Search

خطبے

ርዕስ 9፡ ሮሜ (በሮሜ መጽሐፍ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[Chapter 4-1] የሮሜ መግቢያ ምዕራፍ 4

ጳውሎስ በሮሜ 4፡6-8 ላይ በእግዚአብሄር ፊት ብሩካን ስለሆኑ ሰዎች ይናገራል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት በውኑ የተባረከ ሰው የዓመፃ ምግባሮቹ ይቅር የተባሉለትና ሐጢያቶቹ የተከደኑለት ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› (ሮሜ 4፡8)
 
ከዚያም ጳውሎስ አብርሃም የተባረከ ሰው ስለመሆኑ ያስተዋውቃል፡፡ ጳውሎስ አብርሃምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውሰጥ የተጠቀሰ አርአያ ሰው አድርጎ በመጠቀም እውነተኛና የተባረከ እምነት ምን እንደሆነ ያብራራል፡፡ አብርሃም በሥራዎቹ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ የሚመካበት አንዳች ነገር ይኖረው ነበር፡፡ እውነቱ ግን እንደዚያ አለመሆኑ ነው፡፡ እርሱ ያገኘው የእግዚአብሄር ጽድቅ በእግዚአብሄር ቃሎች በማመን ብቻ የተገኘ ነበር፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሊጸድቅበትና ሊባረክበት የሚችልበት እምነት ልክ እንደ አብርሃም በእግዚአብሄር ቃሎች የሚያምን ጥሬ እምነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ላይ ሰው በእርሱ ቃሎች በማመን እንዴት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሊያገኝ እንደሚችል ይናገራል፡፡
 
በምድር ላይ እየኖረ ፈጽሞ ሐጢያትን የማይሰራ ሰው የለም፡፡ ከዚህም በላይ እኛ ሰዎች ሰማይን ከሚሸፍነው ደመና በላይ ብዙ ሐጢያት እንሰራለን፡፡ በኢሳይያስ ውስጥ ሐጢያቶቻችንና መተላለፎቻችን እንደ ደመና መሆናቸው ተጽፎዋል፡፡ (ኢሳይያስ 44፡22) ስለዚህ በሰዎች ሁሉ መካከል በኢየሱስ ጽድቅ ሳያምን ከእግዚአብሄር ጽድቅ ማምለጥ የሚችል ሰው የለም፡፡
 
ኢየሱስ የተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ፈጽሞዋል፡፡ ሁሉም ሐጢያትን ይሰራል፡፡ ዳግም የተወለዱና ዳግም ያልተወለዱ በሥጋቸው ሐጢያቶችን ይሰራሉ፡፡ ከዚህም በላይ የማናውቃቸውን ሐጢያቶች ሳይቀር እንሰራለን፡፡ ስለዚህ ለእነዚያ ሐጢያቶች ሊፈረድብን የታጨን ሰዎች ነን፡፡
 
ሰው ቅንጣት ታህል ሐጢያት ካለበት በእግዚአብሄር ፍትህ ፊት መሞት እንደሚኖርበት ማወቅ አለበት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሐጢያት ደመወዝ ሞት ነው ተብሎዋል፡፡ (ሮሜ 6፡23) ስለዚህ የእግዚአብሄርን ሕግ ማስተዋልና ማመን ይኖርብናል፡፡ በአእምሮዋችንና በምግባሮቻችን ለሰራናቸው ሐጢያቶች ዋጋ መክፈል አለብን፡፡ የሐጢያት ችግር የሚፈታው የሐጢያትን ዋጋ በሙሉ ስንከፍል ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ምንም ያህል ጠንክረን ብንሞክርም ገናም የሐጢያትን ዋጋ ካልከፈልን የሐጢያት ፍርድ ጉዳይ አይጠናቀቅም፡፡ እኛ ማወቅ የሚገባን ነገር ቢኖር በኢየሱስ የሚያምን ነገር ግን ሐጢያት ያለበት ሰው በራሱ ሐጢያቶች የሚፈረድበት መሆኑን ነው፡፡
 
የምንኖረው በሁሉም አይነት በትንሽና በትልቅ፣ በሚታወቅና በማይታወቅ፣ በውዴታና በግዴታ በሚሰሩ ሐጢያቶች በተጥለቀለቀው በዚህ ዓለም ላይ ነው፡፡ ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› በሚለው በእግዚአብሄር ሕግ መሰረት በሐጢያታችን ምክንያት መኮነን የሚገባን ሰዎች መሆናችንን ከማመን በቀር ሌላ ልናደርግ የምንችለው ነገር የለም፡፡
 
ሰው ሐጢያቱ እንዲከደንለት የሚፈልግ ከሆነ በውሃው፣ በደሙና በመንፈስ ቅዱስ በመጣው በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን የሐጢያት ስርየትን ማግኘት አለበት፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን የሐጢያት ስርየትን ያገኘ ሰው እግዚአብሄር በጥምቀትና በደም ሐጢያቶችን ሁሉ ስለወሰደ ሁልጊዜም የምስጋና መስዋዕትን መሰዋት ከመቻሉም በላይ ተገቢ ብቃቶችም አሉት፡፡ ጌታችን በጥምቀቱ፣ በደሙና በትንሳኤው የእኔን እንደ ደመና ያሉ ሐጢያቶች ጨምሮ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ አስቀድሞ ስለወሰደ የዘላለም ሕይወትን ለሰጠን ጌታ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ በመጠመቅና በመስቀል ላይ በመሞት በዮርዳኖስ ወንዝ ሐጢያቶችን ሁሉ ባይወስድ ኖሮ ሲዖል በመውረድ የሞትን ዋጋ በከፈልን ነበር፡፡ እርሱ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ ፈጽሞ ባይደመስስ ኖሮ እንዴት ልናመሰግነው እንችላለን? ልቦቻችን በሐጢያት የተሞሉ ቢሆኑ ኖሮ በቅዱሱና በከበረው አምላካችን ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሄርን ስም ማመስገን ይቻለን ነበር? በልባችን ውስጥ ሐጢያት እያለብን ‹‹እርሱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ይቅር ብሎናል!›› በማለት ለጽድቁ የምስጋናን መስዋዕት በእርግጥ ማቅረብ እንችላለን? አንችልም፡፡
 
አሁን ግን ስለ ጽድቁ ልናመሰግነው እንችላለን፡፡ ይህ ሁሉ የተቻለው በለበስነው የእግዚአብሄር የጽድቅ ስጦታ በማመናችን ነው፡፡
 
 

ጳውሎስ እግዚአብሄር ባደረገው ነገር በማመን የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንዳገኘን ተናግሮዋል፡፡

 
‹‹እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ዘንድ አይደለም፡፡ መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሄርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ ለሚሰራ ደመወዝ እንደ እዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡ ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› (ሮሜ 4፡1-5)
 
እዚህ ላይ አብርሃምን እንደ ምሳሌ በመውሰድ እንዴት ጽድቅ እንደሚገኝ ያብራራል፡፡ ሰው ለሰራው ሥራ ደመወዝ መቀበሉ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳች ጥሩ ነገር ሳናደርግ ወይም በእግዚአብሄር ፊት ፍጹም የሆነ ሕይወት ሳንኖር ዳግም በመወለድ መጽደቃችን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሄር ስጦታ እንጂ የሥራዎቻችን ደመወዝ አይደለም፡፡
 
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡›› ይህ ሐጢያተኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስዋዕታዊ ደሙ እንዴት ከሐጢያት እንደሚድን የሚናገር ነው፡፡ ይህ ደህንነት በእግዚአብሄር ጽድቅ ለሚያምኑ ሁሉ የተባረከ የሐጢያት ስርየት ስጦታ ነው፡፡
 
የሐጢያተኛው ደህንነት በእግዚአብሄር ጽድቅ የተሰጠ ፍጹም ስጦታ ነው፡፡ ሐጢያተኛ ሆኖ የተወለደ ሰው ሐጢያት ከመስራት በቀር ሌላ ምርጫ የለውም፡፡ ያለ ጥርጥር ሐጢያተኛ መሆኑን ለእግዚአብሄር ከመናዘዝ በቀር ሌላ ምርጫ የለውም፡፡ የዚህ ሐጢያተኛ ሐጢያቶች አንዳንድ የገነኑ የክርስትና ትምህርቶችን በማመን በሚያደርጋቸው ትጋት የተሞላባቸው የንስሐ ጸሎቶች ሊወገዱ አይችሉም፡፡
 
ሐጢያተኛ በእግዚአብሄር ፊት በራሱ ጽድቅ የሚመካበት ምንም ነገር የለውም፡፡ ‹‹እኛ ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፡፡ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፡፡›› (ኢሳይያስ 64፡6) ስለዚህ ሐጢያተኛ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በፈጸመው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባደረገው የስርየት ሞት በተፈጸመው የእግዚአብሄር ጽድቅ ከማመን በቀር ሌላ ምርጫ የለውም፡፡ ሐጢያተኛ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት ማድረግ የሚችለው ሌላ ተጨማሪ ነገር የለም፡፡ የሐጢያት ስርየት ማግኘት የምትችሉት በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ብቻ ነው፡፡
 
ሐጢያተኞች ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው የማስተሰርያ ደም አማካይነት ጽድቁን ማግኘት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሐጢያተኛው ከሐጢያቱ መዳንን እንዲያገኝ የሚያስችለው በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመኑ ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሄር የጽድቅ ስጦታ ነው፡፡
 
 

ሐዋርያው ጳውሎስ ሐጢያተኞች እንዴት እንደሚድኑ ተናግሮዋል፡፡

 
ጳውሎስ አብርሃምን እንደ አይነተኛ ምሳሌ በመጠቀም ይህንን ያብራራል፡፡ ‹‹ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቆጠርለትም፡፡›› ሐዋርያው ጳውሎስ ሰው የሆነ አይነት የሕግ ሥራ በመስራት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት እንደማይችል መናገሩ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ መንፈሳዊ ግርዘትን በሚናገሩት የጽድቅ ቃሎች በማመን ነው፡፡
 
የእግዚአብሄር ጽድቅ በሰዎች ጥረቶች ወይም ምግባሮች ሊገኝ የማይችል እውነት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ እንደሚከተለው ነው፡፡ እናንተና እኔ ወደ ዘላለም ጥፋት ለመግባት የታጨን ሰዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን አዳኛችን ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ በመጠመቅ ሐጢያቶችን ሁሉ ወሰደ፡፡ ከዚያም የሐጢያቶችን ዋጋ ሁሉ በደሙ በከፈለበት መስቀል ላይ ሐጢያቶችን ሁሉ በጀርባው ተሸከመ፡፡ በዚህም ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሁሉ ፈጸመ፡፡ የእርሱ የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ሐጢያተኞችን ከዘላለም ሞት ያዳነውን የእግዚአብሄርን ጽድቅ ፈጸሙ፡፡
 
 
በእግዚአብሄር ቃሎች የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት ይችላሉ፡፡
 
ቁጥር 5 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢያተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡››  
 
ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ‹‹ሐጢያተኛን›› እንደ ምሳሌ በመጠቀም ወደ እግዚአብሄር ጽድቅ የሚያደርሰውን መንገድ ያብራራል፡፡ ‹‹ሐጢያተኞች›› እግዚአብሄርን የማይፈሩ ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ አሳፋሪ ሐጢያቶችን የሰሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎች ሁሉ ‹‹የሐጢያት ክምር›› ናቸው ብለው የሚናገሩት የእግዚአብሄር ቃሎች በእርግጥም ትክክል ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ የሰው ዘር እውነተኛው ተፈጥሮ የእግዚአብሄርን አስፈሪ ፍርድ እስኪቀበል ድረስ ሐጢያት ከመስራት በቀር ሌላ ምርጫ የሌለው መሆኑም እንደዚሁ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እኛን ሐጢያተኞችን ሐጢያት አልባ ናችሁ ብሎ ከጠራንና እምነታችንንም ጽድቅ አድርጎ ከቆጠረልን ይህንን ማድረግ የቻለው ከእግዚአብሄር ጽድቅ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
 
እግዚአብሄር ለእኛ ለሐጢያተኞቹ ተናገረን፡፡ ጌታ የዓለምን ሐጢያቶች በሙሉ ለመውሰድ የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ሊቀ ካህን በሆነው በአጥማቂው ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ‹‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› የሚሉትን ቃሎቹን ለመፈጸምም በመስቀል ላይ ባፈሰሰው የስርየት ደሙ የሐጢያቶችን ዋጋ መክፈል ነበረበት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበለው ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ የሐጢያቶቻችንን ዋጋ ሁሉ በጽድቁ እንደከፈለ ታምናላችሁን? እግዚአብሄር በእርሱ ጽድቅ የሚያምኑትን ሰዎች እምነት ጽድቅ አድርጎ ቆጥሮላቸዋል፡፡ ይህ የከረረ አባባል ሳይሆን ቀና ከሆነው የእግዚአብሄር ጽድቅ የፈለቀ እውነት ነው፡፡
 
ስለዚህ እግዚአብሄር አብ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምነውን ሰው ‹‹በትክክል አንተ ሕዝቤ ነህ፡፡ በጽድቄ ታምናለህ፡፡ አሁን አንተ የእኔ ልጅ ነህ፡፡ አንተ ሐጢያት አልባ ነህ፡፡ ለምን? በልጄ ጥምቀትና ደም ሐጢያቶችህን ሁሉ በመውሰድ ሐጢያት አልባ አድርጌሃለሁና! እርሱ ‹የሐጢአት ደመወዝ ሞት ነው› በሚሉት ቃሎች መሰረት ደሙን በማፍሰስ የሐጢያቶችን ዋጋም እንዲሁ ከፍሎዋል፡፡ ዳግመኛም ከሙታን ተነሳልህ፡፡ ስለዚህ እርሱ አዳኝህና አምላክህ ነው፡፡ በዚህ ታምናለህን?›› ይለዋል፡፡
 
‹‹አዎ አምናለሁ፡፡›› ያን ጊዜ እግዚአብሄር እንዲህ በማለት ይቀጥላል፡፡ ‹‹በልጄ የጽድቅ ምግባሮች የተጠናቀቀውን ጽድቄን ሰጥቼሃለሁ፡፡ አሁን አንተ ልጄ ሆነሃል፡፡ በውሃውና በልጄ ደም በጉዲፈቻ ተቀብዬሃለሁ፡፡››
 
ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች ሁሉ -- አስቀድሞ የሰራናቸውን ሐጢያቶችና ወደፊት የምንሰራቸውን ሐጢያቶች -- ዮሐንስ በሰጠው ጥምቀት በአንድ ጊዜ ወስዶዋቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ እግዚአብሄር በአምላክ ጽድቅ የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ በጽድቁ ሸፍኖ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ አድኖዋቸዋል፡፡ ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጆች ናችሁና፡፡ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስ ለብሳችኋልና፡፡›. (ገላትያ 3፡26-27) አሁን ጥያቄው በውኑ የእግዚአብሄርን ቃል በልባችን እናምነዋለን ወይስ አናምነውም የሚለው ነው፡፡ ብናምን እንጸድቃለን፡፡ ባናምን ግን የእግዚአብሄርን ጽድቅ እናጣለን፡፡
     
 
በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኛ የሆነ እንኳን…
 
በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኛ ለሆኑ ሰዎች እንኳን ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች በአንድ ጊዜ እንደወሰደ ቢያምኑ የእርሱ ጽድቅ የእነርሱ ሊሆን እንደሚችል ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ጽድቁን ለእያንዳንዱ አማኝ በትክክል ሰጥቶዋል፡፡ በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምን ማንኛውም ሰው ከዚህ ዓለም ሐጢያቶች ሁሉ ይድናል፡፡ እግዚአብሄር አባታችን በእርሱ ጽድቅ ለሚያምኑ ምዕመናኖች የእርሱ ልጆች እንደሆኑ ነግሮዋቸዋል፡፡ ‹‹አዎ አሁን ሐጢያት አልባ ናችሁ፡፡ ልጄ ኢየሱስ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ አድኖዋችኋል፡፡ ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ድናችኋል፡፡››
 
እኛ ሐጢያተኞች ብንሆንም እግዚአብሄር እኛ ጻድቃን መሆናችንን ለማረጋገጥ ጽድቁን በእኛ ላይ አትሞታል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ዘላለማዊ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በእርግጥም ለሰው ዘር ሁሉ ትክክለኛውን ሥራ ሰርቶዋል፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ከዚህ ዓለም ሐጢያቶች ሁሉ የዳኑት በእግዚአብሄር ጽድቅ ነው፡፡ እግዚአብሄር በእርሱ ጽድቅ ላይ ያላቸውን እምነት በመመልከት ሐጢያተኞችን ሐጢያት አልባ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡ ‹‹ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› ምክንያቱም የእግዚአብሄርን ጽድቅ በእምነት አግኝቷልና፡፡
እግዚአብሄር ‹‹ጻድቃን ናችሁን?›› ብሎ ይጠይቀናል፡፡ እኛም በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያተኞች የመሆናችንን እውነታ እናምናለን፡፡ ይህንን እውነታ ስናምን ኢየሱስ ለሐጢያተኞች በመጠመቁ፣ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰሱና የዓለምን ሐጢያቶች የወሰደውም የእግዚአብሄር ጽድቅ እንጂ የእኛ ጥረቶች ባለመሆናቸው አመስጋኞች ነን፡፡ ነገር ግን እኛ ሕጉን በሚገባ መታዘዝ የምንችል ሰዎች ስለመሆናችን የምናስብ ከሆነ ፈጽሞ አመስጋኞች ልንሆን አንችልም፡፡ በእርሱም ጽድቅ አናምንም፡፡
 
‹‹ሐጢአተኛውን በሚያጸድቅ›› በእግዚአብሄር ጽድቅ የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንደ ስጦታ ይቀበላል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነትና ፍርድ ለሚያምኑ ሰዎች ስጦታ ሆኖ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ጽድቅ ለማያምኑ ሰዎች የእግዚአብሄር በረከትና ጸጋ ሁሉ ይቆለፍባቸዋል፡፡
 
ዳግም ለተወለደ ጻድቅ ሰውም ቢሆን በኢየሱስ የጸናው የእግዚአብሄር ጽድቅ በየቀኑ አስፈላጊ ነው፡፡ እኛም በእግዚአብሄር ጽድቅ የምናምን ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር በየቀኑ ሐጢያት ከመስራት የማንቆጠብ ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ ሐጢያቶችን ሁሉ የመውሰዱን አስደሳቹን የእግዚአብሄር ጽድቅ የምስራች በየቀኑ ለራሳችን ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡ አስደሳቹን የምስራች በምንሰማበት ጊዜ ሁሉ ነፍሳችን ይታደሳል፡፡ ልባችንንም በሚጎርፍ ጉልበት ያጠነክርልናል፡፡ አሁን ‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል›› የሚለውን ምንባብ ተረዳችሁትን? ይህ ጥቅስ በዚህ ዓለም ላይ ለሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚናገር ነው፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስ ሰው እንዴት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ማግኘት እንደሚችል በአብርሃም ምሳሌ በዝርዝር ይናገራል፡፡ ‹‹የሚሰራ›› ሰው ግን የእግዚአብሄርን ደህንነት ከማመስገን ይልቅ እግዚአብሄርን ይቃወማል ተብሎዋል፡፡ ‹‹የሚሰራ›› ሰው በእግዚአብሄር ጽድቅ ስለማያምን አያመሰግንም፡፡ ቁጥር 4 ጥሩ ሥራዎችን በመስራት ሰማይ መግባት የሚሞክር ሰው የእግዚአብሄር ጽድቅ እንደማያስፈልገው የሚናገር ነው፡፡
 
ለምን? በጎ ምግባሮችን በማድረግና በየቀኑ የንስሐ ጸሎቶችን በማነብነብ ሐጢያቶቹን ለማንጻት ስለሚሞክር የእግዚአብሄር ጽድቅ በእርሱ ዘንድ አይገኝም፡፡ እንደዚህ አይነት ሰው የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሚገባ መቀበል አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ሰናይ የሚመስሉ ምግባሮች በፈቃዱ አይተውምና፡፡ ነገር ግን እያለቀሰና እየጾመ የንስሐ ጸሎቶችን እየጸለየ የነፍሱን ደህንነት ለማግኘት ይሞክራል፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ የሚሰጠው ከልቡ በእርሱ የጽድቅ ቃሎች በማመን ብቻ ነው፡፡
           
 
ለሚሰራ ደመወዝ እንደ ጸጋ ነው!
 
‹‹ነገር ግን ለማይሰራ ሐጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል፡፡›› (ሮሜ 4፡5)
 
ወንድሞች ይህ ጥቅስ እግዚአብሄርን ከሚያውቅና ልክ እንደ አብርሃም በእግዚአብሄር ቃሎች ከሚያምን ሰው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እኛን ሐጢያተኞችን ባዳነው በደህንነት ጌታ እናምናለን፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሁለት አይነት ክርስቲያን ምዕመናኖች አሉ፡፡ በቁጥር 4 ላይ ‹‹የሚሰራ›› ሰው ተጠቅሶዋል፡፡ እንዲህ ያለ ሰው የእግዚአብሄርን ማዳን እንደ ዕዳ እንጂ እንደ ስጦታ አይቆጥረውም፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች በኢየሱስ ካመኑ በኋላ በእግዚአብሄር ፊት መታወቅ የሚፈልጉት በሰናይ ምግባሮቻቸው በመሆኑ የእግዚአብሄርን የደህንነት ጽድቅ ለመቀበል እምቢተኞች ናቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለመቀበል ከእናንተ የሚያስፈልገው መስዋዕት ምን አይነት ይመስላችኋል?
 
በጎ ምግባሮቻችሁን ይዛችሁ በእግዚአብሄር ፊት ብትቀርቡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ባለማግኘታችሁ ሐጢያተኛ ትሆናላችሁ፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች የሚደግፉት የቅድስና ትምህርት የእግዚአብሄርን የጽድቅ ስጦታ በመቃወም የእግዚአብሄር ጠላቶች አድርጎዋቸው ከመጠን በላይ ሰናይ ምግባሮችን እንዲያደርጉ ያደፋፈራቸው መሆኑን ታውቃላችሁን? መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ቀስ በቀስ የምናገኝ ስለመሆኑ አይናገርም፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ በሥራዎቻችን ማግኘት እንደምንችልም አይናገርም፡፡
 
‹‹የሰውን ሥራዎች›› የሚደግፉ የንስሐ ጸሎቶችን በማቅረብ ልትቀደሱ እንደምትችሉ ያስተምራሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያቶቻችሁን ቢያስወግድም ንጹህና ሰናይ ሕይወትን ብትኖሩ የበለጠ መጽደቅ ትችላላችሁ፤ እስክትሞቱ ድረስ በቅድስና ብትኖሩም ትድናላችሁ ይላሉ፡፡
 
ነገር ግን የእግዚአብሄር ጽድቅ ከሰው ምግባሮች ጋር አይጣጣምም፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚቃወሙ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ይወዳጃሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የጌታን ጽድቅ ስለማይቀበሉ በጌታ ፊት የሐጢያት ስርየትን ሊቀበሉ አይችሉም፡፡
 
ወንድሞች እኛ 100% ሐጢያተኞች ነበርን፡፡ ነገር ግን እውነታው ብዙ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት በተሳሳተ የእምነት ጎዳና ላይ እየተጓዙ መሆናቸው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ጻድቅ እንደሆኑ ስለሚያስቡ በእግዚአብሄር ጽድቅ አያምኑም፡፡ በራሳቸው መንገድ የንስሐ ጸሎቶችን በመጸለይ በየቀኑና ወደፊት ለሚሰሩዋቸው ሐጢያቶች ይቅርታን ማግኘት እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢያንስ የተወሰነ መጠን ያለው በጎነት በውስጣቸው ስላለ የእግዚአብሄርን ጽድቅ ሳይፈልጉና ሳያምኑበት በጎ ሥራዎቻቸውን ከፊት ያስቀድማሉ፡፡
 
ጻድቅ መሆን የሚችል ምን አይነት ሰው ነው? የንስሐ ጸሎቶችን በማቅረብ ያልተካኑ ሰዎች ጻድቅ መሆን ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የኑዛዜ ጸሎቶችን ማቅረብ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በተሳሳተ መንገድ እንደማትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ ‹‹የጻድቅ ሕይወት›› ጉዳይ ላይ በኋላ የምለው ይኖረኛል፡፡ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የሚቃወሙ ሰዎች የተወሰኑ ሰናይ ምግባሮችን ማድረግ፣ ጾም ጸሎቶችን ማድረግ ወይም የተቀደሰ ሕይወት መኖርን አብዝተው ያስባሉ፡፡
 
ነገር ግን በልባቸው የኢየሱስን የሐጢያት ስርየት በመቀበል ከሐጢያተኛ ሁኔታቸው መጽደቅ የሚችሉት በምግባሮቻቸው ብቁ እንዳልሆኑ የሚያውቁ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን ብቸኛው ነገር በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመንና በእኛ ጽድቅ ውስጥ ምንም የሚያስመካ ነገር እንደሌለ ማወቅ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ልናምነው የሚገባን ነገር ቢኖር ‹‹አምላካችን ሆይ! እንዲህ አይነት ሐጢያቶችን አድርገናል፡፡ እኛ እስክንሞት ድረስ ሐጢያትን በማድረግ የምንቀጥል ነን›› ማለት ነው፡፡ በቅንነት ልንናዘዘው የሚገባን ብቸኛው ነገር ይህ ነው፡፡ ልናደርገው የሚገባን ሌላው ነገር ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ጽድቁን የፈጸመ መሆኑን ነው፡፡
 
እያንዳንዱ ሐጢያተኛ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ከሐጢያቶቹ ሙሉ በሙሉ መዳን ይችላል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ላይ ባለን እምነት እንመካለን፡፡ ምክንያቱም እኛ በሐጢያት ውስጥ መጥፋት የነበረብን ሰዎች ከሐጢያት ሁሉ ድነናልና፡፡
          
 
በውኑ የተባረከ ሰው ማነው?
 
በእግዚአብሄር ፊት ብሩክ የሆነ ሰው ማነው? መጽሐፍ ቅዱስ የተባረከን ሰው እንደሚከተለው ይገልጠዋል፡- ‹‹አመጻቸው የተሰረየላቸው ሐጢአታቸውም የተከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡›› ሰው በእግዚአብሄር ፊት አንዳች በጎ ምግባሮችን ማድረግ ባይችል፣ አለመብቃቶችና ድካሞች ቢኖሩበት ወይም ሁሉንም ወይም የተወሰኑትን የእግዚአብሄር ሕግ ክፍሎች መጠበቅ ባይችል እግዚአብሄር በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ባስወገደው የእግዚአብሄር ጽድቅ ለሚያምኑ ምዕመናኖች የሐጢያት ስርየትን በረከት ሰጥቶዋል፡፡ የዚህ አይነት ሰዎች በእግዚአብሄር ጽድቅ ያምናሉ፡፡ በእግዚአብሄር ፊትም እጅግ የተባረኩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እጅግ ብዙ ቁጥር ካላቸው ሰዎች ውስጥ በፊቱ የተለየ በረከትን አግኝተዋልና፡፡ በእግዚአብሄር ጽደቅ በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ እንደተናገረም አምነናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ብሎ ቢናገርም በቃሉ ላይ የምንጨምረው አንዳች ነገር አለን? የምንጨምረው  ምንም ነገር የለም፡፡
 
በዚህ ዓለም ላይ ኢየሱስ አዳኛቸው እንደሆነ ቢናገሩም በበጎ ምግባሮቻቸው ደህንነትን ለማግኘት የሚሞክሩ ብዙ ሰዎች አሁንም አሉ፡፡
 
ኢየሱስ በዮሐንስ መጠመቁን በመስቀል ላይ ደሙን ማፍሰሱንና ከሞተ በኋላ መነሳቱን በሚናገረው ከሐጢያት የመዳን የእግዚአብሄር እውነት ላይ የምንጨምረው አንዳች ነገር አለን? የለም፡፡ 
 
ሆኖም የዘመኑ ክርስቲያኖች በእግዚአብሄር ጽድቅ ስለማመን በሚጫወቱት ሚና ላይ በጣም ግራ ተጋብተዋል፡፡ ሰዎች በኢየሱስ በማመን ደህንነትን ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን አንድ ጊዜ በኢየሱስ ማመን ከጀመሩ አሁንም ገና ቀስ በቀስ መቀደስ፣ ሰናይ ሕይወት መኖርና ሕጉን በእግዚአብሄር ቃሎች መሰረት መጠበቅ ያለባቸው መሆኑ ለደህንነታቸው እንደሚያስፈልግ ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ሰዎች ግራ ተጋብተዋል፡፡
 
ምንም እንኳን አባባላቸው ከጻድቃን ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም የእግዚአብሄርን ጽድቅ ከሚያውቀውና ከሚያምነው እምነት ግን በጣም የራቀ ነው፡፡ ሰው በሚገባ በጌታ ማመን የሚችለው እንዴት ነው? ይህ የሚቻለው የእግዚአብሄርን ጽድቅ በያዘው የውሃና የመንፈስ ቅዱስ ቃሎች ጠንካራ እምነት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ያን ጊዜ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ እንድናለን፡፡ የእግዚአብሄር እውነት የእግዚአብሄር ጽድቅ በግል በተገለጠበት የእርሱ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በማመን ከሐጢያቶች ሁሉ እንድንድን ያስችለናል፡፡
 
ቀስ በቀስ ስለ መቀደስ፣ በሁኔታ ላይ ስላልተመሰረተ ምርጫና የስም ጽድቅ ከያዙ የማይረቡ የክርስቲያን ተምህርቶች ወይም ሰው የአሳማ ሥጋ ባለ መብላት ወይም ሰንበቶችን በመጠበቅ ውሎ አድሮ መዳን ይችላል ከሚለው የሐሰት እምነት መላቀቅ ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ያሉ የማይረቡ ነገሮችን ከሚናገሩ ሰዎች መራቅ ይገባናል፡፡ ንግግራቸው መደምደሚያ ወይም ትክክለኛ መልሶች የለውም፡፡
 
ወንድሞች አንዳች ሰናይ ነገር ሳናደርግ በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ከሐጢያት የዳንበት እምነት ትክለኛ እምነት ነው ወይስ አይደለም? -- አዎ ያ ትክክለኛ እምነት ነው፡፡ -- የእግዚአብሄርን ጽድቅ ለማግኘት ምን አይነት ሥራዎችን ሰራን? በእግዚአብሄር ፊት አንዳች በጎ ምግባሮችን አድርገናልን? -- አላደረግንም፡፡ -- በራሳችን አስተሳሰቦች ላይ በመመርኮዝ ፍጹማን ነን? -- አይደለንም፡፡ -- ይህ ማለት እንደወደድነው መኖር እንችላለን ማለት ነውን? -- አይደለም፡፡ --የእርሱ ልጆች መሆን ያለብን የሐጢያት ስርየትን በማግኘትና በትክክለኛው እምነት አማካይነት መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ነው ማለት ነው፡፡
 
ሰዎች በፍጹም ጥሩ ሕይወትን መኖር አይችሉም፡፡ ነገር ግን ሰው ባይሰራ እንኳን በኢየሱስ በተሰጠው ጽድቅ እስካመነ ድረስ ከሐጢያቶች ሁሉ የዳነ ብሩክ ሰው ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከመነሻው ጥሩ ሕይወትን የመኖር ችሎታ የለውም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር አዝኖልን ኢየሱስን ወደዚህ ዓለም በመላክ የዓለምን ሐጢያቶች መውሰድ ይችል ዘንድ በአጥማቂው ዮሐንስ እንዲጠመቅ አደረገው፡፡ ከዚያም ኢየሱስ ሐጢያቶችን በመስቀል ላይ ተሸክሞ የሐጢያትን ችግር ፈታ፡፡
 
ከሩቅ ምስራቅ ምሳሌያዊ አባባሎች ውስጥ ‹‹አንድ ሰው ለሌሎች በጎነት ሲል ሕይወቱን መስዋዕት ማድረግ ይገባዋል›› የሚል አባባል አለ፡፡ አንድ ሰው ሲሰምጥ ከመስመጥ ያዳነውን ሰው ለከፈለው የበጎነት መስዋዕት ያወድሱታል፡፡ ወንድሞች እየሰጠመ ያለን ሰው ማዳን የተለመደ ቢሆንም ስለዚህ ነገር በጣም አጋንነን እናስባለን፡፡
 
‹‹ኢንግዋ-ኡንጉቦ›› ተብሎ የሚጠራ አባባል ደግሞ ይኸውላችሁ፡፡ ይህ አንድ ሰው ጥሩ ሕይወት የሚኖር ከሆነ ወደፊት ይባረካል፤ ነገር ግን መጥፎ ሥራ ከሰራ ይቀጣል ማለት ነው፡፡ ወንድሞች በውኑ ሕይወቱን ለሌላው ሰው በነጻ የሚሰጥ ሰው አለን? ከአንድ በላይ በሆነ የጾታ ፍቅር ውስጥ እንኳን ወንዶችና ሴቶች እርስ በርሳቸው የሚፋቀሩትና የሚተጋገዙት ፍላጎታቸው ስለሚሟላላቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ሁሉ በመሰረቱ ራስ ወዳዶች ናቸው፡፡
 
ስለዚህ በሰዎች ውስጥ ምንም ሰናይ ነገር ሊኖር አይችልም ይላል፡፡ እኛም አንዳች ጥሩ ሥራዎችን ፈጽሞ ሰርተን ባናውቅም እጅግ አስጸያፊ የሆኑትን ሐጢያቶቻችንን ያስወገደውን የእርሱን ጽድቅ በተጨባጭ እንደግፈውና እናምንበት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ በጥንቃቄ መመርመር ይገባናል፡፡ አምላካችን በሰጠን የእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳን አለብን፡፡
            
 
ከአመጻ ምግባሮቻችሁ ሁሉ የሐጢያቶችን ስርየት ማግኘት ይገባችኋል፡፡
 
በእግዚአብሄር ፊት የዓመጻ ምግባሮች ምንድናቸው? በእግዚአብሄር ፊት የፈጸምናቸው ስህተቶች በሙሉ የዓመጻ ምግባሮች ናቸው፡፡
 
እናንተና እኔ ሐጢያቶቻችን በእግዚአብሄር ፊት ሊከደኑልን የሚችሉት እንዴት ነው? ወፍራም የጥይት መከላከያ ጥብቆ ሐጢያቶቻችንን መሸፈን ይችላልን? ወይም እጅግ ጠንካራ ከሆነ ብረት የተሰራ 1 ሜትር ውፍረት ያለው የብረት ዕቃ ጦር በእግዚአብሄር ፊት ሐጢያቶቻችንን መሸፈን ይችላልን? ወንድሞች ጥሩ ምግባሮችን በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት የሰራናቸውን ስህተቶችና እንከኖች ይሸፍኑልናልን? አይሸፍኑልንም፡፡ ሰው የሚሰራቸው በጎ ሥራዎች ራስን ከማጽናናት ባለፈ ምንም የሚፈይዱት ነገር የለም፡፡ ሰው በጎ ሥራዎችን በመስራት ሕሊናውን እያጽናና ከእግዚአብሄር ቅን ፍርድ ማምለጥ አይችልም፡፡
‹‹…ሐጢአታቸውም የተከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡›› መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ይህንን ነው፡፡ ወንድሞች ሐጢያቶቻችን በእግዚአብሄር ፊት እንዲከደኑልን የምንወድ ከሆነ ያን ለማድረግ ብቸኛው መንገድ እኛን ባዳነበት በእግዚአብሄር ጽድቅ ማመን ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን፣ ሐጢያቶቻችንን መውሰዱንና  በመስቀል ላይ በይፋ መሞቱን ይጨምራል፡፡ ይህ የሆነው ኢየሱስ በመጠመቅ የዓለምን ሐጢያቶች ስለወሰደና በመስቀል ላይ በመሞትም ፍርድን ስለተቀበለ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጽድቅ ይህ ነው፡፡ ሰው በእርሱ ጽድቅ ሲያምን ሐጢያቶች ሁሉ ይከደናሉ፡፡
 
ሰው በበጎ ምግባሮቹ ሐጢያቶቹን ለመሸፈን ቢሞክርም ይህ በእግዚአብሄር ፊት ምንም አይጠቅምም፡፡ የእናንተንና የእኔን ሐጢያቶች መሸፈን የሚችሉት ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ የሰራቸው የጽድቅ ሥራዎች ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ሊፈረድብን፣ ልንጠፋና በሐጢያቶቻችን ምክንያት የእግዚአብሄርን ቁጣ በመቀበል ሲዖል ልንወርድ የነበርን ሰዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅና በመስቀል ላይ በመሞት የእግዚአብሄርን ጽድቅ ፈጸመልን፡፡ በዚህ ልታምኑ ይገባችኋል፡፡ ሐጢያቶቻችን የሚከደኑት በእግዚአብሄር ጽድቅ በማመን ነው፡፡ ለምን? የእግዚአብሄር ጽድቅ በጥምቀቱና ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት አስቀድሞ ለዓለም ሐጢያት በሙሉ ትክክለኛ ካሳ ሰጥቶዋልና፡፡ እናንተና እኔ ይህንን እውነት በማመን ሐጢያቶቻችን ሊከደኑልን ይችላሉ፡፡
 
ብሩክ የሆነ ሰው ምን አይነት ሰው ነው? የዚህ አይነት እምነት ያለው ሰው የተባረከ ሰው ነው፡፡ ‹‹አመጻቸው የተሰረየላቸው ሐጢአታቸውም የተከደነላቸው ብጹዓን ናቸው፡፡ ጌታ ሐጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብጹዕ ነው፡፡›› የዚህ አይነት እምነት ያለው ሰው ብጹዕና የተባረከ ነው፡፡ እናንተና እኔ የዚህ አይነት እምነት አለን? በውኑ የተባረከ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃና በመንፈስ ቅዱስ እንዳዳነን የሚናገሩትን የእግዚአብሄር ቃሎች በልቡ የተቀበለ ሰው ነው፡፡ ኢየሱስን ከውሃውና ከደሙ ጋር አብሮ የተቀበለ ሰው በእርግጥም የተባረከ ሰው ነው፡፡
 
እኛ በእግዚአብሄር ጽድቅ የምናምን ሰዎች አንዲት ቅንጣት የሰውን አስተሳሰብ ወይም ሥነ ምግባር ያልያዘውን አስገራሚ ደህንነት በእምነት ተቀብለናል፡፡ በዚህ እምነት የሚያምን፣ ይህንንም በልቡ ውስጥ የሚይዝና እውነተኛውን ወንጌል መስበክ የሚችል ሰው በእርግጥም የተባረከ ሰው ነው፡፡
 
ወንድሞች በእግዚአብሄር ጸጋ ላይ የገዛ ራሳችሁን የተወሰኑ ሰናይ ምግባሮች በመጨመር የእግዚአብሄር ልጆች ለመሆን ወይም ከሐጢያት ለመዳን አትሞክሩ! ጥሩ ሰው ናችሁን? ሰው ጥሩ ሳይሆን ጥሩ ለመሆን ቢሞክርና ሊሆን እንደሚችል ቢያስብ ይህ ዕብሪት ነው፡፡ አንድ ደሃ ሰው ከአንድ ቢሊንየር ሰው ትልቅ አልማዝ በስጦታ መልክ ቢያገኝ ደሃው ሰው ማድረግ የሚያስፈልገው ብቸኛው ነገር ‹‹አመሰግናለሁ›› ማለት ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ጽድቅም ይኸው ነው፡፡
 
ሮሜ ምዕራፍ 4 በእግዚአብሄር ስለተባረኩ ሰዎች ይናገራል፡፡ እነዚህ ሰዎች ይናገራል፡፡ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሄርን ጽድቅ በያዙት የወንጌል ቃሎች በማመናቸው ከሐጢያት ሁሉ ድነዋል፡፡
 
ይህ በረከት የእናንተም እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡