Search

布道

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-10] በመታጠቢያው ሰን የተገለጠው እምነት፡፡ ‹‹ ዘጸዓት 30፡17-21 ››

በመታጠቢያው ሰን የተገለጠው እምነት፡፡
‹‹ ዘጸዓት 30፡17-21 ››
‹‹ከዚያም እግዚአብሄር ሙሴን አለው፤ ለመታጠቢያ ከናስ ማስቀመጫው ጋር የናስ ሰን አብጅ፡፡ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት፡፡ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በውስጡ ባለው ውሃ እጃቸውንና እገራቸውን ይታጠቡበታል፡፡ ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ እንዳይሞቱ በውሃ ይታጠቡ፡፡ እንዲሁም ለእግዚአብሄር የእሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠባሉ፡፡ ይህም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለአሮንና ለትውልዶቹ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፡፡››
 
 
በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ ያለው የመታጠቢያው ሰን፡፡ 
 
የናሱ የመታጠቢያ ሰን
 
ቁስ፡- ከነሐስ የተሰራ ሲሆን ሁልጊዜም በውሃ የተሞላ ነበር፡፡
 
መንፈሳዊ ትርጉም፡- ነሐስ ማለት የሰው ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ፍርድ ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች ኩነኔ በሙሉ ለመሸከም በዮሐንስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ ስለዚህ የመታጠቢያው ሰን ትርጉም እነዚህ ሐጢያቶቻችን በሙሉ በጥምቀቱ ወደ ኢየሱስ መሻገራቸውን በማመን ከሐጢያቶቻችን በሙሉ መታጠብ የምንችል መሆናችንን የሚያሳይ ነው፡፡
 
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉት ካህናቶችም እንደዚሁ እንዳይሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ከመግባታቸው በፊት እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠባሉ፡፡ ነሐስ በሐጢያቶች ላይ የሚመጣውን ፍርድ ያመለክታል፡፡ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ያለው ውሃም ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በራሱ ላይ የወሰደበትን ከዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር የመታጠቢያው ሰን ኢየሱስ ወደ እርሱ የተሻገሩትን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ መውሰዱንና የእነዚህን ሐጢያቶች ኩነኔ መሸከሙን ይነግረናል፡፡ በብሉይ ኪዳን የመታጠቢያው ሰን ማለት የመገናኛው ድንኳን ሰማያዊ ማግ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ደግሞ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀት ማለት ነው፡፡ (ማቴዎስ 3፡15፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)
 
ስለዚህ የመታጠቢያው ሰን የኢየሱስን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ይህም ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን፤ በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶቻችንን ጨምሮ የመሸከሙንና ከ2,000 ዓመታት በፊት ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ያስወገደ በመሆኑ እውነት እምነታችንን የምናጸናበት ስፍራ ነው፡፡
 
በዚህ ዓለም ላይ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ የተወለዱ ጻድቃን አሉ፡፡ እነዚህ ሐጢያቶቻቸው በሙሉ በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በጥሩ በፍታ በተገለጡት የኢየሱስ ሥራዎች ይቅር መባላቸውን በማመን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የተቀበሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሐጢያትን ስርየት የተቀበሉ ጻድቃን የቀን ተቀን ሐጢያቶቻቸውን ችግር ለማቃለል የሚመጡበት ስፍራ የመታጠቢያው ሰን እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ጻድቃን በየቀኑ ሐጢያቶችን በሚሰሩበት ጊዜ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ወዳለው የመታጠቢያ ሰን ይመጡና እጆቻውንና እግሮቻቸውን ይታጠባሉ፡፡ በዚህም ኢየሱስ በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል በማመናችን ቀድሞውኑም በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ይቅር ያለን የመሆኑን እውነታ ያጸናልናል፡፡
 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ውሃ አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሄርን ቃል ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሎዋል፡፡ ነገር ግን የውሃ እጅግ አስፈላጊው ትርጉም የኢየሱስ ጥምቀት ነው፡፡ ኤፌሶን 5፡26 እንዲህ ይላል፡- ‹‹በውሃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት፡፡›› ዮሐንስ 15፡3 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እናንተ ስለነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሃን ናችሁ፡፡›› የመታጠቢያው ሰን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት የተቀበሉት ቅዱሳን ሥጋቸው ምንም ያህል ብቁ ባይሆንም ጌታ ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ይቅር እንዳላቸው ማረጋገጫን እንዲይዙ ያስችላቸዋል፡፡
 
1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 እና 22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን ዕድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአበሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡ እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ሐይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሄር ቀኝ አለ፡፡›› ከእነዚህ ቁጥሮች ጥቂት ቀደም ብሎ ጴጥሮስ በኖህ ዘመን የሆነውን የጥፋት ውሃ መንፈሳዊ ትርጉም አብራርቷል፡፡ ኖህ ሐጢያተኞችን ቢያሰጠነቅቅም በሐጢያት እስራት ውስጥ ከነበሩትና የቀደመውን ዓለም ርኩሰት በሙሉ በሚያስወግደው የጥፋት ውሃ ውስጥ ካለፉት ውስጥ በውሃው አማካይነት የዳኑት ስምንት ነፍሳት ብቻ ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የጥፋት ውሃ በእግዚአብሄር ቃል ፈጽሞ ያላመኑትን ሁሉ አጠፋቸው፡፡ አሁን ደግሞ ጴጥሮስ ከጥፋት ውሃ ኩነት ውስጥ የኢየሱስ ጥምቀት የዚህ ምሳሌ እንደሆነ አብራርቷል፡፡ ስለዚህ የመታጠቢያው ሰን ዳግመኛ በእግዚአብሄር ፊት የዳንበትንና ከዳንን በኋላ ያለውን ሁኔታችንንም የምናረጋግጥበት ስፍራ ነው፡፡
 
በእምነት ከሐጢያቶቻቸው የዳኑ ቅዱሳን በመታጠቢያው ሰን ውሃ፣ (የኢየሱስ ጥምቀት) ነሐስ (በሐጢያቶች ላይ የሚወርድ ፍርድ) እና ኢየሱስ ከሐጢያቶቻቸው ያዳናቸው መሆኑን በማመን የእግዚአብሄርን ጸጋ ይጎናጸፋሉ፡፡ በድካሞችና በጉድለቶች የተሞላን በመሆናችን ራሳችንን ጻድቃን አድርገን መቁጠር ባንችልም በኢየሱስ ጥምቀትና (ሐጢያቶቻችን መሸከም ማለትም ውሃ) በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ (የሐጢያቶች ኩነኔ ማለትም ነሐስ) ያለንን እምነት እንደገና ቀድሰን በመስጠት ሙሉ በሙሉ ጻድቃን መሆናችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ሁላችንንም ከሐጢያቶቻችንና ከእነዚህ ሐጢያቶች ኩነኔ በሙሉ ቀድሞውኑም ባዳነን የእግዚአብሄር ቃል በማመናችን ሁልጊዜም ሐጢያት አልባ ጻድቃን ልንሆን እንችላለን፡፡
 
እኛ ያመንበት የእግዚአብሄር ቃል ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ እንደወሰደ፣ በእኛም ፋንታ የሐጢያቶችን ኩነኔ በሙሉ በመሸከም በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰና ሙሉ በሙሉም ከሐጢያቶቻችን እንዳዳነን ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ያስቀመጠው ሁኔታዎች ምንም ሊሆኑ ቢችሉም እኛን ፈጽሞ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የዳንን ስለመሆናችን እምነታችንን እንድናጸና ነው፡፡
 
 
ከቀን ተቀን ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ ለዘላለም ነጻ ወጥታችኋልን?
 
ኢየሱስ የፋሲካውን ሕብስትና ወይን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከተካፈለ በኋላ በመጨረሻው እራት ወቅት በመስቀል ላይ ከመሞቱ በፊት የጴጥሮስንና የሌሎቹን ደቀ መዛሙርት እግሮች በውሃ ሊያጥብ ፈለገ፡፡ ኢየሱስ ቀድሞውኑም ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት የደቀ መዛሙርቱን ሐጢያቶች በሙሉ ስለወሰደ የመታጠቢያውን ሰን እውነት ሊያስተምራቸው ፈለገ፡፡ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ የፋሲካ ጠቦት ሆኖ በእንጨት ላይ በመሰቀል የሐጢያትን ዋጋ እንደሚከፍል ነግሮዋቸዋል፡፡ ስለዚህ አስራ ሁለቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብቁ ባይሆኑም ዳግመኛ ከቶውኑም ሐጢያተኞች አልሆኑም፡፡
 
ኢየሱስ እግሮቻቸውን የማጠቡ እውነት የእውነት ቃል የመሰከረውን ማለትም ኢየሱስ ቀድሞውኑም የዓለም ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ ያስወገደ መሆኑን አረጋግጦላቸዋል፡፡ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ አዳኝ እንደሆነ ሁልጊዜም ለዓለም ሕዝብ የሚሰብኩትና ቀድሞውኑም የፈጸመውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚያሰራጩት ለዚህ ነው፡፡ (ዕብራውያን 10፡1-20) ስለዚህ የመታጠቢያው ሰን ይህንን እውነት በማመን ከሐጢያቶቻቸው በሙሉ የዳኑትን የኢየሱስን ጥምቀት እንዲያስታውሱ ይፈቅድላቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ራሱ ያዳናቸው የመሆኑን የደህንነት አመኔታም ይሰጣቸዋል፡፡
 
 
መጽሐፍ ቅዱስ የመታጠቢያውን ሰን መጠን አልመዘገበም፡፡ 
 
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያለው የእያንዳንዱ ነገር መጠን የተመዘገበ ቢሆንም የመታጠቢያው ሰን መጠን ግን አልተመዘገበም፡፡ ይህም የእግዚአብሄር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የመውሰዱ እውነታ ከልክ በላይ ታላቅ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔያችን ያዳነን የኢየሱስ ፍቅር ወሰን የለሽ እንደሆነም ይነግረናል፡፡ የመታጠቢያው ሰን መጠን ልክ የሌለውን የእግዚአብሄርን ታላቅ ፍቅር ይገልጣል፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን በሕይወት እስካሉ ድረስ ሐጢያት ለመስራት የታጩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድና በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን በማፍሰስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለዘላለም ደመሰሳቸው፡፡
 
የመታጠቢያው ሰን የተሰራው በመገናኛው ድንኳን የሚያገለግሉት ሴቶች ያመጡትን የነሐስ መስተዋቶች በማቅለጥ ነበር፡፡ (ዘጸዓት 38፡8) ይህ ማለት የእግዚአብሄር ቃል በሐጢያተኞች ላይ የደህንነትን ብርሃን በማብራት ጨለማቸውን ያስወግዳል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን ያዘጋጀው እርሱ ራሱ ሐጢያቶቻችን ማንጻት ይችል ዘንድ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ ይህ የእውነት ቃል በልባቸው ጥልቅ ውስጥ በተደበቁት የሰዎች ሐጢያቶች ላይ ብርሃኑን በማብራት ሐጢያቶቻቸውን ለዘላለም አስወግዶ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ሰጣቸው፡፡ ጻድቃንም አደረጋቸው፡፡ በሌላ አነጋገር የመታጠቢያው ሰን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ሐጢያተኞቹን ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሄር ቃል ያዳነን የመሆኑን እውነት በግልጽ የመመስከሩን ሚና ይጫወታል፡፡
 
 
የመታጠቢያውም ሰን የተሰራው እንዲሁ ከነሐስ ነበር፡፡ 
 
የመታጠቢያውን ሰን ለመስራት ጥቅም ላይ የዋለው ነሐስ ትርጉም ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ነሐስ እኛ ልንጋፈጠው የነበረውን የሐጢያት ኩነኔ ያመለክታል፡፡ ይበልጥ ግልጽ ለመሆን ነሐስ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወደ መስቀል በመውሰድ በእኛ ፋንታ እንደተኮነነ ይነግረናል፡፡ ለሐጢያቶቻችን በእርግጥ መኮነን የነበረብን እኛ ነበርን፡፡ ነገር ግን በመታጠቢያው ሰን ውሃ አማካይነት ሐጢያቶቻችን በሙሉ እንደጸዱ ዳግመኛ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ በዚህ የሚያምኑ በእምነታቸው አማካይነት ፍርድን ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ አንዳች ፍርድ አይጠብቃቸውም፡፡
 
በውሃ የተሞላው የመታጠቢያው ሰን ‹‹በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ኢየሱስ ቀድሞውኑም ሐጢያቶቻችሁን እንዳነጻና ሙሉ በሙሉ እንዳዳናችሁ›› ይነግራችኋል፡፡ በሌላ አነጋገር የመታጠቢያው ሰን የሐጢያት ስርየትን ያገኙ ጻድቃን ከሐጢያቶቻቸው ነጽተው ለመዳናቸው ትክክለኛ ማረጋገጫ ነው፡፡
 
የሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ የሐጢያትን ፍርድ ሲያመለክት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ካሉት ቁሳ ቁሶች መካከል ከሰማያዊው ማግ ጋር የሚዛመደው የመታጠቢያው ሰን ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ እንደወሰደ ይነግረናል፡፡
 
ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት የምንችለው የመገናኛውን ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር ከፍተን በመግባትና የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያና የመታጠቢያውን ሰን በማለፍ ነው፡፡ እግዚአብሄር ወደሚኖርበት የመገናኛው ድንኳን መግባት የሚችሉት የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያና የመታጠቢያውን ሰን በእምነት ማለፍ የሚችሉ ብቻ ናቸው፡፡ ወደ ቅድስቱ ክፍል መግባት የሚችሉት በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ባለው የመታጠቢያው ሰን በማመን የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉ ብቻ ናቸው፡፡
 
አንድ ሰው በራሱ ጉልበት ወደ ቅድስቱ ስፍራ ለመግባት ቢሞክር እሳት ከቅድስቱ ስፍራ ወጥቶ ይበላዋል፡፡ የአሮን ልጆች እንኳን ከዚህ አላመለጡም፡፡ አንዳንዶቹም እንደሞቱ ይታወቃል፡፡ (ዘሌዋውያን 10፡1-2) እግዚአብሄር ሐጢያቶችንና ፍርድን በጽድቅ መሸከሙን የማያውቁና ይህንን እውነት ችላ የሚሉ በሐጢያቶቻቸው ምክንያት ይሞታሉ፡፡ እጅግ በላቀው ከሐጢያት መዳን በማመን ፋንታ በራሳቸው አስተሳሰቦች በማመን ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎች ለሐጢያቶቻቸው የእግዚአብሄር እሳት እንደሚወርድባቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ ከዚህ ከማይቀረው የሐጢያት ፍርድ የተነሳ በውጤቱ የሚጠብቃቸው ነገር ቢኖር ሲዖል ብቻ ነው፡፡
 
ኢየሱስ ከሐጢያት የመዳናችንን ነገር ያጠናቀቀው በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በጥሩ በፍታ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት እንችላለን፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ የዳንነው በዚህ እውነት በማመናችን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ዘር ከሐጢያት ለማዳን ያቀደው ከፍጥረት በፊት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው በሰማያዊው ማግ፣ (የኢየሱስ ጥምቀት) በቀዩ ማግና (ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱ) በሐምራዊው ማግ (እግዚአብሄር ሰው መሆኑ) እውነት አማካይነት የእርሱን ፈቃድ በዝርዝር እንወቅ፡፡ በዚህ ዕቅድ መሰረት በእነዚህ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማጎች በተገለጡት የኢየሱስ ሥራዎች አማካይነት በእርግጥም ሐጢያተኞችን በሙሉ ከሐጢያቶቻቸውና ከበደሎቻቸው አድኖዋቸዋል፡፡
 
1ኛ ዮሐንስ 5፡4 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው፡፡›› ይህን ተከትሎ በቁጥር 10 ላይም እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእግዚአብሄር ልጅ የሚያምን በራሱ ምስክር አለው፡፡›› ይህ የደህንነት ምስክር ምንድነው? በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ አማካይነት ደህንነታችንን የሰጠን የወንጌል እውነት በእግዚአብሄር ልጅ ያለን የእምነታችን ምስክርነት ነው፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 5፡6-8) በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን አንጽቶን የራሱ ሕዝብ ያደረገን ለመሆኑ ማስረጃው የምናምንበት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የምንድንበት፣ ወደ ቅድስቱ ስፍራ የምንገባበት፣ በእግዚአብሄር የተሰጠንን የሕይወት እንጀራ የምንመገብበት፣ በእርሱ ጸጋ ውስጥ የምንኖርበት ብቸኛው መንገድ በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር ሕብረት ፈጥረን አሁኑኑ መዳንና የእምነት ሕይወታችንን መኖር አለብን፡፡
 
በእርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሄርን ቃል መመገብ የምንችለው፣ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር የምንተባበረውና ጸሎቶቻቸው በእግዚአብሄር ዘንድ የሚሰማላቸው ጻድቃን ሆነን የምንኖረው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት ነው፡፡ በዚህ እውነት ስናምን የሰማያዊው፣ የሐምራዊውና የቀዩ ማግ እምነት ያላቸውና በፊቱም የእግዚአብሄርን ጸጋ ተጎናጽፈው የሚኖሩ ጻድቃን ልንሆን እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ሕዝብ ብቻ የሚኖረው የእምነት ሕይወት የሚመጣው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ በልባችን በኢየሱስ ጥምቀት፣ ባፈሰሰው ደሙ፣ በሞቱና ኢየሱስ ራስ አምላክ እንደሆነ በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን እንችላለን፡፡ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ እንድትኖሩ የሚያስችላችሁ እምነት በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ላይ ያላችሁ እምነት ነው፡፡
 
በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ‹‹ማድረግ የሚኖርብን ነገር በኢየሱስ ማመን ብቻ ነው? በእነዚህ ሁሉ ግራ መጋባቶች ለምን እንቸገራለን? በማይረቡ ንግግሮች ጊዜያችንን አናጠፋ፡፡ ተስማሚ ነው ብለን በምናምነው በማንኛውም ነገር እንመን›› ይላሉ፡፡ እኛ ለእነዚህ ሰዎች በክርስትና ውስጥ ችግር ፈጣሪዎች እንመስል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጣም ግልጽ የሆነው ነገር የሐጢያቱን ስርየት ሳያገኝ በኢየሱስ የሚያምን ሰው የዘላለም ኩነኔ የሚገጥመው መሆኑ ነው፡፡ በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ ወንጌል ሙሉ በሙሉ የማያምን እምነት ሐሰተኛና እንከን ያለበት እምነት ነው፡፡ እንዲያውም ኢየሱስን አዳኝ አድርጎ አለማመን ነው፡፡
 
እኔ የአንድን እንግዳ ሰው ሞገስ ለማግኘት ፈልጌ ለዚህ እንግዳ ሰው በጭፍን ‹‹በአንተ አምናለሁ›› ብዬ ሙጭጭ ብል ይህ ሰው ‹‹ይህ ግለሰብ በእርግጥም በእኔ ያምናል›› ብሎ በማመን በዚህ ይደሰታልን? በተቃራኒው ምናልባት ‹‹ታውቀኛለህን? የማውቅህ አይመስለኝም›› ይል ይሆናል፡፡ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ለማድረግ በመሞከር በሚያባብሉ ዓይኖች ተመልክቼው እንደገና ‹‹ነገር ግን አሁንም በአንተ አምናለሁ›› ብለው ያን ጊዜስ ደስ ይለዋልን? አእምሮውን ለማንበብና የእርሱን ድጋፍ ለማግኘት የምሞክር ዕብድ መስዬ ልታየው እችላለሁ፡፡
 
እግዚአብሄርም በጭፍን በእርሱ በሚያምኑ ሰዎች አይደሰትም፡፡ ‹‹በእግዚአብሄር አምናለሁ፤ ኢየሱስ የሐጢያተኞች አዳኝ በመሆኑ አምናለሁ›› ስንል ኢየሱስ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች እንዴት እንዳስወገደ ካወቅንና ካመንን በኋላ እምነታችንን መግለጥ አለብን፡፡ ምንም ዓይነት ጥንካሬ የሌለን ይመስል በደፈናው በዕውር ድንብር የምናምን ከሆንን በጭራሽ መዳን አንችልም፡፡ መዳን የምንችለው በመጀመሪያ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን እንዴት እንዳስወገዳቸው በግልጽ በማወቅ ስናምን ብቻ ነው፡፡ በአንድ ሰው እንደምናምን ስንናገር በዚህ ሰው በተጨባጭ እንተማመናለን፡፡ ምክንያቱም ይህንን ሰው በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ የሚታመን ሰውም እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በሚገባ በማናውቀው ሰው መተማመን ማለት ወይ እየዋሸን ነው አለበለዚያም ለክህደት የታጨን ሞኞች ነን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ እናምናለን ስንል ኢየሱስ እንዴት ሐጢያቶችንን በሙሉ እንዳስወገደ በትክክል ማወቅ አለብን፡፡ ጌታችን በመጨረሻዋ ሰዓት የማይተወንና ዳግመኛ የተወለድን ልጆች ሆነን ሰማይ የምንገባው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡
 
ወደ ሰማይ ሊመራን የሚችለው እምነት የሰማያዊው፣ የሐምራዊውና የቀዩ ማግ እምነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እውነተኛው እምነት በውሃው፣ (የኢየሱስ ጥምቀት) በደሙና (የኢየሱስ ሞት) በመንፈስ ቅዱስ (ኢየሱስ አምላክ ነው) አማካይነት ባዳነን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማመን ነው፡፡ የጌታችን ጸጋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ማወቅና በእርሱም ማመን አለብን፡፡ ምክንያቱም ወደ ደህንነታችን የሚመራን በዚህ እውነት ማመን ነውና፡፡
 
የአንድ ሰው እምነት ሙሉ መሆኑና አለመሆኑ የሚወሰነው ይህ ሰው እውነትን በማወቁና ባለማወቁ ነው፡፡ ኢየሱስ አዳኛችሁ መሆኑን ማመን የምትችሉት በልባችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስታምኑ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የሐጢያት ስርየትን የሰጠን ይህ ኢየሱስ አዳኛችን የመሆኑ እምነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን እውነተኛ እምነት ነው፡፡
 
 

የመታጠቢያው ሰን ሐጢያቶቻችን ይቅር መባላቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ 

 
የመታጠቢያው ሰን በውሃ ተሞልቷል፡፡ የተቀመጠውም ከቅድስት ክፍል ፊት ለፊት ነው፡፡ የመታጠቢያው ሰን የሐጢያት ስርየትን እንደተቀበልን ራሳችንን የምናስታውስበትና በእምነት መቀበላችንን የምናረጋግጥበት ስፍራ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሄር የአማኞችን ሐጢያቶች በሙሉ እንዳስወገደ ማረጋገጫ ነው፡፡ በቅድስቱ ስፍራ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት በቆሸሹ ጊዜ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በመታጠቢያው ሰን ውስጥ እንደሚታጠቡ ሁሉ የሐጢያት ስርየትን የተቀበሉትም ሐጢያት በሰሩ ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ በይፋ ተኮንኖ ቀድሞውኑም ያረከሱዋቸውን እነዚህን ሐጢያቶች እንደደመሰሰና እንዳስተሰረየ ዳግመኛ ራሳችንን በማስታወስና ይህንንም በእግዚአብሄር ቃል በማረጋገጥ ከእነዚህ ሐጢያቶቻችን እንነጻለን፡፡
 
የምንረክሰው በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር ሐጢያት በመስራት ስለምንቀጥል ነው፡፡ ታዲያ የሚያረክሱንን እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ ማንጻት የሚገባን በምንድነው? የምናነጻው የነገሥታት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2,000 ዓመታት በፊት የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር መምጣቱን፣ በጥምቀቱም ሐጢያቶቻቸውን በሙሉ በራሱ ላይ መውሰዱን፣ በመስቀል ላይ ደሙን ማፍሰሱንና በዚህም የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ሁሉ ይቅር ማለቱን በማመን ነው፡፡ የሐጢያት ስርየት መቀበል የምንችለውና በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች ማስወገድ የምንችለው ኢየሱስ በመጠመቅ ሐጢያቶችን በሙሉ በራሱ ላይ የወሰደ የመሆኑን እውነት ስናምን ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በየቀኑ ከምንሰራቸው ሐጢያቶች መንጻት የምንችለው እግዚአብሄር ቀደሞውኑም በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ አማካይነት ያስወገዳቸው ስለመሆኑ በዚህ እውነት ስናምን ብቻ ነው፡፡
 
 
የመታጠቢያውን ሰን እውነት የሚያውቅና የሚያምን እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡
 
በመታጠቢያ ሰን ሳናምን እግዚአብሄር ወደሚያድርበት ቅድስት ስፍራ በፍጹም መግባት አንችልም፡፡ ምግባሮቻችንን ሁልጊዜም ፍጹም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ድካሞች ስላሉብን በየጊዜው ሐጢያት እንሰራለን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር የሰጠን ደህንነት ፍጹም ነው፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄር ቃል ፍጹም ነውና፡፡ እግዚአብሄር ድካሞቻችንን ፍጹም በሆነው ደህንነቱ ስላስወገደ በእምነት ወደ ቅድስቱ ስፍራ በድፍረት መግባት እንችላለን፡፡ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ የማያልፉ በጭራሽ ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት አይችሉም፡፡ እኛ ወደ ቅድስቱ ስፍራ ለመግባት ብቁ የሆነው ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ወደዚህ ምድር መጥቶ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ አማካይነት በተተነበየው መሰረት በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ ወንጌል የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ያስወገደ በመሆኑ እውነት ስላመንን ነው፡፡ እግዚአብሄር ቀድሞውኑም ሐጢያቶቻችንን ደምስሶ ሐጢያት አልባ እንዳደረገን ሳናምን ወደ ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት አንችልም፡፡
 
በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ሳናምን ወደ እግዚአብሄር መቅደስ መግባት እንደማንችል ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማናምን ከሆነ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በሚሰበከው ቃሉ ወደ እርሱ በመጸለይ፣ ጸጋውን በመቀበልና ከአገልጋዮቹና ከቅዱሳኑ ጋር በመኖር አምነን ወደ እግአብሄር የጸጋ ዙፋን በመቅረቡ በረከት አንደሰትም፡፡ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ አብረውን ከሚያምኑ ምዕመናኖች ጋር ሕይወታችንን ልንኖር፣ ቃሉን ልንሰማ፣ ልናምንና ወደ እርሱ ልንጸልይ የምንችለው እግዚአብሄር ቀድሞውኑም በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ አማካይነት ከሐጢያቶቻችን እንዳዳነን ስናምን ብቻ ነው፡፡
 
የመታጠቢያው ሰን ከሐጢያት ለመዳናችን የመጨረሻው ማረጋገጫ ነው፡፡ እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን በቅድስቱ ስፍራ ፊት ለፊት ያስቀመጠውና በውሃ የሞላው በሐጢያት ስርየት ወንጌል ለሚያምኑት የእምነት ማረጋገጫን ለመስጠት ነው፡፡ ይህ የመታጠቢያ ሰን የሚያምኑትን ጻድቃን የረከሱ ሕሊናዎች ያነጻል፡፡
 
1ኛ ዮሐንስ 2፡1-2ን እናንብብ፡- ‹‹ልጆቼ ሆይ ሐጢአትን እንዳታደርጉ ይህንን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ሐጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የሐጢአታችን ማስተሰርያ ነው፡፡ ለሐጢአታችንም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ሐጢአት እንጂ፡፡›› አሜን፡፡
 
ሐጢአት ብንሰራ ከእግዚአብሄር ዘንድ የሆነ ጠበቃ አለን፡፡ እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ የረከሱትን የጻድቃን ልቦች በውሃ አጥቦ አንጽቶዋቸዋል፡፡ ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት ባለው ቀን በመጨረሻው እራት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን በአንድ ላይ ሰብስቦ በመታጠቢያው ሳህን ውስጥ ውሃ ከጨመረ በኋላ እግሮቻቸውን ማጠብ ጀመረ፡፡ ‹‹እኔ በተጠመቅሁ ጊዜ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ፣ በኋላ የምትሰሩዋቸውን ሐጢያቶችም ጨምሮ ተሸከምሁ፡፡ በእናንተ ፋንታም በመስቀል ላይ እኮነናለሁ፡፡ ወደፊት የምትሰሩዋቸውንም ሐጢያቶች እንደዚሁ በራሴ ላይ ወስጃለሁ፤ ደምስሻቸዋለሁ፡፡ የእናንተም አዳኝ ሆኛለሁ፡፡››
 
ኢየሱስ በፋሲካው የመጨረሻ እራት ወቅት የደቀ መዛሙርቶቹን እግሮች ያጠበው ይህንን ሊነግራቸው ነው፡፡ ኢየሱስ እግሩን እንዳያጥበው እምቢተኛ ለሆነው ጴጥሮስ እንዲህ አለው፡- ‹‹እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ፡፡›› (ዮሐንስ 13፡7) ኢየሱስ ከልባቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑት ፍጹም አዳኛቸው ሊሆን ፈለገ፡፡ ኢየሱስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ለሚያምኑት የዘላለም አዳኛቸው ሆንዋል፡፡
 
 
የመታጠቢያው ሰን ጠቀሜታው፡፡ 
 
የመታጠቢያው ሰን ጠቀሜታው፡፡
የመታጠቢያው ሰን ለእግዚአብሄር መስዋዕቶችን በማቅረብ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሲሰሩ የነበሩትን ካህናቶች ርኩሰት ሁሉ ለማስወገድ ያገለግላል፡፡ ካህናቶች የእስራኤልን ሕዝብ ሐጢያቶች ለማስተሰረይ በእግዚአብሄር ፊት መስዋዕት ሲያቀርቡ፣ ለመስዋዕት የቀረበውን እንስሳ ሲያርዱ፣ ደሙን ሲያፈስሱና ሲቆራርጡት በእነርሱ ላይ የቀሩትን ቆሻሻዎች አጥበው ማስወገድ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ካህናቶቹ መስዋዕቶችን ሲያቀርቡ ስለሚቆሽሹ በውሃ መታጠብ ነበረባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ርኩሰት የሚወገድበት ስፍራም የመታጠቢያው ሰን ነበር፡፡
 
በመንፈሳችን ወይም በሥጋችን ሐጢያት በምንሰራበት ጊዜ፣ የእግዚአብሄርን ትዕዛዛት በመጣስ በምንረከስበት ጊዜ ሁሉ በዚያ የመታጠቢያ ሰን ውሃ መንጻት አለብን፡፡ ካህናቶች ሰውነታቸው አንዳች ንጹህ ያልሆነ ወይም ቆሻሻ ነገር ሲነካ ወደዱም ጠሉም የቆሸሸውን የሰውነታቸውን ክፍል በውሃ መታጠብ ነበረባቸው፡፡
 
ልክ እንደዚሁ በእግዚአብሄር የሚያምኑ ሁሉ ከቆሻሻ ወይም ንጹህ ካልሆነ አንዳች ነገር ጋር ሲነካኩ የመታጠቢያው ሰን ውሃ እንደዚህ ያለውን ርኩሰት ሁሉ ለማንጻት ያገለግላል፡፡ በአጭሩ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ያለው ውሃ እንዲያገለግል የተሰጠው ዳግመኛ የተወለዱትን ሰዎች ርኩሰት ሁሉ ለማንጻት ነው፡፡ ስለዚህ የመታጠቢያው ሰን የእግዚአብሄርን ምህረት ይዞዋል፡፡ የመታጠቢያው ሰን ትርጉም ማመን ወይም አለማመን የምንመርጥበት የአማራጭ ዕቃ አይደለም፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ለሚያምኑት በጣም አስፈላጊ የሆነ ዕቃ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች መጠን በሙሉ ቁመታቸው፣ ርዝመታቸውና ወርዳቸው ምን ያህል ክንድ እንደሆነ በመዘርዘር አስቀምጦዋቸዋል፡፡ ነገር ግን የመታጠቢያውን ሰን መጠን አልዘረዘረም፡፡ ይህ የመታጠቢያውን ሰን ብቻ የሚመለከት ባህርይ ነው፡፡ ይህም በየቀኑ ሐጢያት በምንሰራው በእኛ ላይ መሲሁ ያለውን ማለቂያ የሌለው ፍቅር ይገልጣል፡፡ በዚህ የመሲሁ ፍቅር ውስጥ በእጆች መጫን መልክ ሐጢያቶቻችንን ባስወገደው ጥምቀቱ ውስጥ ይገኛል፡፡ ካህናቶቹ ተግባራቶቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ ስለሚቆሽሹ ብዙ ውሃ ጥቅም ላይ ስለሚውል የመታጠቢያው ሰን ሁልጊዜም በውሃ መሞላት አለበት፡፡ ስለዚህ የመታጠቢያው ሰን መጠን ከፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡የመታጠቢያው ሰን ከነሐስ የተሰራ በመሆኑ ካህናቶቹ በውስጡ ባለው ውሃ በሚታጠቡበት ጊዜ ሁሉ ስለ ሐጢያት ፍርድ ወደ ማሰብ ይመጡ ነበር፡፡
 
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉት ካህናቶች በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ባለው ውሃ የእጆቻቸውንና የእግሮቻቸውን ቆሻሻ በሙሉ መታጠብ ነበረባቸው፡፡ ነሐሱ የእግዚአብሄርን ፍርድ የሚያሳይ ከሆነ ውሃው ደግሞ ከሐጢያት መታጠብን ያመለክታል፡፡ ዕበራውያን 10፡22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰውነታችንንም በጥሩ ውሃ ታጥበን፡፡›› ቲቶ 3፡5ም እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ፡፡›› ልክ እንደ እነዚህ ምንባቦች የአዲስ ኪዳንም ቃል ቆሻሻን በጥምቀት ውሃ ስለ ማስወገድ ይነግረናል፡፡
 
ካህናቶች በሕይወታችን ውስጥ የተከማቸውን ርኩሰት በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ባለው ውሃ ካስወገዱ እኛም ዛሬ ዳግመኛ የተወለደን ክርስቲያኖች በሕይወታችን ውስጥ የሰራናቸውን የቀን ተቀን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በኢየሱስ ጥምቀት በማመን ማስወገድ እንችላለን፡፡ በብሉይ ኪዳን ያለው የመታጠቢያው ሰን ውሃ መሲሁ ወደዚህ መድር መጥቶ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ እንዳስወገደ ያሳየናል፡፡
 
እግዚአብሄር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ከዮሐንስ ጥምቀት ወደ እርሱ ያሻገረው የእስራኤል ሕዝብ የሰሩትን ሐጢያቶች ብቻ ሳይሆን በመላው ሰብዓዊ ታሪክ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሰሩዋቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ጭምር ነው፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ በማቴዎስ 3፡15 ላይ እንዲህ አለ፡- ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጸድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› ኢየሱስ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በሰውነቱ ላይ ወሰደ፡፡
 
ስለዚህ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በጥምቀቱ አማካይነት ወደ መሲሁ ኢየሱስ የተሻገሩ በመሆናቸው እውነት በማመን ሁላችንም በልባችን ውስጥ ካለው የሐጢያቶች ርኩሰት ሁሉ መንጻት እንችላለን፡፡ በዚህ እውነት በማመን ሁላችንም በልባችን ውስጥ ካለው የሐጢያቶች ርኩሰት ሁሉ መንጻት እንችላለን፡፡ በዚህ እውነት በማመን ቀድሞውኑም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ወደ ኢየሱስ ስላሻገርን ማድረግ የሚኖርብን ነገር ቢኖር የእግዚአብሄር ልጅ የዓለምን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ እንደተሸከመ፣ እንደተሰቀለ፣ ደሙን እንዳፈሰሰ፣ ለሰው ዘር በሙሉም ፍጹም መስዋት እንደሆነና ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንዳዳነን ማመን ብቻ ነው፡፡ ይህንን በልባችሁ ታምናላችሁን? መሲሁ የመስዋዕት ቁርባናችን መሆኑን ከልባቸው የሚያምኑ ለዘላለም ይድናሉ፡፡
 
 

በየቀኑ የምንሰራቸው ሐጢያቶች ችግር በኢየሱስ ጥምቀት በማመን ሊወገድ ይችላል፡፡ 

 
መጽሐፍ ቅዱስ በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች እንዴት ማስወገድ እንደምንችል ይነግረናልን? በብሉይ ኪዳን ካህናቶች ርኩሰታቸውን በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ባለው ውሃ እንደሚያነጹ ሁሉ በአዲስ ኪዳንም ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት በራሱ ላይ በመውሰድ የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንደፈጸመ በማመን በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች ስርየት መቀበል እንችላለን፡፡ በመጨረሻም በእውነት በማመን ሐጢያቶች ሁሉ ይወገዳሉ፡፡
 
የእስራኤል ሕዝብ ለእግዚአብሄር የሐጢያት መስዋዕታቸውን ሲያቀርቡ እንደ በግ ወይም ፍየል ያለ ነውር የሌለበት የመስዋዕት እንስሳ ወደ መገናኛው ድንኳን በማቅረብ ሐጢያቶቻቸውን በመናዘዝ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጭኑና ሐጢያቶቻቸውን የተቀበለውን ይህንን የመስዋዕት እንስሳም ያርዱታል፡፡ ከዚያም አንገቱን ይቆርጡትና ደሙን ያፈሱታል፡፡ በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያ ቀንዶች ላይ የተወሰነ ደም ይቀባሉ፡፡ የቀረውንም ደም ደግሞ መሬት ላይ ያፈስሱታል፡፡ (ዘሌዋውያን 4) ዓመቱን ሙሉ የሰሩዋቸውም ሐጢያቶች ቢሆኑ በስርየት ቀን በሚቀርበው መስዋዕት አማካይነት በእምነት ለአንዴና ለመጨረሻ ይወገዳሉ፡፡ (ዘሌዋውያን 16) በመጨረሻም በብሉይ ኪዳን የሐጢያት መስዋዕት በሚቀርብበት ተመሳሳይ ዘዴ ማለትም ሐጢያቶቻችንን ለመደምሰስ በመጣው መሲህ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን የሐጢያት ስርየታችንን እንቀበላለን፡፡
 
በብሉይ ኪዳን የነበረው የእጆች መጫን ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን ከተቀበለው ጥምቀት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ መሲሃችን በዮሐንስ በመጠመቅና በመሰቀል ከሐጢያቶቻችን በሙሉ አስወገደ፡፡ እግዚአብሄር ፈጽሞ ከሐጢያቶቻችን ያዳነን በመሲሁ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ሥራዎች ባይሆን ኖሮ ከሐጢያቶቻችንን ይቅርታን ለማግኘት ሌላ ምን ማድረግ እንችል ነበር? ማስታወስና ማመን የሚኖርብን ነገር ቢኖር ከድካሞቻችን የተነሳ በሕይወታችን ውስጥ በየቀኑ ሐጢያትን ብንሰራም እንኳን እነዚህ ሐጢያቶችም በሙሉ በውሃውና በደሙ በመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ተወግደዋል፡፡ በእግዚአብሄር ብናምንም ከጉድለቶቻችን የተነሳ አሁንም በድካሞቻችንና በመተላለፎቻችን ውስጥ እንወድቃለን፡፡ ነገር ግን ይህንን ሁሉ የሚያውቀው አምላካችን መሲሁን ወደዚህ ምድር በመላክና በጥምቀት አማካይነት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በራሱ ላይ እንዲወስድና መስዋዕት እንዲሆን አድርጎ አዳነን፡፡
 
እግዚአብሄር የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያና የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ላይ በማስቀመጥ የእግዚአብሄር ቤት ወደሆነው መቅደስ ከመግባታችን በፊት በየቀኑ የሰራናቸውን ሐጢያቶች በሙሉ እንድናስወግድ ፈቅዶልናል፡፡ ይህ ማለት ግን በየቀኑ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በንስሐ ጸሎቶች ማስወገድ አለብን ማለት አይደለም፡፡ በተቃራኒው ከሐጢያቶቻችን በሙሉ የሚያነጻን በመሲሁ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ባለን እምነት ነው፡፡ እግዚአብሄር ጻድቃን በኢየሱስ ካመኑ በኋላ ስህተቶችን፣ ሐጢያቶችንና የተሳሳቱ ነገሮችን ሲያደርጉ የመታጠቢያው ሰን አምላክ በሆነው በመሲሁ ጥምቀት በማመን ከእነዚህ ሁሉ ሐጢያቶች መንጻት እንደሚገባቸው ወስኖዋል፡፡
 
ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ሐጢያቶችን መሸከሙና ለሐጢያቶች ሁሉ መኮነኑ ተመሳሳይ ነገር እንደሆነ አድርገው ለመመልከት ያዘነብላሉ፡፡ በዕውር ድንብርም ሁለቱንም በአንድ ማሰርያ ሊያስሩዋቸው ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን ከድካሞቻችን የተነሳ በየቀኑ ሐጢያት ስለምንሰራ የሐጢያት መንጻትና የሐጢያት ፍርድ በሁለት መከፈል አለባቸው፡፡ ኢየሱስ ከዮሐንስ የተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ የሆነው ሞቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ የሚሸከምባቸው፣ ለእነዚህ ሐጢያቶች የሚኮነንባቸውና ከእነዚህ ሐጢያቶችም ፈጽሞ እኛን የሚያድንበት መንገድ ናቸው፡፡ በዚህ እምነት የሐጢያቶቻችንን ፍርድ በአንድ ጊዜ መቀበል እንችላለን፡፡ ስለዚህ በየቀኑ የምንሰራቸው ሐጢያቶቻችን ችግር የሚፈታው በመሲሁ ጥምቀት በማመን ብቻ ነው፡፡ ፍጹም የሆነ ደህንነት የሚፈጸመው እነዚህን ሁለቱን ክፍሎች ማለትም ጥምቀትንና መስቀልን በማቆራኘት ነው፡፡ ፍጹም የሆነው የሐጢያት ስርየት እውነት ይህ ነው፡፡ ለሐጢያቶቻችን ችግር መፍትሄውን በሚመለከት የኢየሱስን ጥምቀትና መስቀሉን እርስ በርስ ስለ መለያየት ማሰብና በዚህም ማመን ይኖርብናል፡፡
 
ካህናቶች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለመስዋዕት የሚቀርቡትን እንሰሶች በሚያርዱበት ጊዜ በቆሻሻዎችና በሚፈናጠር ደም ይረክሱ ነበር፡፡ ምን ያህል ቆሻሾች እንደሆኑ እንኳን ማሰብ መጀመር አልቻልንም፡፡ ካህናቶቹ ከርኩሰታቸው ሁሉ መንጻት ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ በሚገኘው የመታጠቢያው ሰን ውስጥ ባለው ውሃ ካላጸዳ ይህ ግለሰብ በላዩ ላይ ካለው ቆሻሻ ጋር ከመኖር በስተቀር ሊያደርገው የሚችለው ነገር አይኖርም፡፡
 
ሊቀ ካህኑ በራሱ ላይ ሁሉም ዓይነት ቆሻሻ ቢኖርበትም በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ላይ የመታጠቢያው ሰን ስላለ ሁልጊዜ መነጻት ይችላል፡፡ ካህኑ ዓመቱን በሙሉ ከተሰሩ ሐጢያቶች ይቅርታን ቢያገኝም ይህ ግለሰብ መንጻት የሚችለው በዚህ ሁኔታ በየቀኑ ከሚሰራቸው ሐጢያቶች በመታጠብ ነው፡፡ እግዚአብሄር ቁርባኖችን ለእርሱ የሚያቀርቡለት ካህናቶች በዚህ ሁኔታ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ መታጠብ እንደሚገባቸው ወስኖዋል፡፡ በዚህም እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን ለምን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ እንዳስቀመጠው መገንዘብ እንችላለን፡፡ ይህ የመታጠቢያ ሰን ለምን በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያና በመቅደሱ መካከል እንደተቀመጠም ማወቅ እንችላለን፡፡
 
 
የመታጠቢያው ሰን ለምን ያስፈልገናል? 
 
በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ያለው እውነት በዮሐንስ 13 ላይ ተገልጦዋል፡፡ ኢየሱስ የመጨረሻውን እራት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከበላ በኋላ በፋሲካው ወቅት እግሮቻቸውን ማጠብ ጀመረ፡፡ የጴጥሮስም ተራ ደረሰ፡፡ ኢየሱስ የእርሱን እግር ለማጠብ ሲሞክር ጴጥሮስን እግሮቹን ያጥበው ዘንድ እንዲዘጋጅ ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ ‹‹እግርህን ማጠብ የነበረብኝ እኔ ነበርሁ፡፡ ጌታ የሆንከው አንተ እንዴት እግሬን ታጥበኛለህ?›› በማለት አመነታ፡፡
 
ጴጥሮስ ያመነታው አንድ መምህር የራሱን ደቀ መዛሙርቶች እግር ማጠቡ ተገቢ አይደለም ብሎ በማሰቡ ነበር፡፡ ‹‹መምህሬ እግሮቼን እንዲያጥብ ለመጠየቅ እንዴት እደፍራለሁ? አልደፍርም፡፡››
 
ጴጥሮስ በኢየሱስ አገልግሎት ለመገልገል እምቢተኛ መሆኑን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ለጴጥሮስ የነገረው ነገር ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡
 
‹‹እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ፡፡›› (ዮሐንስ 13፡7) ለምን እግሮችህን እንደማጥብ አሁን መረዳት አትችልም፡፡ ነገር ግን የምትሰራቸው ሐጢያቶችህ ችግር የሚቃለልበት ቁልፍ በእርግጥም ይህ ነው፡፡ ከአሁን ጀምሮ ብዙ ሐጢያቶችን ትሰራለህ፡፡ ነገር ግን ቀድሞውኑም ወደፊት የምትሰራቸውንም ሐጢያቶች በራሴ ላይ ወስጃለሁ፡፡ በእነዚህ ሐጢያቶች ምክንያትም አሁን በመስቀል ላይ ደሜን ማፍሰስ አለብኝ፡፡ ስለዚህ እኔ ወደፊት የምትሰራቸውን ሐጢያቶችህንም እንኳን የወሰድሁ መሲህ እንደሆንሁ ማወቅና ማመን አለብህ፡፡
 
በጴጥሮስ አእምሮ ውስጥ መሲሁ እግሮቹን ማጠቡ ተገቢ እንዳልሆነ መሰለው፡፡ ለመታጠብ እምቢተኛ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን ‹‹ከዚህ በኋላ ታውቀዋለሁ›› አለው፡፡ እግሩንም አጠበው፡፡
 
‹‹ከእኔ ጋር ሕብረት ሊኖርህ የሚችለው እግሮችህን ሳጥብልህ ብቻ ነው፡፡ ለምን እግሮችህን እንደማጥብልህ አሁን አታውቅም፡፡ ከተሰቀልሁና ወደ መንግሥተ ሰማይ ካረግሁ በኋላ ግን እግሮችህን ለምን እንዳጠብሁ ታውቃለህ፡፡ የአንተ መሲህ ስለሆንሁ ቀድሞውኑ ወደፊት የምትሰራቸውን ሐጢያቶች እንኳን ተሸክሜያለሁ፡፡ ለሐጢያቶችህም መስዋዕት በመሆን አዳኝህ ሆኛለሁ፡፡››
 
ጌታችን እንዳለው በወቅቱ ጴጥሮስ አንዱንም አላስተዋለም፡፡ ከጌታ ትንሳኤ በኋላ ግን ወደ ግንዛቤ መጣ፡፡ የእርሱን ተጨባጭ ሐጢያቶች የደመሰሰው ሁነትም በእርግጥ ይህ ነበር፡፡
 
‹‹እኔ በዓለም ላይ ሐጢያቶችን ስለምሰራ መሲሁ ኢየሱስ እነዚህን ሐጢያቶቼን ከመጥምቁ ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ በራሱ ላይ እንደወሰደ አምን ዘንድ ጌታ እግሮቼን አጠበ! የመሲሁ ጥምቀት እነዚህን የወደፊት ሐጢያቶቼንም ቢሆን አስወግዶዋቸዋል! ኢየሱስ እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ በመቀበል የዓለምን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ወስዶ በመሰቀል የሐጢያቶችን ኩነኔ ሁሉ ተሸከመ! ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት በተጨባጭና ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡››
 
ጴጥሮስ ይህንን ተረድቶ ወደ ማመን የመጣው ጌታን ሦስት ጊዜ ከካዳው በኋላ ነበር፡፡ በ1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ላይ እንደዚህ ያለው ለዚህ ነው፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡›› እዚህ ላይ ‹‹ምሳሌ›› የሚለው ቃል ትርጉም ‹‹ጥላ የሆነለት ወይም ከቀድሞው ምሳሌ ጋር የሚመሳሰል ማለት ይህም በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተዛማጅነት ያለው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያለው ተምሳሌት ማለት ነው፡፡›› ስለዚህ ቀደም ያለው አውደ ንባብ የኢየሱስ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለው ‹‹ውሃ›› ምሳሌ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡
 
በብሉይ ኪዳን የዓመቱን ሐጢያቶች በሙሉ ለማስተሰረይ በስርየት ቀን ለእግዚአብሄር መስዋዕት ሲቀርብ የእስራኤልን ሕዝብ የሚወክለው ሊቀ ካህን እጆቹን በመስዋዕቱ እንስሳ ላይ በመጫን ሐጢያቶቻቸውን በመስዋዕቱ ላይ ለማሻገር እስራኤሎች የሰሩዋቸውን ሐጢያቶች ይናዘዛል፡፡ ይህ እጆችን የመጫን ዘዴ ከኢየሱስ ጥምቀት ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ለመስዋዕት የቀረበው እንሰሳ ወደ እርሱ የተሻገሩለትን የእስራኤሎችን ሐጢያቶች በሙሉ በመውሰዱ እስከ ሞት ድረስ መድማት ነበረበት፡፡ ጉሮሮው ይቆረጣል፡፡ ወዲያውም ደሙን ሁሉ ያፈስሳል፡፡ ከዚህም ካህናቱ ቆዳውን ይገፍፉታል፤ ይቆራርጡታል፡፡ ሥጋውን በእሳት በማቃጠል ለእግዚአብሄር ያቀርቡታል፡፡
 
የብሉይ ኪዳን የመስዋዕት ቁርባን እውነተኛ አካል የሆነው መሲህ ወደዚህ ምድር መጥቶ በእጆች መጫን አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ተቀበለ፤ በመስቀል ላይም ደሙን አፈሰሰ፡፡ በእኛ ፋንታም ሞተ፡፡ ስለዚህ ዛሬ እናንተና እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ሙሉ በሙሉ የሐጢያቶቻችንን ስርየት ተቀብለናል፡፡ እነዚህ ሐጢያቶች ጌታችን በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ቀድሞውኑም መንጻታቸውን በማመን በየቀኑ የምንሰራቸውንም ሐጢያቶች ማስወገድ አለብን፡፡ ይህንን እውነት ማወቅና በእርሱም ማመን አለብን፡፡ በየቀኑ ከምንሰራቸው ሐጢያቶች ነጻ መውጣት የምንችለው ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድ በጥምቀቱ እንዳስወገዳቸው በማመን ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በየቀኑ ሐጢያቶችን በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለንን እምነት እናጸናለን፡፡ እነዚህ በየቀኑ የምንሰራቸው ሐጢያቶች ቢሆኑም ቀድሞውኑም በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ የተደመሰሱ የመሆናቸውን እውነት በማመን በማናቸውም ሁኔታ ደህንነታችንን ልናጣ አንችልም፡፡ ልባችን በጸጸት በሚጠቃበት ጊዜ ሁሉም ይህንን በአንድ ጊዜ መመለስ እንችላለን፡፡
 
ኢየሱስ በቀን ተቀን ሕይወታቸው የሐጢያት ስርየት ያገኙ ጻድቃኖች በየቀኑ የሚሰሩዋቸውን ሐጢያቶች ቀድሞውኑም ስለደመሰሰ የሐጢያትን ስርየት በውሃው፣ በደሙና በመንፈሱ ያገኙ እነዚህ ጻድቃኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ባላቸው እምነት አማካይነት በየቀኑ ከሚሰሩዋቸው ሐጢያቶች እንዲታጠቡ እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን ፈቅዶላቸዋል፡፡
 
እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን የሚያገለግሉ ሴቶች የሚጠቀሙባቸውን የእጅ መስታወቶች በመሰብሰብና በማቅለጥ የመታጠቢያውን ሰን የሰራው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ መስታወቶች ማንነትን ያንጸባርቃሉና፡፡ ተጨባጭ ሐጢያቶቻችን በምንሰራበትና ከድካሞቻችን የተነሳ ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ወደ መታጠቢያው ሰን ሄደን እጆቻችንንና እግሮቻችንን መታጠብ ይኖርብናል፡፡ የመታጠቢያው ሰን ሚና ኢየሱስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ በራሱ ላይ እንደወሰደ እኛን ማስታወስ ነው፡፡ ጌታችን እስራኤሎች የእነዚህን ሴቶች መስታወቶች በማቅለጥ የመታጠቢያውን ሰን እንዲሰሩ፣ በውሃ እንዲሞሉትና ካህናቶችም በዚህ ውሃ የእጆቻቸውንና የእግሮቻቸውን ቆሻሻ እንዲያስወግዱ የፈቀደው የሐጢያት ስርየትን ላገኙት ጻድቃን ይህንን እውነት ለማስተማር ነው፡፡
 
ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ፈጣሪና የሰው ዘር አዳኝ እንደሆነ እናምናለን፡፡ መሲሁ የሰው ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር በመምጣት ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት ወደ ገዛ ሰውነቱ የተሻገሩትን ሐጢያቶች በሙሉ መቀበሉን ማስታወስ ይገባናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እውነተኛ ሐጢያቶችን በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ በድካሞቻችን እንወድቃለን ወይም ድካሞቻችን ይገለጣሉ፡፡ መሲሁ በሥጋ እንደመጣ፣ እንደተጠመቀ፣ እንደተሰቀለና በዚህም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደደመሰሰ ማስታወስ ይገባናል፡፡
 
ይህንን አስታውሰን የምናምንበት ከሆነ የሐጢያት ስርየትን ብንቀብልም እንኳን ዳግመኛ በሐጢያቶቻችን እንታሰርና ወደ ቀድሞው ሐጢያተኛ ማንነታችን እንመለሳለን፡፡ ስለዚህ በድካሞቻችንና በጉድለቶቻችን ምክንያት የሰራናቸው ሐጢያቶች በሙሉ አስቀድመው በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ የተሻገሩ መሆቸውን በየቀኑ ማመን አለብን፡፡ በየቀኑ መሲሁ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ እንደወሰደና እንዳስወገዳቸው ማስታወስ፣ ደግመን ማመንና ማረጋገጥ አለብን፡፡
 
በዚህ ምድር ላይ ኢየሱስ በዮሐንስ በመጠመቅና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ የዓለምን ሐጢያቶች መሸከሙን ሳያምን በኢየሱስ ብቻ በማመን የሐጢያት ስርየትን ማግኘት አይችልም፡፡ ሰዎች የሐጢያት ስርየታቸውን ቢያገኙም በየቀኑ ሐጢያቶችን የማይሰራ አንድም ሰው የለም፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ በኢየሱስ ጥምቀት የማያምን ከሆነ ሐጢያተኛ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄርም ፈቃድ ለእያንዳንዱ ሰው ፈጽሞ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ እግዚአብሄር ልጁን የሰጠን በዮሐንስ እንዲጠመቅና በመስቀል ላይ ደሙን እንዲያፈስስ አሳልፎ የሰጠው ለዚህ ነው፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስን መሲሃችን አድርገን ካመንነው ሐጢያቶቻችን ሁሉ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት ወደ እርሱ መሻገራቸውንና የዓለምን ሐጢያቶች ወደ መስቀል በመውሰድ ኩነኔያችንን በሙሉ መሸከሙን፣ መሰቀሉንና ደሙን ማፍሰሱን ማመን አለብን፡፡ የሐጢያታችንን ስርየት የምናገኘው በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመን ነው፡፡ በዚህ እውነት በማመን ሐጢያቶቻችን በሙሉ ተደምስሰዋል፡፡ በልባችን በእግዚአብሄር ፍቅር በማመናችን ወደ ጽድቅ ደርሰናል፡፡ አሁን ልባችን ሐጢያት አልባ ንጹህና ነውር የለሽ ነው፡፡ ነገር ግን በሥጋችን ውስጥ አሁንም ጉድለቶች አሉ፡፡ የኢየሱስን ጥምቀት በየቀኑ ማስታወስና ይህንን እምነት ሁልጊዜም ለራሳችን ማስታወስ ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ጉድለቶቻችንና ድካሞችን በሚገለጡበት ጊዜ ሁሉ፣ ክፉ አስተሳሰቦች በሚነሱበትና እኛም በምንረክስበት ጊዜ ሁሉ፣ ምግባሮቻችንን ፈር በሚለቁበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት እነዚህን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ እንደገና በዚህ እውነት በማመናችን ልባችንን እንዳነጻ በምናስታውስበት ጊዜ ጌታችን ይደሰታል፡፡
 
ሐጢያት በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ በመጀመሪያ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያቶቻችንን ማመን አለብን፡፡ ከዚያም እነዚህ ሐጢያቶች በሙሉ አስቀድሞ በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ እንደተሻገሩ ዳግመኛ ማመን አለብን፡፡ በኢየሱስ የጥምቀት ስራ መንጻትን ስላገኘን በየቀኑ በዚህ ሥራ በማመን ከምንሰራቸው ሐጢያቶችም መንጻት አለብን፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ማስወገድ የምንችል የመሆናችንን እውነታ ፈጸመን ማስታወስና ማመን የሚገባን ለዚህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያና በመገናኛው ድንኳን መካከል ለምን እንዳስቀመጠው መርምረናል፡፡ እግዚአብሄር የመታጠቢውን ሰን በሚቃጠለው መስዋዕት መሰውያና በመገናኛው ድንኳን መካከል ያስቀመጠው በእርሱ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ንጹህ ሰውነትና ልብ ይዘን እንድንቀርብ ነው፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀሉ አማካይነት ፍጹም የሆነ የሐጢያት ስርየትን ያገኘን ጻድቃን ከሆንን በኋላም ቢሆን በውዴታም ሆነ ሳንወድ ሐጢያትን በምንሰራበት ጊዜ ሁሉ ልባችን ለርኩሰት ያዘነበለ ነው፡፡ የሚቃጠለውን መስዋዕት መሰውያ አልፈን በእግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ ይህንን ርኩሰት በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ማንጻት የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ እጅግ ትንሽ ርኩሰት እንኳን ብትኖርብን ወደ እግዚአብሄር ፊት መቅረብ ስለማንችል ራሳችንን በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ባለው ውሃ አጥበን በንጽህና ወደ እግዚአብሄር ፊት መግባት እንችል ዘንድ እግዚአብሄር የመታጠቢያውን ሰን በሚቃጠለው መስዋዕት መሰዊያና በመገናኛው ድንኳን መካከል አስቀመጠው፡፡
 
 
በእግዚአብሄር ፊት በጎ ሕሊና የሚባለው ምን ዓይነት ሕሊና ነው? 
 
1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 የኢየሱስን ጥምቀት ‹‹ለእግዚአብሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ›› በማለት አብራርቶታል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹በጎ ሕሊና›› ኢየሱስ በየቀኑ የሚሰሩትን ሐጢያቶች በሙሉ ጨምሮ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በዮርዳኖስ ወንዝ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ያስወገደ መሆኑን የሚያምን ሕሊና ነው፡፡ ጌታችን በራሱ ሰውነት ላይም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በሥጋው ስለተሸከመ በመስቀል ላይ መሞት ነበረበት፡፡ እርሱ ያደረገውን ችላ ብንልና ባናምንበት ሕሊናችን ክፉ ነገር ብቻ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በእርሱ ጥምቀት ማመን የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት በጎ ሕሊና ሊኖረን ይገባል፡፡ በሥጋችን መቶ በመቶ ፍጹም የሆነ ሕይወት መኖር ባንችልም ቢያንስ በሕሊናችን በእግዚአብሄር ፊት በጎ ሕሊና ሊኖረን ይገባል፡፡
 
ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በፊት በኮርያ ጦርነት ወቅት ኮርያ የፍርስራሽ ክምር ሆና በነበረ ጊዜ ችግሯን ለመጋራት የውጪ ዕርዳታዎች በገፍ ገቡ፡፡ በመጀመሪያ ይህንን ዕርዳታ ማግኘት የነበረባቸው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ልጆች ቢሆኑም እንደዚያ ከመሆን ፋንታ አንዳንድ የማያፍሩ ሰዎች በእነዚህ ዕርዳታዎች ኪሶቻቸውን በማደለብ የራሳቸውን ሐብት አከማቹ፡፡ ሕሊና አልነበራቸውም፡፡ የውጪ አገሮች የዱቄት ወተት፣ የስንዴ ዱቄት፣ ጫማዎች፣ ልብሶችና ሌሎች የዕርዳታ አቅርቦቶች ሲሰጡ ዕርዳታ አድራጊዎቹ ይህንን ያደረጉት የተራቆቱና ተርበው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዲለብሱና በተገቢው መንገድ እንዲመገቡ ነበር፡፡ አንዳንድ ክፉ የሆኑ ባለሥልጣናትና አጭበርባሪዎች እነዚህን የዕርዳታ ስጦታዎች ለራሳቸው ጥቅም ማዋላቸውን በጭራሽ ሊያምኑ አይችሉም፡፡
 
በጎ ሕሊና ያላቸው ሰዎች በድሆች መካከል ያለ አድልዎ ያከፋፍሉ ነበር፡፡ ከውጪ የመጡትን ዕርዳታዎች የራሳቸውን ሐብት ለማደለብ እንደ ዕድል አድርገው በመቁጠር ፋንታ በረሃብ እየሞቱ ባሉ ድሆች መካከል ያለ አድልዎ እያከፋፈሉ በእግዚአብሄር ፊት የሚያፍሩበት ምንም ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም በጎ ሕሊና ይዘው ኖረዋልና፡፡ ይህንን ያላደረጉት ግን የራሳቸው ሕሊና ሌቦች ስለመሆናቸው ይከሳቸዋል፡፡ እነዚህ ሌቦች ቢመለሱና አሁንም እንኳን በኢየሱስ ጥምቀት ቢያምኑ ከሐጢያቶቻቸው ሊነጹ ይችላሉ፡፡
 
ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ለመውሰድና የሰራናቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ለመደምሰስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ተጠመቀ፡፡ በዚህ ሁኔታ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በአንድ ጊዜ አስወገዳቸው፡፡ በእርሱ ጥምቀት የማያምኑትን አላማኒዎች ‹‹በእርሱ ጥምቀት ባለማመናችሁ የሚያኩራራችሁ ምንድነው? የማታምኑት ምን ተማምናችሁ ነው? በእርሱ ጥምቀት ሳታምኑ ወደ መንግሥቱ ለመግባት ብቁ ናችሁን?›› በማለት ልወቅሳቸው እወዳለሁ፡፡
 
በጎ ሕሊና ያለን ሰዎች ለመሆን ከልባችን የምንሻ ከሆነ የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በሙሉ ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት ማስወገድ አለብን፡፡ ይህንን ለማድረግ ኢየሱስ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የሰራናቸውን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ ሁሉንም እንዳስወገዳቸው ከልባችን ማመን አለብን፡፡ መሲሃችን ኢየሱስ ወደ መስቀል ከመሄዱ በፊት በዮሐንስ የተጠመቀው ለዚህ ነበር፡፡
 
ኢየሱስ በምንዝር ለተያዘችው ሴት ‹‹እኔም አልኮንንሽም፤ እኔም አልፈርድብሽም›› አላት፡፡ ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ አስቀድሞ የዚህችን ሴት የምንዝርና ሐጢያት በራሱ ላይ ወስዶ የዚህን ሐጢያት ኩነኔም ተሸክሞ ነበርና፡፡ እርሱ እንዲህ አለ፡- ‹‹ለሐጢያቶችሽ የምኮነነው እኔ ነኝ፡፡ በእኔ ጥምቀት በማመን ግን ከሐጢያቶችሽ ሁሉ ታጠቢ፡፡ በእኔ በማመንም ከሐጢያቶችሽ ሁሉ ዳኚ፡፡ ከሕሊናሽ ሐጢያቶች ነጽተሸ ዳግመኛ እንዳትጠሚ ከሚያደርግሽ ከእኔ ውሃ ጠጪ፡፡››
 
ዛሬ እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችን ያዳነን ኢየሱስ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ በእርግጥም ሐጢያቶቻችንን እንደወሰደና ሁሉንም እንዳስወገደ ታምናላችሁን? ጌታችን በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን አነጻ፡፡ አሁን በበጎ ሕሊና ወደ እግዚአብሄር እንቀርባለን፡፡ ለምን? ምክንያቱም ጌታችን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ በጥምቀቱ በማንጻት እነዚህን ሐጢያቶች ወደ መስቀሉ ወስዶ በዚያ በእኛ ፋንታ በመሰቀል ተኮነነ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳ፡፡ ኢየሱስ ከረጅም ጊዜ በፊት ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ በ33 ዓመት ዕድሜውም ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ በጥምቀቱ ሁሉንም አስወገዳቸው፡፡
 
ጌታችን የምንሰራቸውን ሐጢያቶች በሙሉ በራሱ ላይ በመውሰድና በማስወገድ ወደ እግዚአብሄር ፊት እንድንቀርብና ጻድቅ እንድንሆን በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት አማካይነትም ለሐጢያቶቻችን ሁሉ እንድንኮነን አስቻለን፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄር አባታችን ብለን መጥራትና በፊቱ መቅረብ የምንችለው በዚህ ጌታ በማመን ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የውሃ፣ የደምና የመንፈስ ሥራዎች የሚያምኑ በጎ ሕሊና አላቸው፡፡ በተቃራኒው በጌታ የጽድቅ ምግባሮች በጥምቀቱና በስቅለቱ የማያምኑ ሕሊናቸው ክፉ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
 
 
በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል አጥብቀው የማይዙት እምነታቸው ባዕድ አምልኮ ስለሆነ ነው፡፡
 
ብዙ ዋሾዎች ተራ ጌታ ይመስል የእግዚአብሄርን ቃል ጥለውታል፡፡ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት በእምነታችን በጎ ሥራ መስራት እንዳለብን ብቻ ይሰብካሉ፡፡ ደህንነትን በሚመለከት ግን ስለ መስቀሉ ደም ብቻ ያወራሉ፡፡ እግዚአብሄርን በሥጋ ልምምዳቸው አማካይነት ለመገናኘት ሲሉም በመጸለይና በመጾም ወደ አንድ ተራራ መውጣት እንደማይኖርባቸው በተሳሳተ መንገድ ያስባሉ፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የበለጠ የተሳሳተ አንዳች እምነት ሊኖር ባይችልም ስለዚህ እምነት ፈጽሞ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ‹‹በሐጢያቶቼ ተሰቃይቻለሁ፤ ስለዚህ ሌሉትን ሁሉ በመጸለይ ቆየሁ፡፡ ሲነጋ ድንገት እሳት በላዬ ላይ ሲወርድብኝ ተሰማኝ፡፡ ልክ በዚያ ጊዜ አእምሮዬ ጥርት አለ፡፡ የልቤ ሐጢያቶች በሙሉም እንደ በረዶ ነጭ ሆኑ፡፡ ዳግመኛ የተወለድሁት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ሐሌሉያ!›› ይላሉ፡፡
 
የዚህ ዓይነት አስተሳሰቦች የእግዚአብሄርን ቃል ከንቱ የሚያደርጉ ሰው ሰራሽ፣ በድንቁርና የተሞሉና የሞኝ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር እንደዚህ ያለ የማይረባ ነገር በመናገር ሰዎችን የሚያስቱትንና ሌሎችን ወደ ሲዖል እሳት የሚነዱትን በብዙ እጥፍ እንደሚቀጣቸው ማስታወስ አለባችሁ፡፡
 
‹‹ጆሮዎቼ በብዙ ተጎድተዋል፡፡ ነገር ግን ብናምን እንደምንፈወስ ጌታ በተናገረው አምናለሁ፡፡ እለዚህ አቤቱ አምናለሁ! በማለት ስቃዬን እቋቋማለሁ፡፡ እንደዚህ ሳምን ያን ጊዜ ስቃዩ በሙሉ ይጠፋል!››
 
‹‹የጨጓራ አልሰር ስለነበረብኝ አንዳች ነገር በምበላበት ጊዜ ሁሉ ሐይለኛ ቁርጠት ይሰማኝ ነበር፡፡ ስለዚህ ከመመገቤ በፊት አቤቱ እዚህ ላይ እያመመኝ ነው፡፡ አንተ ግን በእምነት የምንጸልይበትን ነገር ሁሉ እንደምትሰማ ተናግረሃል፡፡ እኔ አሁንም በቃልህ አምናለሁ ብዬ ጸለይሁ፡፡ በእርግጠኝነት የመፍጨት ችግር የለብኝም!››
 
እነዚህ ሁሉ ምንድናቸው? እነዚህ ነገሮች ሰዎች ጌታን በቃሉ አማካይነት ያልተገናኙባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ቃሉን የማያምነውን የእምነታቸውን ዋሾነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እነዚህ በቃሉ አማካይነት ለጸሎቶቻቸው የተቀበሉዋቸው ምላሾች አይደሉም፡፡ ነገር ግን አስማታዊ የሆኑ የእነርሱ እምነት ናቸው፡፡ እነርሱ በእግዚአብሄር የሚያምኑት በቃሉ ሳይሆን በራሳቸው ስሜቶችና ልምምዶች ላይ በተመረኮዘ የተሳሳተ ግራ መጋባታቸው ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ነገር በዛሬዎቹ ክርስቲያኖች መካከል እጅግ ብዙ የዚህ ዓይነት አስማቶች መኖራቸው ነው፡፡
 
የእግዚአብሄርን ቃል ገፍቶ በስሜቶቻቸው ወይም በልምምዶቻቸው ላይ በመመርኮዝ በኢየሱስ በዕውር ድንብር ማመን ከባዕድ አምልኮ እምነት የተለየ አይደለም፡፡ በቃሉ ሳያምኑ በኢየሱስ እናምናለን የሚሉ ሰዎች በአጋንንቶች ተይዘው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማየት ራሳቸውን መመርመር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ‹‹እየጸለይሁ ሳለሁ ጌታን አገኘሁ፡፡ ኢየሱስ በሕልሜ ተገለጠልኝ፡፡ በትጋት ጸለይሁ፡፡ ከሕመሜም ተፈወስሁ፡፡›› ጥሩ አንደበት ያለው ሁሉ እንዲህ ማለት ይችላል፡፡ ነገር ግን ግልጽ የሆነው ነገር ይህ በእግዚአብሄር የተሰጠ እምነት አለመሆኑ ነው፡፡ በሰይጣን የተሰጠ የሐሰት እምነት ነው፡፡
 
ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በየቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ራሱን ለእኛ ገልጦልናል፡፡ ጌታችን በዚህ ዘመን በአዳዲስና በተለያዩ መንገዶች ራሱን ይገልጥልናልን? በእግሮቹ እጅግ ትልቅ ሰንሰለት እየጎተተ ሁለመናው በደም ተበክሎ በራሱ ላይም የእሾህ አክሊሎች ጭኖ ‹‹አያችሁ፤ ለእናንተ በብዙ የተሰቃየሁት እንደዚህ ነው፡፡ አሁን ለእኔ ምን ታደርጉልኛላችሁ?›› ጌታችን ራሱን የሚገልጥልን እንደዚህ ነውን? ይህ አይረቤ ነው!
 
ነገር ግን የዚህ ዓይነት ሕልም ካለሙ በኋላ በእግዚአብሄር ፊት ‹‹ጌታ ሆይ አገልጋይህ እሆናለሁ፡፡ በቀረው የሕይወት ዘመኔ ከሙሉ ልቤ አገለግልሃለሁ፡፡ እዚህ ላይ የጸሎት ቤት እሰራለሁ፡፡ እዚህ ላይ ቤተክርስቲያን እሰራለሁ፡፡ በቀሪው የሕይወት ዘመኔ መስቀሌን በጀርባዬ እሸከማለሁ፡፡ በመላው አገሬና በመላው ዓለምም አንተን እመሰክራለሁ›› በማለት ስለት የሚሳሉ ሰዎች አሁንም አሉ፡፡
 
እንደዚህ ዓይነት ራሳቸውን የሰጡ ሰባኪዎችን በቀላሉ በየመንገዱና በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ላይ ማግኘት እንችላለን፡፡ ኢየሱስን በሕልሞቻቸው ካዩ ወይም እየጸለዩ ሳሉ የጌታን ድምጽ ከሰሙ በኋላ ልክ እንደዚህ ለመኖር መወሰናቸውን የሚናገሩ ሁሉ ጠንቋዮች ናቸው፡፡ ጌታ ግን ራሱን የሚገልጠው በቃሉ አማካይነት ብቻ ነው፡፡ ቃሉ በሙሉ ለሰው ዘር ሙሉ በሙሉ በተሰጠበት በተለይ በዚህ ዘመን በሕልም ወይም እየጸለይን ሳለን አይናገረንም፡፡ ሕልሞች የሚመጡት ውስብስብ ከሆነው የሰው ልዕለ አእምሮ ክልል ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የዚህ ዓይነት ሕልም የሚኖራቸው ለዘብተኛ በሆነው ፍቅራቸው ስለ ኢየሱስ ሁሉንም ዓይነት አሳቦች ስለሚይዙና በጣም ብዙ ስለሚያስቡ ነው፡፡
 
አእምሮዋችሁ ከማንቀላፋቱ በፊት በአንድ በሆነ ነገር ላይ በጥልቀት የሚያስብ ከሆነ በሕልማችሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ስትወጣጠሩ ራሳችሁን ማየታችሁ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ሕልሞች ከልዕለ ንቃተ ሕሊናችሁ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ በጣም ብዙ የምናስብ ከሆነ ሁሉንም ዓይነት እንግዳ ሕልሞች እናስተናግዳለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከእምነት ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የአካላዊ ለውጦች ወይም የልዕለ ንቃተ ሕሊና ነጸብራቆች ብቻ ናቸው፡፡
 
ሰዎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ ደሙን ሲያፈስስ አብዝተው የሚያስቡ ከሆነ በሕልማቸው በራሱ ላይ የእሾህ አክሊሎች ጭኖ የሚገለጠው ለዚህ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሕልም ማየት በራሱ ስህተት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህንን ሕልም አክብዶ መውሰድ የከፋ ስህተት ነው፡፡ ኢየሱስ በፊታቸው ተገልጦ ሁለመናው እየደማ ‹‹ምን ታደርግልኛለህ? ቀሪ ሕይወትህን በሙሉ እንደ ባህታዊ ለእኔ ትኖራለህ? ለእኔ የሚሆን ንብረት የለህምን?›› ቢላቸውስ? ሞኝ የሆኑ ሰዎች እንደዚህ ለመኖር ሲሉ ያላቸውን ንብረት ሁሉ ይተዋሉ፡፡ ሕልሙን አክብዶ በማየት በፍርሃት የተሞላ አንዳች ሰው አለን? ወይም ከዚህ ሕልም የተነሳ ሕይወቱ የተለወጠ ሰው አለን? ይህ ጥንቆላ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የሚገናኘን በቃሉ አማካይነት ነው፡፡ እርሱ እኛ በሕልም ወይም በጸሎት ላይ ሳለን በሕልም የምንገናኘው ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ውስጥ ተጽፎዋል፡፡ መንፈሳችን በቃሉ አማካይነት እርሱን ሊገናኘው የሚችለው ይህ ቃል ሲሰበክልን በመስማትና በልባችን በመቀበል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መንፈሳችሁ ጌታን መገናኘት የሚችለው በቃሉና በቃሉ አማካይነት ብቻ ነው፡፡
 
ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ መውሰዱን ያወቅነው ከቃሉ ነው፡፡ በልባችን ወደ ማመን የደረስነውም ይህንን ቃል በመስማት ነው፡፡ ኢየሱስ ለምን በመስቀል ላይ መሞት እንደነበረበት ለቀረበው ጥያቄ መልሱ የሚገኘውም በቃሉ ውስጥ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተውና ያዳነን ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ስለወሰደ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ወደ ማወቅ የምንመጣው በቃሉ ነው፡፡ በእርሱ ወደ ማመን የምንደርሰውም በቃሉ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ያወቅነውና ያመንነውም በቃሉ አማካይነት ብቻ ነው፡፡
 
 
በእግዚአብሄር ማመን የቻልነው እንዴት ነው? በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል አይደለምን? 
 
የእግዚአብሄር ቃል የሚባል ነገር ባይኖር ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ያስወገደውን ኢየሱስን እንዴት ልንገናኘውና ልናምንበት እንችል ነበር? የእግዚአብሄር ቃል የሚባል ነገር ባይኖር ኖሮ እምነታችን ከንቱ ይሆን ነበር፡፡ ‹‹የማስበው ይህንን ነው፡፡›› የራሳችንን አስተሳሰቦች እንናገር ይሆናል፡፡ ይህ ግን እውነት አይደለም፡፡ ልባችን እውነት ባልሆነው ነገር ከተሞላ ተጨባጩ እውነት ወደ ልባችን ሊገባ አይችልም፡፡ መነገር ያለበት ትክክለኛ ነገር ‹‹የማስበው እንደዚህ ነው›› ማለት ሳይሆን ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ይህንን ነው›› የሚለው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በእግዚአብሄር የተነገረው እውነት ወደ ልባችን ይገባና በቀደምት አስተሳሰቦቻችን ውስጥ ያሉትን ስህተቶች ያርማል፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላችሁ እምነት የተሰራው ከምንድነው? ከራሳችሁ አስተሳሰቦች የተሰራ ነውን? ወይም ዳግመኛ የተወለዳችሁት ቃሉን በመስማት ይህንን በማወቃችሁና በማመናችሁ ነው? እግዚአብሄርን በልባችን ወደ ማመንና ወደ መገናኘት የመጣነው በቃሉ አማካይነት ነው፡፡ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተፈተለው ለዚህ ነው፡፡
 
በመታጠቢያው ሰን ውስጥ ያለው ውሃ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ የወሰደበትን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ‹‹አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) ኢየሱስ የዓለምን ሐጢያቶች በራሱ ላይ የወሰደበትን ጥምቀት ወደ ማወቅ የመጣነው በእግዚአብሄር ቃል አማካይነት ነው፡፡ እናንተና እኔ በሕይወት ዘመናችን የሰራናቸውን ሐጢያቶቻችንን በሙሉ የወሰደውን የኢየሱስን ጥምቀት ያወቅነው ከቃሉ በመሆኑ ይህ ቃል በልባችን ውስጥ የጥምቀት እምነት እንዲኖረን አድርጓል፡፡ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ የተገለጠውን እውነት ያገኘነው በቃሉ አማካይነት ነው፡፡
 
የመታጠቢያው ሰን ከነሐስ መሰራቱን ያወቅነው ከእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነሐስ የሚያመለክተው ፍርድን ነው፡፡ ስለዚህ ከነሐስ የተሰራው የመታጠቢያ ሰን ትርጉም ራሳችንን መልሶ በሚያሳየን መስተዋት በተመሰለው በሕጉ ፊት ራሳችንን በምንመለከትበት ጊዜ ሁላችንም ለኩነኔ የታጨን መሆናችንን የሚገልጥ ነው፡፡ የመታጠቢያው ሰን በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋቶች የተሰራው ለዚህ ነው፡፡ ጌታ ወደዚህ ምድር በመምጣት፣ በመጠመቅና በመስቀል ላይ በመሞት በሐጢያቶቻችን ምክንያት ከመኮነን ማምለጥ የማንችለውን አዳነን፡፡ በተጻፈወ የእግዚአብሄር ቃል አማካይነት ኢየሱስ የሄደውና የሐጢያትን ኩነኔ የተሸከመው ስለተጠመቀ ነው፡፡ እኛም የዳንነው ይህንን እውነት በልባችን በመቀበልና በማመን ነው፡፡ እናንተስ? ድናችኋልን?
 
ጥንቆላን የሚከተል አንድ የእምነት ድርጅት አባሎቹ የዳኑበትን ትክክለኛ ጊዜ ወሩንና ቀኑን ማወቅ እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ በዚህ የእምነት ድርጅት ውስጥ የሚያገለግለው መጋቢ በብዙ ምዕመናኖች ፊት በኢየሱስ ያመነውና የዳነው ለጸሎት አንድ ተራራ ላይ ወጥቶ ከንቱ መሆኑን በተረዳ ጊዜ እንደሆነ መስክሯል ይባላል፡፡ በኩራትም ዳግመኛ የተወለደበትን ትክክለኛ ቀንና ጊዜ ከቶውኑ እንደማይረሳውም ተናግሯል፡፡ ይህ ከጥሩው በፍታ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌላ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከስሜት የመነጨ ነው፡፡ የዚህ መጋቢ እምነት ከሰማያዊው፣ ከሐምራዊው፣ ከቀዩ ማግና ከጥሩው በፍታ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ በዚህ የእምነት ድርጅት የተስተማረው ደህንነት በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ከሚገኘው እውነተኛ ደህንነት ጋር አንዳች የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የራሳቸው ፈጠራ ነው፡፡
 
አንድን ሰው በሌላ ነገር ቁጥጥር ስር ማዋል በእርግጥም ይቻላል፡፡ ሰዎች ሐጢያት አልባ መሆናቸውን በመናገር የሚቀጥሉ ከሆነና ልክ እንደዚሁ ደጋግመው የሚያስቡ ከሆነ በራሳቸው ቁጥጥር ስር ይወድቁና በራሳቸው ሐጢያት አልባ ይሆናሉ፡፡ ይህንን አስማት ለራሳቸው የሚደግሙት ከሆነ በተጨባጭ ሐጢያት አልባ የሆኑ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነት ስሜቶች እስከ መጨረሻው ሊዘልቁ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ብዙም ሳይቆይ እንደገና በራሳችን ላይ ደግምቱን በመድገም ‹‹ሐጢያት አልባ ነኝ፡፡ ሐጢያት አልባ ነኝ›› በማለት መደጋገም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ እንዴት ያለ በራስ ላይ ያነጣጠረ እውነት ያልሆነ ዕውቀት አልባና በባዕድ አምልኮ ላይ የተመሰረተ እምነት ነው!
ጥሩው በፍታ የእግዚአብሄርን የብሉይና የአዲስ ካዳናት ቃል ያመለክታል፡፡ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ የቅድስቱ ስፍራና የቅድስተ ቅዱሳኑ የመግቢያ በሮች በሙሉ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ መፈተላቸው ኢየሱስ በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ውስጥ በትክክል በተጻፈው መሰረት የደህንነታችን በርና አዳኛችን መሆኑን ይናገሩናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄርን ከልቤ አመሰግነዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የነገረን ይህ ደህንነት እንዴት የተረጋገጠ ነው!
 
በምጸልይበት ጊዜ ስሜቶቼ ላይ የማልደግፈው ወይም ለታይታ የማላደርገው ለዚህ ነው፡፡ ሁሉን ለእግዚአብሄር በመስጠትና በእርሱ በመታመን እጸልያለሁ፡፡ ‹‹አባት ሆይ እባክህ እርዳን፡፡ ወንጌልን በመላው ዓለም እንድንሰብክ አድርገን፡፡ አብረውኝ የሚያገለግሉትንና ቅዱሳኖችን ሁሉ ጠብቃቸው፡፡ ወንጌልን ማገልገል የሚችሉ ሰራተኞችን ስጠን፡፡ ይህ ወንጌል እንዲሰራጭ ፍቀድ፡፡ ምዕመናኖችም ቃልህን እንዲያውቁና እንዲያምኑ አድርግ፡፡›› በምጸልይበት ጊዜ የምለው ሁሉ ይህንን ነው፡፡ ስሜቶቼን ለማነሳሳትና ለማልቀስ በመሞከር አይጸልይም፡፡ የማይረቡ ነገሮች የጸሎቶቼ ክፍል አይደሉም፡፡
 
የቻሉትን ያህል አጥብቀው ቢሞክሩም ስሜቶቻቸውን ማነሳሳት የማይችሉ አንዳንድ ሰዎች ሌሎች ሰዎች ከምር እንዲመለከቱዋቸው ዕንባዎችን ለማፍሰስና ጸሎቶቻቸውን ለማስመሰል ሲሉ ከረጅም ጊዜ በፊት የሞቱ አባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን ያስባሉ፡፡ የዚህ ዓይነት የፈጠራ ጸሎቶች እግዚአብሄርን የሚያቅለሽልሹ ቆሻሻ ነገሮች ናቸው፡፡ ሰዎች የኢየሱስን ስቅለት በማሰብና በዕውር ድንበር ‹‹አቤቱ በአንተ አምናለሁ!›› እያሉ በመጮህ ስሜቶቻቸውን ለማነሳሳትም ይሞክራሉ፡፡
 
ይህ ማለት ግን የእነዚህ ሰዎች እምነት ጠንካራ ነው ማለት ነውን? ስለ ሐጢያቶቻቸው የምታስቡና ‹‹ጌታ ሆይ ሐጢያት ሰርቻለሁ፡፡ በጽድቅ እንድኖር እርዳኝ›› በማለት ስሜቶቻችሁን ለማነሳሳት የምትሞክሩ ከሆነ በእርግጥም ስሜቶቻችሁን ማነሳሳት ትችላላችሁ፡፡ የዚህ ዓይነት ስሜታዊ ልምምድ መያዝና ጥሩ የልቅሶና ጊዜ ማሳለፍ ብዙ ውጥረትን ስለሚቀነስ ብዙ ሰዎች የተሐድሶ ስሜት ይሰማቸውና እምነት ማለት ይህ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ሕይወታቸው አሁንም በችግር ውስጥ የተሐድሶ ስሜት ይሰማቸውና እምነት ማለት ይህ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ሕይወታቸው አሁንም በችግር ውስጥ ያለ ቢሆንም ቢሆን ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ሐይማኖታዊ ሕይወታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
 
 

ጌታ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ወደ እኛ እንደመጣ ማመን አለባችሁ፡፡ 

 
ጌታችን በቃሉ አማካይነት ወደ እኛ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ስሜቶቻችሁን መጠበቅ የለባችሁም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ቃል ምን እንደሚላችሁ ማድመጥ አለባችሁ፡፡ አስፈላጊው ነገር በልባችሁ በዚህ ቃል ማመን አለማመናችሁ ነው፡፡ በምትጸልዩበት ጊዜ በስሜቶቻችሁ ላይ ለማተኮር አትሞክሩ፡፡ በፈንታው ግን ስሜቶቻችሁን በተገቢው መጠን ልትቆጣጠሩዋቸው ይገባችኋል፡፡ ለምን? ምክንያቱም በስሜት ቀዳዳዎቻቸው ለመጠቀም ሲሉ ስሜቶቻቸው የሚነሳሳና የሚቀሰቀሰውን ሰዎች የሚቀርቡ ብዙ ዋሾዎች በዚህ ዓለም ላይ አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስሜቶቻቸውን በመከተል ማመዛዘን ይሳናቸዋል፡፡ ‹‹ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃት›› በሚል ማስታወቂያ ስም የሚደረጉ የመነቃቃት ጉባኤዎች አብዛኛውን ጊዜ ዓላማቸው የተሳታፊዎቹን ስሜት ማነሳሳት ብቻ ነው፡፡
 
ነገር ግን አሁን ዳግመኛ ስለተወለድሁ ለማድረግ ብሞክር እንኳን የዚህ ዓይነት መነቃቃት ላደርግ አልችልም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄር ቃል ስብከት እነዚህ ታላላቅ የዓለም መንፈሳዊ የመነቃቃት ጉባኤዎች እንደሚያደርጉት የሰዎችን ስሜቶች የሚያነሳሳ አይደለምና፡፡ እኔ በእውነት ቃል ዳግመኛ ስለተወለድሁ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለመደውን ስሜታዊ ገጽታዬን ደህና ሰንብት ካልሁት ቆይቻለሁ፡፡
 
እኛ የእግዚአብሄርን ቃል የሰማን ጻድቃን አእምሮዋችንን ተጠቅመን በልባችን ስለምናምን ፈጽሞ በስሜቶቻችን አንነዳም፡፡ አንድ ሰው ልክ እንደተጻፈው የእግዚአብሄርን ቃል ነግሮን እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ፈጥነን በመረዳትና ይህ ግለሰብም በእርግጥ በቃሉ በማመን ነግሮን እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ፈጥነን በማወቅ በእውነት እናምናለን፡፡ የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት የምናውቅና የምናምን በልባችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ስላለን የስሜት መነቃቃት ከእውነት የራቀ ነገር መሆኑን ተገንዝበናልና፡፡ በልባችን የምንቀበለው ተጨባጩን እውነት ብቻ ነው፡፡
 
ኢየሱስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቁ ማግና በጥሩው በፍታ ወደ እኛ መጣ፡፡ ይህ እውነት ምንኛ ድንቅ ነው? እናንተን ያዳናችሁ የጌታችን ፍቅር ምንኛ ግሩም ነው? በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ በተጻፉት የኢየሱስ አራት እጥፍ ሥራዎች አማካይነት ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ እንደወሰደ፣ በመስቀል ላይ እንደሞተና ጽድቅን ሁሉ በመፈጸምም እንዳዳናችሁ ሁላችንም ወደ ማመን መጥተናል፡፡
 
ይህንን እውነት በልባችሁ ውስጥ ታምናላችሁን? ወንጌልን የሚሰብኩ በጥሩው በፍታ ክልል ውስጥ ሆነው ሊያሰራጩት ይገባል፡፡ ያም ማለት የብሉይና የአዲስ ኪዳናት የእግዚአብሄር ቃልና ይዘቶቹ ሰማያዊው፣ ሐምራዊውና ቀዩ ማግ መሆን አለባቸው፡ ይህንን ወንጌል የሚያደምጡትም በልባቸው ሊቀበሉትና ከልባቸው ሊያምኑት ይገባል፡፡
 
 

የመታጠቢያው ሰን ውሃ ሐጢያቶቻችንን ያስወግዳል፡፡ 

 
ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በራሱ ላይ ወስዶ ሁሉንም አስወገዳቸው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት የመታጠቢያውን ሰን ያመለክታል፡፡ ከሐጢያቶቻችን የተነሳ ለሲዖል ታጭተን የነበርነውን ሁሉ አንጽቶን በእግዚአብሄር ፊት እንድንቆም አስችሎናል፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በመውሰዱ ወደ መስቀል ሄደ፡፡ እስከ ሞት ድረስ በመስቀል አስወገዳቸው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀትና መስቀሉ ኢየሱስ የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ በሙሉ እንደተሸከመ ይመሰክራሉ፡፡ ኢየሱስ በጥምቀትና በመስቀል አማካይነት ደህንነታችንን ሁሉ ፈጽሞዋል፡፡
 
የንስሐ ጸሎቶችን ማድረግ ፈጽሞ ከሐጢያቶቻችን ሊያነጻን አይችልም፡፡ ሐጢያቶቻችን በሙሉ የተወገዱት ኢየሱስ አስቀድሞ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ስለወሰደ ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጻ መውጣት የምንችለው ይህንን ቃል በማድመጥና ኢየሱስ ለእኛ ባደረገው ነገር በማመን ነው፡፡ ኢየሱስ ለተሸከመው ኩነኔ ምስጋና ይግባውና በጥምቀቱ ላይ ባለን እምነት የሐጢያት ኩነኔያችንን በሙሉ ቀድሞውኑም አስወግደናል፡፡ በእርግጥም በእምነት ድነናል፡፡ ደህንነት በአንድ በኩል በጣም ቀላል ነው፡፡ በደህንነት ስጦታና ፍቅር ብናምን መዳን እንችላለን፡፡ የማናምን ከሆንን ግን መዳን አንችልም፡፡
 
 
እግዚአብሄር ከፈጸመው ደህንነት ውጪ ለመዳን እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር የለም፡፡ 
 
በእግዚአብሄር ባይሆን ኖሮ ለመዳን ማድረግ የምንችለው አንዳች ነገር ሊኖረን አይችልም ነበር፡፡ ጌታችን ከፍጥረት በፊት በዚህ መንገድ ሊያድነን በመወሰኑና ደህንነታችን በመፈጸሙ ሁሉም ነገር በእግዚአብሄር ወሳኔ ላይ ያረፈ ነው፡፡ እግዚአብሄር አብ በልጁና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ሊያድነን ወሰነ፡፡ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስም አንድያ ልጁን ኢየሱስን ወደዚህ ምድር ላከው፡፡ ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሆነውና እነዚህን የደህንነት ሥራዎች የሚፈጽምበት ጊዜ ሲመጣ አብ ክርስቶስ እንዲጠመቅና በመስቀል ላይ እንዲሞት በማድረግ ትንሳኤን ከሰጠው በኋላ አዳነን፡፡ እኛ የዳንነው ከብሉይና ከአዲስ ኪዳናት ቃል ጌታ ለእኛ ያደረገልንን በመማራችንና በማወቃችን ይህንንም በልባችን በማመን ነው፡፡ በልባችን በማመን መዳን ማለት እምነትን በልባችን ውስጥ መቀበል ማለት ነው፡፡
 
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የእግዚአብሄር ቃል እንደሆነ ታምናላችሁን? ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ ጀምሮ በሕይወት የሚኖረው አምላክ ራሱና ቃሉ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሆኑት ብሉይና አዲስ ኪዳናት አማካይነት እግዚአብሄርን ልናውቀውና ልንገናኘው እንችላለን፡፡ በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ቃል አማካይነትም እርሱ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት እንዳዳነን መረዳትና ማመን እንችላለን፡፡ በዚህ እውነት በተጨባጭ የሚያምኑ የዳኑ በመሆናቸው ይህ ቃል በእርግጥም ሐይል እንዳለው መመስከር ይችላሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በራሳችን ጠባብ አስተሳሰቦች መመዘንና መለካት አይገባንም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እንዴት በትክክል እንዳዳነን ከቃሉ መረዳት አለብን፡፡
 
ሁላችሁም ከብሉይና ከአዲስ ኪዳን የሰማያዊውን፣ (የኢየሱስ ጥምቀት) የሐምራዊውን፣ (ኢየሱስ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑ) ከቀዩ ማግና (መስቀሉ) ከጥሩው በፍታ (በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያለው የእግዚአብሄር ቃል) አድምጣችሁ እንድታምኑ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልይማለሁ፡፡ በቀሪው የሕይወት ዘመናችሁ የእግዚአብሄርን ቃል አስወግዳችሁ የእርሱን ቃል በራሳችሁ የመለኪያ በትር የምትመዝኑት ከሆነ በጭራሽ አትድኑም፡፡
 
ራሳችሁን የእግዚአብሄርን ቃል በሚገባ የማያውቅ አድርጋችሁ የምትመለከቱ ከሆነ የእምነት አባቶች የተናገሩትን በጥንቃቄ ማድመጥ አለባችሁ፡፡ መጋቢዎች፣ ሰራተኞች ወይም ተራ ምዕመናን ቢሆኑም እነርሱ የሰበኩትን የእግዚአብሄር ስታደምጡና እነርሱ የሰበኩት ስብከትም በእርግጥም በእግዚአብሄር ፊት ትክክል ከሆነ ማድረግ ያለባችሁ ነገር ትክክል መሆኑን መገንዘብና በልባችሁ ማመን ነው፡፡
 
ቃሉን የሚያሰራጩ ይህንን የሚያደርጉት ቀላል ሳይሆን የሚያሰራጩት ነገር በእግዚአብሄር ፊት ትክክል ስለሆነ ነው፡፡ ትክክለኛውን እውቀት በእግዚአብሄር ፊት የሚሰብኩት ለዚህ ነው፡፡ ያም ማለት የውሃውንና የመንፈስን ወንጌል የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት ይሰበካል፡፡ ከማንም እንስማው እውነተኛ የእግዚአብሄር ቃል ከሆነ አዎ ብለን ከመቀበል በቀር ሌላ ልናደርግ የምንችለው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ አንዲትም ፊደል ስህተት የለበትምና፡፡
 
በእግዚአብሄር ቃል ማመን አለብን፡፡ ‹‹ማመን›› ማለት ምንድነው? መቀበል ማለት ነው፡፡ መታመን ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታችን ስለ እኛ ስለተጠመቀ ድካማችንን ሁሉ ለእርሱ አሳልፈን በመስጠት በእርሱ ላይ እንደገፋለን፡፡ ‹‹ጌታ በእርግጥ ይህንን በማድረግ አድኖኛልን? በአንተ እታመናለሁ፤ አምንሃለሁም፡፡›› እውነተኛ እምነት እንደዚህ ማመን፡፡
 
በዚህ ዓለም ላይ ባሉት የቃለ እግዚአብሄር ምሁራን መካከል ትክክለኛውን ነገር የሚያውቅና የሚያምን ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደ መታጠቢያው ሰን ከመድረሳቸው በፊት እንኳን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር ላይ ስለሚቆሙ ወደ አደባባዩ መግባት አይችሉም፡፡ ስለ መገናኛው ድንኳን በሚሰብኩበት ጊዜ የአደባባዩን በር ሆነ ብለው በብልሃት ለማለፍ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ስለ መገናኛው ድንኳን የሚናገሩ መጽሐፎችን በሚያሳትሙበት ጊዜም የአደባባዩን ባለ 9 ሜትር አጥር የሚሸፍነውን ግዙፍ የመግቢያ በር የማያካትቱ ስዕሎችን ይሰነቅራሉ፡፡
 
አልፎ አልፎ ስለ መገናኛው ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር በድፍረት የሚሰብኩ አንዳንዶች አሉ፡፡ ነገር ግን መሰረታዊ የሆነውን የሰማያዊውን ማግ ፍሬ ነገር ስለማያውቁ ‹‹ሰማያዊ የሰማይ ቀለም ነው›› ብቻ ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሰማያዊው ማግ ኢየሱስ ራሱ አምላክ እንደሆነ የሚገልጥ የሰማይ ቀለም ሲሆን ቀዩ ማግ ደግሞ ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን ያመለክታል በማለት ሆነ ብለው በብልሃት የመገናኛውን ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር እውነት ያልፉታል፡፡ ሐምራዊው ማግስ? ሐምራዊው ኢየሱስ የነገሥታት ንጉሥና ራሱም አምላክ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የኢየሱስ መለኮታዊነት ቀድሞውኑም በሐምራዊው ማግ ውስጥ በሚገባ ስለተገለጠ እውነቱን በሌላ የማግ ቀለም መድገሙ አስፈላጊ አይደለም፡፡
 
የሰማያዊው ማግ እውነት ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በዮሐንስ በመጠመቅ የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ በራሱ ላይ መውሰዱን ይነግረናል፡፡ የዚህ ዓለም የቃለ እግዚአብሄር ምሁራን ግን ይህንን የኢየሱስን ጥምቀት ስለማይረዱ አያውቁትም፤ አይደብቁምም፡፡ ነገር ግን የራሳቸውን የማረባ ነገር ይለፈልፋሉ፡፡ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው የመጣውን ኢየሱስን ባለማመናቸው ዳግመኛ ያልተወለዱ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶችን በሙሉ በራሱ ላይ እንደወሰደና ኩነኔያቸውን እንደተሸከመ አያውቁም፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ዕውራን ሆነዋል፡፡ ቃሉን መረዳትም አይችሉም፡፡ ስለዚህ በራሳቸው አስተሳሰቦች ላይ ተመርኩዘው የእግዚአብሄርን ቃል በዘፈቀደ በመተርጎም የሐይማኖት አካል አድርገውታል፡፡ ‹‹በኢየሱስ እመን፤ ያን ጊዜ ትድናለህ፡፡ ከአሁን ጀምረህ ጥሩና ገር ሰው ሁን›› በማለት ያስተምራሉ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት መልካም ምግባሮቻውን በሚያጎላ መልኩ ወደ ተራ ሐይማኖት ቀይረውታል፡፡
 
ሰዎች ምንም ያህል አብዝተው ቢሞክሩም ጥሩ መሆን ሰለማይችሉ ጥሩ ለመሆን የሚሞከረውን የሰው ዘር ፈቃድ በሚተነኩሱ እንደዚህ ባሉ ቃሎች በቀላሉ ይታለላሉ፡፡ ሐይማኖቶች የሚከተሉት ያንኑ የጥንት ዘዴ ነው፡፡ ‹‹ከሞከርህ ማደረግ ትችላለህ›› ወይም ‹‹ቅዱስ ለመሆን የቻልከውን ያህል ሞክር›› ሁሉም ሐይማኖቶች የሚጋሩት አንዱ ጉዳይ ለሰው ዘር በጎ ሐሳቦች፣ ጥረቶችና ፈቃድ ከፍተኛ ግምት መስጠታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የቡድሃን ሐይማኖት በሚመለከትስ? የቡድሃ ሐይማኖት በሰው ዘር ማለቂያ የሌላቸው ጥረቶችና ፈቃድ ላይ በማተኮርና ‹‹አትግደል፤ እውነትን ፈልግ፡፡ በጎ ነገር አድርግ›› በማለት ተከታዮቹ በራሳቸው ቅዱሳን ለመሆን እንዲሞክሩ ያስተምራሉ፡፡ በተወሰኑ መንገዶች አስተምህሮቶቹ ከክርስቲያን እምነት ትምህርቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ክርስትናና የቡድሃ ሐይማኖት በአንድ በኩል እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ቢሆኑም በሌላ በኩል በቅርብ የተዛመዱ ሆነው የሚታዩበት ምክንያት ሁሉቱም ተራ ሐይማኖቶች በመሆናቸው ነው፡፡
 
ሐይማኖትና እምነት እርስ በርሳቸው ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው፡፡ እውነተኛው እምነት በእግዚአብሄር ጽድቅ አማካይነት በብቸኛው ያዳነን ጌታችን የሰጠንን ስጦታ ማመን ነው፡፡ እምነት ማለት ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ ሐጢያቶቻችንን በራሱ ላይ ለመውሰድ መጠመቁንና የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ ሁሉ በመሸከም መሰቀሉን በማመን የሐጢያት ስርየትን ማግኘት ማለት ነው፡፡ እምነት ማለት ጌታ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት እኛን በማዳን ከሐጢያቶቻችን ሁሉና ከኩነኔ ነጻ እንዳወጣን ማመን ነው፡፡
 
 

እግዚአብሄር ቀድሞውኑም እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችንን ሁሉ አድኖናል፡፡ 

 
ስለዚህ እኛ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ይህንን በልባችን ማመንና መቀበል ነው፡፡ በእውነት ታዛዥ የሆኑ የእግዚአብሄር ልጆች በእርሱ ፊት ማድረግ የሚኖርባቸው ይህንን ነው፡፡ ሌላው ነገር ሁሉ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ስለወደዳችሁ አንድያ ልጁን ወደዚህ ምድር ላከው፡፡ እንዲጠመቅ በማድረግም ሐጢያቶቻችሁን በራሱ ላይ እንዲወሰድ አደረገው፡፡ እንዲሰቅልና እንዲደማም በማድረግ እርሱን በመኮነን እንዲሞት አደረገው፡፡ ትንሳኤንም ሰጠው፡፡ በዚህም ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ አዳናችሁ፡፡
 
በዚህ እውነት የማታምኑ ከሆነ እግዚአብሄር ምን ይሰማዋል? አሁንም እንኳን የእርሱን ልብ የሚያስደስቱ የእርሱ ታዛዥ ወንዶችና ሴቶች ልጆች መሆን ከፈለጋችሁ እግዚአብሄር በልጁ አማካይነት ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ ደምስሶ እንዳዳናችሁ ማመን አለባችሁ፡፡ በልባችሁ አምናችሁ የምታመሰግኑ ከሆነ ያን ጊዜ በአንደበታችሁም መመስከር አለባችሁ፡፡ በእርሱ ማመን እየፈለጋችሁ በልባችሁ ማመን በጣም አስቸጋሪ መስሎ ይሰማችኋልን? እንግዲያውስ እምነታችሁን በአንደበታችሁ በግልጽ ለመመስከር ሞክሩ፡፡ በዚህ መንገድ ማመናችሁን ስትመሰክሩ እምነት ይተከልና ቀስ በቀስ ያድጋል፡፡ እምነት ገንዘብ የሚሆነው በድፍረት ለጨበጡት ብቻ ነው፡፡
 
ለጥቂት ጊዜ እኔ እውነተኛ የአልማዝ ቀለበት እንዳለኝ እንገምት፡፡ ይህንን ቀለበት ለእናንተ ለመስጠት ፈለግሁ እንበል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ቀለበቱ ከእውነተኛው አልማዝ የተሰራ መሆኑን ስለማያምን ሊቀበል እምቢተኛ ሆነ፡፡ ቀለበቱ እውነተኛ አልማዝ ቢሆንም ይህ ሰው ግን ስላለመነበት ለእርሱ አልማዝ አይደለም፡፡ ስለዚህ እውነተኛውን የአልማዝ ቀለበት የማግኘቱን ዕድል አጥቷል፡፡
 
እምነትም ልክ እንደዚህ ነው፡፡ ሥልጣን ያለው የጌጣጌጥ ባለሙያ ቀለበቱ የተሰራው ከእውነተኛ አልማዝ እንደሆነ የሚናገር የጽሁፍ ማስረጃ ቢያቀርብ እንደዚያ መሆኑን ያምኑ ነበር፡፡ እግዚአብሄር እርሱ የሰጠን ደህንነት እውነት እንደሆነ በተጻፈው ቃሉ አማካይነት በዝርዝር ነግሮናል፡፡ ቃሉ ይህንን በመመስከሩ በዚህ ደህንነት የሚያምኑ የእምነት ሰዎች ናቸው፡፡ ‹‹ይህ በእርግጥም እውነት መሆኑን ማመን ይከብደኛል፡፡ ነገር ግን አንተ ፍጹም የሆነከው አምላክ ስለተናገርህ ግን እንደዚያ አምናለሁ፡፡›› ሰዎች እንደዚህ ሲያምኑ ያን ጊዜ የእምነት ሰዎች ይሆናሉ፡፡ እጅግ የከበረው ስጦታም በተስፋው ቃል መሰረት የእነርሱ ይሆናል፡፡
 
በሌላ በኩል የተለየ እምነትም አለ፡፡ አንድ አጭበርባሪ አስመሳይ የአልማዝ ቀለበት አዘጋጀ ብለን እንገምት፡፡ አንድ ሰው በቀለበቱ ላይ ባሉት የሚያብረቀርቁ ቀለማቶች ተማርኮ እውነተኛ ቀለበት እንደሆነ በማመን ገዛው፡፡ ይህ ሰው ጥበብ የተሞላበትን ምርጫ እንዳደረገ ሙሉ በሙሉ አምኖዋል፡፡ ነገር ግን ተታሎ ነበር፡፡ ሰዎች ቀለበቱ የተሰራው ከአልማዝ ሳይሆን ከአልማዝ እንደተሰራ በሚናገሩ የሐሰት ምስክሮች ሲያምኑ ይህ አስመሳይ አልማዝ ለእነዚህ ሰዎች እውነተኛ አልማዝ መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ምክንያቱም ቀለበቱ የተሰራው ከአልማዝ ነው ብለው በጭፍን ያምናሉና፡፡ ነገር ግን ያገኙት አልማዝ አስመሳይ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ የሐሰት እምነት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ስለ እምነታቸው ቢተማመኑም እምነታቸው ውሸት፣ መሰረት የሌለውና ከጥንቆላ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም ከእግዚአብሄር የመጣ አይደለምና፡፡
 
እግዚአብሄር ‹‹በፊቴ ሌሎች አማልክቶችን አታምልክ›› በሎዋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ራሱ እግዚአብሄር ነው፡፡ ቃሉ ከውሃና ከመንፈስ እስካልተወለድን ድረስ የእግዚአብሄርን መንግሥት ማየት እንደማንችል (ዮሐንስ 3፡5) ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ የተፈተለውን የመገናኛውን ድንኳን አደባባይ የመግቢያ በር አስቀድመን አልፈን ሳንገባ ወደ መገናኛው ድንኳን አደባባይ ውስጥ መግባት እንደማንችል እየነገረን ነው፡፡ አስቀድመው እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን የመታጠቢያው ሰን ውስጥ ያላነጹ ወደ መገናኛው ድንኳን ሊገቡ አይችሉም፡፡ እውነት የሆነው ቃል ይህ ብቻ ስለሆነ ከዚህ ውጪ የሆነ ሌላ ማንኛውም ነገር በሙሉ አስመሳይ ነው፡፡
 
እውነተኛ እምነት በእውነት ላይ የተመሰረተ እምነት ብቻ ነው፡፡ በማንኛውም ሌላ ነገር ላይ የተመሰረተ እምነት በሙሉ አስመሳይ ነው፡፡ ሰዎች ምንም ያህል በትጋት ቢያምኑም የእግዚአብሄር ቃል ያልሆነው ነገር እስከ መጨረሻው ድረስ የእግዚአብሄር ቃል አይደለም፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ እንደወሰደ ሲነግራችሁ እናንተ ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር ማመን ብቻ ነው፡፡ ይህንን እንዳደረገ የተናገረው እግዚአብሄር ስለሆነ ቃሉ ላይ ያለው እምነት ተጨባጭ ነው፡፡ ጌታችን በትክክል ይህንን አድርጎ ባይሆን ኖሮ ስህተቱ የእርሱ ይሆን ነበር፡፡ የእናንተ እምነት ግን ስህተት አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል እግዚአብሄር ይህንን በተጨባጭ አድርጎት ከሆነና እናንተ ግን ባለማመናችሁ ካልዳናችሁ ይህ በግልጽ የእናንተ ሐላፊነት ነው፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን ማመን ብቻ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር በቤተክርስቲያኑ አማካይነት የነገረንን ማመን አለብን፡፡ ታምናላችሁን?
 
በቤተክርስቲያን በኩል የተነገረው ቃል ምንድነው? በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ወደ እኛ የመጣው የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን የመውሰዱን፣ ኢየሱስ ራሱ አምላክ የመሆኑንና የሐጢያቶቻችንን ኩነኔ በሙሉ በመስቀል ላይ የመሸከሙን የእግዚአብሄር ቃል ታሰራጫለች፡፡ ኢየሱስ በዚህ መንገድ ያዳነን በመሆኑ እውነት ማመን በእግዚአብሄር ዋስትና የተሰጠው የእውነተኛው አልማዝ እምነት ነው፡፡
 
በመጀመሪያው የእግዚአብሄርን ፈቃድና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተገለጡትን መንፈሳዊ ትርጉሞች አውቀን ስለ እነርሱ ስንናገር ያን ያህል ቀላል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስለ እነርሱ ሳናውቅ ስለ መገናኛው ድንኳን ውጪያዊ ገጽታ፣ ለመገናኛው ድንኳን ጥቅም ላይ ስለዋለው እውነተኛ የዕብራይስጥ ቃል ወይም ስለ ታሪካዊ አመጣጡ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እውቀት ብቻ ከያዝን ራሳችንን ከመታመም በስተቀር ምንም የምንጠቀመው ነገር አይኖርም፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀት እመኑ፡፡ ኢየሱስ በልባችን ውስጥ ያሉትን የጨለማና የርኩሰት ሐጢያቶች በሙሉ በጥምቀቱ አንጽቷል፡፡ ጥምቀት ማለት ሐጢያትን ማስወገድ፣ መሻገር፣ መቅበር፣ ማስተላለፍና መሸፈን ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በራሱ ላይ የተሸከመው ይህንን ጥምቀት በመቀበሉ ነው፡፡ አሁን በዚህ የማያምኑ ይሞቱና ወደ ሲዖል ይጣላሉ፡፡ ‹‹የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውሃን ትጨምርበታለህ፡፡ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይጣጠቡበታል፡፡ ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ ለእግዚአብሄርም የእሳት መስዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል፡፡ እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፡፡ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል፡፡›› (ዘጸዓት 30፡18-21) አለማመን መረገም ነው፡፡ አለማመን ወደ ሲዖል መጣል ነው፡፡ ካላመናችሁ የየሆዋ እርግማንና ጥፋት በእናንተ ላይ ይወርዳል፡፡ እናንተም ወደ ዘላለም እሳት ትወረወራላችሁ፡፡
 
‹‹እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፡፡›› እግዚአብሄር ለሊቀ ካህኑ ይህንን ነገረው፡፡ እርሱና የእርሱ ዘሮች በትውልዳቸው ሁሉ በዚህ እንዲኖሩ ይህ የዘላለም ሕግ እንደሆነ ነገሮታል፡፡ ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ የሚያምን ማንኛውም ሰው በእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ማመን አለበት፡፡ እምነት ገንዘብ የሚሆናቸው በድፍረት ለተቀበሉት ነው፡፡ ደህንነት የእናንተ የሚሆነው በእምነት በልባችሁ ውስጥ ስትቀበሉት ነው፡፡ እውነት የሚጠቅመን ስናምንበት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር በነገረን ማመን አለብን፡፡ ለልብ ትልቅ እንቅፋት የሚሆነው አለማመን ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ካህናቶች በፊቱ ሲቀርቡ በመጀመሪያ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በነሐሱ የመታጠቢያ ሰን ውስጥ ማጽዳት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ በመታጠቢያው ሰን ውስጥ የተገለጠው ይህ እምነት የሌለው ሰው ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት ይሞታል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምናችሁ በመንጻት ወደ እግዚአብሄር ፊት ቅረቡና ከሞት አምልጡ፡፡ የእግዚአብሄርንም መንግሥት ስጦታችሁ አድርጋችሁ ተቀበሉ፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ምንም ያህል ብትከራከሩና ሙጭጭ ብትሉ ዕድል በተሰጣችሁ ጊዜ ባለማመናችሁ እንደምትኮነኑ በጣም የተረጋገጠ ነው፡፡ ከመካከላችሁ እውነትን ባለማመን የሚኮነን ሰው እንዳይኖር ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልይማለሁ፡፡
 
በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻችሁን በደመሰሰው የደህንነት እውነት የማታምኑ ከሆነ ክፉኛ ትጎዳላችሁ፡፡ ታምናላችሁን? በመታጠቢያው ሰን አማካይነት ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔያችን ስላዳነን እግዚአብሄርን ማመስገን አለብን፡፡
 
የመገናኛው ድንኳን ቀሪ ክፍል የዚህ መጽሐፍ ተከታይ በሆነው መጽሐፍ ውስጥ ይብራራል፡፡ በእነዚህ መጽሐፎች ውስጥ ባሉት መልዕክቶች አማካይነት ሁላችሁም የእግዚአብሄር ልጆች የመሆን ዕድል እንደሚኖራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡