Search

דרשות

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-23] የመገናኛው ድንኳን  አደባባይ ምሰሶዎች፡፡ ‹‹ዘጸዓት 27፡9-21››

የመገናኛው ድንኳን  አደባባይ ምሰሶዎች፡፡
‹‹ዘጸዓት 27፡9-21›› 
‹‹የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ፡፡ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፡፡ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፡፡ ከናስ የተሰሩ ሃያ ምሰሶችና ሃያ እግሮች ይሁኑለት፡፡ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ፡፡ እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፣ ከናስ የተሰሩ ሃያ ምሰሶች፣ ሃያም እግሮች ይሁኑ፡፡ በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፣ አስርም ምሰሶች፣ አስርም እግሮች ይሁኑለት፡፡ በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን፡፡ በአንድ ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አስራ አምስት ክንድ ይሁን፡፡ ምሰሶቹም ሦስት እግሮቹም ሦስት ይሁኑ፡፡ ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊም፣ ከቀይም ግምጃ፣ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሰራር የተሰራ ሃያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል፡፡ ምሰሶቹም አራት እግሮቹም አራት ይሁኑ፡፡ በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፣ የብርም ኩላቦች፣ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው፡፡ የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፡፡ ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፣ ካስማዎቹም ሁሉ፣ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ የናስ ይሁኑ፡፡›› 
 

ይህ ምንባብ የመገናኛውን ድንኳን ምሰሶዎች፣ የመጋረጃ በሮች፣ ነጩን የጥሩ በፍታ መጋረጃዎች፣ ዘንጎች፣ ኩላቦች፣ የናስ እግሮችና የናስ ካስማዎች ያብራራል፡፡ የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሄር የሚያድርበት ስፍራ ነበር፡፡ ባለ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው አደበሰባይ መጠኑ በግምት 45 ሜትር (የሰሜኑና የደቡቡ ጎኖች) በ22.5 ሜትር ((የምሥራቅና የምዕራቡ ጎኖች) የሆነ ልኬት ነበረው፡፡ የመገናኛው ድንኳን ራሱ አራት መደረቢያዎች ያሉት ጣሪያ የያዘ ትንሽዬ መዋቅር ነበር፡፡ በአንጻሩ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ ልክ እንደተለጠጠ አደባባይ ሰፊ ነበር፡፡
የአደባባዩ ምሰሶዎች ቁመት 2.25 ሜትር ነበር፡፡ በዙሪያው ያለው አጥርም 60 ከሚሆኑ የእንጨት ምሰሶዎችና ከመገቢያው በር በስተቀር በሁሉም ወገን ነጭ ማግ በሆኑ መጋረጃዎች የተሠራ ነበር፡፡ አጥሩ የተሠራው ከእነዚህ የእንጨት ምሰሶዎች፣ ጫፎቻቸውን ከሸፈኑ ዘንጎችና ከብር ኩላቦች ነበር፡፡ ከብር በተሠሩ ዘንጎች ላይ ሁለት የብር ኩላቦች ተደርገውባቸዋል፡፡ ምሰሶዎቹን እርስ በርስ ለመደገፍም ከእነዚህ ኩላቦች ጋር ረጃጅም ዘንጎች ተያይዘዋል፡፡ ከዚያም እነዚህ የብር ዘንጎች በመሬቱ ላይ ከናስ ካስማዎች ጋር ተቆራኝተው ምሰሶዎቹን በሚገባ ያጠብቁዋቸዋል፡፡ 
 
 

በመገናኛው ድንኳን ምሰሶዎች ውስጥ የተገለጡት መንፈሳዊ ትርጉሞች ምንድናቸው? 


የመገናኛው ድንኳን አደባባይ ምሰሶዎች ምን ይነግሩናል? ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን ከዓለም ሐጢያቶች እንዳዳነን በግልጥ ይነግሩናል፡፡ የመገናኛው ድንኳን አደባባይ የእንጨት ምሰሶዎች እናንተን እኔን ማለትም ዳግመኛ የተወለደውን ቅዱስ ሁሉ ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ የአደባባዩ እንጨት ምሰሶዎች በታች ያሉት የናስ እግሮችስ ምን ይነግሩናል? በሐጢያቶቻችን ምክንያት ኩነኔያችንን ከመጋፈጥ በቀር ማምለጥ የማንችል መሆናችን እውነት ቢሆንም እግዚአብሄር ግን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንዳዳነን ይነግሩናል፡፡
በሌላ በኩል ከእንጨት የተሠሩት ምሰሶዎች በብር ዘንጎች መሸፈናቸው እግዚአብሄር በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ወንጌል አማካይነት ሐጢያተኞችን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ በማዳን የደህንነትን ስጦታ እንደሰጠን ይነግሩናል፡፡ በእነዚህ የብር ዘንጎች ላይ የብር ኩላቦች የሚደረጉ መሆኑና የብር ማሰሪያዎችም ከእነዚህ ኩላቦችና በመሬት ላይ ከሚተከሉት የናስ ካሰማዎች ጋር የሚታሰሩ መሆናቸው በሐጢያቶቻችን ምክንያት ማስወገድ የማንችለው ሞት ቢገጥመንም ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ እውነት ማለትም በደህንነት ወንጌል አማካይነት የሐጢያት ስርየት ስጦታን እንደሰጠን ይነግሩናል፡፡
የመገናኛው ድንኳን አደባባይ ምሰሶዎች በዚህ መንገድ ጌታ ወደዚህ ምድር በመምጣት፣ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ፣ የሐጢያትን ፍርድ ሁሉ በመሸከምና ክቡር ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ መሥዋዕት በመሆን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንዳዳነን ያሳየናል፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ አድኖን የእግዚአብሄር ሕዝብ ያደረገንን የሐጢያት ስርየት ስጦታ ያሳዩናል፡፡ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ያለውን አጥር የሚያዋቅሩት እነዚህ የእንጨት ምሰሶዎች ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ አገልግሎት ማለትም በጥምቀቱና ባፈሰሰው ደሙ ለአንዴና ለመጨረሻ ሐጢያተኞችን ሁሉ ፈጽሞ ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ እንዳዳናቸው ይነግሩናል፡፡ ይህ እውነት በጣም ተጨባጭ ስለሆነ ለዚህ ከማመስገንና በመላው ዓለም ይህንን እውነት ከማሰራጨት በቀር የማደርገው ሌላ ነገር የለም፡፡
 
 

ከምሰሶዎቹ በታች ያሉት የናስ እግሮች፡፡ 


በዚህ አጥር ላይ የቆሙት ምሰሶዎች እግሮች የተሠሩት ከናስ ሲሆን ከምሰሶዎቹ በላይ ያሉት ዘንጎች፣ ኩላቦቻቸውና ሲባጎዎቻቸው በሙሉ ከብር የተሠሩ ነበሩ፡፡
ማርቆስ 7፡21-22 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው፡፡›› ሁላችንም የተወለድነው እነዚህን ክፉ ሐጢያቶች በሙሉ በልቦቻችን ይዘን ነው፡፡ እግዚአብሄር እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ በቀሪው ዘመናችን በእነዚህ ሐጢያቶች ውስጥ ሆነን የምንኖረውና በዚህ የሐጢያት መንገድ ከመኖር በቀር ራሳችንን መርዳት የማንችለው ለዚህ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ይህንን ቃል ልክ እንደተጻፈው አድርገን ብንቀበለው መሠረታዊ ባህሪያችን በሐጢያት የተሞላ ስለሆነ የሐጢያቶቻችንን ፍርድ ማስወገድ እንደማንችል ከመናዘዝ በቀር ልናደርገው የምንችለው ነገር የለም፡፡
ነገር ግን ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እንደ እኛ ያለነውን ጎስቋላ ፍጥረቶች ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ ጌታችን ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በገዛ ስጋው ተቀብሎ በመውሰድ፣ የዓለምን ሐጢያቶች ወደ መስቀል በመውሰድ ለእነዚህ ሐጢያቶች ም በሙሉ ኩነኔን መቀበል ችሎዋል፡፡ ኢየሱስ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ያዳነን በዚህ መንገድ ነው፡፡ 
ለዚህ እግዚአብሄርን እንደሚገባ አላመሰገንነውም! ሁላችንም ለሐጢያት የታጨን ሆነን ሳለን እግዚአብሄር ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እኛን ያዳነበት ማዳን በዚህ ዓለም ሁሉ ላይ እጅግ የከበረ እጅግ የተባረከና እጅግ በስጋ የማይተመን ስጦታ ነው፡፡ ራሳችንን ለጌታ ከማጎንበስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እውነት ባዳነን በዚህ እውነት ከማመንና ለዚህም ጌታን ከማመስገን በቀር ልናደርገው የምንችለው ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር ለመገናኛው ድንኳን አደባባይ ጥቅም ላይ በዋሉት ቁሳ ቁሶች አማካይነት የጌታችን ማዳን ምንም የማይጎድለው ፍጹም እውነት እንደሆነ እያሳየን ነው፡፡
የመገናኛው ድንኳን የተሠራባቸው ቁሳ ቁሶች ምስጢራት በሙሉ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አንደምታዎች አማካይነት የሚፈቱ ናቸው፡፡ የደህንነት ምስክር ከሰማያዊው፣ ከሐምራዊው፣ ከቀዩ ማግና ከጥሩው በፍታ ወንጌል ውጭ ፈጽሞ መፈታት የማይችል እውነት ነው፡፡ የመገናኛው ድንኳን ስርዓት አንደምታዎች በሙሉ ከመሥዋዕት ስርዓቱ ምስጢር ጋር ተዳምረው በእነዚህ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀይ ማግና በጥሩው በፍታው ውስጥ ተደብቀዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እናንተና እኔ በሐጢያቶቻችን ምክንያት በእግዚአብሄር ፊት ለሲዖል የታጨን ሰዎች ነበርን፡፡ አሁንም እንኳን በሐጢያት እየቀጠልን እንደሆንን ግልጥ ነው፡፡ ጌታ ግን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ፍጹም የሆነ የሐጢያቶች ስርየት ሰጠን፡፡ በዚህ የደህንነት ስጦታ በማመን ይህንን የሐጢያቶች ስርየት ተቀብለናል፡፡ በመንግሥቱ ክብርና ግርማ ሞገስ እንደሰት ዘንድ የእርሱ ወራሾች መሆን የቻልነው እግዚአብሄር ፈጽሞ ከሐጢያቶቻችን ስላዳነን ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሰጠን ደህንነት ውጪ ዳግመኛ የተወለድን የእርሱ ልጆች የምንሆንበት ሌላ መንገድ የለም፡፡ ጌታችንን የምናመሰግነው ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ስላዳነን ነው፡፡
እኛ የሐጢያቶቻችንን መጠን በራሳችን መለኪያዎች ብቻ በመለካት መሠረታዊ ማንነታችንን በሚመለከት በተጨባጭ ማን እንደሆንን ሁልጊዜም አናውቅም፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ሐጢያቶችን መሥራት ወይም አለመሥራታችን ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ምግባሮቻችን ምንም ይሁኑ ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ ከቀድሞውም ለሲዖል የታጩ አስከፊ ሐጢያተኞች ነንና፡፡ ነገር ግን ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ ጌታ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሰጠው ተስፋ መሠረት በአዲስ ኪዳን ዘመን ወደ እኛ መጥቶ በተስፋው ቃል መሠረት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ወሰደ፡፡ እነዚህን ሐጢያቶች በመስቀል ላይ ተሸክሞ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ በመሥዋዕቱ የሐጢያቶቻችንን ሁሉ ዋጋ ከፈለ፡፡ በዚህም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አድኖን የደህንነትን ስጦታ ሰጠን፡፡ እናንተና እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የምንድንበትን የደህንነት ስጦታ የተቀበልነው በዚህ መንገድ ነው፡፡
 

 
የነጩ በፍታ መጋረጃዎች በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ምሰሶ ላይ ለምን ተንጠለጠሉ? 


በመገናኛው ድንኳን አደባባይ በአጠቃላይ 60 ምሰሶዎች ተተክለው ነበር፡፡ ሁሉም ከነጭ በፍታ በተጠለፉ መጋረጃዎች ተሸፍነው ነበር፡፡ እነዚህ መጋረጃዎች እኛ ሁላችን በሐጢያቶቻችን የረከስን ርኩሳን ፍጥረታቶች በመሆናችን በሐጢያቶቻችን ተኮንነን ወደ ሲዖል መጣል ያለብን ብንሆንም ጌታችን ግን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ እንዳነጻን ይነግሩናል፡፡ በሌላ አነጋገር መጋረጃዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ እንዳስወገዳቸው ይነግሩናል፡፡ 
ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ የሰው ዘር ወኪል በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ ኢየሱስ ተሻገሩ፡ ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ የዓለምን ሐጢያቶች ከተቀበለ በኋላ የሐጢያተኞችን ኩነኔ ለመሸከም ተሰቀለ፤ ደሙንም አፈሰሰ፤ ከዚያም ዳግመኛ ከሙታን ተነሳ፡፡ ከሙታን ከተነሳ በኋላም አሁን ሕያው አዳኛችን ሆንዋል፡፡ ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አገልገሎቱ አማካይነት የፈጸመው የደህንነት ስጦታ ይህ ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ያዳነንና የእግዚአብሄር ልጆች እንሆን ዘንድም ነውርና አንዳች ድካም የሌለብን ያደረገን የጌታችን ፍቅር ይህ ነው፡፡ ጌታችን ይህንን የደህንነት ስጦታ ለእኛ በመስጠት በዚህ እውነት የምናምነውን ሰዎች የራሱ የእግዚአብሄር ሕዝብ አድርጎናል፡፡ 
በመገናኛው ድንኳን ምሰሶዎች ላይ የተንጠለጠለው ነጩ በፍታ ስለ እግዚአብሄር ቅድስና ይነግረናል፡፡ ስለ እኛም ቅድስናና ስለ እውነተኛ ምዕመናን ቅድስናም ይናገራል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ልጆች ለመሆን ከፈለግን እኛም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ነጽተን በኢየሱስ የሰማያዊ፣ የሐምራዊና የቀይ ማግ አገልግሎት በማመን ቅዱሳን መሆን አለብን፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ነግሮናል፡- ‹‹እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፡፡›› (ዘሌዋውያን 11፡45) ነገር ግን በምግባሮቻችን እንዴት ቅዱሳን ልንሆን እንችላለን? ምንም ያህል ተግተን ብንሞክርም ሐጢያት መሥራትን ማስወገድ ስለማንችል በገዛ ጥረቶቻችን ፈጽሞ ቅዱሳን ልንሆን አንችልም፡፡ ነገር ግን ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ እንደ እናንተና እንደ እኔ ያለነውን ፍጡራኖች ሙሉ በሙሉ አንጽቶናል፡፡ እናንተና እኔ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄር ሕዝብ የሆንነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ ወንጌል ከማመንና ከሐጢያቶቻችንም በመንጻት ቅዱሳን ከመሆን በቀር ሌላ መንገድ የለም፡፡
 
 
የናስ እግሮችና የናስ ካስማዎች፡፡ 
 
የብር ዘንጎች በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ተለብጠዋል፡፡ የብር ኩላቦችና የብር ሲባጎዎችም ምሰሶዎቹን እርስ በርሳቸው ለማያያዝና ለማጠንከር አገልግለዋል፡፡ እያንዳንዱ ምሰሶ በናሱ እግር ላይ ተተክሎዋል፡፡ ጥንድ የሆኑ ካስማዎችም በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ያለውን እያንዳንዱን የአጥር ምሰሶ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች እስከ መሬት ድረስ አቆራኝተውታል፡፡
ይህም በሐጢያቶቻችን ምክንያት ለመኮነንና ወደ ሲዖል ለመጣል የታጨን ብንሆንም እግዚአብሄር ግን ከሐጢያቶቻችን ያዳነንን የደህንነት ስጦታ በመስጠት የራሱ ቅዱሳን ሕዝብ እንዳደረገን ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ የደህንነት ጸጋ አማካይነት የእርሱ ቅዱሳን ሕዝብ ስላደረገን ለጸጋው እግዚአብሄርን ከማመስገን በቀር የምናደርገው ነገር የለም፡፡ በዚህ የሰማያዊው፣ የሐምራዊው፣ የቀዩ ማግና የጥሩው በፍታ ቃለ እውነት አማካይነት በእግዚአብሄር በማመናችን እግዚአብሄርን ማመስገን ብቻ ሳይሆን ይህንን ቃል ማሰራጨትም አለብን፡፡
በጭራሽ ሐጢያት የማንሠራበት አንዳች ቀን አለ? የለም! በእግዚአብሄር ቃል አምነን በጸጋው አማካይነት ዳግመኛ የተወለድን ሰዎች እንኳን በየቀኑ ሐጢያት እንሠራለን፡፡ ትንሽ የሚቃወመን ወይም የማይወዳጀን ሰው እንኳን ካለ ጊዜ ሳናጠፋ ይህንን ሰው እያብጠለጠልን እንረግመዋለን፡፡ መኪናችሁን በሰላም እየነዳችሁ ሳለ ድንገት አንድ ሰው አቋርጦ ቢገባባችሁና አደጋ ሊፈጥርባችሁ ተቃርቦ ቢሆን በዚህ ግድየለሽ ሾፌር አትበሳጩምን? ትበሳጫላችሁ! እኔ ያንን ከንቱ ሾፌር የመኪናዬን ጡሩንባ በማስጮህ እረግመው ይሆናል፡፡ ነገር ግን መደረግ ያለበት ትክክለኛው ነገር ይህ ነውን? ይህ መደረግ ያለበት ትክክለኛ ነገር አይደለም፡፡ ችግሩ ግን በማንኛውም ቅጽበት ሐጢያት የምንሠራ ፍጡራን መሆናችን ነው፡፡
እኛ ከድካሞቻችን የተነሳ ለሲዖል የታጨን ፍጥረታቶች ነን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ‹‹እርሱ የቀደሰልንን አዲስና ሕያው መንገድ›› (ዕብራውያን 10፡20) ሰጠን፡፡ ይህ በእግዚአብሄር አብ ፈቃድ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የፈጸመው ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡
እግዚአብሄር የሰጠን የደህንነት ስጦታ ምንድነው? እርሱ በአራቱ የመገናኛው ድንኳን ማጎች በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት የተፈጸመውን ከሐጢያቶቻችን የምንድንበትን የደህንነታችንን ስጦታ ሰጠን፡፡ ታዲያ እግዚአብሄርን ማመስገን እንዴት ይሳነናል? ይህንን እውነተኛ ደህንነት ተቀብለን ሳለን ልቦቻችን በእውነተኛ ሰላም ለምን አይሞሉም? ወርቅ ወይም ብር በመክፈል ደህንነታችንን ፈጽሞ ማግኘት አንችልም፡ ደህንነታችን እንደ እንፋሎት ወይም ፈጥኖ እንደሚጠፋ የማለዳ ጤዛም አይደለም፡፡ ነገር ግን ለዘላለም ፈጽመን ድነናል፡፡ እግዚአብሄር ሐጢያተኞችን አብዝቶ ስለወደደ የደህንነት ጸጋውን ነጻ ስጦታ አድርጎ ሰጣቸው፡፡ በዚህ ስጦታም ለእኛ ለምዕመናን ጽድቁን አለበሰን፡፡
የመገናኛው ድንኳን አጥር ከተሠራባቸው ቁሳ ቁሶች መካከል ከመሬት ጋር የተገናኙት እግሮችና ካስማዎች በሙሉ የተሠሩት ከናስ ነበር፡፡ ነገር ግን በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉት ዘንጎች የተሠሩት ከብር ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ታሪኮች እኛ ሁላችን በመሠረቱ ለሲዖል የታጨን ብንሆንም በጌታችን የተሰጠውን የደህንነት ስጦታ በመቀበል የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችንን ያሳያሉ፡፡ ሁላችንም በቃሉ በማመን ይህንን ስጦታ ተቀብለናል፡፡ ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ ከሐጢያቶቻችን የዳንንበት ይህ የተቀበልነው ደህንነት ምን ያህል አስተማማኝ ነው? ይህ እግዚአብሄር ሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ፈጽሞ ሊለወጥ የማይችል አስተማማኝ ደህንነታችንና በረከታችንም ነው፡፡ እግዚአብሄርን በሁለንተናችን እንደሚገባ ልናመሰግነው ያልቻልነው ይህንን ስለምናውቅ ነው፡፡
እናንተና እኔ ከሐጢያቶቻችን መዳናችን በእርግጥም የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ደህንነታችን ድካሞቻችን በሚገለጡበት ጊዜ ሁሉ በቀላሉ የሚከስም እንከን ያለበት ደህንነት አይደለም፡፡ ጌታችን እንደ እኔና እንደ እናንተ ላለነው ጎስቋላ ሐጢያተኞች ወደዚህ ምድር መጥቶ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የደህንነትን ስጦታ ሰጠን፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት የሚያምኑ ሁሉ ለዘላለም ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ይድናሉ፡፡ ጌታችን ሐጢያተኞችን ያዳነበትን ማዳን ፍጹም ስለሆነና የስጋችንን አለመብቃቶች፣ ድካሞችና እንከኖች ሁሉ ስለወሰደ ከሐጢያት ጋር የሚያገናኘን አንዳች ነገር እንዳይኖር ምሉዓን አድርጎናል፡፡ ሰማያዊውን፣ ሐምራዊውን፣ ቀዩን ማግና ጥሩውን በፍታ በግልጥ አውቀው የሚያምኑበት ሰዎች በሙሉ ለዘላለም ፈጽመው ይድናሉ፡፡
እግዚአብሄር የሰጠን ይህ የደህንነት ስጦታ ምንኛ ክቡርና ያማረ ነው? እኔ ለዚህ የደህንነት ስጦታ ከልቤ አመስጋኝ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ልቦቻችንን በሚገባ አሳርፎልናልና፡፡ አብዝቶም አጸናንቶናል፤ ባርኮናልም፡፡ ጌታችን ልቦቻችንን አሳርፎዋል፡፡ ‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ›› (ማቴዎስ 11፡28) ያለው ለዚህ ነው፡፡ ከሐጢያቶቼ ሁሉ የዳንሁበትን ይህንን የቤዛነት ስጦታ ስለሰጠኝ እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችሁም ለእግዚአብሄር በጣም ክቡር እንደሆናችሁ አምናለሁ፡፡ እግዚአብሄር እናንተንና እኔን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ወንጌል አድኖናል፡፡ እግዚአብሄር ይህንን የደህንነት ስጦታ በዚህ ቃል ለሚያምኑ ሁሉ እንደሰጠ ተናግሮዋል፡፡ እኔ እርሱ በተናገረው ስለማምን እናንተም እንደዚሁ ለእግዚአብሄር በጣም ክቡር እንደሆናችሁ አስባለሁ፤ አምናለሁም፡፡
በቅርቡ ከአቅማችን በላይ ለእግዚአብሄር ሥራ በትጋት እየሠራን ሳለ በድካም የተሸነፍንባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ስጋችንን ለማበርታት አብረን እንጀራ በምንቆርስበት ጊዜ አብረውኝ የሚሠሩትን ሠራተኞች ለማጽናናትና ለማበረታታት እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን በስጋ ማጽናናት መጽናናት በትክክል እንደማንችል አውቃለሁ፡፡ የምንበረታታው እውነተኛ መጽናናታችን የሆነውን ጌታ የሰጠንን አስተማማኝ ደህንነታችንንና ለዓለም የማይታወቀውን ሰላም በማሰብ ነው፡፡ እግዚአብሄር አስቀድሞ ለልቦቻችን በሰጣቸው መንፈሳዊ በረከቶች ረክተን ተጽናንተናል፡፡ እግዚአብሄር በሰጠን በዚህ የደህንነት ስጦታ ውስጥ ታላላቅ ሽልማቶችና በረከቶች ስለምንቀበል ልቦቻችን ይህ ዓለም የማያውቃቸው ሰላምና በረከቶች አሉዋቸው፡፡
እግዚአብሄር ለእያንዳንዳችሁ ፍጹም የሆነውን የደህንነት ስጦታ ሰጥቶዋችኋል፡፡ በዚህ ዓለም ከሚታወቅ ሁሉ እጅግ የላቀው ስጦታ ይህ ነው፡፡ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ሳያምኑ ለሐይማኖት ባላቸው ቀናዒነት ብቻ ሐጢያት አልባ እንደሆኑ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ቀናዒነት የተሞሉት ስሜቶቻቸው ብዙም ሳይቆዩ ይተናሉ፡፡ በራሳቸው አስተሳሰቦች ያገኙት ሰላምም ትንሽ ሐጢያት ሲሰሩ ወይም ትንሽ መከራ ሲገጥማቸው ልክ እንደ ማለዳ ጤዛ ይጠፋል፡፡
ነገር ግን ጌታ በሰጠው የሰማያዊ፣ የሐምራዊ፣ የቀይ ማግና የጥሩ በፍታ ደህንነት የሚያምኑ ሰዎች ግን ብዙ መከራ በገጠማቸው ጊዜ የአእምሮ ሰላማቸው ይበልጥ ብሩህ ሆኖ ያበራል፡፡ ብንረገጥ፣ ብንጎዳና ብናዝንም በልቦቻችን ውስጥ ካለውና እግዚአብሄር ከሰጠን የደህንነት ስጦታ ፍጹምነትና ምስጋና ይፈልቃል፡፡ እኛ ሙሉ በሙሉ ስለዳንን በጭራሽ ወደ ግብጽ አንመለስም፡፡ ዳግመኛም ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔያችን ጋር አንገጣጠምም፡፡ እርሱን ሁልጊዜ በእምነታችን እናመሰግነው ዘንድ እግዚአብሄር እርሱ የሰጠንን ይህንን የደህንነት እውነት የምናውቀውንና የምናምነውን ባርኮናል፡፡ በእምነታችን እግዚአብሄርን የምናመሰግነው ለዚህ ነው፡፡
ይህንን አስተማማኝ የሰማያዊ፣ የሐምራዊና የቀይ ማግ ደህንነት ተቀብዬ እግዚአብሄር ወዶኝ፣ አብዝቶ ባርኮኝና ይህንን የከበረ ወንጌል እንድሰብክ አድርጎኝ ሳለ እግዚአብሄርን እንደሚገባው አላመሰገንሁትም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚገቡኝ እንዳልሆኑ አውቃለሁ፡፡ ጌታን በየቀኑ ባመሰግነው እንኳን ለወንጌል ብቻ እንድኖር ስላደረገኝ እንደሚገባው አላመሰገንሁትም፡፡ ለዘላለም ላመሰግነው ይገባኛል፡፡ እግዚአብሄርን ስለሰጠን ታላቅ የደህንነት ስጦታ ሳመሰግነውና በምስጋና የተሞላውን ልቤን ስገልጥ ቃላቴና አገላለጦቼ ምን ያህል ብቃት እንደሌላቸው እገነዘባለሁ፡፡
እኛ የሰማያዊው፣ የሐምራዊው፣ የቀዩ ማግና የጥሩው በፍታ ወንጌል ሆኖ በተገለጠው ደህንነት እናምናለን፡፡ ኢየሱስ ለእናንተ ሲል ወደዚህ ምድር ተወለደ፤ በ30 ዓመቱ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችሁን በሙሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ እነዚህን ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ ተሸከመ፡፡ ደሙንም አፍስሶ ሞተ፡፡ ከሙታንም ተነሳ፡፡ አሁን በእግዚአብሄር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦዋል፡፡ ይህንን እምነት እስካልካድን ድረስ አንድ ጊዜ የተቀበልነው ይህ ደህንነት በጭራሽ ከንቱ አይሆንም፡፡ ምንም ያህል ድካሞች ቢኖሩብንም፣ ምንም ያህል ስህተቶችን ብንሠራም ሁላችንም ፍጹም የሆነውን የደህንነት ስጦታ ለብሰን የገዛ ራሱ ሕዝብ ሆነናል፡፡

 

በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ምሰሶዎች ላይ የተንጠለጠለው ጥሩው ነጭ በፍታ፡፡ 


ለጥቂት ጊዜ ከጥሩ በፍታ የተሠሩትን ነጫጭ መጋረጃዎች ስትመለከቱ አስቡ፡፡ እነዚህ ከጥሩ በፍታ የተሠሩት ነጫጭ መጋረጃዎች ከናይሎን ጨርቅ የተሠሩ ሳይሆኑ ከነጭ የተልባ እግር ማግ የተሠሩ ነበሩ፡፡ እንደዚህ ያሉትን ነጫጭ የበፍታ መጋረጃዎች በምድረ በዳ ላይ ብትሰቅሉዋቸው ብዙም ሳይቆይ ይቆሽሻሉ፡፡ ታዲያ እግዚአብሄር አነዚህን ነጫጭ መጋረጃዎች ያንጠለጠለው ያለ ምክንያት ነውን? ብዙም ሳይቆዩ እንደሚቆሽሹ አያውቅምን? እስራኤሎች እነዚህን ነጫጭ መጋረጃዎች እንዲሰቅሉ የነገራቸው በእምነት አማካይነት ይህንን ስጦታ ለተቀበልነው ለእኛ የሰጠንን የደህንነት ስጦታ ለማሳየት ነው፡፡ ከረከሱት ሐጢያቶቻችን ሁሉ ሙሉ በሙሉና በንጽህና እንዳዳነን በግልጥ እንድናውቅና በልቦቻችን ውስጥ እንድንቀበል ለማድረግ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለእስራኤሎች እነዚህን ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነጫጭ መጋረጃዎች እንዲሰቅሉ ነገራቸው፡፡ ይህም በነጫጮቹ መጋረጃዎች የተገለጠውን የእርሱን ፍጹም የሆነ ደህንነት በማየትና በማመን ለዘላለም ልናወድሰውና ልናመሰግነው እንደሚገባን ይጠቁማል፡፡ እግዚአብሄር በእነዚህ ጥሩ ነጫጭ የበፍታ መጋረጃዎች አማካይነት ሙሉ በሙሉ የደህንነትን ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ እርሱ የሰጠን ደህንነታችን ልክ እንደዚህ ጥሩ ነጭ በፍታ ነው፡፡
እኛ በእርግጥም በሐጢያት ምክንያት ለሲዖል ከመታጨት ማምለጥ የማንችል የተከሰስንና የተጎሳቆልን ሰዎች ነን፡፡ በቀን ውስጥ ብቻ የአእምሮዋችንን መጎናጸፊያዎች ብዙ ጊዜ ማጠብ የሚኖርብን ሰዎች ነን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ልቦቻችንን ፈጽሞ እንደ አመዳይ አነጻቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታችን እንደ እኛ ያሉ ሰዎችን ምሉዓን አድርጎዋቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ሐይል እጅግ ታላቅና ዕጹብ ድንቅ ስለሆነ አስጠሊታ፣ የረከስንና በቀላሉ የቆሸሽነውን እኛን የራሱ ቅዱስ ሕዝብ ወደ መሆን ቀየረን፡፡ 
ዛሬ በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል የምናምን እናንተና እኔ ይህንን ፍጹም የደህንነት ስጦታ ከእግዚአብሄር ተቀብለናል፡፡ የልብ ሐጢያቶቻችን በሙሉ ፈጽሞ ነጽተዋል፡፡ እንደ በረዶም ነጭ ሆነናል፡፡
አሁንም ድረስ በልቦቻችሁ ውስጥ ሐጢያት አለባችሁን? በእርግጥም የለባችሁም! ልቦቻችሁ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ አጥር ላይ እንደተሰቀለው ንጹህ ነጭ በፍታ ሆነዋል፡፡ እናንተና እኔ በዚህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ነጽተናል፡፡ በመሠረቱ በሐጢያቶቻችን ምክንያት ለመኮነን የታጨን ብንሆንም የሆኖ ሆኖ ድነናል፡፡ ይህ ደህንነት የመጣው ከእኛ መልካምነት ወይም ታማኝነት ሳይሆን የመገናኛው ድንኳን ምሰሶዎች በብር ሲባጎዎች በአንድ ላይ ታስረው ከብር ዘንጎቻቸው ጋር እንደተያያዙ የናስ ካስማዎች ሐይልን ካጎናጸፈን ከእግዚአብሄር ጸጋ ነው፡፡ እኛ በእርግጥም ለሲዖልና ለኩነኔ የታጨን ብንሆንም እግዚአብሄር የደህንነት ስጦታውን እንዳጎናጸፈን በማመን ሁላችንም የእርሱ የዳንን ሕዝቦች እንሆናለን፡፡ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ አጥር ላይ የተገለጠው እውነት ይህ ነው፡፡
የመገናኛው ድንኳን 60 ምሰሶዎች የሚያመለክቱት እኛን እውነተኛ ምዕመናኖችን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህ ምሰሶዎች እያንዳንዳቸው እያንዳንዳችንን ያመለክታሉ፡፡ እኛ የእግዚአብሄር ሕዝብ መሆንና ወደ ቤቱም መግባት የማንችል ሰዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ይህንን የደህንነት ስጦታ እንደ እኛ ላለነው ከንቱ ሰዎች ሰጠን፡፡ እርሱ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ የደህንነትንም ስጦታ አጠናቀቀ፡፡ ይህንን የእውነት ስጦታም ሰጠን፡፡ ይህንን እውነት በማወቃችንና በማመናችንም ሙሉ በሙሉ አዳነንና ዳግመኛ ፈጽሞ የማንረገም የራሱ ሕዝቦች አደረገን፡፡
ይህ ምንኛ ድንቅ በረከት ነው? ልክ እንደ መገናኛው ድንኳን ምሰሶዎች እኛም በራሳችን ብቻችንን መቆም አንችልም፡፡ ነገር ግን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ከዳንን በኋላ የማንወድቀው ፍጹም በሆነው በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የምናምን እኛ ምዕመናን ሁላችንም በዚህ ጸጋ ስለምናምንና በአንድ ላይ ስለተሳሰርን ነው፡፡ በመጀመሪያ እኛ ለሲዖል ከመታጨት ማምለጥ የማንችል ከንቱ ሰዎች ብንሆንም ጌታ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ቃል አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አንጽቶን በግሉ ኩነኔያችንን ሁሉ በመሸከም ሁላችንንም ሙሉ በሙሉ እንዳዳነን ማመን አለብን፡፡ በማንኛውም ጊዜ በእግዚአብሄር ፊት መቆም፣ እርሱን ማመስገን፣ ሥራዎቹን መሥራትና ሁልጊዜም ለዚህ የደህንነት ስጦታ እርሱን ማወደስ የምንችለው በዚህ እምነት ነው፡፡ 
ከስጋችን ድካም የተነሳ የምንሰናከልባቸው ወቅቶች አሉ፡፡ ከሐጢያቶቻችንና ከኩነኔያችን እንደዳንን ብናምንም ከዳንን በኋላ ለምን እንዲህ ባለ መንገድ እንደምንኖር ግራ ተጋብተን የምንደክምባቸውና የምንሰለችባቸው ወቅቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ባሉ የስጋ አስተሳሰቦች ብንታወክም ከዳንን በኋላ ከእግዚአብሄር የማንኮበልለውና እምነታችንን ያለ ማመንታት የምንኖረው ወደኋላ መለስ ብለን በእርግጥ ማን እንደነበርን ስንመለከት እግዚአብሄር ለሰጠን የደህንነት ስጦታና የአርነት ጸጋ ይበልጥ አመስጋኞች ስለምንሆን ነው፡፡
ሁላችንም በእምነታችን ጸንተን የምንቆመው ለዚህ ነው፡፡ ለእውነተኛው ወንጌል ምስጋና ይግባውና ከግራ መጋባቶቻችን ሁሉ ነጻ ወጥተን እንደገና በእምነት መቆም እንችላለን፡፡ ሁልጊዜም በድካሞች የተሞላን ብንሆንም ፍጹም ለሆነው ደህንነቱ እግዚአብሄርን እናመሰግነዋለን፡፡ ጥቂትም ብትሆን አንኩራራም፡፡ በፋንታው በዚህ የደህንነት ስጦታ አማካይነት ልጆቹ ስላደረገን፣ በፊቱ በጽናት ስላቆመንና የካህናቱንም ተግባራት በታማኝነት እንድናከናውን ስላደረገን እናመሰግነዋለን፡፡ ጽኑዎች የሚያደርገንና በእምነታችን በጽናት እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሄር የሰጠንን ታላቅ የደህንነትና የጸጋ ስጦታ የመቀበላችን እውነታ ነው፡፡ መሠረታዊውን ባህሪያችንን እንድናውቅ እግዚአብሄር በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ቃል አማካይነት የሐጢያት ስርየትን ተቀብለን ጌታን ከማገልገል በቀር አማራጭ የለንም፡፡
ይህ ምን ያህል ሊወደስ እንደሚገባው በማወቅና በመገንዘብ በልባችን ስንቀበለው እምነታችን ዳግመኛ አይናወጥም፡፡ ጽኑ ይሆናል፡፡ ሰዎች ምንም ያህል ማታለያዎች ቢወረውሩብን ክቡር በሆነው የመስቀሉ ደም በማመን ብቻ እነርሱ ራሳቸውም ስለሞቱ አሁን ፍጹማን መሆናቸውን በመናገር ምንም ዓይነት አይረቤ ነገር ቢያውጁም እምነታችን ሊናወጥ አይችልም፡፡ መሠረታዊው ተፈጥሮዋችን በጣም ክፉ ቢሆንም ጌታ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ያዳነን በመሆኑ የታመነ እውነት በማመን ሁላችንም እንደ እነዚህ ያሉ ውሸቶችን በድፍረት መዋጋትና ጽኑ በሆነው እምነታችን መቆም እንችላለን፡፡
በዚህ መንገድ ‹‹ምንኛ የዳንነው በከበረው የመስቀሉ ደም በማመን ብቻ ነውን? በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ ከተፈጸሙት የደህንነት ፍሬ ነገሮች አንዱን ብንተው የምንኮራበት ምንም ነገር አይኖረንም፡፡ ይህ ምንኛ አይረቤ ነው?›› በማለት እነዚህን ውሸቶች መዋጋት እንችላለን፡፡
ነገር ግን እግዚአብሄር ከሰጠን የደህንነት ጸጋ ብንኮበልል የራሳችንን ትክክለኛ ማንነት ማየት አንችልም፡፡ በዚህ የተነሳም በራሳችን የምንተማመንና ኩራተኞች ስለምንሆን መጨረሻችን ክፉ መሆን ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄርን የደህንነት ስጦታ በላቀ ደረጃ ማግኘት የምንችለው ማንነታችንን በትክክል በመመልከት ነው፡፡ ‹‹ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሄር ፈቃድ በኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ እናንተ ነውና›› (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡16-18) የሚለውን ምክር የምንታዘዘው በዚህ መንገድ ነው፡፡ 
እያንዳንዱ ምሰሶ በብር ሲባጎዎች ተደግፎ ከናስ ካስማዎች ጋር እንደታሰረ ሁሉ እኛም በእግዚአብሄር ፊት በተጨባጭ በጽናት የምንቆመው ጌታ ስለ እኛ እርግማኖቻችንን ሁሉ እንደተሸከመ በማመን ነው፡፡ ስለዚህ ተሰናክለን ብንወድቅ እንኳን በጽናት በሚደግፈን የብር ሲባጎ እንደገና ሚዛናችንን መጠበቅ እንችላለን፡፡ እያንዳንዱ የብር ሲባጎ ከኩላቦቹና ከካስማዎቹ ጋር ተያይዞ ምሰሶዎቹን አጽንቶ ይደግፋቸዋል፡፡ ልቦቻችን በእርግጥ ማን እንደሆንን ስለሚያውቁና በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ አማካይነት ያዳነን የእግዚአብሄር ጸጋ ስላለ አንፍገመገምም፡፡ ከዚህ የተነሳ ቀጥ ብለን እንቆማለን፡፡ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንወዛወዝም፡፡
እግዚአብሄር ከሰጠን ፍጹም የደህንነት ስጦታና ከእግዚአብሄር ጽድቅ የተነሳ ወደ ፊታችን ወይም ወደኋላችን አንወድቅም፡፡ ወደ ጎንም አንወድቅም፡፡ ነገር ግን በናሱ እግሮች ጸንተን እንቆማለን፡፡ የናሱ እግሮች አስቀድሞ ለሲዖል የተኮነን እንደነበርን ይጠቁማል፡፡ ከማይቀረው ኩነኔ ስፍራ እንደዳንን ራሳችንን በማስታወስ ሁልጊዜም እግዚአብሄርን እያመሰገንን በእምነት ጸንተን እንቆማለን፡፡
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ዕጹብ ድንቅ የደህንነት እውነት ነው፡፡ ይህ ደህንነት በዚህ ዓለም ላይ ከሚገኙት በርካታ የቃለ መለኮት ሴሚናሪዎችና አስመራቂ ትምህርት ቤቶች ሊገኝ አይችልም፡፡ ይህ እምነት መሠረትና ቁም ነገር ስለሆነ የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እውነት የማያውቅና የማይማር ማንኛውም ቃለ መለኮት ተፈረካክሶ እንደሚወድቅ በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት ይመስላል፡፡ የእውነተኛ እምነታችሁ መሠረት ልክ እንደ ብርቱ የዕብነ በረድ ዓለት ጠንካራ መሆን አለበት፡፡
 
 
የነገረ መለኮት ትምህርት ምንድነው? 

በጥቅሉ አነጋገር የነገረ መለኮትን ትምህርት የሚከፋፍሉ ሁለት ዋና ዋና ቅርንጫፎች አሉ፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ያነጣጠረ የነገረ መለኮት ትምህርትና በሰው አስተሳሰቦች ላይ ያነጣጠረ የነገረ መለኮት ትምህርት አለ፡፡ ከሁለቱ አንዱ ወይም ሁለቱም በእያንዳንዱ ሴሚናሪ ውስጥ ይስተማራሉ፡፡ በቀላል አነጋገር በቃሉ ላይ በጥብቅ የተመሠረተ እምነት በእግዚአብሄር ላይ ያነጣጠረ ሲሆን በቃሉ ውስጥ የሰዎችን አስተሳሰቦች የሚቀበል እምነት ደግሞ በሰው አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሰው አስተሳሰብ የሚያምኑ የነገረ መለኮት ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ በተጨባጭ በሚናገረው ነገር ላይ ያን ያህል ፍላጎት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ምሁራዊ አቋሞቻቸው ተቀባይነት ያገኙ ምሁራን ባብራሩዋቸው አመለካከቶች ወይም በሚከተሉዋቸው ተከታዮች ላይ ተመሥርቶ ሊደገፉ ወይም ሊተቹ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በሰው አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ የነገረ መለኮት ትምህርት ትክክለኛ የነገረ መለኮት ትምህርት ተደርጎ በጭራሽ ሊቆጠር አይችልም፡፡
በአጠቃላይ የነገረ መለኮትን ትምህርት የሚያጠኑ ሰዎች የእነርሱ የነገረ መለኮት ትምህርት አመለካከቶች ብቻ ትክክል እንደሆኑ አድርገው ይከራከራሉ፡፡ ለምሳሌ በሰንበት ቀን ላይ ብቻ ትልቅ ትኩረት በሚያደርገው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል የሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል የፕሪስባይቴርያን ቤተክርስቲያን አምስቱ የካልቪናውያን ነጥቦች ተብለው የሚጠሩትን ብቻ ተቀብላለች፡፡ አርሜናዊነትም እግዚአብሄር ቢያድነንም የሰው ዘር በዚህ እውነታ በውዴታ ማመን አለበት ብለው ይከራከራሉ፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች አርሜናዊነት መጽሐፍ ቅዱስን በሰው አመለካከቶች የሚቀርብና የሚተረጉም የነገረ መለኮት አቋም ተብሎ ሊታይ ይችላል፡፡
በአንጻሩ የካልቪናውያንን አምስቱን ነጥቦች በምንመለከትበት ጊዜ እምነቱ በመጠኑም ቢሆን በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሠረተ ነገር ግን በጣም አደገኛ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ለምን? ምክንያቱም የካልቪን ተከታዮች ‹‹ከመወለዳችሁ በፊት አንዳንዶቻችሁ አስቀድሞ የእርሱ ሕዝብ ሆናችሁ በእግዚአብሄር ተመርጣችኋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከእርሱ ምርጫ ወጥተዋል፡፡ የእግዚአብሄር ሉዓላዊ ምርጫ ብቻ ነው ያለው›› ብለው በመከራከር አስቀድሞ የመወሰንና የመመረጥ ትምህርቶቻቸውን ይደግፋሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ጎጂ አባባሎች በእግዚአብሄር ቃል ተደጋፊነት የላቸውም፡፡
ስለዚህ እነዚህን ትክክለኛ ትምህርቶች ተብዬዎችን በእግዚአብሄር ቃል ስንመዝናቸው ከእውነት በጣም የተለዩ መሆናቸውን መረዳት እንችላለን፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ወደ እውነት መቅረባቸው እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ የብዙ ቤተክርስቲያናት የክርስትና ቃለ እግዚአብሄራዊ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በጣም የራቁ ናቸው፡፡ በትምህርቶቻቸው ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋር የሚጣጣሙ አንዳንድ ክፍሎች መኖራቸው እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ ትምህርቶቻቸው ወደ እግዚአብሄር ቃል ለመቃረብ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ የተሳሳቱ ትምህርቶችን መማር ማቆም ያለብን ለዚህ ነው፡፡
 
 

የሐጢያት ስርየታችን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ 

 
በእግዚአብሄር ቃል በልባቸው ለሚያምኑ ሰዎች እግዚአብሄር ደህንነቱን በስጦታ መልክ አበርክቶላቸዋል፡፡
የመገናኛው ድንኳን አጥር በ60 የእንጨት ምሰሶዎች የተሠራ ነበር፡፡ ከእነዚህ ምሰሶዎች ጫፍ ላይ የብር ዘንጎች ተደርገዋል፡፡ ከታች ደግሞ የናስ እግሮች ተተክለዋል፡፡ እያንዳንዱ ምሰሶ እርስ በርሱ በብር ሲባጎ ተያይዞ መሬት ውስጥ ከተተከሉ ካስማዎች ጋር ታስሮዋል፡፡ የእንጨት ምሰሶዎቹ በ5 ክንድ ወይም 2.25 ሜትር ክፍተት የቆሙ ነበሩ፡፡ በእነዚህ ምሰሶዎች ላይም ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነጫጭ መጋረጃዎች ተንጠልጥለውባቸው ነበር፡፡ 
እነዚህ ምሰሶዎች በእነዚህ የናስ ካስማዎች በጥብቅ ስለታሰሩና በብር ሲባጎዎችም እርስ በርሳቸው በሚገባ ስለተያያዙ ከጥሩ በፍታ የተሠሩት ነጫጭ መጋረጃዎች ከቦታቸው ሊወገዱ አይችሉም፡፡ ከነጫጭ በፍታ የተሠሩት መጋረጃዎች በደንብ በተተከሉት በእነዚህ የእንጨት ምሰሶዎች ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው መጋረጃዎቹ በእያንዳንዱ አቅጣጫ ቢውለበለቡም ጽኑና ባሉበት የሚቆዩ ሆነው ይቀራሉ፡፡
ከነጫጭ በፍታ የተሠሩት መጋረጃዎች የእግዚአብሄርን ቅድስናና ጽድቅ ያመለክታሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የእግዚአብሄር ጽድቅ ከእንግዲህ ወዲያ ፈጽሞ ሊናወጥ የማይችል ጽኑ እምነት ያለን ሰዎች እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ማዳን ላይ ያለን እምነት በማይወድቀው የእግዚአብሄር ጸጋ የጸና ነውና፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ፍጹም የሆነ ደህንነት ከእርሱ የተበረከተ ስጦታ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡ ምንኛ አመስጋኞች ነኝ! እናንተና እኔ በእምነት የዳንነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ 
በአንጻሩ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖችን ስመለከት ጉራማይሌ፣ አስቂኝና አሳዛኝ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ፡፡ በእግዚአብሄር እናምናለን፤ ቃሉንም እናሰራጫለን ቢሉም በጣም መሠረታዊ የሆኑትን የእውነተኛ ክርስትና ጉዳዮች እንኳን በትክክል እንደማያውቁ በማየቴ አዘኛለሁ፤ ተስፋም ቆርጫለሁ፡፡
በቅርቡ አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤተ ተማሪዎቻችን መሠረታዊ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ላይ ደካማ በመሆናቸው ብዙዎች ሲጨነቁ ነበር፡፡ በእርግጥ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ችላ ወደ ማለቱ የሚያዘነብሉ ተማሪዎች በትምህርቶቻቸው ጥሩ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ የኮሌጅ ተማሪዎችን በሚፈልጉዋቸው ሙያዊ ትምህርቶች ለማሰልጠንና ለሥራ ገበታቸው ለማዘጋጀት ይበልጥ ወደ ተራቀቀው ዕውቀት ከማለፋቸው በፊት የመጀመሪያ ትምህርቶችን መሠረታዊ ነገሮች በትክክል እንዲያውቁ ዩኒቨርሲቲዎች ማረጋገጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ሙከራዎች ሁልጊዜም የሚሳኩ እንደማይመስሉ ግልጥ ነው፡፡
ይህንን ታሪክ ያቀረብሁት የዚህን ዓለም ዕውቀት መረዳት የሚቻለው መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች በትክክል በመረዳት እንደሆነ ሁሉ ትክክለኛ እምነት ሳይኖር በእግዚአብሄር ማመንም በነውጥ እንደሚናጥ ለማብራራት ነው፡፡ እውነተኛው እምነት በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የሚያምነው እምነት ነው፡፡ ከዚህ መሠረታዊ እምነት ውጭ ያለው እያንዳንዱ ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ሰዎች በመጀመሪያ በኢየሱስ እንደሚያምኑ በመናገር ቢደሰቱና ለእግዚአብሄር ቀናዒ ቢሆኑም ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ ወዲያው የራሳቸው ጽድቅ ያልቃል፡፡ ደስታቸውም ይተናል፡፡ ጉልበታቸውም ሁሉ ተሟጦ ያልቃል፡፡ መጨረሻቸውም አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ካሉት ሐጢያቶቻቸው የተነሳ በእግዚአብሄር ላይ ያላቸውን እምነት ማውገዝ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ክስተት የተከሰተው መሠረታዊ የሆነው የክርስትና እምነት ዕውቀት ስለጎደላቸው ነው፡፡
በመካከላችሁ አካል ጉዳተኛ የሆነ ሰው አለን? እግሮቻቸው ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ደረጃዎችን በሚወጡበት ጊዜ እጅግ ይቸገራሉ፡፡ ደረጃዎችን ለመውጣት በሚፍጨረጨሩበት ጊዜ አንድ ሰው ቢረዳቸውና ቢያግዛቸው ጥሩና የሚያስመሰግን ተግባር አይደለምን? ነገር ግን ሁሉም ባይሆኑም ‹‹ተወኝ፤ ራሴ አደርገዋለሁ›› የሚሉ አንዳንድ ቁጡ አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ በጥቅሉ አካል ጉዳተኞች ትልቅ የሆነ የራስ ክብር አላቸው፡፡ አንዳንዴም ግትሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ከሚሰማቸው የበታችነት፣ የሽንፈትና የጎዶሎነት ስሜት የተነሳ ልቦቻቸው ሊደነድኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቻቸው የሌሎችን ደግነት በትክክለኛ መንገድ ከማየት ይልቅ ዋናውን ዓላማ አጣመው የሚመለከቱት ለዚህ ነው፡፡
በአካል ጉዳተኝነታቸው ምክንያት አንዳች የበታችነት ስሜት ሊሰማቸው አያስፈልግም፡፡ በጉድለቶቻቸውም ጥሩ ስሜት ላይሰማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ጉድለቶች ይዞ መኖር ሐጢያት አይደለም፡፡ ሆኖም ከጉድለቶቻቸው የሚመነጩትን ሁሉንም ዓይነት የተዛቡ አስተሳሰቦች በማስተናገድ እነዚህ መጥፎ ስሜቶች ስፍር ቁጥር ወደሌላቸው የበታችነት ስሜቶች እንዲያድጉ የሚፈቅዱ ከሆነ በመጨረሻ በትክክል በልባቸውም አካለ ጎዶሎዎች ሆነው ያርፉታል፡፡ አካል ጉዳተኛ ሰው ከሆናችሁ ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር ቢኖር ራሳችሁን በትክክል መረዳትና ዕርዳታ በሚያስፈልጋችሁ ጊዜ ዕርዳታን መሻት የምትችሉ ከሆናችሁ ደግሞ በራሳችሁ መሬት ላይ ጸንታችሁ መቆም ነው፡፡
የማላውቀው አንዳች ነገር በሚኖርበት ወይም አንዳች እገዛ ማግኘት በሚያስፈልገኝ ጊዜ ሁሉ ሌሎች እንዲያግዙኝ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ የሚጎደለኝ ነገር ስላለ የሌሎችን ዕርዳታ ከመጠየቅ በቀር የማደርው ነገር የለኝም፡፡ ስለዚህ ነገር የሚያውቅ ሌላ ሰው ሲራራልኝና ሲያግዘኝ ይህንን ሰው አመሰግነዋለሁ፡፡ በስጋችን ድካሞች ቢኖሩብንም ልቦቻችንን እንዲያሰናክሉ የምንፈቅድበት ምንም ምክንያት መኖር የለበትም፡፡ ስለዚህ ማድረግ የሚኖርብን ነገር ቢኖር ድካሞቻችንን ማወቅና እነዚህን ድካሞቻችንን ምሉዕ አድርጎ ይህንን ወንጌል በትጋት እንድናገለግል ባደረገን የሰማያዊው፣ የሐምራዊው፣ የቀዩ ማግና የጥሩው በፍታ ደህንነት ማለትም በጌታችን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማመን ነው፡፡ የምንኮራውና ጌታን የምናመሰግነው በዚህ የጌታችን ወንጌል ውስጥ ስላለን ነው፡፡ በእምነታችን አማካይነት በእግዚአብሄር የተሰጠውን የደህንነት ስጦታ ስለተቀበልን ማድረግ የሚኖርብን እርሱን ማመስገን ብቻ ነው፡፡ በዚህ የደህንነት ስጦታ ማረፍ፣ እርስ በርስ መዋደድና አንድ መሆን እንችላለን፡፡
ብዙዎቹ የዘመኑ ከርስቲያኖች እምነታቸው በሁሉም አቅጣጫዎች የሚናጠው በእምነታቸው መሠረታዊ ነገሮች ላይ ደካሞች ስለሆኑ ነው፡፡ ጌታችን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ እናንተንና እኔን አድኖናል፡፡ የደህንነትን ስጦታ ተቀብለን ምሉዓን የምንሆነው ይህንን በማወቅና በማመን ብቻ ነው፡፡ እኛ ከመጀመሪያውም ለሲዖል የታጨን ነበርን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ፍጹም የሆነውን ደህንነት በመስጠት ሙሉ በሙሉ ስላዳነን ፍጹም የሆንን የእርሱ ልጆች ሆነናል፡፡ በእምነታችን አስቀድመን የደህንነትን ስጦታ ስለተቀበልን የእግዚአብሄር ሕዝብ መሆናችንን በማመን ሕይወታችንን የምንኖርና በዚህ የእምነት ክልል ውስጥ የምንቆይ ከሆንን በጌታ ውስጥ ሆነን እምነታችንን በስኬት መኖር እንችላለን፡፡
በትክክል ዳግመኛ ከተወለድን በኋላ ወደ ልባችን ሁለት አዳዲስ ለውጦች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን ለውጦች ከዚህ በፊት አልተለማመዳችኋቸውም፡፡ ከዚህ በፊት ለሌሎች የነበረኝ ፍቅር በግብዝነት የተሞላ ነበር፡፡ በልቤ እየጠላኋቸው ያለ ልክ እንደምወዳቸው አስመስል ነበር፡፡ አሁን ግን ሌሎችን በትክክል ከልቤ እወዳቸዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ፍጹም የሆነውን የደህንነት ስጦታ ስለሰጠንና ይህም ወንጌል እጅግ ክቡር ስለሆነ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በዓይኖቼ ፊት ክቡርና ተወዳጅ መስለው ይታዩኛል፡፡ ላልወዳቸው ብሞክርም እነርሱን ከመውደድ በቀር የማደርገው ነገር የለም፡፡
ሁለተኛው ለውጥ ከቀድሞው በተቃራኒ ለሌሎች ስሜት መጠንቀቄ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ሰው እኔ የማልደግፈውን ነገር በሚያደረግበት ጊዜ ሁሉ ያ ሰው ማንም ይሁን ክፉኛ እወቅሰው ነበር፡፡ አሁን ግን የሰውን ድካሞች ሁሉ መመልከት እንደሚያስፈልገኝ፣ ከእነርሱ ጋር በሚኖረኝ ግንኙነትም ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን እንደሚገባኝና ከለላ ሲያስፈልጋቸው መከለል፣ መወቀስ ሲኖርባቸውም መውቀስ እንደሚያስፈልገኝ ሁሉንም በተገቢው መንገድ ማድረግ እንደሚኖርብኝ ወደ መረዳቱ ደርሻለሁ፡፡ ድካሞች ወይም ጉድለቶች ያሉባቸው ሰዎች ልቦቻቸው በቀላሉ ሊደነድኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ድካሞቻችንን ይበልጥ አውቃለሁ፡፡ እነርሱን በድብቅ መርዳት የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ፡፡ የእኔ ዕርዳታ እጅጉን እንደሚያስፈልጋቸው እያወቅሁም እንኳን ልረዳቸው የማይገባኝ ወቅትም አለ፡፡ እነዚህን ነገሮች ወደ ማወቁ የደረስሁት ሰዎች እንደዚህ ያሉ ደካማ ፍጡራን በመሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው ጊዜም በእምነቴ ጠንካራና ደፋር ነኝ፡፡
በጣም ደካማ ከመሆናቸው የተነሳ ሌሎችን መውቀስ የማይገባን ወቅት አለ፡፡ እንዲያው ዝም ብለን ከማለፍ ይልቅም አበክረን ልንወቅሳቸው የሚያስፈልገን ወቅትም ደግሞ አለ፡፡ ፍላጎቶቻቸውን ይበልጥ ማወቅ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው፡፡ በእምነት አንጻር ሲታይ ግን ለእነርሱ ያለን ፍቅር አስተማማኝ፣ ፍጹም፣ ትክክለኛና ጠንካራ ነው፡፡ ሁኔታዎቻቸውን ከስጋዊ አመለካከት አንጻር የምንመለከታቸው ከሆነ ማየት የምንችለው ነገር ቢኖር የሚያስጨንቁ ነገሮችን ብቻ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ በጣም ደካሞችና የማንበቃ ስለሆንን ስለ ደካማው ስጋችን መጨነቅ ከጀመርን ሳንጨነቅ ወይም በአሳብ ሳንናወጥ የሚያልፍ ቀን አይኖርም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በሰጠን ፍጹም እምነት ላይ ስንቆም ጭንቀቶቻችንና ስጋቶቻችን ሁሉ ይከስማሉ፡፡ ኢየሱስ እንደ እኛ ያለነውን ደካሞችና የረከስን ሰዎች በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩ በፍታው አድኖን በጎ ሥራዎቹን የምንሠራለት ዕቃዎች ስላደረገን ይህ የእምነት ማደፋፈሪያ ከማንኛውም ሌላ ነገር ይልቅ ጠንካሮች ሊያደርገን ይገባል፡፡ 
የልባችን መጽናናት የሚመጣው ጌታ ለልቦቻችን ከሰጠው ፍጹም የሆነ የደህንነት ስጦታ ነው፡፡ ከስጋዊ ትሩፋቶች የፈለቁ ለሌሎች ማጽናኛዎች ሁሉ አላፊዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችን በስጋዊ ቃላት ማጽናናት ልናጽናናቸው ብንፈልግም የስጋ መጽናናት ዋጋ የለውም ማለት አይደለም፡፡
ነገር ግን ግልጥ የሆነው ነገር እኛ ራሳችን ደካሞች በመሆናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሙሉ በሙሉ ያዳነን መሆኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ፣ እህቶቹ፣ ማርያምና ማርታ፣ እንደዚሁም ጎረቤቶቹ ሲያለቅሱ በተመለከተ ጊዜ እንደቃተተ ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ሰዎች በሐጢያቶቻቸው ምክንያት መሞታቸው ምን ያህል ልብን እንደሚሰብር ስለተመለከተ ራራላቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን በአብ ፈቃድ መሠረት ስለመጣ ‹‹እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ›› (ዮሐንስ 11፡25) በማለት በሐጢያቶቻችን ምክንያት ሊሞቱ የነበሩትን አዳናቸው፡፡ በመንፈስና በስጋም አጽናናን፡፡
እናንተና እኔም እንደዚሁ እነዚህ ሁለቱ የመንፈስና የስጋ ክፍሎች አሉን፡፡ ስለዚህ በስጋ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ በስጋም በመንፈስም መጽናናት እንፈልጋለን፡፡ ይህ የሰማያዊው፣ የሐምራዊው፣ የቀዩ ማግና የጥሩው በፍታ እምነት እንዲኖረንም እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሄር በሰጠን የደህንነት ስጦታ አምነን መደሰትን በማወቅ፣ ይህንን የደህንነት ስጦታ በመጠበቅና ይህንን ስጦታ የተቀበልን ሰዎች መሆናችንን ለራሳችን በማስታወስ ልቦቻችን በእርግጥም በክርስቶስ ሊደሰቱ ይችላሉ፡ ለእግዚአብሄር ክብርን የምንሰጠው በዚህ መንገድ ነው፡፡
እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን ልክ እንደ መገናኛው ድንኳን ምሰሶዎች በእምነት ተክሎናል፡፡ በእምነት እንደንኖርም ጠይቆናል፡፡ ስለዚህ የስጋ ጉደለቶቻችን በየቀኑ ቢበዙም መኮነን የሚገባን መሆናችንን በመገንዘብ የእግዚአብሄር ማዳን ምን ያህል ክቡር እንደሆነ በልባችን ጥልቀት ውስጥ ይሰማናል፡፡ እናንተም ደግሞ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ አጥር የተገለጠውን ይህንን የደህንነት እውነት ወደ መረዳቱ መምጣት ትችላላችሁ፡፡
አሁን በምሥራቁ ወገን ያለውን የመገናኛውን ድንኳን አደባባይ በር ከፍታችሁ መግባት ትችላላችሁ፡፡ ይህንን የመገናኛውን ድንኳን በር ከፍታችሁ ስትገቡ መጀመሪያ የምታዩት አንድ ነገር አለ፡፡ ያ ምን ሊሆን ይችላል? ከሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ በቀር ሌላ ነገር አይደለም፡፡
የሚቃጠለውን መሥዋዕት መሠውያ በእምነት ስታልፉት የእነርሱን የመታጠቢያ ሰን ታገኛላችሁ፡፡ ይህንን የመታጠቢያ ሰን ስታልፉ በመጨረሻ የእግዚአብሄር ቤት ወደሆነው ወደ ራሱ ወደ መገናኛው ድንኳን ትገባላችሁ፡፡ ይህንን በእምነት ስትመለከቱት እነዚህ ነገሮች ሁሉ በቀላሉ የተከናወኑ ናቸው፡፡ የመገናኛው ድንኳን ቃል በመጀመሪያ በጣም ግራ የሚያጋባ መስሎ ቢታይም እናንተና እኔ ልናስተውለው በእርግጥም በጣም ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የእምነት መሠረታችን ጠንካራ ስለሆነ አስቀድመን በያዝነው ትክክለኛ የእምነት መርህ ውስጥ ሆነን እንመለከተዋለን፡፡ የእግዚአብሄር ደህንነት በዋጋ የማይተመን ስለሆነ ማንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ስርዓት አማካይነት ያስተውለው ዘንድ ቀላል አድርጎለታል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው ይህንን የመገናኛውን ድንኳን ቃል በራሱ አስተሳሰቦች በተሳሳተ መንገድ እንዳይተረጉመው ለመከላከል ሲል እግዚአብሄር ገና ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች ዓይኖች እንዳያዩት አድርጓል፡፡ ስለዚህ የነገረ መለኮት ምሁራኖችም እንኳን ትክክለኛው መሠረታዊ እምነት ከሌላቸው የመገናኛው ድንኳን አደባባይ በር ለምን ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ እንደተሠራ ትክክለኛውን መንፈሳዊ ትርጉም መቼም ቢሆን መናገር አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር ይህንን እውነት እንደ እነዚህ ካሉት ዋሾዎች ሰውሮታልና፡፡
ሰማያዊው ማግ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ የተቀበለውን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ በእጆች መጫን በተቀበለው ጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በራሱ ላይ ወሰደ፡፡ ቀዩ ማግ ኢየሱስ ለሐጢያቶቻችን ሁሉ በመስቀል ላይ እስከ ሞት ድረስ የደማበትን መሥዋዕትነት ያመለክታል፡፡ ሐምራዊው ማግ ኢየሱስ ራሱ አምላክ እንደሆነ ይገልጣል፡፡ ጥሩው በፍታ አምላክ የሆነው እርሱ ራሱ ለእኛ ለሰው ዘሮች በሙሉ ቃል የገባበት የደህንነት ቃል ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎች እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር የገለጠውን እውነት ልክ እንደዚህ በትክክል ሊናገሩት አይችሉም፡፡
እግዚአብሄር ከሰው ዘር ጅማሬ ማለትም ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ ለባሮቹ ሁሉ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፡- ‹‹እናንተን ለማዳን በውሃ፣ በደምና በመንፈስ አማካይነት ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በእርግጥም አድናችኋለሁ፡፡›› ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቃል መሠረት ወደዚህ ምድር መጥቶ ተጠመቀ፡፡ ደሙንም አፍስሶ ሞተ፡፡ ከሙታንም ተነሳ፡፡ በዚህም አዳነን፡፡ ጥሩው በፍታ የእግዚአብሄር ቃል ተስፋ ነው፡፡ የቃሉም ፍጻሜ ደግሞ ነው፡፡ ሰማያዊው፣ ሐምራዊውና ቀዩ ማግ ስለ ኢየሱስ ጥምቀት፣ እርሱ አምላካችን ስለመሆኑና የዓለምን ሐጢያቶች በመቀበል የሐጢያት ኩነኔያችንን ሁሉ ተሸክሞ ደሙን ያፈሰሰልን ስለመሆኑ ይነግሩናል፡፡ ኢየሱስ ዳግመኛ ከሙታን በመነሳት እንዳዳነንም ይነግሩናል፡፡ ይህ የሰማያዊው፣ የሐምራዊውና የቀዩ ማጎች እውነት ዘላለማዊ የደህንነት እውነት ስለሆነ አፈንጋጭ አመለካከት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡
እግዚአብሄር ለእናንተና ለእኔ ይህንን የደህንነት ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ የምሰሶዎቹ ጫፎች በብር ዘንጎች ተለብጠው ነበር፡፡ እኛ የደህንነትን ስጦታ ከእግዚአብሄር የተቀበልን ሰዎች መሆናችንን ሁልጊዜም ማስታወስ አለብን፡፡ ጻድቃን ሐጢያት አልባና የእግዚአብሄር ሕዝብ የሆንነው ይህንን ስጦታ በመቀበል ስለሆነ ከዚህ ስጦታ በስተቀር ፈጽሞ የምንኮራበት ምንም ነገር የለንም፡፡ የምንኮራበት አንድ ነገር ቢኖር ይህ የሰማያዊው፣ የሐምራዊው፣ የቀዩ ማግና የጥሩው በፍታ እምነት ያለን የእግዚአብሄር ልጆች መሆናችን ብቻ ነው፡፡ ይህ መሆን የቻለው ኢየሱስ ክርስቶስ በብቸኛው መልካምና ክቡር የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሐጢያቶቻችን ስላዳነን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ምሉዓን የሆንነው እግዚአብሄር የደህንነትን ስጦታ ስለሰጠን ብቻ መሆኑን በማመን በዚህ እምነት መኖር አለብን፡፡ የራሱ የእግዚአብሄር ሕዝብ የሆንነውም በዚህ ስጦታ አማካይነት ነው፡፡ 
ይህንን ስለ መገናኛው ድንኳን የሚናገረውን ቃል ለማሰራጨት እጅግ አመቺው ጊዜ አሁን እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ብዙ ሰዎች ፈጽሞ ስሜት በማይሰጥ ከመከራ በፊት ስለሚሆን ንጥቀት በሚናገረው ጽንሰ አሳብ ግራ የተጋቡበት ወቅት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን የዮሐንስ ራዕይን መጽሐፍ ቃል በመስበክ ብዙዎች የተሳሳተ እምነታቸውን ጥለው እውነተኛውን እምነት ይይዙ ዘንድ የሚችሉበትን አመቺ ጊዜ አዘጋጀልን፡፡ በዚህ ዘመንም እንደዚሁ የሰማያዊውን፣ የሐምራዊውን፣ የቀዩን ማግና የጥሩውን በፍታ እምነት መስበክ ያለብን መሆኑ በጣም ተገቢ ነው፡፡
እኛ የደህንነትን ስጦታ ከእግዚአብሄር ስለተቀበልን ይህንን አስተማማኝ የደህንነት ስጦታ ማሰራጨቱ ከፍተኛ ደስታን የሚሰጥ ተግባር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ምስጋናዬን ሁሉ ለእግዚአብሄር አቀርባለሁ፡፡