Search

布道

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[18-1] የባቢሎን ዓለም ወደቀ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 18፡1-24 ››

የባቢሎን ዓለም ወደቀ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 18፡1-24 ››
‹‹ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች፡፡ በብርቱም ድምጽ፡- ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፤ ወደቀች፤ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፤ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፡፡ አሕዛብም ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ የምድር ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ሐይል የተነሳ ባለጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ፡፡ ከሰማይም ሌላ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሕዝቤ ሆይ በሐጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፡፡ ሐጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሄርም ዓመጻዋን አሰበ፡፡ እርስዋ እንደሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፡፡ እንደ ሥራዋም ሁለት ዕጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፡፡ ራስዋን እንዳከበረችና እንደተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጡአት፡፡ በልብዋ፡- ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ ባልቴትም አልሆንም ሐዘንም ከቶ አላይም ስላለች ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ሐዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፡፡ በእሳትም ትቃጠላለች፡፡ የሚፈርድባት እግዚአብሄር ብርቱ ነውና፡፡ ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው፡- አንቺ ታላቂቱ ከተማ፤ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ወዮልሽ ወዮልሽ፤ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ፡፡ የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለም፡፡ የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፡፡ ጭነትም፣ ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ፣ ዕንቁም፣ ቀጭንም፣ ተልባ እግር፣ ቀይም ሐርም፣ ሐምራዊም ልብስ፣ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፣ እጅግም ከከበረ እንጨት፣ ከናስም፣ ከብረትም፣ ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋም፣ ቅመምም፣ የሚቃጠልም ሽቱ፣ ቅባትም፣ ዕጣንም፣ የወይን ጠጅም፣ ዘይትም፣ የተሰለቀ ዱቄትም፣ ስንዴም፣ ከብትም፣ በግም፣ ፈረስም፣ ሰረገላም፣ ባርያዎችም፣ የሰዎችም ነፍሳት ነው፡፡ ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፡፡ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም፡፡ እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፡- በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጎናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት ወዮላት፤ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሳ በሩቅ ይቆማሉ፡፡ የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባህርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፡- ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ፡፡ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያነቡ፡- በባህር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለጠግነትዋ የተነሣ ባለጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት ወዮላት፤ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ፡፡ ሰማይ ሆይ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ነቢያትም ሆይ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ እግዚአብሄር ፈርዶላችኋልና፡፡ አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባህር ወረወረው እንዲህ ሲል፡- ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም፡፡ በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምጽ፣ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፡፡ የእጅ ጥበብም ሁሉ፣ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፡፡ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፡፡ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና፡፡ በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች፡፡
ሰዎች እግዚአብሄር ሥራዎቹን እንዲሰሩለት ወደዚህ ምድር በላካቸው አገልጋዮቹ አማካይነት የእግዚአብሄርን የበረከቶችና የእርግማኖች ስብከቶች መስማት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም ከሐጢያቶቻችሁና ከሐዘናችሁ ሁሉ ነጻ ለመውጣት በእነዚህ የእግዚአብሄር አገልጋዮች የተሰበከውን የሰማይ መንፈሳዊ የበረከት ቃል በልባችሁ መቀበልና ማመን ይገባችኋል፡፡
 
ቁጥር 2፡- በብርቱም ድምጽ፡- ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፤ ወደቀች፤ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፤ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፡፡
‹‹ባቢሎን ወደቀች›› በሚለው ሐረግ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ባቢሎን የሚለውን ቃል የተጠቀመው ሥጋዊውን ዓለም ለማመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ሰዎች ጉልበቶቻቸውን አስተባብረው እግዚአብሄርን ለመቋቋም በመሻት የተገነባውንና በዚህም ምክንያትም በእግዚአብሄር የፈረሰውን የባቤል ግምብ እናገኛለን፡፡ ከላይ ያለው ምንባብ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች ሲል ይህ ዓለም እንደሚወድቅ እየነገረን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ይህ ዓለም አሁንም ደህና ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ሊወድቅ ይችላል?›› ይሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች አንድ በአንድ በሚወርዱበት ጊዜ ልክ የባቤልን ግምብ እንዳፈረሰው ይህንን ዓለምም እንደሚያፈርሰው እዚህ ላይ እየነገረን ነው፡፡
ይህ ዓለም በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በእግዚአብሄር የሚጠፋበት ምክንያቱ ታዲያ ምንድነው? ምክንያቱም የዚህ ዓለም ሕዝብ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትን ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን ከጸረ ክርስቶስ ጋር ተባብረው በመግደላቸውና እስከ መጨረሻውም ድረስ እግዚአብሄርን በመቃወማቸው ነው፡፡ ሌላው ምክንያትም ይህ ዓለም ‹‹የአጋንንቶች መጠጊያ›› ስለሆነ ነው፡፡
ሁኔታው ይህ የሆነው ለምንድነው? ማለትም ይህ ዓለም የአጋንንቶች መጠጊያ የሆነው ለምንድነው? ምክንያቱም የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ ብዙ ሰዎች ለጸረ ክርስቶስ ስለሚያጎበድዱና ከእርሱ ዘንድ የሰይጣንን ምልክት በመቀበል የዚህ ክፉ አገልጋዮች ስለሚሆኑ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘንዶው ሰይጣንን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሎዋል፡፡ አጋንንቶችም የዘንዶው አገልጋዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ዓለም የአጋንንቶች መጠጊያ ሆንዋል ሲል የዘንዶው አገልጋይ የሆነው ጸረ ክርስቶስ ዓለምን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል ማለት ነው፡፡ የመጨረሻው ዘመን ዓለም የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በሚወርዱበት ጊዜ ከልክ ያለፈ የመከራዎች ዘመን ይገጥመዋል፡፡ ይህ ዓለም የዘንዶው ዓለም ይሆናል፡፡ አጋንንቶችም መላው ዓለም የእነርሱ የሆነ ይመስል ይፈነጫሉ፡፡ ይህም ዓለም እግዚአብሄር በሚያፈስሳቸው በሰባቱ ጽዋዎች የመጨረሻ መቅሰፍቶች በፍጥነት ይወድቃል፡፡
 
ቁጥር 3፡- አሕዛብም ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፤ የምድር ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ሐይል የተነሳ ባለጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ፡፡
እዚህ ላይ ጥቅሱ በግልጽ እንደሚናገረው በምድር ላይ ያሉ ‹‹አሕዛብ ሁሉ›› የዓለምን ዝሙት ቁጣ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል፡፡ በሌላ አነጋገር የዚህ ዓለም ሕዝብ ይህንን ዓለም እንደ አምላክ አስበውት አምነውታል፤ ተከትለውታል፡፡ ከእግዚአብሄር ይልቅ ይህንን ዓለም ወደዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም የሐጢያት ምንጭ ሆንዋል፡፡ ሕዝቡም በሐጢያት ሰክረው ሕይወታቸውን ኖረዋል፡፡
ውጤቱም ዓለም በሐጢያት መውደቁ ነው፡፡ ሰዎች ልክ እግዚአብሄርን እንደሚከተሉ ዓለምን ስለወደዱና ስለተከተሉ የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በማውረድ ያጠፋቸዋል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሄር በሚያወርዳቸው በእነዚህ ሰባት ጽዋዎች መቅሰፍቶች ይጠፋና ወደ ሲዖል ይጣላል፡፡
እግዚአብሄር ጌታ በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል አሁኑኑ ካላመነ እያንዳንዱ ሰው በመጨረሻ የሚገጥመው የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እንደሚሆን ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያውን እየሰጠን ነው፡፡ በዚህ ወንጌል የማታምኑና ማስጠንቀቂያውን ሰጥቶዋችሁ ሳለ እግዚአብሄርን በመቃወም የምትቀጥሉ ከሆናችሁ በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ከመቀጣታችሁም በላይ ዘላለማዊውን የሲዖል ቅጣትም ትቀበላላችሁ፡፡
ስለዚህ ሰዎች ታላላቅና አስፈሪ ከሆኑት የእግዚአብሄር መቅሰፍቶች ያመልጡ ዘንድ አሁኑኑ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን እንዳለባቸውና በተቻለ ፍጥነትም ወደ እውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል እምነት መመለስ እንደሚገባቸው መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
ብዙ የዓለም ነገሥታቶችና ነጋዴዎች በቁሳዊ መትረፍረፍ ብዙ ሐብት ቢያከማቹም ይህ ዓለም እግዚአብሄር ባመጣቸው ታላላቅ መቅሰፍቶች ሲፈረካከስ ሲያዩ መጨረሻቸው ማልቀስ፣ ዋይ ማለትና ሙሾ ማውረድ ይሆናል፡፡
ስለዚህ ሁላችንም ለሰው ሁሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ እንዳለብንና ሕይወታቸንንም አዲሱን ሺህ ዓመት አርቀን በማሰብ መኖር እንዳለብን ከቶውኑም መርሳት የለብንም፡፡ እያንዳንዱ የሰው ዘር ከታላላቆቹ መቅሰፍቶች ያመልጥ ዘንድ ሰውን ሁሉ ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መምራት አልብን፡፡
 
ቁጥር 4፡- ከሰማይም ሌላ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሕዝቤ ሆይ በሐጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፡፡
‹‹ሕዝቤ ሆይ በሐጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፡፡›› ይህ ለቅዱሳኖች የተነገረ የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ቅዱሳን በመጨረሻው ዘመን የሚኖረው ዓለም አካልና የእርሱ ባሮች ሆነውም ሕይወታቸውን መኖር የለባቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም ቅዱሳን ሆነው የነበሩትም እንኳን በመጨረሻው ዘመን በሚኖረው ዓለም ሐጢያት ውስጥ ከወደቁ እግዚአብሄር አስፈሪ በሆኑት መቅሰፍቶቹ ከሚፈርደው ፍርድ ማምለጥ አይችሉም፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ለቅዱሳኑ ሁሉ ፍጻሜያቸው የዓለም ባሮች ሆነው ቁጣውን እንዳይቀበሉ እየነገራቸው ነው፡፡
 
ቁጥር 5፡- ሐጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሄርም ዓመጻዋን አሰበ፡፡
እግዚአብሄር በእርግጥም የዚህን ዓለም ሐጢያቶችና ዓመጻዎች በሙሉ ያስባል፡፡ የሚጠብቀውም የፍርዱን ቀን ብቻ ነው፡፡ አንድ ቀን ድንገት ጸረ ክርስቶስ ሲገለጥ እግዚአብሄር እንዳቀደው ጥፋት ፈጥኖ መላውን ዓለም ይሸፍናል፡፡ ሆኖም አሁንም ድረስ ይህ ዓለም እስከ ዘላለም ይቀጥላል እንጂ አይጠፋም ብለው የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡
ሆኖም ይህ ዓለም እነርሱ እንደሚያስቡት አይቆይም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በሚያወርዳቸው የሰባቱ መለከቶችና የሰባቱ መቅሰፍቶች ድንገት ይወድማል፡፡ የዘመኑ መጨረሻ ሲመጣ እግዚአብሄር በዓለም በየስፍራው መከራዎችን በማምጣት ያጠፋዋል፡፡ ስለዚህ በእምነት ሕይወታችን እስከ መጨረሻው ድረስ ትጉሃን በመሆን የኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በእርግጥም እንደሚመጣ የምናምንበትን እምነታችንን ጸንተን መያዝ አለብን፡፡
እግዚአብሄር በዚህ ምድር ላይ ሰባቱን ጽዋዎች ያፈስሱ ዘንድ መላእክቶቹን ከማዘዙ በፊት የዓለም ሐጢያቶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ስለሚሰራጩ ይህ የእግዚአብሄርን ፍርድ ለመቀበል ከተገቢው በላይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር የዓለምን ሐጢያቶች ያስባል፡፡ ጥፋቱንም ከእንግዲህ ወዲህ አያዘገይም፡፡ ከዚህም በላይ ጸረ ክርስቶስና የዓለም ሕዝቦች የእግዚአብሄርን ሕዝብ በማሳደድ ቅዱሳን እምነታቸውን እንዲክዱ ያስገድዱዋቸዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በሚሆኑበት ጊዜ ይህ ዓለም የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ይቀበላል፡፡
 
ቁጥር 6፡- እርስዋ እንደሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፡፡ እንደ ሥራዋም ሁለት ዕጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፡፡
እዚህ ላይ ‹‹እርስዋ እንደሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹እርስዋ›› የተባለችው የምታመለክተው ማንን ነው? ይህ የሚያመለክተው ይህንን ዓለም ማለትም በውስጡ የሚኖሩትን ሐጢያተኞች ጸረ ክርስቶስንና ሰይጣንን ነው፡፡ ይህም እግዚአብሄር እነርሱ ቅዱሳኖችን እንዳሳደዱ፣ እንዳሰቃዩ፣ እንዳስቸገሩና እንደገደሉ ሁሉ ብድራትን እንደሚመልስባቸው ይነግረናል፡፡
ቁጥር 6 ‹‹በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት›› ይላል፡፡ ይህ እግዚአብሄር የዲያብሎስን ውሸቶች በማሰራጨት ሰዎችን ወደ ሲዖል የነዱት የዓለም የሐሰት ሐይማኖቶች በሙሉ ይቀጡ ዘንድ ለመላዕክቶቹ የሰጠው ትዕዛዝ ይህ ነው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር የዛሬው ክርስትና የእግዚአብሄርን ቃል ከሰይጣን ትምህርቶች ጋር በመቀላቀልና ሰዎችን ወደ ዲያብሎስ በመምራት የሐሰት ትምህርቶችን ሐጢያት በመስራቱ እግዚአብሄር ቁጣውንና ቅጣቱን ያወርድበታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያላመኑ ክርስቲያኖች የዓለም ሰዎች የሚቀበሉትን ዓይነት ተመሳሳይ ቅጣት ይቀበላሉ፡፡
 
ቁጥር 7፡- ራስዋን እንዳከበረችና እንደተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጡአት፡፡ በልብዋ፡- ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ ባልቴትም አልሆንም ሐዘንም ከቶ አላይም ስላለች፡፡
እግዚአብሄር እዚህ ላይ የእነዚህን ትዕቢተኛ ሰዎች ሐጢያቶች በስቃይና በሐዘን ብድራት እንደሚመልስ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር ዳግመኛ ያልተወለዱ የዓለም ሰዎችንና ያላመኑ ሥጋዊ የዓለም ሰዎችን ስለ ሐጢያቶቻቸው በመጠየቅ ይቀጣቸዋል፡፡
እነርሱ ግን ‹‹ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ ባልቴትም አልሆንም፤ ሐዘንም ከቶ አላይም›› በማለት በኩራታቸው ይቀጥላሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በመቅሰፍቶቹ ያጠፋቸዋል፡፡ እግዚአብሄር በሚያወርዳቸው ታላላቅ መቅሰፍቶችም ሁሉም ዓለማዊ ንብረቶቻቸውንና የሚወዱዋቸውን ሁሉ በተመሳሳይ ጊዜ በማጣት ይሰቃያሉ፡፡
 
ቁጥር 8፡- ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ሐዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፡፡ በእሳትም ትቃጠላለች፡፡ የሚፈርድባት እግዚአብሄር ብርቱ ነውና፡፡
የሞት መቅሰፍቶች የሆኑት ሰባቱ መቅሰፍቶች ሲወርዱ በዚህ ዓለም ላይ በአንድ ቀን ሐዘንና ራብ ይመጣሉ፡፡ በዚህም ጸረ ክርስቶስና የእርሱ ዓለማዊ ተከታዮች በሙሉ ለዘላለም በሲዖል ይቃጠሉ ዘንድ ይቀጣሉ፡፡
 
ቁጥር 9፡- ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፡፡
የዓለም ሕዝቦችና ነገስታቶች ዓለማቸው በእሳትና በመሬት መናወጦች ተውጣ በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ስትጠፋ በራሳቸው ዓይን ያያሉ፡፡ ስለዚህ የዓለም ነገሥታቶች ለደረሰባቸው ጥፋት ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፡፡
 
ቁጥር 10፡- ስቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው፡- አንቺ ታላቂቱ ከተማ፤ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን ወዮልሽ ወዮልሽ፤ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ፡፡
ይህ ዓለም እንደማይወድቅ ያላመኑ ሰዎች መላው ዓለም በዓይኖቻቸው ፊት በተጨባጭ ሲፈረካከስ ሲያዩ በፍርሃት ይመታሉ፡፡ በውበቱ በሚያብለጨልጨው ዓለም ላይ የእግዚአብሄር ፍርድ በአንድ ቀን ይወርዳል፡፡ ሁሉም በአንድ ጊዜ ይወድቃል፡፡
 
ቁጥር 11-13፡- የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለም፡፡ የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፡፡ ጭነትም፣ ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ፣ ዕንቁም፣ ቀጭንም፣ ተልባ እግር፣ ቀይም ሐርም፣ ሐምራዊም ልብስ፣ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፣ እጅግም ከከበረ እንጨት፣ ከናስም፣ ከብረትም፣ ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋም፣ ቅመምም፣ የሚቃጠልም ሽቱ፣ ቅባትም፣ ዕጣንም፣ የወይን ጠጅም፣ ዘይትም፣ የተሰለቀ ዱቄትም፣ ስንዴም፣ ከብትም፣ በግም፣ ፈረስም፣ ሰረገላም፣ ባርያዎችም፣ የሰዎችም ነፍሳት ነው፡፡
የዓለም ጥፋት በሚቃረብበት ጊዜ መግዛት ወይም መሸጥ የሚችል ማነው? የምድር ነጋዴዎችም እንደዚሁ በዓለማቸው መጥፋት ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲያወርድ ማንም በመላው ዓለም ላይ ምንም ነገር አይገዛም፡፡ ይህ ዓለም ዳግመኛ ከቶውኑም አይገነባም፡፡ በእርሱ ፍርስራሽ ላይ የሚገነባው የክርስቶስ መንግሥት ብቻ ይሆናል፡፡
ሰዎች እስከዚህች ቀን ድረስ ራሳቸውን የሚያቀማጥሉባቸው ማቀማጠያዎች የንግድ ዕቃዎች ዝርዝር ቀርቦዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንድ ቀን ውስጥ ዋጋ የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ ዳግመኛ እነዚህን ዓለማዊ ነገሮች የሚሻ ሰውም አይኖርም፡፡ የዓለም ሐይማኖቶች የነገዱት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ነው፡፡ የዓለም ሐይማኖቶች ለገንዘብ ካላቸው ፍቅር የተነሳ የሰዎችን ነፍሳት በገንዘብ ለመሸጥ ሳያመነቱ ሊታሰብ የሚችለውን ነገር ሁሉ አድርገዋል፡፡
 
ቁጥር 14-18፡- ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፡፡ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም፡፡ እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ፡- በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጎናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት ወዮላት፤ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሳ በሩቅ ይቆማሉ፡፡ የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባህርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ፡- ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ፡፡
ስለዚህ ሰዎች ዳግመኛ ዓለማዊ ሐብቶቻቸውን ከቶውኑም አያገኙትም፡፡
በዚህ ዓለም አማካይነት ባለጠጋ የሆኑ ነጋዴዎች ዓለማቸው ሲወድም ሲያዩ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ በተስፋ መቁረጥ ያለቅሳሉ፡፡ ምክንያቱም ዓለም ሲወድቅ እነርሱም ከእርሱ ጋር አብረው ይወድቃሉና፡፡ ያከማቹት ሐብትም በአንድ ቀን ውስጥ ይወድማሉ፡፡
በዓለማዊ ሐብት ላይ የተገነቡት ሐይማኖቶች ሲወድቁ የዚህ ዓለም ሕዝቦችም ‹‹ወዮ! ወዮ!›› እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ ዓለምን የሚያካልሉ ዓለም ዓቀፍ ነጋዴዎችና መርከበኞችም እንደዚሁ ያለቅሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹የሰው ዘር ከገነባው ከዛሬው ሥልጣኔ የበለጠና የተሻለ ሌላ ሥልጣኔ እንዴት ይኖራል?›› በማለት ተስፋ ቆርጠው ያለቅሳሉ፡፡
 
ቁጥር 19፡- በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያነቡ፡- በባህር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለጠግነትዋ የተነሣ ባለጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት ወዮላት፤ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ፡፡
ዓለም በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲወድም በማየት ይህ ዓለም ለዘላለም ይቆያል ብለው ያሰቡ ሁሉ በታላቅ ሐዘን ያለቅሳሉ፡፡ ገናም በዚህ ዓለም ላይ የቀሩት ሰዎች መላው ዓለም በአንድ ጊዜ እግዚአብሄር ባወረዳቸው በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲወድም ሲያዩ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ልቅሶዋቸው በሙሉ ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ያን ጊዜ ይህ ዓለምና በውስጡ ያለው እያንዳንዱ ነገር አስቀድሞ ጠፍቷልና፡፡ ያን ጊዜ ለማልቀስ ጉልበት ኖሮዋቸው ከሆነ ሊያለቅሱ የሚገባቸው ስለ ራሳቸው ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ለሲዖል ታጭተዋልና፡፡ ከዘላለም ጥፋታቸው ለመዳንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን ይኖርባቸዋል፡፡
 
ቁጥር 20፡- ሰማይ ሆይ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ነቢያትም ሆይ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ እግዚአብሄር ፈርዶላችኋልና፡፡
በአየር የተነጠቁት ቅዱሳን የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲወርዱ ይደሰታሉ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በእነዚህ መቅሰፍቶች ሁሉንም ይበቀልላቸዋልና፡፡ እግዚአብሄር በጠላቶቹ ላይ አስፈሪዎቹንና ታላላቆቹን መቅሰፍቶች ማውረዱ ትክክል ነው፡፡
 
ቁጥር 21፡- አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባህር ወረወረው እንዲህ ሲል፡- ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም፡፡
እግዚአብሄር እዚህ ላይ ወፍጮ ወደ ባህር እንደሚጣል ይህም ዓለም ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይገኝ ይናገራል፡፡ ያን ጊዜ ጌታችን መላውን ዩኒቨርስና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ያድስና ይህችን ምድር ወደ ክርስቶስ መንግሥት የመለወጡን ሥራውን ይፈጽማል፡፡
 
ቁጥር 22፡- በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምጽ፣ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፡፡ የእጅ ጥበብም ሁሉ፣ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፡፡
የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲያበቁ ሰዎች ከዚህ በፊት በዚህ ዓለም ላይ ሲሰሙት የነበረው የዘፈን ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ አይሰማም፡፡ የጥበበኞችም መዶሻዎች ከእንግዲህ ወዲህ አይሰሙም፡፡
 
ቁጥር 23፡- የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፡፡ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና፡፡
የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ሲጠናቀቁ ይህ ዓለም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ የመብራት ብርሃንን አያይም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም የሙሽራውንና የሙሽራይቱን ድምጽም አይሰማም፡፡ የዓለም አስማተኞች ማታለልም እንዲሁ ያበቃል፡፡ ዓለም አብቅቶለታልና፡፡
 
ቁጥር 24፡- በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት፡፡››
እግዚአብሄር የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በዚህች ምድር ላይ የሚያወርደው የሰይጣን አገልጋዮች የእርሱን ነቢያትና ቅዱሳን ደም ስላፈሰሱ ነው፡፡