Search

خطبے

ርዕስ 10፡ ራዕይ (በራዕይ ላይ የተሰጡ ሐተታዎች)

[8-2] የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ቃል በቃል የሚፈጸሙ ናቸውን? ‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 8፡1-13 ››

የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ቃል በቃል የሚፈጸሙ ናቸውን?
‹‹ ዮሐንስ ራዕይ 8፡1-13 ››
 
በራዕይ 5 ላይ ኢየሱስ የወሰደውና በሰባት ማህተሞች የታተመ መጽሐፍ ይታያል፡፡ ይህ ማለት ኢየሱስ የእግዚአብሄር ሥልጣንና ሐይል ሁሉ በአደራ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ዓለምን እንደ እግዚአብሄር ዕቅድ ይመራታል ማለት ነው፡፡ ራዕይ 8 የሚጀምረው ‹‹ሰባተኛውንም ማህተም በፈታ ጊዜ እኩል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ፡፡ በእግዚአብሄርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላዕክት አየሁ፡፡ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው›› በሚል ምንባብ ነው፡፡ በዚህም ኢየሱስ የመጽሐፉን ሰባተኛውን ማህተም በመፍታት ሊመጡ ያሉ ነገሮችን ያሳያል፡፡
 
ምዕራፍ 8 የሚጀምረው የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በቅዱሳን ጸሎቶች እንደሚጀምሩ ለእኛ በመንገር ነው፡፡ ከቁጥር 6 ጀምሮ ምዕራፉ በዚህች ዓለም ላይ ስለሚወርዱት የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ይናገራል፡፡
 
 

የመጀመሪያው መለከት መቅሰፍት፡፡ 

 
የመጀመሪያው መለከት-- ቁጥር 7፡- ‹‹ፊተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፡፡ ወደ ምድርም ተጣለ፡፡ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፡፡ የዛፎችም ሲሶ ተቃጠለ፡፡ የለመለመም ሳር ሁሉ ተቃጠለ፡፡››
 
ማወቅ የሚገባን የመጀመሪያው ነገር እኛ ቅዱሳን የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች በምድር ላይ በሚወርዱበት ጊዜ በመካከላቸው መሆን ወይም አለመሆናችንን ነው፡፡
 
እዚህ ላይ ሰባቱን መለከቶች የሚነፉ ሰባት መለከቶች ይመጣሉ፡፡ ከእነዚህ ሰባት መቅሰፍቶች በመጀመሪያዎቹ ስድስት መቅሰፍቶች ውስጥ ለማለፍ በዚህ ምድር ላይ እንደምንቆይ መረዳት አለብን፡፡ ሰባተኛው መለከት በሚነፋበት ጊዜም እንደምንነጠቅ ይህንንም ተከትሎ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እንደሚወርዱም መገንዘብ አለብን፡፡
 
የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ከደም ጋር የተቀላቀለ በረዶና እሳት በምድር ላይ ዘንቦ የምድርን ሲሶና የዛፎችን ሲሶ እንደሚያቃጥል ቁጥር 7 ይነግረናል፡፡ በሌላ አነጋገር የዓለምና የተፈጥሮ ሲሶ ይቃጠላል፡፡
 
ተፈጥሮ እንዲህ ሲቃጠል በሕይወት እንኖራለንን? ከደም ጋር የተቀላቀለ በረዶና እሳት በእኛ ላይ ሲዘንብና ዛፎችም ወደ አመድነት ሲቀየሩ አመድ እስኪሆኑ ድረስ በተቃጠሉ በእነዚህ የተፈጥሮ ስነ ምህዳሮች ተከበን መኖር እንችላለንን? በዚህ ከደም ጋር በተቀላቀለ በረዶና እሳት ዝናብ የምንኖርባቸውን ቤቶቻችንን የምናጣና ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችና ኮረብታዎችም ሲቃጠሉ የምናይ ከመሆኑ ያፈጠጠ እውነታ ጋር በተጨባጭ ስንገጣጠም ማናችንም በመኖር የመቀጠል አንዳች ፍላጎት አይኖረንም፡፡ ለመኖር ብንፈልግም እንኳን እንደዚያ ማድረግ አንችልም፡፡
 
እናንተና እኔ በዚህ በፊተኛው መቅሰፍት ውስጥ የምናልፍ መሆናችንን አትርሱ፡፡ ወደዚህ አስከፊ መቅሰፍት ውስጥ እየገባን መሆኑ ሲገለጥልን ያን ጊዜ ጸረ ክርስቶስም በዚህች ምድር ላይ እንዳለ መገንዘብ አለብን፡፡ እነዚህ መቅሰፍቶች የሚጀምሩት ጸረ ክርስቶስ ዓለምን ለመግዛት በመሻት ሙሉ በሙሉ ከመገለጡ በፊት ስለሆነ የዓለም መሪዎች መቅሰፍቶቹን ለመቋቋም የተባበረ ግንባር መፍጠር ይጀምራሉ፡፡ አንድ ገዥም አንድ ትልቅ ሥልጣን ለመፍጠር ሌሎች ሰባት ገዥዎችን ያስተባብራል፡፡
 
ያን ጊዜ ጸረ ክርስቶስ በዚህ ሒደት በተለመደ መልኩ አምባገነን ገዥ ሆኖ ብቅ ይላል፡፡ ጸረ ክርስቶስ የተፈጥሮን ጥፋት በመቆጣጠርና በማደስ ያለውን ታላቅ ብቃት ሲያሳይ ብዙዎች በሥልጣኑ ተደንቀው መለኮት እንደሆነ አድርገው በማሰብ እርሱን መከተል ይጀምራሉ፡፡ የእርሱ ደጋፊዎችም ቀስ በቀስ ነገር ግን በእርግጠኝነት ብቅ ይላሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ሲነፋ የምድርን ሲሶ የሚያቃጥለው ከሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች አንዱ እንደሚወርድ ይነግረናል፡፡ ይህ መቅሰፍት ሲወርድ እኛ ቅዱሳኖችና የዓለም ሕዝብ በዚህ ምድር ላይ እንኖራለን፡፡ ያን ጊዜ በዓለም ላይ ምን ይከሰታል? በዓለም ላይ ውጥንቅጥ፣ ፍርስራሾችና ሬሳዎች ይበዛሉ፡፡ ቁስለኞች በየስፍራው ይጋደማሉ፡፡ ከባቢ አየሩም መላውን ዓለም ያጥለቀለቀው የእሳት ባህር በፈጠረው ጢስና መርዛማ ጋዝ ይሸፈናል፡፡ እሳቱ የፈጠረው አለም አቀፍ በረሃማነት ምድሪቱ ኦክሲጅንን ለማፍለቅ ያላትን አቅም ክፉኛ ስለሚቆርጠው አየሩ ኦክሲጂን አልባ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው መቅሰፍት ብቻውን የመኖር ፍላጎታችንን እንኳን ሳይቀር በመውሰድ ይህንን ዓለም ወደ አመድነት ይቀይረዋል፡፡
 
ከዚህ መቅሰፍት በመማር ብልህ የሆነ ምርጫ ማድረግ አለብን፡፡ አሁን ባለው የተመቸ ዓለም እየኖርን ሊመጡ ያሉትን ታላላቅ መቅሰፍቶችና መከራዎች እንፈራ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ፍርሃት ተላቀን ደፋሮች መሆን እንችላለን፡፡ የዓለም ተፈጥሮ ሲሶው ሲቃጠልና ሰዎችም በየስፍራው ሲያለቅሱ ይህ ከመሆኑ በፊት መቅሰፍቱ እንደሚመጣና ሊመጡ ያሉ ተጨማሪ መቅሰፍቶችም እንዳሉ አስቀድመን አውቀናል፡፡ እኛ ተስፋ ስላለን በእርሱ ልንሞላ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሥጋ ለባሽ ስለሆንም አንዳንድ ጊዜ በፍርሃት ልንመታ እንችላለን፡፡ ነገር ግን የዚህችን ዓለም የወደፊት ዕጣ ፈንታ ስለምናውቅ ተስፋችንን በእግዚአብሄር መንግሥት ላይ እንጂ በዚህች ምድር ላይ አናደርግም፡፡ በዚህ ዓይነት እምነትና በውስጣችን በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ደፋሮችና ጀግኖች መሆን እንችላለን፡፡
 
የዓለም ሰዎች ሰቆቃ ከፍ ብሎ ይሰማል፡፡ ቤተሰቦቻችን የሐጢያቶቻቸውን ስርየት ካልተቀበሉት መካከል ከሆኑ እኛም እንደዚሁ እናለቅስ ይሆናል፡፡ ከሥጋ ቤተሰቦቻችን አንዳንዶቹ ከሐጢያቶቻቸው ስላልተዋጁ ለፍርፋሪ ምግብ ሲሉ ለጸረ ክርስቶስ ሊሸጡን ይችሉ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ሌሎች የሐጢያቶቻቸውን ስርየት እንዴት መቀበል እንደሚችሉ ሊጠይቁን ወደ እኛ ይመጡ ይሆናል፡፡ ይህ የሚሆን ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ያን ጊዜ የመዳን ዕድል አላቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች ሲመጡ የመላው ዓለም ሲሶ እንደሚሞት ይነግረናል፡፡ ይህ ማለት የዓለም ሁለት ሶስተኛው እጅ ይተርፋል ማለት ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ ሲሶ ተቃጥሎ ሲሞት ሰማዕት የምንሆንበትና ጌታችን የሚመጣበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሄር ከሰማይ ከደም ጋር የተቀላቀለ እሳትና በረዶ እንደሚያዘንብ ተናግሮዋል፡፡
 
እግዚአብሄር በረዶና እሳት በእኛ ላይ ሲያዘንብ ልናርቃቸው አቅም አልባዎች እንሆናለን፡፡ መላውን ዓለም ከሚወርደው እሳትና በረዶ መሸፈን የሚችል የመከላከያ ጋሻ ሰርቶ በከባቢ አየሩ ላይ ማስቀመጥ በሳይንሳዊ ዕመርታም ቢሆን የማይቻል ይሆናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት መከላከያ ብንሰራም ከጌታ ዘንድ የሚመጣውን የመቅሰፍት ሐይል መቋቋም አይችልም፡፡ እነዚህ መቅሰፍቶች በእርግጥም በተጨባጭ በእኛ ላይ የሚወርዱ የመሆናቸውን እውነታ በልባችን መቀበልና የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃሎች ከልባችን በማመን አሁን የምንኖረውን ሕይወት መኖር አለብን፡፡
 
በቅርቡ ስፋታቸው 45 ሳንቲ ሜትር የሆኑና የሰው ጭንቅላት የሚያካክሉ የበረዶ ድንጋዮች በቻይና እንደወደቁ በዜና ሰማሁ፡፡ እነዚህ የሰው ጭንቅላት መጠን ያላቸው የበረዶ ቁራጮች አስገራሚ በሆነ የአወዳደቅ ፍጥነት ጣሪያዎችን እየበሱና በመንገዳቸው ላይ ያለውን ነገር ሁሉ እያወደሙ ወደቁ፡፡ በመጀመሪያው መቅሰፍት ላይ የሚወርደው ጉልበቱ ከዚህም የሚበልጥ ነው፡፡ በቻይና ላይ ከወረዱት ከእነዚህ የበረዶ ድንጋዮች ይበልጥ በጣም አውዳሚ የሆነውና የዚህችን ምድር ሲሶ የሚበላው እሳት በእርግጥም እንደሚወርድ በልባችን ማመን አለብን፡፡ ይህንን እምነት በልባችን መጠበቅ አለብን፡፡ ይህ መቅሰፍት በእርግጥም ሲመጣ በዚህ እምነት ማድረግ ያለብንን ማድረግ አለብን፡፡ ይህ ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋ ማመን አለብን፡፡ መቅሰፍቱን በዚህ እምነት ለመጋፈጥ ቆራጥ መሆንና ራሳችንን ሰማዕት ለማድረግም መወሰን አለብን፡፡ ሰባቱ መለከቶች ሲነፉ ሰባቱ መቅሰፍቶች በእርግጥም በዚህ ዓለም ላይ ይወርዳሉ፡፡ ይህ ከእነዚህ መቅሰፍቶች የመጀመሪያው ነው፡፡
 
 

እግዚአብሄር የሚያወርደው የሁለተኛው መለከት መቅሰፍት፡፡ 

 
ሁለተኛው መለከት-- ቁጥር 8-9፡- ‹‹ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባህር ተጣለ፡፡ የባህርም ሲሶው ደም ሆነ፡፡ በባህርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፡፡ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ፡፡››
 
ቅዱሳን በዚህ በሁለተኛው መቅሰፍት ውስጥም የሚኖሩ የመሆናቸውን እውነታ ትኩረት ልናደርግበት ይገባናል፡፡
 
እዚህ ላይ ታላቅ ተራራ የሚመስል ነገር ወደ ባህር ተጥሎ የባህርን ሲሶ ደም እንዳደረገና የሕያዋን ፍጥረታቶችን ሲሶ እንደገደለ ይናገራል፡፡ የዘመኑ መጨረሻ ሲመጣ የዩኒቨርስ ሥርዓት ይፈረካከስና የከዋክብቶችን ሥርዓተ ስብስብ በማዛባት እርስ በርሳቸው እንዲጋጩና እንዲፈረካከሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም ብዙ ተወርዋሪ ኮከቦች ከምድር ጋር ለመላተም ወደ ምድር ይምዘገዘጋሉ፡፡ ከእነዚህ ተወርዋሪ ኮከቦች አንዳንዶቹ ከባቢ አየሩን ሰንጥቀው በማለፍ ባለ በሌለ የማቃጠል ጉልበታቸው ባህር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በባህር ውስጥ የሚኖሩትን ፍጥረታቶች ሲሶ በመግደልም የባህሩን ሲሶ ወደ ደም ይቀይሩታል፡፡ የመርከቦችንም ሲሶ ያወድማሉ፡፡ ከሰባቱ መለከቶች መቅሰፍቶች መካከል የሁለተኛው መለከት መቅሰፍት ይህ ነው፡፡
 
ይህ በሚሆንበት ጊዜ የባህር አሳ መብላት ወይም በውስጡ መዋኘት ይቻለናልን? ከእንግዲህ ወዲህ ሁለቱም አይቻሉም፡፡ አንድ ታላቅ ተራራ የሚመስል አስትሮይድ ባህር ላይ ሲወድቅ የባህር ሲሶም ወደ ደም ይለወጣል፡፡ በውስጡ ያሉ ሕያዋን ፍጥረታቶች ሲሶ ይሞታሉ፡፡ ሬሳቸውም ባህሩን ያገማዋል፡፡ ማዕበሎችና የመሬት መናወጦችም የሚያጠፉት መርከቦችን ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰዎችንም ይገድላሉ፡፡
 
አንድ አስትሮይድ ባህር ላይ ወድቆ ምድርን የሸፈነ ታላቅ ማዕበል ሲፈጥር የሚያሳይ ፊልም ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡ የፊልሙ አዘጋጆች ይህንን ፊልም ሲሰሩ የዘመኑ መጨረሻ ስዕል በአእምሮዋቸው ውስጥ ፍንትው ብሎ የታያቸው ለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ታላላቅ ጥፋቶች ምድርን የሚመቱ መሆናቸውን የማያምኑ ሰዎች እንኳን በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት እውነት ነው፡፡ በሚወርዱ ተወርዋሪ ኮከቦች መቅሰፍት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ነገር ግን የሚወድመው የዓለም ሲሶ ብቻ ስለሆነ እናንተና እኔ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እስከሚወርዱ ድረስ በዚህች ምድር ላይ መኖራችንን እንቀጥላለን፡፡
 
ሰዎች ከዚህ ቀደም ንጥቀት የሚሆነው ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን የቅድመ መከራ ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ሲመጣ ብዙ የሥነ መለኮት ምሁራን በዚህ የቅድመ መከራ ንጥቀት ማመን ጀመሩ፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ የሺህ ዓመቱን መንግሥት የሚክደው ሺህ አመት የለም የሚለው ጽንሰ አሳብ አሁን ብቅ ማለቱ ነው፡፡ የሥነ መለኮት ምሁራን የራዕይን ሙሉ ቃል መፍታት ባለመቻላቸው አሁን ከቃሎቹ ሁሉ ለመሸሽ ብቻ እየሞከሩ ነው፡፡ ከሚመጡት መቅሰፍቶች የተነሳ በዚህች ምድር ላይ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ተስፋቸውን ጌታ ቃል በገባው የሺህ ዓመት መንግሥትና በአዲሱ ሰማይና ምድር ላይ ብቻ በማኖር ሁኔታውን ከሚጋፈጡ ዳግመኛ የተወለዱ ቅዱሳን ጋር ያላቸውን ጉልህ ልዩነት ያሳያሉ፡፡
 
የዘመኑ መጨረሻ ወደ እኛ ሲቃረብ እምነታችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህንን በማድረግ ፋንታ ትክለኛውን እምነት ለመሸሽ በመሞከር ስለ ቅድመ መከራ ንጥቀት ወይም ስለ ሺህ ዓመት አልባ መነጋገር ይመርጣሉ፡፡ እነርሱ የቀን ተቀን ሥራቸውን ሲሰሩና የሰላም ሕይወታቸውን ሲኖሩ ኢየሱስ በደመና እንደሚመጣ ስለሚያምኑና በማናቸውም መቅሰፍቶች ውስጥ ሳያልፉ በቀጥታ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንደሚነጠቁ ስለሚያምኑ እምነታቸውን በጭራሽ ለታላቁ መከራ እያዘጋጁት አይደለም፡፡
 
በመጀመሪያ ዕይታ እነዚያ የሚዝናኑና ለታላቁ መከራ የማይዘጋጁ ሰዎች ደፋሮች መስለው ይታዩ ይሆናል፡፡ ዳግመኛ ያልተወለዱ ሐጢያተኞች በታላቁ መከራ ፊት ደፋሮች መስለው የሚታዩበት ምክንያት ነፍሳቸው የሐሰተኛ ነቢያቶችን ውሸቶች ስለጠጣች ሙት በመሆንዋና ዳግመኛም በውስጣቸው የቀሩ ምንም መንፈሳዊ ፍላጎቶች ስለሌላቸው ነው፡፡ ሰዎች ነፍሳቸው አስቀድማ ስለሞተች አይሰሙም፡፡ ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል ተወልደው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንዲገቡ (ዮሐንስ 3፡5) የሚያስችላቸውን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌልም ያጥላላሉ፡፡
ዳግመኛ የተወለዱ ሰዎች ግን የአሁኑ ኑሮዋቸው ምንም ያህል የተመቸ ቢሆንም እምነታቸውን ለዘመኑ መጨረሻ መከራዎች ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ በአእምሮዋቸው ውስጥ ወንጌልን ለእግዚአብሄር ታማኝ ለሆኑት የመስበክ ፍላጎታቸውን ጠብቀው መያዝ እነርሱም ደግሞ በመከራው ዘመን በተቻለ መጠን ብዙ ነፍሳቶችን ማዳን ይችሉ ዘንድ ለወደፊቱ አስቀድመው መዘጋጀት አለባቸው፡፡
 
በቅርቡ የሚመጣውን ታላቅ መከራ ችላ ማለት በማይታመን ሁኔታ ሞኝነት ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ከኮርያ ጦርነት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ በመቅሰፍቶቹ ፊት ረዳት አልባ ይሆናሉ፡፡ የኮርያ ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት አሜሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰሜን ኮርያ ጦር መንቀሳቀሱን አውቃ ደቡብ ኮርያ ድንገት ልትወረር እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡ የደቡብ ኮርያ መንግሥትና ጦር ግን ማስጠንቀቂያውን ሙሉ በሙሉ ችላ በማለት ወታደሮችን ለዕረፍት እስከ መስደድና የግምባር ሐላፊዎችም በትክክለኛው የወረራ ቀን የሳምንት መጨረሻ ቀናቸውን እንዲደሰቱበት እስከ መፍቀድ ድረስ ርቀው ሄዱ፡፡
 
የሰሜን ኮርያን ወረራ የሚያሳይ መረጃ እያላቸው እንኳን የሰሜንን ጥቃት መቀልበስ ስላልቻሉ እስከ ሰሜናዊው ማዕዘን ጫፍ ድረስ እንዲያፈገፍጉ ተደረጉ፡፡ ደቡብ ኮርያ ወታደሮችዋን ከዕረፍት እንዲመለሱ በመጥራት ሰራዊቱን ለጦርነት ማደራጀት በሞከረችበት ጊዜ የጦሩ ግምባር ቀድሞውኑም ተጥሶ ነበር፡፡ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከማፍገፈግ በስተቀር ምርጫ አልነበረውም፡፡
 
እግዚአብሄር ስለ መጨረሻው ዘመን የነገረንን ቃል የማናምን ከሆነ የሚደርስብን ወዮታ የዚህ ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉን ከልባችን የምናምን ከሆነ እንዲህ ካለው ወዮታ ማምለጥ እንችላለን፡፡ ራዕይ በመከራው ዘመን ስለሚኖር መሸሸጊያ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ትክክለኛውን ስፍራ አይነግረንም፡፡ የሆኖ ሆኖ ቅዱሳን እንደሚጠለሉና ተሸሽገው እንደሚመገቡ ይነግረናል፡፡ ይህ መሸሸጊያ የሚያመለክተው ሌላ ነገርን ሳይሆን ቤተክርስቲያንን ነው፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ላይ መጠለያ ማግኘት የሚችለው የት ነው? አንዳንድ ሰዎች ወደ እስራኤል ቢሸሹ እንደሚተርፉ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በእስራኤል ውስጥ ይበልጥ የከፉ መከራዎች ይገጥሙዋቸዋል፡፡ ጸረ ክርስቶስ ራሱ ዋና መስሪያ ቤቱን በእስራኤል ስለሚያደርግ መቅሰፍቶቹ በዚያ ይበልጥ እንደሚበረቱ ማወቅ ይኖርባችኋል፡፡
 
ይህ የመከራዎች ቃል በአሁኑ ጊዜ ፈጥኖ ተጨባጭ መስሎ ባይታይም ይህንን በልባችሁ አውቃችሁ ለወደፊቱ ልትዘጋጁ ይገባችኋል፡፡ ከልባችሁ ልታምኑት ይገባል፡፡ በዚህ እምነትም በዚህ በታላቁ የመከራ ዘመን ውስጥ እየኖራችሁ ያላችሁ በመምሰል ወንጌልን ለሰዎች መስበክ አለባችሁ፡፡ የሰዎችን ልብ ማዘጋጀትና የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለእነርሱ በመስበክ ወደ መጠለያቸው ልትመሩዋቸው ይገባችኋል፡፡ እግዚአብሄር በቤተክርስቲያኖቹ ውስጥ ጠብቆ ያቆየን ለሰዎች ሊመጡ ያሉትን እነዚህን ነገሮች በመስበክ እምነታቸውን ለመጨረሻው ዘመን እንዲያዘጋጁ ለመርዳት ነው፡፡
 
እያደረግን ያለውን ነገር የምናደርገው ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሙሉ ሐይላችን የምንሰብከው ለዚህ ነው፡፡ እኛ በዚህ ዘመን የራዕይን ቃል የምንሰብከው በራሳችን ለመኩራራት ሳይሆን ነገር ግን ለዛሬው ዘመን ምዕመናኖችና አላማኒዎች በጣም አስፈላጊ የሆነ ቃል ስለሆነ ነው፡፡ መከራዎቹና መቅሰፍቶቹ በእኛ ላይ ሲወርዱ ልቦቻችን የማይናወጡት ከአሁን ጀምረን ይህንን እምነት በማዘጋጀት ብቻ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር የእርሱን ልዩ ጥበቃ እንደሚያደርግልን የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን እየኖርን ያለነው አስፈሪ፣ አዳጋችና አስቸጋሪ ዓለም ውስጥ በመሆኑ በመጨረሻው ዘመን ምን ሊመጣ እንዳለ ካወቅንና መከራዎቹን ድል ለማድረግ እምነታችንን ካዘጋጀን ወንጌልን በይበልጥ ማሰራጨት እንችላለን፡፡ በእግዚአብሄር መንግሥት ላይ ታላቅና ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ተስፋን ስለምናኖርም በዓለም ፍሰት ፈጽሞ አንወሰድም ወይም እምነታችንን አንሸጥም፡፡ ነገር ግን በፋንታው ተጨማሪ የእምነት ሥራዎችን እንሰራለን፡፡ የራዕይን ቃል የምንሰብከውና ብዙ የእምነት ሥራዎችን የምንሰራው ለዚህ ነው፡፡
 
 
የሦስተኛው መለከት መቅሰፍት፡፡ 
 
ሦስተኛው መለከት--ቁጥር 10-11፡- ‹‹ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፡፡ በወንዞችና በውሃ ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ፡፡ የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፡፡ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፡፡ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡››
 
ቅዱሳን በሦስተኛው መቅሰፍት ውስጥም ይኖራሉ፡፡ የሁለተኛው መለከት መቅሰፍት የወረደው በባህር ላይ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሦስተኛው መለከት መቅሰፍቱን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ ያወርዳል፡፡ እዚህ ላይ ከሰማይ የሚወርደው ታላቁ ኮከብ የሚያመላክተው ጅራታም ኮከብን ነው፡፡ በጅራታም ኮከቡ የተመቱት ወንዞችና የውሃ ምንጮች ወደ እሬትነት ስለሚለወጡ መራራ ይሆናሉ፡፡ በጥንት ዘመን ሰዎች እሬትን ፈጭተው ለመድሃኒትነት መመገብ ያዘወትሩ ነበር፡፡ ይህም ከሚታሰበው በላይ መራራ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ መራራ እሬት በመላው የዓለም የውሃ አቅርቦቶች ላይ ስለሚሰራጭ ሰዎች ይህንን በመጠጣት እንደሚሞቱ ይነግረናል፡፡
 
የዓለም ንጹህ ውሃ ወደ እሬትነት ሲቀየር ብዙ ሰዎች ከዚህ የተነሳ ይሞታሉ፡፡ ነገር ግን ጌታ ሕዝቡን በዚህ መቅሰፍት ሁሉ ውስጥ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለከፍተኛ ሞት በእጅጉ ሊሆን የሚችለው ምክንያት ምናልባትም በጅራታም ኮከቡ መውደቅ ከተፈጠሩ በውሃ ውስጥ ከሚገኙ አንዳች ዓይነት የባዮ ኬሚካል ለውጦች የተነሳ ከሚፈጠሩ አንዳንድ ውሃ ወለድ በሽታዎች የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ አነጋገር ሰዎች የሚሞቱት ውሃው መራራ ስለሆነ ሳይሆን በሌላ ነገር ምክንያት ነው፡፡ እኛ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እውነተኛ እንደሆኑ እናውቃለን፤ እናምናለንም፡፡ ወደፊትም ያለ ምንም መሳሳት ይፈጸማሉ፡፡
 
 
የአራተኛው መለከት መቅሰፍት፡፡ 
 
አራተኛው መለከት-- ቁጥር 12፡- ‹‹አራተኛውም መልአክ ነፋ፡፡ የጸሐይ ሲሶና የጨረቃም ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፡፡ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ የቀንም ሲሶ እንዳያበራ እንዲሁም የሌሊት፡፡››
 
ቅዱሳን በዚህ በአራተኛው መቅሰፍት ውስጥም በዚህ ምድር ላይ እንደሚኖሩ አትርሱ፡፡
የቀኑ ሲሶ የማያበራ ከሆነ የቀኑ ብርሃን ከአማካዩ የሰባትና የስምንት ሰዓታት ወደ አራት ሰዓታት ቀንሶዋል ማለት ነው፡፡ ጨረቃና ከዋክብትም የብርሃናቸውን ሲሶ ስለሚያጡ መላው ዓለም ይጨልማል፡፡ በሌላ አነጋገር ብሩህ የቀን ብርሃን መኖር ሲገባው ድንገት ጨለማ ይመጣል፡፡ ንጥቀት የሚለው ፊልም የተከተለው የቅድመ መከራን ንጥቀት ጽንሰ አሳብ ቢሆንም በውስጡ ግን መላው ዓለም ብሩህ በሆነ የቀን ብርሃን ወደ ጨለማ በመለወጥ ሰው ሁሉ እንዲጮህና እንዲንቀጠቀጥ ሲያደርግ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ስለዚህ ነገር ራሳችሁ አስቡ፡፡ ከጠዋቱ 11 ሰዓት መሆን ሲገባው ድንገት ጸሐይ ትጠፋና ብርሃን አይኖርም፡፡ እናንተም ደግሞ በሞት መልአክ የተጎበኛችሁ ይመስል በፍርሃት ትርዳላችሁ፡፡
 
እንዲህ ባለ የጥፋት ዘመን ውስጥ መኖር እንደሚኖርብን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ልትፈሩ አይገባችሁም፡፡ እግዚአብሄር ይጠብቀናል፤ አብዝቶም ይባርከናል፡፡ በዚህ ጊዜ እምነታችሁ ስለጠነከረ እግዚአብሄር ጸሎቶቻችሁን ይመልሳል፡፡ ወደ እርሱ በምትጸልዩበት ቅጽበትም ስለ እናንተ ይሰራል፡፡ እግዚአብሄር እስከ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር እንደሚሆን ተስፋ ስለሰጠ በመጨረሻው ዘመን በሚመጣው ታላቅ መከራ ውስጥ ፈጽሞ ብቻችንን አይተወንም፡፡ ያለ ምንም ጥርጣሬ እርሱ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር እንዲህ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ስለሚሆን እንደሚጠብቀንና በሕይወት እንድንኖር እንደሚፈቅድልን ማመን አለብን፡፡ ይህንን እምነትም ለሌሎች ማሰራጨትና የእነርሱንም እምነት ደግሞ ማዘጋጀት አለብን፡፡
 
 
ሦስት ሊመጡ ያሉ ተጨማሪ መቅሰፍቶች፡፡ 
 
ቁጥር 13 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አየሁም አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምጽ፡- ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላዕክት መለከት ስለሚቀረው ድምጽ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፣ ወዮላቸው፣ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ፡፡››
 
መልአኩ ሦስት ጊዜ ወዮላቸው ብሎ ስለጮኸ በዚህች ምድር ላይ ተከታትለው የሚመጡ ሦስት ተጨማሪ መቅሰፍቶች ይኖራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከሰባቱ መቅሰፍቶች ውስጥ ሦስት ተጨማሪ መቅሰፍቶች ገናም ይቀራሉ፡፡ በሰባተኛው መለከት ወቅት ንጥቀታችን ተግባራዊ እንደሚሆን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ስድስት መለከቶች መቅሰፍቶች በሙሉ ሲጠናቀቁና ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ቅዱሳን ወዲያውኑ ትንሳኤን አግኝተው ይነጠቃሉ፡ ቅዱሳን ሁሉ ተነጥቀው ጌታን በአየር ላይ ሲገናኙ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች ያን ጊዜ በዚህች ምድር ላይ ይወርዳሉ፡፡
 
ይህች ምድር በቅርቡ ወደ ሰባቱ መለከቶችና ወደ ሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች እንደምትገባ መረዳት አለብን፡፡ የሰባቱ ጽዋዎች መቅሰፍቶች የሚወርዱት እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ በሰባተኛው መለከት መቅሰፍት ጊዜ ነው፡፡ እነዚህን ከሙሉ ልባችን ማመን አለብን፡፡ እምነታችን በእነዚህ ሁሉ መቅሰፍቶች ውስጥ ጸንቶ በመቆም ይጠንክር ዘንድ እምነታችንን አሁኑኑ መንከባከበ አለብን፡፡ ሰዎች በቅድሚያ ስለ መጨረሻው ዘመን ዕውቀት ሳይኖራቸው ቢያምኑ መከራው በእርግጥ በሚመጣበት ጊዜ በጣም ስለሚደነግጡ መጨረሻው ክህደት ሊሆን ይችላል፡፡
 
ስለዚህ እኛ በመጨረሻው ዘመን ድል አድራጊዎች ለመሆን ከፈለግን በእነዚህ ነገሮች የሚያምነው እምነታችን ትክክለኛ በሆነ የመጨረሻው ዘመን ዕውቀት መታጀብ አለበት፡፡ ዛሬ ፍጻሜው ወደ እኛ በጣም ተቃርቦ ሳለ ፈጽሞ ቤተክርስቲያንን ቸል ማለት ወይም ከእርስዋ በጣም ርቀን መውደቅ የለብንም፡፡ ልባችን በሙሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ መቆራኘት አለበት፡፡ ምንም ነገር ቢፈጠር እርስ በርሳችን ተያይዘን በእምነት እየኖርን በቤተክርስቲያን በኩል በተሰበከልን የእግዚአብሄር ቃል ሁላችንም ማመን አለብን፡፡
 
እነዚህ መቅሰፍቶች ሲመጡ ከቤተሰቦቻችን፣ ከዘመዶቻችን ወይም ከወዳጆቻችን ያልዳኑ አንዳንዶች እናንተን ይከተሉዋችሁ ይሆናል፡፡ በሰላሙ ጊዜም ቢሆን ጌታችን ዘመዶቻችን፣ ወንድሞቻችንና ወላጆቻችን እነማን እንደሆኑ በተጠየቀ ጊዜ ቤተሰቦቻችን፣ ወላጆቻችንና ወንድሞቻችን የአብን ፈቃድ የሚያደርጉ ብቻ እንደሆኑ ነግሮናል፡፡ የመከራው ዓለም ሲመጣ ዳግመኛ የተወለዱት በእርግጥ እውነተኛ ወንድሞቻቸው፣ እህቶቻቸውና ቤተሰባቸው ማን እንደሆኑ በግልጽነት ያውቃሉ፡፡ አሁን በዚህ እምነት እርስ በርሳችን ስለምንግባባና ስለምንረዳዳ እግዚአብሄርም እናንተንና እኔን አስቀድሞ ከእነዚህ መቅሰፍቶች ስላዳነን ይከልለናል፡፡ ከመቅሰፍቶቹም ይጠብቀናል፡፡ ልጆቹ አድርጎም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ይንከባከበናል፡፡ ይህ እምነት በውስጣችን በጽናት መከተል አለብን፡፡
 
በመጨረሻው ዘመን ለጸረ ክርስቶስ አሳልፈው የሚሸጡን ሰዎች የራሳችን የሥጋ ቤተሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦቻችንና ዘመዶቻችን ቢሆኑም በውሃና በመንፈስ ዳግመኛ ያልተወለዱ ከሆኑ እምነታችን እነርሱን ከመጀመሪያውም እንግዶች እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸው ዘንድ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር እነርሱ ከእውነተኛ እንግዶች ይልቅ እጅ የከፉ ነገሮችን በእኛ ላይ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የሥጋ ቤተሰቦቻችን መሆናቸው ከቁም ነገር የሚገባ አይደለም፡፡ ካልዳኑ ጠላቶቻችን መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሄር ቃል ለሰማነው ነገር ልባችንን መክፈትና ይህም እውነት መሆኑን ማመን አለብን፡፡
 
እግዚአብሄር ዲንና እሳትን በእነርሱ ላይ በማዝነብ ሰዶምንና ገሞራን ወደ እሳት ባህርነት እንደለወጣቸው በዚህ በመጨረሻው ዘመንም ይህንኑ መቅሰፍት በሐጢያተኞች ላይ ያወርዳል፡፡ እግዚአብሄር ሰዶምንና ገሞራን ማጥፋቱ በአርኪዎሎጂ መረጃዎች የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡
 
በዚህ ዘመን ምድር ከአስትሮይዶች ጋር ተጋጭታ የሰው ዘር እንደሚጠፋ የሚያሳዩ ብዙ ፊልሞች ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ፊልሞች የተሰሩት በመጨረሻው ዘመን በዚህች ምድር ላይ የሚወርዱትን መቅሰፍቶች በመዘገበው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ተወርዋሪ ኮከቦች በምድር ላይ የመውደቃቸው ዕድል በእርግጥም ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህ መቅሰፍቶች በዚህች ዓለም ላይ የመውረዳቸው ጉዳይ በጣም ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡
 
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ምድር በጥንት ዘመን በአንዳንድ ታላላቅ ለውጦች ውስጥ ማለፍዋን የሚያሳየው ከዳይኖሰሮች ቅሪተ አካሎች የተገኘው የፖሊዮንቶሎጂካል ማስረጃ ነው፡፡ የጠፉ ሕይወተ ቅርጾች በቅሪተ አካሎቻቸው አማካይነት ቀደም ብለው በሕይወት እንደነበሩ ይነግሩናል፡፡ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ይህ ዳይኖሰሮችን ጨምሮ የጥንተ ሕይወት ቅርጽ መጥፋት የሚገለጠው ምድር ከአስትሮይድ ጋር ክፉኛ በመጋጨቷ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ስለዚህ በራዕይ 8 ላይ የተጻፈው የተወርወሪ ኮከቦች መቅሰፍቶች በዚህች ዓለም ላይ መውረዳቸው የሚሆን ነገር ነው፡፡
 
 
በጣም ሩቅ ባልሆነው የወደፊት ጊዜ… 
 
እነዚህ መቅሰፍቶች በጣም ሩቅ ባልሆነ የወደፊት ጊዜ ውስጥ በዚህች ምድር ላይ እንደሚወርዱ መገንዘብ አለብን፡፡ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ቀደም ብለው ሰውን ለማዳቀል ሞክረዋል፡፡ ይህም አስፈሪ የሆነ የእግዚአብሄር ተግዳሮት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በዚህ ዘመን እነዚህን መቅሰፍቶች በሙሉ ለማውረድ ተዘጋጅቷል፡፡ የሰው ዘር በሳይንስ ሐይል ላይ ተደግፎ እግዚአብሄርን መርሳት የለበትም፡፡
 
አሁን የሰው ዘር በሳይንሳዊ ዕውቀቱ ሐይል በዓለም ላይ ለሚወርዱት መቅሰፍቶች ሁሉ ምለሽ ለመስጠት እየሞከረ ነው፡፡ ነገር ግን የትኛውም ሳይንሳዊ ጥርመሳ የእግዚአብሄርን መቅሰፍቶች መከላከል አይችልም፡፡ ምክንያቱም መቅሰፍቶቹ የሰው ዘር ከዚህ በፊት ካለፈባቸው ከማናቸውም ሌሎች ጥፋቶች ሁሉ እጅግ የከፉ ናቸውና፡፡ የዛሬውን ሰው ሰራሽ ሳይንሳዊ እመርታ ስንመለከት የሰው ዘር እርሱን ለመምሰል በመሻት የእግዚአብሄር ሥልጣን እየተገዳደረ መሆኑን ማየት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሳይንሳዊ እመርታው ምንም ያህል የተራቀቀ ቢሆንም እግዚአብሄር የሚያወርዳቸውን መቅሰፍቶች ማንም ሊያቆማቸው አይችልም፡፡ እነዚህን ሁሉ መቅሰፍቶች የጠራው ሌላ ማንም ሳይሆን የሰው ዘር ራሱ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ከሚያመጣቸው መቅሰፍቶች የማምለጫው ብቸኛው መንገድ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት የደህንነትን እውነት ማወቅና በእርሱም በማመን በጌታ ክንዶች ውስጥ መሸሸግ ነው፡፡ ይህንን አስፈሪ የእግዚአብሄር ፍርድ ለማምለጥ ብቸኛው መንገድ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያላችሁ እምነት መሆኑን በመረዳትና በማመን ከእነዚህ መቅሰፍቶች አምልጡ፡፡
 
በረከቶችና እርግማኖች ሁሉ ያሉት በእግዚአብሄር እጆች ላይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ይህችን ምድር ለማቆየት ከወሰነ ምድር ትኖራለች፡፡ ካልሆነ ግን ትጠፋለች፡፡ በዚህ ዘመን ስትኖሩ የእግዚአብሄርን ቃል የምታምኑና በንጽህና የምትከተሉ ከሆናችሁ እርሱንም ይበልጥ የምትፈሩት ከሆነ እግዚአብሄር ሊመጡ ካሉት ከእነዚህ አስፈሪ መቅሰፍቶች ልትጠለሉበት ወደምትችሉበት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ይመራችኋል፡፡
አሁንም እንኳን በመላው ዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በመሬት መናወጦች፣ በሐይለኛ አውሎ ነፋሶችና በበሽታዎች እየሞቱና በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እየተነሱ በየስፍራው የሚያደርጉዋቸው ጦርነቶች ማብቂያ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ጸረ ክርስቶስ በቅርቡ ወደፊት በሚገለጥበትና እንዲህ ያለው የትርምስ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን አጣዳፊ ችግሮች በሚፈታበት ጊዜ ብዙ ሰዎች ይከተሉታል፡፡ ያን ጊዜ ይህም በዚህ ምድር ላይ በሚወርዱት እጅግ አስፈሪ መቅሰፍቶች ይታጀባል፡፡ በመጨረሻም ይህ ዓለም እግዚአብሄር በሚያመጣቸው በእነዚህ መቅሰፍቶች ሙሉ በሙሉ ይጠፋል፡፡
 
እግዚአብሄር አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይፈጥርና ከሐጢያት ለዳኑት ያወርሳቸዋል፡፡ እግዚአብሄር አዲስ ሰማይና ምድር የሚፈጥርበት ዓላማ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ ለተወለዱት ለማውረስ ነው፡፡ በቅርቡ እግዚአብሄር የመጀመሪያውን ዓለም ያጠፋና ሁለተኛውን ዓለም ያመጣል፡፡ የጥንት ዳይኖሰሮች እንደጠፉ ሁሉ ይህ ዘመናዊው ሳይንሳዊ ሥልጣኔም እንዲሁ ይጠፋል፡፡ እኛም እግዚአብሄር ያመጣውን የአዲሱን ዓለም አዲስ ጅማሬ በራሳችን ዓይኖች እናያለን፡፡
 
አሁን እንዴት ልንኖር እንደሚገባን ማሰብ አለብን፡፡ በአሁኑ ምንባብ ላይ እንደተመዘገበው ሊመጡ ባሉት መቅሰፍቶች ሁሉ ማመንና በእምነት ለቀጣዩ ዓለም እየተዘጋጀን ቀሪውን ሕይወታችንን ለእግዚአብሄር ጽድቅ መኖር አለብን፡፡ የራዕይን የትንቢት ቃል ማወቅ አለበብን፡፡ አሁን ይህንን የምለው ቀኑ ሲመጣ የደረሳችሁበት ዕውቀት ሁሉ ለእምነታችሁ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ማስረጃ ስለሚሆን ነው፡፡
 
በማርስና በጁፒተር መካከል ከተበታተኑት አስትሮይዶች ጀምሮ በማይታወቁ ዑደቶች ውስጥ እስካሉት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ጅራታም ኮከቦች ድረስ ከምድር ጋር የመጋጨት አቅም ያላቸው የሕዋ ነገሮች በጥቅሉ ‹‹ወደ ምድር የተቃረቡ ነገሮች›› ተብለው ይጠራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ናሳ በሶላር ሲስተም ውስጥ ብቻ 893 የሚታወቁ ወደ ምድር የተቃረቡ ነገሮችን ዝርዝሮች አስታውቋል፡፡ ወደ ምድር ከቀረቡት ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ከምድር ጋር ቢጋጭ በዚህ ግጭት የሚፈጠረው ውድመት ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ አውዳሚው ግጭት ምናልባትም በሺህዎች የሚቆጠሩ የኒውክሌር ቦምቦች በአንድ ላይ ከሚያመጡት ጥፋት የላቀ ነው፡፡
 
ያን ጊዜ በዚህች ምድር ላይ ምን እንደሚከሰት አስቡ፡፡ የምድር ጥብቅ ደኖች፣ ውሃና መርከቦች ይወድማሉ፡፡ ስለዚህ የሰው ዘር በሙሉ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመንና ለዘላለም ሕይወት እየተዘጋጁ ሕይወታቸውን መኖር አለባቸው፡፡
 
የተፈጥሮ መቅሰፍቶች በዚህች ምድር ላይ በሚወርዱበት ጊዜ የጸሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት ሲሶ እንደሚጨልሙ ነግሮናል፡፡ ይህንን የሚያውቁት ግን ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ የሚያምኑትም በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑና እውነቱን የሚሰብኩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡
 
አእምሮዋችን መንቃት አለበት፡፡ እነዚህ መቅሰፍቶች በእርግጥም ይመጣሉ፡፡ ቀሪ ሕይወታችንን በምን ዓይነት እምነትና ቆራጥነት መኖር እንደሚገባን ማወቅ አለብን፡፡ እናንተና እኔ የዛሬው ዘመን ከታላቁ መከራ አንድ እርምጃ ብቻ የራቀ እንደሆነ ማመን አለብን፡፡ ቀሪውን ሕይወታችንንም በልባችን ውስጥ ምንም ዓይነት የጥርጥር ፍንጭ ሳይኖር መኖር አለብን፡፡
 
አሁን ይህ መከራ እንደሚመጣ በሚናገረው የትንቢት ቃል በማመን የማንኖር ከሆንን ልባችን ባዶ ይሆናል፡፡ ዓላማችንም ይከስራል፡፡ በሕይወት ጭንቀቶችም ሽባዎች እንሆናለን፡፡ ይህ መሆን የለበትም፡፡ ይህንን ዓለም ፈጽሞ ትተን የማንኖር ይመስል በዚህ ዓለም ላይ ተስፋችንን በማኖር መኖር የለብንም፡፡ ትንሽ ሳይንሳዊ ዕውቀት ያላቸው ብዙዎች ይህ ዓለም ተስፋ እንደሌለው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ እግዚአብሄር በእርግጥም ይህንን ዓለም ያጠፋዋል፡፡
 
እግዚአብሄር አዲሱን የኢየሱስ መንግሥት በመስራት ጻድቃን በውስጡ እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ሰዎች ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፡፡
 
በእግዚአብሄር ፊት የራሳችንን ፈቃድና አስተሳሰቦች መጣልና በትህትና የእርሱን የትንቢት ቃል መቀበልና ማመን አለብን፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ልንሰብክና ከዚያም ጌታችን ሲመጣ ልንገናኘው ይገባናል፡፡ ለዚህ የእግዚአብሄር ሥራ እንኑር፡፡ ጌታ ወደዚህ ምድር ሲመለስ አዲስ ሕይወት እንቀበላለን፡፡ አካሎቻችንም እርሱን መስለው ይለወጣሉ፡፡ እኛም እርሱ እንደነገረን በእርሱ አዲስ ዓለም ውስጥ እንኖራለን፡፡ 
 
የጌታን መምጫ ትክክለኛ ቀንና ጊዜ አናውቅም፡፡ ነገር ግን የዓለምን ምልክቶች በማየት በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመዘገቡት መቅሰፍቶች በሙሉ ወደ እኛ በጣም እየተቃረቡ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በተነበየውና የደህንነትን መንገድ ባሳየን አምላክ እናምናለን፡፡