Search

خطبے

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[2-8] ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡ ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡18-29 ››

ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን የተጻፈ ደብዳቤ፡፡
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 2፡18-29 ››
‹‹በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ እንደ እሳት ነበልባል ያሉ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሄር ልጅ እንዲህ ይላል፡፡ ሥራህንና ፍቅርህን፣ እምነትህንም፣ አገልግሎትህንም፣ ትዕግስትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ፡፡ ዳሩ ግን ነቢይ ነኝ የምትለውን፣ ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፡፡ ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም፡፡ እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፡፡ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፡፡ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፡፡ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡ ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፡፡ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ፡፡ ድል ለነሳውና እስከ መጨረሻውም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፡፡ በብረት በትርም ይገዛቸዋል፡፡ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፡፡ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡›› 
 
 
ትንታኔ፡፡ 
 
ቁጥር 18፡- ‹‹በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ እንደ እሳት ነበልባል ያሉ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሄር ልጅ እንዲህ ይላል፡፡››
የትያጥሮን የስህተት አድራጎት የኤልዛቤል ትምህርቶች ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገቡ መፍቀድዋ ነበር፡፡ የንጉሥ አክዓብ ሚስት ኤልዛቤል ጣዖት አምልኮን ወደ እስራኤል በማስገባት ዝሙትን እንዲፈጽሙና ለጣዖታት የታረዱ መስዋዕቶችን እንዲበሉ ሕዝቡን አባበለች፡፡ ኢየሱስ ‹‹እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች›› ያሉት ሆኖ መገለጡ እግዚአብሄር በእርሱ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ የተሳሳተ እምነት ያላቸውን እንደሚነቅፍና እንደሚፈርድባቸው የሚገልጥ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡
 
ቁጥር 19፡- ‹‹ሥራህንና ፍቅርህን፣ እምነትህንም፣ አገልግሎትህንም፣ ትዕግስትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ፡፡››
ነገር ግን በዚያው ጊዜ እግዚአብሄር ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን አገልጋዩና ለቅዱሳኖቹ ሥራዎቻቸው ከበፊቱ ይልቅ አሁን የተሻሉ እንደሆኑ ነግሮዋቸዋል፡፡
 
ቁጥር 20፡- ‹‹ዳሩ ግን ነቢይ ነኝ የምትለውን፣ ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡››
የትያጥሮን ቤተክርስቲያን ችግር የሐሳዊቷን ነቢይት ትምህርቶች መቀበልዋ ነበር፡፡ ኤልዛቤልን የምትመስል ጋለሞታይቱን ሐሳዊት ነቢይት ወደ ቤተክርስቲያን እንድትገባ በመፍቀድዋና የእርስዋን ትምህርቶች በመቀበልዋ የቅዱሳኖችዋ ልቦች መጨረሻቸው የሥጋቸውን ፍትወት መሻት ሆነ፡፡ ከዚህ የተነሳ የእግዚአብሄር አስፈሪ ቁጣ በእነርሱ ላይ ተገልጦ ነበር፡፡
የእግዚአብሄር እውነተኛ ቤተክርስቲያን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑትን ሰዎች ቅዱሳን ብላ አትጠራቸውም፡፡ በልባቸው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የሌለባቸውንም ሰዎች በቤተክርስቲያን የአመራር ቦታዎች ላይ አያስቀምጥም፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ሰዎች እግዚአብሄርን ከመሻት ይልቅ ሥጋንና ዓለምን ስለሚሹ በእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ በፍጹም ሊፈቅድላቸውና ተቀባይነት ሊያገኙ አይችሉም፡፡
 
ቁጥር 21፡- ‹‹ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፡፡ ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም፡፡››
መንፈስ ቅዱስን ያልተቀበሉ ከሥጋ የሆኑ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ መለየትና መስማት እንደማይችሉ ይህ ይነግረናል፡፡ ሐሳዊቷ ነቢይት ከዝሙትዋ ንስሐ ያልገባችው ለዚህ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በመንፈስ ሰይፍ ተመትታ በሥጋና በመንፈስ ተኮነነች፡፡
በእውነተኛዋ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ሆነው ሊጸኑ የሚችሉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማያምኑ ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ ምንም ያህል ግሩም መጋቢ ቢሆኑም የእግዚአብሄርን ልጆች ወደ እርሱ የሚመሩ ታማኝ መሪዎች አይሆኑም፡፡ ስለዚህ ሐሰተኛ ነቢያቶችን ለይተን በማወቅ ከቤተክርስቲያኖቻችን ማባረር አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን የሰይጣንን ማታለያዎች ሁሉ መቋቋምና እርሱን መንፈሳዊ ሆና መከተል የምትችለው ይህንን በማድረግ ብቻ ነው፡፡
 
ቁጥር 22፡- ‹‹እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፡፡ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፡፡››
ይህ ምንባብ የእግዚአብሄር አገልጋይ ዋሾዎችን የሚለይና የሚያጋልጥ ካልሆነ እግዚአብሄር ራሱ መንፈሳዊ ዝሙትን የሚፈጽሙትን እንደሚያገኛቸውና በታላቅ መከራ ውስጥ እንደሚጥላቸው ይናገራል፡፡ የእግዚአብሄር ቅዱሳንና አገልጋዮች እግዚአብሄር ራሱ የራሱን ቤተክርሰቲያኖች በንጽህና እንሚጠብቃቸውና በቀናው መንገድ እንደሚመራቸው መገንዘብ አለባቸው፡፡
በእግዚአብሄር እውነተኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሐሰተኛ ነቢያት ቦታ የለም፡፡ ሐሰተኛ ነቢያቶች ቢኖሩ እግዚአብሄር ራሱ ፈልጎ ያገኛቸውና ይፈርድባቸዋል፡፡ በእነዚህ ሐሰተኛ ነቢያቶች በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ግራ መጋባት ቢፈጠር እግዚአብሄር በታላቅ መከራ እንደሚቀጣቸው የተረጋገጠ ነው፡፡
 
ቁጥር 23፡- ‹‹ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፡፡ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡››
እግዚአብሄር ሁሉም ሰው የራሱን ቤተክርስቲያን እንደሚጠብቅ ያውቅ ዘንድ ሐሰተኛ ነቢያቶችን ከቤተክርስቲያን ያባርራል፡፡ ቅዱሳኖችም እግዚአብሄር ቤተክርስቲያናቸውን እንደሚጠብቅላቸውና የበጎ እምነት ምግባሮቻቸውንም እንደሚሸልም ይረዳሉ፡፡
 
ቁጥር 24፡- ‹‹ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፡፡››
ይህ ማለት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን አስቀድመው የእግዚአብሄር ቅዱሳን የሆኑ ሰዎች እምነታቸውን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከመጠበቅ ውጪ ሌላ መንገድ የላቸውም፡፡ እውነተኛዋ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ሁልጊዜም ወንጌልን መስበክ ያለባት ብቻ ሳትሆን በዚህ ወንጌል ባላት እምነትም ዋሾዎችን ማጋለጥ አለባት፡፡
 
ቁጥር 25፡- ‹‹ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ፡፡››
ምዕመናን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላቸውን እምነት በፍጹም መጣል የለባቸውም፡፡ ጌታችን እስከሚመጣበት ቀን ድረስም አጥብቀው መያዝ አለባቸው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌላቸው ውስጥ ሰይጣንን ለማሸነፍ ከበቂ በላይ የሆነ ትልቅ ሐይልና ሥልጣን አለ፡፡ ቅዱሳን በዚህ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት ይችላሉ፡፡ ቅዱሳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌላቸው ቢኖሩና በእውነተኛዋ የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ቢቆዩ እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስ ድል ማድረግና ማሸነፍ ይችላሉ፡፡
 
ቁጥር 26፡- ‹‹ድል ለነሳውና እስከ መጨረሻውም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፡፡››
ቅዱሳን እግዚአብሄር በሰጣቸው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በማመን ጠላቶቻቸውን ሁሉ ማሸነፍ ይችላሉ፡፡ ይህ የእምነት ተጋደሎ ሁልጊዜም ድልን የሚሰጠን ተጋድሎ ነው፡፡ ቅዱሳን ሁሉ ጸረ ክርስቶስን በመጨረሻው ዘመን ተዋግተው ያሸንፋሉ፡፡ ከዚህ የተነሳም ከጌታ ጋር አብረው የሚነግሱበት ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡
 
ቁጥር 27፡- ‹‹በብረት በትርም ይገዛቸዋል፡፡ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፡፡››
ጌታ ሰማዕት ለሆኑት ቅዱሳኖቹ የንግሥና ሥልጣኑን ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ድል የነሱ ሰዎች ምንባቡ እንደሚገልጠው የሸክላ ዕቃን ማድቀቅ በሚችል እንደ ብረት በትር ብርቱ በሆነ ሥልጣን ይገዛሉ፡፡
 
ቁጥር 28፡- ‹‹የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ፡፡››
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ጠላቶችን የሚዋጉ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል እውነት የመረዳት በረከት ይሰጣቸዋል፡፡
 
ቁጥር 29፡- ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡››
ቅዱሳን ሁሉ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኩል የሚመጣውን የመንፈስ ቅዱስ ድምጽ መስማት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም መንፈስ በእግዚአብሄር አገልጋዮች በኩል ለቅዱሳን ሁሉ ይናገራልና፡፡ ቅዱሳን በእግዚአብሄር ቅዱሳን በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን በኩል የሰሙትን የእርሱን ድምጽ ማወቅ አለባቸው፡፡