Search

خطبے

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-18] የሕብስቱ ገበታ፡፡ ‹‹ ዘጸዓት 37፡10-16 ››

የሕብስቱ ገበታ፡፡
‹‹ ዘጸዓት 37፡10-16 ››
‹‹ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ቁመቱም አንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ፡፡ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት፡፡ በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት፡፡ አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ፡፡ ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ፡፡ ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው፡፡ ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፣ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን፣ ጽዋዎቹንም፣ መቅጃዎችንም ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው፡፡››
 
 

በልቦቻችንን ውስጥ ክፈፍን በማድረግ የሕይወትን እንጀራ የሚመገቡ ሰዎች መሆን አለብን፡፡ 

 
የሕብስቱ ገበታ
 
በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከሚገኙት ዕቃዎች አንዱ የሆነው የሕብስት ገበታ ከግራር እንጨት የተሰራና በንጹህ ወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡ ርዝመቱ ሁለት ክንድ (3 ጫማ)፣ ቁመቱ አንድ ተኩል (2.2 ጫማ)፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ (1.5 ጫማ) ነበር፡፡ በሕብስቱ ገበታ ላይ ሁልጊዜም 12 ሕብስቶች ይቀመጡበታል፡፡ እነዚህን ሕብስቶች መብላት የሚችሉት ካህናቶች ብቻ ነበሩ፡፡ (ዘሌዋውያን 24፡5-9)
 
ከሕብስቱ ገበታ ባህሪያቶች መካከል በዙሪያው ሁሉ አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ ያለው መሆኑ፣ በዚህ ክፈፍ ዙሪያ ሁሉ የወርቅ አክሊል የተደረገ መሆኑ፣ በአራቱም ማዕዘኖች አራት የወርቅ ቀለበቶች መደረጋቸው፣ ቀለበቶቹም ገበታውን ለማጓጓዝ የሚያገለግሉና ከግራር እንጨት ተሰርተው በወርቅ የተለበጡ መሎጊያዎችን የያዙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በገበታው ላይ ያሉት ዕቃዎች፣ ወጭቶች፣ ጽዋዎች፣ ጭልፋዎችና መቅጃዎች ሁሉም ከወርቅ የተሰረሩ ነበሩ፡፡
 
ዘጸዓት 37፡11-12 ይህንን መዝግቦዋል፡- ‹‹በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፡፡ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት፡፡›› በእግዚአብሄር ቤት ቅድስት ስፍራ ውስጥ የሚገኘው የሕብስት ጠረጴዛ የአንድ ጋት ያህል ከፍ ያለው ክፈፍ ነበረው፡፡ በክፈፉም ዙሪያ የወርቅ አክሊል ተደርጎለት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን እንዲህ ያለ ክፈፍ እንዲያደርግ ያዘዘው ለምንድነው? ይህ ሳንቲ ሜትር ያህል ርዝማኔ ያለው የጋት ክፈፍ በገበታው ላይ ሕብስት እንዳይወድቅ የሚከላከል ነበር፡፡
 
በሕብስቱ ገበታ ላይ ያለውን ሕብስት መብላት የሚችሉ ካህናቶች ብቻ እንደሆኑ ሁሉ ይህንን ሕብስት በመንፈሳዊ መንገድ መብላት የሚገባንም እኛ ነን፡፡ ይህንን ሕብስት መብላት የሚችሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም በማመን ከሐጢያት የዳኑና የዘላለምን ሕይወት የተቀበሉ ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ደህንነታቸው አድርገው ያመኑ ብቻ ናቸው፡፡
 
የጋት ያህል ርዝመት ያለው ክፈፍ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚገኘው የሕብስቱ ጠረጴዛ ስለተደረገ ሕብስቱ ተንሸራቶ እንዳይወድቅ ማረጋገጫ ሆንዋል፡፡ በየሰንበቱ ትኩስና አዲስ የተጋገረ ሕብስት በገበታው ላይ ይቀመጣል፡፡ የአንድ ጋት ርዝመት ያለው ክፈፍ በሐብስቱ ጠረጴዛ ዙሪያ የተሰራ የመሆኑን እውነት የተለየ ትኩረት ልናደርግበት ይገባናል፡፡ ክፈፉም ዙሪያውን በውርቅ አክሊል ተከቦዋል፡፡
የሕብስቱ ጠረጴዛ ክፈፍ ደህንነትን የሚሰጠንንና የዘላለምን ሕይወት እንድንቀበል የሚያስችለንን የእግዚአብሄር ቃል በልቦቻችን ውስጥ መያዝ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ ይህም ለመገናኛውም ድንኳን የመግቢያ በር ጥቅም ላይ የዋሉት የሰማያዊ፣ የሐምራዊ፣ የቀይ ማግና የጥሩ በፍታ መንፈሳዊ እምነት ሊኖረን የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በመስቀሉ ደም ስናምን ብቻ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች የሆኑት በእነዚህ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ ውስጥ በተገለጠው በዚህ እውነት የሚያምኑ ብቻ እንደሆኑ ከዚህ መገለጥ እንገነዘባለን፡፡
 
በዚህ መንገድ እስካላመንን ድረስ ከጌታ ጋር አንዳች ዕድል ስለማይኖረን የሕይወትን እንጀራ የምንሻ ሰዎች ካለን በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምን እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ተጨባጩ የደህንነት ወንጌል የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ብቻ እንደሆነ ማመን አለብን፡፡ በአጭሩ እግዚአብሄር እየነገረን ያለው ነገር የደህንነት ቃል ከእኛ እንዳይንሸራተት በልቦቻችን ውስጥ የእምነትን ክፈፍ ማድረግ የሚገባን መሆኑን ነው፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ለእኛ ተሰጠን ከጥንቷ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ከዚህ ከጥንቷ ቤተከርስቲያን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሄር በዚህ ወንጌል የሚያምኑትን ሰዎች ሐጢያቶች አንጽቶዋል፡፡ ዛሬም እንደ ቀድሞው እግዚአብሄር በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሚያምኑትን ነፍሳቶች እንደሚያድን እናያለን፡፡ እኛ በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር በተገለጠው እውነት በማመን ድነናል፡፡ እግዚአብሄርም ክፈፉን በልቦቻችን ውስጥ በመስራት በመንፈሳዊ ሁኔታ እንድንኖር አስችሎናል፡፡
 
ጌታ በሰጠን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመናችን የዘላለምን ሕይወት አግኝተናል፡፡ በዚህ የእውነት ወንጌልም የሕይወትን እንጀራ ከሌሎች ጋር መጋራት ችለናል፡፡ የእግዚአብሄርን የጽድቅ ሥራዎች ማገልገልም ችለናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እያመንን እንኳን ጊዜ ሲነጉድ ይህን የወንጌል እውነት አጥብቀን መያዝ ተስኖን ብንለቀው ሕይወታችንን አጣን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሁልጊዜ በእምነት እያሰላሰልን በልቦቻችን ውስጥ የእምነትን ክፈፍ ማቆም አለብን፡፡
 
 

በልቦቻችን ውስጥ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የሚያምን እምነት ሊኖር ይገባል፡፡ 

 
ሰዎች በዚህ እውነት የማያምኑ ከሆኑ ከሐጢያቶቻቸው ሊድኑ አይችሉም፡፡ በእርግጥ እንደዳኑ ያምኑ ይሆናል፤ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ልቦቻቸው በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ የተገለጠውን የውሃና የመንፈስ ወንገል ስላልያዙ አለ የሚሉትም ይህ ደህንነት ሕጸጽ ያለበት ነው፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል እውነት መሆኑን አለማመን ጌታን ከመተው ጋር የሚመሳሰል ሐጢያት ነው፡፡ የሕይወት እንጀራ የግላችን ልናደርገው የሚያስፈልግ ነገር ብቻ ሳይሆን ወደ አፋችን አስገብተን የምናኝከው፣ የምናላምጠውና እውነቱን የእኛ የምናደርግበት አንዳች ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን እውነት ሳናምንና በልቦቻችን ውስጥ ሳንይዝ በምንሰማራበት ጊዜ የደህንነት እውነት ወዲያውኑ ከልቦቻችን ውስጥ ብን ብሎ ይጠፋል፡፡
 
አስቀድማችሁ ከሐጢያት ድናችሁ ሳለ እንዲህ ያለውን የከበረ ደህንነት እንዴት ልታጡት እንደምትችሉ ግራ ተጋብታችሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብዙዎች መጀመሪያ ላይ እውነቱን በደስታ ቢቀበሉም የእግዚአብሄርን ቃል አጥብቀው ባለመያዛቸው ፍጻሜያቸው ሞት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የእምነት ሥር በእውነት ወንጌል ላይ አልተተከለምና፡፡
 
ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ኢየሱስ ‹‹በዘሪው ምሳሌ›› ውስጥ ስለ አራት ዓይነት የልብ መሬቶች እንዳሉ ተናግሮዋል፡፡ (ማቴዎስ 13፡3-9፤18-23) በዚህ ምሳሌ ውስጥ የእግዚአብሄር እውነት ዘሮች በአራት የተለያዩ የሰው ዘር የልብ መሬቶች ላይ ተዘርተው ነበር፡፡ የመጀመሪያው መሬት መንገድ ዳር ነበር፡፡ ሁለተኛው መሬት ጭንጫ ነበር፡፡ ሦስተኛው መሬት እሾማ ነበር፡፡ አራተኛው መሬት መልካም መሬት ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያዎቹ በሦስቱ መሬቶች ላይ የወደቁት ዘሮች ፍሬ አላፈሩም፡፡ ፍሬ ያፈሩት በአራተኛው መሬት ማለትም በመልካሙ መሬት ላይ የወደቁት ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ብዙ ሰዎች እውነተኛ የደህንነት እውነት የሆነውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በአንድ ወቅት ሰምተው ቢቀበሉም መሃከል ላይ ደህንነታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የልባችን መሬት ጥሩ ካልሆነ ጌታ የሰጠንን ደህንነት ልናጣ እንችለለን፡፡
 
በልቦቻችን ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ በመጣው ደህንነት የምናምን ከሆነ የልቦቻችን መሬት ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች እምነታቸው በእግዚአብሄር ላይ አጥብቆ ባለመተከሉ የተነሳ እምነታቸውን ለመደገፍ አቅም ስለሚያንሳቸው ደህንነታቸውን ሲያጡ እንመለከታለን፡፡ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ መቆየት፣ በየቀኑ የሕይወትን እንጀራ መመገብና በእምነት ማደግ ያለብን ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው እውነት እምነታችን ያድግ ዘንድ በየቀኑ እየተንከባከበን ነው፡፡
 
በየቀኑ የተቀበልነውን የሐጢያት ስርየት በልቦቻችን ውስጥ ማጽናት አለብን፡፡ በልቦቻችን ውስጥ መገኘት ያለበት እውነት በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ደህንነት ነው፡፡ ይህ የደህንነት እውነት የሐጢያት ስርየትን በተቀበሉት ሰዎች ልቦች ውስጥ አለ፡፡ በዚህ በውሃና በመንፈስ ወንጌል ላይ ያለንን እምነታችንን በማደስ በየቀኑ እንደ እግዚአብሄር ልጆች መኖር እንችላለን፡፡
 
ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑትም ቢሆኑ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውን የእግዚአብሄርን የጽድቅ ወንጌል በየቀኑ ማሰላሰልና እምነታቸውን ማጽናት አለባቸው፡፡ ለምን? የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሁልጊዜ አጥብቀን ካልያዝነውና ካላጸናነው በማንኛውም ጊዜ ልናጣው እንችላለን፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ ለተበተኑት አይሁዶች የተናገረውን ሁልጊዜም ማስታወስ አለብን፡- ‹‹ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል፡፡›› (ዕብራውያን 2፡1)
 
ዛሬ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በሚያውቁት መካከል እንኳን በወንጌል ላይ ያላቸው እምነት ከጊዜ መንጎድ ጋር የደበዘዘባቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ የሆነው አስቀድመው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ቢያምኑም በቅድስቱ ስፍራ የሕይወትን እንጀራ ያለማቋረጥ መብላት ስለተሳናቸው ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ልቦቻቸው በእውነተኛው እምነት አልጠራም፡፡
 
በዚህ ዓለም ላይ እርሾ ያለበት እንጀራ ማለትም ከገዛ ሥጋቸው የመነጩ ትምህርቶችን በመመገብ ጻድቃንን ለመግደል የሚሞክሩ ብዙ የሰይጣን አገልጋዮችም አሉ፡፡ የሐሰት ወንጌል ወደ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ከገባ እውነት ከውሸቶች ጋር ይቀላቀልና ምዕመናንን በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ወደማያገኙበት ሰውነት ይለውጣቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እውነቱን ያውቃሉ፤ ነገር ግን አያምኑበትም፡፡ ምክንያቱም የእምነት ክፈፋቸውን አልሰሩምና፡፡ ከዚህ የተነሳ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያቱ እንደዳነ ሰው አይሆኑም፡፡ ምሳሌ 22፡28 እንዲህ ይላል፡- ‹‹አባቶችህ የሰሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፡፡››
 
ስለዚህ የእምነታችንን ድንበር አለማፍለስ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የእውነተኛ እምነት ድንበራችንን በግልጽ ማስቀመጥና ጌታ እስከሚመጣ ድረስ መጠበቅ አለብን፡፡ የሕይወትን እንጀራ ሁልጊዜ የምንመገበው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጌታ በልባችን ማዕከል ውስጥ የሚያድረውም ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እኛም የዘላለም ሕይወት ሊኖረን የሚችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ምንም ያህል የተትረፈረፈ እንጀራ ቢሰጠንም ክቡርነቱን ካልወደድነውና በልቦቻችን ውስጥ አጥብቀን ካልያዝነው ወይም የልቦቻችንን ክፈፍ አስወግደን እንጀራው ከገበታው ላይ ተንሸራትቶ እንዲወድቅ የምናደርግ ከሆነ ፍጻሜያችን የጥፋት ልጆች መሆን ይሆናል፡፡
 
አንዳንዶቻችን የሐጢያት ስርየታችንን የተበልነው በቅርቡ ነው፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰሙ አስርት ዓመታቶች ቢሆናቸው ነው፡፡ በየቀኑ የምንሰማው ስለ ውሃውና ስለ መንፈሱ ወንጌል በመሆኑ አንዳንዶቻችን የውሃውና የመንፈሱ ‹‹ውሃ›› ወንጌል የሚለውን ቃል ስንሰማ ወዲያውኑ መታከታችን አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም የእውነተኛውን ወንጌል እንጀራ በመብላት መቀጠል አለብን፡፡ ይህንን ለምን ያህል ጊዜ ማድረግ አለብን? ጌታ እስከሚመለስበት ቀን ድረስ ማድረግ አለብን፡፡
 
እኔ ሁልጊዜ በተደጋጋሚ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ስለምሰብክ አንዳንዶቻችሁ ታጉረመርሙ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለም-ን በዚህ መንገድ እንደምሰብክ ማወቅ ያስፈልጋችኋል፡፡ ይህንን የማደርገው የእግዚአብሄር ሰራተኞች እንሆን ዘንድ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በማሰላሰል እምነታችን ይበልጥ መጠንከር ያለበት በመሆኑ ነው፡፡ እኛ በዚህ ዘመን ለሚኖሩ ነፍሳቶች ታማኝ ጠባቂዎች የመሆንን ሚና መጫወት አለብን፡፡ ዳግመኛ ለተወለዱ ነፍሳቶችም ይህ እውነተኛው የውሃና የመንፈስ ወንጌል የሕይወት እንጀራና እውነተኛ የእምነት ምግብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እንጀራ በየቀኑ መመገብ ይኖርብናል፡፡ ለራሳችን ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም ደግሞ የራሳቸውን የሐጢያት ስርየት ይቀበሉ ዘንድ በየቀኑ ልናቋድሳቸው ይገባናል፡፡
 
ጻድቃን የሚመገቡት እንጀራ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ቃል ማሰራጨትና ሰዎችን ከጨለማው ሥልጣን አውጥቶ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት ማፍለስ ነው፡፡ (ዮሐንስ 4፡34፤ ቆላስያስ 1፡13) የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል እንጀራ መመገብ ችላ የምንል ከሆነ መታመማችን ወይም መሞታችን የማይቀር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከእምነታችን መድከም የተነሳ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለን እምነት ሊደክም ይችላል፡፡ ነገር ግን በችግር ጊዜ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል አጥብቃችሁ ከያዛችሁ ነፍሳችን ይበልጥ ጠንካራ ለመሆን ዕድል ታገኛለች፡፡
 
ይህንን የእውነት ወንጌል ስናደምጥና ስናሰላስል አብዝተን በሰማነው ቁጥር ነፍሳችን አብዝታ ትባረካለች፡፡ እምነታችንም ይበልጥ ይጠነክራል፡፡ በልቦቻችን ውስጥም የደስታ ብርታት አብዝቶ ሲነሳ እናያለን፡፡ በየቀኑ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መሰማት፣ ማጽናትና በዚህ ወንጌል ላይ ያለንን እምነታችንን ማጥራት ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከብር ዝገትን አስወግድ፤ ፈጽሞም ይጠራል፡፡›› (ምሳሌ 25፡4) እምነታችን መጥራት ያስፈልገዋል፡፤ ማለትም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመስማት መቀጠል፣ በልባችን ውስጥ መቀበልና በየጊዜውም ማሰላሰል ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም በሕይወት እንድንኖር የሚያደርገን የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነውና! ኢየሱስ በጌታ ጸሎት ውስጥ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን›› እንዳለ ጌታችን በእርግጥም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ሰጥቶናል፡፡ በዚህ መንገድ እንድንጸልይ የነገረን ለዚህ ነው፡፡
 
እግዚአብሄር ወደሰጠን የሐጢያት ስርየት ደህንነት ስንመጣ እምነታችን ከሐጢያት ከመዳናችን በፊት እንዴት እንደነበር ግልጽ ማድረግ አለብን፡፡ ‹‹ይህንን እውነት ከማወቄ በፊት ከሐጢያት አልዳንሁም ነበር፡፡›› በወቅቱ በኢየሱስ ብናምንም ከሐጢያት የዳንን እንዳልነበርን በግልጽ ማመን አለብን፡፡ ‹‹በዚያን ወቅት ሙሉ በሙሉ ከሐጢያት አልዳንሁም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል መስማት ስቀጥል በልቤ አመንሁበት፡፡
 
ከዚህ ቀደም ኢየሱስ አዳኜ መሆኑን ባምንም ደህንነቴ ፍጹም አልነበረም፡፡ አሁን ግን እውነተኛውን የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማድመጥ በእርግጥ ድኛለሁ፡፡ አሁን በእርግጥም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምናለሁ፤ ከልቤ አምነዋለሁ፡፡›› የእውነተኛ ደህንነት ስጦታ ከሰማይ ወደ ልባችሁ የሚወርደው ጌታ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ደሙ ሙሉ በሙሉ ከሐጢያት እንዳዳናችሁ ስታውቁና ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ በእውነት የሚያምን ይህ እምነት የሚያድናችሁ እውነተኛ እምነት ነው፡፡
 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው የውሃና የመንፈስ ወንጌል ከዚህ በፊት ከነበረን እምነት የተለየ ነው፡፡ እኛ በዚያን ወቅት ፍጹም በሆነው በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ፋንታ በመስቀሉ ደም ወንጌል ብቻ ማመንና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን መጀመሪያ ላይ ተመሳሳይ ይመስል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይህንን የውሃና የመንፈስ ወንጌል ከማወቃችሁ በፊት በመስቀሉ ደም ብቻ ስታምኑ አልነበረምን? ያን ጊዜ ሐጢያቶቻችሁ በሙሉ ተወግደው ነበርን? በጭራሽ! ኢየሱስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ብቻ ስታምኑ አሁንም በልቦቻችሁ ውስጥ ሐጢያቶች አሉ፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በሚያምነው እምነትና በመስቀሉ ብቻ በሚያምነው እምነት መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፡፡
 
ግልጽ የሆነው ልዩነት በመስቀሉ ደም ብቻ የሚያምኑ አለመዳናቸውና በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑት ግን ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ መዳናቸው ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳቸው ያለ ምንም መሳሳት የተለየ ነው፡፡ ተራ ሰዎች ግን ይህንን አያስተውሉትም፡፡ ሁለቱ ወንጌሎች ተመሳሳይ መስለው ቢታዩም በሁለቱ መካከል ሊጠብብ የማይችል ትልቅ የእምነት ክፍተት አለ፡፡ የዘላለምን ሕይወት እንድናገኝ ወይም እንድናጣ የሚያደርገን ጥቂት ልዩነት በኢየሱስ ጥምቀት ማመን አለማመናችን በሚሆንበት ጊዜ በእነዚህ በሁለቱ እምነቶች መካከል ፈጽሞ ሊታረቅ የማይችል ልዩነት እንዳለ መረዳት እንችላለን፡፡
 
ከሐጢያት የምንድንበትን ድንበር የሚያዋቅረው እምነት በትክክል ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡ ከሐጢያት ለመዳን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ማመን አለብን፡፡ ይህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የሐጢያት ስርየት እውነት ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከማመናችሁ በፊት በእርግጥም የዳናችሁ እንዳልነበራችሁና አሁን በእርግጥ በእውነተኛው ወንጌል ከልባችሁ እንደምታምኑ ስትቀበሉ ግልጽ የሆነው የደህንነት አቋም የእናንተ ይሆናል፡፡
 
በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከልባችሁ የምታምኑ ከሆነ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በመስማትና በማመን የሐጢያቶቻችሁን ስርየት እንደተቀበላችሁ ይህንን በግልጽ በእግዚአብሄር ፊት ማመን አለባችሁ፡፡ አሁን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት ካመናችሁ ማስረጃውን ያለ ምንም መሳሳት በልቦቻችሁ ውስጥ ታገኙታላችሁ፡፡
 
በእግዚአብሄር ፊት እምነታችንን በጥንቃቄ መመርመር አለብን፡፡ እምነታችንን መመርመር አያሳፍርም፡፡ ለመጀመሪያ በኢየሱስ ካመናችሁበት ጊዜ ጀምሮ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከሙሉ ልባችሁ ለማመን አምስት ዓመት ወስዶባችሁ ከሆነ ፈጽሞ የሚያሳፍር ነገር የለም፡፡ ለመዳን 10 ዓመታት ፈጅቶባችሁ ከሆነ ይህ በጭራሽ የሚያሳፍር አይደለም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው በረከት ነው፡፡
ነገር ግን እውነታው የሚያሳየው ከሐጢያት እንደዳኑ የሚያስመስሉ ብዙዎች መኖራቸውን ነው፡፡ ሆኖም ሁሉን የሚመረምረው መንፈስ ቅዱስ እምነታቸውን አያረጋግጥላቸውም፡፡ ምክንያቱም በቅንነት ግልጽ የሆነ የደህንነት መስመር አላሰመሩምና፡፡ አሁንም ቢሆን የደህንነታችንን የድንበር መስመር በግልጽ ማስመር ጠቢብነት ነው፡፡ እዚህ ላይ አስፈላጊው ነገር የዳንበትን ትክክለኛ ቀን ማወቁ ሳይሆን ከመዳናችን በፊትና በኋላ ባለው መካከል በግልጽ መለየትና ፍጹም የሆነውን እምነታችሁን በግልጥ መመስከር ነው፡፡
 
 

የእምነት አባቶቻችንም አሁን እኛ በምናምነው በዚሁ ወንጌል አምነዋል፡፡ 

 
የእስራኤል ሕዝብ ቀይ ባህርን ከተሻገሩ በኋላ ወደ ከንዓን ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ለመሻገር በፈለጉ ጊዜ በደህንነት መሻገር የቻሉት በመጀመሪያ የእግዚአብሄርን የምስክር ታቦት የተሸከሙትን ካህናት በተጨባጭ በመከተላቸው ብቻ ነው፡፡ ‹‹ኦ! ለካስ የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር የምችለው እንዲህ ነው›› ብለን የምናስብና በተጨባጭ የማንሻገር ከሆነ ወደ ከንዓን ምድር መግባት አንችልም፡፡ ምክንያቱም በወንዙ ማዶ እንቀራለንና፡፡ ወደ ከንዓን ምድር ለመግባት በጌታ ላይ ባለን እምነት ቀይ ባህርንና የዮርዳኖስን ወንዝ ፈጽመን መሻገር አለብን፡፡
 
በመንፈሳዊ አነጋገር የዮርዳኖስ ወንዝ የሞትና የትንሳኤ ወንዝ ነው፡፡ እኛን ከሐጢያት ያዳነን እምነት ‹‹ወደ ሲዖል መጣል ነበረብኝ፤ ነገር ግን ጌታ ወደዚህ ምድር መጥቶ በጥምቀቱና በመስቀሉ ደም አዳነኝ›› ብሎ የሚያምን እምነት ነው፡፡ ጌታችን እኛን ፈጽሞ ለማዳን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ በመስቀል ላይም ደሙን አፈሰሰ፡፡ በዚህ መንገድ ሐጢያቶቻችንን ወስዶ በእኛ ፋንታ የራሱን ሕይወት አሳልፎ በመስጠት የሐጢያትን ዋጋ ከፈለ፡፡ አሁን በዚህ እውነት ማመንና በልቦቻችን ውስጥ የእምነትን መስመርና የደህንነትን መስመር በግልጽ ማስመር አለብን፡፡
 
የእግዚአብሄርን ቃል ስሰብክ በእርሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ አሁንም ድረስ በልቦቻችን ማዕከል ውስጥ የደህንነትን መስመር በግልጽ ያላሰመሩና ጌታን መከተል ያልቻሉ ብዙዎችን አያለሁ፡፡ ‹‹በዚህ ምድር ላይ ይህንን መስመር ያሰመረ አንዳች ሰው አለን? ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን አድርጓልን? ጴጥሮስ ይህንን አድርጓልን? ማንም ይህንን አድርጎ አያውቅም›› በማለት ለራሳቸው ማማኻኛ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ጳወሎስና ጴጥሮስ ያሉ የእምነት ሐዋርያቶች በሙሉ ይህንን የደህንነት መስመር አስምረዋል፡፡
 
ጳውሎስ ይህንን መስመር ያሰመረው ወደ ደማስቆ ሲጓዝ ስለነበር ከዚህ የተነሳ ብዙውን ጊዜ ‹‹በአንድ ወቅት ባለፉት ዘመናት ወይም በፊት›› የሚሉትን ቃላቶች ‹‹አሁን›› ከሚለው ቃል ጋር በማነጻጸር በተደጋጋሚ ጠቅሶዋቸዋል፡፡ ጴጥሮስም እንደዚሁ ከላይ ያሉትን እነዚያኑ ቃሎች ተናግሮዋል፡፡ (1ኛ ጴጥሮስ 2፡10,25) የመሰከራቸውን ምስክርነቶች ስንመለከት እርሱም ይህንኑ መስመር እንዳሰመረ ማየት እንችላለን፡፡ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሄር ልጅ ክርስቶስ ነህ፡፡›› (ማቴዎስ 16፡16) ‹‹ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአበሄር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፡፡ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው፡፡›› (1ኛ ጴጥሮስ 3፡21) ጳውሎስና ጴጥሮስ ሁለቱም ከደህንነታቸው በፊትና በኋላ ባለው መካከል የእምነትን መስመር በግልጽ አስምረዋል፡፡
 
ስለዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማመናችሁ ወይም የአለማመናችሁ ይህ ጥያቄ የሌላ ሰው ችግር ሳይሆን በአብዛኛው የገዛ ራሳችሁ ነፍስ ችግር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የእግዚአብሄር ባሮች በሙሉ የሐጢያት ችግር እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ ይህ የሁላችንም አስፈላጊ ችግር ስለሆነ እኛው ራሳችን በእምነት ልንፈታው ይገባናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አምነን ከሙሉ ልባችን የሐጢያትን ችግር ስንፈታ እግዚአብሄር በአያሌው ይደሰታል፡፡ እግዚአብሄርን ማስደሰት ትፈልጋላችሁን? እንግዲያውስ ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር ቢኖር ሐጢያተኝነታችሁን ተረድታችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ይህንን ችግር መፍታት ነው፡፡ ይህንን ያህል ዘመን ገና ያልዳናችሁ ከሆናችሁ ‹‹አቤቱ ገና አልዳንሁም›› በማለት መናዘዝ ትችላላችሁ፡፡
 
ኢየሱስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል፡፡›› (ማቴዎስ 16፡19) እኛ በመጀመሪያ ‹‹እግዚአብሄር በውሃና በመንፈስ አዳነኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከልቤ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እውነት አምናለሁ፡፡ ጌታ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት እንዳዳነኝ በጭራሽ አልጠራጠርም›› ብለን ማመን አለብን፡፡
 
ሁላችንም የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ወደ ልቦቻችን መቀበል አለብን፡፡ ‹‹እኔ በዚህ ወንጌል አምናለሁ፤ ይህ እውነት ስለሆነ ጌታ ከበቂ በላይ ሐጢያቶቼን ስለደመሰሰ አሁን በዚህ ወንጌል አምናለሁ፡፡ እስከ አሁን ድረስ በእምነት አልዳንሁም ነበር፡፡›› በዚህ ሁኔታ በጌታ የተሰጠውን ወንጌል ስናውቅና ስናምን እግዚአብሄር ‹‹እምነትህን እደግፋለሁ›› በማለት ይነግረናል፡፡
 
እግዚአብሄር ፈጽሞ ሊያድነን የሚችለውን የውሃውንና የመንፈሱን እውነት አስቀድሞ ሰጥቶን ሳለ እኛ ግን የደህንነትን መስመር ባናሰምርና በዚህ እውነት በማመን ይህንን ደህንነት ባንቀበል እግዚአብሄርም እንደዳነን አድርጎ አያውቀንም፡፡ እግዚአበሄር በማንነታችን እንጂ በግዴታ ስለማይጫነን ከሙሉ ልባችሁ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የማታምኑ ከሆነ የሐጢያት ይቅርታን አይሰጣችሁም፡፡ በሌላ አነጋገር የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በልባችሁ ውስጥ የማትቀበሉ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በልቦቻችሁ ውስጥ አያድርም፡፡
 
ከውሃውና ከመንፈሱ ወንጌል በስተቀር ሌሎች ወንጌሎች ሁሉ ውሸት ናቸው ብለን እንጥላቸዋለን? ወይስ እነዚህ የሐሰት ወንገሎች አሁንም ጠቃሚ ስለሆኑ እነርሱን አውጥቶ መጣል አያስፈልግም ብለን እናስባለን? ራሳችንን መመርመርና ምን ያህል በትክክል እንደምናምን ማየት ያስፈልገናል፡፡ ለጥቂት ጊዜ ያገለገሉ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ወደተከማቹበት ቦታ ደረስን ብለን እንገምት፡፡ አሁንም ጥቅም ላይ ልናውላቸው እንችላለን ብለን በማሰብ ከእነርሱ አንዳንዶቹን ወደ ቤታችን ይዘናቸው መጣን ብለንም እንገምት፡፡ በኋላ ግን አንዳቸውም እንደማያገለግሉና ጥቅም እንደሌላቸው ተረዳን፡፡ አሁንም ይዘን እናቆያቸዋለን ወይስ እንጥላቸዋለን? ሁሉም ጥቅም እንደሌላቸው ከወሰንን በኋላ ሁሉንም መጣል ይኖርብናል፡፡ አንድ ነገር ፈጽሞ የማይጠቅማችሁ ለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ሰትደርሱ በውሳኔያችሁ መሰረት እንዴት እንደምትጥሉትም ማወቅ አለባችሁ፡፡
 
በምድራዊ ጉዳዮች ላይ ልናደርገው የሚገባን ነገር ይህ ከሆነ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ወደሚመለከት ነገር ስንመጣ ድርጊታችን ምን መሆን ይኖርበታል? በመንፈሳዊ ጉዳዮቻችን ውሸቶችን ለመጣል ይበልጥ ቁርጠኞች መሆን አለብን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለንን እምነታችን በመስቀሉ ደም ብቻ ከሚያምነው የሐሰት እምነት የሚለይ ግልጽ መስመር ማስመር አለብን፡፡ በመስቀሉ ደም ላይ ብቻ ማመን ጨርሶ ደህንነትን ሊያመጣልን እንደማይችል ማወቅ አለብን፡፡ ይህንን እንከን ያለበት ትምህርት ቆርጠን መጣል አለብን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ትክክለኛው ወንጌል የትኛው ነው? የመስቀሉ ደም ብቻ ወንጌል ነውን? ወይስ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው? በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምነውና ከሐጢያቶቻችሁ ያዳናችሁ እምነታችሁ እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡
 
በአጭሩ ሁለት ዓይነት ክርስቲያኖች አሉ፡፡ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሚያምኑና ይህንን የማያምኑ ነቸው፡፡ ሁለቱም ተመሳሳይ ሕይወት የሚኖሩ ይመስል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እውነቱ ሁለቱም ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸው ነው፡፡ እንዲያው በአጋጣሚ ከዚህ ቀደም ስታምኑት የነበረው ፍጹም ያልሆነው ወንጌል አሁንም አንዳች ጠቀሜታ ያለው ይመስላችኋልን? በኋላ በአንድ ወቅት ሊጠቅመን ይችላል ብላችሁ በማሰብ አሁንም ድረስ የሙጥኝ ብላችሁ ይዛችሁታልን?
 
የዚህ ዓይነቱ እምነት የውሸት እምነት ነው፡፡ ከሰው ሰራሽ አስተሳሰቦች የፈለቀ አንዳች ነገር ስለሆነ ያለፈውን ያረጀ ስልቻችሁን በሙሉ መጣል አለባችሁ፡፡ በልቦቻችሁ ውስጥ ችግሮች ያሉት እውነት ያልሆኑትንና ውሸቶችን አሁንም ድረስ ስላልጣላችሁ ነው፡፡ የአምላክን ቃል እንድታስወሱ እመክራችኋለሁ፡፡ ‹‹ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይን ዘር አትዝራ፡፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሰራ ልብስ አትልበስ፡፡›› (ዘሌዋውያን 19፡19)
 
 
ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት ያለብን በበሮቹ ውስጥ በማለፍ ብቻ ነው፡፡ 
 
የመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር የተሰራው ከምን ዓይነት ቁሳቁሶች ነው? ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከጥሩ በፍታ ነው፡፡ ከውሃውና ከመንፈሱ የተወለዱ ሰዎች ይህንን የመገናኛውን ድንኳን በር ከፍተው ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት አለባቸው፡፡ ከመገናኛው ድንኳን በር ምሰሶዎች ስር የናስ እግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ የናስ እግሮች የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የደህንነት እውነት መሆኑን እንድናውቅ ያደርጉናል፡፡
 
እነርሱ በእግዚአብሄር ተኮንነን ለሐጢያቶቻችን ከመሞት በቀር ምርጫ ባይኖረንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከውሃና ከመንፈስ ዳግመኛ የመወለድን በረከት በመቀበል የራሱ የእግዚአብሄር ልጆች እንደሆንን ያስተምሩናል፡፡ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት የምንችለው ለመግቢያው በር ጥቅም ላይ ከዋሉት ከአራቱ ማጎች ቀለማቶች በቀዩ ማግ በተገለጠው የኢየሱስ አገልግሎት በማመን ብቻ መዳን እንችላለን የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ መጣል ብቻ ነው፡፡
 
በራሳችን ላይ ያነጣጠሩትን አስተሳሰቦችና እምነት እስካልተውን ድረስ በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው ደህንነት ፈጽሞ ማመን አንችልም፡፡ በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠው እውነት የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ከዚህ ቀደም በመስቀሉ ደም ብቻ ያመንበትንም በራሳችን አስተሳሰቦች ላይ ያተኮረ ስህተት መቀበል አለብን፡፡
 
እግዚአብሄር ቢፈቅድ ወደ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል እውነት ይመራችኋል፡፡ ከሐጢያቶቻቸው ሁሉ ነጽተው የዘላለምን ሕይወት የሚቀበሉት በዚህ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል የሚምኑ ብቻ ናቸው፡፤ የደህንነትን በር መክፈት የምንችለው በዚህ እውነት ከልባችን በማመንና ወደ ቅድስቱ ስፍራ በመግባት ብቻ ነው፡፡
 
ከዚህ ቀደም ይዘችሁት የነበረው አሮጌው እምነታችሁ ስህተት እንደነበር መረዳት ከተሳናችሁ በሐጢያት ቅጣት ትሰቃያላችሁ፡፡ ምክንያቱም መዳን አይቻላችሁምና፡፡ ይህ ከተከሰተ ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባትና የሕይወትን እንጀራ መመገብ የምትችሉት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ወደ ቅድስቱ ስፍራ መግባት ስትችሉ ብቻ ነው፡፡
 
ጌታ ሐጢያቶቻችሁን በሰማያዊው ማግ በጥምቀቱ በማስወገድና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በቀዩ ማግ የሐጢያቶቻችሁን ኩነኔ በመሸከም የእግዚአብሄር ልጆች እንዳደረጋችሁ መረዳት አለባችሁ፡፡ የውሃውና የመንፈሱም ወንጌል ለእናንተ እጅግ የሚያስፈልግ እውነት እንደሆነ በግልጽ መረዳትና ማመን አለባችሁ፡፡ ወደ እግዚአብሄር ቤተክርስቲያን መጥታችሁ የሕይወትን እንጀራ ከጻድቃን ጋር መቋደስ የምትችሉት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል የሰጣችሁ እግዚአብሄር መሆኑን ስታውቁና በዚህ ወንጌል ስታምኑ ብቻ ነው፡፡
 
 

የጌታ ሥጋ የሕይወት እንጀራና የሐጢያት ስርየት ነው፡፡ 

 
ወደ ዮሐንስ 6፡49-53 እንለፍ፡- ‹‹አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም፡፡ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው፡፡ ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፡፡ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡ እንግዲህ አይሁድ፡- ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡›› ኢየሱስ ሥጋውን የሚበሉና ደሙን የሚጠጡ የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው ተናግሮዋል፡፡ ይህ ምንባብ ሁላችንም የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት እንዳለብን ይናገራል፡፡
 
ታዲያ የኢየሱስን ሥጋ የምንበላውና ደሙን የምንጠጣወ እንዴት ነው? የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የምንችለው በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ነው፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ እንደወሰደ በማመን ሥጋውን መብላት እንችላለን፡፡ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን እንደተሸከመና በመስቀል ላይ እንዴት እንደተሰቀለ በማመን ደሙን መጠጣት እንችላለን፡፡
 
በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ በተገለጡት የደህንነት ሥራዎች አማካይነት ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ደምስሶ የራሱ የእግዚአብሄር ልጆች እንዳደረገንም ማመን አለብን፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ከማመናችሁ በፊት ያመናችሁት ነገር ምንም ይሁን ይህ አሮጌው እምነታችሁ ስህተት እንደነበር አውቃችሁ አሁን የኢየሱስን ሥጋና ደም በመያዝና የሕይወትን እንጀራ በመመገብ የእምነትን ክፈፍ መስራት አለባችሁ፡፡
 
ዮሐንስ 6፡53 እንዲህ ይላል፡- ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡›› አሁንም ቢሆን አንዳንድ ሰዎች የሥጋ ወደሙን ትምህርት ለመደገፍ ሲሉ ይህንን ምንባብ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ትምህርት በቅዱስ ቁርባን ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው ሕብስትና ወይን ስርዓቱ በእምነት በሚከናወንበት ጊዜ እውነተኛ ወደሆነ የኢየሱስ ሥጋና ደም ይቀየራል ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ የዮሐንስ 6፡53 ምንባብ ስለ ሥጋ ወደሙ ከመናገር በጣም የራቀ መሆኑን መረዳትና ማመን አለብን፡፡ እንዲያውም የሚናገረው ስለ ውሃውና ስለ መንፈሱ ወንጌል ነው፡፡
 
በቅዱስ ቁርባን ወቅት ተሰልፋችሁ እየጠበቃችሁ ሳለ ካህኑ የሕብስቱን ቁራሽ ወደ አፋችሁ ሲከት ይህ ሕብስት ወደ ኢየሱስ ሥጋነት ይለወጣልን? አይለወጥም! የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የምንችለው ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ የዓለምን ሐጢያቶች በመውሰድ በጥምቀቱ ማንጻቱንና እነዚህን ሐጢያቶችም በመስቀል ላይ ተሸክሞ በመሞት ከሞት እንዳዳነን በማመን ነው፡፡
 
እነዚያ በእምነት የኢየሱስን ሥጋ የሚበሉና ደሙን የሚጠጡ ኢየሱስ በሰማያዊውና በቀዩ ማግ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በመውሰድና የሐጢያት ኩነኔን በገዛ ሥጋው በመሸከም ከሐጢያት እንዳዳነን በሚናገረው እውነት የሚያምኑ ናቸው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና በደሙ ባለን እምነት የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት አለብን፡፡
 
ኢየሱስ ወደ እርሱ የተሻገረለትን ሐጢያቶቻችንን ለመቀበል በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ወደ ማቴዎስ 3፡15-17 እንሂድ፡- ‹‹ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃ ወጣ፡፡ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ፡፡ የእግዚአብሄርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱም ላ ሲመጣ አየ፡፡ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ፡- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፡፡››
 
ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ጽድቅ የፈጸመው በዮሐንስ በተጠመቀና በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ሐጢያቶችን በሙሉ ስለወሰደ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ የዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ወደ አርሱ እንደተሻገሩ በሚናገረው የወንጌል እውነት ላይ ያለን እምነት የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የሚያስችለን እውነተኛ እምነት ነው፡፡
 
ይህንን እውነት ከተረዳችሁት አስቀድማችሁ የኢየሱስን ሥጋ በእምነት በልታችኋል፡፡ የዓለም ሐጢያቶቻችሁ ለአንዴና ለመጨረሻ ወደ ኢየሱስ የተሻገሩ መሆናቸውም እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በሙሉ ልባችሁ ማመን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ እምነት የኢየሱስን ሥጋ እንድትበሉ የሚያስችላችሁ እምነት ነው፡፡ ሐጢያቶቻችሁ በጥምቀቱ አማካይነት ወደ ኢየሱስ ተሻግረዋልን? የኢየሱስን ሥጋ መብላት የምትችሉት ይህንን ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስን ካጠመቀው በኋላ ‹‹እነሆ የዓለምን ሐጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ!›› (ዮሐንስ 1፡29) በማለት ጮኸ፡፡
 
ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት የዓለምን ሐጢያቶች ስለወሰደ ሁሉንም በሥጋው ተሸከመ፤ ተሰቀለ፡፡ ደሙን አፈሰሰና ሞተ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከተሰቀለ፣ እግሮቹና እጆቹ ከተቸነከሩና ደሙን ካፈሰሰ በኋላ ኢየሱስ በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ‹‹ተፈጸመ!›› በማለት ጮኸ፡፡ ከዚያም በሦስት ቀን ውስጥ ከሙታን ተነስቶ 40 ቀን ያህል ከመሰከረ በኋላ ወደተመኘው ሰማይ በትክክል አረገ፡፡ አሁን በእግዚአብሄር አብ ቀኝ ተቀምጦዋል፡፡ ይህንን እውነት ከሙሉ ልባችሁ ታምኑታላችሁን? የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የምትችሉት በዚህ እውነት በማመን ነው፡፡ የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የምንችለው ከሙሉ ልባችን በእውነት ስናምን ነው፡፡ የቅድስቱን ስፍራ እንጀራ መብላት የምንችለው በዚህ እምነት ነው፡፡
 
ጌታችን አብረን በምንሰበሰብበት ጊዜ ሁሉ ሁልጊዜ ሥጋውንና ደሙን እንድናስታውስ አዞናል፡፡ (1ኛ ቆሮንቶስ 11፡26) ስለዚህ አብረን በምንሰበሰብበት ጊዜ ሁሉ የኢየሱስን ሥጋና ደም ማስታወስ አለብን፡፡ በምንሰበሰብበት ጊዜ ሁሉ የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የሚጠበቅብን በእምነት ከሆነ ቅዱስ ቁርባንን እንደ ተለምዶ ሥርዓት አድርገን እንዴት ልናከብረው እንችላለን?
 
እኛ ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን በሥጋው በወሰደበት ጥምቀትና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው የመስዋዕት ደሙ ስለምናምን በየቀኑ ሥጋውንና ደሙን የምናስታውሰው በእምነት ነው፡፡ በየቀኑ የኢየሱስን ሥጋ የምንበላውና ደሙን የምንጠጣው በውሃውና በመንፈሱ እውነት ስለምናምን ነው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡›› (ዮሐንስ 6፡54) እርሱ ሥጋውን የሚበሉትንና ደሙን የሚጠጡትን በመጨረሻው ቀን ያስነሳቸዋል፡፡
እምነታችን የኢየሱስን ሥጋ እንድንበላና ደሙን እንድንጠጣ የማያስችለን ከሆነ የተሳሳተ እምነት መሆኑን ማመን አለብን፡፡ ‹‹ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡ ሕያው አብ እንደላከኝ እኔም ከአብ የተነሳ ሕያው እንደምሆን የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሳ ሕያው ይሆናል፡፡›› (ዮሐንስ 6፡54-57)
 
የጌታን ሥጋ በእምነት የሚበሉና ደሙንም የሚጠጡ ከእርሱ የተነሳ ሕያው ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል የጌታን ሥጋ የማይበሉና ደሙንም የማይጠጡ ይሞታሉ፡፡ ምክንያቱም አላመኑምና፡፡ ነገር ግን የጌታን ሥጋ በእምነት መብላትና ደሙን መጠጣት ለእኛ አስቸጋሪ አይደለም፡፡
 
ለጥቂት ጊዜ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ለመግባት የምንወስደው የደህንነት ፈተና አለ ብለን እንገምት፡፡ ከጥያቄዎቹ አንዱ ‹‹የኢየሱስን ሥጋ እንድትበሉና ደሙን እንድትጠጡ የሚያስችላችሁ እምነት ምንድነው?›› የሚል ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ መመለስ ያለብን እንዴት ነው? እውነቱን የሚያዋቅሩት የኢየሱስ ሥጋና ደም ስለሆኑ በተጨባጭ የጠጣነው ደሙን ሆኖ ሳለ ሥጋውን በልተናል ማለት ይቻለናልን? መልሳችን አድርገን ልንጽፈው የሚገባን የኢየሱስ ጥምቀትና ደም ነው፡፡ መንግሥተ ሰማይ መግባት የምንችለው የኢየሱስን ሥጋ ስንበላና ደሙን ስንጠጣ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተሳሳተ መንገድ ያመንንና የተሳሳተ አስተውሎት የያዝን ብንሆንም ልባችንን መለስ አድርገን የኢየሱስን ሥጋ ከበላንና ደሙን ከጠጣን ፈተናውን እናልፋለን፡፡ አሁኑኑ በዚህ ቅጽበት በኢየሱስ ሥጋና ደም ብናምን ፈተናውን በብቃት እናልፈዋለን፡፡
 
ሰዎች ውጫዊ ገጽታዎችን ይመለከታሉ፡፡ እግዚአብሄር ግን ልብን ጠልቆ ይመለከታል፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ጥምቀትና በመስቀል ላይ ደሙ ስናምን ያን ጊዜ የኢየሱስን ሥጋ እንበላለን፤ ደሙንም እንጠጣለን፡፡ እግዚአብሄር በልቦቻችን በእርግጥም በኢየሱስ ሥጋና ደም ላይ እምነት እንዳለን ለማየት የልባችንን ጥልቅ ይመለከታል፡፡ ስለዚህ ከጥልቅ ልባችን በኢየሱስ ሥጋና ደም የማንም ከሆንን ከሐጢያት አልዳንም፡፡ ከዚህ በፊት ምንም ያህል ስታምኑ የነበራችሁ ብትሆኑም አሁን በኢየሱስ ሥጋና ደም የሚያምን እምነት ካላችሁ መንግሥተ ሰማይ መግባት ትችላላችሁ፡፡
 
የዚህ ዓለም ብዙዎቹ ሐይማኖተኞች በሥጋ ወደሙ ትምህርት ትክክለኛነት ላይ ማለቂያ የሌለው ክርክር ይከራከራሉ፡፡ በእርግጥ የሚያስፈልገው ነገር የኢየሱስን ሥጋ እንድንበላና እንድንጠጣ የሚያስችለን እምነት ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በልባችን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ስናምን ብቻ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት ከሙሉ ልባችን በኢየሱስ ማመን ማለት እውነተኛውን መብል መብላትና እውነተኛውን መጠጥ መጠጣት ነው፡፡
 
 
የኢየሱስን ጥምቀትና ደም የሐጢያት ስርየታችን አድርን ልናምነው ይገባናል፡፡ 
 
ጌታችን እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው፡፡›› (ዮሐንስ 6፡55) ጌታችን የሐጢያትን ኩነኔ በመስቀል ላይ ተሸከመ፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻችንን እንደወሰደ የሚያምነው እምነት የኢየሱስን ደም እንድንጠጣ የሚያስችለን እምነት ነው፡፡ ኢየሱስ ከዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት የልጆቻችንን፣ የወላጆቻችንንና የእያንዳንዳችንን ጨምሮ የሁላችንንም ሐጢያቶች ወስዶዋል፡፡ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስም የእነዚህን ሐጢያቶች ሁሉ ኩነኔ ተሸከመ፡፡ ኢየሱስ በጥምቀቱና በደሙ በዚህ ዓለም ላይ የሚኖረውን የእያንዳንዱን ሰው የሐጢያት ችግሮቻችንን በሙሉ ፈጽሞ አቃለለ፡፡ ኢየሱስ በዚህ መንገድ ሐጢያቶቻችንን በጥምቀቱ እንደወሰደና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም ለሐጢያቶቻችን እንደተኮነነ ማመን የኢየሱስን ደም በእምነት መጠጣት ነው፡፡
 
በዛሬው ዓለም ውስጥ በቃላቸው ብቻ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል እንደሚያምኑ የሚናገሩ ብዙዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ ሥጋና ደም አያምኑም፡፡ በኢየሱስ ሥጋና ደም የሚያምን ምሉዕ እምነት የሌለው ማንኛውም ሰው ከሐጢያት ሊነጻ አይችልም፡፡ ከዚህ ቀደም ብቸኛው እውነት የመስቀሉ ደም እንደነበር አምናችሁ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ትክክለኛውን እውነት ስላገኛችሁ በኢየሱስ ሥጋና ደም በግልጽ የሚያምን እምነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር ድናችኋል ብሎ የሚያውቃችሁ ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ማለትም ከሙሉ ልቡ በኢየሱስ ሥጋና ደም በሚያምን እምነት በተገኘው የሐጢያት ስርየት ላይ ግልጽ የሆነ የደህንነት መስመር ካላሰመራችሁ እምነታችሁ በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም፡፡
 
ጌታችን እንዲህ ብሎዋል፡- ‹‹ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡›› (ዮሐንስ 6፡56) ነገር ግን የኢየሱስን ሥጋ በእምነት ካልበላንና ደሙንም ካልጠጣን ወደ እግዚአብሄር ፊት መቅረብ አንችልም፡፡ በኢየሱስ ሥጋና በደሙ የሚያምን ይህ እምነት የሌለው ማንኛውም ሰው በጌታ ሊኖር አይችልም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ካሉት ከእግዚአብሄር ቅዱሳን ሰራተኞችና አገልጋዮች መካከል ማንም በኢየሱስ ሥጋና ደም ከሚያምነው ከዚህ እምነት በሚያሳዝን ሁኔታ እንዳይወድቅ ልባዊ ተስፋዬ ነው፡፡
 
ሰዶምና ገሞራ በእሳት በወደሙ ጊዜ የሎጥ አማቾች ሎጥ የነገራቸውን የእግዚአብሄር የሕይወት ቃል እንደ ተረት ቆጠሩት፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ከበድ አድርገው በማይወስዱት ላይ የእግዚአብሄር ፍርድ በተጻፈው መሰረት ይወርድባቸዋል፡፡ አላማኒዎች በአለማመን ሐጢያታቸው ይኮነናሉ፡፡ በሐጢያቶቻቸውም ይጠፋሉ፡፡ ይህ እንዲያው በጥቂት ፈገግታዎች ብቻ የምናልፈው አስቂኝ ጉዳይ አይደለም፡፡
 
የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል በኢየሱስ ሥጋና ደም ማመንን ያመለክታል፡፡ ከሐጢያቶቻችን ነጽተን የዘላለምን ሕይወት ያገኘነው በዚህ እውነት በማመን ነው፡፡ የምናምንበት የኢየሱስ ሥጋና ደም እምነት እውነተኛ ወንጌልና ተጨባጭ እውነት ስለሆነ ይህንን እምነት በልቦቻችን መያዝ አለብን፡፡ በመጀመሪያ የእምነትን ክፈፍ በልቦቻችን ውስጥ ከፍ አድርገን በመስራት የእግዚአብሄርን ቃል በሙሉ አጥብቀን መያዝና ከእኛም እንዳያመልጥ በጭራሽ መፍቀድ የለብንም፡፡ በልቦቻችን በማመን እግዚአብሄር የሐጢያተኞችን ሐጢያቶች በሙሉ የደመሰሰ የመሆኑን እውነት መቀበል አለብን፡፡
 
ሁላችሁም በጌታ በተፈጸመው የውሃና የመንፈስ ወንጌል በማመን ከሐጢያቶቻችሁ የሚያድናችሁን የደህንነት እንጀራ እንድትበሉና የዘላለምን ሕይወት እንድታገኙ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጸልያለሁ፡፡