Search

דרשות

ርዕስ 8፡ መንፈስ ቅዱስ

[8-20] እነዚያ መንፈስ ቅዱስን ያገኙት ሌሎች መንፈስ ቅዱስን ያገኙ ዘንድ ይመራሉ ‹‹ ዮሐንስ 20፡21-23 ››

እነዚያ መንፈስ ቅዱስን ያገኙት ሌሎች መንፈስ ቅዱስን ያገኙ ዘንድ ይመራሉ
‹‹ ዮሐንስ 20፡21-23 ››
‹‹ኢየሱስም ዳግመኛ ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ሐጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡››    
 
 
ጌታ ለጻድቃን ምን አይነት ሥልጣን ሰጠ?
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማንኛውንም ሰው ሐጢያቶች ይቅር የማለት ሥልጣን ሰጣቸው፡፡
 
ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 የኢየሱስን ትንሳኤ ዘገባ ይዞዋል፡፡ ጌታ ዳግመኛ ከሙታን ተነሳና ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ›› አላቸው፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ በስጦታ መልክ ከእርሱ ተቀበሉ፡፡ ኢየሱስ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስና የዘላለምን ሕይወት የሰጠው የእርሱ ጥምቀትና ደም ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ እንዳነጻላቸው ላመኑት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ጥምቀት የደህንነት ምሳሌ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ማለት የእርሱ ጥምቀት የሰውን ዘር ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው አዳናቸው ማለት ነው፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21)
 


ኢየሱስ የተጠመቀው ለምንድነው?
 

ኢየሱስ ለምን በዮሐንስ ተጠመቀ? ለዚህ ጥያቄ መልሱ ከማቴዎስ 3፡15 በግልጽ ሊታይ ይችላል፡፡ ‹‹እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና›› እዚህ ላይ ‹‹እንዲህ›› ማለት ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስወገደ ማለት ነው፡፡ የእርሱ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን እጆች በሚጫንበት መንገድ ተመሳሳይ መንገድ የተከናወነ ነበር፡፡ የእርሱ ጥምቀት አላማው የዓለምን ሐጢያቶች ወደ ኢየሱስ ማሻገር ነው፡፡   
‹‹ጽድቅን ሁሉ›› የሚለው ትርጉም ምንድነው? ‹‹ይገባናል›› የሚለው ቃልስ ምንን ያመለክታል? ‹‹ፅድቅን ሁሉ›› ማለት ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች ማስወገድ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ‹‹ይገባናል›› የሚለው ቃል የሚያመላክተው ይህ ሁሉ በእግዚአብሄር አይን በጣም ተገቢና ቀና መንገድ መሆኑን ነው፡፡
ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የሰውን ዘር ሐጢያቶች በሙሉ ወሰደና በእርሱ ላመኑት ሁሉ መንጻትን ሰጣቸው፡፡ ኢየሱስ ተጠመቀ፤ ለሐጢያቶቻቸውም ተፈረደበትና ተሰቀለ፡፡ ይህ የሐጢያት ስርየት ወንጌል ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ የደመሰሰ የሐጢያት ስርየት ነው፡፡
ሰዎች በማቴዎስ 3፡13-17 ላይ የተጻፈውን የኢየሱስ ጥምቀት ምስጢር ቢያስተውሉ የሐጢያቶቻቸውን ስርየትና መንፈስ ቅዱስን ሊቀበሉ ይችሉ ነበር፡፡ ኢየሱስ በይፋ አገልግሎቱ ወቅት--በጥምቀቱ በስቅለቱና በትንሳኤው-- ያደረገው ነገር ቢኖር በእግዚአብሄር አስቀድሞ በተወሰነው መሰረት ወደ ደህንነት የሚያደርሰውን የጽድቅ መንገድ ማዘጋጀት ነበር፡፡ ኢየሱስ በዚህ መንገድ የሐጢያተኞች ሁሉ እውነተኛ አዳኝ ሆነ፡፡ የጥምቀቱና የደሙ ወንጌል ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ያነጻ የደህንነት ወንጌል ነው፡፡
ሰዎች መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችሉት የኢየሱስን ጥምቀትና ደም ወንጌል ሲያውቁና ሲያምኑ ብቻ ነው፡፡ የኢየሱስ ጥምቀት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ስለወሰደ ሐጢያቶቻችን ወደ እርሱ ተሻግረዋል፡፡ እርሱ በሰው ዘር ፋንታ በመስቀል ላይ የሞተው ሞት የእኔ ሞት፤ ትንሳኤውም የእኔ ትንሳኤ ነበር፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ የሐጢያት ይቅርታና መንፈስ ቅዱስን የመቀበያ ወንጌል ነው፡፡
ኢየሱስ የተጠመቀበትን ምክንያት ተረድታችሁ በወንጌል እንደምታምኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያን ጊዜ ሐጢያቶቻችሁ ይደመሰሱና መንፈስ ቅዱስን ትቀበላላችሁ፡፡ ኢየሱስ ለምን ተጠመቀ? የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ ነበር፡፡ ‹‹እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና፡፡›› (ማቴዎስ 3፡15) አሜን ሐሌሉያ!
ዛሬ አንዳንዶች በልሳን መናገር መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ማስረጃ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሆኖም መንፈስ ቅዱስን የመቀበያው እውነተኛ ማስረጃ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስን በተጨባጭ በተቀበሉት ልቦች ውስጥ በታተመው ውብ ወንጌል የሚያምነው ክቡር እምነት ነው፡፡
 
 

ጌታ ለጻድቃን ሰዎች በሙሉ ሐጢያትን ይቅር የማለት ሥልጣን ሰጣቸው  

 
ጌታ ‹‹ሐጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል›› (ዮሐንስ 20፡23) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ሐጢያትን ይቅር የሚሉበትን ሥልጣን ሰጣቸው፡፡ ይህም ደቀ መዛሙርት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሰበኩ ጊዜ ወንጌሉን አድምጠው ያመኑት ሰዎች ሐጢያቶች በሙሉ ይቅርታን እንዳገኙ ይጠቁማል፡፡ ሆኖም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላቸው እምነት ምንም ይሁን እነርሱ የማንንም ሐጢያቶች ይቅር ማለት ይችላሉ ማለት አይደለም፡፡
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የማንንም ሐጢያቶች ይቅር የማለት ሥልጣን አላቸው፡፡ ስለዚህ የተጻፈውን የሚያስተምሩ ከሆነ በዚያ ማመን አለብን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ ሊያነጻ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንደሰጣችሁ ማመን አለባችሁ፡፡ የሐጢያት ይቅርታን አግኝታችሁ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል የምትችሉት ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመስበክ ሰዎችን ሁሉ ከሐጢያቶቻቸው የምናድንበትን ስልጣንም ሰጠን፡፡
 
 
የዓለም ገዥ ሐይል
 
በቀድሞው ኑሮዬ በሚገባ ባልተደለደለ መንገድ ላይ አውቶቡስ እንሳፈር ነበር፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሰዎች ከአውቶቡሱ ይወርዱና ወደ ኮረብታው ይገፉት ነበር፡፡ አንድ ቀን በዚያ መንገድ ላይ የተሰራውን የተርማል ፓወር ፕላንት ለመመረቅ የኮርያ ፕሬዚዳንት መጣ፡፡ ሰዎችም ዜናውን ሲሰሙ መንገዱን በመጥረግና በመንገዱ ዳርና ዳር ዛፎችን በመትከል ፕሬዚዳንቱን ተቀበሉት፡፡ ቀኑ ሲደርስ የሞተር ብስክሌቶች መንገዱን በመምራት ተሳተፉ፡፡ ከእነርሱ ጀርባም የፕሬዚዳንቱ መኪና መጣ፡፡ ሕዝቡም ብሄራዊ ሰንደቅ አላማዎችን ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ‹‹ይህ መንገድ ወጣ ገባ ነው፤ መደልደል አለበት›› የሚል አስተያየት ሰጠ የሚል ወሬ ተናፈሰ፡፡ ከጥቂት ቀኖች በኋላ መንገዱ አስፋልት ተነጠፈለት፡፡
እዚህ ላይ የሆነው ምንድነው? በመንገዱ ሁኔታ ላይ ወሳኝ ለውጥን ለማምጣት ፕሬዚዳንቱ የተናገረው አንድ አላፊ አስተያየት በቂ ነበር፡፡ የአንድ ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ እንዲህ ያለ ትልቅ ሐይል አለው፡፡ ሆኖም በክርስቶስ የተሰጠን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ከዚያ የበለጠ ብርቱ እንደሆነ በሚገባ እናውቃለን፡፡ ይህ ወንጌል እኛን በሕይወታችን ውስጥ ካሉት ሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጻ ሊያወጣን ሐይል አለው፡፡
 
 

ሐጢያትን ይቅር ለማለት የሚያስችል እውነተኛ ሥልጣን

 
‹‹ሐጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል›› የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሐጢያቶቻቸው በሙሉ ይቅር እንደተባሉ የሚናገረውን ወንጌል ሰበኩ፡፡ ለሕዝቡም ‹‹ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስወገደ፡፡ የሚያስጨንቅ ነገር የለም፡፡ ወደፊት ሐጢያት ለመስራት የተወሰናችሁ ብትሆኑም ኢየሱስ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ በየቀኑ የምትሰሩዋቸውን ሐጢያቶች በሙሉ አስቀድሞ በመውሰድ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ ኢየሱስ አዳናችሁ! ይህንን ማመን አለባችሁ!›› ብለው ነገሩዋቸው፡፡
ሐጢያተኞች በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አማካይነት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማድመጥና በማመን ቤዛነትን አግኝተዋል፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ሐጢያትን ይቅር የማለት ሥልጣን ሰጣቸው፡፡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ስለሰበኩ አማኞች የሐጢያትን ስርየት ማግኘት ቻሉ፡፡ ኢየሱስ ሐጢያትን ይቅር ከማለት ሥልጣን ጋር አብሮ ይህንንም ስጦታ ሰጥቶዋቸዋል፡፡
ብዙ ሰዎች ቀደም ብዬ ያሳተምኋቸውን መጽሐፎች አንብበዋል፡፡ እነርሱን ካነበቡ በኋላ ከሐጢያቶቻቸው ድነዋል፡፡ አንዳንዶች ‹‹እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደህንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ›› (ኢሳይያስ 53፡5) የሚለውን በመጥቀስ ኢየሱስ በመስቀል የመጠመቁ ምክንያት የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ የመሆኑን ግንዛቤ አምነው ተቀበሉ፡፡
ኢየሱስ ከትንሳኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ሐጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል›› (ዮሐንስ 20፡22-23) ኢየሱስ የሰዎችን ሐጢያቶች ይቅር እንዲሉ ሥልጣን ሰጣቸው፡፡
በዚህ እውነት ከማመናችን በፊት በግራ መጋባት፣ በባዶነትና በሐጢያት ታስረን ነበር፡፡ አሁን ግን በኢየሱስ ጥምቀትና ደም እምነት ስላለንና ከሐጢያት ነጻ ስለወጣን ይህንን ወንጌል ለሌሎች መስበክ ያለብን እኛ ነን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ሰላምን ሰጣቸው፡፡ ጌታችን ሰላምንና የመንፈስ ቅዱስንም በረከት ሰጠን፡፡ ከእግዚአብሄር ዘንድ ሰላምንና መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን የሐጢያቶቻችንን ስርየት ማግኘት አለብን፡፡
ከሐጢያት ነጻ የሚያወጣን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመናችን ነው፡፡ ሰማያዊ በረከቶችን የሚያመጣልን መንፈሳዊ እምነት ይህ ነው፡፡ ሆኖም በሰው አስተሳሰቦች ላይ የተመሰረተ ጥራዝ ነጠቅ እምነት ወደ ጥፋት ይመራል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ቤዛነትን ማግኘት አለብን፤ ከዚያም መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን፡፡ የዚህ አይነት እምነት ይኖረን ዘንድ ምድራዊ አስተሳሰቦቻችን ትተን እምነታችንን ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል መመለስ አለብን፡፡
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የሚያስፈልገውን እምነት ለማግኘት ኢየሱስ እንደተጠመቀና ስለ እኛ እንደተሰቀለ ማመን ይኖርብናል፡፡ ጌታ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስለምናምን የሐጢያት ስርየትን፣ ሰላምንና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሰጠን፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምነውን የማንኛውንም ሰው ሐጢያቶች ይቅር የሚሉበት ሥልጣን ሰጣቸው፡፡
እኛም በዚህ ወንጌል በማመን መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ሌሎች ብዙዎችም ይህንን እንዲያደርጉ ረድቶዋቸዋል፡፡ ወንጌልን ለባልንጀሮቻችንና ለዓለም ስንሰብክ በልባቸው የተቀበሉት መንፈስ ቅዱስ ይሰጣቸዋል፡፡ እኛ የምንሰብከው ወንጌል ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የማይረዳቸው ከሆነ እውነተኛ ወንጌል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል የምንሰብከው ወንጌል መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንዲችሉ የሚመራቸው ከሆነ ያ ወንጌል እውነተኛ ነው፡፡
ይህ ወንጌል ስላለን ምን ያህል ደስተኞችና አመስጋኞች መሆን ይገባናል በእናንተና በእኔ የተሰበከው ወንጌል እንዲህ ያለ ፍጹምና ከፍ ያለ ወንጌል ነው፡፡ ነገር ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ዛሬ ትክክለኛውን ወንጌል የሚያውቅና በዚህም የሚያምን ሰው ማግኘት በጣሙን አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወንጌል በመላው ዓለም መስበክ አለብን፡፡ ሰዎችም መንፈስ ቅዱን እንዲቀበሉ መርዳት አለብን፡፡
 
 
የውሃውንና መንፈሱን ወንጌል ለመካድ በሰይጣን የተታለሉት
 
እኛ አስቀድመው በኢየሱስ ያመኑትንም ቢሆን እየረዳናቸው ነው፡፡ ከእነርሱ ብዙዎቹ በኢየሱስ ቢያምኑም አሁንም ድረስ መንፈስ ቅዱስን አልተቀበሉም፡፡ ስለዚህ ወንጌልን በመስበክና መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ በመርዳት እያገዝናቸው ነው፡፡
አንድ ሰው በኢየሱስ እያመነ መንፈስ ቅዱስን ካልተቀበለ በእምነቱ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፤ እውነተኛውን እምነት እንደያዙ የሚቆጠሩት ሰዎች በኢየሱስ በማመናቸው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ብቻ ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን እንድንቀበል የሚያስችለን የዚህ ወንጌል እውነት ብቻ ስለሆነ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወቅ አለብን፡፡
እኛ ሌሎች መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይችሉ ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንሰብካለን፡፡ ሆኖም ወንጌልን የሚሰብኩ ብዙ ችግሮች ይገጥሙዋቸዋል፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለተወሰነ ጊዜ ጥረቶችን በማድረግ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ መቀበል ጋር የማይጣጣሙ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ልምምዶች አሉዋቸው፡፡ ስለዚህ እነርሱን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለማንቃት ብዙ ጊዜና መስዋዕትነት አስፈልጓል፡፡
ሁሉም አንድ ሰው በዚህ ወንጌል በማመኑ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንደሚችል የሚያስብ ከሆነ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምን ማን ይኖራል? ሰይጣን እውነተኛው ወንጌል ከመምጣቱ በፊት ሰዎችን በተለየ ወንጌል አሳታቸው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን በኢየሱስ ወንጌል ያመኑ አድርገው ከቆጠሩ በኋላ ሌላ የሚታመን ምን ነገር ይኖራል በማለት ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ወደ መካድና እምቢ ወደ ማለት ይመጣሉ፡፡
በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን እውነተኛ ወንጌል ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን ቀደም ብሎ አሳውሮዋቸዋልና፡፡ ከዚህ የተነሳ በኢየሱስ ማመን ቀላል ሥራ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ሆኖም የእውነተኛውን ወንጌል እውነት ሙሉ በሙሉ መረዳት ጨርሶ ቀላል አይደለም፡፡ እውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በሐሰተኛ ወንጌል ተጋርዶዋል፡፡
ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱና በኢየሱስ የሚያምኑ ከሆኑ ማናቸውም መንግሥተ ሰማይ መግባት ይችላሉ ብለው ያስባሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ እንደ ጸሎትና ጾም ባሉት ጥረቶቻቸው አማካይነት እንደሚሰጣቸው ያምናሉ፡፡ ሆኖም የዚህ አይነት እምነት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል እውነት በጣም የራቀ ነው፡፡ እነርሱ በልሳን መናገርና ሌሎች ተዓምራቶች መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ምልክቶች እንደሆኑ ያስባሉ፡፡
ከዚህ የተነሳ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በእውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ማመን አስፈላጊ በጥቂቱም እንደሆነ አይገነዘቡም፡፡ ሆኖም ሰው መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችለው በእግዚአብሄር ቃል በማመን ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስን የመቀበያውን ምስጢር በቃሎቹ ውስጥ ሰወረው፡፡
 
 
የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የሚሹ ሰዎች
 
በአንድ ወቅት ከአንዳንድ ሰራተኞቻችን ጋር ወደ ታይዋን ሄጄ ነበር፡፡ እዚያ ያሉ ሰዎች ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩ መጽሐፎቻችንን ጠየቁን፡፡ በጃፓንና በሩሲያም የሆነው ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ስለ ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩ መጽሐፎችን የሚፈልጉት የዚህ ዘመን ሰዎች ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ በጉጉት መቀበል ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ያምናሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም በእርግጥ መንፈስ ቅዱስን መቀበል አለመቀበላቸውን እርግጠኞች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የላቸውምና፡፡
በኢየሱስ የሚያምኑና መንፈስ ቅዱስን ተቀብለናል የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን በዘላቂነትና ለዘላለም የተቀበሉ ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ቢያምኑም ይህንን ማድረግ አይችሉም፡፡ አሁን ማድረግ የሚናፍቁት ለዚህ ነው፡፡
በዚህ ዓለም ላይ በሚኖሩት ክርስቲያኖች መካከል መንፈስ ቅዱስን እንደተለማመዱ የሚያስቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች በሕልማቸው ከኢየሱስ ጋር እንደተገናኙ ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎችም አጋንንትን በማስወጣታቸው በውስጣቸው መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ እምነታቸው በግል ልምምድ ላይ የተመሰረተ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሆኖም እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በእርግጥ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ይቀበላሉ፡፡
በአንድ ወቅት ንጹህ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ስለ ማግኘት የሚናገሩ መጽሐፎች ባለመኖራቸው እንግዳ ነገር ነው ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ስላላቸው ልምምዶች ያወራሉ፤ ነገር ግን በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ላይ መጽሐፎች የሌሉት ለምንድነው? እንደ እነዚህ ያሉ መጽሐፎችን በመላው ዓለም በቅርብም በሩቅም ብትፈልጉ ለማግኘት አዳጋች ናቸው፡፡
መንፈስ ቅዱስን ስለመቀበላቸው በተሳሳተ መንገድ የሚናገሩ ሰዎች ኢየሱስን በአካል እንደተገኙትና መንግስተ ሰማይንና ሲዖልንም እንደጎበኙ ይናገራሉ፡፡ ኢየሱስ ‹‹ያለጊዜህ መጣህ፤ በዓለም ላይ የምትፈጽማቸው ብዙ ሥራዎች አሉህ፡፡ ስለዚህ ወደመጣህበት በፍጥነት ተመለስ›› እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የዚህ አይነት ልምምድን ለማመን የሚቸግር ነው፡፡ እነርሱን የተገናኛቸው ኢየሱስ እውነተኛው ኢየሱስ ሊሆን ይችላልን? ኢየሱስ ገናም በልቻቸው ውስጥ ሐጢያት ያለባቸውን ሰዎች ተገናኛቸውን? ኢየሱስ በሐጢያተኛ ውስጥ ይኖራልን?
ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ላይ ያላቸውን የእምነት ደረጃ ጠብቀው ቢያቆዩም ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ እንደሌላቸው እሙን ነው፡፡ ስለዚህ በውስጣችን መንፈስ ቅዱስ ያለን እኛ ሌሎችም ይህንን ስጦታ እንዲቀበሉ የሚመራቸውን ወንጌል ማሰራጨት አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የማይፈልግ ሰው የለም፡፡ ያንን ለማድረግ በውሃና በመንፈስ ወንጌል ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችለው በወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም በምናውቀው የእውነት ወንጌል አማካይነት ከእግዚአብሄር ዘንድ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል እንችላለን፡፡
ሁላችንም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስለሰጠን ጌታን ልመሰግነውና ልናወድሰው ይገባናል፡፡ ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ በእኔ ላይ በማሸነፉ የመንፈስ ቅዱስን ደስታ ተለማምጃለሁ፡፡ ይህ መጽሐፍ ሲታተም ብዙ ሰዎች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ  ይቀበላሉ፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ላሉት ደቀ መዛሙርት ተብዬዎች እንዲህ አላቸው፡- ‹‹አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ፤ ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?›› (የሐዋርያት ሥራ 19፡2)
ሁላችንም መንፈስ ቅዱስን መቀበል አለብን፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖች በዚህ አስቸጋሪ የዓለም ታሪክ ዘመን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በተለየ ሁኔታ ይፈልጋሉ፡፡ እኔ መንፈስ ቅዱስ እንደመራኝ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አስፈላጊ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ እየሰበክሁ ነው፡፡ አርኪ የሆነ ሕይወት ለመኖር በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ እውነት ማመን አለብን፡፡ ይህ በልባችሁ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የመጨረሻው ዕድላችሁ ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል የሚረዳውን ወንጌል ለማሰራጨት የተገደድሁት ኢየሱስ ክርስቶስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስለሰጠኝና በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለለገሰኝ ነው፡፡
 
 
አሕዛቦችም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለባቸው
 
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሌሎች ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንዲቀበሉ እንዴት እንዳገዙዋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይተርካል፡፡ አሕዛቦችም ቢሆኑ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ደቀ መዛሙርት የነበራቸውን አይነት ተመሳሳይ እምነት መያዝ ነበረባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሕዛቦች ወደ እግዚአብሄር አለም ለመግባትም በተለየ ሁኔታ ደቀ መዛሙርት እንደነበራቸው አይነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምን እምነት አስፈለጋቸው፡፡ ስለዚህ እኛ አሕዛቦች የሆንን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በእውነተኛው ወንጌል ማመን ይገባናል፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል አስፈላጊ የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል እንዲያውቅ ጴጥሮስን አሕዛብ ወደሆነው ወደ ቆርኔሌዎስ ላከው፡፡
አይሁድ ምዕመናን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛቦች ላይ እንደወረደ በሰሙ ጊዜ ተገረሙ፡፡ ጴጥሮስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ሲመለስ የተገረዙት ነቀፉት፡፡ ‹‹ወዳልተገረዙት ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 11፡3) ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያ ጀምሮ ሁሉን ነገር አብራራላቸው፡፡
የእርሱ ማብራሪያ በሐዋርያት ሥራ 11፡5-17 ላይ በሚገባ ተሰድሮዋል፡፡ ‹‹እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራዕይ አየሁ፡፡ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፡፡ ይህንም ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች፣ አራዊትንም፣ ተንቀሳቃሾችንም፣ የሰማይ ወፎችንም አየሁ፡፡ ጴጥሮስ ሆይ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምጽ ሰማሁ፡፡ እኔም፡- ጌታ ሆይ አይሆንም፤ ርኩስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና አልሁ፡፡ ሁለተኛም፡- እግዚአብሄር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምጽ ከሰማይ መለሰልኝ፡፡ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፤ እንደገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ፡፡ እነሆም ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ፡፡ መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ፡፡ እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ፡፡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን፡፡ እርሱም መልዓክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፡፡ እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል እንዳለው ነገረን፡፡ ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው፡፡ ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሄር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ እግዚአብሄርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?››
ጴጥሮስ ወዳልተገረዙት ሄዶ ከእነርሱ ጋር መብላት ብቻ ሳይሆን ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት ምስጋና ይግባውና ወንጌልንም እንደነገራቸው ተናገረ፡፡ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ፡፡ ንስሐንና ሕይወትን ለሁሉም-- ለቆርኔሌዎስ፣ ለዘመዶቹና ለቅርብ ባልንጀሮቹ-- የሰጠውን አምላክ አከበሩ፡፡
 
 
መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የሚያስችለው የሐዋርያት ወንጌል

የሐዋርያት ወሳኝ ተልዕኮ ምንድነው?
ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ ነው፡፡
 
ሐዋርያቶች በእርግጥ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰብከዋልን? በመጀመሪያ ሐዋርያው ጴጥሮስ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምኖ እንደነበር ወይም እንዳልነበር እናረጋግጥ፡፡ ጴጥሮስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ አለ፡- ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡›› (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21) ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ሐጢያተኞችን ሁሉ እንዳዳነ በትክክል አመነ፡፡ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜሐጢያቶች ሁሉ ወደ እርሱ እንደተሻገሩና እንደተሰቀለ በኋላም ሁላችንንም ለማዳን እንደተነሳ አመነ፡፡ (ማቴዎስ 3፡15)
ዛሬም የጴጥሮስ አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ጴጥሮስ የሰበከውን ያንኑ ወንጌል የሚሰብኩት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ይህ እውነት አድማጮች ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንዲቀበሉ የሚፈቅድላቸው በቂ እውነት ነው፡፡
ጴጥሮስ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሰበከ ጊዜ  ብዙ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ እኛም ይህንኑ እውነት ስንሰብክ ሰዎች በወንጌል አምነው መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ እናያለን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን እንጂ ኢየሱስን ጌታው አድርጎ በማመን ብቻ እንዲያው በደፈናው ሰማይ እንደሚገባ የሚያምን ሰው መንፈስ ቅዱስን ሊቀበል አይችልም፡፡
ጴጥሮስ በአንድ ወቅት አህዛቦችን በመሬት ላይ ከሚርመሰመሱ ተባዮች ጥቂት የሚበልጡ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ ከመጠመቁ፣ ከመሞቱና ከመነሳቱ በፊት እነርሱ በሕጉ መሰረት እንደ ርኩስ እንስሶች ይታዩ ነበር፡፡ ሆኖም አሕዛቦችም እንኳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ መባረክ ቻሉ፡፡ ስለዚህ ለጴጥሮስ እንዲህ የሚል ድምጽ ተናገረ፡፡ ‹‹ደግሞም ሁለተኛ፡- እግዚአብሄር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 10፡15)
እኛ አሕዛቦች ስለሆንን መንፈስ ቅዱስን ከቶውኑም ልንቀበል አንችልም ነበር፡፡ ነገር ግን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ሊኖረን ይችላል፡፡ ወንጌልን በራሳቸው አስተሳሰቦች ለተሞሉ ሰዎች በትዕግስት ስንሰብክ ብዙውን ጊዜ ወንጌልን ወደ ማመን ሲመጡና በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ እናያለን፡፡ በኢየሱስ ጥምቀትና ደም ወደ ማመን ከመጡ በኋላም በልባቸው ውስጥ ሐጢያት እንደሌለባቸው ሲናገሩ ልናይ እንችላለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ሊኖር የሚችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ይህንን ወንጌል ስንሰብክ አላማችን ሌሎች ሰዎች እንዲያስተውሉት መርዳት ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስንም እንዲቀበሉ መርዳት ነው፡፡ እኛ በምንሰብከው ወንጌል የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ የማግኘታቸው እውነታ በጣም ፋይዳ ያለው ነገር ነው፡፡ በዚያው ጊዜም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ የመቀበላቸው እውነታ ይበልጥ አስፈላጊ ነው፡፡ እኛም ለዓለም ሰዎች ወንጌልን የምንሰበክ ብቻ ሳንሆን ነገር ግን አንድ እርምጃ ወደፊት ገፋ አድርገን በዚያው ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ እንመራቸዋለን፡፡
ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በዚህ አገባብ ልንሰብክ ይገባናል፡፡ ወንጌልን ከሰበክን በኋላ የምናቆም ከሆንን የልፋታችን ትርጉም ከንቱ ይሆናል፡፡ ይህ ወንጌል ሰዎች ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ይቀበሉ ዘንድ እንደሚረዳቸው ማወቅ ይገባናል፡፡ ይህንን በአእምሮዋችን ይዘን ወንጌልን ስንሰብክ የመንፈስ ቅዱስ ነበልባል ልክ እንደ ሰደድ እሳት በመላው ዓለም ይሰራጫል፡፡
አንድ ወንጌላዊ ይህ ወንጌል የዓለም ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ እንደሚመራቸው ሲያምን አገልግሎቱ ሰዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ እንዲቀበሉ መርዳትም ጭምር እንደሆነ በትክክል ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበካችን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የምንሰብከውን ወንጌል በጆሮዎቹ ማድመጥና በልቡ ማመን ብቻ ያስፈልገዋል፡፡ የምንሰብከው ወንጌል በሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ የወንጌል ሐይል በእግዚአብሄር የተሰጠ ሥልጣንና በረከት ነው፡፡
ጴጥሮስ ለአይሁድ ጳውሎስ ደግሞ ለአሕዛብ የተላኩ ወንጌላውያን ነበሩ፡፡ ጴጥሮስ በቤት ሰገነት ላይ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ሰማይ ተከፍቶ በአራቱም ማዕዘኖች የታሰረ እንደ ትልቅ አንሶላ ያለ ነገር ከሰማይ ወረደበት፡፡ በውስጡም መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይበሉ የከለከላቸው ሁሉም አይነት ርኩስ እንስሶች ነበሩበት፡፡
ጴጥሮስ ያልተለመደ ወይም ንጹህ ያልሆነ ነገር በልቶ አያውቅም፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር አርዶ እንዲበላቸው አዘዘው፡፡ ጴጥሮስ ግን ‹‹ርኩስ ወይም የሚያስጸይፍ ነገር ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና›› በማለት ለመብላት እምቢ አለ፡፡ አንድ ድምጽም እንዲህ ሲል ተናገረው፡- ‹‹እግዚአብሄር ያነጻነውን አንተ አታርክሰው፡፡›› ይህ ምንን ይጠቁማል? እግዚአብሄር ኢየሱስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የዓለምን ሐጢያቶች የአሕዛብንም ጨምሮ ማንጻቱን እየተናገረ ነው፡፡
ርኩስ የሆኑትን እንስሶች እንዲያርድና እንዲበላ እግዚአብሄር የሰጠው ትዕዛዝ መንፈሳዊ ትርጉም አሕዛቦችም ደግሞ ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም እንደተላከ፣ የዓለምን ሐጢያቶች እንደወሰደና ለእነዚያ ሐጢያቶች ተኮንኖም እንደተሰቀለ ጴጥሮስን ለማስተማር የታለመ ነበር፡፡
ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላ እንኳን እነዚያን የሕግ ድንጋጌዎች በመንፈሳዊ የእምነት አይኖች በማየት ፋንታ አሁንም ይከተላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር አስቀድሞ የአሕዛቦችንም ሐጢያቶች ጭምር እንዳነጻ በተረዳ ጊዜ ጴጥሮስ ንስሐ ገብቶ አመነ፡፡ ጴጥሮስ ውብ የሆነውን ወንጌል ብልጥግና ይበልጥ በጥልቀት ወደ መረዳት ደረሰ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃሎች በሰበከ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በሚያደምጡት ሰዎች ላይ ሲወርድ ተመለከተ፡፡
የዛሬዎቹ ወንጌላውያን መንፈስ ቅዱስን መቀበል ወይም አለመቀበላቸውን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ነገሩ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመቀበል ወይም ባለመቀበል ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ውብ በሆነው ወንጌል እንዳለ የሚያምን ሰው አንድ ወንጌላዊ የእግዚአብሄርን ቃሎች ሲሰብክ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፡፡ በወንጌላዊው ልብ ውስጥ ያደረው መንፈስም በግለሰቡ ውስጥ ለማደር ይመጣል፡፡ ወንጌላዊውና አድማጩ ልክ እንደ ልጅነት ጓደኞች እርስ በርሳቸው ሕብረት ይፈጥራሉ፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር በሁለቱም ውስጥ ሲያድር ያያሉ፡፡ ወንጌላዊ አድማጩ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመቀበል ከእግዚአብሄር ሕዝብ አንዱ ሲሆን ያያል፡፡
ወንጌልን ስንሰብክ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንዳመኑ ወዲያውኑ መንፈስ ቅዱስ በምዕመናን ላይ ሲወርድ ማየት እንችላለን፡፡ ይህ ከደህንነት የተነጠለ ልምምድ አይደለም፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስበክ የሚገባን ዋናው ምክንያት ይህ ነው፡፡ የምንሰብከው ወንጌል ሌሎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የሚመራ ነው፡፡
ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያላቸው የእግዚአብሄር ልጆች ናቸው፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የአንድ የሐይማኖት ድርጅት ጽንሰ ሐሳባዊ ትምህርት አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንን ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ እምነት ስለሚኖራቸው መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉና የእግዚአብሄር ልጆች ይሆናሉ፡፡ ይህ ምንኛ ታላቅ በረከት ነው! ምንኛ ግሩም ወንጌል ነው! የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚሰብኩ የእግዚአብሄርን መንግሥት በመገንባት ያግዛሉ፡፡ እኛ ወንጌልን ብቻ እንሰብካለን፡፡ እነርሱ ግን መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ፡፡
አንዳንድ ሰዎች በኢየሱስ ማመን አንድ ነገር መንፈስ ቅዱስን መቀበል ደግሞ ሌላ ነገር እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች አሁንም ለመንፈስ ቅዱስ ይጸልያሉ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ላይ የሚወርደው በባሮቹ በኩል የተሰበከውን ወንጌል ሰምተው ባመኑት ላይ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ይሻሉ፡፡ እኛ የምንሰብከው ወንጌል ፍላጎታቸውን ወደ ማሟላት ይመራቸዋል፡፡ ወንጌልን በመላው ዓለም የማሰራጨት ሐላፊነት ያለብን ለዚህ ነው፡፡ እኛ ለታላቁ ተልዕኮ ታማኝ የሆንን የአብ ልጆችና የእርሱ ወራሾች ነን፡፡
ተልዕኮዋችን ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ መፍቀድ መሆኑን በአእምሮዋችን ይዘን ወንጌልን በእምነት መስበክ አለብን፡፡ ወንጌላውያን ለሌሎች ከመስበካቸው በፊት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በትክክል ማመን አለባቸው፡፡ ያን ጊዜ አድማጮቻቸው በወንጌል ላይ ባላቸው እምነት መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ፡፡ በዚህ መንገድ ወንጌልን በሚያምኑት ላይ የዘላለምን ሕይወት እፍ ልንልባቸው እንችላለን፡፡ ግባችን እነርሱ ከጨለማው ሐይል ነጻ እንዲወጡና ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንዲፈልሱ ማድረግ ነው፡፡ ወንጌላውያን በጨለማው ሥልጣን ስር ሊመሞቱ የተመደቡትን ሐጢያተኞች ወደ እግዚአብሄር ልጅ መንግሥት ያፈልሳሉ፡፡ ሐጢያተኞችን ወደ እግዚአብሄር ልጆች መቀየር በጣም አስፈላጊ ሥራ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የሚያስፈልገውን ቁልፍ ስለማያውቁ በራሳቸው ጥረት ሊቀበሉት ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ከንቱ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ የሚያስፈልገው በወንጌል የሚያምን እምነት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከሐጢያቶቹ ነጻ የሚያወጣው እምነት ነውና፡፡
መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁት እንዴት ነው? በጸሎት? ወይም ምናልባት በእጆች መጫን አማካይነት? መንገዱ ያ አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስን የምንቀበለው የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማመን ብቻ ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ በሙሉ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይችል ዘንድ መጸለይና ወንጌልን መስበክ አለብን፡፡
‹‹ሐዋርያ›› የሚለው ቃል ‹‹በእግዚአብሄር የተላከ›› የሚል ፍቺ አለው፡፡ ሐዋርያት ምን አደረጉ? ሰዎች መንፈስ ቅዱስን መቀበል ይችሉ ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ይሰብካሉ፡፡ እናንተም ይህንን ሥራ ከእኛ ጋር አብራችሁ መስራት አትወዱምን? ሁላችንም ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገናል፡፡ ለሰዎች ሁሉም መስበክ አለብን፡፡ ሐሌሉያ! መንፈስ ቅዱስን እንቀበል ዘንድ ጌታ የሰጠን ፍጹም የወንጌል እውነት ይመስገን!