‹‹ ዮሐንስ 8፡31-36 ››
‹‹ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፡- እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው፡፡ እነርሱም መልሰው፡- የአብርሃም ዘር ነን፤ ለአንድም እንኳ ከቶ ባርያዎች አልሆንንም፡፡ አንተ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ አሉት፡፡ ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሐጢአት የሚያደርግ ሁሉ የሐጢአት ባርያ ነው፡፡ ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ፡፡››
ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ውብ በሆነው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ማመንና በእምነት መኖር አለብን፡፡
እውነቱን ታውቃላችሁን? ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹እኔ እውነት ነኝ፡፡›› (ዮሐንስ 14፡6) ስለዚህ ኢየሱስን ማወቅ ማለት እውነትን ማወቅ ማለት ነው፡፡ ውብ በሆነው ወንጌል ለማመናችሁ ምስጋና ይሁንና መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ ይኖራልን? የኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ውብ የሆነው ወንጌል መገለጫ መሆኑን ማወቅና በእርሱም ማመን አለባችሁ፡፡
ዛሬ ሰዎች ‹ዳግም መወለድ› የሚለውን አገላለጽ አዘውትረው ይጠቀሙበታል፡፡ ‹‹ሰዎች ዳግም መወለድ አለባቸው፡፡ ፖለቲካው ዳግም መወለድ አለበት፡፡ ሐይማኖት ዳግም መወለድ ይኖርበታል፡፡›› ቃለ-ሐረጉን የሚጠቀሙበት ‹ከመሻሻል› ጋር አዛምደው ነው፡፡ ዳግም መወለድ ማለት የሥጋን ተፈጥሮ ማሻሻል ማለት አይደለም፡፡ ዳግም መወለድ ማለት ውብ የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማድመጥና በማመን መንፈስ ቅዱስን መቀበል ማለት ነው፡፡
ዳግም እንድንወለድ የሚፈቅድልን የእውነት ቃል ምንድነው?
ሰው ሙሉ አይደለም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ዳግም ለመወለድ መንፈስ ቅዱስን መቀበል አለበት፡፡ በኢየሱስ የሚያምኑ ነገር ግን ዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ብዙ ሰዎችን እናያለን፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁዶች አለቃ ነበር፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 3 ላይ የተጠቀሰው ኒቆዲሞስ በእግዚአብሄር የተሰጠውን ሕግ ለመጠበቅ የሞከረ የይሁዲ ሐይማኖት አለቃ ነበር፡፡ ነገር ግን ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሳያውቅ የሕዝቡ ሐይማኖት መሪ ሆኖ ይሰራ ነበር፡፡
ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ቅዱስ ወንጌል ማመንና በእምነት መኖር አለብን፡፡ ሰው ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል የሚችለው በውሃውና በመንፈስ ቅዱስ ውብ ወንጌል የእውነት ቃሎች ወደ ማመን ሲመጣ ነው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ‹‹ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?›› (ዮሐንስ 3፡12)
ውብ የሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚከተለው ነው፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም ተወለደ፡፡ በ30 አመቱም በዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ከሦስት አመታቶች በኋላም በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ ከዚያም ተነሳ፡፡ እኛንም ከሐጢያቶቻችን ሁሉ አዳነን፡፡ ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁንና ዳግመኛ ከሙታን መነሳቱን ለሚያምኑትም አዳኝ ሆነ፡፡ በዚህ ውብ ወንጌል ላመኑትም የሐጢያቶቻቸውን ስርየትና ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ሰጠ፡፡
አሁንም ድረስ በልቦቻቸው ውስጥ ሐጢያት ያሉባቸው በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ በማመን የሐጢያቶቻቸውን ይቅርታ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያት መስራቱን ማቆም አይችልም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ በመቀበል መዳን አለበት፡፡ ኢየሱስ ውብ በሆነው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አነጻ፡፡ ሐጢያተኞች ሁሉ ውብ የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማድመጥና በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ይባረካሉ፡፡
‹‹ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል፡፡›› (ዮሐንስ 3፡14) በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ሕዝብ ሐጢያቶችን ቢሰሩ፣ በምድረ በዳ በእባቦች ቢነደፉና እየሞቱ የነበረ ቢሆንም ብዙዎቹ በአላማ ላይ የተሰቀለውን የናስ እባብ በማየት በሕይወት ኖሩ፡፡
ልክ እንደዚሁ እኛም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ አግኝተናል፡፡ ኢየሱስ ውብ በሆነው ወንጌል ለሚያምኑት ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ሰጠ፡፡ ሰይጣን ውብ የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል እንዳናውቅ እንቅፋት ሊሆንና የእውነትን መንፈስ እንዳንቀበል ሊከላከል ይሞክራል፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀትና በደሙ ወንጌል ላይ ባለን እምነት በሐጢያቶች ይቅርታና በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ ባረከን፡፡
በዚህ ውብ ወንጌል ብታምኑ ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል ትችላላችሁ፡፡ ይህንን ውብ ወንጌል በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛ ወንጌል አድርጋቸው ትቀበሉታላችሁን? በዚህ ውብ ወንጌል በማመን ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ መቀበል እንደምትችሉ ታምናላችሁን?
ጌታ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የሚያድነንን እውነት እንድናውቅ ነገረን፡፡ ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፡፡›› (ዮሐንስ 8፡32) የሚያድነንንና በዘለቄታዊው መንፈስ ቅዱስ የሚባርከንን ውብ ወንጌል እውነት ታውቁታላችሁን? ይህንን እውነት ብትቀበሉ በእርግጥም ዘለቄታዊውን መንፈስ ቅዱስ ትቀበላላችሁ፡፡