Search

خطبے

ርዕስ 11፡ የመገናኛው ድንኳን

[11-32] የዕጣኑ መሠውያ እግዚአብሄር ጸጋውን የሚለግስበት ስፍራ ነው፡፡ ‹‹ዘጸዓት 30፡1-10››

የዕጣኑ መሠውያ እግዚአብሄር ጸጋውን የሚለግስበት ስፍራ ነው፡፡
‹‹ዘጸዓት 30፡1-10›› 
‹‹የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው፡፡ ርዝመቱ አንድ ክንድ፣ ስፋቱም አንድ ክንድ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ይሆናል፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ይሁኑ፡፡ ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ፡፡ ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፡፡ በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ይሁኑ፡፡ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አድርግ፤ በወርቅም ለብጣቸው፡፡ በምስክሩ ታቦት አጠገብም ካለው መጋረጃ በፊት ታኖረዋለህ፡፡ ይህንም አንተን በምገናኘበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ፡፡ አሮንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው፡፡ ይህ በእግዚአብሄር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል፡፡ ሌላም ዕጣን፣ የሚቃጠለውንም መስዋዕት፣ የእህሉንም ቁርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥም ቁርባን አታፈስስበትም፡፡ አሮንም በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተሰርያ ያደርጋል፤ በዓመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተሰርያ በሚሆን በሐጢአት መሥዋዕት ደም ማሰተሰርያ ያደርግበታል፡፡ ለእግዚአብሄር ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡›› 


የእግዚአብሄር ቤት ወደሆነው ቅድስት ስፍራ ገብተን ቢሆን ኖሮ መጀመሪያ የምናየው መቅረዙን፣ የሕብስቱን ገበታና የዕጣኑን መሠውያ ይሆን ነበር፡፡ የዕጣኑ መሠውያ መቅረዙንና የሕብስቱን ገበታ አልፎ የስርየት መክደኛው ባለበት በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ፊት ለፊት የሚገኝ ነበር፡፡ የዚህ የዕጣን መሠውያ ርዝመትና ስፋት አንድ ክንድ ሲሆን ቁመቱ ደግሞ ሁለት ክንድ ነበር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክንድ በግምት በዛሬው ልኬት 45-50 ሳ.ሜ ነው፡፤ ስለዚህ የዕጣኑ መሠውያ ርዝመቱና ስፋቱ 50 ሳ.ሜ ቁመቱ ደግሞ 100 ሳ.ሜ አካባቢ የሆነ አጭር አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ነበር፡፡ ልክ እንደሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ የዕጣኑ መሠውያም እንደዚሁ በአራቱ የላይኛው ማዕዘኖቹ ቀንዶች ነበሩት፡፡ የዕጣኑ መሠውያ ከግራር እንጨት ተሠርቶ ሙሉ በሙሉ በወርቅ ተለብጦ ነበር፡፡


በመቅደሱ ውስጥ ያለው የዕጣኑ መሠውያ አራት ቀንዶች ነበሩት፡፡
 
ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ የስርየት ቀን መሥዋዕትን በሚያቀርብበት ጊዜ እስራኤሎች ዓመቱን ሙሉ የሠሩዋቸውን ሐጢያቶች የተሸከመውን የመስዋዕቱን እንስሳ ደም በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ላይ በሚገኘው የሚቃጠለው መሥዋዕት መሠውያ ቀንዶች ላይ ይቀባዋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድም ሊቀ ካህኑ ይህንን ደም በዕጣኑ መሠውያ ቀንዶች ላይም ያደርጋል፡፡ ይህ ደም የሚቀርበው ለእግዚአብሄር ስለሆነ የእስራኤልን ሕዝብ ከእግዚአብሄር የለየውን የሐጢያት ችግር ይፈታል፡፡ ሁላችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶችን ስርየት ተቀብለናል፡፡ በዚህ የአዲስ ኪዳን ዘመንም ለጸሎት በእግዚአብሄር ፊት በምንቀርብበት ጊዜ እንቅፋቶችን ሁሉ ለማስወገድ የሚያስችለን ይህ እምነታችን ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሲኖሩ ጻድቃኖችም ቢሆኑ ሐጢያት ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ ጥምቀትና በብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ስርዓት በተመሰለው የመሥዋዕቱ ደም ስለምናምን አሁንም ድረስ ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብና በድፍረት ወደ እርሱ ለመጸለይ እንችላለን፡፡
ጻድቃን በዚህ ዓለም ላይ በሚፈጽሙዋቸው ሐጢያቶች የተነሳ ወደ እግዚአብሄር ፊት ለመቅረብ ቢያመነቱም በዚህ ዘመን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በመታመን በድፍረት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ይችላሉ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የውሃና የደም ወንጌል የምናምን ከሆንን ስጋችንና አእምሮዋችን ደካማ ቢሆኑም እንኳን በድፍረት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንችላለን፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቀደም ብሎ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ጻድቃን ስለሆንን ነው፡፡ ጌታም ቀደም ብሎ በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር ላይ ባሉት ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ በተገለጠው የደህንነት እውነት አማካይነት ከመተላለፎቻችን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ አድኖናል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰላሰል አለብን፡፡ ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀቱና በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አማካይነት ፍጹም የሆነውን ደህነታችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ፈጽሞታል፡፡ በዚህ ደህንነት በሚያምኑትና በማያምኑት መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለ፡፡ ጻድቃን በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያምናሉ፤ያለ አንዳች ማመንታት ወደ እግዚአብሄር መጸለይ የሚችሉት ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ በጥምቀቱና ለእነርሱ ባፈሰሰው ደሙ ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ እንደተቀበለ ያምናሉና፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ኢየሱስ ከአጥማቂው ዮሐንስ በተቀበለው ጥምቀት አማካይነት ሐጢያቶቻቸውን ሁሉ እንደተሸከመና በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስም ለሐጢያቶቹ ሁሉ እንደተኮነነ ማመን አለበት፡፡ በእግዚአብሄር ፊት የእምነት ካህን መሆን የሚችለውና ለራሱና ለሌሎች የሚጸልየው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ የክርስቲያን እምነት ማለት እግዚአብሄር ከዚህ ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ እንዳዳነን ማመን ነው፡፡ የዚህ እምነት መሠረትም በውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ነው፡፡
ሁላችንም በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል አማካይነት በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር ላይ ባሉት ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ጥሩ በፍታ የተገለጠውን የደህንነት እውነት መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህ የወንጌል እውነት በማመንም ሁላችንም ወደ እግዚአብሄር መንግሥት መገባት እንችላለን፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ደህንነታችሁ እንደሆነ፣ እርሱ ሐጢያቶቻችሁን ሁሉ እንደተሸከመና ስለ ሐጢያቶቻችሁ ሁሉም በመስቀል ላይ እንደተኮነነ ታምኑ ዘንድ እጠይቃችኋለሁ፡፡ ያን ጊዜ ለዘላለም ከሐጢያቶቻችሁ ሁሉ ነጻ ትወጣላችሁ፡፡ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት ተቀብላችሁ ነጻ ትወጣላችሁ፡፡ የሐጢያቶቻችሁን ስርየት ተቀብላችሁ ጻድቅ የምትሆኑትና ትክክለኛ እምነት ስለያዛችሁም በእግዚአብሄር ዘንድ የምትመሰገኑት የእግዚአብሄር የኪዳን ወንጌል በሆነው የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ቃል በማመን ብቻ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ደህንነታችሁን አግኝታችሁ ስታበቁ መጀመሪያ የምታደርጉት ነገር ለደህንነት ሥራው ማለትም ለውሃውና ለመንፈሱ ወንጌል በመላው ዓለም መሰራጨት ወደ እግዚአብሄር መጸለይ ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የሚያምኑ ጻድቃን ምዕመናን በእግዚአብሄር ቅድስት ስፍራ ባለው መቅረዝ በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን አማካይነት በዚህ ዓለም ላይ የወንጌልን ብሩህ ብርሃን ማብራት ይችሉ ዘንድ ልክ እንደዚህ ወደ እግዚአብሄር ይጸልያሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን አገልግሎት ለመደገፍና ወንጌል በመላው ዓለም ፍሬ እንዲያፈራ ለማድረግ የሚያስፈልገው ነገር እምነት ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚኖር እያንዳንዱ ሰው የሐጢያቶቹን ስርየት መቀበልና በእምነት ማደግ የሚችለው በባሮቹ የተሰበከውን የእግዚአብሄር ክቡር ቃል በመስማትና በማመን ነው፡፡
ኢየሱስ አዳኛችሁ ስለመሆኑ ያላችሁ እምነት በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ መመሥረት አለበት፡፡ ከሐጢያቶቻችሁ የዳናችሁ ጻድቃን ስለሆናችሁም ወደ ዕጣኑ መሠውያ መቅረብና በቅድስቱ ስፍራ ባለው የስርየት መክደኛ ፊት መቆም አለባችሁ፡፡ ይህ ለምን አስፈላጊ ሆነ? ምክንያቱም በየጊዜው የእግዚአብሄር ጸጋ ያስፈልጋችኋል፡፡ የዕጣኑ መሠውያ ለእግዚአብሄር ጸሎትን የምናቀርብበት ስፍራ ነው፡፡ እዚህ ላይ ዕጣን የሚያመለክተው የቅዱሳንን ጸሎት ነው፡፡ (ዮሐንስ ራዕይ 5፡8) ወደ ዕጣኑ መሠውያ በምንቀርብበትና ወደ እግዚአብሄር በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሄርን ጸጋ እንለብሳለን፡፡ በቅድስቱ ስፍራ ያለው የዕጣኑ መሠውያ የእግዚአብሄርን ጸጋ የምናገኝበት መንገድ በእምነት ወደ እግዚአብሄር መጸለይ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምናምን ምዕመናኖች ሁልጊዜም የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንለብስ ዘንድ ወደ ዕጣኑ መሠውያ መቅረብና ሳናቋርጥ በእምነት ወደ እግዚአብሄር መጸለይ ያለብን ለዚህ ነው፡፡
 


የዕጣኑ መሠውያ የእግዚአብሄርን ዕርዳታ የምንጠይቅበት ስፍራ ነው፡፡


በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን የሐጢያቶችን ስርየት ብንቀበልም በቀሪው የሕይወት ዘመናችን የእግዚአብሄር ዕርዳታ ያስፈልገናል፡፡ እኛ ራሳችንን ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር ለማቆራኘትና የዚህ ዓለም ብርሃን ሆነን መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት ከፈለግን የእግዚአብሄር ጸጋ ሁልጊዜም ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ‹‹አቤቱ እባክህ ዕርዳኝ፤ አጥብቀህ ያዘኝ፤ እምነትን ስጠኝ፤ በመንፈስና በስጋ አበርታኝ፤ እምነቴ እንዳይፍገመገም አበርታው፤ ዓለምን ለመከተል ያለኝን የልብ ፍላጎት ቁረጥ፤ አምላካዊ ያልሆኑ ምኞቶችን ሁሉ አስወግድ›› ብለን በመጠየቅ ያለ ማቋረጥ ወደ እግዚአብሄር መጸለያችን ለሁላችንም አስፈላጊ ነው፡፡ ጻድቃን በነገር ሁሉ ጸጋውን እንዲያገኙና በስጋም በመንፈስም በረከቶቹን እንዲቀበሉ ወደ ዕጣኑ መሠውያ ቀርበው በፊቱ በመንበርከክ እንዲህ እንዲጸልዩ የእግዚአብሄር ፍላጎት ነው፡፡ የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበለ እያንዳንዱ ጻድቅ በዕጣኑ መሠውያ ላይ የጸሎት ሕይወትን ይመራ ዘንድ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው፡፡
እኛ ጻድቃኖች በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል በማመን ዳግመኛ እንድንወለድና ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የዳንን ብንሆንም እግዚአብሄር በቀን ተቀን ሕይወታችን ጸጋውን ይለግሰን ዘንድ ወደ እግዚአብሄር መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት እኛ ጻድቃኖች የሐጢያቶችን ስርየት የተቀበልን ብንሆንም የእግዚአብሄርን ጸጋ እየለበስን የማንቀጥል ከሆነ ጌታ ሁላችንም እንድንጓዝበት በሚፈልገው ጠባብ የሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ የማንችል በመሆናችን ነው፡፡ እግዚአብሄር በጸጋ ላይ ጸጋ የሚሰጣቸው ጻድቃን ወደ እርሱ ሲጸልዩ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነን ቃሉን ስንታዘዝ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጻድቃን ከእርሱ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር የእርሱን መልካም ሥራ ሲያከናውኑ የእግዚአብሄርን ጸጋ ይለብሳሉ፡፡ ቀደም ብሎ እንደተወሳው ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ የመስዋዕቱን እንስሳ ደም በዕጣኑ መሠውያ ቀንዶች ላይ ያደርጋል፡፡ ይህም እኛ ጻድቃኖች ወደ እግዚአብሄር ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ እምነታችንን መናዘዝና ‹‹ጌታ ሆይ አንተ አዳኜ ነህ፤ መለኮታዊ ክብርህን ትተህ የሰው ስጋ በመልበስ ወደዚህ ምድር መጣህ፤ በጥምቀትም ሐጢያቶቼን ሁሉ ተሸከምህ፤ እኔን ለማዳንም በእኔ ፋንታ ደምህን አፈሰስህ›› ማለት እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡ የእርሱን የተትረፈረፈ ጸጋ መልበስ የምንችለው እግዚአብሄር አምላካችንና አዳኛችን ስለመሆኑ የዚህ ዓይነት የማይፍገመገም እምነት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ የሕይወት ገጠመኞቻችን ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም አምላካችንና አዳኛችን ነው፡፡ እርሱ ከሐጢያቶቻችን ሁሉና ከኩነኔያችን ሁሉ ያዳነን አምላክ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ጸጋ የምንለብሰው እንዲህ ባለ የማይፍገመገም እምነት ወደ እግዚአብሄር ስንጸልይ ነው፡፡


በእያንዳንዱ ጸሎታችን ዳግመኛ ደህንነታችንን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ 


እግዚአብሄር አምላካችን መሆኑን ዳግመኛ ማረጋገጥ የምንችለው በጸሎታችን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን በረከቶች የሚያመጣልን ይህ እምነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በእግዚአብሄር የጸጋ ዙፋን ፊት ለመንበርከክ የምንገደደው እግዚአብሄር በእርግጠኝነት እንደሚባርከን ሙሉ በሙሉ ስላመንን ነው፡፡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ላይ ያለን እምነት ወደ እግዚአብሄር በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሄር እያንዳንዱን ጸሎት በእርግጥም እንደሚመልስ ዋስትና ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄር እያንዳንዱን የጻድቃን ጸሎት ያዳመጣል፡፡ ሁላቸውንም ይባርካል፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሄር በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ በቅድሚያ እንደሚከተለው ጸጋውን ማሰላሰል አለብን፡- ‹‹ጌታ ሆይ በአንተ ጽድቅ አምናለሁ፤ ሕይወቴ በጉድለቶች የተሞላ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እንደ አንተ ፈቃድ ለመኖር ብፈልግም እጅግ ብዙ ጉድለቶች አሉብኝ፤ ነገር ግን ጌታ ሆይ አንተ የሰው ስጋ ለብሰህ ወደዚህ ምድር እንደመጣህ፣ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅም ሐጢያቶቼን ሁሉ እንደተሸከምህ፣ በእኔ ፋንታም ለሞት እንደተሰቀልህና በዚህም አዳኜ እንደሆንህ ደግሞ አውቃለሁ፡፡ አንተ የእኔ መሲህና የደህንነቴ አምላክ ነህ፡፡ አንተ ጌታዬ ነህና ጸጋህን እንደምትሰጠኝ በሙሉ ልቤ አምናለሁ፡፡››
ስለዚህ ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ ወደ እግዚአብሄር በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ በቅድሚያ ይህንን የእግዚአበሄር ጸጋ ማሰላሰልና እምነታችንን ሁሉ በእርሱ ላይ ማድረግ አለብን፡፡ ያን ጊዜ የምንፈለገውን ሁሉ ከእግዚአብሄር ለመጠየቅ ድፍረቱ ይኖረናል፡፡ እርሱም እንዲህ ይለናል፡- ‹‹አዎ በእርግጥም አንተ ልጄ ነህ፤ እምነትህ የማይናወጠውን ያህል እኔ በእውነት አምላክህ ነኝ፡፡ አንተም በእውነት ከሕዝቦቼ አንዱ ነህ፡፡ ስለዚህ ጸሎትህን እመልሳለሁ፡፡ ሁልጊዜም እባርክሃለሁ፡፡ በስርየት መክደኛው ላይ እገናኝሃለሁ፡፡ በእኔ ያለህ እምነት የማይናወጥ እንደሆነ፣ መታመንህን በእኔ ላይ ብቻ እንዳደረግህና እኔም አምላክህ እንደሆንሁ በሙሉ ልብህ እንደምታምን ከጸሎትህ መረዳት ችያለሁ፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ሁሉ እኔ በእርግጥም አምላክህ እንደሆንሁ ያውቁ ዘንድ ጸሎትህን እመልሳለሁ፡፡›› 
ስለዚህ እግዚአብሄር ጸጋውን የሚያለብሰንና በረከቶቹን የሚያዘንብልን በጌታችን የደህንነት እውነት ስናምን ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ መዳናችን የታሪኩ ሁሉ ፍጻሜ አይደለም፡፡ በአንጻሩ በእርግጥ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ድነን ከሆነ የእግዚአብሄር በረከቶች ሊጀምሩ መሆናቸውን ማመን ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ በየቀኑ ጸጋውን የምንለብሰው በእግዚአብሄር ጸጋ በመታመን ነው፡፡ አምላክን የሚመሰል ሕይወት መኖር የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ አእምሮዋችንን የሚያስጨንቅ አንዳች ነገር በሚከሰትበት ጊዜ ሁሉ ‹‹ጌታ ሆይ እባክህ እርዳን፤ እባክህ ቤተክርስቲያንህን እርዳት፤ ቤተክርስቲያንህ አሁኑኑ ሥራህን ለመፈጸም የአንተ እርዳታ በጣሙን ያስፈልጋታል›› በማለት ወደ እግዚአብሄር የምንጸልየው ለዚህ ነው፡፡ የዓለምን ጉዳዮች የሚመለከት ቢሆንም በአእምሮዋችን ውስጥ ስጋት ወይም የጸሎት ርዕስ ከተፈጠረ ወደ ዕጣኑ መሠውያ ፊት ቀርበን በጸጋው ዙፋን ፊት በእምነት መጸለይ ይኖርብናል፡፡ ያን ጊዜ ጌታ በነገር ሁሉ ጸጋውን ያለብሰናል፡፡
እዚህ ላይ የዕጣኑ መሠውያ ከእግዚአብሄር ዘንድ ጸጋን የምናገኝበት ስፍራ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋችኋል፡፡ እኛ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሄር የምንጸልየው ለሌላ ዓላማ ሳይሆን የእርሱን ጸጋ ሁሉ ለመልበስ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ወደ እርሱ የምንጸልየው የእግዚአብሄርን በረከቶች ለመቀበል ነው፡፡ አሁን በእምነት ስለዳንን ቀሪ ዘመናችንን በእግዚአብሄር የተስፋ ቃል በመታመንና በረከቶቹን ሁሉ በመቀበል ለመኖር ከፈለግን ሁላችንም ሳናቋርጥ ወደ እግዚአብሄር መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ የዕጣኑ መሠውያ እዚያ የተቀመጠልን የእግዚአብሄርን ጸጋ እንለብስ ዘንድ ነው፡፡
ወደ እግዚአብሄር በምንጸልይበት ጊዜ የሚገጥመን እጅግ ትልቁ ዕንቅፋት ሐጢያት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እንከን የሌለበት ሕይወት የሚኖር ሰው የለም፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሄር ቀርበን በፊቱ በምንጸልይበት ጊዜ የመጀመሪያው የጥርጣሬ ምንጭ ሐጢያቶቻችን ናቸው፡፡ የደህንነትን እውነት ደጋግመን ማሰላሰልና ጌታችን ቀድሞውኑም በመገናኛው ድንኳን መግቢያ በር ላይ ባሉት ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ እንደደመሰሰ በማመን እምነታችንን ማደስ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር በመምጣት በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችንን ተሸክሞ ለእነዚህ ሐጢያቶች ሁሉ መኮነኑን ያለ ማመንታት ማመን አለብን፡፡ ለአምላካችንና ለአዳኛችን ምስጋና ይግባውና ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ተፈትተናል፡፡ የእግዚአብሄርን ጸጋና በረከቶቹን መጠየቅ የምንችለው ይህ እምነት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርም ይባርከን ዘንድ መጸለይ የምንችለው ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የመሥዋዕቱ እንስሳ ደም በዓመት አንድ ጊዜ በዕጣኑ መሠውያ ቀንዶች ላይ የሚደረገው ይህንን ትምህርት በማስተማር የጌታን የደህንነት ስራ ሊያስታውሰን ነው፡፡
 


ወደ እግዚአብሄር በድፍረት መጸለይ የሚችለው የሐጢያቶቹን ስርየት ሁሉ ማግኘቱን ያረጋገጠ ሰው ብቻ ነው፡፡ 


ወደ እግዚአብሄር ስንጸልይ አባታችን ወይም አዳኛችን ብለን እየጠራነው ያለ ምንም ማመንታት የምንፈልገውን ልንጠይቅው እንችላለን፡፡ በዚህ ሁኔታ እንጠራው ዘንድ ነጻ ነን፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሄር በእርግጥም አባታችን፣ ጌታችንና አዳኛችን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሄርን በተለያዩ ስያሜዎች ለመጥራትና ወደ እርሱ ለመጸለይ አናመነታም፡፡ ምክንያቱም እርሱ ፈጣሪያችን ብቻ ሳይሆን አዳኛችንም ጭምር ነውና፡፡
ሁላችንም ወደ ጌታ ልንጸልይ የሚገባን እንዲህ ነው፡- ‹‹ጌታ ሆይ ከሐጢያቶቼ ሁሉ ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ፡፤ በእርግጥ በረከቶችህና ረድኤትህ ያስፈልጉኛል፡፡ ስለዚህ አቤቱ እርዳኝ፡፡ የመንገዴን እያንዳንዲቱን እርምጃ ተቆጣጠር፡፡ አንዳንድ በጎ ነገሮችን አድርጌያለሁ፤ ነገር ግን ደግሞ ብዙ ስህተቶችንም ሰርቻለሁ፡፡ አሁንም ድረስ የምጨነቅባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ጌታ ሆይ ሁሉንም ለአንተ አስረክባለሁ፤ እንድትረዳኝና መንገዴን እንድታቀና እለምንሃለሁ፡፡ ወንጌልህን እንድሰብክላቸውና ለአንተም የተትረፈረፈ ፍሬ እንዲሆኑ ወደ ጠፉት ነፍሳቶች ምራኝ፡፡ የወንጌልን ዘር እዘራባቸው ዘንድ ልባቸውን ከፍተህ የልባቸውን እርሻ በማረስ ቤተክርስቲያንህንም ደግሞ አጽንተህ እንድትይዛትና አገልጋዮችህንም እንድትጠብቅ እለምንሃለሁ፡፡ የውሃውና የመንፈሱ ወንጌል ፍሬያማ ሆኖ ይሰበክ ዘንድ ሁሉንም ባርካቸው፡፡ ይህ ወንጌል በምድር ሁሉ ፊት ይሰራጭ፡፡ ባሪያዎችህ ያንተ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በሚጠብቁት ዓይኖችህ ሥር አድርገህ እንድትጠብቃቸው እለምንሃለሁ፡፡ ጌታ ሆይ ባርከኝ፤ ቤተሰቤን ባርክ፤ ልጆቼንም ባርክ፡፡ ቅዱሳኖችንም ደግሞ ባርክ፤ በክርስቶስ የሆኑትን ወንድሞቼንና እህቶቼን ባርክ፤ ከቤተክርቲያንህ ውጪ ያሉት ኣላማኒዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ በረከቶችህ ተትረፍርፈው ይብዙ፡፡›› ስንጸልይና ተስፋዎቻችንንና ሕልማችንን ሁሉ በዚህ መልክ ለእግዚአብሄር አሳልፈን ስንሰጥ እርሱ በእርግጥም ጸሎታችንን ይመልስና ይባርከናል፡፡ ሁላችንም በጸሎት አማካይነት የእግዚአብሄርን የተትረፈረፉ በረከቶች መቀበል የምንችለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በየቀኑ በጸጋ ላይ ጸጋን የምናገኘውም እንደዚህ ነው፡፡
እግዚአብሄር በጽድቁ ለሚያምኑ ሁሉ አምላክ ነው፡፡ እርሱ ሳይናወጡ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ለሚያምኑትም አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በማይናወጥ እምነታቸው ወደ ጸጋው ፊት በድፍረት ቀርበው ‹‹አቤቱ አንተ አምላኬ እንደሆንህ አምናለሁ፤ አንተ አዳኜ እንደሆንህ አምናለሁ፤ አቤቱ እርዳኝ!›› በማለት ጸጋውንና በረከቶቹን ለሚለምኑ ምዕመናኖቹ ሁሉ ጸጋውን ከመስጠት አይታክትም፡፡
ምዕመናን ጓደኞቼ ሁላችንም ከዓለም ሐጢያቶች መዳናችን የታሪኩ መጨረሻ እንዳልሆነ ነገር ግን ሳናቋርጥ ወደ ጌታ መጸለይ እንደሚያስፈልገን መረዳት ያለብን የመሆኑን አስፈላጊነት እንደሚገባው አበክሬ አልተናገርሁም፡፡ ጌታ ጸሎታችሁን ካልመለሰላችሁ ወይም እንዴት እንደሚጸለይ የማታውቁ ከሆናችሁ እምነታችሁን ደረጃ በደረጃ መመርመርና ጌታ በእርግጥ ለእናንተ ምን እንደሆነ ማሰብ ይገባችኋል፡፡
ከጌታ ጋር ያላችሁን ግንኙነት በግልጥ መረዳት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ጌታ የሰማያትና የምድር ፈጣሪ መሆኑን፣ እናንተን ለማዳንም የሰው ስጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅም ሐጢያቶቻቸሁን ሁሉ እንደተሸከመ፣ በእናነተ ፋንታም በመስቀል ላይ እንደተኮነነ፣ በሦስት ቀናት ውስጥ ዳግመኛ ከሙታን እንደተነሳና አሁንም የእናንተ ሕያው አዳኝ ሆኖ በሕይወት እንዳለ በመረዳትና ከሙሉ ልባችሁ በማመን እምነታችሁ በሚገባ እንደተተከለ እርግጠኞች መሆን አለባችሁ፡፡ አሁን ስለዳናችሁ ጌታ እረኛችሁ እናንተም የእርሱ በጎች ሆናችኋል፡፡ ስለዚህ ጌታ እርዳታውን በምትጠይቁበት ጊዜ ሁሉ መልስ እንደሚሰጣችሁ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊኖራችሁ አይገባም፡፡
 

ቀንና ሌሊት ልንጸልይ ይገባናል፡፡ 

ጌታን በእምነት አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉና በታማኝነት ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሄር የሚጸልዩ በዚህ ዓለም ላይ ሲኖሩ ሳለ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የእርሱን የተትረፈረፈ ጸጋና በረከቶች ይቀበላሉ፡፡ በአንጻሩ በማናቸውም ምክንያት ወደ ጌታ ባይጸልዩም የሚፈልጉትን ሁሉ እንደሚሰጣቸው በትዕቢት በማሰብ ወይም በእግዚአብሄር ቃል ላይ እምነት ስለሚጎድላቸው በትጋት የማይጸልዩ የእግዚአብሄርን በረከቶች ሊቀበሉ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከእምነታቸው ውስጥ የዕጣኑ መሠውያ ጎድሎዋልና፡፡ እርሱ አምላካችሁ እንደሆነ ስለምታምኑ ብቻ እግዚአብሄር የምትፈልጉትን ሁሉ እንደሚሰጣችሁ የምታስቡ ከሆነ እምነታችሁ መስመሩን ስቷል፡፡ ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ በቅድስቱ ስፍራ ውስጥ የዕጣን መሰውያ ባልኖረም ነበር፡፡ እግዚአብሄር የዕጣኑን መሠውያ የሠራው ስለሰለቸው ነው ብላችሁ ታስባላችሁን? በእርግጥ አይደለም! ሊቀ ካህኑ አሮን በየማለዳውና በየምሽቱ በዕጣኑ መሠውያ ላይ አራት ዓይነት ዕጣን ያጨስ ነበር፡ ያን ጊዜ የሚጤሰው ዕጣን ሽታ በአካባቢው ሁሉ ሲናኝ ቅድስቱን ስፍራ ጣፋጭ መዓዛ ይሞላዋል፡፡ ይህ በድፍረት ወደ እግዚአብሄር ፊት እንድንቀርብ የሚያስችለን ግሩም መዓዛ ነው፡፡ ይህ ዕጣን በእግዚአብሄር ፊት ጉድለቶቻችንን የመሸፈን ሐይልም አለው፡፡ ለምሳሌ ሊቀ ካህኑ የዕጣኑ ደመና በምስክሩ ታቦት ፊት ያለውን የስርየት መክደኛ እንደሸፈነ በማረጋገጥ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከመግባቱ በፊት ቅድስተ ቅዱሳኑን በዕጣን መሙላት ነበረበት፡፡ አለበለዚያ ይሞት ነበር፡፡ (ዘሌዋውያን 16፡12-13)
ምዕመናን ጓደኞቼ ወደ እግዚአብሄር በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ የሐጢያቶቻችንን ስርየት አስቀድሞ እንዳገኘን፣ አሁን እግዚአብሄር አምላካችን እንደሆነና ወደ እርሱ በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ ጸጋውን እንደሚሰጠን ሙሉ በሙሉ ማመን ይገባናል፡፡ በዚህ የማይናወጥ እምነት ወደ እግዚአብሄር ፊት ቀርበን በጸጋው ዙፋን ፊት በድፍረት ስንቆም ኩነኔ የማይኖርብን ብቻ ሳንሆን የእግዚአብሄርንም ጸጋ እንለብሳለን፡፡ እግዚአብሄር የተትረፈረፈ ጸጋውን የሰጠን የምህረት አምላክ ነው፡፡
 

ከዕጣኑ መሠውያ ጋር የተያያዙት ቀለበቶችም ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፡፡
 
በእግዚአብሄር መቅደስ ውስጥ ያለው የዕጣን መሠውያ ርዝመቱና ስፋቱ 50 ሳ.ሜ ቁመቱ ደግሞ 100 ሳ.ሜ የሚሆን ስድስት ገጾች ያሉት አራት ማዕዘን መዋቅር ነው፡፡ በመሠውያው በሁለቱ ጎኖቹ ሁለት ጥንድ የወርቅ ቀለበቶች ተያይዘውበት ነበር፡፡ ከዚያም በእነዚህ ሁለት ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ገብተውበት ነበር፡፡ እነዚህ መሎጊያዎችም ከግራር እንጨት ተሠርተው በወርቅ የተለበጡ ነበሩ፡፡ የዕጣኑ መሠውያ በአንጻራዊነት ትንሽ ቢሆንም ከፍ አድርገው የሚሸከሙት ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ ርዝመቱና ስፋቱ 50 ሳ.ሜ ቁመቱ ደግሞ 100 ሳ.ሜ በመሆኑ አንድ ሰው በቀላሉ አንስቶ ሊሸከመው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ልክ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ እንዳሉት እንደ ሌሎቹ ዕቃዎች ሁሉ ይህ ፈጽሞ የተከለከለ ነበር፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ እንደተናገረው እኛ ጻድቃኖች በስምምነት ወደ እግዚአብሄር መጸለይ እንደሚገባን ያመለክታል፡፡ ‹‹ደግሞ እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፡፡›› (ማቴዎስ 18፡19)
እነዚህ የዕጣኑ መሠውያ መሎጊያዎች እኛ ዳግመኛ የተወለድን ሰዎች እግዚአብሄርን በጸሎታችን ልናገለግለው እንደሚገባን ያሳዩናል፡፡ የእምነት ጸሎቶቻችን ለእኛ እግዚአብሄርን የምናገለግልበት መንገድ ናቸው፡፡ አሁን እኛ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ዳግመኛ ስለተወለድን እግዚአብሄርንና ቤተክርስቲያኑን በተለያዩ መንገዶች በጸሎት ቢሆን ወይም በፈቃድ አገልግሎቶቻችን ማገልገል እንችላለን፡፡ ወደ እግዚአብሄር ስንጸልይ ለራሳችን ብቻ አንጸልይም፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሄር ሥራ፣ ለቤተክርስቲያኑ አባሎችና በተለይም ለወንጌል ስርጭት እንጸልያለን፡፡ በሌላ አነጋገር ጸሎቶቻችን በእግዚአብሄር የጸጋ ዙፋን ፊት ቀርበን ምህረትን እንድናገኝ የሚፈቅዱልን ብቻ ሳይሆኑ የእግዚአብሄርን የጽድቅ አገልግሎት እንድናገለግልም ያስችሉናል፡፡ የእግዚአብሄርን መንግሥት ማገልገል የምንችለው በጋራ በመጸለይ ነው፤ አብረውት ላሉት ወንድሞችና እህቶች፣ ለቤተክርስቲያን፣ ለጠፉት ነፍሳት፣ ለእግዚአብሄር መንግሥት መስፋፋትና ለእግዚአብሄር የጽድቅ አገልግሎት ስንጸልይ ይህንን የምናደርገው እግዚአብሄርን ለማገልገል ነው፡፡ በቅድስቱ ስፍራ በዕጣኑ መሠውያ ላይ እግዚአብሄርን የሚያገለግሉትን ካህናቶች ፋይዳ መረዳቱ በጣም አስፈላጊያችን የሆነው ለዚህ ነው፡፡ በዚህ እምነት ከልባችን ወደ እግዚአብሄር መጸለይ ይገባናል፡፡ እግዚአብሄርንና ሕዝቡን ለማገልገል ስንል የእግዚአብሄርን ቃል እንደምንሰብክ ሁሉ እርሱንና ሕዝቡን ለማገልገልም ወደ እግዚአብሄር እንጸልያለን፡፡ ሁላችንም በሚቻለው መንገድ ሁሉ እግዚአብሄርን የማገልገል ይህ ሐላፊነት አለብን፡፡
እግዚአብሄርን የሚመስል የክርስቲያን ሕይወት ለመኖርና የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማገልገል ልታደርጉት የሚያስፈልጋችሁ እጅግ ጠቃሚው ነገር በእግዚአብሄርና በጽድቁ ማመን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል መስበክ፣ ወደ እርሱ መጸለይ፣ የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ማሰራጨትና እግዚአብሄርንና ጽድቁን ማገልገል የምትችሉት በእምነት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ለማገልገል የምናደርገው እያንዳንዱ ነገር በእምነት የሚደረግ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ እስካልተቀበላችሁ ድረስ እግዚአብሄርን የሚመስል የእምነት ሕይወት መኖር አትችሉም፡፡ እግዚአብሄርን ለማገልገል መጸለይ ያለብን የመሆኑን ጠቀሜታ እንደሚገባ አላተኮርሁበትም፡፡ ቅዱሳኖች ወንድሞችና እህቶች እንደዚሁም ልጆቻችን በዕሁድ የሰንበት ትምህርት ላይ ለመገኘት በቤተክርስቲያኖቻቸው በሚሰባሰቡበት ጊዜ ሁሉ ከሁሉ አስቀድመው ጌታን ማገልገል አለባቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ለመካፈል አብረን መሰባሰብ ይኖርብናል፡፡ የእግዚአብሄርንም ጽድቅ ማገልገል ይኖርብና፡፡ እኛ ዳግመኛ የተወለድን ሰዎች ‹‹ጌታ ሆይ ቤተክርስቲያንን አጸናት፤ ባርካትም፡፡ በመላው ዓለም በቤተክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ባሮችህንና ቅዱሳኖችህን አጽናቸው፤ ባርካቸውም፤ ነፍሳቸውንና ልባቸውንም ባርክ፡፡ የተባረከ እምነትንም ስጣቸው፡፡ የጠፉትን ነፍሳቶችም አድን›› በማለት ተስማምተን ስንጸልይ ጸሎቶቻችን እንደ ጣፋጭ መዓዛ ወደ እግዚአብሄር ያርጋሉ፡፡ እግዚአብሄርም በዚህ ጣፋጭ መዓዛ ይደሰትና መልሱን ይሰጠናል፤ ይባርከንማል፡፡ በጸሎታችን የጠየቅነውንም ሁሉ ይመልስልናል፡፡ እግዚአብሄርን በጸሎት ማገልገል ማለት ይህ ነው፡፡ ለፍላጎቶቻችን ብቻ ከመጸለይ ይልቅ የእግዚአብሄርን ሥራ በጸሎቶቻችሁ እንድታስታውሱት ሁላችሁንም እመክራችኋለሁ፡፡
በማናቸውም ምክንያት ከሌላው ይልቅ በቂ ጊዜ ኖሮዋችሁ ጡረታ ወጥታችሁ ቢሆን ወይም ታማችሁ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ቅዱሳን ሁሉ መጸለይ የሚያስፈልጋቸው ሆኖ ሲገኝ ለእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን፣ ለባሪያዎቹና ለቅዱሳኑ በይበልጥ መጸለይ ያስፈልጋችኋል፡፡ በተለይ ይህ ለቤት እመቤቶች በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጌታን ማገልገል የማንችለው ገንዘብ ስለሌለን አይደለም፡፡ ያለ ምንም ገንዘብ ጌታን አብዝታችሁ ማገልገል ትችላላችሁ፡፡ በእምነታችን የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል በቻላችሁት መጠን ማገልገል ትችላላችሁ፡፡ የዕጣኑን መሠውያ ሁለት ሰዎች ይሸከሙት ዘንድ ሁለት መሎጊያዎች በቀለበቶቹ ውስጥ እንደተደረጉ ሁሉ ድሆችም ከእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ጋር ከተስማሙ በእምነት ጸሎቶቻቸው ጌታን ማገልገል ይችላሉ፡፡ ባለጠጎችም እንደዚሁ በሐብታቸው እግዚአብሄርን ማገልገል ይችላሉ፡፡ ‹‹እኔ በሥራዬ በጣም ባተሌ ስለሆንሁ ጌታን የማገለግልበት ጊዜ መመደብ አልችልም›› አትበሉ፡፡ እያንዳንዱ ቅዱስ ሰው በስጦታዎቹ ቢሆን በጸሎቶቹ ቢሆን ወይም ወንጌልን በመስበክ ጌታንና ፈቃዱን በእምነት ማገልገል ይችላል፡፡ ጌታን የማገልገል ፍላጎቱ ካለን ሁላችንም የጌታን ፈቃድ ለማገልገል ከሚገባው በላይ እንችላለን፡፡ እኛ ዳግመኛ የተወለድን ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሄርን በረከቶች ለመቀበል ናፍቆቱ ካለን መቀበል እንችላለን፡፡
 


እግዚአብሄር በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል የምናምነውን ሁሉ ይባርከናል፡፡: 


ጌታ እረኛችን ነው፡፡ ከጌታ ጋር ያለን ግንኙነት በጣም የተቀራረበ ስለሆነ ምንም ነገርና ማንም ሰው መቼም ቢሆን ከእርሱ ሊለየን አይችልም፡፡
ወደ ማቴዎስ 26፡26-28 እንሂድ፡- ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፡፡ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፡- ‹‹እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለሐጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡›› 
‹‹ኢየሱስ›› የሚለው ስም አዳኝ ወይም መሲህ ማለት ነው፡፡ አምላካችንና አለቃችን መሆኑን ለመጠቆም ጌታችን ብለን እንጠራዋለን፤ ጌታችን ኢየሱስ ሁላችንንም ለማዳን አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ እግዚአብሀር ራሱ የሰው ሰጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ከመሞቱ በፊት የመጨረሻውን እራት አዘጋጅቶ ደቀመዛሙርቱን ሰብስቦ ‹‹እንጀራውን ውሰዱና ብሉ፤ ይህ ስጋዬ ነው፡፡ ይህንን ጽዋ ወስዳችሁ ጠጡ፤ ለብዙዎች ስለ ሐጢያት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› በማለት እንጀራውንና ወይኑን ሰጣቸው፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሄር አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር በመምጣትና በብሉይ ኪዳን ውስጥ በትክክል እንደተተነበየው በውሃውና በመንፈሱ አማካይነት የተስፋ ቃሉን በግሉ በመፈጸም አድኖናል ማለት ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ሁኔታ አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር ከመጣ በኋላ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ የዚህን ዓለም ሐጢያቶች በሙሉ ተቀበለ፡፡ ከዚያም በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በዚህም በዚህ ምደር ላይ የሚኖርን የእያንዳንዱን ሰው ኩነኔ ሁሉ ተሸከመ፡፡ ዳግመኛም ከሙታን በመነሳት አዲስ ሕይወት ሰጠን፡፡
የመስዋዕቱ እንስሳ ደም በዕጣኑ መሠውያ ላይ መደረጉ የኢየሱስን ስጋዊ ደም ያመለክታል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ከተሸከመ በኋላ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፡፡ ምስጋና ለዚህ መሥዋዕት ይሁንለትና የዳንነው በዚህ ነው፡፡ ደህንነታችንን ያገኘነው በዚህ የውሃና የመንፈስ ወንጌል ባለን እምነታችን ነው፡፡ ከሐጢያቶቻችን ሁሉ የዳንነው በዕውር ድንብር ወይም በዘፈቀደ እምነት ሳይሆን ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር በመምጣት በጥምቀቱ ሐጢያቶቻችን ሁሉ በስጋው ተሸክሞ ስለ ሁላችን ሲል ደሙን በማፍሰሱ ነው፡፡
እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን የመጋረጃ በር በሰማያዊው፣ በሐምራዊው፣ በቀዩ ማግና በጥሩው በፍታ የተገለጠውን ደህንነታችንን የፈጸመው በዚህ መንገድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሐምራዊው ቀለም የነገሥታት ንጉሥ ሰው መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ኢየሱስ በአጥማቂው ዮሐንስ በመጠመቅ በእኛ ፋንታ ደሙን አፍስሶ የሐጢያቶቻችንን ደመወዝ እንደከፈለ ያስተምረናል፡፡ ጌታ አዳኛችን የሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ቅዱሱን ቁርባን እንድንሳተፍ የሚያስችለን ዋናው እምነት በዚህ በውሃውና በመንፈሱ ወንጌል ያለን እምነት ነው፡፡ ኢየሱስ ለመጨረሻው እራት ሲዘጋጅ ያዘጋጀው እንጀራን ብቻ ሳይሆን ወይንንም ነበር፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ሁለቱንም እንዲበሉና እንዲጠጡ ነገራቸው፤ እዚህ ላይ እንጀራው የሚያመለክተው የኢየሱስን ስጋ ሲሆን አንደምታው እኛን ሐጢያተኞቹን ለማዳን እግዚአብሄር ራሱ ሰው እንደሆነ ነው፡፡ እንጀራው ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በስጋው እንደተሸከመም ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ወይኑ ኢየሱስ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን የሕይወትና የደህንነት ደም ያመለክታል፡፡
ስለዚህ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በምንሳተፍበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሄር ራሱ እኛን ለማዳን የሰው ስጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር እንደመጣ፣ በጥምቀቱም ሐጢያቶቻችንን ሁሉ በስጋው እንደተሸከመ፣፣ በእኛ ፋንታም በመስቀል ላይ እንደተኮነነና በዚህም እኛን አድኖን የግል አዳኛችን እንደሆነ ይህ የማይናወጥ እምነት ይኖረን ዘንድ ለሁላችንም ፈጽሞ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የቅዱስ ቁርባን ስርዓት ያቋቋመበትንና እስከ ምጽዓቱ ድረስም እንዲከበር ያዘዘበትን ትክክለኛ ምክንያት አለማወቃቸው ያሳዝናል፡፡ የእምነት ሕይወታችሁን በጣም አቅልላችሁ ልትመለከቱት አይገባችሁም፡፡ ኢየሱስ አዳኛችሁ እንደሆነ ገናም እርግጠኞች ካልሆናችሁ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ያለውን ሕብስትና ወይን ከመውሰዳችሁ በፊት ስለ እምነታችሁ አጥብቃችሁ ልታስቡ ይገባችኋል፡፡ ስሜታውያን ከመሆን ይልቅ ጌታ በእርግጥ ጌታችሁ መሆን አለመሆኑን በጥንቃቄ አስቡበት፤ ራሳችሁንም ጠይቁ፡፡
እግዚአብሄር የእናንተና የእኔ አምላክ ነው፡፡ የእናንተንና የእኔን ዘሮች ፈጥሮዋል፡፡ በዚህ ምድር ላይ እንድንወለድም ፈቅዶዋል፡፡ ይህ አምላክ ኢየሱስ ራሱ ነው፡፡ ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ የእኛ አዳኝ ሆኖ ወደዚህ ምድር መጣ፡፡ እኛን ለማዳን አዳኛችን ሆኖ ወደዚህ ምድር ከመጣ በኋላ በጥምቀቱ አማካይነት ሐጢያቶቻችንን በሙሉ በስጋው ተሸከመ፡፡ ከዚያም በታማኝነት እነዚህን ሐጢያቶቻችንን እያንዳንዳቸውን ራሱን ከእነዚህ ሐጢያቶች ፈጽሞ ሳያሳርፍ ወደ መስቀል በመውሰድ እኛ ለሐጢያቶቻችን እንዳንኮነን ርጉማኖች ብቻ ሊሸከሙት የሚገባቸውን የመስቀል ቅጣት ተቀበለ፡፡ ጌታ ከኩነኔያችን ሁሉ ያዳነን በዚህ መንገድ ነው፡፡
ስለ ውሃውና መንፈሱ ወንጌል ለቅጽበት እንኳን ብታስቡ ይህንን የደህንነት እውነት በቀላሉ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ ከዓለም ሐጢያቶች ሁሉ መዳን ማለት የውሃውንና የመንፈሱን ወንጌል ወደ ልባችሁ መቀበል ማለት ነው፡፡ ጌታ በውሃውና በደሙ አማካይነት ከሐጢያቶቼ ሁሉ እንዳዳነኝ አምናለሁ፡፡ እኔ ስለ ደህንነቴ ያደረግሁት ምንም ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ በቤተልሄም በጠባብ ግርግም ውስጥ ሲወለድ እዚያ አልነበርሁም፡፡ እግዚአብሄር እንዲያድነኝም በማንኛውም ቅርጽ ወይም መልክ ጣልቃ አልገባሁም፡፡ ነገር ግን ጌታ እኔን ለማዳን ከእኔ ዕቅድ ውጪ የሰው ስጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር መጣ፤ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በመጠመቅ ደሙን በመስቀል ላይ ያፈሰሰው እኔን ለማዳን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አምኛለሁ፡፡
እግዚአብሄር አብ ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድያ ልጁን ሰጠ፡፡ እግዚአብሄር እያንዳንዱን ሰብዓዊ ፍጡር ለማዳን ራሱ መጣ፡፡ በእርግጥም እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችን አድኖናል፡፡ የእናንተና የእኔም አዳኝ ሆንዋል፡፡ ደህንነታችንን ለማግኘት እኛ ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር ራሱ አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ መታመንና እርሱ ለእኛ ያደረገውን የደህንነት ሥራ ወደ ልቦቻችን መቀበል ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ዘንድ ጸጋን መቀበል የሚችሉት የራሳቸውን ብርታት አሟጠው የጨረሱ፣ ከንቱነቱን ተረድተው ጥረቶቻቸውን የተዉና የሐጢያቶቻቸውን ስርየትና ደህንነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሄር አሳልፈው የሰጡ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ በእናንተ አስተሳሰብ ሊስተዋል የማይችል ቢመስልም እግዚአብሄር ራሱ ሁላችንንም ለማዳን ደህንነታችንን በተጨባጭ በሚገባ ፈጽሞታል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር የደህንነት ሥራ ከማመን በስተቀር እኛ የምናደርገው አንዳች ሌላ ነገር የለም፡፡ 


ራሳችሁን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሄር አስረክቡ፡፡

ራሳችሁን ለእግዚአብሄር አሳልፋችሁ መስጠታችሁ ፈጽሞ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ለእናንተ ያደረገላችሁን አስቡ፡፡ እግዚአብሄር ራሱ ሰው ሆነ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ያደረገው እናንተንና እኔን ለማዳን ነው፡፡ ከዚህም በላይ ራሱ አምላክ የሆነው ኢየሱስ ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመሸከምና ለመደምሰስ ስለ እኛ ተጠመቀ፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ ስለ እኛም የከበረ ደሙን በመስቀል ላይ አፈሰሰ፡፡ በዚህም የእያንዳንዱን ሐጢያቶቻችንን ዋጋ ለመክፈል፣ እኛን ከኩነኔያችን ለማዳንና ከፍርዳችን ማምለጥ እንችል ዘንድ በእኛ ፋንታ ተኮነነ፡፡ ከዚያም አዲስና ዘላለማዊ ወደሆነ ሕይወት ይመልሰን ዘንድ በሦስት ቀን ዳግመኛ ከሙታን ተነሣ፡፡ 
አሁን በእግዚአብሄር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦ ሁላችንንም እየጠበቀን ነው፡፡ ያለውን ሁሉ ራሱ አምላክ ለሆነውና ለአዳኙ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነው ማን እንደሆነና ከሙሉ ልቡም በእርሱ የሚያምነው ማን እንደሆነ ለማየት እየጠበቀ ነው፡፡ ኢየሱስን የተቀበሉ ያላቸውን ሁሉ ለእግዚአብሄር የሚያስረክቡ ናቸው፡፡ እነርሱ እግዚአብሄር ፈጽሞ እንዳዳናቸው ያምናሉ፡፡ ለደህንነታቸው አንዳች ያደረጉት ነገር እንደሌለ ያውቃሉ፡፡ እግዚአብሄር በመገናኛው ድንኳን የመግቢያ በር በሰማያዊው፣ በሐምራዊውና በቀዩ ማግ በተገለጠው የደህንነት እውነት አማካይነት ያዳናቸው ከፍቅሩ የተነሳ ብቻ እንደሆነ እርግጠኞች ናቸው፤ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሄር አሳልፈው ለሰጡና እግዚአብሄርንና ቃሉን ወደ ልባቸው ለተቀበሉ እንዲህ ላሉ ሰዎች ሁሉ እግዚአብሄር ልጆቹ የመሆንን መብት ሰጥቶዋቸዋል፡፡
ከቅዱሱ ቁርባን ከመሳተፋችሁ በፊት ሁላችሁም ይህንን የደህንነት እውነት በግልጥ እንድታስተውሉት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ኢየሱስ ጥምቀትን የተቀበለው ሐጢያቶቻችንን ሁሉ ለመሸከምና ለእነርሱም ስርየትን ለማድረግ ነው፡፡ ኢየሱሰ በስጋ የሞተው እናንተንና እኔን ከሐጢያቶቻችን ሁሉ ለማዳን ነው፡፡ ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ሐጢያቶቻችንን ከተሸከመ በኋላ ለሞት ተሰቀለ፡፡ በእኛ ፋንታም ደሙን ሁሉ አፈሰሰ፡፡ እኛን ከሐጢያት ፍርድ ሊፈታንና ጻድቃን ሊያደርገን በዚህ ሁኔታ ተኮነነ፡፡
እግዚአብሄር ጸጋውን ያለብሰን ዘንድ በቅድስቱ ስፍራ ውስጥ ለምንኖረውና ለምንጸልየው ሁሉ የዕጣኑን መሠውያ ሰጥቶናል፡፡ ከእግዚአብሄር ዘንድ ጸጋን የምናገኝበት ስፍራ ይህ ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን ሙሉ በሙሉ ለጌታ አሳልፋችሁ ትሰጡ ዘንድ ሁላችሁንም እመክራችኋለሁ፡፡
ሐሌሉያ!