድንመላለስ ይመራናል፡፡    
እግዚአብሄር በመንፈስ የምንመላለስበትን ሐይል ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ እኛ የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅርታ ያገኘን ሰዎች በመንፈስ መመላለስ ይኖርብናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ሐጢያቶቻቸው ይቅር ስለተባሉ አመስጋኞች መሆንና ለጠፉት መዳን ይሆንላቸው ዘንድ ውብ የሆነውን ወንጌል ለመስበክ ራሳቸውን መቀደስ አለባቸው፡፡ አንድ ሰው የሐጢያቶቹን ይቅርታ ቢያገኝና ዳግም ቢወለድም እንደ ሥጋ ምኞት የሚመላለስ ከሆነ ከጌታ ቤተክርስቲያን ይነጠልና ጌታን ማገልገል አይችልም፡፡ እናንተና እኔ እስከ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል መኖር ይገባናል፡፡
 
 
በጭራሽ ትምክህተኞች አትሁኑ፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ኑሩ
 
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ፡፡›› ትምክህት ምንድነው? በሥጋ ምኞት መመላለስ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ለራሳቸው ትምክህት የሚኖሩ ብዙ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ገንዘብን ያከማቻሉ፡፡ ለሥልጣን ይጋደላሉ፡፡ ዓለማዊ ውበትን ይወዳሉ፡፡ ለአሁኑ ዓለም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚታመኑ አይደሉም፡፡ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በስብሰው ይጠፋሉ፡፡ በሥጋ የሚመላለሱ ሰዎች ትምክህተኞች ተብለው የተጠሩት ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ብልጥግና ቢኖራቸውም በልባቸው ውስጥ እውነተኛ ሰላምና እርካታ አላቸውን? የሥጋ ፍሬ ውሎ አድሮ ይበሰብሳል፡፡ ምድራዊ ነገሮች ለሌሎች ነፍሳቶች ጥቅም የላቸውም፡፡ የሚጠቅሙት ራስን ብቻ ነው፡፡ ለሰው ሥጋ ብቻ የሚጠቅሙ ናቸው፡፡   
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያለውን የሚበትን አለ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ ይደኸያልም፡፡›› (ምሳሌ 11፡24) ዳግም ያልተወለዱ እጅግ ብዙ ገንዘብ ለማከማቸት ይሞክራሉ፡፡ ዓለማዊ ነገሮች ለእነርሱ ሁሉንም ነገር ማለት ስለሆኑ በውስጣቸው ለሌሎች የሚያስቡበት ሥፍራ የለም፡፡ ለራሳቸው ሕይወት ብቻ የሚያስቡት ለዚህ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከሚበቃው በላይ የሚያከማች ሰው እንዳለ ይናገራል፡፡ ያ ግን ወደ ድህነት ይመራል፡፡ ሰዎች በሥጋ ምኞት ይመላለሳሉ፡፡ ውጤቶቹ ግን በወንበዴ እጅ ገብቶ ከመሞት ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የትምክህተኝነት ውጤቶች ናቸው፡፡   
 
 
የመንፈስ ቅዱስን ምኞት መከተል የሚወዱ
 
ጳውሎስ ሕይወትን በመንፈስ ለመኖር ፈለገ፤ እንደዚያም አደረገ፡፡ እርሱ በእግዚአብሄር ቃል መሰረት እንዴት በትክክል መኖር እንደምንችል አስተማረን፡፡ በገላትያ 6፡6-10 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል፡፡ አትሳቱ፤ እግዚአብሄር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፡፡ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል፡፡ ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት፡፡ እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ፡፡››   
ጳውሎስ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያውቁ መልካምን ነገር ሁሉ ከአስተማሪዎቻቸው ጋር እንዲካፈሉ መከራቸው፡፡ ‹‹መልካም ነገሮች›› ማለት ደግሞ ውቡን ወንጌል መስበክና በመንፈስ በሚመላለስ ሕይወት  የጠፉ ነፍሳቶችን መመለስ ነው፡፡ እነዚያ ዳግም የተወለዱ ሰዎች ተመሳሳይ አሳብ ፍቅርና ተመሳሳይ ብያኔ ይዘው ወንጌልን ከሚሰብኩና በመንፈስ ከሚመላለሱ ሰዎች ጋር መቀላቀል አለባቸው፡፡ 
‹‹ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል፡፡›› መልካም ነገሮች ማለት በቤተክርስቲያን በኩል ሌሎችን ከሐጢያቶቻቸው ማዳን ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ እያንዳንዱን ነገር በተመሳሳይ አሳብ በተመሳሳይ ጸሎትና በተመሳሳይ ራስን መስጠት እንድናደርግ ነገረን፡፡ 
ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹አትሳቱ እግዚአብሄር አይዘበትበትም፤ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹መዘበት›› ማለት ‹‹ማላገጥና ማፌዝ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹አትሳቱ እግዚአብሄር አይዘበትበትም፤ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና›› ማለት በእግዚአብሄር ላይ አታላግጡ፤ አታፊዙም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በራሱ ቃሎች በመተርጎምና በእነዚያ ቃሎች ከማመን በመጉደል የእግዚአብሄርን ቃሎች በዘፈቀደ መውሰድ የለበትም፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡›› ይህ ማለት ሥጋን የሚዘራ ሰው መበስበስን ያጭዳል፤ ነገር ግን መንፈስን የሚዘራ ሰው የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል ማለት ነው፡፡ 
ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ብንኖር ምን እናጭዳለን? የዘላለምን ሕይወትና ከሐጢያቶቻችንም ደህንነትን እናገኛለን፡፡ ሌሎች በእግዚአብሄር በረከቶች አማካይነት ከሐጢያቶቻቸው ቤዛነትንና የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ በመምራት የመንፈስን ፍሬዎች እናጭዳለን፡፡ 
ለገዛ ሥጋቸው የሚኖሩ ሰዎችን በሚመለከትስ? እነርሱ መበስበስን ያጭዳሉ፡፡ በመጨረሻም ይሞታሉ፡፡ ከሞቱ በኃላ የሚቀርላቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ሰው ባዶ እጁን ተወልዶ ባዶ እጁን ይሞታል፡፡
ሌሎችን ከሐጢያቶቻቸው የማዳን ሥራ የሚሰራ ከሆነ የመንፈስን ፍሬ ያጭድና የዘላለምን ሕይወት ያገኛል፡፡ ነገር ግን በሥጋ ምኞት መመላለሱን ከቀጠለ መጨረሻው መበስበስን ማጨድ ይሆናል፡፡ ከዚያም ዕርግማኖችን ያጭድና ዕርግማኖቹን ለሌሎች ያሻግራል፡፡ ስለዚህ በእምነት ስለ መኖር እያንዳንዱን ነገር የሚያውቀው ጳውሎስ በሥጋ እንዳንመላለስ መክሮናል፡፡
‹‹ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት፡፡›› ጳውሎስ በመንፈስ የተመላለሰ የእግዚአብሄር ባርያ ነበር፡፡ ሰዎች እርሱ በመንፈስ እንደተመላለሰ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲመለከቱ አንዳንዶች ‹‹ጳውሎስ ወደ ግራ ሂድና ከአንድ ሰው ጋር ተገናኝ፡፡›› ወይም ‹‹ከዚህ ሰው ራቅ›› የሚሉ አይነት ነገሮችን ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ያዘዘው መስሎ ይሰማቸው ይሆናል፡፡ ይህ ግን እውነት አይደለም፡፡እርሱ በመንፈስ የተመላለሰው የደህንነትን ወንጌል ለሌሎች በመስበክና ነፍሳቸውን ለማዳን በማገዝ ነበር፡፡ ጳውሎስ በመንፈስ ከሚመላለሱ ጋር በመተባበርም ጌታን አገልግሎዋል፡፡ በክርስቲያኖች መካከል በሥጋ ምኞት እንጂ በመንፈስ የማይመላለሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጳውሎስን አልተቀበሉትም፡፡ ነገር ግን ተቃወሙት፤ አላገጡበትም፡፡ ጳውሎስ ከተቃወሙትና የኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ከሰደቡት ጋር አንዳች ቁርሾ እንደሌለው ተናገረ፡፡   
በመንፈስ መመላለስ ከፈለጋችሁ በወንጌል መኖር ይኖርባችኋል፡፡ የተገረዙት ጳውሎስን አሳደዱት፡፡ በገላትያ 5፡11 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹ነገር ግን ወንድሞቼ ሆይ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል እንቅፋት ተወግዶዋል፡፡›› የተገረዙት ‹‹አንድ ሰው በኢየሱስ አምኖ ዳግም ቢወለድም መገረዝ አለበት፡፡ የሥጋ ሸለፈቱን ካልተገረዘ የእግዚአብሄር ልጅ አይደለም›› በማለት በግርዘት ምግባር የሚኩራሩ ናቸው፡፡ ለምን አሳደዱት? ጳውሎስ ቤዛነትና የዘላለም ሕይወት ሊገኝ የሚችለው በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ብቻ መሆኑን ስላመነ ነው፡፡ የሰበከውም ይህንኑ ነው፡፡
ሰዎችን ጻድቃን የሚያደርጋቸው እምነት የሚመጣው እውነትን ከመማርና ከመስበክ ነው፡፡ ጳውሎስ የውሃውና የመንፈሱ እውነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተረዳ፡፡ እውነቱን ያወቁ በመንፈስ መመላለስ እንደሚችሉና መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው አመነ፡፡ የሰበከውም ይህንኑ ነው፡፡ የተገረዙት ግን ግርዘት አንድ ሰው ለመዳን በያዘው እምነቱ ውስጥ አስፈላጊ ክፍል ነው ብለው አመኑ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ከሰጠው ሌላ የተለየ ወንጌል የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ መጨመር ወይም ከዚያ አንዳች ነገር መቀነስ የለብንም፡፡ 
ጳውሎስ በመንፈስ በተመላለሰ ጊዜ በወዳጆቹ አይሁዶች ተገለለ፤ ተሳደደም፡፡ ‹‹በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፡፡ ነገር ግን ስለ ኢየሱስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው፡፡ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳን ሕግን አይጠብቁም፡፡ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፡፡›› (ገላትያ 6፡12-15) ጳውሎስ ለተገረዙት እንዲህ አላቸው፡- ‹‹በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፡፡ ነገር ግን ስለ ኢየሱስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው፡፡››  
ጳውሎስ በሥጋ ምኞት የተመላለሱትን ወቀሳቸው፡፡ እነርሱ በድርጊታቸው በሥጋ ምኞት ተመላለሱ፡፡ እነርሱን የመሰሉ ብዙ ሰዎችም አሉ፡፡ ጳውሎስ ግን ከእነርሱ ጋር ያለውን ወዳጅነት አቆመ፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፡፡›› ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀውና በመስቀል ላይም ሕይወቱን የሰጠው ጳውሎስንና እግዚአብሄር የሚጠራቸውን ሁሉ ለማዳን ነው፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና፡፡›› ለዓለም የሞተው  ጳውሎስ ዳግመኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ሆነ፡፡
እኛ በተጨባጭ በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ ሆነን ሞተናል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ይህንን እውነት እንረሳዋለን፡፡ ልናምነው ይገባናል፡፡ በዚህ እውነት የማናምን ከሆንን በሥጋ ምኞትና በቤተሰቦቻችን ታስረናል፡፡ ይህ ደግሞ ከጌታ ጋር እንዳንመላለስ እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ሥጋችን በጣም ደካማ ስለሆነ ቤተሰቦቻችን እንኳን ጌታን እንድንከተል ሊያግዙን አይችሉም፡፡ ሊረዳን የሚችለው ጌታ ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን ለዓለም ተሰቅለናል፡፡ የሞተ ሰው ምድራዊ የሆኑ ሰዎችን በምድራዊ ጉዳዮች እንዴት ሊረዳቸው ይችላል? በዚህ ዓለም ላይ የሞቱ ሰዎች የዓለምን ነገሮች የራሳቸው ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ 
ኢየሱስ ተነስቷል፡፡ የእርሱ ትንሣኤ በአዲስ ሕይወት ዳግም እንድንወለድ ፈቅዶልናል፡፡ እዚህ አዲስ ሥራ፣ አዲስ ቤተሰብ፣ አዲስ ተስፋ አለን፡፡ እኛ ዳግም የተወለድን ሰዎች ነን፡፡ እኛ የሰማይ ወታደሮች ስለሆንን የእግዚአብሄርን ቃል ለመስበክ ሐላፊነት አለብን፡፡ ጳውሎስ ሌሎች በሥጋዊ መንገዶች ሳይሆን በመንፈሳዊ ዘዴዎች ደህንነትን ያገኙ ዘንድ በመርዳት ሰው እንደሆነ መሰከረ፡፡ አስቀድሞ እንደሞተና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ዳግም እንደተወለደም ተናገረ፡፡ እኛም ስለ እምነታችን ተመሳሳይ ምስክርነቶችን ለመስጠት የምንደፍር አይነት ሰዎች እንድንሆን እንታገል፡፡
ጳውሎስ በገላትያ 6፡17-18 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹እኔ የኢየሱስን ማህተም በሥጋዬ ተሸክሜያለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ፡፡ ወንድሞች ሆይ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን አሜን፡፡›› ጳውሎስ የጌታ ኢየሱስን ማህተም ተሸክሞዋል፡፡ በመንፈስ ለመመላለስ ሲል ስለ ጌታ ጤናውን አልተንከባከበም፡፡ ቀስ በቀስ የአይኑን ብርሃን እያጣ ስለነበር መጻፍ እንኳን አልቻለም፡፡ ስለዚህ እርሱ የእግዚአብሄርን ቃሎች ሲናገር እንደ ጠርቲስ ያሉ አጋሮቹ የመዘገቡዋቸው የጳውሎስ መልዕክቶች ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ በሥጋ ደካማ የነበረ ቢሆንም በመንፈስ መመላለስ በመቻሉ ደስተኛ ነበርና እንዲህ አለ፡- ‹‹ነገር ግን የውጪው ሰውነታችን ቢጠፋም እንኳን የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፡፡›› (2ኛ ቆሮንቶስ 4፡6)
ጳውሎስ በመንፈስ እንደሚመላለሱ አይነት ሰዎች እንደንሆን ይመክረናል፡፡ እርሱ እንዲህ አለ፡- ‹‹በመንፈስ መመላለስ ማለት ለወንጌል መኖር ማለት ነው፡፡›› እናንተና እኔ በመንፈስ መመላለስ ምን ማለት እንደሆነ በአእምሮዋችን መያዝ ይኖርብናል፡፡ ከንቱ የሆኑ ነገሮችን መከተል የለብንም፡፡ በፋንታው ወንጌልን ማገልገልና ለእርሱ መኖር ይኖርብናል፡፡ በቀሪው ዕድሜያችን በእምነት በመንፈስ እንመላለስ፡፡
አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስላመንን እውተነኛው መንፈስ በልባችን ውስጥ አለ፡፡ ከወንጌል ጋር ተስማምተን የምንጸልየውን ጸሎት እግዚአብሄር በደስታ ይመልሳል፡፡ የመንፈስን ፍሬ ማፍራት ማለት በመንፈስ መመላለስና ነፍሳቶችን መቤዠት ማለት ነው፡፡ እናንተ በመንፈስ ስትመላለሱና ለወንጌል ስትኖሩ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ታጋሽነት፣ ደግነት፣ ቸርነት፣ ታማኝነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት የሆኑትን የመንፈስ ፍሬዎች ማፍራት ትችላላችሁ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመስበክ መከራን መቀበል፣ ታጋሽ መሆን፣ ደግነትን መለማመድና ለጠፉት ነፍሳት በጎን ማድረግ አለብን፡፡  
የመንፈስ ፍሬዎች ፍሬያማ የሚሆኑት በጎን በማድረግና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸውን በጎ ነገር በማድረግና ወንጌል በመስበክ የጠፉ ነፍሳቶችን ለሚያድኑት ነው፡፡ የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራትና በመንፈስ መመላለስ የሚያስችለው ይህ ነው፡፡