Search

דרשות

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[14-1] ትንሳኤን ያገኙና የተነጠቁ ሰማዕታት ምስጋና ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 14፡1-20 ››

ትንሳኤን ያገኙና የተነጠቁ ሰማዕታት ምስጋና
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 14፡1-20 ››
‹‹አየሁም እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፡፡ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጸፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ፡፡ እንደ ብዙም ውሃ ድምጽና እንደ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ከሰማይ ደምጽን ሰማሁ፡፡ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምጽ ሰማሁ፡፡ በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎች ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፡፡ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም፡፡ ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፤ ድንግሎች ናቸውና፡፡ በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ለእግዚአብሄርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው፡፡ በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም፡፡ በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም፣ ለነገድም፣ ለቋንቋም፣ ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፡፡ በታላቅ ድምጽም፡- የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሄርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም፣ ባሕርንም፣ የውሃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ፡፡ ሌላም ሁለተኛ መልአክ፡- አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቁጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፤ ወደቀች እያለ ተከተለው፡፡ ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው በታላቅ ድምጽ እንዲህ እያለ፡- ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩ ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቀል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሄር ቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፤ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሰቃያል፡፡ የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፡፡ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም፡፡ የእግዚአብሄርን ትዕዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው፡፡ ከሰማይም፡- ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፡፡ መንፈስ፡- አዎን ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ አየሁም፤ እነሆም ነጭ ደመና፤ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦዋል፡፡ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው፡፡ ሌላም መልአክ ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፡- የማጨድ ሰዓት ስለደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፤ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፡፡ ምድርም ታጨደች፡፡ ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጨድ ነበረው፡፡ በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን፡- ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቁረጥ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጠራ፡፡ መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቆርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሄር ቁጣ መጥመቂያ ጣለ፡፡ የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፤ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ፡፡›› 
 
 

ትንታኔ፡፡ 

 
ቁጥር 1፡- አየሁም እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፡፡ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጸፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ፡፡
ይህ የሚናገረው ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን በጸረ ክርስቶስ ሰማዕት ከሆኑ በኋላ ትንሳኤንና ንጥቀትን አግኝተው ጌታን በሰማይ ማመሰገናቸውን ነው፡፡ ጸረ ክርስቶስ ሰማዕት ያደረጋቸው ቅዱሳንና ያንቀላፉት ቅዱሳን አሁን በሰማይ ጌታን በአዲስ ቅኔ እያመሰገኑት ነው፡፡ በቁጥር 4 ላይ 144,000 ይህንን ቅኔ እንደዘመሩ እናያለን፡፡ የሚነጠቁት ቁጥር 144,000 ሰዎች ብቻ ይሆኑ የሚል ግርምታ ሊፈጥርባችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ 14 ቁጥር የሚያመለክተው ሁሉን ነገር መለወጡን ነው፡፡ (ማቴዎስ 1፡17)
ከቅዱሳን ሰማዕትነትና ንጥቀት በኋላ ጌታ ይህንን ዓለም ፈጽሞ ወደ አዲስ ዓለምነት እንደሚቀይረው መረዳት አለብን፡፡ ጌታችን በዚህ ዓለም ፋንታ ከሕዝቡ ጋር አብሮ የሚኖርበት ዓለም ይመሰርታል፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ ይህ ነው፡፡
ጌታን በሰማይ የሚያመሰግኑ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ሳሉ ክርስቶስ በሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ቅዱሳን የሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ በግምባሮቻቸው ላይ የበጉና የአብ ስሞች ተጽፈውባቸዋል፡፡ እነርሱ አሁን የክርስቶስ ናቸው፡፡
 
ቁጥር 2፡- እንደ ብዙም ውሃ ድምጽና እንደ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ከሰማይ ደምጽን ሰማሁ፡፡ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምጽ ሰማሁ፡፡
በሰማይ ያሉት ቅዱሳን በጌታ የተሰጠውን ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት የሆኑ አምላካቸው ጌታቸው ብቻ በመሆኑ እውነት ያመኑና ከዚያ በኋላ ትንሳኤን ያገኙ ናቸው፡፡ የአካሎቻቸውነ ትንሳኤ አግኝተው በጌታ ሐይል ስለተነጠቁ ለደህንነታቸውና ለሰጣቸው የሥልጣን በረከት በሰማይ ያመሰግኑታል፡፡ የምስጋናቸው ድምጽ ልክ እንደሚፈስስ የውሃ ፍሰት ውብ ነጎድጓድም ግርማ ሞገስ ያለው ነው፡፡ ሁሉም በዚህ ምድር ላይ ሳሉ በጌታ በተሰጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ለዘላለም ከሐጢያቶቻቸው ድነዋል፡፡
 
ቁጥር 3፡- በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎች ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፡፡ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም፡፡
እዚህ ላይ 144,000 ሰዎች የሚያመላክቱት የተነጠቁትን ቅዱሳን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 14 ቁጥር አዲስ ለውጥ ማለት ነው፡፡ ጌታን በአዲስ ቅኔ በሰማይ ሊያመሰግኑት የሚችሉት በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የሐጢያት ስርየታቸውን አግኝተው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ባላቸው እምነት ዳግመኛ በመወለድ የተለወጡ ናቸው፡፡ ጌታ እዚህ ላይ እነርሱ 144,000 እንደሆኑ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡
ከእነርሱ ውጭ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ለሰጠው የደህንነት በረከት ጌታን ሊያመሰግን የሚችል ሌላ ማንም የለም፡፡ ስለዚህ ጌታችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ባገኙና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በተቀበሉ ሰዎች ይመሰገናል፡፡
 
ቁጥር 4፡- ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፤ ድንግሎች ናቸውና፡፡ በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ለእግዚአብሄርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው፡፡
ቅዱሳን እምነታቸውን በማናቸውም ዓለማዊ ሥልጣን ወይም ሐይማኖቶች ያላረከሱ ናቸው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እምነታቸውን በቀላሉ የሚቀይሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በጌታ ጥምቀትና በመስቀሉ ላይ ደሙ በማመን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያገኙ ቅዱሳን በዚህ ዓለም ላይ ባለ በማንኛውም ነገር እምነታቸውን አይቀይሩም፡፡
ወደ ሰማይ አርገው ጌታን የሚያመሰግኑ ቅዱሳን በጌታ የተሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ያለ ማወላወል የያዙና እምነታቸውን የጠበቁ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ስለዚህ ጌታን በመንግሥተ ሰማይ የሚያመሰግኑት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን በጌታ የተነጠቁ ናቸው፡፡
በቁጥር 4 አጋማሽ ላይ እንዲህ ተጽፎዋል፡- ‹‹በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው፡፡›› በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ በአንድ ጊዜ የነጹ ዳግመኛ ከተወለዱ በኋላ ጌታን ወደሚሄድበት ሁሉ ሊከተሉት ይገባል፡፡ እነርሱ የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ስለተቀበሉ በልባቸው ውስጥ ጌታን ወደሚሄድበት ሁሉ በደስታ ለመከተል ፈቃደኝነት አለ፡፡ በመጨረሻው ዘመን ስለ እምነታቸው በጸረ ክርስቶስ ሰማዕት ከሆኑ በኋላ በጌታ ትንሳኤን አግኝተውና ተነጥቀው ጌታን በሰማይ ያመሰግኑታል፡፡
እንዲህ ተብሎም ተጽፎአል፡- ‹‹ለእግዚአብሄርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው፡፡›› በዚህ ዓለም ላይ ከሚኖሩ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ጌታ በሰጠው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ የዳኑት ጥቂቶች ብቻ ነው፡፡ ጌታችን በኤርምያስ 3፡14 ላይ እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡፡ ‹‹አንዱንም ከአንዲት ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳለሁ፡፡ ወደ ጽዮንም አመጣቸዋለሁ፡፡›› የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ተቀብለው የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ያገኙ እንዲህ ጥቂቶች ናቸው፡፡
እነርሱ የበጉ በመሆናቸው ጌታ እንደሰጣቸው ተስፋዎች ሁሉ የትንሳኤን በኩራት የሚቀበሉ፣ በጌታ ሐይል የሚነጠቁና ለዘላለም ክርስቶስን የሚያመሰግኑት እነርሱ ናቸው፡፡ በዚህ ምድር ላይም እንደዚሁ ጌታን ወደሚመራቸው ሁሉ የሚከተሉት እነርሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሄር ጸጋና ሐይል የሚሆኑ ናቸው፡፡
 
ቁጥር 5፡- በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም፡፡
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ይህንን እውነተኛ ወንጌል በአንደበቶቻቸው መስበክ ይችላሉ፡፡ ዛሬ ወንጌልን በራሳቸው መንገድ የሚሰብኩ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም እውነተኛውን የውሃና የመንፈሱ ወንጌል በትክክል የሚሰብኩ ከእነርሱ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
በመስቀል ላይ የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ብቻ የሚሰብኩ ሰዎች ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እየሰበኩ አይደሉም፡፡ ለምን? እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌል ሌላ ወንጌል ሳይሆን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ ነው፡፡ በጻድቃን ልቦች ውስጥ ያሉት ሐጢያቶች ሁሉ በእውነተኛው ወንጌል ቃል ስለተወገዱ ይህንን ወንጌል በሙሉ አመኔታ በአንደበቶቻቸው መስበክ ይችላሉ፡፡
 
ቁጥር 6-7፡- በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም፣ ለነገድም፣ ለቋንቋም፣ ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፡፡ በታላቅ ድምጽም፡- የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሄርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም፣ ባሕርንም፣ የውሃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ፡፡
ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማወጃቸውን መቀጠል አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የመስበክ ሥራ ቅዱሳኖች እስከሚነጠቁበት ቀን ድረስ በዚህ ምድር ላይ መቀጠል አለበት፡፡
እምነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ በጸረ ክርስቶስ ሰማዕት የሚሆኑት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው፡፡ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚነጠቁትም እነርሱ ብቻ ናቸው፡፡ ሰው ሁሉ እግዚአብሄርን መፍራት፣ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና በዚያውም የሐጢያት ስርየታቸውንና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል አለባቸው፡፡ የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በምስጋና ማመን ካልቻሉ በኢየሱስ ያላቸው እምነት በሙሉ ከንቱ ይሆናል፡፡
ዩኒቨርስን በሙሉና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረው ሌላ ማንም ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ዘር ኢየሱስ ክርስቶስን የእነርሱ ፈጣሪና ሐጢያቶቻቸውን ይቅር ብሎ ደህንነታቸውን የሰጣቸው አምላክ አድርገው ሊቀበሉትና በዚህ መሰረትም ሊሰግዱለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገሮች በእርሱ የተሰሩና የተጠናቀቁ ናቸውና፡፡ ሰዎች ሁሉ በልባቸው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ከመላው ሐጢያቶቻቸው ይቅርታን አግኝተው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በረከት መቀበል ይችላሉ፡፡
አሁን ይህ ዓለም ኢየሱስ እግዚአብሄርን በሚቃወሙት ላይ የሚሰጠውን ፍርድ ለመቀበል መዘጋጀት አለበት፡፡ እኛም ደግሞ እንደዚሁ በቅርቡ በጌታ የሚነጠቀውን እምነታችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሄር ፍርድ ወደ እኛ እየተቃረበ ነውና፡፡ ለንጥቀት የመዘጋጀቱ መንገድ ጌታ በሰጠው በውሃወና በመንፈሱ ወንጌል ቃል ማመን ነው፡፡ ለምን? አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችለው በእርሱ ወንጌል በማመን ብቻ ነውና፡፡ የመጨረሻዎቹ ቀኖች ሲመጡ እነርሱ በንጥቀታቸው በጌታ ከፍ የማለትን ክብር ይጎናጸፋሉ፡፡
ሐጢያተኞች በሙሉ በተቻለ ፍጥነት ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረታት የደህንነት አምላክ መሆኑን ማመንና በዚያው መሰረትም ማምለክ ይገባቸዋል፡፡ የውሃውንና የመንፈሱንም ወንጌል በልባቸው ውስጥ መቀበልና የማዳኑን ጸጋና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታም መረከብ አለባቸው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያመልኩ ሰዎች ጌታ የሰጠውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባቸው ይቀበላሉ፡፡ አይጥሉትም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄርን ማምለክ የሚችሉት እንደዚህ ነውና፡፡
 
ቁጥር 8፡- ሌላም ሁለተኛ መልአክ፡- አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቁጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፤ ወደቀች እያለ ተከተለው፡፡
ይህ ዓለም አስፈሪ በሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ይወድማል፡፡ ሐይማኖቶቹ በሐሳዊ ትምህርቶች ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ እግዚአብሄር ያጠፋቸዋል፡፡ እነዚህ ዓለማዊ ሐይማኖቶች ሰዎች ከራሱ ከእግዚአብሄር ቃል ይልቅ ዓለምን እንዲከተሉ አድርገዋቸዋል፡፡ እግዚአብሄርን የመቃወሚያ መሳርያዎች ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም ይጠፋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ እግዚአብሄርን ትቶ እነዚህን ዓለማዊ ሐይማኖቶች ተከትሎዋልና፡፡
እነርሱ ዓለማዊ ሐይማኖቶችን መከተላቸው ሐሳዊ አማልክት የሆኑትን አጋንንቶች ተከትለዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ይህንን ዓለም በቁጣው ያጠፋዋል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያለው እያንዳንዱ ነገርና የሐሰት ሐይማኖቶቹ በሙሉ በእግዚአብሄር ይወድማል፡፡ የእግዚአብሄርን ቁጣ ወይን ጠጅም ይጠጣል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄርን የሚቃወሙ ሰዎች እንደዚሁም በዓለማዊ ሐይማኖቶች ላይ እንደ ተባዮች ተጣብቀው የሚኖሩ አጋንንቶች ሁሉም በእግዚአብሄር መቅሰፍቶች ወድመው ወደ ዘላለማዊው ሲዖል ይጣላሉ፡፡
 
ቁጥር 9-10፡- ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው በታላቅ ድምጽ እንዲህ እያለ፡- ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩ ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቀል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሄር ቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፤
እግዚአብሄር እዚህ ላይ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ ወይም ምልክቱን በግምባሩ የሚቀበል ማንም ቢኖር የሲዖል ቅጣትን እንደሚቀበል ለሰው ሁሉ ማስጠንቀቂያን ሰጥቷል፡፡ ሰይጣን በብዙ ሰዎች ውስጥ በመስራት የሰው ዘር ሁሉ በጸረ ክርስቶስ አምሳል ለተሰራው የጣዖት ምስል እንዲሰግድ ያስገድደዋል፡፡ ነገር ግን ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ከጸረ ክርስቶስ ጋር ተዋግተው እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት ይሆናሉ፡፡ ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን እምነታቸውን ለመጠበቅ ጸረ ክርስቶስን እንዲህ መቃወምና ሰማዕት መሆን አለባቸው፡፡
ማንም ለጸረ ክርስቶስ በማጎብደድ በምስሉ ፊት የሚንበረከክና የስሙን ምልክት ወይም ቁጥር የሚቀበል ከሆነ ወደ ዘላለማዊው የእሳትና ዲን ባህር ውስጥ እንዲወረወር የሚያደርገውን የእግዚአብሄር ቁጣ ያከማቻል፡፡ የመከራው ዘመን ሲመጣ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሄር መጸለይ፣ በጌታ ያላቸውን እምነት መጠበቅና ተስፋቸውንም በመንግሥቱ ላይ ማኖር አለባቸው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንም ጸረ ክርስቶስን መቃወምና እምነታቸውን መጠበቅ፣ ከሰማዕትነታቸው፣ ከትንሳኤያቸውና ንጥቀታቸው ጋር መቀላቀልና በዚህም በመንግሥቱ ውስጥ ከጌታ ጋር ለዘላለም የመኖርን በረከት መቀበል አለባቸው፡፡
 
ቁጥር 11፡- በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሰቃያል፡፡ የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፡፡ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም፡፡
ሰይጣንን እንደ አምላክ ተቀብለው የሚሰግዱለት የእግዚአብሄር መቅሰፍቶች ይወርዱባቸዋል፡፡ ለዘላለም ዕረፍት በሌለው ሲዖል ውስጥ ይሰቃያሉ፡፡ በመጨረሻው ዘመን ለጸረ ክርስቶስ የሚያጎበድድና ምስሉን አምላክ አድርጎ በመቁጠር የሚሰግድ ማንኛውም ሰው በእግዚአብሄር ቁጣ በተሞላው የእሳትና የዲን ባህር ውስጥ ይሰቃያል፡፡ አውሬውንና ምስሉን የሚከተልና የአውሬውን ምልክት የሚቀበል ማንም ቢኖር ቀንና ሌሊት ዕረፍት አይኖረውም፡፡
 
ቁጥር 12፡- የእግዚአብሄርን ትዕዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው፡፡
ቅዱሳን ጌታ ተስፋ በሰጣቸው ሐብት፣ ክብርና በረከት ሁሉ ስለሚያምኑ በትዕግስት መጽናት አለባቸው፡፡ ጌታ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩ ቅዱሳን የሰጠው ተስፋ ከሰማዕትነታቸው በኋላ ከእርሱ ጋር የመኖርን በረከት እንደሚሰጣቸው የሚናገር ነው፡፡ በጌታ ሐይል ትንሳኤያቸውን ካገኙ በኋላ ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ፡፡
ቅዱሳን በትዕግስት የሚጸኑት ከጌታ ጋር ወደ በጉ ሰርግ እራት እንዲገቡ፣ ለሺህ ዓመት ከእርሱ ጋር እንዲነግሱና ሁልጊዜም በመንግሥተ ሰማይ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ በሚፈቅድላቸው በዚህ በረከት ስለሚያምኑ ነው፡፡ የመጨረሻው ዘመን ሲመጣ ቅዱሳን እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት መሆን ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጊዜው በሚመጡት መከራዎች ውስጥ በትዕግስት መጽናት አለባቸው፡፡
አሁን በዚህ ዘመን የሚኖሩ ቅዱሳን ጸረ ክርስቶስ በእነርሱ ላይ በሚሰነዝራቸው ዛቻዎቹ፣ ግፊቶቹና ማባበያዎቹ እምነታቸውን እንዲክዱ ሲጠይቃቸው በጌታ ተስፋዎች በማመን ሰማዕትነታቸውን መቀበል አለባቸው፡፡ ለምን? ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የጌታችን በረከቶች በሙሉ እንደገባው ተስፋው ይፈጸማሉና፡፡ ቅዱሳኖች ሁሉ ሽልማቶቻቸውን መቀበል የሚችሉት በእግዚአብሄር ቃልና በጌታ ላይ ያላቸውን እምነታቸውን በመጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በጌታ ቃል ላይ ያላችሁን እምነት ጠብቁ፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ በቃሉና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት የጠበቁትን ቅዱሳኖች ሙሉ በሙሉ አዲስ በሆነው የእርሱ ዓለም ውስጥ ይቀበላቸዋል፡፡
የጌታን ወንጌል የሚያገለግሉ ቅዱሳን በመከራው ዘመን በሚገጥሙዋቸው ችግሮች ሁሉ ውስጥ ለምን በትዕግስት መጽናት እንዳለባቸው የሚናገሩ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡
ሮሜ 5፡3-4 እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን መከራ ትዕግስትን እንዲያደርግ፣ ትዕግስትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፡፡›› በጌታ በማመን በታላቁ መከራ ውስጥ የሚጸኑ ቅዱሳን ከእርሱ ዘንድ ትንሳኤያቸውንና ንጥቀታቸውን ተቀብለው በመንግሥቱ ውስጥ በመንገስ የበረከትን ሕይወት ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በእምነታችን በመከራው ውስጥ መጽናት አለብን፡፡ ቅዱሳን በጌታ ያላቸውን እምነት በመጠበቅ በመጨረሻው ዘመን በሚመጣው ታላቅ መከራ ውስጥ በትክክል ይጸናሉ፡፡ ቅዱሳን ጌታ በዚህ ዓለምና በሰማይ በሚፈጽምላቸው በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ምናሉ፡፡
 
ቁጥር 13፡- ከሰማይም፡- ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፡፡ መንፈስ፡- አዎን ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡
ይህ ቁጥር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብጹዓን ናቸው›› ይላል፡፡ ለምን? ምክንያቱም የመከራው ዘመን ሲመጣ ማለትም ጸረ ክርስቶስ ዓለምን ሲገዛ ያን ጊዜ በዚህች ምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሐጢያተኛ በሙሉ ይጠፋል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን መጭውን የክርስቶስ መንግሥት ተስፋ ማድረግ፣ እምነታቸውን መጠበቅና የእምነት ሰማዕትነታቸውንም መቀበል አለባቸው፡፡ ለጌታ ክብርን ይሰጡ ዘንድ ሰማዕትነትን የሚቀበሉ የተባረኩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕትነታቸውን መቀበል አለባቸው፡፡
ያን ጊዜ ጌታ እነርሱን ወደ መንግሥቱ ለመውሰድ ትንሳኤያቸውንና ንጥቀታቸውን በመፍቀድ ለቅዱሳኑ ይጠነቀቅላቸዋል፡፡ ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ የደከሙት ድካም ሁሉ ያበቃል፡፡ እነርሱም ጌታ በሚሰጣቸው ሽልማት እየተደሰቱ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ሁሉ ከጌታ ጋር የመንገስና የዘላለም ደስታ ይኖራቸዋል፡፡ የእርሱ መንግሥት፣ ሐብትና ክብርም ለዘላለም የእነርሱ ይሆናል፡፡
በመጨረሻው ዘመን እምነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሰማዕት የሆኑ ብጹዓን የተባሉት ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም በሺህው ዓመት መንግሥቱና በዘላለማዊው መንግሥተ ሰማይም ውስጥ በሙሉ ብልጥግናና ክብር ለዘላለም ይኖራሉና፡፡
 
ቁጥር 14፡- አየሁም፤ እነሆም ነጭ ደመና፤ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦዋል፡፡ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው፡፡
ይህ ቁጥር ጌታ ቅዱሳንን ለመንጠቅ እንደሚመጣ ይነግረናል፡፡ ጌታ የቅዱሳን አለቃ ስለሆነ እምነታቸውን ለመጠበቅ ሰማዕት የሆኑትን ቅዱሳን ያስነሳቸውና በንጥቀት ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ይወስዳቸዋል፡፡ በታላቁ መከራ ዘመን ቅዱሳኖች እንደሚነጠቁ በሚገባ የተረጋገጠ ነው፡፡
 
ቁጥር 15፡- ሌላም መልአክ ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፡- የማጨድ ሰዓት ስለደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፤ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡
ይህ ቁጥር የቅዱሳን ንጥቀት በጌታ እንደሚጠናቀቅ ያመለክታል፡፡ በሌላ አነጋገር ቅዱሳኖች በስፋት ሰማዕትነትን ከተቀበሉ በኋላ ንጥቀት ይሆናል፡፡ ጌታ ያን ጊዜ ላንቀላፉት ቅዱሳን ሰማዕት ከሆኑት ቅዱሳን ጋር አብሮ ንጥቀትን ይፈቅድላቸዋል፡፡ የቅዱሳን እምነት የሚጠናቀቀው በደህንነታቸው፣ ሰማዕትነታቸው፣ ንጥቀታቸውና የዘላለም ሕይወት ነው፡፡ ቅዱሳኖች የሚነጠቁበት ዘመን በጸረ ክርስቶስ ስደት ሰማዕት ከሆኑና በተመሳሳይ ጊዜ ትንሳኤን ካገኙ በኋላ ነው፡፡
 
ቁጥር 16፡- በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፡፡ ምድርም ታጨደች፡፡
ይህም ቁጥር እንደዚሁ የቅዱሳኖችን ንጥቀት ያመለክታል፡፡ ንጥቀት ማለት ቅዱሳኖችን በአየር ላይ ማንሳት ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ማለት ቅዱሳን ወደ አየር ተወስደው ከጌታ ጋር ወደ ምድር ይወርዳሉ ማለት ነውን? አዎ! ቅዱሳን ከተነጠቁ በኋላ ጌታችን የሰባቱን ጽዋዎች መቅሰፍቶች በማውረድ ምድርን፣ ባህርንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ያጠፋል፡፡ ዓለምን እንዲህ አድርጎ ካወደመ በኋላ ከተነጠቁት ቅዱሳን ጋር አብሮ ወደዚህ ምድር ይወርዳል፡፡
ያን ጊዜ ጌታና የእርሱ ቅዱሳን ለሺህ ዓመት በዚህች ምድር ላይ ይነግሳሉ፡፡ የበጉ ሰርግ እራት ሲጠናቀቅም ወደ ዘላለማዊው መንግስተ ሰማይ ያርጋሉ፡፡ ቅዱሳን ለበጉ ሰርግ እራት ከጌታ ጋር ሲቀለቀሉ ጌታም ቀደም ብሎ መላውን ዓለምና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ አድሶዋል፡፡
ቅዱሳኖች ከተጠነቁ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ከጌታ ጋር በአየር ላይ ይቆያሉ፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በሙሉ ሲጠናቀቁም ከእርሱ ጋር ለሺህ ዓመት ለመንገስ ወደታደሰችው ምድር ይወርዳሉ፡፡ ያን ጊዜ ከጌታ ጋር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ይገቡና ለዘላለም ከእርሱ ጋር ይኖራሉ፡፡
 
ቁጥር 17፡- ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጨድ ነበረው፡፡
እዚህ ላይ የተገለጠው መልአክ የፍርድ መልአክ ነው፡፡ ይህ መልአክ እግዚአብሄርን በተቃወሙት የዓለም ሕዝቦች ላይ ታላላቅ መቅሰፍቶችን በማውረድ ወደ ዘላለም እሳት ይወረውራቸዋል፡፡ የእርሱ ተግባር ገና ዳግመኛ ያልተወለዱ የዓለም ሐጢያተኞችን በሙሉ ከጸረ ክርስቶስና ከአገልጋዮቹ ጋር አብሮ በማሰር ወደ ጥልቅ ጉድጓድ መጣል ነው፡፡
 
ቁጥር 18፡- በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን፡- ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቁረጥ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጠራ፡፡
ይህ ቃል አሁን ሐጢያተኞች እግዚአብሄርን ለተቃወሙበት ሐጢያታቸው ከእግዚአብሄር ዘንድ ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜ እንደመጣ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሄር በወሰነው ጊዜ ዕቅዶቹን ተግባራዊ የሚያደርግባቸው ሰዓቶች አሉት፡፡ እግዚአብሄር በሐጢያተኞች ላይ የእሳት ፍርዱን ለማውረድ ሐጢያተኞችን ሁሉና እግዚአብሄርን የተቃወሙትን ሁሉ በአንድ ላይ ይሰበስባቸውና ይቀጣቸዋል፡፡
 
ቁጥር 19፡- መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፤ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቆርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሄር ቁጣ መጥመቂያ ጣለ፡፡
ይህ ቃል ከቅዱሳኖች ንጥቀት በኋላ ጸረ ክርስቶስና ሐጢያተኞች በሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች በአያሌው እንደሚሰቃዩ ያሳያል፡፡ እግዚአብሄር በዚህችም ምድር ላይ እንደዚሁ አስፈሪ መቅሰፍቶቹን በእነርሱ ላይ በማውረድ ቁጣውን በሐጢያተኞች ላይ ያመጣል፡፡ ከዚያም ይህንን ተከትሎ የሲዖል ቅጣት ይመጣል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ በእነዚህ ሐጢያተኞች፣ በጸረ ክርስቶስና በተከታዮቹ ላይ የሚያወርዳቸው መቅሰፍቶች የጽድቅ ቁጣው ናቸው፡፡ እግዚአብሄር እርሱን በሚቃወሙት ሐጢያተኞች ላይ የሚያደርገው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ይህ ነው፡፡
 
ቁጥር 20፡- የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፤ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ፡፡
እዚህ ላይ ያለው ቁጥር በእነርሱ ላይ በሚፈሱት የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች የሚመጣው የእግዚአብሄር ቁጣ ቅጣት ምን ያህል የከፋና ገናም በዚህች ምድር ላይ በቀሩት ሰዎችና ሕያዋን ፍጥረታቶች ላይ የሚያደርሰው ስቃይ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ እነዚህ መቅሰፍቶች መላውን ዓለም እንደሚያወድሙም ይነግረናል፡፡ ቅዱሳን ሰማዕት ሲሆኑ፣ ትንሳኤን ሲያገኙና ሲነጠቁ ከዚህች ቅጽበት ጀምሮ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ቁጣ ይወርዱና ሁሉን ነገር ወደ ፍጻሜ ያመጡታል፡፡
በሰማይ ካሉት ቅዱሳኖችና በእግዚአብሄር አጠገብ ከቆሙት መላዕክቶች በስተቀር ከእነዚህ አስፈሪ መቅሰፍቶች የሚያመልጥ ማንም አይኖርም፡፡ በሌላ በኩል እግዚአብሄርን የሚቃወሙ ሰዎች የሚጠብቃቸው የሲዖል ቅጣት ብቻ ነው፡፡ በአንጻሩ ያን ጊዜ ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳኖች ራሳቸውን በአየር ላይ ለማዳኑ እርሱን እያመሰገኑት ከጌታ ጋር በሰርጉ እራት ፌሽታ ላይ ያገኙታል፡፡ ቅዱሳን ከዚያን ጊዜ ጀምረው በዘላለም በረከቶቹ ውስጥ ለዘላለም ከጌታ ጋር ይኖራሉ፡፡